Administrator

Administrator

 አፍሪካ 1 ትሪሊዮን ዶላር ከሚደርሰው የአፍሪካ አመታዊ አለማቀፍ ንግድ ውስጥ የአህጉሪቱ አገራት ያላቸው ድርሻ 15 በመቶ ብቻ መሆኑን ኦልአፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡ የአፍሪካ ኤክስፖርት ኢምፖርት ባንክ ሰሞኑን ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ አፍሪካ አገራት በአመታዊው የአህጉሪቱ አለማቀፍ ንግድ ውስጥ ያላቸው ድርሻ 150 ቢሊዮን ዶላር ያህል ብቻ ነው፡፡
የአገራቱ የንግድ ድርሻ አነስተኛ ሊሆን የቻለው አገራቱ በቂ የአለማቀፍ ንግድ ገበያ መረጃ ስለሌላቸውና ንግዱን የሚደግፍ በቂ መሰረተ ልማት ለመገንባት ባለመቻላቸው ነው ብሏል ተቋሙ፡፡ አንዳንድ አገራት የአፍሪካ የንግድ ስምምነትን አለመፈረማቸው የንግድ ተሳትፎ ድርሻቸውን ዝቅ እንዳደረገባቸውም ተቋሙ ኣስታውቋል፡፡

ጥቁርና ነጭ ቴሌቪዥን ፋሽኑ ካለፈበትና ባለቀለም ቴሌቪዥን ከመጣ ከ50 አመታት በላይ ቢሆነውም፣ በእንግሊዝ ከ7 ሺህ በላይ ቤተሰቦች አሁንም ጥቁርና ነጭ ቴሌቪዥን እንደሚያዩ ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
በእንግሊዝ ባለቀለም ቴሌቪዥን ገበያ ላይ የዋለው እ.ኤ.አ በ1967 እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ በአገሪቱ 7 ሺህ 161 ያህል ቤተሰቦች አሁንም ድረስ ቴሌቪዥናቸውን እንዳልቀየሩ አመልክቷል፡፡ ባለቀለም ቴሌቪዥን ከመጣ በኋላ ጥቁርና ነጭ ቴሌቪዥን የሚገዙ የአገሪቱ ዜጎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ቢሆንም አንዳንዶች ግን ለመቀየር አለመፈለጋቸውን ዘገባው አስረድቷል፡፡

 በፈረንጆች አመት 2018 ያለፉት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመግባት በጉዞ ላይ ሳሉ በባህር ውስጥ ሰጥመው የሞቱ የተለያዩ አገራት ስደተኞች ቁጥር፣ ከ2ሺህ በላይ መሆኑን ተመድ አስታውቋል፡፡የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ተቋም ያወጣው ሪፖርት እንደሚለው፤ በሜዲትራኒያን ባህር በአስቸጋሪ ጉዞ ውስጥ አልፈው ወደ አውሮፓ ለመግባት ሲሞክሩ ለተለያዩ አሰቃቂ አደጋዎችና ለሞት የሚዳረጉ ስደተኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ይገኛል፡፡
ህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ስደተኞችን በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ ማጓጓዛቸው መበራከቱን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ አደጋዎች በሚከሰቱበት ጊዜ ፈጥነው የሚደርሱና የነፍስ አድን ስራ የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑና አለማቀፍ ተቋማት ስራቸውን እንዳይሰሩ መታገዳቸው ለሟቾች ቁጥር መጨመር አንዱ ምክንያት መሆኑንም አመልክቷል፡፡

Saturday, 10 November 2018 13:16

ጀግንነት በየፈርጁ!

 በአሜሪካ ሚኔሶታ ግዛት ነው፡፡   
ለአሜሪካዊው የእሳት አደጋ ሠራተኛ ጀሬሚ ቦሮሳ ልዩ ቀን ነበረች፡፡ ከወደፊት የህይወት አጋሩ ክሪስታ ቦላንድ ጋር ትዳር የሚመሰርቱበት የጋብቻ  ዕለት፡፡ ሙሽሮቹና ጥቂት ዘመድ ወዳጆቻቸው፣ የማስታወሻ ፎቶግራፍ ለመነሳት፣ የእሳት አደጋ መከላከያ ጣቢያው ጋ ተሰባስበው ነበር፡፡ ይሄን ጊዜ ነው  ቦሮሳ  ከሥራ ባልደረቦቹ  ያልጠበቀው የስልክ ጥሪ የደረሰው፡፡ በአቅራቢያ በሚገኝ የመኖሪያ ቤት ላይ  የእሳት ቃጠሎ ደርሶ፣ የሰው ሃይል ስላነሳቸው ነበር  የደወሉለት፡፡ ጀሬሚ ቦሮሳ  እረፍት ላይ  ቢሆንም፣ ለባልደረቦቹ ድንገተኛ የእርዳታ ጥያቄ ጆሮ ዳባ ልበስ አላለም፡፡ ከመቅጽበት የሠርግ ሥነስርዓቱን አቋርጦ ሄደ እንጂ፡፡ በደቂቃዎች ውስጥም ዩኒፎርሙን ለብሶ  ባልደረቦቹን ተቀላቀለ፡፡   
ከሁለት ሰዓት በኋላ  ግዳጁን ተወጥቶ፣ ወደ ሠርግ ሥነሥርዓቱ ሲመለስ፤ “እንግዶች በሙሉ ቆመው  በጭብጨባ ተቀብለውታል” ብላለች፤ውድ ባለቤቱ  ክሪስታ ቦላንድ፡፡ ከዚህ በኋላ ነበር ሠርጋቸውን በዳንስ ያደመቁት፡፡ በጀግንነት ተግባር የታጀበ፣ አይረሴ  ሠርግ  ይሏል ይኼ ነው፡፡      
*   *   *
የአየርላንድ ተወላጇ ካይትሮይና ላሊ፤ ከዱብሊን  ትሪንቲ ኮሌጅ የተመረቀችው የዛሬ 14 ዓመት ነበር፡፡ በ2015  ወደ ኮሌጁ የተመለሰችው ትምህርቷን ለመቀጠል አልነበረም፡፡ በጽዳት ሠራተኛነት ተቀጥራ ለመሥራት እንጂ፡፡ ይሄኔ ነበር “Eggshells”  የተሰኘው የበኩር  ረዥም ልብወለዷ ለንባብ የበቃው፡፡  ይሄን ልብወለዷን የጻፈችው  ከሥራ ውጭ በቆየችባቸው  ዓመታት ነበር፡፡     
 ባለፈው ሳምንት ታዲያ ልታምነው ያዳገታትን  ዜና ሰማች፡፡ “Eggshells”  የተሰኘው  መጽሐፏ የኮሌጁን ከፍተኛ የሥነጽሁፍ ሽልማት አሸነፈ፡፡ ሩኔይ የአየርላንድ ሥነጽሁፍ ሽልማት፤ “የላቀ ተስፋ” ለሚጣልባቸው፣ ዕድሜያቸው  ከ40 ዓመት በታች ለሆኑ ጸሐፍት የሚሰጥ ዓመታዊ ሽልማት ነው፡፡ የሥነጽሁፍ ሽልማቱ 11 ሺ 500 ዶላርም (300 ሺ ብር ገደማ) ይጨምራል፡፡  ሽልማቱን ማሸነፏ “ፍጹም ተዓምር ነው” ያለችው  ላሊ፤ በአሁኑ ወቅት ሁለተኛ ልብወለዷን በመጻፍ ላይ እንደምትገኝ ታውቋል፡፡ ማን ያውቃል፣ ለሁለተኛ  ሽልማት ትበቃ ይሆናል፡፡      
ምንጭ፡- (THE WEEK October 12,2018)

 በህይወት ከሌሉ የአለማችን ዝነኞች ከፍተኛውን ገቢ በማግኘት ላለፉት አምስት አመታት በመሪነት የዘለቀው የፖፕ ሙዚቃ ንጉስ ማይክል ጃክሰን ዘንድሮም በ313 ሚሊዮን ፓውንድ አመታዊ ገቢ በአንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጡ ተዘግቧል፡፡
ማይክል ጃክሰን ከኤሚ ሚዩዚክ ፐብሊሺንግ በተባለው አሳታሚ ኩባንያ ውስጥ ካለው የአክስዮን ድርሻና በህይወት ሳለ የሰራቸውን ሙዚቃዎች ለማሳተም ከኩባንያዎች ጋር የተደረጉ ስምምነቶችን ጨምሮ በድምሩ 313 ሚሊዮን ፓውንድ ማግኘቱን የዘገበው ፎርብስ መጽሄት፤ ድምጻዊው ከዚህ አለም በሞት ከተለየበት እ.ኤ.አ 2009 በኋላ ባሉት አመታት በድምሩ 1.8 ቢሊዮን ፓውንድ ገቢ ማግኘቱን የጠቆመው ዘገባው፣ በህይወት ከሌሉ የአለማችን ዝነኞች በገቢ የሁለተኛነት ደረጃን የያዘው ሌላው ዘመን አይሽሬ ድምጻዊ ኤልቪስ ፕሪስሊ ሲሆን፣ ኤልቪስ ባለፉት 12 ወራት ጊዜ ውስጥ 31 ሚሊዮን ፓውንድ ገቢ ማግኘቱን አመልክቷል፡፡
በተወለደ በ42 አመቱ እ.ኤ.አ በ1977 ከዚህ አለም በሞት የተለየው ኤልቪስ ፕሪስሊ ባለፉት 12 ወራት የተጠቀሰውን ገቢ ያገኘው ከቀድሞ ሙዚቃዎቹ ሽያጭና ከሌሎች ገቢዎች እንደሆነ ተነግሯል፡፡
ዝነኛው የጎልፍ ተጫዋች አርኖልድ ፓልመር በ27 ሚሊዮን ፓውንድ የሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ፣ ታዋቂው ካርቱኒስት ቻርለስ ሹልዝ በ26 ሚሊዮን ፓውንድ አራተኛ፣ የሬጌው ሙዚቃ ንጉስ ቦብ ማርሌ ደግሞ በ18 ሚሊዮን ፓውንድ አምስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
በፎርብስ መጽሄት የዘንድሮ የአለማችን ሟች ዝነኞች ገቢ ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት ሌሎች ዝነኞች መካከል እውቋ የፊልም ተዋናይ ማርሊን ሞንሮ የምትጠቀስ ሲሆን፣ በ11 ሚሊዮን ፓውንድ የ11ኛ ደረጃን ይዛለች፡፡


 2.6 ቢሊዮን ወርሃዊ ተጠቃሚዎች፣ 33 ሺህ 606 ሰራተኞች አሉት


     ታዋቂው ማህበራዊ ድረገጽ ፌስቡክ እስካለፈው መስከረም በነበሩት ያለፉት ሶስት ወራት ብቻ የ13.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱንና በየዕለቱ የሚጠቀሙ ደንበኞቹ ቁጥርም 1.49 ቢሊዮን መድረሱን አስታውቋል፡፡
የፌስቡክ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ማርክ ዙክበርግ ባለፈው ማክሰኞ ይፋ ባደረጉት መረጃ እንዳሉት፣ በአሁኑ ወቅት ፌስቡክ፣ ዋትዛፕ፣ ኢንስታግራምና ሜሴንጀር የተሰኙትን የኩባንያው አገልግሎቶች የሚጠቀሙ ወርሃዊ ደንበኞች ቁጥር ከ2.6 ቢሊዮን በላይ ደርሷል፡፡
ፌስቡክ ባለፉት ሶስት ወራት ካገኘው ገቢ 92 በመቶ ያህል ድርሻ የያዘው ከሞባይል ስልኮች ማስታወቂያዎች ያገኘው ገቢ መሆኑን የጠቆሙት ዙክበርግ፣ ኩባንያው ከዚህ ማስታወቂያ 12.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱንና በፌስቡክ የተለያዩ ምርቶቻቸውንና አገልግሎቶቻቸውን የሚያስተዋውቁ ኩባንያዎች ቁጥር ከ6 ሚሊዮን በላይ መድረሱንም አስረድተዋል፡፡
በየዕለቱ በፌስቡክ፣ ዋትሳፕና ሜሴንጀር አማካይነት 100 ቢሊዮን ያህል የጽሁፍና የምስል መልዕክቶች እንደሚላኩ የተነገረ ሲሆን፣ ከ90 ሚሊዮን በላይ ኩባንያዎችም የፌስቡክ ገጾችን ከፍተው ራሳቸውን እያስተዋወቁና ስራዎቻቸውን እያቀላጠፉ እንደሚገኙ ዘገባው አስረድቷል፡፡
ባለፈው የካቲት ወር ላይ በተጀመረው የፌስቡክ የክፍት የስራ ቦታ ማመልከቻ አፕሊኬሽን አማካይነት በተለያዩ የስራ ቦታዎች ላይ ለመቀጠር የቻሉ ደንበኞች ቁጥርም ከአንድ ሚሊዮን በላይ መድረሱን የጠቆመው ዘገባው፣ ፌስቡክ የሰራተኞቹን ቁጥር 33 ሺህ 606 ማድረሱንንም አክሎ ገልጧል፡፡

   በአገሪቱ ከ88 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በከፋ ድህነት ውስጥ ይገኛሉ

    ባለፉት አራት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ1.1 ሚሊዮን በላይ ናይጀሪያውያን ወደ ከፋ ድህነት መግባታቸውንና በከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኙ የአገሪቱ ዜጎች ቁጥር 88 ሚሊዮን መድረሱን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
ተቀማጭነቱን በቪየና ያደረገው ወርልድ ፖቨርቲ ክሎክ የተሰኘ ተቋም ይፋ ባደረገው አለማቀፍ ሪፖርት እንዳለው፣ ከ1.9 ዶላር በታች ዕለታዊ ገቢ ባላቸው ወይም በከፋ ድህነት ውስጥ በሚገኙ ዜጎች ብዛት ናይጀሪያ ከአለማችን አገራት በቀዳሚነት ትገኛለች፡፡
በናይጀሪያ ድህነት ስር እየሰደደ እንደሚገኝ የጠቆመው ተቋሙ፣ መንግስት ችግሮችን ለመፍታት እያደረገ ያለው ጥረት በቂ አለመሆኑንና አገሪቱ በ2030 ከድህነት ለመውጣት ያስቀመጠችውን ግብ ለማሳካት እንደማትችል የሚያመላክቱ ሁኔታዎች መኖራቸውንም አስረድቷል፡፡ የቢልና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ያወጣውን ትንበያ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በመጪዎቹ 12 አመታት ጊዜ ውስጥ ከአለማችን እጅግ ድሃ ሰዎች መካከል ከ40 በመቶ በላይ የሚሆኑት በናይጀሪያ እንደሚገኙ ይጠበቃል፡፡
የአለም ባንክ በበኩሉ፤ በመላው አለም በከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር ከ1.6 ቢሊዮን በላይ መድረሱን ያስታወቀ ሲሆን፣ ከ29 በመቶ በላይ የሚሆኑትም ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገራት እንደሚኖሩ አስረድቷል፡፡


 ከአራት ወራት በፊት ከአሜሪካው አቻቸው ዶናልድ ትራምፕ ጋር ታሪካዊ የተባለውን ስብሰባ በማድረግ ከአለም ጋር የነበራቸውን ለአመታት የዘለቀ ኩርፊያ የደመሰሱት የሰሜን ኮርያው ፕሬዚዳንት ኪም ጆንግ ኡን፣ በቅርቡም አገራቸው የተጣሉባት ማዕቀቦች እንዲነሱላት ለማግባባት በማሰብ ከ5 የአለማችን አገራት መሪዎች ጋር ተገናኝተው ለመምከር ማቀዳቸውን ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡
ኪም ጁንግ ኡን ከደቡብ ኮርያው ፕሬዚዳንት ሙን ጃኢን እና ከቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂፒንግ ጋር በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገናኝተው እንደሚወያዩ መነገሩን የጠቆመው ዘገባው፣ ከጥቂት ወራት በኋላም ከጃፓኑን ፕሬዚዳንት  ሺንዙ አቤ ጋር ይገናኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል፡፡
ከአሜሪካው አቻቸው ዶናልድ ትራምፕ ጋር በመጪው ወር በድጋሚ ለመገናኘት ሳያስቡ አልቀሩም የተባሉት የወትሮው አመጸኛ ኪም ጁንግ ኡን፣ በዚያው ሰሞን ወደ ሩስያ አቅንተው ከፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ስብሰባ ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅና “ይምጡና እንማከር” ብለው ለሮማው ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ የክብር ግብዣ መላካቸውንም ዘገባው ገልጧል፡፡

 በመላው አለም በሚገኙ የተለያዩ አገራት ባለፉት አስር አመታት በድምሩ ከ1 ሺህ በላይ ጋዜጠኞች እንደተገደሉና በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በየዕለቱ በአማካይ አንድ ጋዜጠኛ እንደተገደለ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል፡፡የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው መረጃ እንዳለው፣ ጋዜጠኞቹ ዘገባዎችን በሚሰሩበትና ለህዝብ በሚያቀርቡበት ወቅት በስራ ገበታቸው ላይ እያሉ የተገደሉ ናቸው፡፡ባለፉት አስር አመታት በእነዚህ ጋዜጠኞች ላይ ግድያ ከፈጸሙት ሰዎች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት ግድያውን በመፈጸማቸው በህግ ተጠያቂ እንዳልተደረጉና እንዳልተቀጡ ድርጅቱ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡በአለማችን የተለያዩ አገራት ግድያን ጨምሮ በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰው ጥቃት እያደገ መጥቷል ያለው ተቋሙ፣ መንግስታት በመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ላይ ጥቃት እንዲፈጸም የሚገፋፉ የጥላቻ ንግግሮችንና አባባሽ ድርጊቶችን እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ ብለነዋል፤ ማንም ስላልሰማን ደግመን እንለዋለን ይላል - አንድ የጥንት ታሪክ ፀሐፊ፡፡ የእኛም እንደዚያው ነው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት ደገኛ ገበሬዎች አብረው ይኖሩ ነበር፡፡ ሳር ቤት ነው ያላቸው፡፡ ደሳሳ ጎጆዎች ናቸው፡፡ በድንገት አንድ ቀን የአንደኛው ገበሬ ቤት ተለወጠ፡፡ ቆርቆሮ ቤት ሆነ፡፡ ጎረቤትየው ደነገጠና፤
“ወዳጄ፤ እንዴት ይሄ ቤትህ ሊለወጥ ቻለ? ምን ተዓምር ተገኘና ነው?”
ገበሬው፤
“አየህ በሬዎቼን ሸጥኳቸውና ታች ቆላ ወርጄ ብረታ ብረት ገዛሁ፡፡ ከዚያ ደጋ አምጥቼ ለቀጥቃጩ፣ ለባለእጁ፣ ማረሻ ለሚፈልገው ገበሬ ሸጥኩ፡፡ ብዙ ብር አገኘሁ፡፡ ቤቴን ለወጥኩ፡፡ አጥሬን ለወጥኩ፡፡ ራሴን ለወጥኩ!”
“በቃ፤ እኔም እንዳንተ አደርጋለሁ” አለና ሄዶ በሬዎቹን ሸጠ፡፡ ከዚያም ገበያ ገብቶ ማጭድ፣ አካፋ፣ ዶማ፣ ማረፊያ፣ ገሶ … ብቻ አለ የሚባል የብረት ግብዓት ገዝቶ፣ ተሸክሞ፣ ወደ ደጋ ዳገቱን ተያያዘው፡፡
ሆኖም ያን ሁሉ ብረት አቅሙ አልችል አለና ዳገቱ ወገብ ላይ ተዝለፍልፎ ወደቀ፡፡ የመንደሩ ሰው በዚያ ሲያልፍ አየውና፤
“አያ እገሌ ምን ሆነህ ነው?”
“ያ ጎረቤቴ ገበሬ ጉድ አርጎኝ ነው!”
“ምን አደረገህ?”
“ንግድ ጀምሬያለሁ ብሎ የንግዱን ጠባይ ነገረኝ፡፡ ባለኝ መሰረት ንግድ ውስጥ ገባሁ”
“ታዲያ እሱ ምን በደለህና ነው ጉድ አደረገኝ የምትለው?”
“ትርፉን ነግሮ መከራውን ሳይነግረኝ!”
***
አያሌ ትርፍ ያስገኛሉ የተባሉ ነገሮች መከራ እንዳላቸው መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ቀላል የሚመስሉ ግን ውስብስብ የሆኑ፣ ውስብስብ ሆነው የባሰ የሚወሳሰቡ፣ ሳንማርባቸው ያለፉ፣ ተምረንባቸው የተረሱ፣ ጨርሶ ያላጠናናቸው ብዙ ብዙ ቁምነገሮች አሉ፡፡
“ከበሮ በሰው እጅ ያምር
ሲይዙት ይደናገር!” የሚባለው ተረት፣ ለተሿሚዎቹ ሁሉ የማስጠንቀቂያ ደወል ነው! በተለይ ሴት ተሿሚዎች መብዛታቸው አኩሪ የመሆኑን ያህል ኃላፊነታቸውን መወጣታቸው፣ ከሙስና የፀዱ መሆናቸው፣ የፆታ እኩልነትን ማበልፀጋቸው፣ ለበርካታ ሴቶች አርአያ መሆናቸው፣ ከወንዶች ይልቅ ዝርዝር ጉዳይ ላይ የማተኮር ክህሎታቸው (Meticulousness) እጅግ የላቁ ያደርጋቸዋል! ይሄ ቢሳካልን ላሜ ወለደች ነው! ይህን ዕድል እንደ ሌሎች ያመለጡን ዕድሎች እንዳይሆን መትጋት ያስፈልጋል፡፡ የእናቶች ፀጋ በእጃችን ነው፡፡ የህፃናት ፀጋ በእጃችን ነው፡፡ የትምህርት ፀጋ በእጃችን ነው! የሚያስጎመጅ ዕድል ባያመልጠን መልካም ነው! የዲሞክራሲ፣ የፍትህ፣ የተስፋ፣ የራዕይ ጊዜ እየጀመረ ነውና እንጠቀምበት! ለብዙ ዓመታት የጮህንለት የሴቶች አጀንዳ መልካም ጉዞ ይጓዝ ዘንድ የወንዶችም የሴቶችም ጥያቄ አድርገን እንየው፡፡ አለበለዚያ “የማያስተኛ ነገር ነግረውን ተኝተው አደሩ” ይሆንብናል!!

Page 4 of 409