Administrator

Administrator

      መድረክ፤ ባለፉት 3 ሳምንታት ከአዲስ አበባ ከተማ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ በኦሮምያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተደረጉ ተቃውሞዎች የተሳተፉ 2ሺህ 627 ሰዎች በመንግስት ሃይሎች ታስረዋል ማለቱን ሮይተርስ ትናንት ዘገበ፡፡
የፓርቲው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፤ መንግስት ተቃዋሚዎችን ያሰረው በቀጣይ ተመሳሳይ ተቃውሞዎች እንዳይደረጉ ለመከላከል በማሰብ ነው ሲሉ መናገራቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በኦሮምያ ክልል በሚገኙ 12 የተለያዩ አካባቢዎች 2 ሺህ 627 ሰዎች በመንግስት ቁጥጥር ስር ውለዋል ማለታቸውንም ገልጿል፡፡
የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ከማስተር ፕላኑ ጋር በተያያዘ በኦሮምያ ክልል በተደረጉ ተቃውሞዎች ከ200 ያህል፤ ሰዎች ሳይገደሉ አልቀሩም ማለታቸውንም ዘገባው አስታውሷል። በጉዳዩ ዙሪያ የመንግሥት ኃላፊዎችን ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካ ሮይተርስ ጠቁሟል፡፡

ሊቀመንበሩን ጨምሮ አምስት የሠማያዊ ፓርቲ አመራሮች እንዲባረሩና እንዲታገዱ በስነስርአት ኮሚቴ የተላለፈውን ውሣኔ የፓርቲው ኦዲትና ኢንስፔክሽን ውድቅ አድርጐታል፡፡
የስነስርአት ኮሚቴው በምርጫ 2007 አምስት አመራሮች ያለአግባብ የፓርቲውን ገንዘብ አባክነዋል በሚል የቀረበለትን ክስ ሲመረምር ቆይቶ ባሳለፍነው ሣምንት ውሣኔ ሰጥቶ የነበረ ሲሆን በውሣኔውም የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነትና የሂሣብ ክፍል ሃላፊው አቶ ወረታው ዋሴ ከፓርቲው ሙሉ ለሙሉ እንዲባረሩ፤ የፓርቲው ም/ሊ/መንበር የነበሩት አቶ ስለሺ ፈይሳና የምክር ቤት አባልዋ ወ/ት ወይንሸት ሞላ፣ ለሁለት አመት እንዲታገዱ እንዲሁም አቶ ጌታነህ ባልቻ ለሶስት ወር እንዲታገዱ ያሳለፈውን ውሣኔ፣ የፓርቲው ኦዲትና ኢንስፔክሽን “አግባብ አይደለም” በማለት ሽሮታል፡፡
ለተከሳሾቹ ከመገለፁ በፊት በማህበረሰባዊ ሚዲያዎች ውሳኔው ይፋ መሆኑ አግባብ አለመሆኑን የጠቀሰው የኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚቴው፤ ውሳኔውም የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ ያልተከተለና የስነ ስርዓት ቅጣት አላማን ያላገናዘበ ነው ብሏል፡፡
መባረራቸውና መታገዳቸው ተገልፆ የነበረው የፓርቲው አመራሮች፤ መደበኛ ስራቸውን እንዲቀጥሉ የወሰነው  የኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚቴው፤ በማህበራዊ ድረ ገፆች ይሄን አስመልክቶ የሚካሄዱ ዘመቻዎች መቆም እንዳለባቸውም አሳስቧል፡፡

የወልቃይት ወረዳ በአማራ ክልል ውስጥ መሆን አለበት የሚል ጥያቄ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያስገቡ አቤቱታ አቅራቢዎች፤ ምላሽ እንዳልተሰጣቸው የተናገሩ ሲሆን ፌዴሬሽን ም/ቤት በበኩሉ፤ በመጀመሪያ ጥያቄው መታየት ያለበት በክልል ምክር ቤት ነው የሚል ምላሽ ሰጥቻለሁ አለ፡፡
ጥያቄ በማንሳታችን በደል እየተፈፀምብን ነው በማለት አቤቱታ አቅራቢዎቹ ገልፀዋል፡፡ የወረዳው አስተዳደር ግን አስተባብሏል - የወረዳው ነዋሪዎች አይደሉም በማለት፡፡
ጥያቄያችንን ለፌዴሬሽን ምክር ቤትና ለተለያዩ የመንግስት አካላት በተደጋጋሚ አሰምተናል ያሉት አቤቱታ አቅራቢዎች፤ የወረዳው ባለስልጣናት እንግልትና በደል እየፈፀሙብን ነው ብለዋል፡፡
ህግን ተከትለን የወልቃይት ጠገዴ ወረዳ በአማራ ክልል ስር እንዲሆን ጥያቄ ማንሳት የጀመርነው በ1983 ዓ.ም ነው በማለት የተናገሩት አቤቱታ አቅራቢዎች፤ “ጥያቄያችን ምንም የፖለቲካ ፍላጎት ባይኖረውም አላግባብ ተፈርጀን እንግልት እየደረሰብን ነው ብለዋል፡፡
የወልቃይት ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ጀጃው ደሞዝ በበኩላቸው፤ “ጥያቄ ማንሳት ያለበት የወረዳው ህዝብ እንጂ በሌላ አካባቢ የሚኖር ግለሰብ አይደለም፤ ህዝቡ እንዲህ አይነት ጥያቄ አላነሳም” ብለዋል፡፡
ጥያቄ አቅርበዋል የሚባሉት ሰዎች የወረዳው ነዋሪዎች አይደሉም ያሉት አቶ ጀጃው፣ የወረዳው ማህበረሰብ በመልካም አስተዳደርና በልማት ስራዎች ላይ እየተረባረበ ነው ብለዋል፡፡

    የሴባስቶፖል ሲኒማና ኢንተርቴይመንት ባለቤት፣ የፊልም ደራሲና ዳይሬክተሩ አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ፤ በ“ሶስት ማዕዘን” ፊልም ምክንያት ከቀረበበት የ10 ሚሊዮን ብር የፍትሃ ብሄር ክስ በነፃ ተሰናብቷል፡፡
አርቲስቱ “ሶስት ማዕዘን” የተሰኘውን ፊልም ደራሲ አትንኩት ሙሉጌታ በ2000 ዓ.ም ካሳተመው “ፍቅር ሲበቀል” መፅሃፍ ወስዶ ነው የሰራው የሚል ክስ የቀረበበት ነሐሴ 13 ቀን 2006 ዓ.ም ሲሆን ከሳሽ ደራሲ አትንኩት፣ለደረሰባቸው የሞራል ጉዳት የ10 ሚሊዮን ብር ካሳ እንዲከፈላቸው ጠይቀው ነበር፡፡
አቤቱታው የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት 18ኛ ፍ/ብሔር ችሎት፣ በከሳሽ የቀረቡ የሰውና የሠነድ ማስረጃዎችን እንዲሁም በተከሳሽ የቀረቡ ተመሳሳይ ማስረጃዎችን ከመረመረ በኋላ የከሳሽ ማስረጃ ክሱን በአግባቡ የሚያስረዳ ሆኖ እንዳላገኘውና ክሱ ያለ አግባብ የቀረበ መሆኑን በመግለፅ ከትናንት በስቲያ ውድቅ አድርጎታል፡፡ አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ በክሱ ሂደት የደረሰበትን ጉዳትም በዝርዝር መጠየቅ እንደሚችል ፍ/ቤቱ አስታውቋል፡፡
 የክሱን መመስረት ተከትሎ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ የተሰራጩ ዘገባዎች፣ በስራውና በሞራሉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሱበት የገለጸው አርቲስቱ፤በእቅድ የያዛቸው ስራዎችም እንደተሰናከሉበት ተናግሯል፡፡  

- ቡድኑ 5 ኢትዮጵያውያን አባላት አሉት ተብሏል
- በስደተኞች ጀልባ አደጋ ከሞቱት መካከል አንደኛው ኢትዮጵያዊ ነው ተባለ

   በኩዌት በቤት ሰራተኝነት ተቀጥረው የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ከቀጣሪዎቻቸው ቤት በማስኮብለል ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ሌላ ቦታ በማስቀጠርና ገንዘብ በመሰብሰብ ህገወጥ ስራ ላይ ተሰማርቷል የተባለ ቡድን ከትናንት በስቲያ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉን ገልፍ ዲጂታል ኒውስ ድረገጽ ዘገበ፡፡
አምስት ኢትዮጵያውያንን በአባልነት የያዘውና ህጋዊ ፍቃድ ሳያወጣ በተጭበረበረ ሰነድ የሚንቀሳቀሰው ይህ ቡድን፣ በአገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የቤት ሰራተኞችን ከፍ ባለ ደመወዝ እናስቀጥራችኋለን እያለ ከተቀጠሩበት ቤት በማስኮብለል በድብቅ ቦታ እያቆዩ ለሌሎች ቀጣሪዎች ይሸጣል መባሉን ዘገባው ገልጧል፡፡
ከቡድኑ ጋር ይሰራሉ የተባሉ ኢትዮጵያውያንና የሌሎች የአፍሪካ አገራት ዜግነት ያላቸው 17 ወንዶችና 13 ሴቶችም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል ያለው ዘገባው፣ የቡድኑ አባላትና ተባባሪዎቻቸው ለፍርድ ቀርበው ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው አስታውቋል፡፡በተያያዘ ዜና የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ስደተኞችን ጭና በሜዲትራኒያን ባህር ላይ ስትቀዝፍ በነበረች ጀልባ ላይ ከትናንት በስቲያ በደረሰ የመስጠም አደጋ ለህልፈተ ህይወት ከተዳረጉትና አስከሬናቸው ከተገኘ 9 ሰዎች መካከል አንደኛው ኢትዮጵያዊ እንደሆነ መረጋገጡ ተዘግቧል፡፡
የግብጹ ዴይሊ ኒውስ ድረገጽ ያወጣው ዘገባ፣ በአደጋው ለህልፈተ ህይወት የተዳረገው ኢትዮጵያዊ የ43 አመት ጎልማሳ መሆኑ መረጋገጡን ከመግለፅ በስተቀር፣ ስለ ሟቹ ማንነት ዝርዝር መረጃ አልሰጠም፡፡





   ተቃውሞ የበረታባቸው የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ፤ በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርበዋል በሚል ሰሞኑን በስፋት ሲሰራጭ የሰነበተውን መረጃ ፓርቲያቸው አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ ማስተባበሉን ሮይተርስ ዘገበ፡፡
የአገሪቱን ኢኮኖሚ በቅጡ መምራት አቅቷቸዋል፣ ከባለሃብቶች ጋር በመመሳጠር የአገር ሃብት ይመዘብራሉ በሚል ተቃውሞ ያየለባቸው ፕሬዚዳንት ዙማ፣ ሰሞኑን በተካሄደው የፓርቲው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርበዋል በሚል የተለያዩ ጋዜጦችና ድረገጾች መዘገባቸውን ያስታወሰው ሮይተርስ፤ የፓርቲው ቃል አቀባይ ግን፣ መረጃው ሃሰተኛ ነው ሲሉ ማስተባበላቸውን ጠቁሟል፡፡
“ይህ ፍጹም መሰረተ ቢስና ሃሰተኛ መረጃ ነው!... እንዲህ አይነት ነገር አልተደረገም!” ብለዋል የአፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ ቃል አቀባይ ዚዚ ኮድዋ፣ ጋዜጦቹና ድረገጾቹ ያሰራጩትን ዘገባ ሲያስተባብሉ፡፡
የፕሬዚዳንቱ ፓርቲ በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ አለመተማመን እንዲሰፍን አድርጓል፣ ኢኮኖሚውንም አደጋ ውስጥ ከትቶታል በሚል ከፖለቲከኞች ትችት እየተሰነዘረበት እንደሚገኝ ያስታወሰው ዘገባው፣ የአገሪቱ የጸረ ሙስና ኮሚሽንም ፕሬዚዳንቱ የተጠረጠሩበትን ድርጊት እንደሚመረምር ባለፈው ማክሰኞ ማስታወቁን አክሎ ገልጧል፡፡

 ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ትሻላለች ተብሏል
    ሰስቴኔብል ዴቨሎፕመንት ሶሊዩሽንስ ኔትዎርክ የተባለ ተቋም በአፍሪካ አህጉር በደስተኝነት ቀዳሚ ናቸው ያላቸውን አገራት ዝርዝር ይፋ ማድረጉን ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት፣ የማህበራዊ ድጋፍ፣ አማካይ ዕድሜ፣ ለሙስና ያለውን አመለካከትና የመሳሰሉትን መስፈርቶች በመጠቀም አገራቱን በደረጃ ያስቀመጠው የተቋሙ ሪፖርት፤አልጀሪያን ከአፍሪካ እጅግ ደስተኛዋ አገር በማለት በቀዳሚነት አስቀምጧታል። ሞሪሽየስና ሊቢያ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን የያዙ ሲሆን ሶማሊያ፣ ቱኒዝያ፣ ናይጀሪያ፣ ዛምቢያ፣ ናሚቢያ፣ ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ በቅደም ተከተል እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
ከአለማችን አገራት በደስተኛነት የመጨረሻውን ደረጃ ከያዙት አስር አገራት መካከል ስምንቱ አፍሪካውያን ናቸው ያለው ዘገባው፣ እነሱም ማዳጋስካር፣ ታንዛኒያ፣ ላይቤሪያ፣ ጊኒ፣ ሩዋንዳ፣ ቤኒን፣ ቶጎ እና ብሩንዲ መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡
ተቋሙ በአለማቀፍ ደረጃ ባደረገው የአገራት የደስተኝነት ሁኔታ ጥናት፣ የመጀመሪያዎቹን 100 ደረጃዎች ከያዙት አገራት መካከል መካተት የቻሉት የአፍሪካ አገራት አምስት ብቻ መሆናቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

   ከ400 አመታት በፊት ከዚህ አለም በሞት የተለየው እንግሊዛዊው ባለቅኔ ዊሊያም ሼክስፒር የራስ ቅል ከመቃብሩ ውስጥ ባልታወቁ ዘራፊዎች መሰረቁ በአርኪዎሎጂስቶች ጥናት መረጋገጡን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ከትናንት በስቲያ ዘገበ፡፡
እንግሊዛውያን ተመራማሪዎች በስታንፎርድ የቅዱስ ስላሴ ቤተክርስቲያን ውስጥ በሚገኘው የዊሊያም ሼክስፒር መቃብር ላይ ባደረጉት የራዳር ፍተሻ፣ የባለቅኔው የራስ ቅል መቃብሩ ውስጥ እንደሌለ ማረጋገጣቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ የመቃብሩ የላይኛው ክፍልም ከረጅም አመታት በፊት ተከፍቶ እንደነበር የሚያሳይ ምልክት መገኘቱን ገልጧል፡፡
በዚሁ ምልክት ላይ በተደረገ ምርመራ፣ የራስ ቅሉ የተዘረፈው በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሳይሆን እንደማይቀር መገመቱ የተነገረ ሲሆን፣ የራስ ቅሉ መጥፋት የታወቀው ባለቅኔው ከዚህ አለም በሞት የተለየበትን 400ኛ አመት በማስመልከት ዶክመንተሪ ፊልም በሚሰራበት ወቅት መሆኑንም አስረድቷል፡፡
ሼክስፒር ከሚወዳት ባለቤቱ አና ሃትዌይ ጎን መቀበሩን ያስታወሰው ዘገባው፣ የመቃብር ስፍራው ለረጅም አመታት በበርካታ የባለቅኔው አድናቂዎች ሲጎበኝ የኖረ ትልቅ ስፍራ እንደነበርም አክሎ ገልጧል፡፡

 በመላ አውሮፓ እጅግ የከፉ ጥቃቶችን ለመሰንዘር ዝቷል
      ባለፈው ማክሰኞ በቤልጂየም መዲና ብራስልስ በፈጸማቸው የሽብር ጥቃቶች ከሰላሳ በላይ ሰዎችን ለሞት፣ ከ300 በላይ የሚሆኑትን ደግሞ ለመቁሰል አደጋ የዳረገው አሸባሪው ቡድን አይሲስ፣ ገና ምን አይታችሁ፤ አውሮፓንና ሊያጠፉኝ የተነሱ አገራትን በሽብር በማናወጥ እጅግ የከፋ ጥፋት አደርሳለሁ ሲል መዛቱ ተዘግቧል፡፡
የሽብር ቡድኑ ባሰራጨው መግለጫ፣ በእኔ ላይ ተባብረው በተነሱ የአውሮፓ አገራትና አጋሮቻቸው ላይ ሌሎች የከፉ የሽብር ጥቃቶችን እንዲፈጽሙ አደገኛ ፈንጂዎችንና የጥፋት መሳሪያዎችን ያስታጠቅኳቸው ወታደሮቼ፣ በቀጣይም ገና ብዙ ጥፋት ያደርሳሉ ሲል መዛቱን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
አይሲስ በህቡዕ ያደራጃቸውና 600 ያህል በከፍተኛ ሁኔታ የሰለጠኑ ወታደሮችን ያቀፉ ከመቶ በላይ የሽብር ህዋሶች በተለያዩ የአውሮፓ አገራት ውስጥ ከባድ ጥቃት ለመፈጸም በተጠንቀቅ ላይ እንደሚገኙ የዘገበው ዘ ሰን በበኩሉ፣ ጽንፈኛው ቡድን ለንደንና በርሊንን ጨምሮ በታላላቅ የአውሮፓ ከተሞች ከፍተኛ ጥቃት የሚያደርሱ ጥቃቶችን ለመሰንዘር ተዘጋጅቷል ብሏል፡፡
የአይሲስ ከፍተኛ አመራር በየአገራቱ ለሚገኙት የሽብር ህዋሶቹ መሪዎች የሽብር ጥቃቶችን ለመፈጸም ዝግጅታቸውን እንዲያጠናቅቁና ጥቃቶቹ የሚፈጸሙባቸውን ቦታዎችና አፈጻጸማቸውን ሲመርጡ፣ በአህጉሪቱ ከፍተኛ ቀውስ የሚፈጥሩና የብዙዎችን ህይወት የሚቀጥፉ መሆናቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆን እንዳለበት መመሪያ መስጠቱንም ዘገባው ገልጧል፡፡
የብራስልሱን አሰቃቂ የሽብር ጥቃት ተከትሎ የአውሮፓ አገራት የደህንነት ሃይላቸውን በማጠናከር ተጠምደው መሰንበታቸውን የዘገበው ቢቢሲ፣ ፈረንሳይ ተጨማሪ 1 ሺህ 600 ፖሊሶችን በባቡር ጣቢያዎች፣ በአውሮፕላን ማረፊያዎችና በድንበር አካባቢዎች ማሰማራቷን ጠቁሞ፣ አስቸኳይ ስብሰባ የጠሩት የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩንም የአገሪቱ የደህንነት ቁጥጥርና የፖሊስ ሃይል እንቅስቃሴው በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጠናከር ማዘዛቸውን ጠቅሷል። ጀርመንና ሌሎች የአውሮፓ አገራትም ዜጎቻቸውን ከአይሲስ ሊፈጸም ከሚችል የሽብር ጥቃት ለመከላከል የተጠናከረ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

 በፍራንሴስ ዊሊያምስ ተዘጋጅቶ የታተመው “Understanding Ethiopia: Geology and Scenery” የተሰኘ መጽሐፍ የፊታችን ሀሙስ ከምሽቱ 11 ሰዓት እስከ 12 ሰዓት ተኩል 22 ማዞሪያ ድንበሯ ሆስፒታል አጠገብ በሚገኘው ሮድ ራነር ባር እና ሬስቶራንት ውስጥ ይመረቃል፡፡
መጽሐፉ ያለምንም ሙያዊ ቋንቋ፣ ለሁሉም ሰው በሚገባ መልኩ እንደተሰናዳ የተገለፀ ሲሆን በብዙ ባለቀለም ካርታዎችና ፎቶግራፎች የደመቀና የተሞላ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡
የምረቃ ሥነስርዓቱን መግቢያ ንግግር የሚያደርጉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስኩል ኦፍ ኸርዝ ሳይንስ መምህር ፕሮፌሰር ገዛኸኝ ይርጉ ሲሆኑ መጽሐፉ በዕለቱ በ20 ዶላር ወይም በ400 ብር ገደማ ለሽያጭ እንደሚቀርብ ታውቋል፡፡ የምረቃ ሥነስርዓቱን የአዲስ አበባው “ኢትዮጵያን ኳድራንትስ” እና የአዴላይድ ዩኒቨርሲቲ፣ኸርዝ ሳይንስ መምህሩ ፍራንሴስ ዊሊያምስ በመተባበር እንዳዘጋጁት ለማወቅ ተችሏል፡፡