Administrator

Administrator

የታዋቂው የቴሌቪዥን ሾው አቅራቢ ሠይፉ ፋንታሁን እና የባለቤቱ ወ/ሮ ቬሮኒካ ኑረዲን የሠርግ መልስ ስነስርአት በነገው ዕለት በመቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ይከናወናል፡፡ ሙሽሮቹ የመልስ ስነስርአቱን ከ550 በላይ አረጋውያንና የአዕምሮ  ህሙማን ጋር ከቀኑ 7 ሰአት ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች ያከብሩታል ተብሏል፡፡ ባለፈው ጳጉሜ 1 ሰርጉን በሸራተን አዲስ በደማቅ ስነስርአት የፈፀመው ሰይፉ፤ለሠርጉ ሊያውለው አቅዶት የነበረውን 300ሺህ ብር ለመቄዶኒያና ለሙዳይ በጐ አድራጐት ድርጅት መለገሱ ይታወቃል፡፡ በመልሱ ላይ የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ ታዋቂ ግለሰቦችና ከ5ሺህ በላይ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙ ማዕከሉ ጠቁሟል፡፡  በሥነሥርዓቱ ላይ የመቄዶንያ አረጋውያን፤ ሙሽሮችን የሚመርቁ ሲሆን  ሙሽሮቹም ከነሚዜዎቻቸውና ቤተሰቦቻቸው በማዕከሉ የሚገኙ አረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማንን እንዲሁም አልጋ ላይ የዋሉ ህሙማንን ይጐበኛሉ ተብሏል፡፡ ለአረጋውያን ስጦታ የመስጠትና ጋቢ የማልበስ ፕሮግራም እንደሚኖር ያመለከተው ማዕከሉ፤ አረጋውያንም የእንኳን ደስ አላችሁ ግጥሞችና መነባንቦችን ያቀርባሉ ብሏል፡፡   
በማዕከሉ ከዚህ ቀደም የተለያዩ ሰዎች የሠርግ፣ የቀለበት፣ የልደት፣ የምረቃ ስነስርአት እንዲሁም የሙት አመት መታሰቢያዎች የማከናወን ልምድ እንዳላቸው ታውቋል፡፡ መቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል መንግስት በነፃ ባበረከተለት 30ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ሰጪ ማዕከል ለመገንባትና የተገልጋዮችን ቁጥር ወደ 3ሺህ ለማሳደግ እየሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ማዕከሉን ለመገንባትም 300 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ መነገሩ ይታወሳል፡፡ 

  • ፖፕ አቡነ ቴዎድሮስ፣ የደመራ በዓልን በመስቀል ዐደባባይ ያከብራሉ
  • አክሱም ጽዮንን፣ ጎንደርን፣ ላሊበላንና የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ይጎበኛሉ


  የግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የሃይማኖት አባቶች፣ በሃይማኖታዊ ጉዳዮችና በማኅበራዊ ግንኙነቶች ዙሪያ በአዲስ አበባ እንደሚመክሩ ተገለጸ፡፡
በእስክንድርያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፖፕ እና የመንበረ ማርቆስ ፓትርያርክ አቡነ ቴዎድሮስ ካልዕ ከሚመራው ልኡክ ጋር በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ የሚካሔደው ምክክር፤ የኹለቱን አገሮችና አብያተ ክርስቲያናት የቆየ ታሪካዊ፣ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ግንኙነት አጠናክሮ በማስቀጠል ወደ ከፍተኛ መተማመን እንዲያመራ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፤ ተብሏል፡፡
በክርስትናው አስተምህሮ ባላቸው የትምህርተ ሃይማኖት አንድነት፣ “እኅትማማች” የሚባሉት ኹለቱ አብያተ ክርስቲያናት፣ የጋራ ተልእኮዎቻቸውን በአንድነት በመፈጸም ጥንታዊውንና ታሪካዊውን ግንኙነታቸውን ለማዳበር የጋራ ኮሚቴ እንዲቋቋም የኢትዮጵያው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ባለፈው ዓመት ጥር ባደረጉት የግብጽ ይፋዊ ጉብኝታቸው ወቅት ጠይቀዋል፡፡
የግብጹ አቻቸው ፖፕ አቡነ ቴዎድሮስም ጥያቄውን በመቀበል፤ በሃይማኖታዊ፣ በጤና እና በማኅበራዊ ጉዳዮች ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር አብሮ የሚሠራና በሊቀ ጳጳስ የሚመራ ኮሚቴ ለመሰየም ዝግጁ መኾናቸውን አስታውቀው እንደነበር ተወስቷል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ፣ ፈለገ ግዮን ተብሎ የሚታወቀውና ኹለቱ አገሮች በጋራ የሚጠቀሙበት ተፈጥሯዊው የዓባይ ውኃ የማኅበራዊ ትስስሩ መሠረት ሲኾን በዝግ በሚካሔደው የኹለቱ ቅዱሳት ሲኖዶሳት ምክክርም ዐቢይ ትኩረት እንደሚያገኝ ተጠቁሟል፡፡
የዓባይ ውኃን በመተማመን ከተጠቀሙበት ከኹለቱ አገሮች አልፎ ለመላው አፍሪካ የሚበቃ የአምላክ በረከት እንደኾነ ለግብጽ ባለሥልጣናት የተናገሩት ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ “የግብጽ እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድ የሚኾኑት የእግዚአብሔር ጸጋ በኾነው በዓባይ ነው፤ እግዚአብሔር አንድ ያደረገውን ደግሞ ሰው ሊለያየው አይችልም፤” ያሉ ሲኾን ፖፕ አቡነ ቴዎድሮስም፤ “እኛ የግብጽ ሕዝቦች ከዓባይ ወንዝ አንድ ብርጭቆ ውኃ በጠጣን ቁጥር ኢትዮጵያን እናስታውሳታለን፤” ማለታቸው ተጠቅሷል፡፡
በወቅቱ ፖፕ አቡነ ቴዎድሮስ ካልዕ በ2008 ዓ.ም. የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ላይ እንዲገኙ ከፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በቀረበላቸው ግብዣ፣ ትላንት ሌሊቱን ዘጠኝ አባላት ያሉትን የሃይማኖት አባቶች ልኡክ በማስከተል ዐዲስ አበባ የገቡ ሲኾን ከዛሬ ጀምሮ የአምስት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ያደርጋሉ፡፡  ለጉብኝቱ የወጣው መርሐ ግብር እንደሚያመለክተው ፓትርያርኩ፣ ትላንትና መስከረም 14 ቀን ሌሊት 9፡00 ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና የፕሮቶኮል ባለድርሻ አካላት አቀባበል ከተደረገላቸው በኋላ፣ በዛሬው ዕለት ከጠዋቱ 2፡30 በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የመንበረ ፓትርያርኩና የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት፣ የእንኳን ደኅና መጡ ፕሮግራም ይደረግላቸዋል፤ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋርም ይወያያሉ ተብሏል፡፡
ጠዋት በቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል ተገኝተው ጸሎተ ቅዳሴውን በመምራት፣ ሥርዐተ ቅዳሴውን የሚያከናውኑ ሲኾን ከቀትር በኋላም በመስቀል ዐደባባይ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ጋር የመስቀል ደመራ በዓልን ያከብራሉ፡፡
ከመስከረም 17 - 19 ቀን የርእሰ አድባራት ወገዳማት አኵስም ጽዮን ማርያምን፣ የጎንደርን፣ የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትንና ታሪካዊ ስፍራዎችን፣ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን እንዲኹም በአዲስ አበባ የሰበታ ጌቴሰማኔ ቤተ ደናግል ወጠባባት ገዳምንና የጎፋ መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል በመጎብኘት ጸሎት እንደሚያደርጉና እንደሚባርኩ ታውቋል፡፡ በግብፅና በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ታሪክ የኹለቱ እኅትማማች አብያተ ክርስቲያናት ትብብር እንደ ድልድይ ይታያል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የራሷን ፓትርያርክ በ1951 ዓ.ም እስከሾመችበት ጊዜ ድረስ ለ1600 ዓመታት ከግብጽ ቅዱስ ሲኖዶስ በሚሾሙ ጳጳሳት ስትመራ ቆይታለች፡፡ በሀገራቱ መንግሥታት ምክክር ጭምር የመንበሩ ነጻነት ከተገኘም በኋላ የሚካሄዱ ፕትርክናዊ ጉብኝቶች ለውጭ ግንኙነታቸው መጠናከር አስተዋፀኦ እንዳለው ይታመናል፡፡

     ባለፈው ማክሰኞ 80ኛ የልደት በዓላቸውን ያከበሩት አንጋፋው ክላርኔት ተጫዋች መርአዊ ስጦት ተሸለሙ በዳኒ ሮጎ የማስታወቂያ ስራና ፊልም ፕሮዳክሽን ድርጅት አስተባባሪነት በሃርመኒ ሆቴል በተዘጋጀው አርቲስቱን የማክበርና የማመስገን ስነ - ስርዓት ላይ ልጃቸው ኢትዮጵያ መርአዊ ላለፉት 60 ዓመታት የተጫወቱበትን ክላርኔት ያበረከተችላቸው ሲሆን የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበርም ክብራቸውን የሚገልፅ የምስጋና የምስክር ወረቀት እንዳበረከተላቸው ተገልጿል፡፡ በእለቱ አቶ አብነት ገብረመስቀል የ50 ሺህ ብር ስጦታ ያበረከቱላቸው ሲሆን የጃዝ አምባዎቹ ያሬድ ተፈራ፣ አበጋዝ ክብረወርቅ፣ ግሩም መዝሙር፣ ሳምሶን ጃፋር፣ ፋሲል ዊሂር እና አክሊሉ ዘውዴ ለአርቲስቱ ክብር እያንዳንዳቸው ሙዚቃ ተጫውተውላቸዋል፡፡ አርቲስት ጌትነት እንየው፣ ፍቃዱ ተክለማርያምና ሙዚቀኛው ግርማ ይፍራሸዋም በየግላቸው ስጦታ ያበረከቱላቸው ሲሆን ጌትነት እንየው “ድንቅ” የተሰኘ ግጥም እንደገጠመላቸውም የዳኒ ሮጎ ስራ አስኪያጅ አርቲስት ዳንኤል ተገኝ ተናግሯል፡፡
 አቶ አብነት ገ/መስቀል አርቲስቱን እስከመጨረሻው ለመደገፍ ቃል የገቡ ሲሆን የላንድ ማርክ ሆስፒታል ባለቤት ፕ/ር ከበደ ወሌም በማንኛውም ሁኔታ ለህክምና ሲመጡ ሆስፒታላቸው በነፃ እንደሚያክማቸው ቃል ገብቷል፡፡ ቲሞኒየር ልብስ ስፌትም በእለቱ ሙሉ ልብሳቸውን በማልበስ ለአርቲስቱ ያለውን አድናቆት ገልጿል፡፡ 

ሳምሰንግ ምርቶቼ በስፋት መቸብቸባቸውን ይቀጥላሉ ብሏል

      በአለማችን የስማርት ፎን ገበያ ቀዳሚዎቹ ተፎካካሪዎች ሆነው ለአመታት የዘለቁት ሳምሰንግ እና አይፎን፣ ፉክክራቸው ከገበያ አልፎ ችሎት የደረሰ የቴክኖሎጂው ዘርፍ ባላንጣዎች ከሆኑ ሰነባብተዋል፡፡
“ሳምሰንግ የራሱን ፈጠራ እንደመስራት የእኔን እያየ ይኮርጃል” በሚል ሲማረርና ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ ለመሰረተው ክስ፣ ተገቢ ውሳኔ የሚያገኝባትን ዕለት ለአመታት በጉጉት ሲጠባበቅ የነበረው አይፎን ከሰሞኑ በለስ ቀንቶታል፡፡
በዋሽንግተን የፌዴራል ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ባለፈው ሳምንት ሃሙስ የተሰየመው ችሎት፣ “ከአሁን በኋላ ከአይፎን እያየህ መኮረጅህን እንድታቆም፤ ከዚህ በፊት የኮረጅካቸውን ሶፍትዌሮችም ዛሬ ነገ ሳትል መጠቀም እንድታቆም” ሲል ለሳምሰንግ ጥብቅ ትዕዛዝ አስተላልፏል - ሲኤንኤን እንደዘገበው፡፡
ሳምሰንግ በበኩሉ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ በሰጠው መግለጫ፣ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በምርቶቹ ተወዳጅነት ላይ ይህ ነው የሚባል አሉታዊ ተጽዕኖ እንደማይፈጥር ገልጾ፣ ጋላክሲ በሚል መጠሪያ የሚያመርታቸው ስማርት ፎኖቹ በቀጣይም በአለም ዙሪያ በስፋት መቸብቸባቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቋል፡፡
አይፎን ፈጠራዎቼን እየኮረጀ አስቸግሮኛል በሚል በሳምሰንግ ላይ ክስ የመሰረተው ከ3 አመታት በፊት እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ ወቅቱ ሳምሰንግ ኩባንያ ጋላክሲ ኤስ 2 የተሰኘውን ስማርት ፎን ለገበያ ያበቃበት እንደነበርና ከዚያ በኋላም፣ በዚህ አመት ለገበያ ያበቃውን ጋላክሲ ኤስ 6 ጨምሮ የተለያዩ አይነት የተሻሻሉ የጋላክሲ ምርቶቹን ማውጣቱን ጠቁሟል፡፡
አይፎን ክሱን የመሰረተው በጋላክሲ ኤስ 2 ላይ ሲሆን፣ ክሱ ሳምሰንግ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ያመረታቸውን ስማርት ፎኖች የማይመለከት በመሆኑ የፍርድ ቤቱ  ውሳኔ ለአይፎን ያን ያህልም ተጠቃሚ እንደማያደርገው ተዘግቧል፡፡ ሁለቱ ኩባንያዎች በፈጠራ ባለቤትነት ጉዳይ መካሰስ ከጀመሩ ብዙ ጊዜ እንደሆናቸው የታወቀ ሲሆን በቅርቡም “ሳምሰንግ ከአይፎን ኮርጀሃል” በሚል 980 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፍል ተወስኖበት እንደነበር ተጠቁሟል፡፡

 መንግስት በበኩሉ፣ ከ700 ሚ ዶላር በላይ በመዝረፍ ከሷቸዋል
   ሩስያዊው ቢሊየነር ሰርጊ ፑጋቼቭ፣ ፕሬዚዳንት ብላድሚር ፑቲን እና ታማኞቻቸው በህገወጥ መንገድ በሸረቡብኝ ሴራ ግዙፉን የባንክ ኩባንያዬን ለኪሳራና ለውድቀት ዳርገውታል፣ የአገሪቱ መንግስት 10 ቢሊዮን ዶላር ካሳ ሊሰጠኝ ይገባል ሲሉ ክስ መመስረታቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
ከታዋቂ የአገሪቱ ባንኮች አንዱ የነበረው ሜዝፕሮም ባንክ ድንገት ተንኮታኩቶ የወደቀባቸውና በባንኩ ዘርፍ ከሚታወቁ የአገሪቱ ባለጸጎች አንዱ እንደነበሩ የሚነገርላቸው ሰርጊ ፑጋቼቭ፤ ፕሬዚዳንት ፑቲንና ታማኞቻቸው ዋና ዋናዎቹን ንብረቶቼን ነጥቀው ኩባንያዬን ለውድቀት ዳርገውታል ሲሉ፣ ባለፈው ሰኞ ዘ ሄግ በሚገኘው ቋሚ የግልግል ፍርድ ቤት ላይ ክስ መመስረታቸውን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የሩስያ መንግስት በበኩሉ፤ እ.ኤ.አ በ2008 ተከስቶ የነበረውን የገንዘብ ቀውስ ተከትሎ ሜዝፕሮም የተባለውን የግለሰቡን ባንክ ለመደጎም በማሰብ የመደበውን ከ700 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዘርፈው ለግል ጥቅማቸው አውለዋል በሚል፣ በስደት እንግሊዝ ውስጥ በሚገኙት ሰርጊ ፑጋቼቭ ላይ ክስ መመስረቱንና ግለሰቡ ተላልፈው እንዲሰጡት የእንግሊዝን መንግስት እንደጠየቀ ያስታወሰው ዘገባው፤ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን እያጣራ ባለበት ሁኔታ ላይ በመሃል ቢሊየነሩ ከእንግሊዝ መውጣታቸውን ጠቁሟል፡፡
የሩስያን መንግስት ክስ ተከትሎ የእንግሊዝ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተለያዩ የአለም አገራት ውስጥ የሚገኙና 1.3 ቢሊዮን ፓውንድ የሚያወጡ የሰርጊ ፑጋቼቭ ሃብቶች እንዳይንቀሳቀሱ ያዘዘ ሲሆን ቢሊየነሩ ግን ከሩስያ የተሰነዘረባቸውን ክስ፣ መሰረተ ቢስና ፖለቲካዊ መነሻ ያለው ውንጀላ ነው ሲሉ ማጣጣላቸው ተነግሯል፡፡
ፕሬዚዳንት ብላድሚር ፑቲን ወደ ስልጣን እንዲወጡ በማገዝ ረገድ ቁልፍ ሚና እንደተጫወቱ የሚነገርላቸው ቢሊየነሩ ፑጋቼቭ፣ ከእንግሊዝ ከወጡ በኋላ ወደ ፈረንሳይ ሳይሄዱ እንዳልቀሩ ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

 ወታደራዊው ሃይል ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ባካሄደው መፈንቅለ መንግስት ከስልጣን የወረዱትና በግዞት የቆዩት የቡርኪና ፋሶው የሽግግር መንግስት ፕሬዚዳንት ሚሼል ካፋንዶ ረቡዕ ዕለት ወደ ስልጣናቸው መመለሳቸውን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ፕሬዚዳንት ሚሼል ካፋንዶ ወደስልጣናቸው መመለሳቸውን ይፋ ያደረጉት፣ የመፈንቅለ መንግስቱ መሪና ለአንድ ሳምንት በስልጣን ላይ የቆዩት የአገሪቱ መሪ  ጄኔራል ጊልበርት ዴንድሬ የስልጣን ሽግግሩን ለመታዘብ ወደ አገሪቱ በመግባት ላይ የነበሩ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎችን ለመቀበል ወደ አውሮፕላን ማረፊያ ባመሩበት ወቅት ነው ብሏል ዘገባው፡፡
የምዕራብ አፍሪካ አገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ኢኮአስ በሽግግር መንግስቱና በወታደራዊው ሃይል መካከል የተፈጠረውን ግጭት በሰላማዊ ድርድር ለመፍታት ያስችላል በሚል ባቀረበው የድርድር ሃሳብ መሰረት፣ አገሪቱ ወደ ብጥብጥ እንዳትገባ የመፈንቅለ መንግስቱ መሪዎች ከቤተ መንግስቱ እንዲርቁ መደረጋቸውን ተከትሎ ፕሬዚዳንት ኮፋንዶ ወደ ስልጣናቸው እንደተመለሱ ማወጃቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡በወታደራዊው ሃይልና መፈንቅለ መንግስቱን በተቃወሙ የአገሪቱ ዜጎች መካከል በተነሳው ግጭት ከ10 በላይ ሰዎች መሞታቸውንና ከ100 በላይ የሚሆኑ የአገሪቱ ዜጎችም መቁሰላቸው ተነግሯል፡፡
ባለፈው አመት ጥቅምት ወር ላይ በተቀሰቀሰው ህዝባዊ አመጽ ከስልጣናቸው የወረዱትን የቀድሞውን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ብሌስ ኮምፓዎሬን ተክቶ መንበረ መንግስቱን የተረከበው የቡርኪና ፋሶ የሽግግር መንግስት፣ በመጪው ጥቅምት ወር በሚደረግ ምርጫ ስልጣኑን ለማስረከብ እቅድ እንደነበረውም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

    13.50 ዶላር የነበረው መድሃኒት፣ 750 ዶላር ገብቷል
    
   ኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ዜጎች በሚወስዱት መድሃኒት ላይ የ5,000% የዋጋ ጭማሪ ያደረገው የአሜሪካ መድሃኒት አምራች ኩባንያ፣ ከታማሚዎች፣ ከመብት ተሟጋች ቡድኖች፣ ከህክምና ማህበራት፣ ከፖለቲከኞችና ከማህበራዊ ድረገጽ ተጠቃሚዎች ከፍተኛ ተቃውሞ እንደገጠመውና ዋጋውን ለመቀነስ ማሰቡን እንደገለፀው ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ቱሪንግ ፋርማሲዩቲካልስ የተባለው የመድሃኒት አምራች ኩባንያ፤ ዳራፕሪም በመባል የሚታወቀውን የመድሃኒት ምርቱን የመሸጫ ዋጋ ከ13.50 ዶላር ወደ 750 ዶላር ማሳደጉን ማስታወቁን ተከትሎ ከታማሚዎችና ከተለያዩ አካላት ከፍተኛ ተቃውሞ እንደገጠመው የጠቆመው ዘገባው፣ የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚም የተወሰነ የዋጋ ቅናሽ ለማድረግ ማሰባቸውን እንደተናገሩ ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የዋጋ ጭማሪው ያስነሳውን ተቃውሞ ለማጣጣል የሞከሩት የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ማርቲን ሸክሬሊ፣ ተቃውሞውን የሚሰነዝሩት ስለ መድሃኒት አምራች ኢንዱስትሪው አካሄድ በቂ ግንዛቤ የሌላቸው ሰዎች ናቸው፤ የዋጋ ጭማሪውን አድርገን የምናገኘውን ተጨማሪ ገንዘብ ሌሎች መድሃኒቶችን ለመፍጠር ለምናደርገው ምርምር ለማዋል ነበር ያሰብነው ብለዋል፡፡
ዋና ስራ አስፈጻሚው ማርቲን ሸክሬሊ በትዊተር ገጻቸው ላይ የተሰነዘረባቸውን ከፍተኛ ተቃውሞ ተከትሎ፣ ቱሪንግ ፋርማሲዩቲካልስ የተባለው ኩባንያቸው በቅርቡ ከህብረተሰቡ የመግዛት አቅም ጋር የሚመጣጠን የዋጋ ቅናሽ እንደሚደርግ ቢናገሩም፣ ምን ያህል የዋጋ ቅናሽ ለማድረግ እንደታሰበ በግልጽ አላሳወቁም፡፡
ኩባንያው ዳራፕሪም የተባለውንና የቶክሶፕላዝሞሲስ የፓራሳይት ኢንፌክሽንን በማከም ረገድ ፍቱን የሆነውን መድሃኒት አምርቶ የመሸጥ ፍቃድ ያገኘው በቅርቡ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፣ ኤችአይቪ ኤድስን በመሳሰሉ በሽታዎች የተጠቁና በሽታን የመከላከል ተፈጥሯዊ አቅማቸው ደካማ የሆኑ ታማሚዎች መድሃኒቱን በስፋት እንደሚወስዱ ገልጧል፡፡
በተያያዘ ዜናም በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የሚሰነዘሩ ሃሳቦችን መነሻ በማድረግ ቢቢሲ ባወጣው ዘገባ፣ በአሁኑ ወቅት በአገረ አሜሪካ አይንህን ለአፈር በመባልና በመጠላት ረገድ፣ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ያደረገውን ኩባንያ የሚመሩት የ32 አመቱ ማርቲን ሸክሬሊ ቱሪንግ፣ ቀዳሚውን ስፍራ ሊይዙ እንደሚችሉ ጠቁሟል፡፡

    በስኳር በሽታ ሳቢያ የተጐዱ የልብ የደም ቱቦዎችና የሰውነታችን ውስጣዊ አካላቶች የአበባ ጐመን በመመገብ በፍጥነት እንዲጠገኑ ማድረግ እንደሚቻል በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች ገለፁ፡፡
 በአሜሪካ ዋርዊክ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ባሉ ምሁራን የተደረገና በቅርቡ ይፋ የሆነ አንድ ጥናት እንዳመለከተው፤ በአበባ ጐመን ውስጥ የሚገኘውና ሰልፎራፔን የተሰኘው ንጥረ ነገር የደም ቱቦዎችን የሚጠብቁ ኢንዛይሞች በብዛት እንዲመረቱ ያደርጋል፡፡ ይህም በሴሎች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሞሎኪውሎች ቁጥር እንዲቀነስ እንደሚያደርግ ባለሙያዎቹ ገልፀዋል፡፡ ከስኳር በሽታ ጋር ግንኙነት ያለውና Hyperglycemia በመባል የሚጠራው ከፍተኛ የጉሉኮስ መጠን በደም ስሮች ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት በአበባ ጐመን ውስጥ የሚገኘው ሰልፎራፔን የተባለው ኢንዛይም እንደሚጠግነው መረጋገጡንም ምሁራኑ ተናግረዋል፡፡ የስኳር ህሙማን ከጤናማዎቹ በአምስት እጥፍ ለልብ በሽታዎች የተጋለጡ ናቸው፡፡ የስኳር ህመም በልብ ደም ስሮች ላይ በሚያስከትለው ጉዳት ሳቢያ ስትሮክና የልብ ድካም ይከሰታል፡፡

ለጤናዎ 10 ጠቃሚ ምግቦች
ፈረሰኛ ለስኳር ህሙማን ይመከራል
የምንመገባቸውን ምግቦች በማስተካከል ጤናችን የተጠበቀ ማድረግ እንደሚቻል የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡ ቀጥሎ የተዘረዘሩት 10 የምግብ ዓይነቶች ሰውነታችን የበሽታ መከላከል አቅሙን እንዲጨምር በማድረግ፣ ጤናማና ደስተኛ ህይወት ለመምራት እንደሚያስችለን Changeone.com ከተሰኘው ድረ ገፅ ያገኘነው መረጀ ያመለክታል፡፡ እነዚህ ለጤናዎ ጠቃሚ የሆኑ አስር የምግብ አይነቶች የሚከተሉት ናቸው፡-
አሣ - ከእንስሳት የሚገኘውን ሥጋ የሚተካውና ጥሩ የፕሮቲን ምንጭ የሆነው አሣ Omega 3 ለተባለው ፋቲአሲድ ዋንኛ ምንጭ በመሆንም ይታወቃል፡፡ እነዚህ ፋቲአሲዶች የደም ቅዳዎቻችን ንፁህ እንዲሆኑ ያደርጋሉ፡፡ አሣ በተለይ ለስኳር ህሙማን ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው የምግብ አይነት ነው፡፡ የስኳር በሽተኞች አብዛኛውን ጊዜ (HDL) የተሰኘው ጠቃሚ ኮሌስትሮል እጥረት ይታይባቸዋል፡፡ Omega 3 ይህንን የኮሌስትሮል እጥረት በማስተካከል ይታወቃል፡፡
በሣምንት ቢያንስ ሁለት ቀን አሣን መመገብ ለጤና እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ሳልመን፣ ማካፌል እና ቱና የተባሉት የአሣ ዓይነቶች የፋቲ አሲዱ ዋንኛ መገኛዎች ናቸው፡፡
የዶሮ ስጋ
ፈረሰኛ የምንለው የዶሮ ብልት፤ ለስኳር ህሙማን እጅግ በጣም ተመራጭና ጠቃሚ የምግብ አይነት ነው፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች ፈረሰኛን “ተአምረኛው ምግብ” ሲሉ ይጠሩታል፡፡ ፈረሰኛ የሥጋ ምግቦች ከያዙት የስብና የኮሌስትሮል መጠን በእጅጉ ያነሰ ነው የያዘው፡፡ በ85 ግራም ፈረሰኛ ውስጥ 142 ካሎሪና 3 ግራም ስብ ብቻ ይገኛል፡፡
እርጐ
እርጐ በፕሮቲንና ክብደትን ለመቀነስ በሚረዳው ካልሲየም በተባለው ንጥረ ነገር የዳበረ ነው፡፡ በርካታ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ በካልሲየም የዳበሩ ምግቦችን የሚመገቡ ሰዎች በቀላሉ ክብደታቸውን ለመቀነስ ይችላሉ፡፡ ደስተኛና ጤናማ ህይወት እንዲኖርዎ የእርጐ ወዳጅ ይሁኑ፡፡ ቁርስዎን ቅባት የሌለው እርጐ በመውሰድ ይጀምሩ፡፡
አትክልቶች
አትክልቶች በተፈጥሮአቸው ዝቅተኛ ካሎሪ ነው ያላቸው፡፡ በፋይበር (አስር) የበለፀጉም ናቸው፡፡ የምግብ ገበታዎን ለጤና ከፍተኛ ጠቀሜታ ባላቸው ንጥረ ነገሮች በዳበሩት አትክልቶች ሞሉት ማለት የደም ስኳር መጠንዎን ተቆጣጠሩ ማለት ነው፡፡
ፍራፍሬ
ፍራፍሬዎች የከፍተኛ ፋይበር ምንጭ ሲሆኑ ዝቅተኛ ስብና ዝቅተኛ ካሎሪን በመያዝም ይታወቃሉ፡፡ ፍራፍሬዎች ልባችንን፣ ዓይናችንንና ጥርሶቻችንን ከበሽታ በሚከላከሉ አንቲኦክሲደንቶች የበለፀጉ ናቸው፡፡ ፍራፍሬዎችን ከጭማቂው ይልቅ እንዳለ መመገብን ይምረጡ፡፡ በርካታ ለጤና ጠቃሚ የሆኑ ነገሮች በፍሬው ላይ ስለሚገኙና እነዚህ ጠቃሚ ነገሮች በሚጨመቅበት ወቅት ስለሚጠፉ ፍሬውን እንዳለ መመገቡ ጠቀሜታው ከፍ ያለ ይሆናል፡፡ ፍራፍሬዎች በተፈጥሮ ስኳርና ካሎሪ የበለፀጉ በመሆኑ በብዛት ከመመገብ መታቀብ ይኖርብናል፡፡
ለውዝ
ለውዝ የቫይታሚን E ዋንኛው ምንጭ ነው፡፡ ይህ ቫይታሚን በውስጡ የያዘው አንቲኦክሲደንት ሴሎችን በመጠበቅ የነርቭና የአይን ጉዳት እንዳይከሰት ያደርጋል፡፡ ለውዝ በበርካታ ጠቃሚ የስብ አይነቶች የተሞላ የምግብ አይነት ነው፡፡ እነዚህ ስቦች የልብ በሽታን በመከላከልና ኢንሱሊን ያለመቀበል ሂደትን በመቀነስም ይታወቃሉ፡፡ የደም ውስጥ የስኳር መጠንንም ለመቆጣጠር ያስችላሉ፡፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ ለውዝን አዘውትሮ መመገብ ክብደትን ለመቀነስ ይረዳል፡፡ የስኳር ህመምተኛ ከሆኑ ግን ለውዝን አዘውትረው አይመገቡ፡፡
ቀረፋ
በምግብዎ ውስጥ ቀረፋን ጣል የሚያደርጉ ከሆነ፣ አስገራሚ በሆነ ሁኔታ የደምዎ የስኳር መጠን ቀንሶ ያገኙታል፡፡ በቀረፋ ውስጥ የሚገኙ ንጥረ ነገሮች ሰውነታችን ኢንሱሊንን በአግባቡ እንዲጠቀም ያደርጉታል፡፡ በስኳር ህሙማን ላይ የተደረገ ጥናት፤ ግማሽ ማንኪያ ቀረፋ በየዕለቱ የሚወስዱ ሰዎች የደም የስኳር መጠናቸው በአስገራሚ ሁኔታ ቀንሶ ተገኝቷል፡፡ የቀረፋን ዱቄት በዳቦ ወይንም በሌሎች ምግቦችዎ ውስጥ በመጨመር ይመገቡ፡፡ እንጨቱንም በሻይ መልክ እያፈሉ በመጠጣት ጤናዎን ይጠብቁ፡፡
ጥራጥሬ
የጥራጥሬ ምግቦች በፋይበር የበለፀጉ ናቸው፡፡ አዘውትረው ቢመገቧቸው ጤናዎን ለመጠበቅ በእጅጉ ይጠቅምዎታል፡፡
የወይራ ዘይት
የወይራ ዘይት በልብ በሽታ የመያዝ ዕድልን ይቀንሳል፡፡ የደም የስኳር መጠንን ያረጋጋል፡፡ ምግብዎን በወይራ ዘይት አብስሎ ሲመገቡ ራስዎን ከተለያዩ በሽታዎች ይታደጋሉ፡፡ ይሁን እንጂ የስኳር ታማሚ ከሆኑ፣ የወይራ ዘይትን አዘውትረው ከመመገብ ይቆጠቡ፡፡  

በአገራችን ከአምስት ህሙማን አንዱ መድሃኒቶችን በስህተት ይወስዳል
የሃኪሙን የእጅ ፅሁፍ ማንበብ የሚያዳግታቸው ፋርማሲስቶች በዝተዋል

በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በተደረገለት ሙሉ ምርመራ የጉበት ህመምተኛ መሆኑ ሲነገረው ድንጋጤው ልክ አልነበረውም፡፡ ህመሙ ዕለት ከዕለት እየተባባሰበት በመሄዱ ምክንያት ወደ ሆስፒታል ሄዶ ምርመራ ለማድረግ ሲወስን፣ ሃኪሙ ህመሙን አውቆለት ፈዋሽ መድሃኒት እንደሚያዝለት፣ ከበሽታውም እንደሚያገግም ጽኑ እምነት ነበረው፡፡
ከሃኪሙ የተፃፈለትን የመድሃኒት ማዘዣ ይዞ መድሃኒቱን ፍለጋ ወጣ፡፡ በከተማው ውስጥ ያሉ በርካታ መድሃኒት ቤቶችን ቢያስስም መድሃኒቱን ማግኘት አልቻለም፡፡ ቆይቶ ግን መድሃኒቱ በአንድ ፋርማሲ ውስጥ እንደሚገኝ ሰማ፡፡ ለመድሃኒቱ የተጠየቀውን ዋጋ ከፍሎ ገዛ፡፡ ችግሩ ግን ስለመድሃኒቱ አወሳሰድ ፋርማሲስቱ የነገረው ነገር አልነበረም፡፡ የገዛውን መድሃኒት ይዞ ወዳዘዘለት ሃኪም ሄደ፡፡ ሃኪሙ ዘንድ ቀርቦ መድሃኒቱን በብዙ ፍለጋ ማግኘቱን በመግለጽ፣ ስለአወሳሰዱ እንዲነግረው ጠየቀው፡፡ ሃኪሙ በጣም ተገርሞ፤
“ለመሆኑ መድሃኒቱ የተገዛው ከፋርማሲ ውስጥ ነው?” ጠየቀው
“አዎ” አለ ታካሚው፡፡
“ታዲያ እንዴት ፋርሚሲስቱ ስለአወሳሰዱ ሳይነግርህ ቀረ?” በማለት መድሃኒቱን ከነማዘዣው ከህመምተኛው ላይ ተቀብሎ አየው፡፡ ታካሚው በሃኪሙ ፊት ላይ ያየው ከፍተኛ ድንጋጤ እሱኑ ይበልጥ አስደነገጠው፡፡
“ችግር አለ?” ሲል ጠየቀው ሃኪሙን
“እርግጠኛ ነህ እኔ ላዘዝኩልህ የተሰጠህ መድሃኒት ይሄ ነው?” ሲል ጠየቀው ታማሚውን፡፡
“ጌታዬ 486 ብር የከፈልኩበት መድሃኒት እኮ ነው እንዴት ብዬ ከሌላ መድሃኒት ጋር እቀላቅለዋለሁ”
ለዚህ መድሃኒት መግዣ ያወጣውን 486 ብር ለማግኘት የተጋፈጠውን ውጣ ውረድ የሚያውቀው እሱ ብቻ ነው፡፡ ሃኪሙ በጣም አዘነ፡፡
ታካሚው ከፋርማሲ ገዝቶ ያመጣው መድሃኒት፤ ለማህፀን ህክምና የሚያገለግልና ለሴቶች ብቻ የሚታዘዝ ነበር፡፡ ሁኔታው እጅግ ቢያስደነግጠውም ለመድሃኒቱ ያወጣው ገንዘብ ኪሣራ ላይ ሊወድቅ መሆኑ ይበልጥ አበሳጨው፡፡ ወደ ፋርማሲው ሄዶ ስለጉዳዩ በመንገር፣ ገንዘቡን እንዲመልሱለት ለማድረግ መድሃኒቱን ተቀብሎ ወደዚያው አመራ፡፡ ፋርማሲው ውስጥ ላገኘው ሰውም ሁኔታውን አስረዳ፡፡ በወቅቱ የተገኘው ባለሙያ፤ ከሰውየው ላይ መድሃኒቱን ተቀብሎ አየው፡፡ ምናልባት የፋርማሲ ባለሙያው በስህተት ሰጥቶት ሊሆን እንደሚችል ነግሮ፣ በማዘዣው ላይ የተፃፈውን መድሃኒት ሊሰጠው እንደሚችል አግባባው፡፡ ይሁን እንጂ ይህኛውም ሰው በመድሃኒት ማዘዣው ላይ የተፃፈውን ጽሑፍ በአግባቡ በማንበብ ተገቢውን መድሃኒት ሊሰጠው አልቻለም፡፡ ይልቁንም “መድሃኒቱ እኛ ጋ የለም ሲል” ማዘዣውንና ታማሚው ቀደም ሲል የከፈለውን 486 ብር መልሶ በመስጠት አሰናበተው፡፡
ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝን ይህንን መረጃ ያገኘሁት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለህክምና መጥቶ ካገኘሁት አንድ ታካሚ ነው፡፡ ታካሚው ከሃኪሙ የተፃፈለትን መድሃኒት በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ከሚገኘው የመድሃኒት መሸጫ ፋርማሲ ለማግኘት ባለመቻሉ ነበር መድሃኒቱን ፍለጋ ከተማውን ሲያስስ የከረመው፤ ይሁን እንጂ በአብዛኛው መድሃኒት ቤቶች ውስጥ መድሃኒቱን ለማግኘት አልቻለም፡፡ ከዚህ የከፋው ደግሞ ከበሽታው ጋር ፈጽሞ የማይገናኝና ምናልባትም ለከፋ ችግር ሊያጋልጠው የሚችል መድሃኒት ባለሙያ ነኝ ብሎ ከተቀመጠ የመድሃኒት ቤት ሰራተኛ መሰጠቱ ነው፡
ወደ ሆስፒታሉ ተመልሶ የመጣው ሃኪሙ መድሃኒቱን በሌላ መድሃኒት ቀይሮ እንዲፅፍለት ለመጠየቅ መሆኑን አጫውቶኛል፡፡ ለፍለጋው በተዘዋወረባቸው በርካታ መድሃኒት ቤቶች ውስጥ ያገኛቸው የፋርማሲ ባለሙያዎች፤ በማዘዣው ላይ የተፃፈው የሃኪሙ የእጅ ጽሑፍ ፈጽሞ የማይነበብ መሆኑንም ነግረውታል፡፡ ስለዚህም ሃኪሙ ሊነበብ በሚችል መልኩ ማዘዣውን እንዲፅፍለት እንደሚጠይቀውም ገልፆልኛል፡፡
አለም አቀፉ የጤና ድርጅት (WHO) ለፋርማሲ ሙያ በሰጠው ትርጓሜ፤ የፋርማሲ ባለሙያ ማለት፣ ከሃኪም በሚሰጠው ትዕዛዝና መመሪያ መሠረት፣ መድሃኒቶችን ለህሙማን ማደል፣ ስለመድሃኒቱ አወሳሰድ፣ መድሃኒቱ ስለሚኖረው የጐንዮሽ ጉዳትና ከመድሃኒቱ ጋር ሊወሰዱና ላይወሰዱ ስለሚችሉ ምግብና መጠጦች በግልጽ ለህመምተኛው የሚያሳውቅ ሰው ነው፡፡ የፋርማሲ ባለሙያው መድሃኒቶችን ለህሙማን ከማደል በዘለለ ከህሙማኑ ጋር ጥብቅ መግባባትን ማድረግ የሚችል መሆን ይኖርበታል፡፡ ባለሙያው ሁልጊዜም ከህመምተኛው ጀርባ ሆኖ ስለህመምተኛው የሚጨነቅና የሚያስብ ሰው ነው፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፋርማሲ ት/ቤት መምህር ዶክተር ተስፋዬ ታረቀኝ እንደሚናገሩት፤ “የፋርማሲ ሙያ እንደ ህክምና ሙያ ሁሉ ትልቅ ከበሬታ ሊሰጠው የሚገባና በአግባቡ የሰለጠነ የሰው ሃይልን የሚጠይቅ ነው፡፡ የፋርማሲ ባለሙያዎች ከህክምና ባለሙያዎች ጋር ጥብቅ ትስስር ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የፋርማሲ ባለሙያ ማለት ከሃኪሙ በሚሰጠው ማዘዣ መሠረት ታማሚው መድሃኒቱን በአግባቡ መውሰድ እንዲችል ተገቢውን መመሪያ የሚያስተላልፍ ሙያተኛ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አሁን የሚታየው ነገር ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ታካሚው መድሃኒት ፍለጋ በሚሄድባቸው ፋርማሲዎች ውስጥ ያሉ ሰዎች ሙያውን በሚገባ ያውቁታል ለማለት ፈፅሞ አያስደፍርም፡፡ አንዳንድ ፋርማሲስቶች፤ የመድሃኒት ማዘዣዎች አልነበብ ሲላቸው፣ በደንበኞች ፊት ሃኪሞችን ከፍ ዝቅ አድርገው ሲሳደቡና ሲያዋርዱ ይታያል፡፡ ይህ ደግሞ ለሙያው የሚሰጠውን ግምት በእጅጉ የሚያወርድና በሃኪሙና በህመምተኛው መካከል መተማመን እንዳይኖር የሚያደርግ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የመድሃኒት ማዘዣዎችን በሚገባ አንብቦና ተረድቶ መድሃኒቶችን ለህሙማን የሚያድል የፋርማሲ ባለሙያ ማግኘቱ እጅግ አስቸጋሪ እየሆነ የመጣ ጉዳይ ነው”
በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በቅርቡ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሃኪም መድሃኒት ከታዘዘላቸው ታካሚዎች ከአምስቱ አንዱ መድሃኒቶችን በስህተት ይወስዳል፡፡ ሃኪሞችን የፋርማሲ ባለሙያዎችን፣ ነርሶችንና ህሙማንን ያካተተው ጥናቱ፤ በመድሃኒት አስተዛዘዝ ዙሪያ ከባድ ችግር እየተከሰተ መሆኑን ይጠቁማል፡፡
አንዳንድ የጤና ባለሙያዎች የሚጽፉት የመድሃኒት ማዘዣ የማይነበብና የተሟላ መረጃ የሌለው ሲሆን የሃኪሙን የእጅ ጽሑፍ በሚገባ አንብቦና ተረድቶ ተገቢውን መድሃኒት ለህመመተኛው የሚሰጥ የፋርማሲ ባለሙያ ማግኘትም አስቸጋሪ ሆኗል፡፡
ህሙማኑም ስለታዘዘላቸው መድሃኒት አወሳሰድ ሃኪማቸውን አይጠይቁም፡፡ የፋርማሲ ባለሙያዎቹም፤ ለህሙማኑ መድሃኒቱን ሲሰጡ ስለአወሳሰዱ፣ ስለመድሃኒቱ ባህሪያትና ስለጐንዮሽ ጉዳቱ አይናገሩም፡፡
ይህ የሚያሳየው ደግሞ ህመምተኛው ስለሚወስደው መድሃኒት ምንነትና አወሳሰድ ሳያውቅ በስህተት መድሃኒቶችን ለመውሰድ መገደዱን ነው፡፡
በጥናቱ እንደተመለከተው፤ ብዙውን ጊዜ ህሙማን መድሃኒት ፍለጋ ከፋርማሲ ፋርማሲ የሚንከራተቱት መድሃኒቱ በፋርማሲው ሳይገኝ ቀርቶ ሳይሆን የፋርማሲ ባለሙያው ማዘዣውን አንብቦ መረዳት ባለመቻሉ ምክንያት መሆኑን አመላክቷል፡፡ ይህ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባና ሁሉም ሙያተኞች የሙያውን ሥነምግባር አክብረው፣ ተገቢውን ህክምናና መድሃኒት ለህመምተኛው መስጠት እንዳለባቸው ይኸው ጥናት ይገልፃል፡፡
በሰለጠነው ዓለም የመድሃኒት ማዘዣዎች በዲጂታል ማሽኖች እየተተኩ ነው፡፡
ልክ እንደ ባንክ ኤቲኤም ማሽን፣ በደንበኞቹ በቀረበለት የመድሃኒት ማዘዣ መሠረት ትክክለኛውን መድሃኒት አውጥቶ ከነአወሳሰድ መመሪያው ለህሙማኑ መስጠት የሚችል መሣሪያ አገልግሎት ላይ ውሏል፡፡
መድሃኒቶች ከበሽታ በመፈወስ ነፍስን የመታደጋቸውን ያህል በአግባቡ ካልተያዙና አገልግሎት ላይ ካልዋሉ አጥፊ የመሆን ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ ስለዚህ ለህይወት ደህንነት የተሰራልን መድሃኒት አጥፊያችን እንዳይሆን፣ እራሳችንን ጨምሮ የሚመለከተው አካል ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡       

“ልጃገረዶች አግብተው እስኪያልቁ ድረስ እንኖራለን”

   በጎፋ ብሄረሰብ መስቀል የበአላት ሁሉ አውራ ነው፡፡ ለ7 ተከታታይ ቀናት የሚያከብሩት ልዩ በዓላቸው ነው፡፡ አሁን የሥራ ጊዜን እንዳይሻማ በሚል ተቀንሶ ነው እንጂ ድሮ ለ15 ቀናት ነበር የመስቀል በዓል የሚከበረው፡፡
የዘንድሮ አከባበር ግን የተለየ ነው፡፡ ጐፋዎች የመስቀል በአልን ለመጀመሪያ ጊዜ በአደባባይ ተሰባስበው በተለያዩ ባህላዊ ስርአቶች በመናገሻቸው በሳውላ ከተማ እያከበሩ ይገኛሉ፡፡ “ማስቃላ ዮ!” (እንኳን ለመስቀል በአል አደረሰን) ሰሞነኛ የሠላምታና የመመራረቂያ ቋንቋቸው ነው፡
ብሄረሰቡ በአሉን መቼ ማክበር እንደጀመረ የሚጠቁም አረጋጋጭ ማስረጃዎች ባይኖሩም በአካባቢው ከ100 ዓመታት ቀደም ብሎ (ክርስትና ከመስፋፋቱ በፊት) ከአሁኑ አከባበር ጋር ተመሳሳይነት ባለው መልኩ በመስከረም ወር ይከናወን እንደነበር የሀገር ሽማግሌዎችና የመስቀል በአል አከባበርን ያጠኑ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ ክርስትና ከመጣ በኋላ ይበልጥ የሀይማኖት ይዘቱንም የባህል ትውፊቱንም አስማምቶ ማክበር እንደተጀመረም ይገለፃል፡፡
ወርሃ መስከረም ወይም በብሄረሰቡ አጠራር ጉስታማ፤ የጭፈራና የደስታ ወር ነው - ለጎፋዎች፡፡ የእድሜ ባለፀጋዎች ልጆቻቸውን የሚመርቁበት፣ ወጣቶች እጮኛ የሚመርጡበት፣ በብሄረሰቡ ተወዳጅ የሆኑት “ግሶሌ”፣ “ሄራሶ”፣ “ጋዜ”፣ “ባራንቼ”፣ “ሆሴ” … የመሳሰሉት ባህላዊ ዜማዎች ጐልተውና ደምቀው የሚዜሙበት የፌሽታ ወቅት ነው - መስከረም፡፡
በአሉን ለመታደም ከአዲስ አበባ በ516 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ሳውላ ባቀናንበት ወቅትም እነዚህ የወርሃ መስከረም የደስታ ዜማዎች የበአሉ ማድመቂያ ሆነው ሰንብተዋል፡፡
ጎፋዎች የመስቀል በአልን ለመቀበል ቅድመ ዝግጅት የሚያደርጉት ከመስከረም 1 ጀምሮ ነው፡፡ ለተከታታይ 15 ቀናት እያንዳንዱ አባወራ የቤት እንስሳቱ እንዳይራቡበት ለ7 ተከታታይ ቀናት የሚበቃ መኖ ያዘጋጃል፡፡ ሴቶች ለበአሉ ባህላዊ ምግብና መጠጥ በማዘጋጀት ሥራ ይጠመዳሉ፡፡ የደመራው እለት እየተቃረበ ሲመጣም ወንዶች ለደመራ የሚሆነውን የተመረጠ “ግን ግና” የተባለ እንጨት መርጠው ያዘጋጃሉ፡፡ ህፃናት ልጆች ከብቶቻቸውን እያገዱ “መስቀል እንኳን መጣህልን፣ የኛ ደስታ፣ የኛ መዝናኛ መስቀል እንኳን መጣህልን፡
ሎያ ባይ ሎያ ባይ
ሎያ ባይ ማስቃላ ባይ
ማስቃላ ኡፋይስ ባይ
ሙሰ ሀሹ ባይ”… እያሉ በደስታ ያዜማሉ፡፡
አባወራዎች የደረሰ አዝመራ በደቦ ይሰበስባሉ፣ ያልደረሰውን ያርማሉ፣ ለእርድ የሚሆን በሬ ይገዛሉ፡፡ የመስከረም ወር ለጎፋዎች ሀብታም ከድሃ እኩል የሚሆኑበት ነው፡፡ “ጉስታ ጉስቴስ ጊታ ጊቴኤስ” ይባላል፤ ወሩ ላለው ይጨምራል፣ ለድሃውም ይሞላለታል ተብሎ ይታሰባል፡፡ በዚህም ሁሉም ለበአሉ የሚያደርጉት ዝግጅት እኩልነትን መርህ ያደረገ ይሆናል፡፡
የጎፋዎች ደመራ
መስከረም 16 የደመራ ቀን ነው፡፡ ለደመራ የሚተከለው ለቤት መስሪያ የሚውል ረጅም ቀጥ ያለ እንጨት ነው፡፡ በደመራው ጫፍ አደይ አበባ ይታሰራል፤ ይህም ተስፋን አመላካች ነው፡፡ የችቦ አስተሳሰርና የደመራው አቆራረጥ፣ የቤተሰቡን ቁጥርና እድሜ ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው፡፡ በረጅሙ ደመራ ዙሪያ የሚቀመጡት ጨፈቃዎች (ሶልዜ ይሉታል) በቤተሰቡ አባላት የእድሜ ደረጃ ቁመታቸው ተመጥኖ ይዘጋጃል፡፡ ረጅሙ ለአባወራው፣ ቀጥሎ ያሉት ከታላቅ እስከ ታናሽ ወንድ ልጆች እንዲይዙት ይደረጋል፡፡ የደመራ እንጨት በማስቀመጡ ስነስርአት ላይ ሴቶች ፈፅሞ አይሳተፉም፡፡ ሴቶች ከደመራው በኋላ የሚበላ ገንፎና የሚጠጣ ነገር ያሰናዳሉ፡፡
ወንዶቹ በእድሜ ደረጃቸው የያዙትን ጨፈቃ፣ በረጅሙ ምሰሶ ዙሪያ ለማስቀመጥ ሶስት ጊዜ “መስቀላ ዮ! ዮ! ዮ!…” እያሉ ይዞራሉ፡፡ ይህም ሁሉ ነገር የሚፀናው በ3 ነው ከሚል የብሄረሰቡ እምነት የመነጨ ነው ይላሉ አቶ በላይ፡፡ ሽማግሌ እንኳ ሲመረጥ ወይ ሶስት ወይ 5 አሊያም 7 ነው የሚሆነው፤ ምክንያቱም በውሳኔዎች የድምፅ ብልጫ እንዲፈጠር ነው፡፡
ለደመራው ረጅምና ዝንፍ ያላለ ቀጥ ያለ እንጨት የሚመረጥበት ምክንያትም ልጆች በአስተሳሰብና በአመለካከት ጤናማ ሆነው እንዲያድጉ፣ ዘመኑ የሰላምና የስኬት እንዲሆን በመመኘት ነው፡፡ በመስቀል በአል በምንም አይነት መንገድ ጠማማ እንጨት ከደመራው ጋ አይቀላቀልም፡፡
ለዓይን ያዝ ሲያደርግ የቤቱ አባወራ (አባወራው በህይወት ከሌለ) የቤቱ ታላቅ ልጅ፣ ሁሉንም ችቦዎች ይዞ ለገንፎ ማብሰያ ከሚነደው እሳት ስር በመለኮስ፣ የቤቱን ምሰሶ በመዞር፣ የከብቶች ጋጣና በሩን በተለኮሰው እሳት እየነካካ፣ “መስቀላ ዩ! ዮ! ዮ!” እየተባለ ወደ ደጅ ይወጣል፡፡ አባት መጀመሪያ ችቦውን ከደመራው ካቀጣጠለ በኋላ ልጆች እንደየቅደም ተከተላቸው ባህላዊ ጨዋታዎችን እየተጫወቱ ችቧቸውን ያለኳኩሳሉ፡፡
በሚነደው ደመራ ዙሪያም “መስቀላ ዮ! ዳናው ዳና አልባ ዙማዳን ዳና” (መስቀል እንኳን መጣህልን … በአካባቢው እንደሚገኘው አልባ ዙማ ተራራ ገና ረጅም ዘመን እንኖራለን) “ከንቲ ሻላዳን ዳና” (በአካባቢው እንደሚገኘው ክንቲ ሻላዳ አለት ገና እንኖራለን) እያሉ ያዜማሉ፡፡ ዜማው በዚህ አያበቃም፤ “ሀረይ ካጨ ከሳናዳን፣ ገላኦ ገል ውራናስ ዳና” (አህያ ቀንድ እስኪያበቅል…. ልጃገረዶች አግብተው እስኪያልቁ ድረስ እንኖራለን) እያሉ እርስ በእርስ ይሸካከማሉ፡፡ ተቃቅፈው በመጨፈርም የእርስ በርስ ፍቅራቸውን ይገልፃሉ፡፡
በደመራ ሀዘን (ለቅሶ) የለም
የደመራ እለት የሞተ ሰው ካለ አይለቀስም፡፡ ከደመራ በኋላ የሀዘን ማስረሻ ጭፈራ እየተጨፈረ፣ ለቀስተኛው በራፍ ላይ ይዞራል፡፡ ከእንግዲህ ሀዘን የለም ይባላል፡፡ ሟች በመስቀል እሳት ተበልቷል (ማስቃላ ታማን ሜቴትስ) ይባላል፡፡ ለቀስተኞች ለቅሶውን አቁመው፣ “መስቀላ ዮ! ዮ” እያሉ ወደ ተጀመረው የመስቀል በአል ይመለሳሉ፡፡ ለበአሉ የተዘጋጀው ሰንጋም በ17 በዋናው በአል እለት ይታረዳል፡፡ ለ7 ቀናት ያህልም መከበሩን ይቀጥላል፡፡ (ድሮ ለ15 ቀናት ነበር የሚከበረው)
ሳምንቱን ሙሉም ስጋና በቅቤ የተዘጋጀ ገንፎ ብቻ እየተበላ፣ ቦርዴና ሌሎች መጠጦች እየተጠጡ ይሰነበታል፡፡ ከብቶችም የተዘጋጀላቸውን መኖ ይመገባሉ፡፡ አባወራዎች በበአሉ መዳረሻም ሆነ እስከ በአሉ ፍጻሜ ድረስ ከቀዬው መራቅ የለባቸውም፡፡
በመጨረሻም ደማቅ የመስቀል አሸኛኘት ስነ ስርአት “ሆሴ” እና “ጋዜ” በተባሉ ጭፈራዎች ደምቆ ይከናወናል፤ “ሰሮ ያራደሳ ሰሮ ረባ” (መስቀል በደህና መጥተህልናል በደህና ሂድ) ተብሎም ይመረቃል፡፡ “ሆሴ ማስቃላ ላይታን ሳሮያ!” (መስቀል ደህና ሁን! በዓመቱ ደህና ተመለስ) እየተባለ በአሉ ይሸኛል፡፡ ከዚያን ቀን በኋላ ስለመስቀል አይወራም፡፡
በአሉን ምክንያት አድርገው ከሚከናወኑ ተግባራት አንዱ ጎረምሶች የወደፊት ውሃ አጣጫቸውን የሚመርጡበት ሥነ ስርአት ነው፡፡ ልክ በሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ለጥምቀት በአል እንደሚደረገው መተጫጨቱ የሚፈፀመው በሎሚ ነው፡፡ በጭፈራ ወቅት ወንዱ የበሰለ ባለቢጫ ቀለም ሎሚ ልቡ ለከጀላት ልጃገረድ ይሰጣል፡፡ ሴቶችም መልስ የሚሰጡት በሎሚ ነው፡፡ ሶስት አይነት ሎሚ ያዘጋጃሉ፡፡ እንስቷ፤ የጠየቃትን ወንድ የማትፈልገው ከሆነ ያልበሰለውን ትሰጠዋለች፣ ልቧ ከጅሎት ትንሽ ጊዜ እንዲጠብቃት ከፈለገች እንደ መብሰል ያለውን ሎሚ ትሰጣለች፤ ሙሉ በሙሉ የምትፈልገው ከሆነ ደግሞ የበሰለውን ሎሚ ከጡቶቿ መሃል አውጥታ ትሰጠዋለች፡፡ የበሰለ ሎሚ ያገኘ ወንድ፣ ከዚያን ቀን ጀምሮ የሰርግ ዝግጅት ማድረግ ይጀምራል፡፡ ጥንዶቹ እንደ ምርጫቸው በጥቅምት ወይም በጥር ይጋባሉ፡፡
ጥቂት ስለጎፋዎች
የጎፋ ብሄረሰብ በደቡብ ክልል ከአዲስ አበባ 516 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በጋሞ ጎፋ ዞን በደንባ ጎፋ ወረዳ ውስጥ ከሚገኙ 5 ነባር ብሄረሰቦች አንዱ መሆኑን በብሄረሰቡ ላይ የቀረቡ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ብሄረሰቡ ከሚኒልክ ዘመን ጀምሮ ከነባሩ የማዕከላዊ መንግስት አስተዳደር ጋር የነበረው ግንኙነት ጥብቅ እንደነበርም ይነገራል፡፡ በተለይ በአድዋ ጦርነት ጊዜ ጎፋዎች የፈፀሙት ጀግንነት በአፄ ምኒልክ ዘንድ ሞገስን አግኝቶ ነበር፡፡ የጣሊያንን ቅኝ ገዢ ኃይል አድዋ ላይ ለማስቆም በተደረገው የሞት ሽረት ተጋድሎ፣ ጎፋዎች ስንቅና የጦር መሳሪያ በማቀበል ለመላው ጥቁር ህዝብ ኩራት ለሆነው የአድዋ ድል ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡
ለዚህም ተጋድሏቸው መታሰቢያ ይሆን ዘንድ በአዲስ አበባ በስማቸው ቦታ ተሰይሞላቸዋል፡፡ የጎፋ ሰፈር፡፡
ወደ ሻሸመኔ አካባቢ የሚገኘው የጎፋ በር እየተባለ የሚጠራ ስፍራም በጦርነቱ ወቅት የብሄረሰቡ ተወላጆች ሰፍረውባቸው የነበረ ሲሆን ስያሜውን ያገኙት በዳግማዊ ምኒልክ በጎፈቃድ እንደሆነ ታሪክ ይጠቁማል፡፡
ጎፋዎች ቀደምት አባቶቻቸው ቅኝ ገዢውን የጣሊያን ጦር በመስዋዕትነት ለመመከታቸው ማስታወሻ ይሆን ዘንድም በሚለብሱት ባህላዊ ልብስ ላይ (2020 ይሉታል) ባለቀይ ቀለም ጥለትን ይጠቀማሉ፡፡
ባህላዊ አልባሳቶቻቸው ሲዘጋጅም ምንም ይሁን ምን ቀይ ቀለም ከላይ ተደርጎ ነጭና አረንጓዴ እንዲከተሉት ይደረጋል፡፡ ነጩ ሠላምን፣ አረንጓዴው የብሄረሰቡን አምራችነትና የአካባቢውን አረንጓዴ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ እንደሚወክል የብሔረሰቡ ተወላጆች ይናገራሉ፡
“መስቀላ ዮ! መልካም የመስቀል በዓል!”
“አህያ ቀንድ እስኪያበቅል ድረስ እንኖራለን!”
“ልጃገረዶች አግብተው እስኪያልቁ ድረስ እንኖራለን!”