Administrator

Administrator

  “የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህል ከአያት ቅድመ አያቶቻችን የመጣ ነው”

                   በጉራጌ ዞን፣ የዶቢ ደብረ ፀሀይ ቅዱስ ጊዮርጊስ
የልማት፣ የቀብርና መረዳጃ ማህበር በ1923 ዓ.ም ነው የተቋቋመው፡፡ 86 ዓመታትን አስቆጥሯል። የማህበሩ መስራቾች የዶቢ ተወላጆች ናቸው።ተወላጆቹ በተለያየ ምክንያት ከቀዬአቸው ወጥተው አዲስ አበባ ይገባሉ፡፡ ያገኙትን እየሰሩም ራሳቸውን እስኪችሉና “ሰው” እስኪሆኑ ይቆያሉ።
በተሰማሩበት የሥራ መስክ ውጤታማ ሲሆኑ ቀዬአቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ባያስታውሱም ማህበራቸው ያስታውሳቸዋል፡፡ የተወለዱበትንአካባቢ ያለማሉ፡፡ ት/ቤቶችን፣ ጤና ጣቢያዎችን ይገነባሉ፡፡ መንገዶችንና ድልድዮችን ይሰራሉ። ልማት ብቻ አይደለም፤ ማህበራዊ ትስስርም
አለው፡፡ የዶቢ ተወላጆች በደስታም በሀዘንም ጊዜ አይለያዩም፤ ይሰባሰባሉ፡፡ በንግድ የከሰረን መልሶ ማቋቋም የተለመደ ነው፡፡ ማህበሩ ደግሞ በገንዘብ፣ በእውቀት፣ በማስተባበርና ልማትን በሀላፊነት በመምራት ለትውልድ ቀዬው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አባላቱ በየአስር ዓመቱ
ባህላዊ ሹመትይሰጣል፡፡ባለፈው እሁድ ተረኛው፣ የ71 ዓመቱ የዕድሜ ባለጸጋ አቶ ተሰማ በየነ ነበሩ፡፡ በልማት ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የአዝማችነት ማዕረግ
ተሰጥቷቸዋል፡፡ ባለቤታቸው ወ/ሮ እልፍነሽ ተመስገንም በአገሩ ባህል መሰረት፣‹‹ኢቴ›› (እቴጌ) የተሰኘውን ማዕረግ አግኝተዋል፡፡ ማህበሩ በአካባቢው የተጣላን ሲያስታርቁ፣ ህዝቡን ሲያስተምሩና ሲገስፁ ለአንድ ክፍለ ዘመን የዘለቁትን የአቶ ኬርስማ ፎሌን የ100ኛ ዓመት የልደት
በዓልንም በዕለቱ አክብሯል። የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ባህላዊ ማዕረግ ከተሾሙት ከአዝማች ተሰማ በየነ ጋር በማዕረጋቸው፣
በልማት ተሳትፏቸው፣ በትዳራቸውና በአጠቃላይ ህይወታቸው ዙሪያ እንዲህ አውግታለች፡-
     ሹመቱ ለእርስዎ ምን ትርጉም ይሰጥዎታል?
እኔ ሹመቱን ከባህላችን፣ ከጥንት ታሪካችን አኳያ ስለምመለከተው፣ ትልቅ ትርጉም ነው ያለው። ይሄ ማዕረግ የሚሰጠው በተለያየ አይነትና
ጊዜ፣ ለህዝቡና ለአካባቢው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከተ ሰው ነው፡፡ እኔም ይሄ ማዕረግ ሲሰጠኝ ደስታዬ ወደር የለውም፡፡ እርግጥ እስከ ዛሬ
ከህዝቡ ጋር በመተባበር፣ ለአካባቢው የተለያየ የልማት ስራ ሰርተናል፡፡ በግሌ ይሄን የልማት ስራ በገንዘብም በእውቀትም፣ ልማቱን በሀላፊነት
በመምራትም ስሰራ፣ ይህን ማዕረግ አገኛለሁ ብዬ አይደለም። ለራሴ አዕምሮ ያሳመንኩትን፣ ለወገንና ለአካባቢ በጎ ማድረግ የሚለውን መርህ
ከጫፍ ለማድረስና ጤናማና ሰላማዊ ህይወት ለመምራት እንድችል ነው፡፡ ለህብረተሰቡ ይጠቅማል ያልኩትን ነገር ለመስራት ተነሳሁ፤
ተሳካልኝ፡፡ ማህበረሰቡ ልዩ ቦታ ለሚሰጠው ማዕረግም በቃሁ፤ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡
በማህበሩ የአዝማችነት ማዕረግ ሲሰጥ እርስዎ ስንተኛ ነዎት?
እንግዲህ ታሪኩን ከገጠሩ ጀምረን ስንመለከት፣ አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን በአካባቢው ባህል መሰረት፣ የተለያዩ አስተዋፅኦ ላበረከቱ፣
በእድሜ ለበሰሉ ሰዎች የሚሰጡት ማዕረግ ነበር፡፡ ዛሬ ዛሬ ደግሞ ብዙ ነገሮች ተለውጠዋል፡፡ ምናልባትም ቀኛዝማችና ግራዝማች፣ ፊታውራሪ
ወደሚለው ተሸጋግሯል፡፡ ይሄ ቀኛዝማች ግራ አዝማች የሚለው ማዕረግ፣ ከእኛ “አዝማች” ከሚለው ባህላዊ ማዕረጋችን ጋር ምንም አይነት
ግንኙነት የለውም። ባህላችን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከተ ወጣት፤ “አበጋዝ” የሚል ማዕረግ ይሰጣል፡፡ “አዝማች” ግን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ
ለአካባቢው የሰራ፣ ዕድሜውም ገፋ ያለ፣ በማህበረሰቡ እውቅና ላለው ሰው የሚሰጥ ማዕረግ ነው፡፡ ስንተኛው ሰው ነህ ላልሺው፣ ከጥንት

ጀምሮ ለዘመናት የዘለቀ በመሆኑ፣ ስንተኛ እንደሆንኩ ለማወቅ ይቸግረኛል፡፡
እስኪ ከተሳተፉባቸው የልማት ስራዎች ጥቂቶቹን ይንገሩኝ?
እንግዲህ አካባቢያችን በጠቅላላ “ሰባት ጎጎት ዶቢ” ይባላል፡፡ ይሄ ዛሬ የምታይው በሰባት ጎጎት አካባቢ ካሉ ማህበሮች፣ አንዱ የሆነው የዶቢ
ማህበር ነው፡፡ እርግጥ እኔ ልማቱን ስመራና ሳስተባብር፣ በአጠቃላይ የሰባት ጎጎትን እንጂ የዶቢን ብቻ አይደለም፡፡ በዚህ አስተዋፅኦ እንደ
ማንኛውም የአካባቢው ተወላጅ በመንገድ ስራ፣ በትምህርት ቤት፣ በቤተ ክርስቲያን … ከሌላው ማህበረሰብ ጋር የሚያገናኙ የልማት ስራዎችን  
ስንሰራ ቆይተናል። በዚህም ህዝቡ በመንገድ እጦት ይደርስበት የነበረው እንግልት፣ ተማሪዎች ለከፍተኛ ትምህርት ርቀው መሄዳቸው ቀርቷል፡፡
ህብረተሰቡ ከአምላኩ የሚገናኝበት ቤተ እምነትም በበቂ ሁኔታ አግኝቷል፡፡
ወደ ልጅነትዎ ዘመን ልመልስዎና… ከአገርዎ እንዴት ነው  ወደ አዲስ አበባ የመጡት?
ከአገሬ የወጣሁት የተሻለ ህይወት ለመምራት ነው፡፡ ከገጠር ወደ ከተማ ሲመጣ ለውጥ እንዳለ ይታወቃል፡፡ እኔም እስከ 15 ዓመቴ በቤተሰቦቼ
ጉያ ሆኜ፣ አቅሜ የሚፈቅደውን ያህል ሳገለግላቸውና ከእነሱም ስገለገል ከቆየሁ በኋላ፣ ራሴን ወደምችልበት እድሜ ስደርስ፣ ወደ አዲስ አበባ
መጣሁ፡፡ እዚህም ዘመድ ቤት ተቀጥሬ መስራት ጀመርኩኝ፡፡
ዘመድ ቤት የተቀጠሩት በምን ስራ ነበር?
ዘመዶቼ የመጠጥ ማከፋፈያ ነበራቸው፡፡ እዚያ ማከፋፈያ ውስጥ ስሰራ ቆየሁ፤ ልምድም አገኘሁ። መቼም ሁሌ ተቀጥሮ መስራት የለምና፣ በ1972
ዓ.ም “ተሰማ በየነ የመጠጥ ማከፋፈያ” የተሰኘውን ድርጅቴን አቋቋምኩኝ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ራሴንና ቤተሰቤን፣ አልፎ ተርፎም ወገኔን
ለመርዳት አስችሎኛል፡፡ አየሽ መልካም መስራት ለራስ ነው፡፡ መልካም ስታደርጊ ይዞ የሚመጣው በረከት በገንዘብ የሚለካ አይደለም፡፡ ጤናማ
ትሆኛለሽ፤ ቤተሰብ ይባረካል፡፡ በአጠቃላይ ልጅ ይወጣልሻል፡፡ እኔም እንግዲህ የዚህ በረከት ተቋዳሽ ነኝ፤ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ እንደሰማሁት ዕለቱ ለእርስዎ ድርብ በዓል እንደሚባለው ነው፤ አንድም በባህሉ እጅግ ክቡር የሆነውን ማዕረግ ተሸልመዋል፣ አንድም በቅርቡ 50ኛ ዓመት የጋብቻ የወርቅ ኢዩቤልዩ በዓል አክብረዋል፡፡ ዛሬ ‹‹ኢቴ›› (እቴጌ) የተሰኘ ውድ ማዕረግ ከተሰጣቸው ባለቤትዎ ጋር እንዴት
ተገናኛችሁ?…
እኔና ባለቤቴ ወ/ሮ እልፍነሽ የተገናኘነው በአካባቢያችን ባህል፣ በቤተሰብ ደረጃ ነው፡፡ የአንድ አካባቢ ተወላጆች ነን፡፡ እኔም አላውቃት፤ እሷም
አታውቀኝም፡፡ በወቅቱ በነበረው ባህል፣ ልጆች በወላጆቻቸው አማካኝነት ነው ጋብቻ የሚፈፅሙት። ቤተሰቤ የእሷን ቤተሰቦች፣ ‹‹ልጃችሁ
ለልጃችን›› ብሎ ጠየቀ፤ ተፈቀደ። ሚያዚያ 30 ቀን 1938 ዓ.ም በአካባቢው የሰርግ ስርዓት ተጋብተን፣ እስካሁን በመከባበር በመቻቻል፣ 50
ዓመታትን ዘልቀናል፡፡ አንዳንዴ የከረረ ነገር ባይኖርም፣ ጊዜያዊ ሽኩቻ ሲኖር፣ አንዱ ሲቆጣ ሌላው ቀዝቅዞ ነው የኖርነው፡፡
ምን ያህል ልጆች አፈራችሁ?
11 ልጆችን ወልደናል፡፡ ከአብራካችን ክፋዮች በተጨማሪ የእሷንም የእኔንም የወንድም የእህት ልጆች በማሳደግ፣ አስተምረን ድረናል፡፡ 15 የልጅ
ልጆች አግኝተን፣ የአያትነትን ፀጋ አጣጥመናል። በቅርቡ ደግሞ ቅድመ አያት እንሆናለን፡፡ እኛ ልጆቻችንን ድረን ነበር፤ በቅርቡ 50ኛ ዓመት
የጋብቻ በዓላችንን ምክንያት በማድረግ፣ መልሰው እኛኑ ደግሰው ድረውናል፡፡ እኔ በእውነት ከዚህ በላይ በረከት ምን እንደሆነ አላውቅም፤
እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ ጤና ሀብት፣ እድሜ፣ ልጅ፣ የልጅ ልጅ፣ ተቀባይነትና ክብር ማግኘት… ብዙዎች የሚመኙት ፀጋ ነው፡፡ እኛ በዚህ
በኩል እግዚአብሔር አድሎናል።
ረጅም ዓመት በትዳር ተቻችሎና ተሳስቦ በሰላም የመኖር ምስጢሩ ምንድን ነው?
የመጀመሪያውና የመጀመሪያው ነገር በራስ መተማመን ነው፡፡ በራሱ በማንነቱ የሚተማመን ሰው፣ ወደ ትዳር ሲገባ፣ “እኔ” የሚለውን ነገር
አቁሞ፣ “እኛ” ማለት ይጀምራል፡፡ ወደ መተሳሰብና መረዳዳት ይገባል፡፡ የትዳር ትስስር ቃል ኪዳንም፣ በችግርም ሆነ በደስታ፤ በሀዘንም ሆነ
በፍስሃ የትዳር አጋርን መጋራት ነው፡፡ ይህን መስዋዕትነት ከፍሎ ከሚገኘው በረከት ተቋዳሽ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ባልም ሚስትም
ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ከተወጡ፣ ትዳር የማይሰምርበት ምክንያት የለም፡፡   
በትውልድ አካባቢዎ ብቻ ሳይሆን ለረጅም አመታት በኖሩበት አዲስ አበባም ከፍተኛ የልማትና የበጎ አድራጎት ተሳታፊ እንደሆኑ ሲነገር
ሰምቻለሁ፡፡ እስኪ የአዲስ አበባ ተሳትፎዎን ይንገሩኝ?
ባለሁበት አካባቢ ማለትም በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ፣ በተለይ በደርግ ዘመን የቀበሌ ሊቀመንበርም ነበርኩኝ፡፡ በዚያን ጊዜም መንገድ በማሰራት፣
ትምህርት ቤቶችን በማጠናከር፣ የተቸገሩ ወገኖች እርዳታ እንዲያገኙም በማስተባበር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጌያለሁ። በልማትም ሆነ ሌሎችን
ለመደገፍ በሚደረግ ጥሪ ካመንኩበት ወደ ኋላ አልልም፡፡ ባለቤቴም ‹‹ይህን ለምን አደረግህ?›› አትለኝም፤ እንዲያውም ታበረታታኛለች እንጂ፡፡
በቅርቡ ለምሳሌ ለልብ ህሙማንና በደም ካንሰር ለሚሰቃዩ ወገኖች እንዲሁም በአካባቢያችን ላሉ እረዳት ለሌላቸው አይነስውራን የበኩሌን
አድርጌያለሁ፡፡ በምሳሌነት የምጠቅሰው ሌላው አንድ አብሮ አደጌ ነው፤ ግን ረዳት የለውም፡፡ በቅርቡ ባጋጠመው ህመም ኮሪያ ሆስፒታል
አስገብቼ፣ እስከ 50 ሺህ ብር በሚደርስ ወጪ አሳክሜው ከሞት ተርፏል፡፡ ጤናማና ጎረምሳ በነበርኩበት ጊዜ የቀይ መስቀል አባልም ነበርኩ፡፡
አሁን ይህን ሁሉ የምነግርሽ ለጉራና ይህን አደረግሁ ለማለት ሳይሆን፣ አንደኛ ጥያቄሽ መመለስ ስላለበት፤ ሁለተኛ ሌሎች ለበጎ አድራጎት
እንዲነሳሱ ለማድረግ ነው፡፡
አሁን በጤናዎት ላይ ችግር አጋጥሞዎታል እንዴ?
 አንዳንድ ነገሮች አሉ፡፡ ከእድሜ ጋር አብረው የሚመጡ ናቸው፡፡ ይህ እንግዲህ ምንም ሊደረግ የማይችል ነው፡፡ ነገር ግን በእድሜ ዘመኔ
በሰራኋቸው ስራዎች እኮራለሁ፡፡ ለበጎ አድራጎት ወይም ለእርዳታ በማወጣው ገንዘብ አልቆጭም፡፡ ባለቤቴም እንዲሁ ናት፤ በጉዳዩ
እስካመንኩበት ጊዜ ድረስ ያለኝን ማካፈል ግዴታዬ ነው ብዬ ስለማስብ አደርጋለሁ፡፡
በትውልድ አካባቢያችሁ ት/ቤት፣ መንገድ፣ ድልድይ፣ ቤተ ክርስቲያን ሰርታችኋል፡፡ አሁንስ በአካባቢያችሁ የጎደለ ነገር የለም?
እኛ ከአባቶቻችን የወረስናቸው ጥሩ ነገሮች አሉ። ከነዚህም መካከል ለሰው ማዘንና ሩህሩህ መሆን ነው። ከራስ ይልቅ ለሌላው መኖርን አስተምረውናል። በአካባቢው ብዙ ጉድለቶች ነበሩ፡፡ እነሱ ወቅቱ ስላልፈቀደላቸው ት/ቤት፣ መንገድ፣ መብራት፣ ውሃና ቤተ ክርስቲያን መስራት አልቻሉም፡፡ ነገር ግን ሁሉም ለሰው ልጅ በጣም አስፈላጊ ናቸው፡፡ አሁን ሆስፒታሎች ተገንብተዋል፤ ት/ቤቶችም፣ መንገዶችም ተሰርተዋል፡፡ መንገዶችን ስንሰራ፣ ከመንግስት ምንም ሳንጠይቅ በራሳችን ጥረት ነው፡፡ ከዋና መንገድ ሁሉ አልፈን፣ በየቅያሱም  እየገባን መንገድ ተሰርቷል፡፡ በቅርቡ መንግስት የሰራነውን መልካም ስራ በማየት፣  ከእኛ ቀጥሎበታል፡፡ አካባቢያችን ለም ነው፤ ውሃ አለ። መብራት ከፊሉ ማግኘት ጀምሯል፡፡ ቀስ በቀስ ይዳረሳል፡፡ይሄን ያህል አለማም የምንለው ጎልቶ የታየን ችግር የለም፡፡ ውሃን በሚመለከት፣ እንኳን የእኛን፣ አርሲን በሙሉ የሚያጠግብ ጅረት አለ፡፡ በባለሙያ አስመርምረነዋል፡፡ መንግስትም ሆነ የእኛ አቅም ጎልብቶ በደንብ ስንገፋ፣ በአካባቢው ችግር መቶ በመቶ ይጠፋል፤ ሁሉም በእጃችን ነው፡፡
ማህበረሰባችሁ ያለውን የትብብርና የመደጋገፍ ባህል ለሌላው አካባቢ ማህበረሰብ ለማካፈል ምን ታስባላችሁ? ከዋናው የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር ጋር ያላችሁስ ግንኙነት ምን ይመስላል?
ከጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለን፡፡ በስሩ ካሉት ማህበሮችም አንዱ የኛ የዶቢ ማህበር  ነው፡፡ እንደ ማንኛውም የጉራጌ ተወላጅ ልማቱ ይመለከተናል፤ የምንጠየቀውንም አስተዋፅኦ ሳናመነታ እናደርጋለን፡፡ ለምን? ይህ የልማት ማህበር አሁን የተመሰረተ አይደለም። የትኛውም አካባቢ ልማት ሳይኖር ጉራጌ አካባቢ ነበረ፡፡ በተለይ ወደ ሰባት ቤት ጉራጌ ብትሄጂ፣ በእነ ጀነራል ወልደ ስላሴ በረካ፣ በመንገድ
ልማትና በሌሎችም ተጀምሮ ወደ አለም ገናም ስንሄድ፣ ‹‹አለምገና ወላሞ ሶዶ›› የሚባል የልማት ማህበር ነበር፡፡ በአጠቃላይ ልማታዊው መንግስት መጥቶ፣ ስለ ልማት ምንነትና ጥቅም ለመላ አገሪቱ ካስተዋወቀ በኋላ፣ ሁሉም አካባቢዎች የልማት ማህበር ተቋቋመ እንጂ በፊት የጉራጌ ልማት ማህበር ብቻ ነበር፡፡ ይሄ እንግዲህ ቀደም ብዬ እንደተናገርኩት፣ ከአያት ቅድመ አያቶቻችን የመጣ የልማት፣ የመረዳዳትና
የመደጋገፍ ባህል በመሆኑ በእኛ ይበልጥ እንዲጎለብት ነው ያደረግነው፤ ወደፊትም አይቋረጥም፡፡ ይህን እግዜርም ሰውም ይወደዋል፡፡  ይህን ባህል ለሌላው ማህበረሰብ ለማስተላለፍ ምን እያደረጋችሁ ነው ላልሽው፣ አሁን በቅርቡ ጥያ አካባቢ፣ ይህን ባህል ለማስተዋወቅ ጥረት ተደርጓል፤ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡

Tuesday, 24 January 2017 15:09

የዘላለም ጥግ

  (ታላላቅ ሰዎች በመሞቻቸው ሰዓት)

· “ሚስቴን፣ ልጆቼን፣ የልጅ ልጆቼን ሁልጊዜም እወድ ነበር፡፡ ሀገሬንም እወድ ነበር፡፡ አሁን መሄድ እሻለሁ፡፡ እግዚአብሔር ውሰደኝ”
     ድዋይት ዴቪድ አይዘንአወር - (34ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት)
· “በቃ! እየሄድኩ ነው! እየሄድኩ ነው!”
     አል ጆልሰን (አሜሪካዊ ዘፋኝ፣ የፊልም ተዋናይና ኮሜዲያን)
· “የማዝነው ለአገሬ የምሰዋው አንድ ህይወት ብቻ ስላለኝ ነው”
  (የብሪቲሽን መንግስት ሰልለሃል ተብሎ በኒውዮርክ ሊገደል ሲል የተናገረው)
     ናታና ሃሌ (አሜሪካዊ ወታደር)
· “በመጨረሻ ማርሊን አገኛታለሁ”
(ስለሞተችው የቀድሞ ሚስቱ ማርሊን ሞርኖ የተናገረው)
    ጆ ዲማጊዮ (አሜሪካዊ የቤዝቦል ተጫዋች)
· “በሞት ጥላ ሸለቆ ውስጥ እንኳን ሁለት ሲደመር ሁለት ስድስት አይሆንም”
    ሊዮ ቶልስቶይ (ሩሲያዊ ደራሲ)
· “አምላኬ፤ ምን ተፈጠረ?”
    ልዕልት ዲያና
· “እማዬ፤ እየሞትኩ ነው”
    ብሪታኒ መርፊ (አሜሪካዊ የፊልምና የመድረክ ተዋናይት)
· “ደረቴ ላይ ተኩሱ!”
 (ከወህኒ ቤት አምልጦ ከተገኘ በኋላ፣ ሊገደል ሲል የተናገረው)
    ቤኒቶ ሙሶሎኒ (የጣልያን ፋሺስት መሪ)
· “በአርቴፊሻል መንገድ ዕድሜን ማስረዘም ጣዕም አልባ ነው፡፡ የድርሻዬን ተወጥቼአለሁ፤ አሁን የመሰናበቻ ጊዜ ነው፡፡ በግርማ ሞገስ
እፈፅመዋለሁ፡፡”
   አልበርት አንስታይን (ጀርመናዊ ሳይንቲስት)
· “ይሄ አሟሟት አሰልቺ ነው”
   ሪቻርድ ፌይንማን (አሜሪካዊ ሀኪም፣ ደራሲና ሙዚቀኛ)
· “ወንዙን እንሻገርና ከዛፎች ጥላ ስር እንቀመጥ”
 (በውጊያ ላይ ቆስሎ፣ሊሞት ሲል የተናገረው)
     ስቶንዎል ጃክሰን (አሜሪካዊ ጀነራል)
· “መብራቱን እንዳታበሩት!”
   ኦሳማ ቢን ላደን (የአልቃይዳ መስራችና መሪ)

Sunday, 22 January 2017 00:00

ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ!

   ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት ቆንጅዬ የገበሬ ልጅ፣ ወደ ላሚቱ ትሄድና ወተት ታልባለች፡፡ ወተቱን በጮጮ ጭንቅላቷ ላይ አድርጋ ወደ ቤቷ ስትመለስ፣ አንዳንድ ሀሳቦች ማውጣትና ማውረድ ትጀምራለች፡፡
“አሁን ይህን ወተት እንጥና ቅቤ አወጣለሁ፡፡ ያንን ቅቤ እወስድና ገበያ እሸጠዋለሁ፡፡ ይሄ የመጀመሪያ ሥራዬ ይሆናል፡፡ ከዚያ በማገኘው ገንዘብ ዕንቁላል እገዛለሁ፡፡ ያ ዕንቁላል ጫጩት ይፈለፍልልኛል፡፡ የተፈለፈሉትን ጫጩቶች አሳድጋቸዋለሁ፡፡ እነዚያን እወስድና ገበያ እቸበችባቸዋለሁ፡፡ ከዚያ ያገኘሁትን ብር ቀሚስ፣ ሸሚዝ፣ ሻሽና ጫማ እገዛበታለሁ። ‹ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ› ነውና፣ ያንን ቀሚስ እለብሳለሁ፡፡ ያንን ጫማ እጫማለሁ፡፡ ዝንጥ ብዬ የጥምቀተ - ባህሩ በዓል ዘንድ እሄዳለሁ፡፡
“ያኔ ወንድ ሁሉ እኔን ብቻ ነው የሚያየው፡፡ አንዱ ሲጠቅሰኝ፣ አንዱ “ሎሚ ጣሉባት በደረቷ” ሲል፤ እኔ ግን ምንቅንቅ ምንቅንቅ፣ አንገቴን ወዲህ ንቅንቅ፣ ወዲያ ንቅንቅ እያደረግሁ፣ ወንዱን ሁሉ ጭንቅንቅ አደርገዋለሁ” ስትል፤ ያ ራሱዋ ላይ አስቀምጣው የነበረው ጮጮ መሬት ላይ ወርዶ ይከሰከሳል፡፡ ያ ሁሉ ለብዙ ታቅዶ፣ ለብዙ ታልሞ የነበረው ወተት አካባቢው ላይ ፈሶ ቀረ!!
                                     *      *    *
ብዙ ባለምን፣ ብዙ ባቀድን ቁጥር አንዱንም ሳንተገብረው እንቀራለን፡፡ “ላም አለኝ በሰማይ፣ ወተቷንም አላይ!” የሚለው ተረት ሰለባ እንሆናለን፡፡ በሀገራችን በርካታ ዕቅዶች ይታቀዳሉ፡፡ በርካታ መመሪያዎች ይወጣሉ፡፡ በርካታ አዋጆችም ይታወጃሉ፡፡ በሥራ ላይ የሚውሉት ግን እጅግ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ አያሌ ግምገማዎች ይካሄዳሉ፡፡ ስህተቶችም ይታረሙ ዘንድ አስተያቶችና ሂሶች ይሰጣሉ፡፡ በውጤታቸው ሲታዩ ግን “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” ሆነው ይገኛሉ፡፡ ይህ የሚሆንበት ምክንያት አፋችን የሚናገራቸውን ልባችን ስለማይቀበለው ነው፡፡ “ጥልቅ ተሃድሶ” እንላለን እንጂ ወደ ውስጣችን ያልዘለቀ “የአንገት በላይ” ጉዞ ስምንጓዝ ነው! “ከዋሸህ ሽምጥጥ፣ ከመታህ ድርግም! ማድረግ ነው!” ይል ነበር ሟቹ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን፤ ነብሱን ይማረው፡፡ አባባሉ ግን ቋሚ ነው፡፡ ግምገማ የምናካሂደው ሰዎችን ለማልማት እንጂ ሰዎችን ለማንሳፈፍ መሆን የለበትም! መንቀዝን (Degeneration) ለመቋቋም እንጂ አወዳደቃችንን አሳምርልን (soft - landing) ለማለት መሆን የለበትም፡፡
በየትኛውም መልኩ አገር ቁልቁል እንድታድግ አንመኝም፡፡ ዛሬ፤ በተለይ በዋና ከተማችን በአዲስ አበባ፤ ሌላው ችግር ሳያንሰን ደግሞ አዲስ ችግር እያስተናገድን እንገኛለን - የሞተር ብስክሌተኞች አደጋ! ከችግር ወደ ችግር ጉዞ! “የበላችው ያቅራታል፣ በላይ በላዩ ያጎርሳታል!” ነው ነገሩ፡፡ “ለእግረኞች ቅድሚያ ባለመስጠት” ለሁሉም ችግር መፍትሄ አይሆንም!
“ፓናሲያ” እንደሚሉት፣ ፈረንጆቹ፤ ‹አንድ መድሐኒት ለሁሉ በሽታ መድህን አይሆንም። በሽታን እየለዩ ማከም ነው የሚያድነን!›
እስቲ የሚከተሉትን አባባሎች አንድምታቸውን ልብ እንበል፡፡ ደጋግመን እንላቸዋለን እንጂ አልተማርንባቸውም! ዛሬም እንድገማቸው፡- ‹‹ሞተር ብስክሌት ስትገዛ፣ የሬሣ ሳጥን አብረህ ግዛ!››
አንድ ሰው፤ ‹‹ሞተር ብስክሌተኛ ማነው?›› ተብሎ ተጠየቀ፡፡
ሰውዬው እንዲህ ብሎ መለሰ ይባላል፡-
‹‹ሞተር ብስክሌተኛ ማለት፣ ወደሚቀጥለው ከተማ እሄዳለሁ ብሎ ወደሚቀጥለው ዓለም የሚሄድ ሰው ነው!››
ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ፣ በየተጨናነቀው የመኪና ትራፊክ መካከል ውር ውር፣ ብቅ-ጥልቅ የሚሉ፣ እየተጥመዝመዙ ቁልቁል ሽቅብ የሚበሩ፣ ድንገት ሹክክ እና ድንገት ፈትለክ የሚሉ፤ በርካታ የሞተር ብስክሌቶች አሉ፡፡ አገልግሎታቸው ፈጣንና ቀልጣፋ መሆኑ እያጠያይቅም፡፡ መልዕክቶችን ያደርሳሉ፡፡ ፓስታዎችን ያከፋፍሉ፡፡ የመኪና መለዋወጫ ዕቃዎችን ወደ ተፈለገው ቦታ ያቀብላሉ፡፡ ጫት ያደርሳሉ፡፡ ምግብ በሰዓቱ ይወስዳሉ ወዘተ… ይሄ ሁሉ ደጎናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ክፉ ጎናቸው ግን እየተከሰተ መሆኑ አሳሳቢ ሆኗል፡፡
በከተማችን አዲስ አበባ በሞተር ብስክሌተኞች አደጋ እየደረሰባቸው ያሉ ዜጎች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ ቄራ ቡልጋሪያ አካባቢ መንገድ ሲያቋርጡ በሞተረኛ ተገጭተው የሞቱ የልጆች እናት በጣም ያሳዝናሉ፡፡ በዚሁ ሰሞን በሞተረኛ ተገጭቶ እግሩ የተሰበረ አምራች ወጣት የአልጋ ቁራኛ ሆኗል፡፡ ወደ ትምህርት ቤት ሊማር ሲሮጥ የሞተረኛ ሰለባ የሆነ ታዳጊ ወጣት አለ፡፡ ሌላውን ቤቱ ይቁጠረው፡፡ መርካቶ፣ ጉለሌ፣ ኮተቤ፣ አራት ኪሎ ወዘተ… በርካታ የሞተር አደጋ ተሰምቷል፡፡ ኢትዮጵያ በትራፊክ አደጋ ከፍተኛውን ደረጃ ይዛለች መባሉ መቼም ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው! በአብዛኛው የአሽከርካሪዎች ምን-ግዴነት ወይም ንዝህላልነት መሆኑ ተደጋግሞ ተነግሯል፡፡ ፈረንጆቹ Recklessness የሚሉት  መሆኑ ነው! አሁን አሁን እጅግ እየከፋ የመጣው ግን የሞተር አሽከርካሪዎች አደጋ ነው። አብዛኞቹ አሽከርካሪዎች ወጣቶች ናቸው፡፡ የእሳት-እራት ዘመናቸው ላይ ያሉ ናቸው። ጀብድ ወዳድ፣ (Adventurist) ናቸው፡፡ ተወዳዳሪ የለንም ብለው የሚያስቡ ናቸው። ዛሬ አንዴ ተጥመዝምዘውና አቆራርጠው በፍጥነት አደጋዎችን ማለፋቸውን እንጂ ነገ ምን እንደሚገጥማቸው ከቶም ቁብ የሚሰጡት ጉዳይ አይደለም፡፡ አንዲት ጉብል ከባንክ ገንዘብ አውጥታ ስትሄድ፤ ያስተዋለ ሞተረኛ ወጣት፣ ቦርሳዋን ከእጇ መንትፎ፣ በእግረኛ መንገድ ሲበር፣ ራሱ ተገልብጦ የአካል ጉዳት ደርሶበታል፡፡ ጎበዝ! የሞተረኞች ነገር አደጋው ፈርጀ- ብዙ ነው፡፡ የሚመለከተው የመንግሥት መሥሪያ ቤት ጉዳዬ ሊለው ይገባል! የሞተር ብስክሌተኞች መንጃ-ፈቃድ ሊተፈሽ ይገባዋል! እስከዛሬ ያሉን የአደጋዎች ዓይነት ሳያንሰን ደግሞ የጥቂት ሞተር - ሳይክሊስቶች አደጋ እንቅልፍ- ሊነሳን አይገባም! እናስብበት! ‹‹አደጋ የማይለያት አገር›› የሚል አገላለፅ  መለያ ስማችን ሊሆን አይገባም! ‹‹ለምጣዱ ሲባል አይጢቱ ትለፍ›› እያልን እስከ መቼ ችግሮቻችንን እያስታመምን እንዘልቃለን? ችግሮቻችንን አንድ በአንድ እንምታ!!

  90 ሚ. ዶላር ወጥቶበታል

        አወዛጋቢው ዶናልድ ትራምፕ ከእልህ አስጨራሽ ፉክክርና የቃላት ፍልሚያ፣ ከብዙ ትችትና ውዝግብ፣ ከብዙ አስደንጋጭና አነጋጋሪ ክስተቶች እንዲሁም አለምን ካስደነገጠ ያልተጠበቀ ድል በኋላ፣ በትናንትናው ዕለት ልዕለ ሃያሏ አገር ሊመሩ፤ ቃለ - መሃላ ፈጽመው 45ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆኑ፡፡
ትናንት በዋሽንግተን ዲሲ የተካሄደውን የትራምፕ በዓለ ሲመት በተመለከተ የአለማችን የመገናኛ ብዙሃን ካሰራጯቸው ዘገባዎች ያገኘናቸውን መረጃዎች እነሆ!
የጸጥታ ስጋት
በዓለ-ሲመቱ በሽብርተኞችና ሁከት ፈጣሪዎች እንዳይስተጓጎል ለማድረግ ጥብቅ ፍተሻና የደህንነት ጥበቃ ተደርጓል፡፡ ከ28 ሺህ በላይ የጸጥታ ሃይሎች በተጠንቀቅ ቆመው በዓሉን ከስጋት ለመታደግ ሲሰሩ ውለው አድረዋል፡፡ የተለያዩ ፕሮግራሞች የሚከናወኑባቸው ስፍራዎችም በረዥም መከላከያ አጥሮች ተከልለው ነበር፡፡
በበዓለ-ሲመቱ ላይ የሚቀርቡ የተለያዩ ዝግጅቶችን የሚታደሙ እንግዶች እስከ ስድስት ጊዜ ያህል ፍተሻ እንደተደረገባቸውና ታዳሚዎችም 40 ያህል የተለያዩ ቁሳቁሶችን በዝግጅቶቹ ላይ ይዘው እንዳይገኙ መከልከላቸው ተነግሯል፡፡
ታዳሚ እና ቀሪ
በትራምፕ በዓለ ሲመት ላይ የተገኙ ታዳሚዎች ቁጥር 900 ሺህ እንደሚደርስ የተገመተ ሲሆን ይህ ቁጥር ከተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በዓለ-ሲመት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ነው ተብሏል። በ2009 በተከናወነው የኦባማ በዓለ-ሲመት ላይ 1.8 ሚሊዮን ያህል ሰዎች መታደማቸውን ዘገባዎች አስታውሰዋል፡፡
ተሰናባቹን ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማንና ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማን ጨምሮ፣ የቀድሞዎቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ቢል ክሊንተን፣ ጆርጅ ደብሊው ቡሽና ጂሚ ካርተር ሁሉም ከነባለቤቶቻቸው በዓለ-ሲመቱን ታድመዋል፡፡
በአንጻሩ ደግሞ፣ ከ60 በላይ የሚሆኑ የዲሞክራት ፓርቲ አባላት በበዓለ ሲመቱ ላይ እንደማይገኙ ባስታወቁት መሰረት፣ ሳይገኙ መቅረታቸው ተዘግቧል፡፡
በድጋፍ እና በተቃውሞ የታጀበው በዓል
ይህንን በዓለ-ሲመት ለየት የሚያደርገው በትራምፕ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች ሰልፍ መታጀቡ ነው፡፡ በትራምፕ በዓለ-ሲመት ላይ ሊደረጉ የታቀዱ የተቃውሞ ሰልፎች ብዛት፣ በቅርብ ጊዜ የአገሪቱ ታሪክ እጅግ ከፍተኛው እንደሆነ ተነግሯል። በዋሽንግተንና በሌሎች የአገሪቱ ከተሞች ከበዓለ-ሲመቱ ጋር በተያያዘ ሊካሄዱ ለታቀዱ 30 ያህል የተቃውሞ ሰልፎች ህጋዊ እውቅና መሰጠቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከሁሉም የተቃውሞ ሰልፎች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው ሴቶች የሚያስተባብሩትና 200 ሺህ ያህል የትራምፕ ተቃዋሚዎች ይሳተፉበታል የተባለውና ዛሬ በዋሽንግተን ዲሲ እንደሚደረግ የሚጠበቀው የተቃውሞ ሰልፍ ነው፡፡ አወዛጋቢው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተቃውሞ የገጠማቸው በአገራቸው ብቻም አይደለም፡፡ ተቃውሞው ወደ እንግሊዝም የዘለቀ ሲሆን ትናንት በለንደን የተለያዩ አካባቢዎች ትራምፕን የሚቃወሙ መፈክሮች ተሰራጭተዋል። ሲሆን ከ20 በላይ በሚደርሱ የተለያዩ የእንግሊዝ ከተሞችና በአውስትራሊያ ሲድኒ የተቃውሞ ሰልፎች እንደሚካሄዱ ይጠበቃል፡፡
በፊሊፒንስ የተካሄደው ተቃውሞ ግን ከሁሉም ይብሳል፡፡ ትናንት በማኒላ ትራምፕን ተቃውመው ሰልፍ የወጡ ፊሊፒንሳውያን፤ የአሜሪካን ሰንደቅ አላማ በአደባባይ አቃጥለዋል፡፡
ምን ያህል ገንዘብ ወጣበት?
ለትራምፕ በዓለ-ሲመት በድምሩ 90 ሚሊዮን ዶላር ያህል ገንዘብ ወጪ የተደረገ ሲሆን ይህ ገንዘብ በአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች የበዓለ-ሲመት ወጪ ታሪክ ከፍተኛው ነው ተብሏል፡፡
ብዙዎች ያልታደሙት የሙዚቃ ድግስ
የበዓለ ሲመቱ አካል ከነበሩት ዝግጅቶች መካከል ታዋቂ ድምጻውያን የተሳተፉበትና የሙዚቃ ዝግጅት አንዱ ነበር፡፡ ከትናንት በስቲያ  በተካሄደው የሙዚቃ ዝግጅት 10 ሺህ ያህል ተመልካቾች የታደሙ ሲሆን፣ ይህ ቁጥር ከኦባማ የበዓለ ሲመት የሙዚቃ ታዳሚዎች አንጻር እጅግ አነስተኛ ነው ተብሏል፡፡ በኦባማ የበዓለ-ሲመት የሙዚቃ ዝግጅት ላይ የተገኙ ተመልካቾች ቁጥር 400 ሺህ ያህል እንደነበር ተነግሯል፡፡
በዚህ በዓለ ሲመት ላይ የ16 አመቷ ታዳጊ ድምጻዊት ጃኪ ኢቫንቾ፤ የአሜሪካን የህዝብ መዝሙር ያቀረበች ሲሆን ድምፃውያኑ ቶቢ ኬዝ፣ ላሪ ስቴዋርትና ሪቼ ማክዶናልድም በዓሉን በሙዚቃ ስራዎቻቸው ካደመቁት ታዋቂ ድምጻውያን መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
ካዲላክ ዋን
ትራምፕ ወደ በዓለ-ሲመቱ ያቀኑት እጅግ ዘመናዊና ውድ በሆነቺው አዲሷ ካዲላክ ዋን መኪናቸው ነው፡፡ 1.5 ሚሊዮን ዶላር የወጣባት ይህቺው መኪና፤ የተለያዩ ጥቃቶችን ለመቋቋም እንድትችል ተደርጋ የተሰራች ሲሆን፣ ጥቃት ሊሰነዝርባት በሞከረ ወገን ላይ አፋጣኝ የአጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ ተጠቁሟል፡፡

Saturday, 14 January 2017 16:14

“ESOG… 25ኛ አመት...”

ጥር 25-27 የኢትዮያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር 25ኛ አመት የብር ኢዮቤልዩ፣
ጥር 25-27 የኢትዮያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ESOG ›መታዊ ጉባኤ፣
ጥር 25-27 የአፍሪካ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ፌደሬሽን 2ኛ ጉባኤ ይካሄዳል።
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ከተቋቋመ 25 አመት ሞላው። ጉባኤው የሚከና ወነው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ጤና ጥበቃ ሚኒስር፣ የአለም የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ፌደሬሽን እና የአፍሪካ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ፌደሬሽን በተባባሪነት በማ ዘጋጀት ነው። የኢትዮያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ባለፉት 25 አመታት የሰራቸው ስራዎች ምን እንደሚመስሉ ዶ/ር ደረጀ ንጉሴ የማህበሩ ፕሬዝዳንት እንደሚከተለው አብራርተዋል።
በስነተዋልዶ ጤና የሚያገለግሉ ሙያዊ ትንተናዎችን ለማቅረብ በአገር ደረጃ በሚዋቀሩ የተለያዩ ኮሚዎች ውስጥ በመሳተፍ ሁነኛ የሆነ አስተዋጽኦ አድርጎአል።
ባለፉት 25 አመታት ከ20 በላይ የሆኑ እጅግ ተጠቃሽ የሆኑ ፕሮጀክቶችን ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር አከናውኖአል።
ኤችአይቪ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ ለመግታት ደረጃውን የጠበቀ ሕክምና እንዲሰጥ ከማድረግ አኩዋያ ወደ 70የሚሆኑ የህክምና ድርጅቶች ውስጥ የሚገኙ ባለሙያዎችን ማሰልጠንና በተጨማሪም ክትትል በማድረግ የበኩሉን ሚና ተጫውቶአል።
በመካከለኛ ደረጃ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎችን በማዋለድ ተግባር ላይ የተሸለ ክህሎት ኖሮአቸው በተለይም በኦፕራሲዮን መውለድ የሚያስፈልጋቸውን እናቶች ከመደገፍ አኩዋያ ቁጥራቸው ወደ 47 ለሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች ስልጠና ሰጥቶአል። ይህ ስልጠና እስከ 6 ወር የደረሰ ተከታታይ ስልጠና ሲሆን በተለይም እስፔሻሊስት ሐኪሞች በማይገኙበት ቦታ ለወላድ እናቶች ባለሙያው አስፈላጊውን እገዛ ሊያደርግ የሚችልበት ስራ ተሰርቶአል። በዚህም ፕሮጀክት እስከ መቶ ሺህ እናቶች ተጠቃሚ ሆነዋል።
በወሲባዊ ጥቃት እና ትንኮሳ ዙሪያ በተለይም ሴቶች ጥቃቱ ከደረሰባቸው በሁዋላ ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኙ እና ክትትል እንዲደረግላቸው የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በአዲስ አበባና በተለያዩ መስተዳድሮች ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ 6 ሞዴል ክሊኒኮችን በመመስረት ደረጃውን የጠበቀ ሕክምናና እንክብካቤ እንዲያገኙ አድርጎአል።
በማደግ ላይ ባሉ ክልሎችና በአርብቶ አደሮች አካባቢ የማህረሰቡን የስነተዋልዶ እውቀ ትና ግንዛቤ ከማሳደግ አኩዋያ የሚሰሩ ስራዎች ያሉ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ሙያተ ኞች እርህራሔንና ተገቢ የሆነን የህክምና እርዳታ ለተገልጋዩ ለማዳረስ የሚችሉበትን ስልጠና ማህበሩ በመስጠት ላይ ነው።
ማህበሩ ከ20 በላይ የሚሆኑ ሙያነክ መመሪያዎችን በማዘጋጀት ደረጃውን የጠበቀ ግልጋሎት ለማህበረሰቡ እንዲሰጥ ሲያደርግ ቆይቶአል።
 ስለዚህም በአጠቃላይ ላለፉት 25 አመታት ዘርፈ ብዙ የሆኑ በስነተዋልዶ ጤና ዙሪያ የተሰሩ ስራዎችን ማህበሩ አከናውኖአል። ከዚህም በተረፈ በአገር ውስጥ ከሚካሄዱት እንቅስ ቃሴዎች ባሻገር በምስራቅ ፣በመካከለኛውና በደቡብ አፍሪካ ሐገራት በተመሰረተው የማህጸንና ጽንስ ሕክምና ማህበር ፌደሬሽን ተሳትፎ ከማድረግም ባሻገር ማህበሩን የመምራት ኃላፊነትም ለኢትዮጵያ ጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር የተሰጠበት ሁኔታ ታይቶአል። የአፍሪካው የጽንስና ማህጸን ሕክምና ማህበር ፌደሬሽን በሚቋቋምበት ጊዜ የኢትዮጵያ ጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር አባላት ተሳትፎ ከማድረግም ባሻገር አሁንም በስራ አስፈጻሚ ቦርድ ውስጥ ሁለት የማህበሩ አባላት በመስራት ላይ ናቸው። በአለም አቀፍ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ፌደ ሬሽን ውስጥም ለመጀመሪያ ጊዜ ከሰሐራ በታች ያሉ ሐገራትን በመወከል በስራ አስፈጻሚነት ውስጥ ካሉ 6 ኦፊሰሮች ውስጥ አንዱ የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር አባል ስለሆነ ይህም ማህበሩ ከአገር ውስጥ እንቅስቃሴው አልፎ በአፍሪካና በአለም አቀፍ ደረጃም ሙያዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ያለ ድርጅት መሆኑን ዶ/ር ደረጀ አብራርተዋል።
 የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር 25ኛውን የብር ኢዮቤልዩ እና አመታዊ ጉባኤውን በሚያከብርበት ጊዜ የአፍሪካው የጽንስና ማህጸን ሕክምና ፌደሬሽንም ስብሰባውን አብሮ ያካሂዳል። የአፍሪካው ፌደሬሽን የመጀመሪያውን ስብሰባ ያደረገው እዚሁ አዲስ አበባ ሲሆን በዚያን ጊዜ በስብሰባው የተሳተፉት ወደ 800 የሚሆኑ እንግዶች ነበሩ። የተሳተፉት ሐገራት ብዛትም ወደ 67 ይደርስ ነበር። ሁለተኛው ስብሰባም በኬንያ የተካሄደ ሲሆን አሁን ደግሞ በኢትዮጵያ ሊካሄድ ታቅዶአል። ዶ/ር ይርጉ ገ/ሕይወት የአፍሪካ ጽንስና ማህጸን ሕክምና ፌደሬሽን የመጀመሪው ፕሬዝዳንት የነበሩ ሲሆን አሁንም በአለም አቀፉ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ፌደሬሽን ስራ አስፈጻሚነት የሚሰሩ ናቸው።
 እንደዶ/ር ይርጉ ማብራሪያ በአፍሪካ ውስጥ 54 ሀገራት የሚገኙ ሲሆን በአፍሪካው የጽንስና ማህጸን ሕክምና ፌደሬሽን የተወከሉት ግን 32 ሐገራት ብቻ ናቸው። ይህ የሆነበት ምክንያትም ፌደሬሽኑ አባል የሚያደርገው ግለሰቦችን ሳይሆን በማህበር ደረጃ እውቅና ያላቸውን ሐገራት ብቻ ስለሆነ ነው። አንዳንድ ሐገራት ውስጥ በቂ የጽንስና ማህጸን ሐኪም ባለመኖሩ ወይንም በአንዳንድ ሐገራት ደግሞ ቁጥራቸው አነስተኛ በመሆኑ የተነሳ ማህበር ስላልመሰረቱ በአፍሪካ ፌደሬሽን ላይ መወከል አልቻሉም። ስለዚህም በቀጣዮቹ አመታት በየሀገራቱ በሚኖ ረው የጥንካሬ ደረጃ፣ በሚያፈሩት የሰው ኃይል እና በሚመሰርቱት ማህበር መሰረት የሚወ ከሉት ሐገሮች ቁጥር ይጨምራል የሚል ተስፋ አለን። ኢትዮጵያ ግን ፌደሬሽኑ ከመቋቋሙ በፊትም መስፈርቱን ያሟላች ስለነበረች በፌደሬሽኑ ተሳታፊ ሆናለች። ዶ/ር ርጉ ገ/ሕይወት ይህ ጉባኤ በሚካሄድበት ወቅት ስለሚደረጉት አበይት ክንውኖችም እንደሚከተለው ገልጸዋል።
 በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህር 25ኛ አመት በአልና አመታዊ ጉባኤ እንዲሁም በአፍሪካው የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ፌደሬሽን ስብሰባ ላይ ብዙ ሳይንሳዊ ጽሁፎች የሚቀርቡ ሲሆን ህብረተሰቡን እስከአሁን ከነበረው በተሻለ መንገድ ማገልገል እንዲያስችሉ የተነደፉ የተለያዩ ስልጠናዎች ይሰጣሉ።
ብሰባው ከመጀመሩ ሁለት ቀናት በፊት የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር አባሎችን በምርምር ስራ ማለትም የምርምር ጽሁፎችን በብቃት እና በጥራት የመጻፍ ክህሎት የሚያገኙበትን ስልጠና በአሜሪካ የጽንስና ማህጸን ኮሌጅ ማህበር ከሚመጡ ባለ ሙያዎች ጋር በመሆን እንሰጣለን። ይህም ምርምራቸውንም በጥራት በአገር ውስ ጥም ይሁን ከአገር ውጭ ለህትመት እንዲያበቁ የሚያስችል እውቀትን የሚያዳብር ነው።
የማህበሩ የስብሰባ መክፈቻ ቀንና ከዚያ አንድ ቀን በፊት በተከታታይ በአልትራሳውንድና የእርግዝና ክትትልን በሚመለከት የላቀ ሕክምና መስጠትን የሚያስችል ስልጠና ማህበሩ ከቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ጋር በመሆን ይሰጣል።
ከሌሎች ሐገሮች ከሚመጡ ተመሳሳይ ሙያ ካላቸው ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ማህበሩ የአንድ ቀን ስልጠና ያካሂዳል። በዚሁ ቀን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሃቨቋስቈቄ -ቋሰቄቅቨ የሚባለውን የህክምና ዘዴ በሚመለከት በተለይም የማህጸን ችግሮችን ማወቅና መለየት የሚቻልበትን አዲስ ክህሎት ለማህበሩ አባላት የሚሰጥበት ይሆናል።
የጽንስና ማህጸን ድንገተኛ ሕክምናን በተመለከተ ዘመናዊ ወይንም ወቅታዊ የሆኑ እውቀቶች እና ክህሎቶችን በመፈተሽ አሁን ከሚሰራበት በተሻለ ምን ምስራት ይቻላል የሚለውን ማህበሩ ከአሜሪካው የጽንስና ማህጸን ሕክምና ማህበር ጋር በመተባበር ያካሂዳል።
በማህጸን ጫፍ ካንሰርና ከማህጸን ግድግዳ በሚነሳ ካንሰር ላይ ያሉትን ለውጦች ወይንም ወቅታዊ ግኝቶች ከጀርመንና ከአሜሪካ ከሚመጡ ሙያተኞች ጋር በመተባበር ስልጠና ይሰጣል።
በቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ላይ በተለይም በቋሚነትና ለረጅም ጊዜ በሚያገለግሉ የቤተሰብ እቅድ ዘዴዎች ላይ ግማሽ ቀን የሚወስድ ስልጠና ይሰጣል።
 ዶ/ር ይርጉ በስተመጨረሻም ለስብሰባው በተያዙት ቀናት እ.ኤ.አ ፌብረዋሪ 2-4 ወይንም ከጥር 25-27 ድረስ ስልጠናውን የሚያገኙት የማህበሩ አባላትና ከሌሎችም ሐገራት የሚመጡ ተሳታፊዎች በጣም ዘመናዊና የመጨረሻ የሆነውን እውቀትና ክህሎት የሚያገኙበት መድረክ ነው። በዚህም ወቅት ወደ 60 የሚደርሱ ጥናታዊ ጽሁፎች በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ የሚቀርቡ ሲሆን የባለሙያዎችን እውቀት የሚያሰፋ እና ለህብረተሰቡም ጠቃሚ የህክምና አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል።

የቢራ ገበያውን ከተቀላቀለ አንድ አመት ተኩል የሆነው ሀበሻ ቢራ፤ በገና ዋዜማ ከጆርካ ኤቨንት ኦርጋናይዘር ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ‹‹ኢትዮጵያዊ›› የተሰኘ የሙዚቃ ኮንሰርት ከተገኘው የትኬት ሽያጭ ትርፍ 50 በመቶውን ሽሮሜዳ አካባቢ ለሚገኘው ‹‹ጌርጌሴኖን” የአዕምሮ ህሙማን ማዕከል ለገሰ፡፡ ባለፈው ማክሰኞ የኮንሰርቱን አጠቃላይ ሁኔታ ለመገምገምና ተባባሪ አካላትን ለማመስገን፣ በራማዳ አዲስ ሆቴል በተዘጋጀ የእራት ግብዥ ላይ ነው ግማሽ ሚሊዮን ብሩ የለገሰው፡፡
የሀበሻ ቢራ ማርኬቲንግ ማናጀር አቶ ጌታነህ አስፋው - ለ“ጌርጌሴኖን” የአዕምሮ ህሙማን ማዕከል መስራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ መለሰ አየለ ገንዘቡን ካስረከቡ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ የ“ገና በዓል የምስጋና፣ የመረዳዳት፣ የመጠያየቅና ደምቆ የመታያ በዓል በመሆኑ ከተገኘው የትኬት ሽያጭ ትርፍ ላይ 50 በመቶውን፣ (ግማሽ ሚሊዬን ብሩን) ለአዕምሮ ህሙማን መለገሳችን ያስደስተናል፤ ማዕከሉን በቀጣይ ለመደገፍ ድርጅቱ ዝግጁ ነው” ብለዋል፡፡
ድጋፍ በማጣት ማዕከሉን ወደ መዝጋት ታቀርበው እንደነበር የተናገሩት የ“ጌርጌሴኖን” መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ መለሰ አየለ፤ በተደረገላቸው ድጋፍ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው፣ ሀበሻ ቢራና ሰራተኞቹ ማዕከሉን ሲደግፉ የመጀመሪያቸው እንዳልሆነ ጠቁመው በህሙማኑ ስም አመስግነዋል፡፡ ሀሻ ቢራ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ኮንሰርቱን ያዘጋጀውን ጆርካ ኤቨንትን ያመሰገነ ሲሆን በቀጣይ አብሮ ለመስራት ፍላጎት እንዳለው ገልጿል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሙዚቃ ኮንስርቶችን በማዘጋጀት የሚታወቀው ጆርካ ኤቨንት፤ በአንድ ወር ውስጥ በመጀመሪያ አልበሙ ተወዳጅነት ያተረፈውን የሳሚ ዳንን ኮንሰርት እንደሚያዘጋጅ ገልፆ በቅርቡ አጠቃላይ የኮንሰርቱን መረጃዎች ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ ድርጀቱ በኢትዮጵያ ትልቁን የሙዚቃ ሽልማት ለማዘጋጀት በመሰናዳት ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡

Saturday, 14 January 2017 16:12

የቴክኖሎጂ ጥግ

ግብርና ዛሬ የተለየ መልክ ይዟል-
ገበሬዎቻችን አቅጣጫ ማመላከቻ ቴክኖሎጂ
(GPS) እየተጠ ቀሙ ነው፡፡ የመስኖ
ሥራህን በኢንተርኔት መቆጣጠር መከታተል
ትችላለህ፡፡
ዴቢ ስታብናው
· ኢንተርኔት፤ ደ ለራሲያንናለተደራሲያኖቻቸው
አዳዲስ የተለያዩ ዕድሎችንና ነፃነትን
ፈጥሮላቸዋል፡፡
ፍሬድሪክ ፎርሲዝ
· ኢንተርኔት የዓለማችን ትልቁ ቤተ መፃህፍት
ነው፡፡ መፃህፍቱ በሙሉ ያሉት ግን ወለሉ
ላይ ነው፡፡
ጆን አሌን ፓውሎስ
· በአሁኑ ዘመን እንግሊዝኛ የማይናገርና
ኢንተርኔት መጠቀም የማይችል እንደ ኋላ
ቀር ነው የሚቆጠረው፡፡
ልኡል አል-ዋሊድ፤ ሳኡዲ አረቢያ
· አይፓድ ሰዎች ከሙዚቃ ጋር ያላቸውን
አግባብ ሙሉ በሙሉ ለውጦታል፡፡
ካርል ላገርፊልድ
· ስማርት ቴክኖሎጂ እያደደበን ነው፡፡
ዳኒ ሜኪክ
· ቴክኖሎጂ ህይወትህን ማሻሻል እንጂ
ህይወትህ መሆን የለበትም፡፡
ቢሊ ኮክስ
· ቴክኖሎጂ የሰዎችን መሰረታዊ ፍላጎት ወይም
ተፈጥሮ አይለውጥም፡፡
ፕሪያ ኦርዲስ
· የዛሬ ዘመን ሳይንስ፣ የነገ ቴክኖሎጂ ነው፡፡
ኢድዋርድ ቴለር
· ቴክኖሎጂ ህብረተሰብን ይቀርፃል፤እናም
ህብረተሰብ ቴክኖሎጂን ይቀርፃል፡፡
ሮበርት ዊንተሮፕ ዋይት
· በዓለም ላይ ያሉ ቴክኖሎጂዎች በሙሉ ፈፅሞ
በጎ አስተሳሰብን አይተኩም፡፡
ሃርቬይ ማክኬይ

ለምዝገባ 500 ዶላር? የተሸላሚዎች ዝርዝር ውስጥ አልተካተቱም?


ባለፈው ህዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም በአሜሪካ ካሊፎርኒያ፣ትልቁ የአፍሪካ የፊልም ሽልማት “ናፍካ” ሥነ-ስርዓት ተካሂዷል፡፡ በየዓመቱ የሚካሄደው ይኼው የሽልማት ሥነስርዓት፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በወኪሉ “ቆንጆ ፕሮሞሽን”በኩል ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች እንዲወዳደሩ በሰጠውእድል ተዋንያን፣ ዳይሬክተሮች፣ የሜካፕ አርቲስቶች፣ሲኒማቶግራፈሮችና አንድ የበጎ አድራጎት መስራች በድምሩ
9 ሰዎች በእጩነት ወደ አሜሪካ ተጉዘው ነበር፡፡በተለይም ዝነኞቹ ተዋንያን ግሩም ኤርሚያስና ሩታመንግስተ አብ፤“ምርጥ የህዝብ ምርጫ ተዋንያን” በሚለውዘርፍ አሸናፊ መሆናቸው ተገልፆ፣በአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ተዘግቦ ነበር፡፡ የሽልማቱ ቦታ ላይ ሲደርሱ ግን
ብዙ ችግር እንደገጠማቸው፣ የናፍካው የኢትዮጵያ ተወካይ ሀሰተኛ እንደሆነና በሽልማት ቦታው ላይ ግራ ተጋብተው
እንደነበር፣ ሲወራ ሰንብቷል፡፡ከሽልማት ሥነ ስርዓቱ መካሄድ በኋላ አንድ ወር ከ10 ቀን ያህል በአሜሪካ ቆይቶ የተመለሰው አርቲስት ግሩም
ኤርሚያስ፤ በሽልማቱ ዙሪያ ያለውን እውነታ እንዲገልጽ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛዋ ናፍቆት ዮሴፍ እንደሚከተለው አነጋግራዋለች፡


ለናፍካ ሽልማት ወደ አሜሪካ ያደረጋችሁት ጉዞ ምን ይመስል ነበር?
እንግዲህ ለሽልማት ወደ ካሊፎርኒያ የሄድነው ሐሙስ ዕለት ማታ ነው፡፡ ለ21 ሰዓት በረራ አድርገናል፡፡ አርብ ጠዋት ደረስን፤ ቅዳሜ ሽልማቱ ነበር፡፡ አመሻሽ ላይ ነው ሽልማቱ የተካሄደው፡፡ እኛ ካረፍንበት ራቅ ያለ ቦታ ላይ ነው፡፡ በትራፊክ መጨናነቅና በራሳችንም ምክንያት ወደ አዳራሹ ዘግየት ብለን ብንደርስም፣ ሽልማታችንን ግን ተቀብለናል፡፡
ከዚህ ስለ ሽልማቱ ብዙ ተወርቶ ብትሄዱም፣ እዚያ ከደረሳችሁ በኋላ ችግር እንደገጠማችሁና የእናንተ ስም በተሸላሚዎች ዝርዝር ውስጥ እንዳልተካተተ፣ በተለያዩ የአገር ውስጥ ሚዲያዎች ተወርቷል፡፡ ወሬው ከየት የመጣ ነው?
በዚህ መልኩ የተፈጠረ ችግር የለም፡፡ መድረክ አካባቢ ትንሽ ማስተባበር የጎደላቸው ነገሮች ነበሩ። ለምሳሌ ተሸላሚዎች ስማቸው መድረክ ላይ ተጠርቶ ሽልማቱ ሳይቀርብ፣ ከመድረክ ጀርባ የወሰዱ አሉ፡፡ በሌላ በኩል፤ መድረክ መሪዎቹ “ከ1-5 የወጡ ፊልሞች እነዚህ ናቸው፤ አንደኛ የወጣው ደግሞ ይሄ ነው” ማለት ሲገባቸው፣ ቀድሞ ስክሪን ላይ ይለቀቅ ነበር፡፡ ይሄ አጓጊነቱን ይቀንሰዋል። እና የሽልማት ሂደቱ ላይ በአዘጋጆቹ ችግር ትንሽ የተዘበራረቁ ነገሮች ነበሩ እንጂ እኔና ሩታ ላይ ብቻ ተለይቶ የደረሰ ነገር አልነበረም፡፡ ከዝግጅቱ በኋላ እንዲህ የተዘበራረቀበትን ምክንያት ለማወቅ ሙከራ ስናደርግ፣ ከዚህ በፊት የተካሄዱትን አምስት የናፍካ ሽልማቶች ራሱ ሸላሚው ድርጅት ያዘጋጃቸው ሲሆኑ ጥሩ ሂደት እንደነበራቸው ሰምተናል፡፡ የዘንድሮው ለሌላ ኤጀንት በመሰጠቱ፣ ኤጀንቱ እንደ ጀማሪነቱ ትንሽ ክፍተት እንደተፈጠረበት ነው የተገለፀልን፡፡
ሁለታችሁ ሽልማቱን እንዳላገኛችሁ----በተለይም ሩታ ታጨች በተባለችበት ዘርፍ አንዲት ናይጀሪያዊት ሽልማቱን ይዛ ፎቶ መነሳቷ---እየተወራ ያለው ከምን መነሻ ነው?
እኔ ይሄ ነገር በምን መነሻ እንደተወራ፣ ወሬውን ማን እንዳዛመተውም አላውቅም፡፡ እኛ የሄድነው መዘጋጀቱ እውን በሆነ የሽልማት ስነ-ስርዓት ላይ ለመገኘት ነው፡፡ ሽልማታችንን አግኝተን ተመልሰናል። ይሄ “በሬ ወለደ” አይነት ወሬ በጣም ገርሞኛል፡፡ ሙያችንን እናሳድጋለን ብለን በምንጥርበት ጊዜ፣ እንዲህ አይነት ወፍ ዘራሽ ወሬዎች መናፈሳቸው እጅግ አሳፋሪ ነው፡፡
በናፍካ የኢትዮጵያ ተወካይ ነው የተባለውና የ“ቆንጆ ፕሮሞሽን” ስራ አስኪያጅ አቶ ማይክ በናፍካ እንዳልተወከለ፣ በአሜሪካ የታክሲ ሹፌር እንደሆነና ከኪነ-ጥበብ ጋር ግንኙነት እንደሌለውም ተወርቷል፡፡ ለምዝገባ እያንዳንዳችሁ 500 ዶላር ከፍላችኋል የተባለውስ--- ሰምተኸዋል?
የመጀመሪያው ነገር የናፍካ ተወካይ የታክሲ ሹፌር ከሆነም ነውር አይደለም፡፡ ሹፍርናም የተከበረ ሙያ ነው፡፡ ዋናው ነገር ይህንን እድል ለአገራችን ማምጣቱና የያዘው ራዕይ ትልቅ መሆኑ ነው፡፡ አንድ ሰው ታክሲ እየነዳ ወይም ሌላ ስራ እየሰራ፣ ጎን ለጎን ሌላ ተጨማሪ ስራ ቢሰራ ችግሩ ምንድን ነው፡፡ አየሽ ወሬው ሰውንና የሰውን ሙያ ከመናቅ ይጀምራል፤ ይሄ በጣም ያሳፍራል፡፡ እንደኔ እንደኔ ማይክ ሁሉቃ ወደ ኢትዮጵያ ይዞት የመጣው እድል፣ ለአርቲስቱና ለአገር ይጠቅማል አይጠቅምም የሚለው ነው መታየት ያለበት እንጂ ሌላው ነገር አይደለም፡፡ እንዲህ አይነት ጥሩ ዕድሎች ሲመጡ፣ ለማበላሸትና የሚሰራን ሰው ሞራል ለመንካት የሚደረግ ሩጫ ያሳዝናል፡፡ ዌብ ሳይቱን ናፍካ ብሎ ገብቶ ማየት ይቻላል፤ ሁሉም ነገር በግልፅ ይገኛል፡፡
ሩታን በተመለከተ ስሟ በስነ ስርዓቱ ተጠርቶ፣ መድረክ ላይ ወጥታ ንግግር አድርጋ፣ ሽልማቷን ተቀብላለች፡፡ እኔም እንደዛው፤ ሽልማቴ በቤቴ ይገኛል፡፡ በመጀመሪያ ሚዲያዎች ይህን ወሬ ተቀብለው  ዜና ሲሰሩ፣  እኛን የጉዳዩን ባለቤቶች ለምን አልጠየቁንም? ልክ አሁን አንቺ እንደምትጠይቂን፣ ለምን አልተጠየቅንም፡፡ እኛ በቦታው የነበርነውን የጉዳዩን ባለቤቶች መጠየቅ ነበረባቸው፡፡ ከሆነ አካል ወሬ ሰሙ፤ ዋና ባለቤቶቹን ሳይጠይቁ፣ የአንድ ወገን ሃሰተኛ ወሬ ይዘው ወጡ። ይሄ ነው ሁላችንንም ወደ ኋላ እየጎተተን ያለው፡፡ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ በዝግጅቱ በኩል አንዳንድ ክፍተቶች ነበሩ፤ ለምሳሌ ሰው ስሙ እየተጠራ መድረክ ላይ ሲወጣ፣ ገና አዋርዱ ወደ መድረክ አልመጣም፡፡ ብዙ ተሸላሚ ማለት ይቻላል … ሽልማቱን ከመድረክ ጀርባ ነው የወሰደው፡፡ ይሄ የእኔም ሆነ የሩታ ወይም የሌሎች ተሸላሚዎች ችግር ሳይሆን የአዘጋጁ ነው፡፡ እዚያም የሽልማት ቦታ ላይ የተፈጠረው አንዳንድ ክፍተት እንደዚህ ነው የሆነው፤ አዘጋጆቹ ናቸው ሊጠየቁ የሚገባው፡፡
ተወካዩን በተመለከተ የናፍካ አርማና ማህተም ባለው ደብዳቤ፤ ‹‹On behalf of Nafca›› ተብሎ ስሙ ተጠቅሶ፣ ውክልና የተሰጠበትን ደብዳቤ አይቼ ነው ወደ ጉዳዩ የገባሁት፡፡ እኔ ህፃን ልጅ አይደለሁም፤ በምንም መልኩ ልታለል አልችልም። ወይም ደግሞ ዋንጫ የመሸለም ሱስ የለብኝም። እንዴት የኢትዮጵያን ህዝብ አታልላለሁ፤ ሰው ድምፅ ሰጥቶናል፤ እንዲህ አይነት ወሬ ማውራት የደገፈንን ሰው መናቅ ነው፡፡ እያንዳንዱ ነገር በዶክመንት የተደገፈ፣ በተፈለገው ጊዜ ሊታይ የሚችል ነገር ነው የተካሄደው፡፡ እንደተባለው በአየር ላይ የተናፈሰ ወሬ፣ ወይም በክፍያ የተከናወነ አይደለም። ናፍካም ትልቅ የአፍሪካ የፊልም ሽልማት ነው፤ ለ6ኛ ጊዜ የተካሄደ። እኔም ሩታም ይዘን የመጣነው ኩራታችንን፣ የሚገባንን ሽልማት ነው፤ ይሄ ደረቴን ነፍቼ በኩራት የምናገረው ነው። አንድ ጥቁር አሜሪካዊ የሆነውን ልንገርሽ፡፡ ለሽልማት ስሙ ተጠራ፤ነገር ግን ሽልማቱ የለም፤ ለምን ብሎ ሲጠይቅ፤ ”የአንተን ሽልማት ኢ-ሜይል እናደርግልሃለን” አሉት፡፡ የእኔን ሽልማት ይዞ ነው ፎቶ የተነሳው፤ ይሄ የናፍካ ስህተት ነው። በእንዲህ አይነት ስነ-ስርዓቶች ላይ ትልልቅ ስህተቶች ይፈጠራሉ፡፡ ለምሳሌ በዓለም የቁንጅና ውድድር ላይ አንደኛ ለወጣችው ሽልማቱ መሰጠት ሲገባው፣ ሁለተኛ ለወጣችው ተሰጥቷል፡፡ ይሄ ያጋጥማል፤ ስህተት እየተሰራ ይቀጥል ለማለት ግን አይደለም፡፡
የሽልማቱ ሥነ ስርዓት ከተካሄደ በኋላ፣ ከ1ወር በላይ ቆይታችሁ ነው ወደ አገራችሁ የተመለሳችሁት። እግረ መንገዳችሁን ያከናወናችሁት ነገር ነበር?
ከሄድንበት ፕሮግራም መጠናቀቅ በኋላም እዚያው ሎስ አንጀለስ ስለነበርን መጀመሪያ ያደረግነው ‹‹ዩኒቨርሳል ስቱዲዮ›› የተሰኘውን ትልቅ የፊልም ኩባንያ መጎብኘት ነው፡፡ በጣም አስደናቂ ስቱዲዮ ነው፡፡ አሜሪካ በጣም ከተደነቅኩባቸውና ከተገረምኩባቸው ነገሮች አንዱና ዋነኛው “ዩኒቨርሳል ስቱዲዮ” ነው፡፡ ይህ ስቱዲዮ አንድ የፊልም ባለሙያ ማየት የሚገባው ወሳኝ ቦታ ነው፡፡ ብዙ ልምዶችን ቀስመናል፡፡ ከዚህ በኋላ ያደረግነው በበጎ አድራጎት ዘርፍ የመሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት መስራችና ዳይሬክተር እጩ ነበረች፡፡ በእርግጥ በዚህ ዘርፍ አንዲት ጣሊያናዊት ካቶሊክ በጎ አድራጊ ሴት ናቸው የተሸለሙት፡፡ እናም የተለያዩ ግዛቶች እየተዘዋወርን፣መሰረት ለምትረዳቸው ህፃናትና እናቶች፣ የገቢ ማሰባሰቢያ ስራዎችን ሰርተናል፡፡
በሌላ በኩል፤ብዙዎቻችን የየራሳችን ህልም አለን፡፡ ወደ ህልማችን ለመጠጋት ብዙ ጥረናል። ከተለያዩ የአፍሪካ ፊልም ሰሪዎች ጋር በብዙ ስራዎች ዙሪያ ተነጋግረናል፡፡ በተለይ አንድ የጋና ትልቅ የፊልም ባለሙያ፣ ሆሜስ ማክቪል ይባላል። “One Night in Vegas” እና “Paparazi” በተሰኙ ፊልሞቹ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ባለሙያ ጋር በጣም ተወያይተናል፡፡ በቀጣይ ስለምንሰራውም እየተነጋገርን እንገኛለን፡፡ ዲሲም ሄደን አቶ ታምራት የተባሉ፣ ላለፉት 42 ዓመታት በዲሲ የኖሩ ሰውን አነጋግረናል፡፡ ብቻ ብዙ ነገሮችን ከውነናል፡፡ መቼም ዋናው ህልማችን የናፍካን ሽልማት ወስዶ ለመመለስ ብቻ አይደለም፡፡ ወደ ህልማችን የሚያስጠጋንን ነገር እግረ መንገዳችንን ፈፅመን መጥተናል፡፡
በቆይታህ ካገኘኸው ልምድ የፊልሙን ኢንዱስትሪ ለማሳደግ ምን አስበሀል?
እኔ እንግዲህ ሁሌም ተማሪ ነኝ ብዬ ነው የማስበው፡፡ እኔ እንደ ችግር የማየው፣ ራሳችንን ለሌላው ዓለም አላሳየንም፤ ኤክስፖዠር ያስፈልገናል። እነዚህን ነገሮች ለማድረግ በግሌ እጥራለሁ፡፡ ነገር ግን እድሎች ሲመጡ እንዲህ አይነት ያልተፈጠረ ነገር እያወሩ ሙያውን ከማቀጨጭ፣ በቅን ልቦና ማሰብ፣ መቻቻልና መተራረም የተሻለ ነው፡፡ እድሎችን ባበላሸን ቁጥር፣ ሙያችንን ወደ ዓለም ገበያ ለማቅረብ እንቸገራለን፡፡ በተረፈ አገራችን ላይ ጥሩ ተሰጥኦ ያላቸው ተዋንያን፣ ደራሲያን፣ ዳይሬክተሮች አሉ፡፡ ከመላው ዓለም ጋር መፎካከር የሚችሉ ባለሙያዎች አሉን፡፡ ሌላው የሚጎድለን እርስ በእርስ በሙያችን መደጋገፍና አብሮ የመስራት ነገር ነው፡፡ የናይጄሪያና የጋና ፊልም ሰሪዎች፣ የዓለምን ገበያ የተቀላቀሉት አብሮ የመስራት ባህል ስላላቸው ነው፡፡   



Saturday, 14 January 2017 16:04

የቴክኖሎጂ ጥግ

የፍቅር ጥግ
· ማፍቀር እንጂ በፍቅር መውደቅ የለብንም፤
ምክንያቱም የሚወድቅ ነገር ሁሉ ይሰበራል፡፡
ቴይለር ስዊፍት
· አንድ ላይ መሆን የቱንም ያህል ፈታኝ ቢሆን
ግዴለኝም፤ ከመለያየት የሚብስ ነገር የለም፡፡
ጆሴፊን አንጄሊኒ
· ራሳችሁን ለመሆን ለማይፈቅድላችሁ
ግንኙነት እጅ አትስጡ፡፡
ኦፕራ ዊንፍሬይ
· ከራሱ ጋር በፍቅር የሚወድቅ፣ ማንም
ተፎካካሪ የለውም
ቤንጃሚን ፍራንክሊን
· እናንተ እብደት ትሉታላችሁ፤ እኔ ግን ፍቅር
እለዋለሁ፡፡
ዶን ቢያስ
· ፍቅር አብሮን የተፈጠረ ሲሆን ፍርሃት እዚህ
የተማርነው ነው፡፡
ማርያኔ ዊሊያምሰን
· ፍቅር ባለቤትነትን አይጠይቅም፤ ነፃነትን
ያጎናፅፋል እንጂ፡፡
ራቢንድራናዝ ታጎ
· ፍቅር፤ ፍቅርን የሚያመነጭ ኃይል ነው፡፡
ኤሪክ ፎርም
· ሰዎችን ልትወዳቸው እንጂ ልታድናቸው
አትችልም፡፡
አናይስ ኒን
· ሁለት ነፍሶች ግን አንድ ሃሳብ፤ ሁለት ልቦች
ግን እንደ አንድ የሚመቱ፡፡
ፍሬድሪክ ሃልም
· የማይቻለውን የሚቻል የሚያደርገው ፍቅር
ነው፡፡
የህንዶች አባባል
· ፍቅር፤ በትዳር የሚድን ጊዜያዊ እብደት
ነው።
አምብሮሴ ቢርስ

አለማችን በሲጋራ ሳቢያ በአመት 1 ትሪሊዮን ዶላር ታጣለች
- በ2030 በየአመቱ የሚሞቱ አጫሾች ቁጥር 8 ሚሊዮን ይደርሳል

የሩስያ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እ.ኤ.አ ከ2015 በኋላ ለተወለዱ ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች ሲጋራ እንዳይሸጥ የሚከለክል እጅግ ጥብቅ
ህግ በማውጣት ተግባራዊ ለማድረግ ማቀዱን የእንግሊዙ ዘ ታይምስ ዘገበ፡፡ ቀጣዩን የሩስያ ትውልድን ከሲጋራ ነጻ እንደሚያደርግ ቢታሰብም የአፈጻጸሙ ጉዳይ አጠያያቂ ነው የተባለው የሚኒስቴሩ ዕቅድ፣ እንደታሰበው ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ፣ ሩስያ ከአለማችን አገራት እጅግ ጥብቅ የጸረ-ትምባሆ ህግ ያወጣች የመጀመሪያ አገር ትሆናለች ያለው ዘገባው፤ አገሪቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በትምባሆ ዙሪያ ጉልህ እርምጃዎችን መውሰድ መጀመሯን ጠቁሟል፡፡ ዕቅዱ ጤናማ ዜጋ ለመፍጠር ቢያስችልም፣ በሌላ በኩል ግን ከጥራት በታች የሆነ የትምባሆ ምርት በጥቁር ገበያ ህገወጥ መንገድ እየተሸጠ የዜጎችን ጤና የከፋ አደጋ ላይ እንዲጥል ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት መፍጠሩን እንዲሁም ለሁሉም ዜጎች ሲጋራ አትሽጡ የሚለው ህግ በተጠቃሚዎችና በትምባሆ አምራች ኩባንያዎች ዘንድ ቁጣን ሊቀሰቅስ እንደሚችል መነገሩንም ዘገባው
አመልክቷል፡፡ የሩስያ መንግስት ባለፉት አመታት የሲጋራ አጫሾችን ቁጥር ለመቀነስ በሚል በወሰዳቸው የተለያዩ እርምጃዎች ከፍተኛ ውጤት
ማስመዝገቡን ያስታወሰው ዘገባው፣ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2016 ብቻ የአገሪቱ አጫሾች ቁጥር በ10 በመቶ መቀነሱንም አክሎ ገልጧል፡፡
በተያያዘ ዜናም፣ የአለማችን ኢኮኖሚ በሲጋራ ሳቢያ በየአመቱ 1 ትሪሊዮን ዶላር ገደማ ኪሳራ እንደሚገጥመውና በሲጋራ ማጨስ
ሳቢያ በየአመቱ ለህልፈተ ህይወት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር በመጪዎቹ 13 አመታት፣ 8 ሚሊዮን ያህል ይደርሳል ተብሎ እንደሚገመት
የአለም የጤና ድርጅት ሰሞኑን ባወጣው መረጃ ማስታወቁን ዘገባው አስረድቷል፡፡ ድርጅቱ ባለፈው ማክሰኞ ያወጣውን የጥናት ውጤት
ጠቅሶ ሮይተርስ እንደዘገበው፣ እስካሁን ባለው መረጃ በአለማቀፍ ደረጃ በሲጋራ ሳቢያ 6 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በየአመቱ የሚሞቱ
ሲሆን፣ ይህ ቁጥር እስከ 2030 ድረስ 8 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በሲጋራ ለህልፈተ ህይወት ከሚዳረጉት
ሰዎች መካከል ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት በመካከለኛና በዝቅተኛ ገቢ አገራት የሚገኙ እንደሆኑም ዘገባው ጠቁሟል፡፡