Administrator

Administrator

  በ”አዲስ አድማስ” ጋዜጣ በተለያዩ ርዕስ ጉዳዮች ላይ መጣጥፎችን፣ ወጎችንና አጫጭር ልብወለዶችን በመጻፍ የሚታወቀው ደረጀ ይመር ያዘጋጀው “የሕዳሴው መሐንዲስ” የተሰኘ መጽሐፍ ሰሞኑን ለንባብ በቅቷል፡፡
መጽሐፉ፤ እውነተኛው የሕዳሴው መሐንዲስ ታላቁ የኢትዮጵያ ንጉሥ አጼ ቴዎድሮስ እንደሆኑ የሚያትት መጣጥፍን ጨምሮ ሌሎች ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ፍልስፍናዊ ይዘቶችን የሚዳስሱ ጽሁፎች፣አዝናኝ ወጎችና አጫጭር ልብወለዶችን አካትቶ ይዟል። በ30 ምዕራፎች ተከፍሎ በ202 ገጾች የተቀነበበው መጽሐፉ፤ በ150 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ መጽሐፉን ጃፋር መጻሕፍት መደብር እንደሚያከፋፍለው ታውቋል፡፡   

 “አዝማሪና ውሃ ሙላት” የሚለው የከበደ ሚካኤል ግጥም እንዲህ ይላል፡-
አንድ ቀን አንድ ሰው፣ ሲሄድ በመንገድ
የወንዝ ውሃ ሞልቶ ደፍርሶ ሲወርድ
እዚያው እወንዙ ዳር፣ እያለ ጐርደድ
አንድ አዝማሬ አገኘ፣ ሲዘፍን አምርሮ
በሚያሳዝን ዜማ፣ ድምፁን አሳምሮ፡፡  
“ምነው አቶ አዝማሪ፣ ምን ትሠራለህ?” ብሎ ቢጠይቀው፤
“ምን ሁን ትላለህ አላሻግር ብሎኝ የውሃ ሙላት
እያሞጋገስኩት በግጥም ብዛት
ሆዱን አራርቶልኝ ቢያሻግረኝ ብዬ
“አሁን ገና ሞኝ ሆንኩ ምነዋ ሰውዬ
ነገሩስ ባልከፋ፣ ውሃውን ማወደስ
ግን እንደዚህ ፈጥኖ በችኮላ ሲፈስ
ምን ይሰማኝ ብለህ ትደክማለህ ከቶ
ድምፁን አያሽካካ መገስገሱን ትቶ
እስቲ ተመልክተው፣ ይሄ አወራረድ
ያልሰማው ሲመጣ፣ የሰማው ሲሄድ፡፡”
ተግሣፅም ለፀባይ ካ ልሆነው አራሚ
መናገር ከንቱ ነው፣ ካልተገኘ ሰሚ!
*   *   *
ስንናገር ሰሚ መኖሩን እናረጋግጥ፡፡ ለነማንና ለማን ነው የምንናገረው እንበል፡፡ አንዳንድ ሰው ብዙ ጆሮ አለው፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ፈፅሞ ጆሮ ያልፈጠረበት ነው፡፤
“አሁን የት ይገኛል፣ ቢፈልጉ ዞሮ
መስማት ከማይፈለግ፣ የባሰ ደንቆሮ”  ይሉናል ከበደ ሚካኤል፡፡
“አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይነቃም”ም ያስኬዳል፡፡ ሥልጣን ልብ ያደነድናል፡፡ ጆሮ ያደነዝዛል፡፡ ዐይንን ያስጨፍናል! ህዋሳት በድን ሲሆኑ አገር የልማት ትኩሳቷ ይደነዝዛል! የንቃት ዐይኗ ይጨለመልማል! ተስፋና ምኞት ያስለመልማሉ! እኛ በምሁራዊ ልቦናችን የምንመኝላት መንገድ ው መንገድ ነው ኮረኮንች፣ አሊያም ሊሾ አስፋልት ደሞም ቀለበት ሊሆን ግድ ነው!
መለወጣችን ግድ ነው! ለለውጥ መዘጋጀት ግን የለውጥ ግድ ግድ ነው! ዋናው ችግራችን የተለወጥን እየመሰለን ዘራፍ ማለታችን ነው! ብዙዎቻችን የለውጥ ዕውነተኛውና ሁነኛው ሀሳብ ሳይገባን የተለወጥን ይመስለናል! ምነው ቢሉ… ለውጥ የአንድ ጀምበር ጉዳይ ስላልሆነ ነው! እናርገውም ብንል ከቶም ባንድ ጀምበር አንስማማም! ስለዚህ በብርቱ ማሰብ ያለብን “ዛሬም ትግላችን መራራ፣ ግባችን የትየለሌ” መሆኑን ነው! መስዋዕትነትን አንፍራ! የአቅማችንን ያህል ሩቅ ዕቅድና ሀሳብ አንሽሽ! ዛሬ ሁሉን ባቋራጭ የማሸነፍ ፍላጎት ዘመን ነው (It is a time of short - term mechanisms) የረዥም ጊዜ ዕቅድ ገና ባላወቅንበት አገር “አቋራጭ መንገድ” ፍለጋ ስንባዝን ዓመታት አልፈዋል! ገና ያልፋሉ፡፡  
አሁን መሰረታዊ ፍላጎታችን ስለ ፖለቲካዊ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ አኮኖሚያዊም ነው! ጉዳያችን ማን በልቶ ይደር ማንስ ጠግቦ ይደር? የሚለው ነው፡፡
ህንዶች፤
“እያንዳንዷ ሩዝ ላይ የሚበላት ሰው ስም ተፅፏል” የሚሉት እንደ እኛ ባለ አገር የሚሰራ ሀቅ ነው!! ይሄን ምኔም ልብ እንበል! ነገም ጥያቄያችን ይሄው ነው!

 የእርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር ወደ 8 ሚሊዮን እንደሚያሻቅብ ተጠቆመ

     በቤኒሻንጉልና በምዕራብ ወለጋ አዋሳኝ ሰሞኑን የፀጥታ ኃይሎች የወሰዱትን የህግ ማስከበር እርምጃ ተከትሎ አንፃራዊ መረጋጋት በመስፈኑ ለተፈናቃዮች እርዳታ ማቅረብ መጀመራቸውን የረድኤት ድርጅቶች አስታወቁ፡፡
ቀደም ሲል በግጭቱ ምን ያህል ሰዎች እንደተፈናቀሉ ለማወቅ አስቸጋሪ እንደነበር የጠቆመው የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ፅ/ቤት፤የተፈናቃዮች ቁጥር ሩብ ሚሊዮን መድረሱን አስታውቋል፡፡ ለእነዚህ ተፈናቃዮች አስቸኳይ እርዳታ ለማቅረብም 25.5 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተብሏል።
ከተፈናቀሉት 255 ሺ ያህል ዜጎች መካከል 57 ሺህ የሚሆኑት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ አሶሳና ከማሺ ዞን ውስጥ የሚገኙ ሲሆን 200 ሺ ያህሉ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ተፈናቅለው፣ በምስራቅና ምዕራብ ወለጋ ውስጥ የሰፈሩ መሆናቸውን ጽ/ቤቱ በሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
ከሰሞኑ ተፈናቃዮች ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ የረድኤት ድርጅቶች ምልከታ ያደረጉ ሲሆን ተፈናቃዮቹ አስቸኳይ የህክምና፣የተመጣጣኝ ምግብና የመጠለያ አቅርቦት እንደሚያስፈልጋቸው አስታውቀዋል፡፡ ተማሪዎችም ትምህርት ማቋረጣቸውም በሪፖርታቸው ተመልክቷል፡፡   
ይህን እርዳታ በአስቸኳይ ለማቅረብም 25.5 ሚሊዮን ዶላር ለህክምና ቁሳቁስ፣ለምግብ፣ ለህፃናትና እናቶች አልሚ ምግብ እንዲሁም ለዘይት መግዣ እንደሚያስፈልግ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ፅ/ቤት ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡  
በአጠቃላይ በግጭት ምክንያት በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር በህዳር ወር ከነበረበት 2.2 ሚሊዮን ወደ 2.4 ሚሊዮን ከፍ ማለቱን የጠቆመው ጽ/ቤቱ፤በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት 2019 የአስቸኳይ እርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር ወደ 8 ሚሊዮን እንደሚያሻቅብ አስታውቋል፡፡ ለእነዚህ ዜጎች እርዳታ ለማቅረብ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ብሏል፤የመንግስታቱ ድርጅት፡፡

Saturday, 22 December 2018 13:39

ማራኪ አንቀጾች

 የህልም ነገር

   በህልሜ ጭንቅላቴ ከአንገቴ ተለያይቶና ክንፍ አውጥቶ በጡረታ ድልድይ አናት ላይ እንደ ደመና ሲያንዣብብ አየሁ፡፡ የጡረታ ድልድይ እናቶች በመገረም አንጋጠው ሲያስተውሉ በምጽዐት ቀን የተኮነኑ ነፍሳት ይመስሉ ነበር፡፡
በእንቅልፍ ልብ እራሴን አጽናናለሁ…
“….ማየቱም፣ መናገሩም፣ መስማቱም ያለው ጭንቅላት ላይ ነው፡፡ የሰው ልጅ ምን ሲሆን ከአንገት በታች ተንዘላዝሎ ተፈጠረ? ቢቀር እጅና እግር ነው፣ ለእሱም ቢሆን ክንፍ አለ፣ ኧረዲያ መኖርስ ከአንገት በላይ…
ህልም ሥር የሰደደ ድብቅ ፍርሃት እንደሆነ በራሴ አረጋገጥኩ፡፡ ረድ ሠርዌና አባቱ በእኔ ሟርት ሲወራከቡ፣ ነገሩን ችላ ያልኩት መሰልኩ እንጂ ፍርሃትስ ነበር ማለት ነው፤ ካልሆነ…
የጭንቅላቴ አከናፍ ደክመው አየሩን አልቀዝፍ ሲሉብኝና መውደቄ እርግጥ ሲሆን የጡረታ ድልድይ እናቶች “ተዘጋጅ” እንደተባለ ሰልፈኛ ንቃት ታየባቸው። ምን ሊያደርጉኝ እንደሆን ባላውቅም ፍርሃት አደረብኝ። መቅዘፊያ እንደሌላት ጀልባ ጭንቅላቴ በንፋስ እየተገፋ ሲሄድ ያሰፈሰፉት እናቶች ይንቀሳቀሱ ጀመር፡፡ አቅጣጫውን እያማተሩ ሲደርሱ ጭንቅላቴ ሲወድቅ እኩል ሆነ፡፡ ለመያዝ ሲሻሙ ብርድ ልብሴን እንደ መቃብር ድንጋይ በርቅሼ ተነሳሁ፡፡ ፍርሃቱ አለቀቀኝም፡፡ ቀን ከጐዘጐዝኩበት፣ ማታ ካሸለብኩበት ምንጣፍ ላይ ተነስቼ በሩን ዘጋሁት፡፡ ሰውነቴ በፍርሃት ይንቀጣቀጣል፡፡
“የህልም ዓለም ፍርሃት ስለምን ወደ እውን ዓለም ፍርሃትነት ይሸጋገራል” ስል እራሴን ጠየኩ፡፡ መንፈሳችን የታበተበት የሞት ፍርሃት ልኩ የሚታወቀው በእውን ዓለም ማገናዘብ ሳይሆን በህልም ዓለም ደመ ነፍሳዊ ድንጋጤ ውስጥ ነው፡፡ የእኔ መኖር ለእኔ ሆነ ለተቀረው አለም አስፈላጊነቱ እምን ላይ ነው? እስከ መቼስ ከህልም ዓለም ወደ እውን ዓለም ፍርሃት ሳመላልስ እኖራለሁ?…
…አንዳች የሚስቅብኝ ህቡዕ ልቡና መርማሪ አካል እንዳለ ተሰማኝ፡፡ ስለ ስንፍናዬ በፊቱ ሊያሳፍረኝ እየሞከረ እንደሆነ የገባኝ መሰለኝ፡፡ ያ ልቡናዬን የሚበረብር ኃያል ህቡዕ አካል እርሱ ማነው? ልቡናን የመፈተሽ ስልጣን ማን ሰጠው? እራሱ የሥልጣኑ ሰጪና ተቀባይ ይሆን? ሰጪና ተቀባይ አንድ የሆነበት አካባቢ እንዴት ያለ ፍትህ፣ ንፅህናና ቅድስና ይኖራል?…ይሄ የሰው ልጅ የአፈጣጠር ትብታብ ነው። ሰጪና ተቀባይን፣ አልፋና ኦሜጋን፣ ግዝፈትና ረቂቅነትን በአንድ የሚያዳብል የሰው ልጅ ተንኮል ብቻ ነው፡፡ ግዴላችሁም፤ “ኑ በአካላችን በአምሳላችን እንፍጠር” ያለው ፈጣሪ ሳይሆን እራሱ ሰው ነው፡፡ “ኑ እግዚአብሔርን በአካላችንና በአምሳላችን እንፍጠር”
ከየት ተነስቼ እምን ጋ እንደደረስኩ ጠፋኝ፡፡ ይሁንና ፍርሃቴ ጠፍቶ በሬን ተንደርድሬ በመዝጋቴ በራሴ ላይ ሳቅሁ፡፡ መንፈሴ ተዛና--ለማንበብ አኮበኮብኩ። ወረፋ የሚጠብቁ ብዙ መጻሕፍት አሉብኝ፡፡ አንዳንዶቹ ጀምሬአቸው መንፈሴን ስላጨፈገጉብኝ የተውኳቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ የአልበርት ካሙ “The Plague” ገና ስጀምረው በአይጦች ትርምስ ሲሞላ አቆምኩት፡፡ ሌላው ስሙ የማይያዝልኝ ሩሲያዊ ደራሲ፤ እንግሊዝኛ ተናጋሪዎች በቋንቋቸው ስሙን ሲጽፉ ሳያበላሹበት አይቀርም፡፡ SOLZHENITSYN (ሶልዘኒትሳይን) ይባላል፡፡ “Cancer Ward” ይሄም መጽሐፍ ያው ነው፡፡ ተስፋ የሌለው የነቀርሳ ታማሚ፤ መጨነቅ በመፍራት ተውኩት፡፡ ሦስተኛው የብርሃኑ ዘሪሁን ሦስቱ ማዕበሎች ናቸው፡፡ ረሃብ? ወደ ጐን። አንዳንዶቹን መጻሕፍት ተራ የማስጠብቃቸው የአንድ ደራሲ ሥራዎችን አከታትዬ ላለማንበብ ነው። አንዳንድ ደራሲዎች ደግሞ አንቀጽ የሌለው ሃምሣ ስድስት ገጽ ይጽፋሉ፡፡ ለምሳሌ ፈረንሳዊው ፈላስፋ ሳርት እና አየርላንዳዊው ጀምስ ጆይስ፡፡ ተራራ ወጪ አይደለሁም፤ ገና ዳገት እንዳየሁ ሃሞቴ ፍስስ ይላል። አንቀፅ ያልገባበት ጽሑፍ ደረቱን የሰጠ አቀበት ነው፡፡ አዲዮስ!
ያልተነበቡ መጻሕፍት የሚቀመጡበት ጠረጴዛ የዕዳ መዝገቤ ሆኖ ይወቅሰኛል፡፡ እንደ የንታ ጥምጥም ክርክርም ያለ አመል ያላት የሳጠራ ሼልፍ፣ የድል መዝገቤ ሆና ብሥራቴን ትለፍፋለች፡፡ አንብቤ ባልገቡኝ እንደ ጉርጂፍ እና በርትራንድ ራስል ያሉት ፀሐፍያን ላይም ሥራዎቻቸውን አንብቤ በመጨረሴ ብቻ እኩራራለሁ፡፡
(ከደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ “ታለ በዕውነት ሥም” የተቀነጨበ፤ 2ኛ ዕትም)

    “አቬንጀርስ - ኢንፊኒቲ ዎር” በ2.04 ቢሊዮን ዶላር ቀዳሚ ሆኗል

    በፈረንጆች 2018 አመት በአለማቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ገቢ ያገኙ የአለማችን ምርጥ ፊልሞች ዝርዝር ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ አቬንጀርስ - ኢንፊኒቲ ዎር የተሰኘው ፊልም በ2.04 ቢሊዮን ዶላር አጠቃላይ ገቢ የአንደኛነት ደረጃ ላይ መቀመጡ ተነግሯል፡፡
300 ሚሊዮን ዶላር ያህል ፈጅቶ የተሰራው አቬንጀርስ - ኢንፊኒቲ ዎር፣ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ በማግኘት በታሪክ አራተኛው ፊልም ሆኖ መመዝገቡን የዘገበው ዴይሊ ሚረር፣ ፊልሙ በአመቱ በአሜሪካ ብቻ 678.8 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አመልክቷል፡፡
ዋካንዳ በተባለችና የኢትዮጵያ ተምሳሌት ናት ተብሎ በሚነገርላት የምናብ አገር ላይ ተመስርቶ የተሰራውና ጥቁር ተዋንያን የሚበዙበት ብላክ ፓንተር በአመቱ 1.34 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
210 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገበት ብላክ ፓንተር በፈረንጆች 2018 አመት በአሜሪካ ብቻ ከ700 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱን የጠቆመው ዘገባው፣ ፊልሙ በርካታ ክብረ ወሰን መስበሩንና በአለማቀፍ ደረጃ ተወዳጅ በመሆን በወረፋ መታየቱን መቀጠሉን ገልጧል፡፡
ዡራሲክ ወርልድ - ፎልን ኪንግደም የተሰኘውና በዩኒቨርሳል ፒክቸርስ ፕሮዲዩስ የተደረገው ፊልም በበኩሉ፤ 1.3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት የሶስተኛነት ደረጃን መያዙ ተነግሯል፡፡
ኢንክሪዲብልስ ቱ በ1.2 ቢሊዮን ዶላር፣ ቬኖም በ853 ሚሊዮን ዶላር፣ ሚሽን ኢምፖሲብል - ፎልአውት በ787.4 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደ ቅደም ተከተላቸው፣ ከአራተኛ እስከ ስድስተኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡


 ጋዜጠኞችን በማሰር ቻይና ቀዳሚነቱን ይዛለች

     ስራቸውን በማከናወን ላይ ሳሉ ግድያ የሚፈጸምባቸው ጋዜጠኞች ቁጥር እያደገ መምጣቱንና በ2018 ብቻ በአለማችን የተለያዩ አገራት 63 ያህል ጋዜጠኞች መገደላቸውን ሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ ባወጣው ሪፖርት እንዳስታወቀ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በስራ ገበታቸው ላይ እያሉ የተገደሉ ጋዜጠኞች ቁጥር ከአምናው በ15 በመቶ የጨመረ ሲሆን በአለማችን ለጋዜጠኞች እጅግ አደገኛ የተባሉት የመጀመሪያዎቹ ሶስት አገራትም አፍጋኒስታን፣ ሶርያና የመን ናቸው፡፡
በአመቱ በአፍጋኒስታን 15፣ በሶርያ 11፣ በየመን 8 ጋዜጠኞች መገደላቸውን የገለጸው ተቋሙ፣ በአመቱ 6 ጋዜጠኞች የተገደሉባት አሜሪካም ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ለጋዜጠኞች እጅግ አደገኛ ከሆኑ አስር አገራት ተርታ መሰለፏን አመልክቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአለማችን የተለያዩ አገራት በድምሩ 348 ያህል ጋዜጠኞች በእስር ላይ እንደሚገኙ የጠቆመው ተቋሙ፣ ቻይና 60፣ ግብጽ 38፣ ቱርክ 33 ጋዜጠኞችን በማሰር ከአለማችን አገራት ቀዳሚነቱን እንደሚይዙ አስታውቋል፡፡
በአለማችን የተለያዩ አገራት ታግተው የሚገኙ ጋዜጠኞች ቁጥር 60 ያህል መድረሱን የጠቆመው ሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ፣ ሶርያ 31፣ የመን 17፣ ኢራቅ 11 ጋዜጠኞችን አግተው እንደሚገኙ አመልክቷል፡፡
ባለፉት 10 አመታት በመላው አለም የተገደሉ ጋዜጠኞች ቁጥር 702 ያህል መድረሱን የገለጸው ተቋሙ፣ ባለፉት አስርት አመታት በርካታ ቁጥር ያላቸው ጋዜጠኞች የተገደሉት በፈረንጆች አመት 2012 እንደነበርና በአመቱ 87 ጋዜጠኞች መገደላቸውንም አክሎ አስታውቋል፡፡

የቻይናው የቴሌኮም ኩባንያ ሁዋዌ የፋይናንስ ዘርፍ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዋንዙ ሜንግ በቅርቡ በአሜሪካ መንግስት ግፊት በካናዳ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የተቃወሙና ቻይናውያን ለአገራቸው ምርት ቅድሚያ እንዲሰጡ ለማበረታታት በማሰብ፣ የተለያዩ የአገሪቱ ኩባንያዎች ለሁዋዌ ሞባይል ተጠቃሚዎች ሽልማት እየሰጡ እንደሚገኙ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ከቻይና ስመጥር የቱሪስት መዳረሻዎች አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት ሼኖንግ ማውንቴን ሲኒክ ፓርክ፤ የሁዋዌ ሞባይል ለሚጠቀሙ ጎብኝዎቹ 9.4 ዶላር የሚያወጣውን የመግቢያ ትኬት እየሸለመ እንደሆነ ያስታወቀ ሲሆን በቤጂንግ የሚገኝ አንድ ባር በበኩሉ፤ ለባለ ሁዋዌ ሞባይል ደንበኞቹ የ20 በመቶ ቅናሽ እያደረገ መሆኑ ተዘግቧል፡፡
ሜንፓድ የተባለው ሌላ የቻይና የቴክኖሎጂ አምራች ኩባንያ ደግሞ ሁዋዌ ሞባይል ለሚገዙ ሰራተኞቹ የዋጋ ድጎማ እንደሚያደርግና  በአንጻሩ ደግሞ የአፕል ምርቶችን የሚገዙ ሰራተኞቹን እንደሚቀጣ መዛቱ ተነግሯል፡፡
በአለማችን ሁለተኛው ግዙፍ የስማርት ፎን አምራች ኩባንያ የሆነው የቻይናው ሁዋዌ የፋይናንስ ዋና ሃላፊ ዋንዙ ሜንግ፤ አሜሪካ በኢራን ላይ የጣለችውን የንግድ ማዕቀብ ጥሰዋል በሚል ከሳምንታት በፊት በአሜሪካ ባለስልጣናት ጥያቄ በካናዳ በቁጥጥር ስር መዋላቸውና ጉዳዩ ሁለቱን አገራት ወደ ከፋ ነገር ሊያመራቸው እንደሚችል ሲነገር መሰንበቱ ይታወሳል፡፡

በተገባደደው የፈረንጆች አመት 2018 ብቻ በመላው አለም ከ4 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች በስደት ጉዞ ላይ እያሉ ለሞት መዳረጋቸውን ተመድ አስታውቋል፡፡ አለማቀፉ የስደተኞች ድርጅት ያወጣውን አመታዊ ሪፖርት ጠቅሶ ዘ ጋርዲያን እንደዘገበው፤በአመቱ 4 ሺ 476 የተለያዩ አገራት ዜጎች በስደት ጉዞ ላይ ሳሉ አደጋ፣ ጥቃትና ርሃብን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ለሞት የተዳረጉ ሲሆን ግማሽ ያህሉ ወደ አውሮፓ አገራት ለመግባት ያሰቡ ነበሩ፡፡
ከአለማችን አጠቃላይ ህዝብ 3.4 በመቶ የሚሆነው የኢኮኖሚ ችግር፣ ግጭትና የተፈጥሮ አደጋን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች አገሩን ጥሎ ለመሰደድ እየተገደደ ነው ያለው ድርጅቱ፣ በአመቱ ከ110 ሺህ በላይ የተለያዩ አገራት ስደተኞች ወደ አውሮፓ አገራት መሰደዳቸውን አመልክቷል፡፡


አቶ በረከትና አቦይ ስብሃት ሃሳብ ክፉኛ ተተቸ

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜና እሁድ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት በሃገሪቱ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በተካሄደው ውይይት በአቶ በረከት ስምኦንና በሌሎች ምሁራን የመነሻ ፅሁፍ የቀረበ ሲሆን የአቶ በረከትና የአቦይ ስብሃት ሃሳብ ጠንካራ ትችትና ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡
በዚህ ውይይት መድረክ ላይ አቶ በረከት ባለፉት 27 ዓመታት የገዥው ፓርቲ ሊቀመንበርና የአገሪቱ ጠ/ሚኒስትር ሆነው የመሩትን የአቶ መለስ ዜናዊን፣ የአቶ ኃ/ማርያምን ደሳለኝና የዶ/ር ዐቢይን የአመራር ዘመን እያነፃፀሩ ገምግመዋል፡፡
በአቶ መለስ አመራር ውስጥ ህግ የተከበረባት፣ ልማት የተሳለጠባትና አመራሩም ጠንካራ የነበረበት መሆኑን ያወሱት አቶ በረከት፤ በአንፃሩ በአቶ ኃ/ማርያም ዘመን “ልፍስፍስ” አመራር የነበረበትና አገሪቱ የኋልዮሽ ጉዞ የጀመረችበት ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡ አሁን ያለውን የዶ/ር ዐቢይ አመራር ደግሞ ህገ መንግስቱን የሚጥስ፣ ህግን ማስከበር ያልቻለና ሰላም የደፈረሰበት ሲሉ ገልፀውታል አንዳችም በጎ ነገር ሳይጠቅሱ፡፡
በአቶ መለስና በአቶ ኃይለማርያም የጠ/ሚኒስትርነት ዘመን ቁልፍ ስልጣን ላይ የነበሩት አቶ በረከት ስምኦን፤ እሳቸው በአመራሩ ውስጥ የነበራቸውን ሚና በግምገማቸው አይጠቅሱም፡፡
በትግራይ ዋነኛውን ተቃዋሚ ፓርቲ “አረና” የሚመሩት የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ አቶ አብርሃ ደስታ ግን እውነቱ ከአቶ በረከት አተያይ በተቃራኒ ነው ይላሉ፡፡ አሁን  ሃገሪቱ ለገባችበት የሰብአዊ መብት ጥሰትና ለሙስና ቅሌት መሰረቱ የተጣለው በአቶ መለስ አመራር በመሆኑ የሳቸው መንግስት ጠንካራ ነበር ማለት አይቻልም የሚሉት አቶ አብርሃ፤ የሃገሪቱ የፖለቲካ ችግሮች መነሻም የአቶ መለስ አመራር ነው ብለዋል፡፡
በአቶ መለስ ጊዜ በኢትዮጵያ የአፈና ቁጥጥር እንደነበር የሚገልፁት ምሁሩ፤ ስርአቱም በባህሪው አፋኝ ነበር ይላሉ፡፡ ከዚህ አፋኝነቱ የተነሳ ኢህአዴግ የሚፈልገው አይነት ዝምታና ስርዓት ሰፍኖ እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡ “ስርአቱም የአፈና ቁጥጥርና የአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭነት ውጤት ነበር” የሚሉት የአረናው ሊቀመንበር፤ “አቶ ኃ/ማርያም የተረከቡት አፈናን ነው” ባይ ናቸው፡፡
አቶ ኃ/ማርያም አፈናውን በአግባቡ መያዝ ስላልቻሉም፣ ሃገሪቱ አሁን የደረሰችበት የችግር ማጥ ውስጥ ልትገባ ችላለች ያሉት አቶ አብርሃ፤ ለዚህ ሁሉ ችግር ዋነኛ ተጠያቂው ግን አቶ መለስ እንደነበሩ” ይሞግታሉ፡፡ የአቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ አመራርን በተመለከተ ከአቶ በረከት ሃሳብ ጋር የሚስማሙት አቶ አብርሃ፤ “በእርግጥም ውጤታማ መሪ አልነበሩም” ሲሉ ያረጋግጣሉ፡፡  
አሁን በዶ/ር ዐቢይ ጊዜ ከለውጡ ጋር አብሮ የመጣ፣ ለውጡን በቅንጅት የመምራትና የህግ የበላይነትን የማስከበር ጉድለት መኖሩን የሚጠቅሱት የአረናው ሊቀ መንበር፤በፖለቲካና በዲሞክራሲው ረገድ ግን በርካታ ለውጦች መምጣታቸውን አልሸሸጉም፡፡
“መንግስት ሊገድለኝ፣ ሊያፍነኝ ይችላል የሚል ስጋት በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች መቅረቱን የሚጠቅሱት አቶ አብርሃ፤”በትግራይ ግን ይህ የተለየ ገፅታ አለው” ይላሉ - “አሁንም እንደ ቀድሞው ፖለቲካ በስጋት የሚከወንበት ቀጠና ነው” በማለት፡፡
“አሁን በአገሪቱ የለውጥ ብርሃን ጭላንጭል አለ፤ ይህ የለውጥ ጭላንጭል በጥሩ መንገድ ከተመራ ወደ መልካም ሁኔታ ሊያሻግረን ይችላል” ሲሉም ተስፋ ያደርጋሉ፤ ምሁሩና ፖለቲከኛው፡፡
የአቶ አብርሃን ሃሳብ የሚያጠናክሩት የአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህሩና የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኙ አቶ ስዩም ተሾመ በበኩላቸው፤ “በትግራይ ለውጡን ሸሽተው የመሸጉ ኃይሎች ተስፋ የቆረጡ ስለሆኑ የሚያቀርቧቸው ትንታኔዎች፣ የድሮው ይሻለናል የሚል ቅኝት ያላቸው እንደሚሆኑ ይጠበቃል” ብለዋል፡፡
“የሃገሪቱን ሉአላዊነት ለአደጋ ባጋለጠ የውጪ እዳ የዘፈቀ፣ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈፀመና በሌብነት የተጨማለቀ ስርአት፣ አሁን ካለው ሃገርን በማዳን ስራ ላይ ከተጠመደ መንግስት ጋር ፈፅሞ ለንፅፅር አይቀርብም” የሚሉት አቶ ስዩም፤”ይሄ ፀረ ለውጥ - እንቅስቃሴዎችን የሚያደርግ ቡድን፣ ተስፋ የቆረጠ በመሆኑ፣ ሃገር ከማተራመስ ወደ ኋላ አይልም” ሲሉ ስጋታቸውን ይገልፃሉ፡፡
ከብዙ ዓመታት ስደት በኋላ ወደአገራቸው የተመለሱት የህወሃት መስራች ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ከአቶ በረከት ትንተና ጋር ፈፅሞ አይስማሙም፡፡ “አቶ መለስ አብዮታዊ ዲሞክራሲን አራምዳለሁ ብሎ ዲሞክራሲያዊም አብዮታዊም ያልሆነ፣ የተደናበረ ርዕዮተ ዓለም ይዞ ነው ሀገር ሲመራ የነበረው” ያሉት ዶ/ር አረጋዊ፤ “በዚህም ምክንያት የነበረው ስርአት ፀረ-ዲሞክራሲ ነበር” ብለዋል፡፡  
አቶ መለስ አምባገነናዊ መሪ እንደመሆኑ መጠን፣ በሃገሪቱ የታየው የሰብአዊ መብት ጥሰትና የዜጎች ጭቆና የአምባገንነቱ ውጤት ነው” ይላሉ ዶ/ር አረጋዊ። ቀጥሎ የመጡት አቶ ኃ/ማርያም፤ የመለስን ራዕይ አስቀጥላለሁ፤ ብለው የተነሱ ስለነበሩ የራሳቸውን አሻራ አሳርፈዋል ለማለት ያስቸግራል፤ አመራራቸውም ያልተረጋጋና የእርስ በእርስ መተማመን የጎደለው ነበር ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
አሁን ለውጡን እየመሩ ያሉት እነ ዶ/ር ዐቢይ ኢህአዴግ ቢሆኑም የሚያራምዱት ሃሳብ ይዘት ግን ፀረ ኢህአዴግ ነው ባይናቸው፡፡
“ዲሞክራሲን ለማስፈን ቆርጠው መነሳታቸውን በተግባርም ብዙ ርቀት ሄደው የፖለቲካ እስረኞች በመፍታት፣ በውጭ የነበሩ ፖለቲከኞች ወደሃገር ቤት እንዲገቡ በማድረግ፣ አፋኝ አዋጆችን በማሻሻል … በይዘት ፀረ ኢህአዴግ አቋም ያለው እርምጃ እየወሰደ ያለ ቡድን ነው” ሲሉም በምሳሌ ያስደግፋሉ፡፡
ሌላው አነጋጋሪ የነበረው ጉዳይ በመቀሌው ስብሰባ ላይ አንጋፋው የህውሓት መስራችና መሪ አቶ ስብሃት ነጋ “ዶ/ር ዐቢይ የተመረጡት በአሜሪካኖች ነው” ማለታቸው ነው፡፡
ይህ የአቶ ስብሃት ሃሳብ በስም ማጥፋት የሚያስጠይቅ፣ ማስረጃ የሌለው ውንጀላ ነው ይላሉ - ዶ/ር አረጋዊ፡፡ “አነጋገሩ ማስረጃ የሌለው ቀጥተኛ ስም ማጥፋት ነው፣ ዶ/ር ዐቢይንም ሆነ የለውጥ ኃይሉ መሪ አቶ ለማ መገርሳን ወደ ስልጣን ያመጣቸው የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል ነው” ያሉት ዶ/ር አረጋዊ፤ ከሙስሊሙ የ“ድምፃችን ይሰማ” እንቅስቃሴ ጀምሮ የነበሩ የህዝብ እንቅስቃሴዎች ናቸው የለውጥ ኃይሉን ወደ ስልጣኑ ያመጣው” ብለዋል፡፡
አቶ አብርሃ በበኩላቸው ዶ/ር ዐቢይ በኢህአዴግ ም/ቤት እና ጠቅላላ ጉባኤ መመረጣቸውን ነው የምናውቀው” ይላሉ፡፡ ጉባኤው በሙሉ ድምፅ ሊባል በሚችል መልኩ ጠ/ሚኒስትሩን እንደመረጠ ያስታወሱት አቶ አብርሃ ከዚህ ውጪ አቶ ስብሃት ያሉት ነገር ውሃ የሚቋጥር አይደለም ይላሉ፡፡
የአቶ አብርሃን ሃሳብ የሚያጠናክሩት አቶ ስዩም በበኩላቸው፤ የአቶ ስብሃት ንግግር በርካታ ጉዳዮችን የሚያመላክት ነው ይላሉ፡፡ የቀድሞው  የኢህአዴግ አመራር ሃገሪቱን በውጭ ሃገር እዳ በመዝፈቅ፣ ሉአላዊነቷን አደጋ ላይ ጥሎ ነበር የሚሉት መምህሩ፤ በዚህ ሁኔታ ሃገሪቱ በቻይና ብድርና እዳ ተሰንጋ በጭንቅ ላይ በነበረችበት ጊዜ ነው ዶ/ር ዐቢይ ወደ ስልጣን የመጡት ይላሉ፡፡ “ዶ/ር ዐቢይ ወደ ስልጣን ሲመጡ አሜሪካኖቹ ወዳጅነታቸውን ማጠናከር የፈለጉት ቻይና በአፍሪካ ሃገራት ላይ የደቀነችውን አደጋ ከራሳቸውም ጥቅም አንፃር በማስላት እንጂ ዶ/ር ዐቢይን ለመደገፍ አይደለም” ብለዋል፡፡
“ሃገሪቱን በከፍተኛ የእዳ ጫና ለቻይና ሉአላዊነቷን አሳልፎ ሲሸጥ የነበረ ስርአት፣ አሁን ሃገሪቱን ለመታደግ የሚታገልን መሪ በውጭ ኃይሎች የተመረጠ ብሎ የሚያጥላላበት ሞራላዊ ብቃት የለውም” ሲሉ አቶ ስዩም ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ፡፡
በዚህ ስብሰባ ላይ የአረና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አምዶም ገ/ሥላሴ የሰላ ትችታቸውን ያነሱበት ንግግራቸው በጭብጨባ የመቋረጡ አንድምታ፣ ለውጡን ሸሽቶ መቀሌ የመሸገው ኃይል የተለየ ሃሳብና አስተሳሰብን የማፈን ፍላጎቱ ያለመስከኑን ያመላክታል - ብለዋል ምሁሩ፡፡ ይሄ ሃሳብን አጋችና አፋኝ ኃይል በሃገሪቱ የመጣውን ለውጥ ቢያጥላላ ውሃ የሚቋጥር አይሆንም፤ ለውጡንም የሚገታው አይደለም” ብለዋል - አቶ ስዩም፡፡
ለውጡን የሚቃወሙ ኃይሎች አሁን አጣብቂኝ ውስጥ መግባታቸው እርግጥ ሆኗል የሚለው አቶ ስዩም፤ ከዚህ በኋላ በተስፋ መቁረጥ ያልተገቡ የሀይል እንቅስቃሴዎችን ሊያደርጉ ስለሚችሉ መንግስት ሁኔታውን በጥንቃቄ መከታተል አለበት ብለዋል፡፡
የአሜሪካ መንግስት በበኩሉ፤በአዲስ አበባ በሚገኘው ኤምባሲው በኩል በጉዳዩ ላይ በሰጠው መግለጫው፤ አቦይ ስብሃት “ዶ/ር ዐቢይ የተመረጡት በአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ነው” ማለታቸው መሰረተ ቢስ ውንጀላ ነው ብሏል፡፡ ዶ/ር ዐቢይ የተመረጡት በኢህአዴግ ም/ቤት፣ በአብላጫ ድምፅ እንደሆነ እናውቃለን ያለው ኤምባሲው፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚካሄደውን የለውጥ እንቅስቃሴ ግን እንደግፋለን ብሏል፡፡


በቱርካውያን ባለሃብቶች በሠበታ ከተማ የተቋቋመው አይካ አዲስ የጨርታ ጨርቅ ፋብሪካ ከትናንት ጀምሮ ሥራ ማቆሙን ለሠራተኞቹ አስታወቀ፡፡
4000 (አራት ሺ) የሚሆኑ የፋብሪካው ሠራተኞች ከረብዕ ጀምሮ የሥራ ማቆም አድማ ላይ የሠነበቱ ሲሆን አርብ ጠዋት ወደ ፋብሪካው ሲመለሱ በማስታወቂያ ቦርድ ላይ “ሳይሰራ የሚከፈል ደሞዝ ስለሌለ፣ ፋብሪካው ለጊዜው ስራ አቁሟል” የሚል ማስታወቂያ ተለጥፎ፣ ሠራተኛው እንዲመለስ መደረጉን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የፋብሪካው ባለቤት ቱሪካዊው ዩሱፍ ሃይዲኒ ፋብሪካውን ጥለው ከተሠወሩ ከ6 ወር በላይ መሆኑን የገለፁት ሠራተኞች፤ “ፋብሪካውን የሚያስተዳድረው” ልማት ባንክ ነው የሚል መረጃ እንደደረሳቸው፤ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ፋብሪካውን የሚያስተዳድረው አካል በውል እንደማይታወቅ ተናግረዋል፡፡
ሠራተኛው የስራ ማቆም አድማ ላይ የሰነበተውም “የፋብሪካው የወደፊት እጣ ፈንታና የስራ ዋስትናችን ይረጋገጥልን” በሚል ጥያቄ እንደነበር የገለፁት ሠራተኞቹ፤ ከአርብ ጀምሮ ግን ፋብሪካው ላልተወሰነ ጊዜ ስራ ማቆሙ በማስታወቂያ እንደተገለፀላቸው ተናግረዋል፡፡
ላለፉት 6 ወራት የፋብሪካው መደበኛ ስራ ተቀዛቅዞ መቆየቱን የጠቆሙት ሠራተኞቹ፤ ይሁን እንጂ ሠራተኛው የሚያገኘው ወርሃዊ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም አልተቋረጠም ነበር ብለዋል፡፡

Page 7 of 417