Administrator

Administrator

 ጅቡቲ፤ የሱማሌው ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ፣ በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ ባለፈው ሳምንት ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያቀረቡትን ጥያቄ በጽኑ መቃወሟን ቪኦኤ ዘግቧል፡፡
የሱማሌው ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ ባለፈው ሳምንት በኤርትራ የሶስት ቀናት የስራ ጉብኝት ማድረጋቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ፕሬዚዳንቱ በጉብኝታቸው ወቅት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እ.ኤ.አ በ2009 በኤርትራ ላይ የጣለውን የኢኮኖሚና የጦር መሳሪያዎች ማዕቀብ እንዲያነሳ ጥሪ ማቅረባቸው ጅቡቲን ክፉኛ ማስቆጣቱን አመልክቷል፡፡
በጅቡቲ የሶማሊያ አምባሳደር አደን ሃሰን፤ “የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ለተመድ ያቀረቡት የማዕቀብ ይነሳ ጥያቄ እጅግ አስደንግጦናል፣ በጽኑም እንቃወመዋለን” ሲሉ መናገራቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ “ኤርትራ የይገባኛል ውዝግብ ያለባቸውን የሩሜራ ደሴቶችን ያላግባብ ይዛብናለች፣ ከአስር በላይ ዜጎቻችንንም በእስር ቤት እያሰቃየችብን ነው፣ ስለዚህም ተመድ የጣለባት ማዕቀብ ሊነሳላት አይገባም” በሚል ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውንም ገልጧል፡፡
“ሶማሊያ በአካባቢው ካሉ ጎረቤት አገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን የማጠናከር ህጋዊ መብት ቢኖራትም፣ የረጅም ዘመናት ወዳጃችን የሆነቺው ሶማሊያ ሉአላዊ ግዛታችንን ለወረረቺውና ዜጎቻችንን በእስር ለምታሰቃየው ኤርትራ እንዲህ አይነት ድጋፍ ማድረጓን መንግስታችን በጽኑ ይቃወመዋል” ማለታቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

 ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አዳኝ ሰው ወፎች እያጠመደ ይኖር ነበር፡፡ አንድ ቀን አንዲት የወርቅ ቀለም ያለው ላባ ያላት ወፍ አጠመደ፡፡ ለብዙ ቀናት የወፍ መኖሪያ መረብ ሰርቶ ምግብ እያከማቸና እየቀለበ ካስቀመጣት በኋላ አንድ ቀን፤
“ወፌ ሆይ! እስከዛሬ ስቀልብሽ እንደነበርኩ ታስታውሻለሽ፣ አይደል?” አለና ጠየቃት፡፡
ወፊቱም፤
“አዎን ጌታዬ! ተንከባክበህ፣ አሳምረህ አኑረኸኛል፡፡ ወደፊትም ታኖረኛለህ የሚል ሙሉ ዕምነት አለኝ!” ስትል መለሰች፡፡
“ግን ወፌ!” አለና ጀመረ አዳኙ ጌታዋ፤ “አሁን ሁለት ነገር ለማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ ሁለተኛው የወርቅ ላባሽን መሸጥና መጠቀም ነው፡፡ የመጀመሪያው ደግሞ ላባሽን በቁምሽ መንጨትና መሸጥ ስለማልፈልግ፤ አርጄ እበላሻለሁ፡፡ ከዚያ ላባሽን እሸጠዋለሁ! ሌላ ምንም ለማድረግ አልችልም!” አላት፡፡
ወፊቱ ጥቂት ካሰበች በኋላ፤
“ጌታዬ ሆይ! ያልከው ዕውነት ነው፡፡ ሆኖም አንተ ካሰብከው በላይ ጠቃሚ የሆነ ነገር እሰጥሃለሁ”
“ምን?” አለ ጌትየው፡፡
“አየህ፤ የእኔን ሥጋ መብላትም ሆነ የወርቅ ላባዬን መሸጥ ያለው ጥቅም የአንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ እኔ የምሰጥህ ነገር ግን ዘለዓለም የምትጠቀምበት ነው፡፡”
“ምንድን ነው የምትሰጪኝ?”
“ምክር”
“ምን ምክር?” አለ በጉጉት፡፡
“ሦስት ምክሮችን ነው የምለግስህ፡፡ አንደኛውን እዚሁ እጅህ ላይ ሳለሁ እነግርሃለሁ፡፡
ሁለተኛውን አቅራቢያችን ካለው ዛፍ ላይ ሆኜ እነግርሃለሁ፡፡ ሦስተኛውን አየር ላይ ሆኜ አበስርሃለሁ።”
አዳኙ በሀሳቧ ተስማማና፤
“እሺ፤ የመጀመሪያውን ንገሪኝ” አላት፡፡
ወፊቱም፤ “የመጀመሪያው ምክሬ፤ የማታገኘውን ነገር አትመኝ! የሚል ነው”
አዳኙም፤ “ጥሩ፤ ሁለተኛውን ንገሪኝ” አለና ወደ ዛፉ እንድትሄድ ለቀቃት፡፡
ወፊቱም እየበረረች ዛፉ ላይ አረፈች፡፡ ከዚያም፤ “በእጅህ የገባውን ነገር በጥንቃቄ ያዝ፤ አትልቀቅ” ብላው ወደ አየር ከነፈች፡፡
ይሄኔ አዳኙ በጣም ተናዶ፤
“ወይኔ! ወይኔ! አንቺን መልቀቅ አልነበረብኝም፡፡” እያለ ፀጉሩን ሲነጭ፤
“አሁን ሶስተኛውን ምክሬን ልንገርህ” አለችና ከንዴት አስቆመችው፡፡
“ሦስተኛውን ምክርሽን ልስማ እሺ?” አለ፡፡
ወፊቱም፤
“ባለፈ ነገር አትፀፀት” ብላ ወደ ህዋ አንደኛዋን መጠቀች፡፡
***
የወፊቱ ምክሮች በአሁኑ ወቅት ለእኛ የሚሆኑ ናቸው፡፡ የማናገኛቸውን ነገሮች መመኘት አይኖርብንም። የምንመኘውን ነገር ለማግኘት አቅማችንን፣ ጊዜውንና አካሄዳችንን ከምር ማስላትና ማውጠንጠን አለብን። አለበለዚያ፤
“ምኞቴ እንደጉም መንጥቃ
ተስፋዬ እንደጉድፍ ወድቃ
የወንድሜን ልጆች እንኳ፣ ላባት ርስት ሳላበቃ
የእኔ ነገር በቃ በቃ …” ብለን እንቀራለን (ፀጋዬ ገ/መድህን፣ የከርሞ ሰው፤ አብዬ ዘርፉ)
ቀጥሎ በልቦናችን ሊመዘገብ የሚገባው፣ በእጃችን ያለውን አጥብቀን መያዝን ነው፡፡ ኢትዮጵያ በጀመረችው የለውጥ ጉዞ እያገኘችና እያስመዘገበች ያለው ድል የእስካሁን ዕድሜው አጭር ከመሆኑ በስተቀር አመርቂና ዘላቂ እንደሚሆን፣ ተስፋው እጅግ ያማረ ነው! ይህንን ድል መጠበቅና ተጠንቅቆ መያዝ ተገቢ ነው!! ምነው ቢሉ፤ አንሸራታች ደለልና “ያፋፍ ላይ ድጥ” መቼም ቢሆን ሊያጋጥም ይችላልና! በመሰረቱ፤ ማናቸውም ወደፊት የሚጓዝ ክስተት ከአሮጌ ሥርዓት ጋር መጋጨቱም ሆነ፤ ግራ የተጋባው የህብረተሰብ ክፍል መንገዱና መንፈሱ ሲያቀዣብረው፤ እንደ ተራ ምቀኝነትም ራሱ የሌለበት ነገርና ያልቃኘው ክራር የማይጥመው ወገን መኖሩ፤ ከቶም አስገራሚ አይደለም! እኒህን “የአውቆ አበድም ሆነ የአብዶ - አወቅ” ክፍሎች ወይም ወቅትን በወግ በወጉ አድርገው ለመጠቀም ያልቻሉ ወገኖችን፤ አግባብና ጥንቃቄ ባለው አያያዝ ማቀፍ ብልህነት ነው!
ማንም ጅል የማይስተው ጉዳይ ግን፣ አመራር የሆነ አካል ከጥበብና ከብልሃት ውጪ በሌላ ጎርበጥባጣ ፖለቲካዊ መንገድ እፈታዋለሁ ማለት ዘበት እንደሆነ ነው! ቀሳውስቱን፣ ምሁር ዳያስፖራውን፣ ተቃዋሚውንና በምንም ሰበብ ከሀገር የወጣውን ዜጋ ወደ ቤቱ፣ ወደ ቀዬው፣ ወዳገሩ ሊመልስ የሚችል ዕውቀት፣ ጥበብና ፍቅር ካለን፤ የውስጥ ቅራኔን ለመፍታት እንዴት መላ እናጣለን?! በእጃችን የያዝነውን እናጥብቅ!!
ሶስተኛው ወፋዊ ምክር፡- ባለፈ ነገር አለመፀፀት ነው፡፡ ከትላንትና መላቀቅ! በዕውቀት ያለፈውን መፍታት!!፡፡ ሀገራዊ ዕርቅን በጥንቃቄ ማስፋፋት!! ነገን መሻማት፡፡ ቢቻል ከነገ መስረቅ! (Plagarizing the future)
ዛሬ የኢትዮጵያን ለውጥ ለማምጣት በሚደረገው ሙከራ ውስጥ አንዱ ዓይነተኛ ተግባር ከአናት የተቃኘ ዲሞክራሲን ማስወገድ ነው (Guided democracy እንዲሉ)፡፡ እስካሁንም ዲሞክራሲያዊ አካሄድ እንዲሽመደመድ ያደረገው፤ “ይሄው በልካችሁ የተሰፋ ዲሞክራሲ እኔ ልስጣችሁ” የሚል አባዜ ነው፡፡ ከወዲሁ የከረረውን የማላላት፣ ፅንፍ ይዞ የሚጓዘውን ሃይ የማለት፣ ተቋሚነትን በህብረተሰብ ተሳትፎ የመገንባት ጠንካራ ስራ ይጠብቃል፡፡ ህዝብ “ጉዳዩ የእኔ ነው” እንዲል፣ ውሎ አድሮም የፈረሱን ልጓም እንዲጨብጥ ማድረግ ቀዳሚ እሳቤ መሆን ይኖርበታል፡፡ “እኔ ነኝ ያደረኩለት ዓይነት” አመለካከት፣ ህዝብ አያውቅም ወደሚል ክፉ ግምት ስለሚጥል አደገኛ ነው፡፡ አለበለዚያ፤ በ“እናት ዓለም ጠኑ” የፀጋዬ ገ/መድህን ቴያትር ውስጥ ተውኔታዊ ግነት ባለው መልኩ እንደቀረበውና ገራፊው ገብረየስ ጅሉ ሞሮን፤ “ዕድሜ ለእኔ በል፣ እሥር ቤት ውስጥ እኔ ስገርፍ እያየህ ከአንድ እስከ አርባ ቁጥር ተማርክ” የሚለውን ምፀታዊ አነጋገር ዕውን ከማድረግ የማይተናነስ ስህተት እንፈፅማለን፡፡ ከዚህ ይሰውረን!

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መንግስት 33 ዜጎችን ለህልፈተ ህይወት የዳረገው የኢቦላ ቫይረስ ወረርሽኝ በቁጥጥር ስር መዋሉን ይፋ ባደረገ በቀናት ዕድሜ ውስጥ ቫይረሱ በአገሪቱ ዳግም በወረርሽኝ መልክ መከሰቱ ተዘግቧል፡፡
የአገሪቱ የጤና ሚኒስትር ከትናንት በስቲያ የሰጡትን መግለጫ ጠቅሶ ዘ ጋርዲያን እንደዘገበው፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሰሜን ምስራቃዊ አካባቢ በምትገኘው የኪቩ አውራጃ የተቀሰቀሰው የኢቦላ ቫይረስ ወረርሺኝ አራት ሰዎችን ማጥቃቱ ተረጋግጧል፡፡
በአውራጃዋ ባለፈው ቅዳሜ 20 ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት የዳረገ በሽታ መታየቱን ተከትሎ በተደረገው ምርመራ፣ አራት ሰዎች በኢቦላ ቫይረስ መጠቃታቸውን ለማረጋገጥ መቻሉን የጠቆመው ዘገባው፣ በአዲስ መልክ የተቀሰቀሰው የኢቦላ ወረርሺኝ በቅርቡ ተከስቶ ከነበረውና ባለፈው ሳምንት በቁጥጥር ውሏል ተብሎ ከተነገረለት ወረርሺኝ ጋር ግንኙነት ይኑረው አይኑረው የተረጋገጠ ነገር የለም ብሏል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት በአዲስ መልክ የተቀሰቀሰውን የኢቦላ ወረርሽኝ ለመግታት በአፋጣኝ የህክምና ባለሙያዎች ግብረ ሃይል ማቋቋሙንና ከአገሪቱ መንግስት ጋር እርብርብ ማድረግ መጀመሩንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ኢቦላ ለዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በቀላሉ የማታሸንፈውና በቋሚነት ፈተናዋ ሆኖ የሚቀጥል አገራዊ ተግዳሮት ነው ያሉት የአለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም፤ የአገሪቱ መንግስትና የጤናው ዘርፍ ባለሙያዎች ለችግሩ መፍትሄ ለመሻት ቀጣይነት ያለው እርብርብ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 ለአርእስትነት የተመረጠው አባባል የሴቶች ጤንነትን በሚመለከት በአዲስ አበባ ተደርጎ በነበረ አንድ መድረክ በተበተነ አጀንዳ ላይ መሪ ሐሳብ ሆኖ የቀረበ ነው፡፡ የሴቶችን ጤና በመጠበቁ ረገድ በተለይም የጤናው ዘርፍ ባለሙያዎች በምን መልኩ ዛሬም ነገም ከእሱዋ ጋር መሆን እንደሚጠበቅባቸው የሚያሳዩ ሳይንሳዊ ጽሁፎች የቀረቡበት ነበር፡፡ ሐምሌ 5/2010 በራድሰን ብሉ ሆቴል ለአንድ ቀን በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ እና በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር Roche በተባለ የውጭ ድርጅት አማካኝነት ለአ ንድ ቀን በተደረገው የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም አንዱ አባባል ዛሬ መስራት ታካሚዎች ነገ የሚፈልጉትን ነገር ለማሟላት ይጠቅማል የሚል ሀሳብ ነበረው። በእለቱ ከተነሱት ነጥቦች መካከል መካንነትና የማህጸን ካንሰርን በሚመለከቱ ርእሶች ላይ የተደረጉ ጥናቶች እና እውነታዎች በባለሙያ ዎች ቀርበዋል፡፡ በዚህ እትም ለንባብ ያቀረብነው በተለይም በማህጸን በር ካንሰር ዙሪያ ያለውን ሀሳብ ሲሆን በዚህ ርእሰ ጉዳይ ዶ/ር ታደሰ ኡርጌ የጽንስና ማህጸን ሕክምናና የመራቢያ አካላት ካንሰር ሕክምና እስ ፔሻሊስትን ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ አነጋግረናል፡፡
እንደ ዶ/ር ታደሰ እማኝነት በዚህ በአንድ ቀን የግንዛቤ ማስጨበጫ ውሎ የተነሱ አበይት ጉዳ ዮች ሁለት ናቸው፡፡ እነሱም መካንነት እና የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ዙሪያ ያሉ አሰ ራሮ ችንና አዲስ ቴክኖሎጂን የማስተዋወቅ እና ወደ አፈጻጸሙም እንዴት መግባት እንደሚቻል የተጠቆመ በት ነበር፡፡ በቀጥታ ከእኔ ሙያ ጋር በተያያዘ ማንሳት የምፈልገው ከማህጸን ጫፍ ካንሰር ጋር የተያያዘውን ይሆናል በማለት ዶ/ር ታደሰ የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የማህጸን በር ወይንም ጫፍ ካንሰር መከላከል የምንችለው የካንሰር አይነት ነው፡፡ ካንሰሩ ሳይከሰት አስቀድሞ በምርመራ ወደ ካንሰር የመሄዱን ሁኔታ ማወቅ ስለሚቻል ሕክምናውን በመስጠት ካንሰሩን ለማስቆም የሚያስችል አሰራር አለ፡፡
ዶ/ርታደሰ አያይዘው እንደገለጹትም የማህጸን ጫፍ ካንሰር መከላከል ከሚቻሉ የካንሰር አይነቶች አንዱ ነው፡፡  የቅድመ ካንሰር ምርመራ ዘዴዎች የተለያዩ ናቸው፡፡ ስለሆነም ባደጉት አገራት ያለው የምርመራ ዘዴ የተለያየና ዘመናዊነቱም ከፍ ያለ ሲሆን በእኛ አገር ግን ዝቅተኛ በሆነ ወጪ በየትኛውም የመንግስት ጤና ተቋም ደረጃ (VI ) visual Inspection በሚባለው ምርመራውን ሰርቶ ችግሮች ሲኖሩ ማከም የሚቻልበትን ዘዴ የኢትዮያ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ቀርጾ ወደ ስራው የተገባበት ነው ፡፡  በእርግጥ እኛ የምንጠቀምበት ምርመራ ምን ያህል ጠቀ ሜታዎች አሉት ወይንም ምን ያህል በትክክል ችግሩን በምርመራው አውቆ ሰዎቹን መርዳት ያስችላል ስለሚለው ብዙ ነገር ያለ ሲሆን ነገር ግን በዋናነት ተመራጭ ሆኖ ሳይሆን ከወጪ ጋር ተያይዞ የሚተገበር ነው፡፡ ከወጪም ብቻ ሳይሆን ከሰው ኃይል እንዲሁም ከአቅርቦት አቅም ጋር በማያያዝ ካንሰር ከመከላከል አንጻር ሲታይ የራሱ ችግሮች ቢኖሩትም እንኩዋን ውጤታማ በመሆኑም ነው፡፡
የማህጸን በር ካንሰርን በመከላከል ረገድ ሌሎች ማለትም ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቅም ላይ ከሚው ለው በተሻለ አገልግሎት ላይ የሚውሉ የቴክኖሎጂ ዘዴዎች አሉ፡፡ ለምሳሌም ፡-
ሳይኮሎጂ የሚ ባል ወይንም ሴሎችን ከማህጸን ጫፍ ላይ ወስዶ መመርመር፤
ሌላው አሁን በመለመድ ላይ ያለው የ (HPV)DNA ምርመራ ማለትም ይህንን የማህጸን ጫፍ ካንሰር የሚያመጣ ሕዋስን መመርመር ማለት ነው፡፡
በዚህ ቫይረስ ያልተጠቁ ሴቶች ይህ በሽታ ሊይዛቸው ስለማይችል ብዙ ሴቶችን ይህ ምርመራ ይረዳል፡፡ ስለዚህ ከሌላው ሁሉ ይህ የተሻለ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ከምርመራው ሁኔታ ጀምሮ በምን ያክል ጊዜ መመርመር አለባቸው ?ቫይረሱ ካለባቸው ምን መደረግ አለበት ?ቫይረሱ ከሌለባቸ ውስ ?የሚለውን ሁሉ የያዘ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ነበር እንደ ዶ/ር ታደሰ ኡርጌ ማብራሪያ፡፡ ይህ ዘመናዊ የምርመራ ሂደት በተለይም ዋጋው ከበድ የሚል ነው በሚል ብዙ አገራት ኢትዮ ጵያን ጨምሮ የማይደፍሩት ቢሆንም እንደ ሰብሳቢዎቹ እማኝነት ግን በእርግጥ አንዲት ሴት ለአንድ ጊዜ በምታደርገው ምርመራ ውድ ነው ሊባል ቢችልም ነገር ግን አንዲት ሴት እስከ 65/አመት እድሜዋ ድረስ ልታደርገው ከሚገባት ምርመራ አንጻር ሲታይ ግን ዋጋው ውድ ነው አይባልም፡፡ በዚህ የምርመራ ዘዴ አንዴ ተመርምረው ቫይረሱ የሌለባቸው ከሆነ ለረጅም ጊዜ ሳይመረመሩ መቆየት ይችላሉ፡፡ አንዳንዴም ቫይረሱ ሳይኖርባቸው አንዳንድ ለውጥ ሲከሰት በሌላ ምርመራ ሊገኝ ስለሚችል ይህም ወጪ ያስከትላል፡፡በሌላ በኩል ደግሞ ቫይረስ እያለባቸው ነገር ግን ሳይታወቅና በሁዋላም ቫይረሱ ሊከሰት እየቻለ ግን ሳይታከም ቢቀር ለሚደረገው ሕክምና የሚወጣው ወጪም ሲሰላ ከበድ ማለቱ አይቀርም፡፡ ስለዚህም እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች ስንመረምር በረጅም ጊዜ ሂደት ያለው የዋጋ ውድነት ከአዲሱ ቴክኖሎጂ የሚበልጥ ሳይሆን እንዲያውም የሚያንስ ነው የሚል የግንዛቤ ማስጨበጫ ነጥብ ተነስቶአል፡፡  
የግንዛቤ ማስጨበጨው መድረክ ለተሳታፊዎች በበተነው መረጃ ላይ እንደሚታየው፡-
በአለማችን በየአመቱ ወደ 530.000/የሚጠጉ አዲስ የማህጸን በር ካንሰር ታማሚዎች ይከሰታሉ፡፡
ሰርቫይካል ካንሰር በጊዜው ከታከመ ከ80% በማያንስ ሁኔታ የሚድን በሽታ ነው፡፡
ይሁን እንጂ በአለም አቀፍ ደረጃ በየአመቱ ወደ 270.000/የሚሆኑ ሴቶች በማህጸን በር ካንሰር ምክንያት ለሕልፈት ይዳረጋሉ፡፡
ATHENA የተባለው ጥናት እንደሚያሳየው አብዛኛው ሕመም ከ40/አመት በላይ ካሉት ጋር ሲነጻጸር ከ25-29/ አመት እድሜ በሚገመቱ ሴቶች ላይ ይበዛል፡፡
ዶ/ር ታደሰ እንደሚሉት አሁን በአገራችን በተለይም በመንግስት ሆስፒታሎች የሚደረገው የቅድመ ካንሰርም ሆነ ካንሰሩ ከተከሰተ በሁዋላ የሚደረገው ምርመራ ብዙ ሕመምተኞችን እያገዘ ይገኛል። በግንዛቤ ማስጨበጨው መድረክ ላይ የተነሳው አዲስ ቴክኖሎጂ ደግሞ የቫይ ረስን DNA መመርመርን የሚጠይቅ ነው፡፡ ስለዚህም አሁን እየተደረገ ያለው አዲስ ሳይንሳዊ ውጤቶች ሲኖሩ ቀድመው ወደስራው የተሰማሩ ሐኪሞችን ግንዛቤው እንዲኖራቸው ማድረግ፤ የተሻለ ከሆነና ባለሙያው ነገሩ ከገባው በተለይም ይጠቅማል ብሎ ካሰበ ወደ ሐገር እንዲገባ የተለያዩ መንገዶችን መፈለግ፤ ጥያቄ ማቅረብ፤ የመሳሰሉት ነገሮች  እንዲከሰቱ  ማድረግ እንዲያስችል ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ይህን መመርመሪያ መሳሪያ ወደአገር ለማስገባት የሚያስችል አቅም ያላቸው ድርጅቶችም ስለሁኔታው እንዲያስቡ ለማድረግ ያስችላል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የምርመራ ሁኔታ ከላይ እንደተገለጸው (VI) visual Inspection የሚባለው ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ የሕክምና ዘርፍ ሳይንሱ የትጋ ደርሶአል? የት ኛው ይሻላል? ለሚለው ጥያቄ የተለያዩ ጽሁፎችን ወይንም ጥናቶችን…ወዘተ ከማንበብ በተጨ ማሪ ቴክኖሎጂውን በትክክል በሚያውቁት እንደነዚህ ባሉ ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም መዘጋጀቱ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ በሌላም በኩል ይህ ነገር በትክክል ለኛ ይጠቅማል ወይንስ ?የሚለውንና ለምርምር መነሻ የሚሆኑ ሀሳቦችንም አንስቶ መወያየት ፤የፖሊሲ አቅጣጫንም መፈተሸ የባለሙያው ድርሻ ስለሆነ ከዚህ የሚገኘው ውጤት በቀጣይ ለሚኖሩት ታካሚዎች አገልግሎት አሰጣጥ አስፈላጊ ነው፡፡
ዶ/ር ታደሰ ከጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትነት በተጨማሪ Gynecology oncologist በተባለው የሙያ ዘርፍ  በተለየ እስፔሻሊስትነት ተምረው የመራቢያ አካላትን ካንሰር በመከላ ከልና በማከም ረገድ በአሁኑ ወቅት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ የት ምህርቱን መጀመር አስመልክተን ባነጋገርናቸው ወቅት እና በአሁኑ ጊዜ ያለውን የታካሚ ሁኔታ ሲገልጹ በጳውሎስ ሆስፒታል ደረጃ ሲታይ ያለው የህመምተኛ ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ ቀደም ሲል ስራው ሲጀመር በሳምንት አንድ ቀን በሚኖረው የክሊኒክ ሕክምና በጣም ጥቂት ምናልባትም 4/ እና 5/ ሰዎች ለምርመራ ይቀርቡ ነበር፡፡ አሁን ግን በሳምንት ከ50/በላይ ሕመ ምተኞችን እናያለን፡፡ ይህም የሚሆንበት ምክንያት የካንሰር ሕክምና በአንድ ጊዜ የሚያበቃ ሳይሆን ቀጣይነት ያለው በመሆኑም ነው፡፡ ይህ እንግዲህ በጥቅሉ የመራቢያ አካላት ካንሰርን የሚመለከት ሲሆን ከዚህ ውስጥ አንዱ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ነው፡፡ ስለዚህም አንዳንዶች የካንሰሩ ይዘት በዚህ ሆስፒታል ከሚታይበት ደረጃ ላይ ካልሆነ ለምሳሌም ካንሰሩ ወደ ሽንት ፊኛ ወይንም ወደአጎራባች አካላት ላይ የመታየት አዝማሚያ ካለ  እና የጨረር ሕክምና ካስፈ ለገ ዛሬም ወደጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ይላካሉ፡፡ ግን አሁን በግንዛቤ ማስጨበጫው ፕሮግ ራም ያየነው በሽታ አምጪ ሕዋስ ሳይኖር ወይንም ጉዞውን ሳይጀምር ማለትም ወደፊት ካን ሰር ከ10-15/ አመት ባለው ጊዜ ሊመጣ ይችላል የሚያሰኘውን በሽታ አስቀድሞ ለማስቀረት ውጤታማ የሆነ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ግን አሁንም አገሪቱ በምትችለው አቅም የማህጸን በር ካንሰ ርን መከላከል ስለሚቻል በስራ ላይ ያለውን ቴክኖሎጂ መጠቀም የሁሉም ምርጫ መሆን አለ በት፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን በመንግስት ተቋማት ሳይሆን በግሉ ዘርፍ መሳሪያው ሊኖር ስለሚ ችል የሚፈልጉ አጠያይቀው መጠቀም ይችላሉ ዶ/ር ታደሰ ኡርጌ እንደገለጹት፡፡

 በልዩነቱ ያዘኑ ምእመናንን ይቅርታ ለመጠየቅ ተወስኗል
          “ዋነኛው የጥላቻ ምሶሶ በይፋ ተናደ”/ጠቅላይ ሚኒስትሩ/


    ላለፉት 26 ዓመታት በተፈጠረ አለመግባባት ለሁለት ተከፍሎ የነበረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ወደ አንድነቱ እንዲመለስ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያኒቱ በሁለት ፓትርያርኮች እንድትመራ ከስምምነት ተደረሰ፡፡
ካለፈው ሳምንት እሑድ ጀምሮ በአሜሪካን ዋሽንግተን ዲሲ የተካሔደው የኢትዮጵያውና የአሜሪካኑ ሲኖዶሶች የሰላም ጉባኤ በዕርቅ መቋጨቱን ተከትሎ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት አንድነቷን ከትላንት በስቲያ ሐምሌ 19 ቀን ዐውጃለች፡፡
4ኛው ፓትርርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ፣ በ1984 ዓ.ም. በፖለቲካዊ ግፊትና ጫና መንበራቸውን ለቀው ከተወሰኑ ብፁዓን አባቶች ጋራ መሰደዳቸውን ተከትሎ፣ የአሜሪካው የስደት ሲኖዶስ እና የኢትዮጵያው የሀገር ቤቱ ሲኖዶስ በሚል በተፈጠረ መከፋፈል ቀኖና እንደተጣሰና አስተዳደራዊ ልዩነት እንደተከሠተ ተገልጿል፡፡
ከሁለቱ ሲኖዶሶች የተወከሉ ስድስት ልኡካን አባቶች፣ባለፈው ሰኞ ሐምሌ 16 ቀን ያለአደራዳሪ በቀጥታ ባካሔዱት የአጭር ጊዜ ውይይት፣ መከፋፈሉ እንዲያበቃ ከስምምነት መድረሳቸው ተበሥሯል፡፡ ላለፉት 26 ዓመታት የዘለቀው ልዩነት አብቅቶ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከአንድ ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ እየተቀበለች እንደምትመራ ከትላንት በስቲያ ሐምሌ 19 ቀን፣ በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
በዚሁ ባለ6 ነጥቦች መግለጫ መሠረት፣ ላለፉት 26 ዓመታት በስደት በአሜሪካ የኖሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ፣ በፓትርያርክ ማዕርግ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በመንበረ ፓትርያርኩ በሚዘጋጅላቸው ለክብራቸው የሚመጥን ማረፊያ ይቀመጣሉ፡፡ሁለቱም ቅዱሳን ፓትርያርኮች የሥራ ድርሻ እንደሚኖራቸው በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡ 4ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ፣ በጸሎትና በቡራኬ መንፈሳዊ አገልግሎት ይሰጣሉ፤ 6ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱ አቡነ ማትያስ ደግሞ፣ የአስተዳደሩን (የቢሮውን) ሥራ እያከናወኑ አጠቃላይ አመራር ይሰጣሉ፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ ለሁለቱም ፓትርያርኮች እኩል የአባትነት ክብር የምትሰጥ ሲሆን፤ አገልግሎቷን በምታከናውንባቸው የዓለም ክፍሎች ሁሉ የሁለቱንም ስም በቅደም ተከተል ትጠራለች፡፡
በሁለቱም ሲኖዶሶች በኩል ቀኖናዊ ጥሰት እንደተፈጸመና ሁለተኛው ፓትርያርክ ሰማዕተ ጽድቅ አቡነ ቴዎፍሎስ ለሞት ተላልፈው ከተሰጡበት ጊዜ ጀምሮ መሰል ስሕተቶች በተደጋጋሚ መታየታቸውን መግለጫው አውስቷል፡፡ ይህም፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ከጊዜው ጋራ አብሮ ለመሔድ በሚል የቤተ ክርስቲያኒቱን መብት የማስጠበቅ ሓላፊነቱን ባለመወጣቱ የተከሠተ እንደሆነ አስረድቷል፡፡ ጥፋቱና የዓመታት ልዩነቱ የምእመናኑን ልብ በሐዘን እንደሰበረው ጠቅሶ፣ ያለፉትንም ኾነ በሕይወት ያሉትን በጋራ ይቅርታ ለመጠየቅ ልኡካኑ በጋራ መወሰናቸውን አስታውቋል፡፡ ከሁለቱ ሲኖዶስ መዋሐድ በኋላ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከዳግም ክፍፍል ለመጠበቅና ሉዓላዊነቷን ለማስከበር ቅዱስ ሲኖዶሱ ሕጉንና ሥርዐቱን ያገናዘበ ደንብ እንዲወጣ ልኡካኑ መስማማታቸውን ጠቁሟል፡፡
ከሁለቱም በኩል የተላለፈው ቃለ ውግዘት፣በአንድነት በሚካሔደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እንዲፈታ በሰላም ልኡካኑ በአንድ ድምፅ የወሰነ ሲሆን፣ ከልዩነቱ በፊት የተሾሙ ነባር ሊቃነ ጳጳሳት፣ ስማቸውና ክብራቸው ተጠብቆ በውጭ ሀገርም ኾነ በሀገር ቤት እንዲመደቡና እንዲያገለግሉ፤ ከልዩነቱ በኋላ የተሾሙት ኤጲስ ቆጶሳት፣ ጳጳሳትና ሊቃነ ጳጳሳት ደግሞ ስማቸውን እንደያዙ ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቀበላቸው፣ በውጭም ኾነ በሀገር ቤት አህጉረ ስብከት ተመድበው እንዲያገለግሉ ልኡካኑ ተስማምተዋል። የስም ተመሳስሎ ያላቸው አባቶች፣ እንደቅደም ተከተላቸው ቀዳማይ፣ ካልዓይ፣ ሣልሳይ…ወዘተ በሚል እንዲለዩ ተወስኗል፡፡
ለዕርቅ ሰላሙ ከአዲስ አበባ የተወከሉት ልኡካንና የአስተባባሪው ኮሚቴ አባላት ሰሞኑን የሚመለሱ ሲሆን፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስና አብረዋቸው ያሉት አባቶች፣ ምእመናኑን ተሰናብተው ከነሐሴ አጋማሽ በኋላ እንደሚመለሱ ተጠቁሟል፡፡ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ የሚመራና በዘጠኝ ንኡሳን ክፍሎች የተዋቀረ የአቀባበል ዐቢይ ኮሚቴ መቋቋሙ ታውቋል፡፡
በይፋዊ መግለጫው ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ለዕርቀ ሰላሙ በተደጋጋሚ የተደረጉ ጥረቶች ሳይሳኩ ሲኖዶሳዊ አንድነቱ መዘግየቱን፣መንግሥትም የድርሻውን አለመወጣቱን ጠቅሰው ይቅርታ ጠይቀዋል። “ዋነኛው የጥላቻ ምሶሶ በይፋ ተናደ” በማለት ስምምነቱን ያሞገሱት ዶ/ር ዐቢይ፣ የሁላችን ኩራት የሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከሁለት መከፈሏ ብቻ ሳይሆን በሁለቱም ወገን ውግዘትና ነቀፋ ሲዘራ አያገባኝም ብሎ የቆመ ኃይል ሁሉ ዛሬ ሊጸጸት ይገባዋል፤ ሲሉ ወቅሰዋል። አንድነቱ ቀድሞ ቢመለስ ኖሮ የኢትዮ ኤርትራ ችግር አይዘገይም ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አንድነቱ ከተመለሰ ዘንድ ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱ የውስጥ ችግሮቿን በራሷ ከመፍታት በሻገር ለሀገር ለላምና ልማት የመጸለይ፣ የመገሠጽና የማስታረቅ ተግባሯን እንድትፈጽም አሳስበዋል፡፡
የአንድነቱን መመለስ በሀገር ቤት ለማብሠር ብዙ ሺሕ ምእመናን በተገኙበት በሚሌኒየም አዳራሽና በተለያዩ ከተሞች የዕውቅናና የምስጋና መርሐ ግብር እንደሚደረግም ዶ/ር ዐቢይ አስታውቀዋል፡፡

  ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ይጭነው አጋሠሥ፣ ይለጉመው ፈረስ የነበረው፣ ለምድር ለሰማይ የከበደና ባለሙያ የሆነ፤ ትልቅ ጌታ፤ በአንድ አገር ይኖር ነበር፡፡
አሽከሮቹ፣ ባለሟሎቹ፣ ጋሻ- ጃግሬዎቹ ሥፍር ቁጥር የላቸውም፡፡ ከአሽከሮቹ መካከል ሁለት በጣም የሚተሳሰቡ፣ በጣም የሚግባቡ፣ ስራ ከመሥራታቸው አስቀድመው የሚመካ ኩሩ ቅንና ታታሪ አሽከሮች አሉ፡፡
አንድ ቀን አንደኛው፤ ለሁለተኛው፤
“እንደዚህ ያለ አስተዳደሪ ጌታ ስላለን ዕድለኛ እንደሆንን ይገባሃል?” ሲል ጨዋታ ያነሳል፡፡
ሁለተኛው፤
“እጅግ በጣም ዕድለኞች ለመሆናችን ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ እንዲያውም እስከ ዛሬ ለዋለልን ውለታ ምን ልንከፍል እንችላለን? እያልኩ ሁልጊዜ እጨነቃለሁ፤ እጠበባለሁ፡፡”
አንደኛው፤
“ዕውነትም አንድ ነገር ለማድረግ መቻል አለብን፡፡ እስቲ አንተም አስብበት፤ እኔም ላስብበትና አንድ መላ እንፈጥራለን” አለ፡፡
ሁለቱ ታማኝ አሽከሮች ለውለታው ምላሽ ምን ለማድረግ እንደሚችሉ ማሰላሰላቸውን ቀጠሉ፡፡
የሁለቱ አሽከሮች ወዳጅነት የሚያስገርመው የጎረቤት ሰው፤ አንድ ቀን ወደ ጌትዬው ይመጣና፤
“እኔ እምልህ ወዳጄ፤ አንድ ነገር ልጠይቅህ እፈልግ ነበር” አለው፡፡
ጌትዬውም፤
“ስንትና ስንት ዘመን አብረን የኖርን ጎረቤታሞች ሆነን ሳለን፤ ጥያቄህን በሆድህ ይዘህ እስከዛሬ  መቆየት የለብህም ነበር፡፡ አሁንም የፈለከውን ጠይቀኝ” አለና መለሰለት፡፡
ጎረቤትዬውም፤
“እነዚህ ሁለት ታማኝ አሽከሮችህን፤ ምን ዘዴ ተጠቅመህ ነው እንደዚህ ተዋደውና ተሳስበው እንዲያገለግሉህ ያደረግሃቸው? መቼም በዚህ አገር እንዳንተ ያለ ዕድለኛ ሰው ያለ አይመስለኝም!” አለው፡፡
ጌትዬው የመለሰው መልስ በጣም አስገራሚ ነው፡፡
“ወዳጄ! እርስ በርስ ተጣጥመው እንዲያገለግሉኝ ለማድረግ የተጠቀምኩበት ምንም ጥበብ የለም፡፡ ይልቁንም ሌት ተቀን የምጠበብ የምጨነቅበትን አንድ ነገር ልንገርህ፡-
ለእኔ የሚጠቅመኝ ከሚዋደዱ ይልቅ ቢጣሉ ነበር!”
ጎረቤትዬው በጣም ደንግጦ፤
“ለምን? እንዴት?” ሲል ጠየቀው፡፡
ይሄኔ ጌትዬው፤
“አየህ ወዳጄ! ለእኔ የሚበጀኝ ቢጣሉና አንዱ አንዱን ቢጠብቅልኝ ነበር!” አለው ይባላል፡፡
* * *
“የአልጠግብ ባይ..” አስተሳሰብ፤ ሰው ወደ ጠብ፣ ወደ ጠላትነት፣ ወደ መናቆር፣ ወደ መሰላለል፤ እንዲሄድ የሚያደርግ ነው!
ሰው ከተፋቀረ፣ ከተሳሳቀና ደስ ብሎት ካደረ ይከፋዋል፡፡ ስለዚህም እንቅልፉን አጥቶ ሲያሴር፣ ነገር ሲጠመጥም ያነጋል፡፡ ደግ እንዳይበረክት ይመኛል፡፡ መመኘት ብቻ አይደለም ጥፋት ጥፋቱን ያጎለብታል፡፡ ሰላም ይበጠብጠዋል፡፡ የማሪያም መንገድ ሲታይ ዐይኑ ይቀላል! ወገን ከወገኑ ሲለያይ፣ ዘር ከዘር ሲደማማ፣ ሲቋሰል፤ ህልውና ይረጋገጥለት ይመስለዋል፡፡ እየዘረፈ፣ እየመዘበረ የገነባው ፎቅ ውሎ አድሮ ይነካበት አይመስለውም፡፡ የድሀ ዕንባ ጎርፍ ሆኖ ይወስደው አይመስለውም፡፡ ዘላለም እያባላሁ፣ እያናከስኩ እኖራለሁ፤ ይላል! እንደ ሁልጊዜው፤ ረዥም ጊዜ መኖርን ከዘለዓለማዊነት ጋር ያምታታዋል (He mistakes longevity for eternity)፡፡ የማታ ማታ ግን ተመናምኖ ተበትኖ ያበቃል! ይህ በታሪክ የታየ፣ ነገም የሚታይ ገሀድ ዕውነት ነው፡፡ “ሞት ቢዘገይ የቀረ ይመስላል” ነው ጉዳዩ!
አንድ፤ ጃንሆይ (ቀዳማይ ኃይለ ሥላሴ) ተናገሩት የሚባል መሠረታዊ አባባል አለ፡፡ አቃቤ- ሰዓት ተሰጥቶት ጉዳዩን በቅጥፈት ላስረዳቸው ሚኒስትር ያሉት ነገር ነው ይባላል፡-
“…ያልተሠራውን ሠርቻለሁ እያሉ መደለልና ወደፊትም እሠራለሁ እየተባለ ሐሳብን በሸምበቆ መሠረት ላይ መገንባት፣ ታላቅ ጉዳት የሚያስከትል ስለሆነ፤ የሠራኸውንም ሆነ ወደፊት ለመሥራት የምታስበውን እየለየህ በጥልቀት አጥናው…”
ይህ ዛሬም ላገራችን ባለሥልጣኖች የሚሠራ መሆኑን ልብ እንበል!
ሀገራችን ወደፊት ትራመድ ዘንድ የተደቀኑባትን አንዳንድ ጥያቄዎች በጥንቃቄ መመለስ ይገባታል፡፡
እነዚህ ጥያቄዎች በመሪዎች ጫንቃ ላይ ብቻ የምንጭናቸው ሳይሆኑ የሁላችንንም እርዳ-ተራዳ የሚሹ ናቸው፡፡ ተነጣጥለን የምንታገልባቸው ሳይሆኑ አንድነታችንን ልንፈትሽባቸው ግድ የሚሉ ናቸው፡፡ እነሆ፡-
ምን ዓይነት ዲሞክራሲ እንዲኖረን እንፈልጋለን? ቀጣዩን ሥርዓት ለመገንባት የእስካሁኑን በምን መልክ ብንገላገለው፣ ብንጠግነው ወይም ብናድሰው ይሻላል? ህገ-መንግስቱ ላይ ያየናቸው እንከኖች የቶቹ ናቸው? ምን ቢደረጉ ይመረጣል? ዕውን የሽግግር መንግሥት ያስፈልጋል? በኢትዮ-ኤርትሪያ ዙሪያ የተጀመረው መልካም ጉርበትና እንዴት ይቀጥል? በዝርዝር ጉዳዩን ማን ያውጠንጥን? ቀድሞ በ1983 ዓ.ም ከምናውቀው ግንኙነታችን የተለየ ምን መልክ ይያዝ? ኮንፌዴሬሽን አዋጭ አካሄድ ነው ወይ? የህወኃት እና የአዲሱ ጠ/ሚኒትር አቅጣጫ ግንኙነት ውስጥ የኢትዮጵያ ህዝብ ሚና ምን መሆን አለበት? ከህገ መንግሥት ማሻሻልና ከምርጫው የቱ ይቅደም? ለመሆኑ ፕራይቬታይዤሽን ያዋጣል? የምሥራቅ አፍሪካን መሪነት ማን ይይዛል? ያልተረጋጋውና የማይረጋጋው (ever volatile) የአፍሪካ ቀንድ ዕጣ-ፈንታ ምን ይሆን? በኢትዮጵያ ጉዳይ ዕውነተኛ ህዝበ- ተሳትፎ እንዴት ለማምጣት ይቻላል? ኢህአዴግ ከግንባር ወደ ውህደት ሊመጣ ይቻለዋልን? ህወኃት እና የትግራይ ህዝብ እንዴት ይታያሉ? ዕውነት ህወኃት የመሰነጣጠቅ አደጋ ላይ ነው? የግለሰቦች ብቻ ሳይሆን ተቋማዊ የሆነን ጥንካሬ እንደምን ማምጣት ይቻላል? ሙስና በማስፈራራት ይቆማል? እስካሁን የወጡ ህጎች የፕሬስ፣ የፀረ ሽብር፣ የብሮድካስት ወዘተ እንዴት ይሻሻሉ? ያለው መንግሥት የህዝብ አመፅ የወለደው ነው? አለመረጋጋቱ ተገቷል ወይስ ሊቀጥል ይችላል?...
ጥያቄዎቻችን በርካታ ናቸው፡፡ የሚመለከተው አካል በአግባቡ ሊመልሳቸው ይገባል፡፡ ከእንግዲህ ማድበስበሱም ሆነ ቆይ-ነገ- ማለቱ (Procrastination) ለማንም አይጠቅምም፡፡ ሳንፈታቸው መጓዝና እርምጃ አለመውሰድ ስህተት ነው!! ይህን ስህተት ደግመን ከሠራን “ትላንት ማታ ቤትህ ስትገባ የመታህ የድንጋይ እንቅፋት ዛሬም ከደገመህ፤ ድንጋዩ አንተ ነህ” የሚለው የቻይናዎች አባባል እኛ ላይ ሠራ ማለት ነው፡፡ ሰብሰብ፣ ጠንቀቅና ጠበቅ እንበል! ሁሉንም ደበላልቀን አንድ ላይ ከመፍጨት፣ በየከረጢቱ አስቀምጠን መቋጠር በመልክ በመልኩ ለመፍት ያመቻል፡፡ (From smashed potato to potato-sacks እንደሚሉት መሆኑ ነው)

የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ሃላፊ እና የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት የህዝብ ግንኙነት አደረጃጀት አማካሪ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ጌታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል፡፡
አቶ ተስፋዬ ጌታቸው የአማራ ክልል የገበያ፣ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ ሆነው የሠሩ ሲሆን የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ፅ/ቤት ሃላፊ ሆነው ከተሾሙ ጥቂት ወራትን ብቻ ነበር ያስቆጠሩት፡፡
በአሜሪካን ሃገር በህክምና ላይ ሣሉ ህይወታቸው ያለፈው አቶ ተስፋዬ፤ በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ በብርቱ ይደግፉ ከነበሩ አመራሮች ተጠቃሽ እንደነበር ታውቋል፡፡


ከተለያዩ የአለማችን አገራት ወደ ኢትዮጵያ ከሚገቡት የተለያዩ ከባድና ቀላል ተሽከርካሪዎች መካከል 85 በመቶ ያህሉ በውጭ አገራት ለ20 አመታትና ከዚያ በላይ አገልግሎት የሰጡ መሆናቸውን አንድ አለማቀፍ ሪፖርት አስታውቋል፡፡
ሴንተር ፎር ሳይንስ ኤንድ ኢንቫይሮመንት የተሰኘው ተቋም ባለፈው ማክሰኞ ይፋ ባደረገው አለማቀፍ የጥናት ሪፖርት እንዳለው፣ በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ አገልግሎት በመስጠት ላይ ከሚገኙ ተሽከርካሪዎች መካከል አብዛኞቹ 30 አመታትና ከዚያ በላይ ያገለገሉ ናቸው ተብሎ ይገመታል፡፡
በኢትዮጵያ አገልግሎት የሚሰጡ የከባድና ቀላል ተሽከርካሪዎች ቁጥር ባለፉት 15 አመታት በስድስት እጥፍ ያህል ማደጉን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ከተመረቱ ረጅም ጊዜ ያስቆጠሩ ተሽከርካሪዎች ከውጭ አገራት እንዳይገቡ የሚከልክል የዕድሜ ገደብ ህግና መመሪያ አለመኖሩንና ለረጅም ጊዜ አገልግሎት የሰጡ በርካታ ተሽከርካሪዎች ወደ አገሪቱ እንደሚገቡ አመልክቷል፡፡
በርካታ የአፍሪካ አገራት ለረጅም ጊዜ አገልግሎት የሰጡ አሮጌ መኪኖችን ካደጉት አገራት በከፍተኛ መጠን እንደሚያስገቡ የጠቆመው የተቋሙ ሪፖርት፣ ይህም የአገራቱን ዜጎች ከአካባቢ ብክለት ጋር ተያይዘው ለሚከሰቱ የጤና ችግሮችና ለመኪና አደጋዎች እየዳረገ እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡

Saturday, 21 July 2018 14:08

ሰሞነኛ ወሬዎች

 የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ሠራተኞች አድማ

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ሠራተኞች፤ ደሞዝና ጥቅማጥቅም አነሰን በሚል በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ለሁለት ቀናት የሥራ ማቆም አድማ አደረጉ፡፡
በጥቅማጥቅም ጉዳይ ከምድር ባቡር አስተዳደር ጋር የተስማሙ ሲሆን በደሞዝ ጉዳይ ግን ለወደፊት እንስማማለን ብለው ከሁለት ቀናት አድማ በኋላ ሐሙስ እለት ስራቸውን ጀምረዋል። በሥራ ማቆም አድማው ምድር ባቡር 1 ሚሊዮን ብር ያህል ሳያጣ እንዳልቀረ ይገመታል፡፡

     አዲስ አበባ አዲስ ከንቲባ አግኝታለች

የአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ ሆነው ለ5 ዓመታት ያገለገሉት አቶ ድሪባ ኩማ ከስልጣን ተነስተው የካናዳ አምባሣደር ሆነው መሾማቸውን ተከትሎ፣ አዲስ አበባ የምክር ቤቷ አባል ባልሆኑት ኢንጂነር ታከለ ኡማ እንድትመራ ተወስኗል፡፡
ኢንጂነር ታከለ ኩማ የቀድሞ የሰበታ ከተማ ከንቲባ ሲሆኑ አዲስ አበባን በምክትል ከንቲባነት ያስተዳድራሉ፡፡ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ እና ዶ/ር ሠለሞን ም/ከንቲባዎች ሆነዋል፡፡

        እንባ ያራጨው የመጀመሪያው የአስመራ በረራ
 
ኤርትራና ኢትዮጵያ በይፋ እርቅ ማውረዳቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፈው ረቡዕ 460 ተጓዦችን ከአዲስ አበባ አሳፍሮ ወደ አሥመራ የበረረ ሲሆን በዚህ ከ20 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገ ታሪካዊ በረራ፤ ለዓመታት የተቆራረጡና የተነፋፈቁ ቤተሰቦች በእንባ እየተራጩ ናፍቆታቸውን ተወጥተዋል፡፡
“ይህ የተፈጠረው ሰላም በጣም ያስደስታል፤ ከሰማይ የመጣ ነው የሚመስለው” ብሏል፤ ከ20 ዓመት በኋላ ከቤተሰቦቹ ጋር የተገናኘ ኤርትራዊ ወጣት፡፡
ይህን የጉዞ ቡድንም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሣለኝ እና ባለቤታቸው ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ መርተውታል፡፡

    የደህንነት ሰራተኞች የፓርቲ አባል መሆን አይችሉም

የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት አዲሱ ሃላፊ ጀነራል አደም መሃመድ፤ የደህንነት ባለሙያዎች የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን እንደማይችሉ ገለጹ፡፡
የተቋሙ ሃላፊዎች ሰሞኑን ከሰራተኞች ጋር ባደረጉት ስብሰባ፤ ”የማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል የሆናችሁ ወይ ተቋሙን አሊያም ፓርቲውን ልቀቁ” ብለዋል፤ ጀነራል አደም፡፡ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ በመከላከያ ሚኒስቴርና በደህንነት ተቋም ላይ የሪፎርም ሥራ መጀመሩን መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

    ቴዲ አፍሮ በአዲስ አበባ  ኮንሰርት ያቀርባል

ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) በሚሊኒየም አዳራሽና በመስቀል አደባባይ ኮንሠርት ያቀርባል፡፡ ኮንሠርቶቹ መቼ እንደሚቀርቡ ባይገለፅም ለአዲስ ዓመት ወይም ለመስቀል ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡
በሚሊኒየም አዳራሽ የሚቀርበው ኮንሰርት ከፍ ያለ የመግቢያ ክፍያ የሚኖረው ሲሆን በመስቀል አደባባይ የሚዘጋጀው የሙዚቃ ድግስ ግን በነፃ እንደሚሆን ታውቋል፡፡

      የተቃውሞ ሰልፍ በመቐሌ

ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በግፍ ተፈናቅለናል የሚሉ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በመቐሌ የሠማዕታት ሃውልት ፊት ለፊት ከትናንት በስቲያ ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡
ያለ ምንም ጠያቂ አውላላ ሜዳ ላይ ወድቀናል ያሉት ተጎጂዎቹ፤ ለክልሉ መንግስት በተደጋጋሚ አቤት ብንልም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል።
ተቃዋሚዎቹ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል መጥተው የማያነጋግሩን ከሆነ ከሰልፋችን ንቅንቅ አንልም ብለው እንደነበርና በኋላ ግን በፀጥታ አካላት የማረጋጋት ሥራ መበተናቸውን ለማወቅ ተችሏል።  

      ኢትዮ-ቴሌኮም አዲስ ሥራ አስፈጻሚ ተሾመለት

የኢትዮ-ቴሌኮም ስራ አስፈጻሚ በመሆን ድርጅቱን ለ3 ዓመት የመሩት ዶ/ር አንዷለም አድማሴ፤ ከሃላፊነታቸው ተነስተው ምክትላቸው ወ/ሮ ፍሬህይወት ታምሩ በሥራ አስፈጻሚነት ተሾመዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም በከፊል ወደ ግል ይዞታነት እንዲዘዋወሩ ከተወሰነባቸው የመንግስት የልማት ድርጅቶች አንዱ ነው፡፡ ዶ/ር አንዷለም አድማሴ፤ የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተመድበዋል፡፡

 ጎግል የ5 ቢሊዮን ዶላር ቅጣት ተጣለበት


    ታዋቂው የማህበራዊ ድረገጽ ትዊተር በግንቦትና በሰኔ ወር ብቻ ህገወጥ ድርጊት የሚፈጽሙና የተጭበረበሩ ያላቸውን የ70 ሚሊዮን ያህል ተጠቃሚዎቹን አካውንቶች በመዝጋት አገልግሎቱን እንዳያገኙ ማድረጉን ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል፡፡
የተጭበረበሩና ህገወጥ ድርጊቶችን በሚፈጽሙ ተጠቃሚዎቹ ላይ የሚያደርገውን ቁጥጥርና የሚወስዳቸውን እርምጃዎች እያጠናከረ የመጣው ትዊተር፤ የተጠቃሚዎቹን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ የመቀነስ እርምጃው ገቢውንና ትርፋማነቱን አደጋ ውስጥ እንዳይከተው መሰጋቱን ዘገባው አመልክቷል፡፡
እ.ኤ.አ በ2016 ከተካሄደው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ቅስቀሳ ጋር በተያያዘ ተጠቃሚዎች ያልተገባ ድርጊት መፈጸማቸውን ተከትሎ  የተጭበረበሩ አካውንቶችን በመጠቀም የተሳሳቱ መረጃዎችንና አደገኛ መልዕክቶችን በሚያሰራጩ ተጠቃሚዎች ላይ የሚወስደውን እርምጃ ያጠበቀው ትዊተር፤ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2017 የመጨረሻዎቹ አራት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ የ58 ሚሊዮን ተጠቃሚዎቹን አካውንቶች መዝጋቱን የዘገበው ደግሞ አሶሼትድ ፕሬስ ነው፡፡
በተያያዘ ዜናም፣ የአውሮፓ ህብረት የንግድ ውድድርንና የሞባይል ተጠቃሚ ደንበኞችን ምርጫ የሚገድብ ህገወጥ ድርጊት ፈጽሟል በሚል ባለፈው ረቡዕ በታዋቂው የአሜሪካ ኩባንያ ጎግል ላይ ክብረወሰን የተመዘገበበትን የ5 ቢሊዮን ዶላር ቅጣት ማስተላለፉ ተዘግቧል፡፡
ጎግል የራሱ ምርት የሆነውን አንድሮይድ ኦፐሬቲንግ ሲስተም የሚጠቀሙ የሞባይል ስልኮችን የሚያመርቱ ኩባንያዎችን፣ የራሱ ምርት የሆኑ ሌሎች የፍለጋ አፕሊኬሽኖችን ኢንስቶል እንዲያደርጉ አስገድዷል በሚል ከአውሮፓ ህብረት የተላለፈበትን የገንዘብ ቅጣት ውሳኔ እንደማይቀበልና ይግባኝ እንደሚጠይቅ አስታውሷል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ከሶስት አመታት ምርመራ በኋላ በጎግል ላይ ያስተላለፈው ይህ የገንዘብ ቅጣት፣ በታሪኩ ከንግድ ውድድር ህጎች ጥሰት ጋር በተያያዘ በአንድ ኩባንያ ላይ የጣለው ከፍተኛው ገንዘብ እንደሆነም አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

Page 6 of 400