Administrator
አዲስ አበባ ከአፍሪካ የወደፊት 10 የኢንቨስትመንት ተመራጭ ከተሞች አንዷ ሆነች
አዲስ አበባ ለወደፊት በኢንቨስትመንት ዘርፍ ተመራጭ የሆኑ የአፍሪካ 10 ቀዳሚ አገራት በሚል ግሎባል ኢኮኖሚ ዎች በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት ውስጥ መካተቷን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ተቋሙ በአህጉሪቱ በቀጣይ ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻዎች ይሆናሉ ባላቸው ከተሞች ዝርዝር ውስጥ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ ኢባዳንና ካኖ የተባሉትን የናይጀሪያ ከተሞች፣ የቡርኪናፋሶዋን ኡጋዱጉ፣ የሴኔጋሏን ዳካር፣ የኬንያዋን ናይሮቢ፣ የኮትዲቯሯን አቢጃኒን፣ የሱዳኗን ካርቱም፣ የአንጎላዋን ሉዋንዳና የታንዛንያዋን ዳሬ ሰላም ማካተቱን ሚኒስቴሩ በድረገጹ ያወጣው መረጃ ያሳያል፡፡
ተጨባጭ የኢንቨስትመንት አማራጭ ያለባቸው ከተሞች በቀጣዮቹ ሁለት አስርት አመታት በእጥፍ ያህል እንደሚያድጉ የተነበየው የተቋሙ ሪፖርት፣ እነዚህ ከተሞች ወደሌሎች አገራት የመስፋፋት ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙ የንግድ ተቋማት ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንደሚሆኑም አመልክቷል፡፡
በእነዚህ ከተሞች የሚካሄደውን የመሰረተ ልማት አውታሮች የማስፋፋት እንቅስቃሴ በተፋጠነ ሁኔታ አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ያለው ሪፖርቱ፣ የመሰረተ ልማት አውታሮች መስፋፋት በአህጉሪቱ እድገትን ለማፋጠን ቁልፍ ሚና እንደሚጫወትና ማህበረሰቡን ያቀፈ ዘላቂ እድገት ለማስመዝገብ ወሳኝ እንደሆነ ጨምሮ ገልጧል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና የኤክስፖርት ገቢ በ25 በመቶ እንደሚያድግ ይጠበቃል
አለማቀፍ የቡና ገበያንና ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው
ኢትዮጵያ በመጪዎቹ አስራ ሁለት ወራት ለውጭ ገበያ ከምታቀርበው የቡና ምርት የምታገኘው ገቢ በ25 በመቶ እድገት ያሳያል ተብሎ እንደሚጠበቅ ብሉምበርግ ዘገበ፡፡
በቡና ምርትና በአቅራቢነት ከአለም ቀዳሚ በሆነችው ብራዚል በተከሰተው ድርቅ ምክንያት በአለም የቡና ገበያ ላይ የዋጋ ጭማሪ ይፈጠራል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጸው ዘገባው፣ ኢትዮጵያም በተያዘው የፈረንጆች አመት ለውጭ ገበያ ከምታቀርበው የቡና ምርት 900 ሚሊዮን ዶላር ያህል ገቢ ታገኛለች ተብሎ እንደሚጠበቅ ዘገባው አመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አለምሰገድ አሰፋን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ የአለም ገበያ የቡና አቅርቦት እጥረት የሚቀጥል ከሆነ በኢትዮጵያ የምርት ገበያ አማካይነት ለገበያ በሚቀርበው የአረቢካ ቡና ዋጋ ላይ በፓውንድ የ2 ዶላር ጭማሪ ሊገኝ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ኢትዮጵያ እስካለፈው ሃምሌ ወር መጀመሪያ በነበሩት 12 ወራት ለውጭ ገበያ ካቀረበችው ቡና 719 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቷን ያስታወሰው ዘገባው፣ ይህም ከአንድ አመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር የ3 ነጥብ 7 በመቶ ብልጫ እንዳለው ጠቅሷል። በተመሳሳይ ጊዜ ለውጭ ገበያ ባቀረበችው የቡና ምርት መጠን ላይ የ4 ነጥብ 1 በመቶ ቅናሽ መታየቱንም አመልክቷል፡፡
በዚህ አመት በአገሪቱ 500 ሺህ ቶን ቡና ይመረታል ተብሎ እንደሚጠበቅና፣ ከዚህ ውስጥም ግማሽ ያህሉ ወደተለያዩ አገራት ገበያ የሚላክ እንደሚሆንም ዘገባው ጨምሮ ገልጧል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ከተለያዩ የአለም አገራት አዳዲስ የቡና ምርት ገዢዎችን ለመሳብና አገሪቱ በአለማቀፉ የቡና ገበያ ውስጥ ያላትን ድርሻ ለማሳደግ እየሰራ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡ ወርልድ ቡሊቲን በበኩሉ፤ ከአፍሪካ ቀዳሚዋ የቡና አምራች የሆነችው ኢትዮጵያ ለአለም ገበያ የምታቀርበውን የቡና ምርት የንግድ ምልክት በማውጣት የበለጠ በገበያው ውስጥ ተወዳዳሪ ለማድረግ በአለማቀፍ ደረጃ ታዋቂ ከሆኑ ቡና ገዢ ኩባንያዎች ጋር እየሰራች መሆኗን ዘግቧል፡፡
ከኩባንያዎቹ ጋር የተጀመረው ስራ ህገወጥ የቡና ንግድንና አላግባብ የሚጣል የቡና ዋጋ ተመንን የመከላከል እንዲሁም የአገሪቱን የቡና የንግድ ምልክቶች በመጠቀም ትርፋማነትን የማሳደግ ዓላማ ያለው ነው ተብሏል፡፡
በአገሪቱ በቡና ልማት ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳትፎ የሚያደርጉ 15 ሚሊዮን ዜጎች እንዳሉ የጠቆመው ዘገባው፣ እነዚህ ዜጎች ከሽያጩ የሚያገኙት ገቢ ከ10 በመቶ በታች እንደሆነና የተቀረውን የሚወስዱት በአለማቀፍ ደረጃ የሚገኙ ነጋዴዎችና አከፋፋዮች መሆናቸውን ገልጧል፡፡
እስካሁን ድረስ 34 አገራት በደቡብና በምስራቅ ኢትዮጵያ የሚመረቱ የቡና ዝርያዎች መለያዎችንና የንግድ ምልክቶችን ተቀብለው ለገበያ እያቀረቡ እንደሚገኙ ገልጾ፣ በቀጣይም በአውስትራሊያና በብራዚል ተመሳሳይ ስራ ለመስራት እንቅስቃሴ መጀመሩን አስረድቷል፡፡
አዲስ “ስማርት የኤሌክትሪክ ቆጣሪ” በአገር ውስጥ ማምረት ተጀመረ
የብሄራዊ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የስማርት ቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑ የኤሌክትሪክ ቆጣሪዎችን አምርቶ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ማቅረብ የጀመረ ሲሆን ቴክኖሎጂው በሃገር ውስጥ መሰራቱ የሃገር ደህንነትን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ፋይዳ አለው ተብሏል፡፡
ከውጭ በከፍተኛ ምንዛሬ የሚገቡትን ቆጣሪዎች ሙሉ ለሙሉ እንደሚያስቀር የተነገረለት የኤሌክትሪክ ቆጣሪ “አይቲ ፕላስ ስማርት ኢነርጂ ሜትር” በመባል የሚታወቅ ሲሆን እስካሁን ከሚሰራበት ቴክኖሎጂ በተሻለ ሁኔታ መስራት የሚችሉ የተለያዩ አገልግሎቶችን ያካተተት ነው ተብሏል፡፡
የብኢኮ ም/ዋና ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄነራል ጠና ቁርንዲ ከትናንት በስቲያ ከስራ ባልደረቦቻቸው ጋር በሒልተን ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳስታወቁት፤ ቆጣሪው የወደፊቱን የቴክኖሎጂ እድገት እያንዳንዱ ቆጣሪ ያለሰው ንክኪ ከዋና ማዕከል ጣቢያ ጋር በርቀት መቆጣጠሪያ እየተገናኘ የሚሰራበት በመሆኑ በኃይል አቅርቦት ላይ ያነጣጠሩ ሃገራዊ የደህንነት ስጋቶችን መቆጣጠርና መከላከል ያስችላል ብለዋል።
ደህንነትን ያስጠብቃል የተባለው የኤሌክትሪክ ቆጣሪው፤ ከንድፉ እስከ ምርት ድረስ በብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን እና በስሩ ባሉት ተቋማት የተፈበረከ ሲሆን የፕላስቲክ ክፍሉ በኢትዮ ፕላስቲክ ኢንዱስትሪ፣ የብረታ ብረት ክፍሉ ደግሞ በብረታ ብረትና ፋብሪኬሽን ኢንዱስትሪ እንዲሁም የተለያዩ ምርቶች በህብረት ማኑፋክቸሪንግ ማሽን ግንባታ ኢንዱስትሪ የተመረተ ነው ተብሏል፡፡ ፋብሪካው ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ሲገባም በቀን 1200 ቆጣሪዎችን የማምረት አቅም አለው ተብሏል፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ሲስተም ለጦርነት ጥቃት እንደሚውል ይታወቃል ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ ብ/ጄነራል ጠና ቴክኖሎጂው ሙሉ ለሙሉ የሃገር ውስጥ መሆኑ በኃይል ላይ አነጣጥሮ የሚፈፀም የጦር ጥቃትን በቀላሉ ለመቆጣጠር እንደሚያስችል ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋየር ቢዝነስ ስራ አስፈፃሚ አቶ ቢትወደድ ገ/አሊፍ በበኩላቸው፤ “ቴክኖሎጂው በደንበኛውና በአገልግሎት አቅራቢው መካከል ጥብቅ ቁርኝትን ይፈጥራል፤ ቆጣሪ አንባቢነትን አስቀርቶም ደንበኞች የራሳቸውን ሂሳብ አውቀው በቢል መልክ እንዲከፈሉ ያስችላል” ብለዋል፡፡ ቆጣሪ አንባቢነት ቢቀርም የሚፈናቀል ሰራተኛ አይኖርም፤ ሌሎች ስራዎች ይሰጣቸዋል ሲሉ ኃላፊው ጨምረው ገልፀዋል፡፡
አዲሱ ስማርት ቆጣሪ በርቀት መቆጣጠሪያ የሚታገዝ በመሆኑም አደጋ ሲያጋጥም በቀላሉ ለዋና ማዕከል መልዕክት ስለሚያስተላልፍ ኃይል በመቀነስ መቆጣጠር ያስችላል፤ ቆጣሪው ንክኪ ሲደረግበት በቀጥታ ለማዕከሉ መረጃ ያቀብላል ተብሏል፡፡
ኢብኮ አንዱን ቆጣሪ በ2500 ብር ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያቀርብ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን ቆጣሪው በቅርቡ አገልግሎት ላይ እንደሚውል ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሰር የአለም 1ኛ የሆነችበት ሚስጥር!
መንግስት እንደሚለው፤ ጋዜጠኞችን የሚያዋክበውና የሚያስረው በርካታ ጋዜጠኞች ስርዓት አልበኛና ነውጠኛ ስለሆኑ ይሆን? ወይስ አንዳንድ ተቃዋሚዎች እንደሚሉት፤ መንግስት በጭራሽ የነፃነትን ጭላንጭል የማይፈቅድ የለየለት አምባገነን ስለሆነ?
እንደምታውቁት፤ በዚህ አሳዛኝና አሳሳቢ የአገሪቱ እውነታ ውስጥ፤ “ሕዝቡ” የለበትም። በዚህ ላይ መንግስትና ገዢው ፓርቲ፣ እንዲሁም አብዛኞቹ ተቃዋሚዎችና ፖለቲከኞች ይስማሙበታል። በቃ! “ሕዝቡ”... ለእውነት የቆመ፣ ነፃነት ወዳድ፣ በቅንነነትና በፍትህ የሚያምን፣ ኩሩና የሰላማዊ ነው። ችግሩ ያለው ሌላ ጋ ነው። ማን ጋ? እዚህኛው ጥያቄ ላይ፣ ልዩነት ይመጣል። መንግስት፣ “አመኛ” የሚላቸውን ተቃዋሚ ፓርቲዎችና “የተቃዋሚዎች ልሳን” የሚላቸውን ጋዜጠኞች ይወነጅላል። ተቃዋሚዎች በበኩላቸው፣ መንግስትንና ገዢውን ፓርቲ ይኮንናሉ። እስቲ ሁለቱንም በየተራ እንመልከታቸው።
በቅርቡ በነፃ መፅሔቶች ላይ በቀረበው ክስ ውስጥ ተደጋግሞ የተጠቀሰ ነገር አለ - መፅሔቶቹ አመፅን ይቀሰቅሳሉ የሚል። ገና በፍርድ ቤት ባይረጋገጥም፣ እንዲያው ነገሩ እውነት ቢሆን እንኳ፤ እንደ ወንጀል ተቆጥሮ ያስከስሳል ወይ? አመፅን የሚቀሰቅስ ሁሉ አይከሰስም - ጉዳት ካደረሰ ወይም ደግሞ ካሁን አሁን ጉዳት ያደርሳል የሚል አጣዳፊ ስጋት ካልተከሰተ በቀር። የአመፅ ቅስቀሳ በተጨባጭ አመፅን ካልፈጠረ በቀር ሊያስከስስ አይገባም ማለቴ አይደለም። የአመፅ ቅስቀሳው ለጊዜው ጉዳት ባያደርስም፣ ቢያንስ ቢያንስ አስጊ ከሆነ ... ያኔ ክስ ሊመጣ ይችላል - በግልፅ የሚታይ ደራሽ አደጋ የሚጥር ከሆነ ማለት ነው - (clear and present danger) እንደሚባለው።
ሁለት ምሳሌዎችን ልጥቀስላችሁ። የሶሻሊዝምና የኮሙኒዝም ሃሳቦችን ማሰራጨት፣ ያለ ጥርጥር አመፅን ከመቀስቀስ የተለየ ትርጉም የለውም። የግል ንብረትን ለመውረስና የአንድ “አብዮታዊ ፓርቲ” አምባገነንነትን ለማስፈን፣ ከአመፅ ውጭ ሌላ አማራጭ የለም በማለት የሚሰብኩ ናቸውና። ነገር ግን፤ አያስከስሱም። ለምን? ዛሬ ቅስቀሳው አመፅን አልፈጠረም፤ አጣዳፊ አደጋ ይፈጥራሉ ለማለት የሚስችል ምልክት የለም።
ሌላ መረጃ ልጨምርላችሁ። የአገሪቱ መንግስት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ነባሮቹ የሃይማኖት ተቋማት፣ የንግድ ስርዓቱ ሁሉ የሰይጣን ተወካዮች ናቸው ብለው የሚያምኑ ሰዎች፤ በይፋ እምነታቸውን ይሰብካሉ፤ መንግስትን ጨምሮ የሰይጣን ተወካዮች የተባሉት ተቋማት በሙሉ እንደሚፈራርሱና አመድ እንደሚሆኑ ዘወትር ይሰብካሉ፤ ያንንም ጊዜ ይናፍቃሉ። ግን፣ አመፅ አልፈጠሩም፤ አልያም የአመፅ ጥፋት ለመፍጠር አፋፍ ደርሰዋል የሚያስብል የአደጋ ፍንጭ የለም። ስለዚህ ምንም የሚያስከስስ ወንጀል አልሰሩም። እንዲያውም፤ መንግስታዊው ስርዓት የሰይጣን ተወካይ ነው ብለው መስበክ መብታቸው ስለሆነ ነው፤ በይፋ መፅሔት የሚያሰራጩት፤ በየመንገዱ የሚሰብኩት፤ በየሳምንቱ ከደርዘን በላይ በሆኑ አዳራሾች ጉባኤ የሚያካሂዱት።
በአመፅ “አብዮታዊ አምባገነንነትን” ለማስፈን የሚቀሰቅሱ ቅሪት የኮሙኒዝም አፍቃሪዎችም ሆኑ፣ “መንግስት የሰይጣን እንደራሴ ነው” ብለው የሚያምኑ ሰባኪዎች፡ “ያንን ፃፋችሁ፤ ይሄንን ተናገራችሁ፤ መፅሔት አሳተማችሁ፣ በራሪ ወረቀት በተናችሁ” ተብለው አይከሰሱም። ለምን? አሁን የፈጠሩት አመፅ የለም፤ አሁን የጥፋት አፋፍ ላይ የደረሰ አጣዳፊ አደጋም የለም። ስለዚህ ወንጀል አልፈፀሙም። ወንጀል ካልፈፀሙ ደግሞ፣ መታሰርና መዋከብ የለባቸውም።
“ወንጀል አልሰሩም፣ ሃሳባቸውን ቢገልፅና ቢሰብኩ መብታቸው ነው” ሲባል ግን፤ “ሃሳባቸው ትክክልና ጠቃሚ ነው” ማለት አይደለም። ሃሳባቸው፣ ሙሉ ለሙሉ ስህተት ነው፤ ጎጂ ነው። ነገር ግን፤ “ሃሳባቸው የተሳሳተ ነው፤ ወደፊት ጉዳት ያደርሳል” የምንል ከሆነ፣ ከእነሱ ተሽለን ትክክለኛና ጠቃሚ ሃሳብ እስከያዝን ድረስ መፍትሄው ቀላል ነው። ተአማኒነት እንዳይኖራቸውና “ሆ” ብሎ የሚጎርፍ ተከታይ እንዳያገኙ፣ በሃሳብ ተከራክረን ልናሸንፋቸው እንችላለን - ስህተታቸውንና ጉድለታቸውን በግልፅ በማሳየትና ትክክለኛውንና ጠቃሚውን ሃሳብ በማቅረብ። “መተማመኛህ ምንድነው?” በሉ።
ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚዎች እንደሚሉት፣ “ህዝቡ” ቅዱስ ከሆነ፣ ... አብዛኛው ሰው ለእውነት በመቆምና ነፃነት በመውደድ የእኔነት ክብር የተጎናፀፈ ከሆነ፤ ... ማለትም አገሪቱ የስልጡን አስተሳሰብ ባለቤት ከሆነች... ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ይሆናል።
የአመፅ ቅስቀሳ ከየትም ቢመጣ ሰሚ አያገኝም፤ እያሰለሰ የሚያስርና የሚያዋክብ አምባገነንም አይኖርም። “በስልጡኑና በአስተዋዩ ሕዝባችን” ፊት እየቀረቡ በመከራከር ብቻ ማሸነፍ ይቻላል። መቼም “ሕዝቡ” ስልጡን እስከሆነ ድረስ፣ በሃሳብ ክርክር ላይ፤ ከተሳሳተና ከጎጂ ሃሳብ ይልቅ፣ ትክክለኛና ጠቃሚ ሃሳብ ብልጫ ይኖረዋል። በሌላ አነጋገር፤ ትክክለኛ አስተሳሰብ ካልያዝን ነው፤ ወደ እስርና ወደ ወከባ የምንቸኩለው።
አሁን፣ “አመፅን ቀስቅሰዋል” ተብለው ወደ ተከሰሱት መፅሄቶች እንመለስ። የመጀመሪያው ጥያቄ፣ “አመፅ ቀስቅሰዋል የተባሉት መፅሔቶች፣ በእርግጥ አመፅ ፈጥረዋል ወይ?” የሚል ነው። እስካሁን፣ መፅሄቶቹ አመፅ ስለመቀስቀሳቸው እንጂ አመፅ ስለመፍጠራቸው በመንግስት የተነገረ መረጃ የለም። ይሄ አያከራክረንም። ወደ ሁለተኛው ጥያቄ እንሻገር - “አፋፍ ላይ የደረሰ ግልፅ የአደጋ ስጋትስ ተከስቷል ወይ?”
ስጋትማ መች ይጠፋል ብትሉ አይገርመኝም። ደግነቱ፣ ከሌላው ጊዜ ጋር ሲነፃፀር፣ ዛሬ በአመዛኙ የተረጋጋ ሁኔታ ይታያል። “ሁሉም ነገር አማን ነው” ማለት ግን አይደለም። ኢትዮጵያ እንደ ብዙዎቹ ኋላቀር አገራት በቀላሉ ለአደጋ የምትጋለጥና ብዙም ከስጋት ያልራቀች አገር ናት። እንዲያም ሆኖ መንግስት፣ “በመፅሔቶቹ ምክንያት ስጋት ላይ ወድቄያለሁ” ብሎ በጭራሽ የሚናገር አይመስለኝም።
ደግሞስ፣ በሳምንት አንዴ የሚሰራጩ በጣት የሚቆጠሩ መፅሔቶች እንዴት ለመንግስትና ለገዢው ፓርቲ ትልቅ ስጋት ሊሆኑ ይችላሉ? በየእለቱ ከጥዋት እስከ ማታ የሚሰራጩ በደርዘን የሚቆጠሩ የቲቪና የሬድዮ ጣቢያዎችን ይዞ፤ በመቶ የሚቆጠሩ ጋዜጠኞችንና በሺ የሚቆጠሩ የ”ኮሙኒኬሽን” ባለሙያዎችን ያሰማራ መንግስት፤ ከመሃል አገር እስከ ጠረፍ ድረስ እልፍ ካድሬዎችን አሰማርቶ፣ ከደርዘን በላይ ግዙፍ ማህበራትንና በሚሊዮን የሚቆጠሩ አባላትን ያደራጀ ገዢ ፓርቲ፣ እንዴት በጣት የሚቆጠሩ መፅሔቶችን በክርክር ማሸነፍ ይሳነዋል? በ“ሕዝቡ” ዘንድ ተአማኒነት እንዳይኖራቸውና ለአመፅ “ሆ” ብሎ የሚነሳ ተከታይ እንዳይኖራቸው ማድረግ አቅቶት ስጋት ላይ ይወድቃል?
መንግስትም ሆነ ገዢው ፓርቲ፣ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሚኖራቸው አይመስለኝም። ለዚህም ነው፤ መንግስት “በመፅሔቶቹ ምክንያት አገሪቱ ስጋት ላይ ወድቃለች” ብሎ ሊናገር የማይችለው። አሃ! በአራት መፅሔቶች ሳቢያ የአገሪቱ የመንግስት ስጋት ላይ ከወደቀ፤ ... ወይ መንግስት ትክክለኛና ጠቃሚ ሃሳብ አልያዘም፤ አልያም “ሕዝቡ” ለትክክለኛና ለጠቃሚ ሃሳብ ጆሮ የለውም ማለት ነው።
ያው፣ እንደተለመደው መንግስትና ገዢው ፓርቲ፤ “ፈፅሞ እንከን የለብንም፣ ትክክለኛና ጠቃሚ ሃሳብ ይዘናል” ባይ ናቸው። ስለዚህ ችግሩ ያለው፣ “ሕዝቡ” ላይ ሳይሆን አይቀርም። አመፅ ይቀሰቅሳሉ በሚል የተከሰሱት መፅሔቶች ለመንግስት ስጋት ሊሆኑ የሚችሉት፣ ነውጥ የሚያፈቅርና በትንሽ ቅስቀሳ “ሆ” ብሎ ለመትመም የተዘጋጀ አስተዋይነት የጎደለው ኋላቀርና ግልብ “ህዝብ” ካለ ብቻ ነው።
“ሕዝቡ”፤ ለትክክለኛና ለጠቃሚ ሃሳብ ጆሮ የሌለው፣ በቀላሉ የሚታለል፣ እንደ ከብት እየተነዳና እየተንጋጋ ነውጥን የሚደግፍ ወራዳ ካልሆነ፣ ችግር አይፈጠርም። ለእውነትና ለነፃነት በመቆም የእኔነትን ክብር የተጎናፀፈ “ሕዝብ” ውስጥ፤ የነውጥ ቅስቀሳ ጉዳት አያደርስማ። “የምፅአት ቀን ደርሷልና ወደ ፅዮን ተራራ ውጡ” ብሎ በእንግሊዝና በአሜሪካ ጎዳናዎች ላይ ከሚቀሰቅስ ሰባኪ የተለየ አይሆንም - በዛሬ ዘመን ብዙ ሰሚ አያገኝም፤ ቢሰሙትም ተከታይ ሆነው አይጎርፉለትም።
ልክ እንደዚያው፣ መንግስት እንከን አልባ ከሆነና “ሕዝቡ” ስልጡን ከሆነ፤ በጣት የሚቆጠሩ መፅሔቶች በሳምንታዊ ሕትመት ብቻ ሳይሆን ነጋ ጠባ አመፅ ቢቀሰቅሱ እንኳ ቅንጣት ታህል ስጋት መፍጠር አይችሉም። በእንከን አልባው መንግስት ላይ ስጋት መፍጠር ከቻሉ ግን፤ ያለ ጥርጥር “ሕዝቡ” ላይ ችግር አለ። “ሕዝቡ” ክፉ የአመፅ ጥም አለበት፤ አልያም በጥቂት ቅስቀሳ የሚንጋጋ ተላላ ሞኝ ነው። የዚህን ያህል እጅግ የባሰበት ኋላቀርነት ውስጥ ባይዘፈቅ እንኳ፣ ቢያንስ ቢያንስ የኋላቀርነት ዝንባሌ የተጠናወተው መሆን አለበት። እንዴት? ያው፣ ቅስቀሳ እስካልሰማ ድረስ፣ ጨዋ ይሆናል። ቅስቀሳ የሰማ ጊዜ ግን፤ ናላው ይዞራል፤ ለነውጥ ይነሳል - በሌላ አነጋገር ለነውጥና ለተላላነት የተጋለጠ ነው። “አይ፤ ሕዝቡን አትንካ” ከተባለ፤ ሌላኛ አማራጫችን ጣታችንን መንግስት ላይ መቀሰር ይሆናል። ብዙዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በዚህ ይስማማሉ።
እና ተቃዋሚዎች እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሰርና በማዋከብ የአለም መሪ ለመሆን የምትፎካከረው፣ መንግስት የለየለት አምባገነን ስለሆነ ይሆን? በእርግጥ፣ መንግስት የለየለት አምባገነን ከሆነ፣ ዛሬ ጋዜጠኞችን አሰረ ወይም አዋከበ ብለን እንደ አዲስ የምንገረምበት ምክንያት አናገኝም። እንዲያውም፤ ሳይታሰሩ የቆዩ ጋዜጠኞችና ሳይዘጉ የቆሙ መፅሔቶች መኖራቸው ነው የሚገርመን።
በሌላ አነጋገር፤ ገዢው ፓርቲ የለየለት አምባገነን ከሆነ፣ የግል ነፃ ጋዜጣና መፅሔት የሚባል ነገር ሊኖር አይችልም፤ እንደ ኤርትራ ወይም እንደ ሰሜን ኮሪያ። ጥሩ! ገዢው ፓርቲ “የለየት አምባገነን” ባይሆንም እንኳ... ተራ አምባገነን ቢሆንኮ በቂ ነው። ማሰርና ማዋከብ የዘወትር ስራው ያልሆነ፣ ሰበብ ካገኘ ግን የማያልፍ. ወይም እያሰለሰ የሚነሳበት ለተራ አምባገነን ጋዜጠኞችን የሚያስረውና መፅሔቶችን የሚዘጋው ስጋት ስለፈጠሩበት ላይሆን ይችላል።
እናም፤ መፅሔቶቹ በየሕትመታቸው የሚፅፉት፣ መረጃ ለማሰራጨት፣ “ሕዝቡ”ን ለማሳወቅ፣ ለመልካም ለውጥ ለማነሳሳትና ለመቀስቀስ ቢሆንም፤ “ተችተውኛል፣ ፓርቲው የማልፈልገውን መረጃ ያሰራጫሉ፣ ለመንግስት የማይጥም ሃሳብ ይፅፋሉ፣ ደፍረውኛል” በሚል ከማሰር አይመለስም እንበል። እሺ ይሁን። ግን፤ ይሄን ሁሉ በግላጭ የሚያየው የአገሪቱ “ሕዝብ”፣ ለእውነትና ለነፃነት የቆመው፣ ለፍትህና ለሰው ክብር ፍቅር ያለው “ስልጡኑ ሕዝብ”፣ መንግስትን በመገሰፅ “ተው” ይለዋል? ለመሆኑ፤ ከመነሻው “ሕዝቡን” ማነሳሳትና መቀስቀስስ ለምን አስፈለገ? መንግስት አምባገነን ቢሆንም፣ ሕዝቡ ይህንን ስለማያውቅና ስለማይገባው ይሆን? ወይስ ሕዝቡ የመንግስትን አምባገነንነት ቢያውቅም፣ ለእውነትና ለነፃነት ደንታ ስለሌለው፣ የእኔነት ክብር ስለራቀው ወይም በጣም ፈሪ ስለሆነ ቀስቃሽ ያስፈልገዋል? ያው ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሚሉት መንገድ ስንሄድም፤ “ሕዝቡ” ላይ (እኛው ላይ) ጣታችንን መቀሰራችን አልቀረም።
ለማለት የፈለግኩት ምንድነው? በአንድ በኩል፤ ኢህአዴግና መንግስት ራሳቸውን እንደ እንከን የለሽ በመቁጠር፤ የዚህ አገር ችግር በአራት በአምስት መፅሔቶች ላይ ለማሳበብ የሚያደረጉት ሙከራ ዋጋ የለውም። በሌላ በኩል፤ የብዙዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተቃራኒ ሙከራም አያስኬድም። ኢህአዴግ በአንዳች ምክንያት፣ በምርጫም ሆነ በአመፅ፣ ወይም በሌላ መንገድ ከስልጣን ቢወርድ፣ ኧረ እስከነጭራሹ ጥፍት ቢል እንኳ፣ ተአምረኛ ለውጥ አይመጣም። የአገር ኋላቀርነት በአንዳች ተዓምር ብን ብሎ አይጠፋም።
ከፖለቲካ ተሰናባቹ አቶ ሙሼ ሰሙ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ
የኢህአዴግ አስቸጋሪ ባህሪዎች ትግሉን ውስብስብና እልህ አስጨራሽ አድርገውታል
ተቃዋሚ ፓርቲዎች መንግስት ለመሆን የሚያስችል ቁመና አልፈጠሩም
የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)ን ከመሰረቱት አንጋፋ ፖለቲከኞች አንዱ የነበሩት አቶ ሙሼ ሰሙ ባለፈው ሳምንት ከፖለቲካ ፓርቲ ራሳቸውን ማግለላቸውን አስታውቀዋል፡፡ ኢዴፓን ከ92 ዓ.ም ጀምሮ በህዝብ ግንኙነት ሃላፊነት፣ በዋና ፀሐፊነትና በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉት አቶ ሙሼ፤ ከፓርቲያቸው መልቀቃቸውን ምክንያት በማድረግ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው በአገሪቱ ወቅታዊ ፖለቲካ ዙሪያ በስፋት አነጋግራቸዋለች፡፡ በተለይም በተቃዋሚ ፓርቲዎች የፖለቲካ እንቅስቃሴ ዙሪያ፣ኢዴፓና እሳቸው ለአገሪቱ ስላበረከቱት አስተዋጽኦ፣ስለመጪው ምርጫ፣ ስለተከሰሱት የግል የፕሬስ ውጤቶች፣ ስለኢህአዴግ...እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ተጠይቀው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ከፓርቲ ፖለቲካ ራስዎን እንዳገለሉና ለፓርቲዎ የመልቀቂያ ደብዳቤ እንዳስገቡ በይፋ አስታውቀዋል፡፡ ምክንያትዎን ቢያብራሩልን?
ከኢዴፓ ጋር ላለፉት 15 ዓመታት ቆይቻለሁ፡፡ በፓርቲው ውስጥ የአመራርነት ሚና ነው የነበረኝ፡፡ ሰነድ በማዘጋጀት፣ የፓርቲውን የፖለቲካ ፍልስፍናና አቅጣጫ በመቅረፅ---ስራ እሳተፍ ስለነበር ፋታ ኖሮኝ አያውቅም፡፡ የኢትዮጵያ የተቃውሞ ትግል ጫና የበዛበት ነው፡፡ በዚህ ቦታ በአንድ መስክ ተሰማርቶ መቆየት ቆም ብሎ ራስን ለመፈተሽና ለመገምገም ጊዜ አይሰጥም፡፡ የሄድኩበት መንገድ ምን ያህል ውጤታማ እንደነበረ፣ ከዚህስ ማህበረሰቡ ምን ተጠቅሟል---የሚለውን ለመረዳት ትንፋሽ መውሰድ ---- ራሴን ማረጋጋት አለብኝ ብዬ ወስኛለሁ፡፡ ከተቋማዊ አሰራር ወጣ ብዬ ራሴን መገምገም ፈልጌአለሁ፡፡
የኢትዮጵያ የተቃውሞ ትግል ውስጥ እንደ ባህል የተለመደ ነገር አለ፡፡ ሰዎች ሰሩም አልሰሩም፣ፋይዳ ኖራቸውም አልኖራቸውም ተቃዋሚ ፓርቲ ውስጥ ዝም ብሎ የመቆየት ባህል፡፡ እየታገሉ መኖር ይቻላል፤ ነገር ግን ለመኖር ብቻ የሚኖርበት ሁኔታ አለ፡፡ እዚያ ፓርቲ ውስጥ መቆየቴ አንድ ቀን ለውጥ ይመጣና የማገኘው ጥቅም ይኖራል ብለው የሚያስቡ አሉ፡፡ ወይንም ደግሞ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ይሻሻልና ሚናዬን ለመፈተሽ እድል ይሰጠኛል በሚል ሊቆዩ ይችላሉ፡፡
እኔ ግን በአንድ ፓርቲ ውስጥ እስከአለሁ ድረስ ስራዬን መስራት አለብኝ ብዬ አምናለሁ፡፡ የሚገባውን ሰዓትና ጊዜ ሰጥቼ ኃላፊነቴን መወጣት አለብኝ፡፡ አሁን ባለሁበት ሁኔታ የስራዬ ባህሪ፤ ለረዥም ጊዜ ባለማቋረጥ በትግሉ ውስጥ በመቆየቴ፤ የቆየሁባቸውም ጊዜያቶች በከፍተኛ አመራር ውስጥ በመሆኑ----ቆም እንድልና ራሴን እንድመረምር አስገድዶኛል፡፡ ለእንጀራ የሚሰራ ስራም ቢሆን እኮ 15 ዓመት ይሰለቻል፡፡
የእርስዎን ከፓርቲ ፖለቲካ ራስን ማግለል አስመልክቶ አንዳንድ ወገኖች “መጪውን የ2007 ምርጫ ሽሽት ነው፤ ከፖለቲካ ጫና ራስን ለማግለል ነው” የሚል አስተያየት ሲሰነዝሩ ይሰማል…
ሰዎች ብዙ ነገር ሊሉ እንደሚችሉ እገምታለሁ። ቁምነገሩ ግን ከእኔ እምነትና አስተሳሰብ ጋር ነው ያለው፡፡ በአለፉት 15 የትግል ዓመታት ከተቃዋሚዎችና ከመንግስት በኩል የተለያዩ ጫናዎችን አሳልፌያለሁ፤ ታስሬያለሁ፤ ተሰድጃለሁ፡፡ ይሄን ሁሉ ጫና ተቋቁሜ መጥቻለሁ፡፡ ከ1997 ዓ.ም በኋላ ደግሞ ተቃዋሚው ኃይል የነበረው ጫና፣ ግፊት፣ ስም ማጥፋትና ዘመቻው እጅግ ከባድ ነበረ፡፡ በዚያን ጊዜም ቢሆን ሃሳቤን አልለወጥኩም። ጫናን የምፈራ ቢሆን ኖሮ ወደ ትግሉ አልመጣም ነበር፤ እነዚያን የጫና ዘመኖች ተቋቁሜ አላልፍም ነበር፡፡ በምርጫ ወቅት የስራ ጫና ይበዛል፤ የሚያሳድረው ተፅዕኖም ቀላል አይደለም፡፡ በየአካባቢው ተሂዶ አባላት ከመመልመል ጀምሮ ቅስቀሳ እስከ ማድረግ ያለው ስራ ከባድ ነው፡፡ “እንደዚህ አይነት ከባድ ስራ አሁን መቋቋም ትችላለህ ወይ?” ብትይኝ፣ አሁን አልችልም። እረፍት እፈልጋለሁ፤ ትንፋሽ መውሰድ አለብኝ፤ ራሴንም ቆም ብዬ መገምገም ያስፈልገኛል፡፡ እንደ ሀገራዊ ምርጫ ያለን የምርጫ ዘመቻ ለመምራት ጊዜ ያስፈልጋል፣ መረጋጋትን ---- አእምሮ ነፃ ሆኖ መዘጋጀትን ይጠይቃል።
ምርጫውን ሽሽት ነው የሚሉ ተሳስተዋል ማለት ነው?
በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት አምስት ጊዜ አገር አቀፍ ምርጫ ተደርጓል፤ በአራቱ ተሳትፌያለሁ፡፡ የተለየ የምርጫ ባህሪ የታየበት 1997 ዓ.ም ነው፡፡ የተለየ ባህሪ እንዲኖረው ያደረገው ትግሉ የሄደበት መንገድ የፈጠረው ችግር ነው፡፡ በፖለቲካው ታስሬበታለሁ፡፡ ከምርጫው ውጪ በነበረ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ታስሬያለሁ፣ ተሰድጃለሁ፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ከዚህ በላይ ሊኖር አይችልም፡፡ መጪው ምርጫ እንደዚህ ቀደሙ አስቸጋሪና የተወሳሰበ ነው ብዬ አላምንም፡፡ በውጤቱም ቢሆን ብዙ ትርጉም ያለው ነገር ይገኝበታል ብዬ አላስብም፡፡ ተቃዋሚውም ኃይል በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ መንግስትን የሚገዳደርበት ጉልበት እየፈጠረ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ስለዚህ መጪው ምርጫ ለተቃዋሚው በጎ ነገሮች አያመጣለት ይሆናል እንጂ ችግር የሚከሰትበት ነው ብዬ አላምንም፡፡ የ2007 ዓ.ም ምርጫ ከእኔ ውሳኔ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፡፡
አሁን ባሉት የኢዴፓ አመራሮች ፓርቲው በመጪው ምርጫ ውጤት ያመጣል ብለው ያስባሉ?
ሰዎች እንደየአቅማቸው የተለያየ ባህሪና አቋም ይኖራቸዋል፡፡ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቃሚ የሆኑ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ አሁን ኢዴፓ ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ አመራሮች ወጣቶች ናቸው፡፡ በትግል ተመክሮዋቸው ጠልቀው የሄዱ አይደሉም፡፡ ነገር ግን ሌሎች ጠንካራ ጐኖች አሏቸው። እኛ ስንጀምር ኢዴፓን ኢዴፓ ለማድረግ ትልቁ ጉልበታችን ወጣቶች መሆናችን ነበር፡፡ አሁን አርጅተናል ማለቴ አይደለም፡፡ ሰርተን አይደክመንም፤ ሀሳባችንን በሰዎች ዘንድ ለማስረፅ አንታክትም፡፡ ያ የፓርቲያችን ጠንካራ ጎን አሁንም ኢዴፓ ውስጥ አለ፡፡ አሁን ፓርቲው ውስጥ ያሉት ልጆች እየተማሩ ያሉ ናቸው፡፡ በሚኖሩበት አካባቢ እና በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ልጆች ናቸው። የእኛን ዓይነት ተመክሮ ላይኖራቸውና አጋዥ ኃይል ላይሆናቸው ይችላል፡፡ ይሄ አስቸጋሪም ቢሆን መታለፍ ያለበት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በሰው ላይ እየተማመኑ ፖለቲካ ማራመድ አይቻልም፡፡ እያንዳንዱ ሰው ትግሉን እየተገዳደረ እያሸነፈ፣ እየሰበረ፣ እየለወጠ መሄድ አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ሊቸገሩ ይችላሉ፤ ችግሩ ግን የትግሉ አካል ነው፡፡ አቅማቸውን ለማጠናከርና ለማጎልበት ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡ ያለው ተጨባጭ ሁኔታም ያግዛቸዋል፡፡ ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ቅሬታ የሰላ ነው፡፡ ማህበረሰቡ ለኢህአዴግ ያለው እምነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ መጥቷል። ድህነት፣ ረሃብ፣ ስራ አጥነት፣ የአገልግሎት እጦት፣ የትራንስፖርት ችግር--- እነዚህ ሁሉ ቅራኔዎች በቅጡ ከተያዙና ከተጠቀሙባቸው ሌላ ተጨማሪ መታገያ ያስፈልጋቸዋል ብዬ አላምንም፤ እናም ለውጤት ብዙ ሩቅ አይደሉም፡፡
“ሶስተኛ አማራጭ” የሚለው የፓርቲው ስትራቴጂ አሁንም ቀጥሏል?
ሶስተኛ አማራጭ የፓርቲው መሰረታዊ አቋም ነው፡፡ ይሄን አቋም የሚሸረሽርበት፤ አስተሳሰቡን የሚለውጥበት ምክንያት ይኖረዋል ብዬ አላምንም፡፡ እስካሁን ካለኝ ተመክሮ ለኢዴፓ የተለየ ዋጋ ከሚያሰጡት ነገሮች አንዱና ሊደርስበት ላሰበው ግብ እንደ ትግል ስልት የሚጠቅመው መንገድ ይሄ ብቻ ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ ከዚህ በተረፈ እኔ የምወስነው ጉዳይ አይደለም፡፡ አሁን እኔ ኢዴፓ ውስጥ አይደለሁም፤ ኢዴፓ ውስጥ ያሉ ሰዎች “ለትግል የሚያዋጣን ስልት ይሄ ነው” ብለው እስከአመኑ ድረስ ይቀጥሉበታል፡፡ ይሄ የእነሱ ውሳኔ ነው የሚሆነው።
በ15 ዓመት የትግል ዘመንዎ፣ ለኢትዮጵያ ምን አበረከትኩ ብለው ያስባሉ?
ትልቁ ነገር ኢዴፓን መመስረታችን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ኢዴፓ ፓርቲ እስከሆነበት ጊዜ ድረስ የህብረ ብሄራዊ አስተሳሰብና አጀንዳ እጅግ የተዳከመበት ጊዜ ነበር፤ ህብረ ብሄራዊነት የሚያዋጣ የትግል ስልት እንደሆነ አምነን፤ ህዝቡንም አሰባስበን ለሚፈልገው ግብ ለማድረስ፣ አደረጃጀትን በዚህ መንገድ መቀየድ ጥሩ ነው የሚለውን ነገር እንደ አስተሳሰብ በህብረተሰቡ ውስጥ እንዲሰርፅ ማድረጋችን ትልቁ ድላችን ነው፡፡ በዚያን ወቅት በህብረ ብሄራዊ አስተሳሰብ የተደራጀ ማንም አልነበረም፡፡ ለረዥም ጊዜ በህብረ ብሄራዊነት መደራጀት ተቀባይነት የሌለው አስተሳሰብ ሆኖ የቆየበት ጊዜ ስለነበር፣ ያ ትልቁ አስተዋፅኦዬ ነው እላለሁ፤ እንደ ድርጅት፡፡
ሰላማዊ ትግል ብቸኛው አማራጭ መሆኑን፣ በሰላማዊ ትግል ውስጥም ህገ መንግስቱን ማክበርና ልዩነቶችን በግልፅ አውጥቶ መታገል እንደሚቻል… ይሄን አስተሳሰብ በተቃዋሚ ፓርቲዎችና በህዝቡ ውስጥ ማስረጽ ችለናል፡፡ እኛ ወደ ትግሉ ከመምጣታችን በፊት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአብዛኛው ህገ መንግስቱን የሚያዩበት መንገድ የተዛባ ነበር፡፡ ህገ መንግስቱን ያለመቀበል (አንዳንዶቹ እንደውም ቀዶ መጣል ነው የሚል አስተሳሰብ ነበራቸው) ሁኔታ ይታይ ነበር፡፡ ያንን ሁሉ ማሸነፍ ችለናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ያ ደግሞ ትልቁ አስተዋፅኦ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በኢትዮጵያ የተቃውሞ ትግል ውስጥ በበርካቶቹ ዘንድ የተለመደው መፈክር ነበር፡፡ ብዙዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ርዕዮት ዓለም፤ የፖለቲካ ፍልስፍና አልነበራቸውም፡፡ የፖለቲካ ፍልስፍናን በኢትዮጵያ የተቃውሞ ትግል ውስጥ አስተዋውቀናል፡፡ ማስተዋወቅ ብቻ አይደለም፤ ቀላል የማይባሉ ሰነዶችን አዘጋጅተናል፡፡
የፓርቲውን ፕሮግራም፣ በብሄራዊ እርቅ፣ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ---ወዘተ አምስት ጥራዝ ሰነድ አዘጋጅተናል፡፡ ከዚያም በተከታታይ ሰፊ ሰነድ አዘጋጅቷል ኢዴፓ፡፡ ቀደም ሲል ትግሉን የሚመሩት አስተሳሰቦች ሳይሆኑ መፈክሮች ነበሩ፡፡ ዛሬ ሁሉም የተቃዋሚ ፓርቲዎች የፖለቲካ ርዕዮት አለም ሰነዶች አሏቸው፡፡ ሌላው ኢዴፓ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያስተዋወቀው ለምርጫ ክብር መስጠትን ነው፡፡ በሰላማዊ ትግል ውስጥ ምርጫ ብቸኛው የስልጣን ማግኛ መንገድ እንደሆነ በማያሻማ መልኩ በተቃዋሚው ዘንድ እንዲሰርፅ አድርገናል፡፡ ለምርጫ የሚመጣ ማንኛውም ኃይልም አማራጭ ሃሳብ ይዞ እንዲመጣ (ማኔፌስቶ እንዲያዘጋጅ) አነቃቅተናል፡፡ የመጀመሪያ የማኔፌስቶ ባለቤት ኢዴፓ ነው፡፡ ለቅንጅትም ማኔፌስቶ ያበረከትነው እኛ ነን። ፈፅሞ የተዘነጋውና ትርጉም የለውም ተብሎ ይቆጠር የነበረውን የባህር በር ጥያቄ ዛሬ የሁሉም ፓርቲዎች መፈክር ማድረግ ችለናል፡፡ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ፒቲሽን አስፈርመን ለተባበሩት መንግስታት አቅርበናል፡፡ ውጤቱ ምንድን ነው ብለሽ እንዳትጠይቂኝ፡፡
ከ1997 ዓ.ም የምርጫ ጊዜ በኋላም ትግሉ አደጋ ደርሶበት በነበረበት ጊዜ ማህበረሰቡ ቆም ብሎ ጉዳዩን እንዲያጤን፣ በስሜት ሳይሆን በምክንያት እንዲታገል ሶስተኛው አማራጭን እንደ ሀሳብ ፓርቲው ይዞ መጥቷል፡፡ እነዚህ የጠቀስኩልሽ ነገሮች በሙሉ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የእኔ አሻራ አለባቸው፡፡
ቀጣዩ ምርጫ በ97 ዓ.ም. ከነበረው ምርጫ ጋር ሲነፃፀር ሊሰጠው የሚገባውን ግምት ሊገልጹት ይችላሉ?
በአሁኑ ጊዜ ያሉ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ አሸንፈው ስልጣን የሚይዙ ናቸው ብዬ አላምንም፡፡ ኢህአዴግን ግን ሊገዳደሩት ይችላሉ። በርከት ያለ ቁጥር አግኝተው ተወካዮች ምክር ቤት የመግባት እድል ሊኖራቸው ይችላል፡፡ በተረፈ ግን በተጨባጭ መንግስት ለመሆን የሚያስችል ቁመና አልፈጠሩም፡፡ ግልፅ ነው፤በቂ ህዝብ በደጋፊነት ማሰለፍ አልቻሉም፡፡ ኢህአዴግም ብዙዎች እንደሚያወሩት ዝም ብሎ ለጥቅማቸው፣ ለሆዳቸው፣ ለጊዜያዊ ፍላጎታቸው ያደሩ ሰዎች የተሰበሰቡበት አይደለም፡፡ እንደ ድርጅት በእምነት የሚከተሉት ቀላል የማይባል አባላቶች አሉት። የሚደረገው ውድድር ዝም ብሎ በአየር ላይ ካለ ድርጅት ጋር አይደለም፡፡ ውድድሩ በደንብ በህዝቡ ውስጥ መደላደል ይዞ ከሚንቀሳቀስ ድርጅት ጋር ነው። በፋይናንስ፣ በሰው ሃይል አቅም… መንግስት በመሆኑ ከሚፈጥረው ተፅዕኖ አኳያ በቀላሉ ልታሸንፊው የምትችይው ፓርቲ አይደለም፡፡
ከዚህ አኳያ ተቃዋሚዎችን ስታይ ደግሞ በተቃራኒው ነው፡፡ በሰው ሃይል ሲታዩ በተደጋጋሚ ተመሳሳይ አመራሮች የሚታዩበት እውነታ ነው ያለው፡፡ የተለያዩ ሰዎች በተለያዩ ጊዜ በቅለው ሲጎለብቱና ሲጠነክሩ አናይም፡፡ ሁሌም የተለመዱ ፊቶች፣ ሰዎች፣ አመራሮችን ናቸው ያሉት፡፡ ከአንዱ ፓርቲ ወደ አንዱ ፓርቲ ሲሄዱ ነው የምናው፡፡ ይሄ አንደኛው የድክመታቸው መገለጫ ነው፡፡ በአብዛኛው ከተማ ተከል ናቸው፡፡ ከአዲስ አበባና ከክልል ከተሞቹ ውጭ ገጠር ሄደው አርሶ አደሩን በቅጡ መድረስ የቻሉ አይደሉም፡፡ ለዚህ ምክንያት ሊደረደር ይችላል፡፡ አብዛኛው ማህበረሰብ በገጠር የሚኖር እንጂ በከተማ የሚኖረው 15 ፐርሰንቱ ነው። አጠቃላይ የከተማው 15 ፐርሰንቱ ቢደግፋቸውም እንኳን በምርጫ ሊያመጡት የሚችሉት ነገር የለም፡፡ እነዚህ ሃይሎች ለዚህ ያበቃቸው መሰረታዊ ምክንያት በ1997 ዓ.ም. የተፈጠረባቸው ችግር ነው ከተባለ--- አዎ። በርግጥ ብቸኛው ምክንያት አይደለም፡፡ አብዛኞቹ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአፈጣጠራቸው ችግር አለባቸው፡፡ በውስጣቸው ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ በደንብ ሰርጽዋል ብዬ አላምንም፡፡ በምርጫ ሲወርዱና ሰዎች ሲተኩ አናይም፡፡ በውስጣቸው ዲሞክራሲ ያላበበ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለህዝብ ዲሞክራሲ ለመስጠት ዝግጁ ናቸው ብሎ የሚያምናቸው የለም፡፡ ከባህሪም አኳያ ስታይው እየተካሄደ ያለው ትግል የአስተሳሰብ የበላይነትን ከመፍጠር ይልቅ የአርበኝነት መንፈስ ያየለበት ነው፡፡ የምናየው ኢህአዴግን ለመጣል የሚደረግ ትግል እንጂ አስተሳሰብን በህዝቡ ውስጥ አስርጾ መንግስት ለመሆን የሚያስችል አቅም ወይንም አቋም አይደለም፡፡ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ኢህአዴግ እንዲወድቅ መመኘት ብቻ ነው፡፡ በርዕዮት ዓለም አለምም ደረጃ ጠንከር ጠብሰቅ ብለው የሚሰሩ ነገሮች አይታዩም፡፡ እነዚህ እነዚህ ሁሉ ከመነሻቸው ድክመቶቻቸው ናቸው፡፡
በ1997 ዓ.ም. የተፈጠረው ችግር ደግሞ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በህዝብ ዘንድ የነበራቸውን እምነት እንዲያጡ አድርጓል፡፡ መከፋፈሉ፣ የተፈጠረውን እድል መጠቀም አለመቻላቸው፣ በኋላም ከእስር ቤት ወጥተው ራሳቸውን አጎልብተው በብቃት አለመራመዳቸው ---- ህዝብ የነበረውን እምነት ጥርጣሬ ላይ ጥሎታል፡፡
በዚህ ሁሉ ሂደት የኢህአዴግ አስተዋጽኦ ምንድነው?
የኢህአዴግን ችግርን ማየት ይቻላል፡፡ ኢህአዴግን እንደ ድርጅት ሳየው አንድ የተለየ ተልዕኮ ይዞ እንደመጣ ተዓምር አድርጐ ነው ራሱን የሚያስበው፡፡ ይሄንን የሚደግፈው ደግሞ ሰማዕታትንና የተከፈለውን መስዋዕትነት በመጥቀስ ስለሆነ፣ የአስተሳሰብ የበላይነትን ለመቀበል የተዘጋጀ ድርጅት አይደለም፡፡ ስለዚህ ለረጅም ዘመን በስልጣን ላይ ለመቆየት ሲል ማንኛውም ተፅዕኖ ያደርጋል፡፡ ቀድሞ ግብ አስቀምጦ፣ ከግቤ ከመድረሴ በፊት ማንኛውንም ሃይል መታገስ አልችልም ብሎ የሚያምን ድርጅት ነው፡፡ ምርጫ ይካሄዳል፡፡ ምርጫ ማድረግ ብቻውን ግን አንድን አገር ዲሞክራሲያዊ አያስብላትም፡፡ የምርጫ ውጤትም ትርጉም አለው፡፡
መንግስት በተቃውሞ ትግል ውስጥ ያለው ሚና መንግስት እንደ ኢህአዴግ፤ ኢህአዴግ እንደ ኢህአዴግ ማየት ይቻላል፡፡ መንግስት ብዙ ጊዜ መንግስትነቱና ኢህአዴግነቱ ይምታታበታል፡፡ የዚህ ስርዓት ፈጣሪም ባለቤትም ስለሆነ፣ ይሄ ስርዓት በሌላ አስተሳሰብ ተፈትሾ፣ ከስልጣን ወርዶ ስለማያውቅ ስርዓቱንና ኢህአዴግን መንካት አንድ ሆነዋል፡፡ ስርዓቱን ስትታገይ ኢህአዴግን መታገል ነው፤ ኢህአዴግን ስትታገይ ስርዓቱን መታገል ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች እየተፈራረቁ በመጡበት ሁኔታ መቼም ቢሆን የአስተሳሰብ ለውጥ በአገሪቱ ውስጥ እንዲሰርፅ አያደርግም፡፡ የኢህአዴግ አስቸጋሪ ባህሪዎች ትግሉን ውስብስብ፣ በጣም አድካሚና እልህ አስጨራሽ አድርገውታል፡፡
ስለ ህዝቡስ አስተያየትዎ ምንድነው?
ህዝቡም ጋር ስትመጪ ቀላል የማይባል ችግር አይደለም ያለው፡፡ ህብረተሰቡ ለፖለቲካ ያለው ዝንባሌ በፍርሃትና በስጋት የተሞላ ነው፡፡ የትግሉ ባለቤት መሆን አልቻለም፡፡ ከተቃዋሚዎች የሚቀርብበት ወቀሳ ሊኖር ይችላል፡፡ የማህበረሰቡ ንቃተ ህሊናና ለመረጃ ያለ ቅርበት በራሱ ችግር ነው፡፡ ትግሉ በእነዚህ መንገዶች በማይታገዝበት ሁኔታ የተቃዋሚዎች ሚና ደካማ መሆኑ አይቀርም፡፡ ተቃዋሚዎች ተጨባጭ ሁኔታው የማይፈቅድላቸው ነገር አለ፡፡ ስራውን ለመስራት የሚያስችል በቂ ምህዳር የለም፡፡ ከኢህአዴግ በኩል ያለው ተፅዕኖ በጣም ከባድ ነው፡፡ ማህበረሰቡ ውስጥም ራስን የትግሉ ባለቤት አድርጎ የሚገኘውን ጥቅም ለመጋራት በቂ ተነሳሽነት አታይም፡፡
የተቃዎሚ ፓርቲዎች ወዲያው ተዋህደው ወዲያው መከፋፈል፤ እርስ በርስ መወነጃጀል… ህብረተሰቡን ተስፋ አያስቆርጠውም ይላሉ?
በፖለቲካ አስተሳሰብ ዙሪያ ካልተሰባሰብሽ ጥላቻ ፖለቲካ ሊሆን አይችልም፡፡ ጥላቻ ሊወስድ የሚችለው መንገድ አለ፡፡ ኢህአዴግን መጥላት ብቻ በራሱ በቂ ርቀት ሊወስድ አይችልም፡፡ ፍልስፍና ሆኖ፣ የሰው ልብ ገዝቶ ትግልን ሊያጎለብትና ሊያጠነክር አይችልም፡፡ የመቻቻል፣ እውቅና የመስጠት፣ የተሞክሮ አለመኖር፣ የድርጅታዊ ብቃት ማነስ፣ የስልጣን ጥም---- እነዚህ ሁሉ የሚጫወቱት ሚና አለ፡፡ ከፖለቲካ ፍልስፍናው ውጪ፡፡ በአስተሳሰብ ዙሪያ ስትሰባሰቢ እምነትሽ አስተሳሰብ ይሆናል፡፡ ማንም ያንን አስተሳሰብ ቢያራምደው የአስተሳሰብ ባለቤት እስከሆንሽ ድረስ ችግር አይኖርብሽም፡፡ ሲጀመር የጠራ አስተሳሰብ አይደለም ያለው፡፡ ሁሉም የራሱን አስተሳሰብና እምነት በበላይነት ማራመድ ስለሚፈልግ ሽኩቻው የማያቋርጥ ነው የሚሆነው፡፡ ኢዴፓ ውስጥ ጥሩና ጠንካራ የምለው አስተሳሰባችን የጠራ መሆኑ ነው፡፡ እኛ ግለሰብ ላይ ሳይሆን በአስተሳሰባችን ላይ ነው የምናተኩረው። ቦታው ላይ በተቀመጠው ሰው ችግር የለብንም፡፡ በፓርቲ ውስጥ ክፍፍል የሚያመጡት እነዚህ ናቸው፡፡ በውስጣቸው በርካታ ችግር አለ፡፡ ፖለቲካ በትምህርት የሚመጣ ነገር አይደለም፡፡ በተግባር፣ በተሳትፎ ነው ፖለቲካን ማጠናከርና ማዳበር የሚቻለው። ድርጅት የሚጠነክረውና የሚጎለብተው በተሳትፎ ነው፡፡ ጥሩ ጥሩ ሰዎች ስለተሰበሰቡ አይደለም ፓርቲ ጠንካራ የሚሆነው። ፓርቲ በሂደት ነው ሙሉ የሚሆነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱ፣ የተቃውሞ ፖለቲካ ዕድሜው እና ተመክሮው አጭር ነው፡፡ የሚፎካከሩት ድርጅት ደግሞ ያለው ተሞክሮ ቀላል አይደለም፤ የስርዓቱ ባለቤትና ፈጣሪውም ነው፡፡ ስለዚህ ለተቃዋሚዎች ፈተና ነው፡
በቀጣዩ ምርጫ እንደ ተቃዋሚ ወይንም እንደተፎካካሪ ኢህአዴግን ሊገዳደረው የሚችል ተቃዋሚ ፓርቲ አለ ብለው ያስባሉ?
እኔ ኢዴፓ ነው፣ ነው የምለው፡፡ ኢዴፓ ውስጥ ስላለሁ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ የምርጫ ስርዓቱን ዴሞክራሲያዊ ካደረገው፣ የሚዲያ ተጠቃሚነትን ከፈጠረ፣ ሃሳቦች በደንብ እንዲንሸራሸሩ ሁኔታዎችን ካመቻቸ፣ ሰዎችን ማፈናቀሉን ካቆመ፣ ኢህአዴግን በአስተሳስብ በመገዳደር ብቁ ነው ብዬ የማስበው ድርጅት ኢዴፓ ነው፡፡ የጠራ የጠነከረ አስተሳሰብና አመለካከት ያለው ኢዴፓ ነው፡፡
በቅርቡ የተከሰሱ የግል የፕሬስ ውጤቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ጋዜጠኞችም ሃገር ጥለው ተሰደዋል፡፡ መጪው ምርጫ ነው----
ከትጥቅ ትግሉ በኋላ ለመጀመሪያዎቹ ሶስትና አራት አመታት በህዝቡ ዘንድ ኢህአዴግ ታማኝነት የነበረው ድርጅት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን በህዝብ ላይ ያለው እምነት ሁልጊዜ በጥያቄ የተሞላ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት አማራጭ ሃሳቦች አንዲጎለብቱና እንዲዳብሩ አይፈልግም፡፡ እናም ማድረግ የሚችለው መረጃዎች ወደ ህዝብ የሚደርሱበትን ድልድዩን ማጥፋት ነው፡፡ የግል ጋዜጦች፣ መጽሔቶች ላይ የሚደርስባቸው ቅጥቀጣ እነሱ የተለየ አስፈሪ ስለሆኑ አይደለም፡፡ በማህበረሰቡና በአስተሳሰቡ መሃል ድልድይ በመሆናቸው ነው፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ እነሱ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ድልድዩን ለመስበር ነው፡፡ ህዝብ ባወቀ በነቃ በተደራጀ ቁጥር እንደሚፈታተነው ያውቃል። ህዝቡን ያወናብዱብኛል፣ ህዝቡን ያሳስቱብኛል፣ እኔ ከምፈልገው መንገድ ያስወጡብኛል የሚል ስጋት አለው። ስለዚህ የህዝብ ልሳን፣ አንደበት ሆነው በማገልገል ላይ ያሉትን ጋዜጦች፣ መጽሔቶች ያዳክማል፡፡
አሁን በቅርቡ መጽሄቶች ላይ የደረሰው ነገር ለእኔ ግልጽ ነው፡፡ ኢህአዴግ አለማቀፍ ተጽዕኖውን አይፈልግም፤ ምክንያቱም ተበዳሪ መንግስት ነው፡፡ በተለያዩ መልኩ የሚደርሱበትን ተፅዕኖዎች ከወዲሁ ለመቋቋም እቅድ አድርጎ ኢህአዴግ የወሰደው የሚመስለኝ፣ የክስ ቻርጁን በግላቸው ከመስጠትና ከማሰር በፊት በቴሌቪዥን እንደ ቀይ ሽብር ማወጅ ነው፤ እናም ተነስተው ይጠፉለታል፡፡ ከዚያ ተገላገልኩ ነው የሚለው፡፡ ሙከራው በከፊል ተሳክቷል፡፡ ጋዜጠኞቹ ጥለው እየሄዱ ነው፡፡ በአዋጅ መልክ ክስ ከቀረ 23 ዓመቱ ነው፡፡ ደርግ ነበር ይሄን ያደርግ የነበረው፡፡ እነዚህ መጽሔቶች በብዙ አቅጣጫ ከፋይናንስ፣ ከአደረጃጀት፣ ከሰው ሃይል አኳያ ቀላል የማይባል ጉልበት የፈጠሩ ናቸው፡፡ ባለፈው አምስት ዓመት እንዴት ህትመታቸው፣ ስርጭታቸው፣ እንደሚጎለብትና እንደሚጠነክር ያውቃል። እነዚህን ማዳከም ነው የያዘው፡፡ በእነሱ ምትክ አዲስ ጋዜጣ ያስገባል፤ አቅማቸው ደካማ ነው፣ እየተቆራረጡም እየተንጠባጠቡም ነው የሚቀጥሉት፡፡ በበቂ ደረጃም ህዝቡን አይደርሱም፤ ይቆማሉ፡፡ ስለዚህ ቀጣይነት፣ ወጥነት፣ ተከታታይነት ባለው መንገድ የሚታገሉትን መጽሔቶች ነው እንዲሰደዱ ወይም ፍርድ ቤት እንዲቆሙ ያደረገው፡፡ ይሄ ምርጫው ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ከመፈለግ ውጭ አይደለም፡፡ ሰው ይወናበዳል፣ ተወናብዶ እኔን አይመርጠኝም፤ የሚል ስጋትና ጥርጣሬ ስላለው ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ኢህአዴግ ከእሱ ቁጥጥር ውጪ የሆነ ማንኛውም ሃሳብን ለማራመድ የሚያገለግል መሳሪያ የሚፈልግ አይመስለኝም፡፡ እንደ እኔ አስቡ፣ እንደ እኔ ገምቱ የሚለው ደግሞ አያስኬድም፡፡
በዓለም ላይ የየሀገሩ ስጋት ተብለው የሚጠቀሱ የሀይማኖት፣ የዘር፣ የአምባገነናዊ ስርዓቶች አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ስጋት የትኛው ነው?
ሰዎች በተፈጥሮዋቸው አማራጭ ይፈልጋሉ፤ መፈለግ ብቻ ሳሆን አማራጭንም መፈተሽ ይሻሉ፡፡ አንድ መንግስት ለረዥም ጊዜ እንዲገዛቸው ፈቃደኛ አይደሉም፤ ይሰለቻሉ፡፡ ሰው ስሜቱን፣ ሃሳቡን፣ ፍላጎቱን እንዲያወጣ፣ እንዲገልጽ የሚያደርጉት ጋዜጦች፣ መጽሔቶች ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በተዳከሙ ቁጥር በሰው ውስጥ ያለውን ነገር ለማወቅ እንዴት ይቻላል? ይሄ ደግሞ ወደ አመጽ፣ ወደ አለመረጋጋት ለመለወጥ የማንንም ይሁንታ አይጠብቅም፡፡ በደህንነትና በስለላ መዋቅር የሚቆም አይደለም፤ እንደ ጋዜጦችና እንደ ፓርቲዎች፡፡ ፓርቲዎችን አመራሮችን ሰብስቦ አስሮ፣ ትግሉን ማዳከም ይቻላል፡፡ በህዝብ ውስጥ ያለ ቁጣና ብስጭትን ግን መቆጣጣር አይቻልም፡፡ አንዳንዴ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩ ግጭቶች የዚያ ውጤት ናቸው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ችግር ይገጥማታል ብዬ አላስብም፤ ሊሆንም አይችልም፤ ሆኖም አያውቅም፡፡ ግን ስርዓቱ አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ ስርዓቱ በዚህ መንገድ ያሉትንም እድሎች እያጠበበ፣ እየጨፈለቀ በሄደ ቁጥር ሰዎች በውስጣቸው የሚቀጣጠለው ነገር የበለጠ እየጠነከረ እየጎለበተ ነው የሚሄደው፡፡ ጥያቄያቸው እያደገ ነው የሚመጣው፡፡ የተገኘውን እድል ተጠቅመው ፍላጎታቸውን ለማራመድ ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ይህችን አገር ወደ መልካም አስተዳደርና ወደ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ለመውሰድ ከተፈለገ፣ ተጨባጭ ሁኔታው በሚፈቅደው ልክ አሳታፊ የሆነ ስርዓት መገንባት ያስፈልጋል፡፡ ግዴታ ነው፡፡
ግብጽን ብናይ እስከ አሁን ድረስ መውጣት ባልቻለችበት የፖለቲካ ቀውስ እየታመሰች ነው ያለችው። ቀደም ብሎ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግብጽ ውስጥ በበቂ ሁኔታ ተደራጅተው፤ ትክክለኛ ቦታቸውን አግኝተው፣ ሃሳባቸውን ለመግለፅና ለማራመድ በሩ ክፍት ቢሆን ኖሮ፣ በአመጽና በህዝብ ቁጣ ሳይሆን በተቃዎሚ ፓርቲ ሃይሎች የስልጣን ሽግግር ሀገሪቱ ቀጣይነትዋን ታረጋግጥ ነበር፡፡ ህዝቡ ስሜቱን የገለጸው በምርጫ አይደለም፤ በአመጽ ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መኖራቸው ጥቅሙ ህዝብ ፍላጎቱን በምርጫ እንዲገልፅ እድል ይሰጠዋል፡፡ ስለዚህ ለእኔ የሚታየኝ ስጋት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ መንገድ አልተሰራም፤ ልማት አልተካሄደም እያልኩሽ አይደለም፡፡ ስራ አጥነትን ለመቀነስ እንቅስቃሴ የለም፣ ማለቴ አይደለም፡፡ ግን በዚህች አገር ጉዳይ ያገባኛል ብሎ የተነሳ፣ የእኔ አማራጭ ነው የሚሻለው የሚልም አለ፡፡ ይሄ ሰው ሃሳቡ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ተደምጦ፣ በምርጫ ተሸንፎ ካልሆነ፣ በጉልበት በማፈን እንዳይራመድ ከተደረገ መጨረሻ ላይ ህዝቡ ውስጥ የሚፈነዳው ሌላ ነገር ነው፡፡
የእኛ ስብሰባ ችግር “አልኮል “ኮሌስትሮል እና “ፕሮቶኮል” ናቸው
- የኢራናውያን አባል
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ የሰርከስ ትርዒት ይታይ ነበር፡፡ ከሰርከሱ ጋራ አንድ ግዙፍ ሰው ታየ፡፡ የትርዒቱ አካል ነበር፡፡
ይህ ግዙፍ ሰው አንድ ብርቱካን ያወጣና እንደ ጉድ ይጨምቀዋል - እስከመጨረሻው እንጥፍጣፊ ጠብታ ጨመቀው፡፡ ጉድ ተባለ ተጨበጨበ!
ከዚያ የፕሮግራሙ መሪ፤
“ይህ ታላቅ፣ ጡንቸኛና ጠንካራ ሰው ከጨመቀው በላይ ጨምቆ አንዲት ጠብታ ብርቱካን ጭማቂ ሊያወጣ የሚችል ሰው ካለ ወደዚህ ይምጣ?!” ሲል ጠየቀ፡፡
ሁሉም ፈራ፡፡
ቀጠለ የፕሮግራሙ መሪ፤
“እሺ አንድ ተጨማሪ ነገር ላክል - አንዲት ቅንጣት ላወጣ ሽልማት እሰጣለሁ፡፡ አንድ ሺ ዶላር!” አለ ጮክ ብሎ፡፡
ብረት በማንሳት የሚታወቅ ጉልቤ መንዲስ ጡንቸኛ፤ ወደ መድረኩ እየተጐማለለ መጣ፡፡ ከፕሮግራም መሪው የተጨመቀውን ብርቱካን ተቀበለ፡፡
ከዚያ ባለ - በሌለ - ጉልበቱ እንደ ጉድ እየጨመቀ፤
“እንዴት እንደምፈጠርቀው አሁን ታያላችሁ!” አለና በሁለት መዳፉ ደፈጠጠው፡፡
ግን ምንም ጠብ አላለለትም፡፡
ቀጠለና አንድ ግንበኛ ጡንቻውን ወጣጥሮ፤
“ይሄን ይሄንማ ለእኛ ተዉልን!” አለና ከብረት አንሺው ተቀበለ፡፡
ደጋግሞ ጨመቀው፡፡ አለው! አለው! ላብ - በላብ ሆነ! “ተሸንፌአለሁ” አለና ወረደ፡፡
“ሌላ የሚሞክር አለ?” አለ የፕሮግራም መሪው፡፡
“አትችሉም! ያልኳችሁ ለዚህ ነው”
ከህዝቡ መካከል አንድ አጭር፣ ሲባጎ የመሰለ ኮስማና ከወደኋላ ብድግ አለ፡፡
“እኔ ልሞክር?” አለ፡፡
አገር ሳቀ፡፡ መሪውማ ዕንባው እስኪፈስ ነው የሳቀው፡፡ ሁሉ ሰው የመገላመጥ ያህል እየተገላመጠ አየው፡፡
ቀጫጫው ሰውዬ ግን በኩራት ራሱን ቀና አድርጎ በህዝቡ መካከል ሰንጥቆ ወደ መድረኩ ወጣ፡፡
“አመረርክ እንዴ?” አለው የመድረኩ መሪ፡፡
“አሳምሬ!” አለ ቀጫጫው፡፡
ቀጫጫው ብርቱካኑን መጭመቅ ሲጀምር ሳቁ ቀስ በቀስ ጋብ አለ፡፡
የሚገርም ነገር ተከሰተ፡፡ ወለሉ ላይ ጠብ ጠብ ማለት ጀመረ ብርቱካኑ፡፡
የፕሮግራሙ መሪ እጅግ በጣም በመደነቅ፤ “እንዴት ይሄን ተዓምር ልትፈጥር ቻልክ? አንተ ለራስህ ከአፍ የወደቀች ፍሬ የምታክል?” ሲል ጠየቀው፡፡
ቀጫጫውም፤
“አይ ጌታዬ እኔ የሂሳብ ሰራተኛ - አካውንታንት ነኝ!” አለው፡፡
* * *
ጎበዝ! ባገራችን የመጨረሻዋን ነጠብጣብ ጭማቂ ሂሳብ የሚያሰላ ሰው ባገኘን እንዴት በታደልን ስንቱ በተጋለጠ!
ጉልበት እውነትን አይበልጥም! እርግጥ ጊዜያዊ ጡንቻ ዘለዓለማዊ ሀቅን ይበልጥ የሚመስለን ጊዜ ይኖር ይሆናል፡፡ ግን የዓለምን ታሪክ መለስ ብሎ ማየት ትልቅ ትምህርት ይሆነናል፡፡ ናፖሊዮን ቦናፓርት፣ ሪቻርድ ባለ አምበሳ-ልቡ (The Lion – hearted) ታላቁ እስክንድር፣ ጁሊየስ ቄሣር፣ ጄንጂስ ካሃን … ሁሉም ታላላቅ ነበሩ፡፡ ሁሉም “ከሸክላነት ወደገደልነት” ተሸጋገሩ፡፡ ‘መኳንንትም ሲሻሩ ህዝብ ናቸው’ እንዲል አንጋረ ፈላስፋ። አንድን ህዝብ ለመምራት ታላቅነት በምንም መልኩ ሀቀኛ መለኪያ አይሆንም! ታላቅነት ከየት ይመነጫል? ቢባል አንድና አንድ መለኪያ ብቻ የለውምና! ታላቅ ነኝ ብሎ ዘለዓለማዊነት የተጎናጸፈ የለምና … They mistook longevity for immortality ይሏልና፡፡ ረዥም ዘመንን ከዘለዓለማዊነት ጋር ያምታቱታል ነው ነገሩ!
“የጾምነው ነገር ቢበዛም
መፈሰኪያው ቀን አይቀርም!”
ይላል አንድ ፆመኛ ገጣሚ፡፡ ዕውነት ነው፡፡ እንደሶስተኛው ዓለም ባለ አገር፤ ከፍስኩ ፆሙ ይበዛል። ዲሞክራሲን ከፈሰከው የፆመው ይበዛል፡፡ ፍትህን ካየው ያላየው ይበዛል፡፡ ሀቅን ካገኘው የፆመው ይበረክታል። መልካም መስተዳድርን ከተጎናፀፈው የተራቆተው ይበዛል፡፡ ዞሮ ዞሮ መፆም ተለምዶ ፍስክን አርቆ ማየት ልክ እየመሰለ መጥቷል፡፡ መንገድ ከመጀመራችን በፊት የመንገዱን እርቀት እንመትር ቢባል የሚሰማ ጠፍቷል - ከሁሉም ወገን! አንዴ “እናሸንፋለን”፤ ካሉ “ተነጋግረን እንስማማለን” “እንደሰለጠነ ሰው ተቀራርበን እንፈታዋለን” ማለት እርም ሆኗል፡፡ ስለአገር ምን አገባን”፣ “ስለህዝብ ምን አስጨነቀን?” ማለት ወግና ልማድ የሆነ ይመስላል - በተግባር የለምና!
ዛሬም ከሼክስፔር ጋር፣ በፀጋዬ ገ/መድህን አንደበት፤
“ዛሬ ለወግ ያደረግሽው፣ ወይ ለነገ ይለምድብሻል
ልማድ ፊት እንዳሳዩት ነው፣ ወይ ይጠፋል ወይ ያጠፋል
ከርሞም የሰለጠነ እንደሁ፣ ተፈጥሮ ይሆናል ይባላል” ማለት ተገደናል፡፡
የክረምቱን ሰዓት ስናስተውል፤
“ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት
ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት”
መባሉ ጊዜን አመላካች ብቻ ሳይሆን ያለፈ ድርጊትን አመላካችና ለንጋትና ለመስከረም ዝግጁ መሆንንም ጠቋሚ ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን እንደተምኔት ሳይሆን እንደተጨባጭ ነገር ማስተዋል ይገባናል፡፡ ፅንፍና ፅንፍ እየቆሙ፣ ማዶና ማዶ የጎሪጥ እየተያዩ፣ በደፈረሰ ልብ እያሰሉ፣ የምንመኘውን ዓይነት ለውጥ ማምጣት ከባድ ነው፡፡ ከቶውንም፤ በትንሹ የምንመኛቸውን ነገሮች እንኳ በእጃችን ማስገባት አዳጋች ይሆናል፡፡
የእንግሊዙ ፈላስፋ፣ መሪና ጠበቃ ፍራንሲስ ቤከን፤
“የምንፈልጋቸውና የምንጓጓላቸው ነገሮች ጥቂት፤ የምንፈራቸው ግን ብዙ ሲሆኑ፣ የአዕምሮ ደረጃችን ጎስቋላ ሆነ ማለት ነው” ይለናል፡፡
ግባችንን በውል ለመምጣት የእኛን መንገድ ብቻ “አንደኛ ነው!” የእነ እገሌ ውራ ነው” እያልን በአፈ ቀላጤዎቻችን ብናወራ ራስ-በራስ መሸነጋገል እንጂ ሁነኛ ፍሬ የሚያፈራ ጉዞ አይሆንም፡፡
ጆርጅ በርናርድ ሾው፣ አየርላንዳዊው ፀሐፌ-ተውኔትም “ሰው ነብርን ሲገል ስፖርት ነው ይለዋል፡፡ ነበር ግን ሰውን ሲገል ጭካኔ ነው ይባላል” ይለዋል፡፡ ዕይታችን “ወደ ገደለው” መሆኑ ነው፡፡
ምንጊዜም ሁሉም የየራሱን እንቅፋት መደርደሩ አይቀርም፡፡ በየዘመኑ የምናየው ነው፡፡ ዱሮ ቀኝ መንገደኞች፣ አምስተኛ ረድፈኞች፣ ፀረ-ህዝቦች፣ ሥርዓተ-አልበኞች፣ አስመሳዮች፣ አድርባዮች ወዘተ ይባል እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ይባል የነበረው በሀቅ ነው ወይ? ብሎ ጠይቆ አዎንታዊ ምላሽ ማግኘት ግን ዘበት ነው፡፡ ለሥልጣን መቆያነቱ ግን አያጠያይቅም፡፡ ኢራናውያን እንቅፋቶቻቸውን ሲደረድሩ በየዘመኑ የሚያቅን “የስብሰባ ጠላቶች - አልኮል፣ ኮሌስትሮል፣ ፕሮቶኮል፤ ናቸው” ይላሉ፡፡ እነዚህ እኛንም ሳይመለከቱን አይቀሩምና በጊዜ መጠንቀቅ ነው!!
“ጐጆ እቁብ” የአባልነት ምዝገባ ላልተወሰነ ጊዜ መቆሙን አስታወቀ
ለሁለት ሳምንታት የዘለቀው የ“ጎጆ እቁብ” የአባልነት ምዝገባ ላልተወሰነ ጊዜ ማቆሙንና ገንዘብ የመሰብሰብ ስራው እንዳልተጀመረ መስራቹ አቶ ናደው ጌታሁን የገለፁ ሲሆን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ ከእቁቡ ጋር ይሰራሉ የተባሉ አምስት ባንኮች ምንም አይነት የሥራ ግንኙነት እንደሌላቸው አስታውቀዋል፡፡
“ጐጆ እቁብ” ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ፤ አምስት ባንኮች የጐጆ እቁብ ሰብሳቢ ተደርገው የተገለፁት በስህተት መሆኑን ጠቁሞ ጐጆ እቁብ ግን ስራውን ለመስራት የሚያስችል ዝግ ሂሳብና የቁጠባ ሂሳብ በተለያዩ ባንኮች መክፈቱን አመልክቷል፡፡
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በቡና ኢንተርናሽናል ባንክ፣ በአዋሽ ባንክ፣ በንብ ባንክና በአቢሲኒያ ኢንተርናሽናል ባንክ ዕቁቡን ለመጀመር ሂሳብ መከፈቱን የገለፁት የእቁቡ መስራችና ዳኛ አቶ ናደው፤ ገንዘብ የመሰብሰብ ስራው እንዳልተጀመረና የአባላት ምዝገባ ላልተወሰነ ጊዜ ማቆማቸውን አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ፤ መስራች ነኝ የሚሉት ግለሰብ ስራውን ከባንኩ ጋር ለማከናወን ስምምነት እንደፈፀሙ በተለያዩ ሚዲያዎች መግለጫ መስጠታቸውንና በተለያዩ በራሪ ወረቀቶች ላይ የባንኩን ሎጎ አሳትመው ማሰራጨታቸውን ጠቅሶ ባንኩ ከጎጆ እቁቡ ጋር ምንም አይነት የስራ ግንኙነት እንደሌለው አስታውቋል፡፡ ከእቁቡ ጋር አብሮ ይሠራል የተባለው የቡና ኢንተርናሽናል ባንክ የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ሃላፊ አቶ አበባው ዘውዴ በበኩላቸው፤ ባንካቸው ከጐጆ እቁብ ጋር ምንም አይነት የስራ ስምምነት እንደሌለው ነገር ግን በሶስት ግለሰቦች ስም በቅንፍ ጐጆ እቁብ ተብሎ በአንደኛው የባንኩ ቅርንጫፍ የዝግ ሂሳብ መከፈቱን ገልፀዋል፡፡
በተመሳሳይ ከእቁቡ ጋር አብረው ይሰራሉ የተባሉት አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ አቢሲኒያ ባንክና ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ኃላፊዎች የእቁቡ መስራች እንዳነጋገሯቸው ጠቁመው አብረው ለመስራት ግን ስምምነት አለመፈፀማቸውን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል።
በግድቡ ዙሪያ የሚካሄደው የሶስትዮሽ ድርድር ሰኞ ይቀጥላል
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ለመምከር ታስቦ በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን መካከል የተጀመረውና ከስምንት ወራት በፊት ተቋርጦ የነበረው የሶስትዮሽ ድርድር፣ በመጪው ሰኞ በሱዳን ርእሰ መዲና ካርቱም እንደሚቀጥል ኢጅፕት ኢንዲፐደንት ትናንት ዘገበ።
ከግብጽ የመስኖ ሚኒስትር የተገኘውን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ የሶስቱ ሃገራት የውሃ ሚኒስትሮች በሚሳተፉበት በዚህ ድርድር፣ የግብጽ መንግስት በአባይ ወንዝ የመጠቀም ታሪካዊ መብቱን ባስከበረ መልኩ በአገራቱ መካከል ያለውን ወዳጅነት ለማጠናከርና ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት ተዘጋጅቷል፡፡
ድርድሩ ጊዜን የሚፈጅ፣ ተደጋጋሚ ስብሰባዎችን ማካሄድን እንዲሁም የሁሉንም ተደራዳሪ አካላት ፖለቲካዊ ይሁንታና በመተማመን ላይ የተመሰረተ አካሄድ የሚጠይቅ ከባድ ተልዕኮ እንደሚሆን ዘገባው ከሚኒስቴሩ ያገኘውን መረጃ ጠቅሶ ገልጧል፡፡
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝና የግብጹ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ባለፈው ሰኔ በኢኳቶሪያል ጊኒ በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ላይ በተገናኙበት ወቅት፣ ተቋርጦ የነበረውን የሶስትዮሽ ድርድር እንደገና ማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ መምከራቸውን ዘገባው አስታውሷል።
ኮካኮላ 50ሺ ሰዎች ተጠቃሚ የሚያደርግ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ይፋ አደረገ
የኮካኮላ ፋውንዴሽንና ወርልድ ቪዥን ሪፕሌኒሽ አፍሪካ ኢኒሼቲቭ በተባለው
ፕሮጀክት አማካኝነት በትግራይ ክልል የህብረተሰቡን የጤና ሁኔታ ለማሻሻልና የማያቋርጥ ንፁህ ውሃ ለማቅረብ ያስችላል ያለውን የ19 ማሊዮን ብር ፕሮጀክት ይፋ አደረገ፡፡
ፕሮጀክቱ የአፍሪካ ኢኒሼቲቭ ሶስተኛው ፕሮጀክት ሲሆን ኢንሼቲቩ በኢትዮጵያ ላለፉት ሶስት አመታት ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን ነድፎ በአማራ፣ በደቡብ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በሚገኙ ሰባት የገጠር ወረዳዎች 28 ሚሊዮን ብር በማውጣት ማከናወኑን በትናንትናው እለት ኩባንያው በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡ በዚህም ለ73,400 ዜጐች ንፁህ የመጠጥ ውሃ ማቅረብ መቻሉ ተመልክቷል፡፡
ፕሮጀክቱ ኮካኮላ ኩባንያ እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ ለ2 ማሊዮን አፍሪካውያን ንፁህ የመጠጥ ውሃ ለማቅረብ የገባው ቃል አካል መሆኑ የተገለፀ ሲሆን በትግራይ የሚተገረው ፕሮጀክት 50 ሺህ ሰዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል፡፡
አዳዲሶቹ አማተሮች ይወለዱ ዘንድ እናምጥ!
ባለፈው ሳምንት የአዲስ አድማስ እትም ዳዊት ንጉሱ ረታ፤ የአማተር የኪነ-ጥበብ ክበባቶቻችንን ጉዳይ አንስቶ እንነጋገርበት ዘንድ ጥሪውን አቅርቧል። ዳዊት በአባቱ ሥም አቋቁሞት በነበረው (በኋላ “እሸት” ወደተሰኘ ማህበር ተቀይሯል) እኔም ተሣታፊ ነበርኩ፡፡ ምንም እንኳን በጀመርኩበት ባልዘልቅም ጥሩ የጥበብ ወዳጅ እንድሆን አስችሎኛል፤ ዳዊት እጄን ይዞ ከኪነ ጥበብ ጋር አወዳጅቶኛል፡፡ እናም ታዲያ እንደነዚያ አይነቶቹ አማተር ክበባት እንደዋዛ የመጥፋታቸው ነገር ቢያሳስበው ዳዊት ብዙ ጠይቋል፡፡ በእኔ እምነት እነዚያ ክበባት የመጥፋታቸው ሰበበ ምክንያት በርካታና ዘርፈ ብዙ ነው፤ በጉዳዩ ላይ መወያየታችን የዘገየ ቢሆንም ምን ቢመሽ ጨርሶ አልጨለመምና፣ ዳዊት በቀደደው ገብቼ ጥቂት የማምንበትን ለማለት እሞክራለሁ፡፡
በከተማችን አዲስ አበባና በሌሎች ክልሎች ወጣቶች ለጥበብ ያላቸውን ፍላጎት፣ ተሰጥዖና ዝንባሌን መነሻ እያደረጉ፣በራሳቸው ተነሳሽነት በት/ቤቶችና ቀበሌ አዳራሾች የተፍጨረጨሩበትና ክበባቶቹ በርክተው የተስተዋሉበት ወቅት እንደነበረ ባይዘነጋም፣ ከ1990ዎቹ አጋማሽ ወዲህ እየተቀዛቀዙ… አሁን አሁን ከእነ አካቴው ጠፍተዋል። በእነዚያ ዓመታት ተሰጥኦና ዝንባሌን መሰረት አድርገው ከጥበብ ጋር በጥልቀት እያስተዋወቁ፣ በሙያዊ ሥነ ምግባር እያነፁ፣ እምቅ ችሎታንና ብቁ ክህሎት እያስታጠቁ፣ ልከኛ ጥበበኞችን ለመድረኮቻችን ያበረክቱ የነበሩ ክበባት ዛሬ ላይ የሉም፡፡ አፍላ ጥበበኞችን የሚኮተኩቱ፣ ጥሩ ባለሙያ የማያመርቱ ክበባት እንዲሁ ዝም ብለው አልከሰሙም፤ ደጋፊ፣ አጋዥና “አለሁ” ባይ እያጡ፣ ተሰባስቦ ጥበብን መከወኛ ሥፍራ እየተነፈጉ፣ ትላንት ኮትኩተው ያሳደጉት የዛሬው ዝነኛም አዙሮ የመመልከት አቅም አጥ ሆኖ፣ ውለታቸውን እየዘነጋ የሚተኩትን ተከታይ ባለተራዎችን ማገዝ የተሳነው የመሆኑን ነገር እንደ አንድ የመክሰማቸው ምክንያት ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡
በእግር ኳስ የስፖርት ሜዳ ተጋጣሚ ቡድኖች ወደ ሜዳ ሲገቡ ታዳጊ ህፃናትን አስከትለው የሚገቡት ለምን ይመስለናል? ተኪነትን ለማጎልበትም አይደል? በአገራችን የጥበብ ሜዳችን ላይስ? ገጣሚና ጋዜጠኛ ነቢይ መኮንን በአንድ ግጥሙ “የሀገሬ ሰው እኮ መሠላል አወጣጥ ያውቃል” እንዳለው፤ የሃገሬ ዝነኛ ከያኒያን መሰላሉን እየወጡ የረገጡትን እየነቀሉ ይሆን? ለአማተር ክበባቶቻችን መክሰምና ለአዳዲስ ክበባቶች አለመፈጠር እንደ ጉልህ ምክንያት ሊወሰድ የሚገባው ሌላ ነገር መንግስታዊ ቸልተኝነትና ዝንጋታ ነው! ጥቂት ማሳያዎችን እንመልከት፡- መንግስት የወጣቶችን የሥራ አጥነት ለመቅረፍ “የጥቃቅንና አነስተኛ ሥራዎች ልማት ፕሮግራም” አዘጋጅቶ እየተገበረ እንደሆነ ይታወቃል። ግን ደግሞ በኪነ ጥበባዊ ሥራዎች ላይ ተደራጅቶ ስለመስራት መንግስታዊ ፕሮግራሙ የሚለው ነገር የለም፤ ቴአትር ለማዘጋጀት፣ የግጥም መፅሐፍ ለማሳተም ወይ ደግሞ ፊልም ሰርቶ ለማሳየት ብድር አይሰጥም… ማበረታቻም የለም፡፡ በመላው አገሪቱ ባሉ ክልሎችና ከተማዎች (እስከታችኛው መንግስታዊ መዋቅር ድረስ) ባህልንና ኪነ-ጥበብን የማስፋፋት ኃላፊነት የተጣለበት በአዋጅ የተቋቋመ “ባህልና ቱሪዝም መ/ቤት” ቢኖርም አማተር ክበባትን ለመፍጠር ሲጨነቅ አይስተዋልም፡፡
በአንድ ወቅት እኔው እራሴ ወደ አዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሄጄ፣ አማተር ክበብ ለመመስረት ሞዴል /መነሻ/ መተዳደሪያ ደንብና ሌሎች መስፈርቶች ጠይቄ ማግኘት አልቻልኩም፤ ግን ደግሞ ካፒታል ኖሮት፣ ንግድ ፈቃድ አውጥቶና ሰፊ በጀት መድቦ ፕሮሞሽንና የፊልም ፕሮዳክሽን በማቋቋም በጥበባዊ ንግድ ስራ ላይ መሰማራት ለሚፈልግ ሰው፣ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ለመስጠት ግልፅ መሥፈርት ወጥቶ፣ ባለሙያ ተቀጥሮ፣ የስራ ሂደት ቢሮ ተከፍቶላት አይቻለሁ፡፡ ይህ ቢሮ በከተማ ደረጃ ከቅርብ አመታት ወዲህ አማተሮች የሚወዳደሩበት የባህል ፌስቲቫል በአመት አንድ ጊዜ ብቻ እያዘጋጀ ይገኛል፤ ለአማተር የኪነ ጥበብ ባለሙያ አፍላ ወጣቶቻችን ነፃና የአጭር ጊዜ የተሰጥኦ ማጎልበቻ የሥልጠና እቅድ ይዞ መስራት እንኳን አልተቻለውም፡፡
ቴአትር ቤቶቻችንም ለአማተሮቹ በራቸው ዝግ ነው፤ የተተመነውን የአዳራሽ ኪራይ ክፍያ መክፈል ካልቻሉ በስተቀር በነፃ ወይም በዝቅተኛ የኪራይ ዋጋ መድረኮቻቸውን አይቸሩም፡፡ በየት/ቤቶቻችን “የተጓዳኝ ትምህርት ክፍል” በሚል የሚኒ ሚዲያ፣ የቴአትርና የሙዚቃ ክበባት ተመስርተው ተማሪዎች ከመደበኛው የትምህርት ክፍለ ግዜ ውጪ ይሳተፉባቸው የነበሩ ቡድኖች ዛሬ የሉም፤ ቢኖሩም በጣት የሚቆጠሩና የተፋዘዙ ናቸው፡፡ በርካታ የሬድዮ ጣቢያዎች፣ ሁለትና ሶስት የቴሌቪዥን ቻናሎች እያሉን ለአማተሮች የሚሆን ነፃ የአየር ሠዓት ግን የለንም፤ የተለያዩ የኪነ-ጥበብ (በተለይ የሥነ-ፅሁፍ) ሥራዎች በአማተሮች አማካኝነት ይቀርቡባቸው የነበሩ ማዕከላት እነ ፑሽኪን (የሩሲያ የሳይንስና ባህል ማእከል)፣ ኢትዮ አሊያንስ ፍራንሴስ እና ገተ… እንኳን ዛሬ ዛሬ ተፋዘዋል፡፡ እነዚህም ቢሆኑ በውጭ ሀገራት ኤምባሲዎች መልካም ፈቃድ የተቋቋሙ ማዕከላት መሆናቸውን ስናስተውል እንደ ሀገር አማተሮች ምን ያህል እንደተዘነጉ እንረዳለን፡፡ አስገራሚው ነገር ደግሞ ትላንት ከትላንት ወዲያ የመከወኛና የመሰባሰቢያ ሥፍራ ባልነበረበት እንደ አሸን የፈሉ ክበባት፣ ዛሬ በተለይ በከተሞቻችን “የወጣት ማዕከላት” በየመንደሩ ተገንብተው እያለ፣ የማዕከላቱ አዳራሾች ተሰብሳቢ ጭብጨባ እንጂ የአማተሮቻችን ድምፅ አይሰማባቸውም፡፡
ለምን?? የሙያ ማህበሮቻችንስ? የደራሲያን ሆነ የፊልም ሰሪዎች፣ የሙዚቀኞች ይሁን የቴአትር ባለሙያዎች… ብቻ የቱም ይሁን፤ ጊዜ ቀንቷቸው በፕሮፌሽናል መድረኩ ላይ ላሉት እንጂ ለአማተሮቹ ምን ቦታ አላቸው? ምንም! በደራሲያን ማህበር አባል ለመሆን መፅሐፍ ማሳተም እንጂ መፃፍና ሥነ-ፅሁፋዊ ተሰጥኦ እንደመስፈርት አይቆጠርም፡፡ የትላንቶቹ አማተር ክበባት ለበርካታ ማህበራዊ ችግሮቻችን መወገድ ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ የኤችአይቪ/ኤድስ በሽታ ዛሬ ላይ ስርጭቱ እንዲቀንስ፣ ታማሚዎች ላይ ይደርስ የነበረው አድሎና መገለል እንዲቀር እነዚያ ክበባት መዝሙር ዘምረው፣ ድራማ ሰርተውና ግጥም ፅፈው ህብረተሰቡ አዎንታዊ የባህርይና የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጣ ተረባርበዋል፡፡ ኤችአይቪ/ኤድስ የስርጭቱ መጠን እየቀነሰ ቢመጣም ሌሎች ችግሮች የሉብንም? የባህልና ትውፊት መጥፋቱስ? ከምዕራብ ሀገራት በአስገራሚ ፍጥነት እየወረሩን ያሉ መጤና ጎጂ ልምዶችስ?... የአማተር ክበባቶቻችን ጥበባዊ ውጊያ አያሻቸውም? በሁለንተናዊ የ“ህዳሴ” ጉዞ ላይ እንደምንገኝ በተደጋጋሚ ይገለፃል፡፡
ለመሆኑ የ“ህዳሴ ጉዞ” ጥበባዊ እገዛ አያስፈልገውም? በዜጎች ደረጃ የአመለካከት ለውጥ ሳይመጣ ያደገና የበለፀገ ሃገር የትኛው ይሆን? አብዝቶ የሚወራለት “ልማታዊ ኪነ-ጥበብ” እንዴትና በማን አማካኝነት ነው ሊሰራ የሚችለው? በአማተሮችና በክበባቶቻቸው አይደለምን? ሀገር ያለወጣት ምንም ናት! መተካካት ደግሞ ተፈጥሮአዊ ህግ ነው! ኖሮ ኖሮ ማለፍ ግድ ነው!... አይቀርም! ስለ ነገው የኪነ-ጥበብ ኢንዱስትሪያችን ሥናስብ፤ ተተኪን ኮትኩቶ ስለማሳደጉ ካልተጨነቅን ነገን ማሰብ ትርፉ ድካም ይሆናል፡፡ የንጉሱ ረታ ልጅ ዳዊት እንዳለው፤ ማንም በነሸጠው ግዜ አሊያ ደግ ገንዘብ ስላለውና መንገዱ አልጋ ባልጋ ስለሆነለት ወይም መልክና ቁመናው ስላማረለት ብቻ ወደ ጥበብ ባህር ዘሎ እየገባ “ልዋኝ” ካለ መንቦጫረቅ ይሆንና ባህሩ ይረበሻል፤ ሲብሥም ሊደርቅ ይችላል፡፡ የባህል ፖሊሲያችን ሊከለስ፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ፕሮግራሙም ሊሻሻል፣ የባህልና ቱሪዝም መ/ቤቶቻችንም ቆም ብለው ሊያጤኑ፣ ባለ ጊዜዎቼ “ጥበበኞችም” አንገታቸውን አዙረው ሊመለከቱ ግድ ነው! የጠፉት ክበባት ይመጡ ዘንድ እንትጋ! አዳዲሶቹ አማተሮችም ይወለዱ ዘንድ እናምጥ!!