Administrator

Administrator

 ዋና አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ስኬታማነት የወዳጅነት ጨዋታ ያስፈልገኛል አሉ፡፡ ቡድናቸው ከመስከረም ወር በፊት ከጠንካራ ቡድን ጋር በመጋጠም አቋሙን መፈተሽ አለበት ብለዋል፡፡ ዋልያዎቹ  በመጭው 2008 ዓ.ም በጥቅምት ወር በአፍሪካ ዋንጫ፤ በቻን እና በዓለም ዋንጫ የማጣርያ ግጥሚያዎች ይኖሩታል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ከሲሸልስ በ5ኛው የቻን ውድድር የመጨረሻ ዙር ማጣርያ ከብሩንዲ በዓለም ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ ከስዋቶሜ ፕሪንስፒ በሚያደርጋቸው 3 ጨዋታዎች በጥቅምት ወር ይፈተናል፡፡ ዋና አሰልጣኝ ዮሃንስ ከሶስቱ የማጣርያ ግጥሚያዎች በተለይ አስቀድሞ ከሲሸልስ ጋር  ከሜዳ ውጭ ለሚያደርጉት  የአፍሪካ ዋንጫ ሁለተኛ የምድብ ማጣርያ ጨዋታ ትኩረት አድርገዋል፡፡ ስለሆነም አቋማቸውን ለመፈተሽ በመስከረም ወር በፊት የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል በ2018 እኤአ ላይ ራሽያ ለምታስተናግደው 21ኛው የዓለም ዋንጫ የቅድመ ማጣርያ ድልድል ከሳምንት በፊት ወጥቷል፡፡ አፍሪካን የሚወክሉትን 5 ብሄራዊ ቡድኖች ለመለየት የሚደረገው ማጣርያ በሶስት ምእራፎች የተከፈለ ነው፡፡ ከአህጉሪቱ 53 ብሄራዊ ቡድኖች ኢትዮጵያ ከ28 እስከ 53 ባለው ደረጃ ስለተያዘች 3ቱን የማጣርያ ምእራፎች ማለፍ ይጠበቅባታል፡፡ በመጀመርያው ዙር የቅድመ ማጣርያ ምዕራፍ 26 ብሄራዊ ቡድኖች አንዷ ኢትዮጵያ ስትሆን የደርሶ መልስ ጨዋታዎቹ ወደ ሁለተኛው ዙር ማጣርያ የሚገቡትን 13 ቡድኖች ይፈጥራሉ፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በዚህ የመጀመርያ ዙር ማጣርያ ለደርሶ መልስ ጨዋታ የተደለደለው ከስዋቶሜ እናፕሪንሲፒ ጋር ነው፡፡ የመጀመርያውን ጨዋታ ከሜዳ ውጭ  የመልስ ጨዋታው በሜዳ ላይ የሚደረግ ይሆናል፡፡ በመካከለኛው የአፍሪካ ዞን የምትገኘው ስዋቶሜናፕሪንሲፒ በፊፋ የእግር ኳስ ደረጃዋ 188ኛ ናት፡፡ በሁለተኛ ዙር የኢትዮጵያ ተጋጣሚ የምትሆነው ከመካከለኛው አፍሪካ ዞን የምትወከለው ኮንጎ ኪንሻሳ ናት ቀይ ሴይጣኖች በሚል ቅፅል ስም ትታወቃለች፡፡ በሁለተኛ ዙር ማጣርያ ቀጥታ የገቡት ብሄራዊ ቡድኖች ከ1 እስከ 27 ደረጃ ያላቸው ሲሆኑ በመጀመርያ ዙር ማርያ ካለፉት 13 ብሄራዊ ቡድኖች ጋር በዚህ ምእራፍ  አገራት የደርሶ መልስ ትንቅንቅ የሚያደርጉ ይሆናል፡፡ በሁለተኛ ዙር የ40 ብሄራዊ ቡድኖች ትንቅንቅ ጥለው ማለፍ የሚችሉት  ብሄራዊ ቡድኖች ደግሞ ወደ የመጨረሻው እና ሶስተኛው ዙር በሆነው የምድብ ማጣርያ ገብተው በአምስት ምድቦች ተከፍለው የዓለም ዋንጫ ቲኬታቸውን ለመቁረጥ ይፋለማሉ፡፡

 የሰላም ጓዶች አስደማሚ ጋብቻ
   ፕሬዜዳንት ባራክ ኦባማ ባለፈው ሐምሌ የማርያም ዕለት ከሰአት በኋላ   በአፍሪካ ህብረት ኔልሰን ማንዴላ  አዳራሽ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፤ በመላው አፍሪካ ከተሰማሩት የአሜሪካ የሰላም ጓዶች  ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት  ናቸው ማለታቸው እውነታቸውን ነው፡፡ ከእነኝህ ወጣት አሜሪካዊያን  የሠላም ጓዶች  መካከል አንዱ የሥራ ባልደረባዬ ነው፡፡ ታዲያ የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን  ንግግር ስሰማ፣ ይኸ የሠላም ጓድ  እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ከአገሩ ልጅ ጋር  ያደረገው የጋብቻ ስነ ሰርአት ትዝ አለኝ፡፡
ይህ  ባልደረባችን  ባለፈው ሰኔ ወር አጋማሽ አንድ እሮብ ከሰአት በኋላ እያንዳንዳችን ጋ እየመጣ “ተነገ ወዲያ አርብ ሠርጌ ነው፤ ስለዚህ በ12፡30 ከኢድናሞል ወረድ ብሎ በሚገኘው--- ሬስቶራንት እንገናኝ፤ አለባበስ ቀለል ያለ ይሁን፤ሱፍና ክራቫት አስፈላጊ አይደለም” ብሎ ነገረን፡፡ እኛም ˝..ጥላኝ ሄደች በሀምሌ ጨለማ..˝ በሚባልበት የክረምት ወራት የሚደረግ  የፈረንጅ ሰርግ ላይ  ለመታደም   በሶሻል ኮሚቴአችን አማካኝነት መጠነኛ ስጦታ አዘጋጅተን የእራት ግብዣው ቦታ ተገኘን፡፡ ሙሽሮቹ እስኪመጡም ቢራችንን እየጠጣን ጠበቅናቸው፡፡
ወደ አመሻሹ ላይ ሙሽራው ሻሩናስና  ሙሽሪት ኤሪካ  እግብዣው ቦታ ሲደርሱ ደስታ በፊታቸው ላይ ይነበብ ነበር፤  ይፍነከነካሉ፤ያገኙትን ሁሉ መሳም ፤አብሮ ፎቶ መነሳት፤የሰርግ እለት ወሎአቸውን ማስረዳት፤በደረሱበት ጠረጴዛ ሁሉ መጠጥ ማስቀዳት፤ብቻ ምን አለፋችሁ ደስታቸው መጠን ያለፈው ሆነ፡፡ ሙሽሮቹ በተናጠል እያንዳንዱ ጠረጴዛ ላይ እየሄዱ  የሰርጋቸውን አዋዋል ይነግሩን ገቡ፡፡ የሙሽሮቹን  የሠርግ ቀን  ውሎ  እስቲ ላስቃኛችሁ፤
ሙሽሪትና ሙሽራው አዘውትረው በርገር ወደሚበሉበት ካፌ ሄደው ቁርስ ከበሉ በኋላ ዘወትር እንደሚያደርጉት ሁሉ ወደሚያውቁት ሊስትሮ ሄደው ጫማቸውን በማስጠረግ የሠርግ ቀናቸውን ጀመሩ
ወደ ውጪ ጉዳይ ሚ/ር  በመሄድ የጋብቻ ሰርተፊኬታቸውን  ለማግኘት  የሚያስችለውን  ወረቀት አገኙ
ወደ ጉለሌ ክ/ከተማ የወሳኝ ኩነቶችና የኗሪዎች አገልግሎት ጽ/ቤት ሄደው የጋብቻ ፊርማቸውን  በማኖር፣ የጋብቻ ሰርተፊኬታቸውን ተቀበሉ፤የቀለበት ስነሰርአታቸውንም በዛው አካሄዱ
የወረቀት ስራው ከተጠናቀቀ በኋላ ሙሽሮቹ ቀደም ሲል  በተደጋጋሚ  ወደተዝናኑበት  አንዲት መኪና ተከራይተውና ፎቶግራፍ የሚያነሳውን ጓደኛቸውን ይዘው  ወደ  እንጦጦ ተራራ አቀኑ፡፡ እንጦጦ ተራራ ላይ ከሚኖሩ  ሀጻናት ጋር  በተለይ ሙሽሪት ˝ እቴ እሜቴ የሎሚ ሽታ ˝ ን  ተጫወተች ፤ሙሽሮቹ እከብቶች ግጦሽ ሜዳ ላይ ተንሸራሸሩ፤ፎቶ ተነሱ፤ተሳሳሙ፤ታስሮ እንደተለቀቀ እምቦሳ ቧረቁ፤ አንድ ጎጆ ቤት ገብተው የሚወዱትን ጠላ ጠጡ፤ የእንጦጦ ህጻናት ˝መልካም ጋብቻ˝ በማለት እቅፍ አበባ አበረከቱላቸው
ከእንጦጦ መልስ እግረ መንገዳቸውን ሽሮ ሜዳ የአገር ልብስ መሸጫ ሱቅ ወዳለው  ጓደኛቸው  ጎራ ብለው ሰርጋቸውን እያከበሩ መሆናቸውን በመንገርና በማስደመም  ጓደኛቸው  ሱቅ ውስጥ ፎቶ ተነሱ፤ተያይዘውም በአቅራቢያው ወደሚገኘው ጠጅ ቤት ሄደው ጠጅ ጠጡ፤ ጠጅ ቤት ለነበሩት መሸተኞች ሙሽሮች መሆናቸውን በመግለጥ መሸተኛውን የሰርጋቸው ደስታ ተካፋይ አደረጉ፤ ፎቶም ከመሸተኛው ጋር ተነሱ፡፡
 ከዛም ሙሽራው በተደጋጋሚ ምሳ ወደሚበላበት ሬስቶራንት ሄደው በኢትዮጵያዊ ጉርሻ የታጀበ እንጀራ በወጥና ፒዛ በሉ
ወደ አዲስ አበባ መሀል ከተማ መስቀል አደባባይ ከመድረሳቸው በፊት አንድ በግ ተራ በመሄድ ከበግ ሻጮች፤ ገዢዎችና ከበጎቹ  ጋር ፎቶ ተነሱ
መስቀል አደባባይ እንደደረሱ አላፊ አግጋዳሚውን ሰብሰብ በማድረግ ጮክ ብለው  ˝ “ወዳጆቻችን ፤ዛሬ ሰርጋችን ነው!˝ ብለው ገለጻ ቢጤ አደረጉ፤ከዛም ሙሽሪት የያዘችውን እቅፍ አበባ ወደ ሰማይ በተነችው፤ የተሰበሰበው ጥቂት  ተመልካችም አበባውን እየተሻማ ተቀራመተው
ከዛ ወደ ቤታቸው በመሄድ እረፍት አድርገው እራት ወደተዘጋጀበት ሬስቶራንት አመሩ
እኛ ታዳሚዎች ዘመን የማይሽረውን ˝ ሙሽራዬን˝ እያዜምን ተቀበልናቸው፤ቁጥራችን ከ35 አይበልጥም ነበር
የምግብና መጠጥ መስተንግዶው ቀጠለ፤ከሁሉም አገሪቱ ማዕዘናት  ያሉ ባህላዊ  ጨዋታዎች ድምጻቸው  ከፍ  ብሎና ከቀደምት የእንግሊዝኛ ዘፈኖች ጋር ተቀላቅሎ   ተደመጡ፤እስክስታ ተመታ፤ዳንሱ ቀለጠ
 በመጨረሻ የኬክ መቁረሱ ሥነስርአት ተከናወነ፤ እሱንም ተከትሎ ከዚህ በታች የምታዩት የሙሽሮቹ ፎቶግራፍ በጥሩ ፍሬም ሆኖ  በስጦታ መልክ  ተበረከተላቸው፡፡ እኛ ስጦታውን ስናበረክት ከእኛ ቀድሞ ይህ  ምስልና  የሙሽሮቹ የሰርግ  ቀን ውሎ በፌስ ቡክና በኢንስታግራም ተለቆ ነበር ፡፡
 በሰርጉ ማግስት  ከሙሽራው ጋር ቆይታ አድርጌ ነበር፡፡
˝ሻሩናስ ፤ሰርግህን  አስመልክቶ አንድ ጽሁፍ ብጽፍ ፈቃደኝ ነህ?”
˝አዎ ግርማ ደስተኛ ነኝ ፤ሰርጋችንን ወደድከው?”
˝አዎ በጣም ወድጀዋለሁ፤ለእኛ  ወጣቶች እንደ ሞዴል ጋብቻ አድርጌ ስለአየሁት በሰርጋችሁ ላይ አንድ ጽሁፍ  ጋዜጦች ላይ አወጣ ይሆናል ˝
˝ግርማ በጣማ ደስተኝ ነኝ፤ የሰርጉን ፎቶዎች በሙሉ ሰርቨር ላይ እጭናቸዋለሁ ፤ በተጨማሪም  አንድ ጓደኛዬ ፖስት ያደረገውንም እልክልሃለሁ˝
˝በጣም ጥሩ፤ፎቶዎቹ ለጽሁፌ መነሻ  ይሆኑኛል˝
በመጨረሻም በሚቀጥለው ጥቅምት 2008 ላይ 23ተኛ አመቴን የማከብረውን፤ ከሽማግሌ መላክ እስከ ቅልቅል ድረስ ያለውን ኮተተ ብዙ የአበሻ ሰርግ ሁደት  እያሠብኩ፤
˝ሻሩናስ ፤አንድ ጥያቄ  ልጠይቅህ ከወላጆቻችሁና፤ ከዘመዶቻችሁ እርቃችሁ ሰርጋችሁን ለምን በኢትዮጵያ ምድር  ላይ  ለማድረግ  ወሰናችሁ?
˝ ግርማ፤ ለእኔና ለባለቤቴ ኤሪካ ኢትዮጵያ ልዩ ቦታ አላት፤ ስለሆነም  ሰርጋችንን  እዚሁ  በህይወታችን ውስጥ ትልቅ ስፍራ ካላቸው ወዳጆቻችን፤ ከህጻናት ጋር ፤የገጠሪቱ ኢትዮጵያን ስሜት የያዘ፤ አዘውትረን  የምንሄድባቸውን ቦታዎችና ጓደኞቻችንን  የሚያስታውስ ፤ ኢትዮጵያዊ  ስሜት ያለው   እንዲሆንልን  ስለፈለግን ነው˝ ብሎ መለሰልኝ!!
ወጣት ፍቅረኞች  እናንተስ? እኔ መቼም  ይህን ሰርግ ወድጄዋለሁ፤ ከተለመደው ኮተተ ብዙ  የአበሻ  ሰርግ ይልቅ ይኸ ቅልብጭ ያለ የሰላም ጓዶቹ  ሰርግ ይሻላል ባይ ነኝ፡፡ ምክንያቱም ሰርጉ ቀላል፤ አሳታፊና ወጪ ቆጣቢ በመሆኑ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ  ባለፈው የማሪያም ዕለት በንግግራቸው የጠቀሷቸው  የሰላም ጓዶች በአሜሪካና በኢትዮጵያ መካከል  ከንግድና  ኢንቨስትመት  ትስስሩ ጎን ለጎን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማጠናከር ላይ ናቸው፡፡ በላእላይ መዋቅር ደረጃ  በእምዬ ምኒልክ ጊዜ የተጀመረው  የኢትዮ-አሜሪካ መልካም ግንኙነት፣ በታህታይ መዋቅሩም በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ሲጠናከር መሰረተ ሰፊና ስር የሰደደ ይሆናል፡፡
ሰለዚህ  ፕሬዚዳንት ኦባማ ሆይ፤ እባክዎትን ወደ ኢትዮጵያ የሚልኩልንን  የሰላም ጓዶች   የወንድና የሴቱን ቁጥር ባመጣጠነ መልኩ ከፍ ያድርጉልን፤ እኛ ከዚህ እያጋባን እንልካቸዋለን! 

የታሊባን ቃል አቀባይ፤“መሪያችን አልሞተም፣ አሁንም እየመራን ነው“ ብሏል
 
    የአፍጋኒስታን የደህንነት ባለስልጣናት፤ የታሊባኑ መሪ ሙላህ ሞሃመድ ኦማር ከሁለት አመታት በፊት መሞቱን አረጋግጠናል ሲሉ መናገራቸውንና የቡድኑ ቃል አቀባይ በበኩላቸው፤ መሪያችን በህይወት አለ፤ አሁንም እየመራን ነው ሲሉ ማስተባበላቸውን ስካይ ኒውስ ዘገበ፡፡
የአፍጋኒስታን ብሄራዊ የደህንነት ዳይሬክቶሬት ቃል አቀባይ አብዱል ሃሲብ ሳዲቅ እንዳሉት፣ ሙላህ ሞሃመድ ኦማር በጸና ታሞ በነበረበት በካራቺ ከተማ ውስጥ የሚገኝ ሆስፒታል በሚያዝያ ወር 2013 ህይወቱ እንዳለፈ አረጋግጧል፡፡
ሙላህ ሞሃመድ ኦማር ለመጨረሻ ጊዜ በአደባባይ የታየው እ.ኤ.አ በ2001 እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ ግለሰቡ ሞቷል ተብሎ ሲነገር ይህ ለአራተኛ ጊዜ መሆኑንና አሜሪካም በዚህ ሳምንት የወጣውን መረጃ ትክክለኛ ነው ብላ መቀበሏን ገልጧል፡፡
የታሊባኑ መሪ ሙላህ ሞሃመድ ኦማር ልጅ ሙላህ ያቆብ፣ አባቱ ከአመታት በፊት እንደሞተ ማመኑን የጠቆመው ዘገባው፣ ተቀማጭነቱ በፓኪስታን የሆነ አንድ አፍጋኒስታናዊ የታሊባን ከፍተኛ የጦር መሪም፣ ሙላህ ሞሃመድ ኦማር ከአመታት በፊት በተፈጥሯዊ ሞት ከዚህ አለም መለየቱን ለሮይተርስ መናገሩን ገልጧል፡፡
ታሊባንን የመምራት ሃላፊነቱን ልጅዬው ሙላህ ያቆብ እንደተረከበ እየተነገረ ሲሆን፣የታሊባን ቃል አቀባይ ቃሪ የሱፍ አህመዲ በበኩሉ፤መረጃው መሰረተ ቢስ ሃሜት ነው ሲል ማስተባበሉ ተዘግቧል።
እኔ እስከማውቀው ድረስ ሙላህ ሞሃመድ ኦማር አሁንም በህይወት አለ፣ቡድኑን የመምራት ሃላፊነቱንም በአግባቡ እየተወጣ ይገኛል ብሏል ቃል አቀባዩ፡፡

 የትሪፖሊ ፍርድ ቤት የጦር ወንጀል ፈጽሟል በሚል ክስ በተመሰረተበት የቀድሞው የሊቢያ ፕሬዚዳንት ሞኣመር ጋዳፊ ልጅ፣ ሳይፍ ጋዳፊ ላይ የሞት ፍርድ ውሳኔ ማስተላለፉን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
ፍርድ ቤቱ በ2011 በተቀሰቀሰው የአረብ አብዮት የግድያ፣ የግርፋትና የፍንዳታ ተግባራትን በማቀጣጠል ጥፋተኛ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ባለው ሳይፍ ጋዳፊ ላይ በሌለበት የሞት ፍርድ ቢያስተላልፍም፣ ተከሳሹ ግን ድርጊቱን እንዳልፈጸመ መግለጹን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
ከሳይፍ ጋዳፊ በተጨማሪ የቀድሞውን የሊቢያ የደህንነት ሃላፊ አብዱላህ አል ሴኑሲ ጨምሮ ሌሎች ስምንት ሊቢያውያንም በተመሳሳይ ክስ የሞት ፍርድ እንደተፈረደባቸው ዘገባው አስታውቋል፡፡
ከለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ፒኤችዲውን የተቀበለው ሳይፍ ጋዳፊ፤ በአሁኑ ወቅት በዚናታን ከተማ ውስጥ በሚገኝና ለትሪፖሊ መንግስት አሳልፌ አልሰጠውም ብሎ በተቃወመ ወታደር ቤት ውስጥ እንደሚገኝ ዘገባው አስታውሷል፡፡

  የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሙስና ቅሌት እየታመሰ የሚገኘውን አለማቀፉን የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፊፋ ለረጅም አመታት በፕሬዚዳንት የመሩት ሴፕ ብላተር፣ የዓለም የኖቤል ሽልማት ሊሰጣቸው የሚገባ ታላቅ ሰው ናቸው ሲሉ መናገራቸውን ዘሂንዱ ታይምስ ዘገበ፡፡
ፕሬዚዳንት ፑቲን ባለፈው ሰኞ ከስዊዝ ቲቪ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ሃሜት የበዛባቸው የፊፋው ፕሬዚዳንት ሴፕ ብላተር ለአለማችን እግር ኳስ ባበረከቱት አስተዋጽኦ የኖቤል ሽልማት ሊሰጣቸው የሚገባ ታላቅ ሰው ናቸው ብለዋል፡፡  እንደ ብላተር ያሉ ትጉሃን ሰዎች፣ የተሰጣቸውን ሃላፊነት በአግባቡ በመወጣት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ልዩ እውቅና ሊሰጣቸው ይገባል ሲሉም አክለዋል ፕሬዚዳንት ፑቲን፡፡ ብላተር በበኩላቸው፤ የፑቲን ንግግር እንዳስደሰታቸውና ስሜታቸውን እንዳነቃቃው ገልጸው፣ ለፑቲን ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ፑቲንና ብላተር የ2018 የአለም የእግር ኳስ ዋንጫን አዘጋጅ አገር ለመምረጥ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በሩስያ ሴንት ፒተርስበርግ በሚገኘው ኮንስታንቲን ቤተ-መንግስት በተደረገው የመጀመሪያ ዙር እጣ አወጣጥ ስነ-ስርአት ላይ ተገናኝተው እርስ በርስ መወዳደሳቸውን ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

 - ከፌስቡክ ደንበኞች 65 በመቶው በየዕለቱ ይጠቀማሉ
            - ባለፉት ሶስት ወራት ገቢው 4 ቢሊዮን ደርሷል
   ኢንተርኔትን ከሚጠቀሙ 3 ቢሊዮን ያህል የተለያዩ የአለማችን አገራት ዜጎች መካከል ግማሽ ያህሉ ወይም 1.49 ቢሊዮን የሚሆኑት የታዋቂው ማህበራዊ ድረገጽ ፌስቡክ ተጠቃሚ መሆናቸውን ኩባንያው ረቡዕ እለት ማስታወቁን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
የተጠቃሚዎቼ ቁጥር ባለፉት ሶስት ወራት በ13 በመቶ አድጓል ያለው ፌስቡክ፣ ከተጠቃሚዎቹ ውስጥ 65 በመቶ የሚሆኑትም በየዕለቱ አካውንታቸውን ከፍተው የሚጠቀሙ ትጉህ ደንበኞቹ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
የስማርት ፎን ተጠቃሚዎች በየአምስት ደቂቃው ለአንድ ደቂቃ ያህል ጊዚያቸውን ከፌስቡክ ጋር ያጠፋሉ ያለው ፌስቡክ፣ የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት መስፋፋት ለማህበራዊ ድረገጹ ተጠቃሚዎች ቁጥር ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ አስታውቋል፡፡
በስማርት ፎን ተጠቃሚዎች በኩል የሚያገኘው የማስታወቂያ ሽያጭ ገቢ ጠቀም ያለ እንደሆነ የገለጸው ፌስቡክ፣ ገቢው ባለፉት ሶስት ወራት በ39 በመቶ በማደግ 4 ቢሊዮን ዶላር መድረሱንና ከዚህ ውስጥም 2.9 ቢሊዮን የሚሆነውን ከስማርት ፎን ማስታወቂያ እንዳገኘው ጠቁሟል፡፡

Saturday, 01 August 2015 14:48

የየአገሩ ምሳሌያዊ አባባል

የሴት ውበት የክረምት ሌሊትን አያሞቅም።
የዩክሬናውያን አባባል
ውሻ ጭራውን ካልረገጥከው በስተቀር አይነክስህም፡፡
የካሜሩያውያን አባባል
ጓንት ያጠለቀች ድመት አይጥ አትይዝም፡፡
የፈረንሳውያን አባባል
የተውሶ ድመት አይጥ አትይዝም፡፡
የጃፓናውያን አባባል
ትኩረት የሚስቡ ሴቶች ከኋላህ እንዲጓዙ አትፍቀድ፡፡
የካምቦዲያውያን አባባል
ከነገ ጫጩት የዛሬ እንቁላል ይሻላል፡፡
የቬትናማውያን አባባል
ዘማሪ ወፍ መዝሙር እየበላች አትኖርም፡፡
የሩሲያውያን አባባል
አሪፍ ውሻ ተሳስቶ አይጮህም፡፡
የፈረንሳውያን አባባል
ማለፊያ የወይን ጠጅ የያዘ ፋሽኮ ቡሽ አይፈልግም፡፡
የፈረንሳውያን አባባል
ቀበሮ በተመሳሳይ ወጥመድ ሁለቴ አይያዝም፡፡
የላቲን አባባል
 ሞኝ በራሱ ይስቃል፡፡
የናሚቢያውያን አባባል
እግዚአብሔር በሳቅ እንዲፈርስ ከፈለግህ ዕቅድህን ንገረው፡፡
የናሚቢያውያን አባባል
ህፃን፤ እግሮቹ በጨመሩ ቁጥር ክንፎቹ የሚቀንሱ መላዕክ ነው፡፡
የፈረንሳውያን አባባል
አፍህ ቢላዋ ከሆነ ከንፈርህን ይቆርጠዋል፡፡
የአፍሪካውያን አባባል
እግዚአብሔር አንድን አገር መቅጣት ሲፈልግ፣ መሪዎቹን ጥበብ ይነፍጋቸዋል፡፡
የጣልያኖች አባባል

 አሜሪካ በመላው አለም የሚገኙ ዜጎቿ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ አይሲስን የመሳሰሉ አሸባሪ ቡድኖች ከሚሰነዝሯቸው የሽብር ጥቃቶች ራሳቸውን እንዲጠብቁ ማስጠንቀቋን ዘ ሂንዱ ታይምስ ዘገበ፡፡
አሜሪካ በኢራቅ በሚገኘው አይሲስ ላይ ጥቃት መሰንዘሯን ተከትሎ፣ ቡድኑ የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጥ ማሳወቁን ያስታወሰው ዘገባው፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ቡድኑ በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮፓና በእስያ አገራት በሚኖሩ አሜሪካውያንም ሆነ በምዕራባውያን አገራት ዜጎች ላይ የሽብር ጥቃት ሊሰነዝር ስለሚችል ተገቢው ጥንቃቄ እንዲደረግ ማሳሰቡን ጠቁሟል፡፡
ከአይሲስ በተጨማሪ በህንድ የሚንቀሳቀሱት ሌቲን የመሳሰሉ የሽብር ቡድኖች ከሰሞኑ በአገሪቱ ጥቃት ሊሰነዝሩ ይችላሉ ያለው የአሜሪካ መንግስት ማስጠንቀቂያ፣ በህንድ የሚኖሩ አሜሪካውያንም ራሳቸውን ከጥቃት እንዲጠብቁ አሳስቧል፡፡
በምዕራባውያን አገራት ላይ የከፋ ጥላቻ ያላቸው ሃረካት ኡል ጂሃዲ ኢስላሚ እና ሃረካት ኡል ሙጅሃዲንን የመሳሰሉ እስላማዊ አክራሪ ቡድኖች በህንድ በስፋት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ጠቁሞም፣ቡድኖቹ ከዚህ ቀደምም በምዕራባውያን አገራት ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ የሽብር ጥቃቶችን ሲፈጽሙና በርካቶችን ለህልፈተ ህይወት ሲዳርጉ እንደነበር አስታውሷል፡፡
አሸባሪ ቡድኖች በደቡብ እስያ አገራት የሽብር ጥቃት ሊፈጽሙ እንደሚችሉ የሚያመለክቱ መረጃዎች ደርሰውኛል ያለው የአሜሪካ መንግስት፣ ጥቃቶቹ በአሜሪካውያንና በተቋማቷ ላይ ያነጣጠሩ ሊሆኑ እንደሚችሉም ጠቁሟል፡፡

Saturday, 01 August 2015 14:47

የኪነጥበብ ጥግ

ስለ ኪነ - ህንፃ)
እኛ ህንፃዎቻችንን እንቀርፃለን፤ ከዚያም እነሱ እኛን ይቀርፁናል፡፡
ዊንስተን ቸርችል
ማናቸውም የገነባቸውና ጥሩ ነገሮች የማታ ማታ እኛን ይገነቡናል፡፡
ጂም ሮህን
ከተሞች የሰው ልጅ ድንቅ ፈጠራዎች ናቸው፡፡
ዳንኤል ሊቤስኪንድ
በአሜሪካ የቪክቶሪያን ኪነ - ህንፃ በቀጥታ የተቀዳው ከእንግሊዝ ነበር፡፡
ስቲፈን ጋርዲነር
ሎስ አንጀለስ ውስጥ 35 ዓመት ሲሞላችሁ፣ አብዛኞቹን ህንፃዎች በዕድሜ ትበልጧቸዋላችሁ፡
ዴልያ ኢፍሮን
ስለ ሙዚቃ ማውራት ስለ ኪነ-ህንፃ እንደ መደነስ ነው፡፡
ሉዊስ ካህን
ኪነ-ህንፃ ግግር ሙዚቃ ከሆነ፣ ሙዚቃ ፈሳሽ ኪነህንፃ መሆን አለበት፡፡
ኪውንሲ ጆንስ
ኪነ-ህንፃ ዘላለማዊነት ላይ ያለመ ነው፡፡
ክሪስቶፈር ሬን
ሙዚቃን እንደ ፈሳሽ ኪነ ህንፃ እቆጥረዋለሁ።
ጆኒ ሚሼል
ኪነ ህንፃ ጥበብ እንጂ ሌላ ምንም አይደለም።
ፊሊፕ ጆንሰን
ጥሩ ነገር መስራት ቀላል አይደለም፤ ነገር ግን መጥፎ ነገር መስራት እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡
ቻርለስ ኧርነስ
ምንጊዜም ክብ ስሰራ፣ ወዲያውኑ ከዚያ ውስጥ መውጣት እፈልጋለሁ፡፡
አር. ቡክሚኒስተር ፉለር
ቤት የመኖሪያ ማሽን ነው፡፡
ሊ ኮርቡስየር
ልክ እንደ መድሃኒት (ኪነህንፃ) ከማዳን ወደ መከላከል መሻገር አለበት፡፡
ሴድሪክ ፕራይስ
እያንዳንዱ ህንፃ ልክ እንደ ሰው ነው፡፡ ብቸኛና የማይደገም፡፡
አየን ራንድ (ዘ ፋውንቴይንሄድ)

Saturday, 01 August 2015 14:44

የንባብ - አደባባይ!

    ቴክኖሎጂ ሲቀብጥ ትውልድም መልኩን ለቅቆ፣ ጨርቁን ጥሎ እንዳያብድ፣ በትይዩ ቦይ እንዳንለቀው፣ የሚተልምልን መሪ፤ መረን እንዳይወጣ የሚገታ የፍቅር ልጓም ያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ ዕውቀትን በቅጡና በወጉ ለመጠቀም፣ በሥርዐት ለህይወት ጉልበት መስጫ ለማድረግ መማር አንዱ መንገድ ቢሆንም ቅርፅ ለመስጠት፣ ውበት ለማምጣት ደግሞ ንባብ ሻካራችንን እያለሰለሰ፣ ለማህበረሰቡ ምቹ እንደሚያደርገን ይታመናል፡፡  
ከሀገር ውጭም ሆነ በሀገራችን ውስጥ አያሌዎች እሳት የላሱ ጠቢባን ይሆኑ ዘንድ አእምሮዋቸውን ገርቶ፣ ላባቸውን አቅንቶ፣ዘመን የማያቆመው ድምቀት የሰጣቸው ንባብ እንደሆነ ደጋግመን ያወሳነው ጉዳይ ነው፡፡
በእኛም ሀገር የንባብ ባህል እንዲያድግና እንዲጎለብት የተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማት ታላቅ ተጋድሎ አድርገዋል፡፡ ለዚህም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የሀዋሳና የዲላ ዩኒቨርሲቲ በየራሳቸው ያደረጉትን ጥረት ልንዘነጋው የምንችል አይመስለኝም፡፡ ይበልጥ የሚመለከተው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበርም ከነዚሁ ጎራ የሚመደብ ነው፡፡ በግለሰብ ደረጃ ደግሞ ደራሲ ዳንኤል ወርቁ “አዲስ አበባ ታንብብ”ን በመሳሰሉ ፕሮግራሞቹ የተቻለውን ያህል ተግቷል፡፡  በጥቅሉ ሲታይ በሀገራችን የንባብ ባህልን ለማበረታታት የሚደረገው ጥረት በእጅጉ እየበረታና እየደመቀ የመጣ ይመስላል፡፡ ሌላው ቀርቶ በቅርቡ ብቻ የተካሄዱትን የመጻህፍት አውደ ርዕዮች ስናይ ጉዳዩ ምን ያህል የልብ ትርታ እየሆነ መምጣቱን የሚያሳይ ነው፡፡
በተለይ ለዛሬ ጽሁፌ መነሻ የሆነኝ፣በማስተር ፊልምና ኮሙኒኬሽን አዘጋጅነት ከትላንት በስቲያ የተጀመረውና እስከ ነገ (»ሐምሌ 23-26 2007 ዓ.ም) የሚቆየው “ንባብ ለህይወት” የመፃህፍት አውደ-ርዕይ፤በዓይነቱና በይዘቱ ግዙፍና ታላቅ ነው፡፡ ምናልባትም ከዚህ ቀደም ከለመድናቸው የሚለዩ በርካታ አላባዎችን አጭቆ የያዘ ዝግጅት ነው፡፡ ከነዚህም ውስጥ አንዱና ዋነኛ ጠባዩ፣  አውደ ርዕዩ በየዓመቱ በቀጣይነት የሚካሄድ መሆኑ ነው። ከዚህም ሌላ በየክልሉ እንዲላመድ በማድረግ ሀዲዱን ቆንጥጦ ይቀጥላል፡፡
ብዙ ጊዜ ስለ ንባብ ስናወራ፣ ስለ ንባብ ስንሰብክ፣ በእዝነ ህሊናችን የሚመጡት ፊታቸው በጢም የተሞላ፣ ምናልባት ሽበት ጣል ጣል ያደረገባቸው አዛውንትና ጎልማሶች ናቸው፡፡ ንባብ ለህይወት ዓይኖቹን ወደ ችግኞቹም ላይ ጥሏል። ሕፃናት ከሥር ጀምረው እንዲኮተኮቱ፣ እኩይ መልኮችን እንዲዘልሉ ከአሁኑኑ ክትባት ያገኙ ዘንድ ለእነርሱም በቂ ዝግጅት አድርጓል፡፡ የሚመጥኗቸው መፃህፍት፣ የሚያጫውቷቸው አሻንጉሊቶችም ተዘጋጅተዋል፡፡
በዚህ አውደ ርዕይ፣120 ያህል የመፃህፍት አሳታሚዎችና የትምህርት ተቋማት በአንድ ዓላማና ድንኳን ስር ይተሳሰራሉ፡፡ እውነት ለመናገር የትምህርት ተቋማት ተሰባስበው በአንድ ሰፈር መች ተገኝተው ያውቃሉ! … ይኸው አሁን በንባብ ለህይወት ችቦዋቸውን እየለኮሱ ደመራውን ሊያደምቁት ታድመዋል፡፡
በንባብ ለህይወት፣ መጻሕፍት ቢያንስ በ10 በመቶ የዋጋ ቅናሽ ለገበያ የሚቀርቡ ሲሆን ቅናሹ  እስከ 50 በመቶ ሊዘልቅ እንደሚችል አዘጋጆቹ ይገልጻሉ፡፡ ስለዚህ መጻሕፍት ለመሸመትም ጥሩ አጋጣሚ ይሆናል ማለት ነው፡፡ የዘመኑ ቴክኖሎጂ በፈጠረው ዕድል ጎብኚዎች ከ100,000 ሺህ በላይ በመረጡት ርዕሰ ጉዳይ ላይ የተፃፉ መፃህፍትን ሶፍት ኮፒ በነፃ ያገኛሉ ተብሏል፡፡  
በዚህ ዐውደ-ርዕይ ባልተለመደ መልኩ አዳዲስ መጻህፍት ቬሎዋቸውን ለብሰው ብቅ እንደሚሉም ታውቋል፡፡ ከአዘጋጆቹ በተገኘው መረጃ መሰረት፤12 አዳዲስ መፃህፍት እዚያው ተመርቀው፣የደራስያኑ ፊርማ አርፎባቸው፣በትኩሱ ወደ ተደራሲያን እጅ ይገባሉ፡፡
ሌሎቹ ሁለት ታላላቅ የበዓሉ ድምቀቶችም እንደዚሁ ያልተለመዱ ናቸው፡፡ ከነዚህ አንዱ በየሙያ ዘርፉ “አንቱ” የተባሉና በአንባቢነታቸው የተመሰከረላቸው ሰዎች  የንባብ አምባሳደር ተብለው ዕውቅና የሚያገኙበት ሲሆን በቀጣዩ ጊዜ በየትምህርት ቤቱና በሌሎች ክበባት በመገኘት አንብበው የሚያስነብቡበት የኃላፊነት ሹመት ነው። ይህ ደግሞ ዓመቱን ሙሉ ለሚካሄደው የንባብ ልምድ ማበልፀጊያ ጉዞ ትልቁን ድርሻ ሊጫወት እንደሚችል እሙን ነው፡፡  ታዲያ ይህ ሁሉ ዘመቻ፣ ዕውቀትን ጓዳችን ለማስገባት፣ እንደ ሰው አውቀን፣ እንደ ሰው አስበንና የተሻለውን መርጠን እንድንኖር ነው። ማወቅን ካለማወቅ የሚለየው አንዱ፣ ህይወትን የምናጣጥምበትን ምላስ መንጠቁ ሲሆን ሌላኛው ህይወትን የምናጣጥምበትን አቅም መስጠቱ ነወ፡፡ ይህንንም እንድናውቅ የሚያደርገን በልብ አይኖቻችን ላይ የተጋረደው መጋረጃ መነሳቱ ነው፡፡ ይህ አውደርይ የማንበብ ጥቅምንና ወደዚህ የጥቅም እልፍኝ የምንገባበትን መንገድ ለመጥረግ ያዘጋጀው ሌላም ነገር አለ፡፡ በአንድ ወገን የተወዳጅ ደራስያንን ወግ እያነበቡ በማዝናናት፣ በሌላ ወገን ደግሞ የንባብን ጥቅምና ፋይዳ ወደ ኋላ እየፈተሹ፣ ታሪክ በማጣቀስ መወያየትም አለ፡፡
 ሙዚቃ የነፍስ ጥበብ ናት! … በጥበብ እልፍኝ ውስጥ ሽር ብትን እያለች የዓውደ ርዕዩን እልፍኝ ታድምቀው በሚል ጥንታዊውን የሙዚቃ ዓለም በቀደመው ዘመን ከያንያን ዜማ - ታንቆረቁረዋለች ይላሉ - የንባብ ለህይወት አዘጋጆች፡፡ ታዲያ ይህ ቀን አይናፍቅም? … ንባቡስ አይርብም? … የነፍሳችን ከንፈር እስኪላጥ እያፏጨን ብንጠራውስ? … እልልል!