Administrator

Administrator

 ኤርትራ ዝቅተኛ የኢንተርኔት ተጠቃሚ በመሆን አለምን ትመራለች
   በኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ የሆነው ከአጠቃላዩ ህዝብ 1.7 በመቶ የሚሆነው ብቻ ነው መባሉን የአሜሪካው የቢዝነስ መጽሄት ፎርቹን ዘገበ፡፡ኢንተርኔት ላይቭ ስታትስ የተባለው አለማቀፍ ተቋም ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ እጅግ ዝቅተኛ የኢንተርኔት አገልግሎት አቅርቦት ካላቸው አስር የአለማችን አገራት መካከል ስምንቱ በአፍሪካ አህጉር እንደሚገኙና ኢትዮጵያም አንዷ እንደሆነች በጥናት ተረጋግጧል፡፡በኢንተርኔት አገልግሎት አቅርቦት ዝቅተኛነት ከአለማችን ቀዳሚውን ስፍራ የምትይዘው ኤርትራ መሆኗን የጠቆመው ዘገባው፣ ከአገሪቱ ህዝብ የአገልግሎት ተጠቃሚ የሆነው 0.91 በመቶ ብቻ መሆኑን ገልጧል፡፡ከአውስትራሊያ በስተሰሜን የምትገኘው ቲሞር ሌሴቴ ደሴት በ1 በመቶ፣ ማይንማር በ1.16 በመቶ፣ ብሩንዲ በ1.39 በመቶ እንዲሁም ሴራሊዮን በ1.49 በመቶ በኢንተርኔት አቅርቦት ዝቅተኛነት እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል ተብሏል፡፡  ሶማሊያ በ1.51 በመቶ፣ ኒጀር በ1.61 በመቶ፣ ኢትዮጵያና ጊኒ በ1.7 በመቶ እንዲሁም ኮንጎ በ1.92 በመቶ እንደሚከተሉም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

ኢትዮጵያ አምና ወደዚያው ከላከችው ስጋ 58.8 ሚ ዶላር አግኝታለች
     የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የኢትዮጵያ የስጋ ምርት ወደ ግዛቷ እንዳይገባ ከአንድ ሳምንት በፊት ጥላው የነበረችውን ማዕቀብ ማንሳቷን ተርኪሽ ዊክሊ ድረገጽ ትናንት ዘገበ፡፡
ከሳምንት በፊት ከኢትዮጵያ ሰባት ስጋ ላኪ ኩባንያዎች ወደ አገሪቱ ከገባው 36 ቶን የበግ ስጋ ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ አገሪቱ የኢትዮጵያ የስጋ ምርት ወደ ግዛቷ እንዳይገባ ገደብ ጥላ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ ከሚመለከታቸው የኢትዮጵያ መንግስት አካላት ጋር በመነጋገር ችግሩን መፍታት መቻሉን ገልጧል፡፡
ይህን ተከትሎም የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የኢትዮጵያ የስጋ ምርት ወደ ግዛቷ እንዳይገባ የጣለችውን ማዕቀብ ማንሳቷንና አገሪቱ ያሳለፈችው ውሳኔ በዘርፉ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያንን እንዳስደሰተ ዘገባው አስረድቷል፡፡
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የኢትዮጵያን የስጋ ምርት በስፋት በመግዛት ቀዳሚዋ አገር እንደሆነችና ኢትዮጵያ ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከምትልከው የምግብ ኤክስፖርት ምርት በአመት በአማካይ 30 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደምታገኝም ገልጧል፡፡
ኢትዮጵያ ባለፈው አመት ወደ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከላከችው 11.692 ቶን የስጋ ምርት 58.8 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷንም ዘገባው አክሎ አስታውሷል፡፡

  •         የገቢ አሰባሰቡ የአስተዳደር ጉባኤ አባላቱን አወቃቅሷል
  •         ከዕድሳት ዕጦት የሕንጻው ደኅንነት አደጋ ላይ ወድቋል

   በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት፣ ለተለያዩ አገልግሎቶች ከአከራያቸው የሕንጻው ክፍሎች ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የኪራይ ክፍያ አለመሰብሰቡ ተገለጸ፤ ተከራዮች ውዝፍ ዕዳቸውን ከነመቀጫው አጠናቀው እንዲከፍሉ ጽ/ቤቱ አስጠነቀቀ፡፡
የሀገረ ስብከቱን ሕንጻ ለቢሮ፣ ለሕክምና እና ለሱቅ አገልግሎቶች ከተከራዩ ስድስት ተከራዮች ያልተሰበሰበው አጠቃላይ ክፍያ ብር 675 ሺሕ 244 ከ31 ሳንቲም ያህል እንደኾነ ጽ/ቤቱ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ከጻፈው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ማስጠንቀቂያው ከደረሳቸው  መካከል፣ ከሰኔ ወር 2005 ዓ.ም. ወዲህ ኪራያቸውን ሳይከፍሉ የቆዩና እስከ 360 ሺሕ ብር ከፍተኛ ውዝፍ ያለባቸው ተከራዮች እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡ተከራዮች ደብዳቤው በደረሳቸው በሦስት ቀናት ውስጥ ውዝፍ ዕዳቸውን ከነመቀጫው ከፍለው ለጽ/ቤቱ ካላሳወቁ፣ ቢሮዎቻቸውና ሱቆቻቸው እንደሚታሸጉ የተሰጠው ማስጠንቀቂያም የሚገባውን ያህል ተግባራዊ ሳይሆን ከወር በላይ ማስቆጠሩ ተገልጧል፡፡
ኪራዩ በወቅቱ ቢሰበሰብ፣ ገንዘቡ በወቅቱ የነበረውን ዋጋ ያህል ቤተ ክርስቲያኒቱን ተጠቃሚ ያደርግ እንደነበር የሚገልጹ የሀገረ ስብከቱ ምንጮች፣ የፋይናንስና በጀት ዋና ክፍሉን ቀዳሚ ተጠያቂ አድርገዋል፡፡
ዋና ክፍሉ ከኪራዩ የሚሰበሰበውንና የቀረውን ገቢ በየጊዜው ለአስተዳደር ጉባኤው በሪፖርት በማሳወቅ፣ ክፍያው እንዳይወዘፍ ማድረግ የሚገባው ቢሆንም አለማቅረቡ ድክመቱን እንደሚያሳይ ምንጮቹ አስረድተዋል፡፡
በከፍተኛ የክፍያ ዕዳ ከሚታወቁ ተከራዮች መካከል ከአንዳንድ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ግንኙነት ያላቸው እንደሚገኙበት ምንጮቹ ጠቁመው፤ አጀንዳው በአስተዳደር ጉባኤው ስብሰባ ላይ ቀርቦ በታየበት ወቅትም “የገቢ አሰባሰቡ በዝምድና የተሸፋፈነ ነው” በሚል ሓላፊዎቹን እርስ በርስ አወቃቅሶ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በ2001 ዓ.ም. በወቅቱ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል አስተዳደር፣ በከፍተኛ ወጪ ተሠርቶና በቀድሞው ፓትርያርክ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ሕንጻ፣ ባለቤት አልባ እስኪሰኝ ድረስ እያፈሰሰ እንደሚገኝና አስቸኳይ ዕድሳት ካልተደረገለትም ደኅንነቱን አስጊ እንደሚያደርገው ምንጮቹ ይገልጻሉ::

 የታሪክ ፀሐፊ ጋዜጠኛና ዲፕሎማቱ አምባሳደር ዘውዴ ረታ ባለፈው ረቡዕ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ አምባሳደር ዘውዴ ረታ በተለይ “የኤርትራ ጉዳይ”፣ “የተፈሪ መኮንን ረጅም የስልጣን ጉዞ” እና “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት” የሚሉ የታሪክ መፅሃፍትን ፅፈዋል፡፡
በአዲስ አበባ ኦርማ ጋራዥ አካባቢ ነሐሴ 7 ቀን 1927 ዓ.ም የተወለዱት አምባሳደር ዘውዴ፤ እንግሊዝ ሎንደን ከተማ ዕረፍት ላይ እንዳሉ በድንገት በገጠማቸው ህመም ህይወታቸው ማለፉ ታውቋል፡፡አምባሳደር ዘውዴ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በሬድዮ በቤተ መንግሥት ዜና አቅራቢነት የሰሩ ሲሆን፣ በቱኒዚያና በሌሎች ሀገሮች በአምባሳደርነትና በሌሎች የመንግሥት ኃላፊነቶች ላይም ሰርተዋል፡፡አምባሳደር ዘውዴ ረታ በቅርቡ በኤግዚቢሽን ማዕከል በተዘጋጀው “ንባብ ለህይወት” የመፅሃፍ አውደ ርዕይና ሸያጭ ላይ “የአመቱ የንባብ ለህይወት” የወርቅ ብዕር ተሸላሚ የነበሩ ሲሆን “የ2006 የበጐ ሰው” ተሸላሚም ነበሩ፡፡

  ፊልሞች ደህንነታቸው ተጠብቆ ለተመልካች ለማድረስ የሚያስችልና የፊልም ስርቆቶችን ያስቀራል የተባለ አዲስ ቴክኖሎጂ ስራ ላይ ዋለ፡፡
አቢስውድ በተባለ ድርጅት ስራ ላይ የዋለው  አዲስ ቴክኖሎጂ፤ ፊልሞች በአንድ ጊዜ ከአንድ የማሰራጫ ስፍራ ወደተለያዩ ሲኒማ ቤቶች እንዲሰራጩ የሚያደርግና የፊልሙን ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ የሚጠብቅ ነው፡፡
 ድርጅቱ በፊልሞች ላይ የራሱን የይለፍ ኮድ በማድረግ ፊልሞች ያለ ባለቤቱ ፈቃድ እንዳይታዩ ቴክኖሎጂው ይከላከላል ተብሏል፡፡ድርጅቱ ከፊልም ስራዎች ተቀብሎ በየሲኒማ ቤቱ እንዲታዩ ለሚያደርጋቸው ሲኒማዎች ሁሉ ዋስትና የሚሰጥ ሲሆን ፊልሞቹ በምንም መንገድ ያለባለቤቱ ፈቃድ ለተመልካች ቢደርሱ ተጠያቂ የሚሆንበትን አሰራር ተግባራዊ የሚያደርግ ነው፡፡
 ድርጅቱ ፊልሞች በክልል ከተሞችም በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት እንዲታዩ ለማድረግ የሚችል ሲሆን በቀጣይ ከአገር ውጭ ፊልሞች የሚታዩበትን አሰራር ተግባራዊ ለማድረግ እቅድ እንዳለው ተገልጿል፡፡

 “መርካቶ ሰፈሬ” በሚለው የመጀመሪያ አልበሙ ተወዳጅነትን ያተረፈው ድምፃዊው አብዱ ኪያር፤ “ጥቁር አንበሳ” በሚል ስያሜ አራትኛ አልበሙን ሰሞኑን ለአድማጭ አድርሷል፡፡ የአልበሙን መጠሪያ ጨምሮ 11 ዘፈኖች የተካተቱበት የሙዚቃ አልበሙ፤ በአሸብር ማሞ የተቀናበረ ሲሆን ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው ዜማ ስቱዲዮ ውስጥ እንደታተመ በአልበሙ ሽፋን ላይ ተገልጿል፡፡ በግጥምና በዜማ ድምፃዊውን ጨምሮ በርካታ ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን ታዋቂው ሙዚቀኛ ፈለቀ ሀይሉ በሳክስፎን አጅቦታል፡፡ ዘፈኖቹ በፍቅር፣ በአንድነት፣ በትውስታና ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚያጠነጥኑም ለማወቅ ተችሏል፡፡

 ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ ከኢትዮጵስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር፣ ነገ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ በብሔራዊ ቤተ መፃሕፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ በ “አንቀፅ 39” መጽሐፍ ላይ ውይይት እንደሚያካሂድ ገለፀ፡፡ የመጽሐፉ ደራሲ አቶ ውብሸት ሙላት፤ ለውይይቱ መነሻ ሃሳብ እንደሚያቀርቡ የጠቆመው ሚዩዚክ ሜይዴይ፤ የመጽሐፍት አፍቃሪያን በውይይቱ ላይ እንዲታደሙ ጋብዟል፡፡

በወጣት ቴዎድሮስ አበራ የተደረሰው “ሀገርህን ጥላት ልጄ እና ሌሎች ልቦለዳዊ ትረካዎች” ሰሞኑን ለንባብ በቅቷል፡፡ መጽሐፉ አራት ታሪካዊ ልቦለዶችን ያካተተ ሲሆን በሃገርና ፖለቲካ እንዲሁም ባለፈውና በመጪው ትውልድ ዙሪያ ይሞግታል ተብሏል፡፡ በ214 ገፆች የተመጠነው መጽሐፉ፤ በ50 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

Saturday, 03 October 2015 10:39

የኪነት ጥግ

  (ስለ አርትኦት)
ህይወቴ አርትኦት (editing) ይፈልጋል፡፡
ምርት ሳህል
አርትኦት ያስጠላኛል፡፡ መፃፍ ደስ ይለኛል፤ ፅሁፌን መላልሶ ማንበብ፣ መከለስ ግን አልወድም፡፡
ባሪ ሃናህ
አርትኦት እወዳለሁ፡፡ ከፊልም ስራ የምወደው አንዱ  ክፍል ነው፡፡
ስቲቨን ስፒልበርግ
አርትኦት ለብቻ የሚሰሩት ዓይነት ሥራ ነው፡፡
ጆ ዳንቴ
ከምፅፋቸው እያንዳንዱ አራት ቃላት ውስጥ ሦስቱን እሰርዛለሁ፡፡
ኒኮላስ ቦይሉዩ
መሰረዝ መደለዝ የፈጠራ ምልክት ነው፡፡
ሜላኒ ሰርክል
የሚሰርዝ እጅ ብቻ ነው እውነተኛውን ነገር መፃፍ የሚችለው፡፡
ሜይስተር ጆሃን ኢክሃርት
ማንም ደራሲ ያለመታተምን የሚጠላውን ያህል አርትኦትን አይጠላም፡፡
ጄ.ራስል ላይንስ
ሌሎች በአንድ ሙሉ መፅሐፍ ያሉትን ነገር በአስር ዓ.ነገሮች መግለፅ ምኞቴ ነው፡፡
ፍሬድሪክ ኒቼ
ይሄን ደብዳቤ ያስረዘምኩት ለማሳጠር ጊዜ ስላልነበረኝ ነው፡፡
ብሌይዝ ፓስካል
ብዙ ድግግሞሽ፣ መላልሶ በማንበብና በአርትኦት ሊወገድ ይችላል፡፡
ዊሊያም ሳፋየር
ተገቢ ያልሆኑ ቃላትን አስወግድ፡፡
ዊሊያም ስትራንክ ጄአር
ባዶ ገፅን ልትከልሰው አትችልም፡፡
ሊኦናርድ ዎልፍ
በኪነጥበብ ቁጥብነት ሁልጊዜ ውበት ነው፡፡

Saturday, 03 October 2015 10:38

የዝነኞች ጥግ

ሌላውን መምሰል የለባችሁም፤ ማንነታችሁን ውደዱት፡፡
ሊ ሚሼል
ገንዘብ ማሳደዱን ትታችሁ፣ ከልባችሁ የምትወዱትን ነገር ማሳደድ ጀምሩ፡፡
Tony hsieh
ግብ፤ ቀነ-ገደብ የተቀመጠለት ህልም ነው፡፡
ናፖሊዮን ሂል
ሥራችሁን ለማሻሻል ከፈለጋችሁ የማይቻለውን ለመስራት ሞክሩ፡፡
ብሪያን ትሬሲ
መሞከራችሁን እስክታቆሙ ድረስ ተሸናፊዎች አይደላችሁም፡፡
ማይክ ዲትካ
እንደ ቢራቢሮ ተንሳፈፉ፤ እንደ ንብ ተናደፉ፡፡
ሙሃመድ አሊ
የምንቀጥረው በዓለም ላይ ምርጥ ነገሮችን ለመስራት የሚፈልጉ ሰዎችን ነው፡፡
ስቲቭ ጆብስ
ማለም ከቻላችሁ መስራት አያቅታችሁም፡፡
ዋልት ዲዝኒ
ተመሳሳይ ስኬቶችን መድገም አልወድም፤ ወደ ሌሎች ነገሮች ደግሞ መሻገር እሻለሁ፡፡
ዋልት ዲዝኒ
አመለካከት፤ ትልቅ ልዩነት የሚፈጥር ትንሽ ነገር ነው፡፡
ዊንስተን ቸርችል
እግራችሁን በትክክለኛው ቦታ ማኖራችሁን አረጋግጡ፤ ከዚያ ሳትበገሩ ቁሙ፡፡
አብርሃም ሊንከን
በሌላው ሰው ደመና ላይ ቀስተደመና ለመሆን ጣሩ፡፡
ማያ አንጄሎ