Administrator

Administrator

 ማንዴላ በ2.9 ሚ. ዶላር፣ ኢምቤኪ በ1.1 ሚ. ዶላር የግል ቤታቸውን ሰርተዋል
     የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ አግባብ ባልሆነ መንገድ ከመንግስት ካዝና አውጥተው የግል መኖሪያ ቤታቸውን አሳድሰውበታል ከተባለው 23 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ የተወሰነውን ገንዘብ ለመመለስ መስማማታቸውን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ገንዘቡን ለግል ጥቅማቸው በማዋላቸው ሰፊ ውግዘት ሲደርስባቸው የቆዩት ፕሬዚዳንቱ፤ከትናንት በስቲያ የተወሰነውን ገንዘብ ለመመለስ መስማማታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ የገንዘቡን መጠን የሚወስኑት የአገሪቱ ኦዲት ቢሮ ሃላፊና የፋይናንስ ሚኒስትሩ እንደሚሆኑ አመልክቷል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ከመንግስት ካዝና ያወጡትን ገንዘብ፣  ካንድላ ተብላ በምትጠራው የአገሪቱ የገጠር መንደር ውስጥ የሚገኘውን ቤታቸውን ለማሳደስ ማዋላቸው በአገሪቱ ዋነኛ የፖለቲካ ውዝግብ ፈጥሮ መቆየቱን ያስታወሰው ዘገባው፣ ፕሬዚዳንቱ የተወሰነውን ገንዘብ ለመመለስ ቢፈቅዱም፣  የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የመብት ተሟጋቾች ግን በጉዳዩ ዙሪያ የሙስና ምርመራ እንዲደረግ ያቀረቡትን ጥያቄ እንደሚገፉበት ማስታወቃቸውን ገልጧል፡፡
የተወሰነው ገንዘብ በሰፊው የፕሬዚዳንቱ ግቢ ውስጥ አምፊ ቲያትር፣ ትልቅ የመዋኛ ገንዳና ግዙፍ የከብቶች ማድለቢያ ለመስራት መዋሉ የተነገረ ሲሆን፣ የአገሪቱ ህገ መንግስታዊ ፍርድ ቤትም በቀጣዩ ሳምንት ጉዳዩን በተመለከተ የመጀመሪያውን ችሎት እንደሚሰይም ተዘግቧል፡፡
ቀደምት የአገሪቱ ፕሬዚዳንቶችም ለግል ቤቶቻቸው ከፍተኛ የመንግስት ገንዘብ ወጪ ሲያደርጉ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ ዴክለርክ 22 ሺህ ዶላር፣ ማንዴላ 2.9 ሚሊዮን ዶላር፣ ምቤኪ 1.1 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ በማውጣት ቤታቸውን መስራታቸውን አክሎ ገልጧል፡፡

 በዓለም ላይ ነፃነቷን ለማግኘት ላለፉት 60 ዓመታት የታገለችና አሁንም ድረስ ነፃነቷን ያልተጎናፀፈች ብቸኛ አገር ፍልስጤም ናት ያሉት የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ሪያድ ማልኪ፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተገቢውን ትኩረት አልሰጠንም ሲሉ ወቀሱ፡፡
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚያደርጋቸው አንዳንድ ጥረቶች ቢኖሩም አጥጋቢ አይደሉም ብለዋል፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፡፡
“አሁንም ድረስ ልጆቻችን በሰላም ወጥተው በሰላም መግባት አልቻሉም፤ በእስራኤል ወታደሮች የሚገደሉ ህፃናት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል” ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ዛሬም ከ60 ዓመት በኋላ ፍልስጤም ሰላምን እንደናፈቀች ናት ሲሉ ሰሞኑን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ ከ11 ዓመት ዕድሜዬ ጀምሮ በፍልስጤም የሰላም ረ)ቡ እንደነበር አስታውሳለሁ ያሉት ዶ/ር ማልኪ፤ “አሁንም በ60 ዓመቴ ለነፃነት እየተዋጋን ነው፤ ወደፊትም ልጆቼ ነፃነትን ያያሉ ብዬ ዋስትና መስጠት አልቻልኩም፤ ይህ በጣም አሳዛኝ ነው” በማለት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለስቃያችን ምላሽ ሊሰጠን ይገባል ብለዋል፡፡
እኛ ትግላችንን እንቀጥላለን፤ እንዴት እጅ እንደሚሰጥ አናውቅም ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ እኔ ተስፋ ብቆርጥ እንኳን የ13 ዓመት ልጅ በወታደር ስትገደል እያዩ ልጆቼ ተስፋ አይቆርጡም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እስራኤልን አንድ ሃያል አገር ስለምትደግፋት ብቻ ከህግ በላይ ልትሆን አትችልም፤ ለዚህም ነው የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ድጋፍ የምንጠይቀው፤ ብለዋል ዶ/ር ሪያድ ማልኪ፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት የ91 ፕሮጀክቶችን የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰረዙን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን

አስታወቀ፡፡
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጌታሁን ነጋሽ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ ፕሮጀክቶቹ

በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመስራት ፈቃድ ተሰጥቷቸው የነበሩ ሲሆን ፈቃዳቸው የተሰረዘው ፈቃድ ካወጡ በኋላ

በመጥፋትና በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ ለመግባት ባለመቻላቸው ነው፡፡
የፈቃድ መሰረዙን ተከትሎም መሬት የሰጠው አካል መሬቱን፣ ገንዘብ የሰጠው አካል ገንዘቡን፣ እንዲያስመልስ

እንዲሁም መሳሪያዎችን በነፃ ለማስገባት በሂደት ላይ ያሉም እንዲከለከሉ ኮሚሽኑ ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ

ማሳወቁን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
ባለፈው ዓመትም እንዲሁ በማኑፋክቸሪንግና በግብርና ዘርፎች ለመሰማራት ፈቃድ ተሰጥቷቸው በወቅቱ ወደ ስራ

ያልገቡ 357 ፕሮጀክቶች ፈቃዳቸው መሰረዙን አቶ ጌታሁን አስታውሰዋል።
ኮሚሽኑ ባለፈው ሩብ ዓመት 107 አዲስ፣ 23 የማስፋፊያ፣ በድምሩ 130 የኢንቨስትመንት ፈቃዶችን በማኑፋክቸሪንግ፣

በግብርናና በአገልግሎት ዘርፎች የሰጠ ሲሆን ከነዚህ ውስጥም 29ኙ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች መሆናቸውን አቶ

ጌታሁን ገልፀዋል፡፡

  አንድ በእድሜያቸው በግምት ወደ 60/ አመት የሆናቸው አባት ከሀያ አመት በፊት የሚከተለውን ምስክርነት

ሰጥተዋል፡፡
“...እኔ የኢትዮጵያ ሱማሌ ስሆን የምኖረው በጅግጅጋ ነው፡፡ ሴትን ልጅ መግረዝ በሕይወትዋ ላይ እንደመፍረድ

ይቆጠራል የሚል አቋም አለኝ፡፡ ከባለቤ የወለድኩዋቸው ሰባት ልጆች ሲሆኑ አራት ሴትና ሶስት ወንዶች ናቸው።

ለሶስቱ ሴቶች ባለመድረሴ መቸውንም የሚቆጨኝ ነገር ነው፡፡ ሳላስጥላቸው ልክ እንደእናታቸው ተገርዘዋል።

አንዱዋን ልጅ ግን አስጥዬ ወደዘመዶቼ አዲስ አበባ ስለላክሁዋት እሱዋ     አልተገረዘችም፡፡ ድናልኛለች፡፡
“በሴቶች ላይ የሚፈጸም ግርዛት ጀንደር ወይንም ስርአተ ጾታን መሰረት ያደረገ በሴቶች ላይ የሚፈጸም በደል ነው፡፡

ይህ ድርጊት የሴቶችን ሰብአዊ መብት የሚጋፋ መሆኑንም አለም የተስማማበት ጉዳይ ነው። ይህንንም መረጃ

በአለምአቀፍ ደረጃ ያሰራጨው የአለም የጤና ድርጅት ሲሆን አገራትም ያመኑበትና የተስማሙበት በመሆኑ ድርጊቱ

እንዲቆም ሲነገር አመታትን አስቆጥሮአል፡፡
በሴት ልጅ ላይ የሚፈጸም ግርዛት ሲባል በአይነት የተለያየ ሲሆን በብልት አካባቢ የስሜት ሰጪውን ክፍል ሳይነካ

ከሚፈጸመው ጀምሮ ጭርሱንም ሴቷን ስሜት የለሽ እስከሚያደርገው የግርዘት አይነት ድረስ በሶስት ደረጃ የተከፈለ

ነው፡፡ እንደ የአለም የጤና ድርጅት ዘገባ በግምት ከ100 እስከ 140 ሚሊዮን ልጃገረዶችና ሴቶች በአለምአቀፍ ደረጃ

ግርዛት የተፈጸመባቸው ሲሆን ወደ 3/ ሚሊዮን የሚጠጉ ልጃገረዶች  በየአመት በተለይም በአፍሪካ ድርጊቱ ግርዘቱ

ይፈጸምባቸዋል፡፡
በአፍሪካ የሚተገበረውን የሴት ልጅ ግርዛት ለመገመት እንደተቻለው ወደ 98/ በመቶ የሚሆነው በሶማሊያ የሚፈጸም

ሲሆን በንጽጽሩ ደግሞ በኡጋዳ 1/ በመቶ ብቻ ይፈጸማል፡፡የቅርብ ጊዜ ጥናት እንደሚያሳየው ወደ 91.5 ሚሊዮን

የሚሆኑ እድሜያቸው ከ9/ አመት በላይ የሆኑ በአፍሪካ ያሉ ልጃገረዶች  በግርዛት ምክንያት ከሚደርሱ የተለያዩ

ችግሮች ጋር የሚኖሩ መሆኑ ተረጋግጦአል። በኢትዮያ በተካሄደውሃመ ዲሞግራፒክ ኤንድ ኼልዝ ሰርቬይ ወደ 74/

በመቶ የሚሆኑ ልጃገረዶችና ሴቶች በተለያዩ መስተዳድሮች ከሶስቱ አንዱ አይነት ግርዘት እንደተካሄደባቸው ያሳያል፡፡

የሴት ልጅ ግርዛት በቅርብእና በርቀት ወይንም በወደፊት የጤና ሁኔታ ላይ የተለያዩ ችግሮችን እንደሚያስከትል ግልጽ

ነው፡፡ እንደየአለም ጤና ድርጅት መረጃ ግርዘት የተከናወነባቸው ሴቶች በተለይም ልጅ በመውለድ ጊዜ ለተለያዩ

ችግሮች እንደሚጋለጡ ነው፡፡ ይህ ችግርም እንደግርዘቱም አይነት ደረጃው እንደሚለያይ ተጠቁሞአል፡፡
በቅርብ ጊዜ ማለትም በ2013/ በኖርዌይ በተደረገ ጥናት መመልከት እንደሚቻለው ሴቶች በተለይም በሶስተኛ ደረጃ

ያለውን እና በከፋ ሁኔታ የሚፈጸመውን ግርዘት በመገረዛቸው ምክንያት በወሊድ ጊዜ የማህጸን መተርተር፣ በመሳሪያ

ድጋፍ መውለድ በመጎተት፣ የማህጸን መድማት እና አስከፊ በሆነ ሁኔታ ልጅን መገላገል ሊያጋጥማቸው እንደሚችል

ተገልጾአል፡፡
በኢትዮጵያ በሶስተኛ ደረጃ የሚተገበረው እና በሶማሊያ ክልል የሚፈጸመው የግርዛት አይነት እናቶች በወሊድ ጊዜ

በከፍተኛ ሁኔታ እንዲሰቃዩ እና በተራዘመ ምጥ ምክንያትም ልጆቻቸውን እንዲያጡ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል

ግልጽ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ዛሬም በሶማሊያ ክልል በሶስተኛው አይነት ግርዛት ምክንያት ብዙ ሴቶች የሚሰቃዩ ሲሆን ዲሴምበር

2015/ ይፋ በሆነው ጥናትም እንደተጠቆመው ወደ 97/ በመቶ የሚሆኑ ሴቶች የችግሩ ሰለባ ሆነዋል። በእርግጥ

በኢትዮጵያ በሶማሊያ ክልል ችግሩ በስፋት መኖሩ ቢታወቅም ከዚህ ጋር ተያይዞ በመውለድ ጊዜ ያጋጠሙ ችግሮች

በግልጽ ተመዝግበው የተቀመጡበት አሰራር ባለመኖሩ ሁኔታውን ለመረዳት አስቸጋሪ መሆኑን ጥናቱ ጠቁሞአል፡፡

በዚህም መሰረት በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ በተለይም በካራማራ ሆስፒታል እንደውጭው አቆጣጠር ከጃንዋሪ 2015/

እስከ ማርች 2015/ ድረስ የተደረገ ጥናት ወደሆስፒታሉ  ለመውለድ የሚመጡ ሴቶችን ከግርዛት ጋር በተያያዘ በምጥና

ወሊድ ወቅት ምን ችግር አንደሚከሰትባቸው ለይቶ ለማወቅ እንዲረዳ በዶ/ር ሙታሲም አብዱላሂ እና ዶ/ር ወንድሙ

ጉዱ ጥናት ተደርጎአል፡፡
ኦርጋናይዜሽን ፎር ዘ ድቭሎፐምነንት ፎር ውመን ኤንደ ችልድረን ኢትዮጵያ በሚባል በጎ አድራጊ ድርጅት

አስተባባሪነት እና ሌሎች የሚመለከታቸው እና ድጋፍ ሰጪ አካላት ትብብር የተሰራው ጥናት ይፋ በተደረገበት ወቅት

ጥናት አድራጊዎቹ ስለጥናቱ ለአምዱ አዘጋጅ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ለመሆኑ ዛሬም ግርዛት አለ? ተብለው ለተጠየቁት ዶ/ር ሙታሲም የሚከተለውን መልስ ነበር የሰጡት፡፡
“...ግርዛት በኢትዮያ ውስጥ ዛሬም አለ፡፡ ግርዛት መኖሩን በመገናኛ ብዙሀንም በተለያየ ጊዜ ሲነገር የሚሰማ ሲሆን ሃመ

በተደረገው ጥናትም  74/ በመቶ የሚሆኑ ሴቶች የተገረዙ መሆኑ ተረጋግጦአል፡፡ የግርዛት አይነቱ በሶስት ደረጃ

የተከፈለ ሲሆን 3ተኛ የሚባለው ግርዛት እጅግ አስከፊና ሴቶችን የሚጎዳ ነው፡፡ ይህ አይነቱ ግርዘት በአገር አቀፍ ደረጃ

ትንሽ ፐርሰንት ሲሆን በሶማሌ ክልል ግን ከ80/ በመቶ በላይ ሶስተኛውን አይነት ግርዛት የተገረዙ ሴቶች አሉ፡፡

በእርግጥ እኛ ያጠናነው ጥናት ዛሬ የተገረዙትን የሚመለከት ሳይሆን የዛሬ ሀያ እና ከዚያም በላይ በሆኑ አመታት

የተገረዙትንና በወሊድ ወቅት ምን ችግር እንደሚያጋጥማቸው በካራማራ ሆስፒታል ተገኝተን የተመለከትንበት ነው፡፡

በምጥ ሰአት እንደሚቸገሩ እና ልጁ በተገቢው ጊዜ የመውጣት ችግር ፣ካር ለማስገባት ችግር እንደሚያጋጥም፣

የመድማት ሁኔታ እና የመሳሰሉት እንደሚኖሩ በጥናቱ አረጋግጠናል።”
ሌላው ጥናት ያካሄዱት ዶ/ር ወንድሙ ጉዱ ናቸው። እሳቸውም አንደሚሉት፡-
“...ግርዛት በተለያዩ ጥናቶች እንደቀረበው 90/በመቶ እና ከዚያ በላይ የሚፈጸም ሲሆን አስከፊውን አይነት ግርዛት

የተገረዙት ሴቶች ደግሞ ከ84-85 በመቶ የሚሆኑት ናቸው፡፡” ብለዋል፡፡
ጥናቱ በተካሄደበት ወቅት ግርዛት የተፈጸመባቸውንና ያልተገረዙ ሴቶችን ሁኔታም ለማነጻጸር ተሞክሮአል። በወሊድ

ጊዜ የሚያጋጥሙ ችግሮች በሙሉ ማለት ይቻላል... በተደጋጋሚ የሚያጋጥሙት በተገረዙ ሴቶች ላይ መሆኑ ሲረጋገጥ

ያልተገረዙት ላይ ግን እጅግ በተራራቀ እና አልፎ አልፎ በሚባል ሁኔታ የሚታይ ነው።
ዶ/ር ሙታሲም  እንደገለጹትም ...
“...በሱማሌ ክልል ያሉ ሴቶች ግርዛቱ ትክክል እንዳልሆነ እና በተለይም በወሊድ ወቅት አደጋ እንደሚያስትል

ያምናሉ፡፡ ነገር ግን ድርጊቱን ለማስቀረት በቀላሉ የማይቻል በመሆኑ አሁንም አይደረግም ለማለት አይቻልም፡፡

ግርዛቱን ከሚፈጽሙት ግለሰቦች ጀምሮ አስፈጻሚዎቹ ቤተሰቦች በባህል በኢኮኖሚና በማህበራዊ ትስስር ምክንያት

በቀላሉ ሊያስቀሩት እንዳልቻሉ ለማየት ተችሎአል፡፡”
ጥናቱ በተካሄደበት ወቅት ግርዛት የተፈጸመባቸውንና ያልተገረዙ ሴቶችን ሁኔታም ለማነጻጸር ተሞክሮአል። በወሊድ

ጊዜ የሚያጋጥሙ ችግሮች በሙሉ ማለት ይቻላል... በተደጋጋሚ የሚያጋጥሙት በተገረዙ ሴቶች ላይ መሆኑ ሲረጋገጥ

ያልተገረዙት ላይ ግን እጅግ በተራራቀ እና አልፎ አልፎ በሚባል ሁኔታ የሚታይ ነው።
ዶ/ር ወንድሙ ከላይ የተሰጠውን አስተያየት በማጠናከር እንዴት ማስቀረት ይቻላል? ለሚለው፡-
“...በእርግጥ ግርዛቱ በኢትዮጵያ በተለያዩ መስተዳድሮች መፈጸሙ አልቀረም ቢባልም አይነቱ ግን በሶማሌ እና

ተመሳሳይ አካባቢዎች እንደሚፈጸመው 3ተኛው አይነት ማለትም አስከፊው አይደለም፡፡ ባጠቃላይ ግን የትኛውንም

አይነት በየትኛውም ቦታ በሴቶች ላይ ግርዛቱ እንዳ ይፈጸም ለማድረግ ሲፈለግ ብዙ ነገሮችን መነካካት ያስፈልጋል፡፡

ለምሳሌም፡-
ሴቶች እንዳይገረዙ የህግ ከለላ መስጠት፣ ፖሊሲ መንደፍ፣
የሴቶችን የወሳኝነት አቅም ማሳደግ፣
የሴት ልጅ ግርዛት እንዲኖር የሚያስችሉ ምክንያቶች ምን እንደሆኑ በጥናት አረጋግጦ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ፣
ወንዶች በጉዳዩ እንዲሳተፉ ማድረግና የተገረዘች ላግባ አላግብ የሚለውን ሀሳብ ለመወሰን የሚያስችላቸውን አቅም

እንዲያጎለብቱ እና ግርዘትን እንዲያወግዙ ማድረግ፣
የሀይማኖት መሪዎች፣ የቀበሌ፣ የጎሳ አስተዳዳሪዎች የመሳሰሉ ኃላፊነት ቦታ የተቀመጡ ሰዎችም የጉዳዩን አስከፊነት

ተገንዝበው ድርጊቱን ለማስቆም እንዲተባበሩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ባጠቃላይም በተናጠል የሚሰራ ስራ ውጤታማ ስለማያደርግ በተቀናጀ መልኩ የሚመለከተው ሁሉ ተሳትፎ የየበኩሉን

እርምጃ በመውሰድ የሴት ልጅ ግርዛት እንዲቆም ማድረግ ይቻላል፡፡ “ ብለዋል ዶ/ር ወንደሙ ጉዱ፡፡
ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ግርዛት በሶስት ደረጃ ተከፍሎአል፡፡ በኢትዮጵያ ያለውን የግርዛት አይነት ስንመለከት

በሰሜኑ እና በአንዳንድ የሐገሪቱ ክፍል ሲፈጸም የኖረው  አንዱ ሲሆን ሁለተኛውና ሶስተኛው በተለያዩ አካባቢዎች

እንደሶማሌ አፋር ከምባታ አካባቢ ሲፈጸሙ የነበሩ ናቸው፡፡ ሲፈጸሙ /ምየሚለውን አባባል የተጠቀምነው እነዚህ

ድርጊቶች በአሁኑ ወቅት ምን ያህል አይተገበሩም ለሚለው ማረጋገጨ ለጊዜው እጃችን ላይ ስለሌለ ነው፡፡

     - ፈውስም ሆነ ክትባት የለውም፤ እንደ ኢቦላ የከፋ ጥፋት ሊያደርስ ይችላል ተብሏል
                  - በ21 አገራት ተከስቶ፣ 1.5 ሚ ሰዎችን ተጠቂ አድርጓል
       ነፍሰጡር ሴቶችን በማጥቃት የጭንቅላት መጠናቸው አነስተኛ የሆኑና ውስን የአእምሮ እድገት ያላቸው ህጻናት እንዲወለዱ ምክንያት የሚሆነው “ዚካ” የተሰኘ ቫይረስ ወደተለያዩ አገራት በመሰራጨት ላይ መሆኑንና አስቸኳይ እርምጃ ካልተወሰደ እንደ ኢቦላ ቫይረስ በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ የከፋ ጥፋት ሊያስከትል እንደሚችል ተዘገበ።
ዴይሊ ሜይል ከትናንት በስቲያ እንደዘገበው፣ ካለፈው ግንቦት ወር ወዲህ በ21 የካረቢያን፣ የሰሜን አሜሪካና የደቡብ አሜሪካ አገራት የተስፋፋው “ዚካ” ቫይረስ ክፉኛ ካጠቃቸው አገራት መካከል ብራዚል በቀዳሚነት የምትጠቀስ ሲሆን፣ በአገሪቱ ካለፈው ጥቅምት ወር አንስቶ በቫይረሱ ሳቢያ 4ሺህ ያህል የጭንቅላት መጠናቸው አነስተኛ የሆኑ ህጻናት መወለዳቸው ተረጋግጧል፡፡
ቫይረሱን በምትሸከም ትንኝ አማካይነት ወደ ታማሚው የሚገባው “ዚካ” ቫይረስ፣ ምንም አይነት ፈዋሽ መድሃኒትም ሆነ ክትባት እንደሌለው የጠቆመው ዘገባው፣ አሜሪካና ሌሎች አገራት ቫይረሱ በስፋት ተሰራጭቶ የከፋ ጥፋት ከማድረሱ በፊት ክትባቱን ለማግኘት በአፋጣኝ ርብርብ እንዲደረግ ጥሪ ቢያቀርቡም፣ ክትባቱን የማግኘቱ ጥረት አስር አመት ያህል ጊዜ ሊወስድ ይችላል መባሉን ገልጿል፡፡ የአሜሪካ ሳይንቲስቶች የአለም የጤና ድርጅት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የአስቸኳይ ጊዜ የህክምና ባለሙያዎች ኮሚቴ በማቋቋም አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ የጠየቁ ሲሆን፣ በቫይረሱ ክፉኛ የተጠቃችው ብራዚል ፕሬዚዳንት ዲልማ ሩሴፍም የደቡብ አሜሪካ አገራት ቫይረሱን ለመግታት እጅ ለእጅ ተያይዘው እንዲነሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የመካከለኛውና የደቡብ አሜሪካ አገራት፣ ሴቶች በቫይረሱ ሊጠቁ ስለሚችሉ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የማርገዝ ዕቅድ ካላቸው እንዲያራዝሙት መምከራቸው የተጠቆመ ሲሆን፣ የተለያዩ አገራት ነፍሰጡር ሴቶችም ወደ ደቡብ አሜሪካ አገራት እንዳይሄዱ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱ ተነግሯል፡፡
እ.ኤ.አ በ1947 ለመጀመሪያ ጊዜ በኡጋንዳ እንደተገኘ የተነገረለት “ዚካ” ቫይረስ፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአንዳንድ የአፍሪካና የእስያ አገራት ተወስኖ የቆየ ቢሆንም፣ ባለፈው ግንቦት ወር ላይ በብራዚል መከሰቱንና ወደሌሎች የላቲን አሜሪካ አገራት መስፋፋቱንና ከዚያ ጊዜ ወዲህም በአለም ዙሪያ 1.5 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን አይቢ ታይምስ ዘግቧል፡፡
የአውሮፓ የበሽታ መከላከልና ቁጥጥር ማዕከል በበኩሉ፤ “ዚካ” ቫይረስ በቱሪስቶች አማካይነት ወደ አውሮፓ መግባቱንና በቅርቡ በስዊድን አንድ ታማሚ መገኘቱን፣ ሰሞኑንም አንድ የዴንማርክ፣ 6 የእንግሊዝና 2 የጀርመን ዜግነት ያላቸው ሴቶች እንደተገኙ ጠቁሞ ሁለት ጀርመናውያን ሴቶችም በቫይረሱ መያዛቸውን ባለፈው ረቡዕ ማስታወቁን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡

   ሶማሊያና ሰሜን ኮርያ በሙስና አለምን ይመራሉ
    ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተባለው አለማቀፍ ተቋም በአፍሪካ አህጉር ያለው የሙስና ችግር መሻሻል አለማሳየቱንና ሙስና በአህጉሪቱ በሚገኙ አርባ አገራት ውስጥ እጅግ የከፋ ችግር መሆኑን ሰሞኑን ባወጣው አመታዊ ሪፖርት አስታወቀ፡፡
  በአህጉሪቱ የሙስና ችግር ስር እየሰደደ መምጣቱን እንዳስታወቀ የዘገበው ቢቢሲ፣ ሶማሊያ በአፍሪካም ብቻ ሳይሆን በመላው አለም የከፋ የሙስና ችግር ያለባት ቀዳሚዋ አገር ናት መባሉንና ሰሜን ኮርያም በሙስና ከሶማሊያ ጋር የዓለማችን ቀዳሚ ሙሰኛ አገር  መሆኗን ጠቁሟል፡፡
በአህጉሪቱ ሙስና በከፍተኛ ሁኔታ የተስፋፋባቸው አብዛኞቹ አገራት በግጭት ውስጥ ያሉ፣ ፖሊስና ፍርድ ቤትን የመሳሰሉ ተቋማት ደካማ የሆኑባቸውና ገለልተኛ ሚዲያ የሌሉባቸው ናቸው ያለው ተቋሙ፤  ከአፍሪካ አገራት በሙስና ከፍተኛው መሻሻል የታየው በሴኔጋል መሆኑንና፣ አገሪቱ የተለያዩ የጸረ ሙስና ህጎችን ተግባራዊ ማድረጓ በሙስናው ላይ መሻሻል ማሳየቱን አስታውቋል፡፡
በአለማችን ከሶማሊያና ሰሜን ኮርያ በመቀጠል በሙስና መስፋፋት ከሁለተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙት አፍጋኒስታን፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ አንጎላ፣ ሊቢያ፣ ቬንዙዌላ፣ ጊኒ ቢሳውና ሃይቲ ናቸው ተብሏል፡፡አነስተኛ ሙስና አለባቸው ከተባሉት የአለማችን አገራት መካከልም ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ደረጃ የያዙት ዴንማርክ፣ ፊንላንድ፣ ስዊድን፣ ኒውዚላንድና ኒዘርላንድስ እንደሆኑ የተቋሙ አመታዊ የሙስና ሪፖርት አስታውቋል፡፡

   87.4 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት አለው
    87.4 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት ያካበተው የማይክሮሶፍት መስራቹ አሜሪካዊው ቢሊየነር ቢል ጌትስ፣ በዘንድሮው የፈረንጆች አመት 2016 የዓለማችን 50 ቀዳሚ ቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ አንደኛ ደረጃን መያዙን ታይም መጽሄት ዘገበ፡፡
ዌልዝ ኤክስ የተባለውና የአለማችንን ባለጸጎች የሃብት ደረጃ በየአመቱ ይፋ የሚያደርገው ተቋም ከሰሞኑ በድረገጹ ይፋ ያደረገውን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በአመቱ ከቢል ጌትስ በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃን የያዙት ስፔናዊው ቢሊየነር አማኒኮ ኦርቴጋ ሲሆኑ ባለጸጋው 66.8 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት አላቸው፡፡
አሜሪካዊው ቢሊየነር ዋረን ቡፌት በ60.7 ቢሊዮን ዶላር የሶስተኛነት ደረጃን መያዛቸው የተጠቆመ ሲሆን፣ 42.8 ዶላር የተጣራ ሃብት አለው የተባለው የፌስቡኩ መስራች ማርክ ዙክበርግም ስምንተኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን ዘገባው ገልጿል፡፡
በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዕጩ ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡት ማይክል ብሉምበርግ በ42 ቢሊዮን ዶላር ዘጠነኛ ደረጃ መያዛቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ 33.2 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት በማካበት ከአለማችን ሴቶች በሃብት ቀዳሚውን ስፍራ የያዘችው የዎልማርት ኩባንያዋ አሊስ ዋልተን በአለማችን 50 ቀዳሚ ቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ 15ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧንም አመልክቷል፡፡

           በአሜሪካ ኩባንያዎች ታሪክ ከፍተኛውን የሩብ አመት ትርፍ አግኝቷል
     ታዋቂው የቴክኖሎጂ ምርቶች አምራች ኩባንያ አፕል፣ ዝነኛውን የስማርት ፎን ምርቱን አይፎንን ለገበያ ማቅረብ ከጀመረበት እ.ኤ.አ ከ2007 ወዲህ ሽያጩ ለመጀመሪያ ጊዜ መቀነሱን ማስታወቁንና ይሄን ተከትሎም የኩባንያው የአክሲዮን ድርሻ ዋጋ እንደቀነሰ ስካይ ኒውስ ዘገበ፡፡ ኩባንያው በተጠናቀቀው የፈረንጆች አመት የመጨረሻዎቹ ሶስት ወራት 74.8 ሚሊዮን አይፎኖችን በመሸጥ በታሪኩ አነስተኛውን የአይፎን ምርቶች የሽያጭ እድገት ማስመዝገቡንና በቀጣይም ሽያጩ እየቀነሰ እንደሚሄድ ማስታወቁን ዘገባው ገልጧል፡፡
ይሄም ሆኖ ግን፣ አፕል ኩባንያ ምንም እንኳን የአይፎን ምርቶች ሽያጩ ቢቀንስም፣ ባለፈው ሩብ አመት ባገኘው የ18.4 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ትርፉ በአሜሪካ ኩባንያዎች ታሪክ ከፍተኛውን የሩብ አመት ትርፍ ሊያስመዘግብ መቻሉን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
አፕል ኩባንያ የአይፎን ምርቶቹ ሽያጭ መቀነሱን በይፋ ማስታወቁን ተከትሎም፣ ባለፈው ረቡዕ በኩባንያው የአክስዮን ድርሻ ዋጋ ላይ የ4 በመቶ ቅናሽ መመዝገቡንም ዘገባው አብራርቷል፡፡
አይፎን ባለፉት አመታት በስማርት ፎን ገበያ መሪነቱን ይዞ የዘለቀ የአለማችን ታዋቂ ስማርት ፎን መሆኑን ያስታወሰው ዘገባው፣ አፕል ኩባንያ ከአጠቃላይ ገቢው ሁለት ሶስተኛ የሚሆነውን የሚያገኘው ከአይፎን ሽያጩ እንደሆነም ጠቁሟል፡፡

       የምንመገባቸው ምግቦችና መጠጦች ለከፍተኛ ራስ ምታት (ማይግሪን) መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ። በራስ ምታት የመያዝ አጋጣሚዎች በተለያዩ ምክንያቶች (በአየር ፀባይ መለዋወጥ፣ በጠንካራ ሽታዎች፣ በከፍተኛ ብርሃን፣ በሌሎች በሽታዎች ሳቢያ፣ በካፌይን ሱሰኝነት ወዘተ) የሚያጋጥመን ቢሆንም የምንመገባቸው ምግቦችና ወደ አንጀታችን የምንልካቸው የተለያዩ መጠጦችም ለከፍተኛው ራስ ምታት (ማይግሪን) ሊያጋልጡን እንደሚችሉ የአሜሪካ ተመራማሪዎች አስታውቀዋል፡፡ ኔቸር በተሰኘው የምርምር ጆርናል ላይ ተመራማሪዎቹ ይፋ እንዳደረጉት፤የምንመገባቸው ምግቦች ከጭንቅላት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ታይራሚንስና ናይትሪ የተባሉ ኬሚካሎችን በስፋት ይይዛሉ፡፡ እነዚህ ኬሚካሎች ደግሞ የደም ዝውውር ሂደትን በማወክ፣ የራስ ምታትንና የዓይን አካባቢ ህመምን ያስከትላሉ፡፡
ሣይንቲስቶቹ በምርምር አረጋግጠናል ካሏቸውና ከፍተኛ የራስ ምታትን ያስከትላሉ በማለት ከዘርዘሯቸው የምግብና የመጠጥ ዓይነቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
ቀይ የወይን ጠጅ
ቀይ ወይን ለራስ ምታት ህመም የሚያጋልጡ ኮንጀነርስና ታይራሚን የተባሉ ንጥረነገሮችን በብዛት ይይዛል፡፡ ስለዚህም ከሌሎች አልኮል መጠጦች ሁሉ የራስ ምታት ህመምን በማነሳሳት በእጅጉ ይታወቃል። የችግሩ ከፍተኛነት በወሰድነው የቀይ ወይን መጠንና በሽታን በመከላከል አቅማችን የሚወሰን ቢሆንም ቀይ ወይን መጠጣት ለከባድ የራስ ምታት ህመም የሚያጋልጥ መሆኑን አረጋግጠናል ሲሉ ተመራማሪዎቹ ገልፀዋል፡፡ ቀይ ወይን ለራስ ምታት ህመም እንድንጋለጥ የሚያደርገን በአልኮልነቱ ሳይሆን በነጭ ወይን ውስጥ የሌለና በቀይ ወይን ውስጥ ብቻ በሚገኘው ተፈጥሮአዊ ውህድ መነሻነት እንደሆነም እነዚሁ ተመራማሪዎች ጠቁመዋል፡፡  
ቸኮሌት
ቸኮሌትን አብዝቶ መመገብ ለከፍተኛ ራስ ምታት ያጋልጣል፡፡ በተለይም ጠቆር ያለውና ቡናማ ቀለም ያለው የቸኮሌት አይነት ህመሙን በማባባስ ለከፍተኛ ስቃይ የሚዳርግ መሆኑን የጠቆሙት ተመራማሪዎቹ፤ ከካካዋ ቅቤ የሚሰራው ነጭ ቸኮሌት ከራስ ምታት ህመም ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር አለመኖሩን በጥናታቸው ማረጋገጣቸውን ገልፀዋል፡፡
አይስክሬምና ሌሎች ቀዝቃዛ ምግቦች
እንደ አይስክሬም ያሉ በጣም የቀዘቀዙ ምግቦችን በምንመገብበት ወቅት በአፋችን ውስጥ የሚፈጠረው ከፍተኛ ቅዝቃዜ ለከባድ ራስ ምታት ያጋልጠናል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ በአፋችን ውስጥ የተፈጠረው ቅዝቃዜ እስከ ጭንቅላታችን ድረስ ስለሚሰማን እንደሆነም አሜሪካዊያን ተመራማሪዎቹ ጠቁመዋል፡፡
ካፌን
ቡና እና ኮካ መሰል መጠጦች ውስጥ የሚገኘው ካፌን ሱስ የማስያዝ ባህርይ አለው። ይህንን መጠጣት በምናቆምበት ወይንም ሳንጠጣ በምንቆይበት ጊዜ ከባድ የራስ ምታት ህመም ያጋጥመናል፡፡ ካፌይን መውሰድ ያቆሙ ሱሰኞች ለድብርት ስሜት፣ ለመጫጫንና ለከባድ ራስ ምታት ህመም የተጋለጡ ናቸው፡፡ ካፌይኑ የአንጐላችንን ኤሌክትሪካል ሲስተም በማዛባት ሰውነታችን ተጨማሪ የቤታ ንዝረቶችንና አነስተኛ የቴታ ንዝረቶችን እንዲለቅ ያደርገዋል፡፡ ይህ ደግሞ በአንጐላችን ውስጥ የሚካሄደውን ኤሌክትሪካል እንቅስቃሴ በማዛባት ለከፍተኛ የራስ ምታት ህመም እንድንጋለጥ ያደርገናል፡፡
ካፌይን ነክ የሆነ መጠጦችን በጠዋት የመጠጣት ልምድ ያላቸው ሰዎች ካፌይኑ በሕብለ ሰረሰራቸው ውስጥ የሚገኙትን የደምቅዳ ቧንቧዎች በማጥበብ ደም በበቂ መጠን ወደ አንጐል እንዳይገባ ያደርጋል። በዚህ ሣቢያም ከባድ የራስ ምታት ህመም ያጋጥመናል ሲል ተመራማሪዎቹን ዋቢ አድርጐ ኔቸር ዘግቧል፡፡ 

Saturday, 30 January 2016 12:51

ካፌይንና እርግዝና

 ካፌይን ነክ የሆኑ ምግቦችና መጠጦች በእርግዝና ወቅት መውሰድ በፅንሱም ሆነ በእናቲቱ ጤና ላይ ጉዳት እንደሚያስከትል በጥናት መረጋገጡን Neurology የተሰኘ የህክምና ጆርናል ሰሞኑን ዘግቧል፡፡
ነፍሰጡር ሴቶች፤ የማነቃቃትና እንቅልፍን የማባረር ባህርይ እንዳለው የሚታወቀውን ካፌይን በሚወስዱበት ወቅት የልብ ምታቸውና የደም ግፊታቸው በከፍተኛ መጠን እንደሚጨምር   የጠቆመው ዘገባው፤በእናቲቱ ማህፀን ውስጥ የሚገኘው ፅንስም በፕላሴንታ አማካኝነት በሚደርሰው ካፌይን ሳቢያ የልብ ምቱ ሊዛባና ለአደጋ ሊጋለጥ እንደሚችል አመልክቷል።  በተጨማሪም ካፌይኑን አብዝቶ መውሰዱ በተደጋጋሚ ስለሚያሸና ነፍሰጡሯ ሴት ድርቀት እንዲያጋጥማትና ፅንሱ በቂ ፈሳሽ ለማግኘት እንዳይችል እንደሚያደርገው ዘገባው ጠቁሟል፡፡
አብዛኛዎቻችን ካፌይን የሚገኘው በቡናና በለስላሣ መጠጦች ብቻ ውስጥ ነው ብለን እናምናለን ያለው ዘገባው፤ ካፌይን በበርካታ የታሸጉ ምግቦች ውስጥም እንደሚገኝና እነዚህን ምግቦች አዘውትሮ መመገብ ለጤና እክል እንደሚያጋልጥ አመልክቷል፡፡