Administrator

Administrator

ለ700 ጊዜያት ያህል ታጥቦ፣ አገልግሎቱን አላቋረጠም
    ኪዮሴራ የተባለው የጃፓን የሞባይል አምራች ኩባንያ በአለማችን የስማርት ፎን ታሪክ በአይነቱ የመጀመሪያው የሆነውን በውሃና በሳሙና መታጠብ የሚችል ዲንጎ ራፍሪ የተሰኘ አዲስ የሞባይል ቀፎ አምርቶ ትናንት በገበያ ላይ ማዋሉን ሪያሊቲ ቱዴይ ድረገጽ ዘገበ፡፡ ምንም እንኳን ሶኒ ኩባንያን የመሳሰሉ የሞባይል አምራቾች ከዚህ ቀደም ውሃን መቋቋም የሚችሉ ሞባይል ስልኮችን ቢያመርቱም፣ ሞባይሎቹ ሳሙና ከነካቸው የሚበላሹ ነበሩ ያለው ዘገባው፣ ኪዮሴራ ያመረተው አዲስ ሞባይል ግን የሳሙና አረፋ ውስጥ ተዘፍዝፎ ቢውል አይበላሽም ብሏል፡፡
“ይህንን በአይነቱ ልዩ የሆነ ሞባይል ስልክ ያመረቱት የኩባንያችን ተመራማሪዎች፣ የስልኩን ብቃት ለማረጋገጥ ከ700 ጊዜያት በላይ ያጠቡት ሲሆን አንዳችም ችግር ሳይፈጠርበት አገልግሎት መስጠት መቀጠሉን አረጋግጠዋል” ብለዋል የኩባንያው ቃል አቀባይ፡፡ 465 ዶላር የተተመነለት ይህ የሞባይል ስልክ፣ በተለይም ልጆች ለሚበዙባቸው ቤተሰቦች ታልሞ የተመረተ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፣ ሞባይሉ ውሃና የሳሙና አረፋን መቋቋም የሚችል ሽፋን ያለው መሆኑንና፣ ስፒከሮቹን ጨምሮ የተገጠሙለት አካላት በሙሉ በፈሳሽ የማይበላሹ መሆናቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡

 ፔኔዛ በተባለችው የሩስያ ከተማ የሚንቀሳቀሰው ኮሙኒስት ፓርቲ፤ አምባገነኑን የቀድሞው የሩስያ መሪ ጆሴፍ ስታሊንን ለመዘከርና ብዙዎች እንደሚሉት ሰውዬው አምባገነን መሪ አለመሆናቸውን የሚያሳዩ ጥናቶች የሚሰሩበት የጥናት ማዕከል በስማቸው ለመክፈት ማቀዱን አስታወቀ፡፡
ፓርቲው 2016ን የስታሊን አመት በሚል ለማክበር ማቀዱን እንዳስታወቀ የዘገበው ቢቢሲ፣ አመቱን ሙሉ የሚከናወኑ የተለያዩ ስታሊንን የሚዘክሩ ዝግጅቶችን ለማሳካት እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙና በስታሊን ስም ሊቋቋም የታሰበው የጥናት ማዕከልም ሰውዬውን በአምባገነንነት በመወንጀል ያለ አግባብ ስማቸውን የሚያጠፉ አካላትን ፕሮፓጋንዳ የሚያከሽፉ ፊልሞች እንደሚታዩበት የፓርቲው ሃላፊ ጂኦርጂ ካሜኔቭ መናገራቸውን ገልጧል፡፡
የስታሊን አመት ክብረ በዓል ከሁለት ሳምንታት በፊት በሚከፈት የፎቶ ግራፍ ኢግዚቢሽንና የስታሊን የልደት በዓል ስነስርአት የሚጀመር እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፣ በመጋቢት ወር መጀመሪያም ስታሊን የሞተበት ዕለት በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር አስታውቋል፡፡
መጪው የፈረንጆች አዲስ አመት የስታሊን ህገ መንግስት በመባል የሚታወቀው የሩስያ ህገ መንግስት የጸደቀበት 80ኛ አመት መሆኑን ያስታወሰው ዘገባው፣ ኮሙኒስት ፓርቲውም በስታሊን ታላቅነት ዙሪያ ምርምር ለሚያደርጉ ወጣት ተመራማሪዎች የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ማቀዱን አመልክቷል፡፡

     በሪል ኢስቴትና በኮንስትራክሽን ግብአቶች ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ለሦስት ቀናት ሊካሄድ ነው፡፡
አጀት ፕሮሞሽን ከመከር ሪል ስቴት ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና Home up የተሰኘው ይኸው ኤግዚቢሽን፣ በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ የተሰማሩ አካላትን እርስ በርስ ለማገናኘትና የገበያ ትስስርን እንዲፈጥሩ ለማድረግ ከማስቻሉም በላይ ልምድና ተሞክሮአቸውን እንዲለዋወጡ እንዲሁም ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር እንዲተዋወቁ በማድረግ በከተሞች ውስጥ የሚታየውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ጥረግ በማድረግ ላይ የሚገኙትን የዘርፉን አካላት እንደሚያግዝ ተገልጿል፡፡
በሀርመኒ ሆቴል በተዘጋጀ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ኤግዚቢሽኑ የግሉን ዘርፍ ከመንግስት አካላት ጋር በማገናኘትና በማወያየት በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለማስወገድ እንደሚረዳ የጠቆሙት የአጀት ፕሮሞሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሪት ኤልሳቤጥ አድነው፣ ከዚህ በተጨማሪም በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ እየታየ ያለውን የመረጃ ክፍተት በመሙላት ኢንዱስትሪው አድጎ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን ያግዛል ብለዋል፡፡
በኤግዚቢሽኑ የአገር ውስጥና የውጭ አገር የሪል ኢስቴት አልሚዎች፣ የኪንስትራክሽን ግብዓት አቅራቢዎች፣ ፈርኒቸር አምራቾችና የፋይናንስ ተቋማት ተሳታፊ እንደሚሆኑም ተገልጿል፡፡ 

    በቴዎድሮስ በየነ የተዘጋጀው “ህብረ ኢትዮጵያ” የተሰኘ የጠቅላላ እውቀት መፅሀፍ ሰሞኑን በገበያ ላይ ዋለ፡፡ መጽሐፉ ስለኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህል፣ ስፖርት፣ ቱሪዝምና በአጠቃላይ ከ20ሺህ በላይ መረጃዎችን ያከተተ ሲሆን በየትኛውም የእውቀት ደረጃ ላይ ለሚገኝ፣ ማንኛውም አይነት ሰው፣ ያሻውን መረጃ ለማግኘት እንደሚረዳ ተገልጿል፡፡ በ328 ገፆች ተቀንብቦ የተሰናዳው ይህ መጽሐፍ፤ በ69 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

    ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ የመፅሐፍ ንባብ ፕሮግራም ከኢትዮጵስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር በነገው ዕለት ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ “ሰልፍ ሜዳ” በተሰኘው የደራሲ የግርማ ተስፋው መፅሀፍ ዙሪያ ውይይት ያካሂዳል፡፡ በወመዘክር አዳራሽ ለሚካሄደው ለዚህ ውይይት የመነሻ ሀሳብ የሚያቀርቡት አቶ ስለሺ ሀጎስ ሲሆኑ፤ የመፃሕፍት አፍቃሪያን በውይይቱ ላይ እንዲሳተፉ ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ ጋብዟል፡፡

Saturday, 12 December 2015 11:30

የኪነት ጥግ

(ስለ ልምምድ)
በልምምድ ወቅት ስህተቶችን መስራት አለብህ፡፡ ምክንያቱም እንደዚያ ነው የሚሆነውንና የማይሆነውን የምታውቀው፡፡
ክላርክ ፒተርስ
እውነት ብዙ ልምምድ አይፈልግም፡፡
ባርባራ ኪንግሶልቨር
ሦስት ሴት ልጆች አሉኝ፤ እናም ውጤቱ “ኪንግ ሊር”ን ያለ ልምምድ መተወን ሆነ፡፡
ፒተር ኢስቲኖቭ
በአንድ ወቅት በአራት ቀን ልምምድ ለአንድ ትወና መድረክ ላይ ወጥቼ ነበር፡፡
አና ፍሪል
እኔ የ6 ሳምንት የልምምድ ጊዜ ያስፈልገኛል፤ ሴቶች ደግሞ 9 ወራት ያስፈልጋቸዋል፤ ይሄንን ለመገንዘብ 15 ዓመት ፈጅቶብኛል፡፡
ዊሊያም ኸርት
ከመድረክ ይልቅ ፊልምን እመርጣለሁ። ሁልጊዜም ከትወናው በተሻለ ልምምዱን እወደዋለሁ፡፡
ብራድ ዶሪፍ
የልምምድ ሂደቱን ከልቤ እወደዋለሁ፡፡ እነዚያን በቀን 8 ሰዓት የልምምድ ጊዜያት! ተዋናዮችን በእጅጉ ነው የምወዳቸው፡፡
ፐርል ክሊጅ
ምንጊዜም በልምምድ ክፍል ውስጥ ስሆን ደስተኛ ነኝ፡፡ እዚያ ነው ሁልጊዜ ሙሉ አቅሜንና የፈጠራ ችሎታዬን የማገኘው፡፡
ሎውሪ ሜትካልፍ
አንድ ጊዜ ልምምድ ውስጥ ከገባህ በኋላ በክፍሉ ውስጥ ባለው ትርኢት ላይ ማተኮር አለብህ ብዬ አስባለሁ፡፡
ስኮት ኢሊስ
የሻወር ትዕይንት ከመስራት የበለጠ ገልጃጃ ነገር ምን አለ? የሻወር ትዕይንትን ለማለማ መድ፡፡
ኮቢ ስሙልደርስ
ቲያትርን መለማመድ  ለቃለ - ተውኔቱ ስጋ ማልበስ ነው፡፡ ተውኔትን ማሳተም ሂደቱን መገልበጥ ነው፡፡
ፒተር ሻፌር
በቲያትር ልምምድ ወቅት ትኩረቴን በሂደት ላይ ካለው ሥራ ሊያናጥበኝ ከሚችል ምንም  ዓይነት ንባብ ለመታቀብ እጥራለሁ፡፡
ሜርሴዲስ ማክካምብሪጅ

Saturday, 12 December 2015 11:28

የግጥም ጥግ

እዬዬ ማይገልፀው
ምን ይበል አባቷ
ምን ትበል እናቱ
ለወግ ያሰበችው ሲቀጠፍ በከንቱ
ምን ይላል ወገኔ
ጉንጬ በእምባ ሲርስ - አንጀቴ ሲታጠፍ
ኮትኩቼ ያበበው
መዐዛው ሚስበው
የማታ አበባዬ በአጭሩ ሲቀጠፍ
ያቺ ምስኪን እናት
የማታዋን ሳታውቅ በጠዋት ተነስታ
ከዛሬው ወጋገን የነገውን አይታ
ጨርሳ አትሸኘው
ለአይኗ እንኳ ሳስታ
በደንብ እንዳትስመው
ያንን ስርጉድ ጉንጩን
ብሉኝ ብሉኝ ሚለው
ሞልቶ-ትርፍ ፈገግታ
የጠዋት ፀሎቷ - ጅምር በረከቷ - በእንባዋ
 ሲታበስ
የፀበል ማቆርያ - የህመም
ብርታቷ - ሲሰበር ላይታፈስ
እንዴት አሟት ይሆን
ልቧ ውስጧ ሲሞት
ያልጠና አጥንቱ - ያልገራ ጅማቱ - ጎማ
ሲበትነው
ያልቦረቀች ነፍሱ - ጅምር ለጋነቱ - ሲቃ
ሲፈትነው
እህህ አይገልፀው
እዬዬ አይክሰው
እምባዋን ረጭታው -
ከመብሰክሰክ በቀር - ምን ታደርገዋች
አንዴ ፈሷል ነገር - ዳግመኛ አትወልደው -
በምን ታፍሰዋለች
(መታሰቢያነቱ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከትምህርት ቤት ሲመለሱ በመኪና አደጋ ህይወታቸውን ላጡት ህጻናት ይሁንልኝ፡፡)
(ከዘም ዛሚ ፌስቡክ)

Saturday, 12 December 2015 11:26

የዝነኞች ጥግ

 (ስለ ሀብት)
እውነተኛው ሀብት ወርቅ ወይም ብር ሳይሆን ጤና ነው፡፡
ማሃትማ ጋንዲ
ሀብት ህይወትን ሙሉ በሙሉ የማጣጣም አቅም ነው፡፡
ሔንሪ ዴቪድ ቶሪዮ
በቅጡ በሚመራ አገር ድህነት የሚያሳፍር ነገር ነው፡፡ በተበላሸ መንገድ በሚመራ አገር ሀብት የሚያሳፍር ነገር ነው፡፡
ኮንፍሺየስ
ሀብት የሰው የማሰብ አቅም ውጤት ነው፡፡
አየን ራንድ
ገንዘብ ጓደኞችን አይገዛም፤ የተሻለ መደብ ጠላት ግን ማግኘት ትችላለህ፡፡
ስፓይክ ሚሊጋን
ብልህ ሰው ገንዘብን በጭንቅላቱ እንጂ በልቡ ማኖር የለበትም፡፡
ጆናታን ስዊፍት
ገንዘብ የብልህ ሰው ሃይማኖት ነው፡፡
ዩሪፒደስ
ከሀብታም ሰዎች የምወድላቸው ብቸኛ ነገር ገንዘባቸውን ነው፡፡
ናንሲ አስቶር
ሀብታሞች በየቦታው አሉ፤ ነገር ግን ለአገራቸው ዕድገት አስተዋፅኦ አያደርጉም፡፡
ሂላሪ ክሊንተን
ባለፀጎችን ካልወደድክ በቀር ጨርሶ ሀብታም አትሆንም፡፡
ዳግላስ ኩፕላንድ
በመላው ዓለም ሀብታሞች ተወዳጅነት የላቸውም፡፡
ቪክቶር ፒንቹክ
ሀብት ለዓለም ከፍተኛ ጥቅሞችን ያስገኛል፡፡ ሀብታሞች ጀግኖች ናቸው፡፡
ፒ.ጄ.ኦ‘ሮዮርኬ
ገንዘብ እንደ ስድስተኛ ስሜት ነው - እሱ ሳይኖር ሌሎቹን አምስቱን መጠቀም አትችልም፡፡
ሶመርሴት ሟም
የገንዘብ ችግር የሀጢያቶች ሁሉ ሥር ነው፡፡
ጆርጅ በርናርድ ሾው

      በሴቶችና በልጃገረዶች ላይ የሚፈፀሙ ጐጂ ባህላዊ ድርጊቶችን በተለይም የሴቶችን ግርዛት ለመከላከል አገሪቱ እያደረገች ላለው ጥረት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የአውሮፓ ህብረት አስታወቀ፡፡
በየዓመቱ ህዳር 30 ቀን የሚከበረውን የሰብአዊ መብት ቀን ምክንያት በማድረግ ህብረቱ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በአዋሣ ዙሪያ ወረዳ፣ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት የተደረጉ ድጋፎችንና የማህበረሰብ አቀፍ ሥራዎችን ለጋዜጠኞች ባስጐበኘበት ወቅት በህብረቱ የሲቪል ማህበረሰብና የጾታ ጉዳዮች ፕሮግራም መሪ ስቴፋን ካሬት እንደተናገሩት፤ በወረዳዎቹ የሴት ልጅ ግርዛት፣ ያለዕድሜ ጋብቻ፣ ጠለፋንና የውርስ ጋብቻን ለማስቀረት አገሪቱ የምታደርገውን ጥረት ህብረቱ ሲደግፍ ቆይቷል፡፡
በክልሉ በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ እናቶች፣ ህፃናትና ልጆችን መሠረታዊ ችግር በመቅረፍ ለነዋሪዎች የጤና እና የትምህርት እድል ለማስገኘት ለሚሰራው ሴንተር ኦፍ ኮንሰርን የተባለ ማዕከል ድጋፍ የሚያደርገው ህብረቱ፤ በእነዚሁ ወረዳዎች ውስጥ ለሚገኙና ቀድሞ በግርዛት ሥራ ላይ ለተሰማሩ 60 ሴቶች 1500 ብር መቋቋሚያ በመስጠት፣ ከጐጂ ልማዳዊ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ መደረጉም በዚሁ ወቅት ተገልጿል፡፡
ዞኑ በተለይም ከሴት ልጅ ግርዛትና ከውርስ ጋብቻ ጋር በተያያዘ በርካታ ችግሮች የነበሩበት ሥፍራ እንደነበር የገለፁት የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ጌታነህ በበኩላቸው፤ የጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶቹ ሰለባ የሆኑ ሴቶችን መልሶ በማቋቋም ኑሮአቸውን ለማሻሻል ጥረት መደረጉን ጠቁመው፣ በወረዳው ሥር ባሉ ትምህርት ቤቶችና መንደሮች ማህበረሰቡን ለማስተማር ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

 የተለያዩ የስፖርት መሥሪያ መሳሪያዎችን አምርቶ ለገበያ በማቅረብ የሚታወቀው የላይፍ ፊትነስ እናት ድርጅት ብራንዝዊክ ኮርፖሬሽን በዕድሜ ለገፉ ሰዎች ጠቃሚ የሆኑ የስፖርት መስሪያ ዕቃዎችን በማምረት የሚታወቀውን ሳይፈት የተባለ ድርጅት በመግዛት የድርጅቱ አካል ማድረጉን አስታወቀ፡፡
የላይፍ ፊትነስ ፕሬዚዳንት ሚስተር ክሪስ ላውሶን እንደገለፁት ላይፍ ፊትነስ ሳይፊትን መግዛቱ ቁጥራቸው በፍጥነት እያደገ ያለውን በዕድሜ የገፉ ወገኖችን ሊረዳ የሚችል ምርት ለማቅረብ ያስችለናል ብለዋል፡፡
ይህም ድርጅቱ ጡረተኞች እንዲሁም ልዩ እርዳታና እንክብካቤ የሚያሰፈልጋቸው ወገኖች ለሚገለገሉባቸው ቦታዎች፣ ለአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋማት፣ ለማረሚያ ቤቶችና የተአድሶ ሥፍራዎች አስፈላጊ የሆኑ ምርቶችን የስፖርት መስሪያ ለማቅረብ እንደሚያስችላቸው ገልፀዋል፡፡
ላይፍ ፊትነስ ለጂም የሚሆኑ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ምርቶች፣ የመዝናኛ ጠረጴዛዎች እንዲሁም የተለያዩ ዕቃዎች አምርቶ ለገበያ በማቅረብ ቀዳሚ የሆነ ድርጅት ነው፡፡