Administrator

Administrator

   በስፔናዊው ሚጌል ሊያንሶ ተፅፎ የተዘጋጀውና ከ60 በላይ በሚሆኑ ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫሎች ላይ ተሳትፎ፣ 10 ሽልማቶችን ያሸነፈው “Crumbs” (ስብርባሪ) የተሰኘው ሳይንሳዊ ልብወለድ ፊልም፤ ትላንት ምሽት በአቤል ሲኒማ ተመረቀ፡፡ ከዓለም ጦርነቶች ፍፃሜ በኋላ ምን ሊፈጠር እንደሚችል በሚያመለክተው በዚህ ፊልም ላይ ዳንኤል ታደሰ (ጋጋኖ) በመሪ ተዋናይነት የተጫወተ ሲሆን ባሳየው የትወና ብቃትም አድናቆት ተችሮታል ተብሏል፡፡ ለትወናው አምስት ሺህ ዩሮ (125ሺ ብር) እንደተከፈለው ጋጋኖ ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡ ፊልሙ በአውሮፓና በአሜሪካ በተለያዩ ከተሞች ለእይታ ቀርቦ አድናቆትን ያተረፈ ሲሆን ከ60 በላይ ዓለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫሎች ላይ ተሳትፎ፣ ከ10 በላይ ሽልማቶችን ማግኘቱን የፊልሙ ፕሮዲዩሰር አርቲስት ዮሐንስ ፈለቀ ገልጿል፡፡ “ክረምብስ” ፊልምን፣ ለመስራት 200ሺ ዶላር እንደፈጀ ተናግሯል፡፡   

አዞ ከሰው የተሻለ ታማኝ ዘብ ነው፤ በሙስና አታታልለውም!...”

    የኢንዶኔዥያ የጸረ - አደገኛ ዕጾች ብሄራዊ ተቋም ሃላፊ፣ ከአደገኛ ዕጾች ጋር በተያያዘ ተከስሰው ሞት የተፈረደባቸውን ወንጀለኞች ለማቆያነት የሚያገለግልና ዙሪያውን በአዞዎች ተከብቦ ጥብቅ ጥበቃ የሚደረግለት አዲስ የደሴት ላይ እስር ቤት የማቋቋም ዕቅድ እንዳላቸው ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ከሰው ልጆች ይልቅ አዞዎች በአብዛኛው የተሻሉ ጠባቂዎች ናቸው፣ ምክንያቱም ሙስና አይቀበሉም ያሉት የመስሪያ ቤቱ ሃላፊ ቡዲ ዋሴሶ፣ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ተዘዋውረው፣ ለሚገነባው እስር ቤት ጠባቂ ሊሆኑ የሚችሉ እጅግ ጨካኝ የሆኑ አዞዎችን የማፈላለግ ሃሳብ እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡“በቻልነው አቅም ሁሉ በእስር ቤቱ ዙሪያ በርካታ አዞዎችን እናሰማራለን!... አዞዎችን በሙስና
ልትደልላቸውና፣ የፈለግኸውን እስረኛ እንዲያመልጥ እንዲያግዙህ አግባብተህ ልታሳምናቸው አትችልም!...” ብለዋል ቡዲ ዋሴሶ፡፡እስር ቤቱን የማቋቋም ሃሳቡ ገና በእቅድ ደረጃ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፤ የት አካባቢ እንደሚገነባም ሆነ ግንባታው ተጠናቅቆ በይፋ ስራ የሚጀምርበትን ትክክለኛ ጊዜ በተመለከተ ገና ውሳኔ ላይ አለመደረሱን ጠቁሟል፡፡

    አሊባባ የተባለው የቻይና የኢንተርኔት ንግድ ኩባንያ ባለፈው ረቡዕ በተከናወነው ሲንግልስዴይ የተባለ አመታዊ ልዩ የሽያጭ ፌስቲቫል
ባስመዘገበው ሽያጭ፣ በራሱ ተይዞ የቆየውን የዓለማችን የኢንተርኔት ዕለታዊ ሽያጭ ክብረወሰን ያሻሻለ ሲሆን አጠቃላይ ሽያጩ ከ13.8
ቢሊዮን ዶላር በላይ ይደርሳል ተብሎ እንደሚገመት ኤንቢሲ ኒውስ ዘገበ፡፡
ኩባንያው ረቡዕ ዕለት በተከናወነው “የሲንግልስ ዴይ” የሽያጭ ፌስቲቫል ላይ በስምንት ደቂቃ
ውስጥ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማስመዝገቡንና ባለፈው አመት ያገኘውን የ9.3 ቢሊዮን ዶላርየዕለት ሽያጭ ገቢ ለማግኘት
የወሰደበት ጊዜ አምና ከነበረው በግማሽ ያነሰ መሆኑንም ዘገባው ጠቁሟል፡ ፡ኩባንያው በዘንድሮው የ “ሲንግልስ ዴይ” አለማቀፍ
ልዩ የሽያጭ ፌስቲቫል ላይ፣ ከ6 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ ምርቶችን ለሽያጭ ማቅረቡንና በዕለቱም በአንድ ደቂቃ ከ120 ሺህ በላይ የግዢ
ጥያቄዎችንና 60 ሺህ ያህል ክፍያዎችን መቀበል የቻለበት ደረጃላይ መድረሱን ዘገባው አስታውሷል፡፡
ሽያጩ በይፋ በተከፈተ በአንድ ሰዓት ጊዜውስጥ በሞባይል አማካይነት ብቻ 27 ሚሊዮን ግብይቶችን መፈጸሙን ያስተዋወቀው
ኩባንያው፤
በዕለቱ የሸጣቸውን የኤሌክትሮኒክስና የመዋቢያ
ዕቃዎች ጨምሮ ሌሎች ሸቀጦችን በ1.7 ሚሊዮን
መልዕክተኞች፣ በ400 ሺህ መኪኖችና በ200
አውሮፕላኖች ለገዢዎች እንደሚያደርስም አክሎገልጿል፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት ጓደኛሞች ረዥም መንገድ ሊሄዱ ይነሳሉ፡፡ ምክክር ይጀምራሉ፡፡
አንደኛው - እንዲያው ለነገሩ እንዲህ ያለ ረዥም መንገድ ስንጀምር ብዙ ስንቅ መያዝ ነበረብን’ኮ፡፡
ሁለተኛው - ያንተን አላቅም እንጂ እኔ ከቤት የተዘጋጀልኝን ስንቅ ይዣለሁ፡፡
አንደኛው - ምን ምን ይዘሃል?
ሁለተኛው - በሶ፣ ጭኮ
አንደኛው - ሌላስ?
ሁለተኛው - አንድ አገልግል አላቂ ምግብ፣ ለአንድ ቀን የሚሆነን፡፡
አንደኛው - የሚጠጣስ?
ሁለተኛው - የሚጠጣስ ከኮዳዬ ውሃ ሌላ ምንም አልያዝኩም!
አንደኛው - መንገድ ላይ አውሬም፣ ሽፍታም ሊያጋጥመን ይችላል፡፡ ምን መሳሪያ ይዘሃል?
ሁለተኛው - ኧረ መሣሪያስ ምንም አልያዝኩ፡፡ እንዲያው አምላካችንን ተማምኜ ነው የወጣሁ፡፡፡ ለመሆኑ አንተስ ምን ይዘህ ነው የመጣህ?
አንደኛው - እኔ ምግብ፣ መጠጥ፣ መሳሪያ… አንዱንም አልያዝኩም፡፡ የሁለታችንን ልባዊ ፍቅር፣ አብሮ አደግነትና ዝምድናችንን ተማምኜ ነው የመጣሁት፡፡
ሁለተኛው - ይሄንንም ካሰነበተልን ምን እንፈልጋለን፡፡ በዚሁ ተማምነን መንገዳችንን መቀጠል ነው ያለብን፡፡
አንደኛው - በጣም ጥሩ እንግዲህ፤ ልባችንን አንድና ንፁህ አድርገን እንገስግስ፡፡
ሁለቱ ጓደኛሞች ተስማምተው መንገዳቸውን ተያያዙት፡፡ ከተማውን ዘልቀው ገጠር ደረሱ፡፡ ጫካ ጫካውን ሲያቋርጡ በድንገት አንድ ድብ ከፊታቸው ከች አለ፡፡ ይሄኔ አንደኛው በከፍተኛ ፍጥነት ተስፈንጥሮ ዛፍ ላይ ወጣ፡፡ ሁለተኛው የሚያደርገው ጨነቀው፡፡ አንድ ዘዴ ትዝ አለው፡፡ ድብ በተፈጥሮው ሬሣ አይበላም፡፡ ስለዚህ ሰውዬው ድምፁን አጥፍቶ ቢጋደም ድቡ ምንም ላያደርገው ይችላል፡፡
መሬት ላይ ተጋደመ፡፡
ድቡ ወደተኛው ሰው ቀረበና ወደፊቱ ጠጋ አለ፡፡ ከዚያም አሸተተውና ሞቷል ብሎ ጥሎ ሄደ፡፡ ድቡ መሄዱን ያየው ዛፉ ላይ ያለው ሰውዬ፣ ፈጥኖ ወረደና ወደተኛው ጓደኛው በመምጣት እንዲህ ሲል ጠየቀው፤
“ድቡ ወደ ጆሮህ ጠጋ ብሎ ሹክ ያለህ ነገር ምንድነው?”
የተጋደመው ጓደኛውም እንዲህ ሲል መለሰለት፡-
“ወዳጄ ሆይ! ከእንዲህ ከማያስተማምን ከሀዲ ጓደኛ ጋር አብረህ ረዥም መንገድ አትጀምር! ብሎ ነው የመከረኝ!”
*         *         *
ረዥም ጉዞ የሚጠብቀን መንገደኞች መተማመን ይገባናል፡፡ በአንድ ልብ የማይጓዙ መንገደኞች አገር አይገነቡም፡፡ ይልቁንም ቶሎ የመፈራረስ፣ እርስ በርስ የመጠራጠር፣ አንዱ አንዱን ለመጣል የመጣር፣ የመተነኳኮስና የመካካድ ባህሪ ያነግሳሉ፡፡ ተቋማዊ
አደረጃጀታቸውን ጥያቄ ላይ የሚጥለው ይህን ዓይነት ባህሪ ሲኖር ነው፡፡ ቡድናዊነትና ወገናዊነት ከበዛ መንገዶች እንቅፋት ይበዛባቸዋል፡፡ ይህ በፈንታው አገሬውን ይበድላል፡፡
መልካም አስተዳደርን ለማምጣት አስተዳዳሪዎቹ መልካም መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ መልካምነት በድንገት የሚከሰት ነገር አይደለም፡፡
የልብ ንፅህናን ይፈልጋል፡፡ የእጅ ንፅህናንም ይፈልጋል፡፡ ብስለትን ይፈልጋል፡፡ የሙሰኞች ፀር መሆንን ይጠይቃል፡፡ ከስህተት ተምሮ በየጊዜው ራስን ማሻሻልን ይጠይቃል፡፡ ባለጉዳይን ማክበርን ይጠይቃል፡፡ ምዝበራን መከላከልን ይጠይቃል፡፡ ፍትሐዊነትን ይጠይቃል፡፡

እነዚህ ባህርያት ሂደታዊ ናቸው፡፡ እያደር ራስን በመለወጥ የሚመጡ ናቸው፡፡ አብዛኛውን የለውጥ ጉዞ አዲስ አበባ ላይ ማየት የዋና ከተማችን እምብርትነትና ከተሜነት (ሜትሮፖሊታን መሆን) አመላካች ነው፡፡ ብዙ ጥፋቶችም ልማቶችም የሚታዩት ዋና ከተማ ላይ
መሆኑ ቁልፍ ቁልፍ ተቋማትም፣ ሹማንንትም እዚችው ከተማ ላይ መከማቸታቸውን ይነግረናል፡፡ ከየክልሉ ወደ ዋና ከተማይቱ የሚፈልሰው ህዝብ፣ የነዋሪውን ህዝብ ቁጥር መጨመሩ ብቻ ሳይሆን ባለጉዳዩን ያበረክተዋል፡፡ ባለጉዳዩ የመሬት ጉዳይ አለው፡፡
የመኖሪያ ቤት ጉዳይ አለው፡፡ የፍትህ ጉዳይ አለው፡፡ የከፋ የኢኮኖሚ ጉዳይ አለው፡፡ ይህንን ጉዳይ የሚፈታለት፣ የሚያስተናግድለት መልካም አስተዳደር ይሻል፡፡፡ በንፁህ መሰረት ላይ የተቋቋሙ መሥሪያ ቤቶች ከሌሉ፣ ባለጉዳይ አስፈፃሚ ጋር እየተሞዳሞዱ ሥራ
በሚያንቀሳቅሱበት ከተማ፣ መልካም አስተዳደርን መመኘት ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ ብርቱ ቁጥጥርና ብርቱ እርምጃን ይጠይቃል፡፡ እርምጃው እውነተኛ እርምጃ እንዲሆን የተሿሚዎች እከክልኝ ልከክልህ ሰንኮፍ መነቀል አለበት፡፡ ዘረፋና ምዝበራ መቆም አለበት፡፡
ከቢሮ ውጪ የሚደረጉ ውሎችና ድርድሮች መወገድ አለባቸው፡፡ ይህ ትግል ከባድ ቁርጠኝነትን ይጠይቃል፡፡
ተግባሩ ላይ ሳይሳተፉ ወይም ተግባሩን እያደናቀፉ፣ የአደባባይ ስብሰባ ላይ አንደበት ቢያሳምሩና ቢያስጨበጭቡ “ለጌሾው ወቀጣ
ማንም ሰው አልመጣ የመጠጡ ጊዜ ከየጎሬው ወጣ!” እንደሚባለው ነው እሚሆነው፡፡ ተግባሪ ሳይኖር፣ ስለመልካም አስተዳደር ዘማሪው በዛ እንደማለት ነው፡፡ ተግባሪ አመራር ይኖር ዘንድ ውስጡ መፈተሽ ይኖርበታል!

Saturday, 07 November 2015 10:33

የኪነት ጥግ

(ሞዴሊንግና ፋሽን)
• በወንዶች ዓለም ውስጥ ሆኜም እንኳን
ሴትነቴን እወደዋለሁ፡፡ ወንዶች እኮ ቀሚስ
መልበስ አይችሉም፤ እኛ ግን ሱሪ መልበስ
እንችላለን፡፡
ዊትኒ ሂዩስተን
• ፋሽን ይደበዝዛል፤ስታይል ዘላለማዊ ነው፡፡
ይቭስ ሴይንት-ሎውሬንት
• በሁሉም ነገር ውስጥ ውበት ያለ
ይመስለኛል፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች አስቀያሚ
ባሉት ነገር ውስጥ ውበትን ማየት
እችላለሁ፡፡
አሌክሳንደር ማክኩዊን
• ሞዴሊንግ ለእኔ ቆንጆ የመሆን ጉዳይ
አይደለም፤ ለሰዎች የሚመለከቱትና
የሚያስቡት ማራኪ ነገር መፍጠር ነው፡፡
ኪሊ ባክስ
• ሞዴሊንግ በትክክል የዝምታ ትወና ነው፡፡
አሪዞና ሙሴ
• ሞዴሊንግ መቶ ፐርሰንት፣ ቅድምያ
የምሰጠው ቁጥር አንድ ጉዳዬ ነው፡፡
ኬንዳል ጄነር
• ገንዘቤን ባንክ አስቀምጣለሁ፡፡ ከሞዴሊንግ
በኋላ ላለው ህይወቴ ማሰብ አለብኝ።
ዝነኝነቴ ካከተመ በኋላ ለሚኖረው
ህይወቴ።
ኢቫ ሄርዚጐቫ
• ሞዴሊንግ የብቸኝነት ሥራ ነው፡፡
ኪም አሌክሲስ
• አንፈልግሽም እስክባል ድረስ በሞዴሊንግ
እቀጥላለሁ፤ምክንያቱም በጣም
እወደዋለሁ፡፡
ክላውዲያ ስሺፈር
• የሎስ አንጀለስ ፋሽን፣ የሞዴሊንጉ ዓለም
ስታርባክስ ነው፡፡
ጃኒሴ ዲክሰን
• ትወናና ሞዴሊንግ አንዳቸው ከሌላኛቸው
የሚያገናኛቸው ነገር የለም፡፡
ኢሌ ማክፈርሰን

      በ2002 ዓ.ም “ጀነራሎቹ” በሚል ርዕስ ለንባብ የበቃው ታሪካዊ መፅሐፍ፤ አዳዲስ አስገራሚ፣ አሳዛኝና ቀልብ የሚስቡ መረጃዎችን በማካተት እንደገና የተዘጋጀ ሲሆን በነገው ዕለት ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮ በግራንድ ዮርዳኖስ ሆቴል እንደሚመረቅ ደራሲው ሻምበል ኢዮብ እንዳለ ለአዲስ አድማስ አስታወቁ፡፡
በዚህ መፅሀፍ ውሰጥ ደም ያፋሰሰውና ያልተሳካው የግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም ወታደራዊ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ እንዲሁም ጀነራል ተፈሪ በንቲን ጨምሮ የ106 የደርግ አባላትን ጉርድ ፎቶግራፎችና በደርግ ውስጥ በነበረው የስልጣን ሽኩቻ በተለያየ ጊዜ የተገደሉ የጦር ጀነራሎች በርካታ ፎቶግራፎች እንደተካተተቱ ተጠቁሟል፡፡  
መፅሀፉ ቀደም ሲል በ302 ገጾች፣143 ፎቶግራፎችን አካትቶ የቀረበ ሲሆን የአሁኑ 351 ፎቶዎችን በማካተት በ496 ገጾች መዘጋጀቱንና ለ6ኛ ጊዜ መታተሙን ፀሐፊው ገልፀዋል፡፡ ከ2004 እስከ 2007 ባሉት ጊዜያት ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር መፅሀፉን አንብበው አስተያየት ከላኩ ሰዎች የተገኙ ትክክለኛ መረጃዎች የተካተቱበት ነው የተባለው “ጀነራሎቹ”፤ በ165 ብር ለገበያ መቅረቡም ታውቋል። መጽሐፉ እስካሁን አምስት ጊዜ ታትሞ፣ 22ሺህ ቅጂዎች መሸጣቸውንም ጸሐፊው የላኩት መረጃ ያስረዳል፡፡    

     የልጅ ኢያሱ አባት፣ የእቴጌ መነን አያት፣ የደሴ ከተማ መስራችና የአድዋ ግንባር ቀደም ዘማች በነበሩት በወሎው ገዢ በንጉስ ሚካኤል ህይወትና ስራዎች ላይ የሚያጠነጥነው “ሚካኤል ንጉሰ ወሎ ወትግሬ” የተሰኘው መፅሀፍ ሰሞኑን ለንባብ በቅቷል፡፡ በምስጋና ታደሰ የተዘጋጀው ይኼው የታሪክ መፅሐፍ፤በ19ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻና በ20ኛው ክ/ዘመን የነበረውን የወሎ ክ/ሀገርንና የኢትዮጵያ ታሪክን ለማወቅ ለሚሹ በመረጃነት ያገለግላል ተብሏል፡፡  አዘጋጁ ምስጋናው ታደሰ፣ መጽሐፉን በሁለተኛ ዲግሪው የማሟያ ፅሁፍ ላይ ተመስርቶ ማሰናዳቱንና የታሪክ ጥናትና ምርምር ሊያሟሏቸው የሚገቡ መስፈርቶችን ለማሟላት ጥረት ያደረገበት እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡ በ220 ገጾች የተቀነበበው መፅሀፉ፤ በ70 ብር ለገበያ መቅረቡም ታውቋል፡፡

      የ2008 ዓ.ም የ“ባላገሩ ምርጥ” የድምፅ ውድድር አሸናፊ አርቲስት ዳዊት ፅጌ፣ በውድድሩ ሂደት ያገዙትንና ከጎኑ የነበሩትን ድርጅቶችና ግለሰቦች የሚያመሰግንበት ልዩ የሙዚቃ ዝግጅት ዛሬ ምሽት ይካሄዳል፡፡ የዝግጅቱ አስተባባሪ እንደሻው የኪነ-ጥበብ ፕሮሞሽን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ፕሮግራሙ ዛሬ ምሽት በባታ የባህል ምግብ ቤትና መናፈሻ ፓርክ የሚከናወን ሲሆን ምሽቱ ድምፃዊው በውድድሩ ሂደት የረዱትን ድርጅቶችና ግለሰቦች የሚሸልምበትና ከቅላፄ ባንድ ጋር ልዩ የሙዚቃ ዝግጅት የሚያቀርብበት ይሆናል ተብሏል፡፡   
ድምፃዊ ዳዊት ፅጌ በምሽቱ አዲስ የሙዚቃ ስራውን ያቀርባል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ከእውቁ የፒያኖ ተጫዋች ግርማ ይፍራሸዋ፣ ከአርቲስት ግርማ ነጋሽ፣ ከአርቲስት ባህታ ገ/ህይወትና ከአርቲስት ግርማ በየነ ጋር በጋራ እንደሚያቀነቅንም እንደሻው የኪነ-ጥበብ ፕሮሞሽን አስታውቋል፡፡ ባታ የባህል ምግብ ቤትና መዝናኛ ፓርክ እና ኢምር አድቨርታይዚንግ የፕሮግራሙ አጋር እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡  

    በሊንኬጅ አርት ሪሶርስ ሴንተር አዘጋጅነት የሚካሄደው 10ኛው የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫል ከነገ በስቲያ በ11 ሰዓት በኦሮሚያ ባህል ማዕከል ይከፈታል፡፡ እስከ ህዳር 6 ቀን 2008 ዓ.ም ድረስ በሚቆየው የፊልም ፌስቲቫል ላይ ከ70 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ፊልሞች ሳምንቱን ሙሉ እንደሚታዩ የተገለፀ ሲሆን ከአሜሪካ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ከአሜሪካ በሚመጡ የፊልም ባለሙያዎች የአንድ ቀን ኮንፍረንስ ይካሄዳልም ተብሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከእስራኤል በሚመጡ የፊልም ባለሙያዎች ለፊልም ሞያተኞች የግማሽ ቀን ስልጠና እንደሚሰጥ የተጠቆመ ሲሆን ህዳር 6 ቀን 2008 ዓ.ም ለአሸናፊ የፊልም ባለሙያዎች ሽልማት በማበርከት ፌስቲቫሉ እንደሚዘጋ አዘጋጁ ሊንኬጅ አርት ሪሶርስ ሴንተር በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

Saturday, 07 November 2015 10:23

“The show must go on” ለእይታ በቃ

    በሪቻርድ ቪያ የተፃፈው “The show must go on” የተሰኘ ድራማ በአርቲስት ፈለቀ የማር ውሃ አበበ “ትርኢቱ ይቀጥላል” በሚል ተተርጉሞና ተዘጋጅቶ ትላንት ምሽት በሃርመኒ ሆቴል ለእይታ በቃ፡፡ የ30 ደቂቃ ርዝማኔ ያለው ይሄው ፋርስ ኮሜዲ ድራማ፤ በኒውዮርክ ዩኒቨርስቲ ማስተማሪያ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሶል ፕሮሞሽንና በአቶ ሰለሞን ግዛው ፕሮዲዩስ የተደረገው ድራማው፤ በየ15 ቀኑ አርብ በበደሌ ኮሜዲ ምሽት በሃርመኒ ሆቴል ለተመልካች የሚቀርብ ሲሆን አርቲስት ሱራፌል ተካ፣ ሰለሞን ተስፋዬ፣ መስከረም አበራ፣ ሰለማዊት በዛብህ፣ ብሩክ ትንሼ፣ ዳዊት አለሙና ሄኖክ በሪሁን እንደሚተውኑበት ተርጓሚና አዘጋጁ ለአዲስ አድማስ ገልጿል። ድራማው መታሰቢያነቱ ለብሔራዊ ቴአትር 60ኛ ዓመት መሆኑንም አርቲስቱ ተናግሯል፡፡