Administrator

Administrator

    በህፃናት ላይ የሚሰራው ዊዝ ኪድስ፣ በ7 ሃገርኛ ቋንቋዎች የተለያዩ የህፃናት መፅሃፍትን ለማዘጋጀት ማቀዱን ገለጸ፡፡ መፅሃፎቹ በአማርኛ፣ በትግርኛ፣ በሃዲያ፣ በሶማሊኛ፣ በሲዳሞኛ፣ በኦሮምኛና በወላይትኛ ቋንቋዎች የሚዘጋጁ ሲሆን በቀጣይ ሳምንት በሚያካሂደው የ7 ቀናት ወርክሾፕ ላይ የመፅሃፎቹ ዝግጅት ይከናወናል ተብሏል፡፡
ከመስከረም ወር ጀምሮም መፅሃፎቹ ለገበያ እንደሚቀርቡ ተጠቁሟል።  የዊዝ ኪድስ ወርክሾፕ ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ብሩክታዊት ጥጋቡ፤ ድርጅታቸው በአዲሱ ትውልድ ልብ ውስጥ የንባብ ልማድና ፍቅርን ለማስረጽ በማለም ወደ መፅሃፍት ዝግጅት መግባቱን ጠቁመው፣ የህፃናትና  ታዳጊዎች ንባብ መጎልበት ሃገሪቱ ለምትሻው የትምህርት ጥራት አጋዥ ይሆናል ብለዋል፡
በሰባቱ ሃገርኛ ቋንቋዎች የሚዘጋጁት መፅሃፍቱ፤ህፃናትን የሚያነቃቁ የተለያዩ ታሪኮችና ርዕሰ ጉዳዮችን የሚያካትቱ  ይሆናሉ፤ የህፃናቱን እድሜ የሚመጥኑ እንዲሆኑም ይደረጋል ተብሏል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር የዘርፉ ተግዳሮቶች ብሎ ከጠቀሳቸው መካከል አስፈላጊ የሆኑ አጋዥ መፅሃፍት እንደልብ አለመገኘት አንዱ መሆኑን የጠቀሱት ወ/ሮ ብሩክታይት፤ ድርጅታቸው ይህን እጥረት ለመቅረፍ ከትምህርት ስርአቱ ጋር የተጣጣሙ ጥራት ያላቸውን ተነባቢ መፅሀፍት በተለያዩ የሃገሪቱ ቋንቋዎች ማዘጋጀቱን ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ዊዝ ኪድስ በአሁን ወቅት እድሜያቸው ከ3-17 ዓመት ለሆናቸው ህፃናትና ታዳጊዎች 3 የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን እያዘጋጀ ሲሆን ከዚህ ቀደም በ5 ሃገርኛ ቋንቋዎች፣ከ35 በላይ የህፃናት መፅሃፍት አሳትሟል፡፡

የታዋቂው ፖለቲከኛ ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም“አዳፍኔ” ፍርሃትና መክሸፍ” የተሰኘ “መጽሐፍ
ባሳለፍነው ሣምንት ለንባብ በቅቷል፡፡ደራሲው ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም “ሐውልት”በሚል ርዕስ ባሠፈሩት የመታሰቢያ ገፅ ጽሑፋቸው፤ለደጃዝማች ሃይሉ ከበደ፣ ዋጋቸውን ላላገኙለኢትዮጵያ አርበኞች፣ የፋሽስት ኢጣሊያን ወረራለመቋቋም በእንግሊዝ አገርና በአውሮፓ በሙሉየተደረገውን የፖለቲካ ትግል የነጭ ዘረኛነትን አጥሮችሁሉ ተሻግረው ሰው በመሆን በፊታውራሪነትለመሩት ይዘሮ ሲሊቪያ ፓንክረስት፣ የዜግነትግዴታቸውን በአውሮፓ በተለያዩ መንገዶች ለፈፀሙለፀሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃብተወልድ፣ ለአብዲሣ አጋእና ለዘርአይ ደረስ ይሁን ብለዋል፡፡መጽሐፉ የተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እናታሪካዊ ጉዳዮችን የሚተነትን ሲሆን በ280 ገፆችተዘጋጅቶ በ69 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

በማህበራዊና ትምህርታዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር የምትዘጋጀው “ተምሳሌት” መጽሔትና ዌብሳይት የምረቃ ሥነስርዓት ዛሬ ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ በዋቢሸበሌ ሆቴል ሆቴል ይካሄዳል። መጽሔቷ ባለሙሉ ቀለም ህትመት መሆኗን የገለፁት አዘጋጆቹ፤ በአዲስ አበባና በዙሪያው ባሉት ከተሞች እንደምትሰራጭም ገልፀዋል፡፡ ተምሳሌት ዌብሳይት ከመጽሔቷ ጋር በተጓዳኝ አገልግሎት እንደሚሰጥም ታውቋል፡፡
በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይ “ተምሳሌት” መጽሔት እና ዌብሳይትን የማስተዋወቅ ፕሮግራም እንዲሁም የፓናል ውይይት ይካሄዳል ተብሏል፡፡


በአብነት ስሜ የተጻፉት “የቋንቋ መሰረታዊያን” እና “ሳይኪና ኪዩፒድ” የተሰኙ ሁለት መጽሃፍት ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ ለገበያ መብቃታቸውን ጸሃፊው በተለይ ለአዲስ አድማስ ገለጸ፡፡
በቋንቋ ምንነት፣ አመጣጥ፣ የመማር ሂደት፣ ተግባራትና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥነውና 407 ገጾች ያሉት መጽሃፉ፤ በ90 ብር ከ99 ሣ. በአዲስ አበባ እና በተለያዩ ክልሎች በመሸጥ ላይ ይገኛል፡፡ በስድስት ክፍሎችና በአስራ አራት ምዕራፎች የተከፋፈለው መጽሃፉ፣በቋንቋ እና እሳቦት፣ በቋንቋ ሳይንሳዊ ጥናት እንዲሁም በጽህፈት ታሪክ ዙሪያ በጥናት የተደገፉ መረጃዎችንና ትንተናዎችን አካትቷል ተብሏል፡፡
ለገበያ የቀረበው ሌላኛው የደራሲው ስራ “ሳይኪና ኪዩፒድ” የተሰኘ የህጻናት መጽሃፍ ሲሆን አስር ተረቶች፣ አራት መቶ እንቆቅልሾችና አንድ የእንግሊዝኛ ልቦለድ አካትቶ የያዘ ነው፡፡   
አብነት ስሜ ከዚህ ቀደምም “የኢትዮጵያ ኮከብ” እና “ፍካሬ ኢትዮጵያ” የተሰኙና በኮከብ ትንበያ፣ ትንተና እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ መጽሃፍትን ለንባብ ማብቃቱ ይታወሳል፡፡





በፌስቡክ  ለአመታት የተለያዩ ጽሁፎችን በማቅረብ የሚታወቁ ጸሃፊያን በጋራና በተናጠል ያሳተሟቸውን የግጥም፣ የአጫጭር ልቦለዶችና የወጎች ስብስብ መጽሐፍትን ለንባብ እያበቁ ነው፡፡
የአምስት ገጣሚያንን ስራዎች ያሰባሰበው “መስቀል አደባባይ” የተሰኘ የግጥም መድበል ባለፈው ማክሰኞ ገበያ ላይ የዋለ  ሲሆን፣ በፌስቡክ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሂሶችንና ወጎችን በማቅረብ ተወዳጅነትን ያተረፈችው  ህይወት እምሻውም “ባርቾ”በሚል ርዕስ  የአጫጭር ልቦለዶችና የወጎች ስብስብ መጽሃፍ አሳትማለች፡፡
በግጥም መድበሉ የአሌክስ አብርሃም፣ ዩሃንስ ሃብተ ማርያም፣ ረድኤት ተረፈ፣ ዮናስ አንገሶም ኪዳኔ እና ፈቃዱ ጌታቸው ግጥሞች የተካተቱ ሲሆን፣ ገጣሚያኑ እያንዳንዳቸው አስር ግጥሞችን አቅርበዋል፡፡ 150  ገጾች ያሉት የግጥም መድበሉ፣ በ45 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡
የግጥም ስራዎቹን በማሰባሰብ ለህትመት ያበቃው ገጣሚና ደራሲ አሌክስ አብርሃም በተለይ ለአዲስ አድማስ እንደገለጸው፣ መስቀል አደባባይ በቀጣይም በቅጽ ተከፋፍሎ ለህትመት የሚበቃ ሲሆን፣ በፌስቡክም ሆነ በተለያዩ መድረኮች የሚታወቁ ወጣትና አንጋፋ ጸሃፊያንን የግጥም፣ የወግና የልቦለድ ስራዎችን የሚያካትት ይሆናል፡፡ የመስቀል አደባባይ ሁለተኛ ቅጽ ዝግጅት በከፊል መጠናቀቁንም አሌክስ አብርሃም ጠቁሟል፡፡
በሌላ በኩል ወጎችን፣ አጫጭር ልቦለዶችንና በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ መጣጥፎችን  በፌስቡክ በስፋት በማቅረብ የምትታወቀውና በርካታ ተከታዮችን ያፈራችው ህይወት እምሻው፣ የመጀመሪያ ስራዋ የሆነውን ባርቾ የተሰኘ የወጎችና የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ መጽሃፍ፣ ለህትመት አብቅታለች፡፡ 31 ወጎችን፣ 8 ልቦለዶችንና 13 የመሸጋገሪያ አጫጭር ልቦለዶችን ያካተተውና 256 ገጾች ያሉት መጽሃፉ፣ የመሸጫ ዋጋው 60 ብር እንደሆነ ደራሲዋ ለአዲስ አድማስ የገለጸች ሲሆን የፊታችን ሐሙስ  በዋቢ ሸበሌ ሆቴል እንደሚመረቅ ተናግራለች፡፡
በዕለቱ ከ11፤30 ሰኣት ጀምሮ በሚካሄደው የምረቃ ስነስርዓት ላይ በመጽሃፉ ከተካተቱት ታሪኮች አንዱ በአጭር ድራማ መልክ ለታዳሚዎች የሚቀርብ ሲሆን፣ የሙዚቃና የግጥም ስራዎችም ይቀርባሉ፡፡
ፌስቡክ ለበርካታ ወጣትና አንጋፋ ጸሃፍያን ስራዎቻቸውን ለአንባቢ ለማድረስ ሁነኛ አማራጭ እየሆነ የመጣ ሲሆን በማህበራዊ ድረገጹ ላይ በመጻፍ የሚታወቁ በርካቶችም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስራዎቻቸውን በመጽሃፍ መልክ እያሳተሙ በስፋት ለንባብ ማብቃት ጀምረዋል፡፡
በፌስቡክ ከሚታወቁና ከዚህ ቀደም ስራዎቻቸውን ለህትመት ካበቁ ጸሃፊያን መካከል፣ አሌክስ አብርሃም፣ በረከት በላይነህ፣ ሮማን ተወልደ ብርሃን፣ ዮሃንስ ሞላ፣ ሃብታሙ ስዩም፣ ቢኒያም ሃብታሙ፣ ትዕግስት አለምነህ፣ ሄለን ካሳ፣ ዮናስ አንገሶም ኪዳኔ፣ ሜሮን አባተ፣ ብሩክታዊት ጎሳዬ፣ ስመኝ ታደሰ እና ሌሎችም ይገኙባቸዋል፡፡

Saturday, 04 July 2015 10:34

የኪነት ጥግ

(ስለ ፋሽን)
- ጎበዝ የሆነች ሞዴል ፋሽንን በ10 ዓመት
ልትቀድመው ትችላለች፡፡
ይቭስ ሴይንት ሎውሬንት
- እኔ ፋሽን አልሰራም፡፡ ራሴ ፋሽን ነኝ፡፡
ኮኮ ቻኔል
- ልብሶችን ዲዛይን አላደርግም፡፡ እኔ ዲዛይን
የማደርገው ህልሞችን ነው፡፡
ራልፍ ሎረን
- ፋሽን ያልፋል፤ ስታይል (ሞድ) ዘለዓለማዊ
ነው፡፡
ይቭስ ሴይንት ሎውሬንት
- ሴቶች የሚፈልጉትን አውቃለሁ፡፡ የእነሱ
ፍላጎት መዋብ ነው፡፡
ቫሌንቲኖ ጋራቫኒ
- ሽቶ የማትቀባ ሴት ተስፋ የላትም፡፡
ኮኮ ቻኔል
- ስታይል ሳትናገሩ ማንነታችሁን
የምትገልፁበት መንገድ ነው፡፡
ራሄል ዞ
- አንድ ሰው አይተኬ ለመሆን ምንጊዜም
ከሌላው መለየት ይኖርበታል፡፡
ኮኮ ቻኔል
- አለባበስ የኑሮ ዘይቤ ነው፡፡
ይቭስ ሴይንት ሎውሬንት
- እያንዳንዱ ትውልድ በድሮ ፋሽን ይስቃል፤
አዲሱን ግን የሙጥኝ ብሎ ይከተለዋል፡፡
ሔነሪ ዲቪድ ቶሬዩ
- የፋሽን ዲዛይነር ብሆንም ሻንጣዬን በብዙ
ቁሳቁሶች አልሞላም፡፡
ሪም አክራ
- ልብሶችን በማጥለቅና በወጉ በመልበስ
መካከል ልዩነት አለ፡፡
ዋየኔ ክሪሳ
- ግሩም ልብስ ከጥሩ ጫማ ጋር ያምራል፡፡
ሁለቱን መነጠል አትችልም፡፡
ዋይኔ ክሪሳ
- ምንም እንኳን የወንዶች ዓለም ቢሆንም
ሴት መሆኔን እወደዋለሁ፡፡ ወንዶች ቀሚስ
መልበስ አይችሉም፤ እኛ ግን ሱሪ መልበስ
እንችላለን፡፡
ዊትኒ ሂዩስተን
- ለልጃገረድ ተስማሚውን ጫማ ስጧት፤
ዓለምን ድል ትነሳለች፡፡
ማርሊን ሞንሮ
- የማስበው በጥቁር … ነው፡፡
ጋሬዝ ፑግ

Saturday, 04 July 2015 10:30

የፀሐፍት ጥግ

ኑርሁሴን
ሂሮዬ ሺማቡኩሮ
(ስለ ሃያስያን)
- ለማንም ሙገሳም ሆነ ወቀሳ ትኩረት አልሰጥም።
እኔ የምከተለው ስሜቴን ብቻ ነው፡፡
ዎልፍጋንግ አማዴዩስ ሞዛርት
- መፃፍ የሚችሉ ይፅፋሉ፤ መፃፍ የማይችሉ
ይተቻሉ፡፡
ማክስ ሃውቶርን
- አብዛኞቻችን ዘንድ ያለው ችግር በትችት ከመዳን
ይልቅ በሙገሳ መጥፋትን መምረጣችን ነው፡፡
ኖርማን ቪንሰንት ፒል
- ወጣቶች ሞዴሎችን እንጂ ሃያስያንን
አይፈልጉም፡፡
ጆን ውድን
- ሂስ የሚጠይቁ ሰዎች የሚፈልጉት ውዳሴ ብቻ
ነው፡፡
ሶመርሴት ሟም
- ልብህ ትክክል መስሎ የተሰማውን አድርግ፡፡
ትችት እንደሆነ አይቀርልህም፡፡
ኢልኖር ሩስቬልት
- አንድ ሰው ሌሎችን ለማውገዝ ከማሰቡ በፊት
ራሱን ለረዥም ጊዜ መመርመር አለበት፡፡
ሞሌር
- ሃያሲ ስንዝር ከሰጠኸው ተውኔት ልፃፍ ይላል፡፡
ጆን ስቴይንቤክ
- ሂስ የተወለደው ከኪነጥበብ ማህፀን ውስጥ
ነው፡፡
ቻርልስ ባውድሌይር
- ጠንካራ አስተያየቶች የሚሰነዘሩት በሚወዱህ
ሰዎች ብቻ ነው፡፡
ፌዴሪኮ ማዮር
- ሃያሲያን በሥነ ፅሁፍና በሥነ ጥበብ ዘርፍ
ያልተሳካላቸው ሰዎች ናቸው፡፡
ቤንጃሚን ዲስራኤሊ
- አንበሳም ቢሆን ራሱን ከዝንቦች መከላከል
አለበት፡፡
የጀርመናውያን አባባል
- የጎረቤትህን ቤት ብታቃጥል ያንተን ቤት የተሻለ
ገፅታ አያጎናፅፈውም፡፡
ሎ ሆልትዝ
- ሃያስያን ለሚናገሩት ትኩረት አትስጥ፡፡ ለሃያሲ
ክብር ፈፅሞ ሃውልት ቆሞለት አያውቅም፡፡
ዣን ሲቤሊዩስ

ብዙ የናፈቁን ዜናዎች አሉ!

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሁለቱ ልጆች እያወሩ ነው፡፡ አንደኛው ልጅ ምን ይላል… “አባዬ የሁሉም ነገር ዋጋ እየጨመረ ነው ሲል ሰማሁት፡፡”
“ምንድነው የጨመረው?”
“የምግብ፣ የልብስ፣ የቤት ኪራይ ሁሉ ጨምሯል አለ፡፡ ደግሞ ምን አለ መሰለህ!”
“ምን አሉ?”
“የሆነ ነገር ቁጥሩ ቀንሶ ማየት ጓጉቻለሁ አለ፡፡”
ጓደኝየው ምን ቢለው ጥሩ ነው… “ግዴለም፣ የአንተን ሰርተፊኬት ሲያዩ በደንብ የሚቀንስ ቁጥር ያገኛሉ፡፡
ሀሳብ አለን…የኑሮ ማስተካከያ ይደረግልን፡፡ ልክ ነዋ…ለምንም ነገር ማስተካከያ ይደረግ የለም አንዴ!
እናላችሁ…ሥጋ እንኳን በሩብ ኪሎ መሸጥ መጀመሩን ወዳጄ ሲያጫውተኝ ነበር፡፡ እየደረስን ያለንበትን ዘመን እዩልኝማ፡፡ ገና በኪሎና በግራም መለካቷ ቀርቶ በጉርሻ ሊሆን ይችላል፡፡ “ሁለት ጉርሻ ሥጋ ስጠኝ…” ማለት እንጀምር ይሆናል! አይሆንም የሚባል ቃል እየጠፋ ያለባት አገር ነቻ!
እናማ…የኑሮ ማስተካከያ ይደረግልን፡፡
ስሙኝማ…በቲቪ ላይ እኮ የምግብ አሠራር እያየን መጎምጀት ከተውን ከረምን፡፡ ልክ ነዋ… ቦምቦሊኖ ባረረብን ዘመን የምናየው ሁሉ እንቁልልጭ ሆነብና!
የምር ግን… አለ አይደል… የፈጠራ ጊዜ አሁን ነው። በሬድዮና በቲቪ ስለምግብ አሠራር የምታስተምሩን ፈጠራ ቢጤ ጨምሩበታ፡፡ ለምሳሌ ‘ያለበርበሬ ቀይ ወጥን መሥሪያ ዘጠኝ ዘዴዎች’ አይነት ነገር። ደግሞላችሁ… ‘ሹሮ ሽንኩርትና ዘይት ሳይገባባት ውሀና ሹሮዋ ብቻ ተበጥብጠው ጣት የሚያስቆረጥም ወጥ የመሥሪያ ምስጢሮች…’ የሚል ፈጠራ፡፡ ልክ ነዋ…ትንሸ ቆይተን ጣት የምንቆረጥመው ምግብ ስለጣፈጠን ሳይሆን ጉርሻችን ከማነሷ የተነሳ ጣት እየተቀላቀለችብን ሊሆን ይችላል፡፡
ሀሳብ አለን…የምግብ አሠራር የቲቪ ትምህርቱ በመደብ ይከፋፈልልን፡፡ አለ አይደል…
‘በወር አንዴ ሥጋ ለሚበሉ…’
‘በወር አንዴ ሥጋ በህልማቸው ለሚያዩ…’
‘በወር አንዴ ሥጋ የሚባለው ቃል መዝገበ ቃላት ላይ መኖሩ ትዝ ለሚላቸው…’  በሚል መደብ ይከፋፈልልን። ወይንም እንደ ግብር ከፋዮች ‘ሀ’ ‘ለ’ እና ‘ሐ’ ተብለን እንከፋፈል፡፡፡ “የዛሬው የምግብ አሠራር ለ‘ለ’ ምድቦች ብቻ የሚሆን ነው…” ስንባል ቁርጣችንን አውቀን አርፈን እንቀመጣለና!
እናላችሁ… ዘንድሮ… አለ አይደል… “አንተ ምነው ባለቤትህ ከሳችብኝ!” ብሎ አስተያየት አሪፍ አይደለም። አሀ…ነገርዬው ሁሉ ‘ጣራ ነክቶ’ እንዴት ትወፍር! በፊት እኮ “በሽታ እንኳን ያወፍራል…” ይባል ነበር፡፡ ዘንድሮ ኩሽናው ሁሉ ምነዋ ይሄን ያህል መአዛ የለውሳ!
እናማ… “አንተ ምነው ባለቤትህ ከሳችብኝ!” ብሎ አስተያየት ‘ወቅቱን ያላገናዘበ’ ይሆናል፡፡ አሀ… በብር ሦስትና አራት ይገዛ የነበረ እንቁላል አንዱ ሦስት ብር ከሀምሳ ሳንቲም ምናምን ሲሆን እንዴት ሆና ‘ሥጋ’ ታውጣ፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ባል ራሱ ‘አርፎ አይቀመጥ’!  ቂ…ቂ…ቂ….
እኔ የምለው…“ዳየት ላይ ነኝ…” ምናምን የምትሉ እንትናዬዎችን ሌላ ሰበብ አምጡማ፡፡ ኑሮ ራሱ ሁላችንንም ‘ዳየት ላይ’ አድርጎናላ! እናማ…‘ዳየት ላይ’ መሆኑ የግዴታ እንጂ የውዴታ ባልሆነበት…“ዳየት ላይ ነኝ…” አይነት ምክንያት አይሠራም፡፡
ስሙኝማ…በፊት የሆነ ነገር ዋጋው ጣራ ነካ ሲባል የሆነ መሥሪያ ቤት ለ‘ፐብሊክ ኮንሰምሺን’ ለሚሉት ነገርም ቢሆን… “የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት ሥራዎች እየተሠሩ ነው…” ምናምን  የሚባለው ‘ልብ አንጠልጣይ ልብ ወለድ’ እንኳን አሁን፣ አሁን እየቀነሰ ነው፡፡
“እነሱ አንድ ነገር ያደርጉልናል…ዋጋውን ወደ ቦታው መልስው ያረጋጉልናል…” ስንል ተስፋ ቆረጡ እንዴ! አሀ…ወንበር ብቻ ሳይሆን ዋጋም ይረጋጋልና!
እናማ…“በተለይ በምግብ ሸቀጦች ላይ የሚደረገውን ምክንያተ ቢስና ኢፍትሀዊ ዋጋ ንረት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስተካከል የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ሊጀመር ነው…” አይነት ዜና መስማት ናፍቆናል፡ ልከ ነዋ…በሆዳችን ‘ድንቄም ተወሰደ!’ ብንል እንኳን ለጊዜውም ቢሆን ለጆሯችን አሪፍ ዜማ ይሆናላ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ልንሰማቸው የናፈቁን ዜናዎች መአት ናቸው…
‘ከወሩ መግቢያ ጀምሮ በመላ አገሪቱ የጤና አገልግሎት ሙሉ፣ ለሙሉ ነጻ ሆኗል…’
‘ከመጪው ሰኞ ጀምሮ አንድ ኩንታል ጤፍ ከአምስት መቶ ብር በላይ ሲሸጥ የተገኘ ነጋዴ ፈቃዱ ተነጥቆ ከመፋቂያ በላይ የሆነ ምርት እንዳይሸጥ የአራተ ዓመት እገዳ ይጣልበታል…’
‘በበዓላት ወቅት ቀበሌዎች ቤት ለቤት እየዞሩ ኪሎ ቅቤ በሀያ አምስት ብር ማከፋፈል ይጀምራሉ…’
‘የአንድ ኪሎ በርበሬ ከፍተኛ ዋጋ አሥራ አምስት ብር ከሃያ አምስት ሳንቲም እንዲሆን እንትን መሥሪያ ቤት ወሰነ…’
‘ከፍተኛ ባለስልጣኖች በአሥራ አምስት ቀን አንድ ጊዜ መርካቶና ሾላ ገበያ እየሄዱ ራሳቸው እንዲገበዩ የውዴታ ግዴታ ተጥሎባቸዋል…’ (ያን ጊዜ…አለ አይደል…“እንዲህም የሚኖር ሰው አለ!” ይሉ ነበር፡፡)
እንደ እነዚህ አይነት ‘ዜናዎች’− “ካልተረጋገጡ የወሬ ምንጮች…” እንኳን− የምንሰማበት ዘመን ይመጣ ይሆን! መመኘትም የ‘ክላስ’ ጉዳይ እስኪሆን ድረስ እኛም እንመኝ እንጂ!
ካነሳነው አይቀር…ሌሎች የናፈቁን ዜናዎች አሉ…
‘እንትንና እንትን ድርጀቶች ከእንግዲህ መዘላላፍና ትርፍ ቃላት መወራወር ትተው ቁም ነገር ላይ ለማተኮር ተስማምተዋል…’
‘ባለስልጣኖች ለሜዲያ መግለጫ በሚሰጡበት ጊዜ የማስፈራሪያና የንቀት ቃላት ሲናገሩ ቢገኙ የተሰጣቸውን ወንበርና የተሰጣቸውን ቤተ ይነጠቃሉ…’ (ቂ…ቂ…ቂ…. ታየኝ!)
‘በሆነ ባልሆነው ትንሹንም ትልቁንም የሚዠልጡ ስነ ስርአት አስከባሪዎች በእጃቸው አርጩሜ እንኳን እንዳይዙ ይከለከላል…’
አሪፍ አይደል! ያኔ እንዴት አይነት ‘ነፍስ የሆንን’ ሰዎች ይወጣን ነበር፡፡
ደግሞላችሁ ሌሎች የናፈቁን ዜናዎች አሉ…
‘የሰው ሚስት የሚያማግጥ ጭቃ ሹም ሆነ ምስለኔ አይደለም ሴት፣ የሴት ፎቶ የማያይበት በረሀ ለአምስት ዓመት እንዲቀመጥ ይገደዳል…’
‘ሥራ አስኪያጆች ኤክሲኪዩቲቭ ሴክሬታሪዎችን ፊት ለፊት በአካል ሳይሆን በስልክ ብቻ እንዲያገኙ ተወሰነ…’ (ቂ…ቂ…ቂ…)
‘በየመጠጥ ቤቱ መቶና መቶ ምናምን ብር ለመክፈል የመለስተኛ መሥሪያ ቤት ተከፋይ ደሞዝ የሚመስል የብር መአት የሚመዙ ሰዎች ሌላው ተገልጋይ ላይ ለሚደርሰው ማንኛውም የብሽቀት፣ የመጎምጀት፣ የደም ብዛት ችግር ሁሉ ተጠያቂ ይሆናሉ…’
‘ከእንትናዋ ጋር የምትሄደውን እንትናዬ ከሦስት ሰከንድ በላይ ትክ ብለው የሚያዩ ባለመኪኖች መኪናቸውን ተነጥቀው ለአሥራ አንድ ወር በእግራቸው ብቻ እንዲሄዱ ይደረጋሉ…!’ የሚል ዜና ናፍቆናል፡፡ (እግረኞቹ ሁሉ እየተሳቀቁ አሳዘኑና!)
መአት ልንሰማቸው የምንፈልጋቸው ዜናዎች አሉ፡፡ “ሰበር ዜና…ዋጋዋ አልቀምስ ብሎ ሃያ ምናምነኛ ፎቅ ላይ የወጣችው ቲማቲም አንድ ኪሎ በብር ተሀምሳ እንደገባች ተገለጸ…” አይነት ዜና መስማት ናፍቀናል፡፡
“ከፍተኛ የአገሪቱ ባለስልጣናት በመርካቶ፣ በአትክልት ተራና በሾላ ገበያ ባደረጉት ጉብኝት ባዩት የምግብ ግብአቶች ዋጋ ከፍተኛ ድንጋጤ እንዳደረባቸው ምንጮቻችን ገለጹ፡፡ በተለይ አንዱ ባለስልጣን… ‘ኑሮ ይህን ያህል መክበዱን በህልሜም ጠርጥሬ አላውቅም፡፡ ዕንባዬ ነው የመጣው…’ ማለታቸው ተዘግቧል…” አይነት ዜና ናፍቆናል፡፡
የኑሮ መክበድን በተመለከተ ብዙ ልንሰማቸው የምንፈልጋቸው ዜናዎች አሉ፡፡
የከበደውን ኑሮ የሚያቀልልን ዘመን ያፍጥልንማ!
ጀርባችን ሳይሰበር፣ ሰማይ የወጣውን የሸቀጦች ዋጋ የሚሰብር ተአምር ይላክልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

ከዕለታት አንድ ቀን እመት ጦጢት ምግብ ስትሰራ እንስሳት አገኟትና፤
“እመት ጦጢት?”
“አቤት” አለች፡፡
“ሽሮና በርበሬ ማን ያመጣልሻል?” አሏት፡፡
“ባሌ” አለች
“ከየት ያመጣል?”
“ሠርቶ፣ ወጥቶ፣ ወርዶ”
“ሰርቆስ እንደሁ የሚያመጣው በምን ታውቂያለሽ?”
“አምነዋለሁ”
“ቂቤስ ከየት አመጣሽ?”
“ባሌ አመጣልኝ”
“ከየት ያመጣል?”
“ሰርቶ፣ ወጥቶ - ወርዶ”
“ሰርቆስ እንደሁ በምን ታውቂያለሽ”
“ባሌን አምነዋለሁ”
“ከዕለታት አንድ ቀን ሌላ ጦጢት ይዞብሽ ቢመጣስ?”
“ተገላገልኳ! አጋዥ አገኘሁ፡፡ እሷ ምግብ ትሰራለች፤ እኔ እሱን አቅፌ እተኛለሁ”
“እስከ ዛሬ ጦጣ ብልጥ ናት ሲባል ነበር፡፡ ለካ አንደኛ ደረጃ ጅል ነሽ?!”
“ጅልስ እናንተ፡፡ እየሰረቃችሁ መዋችላሁ አንሶ ወደሌላ ለማዛመት ሌብነት፣ ከቤት - ቤት ይዛችሁ የምትዞሩ!! በሉ ሌብነታችሁን ሌላ ቤት ይዛችሁልኝ ሂዱ!” ብላ ከቤት አስወጣቻቸው፡፡
*   *   *
እንደ ጦጣ አለመመቸት ብልጥነት ብቻ ሳይሆን ብልህነትም ነው!
ጥርጣሬ፣ ቅጥፈትና ሌብነት አንድ ህብረተሰብ ውስጥ ሲነግሥ ዕድገት መቀጨጩ አሌ አይሉት ነገር ነው፡፡ የተዋሃደውን ለመነጣጠል፣ የተጋባውን ለማፋታት፣ የተደራጀውን ለመበታተን መሞከርን ያህል እኩይ ተግባር ያጥጣል። የተማረው እንዳልተማረ ይናቃል፡፡ የመንገዱን መነሻ እንጂ መድረሻውን አለማስተዋል የዕለት የሰርክ ህፀፅ ይሆናል፡፡
ሮበርት ግሪን፤
“ፍፃሜውን የማትገምተው ነገር አትጀምር” ይለናል፡፡
ያቀድነው ዕቅድ ከየት ያስጀምረናል? ወዴት ያመራናል? ወዴትስ ያደርሰናል? ግብዐቶቹ ምን ምንድናቸው? ብሎ በቅጥ በቅጡ እያዩ መከታተል፤ እናም እፍፃሜ ሳይደርስ ሌላ ምዕራፍ አለመጀመር፣ በተለይ ትግል ውስጥ ለገባ ቡድን፣ ስብስብ፣ ማህበር ወይም ድርጅት፤ ዋና ነገር ነው፡፡ ሁለተኛው በቂ ዝግጅት ማድረግ ነው። ባጭሩ በአገርኛ ግጥም፡-
“ቀድሞ ነበር እንጂ፣ መጥኖ መደቆስ
አሁን ምን ያደርጋል፣ ድስት ጥዶ ማልቀስ” የሚለውን ማስታወስ ነው፡፡
“ሌሎች አዝመራውን ስለሚሰበስቡት ሰብል ማለም ከንቱ ህልም ነው፡፡ ይልቅ ራስህ መጨረሻውን የምትጨብጠውን ህልም ዛሬውኑ አልም!” ይላሉ አበው፡፡
ህልማችን ዕውን እንዳይሆን እፊታችን የሚደቀኑትን እንቅፋቶች ለይቶ ማስቀመጥ፣ እንቅፋቶቹን አልፎ ለመሄድ የሚገባውን ያህል አቅም መፍጠርና ጉልበትን ማጠራቀም፤ ሳይታክተን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ፣ በፅናት መጓዝ፤ ያስፈልጋል፡፡ ምንጊዜም ቢሆን ሙሉ በሙሉ ማሸነፍና ሙሉ ለሙሉ መሸነፍ አለመኖሩን፣ ማመንና ይልቁንም፤ ጠንካራና ደካማ ጎን ሁሌም መኖሩን ማስተዋል የተሻለ ዕውነታ ነው፡፡
ሁኔታዎች ተለዋዋጭ መሆናቸውንና አዲስ አሸናፊ ምንጊዜም መብቀሉን ለአፍታም አለመዘንጋት ነው፡፡ ተስፋ አለመቁረጥ የሚመነጨው ከዚህ ዕሳቤ ነው። ያለ ሁሌም የሚኖር ይመስለዋል፤ ይላሉ አበው፡፡ ሆኖም ያልፋል፤ ማለታቸው ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የፍትህ አካላት፣ የአስተዳደር ወኪሎች እና ፍርድ ቤቶችም ጭምር፣ ከህብረተሰብ ጋር የሰፋ ግንኙነት መፍጠርና በመዋቅርም፣ በመንፈስም የበለጠ ዲሞክራሲያዊነት እንዲኖራቸው መጣር፤ ዛሬ የዓለም ሁሉ ትጋት ነው፡፡ ከዚህ የድርሻችንን መውሰድ ነው፡፡ ክሊንተን ሮዚተር የተባለው ምሁር፤ “አገር ያለ ዲሞክራሲ፣ ዲሞክራሲ ያለ ፖለቲካ፣ ፖለቲካ ያለ ፓርቲዎች አይኖርም” ይለናል። ይህን እንዲሰራ ለማድረግ ግን ቀና ልቡና ይጠይቃል፡፡ ጤናማ ፓርቲና ጤናማ ፖለቲካዊ ስነ - ልቦናም እነዚህ ውስጥ ወሳኝ ናቸው፡፡ ያሉት ቀና ፓርቲዎች እጅግ ጥቂት ናቸው፡፡  ያሉንን የፖለቲካ ፓርቲዎች ካመናመንንና ካጠፋናቸው     “ከርከሮ አንዲት ፀጉር አለችው፣ እሷን ለማጥፋት ይተሻሻል” የሚለውን ተረት በታሳቢነት ያዝን ማለት ነው፡፡

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ መቀመጫ የኾነችው የቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፥ ጥፋቶች ታርመው ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አሰራር እንዳይሰፍን በሚሹ ጥቂት የአስተዳደር ሰራተኞች፣ በህይወት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ከአድማ ያልተናነሰ እንቅስቃሴ እየተደረገበት መኾኑን አስታወቀ፡፡ የመልካም አስተዳደር ጅምሩን ከፍጻሜ ለማድረስ የቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ የአስተዳደር ክፍሎች እገዛ እንዲያደርጉለትም ጠይቋል፡፡
ለብክነት፣ ለዘረፋ እና ለሙስና ከተመቻቸ አሰራር እንዲሁም በገዳሟ ቀደም ሲል ከመልካም አስተዳደር ዕጦት የተነሳ የተከሰቱ ጥፋቶችን ለማረም ልዩ ልዩ መመሪያዎችንና የውስጥ ደንብ ረቂቆችን ማዘጋጀቱን ሰበካ ጉባኤው ለሀገረ ስብከቱ የዋና ሥራ አስኪያጅ ጽ/ቤት ባቀረበው ሪፖርት ገልጿል፡፡ ይኹንና ለቁጥጥር የሚያመች ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበትን አሰራር ለማስቀጠልና ለማስፈጸም እንዳይቻል ጥቂት የአስተዳደር ሰራተኞች ማኅበረ ካህናቱን በመከፋፈል፣ “ከሰበካ ጉባኤው ጋር ተባብራችኋል” በሚል ከሥራና ከደመወዝ በማገድ፣ በማስጠንቀቂያዎች በማሸማቀቅ፣ መረጃዎችን በማዛባት የሚፈጥሩት ግጭት ኹኔታውን አስቸጋሪ አድርጎብኛል ብሏል፡፡
መመሪያዎቹ እና የውስጥ ደንቡ “ቀድሞ ሲዘርፉበት የነበረውን አካሄድ የሚያስቀር እና አለአግባብ የሚያካብቱትን ጥቅም የሚያስቆም ነው” ያለው ሰበካ ጉባኤው፤ ለህይወት አስጊ ባላቸው ተፅዕኖዎች ሳቢያ በገዳሟ ጽ/ቤት ተገኝቶ በሰላማዊ መንገድ ስራዎቹን ለማከናወንና ሐላፊነቱን ለመወጣት ከማይቻልበት ደረጃ መድረሱን በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡  
እንደ ሰበካ ጉባኤው ገለጻ፥ ቃለ ዐዋዲውን መሰረት አደርጎ ለቤተ ክርስቲያን በሚበጅ መልኩ ያዘጋጃቸው የሰው ኃይል አስተዳደር፣ የፋይናንስ፣ የንብረት እና የግዥ መመሪያዎች በጽ/ቤቱ ልዩ ትርጉም እየተሰጣቸው በመደበኛ ስብሰባ ላይ እንኳን አስተያየት እንዳይሰነዘርባቸው  ዕንቅፋት ተፈጥሯል፤ ማኅበረ ካህናትና ሰራተኞች ገንዘብንና ንብረትን የሚቆጣጠር አካል ቢመርጡም፣ የቆጠራ ሥርዓትን አስመልክቶ ከወራት በፊት በሀገረ ስብከቱ የተላከው መመሪያ ለኮሚቴው ቀርቦ ወደ ተግባር ሳይተረጎም በቢሮ ተሸሽጎ እንደተቀመጠ ነው፤ የቆጠራ ደንቡንና መመሪያውን ከማስፈጸም ይልቅ ከመመሪያው የተነሳ ህገ ወጥ ጥቅም የቀረባቸውን ግለሰቦች በማነሣሣት ለተቃውሞ እንዲቆሙ ይደረጋል፡፡ያለፉት ስድስት ዓመታት የገንዘብ እና ንብረት እንቅስቃሴ በገለልተኛ ኦዲተር እንዲመረመር በፓትርያርኩ ቢታዘዝም “ከቃለ ዐዋዲው ውጭ ነው” በማለት ሒደቱ በሒሳብ ክፍሉ እና በጽ/ቤቱ ተጓትቷል፤ ይልቁንም የሒሳብ ፍተሻ ሒደቱ እና የሰበካ ጉባኤው የተሻሻሉ አሰራሮች ትግበራ ከሚያስከትሉት ተጠያቂነት ለማምለጥ የአስተዳደር ሐላፊዎቹ፣ “ሰበካው እየረበሸን ነው፤ የደመወዝና ጥቅማ ጥቅሞች ዕድገት እንዳናደርግላችሁ ዕንቅፋት ሆኖብናል፤ ከእኛ ጎን ከቆማችሁ ቢሮ አካባቢ እንመድባችኋለን፤ ወዘተ…” በማለት ከማኅበረ ካህናቱ ጋር ማጋጨትና መከፋፈል ስራዬ ብለው ከመያዛቸውም በላይ በዓመት ፈቃድ ሰበብ ከቢሯቸው ይሸሻሉ፡፡
በግንቦት ወር መጨረሻ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ አስኪያጅ ጽ/ቤት የተላከው ይኸው የሰበካ ጉባኤው ሪፖርት፤ ከተደጋጋሚ ጥያቄ በኋላ በቁጥጥር ክፍሉና በሒሳብ ክፍሉ በቀረቡ የገዳሟ የፋይናንስ አቋም ማሳያ ሪፖርቶች ላይ የተካሔደው ንጽጽራዊ ግምገማ፤ ገዳሟ በ2006 ዓ.ም ከየካቲት እስከ ነሐሴ ባሉት ሰባት ወራት ብቻ ከብር 1.5 ሚሊዮን በላይ ተመዝብራለች፤ በዚህ ከፍተኛ የገንዘብ ጉድለት እንቅስቃሴ ሂሳብ ሹሙ፣ ገንዘብ ያዡ፣ ፀሐፊው፣ ቁጥጥሩና የቀድሞው አስተዳዳሪ ተጠያቂዎች እንደሆኑ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም ከንዋያተ ቅድሳት ወርኀዊ ሽያጭ ጋር በተያያዘ ገዳሟ ከታህሣሥ ወር 2007 ዓ.ም በፊት ባሉት ጊዜያት በየወሩ በአማካይ ከብር 100ሺህ በላይ ስትመዘበር መቆየቷን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ለዚህም በዋናነት ተጠያቂው የንብረት ክፍል ሐላፊው እንደሆኑ ገልጿል፡፡
በገዳሟ በገንዘብ ዝውውርና በንብረት አጠባበቅ የሚታየው ከፍተኛ የአሠሰራር ድክመትና የሠራተኞች የአቅም ማነስ የመግባባት ችግር ከመፍጠሩም ባሻገር በልዩ ልዩ የአስተዳደር ክፍሎች ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ሪፖርቱ አክሎ አብራርቷል፡፡
የገዳሟ ጸሐፊ መጋቤ ስብሐት ኃ/ጊዮርጊስ ዕዝራ በበኩላቸው፣ ሪፖርቱ እንዳልደረሳቸው ቢናገሩም የተጠቀሰውን የገንዘብ ጉድለት ጨምሮ የሪፖርቱ ይዘት “ሙሉ በሙሉ ውሸት ነው” በሚል አስተባብለዋል፤ ተጨማሪ ጥያቄዎችንም በስልክ ለመመለስ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡