Administrator

Administrator

   የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ አገሪቱን ከሰርጎ ገቦች ጥቃት ለመከላከል የሚያስችልና ሁሉንም የአገሪቱ ድንበር የሚከልል አጥር የማሰራት እቅድ እንዳላቸው ማስታወቃቸውን ዘ ጋርዲያን ዘገበ፡፡ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ከፍልስጤምና በእስራኤል ዙሪያ ከሚገኙ የአረብ አገራት ድንበር ጥሰው የሚገቡ ሰርጎ ገቦችን የመከላከል አላማ ያነገበ ነው ያሉትን ይህን ድንበርን የማጠር እቅድ ይፋ ያደረጉ ሲሆን፣ አጥሩ ከዚህ በተጨማሪም ከጋዛ ወደ አገሪቱ የሚገቡ የሃማስ ታጣቂዎችን ለመከላከል ተግባር ይውላል ተብሏል፡፡
የድንበር አጥር ፕሮጀክቱ አገሪቱን በረጅም አመታት ሂደት ሙሉ ለሙሉ በደህንነት አጥር ለማጠር የተያዘው ሰፊ እቅድ አካል እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በነባር የድንበር አጥሮች አካባቢ የሚታየውን ክፍተት ለመዝጋት እየተሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአጥር ፕሮጀክቱ ለአገሪቱ ደህንነት ወሳኝ ነው ቢሉም፣ የእስራኤል የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባል የሆኑትና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በደህንነት ፖሊሲ ዙሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተደጋጋሚ አለመግባባት እየፈጠሩ ነው የተባሉት የአገሪቱ የትምህርት ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት ግን እቅዱን መቃወማቸው ተነግሯል፡፡

 የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ባለፈው ጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ በርዕሰ መዲናዋ ካይሮ አቅራቢያ የተሰራን የመኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክት መርቀው በከፈቱበት ወቅት የተነጠፈላቸው እጅግ ረጅም ቀይ ምንጣፍ ሰፊ ተቃውሞ እንደገጠመው ዘ ዴይሊ ሜይል ዘገበ፡፡
4 ኪሎ ሜትር እርዝማኔ እንዳለውና 143 ሺህ ፓውንድ እንደሚያወጣ የተነገረለት የፕሬዚዳንቱ የክብር ምንጣፍ፣ በአገሪቱ ጋዜጦችና በማህበራዊ ድረገጾች ከፍተኛ ውግዘት እንደደረሰበት የጠቆመው ዘገባው፣ ባለፈው ሰኞ ለንባብ የበቃው አል ማቃል የተባለ የአገሪቱ ጋዜጣም፣ አብዛኛውን የፊት ገጹን ምንጣፉን በሚተች ዘገባ መሙላቱን ጠቁሟል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከአንድ አመት በፊት ያወጣው ሪፖርት ከሩብ በላይ ግብጻውያን ከድህነት ወለል በታች እንደሚገኙ መግለጹን ያስታወሰው ዘገባው፣ ለፕሬዚዳንቱ የክብር ምንጣፍ ይሄን ያህል ገንዘብ መውጣቱ ብዙዎችን ማሳዘኑንና ትችት ማስተናገዱን አስታውቋል፡፡ የአገሪቱ መንግስት የጦር ሃይል ተወካይ ብርጋዴር ጄኔራል ኢሃብ አል አህዋጊ በበኩላቸው፤ አወዛጋቢው ምንጣፍ በወቅቱ ፕሬዚዳንት የአብዱል ፈታህ አልሲሲ አስተዳደር የተገዛ አለመሆኑን በማስታወስ፣ ምንጣፉ ከሶስት አመታት በላይ ለሚሆን ጊዜ በመሰል ስነስርዓቶች ላይ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ነው ሲሉ ሊያስተባብሉ ሞክረዋል ተብሏል፡፡

Saturday, 13 February 2016 11:59

ሀበሻ ዊክሊ ----- ከየት ወዴት?

ለቴዲ አፍሮ ኮንሰርት ከ3 ሚ. ብር በላይ በጀት ተይዟል

    አዲስ አበባ ነው ተወልዶ ያደገው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በኮከበ ፅባህ፣ የመሰናዶ ትምህርቱን ደግሞ በዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት ተከታትሏል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ ካምፓስ፣ በኮምፒዩተር ሳይንስ በድግሪ ተመርቋል፡፡ በልጅነቱ ነፍሱ ወደ ኪነ-ጥበቡ ታደላ ስለነበር ፊልም ፕሮዱዩስ የማድረግና የመተወን ህልም ነበረው፡፡ ፓይለት ለመሆን ሁለት ጊዜ ጥረት ቢያደርግም በአንድ ሴንቲ ሜትር የቁመት ማነስ ምክንያት ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡
የዩኒቨርስቲ ተማሪ እያለ በተደጋጋሚ ስኮላርሺፕ ሞክሮ አሜሪካና ካናዳ ያሉ ሁለት ዩኒቨርስቲዎች ቢቀበሉትም ኤምባሲዎቹ ቪዛ አልፈቀዱለትም፡፡ በዚህ ተስፋ የቆረጠው የ28 ዓመቱ ወጣት አዶኒክ ወርቁ ፊቱንና ልቡን ሙሉ በሙሉ ወደ አገሩ መልሶ በትጋት መስራት ጀመረ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ከሀበሻ ዊክሊ ፕሮሞሽን መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አዶኒክ ወርቁ ጋር በህይወቱና በቢዝነስ ሥራው፣ በህልሙና ራዕዩ ዙሪያ ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡ ዝነኛው ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ የሚያቀነቅንበት ኮንሰርት በጊዮን ሆቴል እንደሚያዘጋጅም አውግቷታል፡፡ እነሆ፡-  
   
    እንዴት ነው በቀጥታ ወደ ሁነት አዘጋጅነትና ወደ ቢዝነስ ስራ የገባኸው?
እኔ ኤቨንት ኦርጋናይዝ ማድረግ የጀመርኩት በ1997 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ ነው፡፡ ያኔ ስኩል ካርኒቫል በማዘጋጀት እና፣ ዲጄ ሆኜ እሰራ ነበር፡፡ እነዚህ በዋናነትም ባይሆን ፍላጐቶቼ ነበሩ፡፡ ቢዝነስን በተመለከተ አብዛኛው ቤተሰቤ በንግድ ስራ ላይ የተሰማራ ስለነበር ተማሪም ሆኜ ቤተሰቤን በስራ አግዝ ነበር፡፡ ሆኖም ብዙ ወደ ኪነ ጥበቡ ስለማደላ ፊልሞችን እመለከት ነበር፡፡  
ወደ ውጭ አገር የመሄድ ጉጉት እንደነበረህ ሰምቻለሁ -----
ጉጉቴ ውጭ ሄዶ ለመኖር ሳይሆን ለመማርና ቶሎ ለመለወጥ ነበር፡፡ እንደነገርኩሽ ሆሊውድ የሚሰሩ ፊልሞችን በዲሽ ላይ አያለሁ፡፡ እያንዳንዱ ዲሽ ላይ የማየውን ነገር እመኛለሁ፤ያንን ነገር ለማግኘት የግድ እዛው ቦታው መገኘትና መማር አለብኝ ብዬ አስብ ነበር፡፡ በጣም ልቤ ተሰቅሎ ነበር፡፡ ሆኖም ከአንዴም ሁለት ሶስቴ አልተሳካም፤በዚህ ምክንያት ውጭ የመሄዱን ነገር እርግፍ አድርጌ ተውኩት፡፡
ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀህ እንደወጣህ ሥራ የጀመርከው የት ነው?
ከዩኒቨርሲቲ እንደተመረቅሁ ወደ ቤተሰቤ የቢዝነስ ስራዎች ገባሁ፡፡ እንደ ነገርኩሽ ተማሪም ሆኜ ከቤተሰቤ ጋር በትርፍ ሰዓቴ እሰራ ስለነበር ስራውን አውቀዋለሁ፤ስለዚህ ቤተሰቤን እየወከልኩ በተለያዩ የስራ ቦታዎች ላይ ማገዝ ጀመርኩኝ፡፡ ከዚያም ካሉን በርካታ እህት ኩባንያዎች “ሻካይና” በተባለው ውስጥ ማርኬቲንግ ማናጀር ሆኜ መስራት ቀጠልኩ ማለት ነው፡፡
የራስህን ኮምፒዩተር ቤት የከፈትከው መቼ ነው?
በዚያው ዓመት የ“ሻካይና” ማርኬቲንግ ማናጀር ሆኜ እየሰራሁ “አዶኒክ ኮምፒዩተር ሶሉሽን” የተባለ የራሴን ድርጅት ከፈትኩት፡፡ እንደነገርኩሽ በኮምፒዩተር ሳይንስ ነው የተመረቅሁት፡፡ እውቀቱና ክህሎቱ አለኝ፤ስለዚህ እውቀቴን ወደ ቢዝነስ መለወጥና ራሴን ማሳደግ ስለምፈልግ አብረውኝ የተማሩና ደህና ውጤት የነበራቸውን ልጆች አሰባስቤ፣ የራሴንም እውቀት ጨምሬበት ጥሩ ጥሩ ስራዎችን መስራት ጀመርን፡፡ ለምሳሌ ድርጅቱ ገና እንደተከፈተ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤትን ዌብሳይት ዴቨሎፕ አደረግን፡፡ በጣም የሚገርምሽ ብዙ ልምድ ከነበራቸው በርካታ ድርጅቶች ጋር ተወዳድረን፣ የሥራ ልምድ ሳይኖረን የከንቲባውን ጽ/ቤት ዌብሳይት መስራት ለእኔ ትልቅ ስኬት ነበር፡፡
በመቀጠል “አዶኒክ ጆብስ” የተሰኘ ብዙ ወጪ የወጣበት፣ ሥራንና ሥራ ፈላጊዎችን የሚያገናኝ ዌብሳይት ሰራን፡፡ ሥራ ፈላጊዎች ሲቪ ይዘው ገና ማስታወቂያ አንብበው ነው ስራ የሚፈልጉት፡፡ ይህን ድካም የሚቀንስ ነው፤ አዶኒክ ጆብስ ዌብሳይት፡፡ ሆኖም በወቅቱ እንዲህ አይነት ዌብሳይቶች ስላልተለመዱ እንዲታወቁ ለማድረግ ብዙ ጣርን፤ ነገር ግን አለማምደን ገቢ ለማግኘት በጣም ፈታኝ ነበር፡፡ ለአንድ ዓመት በዚህ መልኩ ከሰራሁ በኋላ ፊቴን ወደ ኪነጥበብ ማዞር ፈለግሁኝ፡፡
ኢቢኤስ ላይ ሀበሻ ዊክሊ የተሰኘ የቴሌቪዥን ፕሮግራም እንደነበረህ አስታውሳለሁ፡፡ ለምን ቆመ?
ዌብሳይት የሚሰራው የኮምፒዩተር ድርጅት እንዳለ ሆኖ፣ ወደ አርቱ የመግባት ፍላጎት ቀድሞም ስለነበረኝ አመቺ ሁኔታዎችን እየጠበቅኩኝ ነበር፡፡ ኢቢኤስ መከፈቱ ጥሩ አጋጣሚ ፈጠረልኝና ጥሩ ፕሮፖዛል ሰርቼ አስገባሁ፤ተቀባይነትም አገኘሁ፡፡ ሁሌም የውጭዎቹን የፊልምና የሙዚቃ ቦክስ ኦፊስ ስመለከት፣ ለምን የእኛ አገር ፊልሞችስ ቦክስ ኦፊስ አይኖራቸውም እላለሁ፡፡ በወቅቱ በእኛ አገር ቴሌቪዥንም ሆነ ሬዲዮ በስፋት የሚያወራው ስለ ውጭ ፊልሞች፣ ስለ ውጭ አክተሮች፣ ስለ ውጭ ሙዚቃ ነበር፡፡ ለምን የሀገራችን ዝነኞች (ሰለብሪቲዎች) አይወራላቸውም የሚል ቁጭት ነበረብኝ፡፡ ይህንን ለመስራት ካለኝ ጉጉት ተነስቼ ነው የፕሮግራሙን ስም ራሱ “ሀበሻ ዊክሊ” ብዬ የሰየምኩት፡፡ በፕሮግራሙ ኢትዮጵያ ውስጥ በሳምንት ውስጥ ምን ምን ኪነጥበባዊ ክንውኖች እንደነበሩ የሚጠቁሙ መረጃዎችና መዝናኛዎች ይቀርቡበት ነበር፡፡ አዳዲስ ፊልሞች፣ አዳዲስ ሙዚቃዎች፣ አዳዲስ የአገራችን ሁነቶች፣ በፕሮግራማችን ይስተናገዱ ነበር፡፡ ወቅቱ ደግሞ አሪፍ አሪፍ ፊልሞች መውጣት የጀመሩበት ነበር፡፡ እነ ፔንዱለም፣ ሂሮሺማ፣ አባይ ወይስ ቬጋስ  መውጣት ስለጀመሩ ለፕሮግራማችን ጥሩ ግብአቶች እያገኘን መጣን፡፡
ታዲያ ለምን አቆማችሁት?
እንግዲህ “ሀበሻ ዊክሊ” አቅማችንን የፈተንንበት፣ወደ መዝናኛው ኢንዱስትሪ ይበልጥ የገባንበትና ከብዙ ሰዎች ጋር የተዋወቅንበት ፕሮግራም ነው፡፡ አንደኛ እኛ የመጀመሪያዎቹ አውት ሶርስ አድራጊዎች ነን፤ ሁለተኛ ኢቢኤስ ያን ጊዜ በ2003 ዓ.ም ማለት ነው በደንብ አይታወቅም ነበር፡
እነዚህ ነገሮች ስፖንሰር ለማግኘትም ሆነ ብዙ ነገር ለመስራት ፈትነውን ነበር፡፡ የቢሮ ኪራይ ነበረብን፣ ካሜራም ተከራይተን ነበር የምንሰራው፡፡ ኤዲተርም አስቸጋሪ ነበር፡፡ በዚያ ፈተና ውስጥ የአንድ የአንድ ሰዓት 50 ፕሮግራሞችን ለአንድ ዓመት ሰራን፡፡ ስራችን ደግሞ ቲቪ ሾው አይደለም፤ ሰባት አይነት የተለያዩ ፕሮግራሞች ይቀርቡበት ነበር፡፡ የተለያዩ ፈጠራዎችን በማከል ፕሮግራሙን ለየት ለማድረግ ሞክረናል፡፡ ያንን ከባድ ፈተና እየተጋፈጠን ነው የቆየነው፡፡ ቦክስ ኦፊስ ለማውጣት ሲኒማ ቤቶችን ማሳመን፣ የፕሮዲዩሰሮች ማህበራትን ማግባባት -----ስንቱ ነገር አሳልፈን መሰለሽ ቦክስ ኦፊስ የጀመርነው፡፡ ዱባይ ሳይቀር ሄደን የአመት በዓል ፕሮግራም ሰርተናል፡፡
ጥሩ እየሆንን፣ ገቢያችንም ደህና እየሆነ ሲመጣ የአንድ ዓመት ኮንትራታችን አልቆ እንቀጥላለን ብለን ስናስብ፣ኮንትራቱ ሳይታደስ ቀረ፡፡ እኛም ትንሽ ተቀይመን ስለነበር በዚያው ቆመ፡፡
አሁንም ሀበሻ ዊክሊ በሚለው ስም ነው ብዙ ስራ እየሰራችሁ ያላችሁት?
ልክ ነው፡፡ የቲቪ ፕሮግራማችን ሲቆም ስሙ በጣም ጥሩ ስለሆነ “አዶኒክ ግሎባል ኢንተርቴይንመንት” የሚለውን ወደ ሀበሻ ዊክሊ ፕሮሞሽን ቀየርነውና ቀጠለ፡፡ የኩባንያው ባለድርሻዎችም እኔና ባለቤቴ ሀና ሆንን ማለት ነው፡፡
ዘንድሮ በ15 ሚ. ብር ለአዲስ ዓመት ባዘጋጃችሁት ኤክስፖ፣ “በጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ” ላይ ለማስመዝገብ በሂደት ላይ የነበሩ ሁለት የፈጠራ ሥራዎችን ለእይታ አቅርባችሁ ነበር፡፡ ሂደቱ ምን ላይ ደረሰ?
አዎ፤ትልቁን ፖስት ካርድ በ50 የበሬ ቆዳ ሰርተናል፡፡ በብራና ለመስራት ስለፈለግን ነው፡፡  በሻማ ትልቁን 15 ሜትር የገና ዛፍ ሰርተናል፡፡ እኛ አዳዲስ ፈጠራዎችን የምንሰራው ስለ አካባቢ ጥበቃ፣ ስለ አየር ንብረት ለውጥ ሰዎችን ለማስተማር ነው፡፡
በላቪሲን ኤክስፖ ትልቁን የገና ዛፍ ከወዳደቁ በርካታ የውሃ ላስቲኮች ሰርተን፣ አካባቢን ከማቆሸሽ በፈጠራ ስራ ላስቲኮችን ስራ ላይ ማዋል እንደሚቻል አስተምረናል፡፡ ብዙ የአገር ውስጥና የውጭ ሚዲያዎችም ሽፋን ሰጥተውት ነበር ብዙ የአገር ውስጥና የውጭ ሚዲያዎች ሽፋን ሰጥተውት ነበር፡፡ ረጅሙም ዛፍ ከሻማ የተሰራው ፀሐይ እየመታው ሲቀልጥ የዓለምን የሙቀት መጨመር ለማሳየት ነው፡፡ ፖስት ካርዱንና የሻማ ዛፉን ጊነስ ላይ ለማስመዝገብ ሂደት ላይ ነን፤ ሌሎች አሟሉ የተባልነውን ለማሟላት እየጣርን ነው፡፡
በዚህ ወር መጨረሻ ላይ በጊዮን ትልቅ የሙዚቃ ኮንሰርት ለማቅረብ ቴዲ አፍሮን አስፈርማችኋል፡፡ እስቲ ዝርዝሩን ንገረኝ ?
እንደ ሁነት አዘጋጅነታችን ትልልቅ ሥራዎችን ሰርተን ተሳክቶልናል፤እየተሳካልንም ነው፡፡ ከቴዲም ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በስራ የምንገናኝባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ እውነት ለመናገር ከቴዲ ጋር ኮንሰርት እንስራ ብለን ብዙም እቅድ ይዘንበት አናውቅም፡፡ ነገር ግን አጋጣሚው ከተፈጠረ ለምን አናደርገውም፣ ለምንስ አንሞክረውም? አልን፡፡ ምክንያቱም ጥሩ ስራ እንደምንሰራ እንተማመናለን፡፡ መጀመሪያ እርሱ አሜሪካ ስለነበረ ብዙ ጉዳዮችን ተወያይተን የጨረስነው ከባለቤቱ ከአምለሰት ሙጬ ጋር ነበር፡፡ ከዚያም ከእርሱ ጋር ተገናኘንና ተወያየን፡፡ አጋጣሚዎቹ ጥሩ ሆኑና ስምምነት ላይ ደረስን፡፡ ኮንሰርቱ የካቲት 26 ቀን የአብይ ፆም ከመግባቱ በፊት ባለው የመጨረሻው ቅዳሜ  ይካሄዳል፡፡ እንግዲህ ሶስት ሳምንት ነው የሚቀረን፡፡
በምን ያህል ክፍያ ተስማማችሁ?
ለቴዲ የምንከፍለውን ለመናገር የእሱን ይሁንታ ማግኘት አለብን፡፡ እኛ ለአጠቃላይ ፕሮግራሙ ግን ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ይዘንለታል፡፡
ዝግጅቱ እንዴት ነው ታዲያ ?
አሁን ሩጫ ላይ ነን፡፡ ምክንያቱም ጥሩ ስራ መስራት አለብን፡፡ አንዳንድ ማሟላት ያለብንን ሁኔታዎች እያሟላን ነው፡፡ እነዚህን ጥንቅቅ አድርገን ስንጨርስ ስለ መግቢያ ዋጋው፣ ስለ ክፍያው  ወዘተ----በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይፋ እናደርጋለን፡፡
ከዚህ ቀደም የቴዲ የተለያዩ ኮንሰርቶች በተለያዩ ምክንያቶች ተሰርዘዋል፡፡ ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር የወሰዳችሁት የተለየ ጥንቃቄ አለ?
እኛ እንደ ሀበሻ ዊክሊ የምንናገረው፤ቴዲ ትልቅና ተወዳጅ ድምፃዊ መሆኑን ነው፤ገበያው እንደሚፈልገው እናውቃለን፡፡ ከዚህ በፊት ስለተሰረዙት ኮንሰርቶች እያሰብን፣ ስራችንን ከመስራት ወደ ኋላ አንልም፡፡ አሁንም በተወዳጅነቱ ከአድናቂዎቹ ጋር እንዲገናኝ በእኛም በእሱም በኩል ማድረግ ያለበንን እያደረግን ነው፡፡ እስካሁን ባለውም ሂደት የገጠመን እንቅፋት የለም፡፡ ተፈራርመናል፡፡ ለአዲስ አበባ አስተዳደርም የማሳወቂያ ደብዳቤ አስገብተናል፡፡
የኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ ባለቤት ለመሆን መወዳደራችሁን ሰምቻለሁ፡፡ እንዴት ሆነ?
እንግዲህ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ባወጣው ማስታወቂያ መሰረት በጣም ጥሩ የሆነ ፕሮፖዛል ቀርፀን አስገብተናል፡፡ ተፎካካሪ ከሆኑት ውስጥ እኛም አለንበት፡፡ ሀበሻ ዊክሊ ወደፊት እንደ ግብ ያስቀመጣቸው ትልልቅ ራዕዮች አሉት፡፡ አንዱና ትልቁ ራዕያችን፤ የራሳችን የቴሌቪዥን ጣቢያ መክፈት ነው፡፡ ሆሊዉድ ውስጥ ያለው የፊልም ደረጃ ወደ አገራችን እንዲመጣም እናስባለን፡፡ ከቴሌቪዥኑ ጣቢያ ሬዲዮው ስለቀደመ እድሉን ለመጠቀም ወደ ሬዲዮው ገብተናል፡፡ ብዙ ዝግጅት አድርገን ነው በውድድሩ የተሳተፍነው፡፡ ከፋይናንሱ ይበልጥ የሬዲዮ ፋይዳና ቴክኒክ ላይ ሰፊ ዝግጅት አድርገናል፡፡
ኤፍኤም ሬዲዮ ሲከፈት ያማከሩ፣ በሬዲዮ ኢንስታሌሽን ስራም ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን አዋቅረንበታል፡፡ ትልቅ ሬዲዮ ጣቢያን ያቋቋሙ ትልቅ ሰው በፕሮፖዛሉ ስራ ላይ ተሳትፈዋል፡፡ የተለየ የሬዲዮ ሀሳብ ይዘናል፤አሁን ያለውን የሬዲዮ ትሬንድ በዜናም፣ በዜና ሰዓትም፣ በአቀራረብም---- በተለይ ከውጭው ጉዳይ ይልቅ በአገራችን ጉዳይ ላይ አተኩረን ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት አለን፡፡
እዚህ አገር ባለሀብቱ ራሱ ስፖንሰር የሚያደርገው በብዛት የሚደመጠውን እንጂ የሚዘገበው ነገር ምንም ይሁን ምን ጉዳያቸው አይደለም፡፡ ይሄ የተበላሸ አስተሳሰብ ነው፤ ይሄን አስተሳሰብ እንቀይራለን ብለናል፡፡ በኦዲዮም በቪዲዮም በደንብ የተደራጀ ስቱዲዮ አለን፡፡ ወደፊት ደግሞ ወደ ቴሌቪዥን ባለቤትነቱ እንሄዳለን፡፡
ባለፈው ያሸነፈ ድርጅት አለ ተብሎ በስም ተጠቅሶ በማህበራዊ ሚዲያው ሲናፈስ ነበር፡፡ መጨረሻው ምን ሆነ?
ጨረታው ሲወጣ 40 ድርጅቶች ለመሳተፍ ሰነድ ወስደዋል፡፡ እስካሁን ባለን መረጃ አራት ድርጅቶች ናቸው ጨረታውን ያስገቡት፡፡ ከአራቱ አንዱ የእኛ ሀበሻ ዊክሊ ነው፡፡ ቴክኒካሊ ጥሩ እንደሆነ ሰምተናል፡፡ ጨረታው የተሰረዘው በፋይናንስ አቅም የተሻለ ድርጅት አልተገኘም በሚል ነው፡፡ አሁን ጨረታው በድጋሚ ወጥቷል፡፡ ማንም እንዳላሸነፈ ባለስልጣኑ በጋዜጣዊ መግለጫው አስታውቋል፡፡ ስለዚህ ለሁለተኛ ጊዜ ጨረታውን ከ15 ቀን በኋላ እናስገባለን፡፡
ባለትዳርና የአንዲት ሴት ልጅ አባት ነህ፡፡ ትዳር ምን ይመስላል?
ባለቤቴ በጣም ጐበዝ፤ቀልጣፋና ጠንካራ ሴት ናት፡፡ ስራውን ከእኔ እኩል ትሰራለች፡፡ በስራ ላይ ጭቅጭቁ፣ የሀሳብ ፍጭቱ አለ፡፡ ቤታችን ስንገባ የምንዋደድ ባልና ሚስቶች ነን፡፡ ኤንጂል አዶኒክ የተባለች ቆንጆ ሴት ልጅ ወልደናል፤በጣም ደስተኞች ነን፡፡ እንደ ጓደኞችም እንደ ሥራ ባልደረቦችም ነን፡፡

የቲማቲም ምርቶችን በማጥቃት ከፍተኛ ውድመት ያደርሳሉ ለተባሉ በሽታዎች፣ ኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች  አዲስ መድሃኒት በምርምር ማግኘታቸውን ገለፁ፡፡
“ኬንት ፓወር” የሚል ስያሜ የተሰጠው ይኸው መድሃኒት፤ በቲማቲም ተክል ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ባክቴሪያና ፈንገሶችን የሚያጠፋና ምርቱ በቫይረስ እንዳይጠቃ የሚከላከል እንደሆነ ተመራማሪዎቹ ተገኘ ዘለቀና ታደሰ ገ/ኪሮስ ሰሞኑን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል፡፡
በአገሪቱ በተለያዩ ወቅቶች በቲማቲም ምርቶች ላይ በሚያጋጥሙ ልዩ ልዩ በሽታዎች ሳቢያ ምርቱ ስለሚቀንስ በበቂ መጠን ለገበያ ሊቀርብ አለመቻሉን የሚናገሩት ተመራማሪዎቹ፤  በምርቱ ላይ የሚደርሰውን ችግር ለመቅረፍ የሚረዳና አምራቹም በለፋው መጠን አምርቶ ለተጠቃሚው ምርቱን በበቂ መጠን የሚያቀርብበትን ሁኔታ ለማመቻቸት አስበው ወደ ምርምር መግባታቸውን ገልፀዋል፡፡ ሁለቱ ተማራማሪዎች፤ ከሁለት ዓመታት እልህ አስጨራሽ የምርምር ጥረትና ትጋት በኋላ ነው የቲማቲም በሽታዎችን ማጥፋትና መከላከል የሚችል መድሃኒት ማግኘታቸውን ይፋ ያደረጉት፡፡
በተመራማሪዎቹ የተገኘው ኬንት ፓወር የተሰኘው ይኸው መድሃኒት፤ ቀደም ሲል ከነበረውና አርሶ አደሩ ከሚጠቀመው ፀረ-ተባይ መድሃኒቶች በዋጋው በእጅጉ ያነሰና በአገልግሎቱ የተሻለ መሆኑን ታውቋል፡፡ በአንድ የቲማቲም ምርት ዘመን፣ በስድስት ሄክታር መሬት ላይ የተዘራውን የቲማቲም ምርት ከበሽታ ለመከላከል ከውጪ የሚገባውን መድሃኒት የሚጠቀም አርሶ አደር ከ63ሺህ ብር በላይ ወጪ ማድረግ ይጠበቅበታል ያሉት ተማራማሪዎቹ፤ አዲሱን “ኬንት ፓወር” ግን በስድስት ሺህ ብር ብቻ ገዝተው፣ በበሽታ ያልተጠቃና በመድሃኒት ያልተበከለ ንፁህ የቲማቲም ምርት ማግኘት እንደሚችሉ ገልፀዋል፡፡ ተመራማሪዎቹ ይህንኑ የምርምር ግኝታቸውን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ አዕምሮአዊ ንብረት ጽ/ቤት ሰርተፍኬት ያገኙ ሲሆን በምርምር ያገኙትን መድሃኒት ለአርሶ አደሩ በስፋት ለማድረስ የሚችሉበትን መንገድ በማመቻቸት ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
የምርምር ውጤታቸውን በፋብሪካ ደረጃ እያመረቱ ለተጠቃሚው ለማድረስ 23 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግና ለፋብሪካው ግንባታ የሚሆን የቦታ ጥናት ማድረጋቸውንም ተመራማሪዎቹ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ጠቁመዋል፡፡ 

ኤኤችዋን ኤንዋን (AHINI) የተባለው አዲሱ ጉንፋን መሰል ኢንፍሌዌንዛ በአዲስ አበባና አካባቢዋ ተቀስቅሶ በነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ሥጋት ፈጥሯል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ የጤና ተቋማት በጥር ወር ብቻ በተደረገ ቅኝት፣ 32 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው መገኘታቸውንና ከእነዚህ መካከልም አራቱ ህይወታቸውን ማጣታቸውን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ዋና ዳሬክተር ዶ/ር ዳዲ ጂማ ተናግረዋል፡፡
ወቅትን ጠብቆ የሚቀሰቀስ ጉንፋን መሰል በሽታ እንደሆነ የተነገረለት የኢንፍሎዌንዛ በሽታ፤በፍጥነት ከሚዛመቱ በሽታዎች መካከል የሚመደብ ሲሆን ተገቢው ህክምና ካልተደረገለትም ለሞት ሊያጋልጥ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡
እንደ ማንኛውም የጉንፋን በሽታ በትንፋሽና ከአፍንጫ በሚወጣ ፈሳሽ አማካኝነት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ሲሆን ትምህርት ቤቶች፣ የህዝብ ትራንስፖርቶች፣ ሲኒማ ቤቶችና ሰዎች በስፋት የሚሰባሰቡባቸው ሥፍራዎች በሽታውን በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው ለማስተላለፍ ምቹ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡ በሽታው በተለይም ዕድሜያቸው ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናትንና ከስልሣ አምስት አመት በላይ የሆናቸውን ሰዎች እንዲሁም ነፍሰ ጡር ሴቶችን በይበልጥ ያጠቃል፡፡ አንድ ሰው ቫይረሱ በሰውነቱ ውስጥ እያለ ምንም አይነት የህመም ስሜቶች ሳይኖሩት በሽታውን ሊያስተላልፍ እንደሚችልና ቫይረሱ ወደ ሰውነታችን ውስጥ ከገባ ጊዜ ጀምሮ ከ5-7 ቀናት ባሉት ጊዜያት ውስጥ በሽታው ወደ ሌሎች ሰዎች እንደሚተላለፍ ዶ/ር ዳዲ ተናግረዋል፡፡
 በስኳር፣ በደም ግፊት፣ በልብና የኩላሊት በሽታዎች መያዝ ለኢንፍሉዌንዛ ይበልጥ ተጋላጭ  የሚያደርግ ሲሆን ሁለቱ በአንድ ላይ በቀላሉ ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉም ተጠቁሟል፡፡ በጉንፋን መሰሉ ኢንፍሎዌንዛ የተያዘ ሰው ከመደበኛው የጉንፋን በሽታ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ምልክቶችን የሚያሳይ ሲሆን ትኩሳት፣ ሳል፣ ራስ ምታት፣ የጉሮሮ መከርከርና የጡንቻ መገጣጠሚያ ህመሞች፣ የአፍንጫ ፈሳሾችና ማስነጠስ የበሽታው ዋንኛ ምልክቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ምልክቶች በታዩ ጊዜ በአፋጣኝ ወደ ህክምና ተቋማት በመሄድ ህክምና ማድረግ እንደሚገባም ተገልጿል፡፡
ኤኤችዋን ኤንዋን የተባለው ኢንፍሌዌንዛ፤ በአሁኑ ወቅት በአለም አቀፍ ደረጃ በፍጥነት በመስፋፋት ላይ ሲሆን በዓለም በየዓመቱ ከ3-5 ሚሊዮን ሰዎች በበሽታው እንደሚያዙና ከ500ሺ በላይ የሚሆኑት በዚሁ በሽታ ሳቢያ ህይወታቸውን እንደሚያጡ ከአለም ጤና ድርጅት የተኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በላብራቶሪ ምርመራ የተገኙት የኢንፍሎዌንዛ በሽታ ናሙናዎች አሜሪካ አገር ወደሚገኘው “ሴንተር ፎር ዲዚዝ ኮንትሮል” (CDC) መላካቸውንና ይህም የተደረገው በሽታው በየጊዜው ባህርይውን ስለሚለዋውጥ፣ ለተጨማሪ ምርመራ እንደሆነ ዶ/ር ዳዲ ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል የአለም ጤና ድርጅት፤አለም አቀፍ የጤና ሥጋት እንደሆነ የጠቆመው የዚካ ቫይረስ በአገራችን መከሰቱን የሚያረጋግጡ መረጃዎች እስከ አሁን አለመገኘታቸውንና አገሪቱ ከቫይረሱ ነፃ መሆኗን የገለፁት የሥራ ኃላፊዎች፤ የቫይረሱን መኖር አለመኖር ለማረጋገጥ የሚያስችል ኬሚካል ከውጪ ለማስገባት በሂደት ላይ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት ቫይረሱ በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ እንደነበር የሚያሳዩ ፍንጮች መኖራቸውም ተጠቁሟል፡፡  

  በወተት ውስጥ የሚኘውን የአፍላቶክሲን ኤም 1 ይዘት ለማወቅ የሚያስችል ምርመራ መጀመሩን “ብሌስ አግሮ ፉድ ላብራቶሪ” አስታወቀ፡፡
በከብቶች መኖ ላይ የሚገኘውንና ከብቶች ከተመገቡት በኋላ በሚሰጡት የወተት ምርት ላይ ዓይነቱን ቀይሮ የአፍላቶክሲን ኤም 1(Aflatoxin M1) የሚሆነውን እንዲሁም ካንሰር የማምጣት አቅም አለው የተባለውን መርዛማ ንጥረ ነገር ይዘት ለማወቅ የሚያስችል የላብራቶሪ ፍተሻ መጀመሩን የገለፀው ድርጅቱ፤ ይህም ወተት አምራች ገበሬው በቅርቡ በተፈጠረው የመረጃ መዛባት ሳቢያ ያጣውን የገበያ ዕድል መልሶ ለማግኘት ያስችለዋል ብሏል፡፡
 ምርመራው፤ ሸማቹ ማህበረሰብ ደረጃውን የጠበቀ የወተት ምርት ለማግኘት የሚያስችለው  እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡ የላብራቶሪ ፍተሻው የተጀመረው በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የወተት አቀናባሪዎች በጠየቁት መሰረት መሆኑን የጠቆመው ድርጅቱ፤ ቀደም ሲል የላብራቶሪ ፍተሻው የሚከናወነው ወደተለያዩ የአፍሪካና የአውሮፓ አገራት በመላክ እንደነበር አስታውሶ፣ አዲሱ አሠራር ይህንን ለማስቀረት ያስችላል ብሏል፡፡  

 ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በአህጉሪቱ በትልቅነቱ ሊጠቀስ የሚችል የህፃናት ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በአዲስ አበባ ሊገባ ነው፡፡
በአለርት ማዕከል ግቢ ውስጥ ይገነባል የተባለው ይኸው የህፃናት ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፤ በዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎች የተሟላና በሙያው በብቃት በሰለጠኑ የጤና ባለሙያዎች የተደራጀ እንደሚሆን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ዶክተር ከሰተብርሃን አድማሱ ተናግረዋል፡፡ የሆስፒታሉ የግንባታ ሥራ በቀጣዩ አመት እንደሚጀመርም ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡
የአለርት ማዕከል በ1.5 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባውን የእናቶች ህክምና መስጫና ማዋለጃ ማዕከል ባለፈው ማክሰኞ መርቀው የከፈቱት የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ፤ ማዕከሉ መንግስት የእናቶችና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ የሚያደርገው ርብርብ አንዱ አካል የሆነውን የጤና ተቋማትን የማስፋፋት ዕቅድ መሰረት በማድረግ የተገነባ መሆኑን ጠቁመው እናቶች በማዕከሉ ተገቢውን ክብካቤና የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ ማድረግ ዋንኛ ሥራው እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
የማዋለጃ ማዕከሉ፤ የቅድመ ወሊድ ክትትል፣ የማዋለድ አገልግሎት፤ የድህረ ወሊድ ክትትል፣ የማህፀን ቀዶ ህክምና፣ የቤተሰብ ምጣኔና የክትባት አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን 22 የመኝታ አልጋዎች፣ 5 የማማጫ አልጋዎች፣ ሁለት የኦፕሬሽን ማድረጊያ ጠረጴዛዎች ያሉትና የሪከቨሪ ስክራብ ሩም የተሟሉለት መሆኑም ታውቋል፡፡

በደራሲ አቤል ወርቁ ደመቀ የተፃፈው “የፍቅር ደረሰኝ” የተሰኘ መፅሀፍ ዛሬ ከረፋዱ 3፡30 ላይ ፒያሳ በሚገኘው አዲስ ብድርና ቁጠባ አዳራሽ ይመረቃል፡፡ የዘመናችንን ፍቅር አጉልቶ ያሳያል የተባለው መፅሀፉ ታሪኮቹን መስሎ ሳይሆን ሆኖ እንደፃፋቸውና ገፀ ባህሪያቱን እንደቀረፃቸው ደራሲው በመግቢያው ጠቁሟል፡፡ በ140 ገፆች የተቀነበበው መፅሀፉ፤ በ40 ብር የሚሸጠው መፅሀፉ ዛሬ ደራሲያን ሀያሲያንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በሚገኙበት ይመረቃል ተብሏል፡፡

የሰዓሊ ሮቤል ብርሃኔ ከ50 በላይ የሥዕል ስራዎች ለእይታ የሚቀርቡበት “The Voice Within” (የራስ ድምፅ) የተሰኘ የስዕል ትርኢት የፊታችን ማክሰኞ ከ11፡00 ሰዓት ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ሙዚየም ይከፈታል፡፡ ለተከታታይ ሰባት ቀናት ለእይታ ክፍት ሆኖ ይቆያልም ተብሏል፡፡
ሰዓሊ ሮቤል ብርሀኔ፤ በዓሉ የስዕል ትርኢት ሲያቀርብ አራተኛ ጊዜው ሲሆን ከሌሎች ሰዓሊያን ጋር ከ20 ጊዜ በላይ በውጭና በአገር ውስጥ ለእይታ አብቅቷል፡፡ ሥዕሎቹ፤ ሰዎች ህሊናቸው እርስ በእርሱ ሲጋጭባቸው መልሱ በገዛ ህሊናቸው ውስጥ እንደሚገኝና ግጭቱም ከኋላ ታሪካቸው ጋር የተሳሰረ መሆኑን አጉልተው ያሳያሉ ተብሏል፡፡

በደራሲ መላኩ ደምለው የተፃፈው “ብልጭታ” የግጥም መድበል የፊታችን አርብ ከቀኑ 9፡00 እስከ 11፡30 ሰዓት በቅርስ ጥበቃና ጥናት ባለስልጣን አዳራሽ ይመረቃል፡፡ በፍቅር፣ በማህበራዊና በስነ-ልቦና ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ 89 ግጥሞችን የያዘው መጽሐፉ በ104 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን በ30 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ የመጽሐፉ፤ ሽያጭ ገቢ ሙሉ ለሙሉ ለኩላሊት እጥበት ማህበር ድጋፍ እንደሚውልም በመጽሐፉ ላይ ተገልጿል፡፡ ደራሲው ከዚህ ቀደም “የንዋይ ጦርነት”፣ “ውብ ያለመልክ” እና “ነጭ ለባሽ” የተሰኙ ረጅም ልቦለድ መጽሐፎችን ለንባብ አብቅቷል፡፡