Administrator

Administrator

“የስዕል ስራዎቿን ለእይታ በማብቃታችን ኩራት ይሰማናል”
                           - የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ
 
ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሰዓሊ ጁሊ ምህረቱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በአለማቀፍ ደረጃ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የስነ-ጥበባት ባለሙያዎች በየአመቱ የሚሰጠውን የ2015 የስነ-ጥበባት ሜዳሊያን ተቀበለች፡፡ኢትዮ- አሜሪካዊቷ ሰዓሊ ጁሊ ምህረቱ በአለማቀፍ ደረጃ እውቅና በተሰጠው የስነ-ጥበብ ስራዋ እና ባህላዊ ዲፕሎማሲን በማጠናከር ረገድ በፈጠረችው ተጽዕኖ ለዚህ ሽልማት መብቃቷን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡የመስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ለአርት ኒውስ ድረገጽ እንደተናገሩት፣ ሰዓሊዋ በሙያዋ ላሳየችው ጉልህ ቁርጠኝነት እንዲሁም አርት ኢን ኢምባሲስ በተሰኘው ፕሮግራምና በአለማቀፍ የባህል ልውውጥ መስክ ላበረከተችው አስተዋጽኦ እውቅና ለመስጠት፣ የዘንድሮውን ሽልማት ከተቀበሉት 7 ሰዓሊያን አንዷ ተደርጋ ተመርጣለች፡፡እ.ኤ.አ በ1970 በአዲስ አበባ የተወለደችው ሰዓሊ ጁሊ ምህረቱ፤ በተለያዩ የውጭ አገር ዩኒቨርሲቲዎች የስነጥበባት ትምህርቶችን የተከታተለች ሲሆን፣ በአለማቀፍ ደረጃ በተዘጋጁ በርካታ የግልና የጋራ የስዕል አውደ ርዕዮች ላይ ስራዎቿን ለእይታ በማብቃትና የታላላቅ ሽልማቶች አሸናፊ በመሆን ትታወቃለች፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ነዋሪነቷ በአሜሪካ ኒውዮርክ ነው፡፡የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጆን ኬሪ በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የጁሊ ምህረቱን ስዕሎች በተመለከተ በሰጡት አስተያየት፣ በተለያዩ አገራት በሚገኙ ኤምባሲዎቻችን ለእይታ ያበቃናቸው የጁሊ ስዕሎች እጅግ ማራኪ ናቸው፣ በስራዎቿ ኩራት ይሰማናል ብለዋል፡፡ ላበረከተችው አስተዋጽኦም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

•    በኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ስትተዳደር ቆይታለች
ከሀያኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አንስቶ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አካል የነበረችው የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሰሞኑን  በራሷ እንድትተዳደር የተወሰነ ሲሆን  አባ መንግስተአብ ተስፋማሪያም የመጀመሪያው የኤርትራ ሊቀጳጳስ ሆነው ተሾሙ፡፡ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ከተነጠለች በኋላም የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን  በአዲስ አበባ ቅርንጫፍና በአንድ የጳጳስ ጉባኤ ስር ስትተዳደር የቆየች ቢሆንም ሰሞኑን ከቫቲካን የወጣ መረጃ፤ የሮማ ካቶሊካዊት ቤ/ክርስትያን አቡን ጳጳስ ፍራንሲስ የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በአስመራ ቅርንጫፍ ራሷን ችላ እንድትተዳደር መወሰናቸውንና አባ መንግስተአብ ተስፋማሪያምን ሊቀጳጳስ አድርገው መሾማቸውን ጠቁሟል፡፡
የኤርትራ የመጀመሪያው የካቶሊክ ሊቀጳጳስ ሆነው የተሾሙት የአስመራ  ሀገረስብከት ጳጳስ  የነበሩት አባ መንግስተአብ ተስፋማርያም፤ ኤርትራ የ23ኛ አመት የነፃነት በአሏን ስታከብር “ወንድምህ የት ነው” በሚል ርዕስ በወቅታዊ የኤርትራ ሁኔታ ላይ በተለይ የወጣቶችን ስደት የተመለከተ  ሀተታና ጥያቄዎችን የያዘ ሰነድ ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ካስረከቡ አራት ጳጳሳት  አንዱ ነበሩ፡፡የጳጳሱን መሾም ተከትሎም የኤርትራ መንግስት ደጋፊ በሆኑ ድረገፆች አቡነ መንግስተአብ ተስፋማርያምን የሚያጥላሉ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያና በኤርትራ የተደረገውን ጦርነት ተከትሎ  የሁለቱ አገራት ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያናት ስብሰባዎቻቸውን በኢትዮጵያም ሆነ በኤርትራ ሊያደርጉ ባለመቻላቸው በሮም ሲያካሂዱ መቆየታቸው ታውቋል፡፡

የደቡብ አፍሪካው ስታንዳርድ ባንክ በመጪው መጋቢት ወር መጨረሻ በኢትዮጵያ ተወካይ ቢሮ
ሊከፍት መሆኑን ቬንቸርስ አፍሪካ ድረገጽ ዘገበ፡፡የአገሪቱ የፋይናንስ ህግ የውጭ አገራት ባንኮች በመስኩ እንዳይሰሩ የሚከለክል እንደመሆኑ፣ ባንኩ ኢትዮጵያ የሚከፍተው ተወካይ መስሪያ ቤት የገንዘብ ብድርና ቁጠባን የመሳሰሉ ስራዎችን እንደማያከናውን የስታንዳርድ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ጣይቱ ወንድወሰንን ጠቅሶ ዘገባው ገልጿል፡፡በአዲስ አበባ የሚከፈተው ቢሮ ስታንዳርድ ባንክ በአገሪቱ ከሚገኙ ኩባንያዎች ጋር መልካም የስራ ግንኙነት ለመፍጠር የሚያስችሉ ስራዎችና የገበያ ጥናቶች የሚከናወንበት እንደሚሆን የገለጸው ዘገባው፤ የቢሮው መከፈት ባንኩ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ስራዎችን ለማከናወን ፍላጎት ላላቸው ደንበኞቹ የማማከር አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዘውም አስረድቷል፡፡

    በአምስት አመቱ የጣሊያን ወረራ ወቅት በውስጥ አርበኛነታቸው የሚታወቁትን ወ/ሮ የሸዋረገድ ገድሌን የህይወት ታሪክ የሚዘክረው መፅሐፍ ዛሬ ከቀኑ 7፡30 ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተ መጽሐፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር) አዳራሽ ይመረቃል፡፡ “ሸዋረገድ ገድሌ፤ የአኩሪ ገድላት ባለቤት” በሚል ርዕስ የታተመው መጽሃፍ፤ ከ1878-1942 ስለኖሩትና በጣሊያን ወረራ ወቅት በዱር በገደሉ ላሉ አርበኞች  መረጃዎችን በማቀበል ታላቅ ገድል ስለፈፀሙት እናት አርበኛ ይተርካል፡፡ የመፅሐፉ ፀሐፊ ደራሲ ሺበሺ ለማ ሲሆኑ መጽሐፉን ያሳተሙት የአርበኛዋ የወንድም ልጅ ዶ/ር ክፍሌ ማርቆስ ገድሌ መሆናቸው ታውቋል፡፡ መፅሐፉ ለአገር ውስጥ በ70ብር፣ ለውጭ በ25 ዶላር ለገበያ የቀረበ ሲሆን በዛሬው የምረቃ ስነስርአት ላይ የቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ እና ሌተናል ጃገማ ኬሎ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

አርቲስት ደበበ እሸቱ ብቸኛው የህይወት ዘመን ተሸላሚ እጩ ሆኗል
በመጪው የካቲት የሚያካሂደውና በኢትዮ ፊልምስ ባለቤትነት የሚመራው የጉማ ፊልም ሽልማት ምርጥ አምስቶች ከትናንት በስቲያ በሃርመኒ ሆቴል ይፋ ሆኑ፡፡ በህይወት ዘመን ተሸላሚነት አርቲስት ደበበ እሸቱ ብቸኛ እጩ መሆኑም ተገልጿል፡፡ በዕለቱ በ17 ዘርፎች በዳኞችና በተመልካች የተመረጡ አምስት አምስት እጩዎች የታወቁ ሲሆን ዘርፎቹም በምርጥ የተማሪ አጭር ፊልም፣ በምርጥ ድምፅ፣ በምርጥ ሙዚቃ፣ በምርጥ ስኮር፣ በምርጥ ሜክአፕ፣ በምርጥ የፊልም ጽሑፍ፣ በምርጥ ቅንብር፣ በምርጥ ሲኒማቶግራፊ፣ በምርጥ ተስፋ የተጣለባት ህፃን ተዋናይት፣ በምርጥ ተስፋ የተጣለበት ህፃን ተዋናይ፣ በምርጥ ረዳት ሴት ተዋናዮች፣ በምርጥ ረዳት ወንድ ተዋናይ፣ በምርጥ ሴት ተዋናይት፣ በምርጥ ወንድ ተዋናይ፣ በምርጥ የተመልካች ምርጫ፣ በምርጥ ዳይሬክተርና በምርጥ ፊልም ጐራ በሚል ተከፋፍለዋል፡፡ መቶ ዳኞች በተሳተፉበት በዚህ ምርጫ ምርጥ አምስቶቹ የታወቁ ሲሆን በቀጣይ ከአንድ እስከ ሦስት የሚወጡት ተለይተው፣ የካቲት 16 ቀን 2007 ዓ.ም ደማቅ የሽልማት ስነ ስርዓት እንደሚካሄድ የኢትዮ ፊልም መስራችና ስራ አስኪያጅ ዮናስ ብርሃነ መዋ ለጋዜጠኞች ተናግሯል፡፡ ፕሮግራሙን ሙሉ በሙሉ ስፖንሰር ያደረገው በደሌ ቢራ ነው፡፡

በታሪካዊቷ ደሴ ከተማ መሀል በሚገኘው ደሴ ህንጻ ላይ ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ ሲኒማ ቤት መከፈቱ ተገለፀ፡፡ “
ዙም ሲኒማ” ቤት 265 ምቹ መቀመጫዎች ያሉት ሲሆን ኤች.ዲ ዘመናዊ ፕሮጀክተርና ዘመኑ የደረሰባቸው የድምፅ ቴክኖሎጂዎች ተገጥሞለታል፡፡
ሲኒማ ቤቱን በባለቤትነት የሚያስተዳድረው የጂታብ ኢንተርቴይመንት ሥራ አስኪያጅ አቶ ታዲዮስ ጌታቸው፤ “ደሴ ካላት ረጅም ዕድሜና የከተማው ነዋሪ ለኪነጥበብ ካለው ጥልቅ ፍቅር አንፃር ደሴ እስካሁን እንዲህ ያለ ዘመናዊ ሲኒማ ቤት ሳታገኝ መቆየቷ የሚያስቆጭ” ነው ብለዋል፡፡
ዳራሹ ከሲኒማ በተጨማሪ እንደ ቴአትር፣ ስታንድአፕ ኮሜዲና  ሰርከስ ለመሳሰሉ ጥበባዊ ትርዒቶች ምቹ በመሆኑ በዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ቢመጡ አብሮ ለመስራት ዝግጁ ነን ብለዋል - አቶ ታዲዮስ፡፡ አስራ አንድ በአምስት (11x5) ሜትር ስፋት ያለው ዘመናዊ ስክሪን የተዘረጋለት አዲሱ ሲኒማ ቤት፤ ከጥር 16 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ በይፋ ስራ የሚጀምር ሲሆን የፊልም ፕሮዱዩሰሮች በሲኒማ ቤቱ ፊልማቸውን እንዲያሳዩ ጥሪ ቀርቧል፡፡   

   ከእለታት አንድ ቀን ከባድ የበረዶ ዘመን መጣና እፅዋትና እንስሳትን በቅዝቃዜ ጨረሰ፡፡ በየእለቱ ሞቶ የሚያድረው ነብስ እጅግ እየረከተ መጣ፡፡ ይሄኔ የባህር አሳዎች መመካከር ጀመሩ፡፡ ከነዚህ አሳዎች መካከልም በጣም እሾካማ የሆኑ አሳዎች አሉ፡፡
አንደኛው አሳ፤ ለሌኛው አሳ፡-
“እስከመቼ ድረስ ዝም ብለን ተቀምጠን በበረዶ ቅዝቃዜ እናልቃለን? ለምን ቢያንስ ተጠጋግተን፣ ተቃቅፈን አንተኛም?” ይለዋል፡፡
ሁለተኛው አሳም፤
“ተቃቅፈንና ተጠጋግተን መተኛቱ ለምን ይጠቅመናል?” ሲል ይጠይቀዋል?
አንደኛው አሳ፤
“በበረዶ ባህር ውስጥ ተራርቀንና ተለያይተን ከሚቀዘቅዘን ተጠጋግተን ብናድር አንዳችን ለአንዳችን ሙቀት እንሰጣለን፡፡ ስለዚህም እርስ በርስ እንክብካቤ የመደራረግ እድል እንፈጥራለን” አለው፡፡ በዚህ ሃሳብ ተስማሙ፡፡ አጠገብ ላጠገብ ሆነው ተኙ፡፡ ሆኖም አንድ ችግር ገጠማቸው፡፡
ሲጠጋጉ ሁሉም እሾሃማ ቆዳ ስለሆነ ያላቸው ያንዱ ቆዳ የሌላኛውን እየወጋው፣ እንደቆንጥር እየጠቀጠቀው ፈፅሞ ለመተኛት አዳገታቸው፡፡ ቢለያዩ ቅዝቃዜው ሊገላቸው ሆነ፡፡ ቢቀራረቡ እሾክ ለሾክ ሆኑና ሊወጋጉ ሆነ፡፡ ምርጫቸው ከሁለቱ አንዱን ማድረግ ሆነ፡- ወይ ተለያይቶ በበረዶው ቅዝቃዜ ማለቅ፤ ወይም ደግሞ እንደምንም እሾክ ለእሾክ ተቻችሎ የጐድን ውጋቱን ችሎ ማደር፡፡
በሁለተኛው ምርጫ ተስማሙ፡፡ ብዙ ሳይገላበጡ፣ ሙቀት እየተለዋወጡ ክፉውን የበረዶ ጊዜ ማለፍ! ጐረቤት ለጐረቤቱ የጐን ውጋት እንዳይሆን መጠንቀቅ፡፡ ውጋቱ ቢኖርም ቁስል ቢፈጠርም ታግሶ፣ ችሎ ማደርን መልመድ! በዚህ ዘዴ ህያው ሙቀት እየተሰጣጡ ያንን ዘመን ተሻገሩ፤ ይባላል!
ገልቱ የራሷ ወጥ ይጣፍጣታል!
ቀጥቃጭ ሲያረጅ ዱልዱም ይቀጠቅጣል
በሀገራችን የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች አንዱ ያንዱን ችግር ችሎ፣ አንዱ ያንዱን ቁስል አክሞ መከራን በትእግስት አልፎ፣ ቢቻልም እሾኩን ነቅሎ፤ ህያው ሙቀት ፈጥሮ አገር ማዳን ባለመቻሉ፤ ብዙ እድልና አጋጣሚ አምልጧል፡፡ ጥቃቅን ችግሮችን በወቅቱ ለማለፍ ባለመቻሉ የመፈረካከስ፣ የመሰነጣጠቅ ከናካቴውም የመበታተን አደጋ ደርቷል፡፡ የእኔ ትልቅ ነኝ …እኔ ትልቅ ነኝ ፍትጊያ ለብዙ መከራ ዳርጓል፡፡ የእኔ ልዋጥ እኔ ልዋጥ ሽኩቻ (Big Fish - Small Fish Theory እንዲሉ ፈረንጆች) ለብዙ አበሳ አጋልጧል፡፡ አገርና ህዝብን ማስቀደምና የጋራ ቤት የሚሰራበትን ወቅት ለየግል ፍልሚያ በመጠቀም አያሌ የአዝመራ ጊዜዎች ባክነዋል፡፡ ልብ ማለት ያለብን ከትላንት የእርስ በርስ አለመግባባት፣ ከትላንት እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ትርምስ ማን ተጠቀመ? የሚለውን ነው፡፡ ዛሬም ከትላንት ለመማር አልረፈደም፡፡ አንድን ወቅት የዓለም ፍፃሜ አድርጐ መፈረጅ ወደ ተስፋ-መቁረጥ ነው የሚያመራው፡፡ ይልቁንም ሁሉን ነገር በትላንት በዛሬና በነገ ሰንሰለት ላይ እንዳለ ክስተት እያዩ፣ በትእግስትና በፅናት መጓዝን ለማወቅ ታላቅ ጥበብ ነው፡፡ አገር “በእድገት ላይ ነን ተብሎ ሊፃፍባት አይችልም፡፡ ወይም እንደ ንግድ በአዲስ መልስ ሥራ ጀምረናል” አይባልባትም፡፡ ዲሞክራሲ የተከለከለች የበለስ ፍሬ የማትሆነው ሁሉን ነገር እንደ ሂደት እያያያዝን ካየን ነው፡፡ ፍፁም የሆነ ዲሞክራሲ እንዳለመኖሩ፤ በተናፅሮ የምናገኘውን ዲሞክራሲ ለመጨበጥም ብዙ ድካም ይጠይቃል - በድሮው ቋንቋ ያለመስዋዕትነት ድል የለም - እንደ ማለት ነው፡፡ ከማማረር መማር ነው ነገሩ!” ጥርስ ነጭ ይሁን አይሁን፤ ግን ይጠንክር” ይላሉ አበው፡፡ አንድም፤ “በካፊያው ምን አስሮጣችሁና ገና ዝናቡ አለ አይደለም ወይ” የሚለውን ልብ ብሎ ማሰብ ነው፡፡
ዲሞክራሲን፤ ፍትሐዊነትን፣ መልካም አስተዳደርን፣ እውነተኛ ምርጫን፣ እኩልነትትን፣ ዲፕሎማሲን፣ ለማግኘት አያሌ አመታትን አሳልፈናል፡፡ እንደ አፍ እንደማይቀልም፣ አውቀናል፡፡ ተገንዝበናል፡፡ አንድም የራሳችንን የሽኩቻ ባህላዊ አሽክላ በቀላሉ ለመላቀቅ ባለመቻል፤ አንድም ደሞ ከውጪ የሚመጣብንን ጫና ለመመከት ባለመታደል፣ ጠንክረን ዳር የመድረስ ነገር የህልም ሩጫ ሲሆንብን ከርሟል፡፡ ዊንስተን ቸርችል፤ “እውነት በጣም እፁብ በመሆኗ በውሸት የክብር ዘቦች መጠበቅ ይኖርባታል” ያለውን እንኳ ለመፈፀም መቻቻል አልሆነልንም፡፡ ድህነትን ለመዋጋት ያላግባብ የመበልፀግን አባዜ አስቀድሞ ማሸነፍ ያስፈልጋል፡፡ ወዲህ እየለፈፉ ወዲህ እየዘረፉ አይሆንም፡፡ ከልብ የማናደርገውን ነገር በአዋጅ ብንናገረው ግማሽ-ጐፈሬ ግማሽ-ልጭት ሆኖ ነው የሚቀረው፡፡ ሕግ ለሁሉም እኩል የሚሰራባት አገር ታስፈልገናለች! “ድካማችን ሁሉ የእንቧይ ካብ፣ የእንቧይ ካብ” የማንልባት አገር ታስፈልገናለች! ሟርት የማይበዛባት አገር ታስፈልገናለች! በአንድ ሰሞን ዘመቻ ብቻ አገር ይለወጣል ከሚል አስተሳሰብ የፀዳች አገር ታስፈልገናለች! ጅራፍ ራሱ ገርፎ እራሱ ሲጮህ የማናይባት አገር ታስፈልገናለች! ራሱ ሰርቆ አፋልጉኝ ይላል እንደተባለው አይን-አውጣ፣ ሌባ እያየን ዝም የማንልባት አገር ታስፈልገናለች! ባንድ በኩል የራሳችንን ድምፅ ብቻ መልሰን ለማዳመጥ ዝግጁ ከሆን፣ በሌላ በኩል እኔ ያልኩትን ብቻ አዳምጡ ካልን፤ የትላንትናን ዜማ ብቻ የምንደግም ከሆነ፤ “ገልቱ የራሷ ወጥ ይጣፍጣታል”፤ “ቀጥቃጭ ሲያረጅም ዱልዱም ይቀጠቅጣል” የሚሉትን ተረቶች ስናሰላስል መክረማችን ነው!

ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ምሽት ብዙዎች በጉስቶ ሬስቶራንት የተደረደሩ የኮካ ኮላ ምርቶችን አተኩረው ሲመለከቱ ያስተዋለ ግር ሊሰኝ ይችላል፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ ሁሉም በኮካ ጠርሙሶች ላይ የሚፈልገው የራሱን ስም ነበር፡፡ ምክንያቱም ኮካ ኮላ የተለመዱ የኢትዮጵያውያን ስሞች የታተመባቸው ምርቶች ማቅረቡን ይፋ ያደረገበት ምሽት ነው፡፡
በእርግጥ ታዳሚው ሁሉ (ጋዜጠኞች፣ አርቲስቶችና ታዋቂ ሰዎች ተገኝተው ነበር) የየራሱን ስም አግኝቷል ማለት አይደለም፡፡ የተወሰኑ የተለመዱ ስሞች ተመርጠው ነው የታተሙት፡፡ ለዚህ ነው ብዙዎች በእልህ ስማቸውን ሲፈልጉ ያመሹት፡፡ የተወሰኑት ፈልገው አግኝተዋል፡፡ ያላገኙትም ግን መፅናኛ አላጡም፡፡
የሚስት ወይም የባል፣ የፍቅረኛ አሊያም የልጆች ወይም የዘመድ ወዳጅ ስሞች ያሉባቸው የኮካ መጠጦችን አግኝተዋል፡፡
እኔ ራሴ ስሜ ያለበት ኮካ ማግኘት ካልቻሉት መካከል አንዱ ነበርኩ፡፡ ሆኖም የባለቤቴ፣ የእናቴና የቅርብ ወዳጄ ስሞች ያሉባቸው ሦስት የኮካ ኮላ ምርቶችን በማግኘቴ ፈንድቄአለሁ፡፡ የበለጠ የፈነደቅሁት ደግሞ ኮካውን ለባለ ስሞቹ ሳጋራቸው ነው፡፡ኮካ የጀመረው አዲሱ የገበያ ትውውቅ ዘመቻም “Share A Coke” የሚል ነው፡፡ የኮካ ኮላ ኢትዮጵያ ብራንድ ማናጀር አቶ ምስክር ሙሉጌታ እንደተናገሩት፤ 200 የወጣቶችና 200 የአዋቂ ኢትዮጵያውያን ስሞችን በመለየት የአዋቂዎቹ ስሞች 1.5 ሊትር በሚይዘው “ከበር ቻቻ” ላይ የታተሙ ሲሆን የቀሩት 200  ስሞች ደግሞ 0.5 ሊትር በሚይዘው “ሽር-ሽር” የኮካ ጠርሙሶች ላይ ታትመዋል፡፡
በኮካ ምርት ላይ ከታተሙት ታዋቂ ስሞች መካከል “ሳባ”፣ “አበበ”፣ “ሃያት”፣ “ቦንቱ”፣ “ዊንታ”… ወዘተ የሚሉ ይገኙባቸዋል፡፡ የግለሰብ ስሞች የሰፈሩባቸው የኮካ ምርቶች በአገር አቀፍ ደረጃ በገበያ ላይ የዋሉ ሲሆን በዋና ዋና ማከፋፈያዎች፣ በሱቆች፣ በሆቴሎችና ሬስቶራንቶች ለሽያጭ እንደቀረቡ ተገልጿል፡፡
የኮካ ኮላ የገበያ ትውውቅ ዘመቻ በአህጉር ደረጃ (በመካከለኛው፣ በምስራቅ፣ በምዕራብና ደቡብ አፍሪካ) በመካሄድ ላይ ሲሆን ይሄም በገበያው ላይ በጐ ተፅእኖ እንደሚፈጥርና የኮካን “ደስታን የማጋራት” ዓለም አቀፋዊ እቅድ እንደሚያጠናክርለት ይጠበቃል ብሏል - ኩባንያው በመግለጫው፡፡ ኩባንያው እንደ ፌስ ቡክ ወይም ትዊተር ያሉ የማህበራዊ ሚዲያዎችን እንዲሁም ሌሎች አሳታፊ የማስታወቂያ መድረኮችን በመጠቀም፣ ደንበኞች የመረጧቸው ስሞች እንዲታተምላቸው ማዘዝ ብቻ ሳይሆን ኮካን የመጋራት አይረሴ የደስታ ቅፅበቶች ላይ ያተኮሩ መልእክቶችን፣ ፎቶዎችን ወይም ቪዲዮዎችን እንዲጋሩ የሚያስችል መሆኑ ታውቋል፡፡


* ጥናቱ ለ15 ዓመታት በአራት አገራት ላይ የተካሄደ ነው
*  ያለ ዕድሜ ጋብቻ ላይ ያልተጠበቀ ውጤት ተገኝቷል
* በህፃንነት የተጎዱ ልጆች ላይ የመሻሻል ሁኔታ ታይቷል
* የትምህርት ጥራት ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን ጥናቱ ያመለክታል

   በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ በአራት የተለያዩ አገራት ለ15 ዓመታት የተካሄደው ልጆች ላይ ያተኮረ የ“ያንግ ላይቭስ” ጥናት ኢትዮጵያንም ያካትታል፡፡ በጥናቱ ላይ የተሳተፈው የፓንክረስት የምርምር ተቋም ዳይሬክተር ዶ/ር አሉላ ፓንክረስት በፕሮጀክቱ ዙሪያ የሰጡንን ማብራሪያ እንደሚከተለው ተጠናቅሮ ቀርቧል፡፡
የ“ያንግ ላይቭስ” ፕሮጀክት
“ያንግ ላይቭስ” የተሰኘው የጥናት ፕሮጀክት በኢትዮጵያ፣ ፔሩ፣ ቬትናምና ህንድ ላይ ለ15 ዓመታት የተካሄደ ሲሆን በልጆች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በየአገሩ በጥናቱ ውስጥ የተካተቱት እ.ኤ.አ በ2000 ዓ.ም የተወለዱና በአሁኑ ወቅት 14 አመት የሞላቸው ልጆች ናቸው፡፡ በእያንዳንዱ አገር ሶስት ሺህ ልጆች ላይ ነው የምናተኩረው፡፡ ሁለት ሺዎቹ በ2000 ዓ.ም የተወለዱ፣ አንድ ሺዎቹ ደግሞ ለማነፃፀሪያ እድሜያቸው ከፍ ያለ አሁን አስራ ዘጠኝ አመታቸው ላይ የሚገኙ ልጆች ናቸው፡፡  ሁለት ሺዎቹን ከተወለዱ ጀምሮ እየተከታተልናቸው ሲሆን እስከ አሁን ድረስ  በልጆቹና በወላጆቻቸው ላይ አራት ዙር ጥናቶች  ተካሂደዋል፡፡
በኢትዮጵያ ጥናት የተካተቱት ክልሎች አዲስ አበባ፣ ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች ሲሆኑ ከተማ ገጠር፣ ሀብታም ቤተሰብ ድሀ ቤተሰብ፣ ሴት ወንድ የሚሉ ስብጥሮችን ባካተተ መልኩ የተካሄደ ነው፡፡  ጥናቱ ድሀ ተኮር በመሆኑ የምግብ ዋስትና ችግር ባለባቸው  በሀያ የተለያዩ ቦታዎች ላይ የተሰራ ነው ፡፡
የጥናቱ ትኩረት
ጥናቱ አመጋገብና ጤና ፣ ትምህርት፣ የልጆች እድገትና የወደፊት አላማቸው ላይ ያተኩራል፡፡ ጥናቱን  የሚያሰራው የኢትዮጵያ የልማት ጥናት ድርጅት ሲሆን  የኮሙኒኬሽን ስራችን ደግሞ ከህፃናት አድን ድርጅት ጋር ነው፡፡ አሁን  በአራተኛው ዙር ጥናት ውጤትና ከአንድ እስከ አራት ዙር በተካሄዱት ጥናቶች ለውጦቹ ምንድን ናቸው የሚለው ላይ አተኩረን እየሰራን ነው፡፡    
ለጥናቱ የተመረጡ አገራት መመዘኛ
ጥናቱ የሚካሄደው በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ በተለያየ የአለም ክፍልና በተለያየ የእድገት ደረጃ ላይ የሚገኙ አገራት በሚል መመዘኛ ነው የተመረጡት፡፡ ኢትዮጵያ ድሀ አገር እንዲሁም  ለጠንካራ እድገትና ለልማት ጥሩ የመንግስት አቋም ያለበት በሚሉ መስፈርቶች ነው የተመረጠችው፡፡ ክልሎቹ የተመረጡበት መስፈርት ደግሞ ጥናቱ የረጅም አመታት ጥናት እንደመሆኑ መጠን ትልቁ ስጋታችን የምንከታተላቸው ልጆች ከአካባቢው እንዳይጠፉ የሚል ነበር፡፡ አርብቶ አደር አካባቢዎች ምናልባት ልጆችን ለመከታተል ያስቸግራል ከሚል አንፃር ነው በጥናቱ ያልተከታተሉት፡፡ ነገር ግን  ተጨማሪ ጥናቶችም ይኖሩናል፡፡ በህፃናት አድን ድርጅት ድጋፍ ለማነፃፀር እንዲያግዘን ትምህርት ቤት ላይ ትኩረት ያደረገ ጥናት በሶማሌና አፋር ክልል ላይ አድርገናል፡፡
ወላጅ ያጡ ልጆች የጉልበት ብዝበዛ፣ በከተማ እድገት ምክንያት ልጆችና ቤተሰቦቻቸው ከአካባቢያቸው ሲፈናቀሉ እንዲሁም ከኮንዶሚኒየም ቤት አሰራር ጋር የተገናኘ ጥናት አካሂደናል፡፡ በቅርቡም አንድ የጀመርነው ወደ አዋቂነት ሽግግርና ቤተሰብ እንዴት እንደሚመሰርቱ፣ እንዴት እንደሚያገቡ፣ እድሜ፣ ወሊድ እና የመሳሰሉት ላይ ያተኮረ ጥናት አለ፡፡
ሌላ የምንጀምረው ጥናት ደግሞ የመዋዕለ ህፃናትና ቅድመ ትምህርት ፕሮግራሞች ላይ ይሆናል፡፡ በጥናቱ ያገኘነው አንድ ነገር ምንድን ነው… የአንደኛ ክፍል ትምህርታቸውን ከመጀመራቸው በፊት በቄስ ትምህርትም ይሁን በመዋዕለ ህፃናት ተምረው ያለፉ ልጆች፣ ሲያድጉ ያንን እድል ካገኙት ጋር ሲነፃፀሩ የተሻለ ውጤት እንደሚያመጡ ነው፡፡ በማንበብ፣ በሂሳብና በማሰላሰል ችሎታቸው የተሻሉ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ይህ የመዋዕለ ህፃናት ደግሞ በመንግስት ብዙ ትኩረት ስላልተሰጠውና ትኩረት የሚሻ ጉዳይ በመሆኑ ይበልጥ ልናጠናው ሀሳብ አለን፡፡ ሌላው የጥናት ትኩረታችን ልጆች ላይ የሚደርስ ጥቃት ነው፡፡
የጥናቱ ውጤቶች
ጥናቱ ከሚያተኩርባቸው አንዱ አመጋገብ ላይ ነው፡፡ ሌላው ትምህርት፣ ሶስተኛው የልጆች እድገት ላይ ነው፡፡ አመጋገብን ስናይ ብዙ ለውጦች ያሉ ቢሆንም አሁንም የአመጋገብ እጥረት ችግር ላይ የወደቁ ልጆች እንዳሉ የጥናት ውጤቱ ያሳያል፡፡ ተስፋ የሚሰጡ ነገሮችም አሉ፡፡  እስከ አሁን አንድ ህፃን ከተፀነሰበት ጊዜ ጀምሮ ያሉት አንድ ሺህ ቀናት ለህፃኑ እድገት ወሳኝ እንደሆኑ ይታመን ነበር፡፡ በነዚህ አንድ ሺህ ቀናት ውስጥ ህፃናት ጥሩ ምግብ ካላገኙ በዕድገት ሂደታቸው የአእምሮና አካላዊ ጉዳት እንደሚያጋጥማቸውና ተስፋ አይኖራቸውም የሚል አስተሳሰብ ነበር፡፡ በጥናት ውጤቱ ግን እኛም ያልጠበቅነው ነገር ነው ያገኘነው፡፡ በልጅነታቸው ከተጎዱት ውስጥ የተወሰኑት በጣም ደህና ሆነው ነው ያደጉት፡፡ ቁመታቸው፣ የትምህርት ደረጃቸው ጨምሮ በብዙ ነገር ጥሩ ሁኔታ ላይ ናቸው፡፡ ከዚህም በመነሳት አንዳንዶቹ በህፃንነታቸው ተጎድተው ለምን ደህና ሆኑ? አንዳንዶቹ ለምን መጥፎ ሁኔታ ላይ ሆኑ? ለውጡን ያመጣው ምንድነው? በሚሉት ላይ አተኩረን ማጥናት እንፈልጋለን፡፡ የምግብ ዋስትና ችግር ትንሽ ተሻሽሎ ነው ያገኘነው፡፡ ልጆቹ የሚመገቧቸው ምግቦች  ስብጥርም ተሻሽሏል፡፡ የንፅህና ጉዳይም ላይ መሻሻሎች አሉ፡፡ ስጋት ሆኖ ያገኘነው የመጠጥ ውሀ ላይ ነው፡፡ የመጠጥ ውሀ ሁኔታ የባሰ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ትምህርት ላይ ጥሩ ተብሎ የሚጠቀሰው ሽፋን ነው፡፡ የገጠርና የከተማ ልዩነት እንዳለ ቢሆንም  የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ተማሪዎች ቁጥር በጣም ከፍ ብሏል፡፡ ከዚያም ሌላ የሴቶች ተማሪዎች ቁጥር ይበዛል፡፡ በትምህርት ላይ ያገኘነው አሳሳቢ ነገር የጥራት ጉዳይ ነው፡፡ ቅድም እንዳልኩሽ የሁለት እድሜ ክልል ነው የምናነፃፅረው፡፡ ይህን ስናደርግ የማንበብና የሂሳብ ችሎታ የመቀነስ አዝማሚያ አሳይቷል፤ በተለይ በገጠር፡፡ ይህ አሳስቦናል፡፡ በተለይ የሂሳቡ ውጤት መቀነሱ ጠለቅ ያለ ጥናት ያስፈልገዋል፡፡ ችግሩ ከትምህርት ቤቶች፣ ከመምህራን ችሎታና ፍላጎት ፣ ከተማሪዎች መብዛት፣ ከልጆች የስራ ጫና… የመሳሰሉት አንፃር መታየት ይኖርበታል፡፡  እዚህ ላይ መጠናት ያለበት ነገር የተማሩ እናቶች ያሏቸው ህፃናት የተሻሉ ሆነው መገኘታቸው ነው፡፡ ሌላው ያለ እድሜ ጋብቻ ላይ ያገኘነው ውጤት ያልጠበቅነው ነው፡፡ በጥናቱ ከተካተቱ ሌሎች አገራት ጋር ሲነፃፀር የኢትዮጵያ ዝቅ ያለ ነው፡፡
የአገራቱ ንፅፅር
አራቱን አገራት ስናነፃፅር፣ እኛ የጠበቅነው ያለ እድሜ ጋብቻ ላይ ኢትዮጵያ ከፍተኛውን ቁጥር ትይዛለች ብለን ነበር፡፡ ውጤቱ ግን በተቃራኒ ነው የሆነው፡፡ ህንድ ከፍተኛውን ቁጥር ይዛለች፡፡
በህንድ አስራ ዘጠኝ አመት ከደረሱ ሴቶች 34 በመቶው አግብተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን አስራ ሶስት በመቶ ብቻ ናቸው ያገቡት፡፡ ከአራቱ አገራት የቀነሰ ቁጥር ነው የተገኘው፡፡ልጆች በመውለድ ደግሞ አንደኛ ፔሩ ናት፤ ምክንያቱም ሳያገቡም ይወልዳሉ፡፡ ውጤቱ በደረጃ ሲቀመጥ፤ ፔሩ፣ ህንድ ፣ ቬትናምና ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ ይህ እጅግ ተስፋ የሚሰጥ ግኝት ነው፡፡ የትምህርት ጥራት ላይ ኢትዮጵያና ህንድ የሚያሳስባቸው አገሮች ሆነው ተገኝተዋል፡፡ የፔሩ ልጆች በተለይ በሂሳብ በጣም የላቁ ናቸው፡፡ የጥራት ችግሩ በህንድና ኢትዮጵያ ተመሳሳይ ሲሆን በሌሎቹ አገራት ሲሻሻል ሁለቱ ላይ ለምን ዝቅ አለ የሚለው ገና ጥናት የሚፈልግ ነው፡፡ ግን አገሮቹ የጀመሩበት ሁኔታ ግምት ውስጥ ሲገባ ኢትዮጵያ ማዳረስ ላይ ጥሩ ውጤት አምጥታለች፡፡
ለዚህ ደግሞ ብዙ ስራ መሰራቱ ይታወቃል፡፡ ትምህርት ቤት መገንባት፣ መምህራንን ማሰልጠን፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማር፣ የመፃፊያ ፊደሎች ለውጥ… ግምት ውስጥ ሲገባ ጥራትን እንደሚነካ የሚጠበቅ ነው፡፡ በአመጋገብና በጤና ረገድ ኢትዮጵያ ችግር የነበረባትና ያለባት አገር ናት፡፡ ግን ሌሎቹም አገሮች ውስጥ ደሀው አካባቢ ችግሮች አሉ፡፡ በጣም የሚገርመው በአራቱም አገሮች በህፃንነት የተጎዱ ልጆች ላይ የመሻሻል ሁኔታ ታይቷል፡፡ ይህ አለምአቀፍ ክስተት ሲሆን ኢትዮጵያም ላይ ተመሳሳይ ውጤት ተገኝቷል፡፡

አቶ አንዳርጋቸው ባለፈው ወር ከባለቤታቸው ጋር በስልክ ተነጋግረዋል

የእንግሊዝ የፓርላማ አባላትን የያዘ የልኡካን ቡድን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ከእስር ማስፈታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ለመደራደር በቀጣዩ ወር ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ ዘ ኢንዲፔንደንት ትናንት ዘገበ፡፡
ሁሉንም የእንግሊዝ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአባልነት የያዘው የፓርላማ አባላት የሰብዓዊ መብቶች ቡድን ምክትል ሊቀመንበር ጀርሚ ኮርባይን የሚመሩት የልኡካን ቡድኑ፣ ከሚመለከታቸው የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጋር በመምከር የሞት ፍርዱ ተፈጻሚ እንዳይሆንና ግለሰቡ ከእስር እንዲፈቱ ለማስቻል እንደሚሰሩ ዘገባው አመልክቷል፡፡አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንግሊዛዊ ዜግነት ያላቸው እንደመሆኑ የእንግሊዝ መንግስት ጉዳዩን አጽንኦት ሰጥቶ መከታተልና ግለሰቡን ከሞት ማዳን ይጠበቅበታል ያሉት ኮርባይን፤ ቡድኑ አቶ አንዳርጋቸው ግልጽ ባልሆነና ተቀባይነት በሌለው የህግ አካሄድ ለእስር ተዳርገዋል ብሎ እንደሚያምን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ አቶ እንዳርጋቸው የአሸባሪ ቡድን አባል ቢሆኑም በእስር ላይ ተገቢው እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑን በተደጋጋሚ መግለፁ ይታወሳል፡፡
የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ቃል አቀባይ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው ነሃሴና ታህሳስ ወር ላይ ከተደረጉት ሁለት የመንግስት ተወካዮች ጉብኝቶች ውጭ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ለመጎብኘት እንዳንችል አግዶናል ብለዋል፡፡
የእንግሊዝ መንግስት የአቶ አንዳርጋቸው ጉዳይ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳስበው ገልጸው፣ በግለሰቡ ላይ የተጣለው የሞት ፍርድ ተፈጻሚ እንዳይሆን በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫና ማድረጉን እንደቀጠለበትም አስረድተዋል፡፡በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቃል አቀባይ በበኩላቸው፤ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የኢትዮጵያን መንግስት ለማፍረስ የሚሰራ አሸባሪ ቡድን አባል ናቸው፣ በእስር ላይ ሆነውም ተገቢው እንክብካቤ እየተደረገላቸው ነው፤ እስረኞችን ማሰቃየት ኢሰብአዊ ድርጊት እንደመሆኑ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ የሚደረግ  አይደለም ሲሉ መናገራቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በቅርቡ ይፋ ያደረገው ሪፖርት ግን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት ከቅርብ አመታት ወዲህ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የሚፈጸምባቸው ስቃይ እያየለ መምጣቱን የሚያመላክት መሆኑን አክሎ ገልጿል፡፡አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፤ ባለፈው ወር እንግሊዝ አገር ወደምትገኘው ባለቤታቸው ስልክ ደውለው መገናኘታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ በአብዛኛው ስለልጆቻቸው ጉዳይ እንዳወሩ፣ ደህንነታቸውን እንደገለጹላቸው፣ እንዲሁም ለልጆቼ የማይሆን ተስፋ መስጠት አልፈልግም ማለታቸውን ባለቤታቸው እንደተናገሩ አመልክቷል፡፡