Administrator

Administrator

Tuesday, 29 December 2015 07:21

የዘላለም ጥግ

(ስለ ሰብእና)
• ጠንካራ ሰብእና አለኝ፤ እናም የማስበውን
እናገራለሁ፡፡
ፔኔሎፕ ክሩዝ
• በኪነጥበብ ውስጥ በጣም የሚያማልለው ነገር
የራሱ የከያኒው ሰብእና ነው፡፡
ፖል ሴዛኔ
• ሰብእናዬን በአለባበሴ እያሳየሁኝ ነው፡፡
ዲውሎን ዋዴ
• ሴትን በአስተዋይነቷና በሰብእናዋ አደንቃታለሁ።
ውበት ብቻውን በቂ አይደለም፡፡
ሮቤርቶ ካቪሊ
• ሃያሲ የኪነጥበብ ስራን የደራሲውን ሰብእና
ሳይጠቅስ መተቸት ሊማር ይገባል፡፡
ኦስካር ዋደልድ
• በሌሎች ዘንድ ማራኪ የሚያደርጋችሁ
ሰብእናችሁ ነው፡፡
ሞሊ ኪንግ
• የእኔ ጀግና አባቴ ነበር፡፡ ሰብእናዬን ያገኘሁት
ደግሞ ከእናቴ ነው፡፡
ማጂክ ጆንሰን
• አንዳንዴ በሌላ ሰው ሰብእና ራሳችሁን
ታጣላችሁ፡፡
ጁሊ ለንዶን
• ደግ ሰዎች የሚወዱትንና ሊሆኑ የሚፈልጉትን
አይነት ሰው ለመሆን እሻለሁ።
ጃሮድ ኪንትዝ
• ሰው የእምነቱ ውጤት ነው፡፡
አንቶን ቼክሆቭ
• ሴት ልጅ ከውልደት እስከ 18 አመት እድሜዋ
ጥሩ ወላጆች ያስፈልጋታል፡፡ ከ18 አመት እስከ
35 አመት እድሜዋ ጥሩ መልክ ትፈልጋለች፡
፡ ከ35 እስከ 55 ጥሩ ሰብእና ሊኖራት ይገባል፡
፡ ከ55 አመቷ ጀምሮ ጥሩ ገንዘብ ትፈልጋለች፡፡
ሶፊ ቱከር
• ለሴት ተዋናይ ስኬታማነት ሰብእና በጣም ወሳኝ
ነገር ነው፡፡
ማ ዌስት
• በስእልና በግጥም፣ ሰብእና ሁሉም ነገር ነው።
ገተ

ከአራቱ ዋና ዋና እቅዶች መካከል፣ አንዱ በከፊል ተሳክቷል።

የመንገድ፣ የባቡር፣ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ...
ሦስቱ አልተሳኩም። እንዲያውም፣ አሳሳቢ ናቸው ተብለዋል - ትናንት በፓርላማ በፀደቀው አዲሱ የአምስት አመት እቅድ።
የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት፣ ‘ንቅንቅ’ አለማለቱና የስራ እድል አለመፍጠሩ
‘አነስተኛና ጥቃቅን’፣ ብዙ ቢወራለትም፣ ጥቃቅን እድገት አለማሳየቱ
ኤክስፖርት መደንዘዙና የውጭ ምንዛሬ እጥረት መፈጠሩ
ምክንያቶቹ፡
መንገድ፣ ባቡር፣ ግድብ... በከፊል የተሳኩት በአብዛኛው በግል ኩባንያዎች ስለተሰሩ ነው።
የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ያልተነቃነቀው፤ መንግስት በኢኮኖሚ ውስጥ ስለገነነና ቢዝነስን ስላቀጨጨ ነው።
በአነስተኛና ጥቃቅን፣ በየአመቱ ከ2 ሚሊዮን በላይ የስራ እድል እየተፈጠረ ነው የሚባለው ወሬ ሃሰት መሆኑን... የአዲስ አድማስ ዘገባ መስከረም 2004 (‘የመንግስት ወከባ - ከፍርሃት የማያላቅቅ የህልም ሩጫ’ በሚል ርዕስ)
ኤክስፖርት መደንዘዙና አሳሳቢ መሆኑ በተደጋጋሚ ተዘግቧል። (“የስራ ፍሬውን ስንነጥቀው ይበረታታል” ብሎ መመኘት ሃጥያት ነው በሚል ርዕስ ታህሳስ 2006 ዓ.ም - አዲስ አድማስ)
የኢትዮጵያ ድህነት፣ በጣም አደገኛ እንደሆነ፣ ለአፍታም ያህል ልንዘነጋው አይገባም ነበር። ግን፣ በተደጋጋሚ እየዘነጋነው፤ በአላስፈላጊ ንትርክና ግጭት ጊዜያችንን እናባክናለን።
ሰዎች፤ ዘንድሮ ያለ እርዳታ አመቱን መዝለቅ የማይችሉ ረሃብተኛና ችግረኛ ኢትዮጵያዊያን፣ ከ18 ሚሊዮን በላይ ናቸው። ድርቅ በማይከሰትበትና ከፍተኛ የእርሻ ምርት በሚሰበሰብበት አመት እንኳ፣ ከአስር ሚሊዮን በላይ ሰዎች፣ ያለ እርዳታ ከአመት አመት መሻገር አይችሉም። የውጭ የእህል እርዳታ ባይኖርኮ፣ ሕዝብ ያልቅ ነበር። ከዚህ የከፋ አደጋና ውድቀት ምናለ?
በከተሞች፣ የስራ ዕድል የሚፈጥሩ የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንቶች፣ የሉም። በ1994 ዓ.ም በመካከለኛና ትላልቅ የኢንዱስትሪ ተቋማት የነበሩ ሰራተኞች ቁጥር መቶ ሺ ነበር። ዛሬ ከአስራ ምናምን ዓመታት በኋላ፣ ቁጥሩ 300ሺ ብቻ ነው። ለዚያውም፣ የሰራተኞቹ አማካይ የገቢ እና የኑሮ ደረጃ ሲታይ፤ በ40% የወረደ ነው (በብር ሕትመትና በዋጋ ንረት ሳቢያ)።
በከተማም ሆነ በገጠር፣ ኢትዮጵያ በክፉ ድህነት (በረሃብና በሥራ አጥነት) ሳቢያ፣ በቀላሉ ሊፈነዳ የሚችል አደገኛ አጣብቂኝ ውስጥ የተቀረቀረች አገር ናት።
ወገኛነት ተጠናውቶን፣ ‘የሃብት ልዩነትና የሃብት ክፍፍል’ እያልን እንደሰኩራለን - ሃብት መፍጠር ባቃተው አገር ውስጥ ሆነን። ስለ ‘ካርቦንዳይኦክሳይድ’ እና ስለ ‘አለም ሙቀት’ እንለፍፋለን - ነዳጅ ለመጠቀም አቅም በሌለው ድህነት ውስጥ ሆነን። መሬትንና ገጠርን፣ ግብርናንና ዘልማዳዊ አኗኗርን እያንቆለጳጰስን እናወራለን - የድህነት አጣብቂኝ ጋር የሙጢኝ ብለን ለመቀጠል።
ሰዎች እናስብ እንጂ። በእርሻ ብቻ፣ ከረሃብ የተላቀቀ አገር፣ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የለም። ያለ ኢንዱስትሪና ያለ ከተማ እድገት፣ ወደ ብልፅግና ለመራመድ ይቅርና፣ ከድህነት... ከረሃብና ከስራ አጥነት መውጣት አይቻልም። በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ፣ የፋብሪካ ምርት ድርሻ፣ ከድሃ የአፍሪካ አገራት ጋር ሲነፃፀር እንኳ፣ ግማሽ ያህል አልተራመደም። (ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ - ገፅ 6)።
የመካከለኛና የትላልቅ ፋብሪካዎች ኢንቨስትመንት አልተስፋፋም። የስራ እድሎችን በገፍ ይፈጥራሉ እየተባለ ብዙ የተወራላቸው፣ “የአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት”፣ በተግባር እንቅስቃሴያቸው ሲታይ፣ ከሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፍ የባሰ ቀርፋና ጎታታ ሆኗል። የፋብሪካ ምርት ፈቅ አለማለቱ መንግስትን ቢያስጨንቅ አይገርምም። እድገት ሲቋረጥና ስራ አጥነት ሲስፋፋ፣ ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ የሆኑ አደጋዎች ይፈጠራሉ። የኢንዱስትሪ ጉዳይ፣ “የሞት ሽረት ጉዳይ ነው” ይላል - የእቅዱ ሰነድ።
ከዚህ የኢንዱስትሪ ልምሻ ላይ፣ የኤክስፖርት ድንዛዜ ሲጨመርበት ደግሞ፣ ይበልጥ ያስፈራል። ለዚህም ይመስላል፣ ሁለተኛው የሞት ሽረት ጉዳይ፣ ኤክስፖርት እንደሆነ ሰነዱ በተደጋጋሚ የሚገልፀው።
በእርግጥም፣ በአለማቀፍ ንግድ፣ የውጭ ምንዛሬን ማሳደግ ካልተቻለ፣ የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንትን ማፋጠን አይቻልም። እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ፣ በአምስት አመታት፣ ኤክስፖርትን ወደ ሦስት እጥፍ ማሳደግ ያስፈልጋል ተብሎ እቅድ ወጥቶ የነበረውም፤ በዚህ ምክንያት ነው።
ነገር ግን፣ ኤክስፖርት አላደገም። የኤክስፖርት ሽያጭ አምና፣ 10 ቢሊዮን ዶላር እንዲደርስ ቢታቀድም፤ አልተሳካም። 3 ቢሊዮን ዶላር ላይ ደንዝዞ ቆሟል። ለምን? በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የመንግስት ድርሻ እየገነነ፣ በተቃራኒው ኢንቨስትመንት እየቀጨጨ ከመምጣቱም በተጨማሪ፣ ኤክስፖርትን ያደነዘዙ ሌሎች ምክንያቶችም አሉ።
አንደኛ፣ ባለፉት አምስት አመታት፣ መንግስት፣ በአላስፈላጊ የምዝገባ ቢሮክራሲና በአጥፊ የዋጋ ቁጥጥር አማካኝነት የአገሪቱን የቢዝነስ ድባብ ሲያተራምስ ቆይቷል።
ሁለተኛ፣ መረን በለቀቀ የገንዘብ ህትመት ሳቢያ፣ የአገሪቱ ብር መርከሱ እየታወቀ፣ የዶላር ምንዛሬ በዚያው መጠን እንዲስተካከል አለመደረጉ፣ ኤክስፖርትን ጎድቷል። የአለም ገንዘብ ድርጅት እንደሚለው፤ የዶላር ምንዛሬ፣ 27 ብር አካባቢ መሆን ነበረበት። ግን አልሆነም።
እንግዲህ አስቡት። ቡና ወይም ጫማ አምርታችሁ ወደ ውጭ በዶላር ብትሸጡ፤ መንግስት ዶላሩን ይወስድና፣ በራሱ ተመን በብር መንዝሮ ይሰጣቸዋል - ለአንድ ዶላር ወደ 21 ብር ገደማ። ከእያንዳንዱ ዶላር ስድስት ብር ይወስድባችኋል ማለት ነው። ምርት ወደ ውጭ የሚሸጡ ሰዎችንና ድርጅቶችን፣ እንዲህ እየዘረፍናቸው፣... ኤክስፖርት በሦስት እጥፍ እንዲያድግ መመኘት፣ ነውር አይደለም?
ለነገሩ፤ መንግስትም፣ አሁን አሁን ይህንን መካድ እየተወ ይመስላል። ብር በመርከሱ ምክንያት፣ የዶላር ምንዛሬ እንደተዛባ አምኗል። ይህም ብቻ አይደለም። ነገርዬው፣ ኤክስፖርትን እንደሚጎዳ፣ ትናንት አርብ በፓርላማ በፀደቀው፣ ባለ 185 ገፅ እቅድ ውስጥ፣ በግልፅ ተጠቅሷል። መጠቀስ ብቻ አይደለም። ባለፉት አምስት አመታት ካጋጠሙ ሦስት ትልልቅ ፈተናዎች መካከል አንዱ፣ ይሄው የብር መርከስ ጉዳይ እንደሆነ ተገልጿል። በገንዘብ ሕትመት ሳቢያ፣ ብር ሲረክስ፣ በዚያው መጠን የዶላር ምንዛሬ አለመስተካከሉ ኤክስፖርትን እንደሚጎዳ ሰነዱ ያመለክታል (ገፅ 53)። የውጭ ምንዛሬ ተመንን ማስተካከልና ለኤክስፖርት አመቺ እንዲሆን ማድረግ እንደሚያስፈልግ በመግለፅ፣ በዋና ዋና እቅዶች ዝርዝር ውስጥ ገብቷል(ገፅ 78)። ጥሩ ነው። በእርግጥ፣ ዘግይቷል። እንዴት?
በብር መርከስና በዶላር ምንዛሬ አለመስተካከል ሳቢያ፣ ኤክስፖርት እየተዳከመ መሆኑን የሚተነትን ፅሁፍ ከሁለት አመት በፊት በአዲስ አድማስ መውጣቱን ማስታወስ ይቻላል።
“‘የስራ ፍሬውን ስንነጥቀው ይበረታታል’ ብሎ መመኘት ሃጥያት ነው” በሚል ርዕስ የቀረበው የያኔው ትንታኔ እንዲህ ይላል።
“ከመነሻው፣ የብር ኖት አለቅጥ ከማተም በመቆጠብ ብር እንዳይረክስ ማድረግ እንጂ፣ ብር ከረከሰ በኋላ፣ የዶላር ምንዛሪን በቀድሞው ተመን ላይ ቆልፎ ማቆየት አያዋጣም። እንዴት ሊያዋጣ ይችላል? በኤክስፖርት መስክ የተሰማሩ አምራቾችና የቢዝነስ ሰዎችን በግድ እየዘረፍናቸው (ከእያንዳንዷ የዶላር ገቢ ስድስት ብር ነጥቀን እየወሰድንባቸው)፤ በየአመቱ  ተጨማሪ ዶላር የሚያመጡ... የውጭ ምንዛሪ ምንጭ እንደሚሆኑልን... አምነን መቀመጣችን፣ እጅግ አላዋቂነትም እጅግ ሃጥያትም ነው።”
ይሄ፣ ከሁለት ዓመት በፊት የተፃፈና የታተመ ነው። ግን፣ እስካሁን፣ ሁነኛ መፍትሄ ስላልተበጀለት፣ ኤክስፖርት እዚያው በድንዛዜ ተገትሮ ቀርቷል። ከሦስት ዋና ዋና አሳሳቢ የአገር ጉዳዮች መካከል አንዱ ሆኖ የሚጠቀስም ሆናል።
ታዲያ፣ ቅጥ ያጣ የገንዘብ ህትመት... መዘዙ ይህ ብቻ አይደለም። መንግስት አለቅጥ በሚያሳትመው ገንዘብ ሳቢያ፣ ‘ብር መርከሱ’፣ እናም የዋጋ ንረት መከሰቱ፣ ብዙ ነገሮችን አበላሽቷል። ኢኮኖሚውን አተራምሷል። ኢንቨስትመንትን አዳክሟል። እንዴት?
ለእውነትና ለመረጃ ክብር የማይሰጥ፣ ጭፍን ፕሮፖጋንዳ
የዋጋ ንረት ሲፈጠር፣ መንግስት ሁሌም፣ በቢዝነስና በንግድ ሰዎች ላይ ነው የሚሳብበው። ግን፤ ውሸት እንደሆነ ይታወቃል። የዋጋ ንረት፣ ከብር መርከስ ጋር (ከገንዘብ ህትመት ጋር) የተቆራኘ እንደሆነ፣ በግልፅ ይታወቃል። ለዚህም፣ ተጠያቂው መንግስት ነው። ነገሩ ውስብስብ አይደለም። መንግስት፣ ከአገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም ጋር በማይመጣጠን ፍጥነት፣ በገፍ ገንዘብ ካሳተመ፤ ብር ይረክሳል፣ የዋጋ ንረት ይፈጠራል። ቁርኝታቸው በጣም የጠበቀ ከመሆኑ የተነሳ፤... ለምሳሌ በአምስት አመት ውስጥ፣ የገንዘብ ሕትመትና ስርጭትን ከኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ጋር በማነፃፀር፣ ምን ያህል የዋጋ ንረት እንደሚፈጠር መገመት ይቻላል።
የዋጋ ንረት= (የገንዘብ ስርጭት ፍጥነት) – (የኢኮኖሚ እድገት ፍጥነት)
ያው፣ የገንዘብ ስርጭት፣ ከሞላ ጎደል፣ ዞሮ ዞሮ በገንዘብ ህትመትና ከዚሁ ጋር ተያይዞ በሚመጣ ‘የባንክ ቼክ’ ላይ የተመሰረተ ነው። እናም፣ ባለፉት አምስት ዓመታት፣በገንዘብ ህትመትና በቼክ አማካኝነት፣ (የገንዘብ ስርጭት ከ54 ቢሊዮን ብር ወደ 167 ቢሊዮን ብር ጨምሯል - የብሔራዊ ባንክ የ2007 የመጨረሻ የሩብ ዓመት ሪፖርት አባሪ - ገፅ 8)። ማለትም... የገንዘብ ስርጭት በየዓመቱ፣ በአማካይ 25% በመቶ ሲስፋፋ ቆይቷል።
የኢኮኖሚ እድገትስ?
ባለፉት አምስት አመታት፣ በአማካይ በ10% እያደገ ነበር።
መረጃዎቹ ግልፅ ናቸው። ኢኮኖሚው አቅም በላይ፣ ምን ያህል የገንዘብ ስርጭት እንደጨመረ መመልከት እንችላለን። 15% ያህል ነው ልዩነቱ። ይሄ ነው፣ ዋነኛው የዋጋ ንረት መንስኤ። የዋጋ ንረት፣ ከወር ወር፣ በተለያዩ ምክንያቶች ሊዛነፍ ይችላል። ሁለት ሦስት አመት፣ ከዚያም እስከ አምስት ዓመት ሰፋ አድርገን ካየን ግን፤ የዋጋ ንረትና የገንዘብ ስርጭት ቁርኝት፣ ፍንትው ብሎ ይታያል።
የዋጋ ንረት = (የገንዘብ ስርጭት ፍጥነት) – (የኢኮኖሚ እድገት ፍጥነት)
የዋጋ ንረት = (25%) – (10%) = 15%
የገንዘብ ስርጭቱ፣ ከአገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም በላይ አለቅጥ መስፋፋቱን በማገናዘብ፤ በየአመቱ በአማካይ 15% የዋጋ ንረት እንደሚከሰት መገመት ይቻላል።
በተጨባጭስ፣ ባለፉት አምስት አመታት፣ ምን ያህል የዋጋ ንረት ተከሰተ?
የሸቀጦችን ዋጋ በየወሩ በማነፃፀር፣ የስታትስቲክስ ባለስልጣን የሚያወጣቸውን መረጃዎች መመልከት እንችላለን።  
በየዓመቱ የሸቀጦች ዋጋ፣ በአማካይ በ15% ሲጨምር እንደቆየ፣ የስታትስቲክስ ባለስልጣን መረጃዎች ያረጋግጣሉ። ይሄ፣ በቀጥታ የሸቀጦችን ዋጋ በማነፃፀር ላይ የተመሰረተ መረጃ ነው።
የገንዘብ ህትመትንና ስርጭትን በማገናዘብ ካገኘነው የዋጋ ንረት ግምት ጋር ተመሳሳይ ነው።
በአጭሩ፤ የገንዘብ ሕትመት፣ ከብር መርከስ ጋር፣ እንዲሁም ከዋጋ ንረት ጋር የተቆራኘ እንደሆነ፣ ከእነዚህ ተጨባጭ መረጃዎች መረዳት ይቻላል። ግን ምን ዋጋ አለው? መረጃንና እውነትን፣ ከምር የማናከብር ከሆነ፣ እስካሁን ያየነው ትንታኔ ሁሉ ከንቱ ይሆናል።  
መንግስት፣ ወጪዎቹን ለመሸፈን፣ አለቅጥ በሚያሳትመው ገንዘብ ምክንያት፣ የዋጋ ንረት እንደሚፈጠር ቢታወቅም፤ ሁልጊዜ በቢዝነስ ሰዎችና በነጋዴዎች ላይ ያላክካል። ለምን? ለዛሬ ብቻ፣ ከወቀሳ ለማምለጥ በመመኘት ሊሆን ይችላል። ግን መዘዞች አሉት።
አንደኛ፤ ለመረጃና ለእውነታ ዋጋ የማይሰጥ፣ የአሉባልታና የፕሮፖጋንዳ፣ የጭፍን እምነትና የጭፍን ስሜታዊነት ባህልን ለማጠናከር፣ በወዶ ዘማችነት እየተሰለፈ እንደሆነ መገንዘብ ይኖርበታል። ዞር ብሎ ግን፣ ‘ተቃዋሚዎች፣ ተጨባጭ መረጃን ለመቀበል የማይፈልጉ፣ የኢኮኖሚ እድገትን የሚክዱ፣ ጭፍን ፕሮፓጋንዳ የሚራግቡ ናቸው’ እያለ  ያወግዛል። ግን፤ ሁለት ወዶ አይሆንም። ያሰኘው ጊዜ.... ‘ተጨባጭ መረጃን በጭፍን ፕሮፓጋንዳ እየሸፋፈነ’፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ፣ ‘ተጨባጭ መረጃ በጭፍን ፕሮፓጋንዳ እንዳይሸፈን እንከላከል’ ብሎ ቢሰብክ፣ ከንቱ ነው።
‘ከገበሬ ጀምሮ እስከ ኢንዱስትሪ ድረስ፣ ኢትዮጵያዊያን፣ በተጨባጭ መረጃ ላይ በተመሰረተ ስልጡን አስተሳሰብ አማካኝነት፣ ውጤታማ ምርታማነትን ማስፋፋትና መበልፀግ ይችላሉ’ ብሎ ይደሰኩራል። ትክክል ነው። ግን፣ ለተጨባጭ መረጃ ክብር የሚሰጥ ባህል፣ በአንዳች ተዓምር አይፈጠርም። በጎን በኩል፣ ለመረጃ ዋጋ የማይሰጥ የጭፍንነት ባህልን ዘወትር እየያጠናከርን፣ እንዴትና ከወዴት ስልጡን አስተሳሰብ ይመጣል? ግን ጉዳቱ ይህ ብቻ አይደለም።
ቢዝነስን እያንቋሸሹ፣ ኢንዱስትሪን ማስፋፋት?
የዋጋ ንረትን በነጋዴዎችና በቢዝነስ ሰዎች ላይ ሲያላክክ፤ የብልፅግና መሰረትንም በእንጭጩ እየሸረሸረ መሆኑን አይገነዘብም። ቢዝነስ ማለት፣ በተፈጥሮው፣ ‘ማጭበርበርና ማታለል’ ማለት እንደሆነ ለማሳመን ዘወትር ይጣጣራል። በሌላ አነጋገር፤ ‘ትርፋማነት’ ማለት ‘አጭበርባሪነት ነው’፣ ‘ባለሃብት’ ማለት ‘አታላይ ነው’ የሚል ስብከት ይግተናል።
እንዲህ፣ ቢዝነስን፣ አትራፊነትን፣ ስኬታማነትን፣ ባለሃብትነትን ሲያንቋሽሽ ይከርምና፤... ትንሽ ቆይቶ ደግሞ፤... “የፈጠራና የምርታማነት ክህሎት፣ የቢዝነስና የትርፋማነት ባህል አልዳበረም። ወጣቶች፣ እየገቡበት አይደለም” በማለት እሮሮ ያሰማል።
አሃ፤ ቢዝነስን የሚያናንቅ ስብከት ለአዲሱ ትውልድ እየጋትን፤ የቢዝነስ ጥበበኞችን በብዛት የሚያፈራ ስልጡን ባህል ለመፍጠር መመኘት... እንዴት አብሮ ይሄዳል?
ግን፣ ነገሩ በስብከት ብቻ የሚቆም አይደለም።
የዋጋ ቁጥጥር እየታወጀበት፣ ፋብሪካ ለመክፈት የሚጓጓ አለ?   
የክልል የንግድ ቢሮዎች፣ የፌደራል የንግድ ሚኒስቴር፣ የሸማቾች ኤጀንሲ... ምናምን... ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ፣ የቢዝነስ ሰዎች ላይ የሚዝቱ፣ ከዛቻም አልፈው፣ የዋጋ ቁጥጥርና የዋጋ ተመን የሚያውጁ፣ የመንግስት አካላት ሞልተዋል።
አሁን አስቡት። እናንተ፣ ለኢንቨስትመንት የሚሆን ገንዘብ ቢኖራችሁ፣ ምን ታደርጋላችሁ? የሳሙና ፋብሪካ ለመክፈት ትሞክራላችሁ? ወይስ የሳሙና ነጋዴ ለመሆን ትወስናላችሁ?
መንግስት፣ ካሁን በፊት እንዳደረገው፣ በማንኛውም ጊዜ፣ የሳሙና ዋጋ ላይ ቁጥጥር እንደሚያውጅና የዋጋ ተመን እንደሚያወጣ ታውቃላችሁ። ይህንን እያወቃችሁ፣ የሳሙና ፋብሪካ ለመክፈት ትደፍራላችሁ?
የሳሙና ንግድ ይሻላል። ስራው ቀለል ይላል። በዚያ ላይ፣ መንግስት የዋጋ ቁጥጥር ቢያውጅባችሁ፤ ብዙ ኪሳራ ሳይደርስባችሁ፣ የሳሙና ንግዳችሁን መተውና፣ ወደ ሌላ ንግድ መግባት ትችላላሁ። የሳሙና ፋብሪካ ግን፣ አስቸጋሪ ነው።
ከኪሳራ ማምለጫ አታገኙም። እና፤ ብዙ ሰው፣ ከፋብሪካ ቢዝነስ ይልቅ ወደ ንግድ ቢዝነስ ቢያተኩር ይገርማል?
በአጠቃላይ፣ መንግስት፣ በቅድሚያ ራሱን ለማስተካከል ይጣር። አደገኛው የድህነት አጣብቂኝ (ከአደገኛው የስራ አጥነትና የረሃብ አጣብቂኝ) መውጣት፣... ከዚያም ወደ ብልፅግና መራመድ የሚቻለው፣ በጭፍን የፕሮፓጋንዳ ባህል አይደለም። ቢዝነስንና ትርፋማነትን በሚያንቋሽሽ የውድቀት ጎዳና፣ ወደ ስኬት መጓዝ አይቻልም።

     ታህሳስ 2 ቀን 2008 ዓ.ም ባወጣው አዲስ አድማስ፤ “የመንግስት ብክነት በቢሊዮንና በሚሊዮን…” በሚል ርዕስ ስር ስለ ሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሰልጠኛ ማዕከል የቀረበው ዘገባ የተሳሳተና ወቅታዊነቱን ያልጠበቀ በመሆኑ ተከታዩ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡
ይህ አንጋፋ የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሰልጠኛ ማዕከል፤ በ1961 ዓ.ም ሲቋቋም በሁለት የሙያ ዘርፎችና በ21 ሰልጣኞች የተጀመረው ስልጠና፤ በአሁኑ ወቅት በ13 የተለያዩ የሙያ ዘርፎች ማለትም በ7 የተለያዩ የሆቴል የሙያ ዘርፎችና በ6 የቱሪዝም የተለያዩ ሙያዎች ከደረጃ 3 እስከ ደረጃ 5 እንዲሁም በዲግሪ መርሃ ግብር በሆቴልና በቱሪዝም ማኔጅመንት ስልጠና በመስጠት ላይ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡ በተገባደደው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ 17 ሺ 884 አስራ ሰባት ሺ ስምንት መቶ ሰማንያ አራት/ ባለሙያዎች በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በመደበኛ፣ በማታ ተከታታይ መርሃ ግብርና በአጫጭር ስልጠና በማሰልጠን ለዘርፉ ኢንዱስትሪ ዕድገትና የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፤ በማድረግ ላይም ይገኛል፡፡ ተቋሙ በእስከአሁን የስራ ዘመኑ፣ በገነት ሆቴል የማስፋፊያ ፕሮጀክት በማጠናቀቅ ተጨማሪ 36 የመማሪያ ክፍሎች፣ 13 የቤተ ሙከራ ክፍሎችና 5 የገላ መታጠቢያ፣ 16 የተለያዩ ቢሮዎችና 35 የወንድና የሴት መፀዳጃ ቤቶች በማስገንባት፣ የኮምፒውተር ቤተ ሙከራ ከተሟላ ከኢንተርኔት ጋር የተገናኘ ስልጠና እየተሰጠበት ይገኛል፡፡ እንዲሁም በተሟላ የመስተንግዶ ቤተ ሙከራ፤ በኮምፒውተርና በኢንተርኔት የተደገፈ የቱሪዝምና ሆቴል ቤተ ሙከራና የተሟላ የቤት አያያዝና ላውንደሪ ቤተ ሙከራ ውስጥ የተለያዩ የሆቴልና የቱሪዝም ሙያ ዘርፎች በማሰልጠን ላይ እንገኛለን፡፡
በተጨማሪም በ5 ሺ 474 የተለያዩ ወቅታዊ የማጣቀሻ መጻሕፍቶች፣ በ47 የኦዲዮ ቪዥዋል የትምህርትና ስልጠና መሣሪያዎች፣ የሙያ ብቃት ምዘና በመውሰድ ብቃታቸውን ባረጋገጡ ብቁ አሰልጣኞች /75% የሁለተኛ ዲግሪ/ ያላቸውና የሙያ ብቃት ምዘና በመውሰድ ብቃታቸውን ባረጋገጡ አሰልጣኞች ስልጠና የሚሰጥ ተቋም መሆኑን ጋዜጣው ልብ ሊለው ይገባል፡፡
ማሰልጠኛ ማዕከሉ የዘርፉ የሙያ ብቃት ምዘና ማዕከል ሆኖ ተመርጦ የምዘና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ይህም የሆነው ማሰልጠኛ ማዕከሉ ለዘርፉ ስልጠና የሚውል የተሟላ የስልጠና ግብአት፣ ቀልጣፋና ውጤታማ የሆነ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋቱ መሆኑን ማስገንዘብ እንወዳለን፡፡
ማዕከሉ ባሳለፍነው የ2007 የትምህርትና ስልጠና ዘመን የአሰልጣኞችን የማሰልጠን አቅም ለማሳደግ ከሞርሸስ፣ ከኬንያ፣ ከቻይና እንዲሁም ከዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በአገር ውስጥ የተለያዩ የሙያ ማሻሻያ ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡ የወቅቱ ሰልጣኞች ከነበሩት ውስጥ 98.26% ሰልጣኞች የሙያ ብቃት ምዘና በመውሰድና ብቃታቸውን በማረጋገጥ ወደ ኢንዱስትሪው እንዲቀላቀሉ ተደርገዋል፡፡
በተጨማሪ ማዕከሉ በሆቴልና ቱሪዝም ዙሪያ የሚያጠነጥኑ 15 ያህል ችግር ፈቺ ጥናታዊ ጽሑፎች በማዘጋጀትና በየዓመቱ 4 ጊዜ 1 ጥናታዊ ኮንፍረንስ በማካሄድ፣ ለዘርፉ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት እንዲዳረስ አድርጓል፡፡ የማማከር አገልግሎትን በተመለከተ ለተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ማለትም በሁሉም ክልላዊ መንግስትና ከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ በሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ለተሰማሩና ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ሙያዊ የማማከር አገልግሎት ሰጥቷል፤ በመስጠት ላይም ይገኛል፡፡
በአሁኑ ጊዜም አንጋፋነቱን ጠብቆ እየታደሰ ያለ ተቋም መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡ በያዝነው የትምህርትና ስልጠና ዘመን በመደበኛ፣ በማታ ተከታታይ ትምህርት ከደረጃ 3 እስከ ደረጃ 5 እንዲሁም በዲግሪ መርሃ ግብር ከ2000 በላይ ሰልጣኞች በሜክሲኮ ካምፓስና በገነት ካምፓስ በማሰልጠን ላይ ይገኛል፡፡ እንዲሁም በአገር ደረጃ በዘርፉ የተሰማራውን የሰው ኃይል ያለበት ደረጃና ለቀጣይ አምስት ዓመታት ለኢንዱስትሪው የሚያስፈልገውን የሰለጠነ የበቃ የሰው ኃይል ፍላጐት የሚያመላክት ደረጃውን የጠበቀ የዳሰሳ ጥናታዊ ጽሑፍ ለባለድርሻ አካላት አቅርበዋል፡፡
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት አገራዊ ተልዕኮና ኃላፊነትን እየተወጣ ያለውን ተቋም ጋዜጣው ባወጣው ዘገባ፤ በማሰልጠኛ ማዕከሉ፡-
የሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ማዕከል የ5 ሚሊዮን ብር አስደናቂ ድራማ
በ8 የቆርቆሮ ክፍሎች ያለ መማሪያ መጽሐፍ
የማሰልጠኛ ክፍሎችን አድሳለሁ ብሎ በቦምብ የታረሱ እያስመሰለ
የኢንተርኔት መስመር መዘርጋት ያቃተው
መጽሐፍ ብርቅ የሆነበት ተቋም
ኮምፒውተር የለም
ማሰልጠኛ ተቋሙ ለስልጠና ጉዳዮች ሳይሆን ለአስተዳደራዊ ጉዳዮች ነው ትኩረት የሚሰጠው
የመኝታ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው ገነት ሆቴል፤ በ5 ሚሊዮን ብር ወጪ ተቦዳድሶ በዝናብ እየተበላሸ፣ ሙጃ እየወረረው የጥንት ዘመን ፍርስራሽ መስሎ አረፈው…
በሚል ያልተገባ፣ ሚዛናዊነቱንና ወቅታዊነቱን ያልጠበቀ ጽሑፍ ማውጣቱን እናሳውቃለን፡፡  
(የሆቴልና የቱሪዝም
ሥራ ማሰልጠኛ ማዕከል)

ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት በቅሎ ስለማንነቷ ጌታዋን ጠየቀች፡፡
“ስላንቺ ማንነት ለማወቅ አንድ ቀላል ጥያቄ ብቻ እጠይቅሻለሁ”
“ምን? ይጠይቁኝ”
“እሺ፡፡ ከእኔ ጋር እስከነበርሽ ድረስ ምን አገልግሎት ስትሰጪኝ ነበር?”
“ያው ሁልጊዜ የማደርገውን ነዋ!” ስትል መለሰች
ጌትዬውም፤
“እኮ ምን?”
“ከአገር አገር እየሰገርኩ እርስዎን ያሻዎ ቦታ ማድረስ”
“መልካም፡፡ እንደዛ ከሆነ መስገር የማን ሥራ ነው ብለሽ ታስቢያለሽ?”
“የፈረስ”
“እንግዲያው አባትሽ ፈረስ ነው”
“ስለዚህ ፈረስ ነኝ ማለት ነዋ!” አለች እየፈነጠዘች፤ “በቃ ለእንስሳት ሁሉ እነግራቸዋለሁ” ብላ ሄደች፡፡
አንድ ቀን ግን ጌታዋ በጠዋት ወደሚቀጥለው ከተማ በርካታ ስልቻ እህል ይዞ መሄድ ነበረበትና ብዙ አህዮች ጭኖ ሲያበቃ፤ የተረፉትን ስልቾች በቅሎዋ ላይ ቀርቅቦ ጫነ፡፡
ይሄኔ በቅሎዋ፤
“ምነው ጌታዬ፤ እንደ ፈረስ እየሠገርሽ የምትሄጂ፤ የፈረስ ልጅ ነሽ ሲሉኝ ቆይተው አሁን እንደ አህያ እንዴት ይጭኑኛል” ስትል ጠየቀች፡፡
ጌትዬውም፤
“በአባትሽ ፈረስ ብትሆኚም፤ በእናትሽኮ አህያ ነሽ፤” አላት፡፡
ቁርጧን ያወቀችው በቅሎ፣ ሸክሟን ይዛ መንገዷን ቀጠለች፡፡
*   *   *
ሀገራችን ሥር ነቀል ለውጥ (Transformation) ያስፈልጋታል ካልን “ማ ቢወልድ ማ?” የሚል አካሄድ ሳይሆን ጠንካራ የሥራ ባህልና የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ እንዲሁም ጽኑ ሥነልቦናዊ እመርታ ያስፈልጋታል፡፡ ይህም በፈንታው ዕውቀት ላይ የተመሠረተ አስተሳሰብና ሙያዊ ብቃትን ይጠይቃል፡፡ ማንነታችን ለውጥን ማገዣ መሰላል እንጂ በራሱ ግብ ስላይደለ እየደጋገምን በአባቴ ፈረስ በእናቴ አህያ የምንልበት ዘመን አይደለም፡፡ ዕድገትን ለማምጣት የሥራ ባህላችንና የአምራችነት ብርታታችን ነው ወሳኙ፡፡ ሁሉም ሰው የፖለቲካ ኮርቻ ላይ ለመፈናጠጥ የሚሽቀዳደም ከሆነ የሚሠሩ እጆች ይዝላሉ፡፡ ጠንካራ መንፈሶች ይዳከማሉ፡፡ ሀገር ተስፋ ታጣለች፡፡
ዛሬ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ግልጽነትና ተጠያቂነት አስፈላጊነቱ ጉልህ ነው፡፡ በቃል ሳይሆን በተግባር መፈተሽ አለበት፡፡ ከቀን ቀን የተጠራቀመው ብሶቶች ወይ መተንፈሻ ወይ መፈንጃ ቅጽበትና ቦታ መሻታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ሰበቦቹ ምንም ይሁኑ ምን እንዳመረቀዘ ቁስል መፈንዳታቸው አሊያም ካንሰር አከል በሸታ መሆናቸው ሁሌም የሚታይ ገሀድ ክስተት ነው፡፡ ያ ደሞ ለጊዜው ሳይሆን ለዘለቄታው አስጊ ነው፡፡
በዚህ ላይ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንደሚወራው አለመሆናቸው ፍተሻን ይፈልጋል፡፡ ዲሞክራሲ “የሚታይ እንጂ የማይበላ ፍሬ” እንደሚባለው አይደለም፡፡ ፓርቲ እንደፈለገው የሚቃኘው (guided democracy) የፖለቲካው መነጋገሪያ መድረክም ሆነ የመጫወቻ ሜዳው እንዲሁም የአጨዋወት ሕጉ ተሳታፊ ቡድኖችን ተስፋ የሚያስቆርጥ መሆን የለበትም፡፡ ለጊዜው ያሸነፍን የሚመስለን ግጥሚያ ሁሉ በረዥሙ ሲታይ ዲሞክራሲን የሚያቀጭጭ ሆኖ ይገኛል፡፡ ያ በፈንታው “አንድ ወደፊት ሁለት ወደ ኋላ” መሄድን ያመጣል፡፡ ዞሮ ዞሮ ጣጣው ላገር የሚተርፍ ጐጂ ባህል ነው፡፡ ኢ-ፍትሐዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል አሟጋች ኢኮኖሚያዊ ዝንፈትን፣ ውሎ አድሮም ምሬትን መውለዱ በዐይን የሚታይ ሀቅ ነው፡፡ የፈጠጠ ሙስና ውስጥ የተዘፈቀ ሥርዓተ - ኢኮኖሚ፣ ሹሞች ከማስወገድ ያለፈ ማስተካከያ ይፈልጋል፡፡ ህዝብ የሚያየውን እንከን ያለሥጋት በግልጽ እንዲናገር የማሪያም መንገድ ሊሰጠው ይገባል፡፡
ችግሮች ሲተሳሰሩ አንዱ አንዱን ይዞ ይወድቃል፡፡ እኛንም ይዞ ይወድቃል፡፡ (Domino Effect እንዲሉ) ሁሉም ወደየወገኑ እየዞረ አገር ሊጠብ አይገባውም፡፡ እንዲያ ከሆነ የሙስናው መረብ በተቃራኒው ይሰፋልና፡፡ የአሁኑ ዘመን የሙሰኞች መረብ “አዞው ወደ ውሃ ሲስብ ጉማሬው ወደሳር ይስባል” የሚለው ተረት ዓይነት ሆኗልና፤ ሁሉ ወደየራሱ ገመዱን እየጐተተ መሆኑን የሚመለከተው የመንግሥት አካል ዐይኑን ከፍቶ ይመልከት!  

ገቢው ከኤክስፖርትና ከለጋሾች ከተገኘው በላይ ነው

   በተገባደደው የፈረንጆች አመት 2015 በአለም ዙሪያ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵውያን ወደ አገር ውስጥ የተላከው ገንዘብ 3.7 ቢሊዮን ዶላር መድረሱንና፣ ይህም በዘርፉ ክብረወሰን የተመዘገበበት እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስታወቀ፡፡
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዲያስፖራ መረጃና ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደመቀ አጥናፉን ጠቅሶ ኤፒኤ እንደዘገበው፣ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ይህን ያህል ገንዘብ አግኝታ የማታውቅ ሲሆን፣ ገንዘቡ  በአመቱ ከወጪ ንግድና ከውጭ አገራት ለጋሾች ከተገኘው በላይ እንደሆነ ተረጋግጧል፡፡
ህንድ በ2014 ብቻ ከዘርፉ 70 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቷን የጠቀሱት አቶ ደመቀ፤ ኢትዮጵያ በዘርፉ የምታገኘው ገቢ አሁንም አነስተኛ መሆኑን ጠቁመው፣ ከዘርፉ የሚገኘውን በቀጣይ አመታት ለማሳደግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

    የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ የኢትዮጵያ፣ የግብጽና የሱዳን ሚኒስትሮች በቀጣዩ ሳምንት በሱዳን ካርቱም ያደርጉታል ተብሎ ለሚጠበቀው የቀጣይ ዙር የሶስትዮሽ ድርድር ዝግጅት ለማድረግ በሚል የውጭ ጉዳይና የመስኖ ሚኒስትሮቻቸውን ከትናንት በስቲያ ሰብስበው ማወያየታቸውን አሃራም ኦንላይን ዘገበ፡፡
ፕሬዚዳንቱ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪና ከመስኖ ሚኒስትር ሆሳም ሞጋዚን ጋር ባደረጉት ውይይት፣ በሶስቱ አገራት መካከል የሚደረጉት ውይይቶች የሁሉንም አገራት መብቶች የሚያስከብር የጋራ መግባባት ላይ የሚያደርሱ ሊሆኑ ይገባል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
ግብጽ የኢትዮጵያውያንን ተገቢ የልማት ፍላጎት ከግምት ውስጥ ታስገባለች፤ የልማት ጥረቶች ግን የግብጻውንን መብቶች ከግምት ውስጥ ያስገቡ መሆን አለባቸው፣ ምክንያቱም አባይ ለግብጽ ብቸኛው የውሃ ምንጭ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
ግብጽና ሱዳን የታላቁ ህዳሴ ግድብ መገንባት በታችኛው የተፋሰሱ አገራት የውሃ ድርሻ ላይ ተጽዕኖ የማያሳድር መሆኑን ለማረጋገጥ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ላለፉት 16  ወራት ያህል ተከታታይ ውይይቶች ሲያደርጉ መቆየታቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡

Saturday, 19 December 2015 11:49

“የተረገመ አዙሪት”

ሰላማዊ ተቃውሞ፣ ከፖሊስ ጋር ግጭት፣ ከዚያ ረብሻና እስር፣ ቃጠሎና ግድያ... ከዚህ አሳዛኝ የጥፋት ሰንሰለት መላቀቅ ያቃተን፤ መውጫ የሌለው አዙሪት የሆነብን ለምንድነው?
እንዲህ አይነት ቀውስ በተፈጠረ ቁጥር፤ መንግስት እየደጋገመ የሚናገረው ነገር አለ። ቅሬታዎችን ማቅረብ፣ ተቃውሞን በሰላም መግለፅ፣ ተፈጥሯዊ መብት ነው ይላል - ሁልጊዜ። እና፤ መንግስት ይህንን መብት ከምር የሚያከብር ከሆነ፤ ለምን... ሰላማዊ ተቃውሞ ወደ ረብሻና ግድያ ይሸጋገራል?
በየጊዜው የሚፈጠሩ ቅሬታዎችንና ተቃውሞዎችን፣ አንድ በአንድ በቀጥታ እያስተናገደ ምላሽ ለመስጠትና ለማስተካከል ቢተጋ ኖሮ፤ ችግሮችን ለመፍታት ከማገዝ አልፎ፤ ረብሻ የማይነካካው ሰላማዊ  ተቃውሞ እንዲለመድ ይረዳ ነበር፡፡
መንግስት ይህንን ሃላፊነቱን አልተወጣም፡፡ ስልጡን የፖለቲካ ባህል እገነባለሁ እያለ ለአመታት ቢናገርም፤ ከነባሩ አዙሪት አልወጣንም፡፡
ነገር ግን፤ መንግስት፣ ሰላማዊ ተቃውሞን ለማስተናገድ ጨርሶ የማይፈልግ ቢሆንም እንኳ፣ በዚህም ሃላፊነቱን ባለመወጣት ዋና ተጠያቂ ቢሆንም እንኳ፣ እኛስ በራሳችን አቅም፣ ሰላማዊ ተቃውሞ ወደ ብጥብጥ እንዳያመራ መከላከል አንችልም?
መቼም፣ አብዛኛው ሰው፣ ጨዋ ነው። የተቃውሞ ድምፅ ለማሰማትና አቤቱታ ለማቅረብ፣ ወደ አደባባይ የሚወጡ ብዙዎቹ ሰዎችም፣ በአመዛኙ የሰውን ሕይወትና ንብረት ለመጉዳት አይፈልጉም። ታዲያ፣ ለምንድነው በየጊዜው፣ እንዲህ አይነት ቀውስ የሚፈጠረው?
እዚህ ላይ ችግር አለ። አብዛኞቹ ሰዎች  ጨዋ ቢሆኑም፣ የሰውን ሕይወትና ንብረት ለመንካት ፍላጎት ባይኖራቸውም፤ በሰላማዊ ተቃውሞ መሃል፤ ዝርፊያንና ጥቃትን ለማስቆም ይቸገራሉ። በሌላ አነጋገር፤ መዝረፍና ማቃጠል ለሚፈልግ ሰው ‘ጥሩ’ አጋጣሚ ይሆንለታል። ከዚያም አልፎ ራሱን፤ ‘ዋና የነፃነት ታጋይ፣ ዋና ተቆርቋሪ፣ ዋና ተወካይ’ አስመስሎ ስለሚሾም፣ ‘ተው የሰው ንብረት አትዝረፍ፣ አታቃጥል’ ብለን በድፍረት አንጋፈጠውም። እንዲያውም፣ አለቃ ወይም መሪ ይሆንብናል።
አንድ መጥፎ ሰው፤ ነገሩን ሁሉ የሚረብሽብን፤ አድራጊ ፈጣሪ የሚሆንብንና ወደ ጥፋት አቅጣጫ የሚመራን፣ አለምክንያት አይደለም። እሱን ለመገሰፅና ለማረም ከሞከርን፤ ‘ከሃዲ፣ ሰርጎ ገብ፣ ተብለን አጣብቂኝ ውስጥ እንዳንገባ እንሰጋለን፡፡ ‘ከሃዲ... ያዘው፣ ፈንክተው’ ብሎ ቢያነሳሳብን፣ በዚያ ግርግር መሃል፣ ምን ሊፈጠር እንደሚችልና ምን ሊደረስብን እንደሚችል ለመገመት ያስቸግራል። “ወደ ጥፋት መንገድ አንሄድም፤ ሰላማዊ ተቃውሟችንን አትረብሽብን” የሚል ትችትንም ሆነ ተግሳፅ መስማት፣ እንደ ጥቃትና እንደ ሽንፈት ይቆጥረዋል - ትችታችን ትክክለኛና ተገቢ ቢሆንም እንኳ። ግን፣ እንዲያው፣ ትችታችን ተገቢ ባይሆንስ? ትችት ስለተሰነዘረበት ብቻ... “ያዘው ፈንክተው”...?
ይሄማ፣ አምባገነን መንግስት ከሚፈፅመው አፈናና ረገጣ በምን ይለያል?
አዙሪቱ ይህንን ይመስላል።
የመንግስት ጭፍን ፕሮፖጋንዳንና ጥፋትን፣ አፈናንና ጉልበተኝነትን ለመቃወም፤ እንከን የሌለው ትክክለኛና ጥርት ያለ ሰላማዊ ተቃውሞ ለማሰማት ብንችል እንኳ፤ እዚያው ከመሃላችን አንድ ሁለት መጥፎ ሰው አይጠፋም። ስልጣን ባይኖረውም፣ ትንሽ “አምባገነን ሊሆንብን ይሞክራል፡፡ እሱ ከሚነግረን ወሬ ውጪ፤ ለየት ያለ አንዳች መረጃ መስማት ያንጨረጭረዋል፡፡ አንዳች የተለየ የአስተያየት አማራጭ ለማየትም አይፈልግም። አለመፈለግ ብቻ አይደለም፡፡ በከሃዲነት እንድንፈረጅ ማድረግ እንደሚችል ያውቃል፡፡ እናም ጭፍን ስሜትን በማራገብና በአሉባልታ፣ በዛቻና በጉልበት፣ ዙሪያውን ‘ዝም’ በማሰኘት፣ አለቃና መሪ ሆኖ ያርፈዋል፡፡ እንደዚህ አይነት ሰው እንደሚኖር ስለምናውቅና ስለምንሰጋም ነው፤ ጭፍን ስሜቶችንና መጥፎ ድርጊቶችን ለማስቆም ብዙም ለመጣር የማንነሳሳው። እናም፤ ሰላማዊው ተቃውሞ፣ በአንድ በሁለት ሰው ተረብሾ ወደ ግርግር ይቀየርብናል። ይሄ አንደኛው ምክንያት ነው፡፡
ሁለተኛው ምክንያትስ?
የተቃውሞ ድምፃችንን ለማጉላላትና እንዳይደበዝዝ መመኘት ተገቢ ቢሆንም፤ ለዚህ በትጋት ከመጣጣር ይልቅ፣ ወደ “ቀላል” የአቋራጭ መንገድ ካዘነበልን፣ ለስህተት እንጋለጣለን፡፡ እንዴት በሉ፡፡  
አንደኛ ነገር፤ የተቃውሞ ድምፅን የሚያበርድና የሚያደበዝዝ ከመሰለን፣ እውነተኛ መረጃንና ምክንያታዊ አስተያየትንም ጭምር ችላ ብለን፣ ሰምተን እንዳልሰማን እናልፋለን። [ከድካምና ከጥረት የሚገላግል አቋረጭ መንገድ ያገኘን ይመስለናል። ግን፤ መዘዝ አለው። በዚሁ ምክንያት፣ አስተዋይ፣ ብልህና ቀና ሰዎችን እያገለልን እንደምንሄድ አናውቅም]። ይህም ብቻ አይደለም።
የተቃውሞ ድምፅን ለማማሟሟቅና ለማድመቅ የሚረዳ እስከመሰለን ድረስ፣ ተገቢ ላልሆኑ ነገሮችም ጭምር ቦታ መስጠት እንጀምራለን፡፡ ለምሳሌ፤ አንድ ሁለት ሰዎች በጭፍን የሚያስተጋቡትን የውሸት መረጃም ሆነ የጥፋት አዝማሚያ፣ ለማስተካከልና ለማረም ከመሞከር ይልቅ፣ አይተን እንዳላየን ማለፍ ይቀለናል። [ለጊዜው፣ ‘ቀላል’ ነው። ነገር ግን፣ እነዚያ በጭፍን ስሜት የተዋጡ አንድ ሁለት ሰዎች፣ ራሳቸውን አለቃና መሪ አድርገው በእኛው ላይ እንዲሾሙ፣ እድል እንከፍትላቸዋለን።] ለዚህም ነው፤ በመጀመሪያው ቀንና በማግስቱ፣ ሰላማዊ የነበረው የተቃውሞ ድምፅ፣ ቀስ በቀስ በረብሻ እየተዋጠና እየተወረሰ እንዳይሄድ ለመከላከል የምንቸገረው።
አንዴ መበላሸት ከጀመረ በኋላ ደግሞ፤ እየከበደና እየተባባሰ ይቀጥላል፡፡
ጭራሽ፣ ‘ይሄ አገር ወዴት እያመራ ነው?” የሚል ጥርጣሬ እስኪያድርብን ድረስ፣ አገር ምድሩ ይቀወጣል። “የተሻለ ነገር ያስገኝ ይሆናል” ብለን የጀመርነው ነገር፤ ከቀድሞው ወደ ባሰ ውጥንቅጥ እንዳያወርደን መስጋት ይመጣል። ያኔ፤ ለጉልበተኛ ባለስልጣን፣ መንገዱ ተመቻቸለት።
ከሰላማዊ ተቃውሞ ይልቅ፣ ረብሻ የሚመቻቸው ባለስልጣናት አሉ። ለምን? አሃ፤ ጥያቄዎችንና ትችቶችን የማስተናገድ ጣጣን ያስቀርላቸዋል፡፡ ሰላማዊ ተቃውሞ በረብሻ ከተወረሰ… በቃ፤ በማንኛውም መንገድ፣ (በፕሮፓጋንዳ፣ በዛቻና በጉልበት)... ሁሉንም ሰው ፀጥ ለማሰኘት፣ በቂ ሰበብ ይሆንላቸዋል። በሕይወት እና በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሱ ሰዎችን ብቻ በህግ ከመዳኘት ይልቅ፤ በዚህችው አጋጣሚና ሰበብ፣ አገሬውን ሁሉ ዝም ለማሰኘት፣ የትችትና የተቃውሞ ድምጽን ጨርሶ ለማጥፋት ይሞክራሉ።
ፕሮፓጋንዳውን፣ አፈናውን፣ ጉልበተኝነቱን፣ ከቀድሞው የባሰ ለማድረግ የሚጠቅም ማመካኛ ይሆንላቸዋል - ረብሻው። ጥያቄዎችን፣ አቤቱታዎችንና ትችቶቸን እያስተናገዱ፣ ስህተቶችን ለማስተካከልና ጥፋቶችን ለማረም ከመትጋት ይልቅ፤ ሁሉንም ሰው ዝም ማሰኘት  ይቀላቸዋል። ለጊዜው፣ ‘ቀላል’ ይመስላል። ግን፤ መፍትሄ አይሆንም። ባለስልጣናትና መንግስታት፣ በሰበብ አስባቡ፣ ‘ገናና’ እየሆኑ መሄድ፤ “ቀላል” መስሎ ቢታያቸውም፤  ብዙም አያዛልቅም። ቢሆንም ግን፤ ሰበብ ተገኘ ተብሎ፣ ‘ገናና’ ለመሆን መሯሯጥ፤ በየአቅጣጫውና የየጊዜው፣ በተደጋጋሚ የሚታይ፣ የተለመደ የበርካታ ባለስልጣናት  ባህርይ ነው። ቀውስ በተፈጠረ ቁጥር፤ ለቀውሱ ሁነኛ መፍትሔ ከማበጀት ይልቅ፤ በዚያ ሰበብ፤ ከዜጐች ላይ ገናና ለመሆን ይገለገሉበታል፡፡
በአገራችን ብቻ ሳይሆን፤ ደረጃው ቢለያይም፣ በሁሉም አገራት፣ የዘመናችን ሦስቱ ዋነኛ አለማቀፍ የቀውስ ምንጮችን ተመልከቱ።
በመንግስት እልፍ ቁጥጥሮችና ጫናዎች ሳቢያ የሚፈጠር “የቅይጥ ኢኮኖሚ ቀውስ”፣ በአለም ዙሪያ፣ ከድሃ እስከ ሃብታም አገራት፤ ሁሉንም እያናወጠ አይደል? ግን፤ ጥፋተኞቹ መንግስታት ብቻ አይደሉም፡፡ እኛም እንተባበራቸዋለን፡፡
በአንድ በኩል፤... የግል ኢንቨስትመንትንና ቢዝነስን፣ የግል ስኬትንና ብልፅግናን፣ በአድናቆትና በአርአያነት ለማየት የሚቸገር ኋላቀር ባህል በአገራችን ሞልቷል። በሌላ በኩል ደግሞ፤... በዚህም በዚያም በአየር ባየር አልያም በሙስና፣ በድጐማም ሆነ በልዩ ድጋፍ ... (ያለ ስራ እና ያለ ጥረት) ሃብት ለማግኘትና ተጠቃሚ ለመሆን መዋከብም የተለመደ ነው፡፡ እነዚህ አዝማሚያዎች፤ በብዙ ዜጐች ዘንድ የሚታዩ ስህተቶች ናቸው፡፡ የመንግስት ምላሽስ?
መንግስት፤ ቢዝነስን የሚያናንቅን ባህል ለመግታትና የአየርባየር ወከባን ለማስተካከል ከመጣር ይልቅ ወደ ነፃ ገበያ ስርዓት ለመጓዝ ከመትጋት ይልቅ፤ በዚሁ ሰበብ፤ ከነአካቴው ቢዝነስንና ነፃ ገበያን በእንጭጩ የሚቀጭ፣ የዋጋ ቁጥጥርና የዋጋ ተመን፣ የገደብና የክልከላ፣ የታክስ ጫናና የመዋጮ ዘመቻ ማካሄድ ቀላል ይሆንለታል።
ያው፤ ቢዝነስ ሳይስፋፋ ደግሞ፣ ከስራ አጥነትና ከድህነት መላቀቅ አይቻልም። አሳዛኙ ነገር፤ በስራ አጥነትና በድህነት እየተማረርን፣ ለዚህ ችግር መፍትሄ እንዲፈለግለት ‘ድማፃችንን ለማሰማት’ አደባባይ ብንወጣ፤ ከሁሉም በላይ ጎልቶ የሚወጣው ድምፅ፣ “የሸቀጦች የዋጋ ቁጥጥር ይደረግ”... የሚል መፈክር ይሆናል።
መንግስት ይህንን አግኝቶ ነው?
በዚሁ ሰበብ፤ ቢዝነስ ላይ፣ ተጨማሪ ጫናና ቁጥጥር በማወጅ፣ ይበልጥ የመንግስትን ገናናነት ለማግዘፍ የሚመኝ ባለስልጣን፣ እንደሚኖር አትጠራጠሩ። በግል ኢንቨስትመንትና በቢዝነስ ላይ ጭፍን ጥላቻን እያራገብን፣ መንገዱን ለመንግስት አመቻቸንለት ማለት ነው። እናም፣ ቢዝነስ እየተደናቀፈ፤ ከስራ አጥነትና ከድህነት ጋር እንደተቆራኘን እንቀጥላለን።
አዙሪት ነው። ለኛ አይበጅም። ለመንግስትም አያዛልቀውም። ቢዝነስን እየገታ፣ ‘ገናና’ መሆን፣ ውሎ ሲያድር መዘዙ እየከፋ ይሄዳል። በጊዜ ካልባነነ፣ መውደቂያው ይሆናል።
ሁለተኛና ሦስተኛ የቀውስ ምንጮች፤ የሃይማኖት አክራሪነትና የዘረኝነት አባዜዎች ናቸው፡፡ በአንድ በኩል፣ መንግስታት፣ የአክራሪነት ሽብርንና የዘረኝነት ግጭትን በቀጥታ ከመከላከል ይልቅ፤ በዚሁ ሰበብ፣ የዜጎችን ቅሬታ፣ ትችትንና ሰላማዊ ተቃውሞን አፍነው ዝም ለማሰኘት፣ ይጠቀሙበታል። በአገሬው ላይ ‘ገናና’ ለመሆን፣ አስተማማኝ ማመካኛ ይሆንላቸዋል። “አገርን ከሽብር ለመታደግ፤ ሕዝብን ከዘረኝነት እልቂት ለማዳን”...እያሉ፤ ያሻቸውን ነገር ለማድረግ ይሞክራሉ።
አሳዛኙ ነገር፤ እኛም፣ እንመቻችላቸዋለን። የተቃውሞ ድምፅን ለማድመቅ የሚጠቅም እየመሰለን፣ ወይም ደግሞ የተቃውሞ ድምፅ እንዳይደበዝዝ በመስጋት፣... በፅናትና በትጋት ትክክለኛ መላ ከማበጀት ይልቅ፤ ሃይማኖትንና ተወላጅነትን ከፖለቲካ ጋር የማደበላለቅ አዝማሚያ፣ አቋራጭ መፍትሄ ሆኖ ይታየናል፡፡ ወይም “ጊዜያዊ ችግር ነው” ብለን በቸልታ እንቀበለዋለን።
በዚሁ አዝማሚያ ለመንሸራተት፣ አእምሯችን ፈቃደኛ ባይሆን እንኳ፤ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችን... አክራሪነትንና ዘረኝነትን የሚያስተጋቡ መጥፎ ሰዎችን በዝምታ ለማለፍ፣ ወይም እንደ ጊዜያዊ ችግር አይተን ቸል ለማለት ይዳዳናል። ነገር ግን፣ አንድ ሁለት ሰው የሚያስተጋባው የዘረኝነት ወይም የአክራሪነት መርዝ፣ ከጎናችን ተሰልፎ በዝምታ ስናልፈው፤... ለአፍታ በአዳማቂነት አገልግሎ፣ በራሱ ጊዜ የሚከስም፣ ተራ ችግር አይሆንልንም።
በተገላቢጦሽ፣ ዋና ጉዳያችንን ሁሉ ጠቅልሎ እየዋጠና እየቀበረ፣ ከመክሰም ይልቅ እየተግለበለበና እየተቀጣጠለ ለመስፋፋት እድል ያገኛል፡፡ ብዙም ሳይቆዩ፤ በሃይማኖት ተከታይነት ወይም በዘር ወደ ማቧደን ይሸጋገራሉ፤ ከዚያም በየፊናቸው የየቡዱኑ አለቃ፣... አድራጊ ፈጣሪ ይሆኑብናል።
እንዲህ፣ ነገር እየተበላሸ፣ አገሬው ወደ መናወጥ እያመራ፤ ብዙዎቻችን ‘የባሰ መጣ’ ብለን መስጋት ስንጀምር፤ መንግስት ምን ያደርጋል?
የአክራሪነትን ሽብር፣ የዘረኝነትን ግጭት እየተከላከለ፤ የዜጎችን ቅሬታና ሰላማዊ ተቃውሞ ለማስተናገድ፤ እንዲሁም... የዜጎችን ነፃነትና መብት ለማስከበር መትጋትና መጣር ይችላል። ግን፤ ይሄ አድካሚ ነው። ከዚያ ይልቅ፤ አክራሪነትንና ሽብርን፤ ዘረኝነትንና ግጭትን በመዋጋት ሰበብ፤ ቅሬታዎችንና ተቃውሞዎችን በሙሉ እያፈነ ‘አይነኬ ገናና መንግስት’ ለመሆን መሞከር ይቀላል።
በእርግጥ፤ ‘ቀላልነቱ’ ለአጭር ጊዜ ብቻ ነው። አፈናው ሲደራረብና የዜጎች እሮሮ ሲባባስ፤ ውሎ አድሮ፣ የተቃውሞ ድምፅ ግንፍል ብሎ መውጣቱ አይቀርም። ግን፤ ምን ዋጋ አለው? ያቺ ታፍና የነበረች የተቃውሞ ድምፅ፣ እንድትጎላ በመጓጓትና እንዳትደበዝዝ በመስጋት፤ መንግስትን የሚቃወም ማንኛውንም ነገር (አክራሪነትንና ዘረኝነትንም ጭምር...) የማስተናገድ አዝማሚያ ይሰፋል። የአቋራጭ መፍትሔ ምርኮኞች እንሆናለን፡፡
ያው፤ በበርካታ አገራት እንደታየው፤ የዜጎች የተቃውሞ ድምፅ፣ በአክራሪዎች ወይም በዘረኞች ድምፅ እየተዋጠ፣ ነገሩ ሁሉ ይቃወሳል። ብዙ ሰዎች በስጋት ይጨነቃሉ።
ያኔ፣ የመንግስት ስራ፣ አክራሪነትንና ዘረኝነትን መከላከል ሳይሆን፣ እግረመንገዱን አገሬውን በአፈናና በጉልበት ዝም ለማሰኘት መሯሯጥ ይሆናል። ኡደቱ ይቀጥላል። የታሪክ ጉዞ ሳይሆን፣ የታሪክ አዙሪት ውስጥ እየተሽከረከሩ፤ መከራን እየደጋገሙ ማየት!

     በብሩንዲ ሶስት ወታደራዊ ጣቢያዎች ላይ በመንግስት ተቃዋሚዎች በተፈጸመ ጥቃት በርካታ ዜጎች መሞታቸውን ተከትሎ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ዛይድ ራድ አል ሁሴን አገሪቱ ዳግም ወደ አስከፊ የእርስ በርስ ጦርነት እያመራች ነው ሲሉ ማስጠንቀቃቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገበ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብሩንዲ የተለያዩ አካባቢዎችና በመዲናዋ ቡጁምቡራ እየተባባሰ የመጣው ግጭት እንደሚያሳስባቸው የገለጹት አል ሁሴን፣ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ ለሶስተኛ ዙር የስልጣን ዘመን በምርጫ እንደሚወዳደሩ መግለጻቸው የቀሰቀሰው ቁጣ በተቃዋሚ ሃይሎችና በመንግስት ደጋፊዎች መካከል ለወራት የዘለቀ ግጭት መፍጠሩንና በርካታ ዜጎች መሞታቸውን አስታውሰዋል፡፡
የፖለቲካ መሪዎችና ከፍተኛ ባለስልጣናትን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትርጉም ያለውና አካታች የሆነ ውይይት በማድረግ በብሩንዲ የተከሰተውን ግጭት ለመግታትና አገሪቱን ከከፋ ጥፋት ለመታደግ እንዲንቀሳቀሱም ጥሪ አቅርበዋል።
ባለፈው ሳምንት አርብ እጅግ የከፋ የተባለ ግጭት መከሰቱንና በመዲናዋ ቡጁምቡራ በሚገኙ ሶስት ወታደራዊ ጣቢያዎች ላይ በመንግስት ተቃዋሚዎች በተፈጸመ ጥቃት 79 ያህል የመንግስት ተቃዋሚዎችና ስምንት ወታደሮች መሞታቸውን ዘገባው አስታውቋል፡፡
አገሪቱ ለረጅም አመታት ከዘለቀውና ከፍተኛ እልቂት ካስከተለው በጎሳ የተከፋፈለ የእርስ በርስ ጦርነት የወጣችው ከአስር አመታት በፊት እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ ፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ ስልጣናቸውን ለማራዘም ማሰባቸው የፈጠረው ተቃውሞና አመጽ፣ አገሪቱን ወደቀድሞው አስከፊ የእርስ በእርስ ጦርነት ሊያስገባት ይችላል የሚል ስጋት መፍጠሩን ገልጧል፡፡
ካለፈው ሚያዝያ ወር አንስቶ የተከሰተው ግጭት፣ በፕሬዚዳንቱ ላይ በተሞከረ ያልተሳካ መፈንቅለ መንግስት ሳያበቃ ተባብሶ መቀጠሉን የዘገበው ቢቢሲ፣ ከአመቱ መጀመሪያ አንስቶ በአገሪቱ ከ600 በላይ ሰዎች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውንና ከ220 ሺህ በላይ ዜጎችም አገራቸውን ጥለው መሰደዳቸውን አስታውሷል፡፡

- አንድ ጠርሙስ ኦክስጂን 27.99 ዶላር ይሸጣል

በቻይና የአየር ብክለት እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ፣ ቪታሊቲ ኤር የተሰኘው የካናዳ ኩባንያ ከተራሮች ላይ ተወስዶ በጠርሙስ የታሸገ ንጹህ አየር ለቻይናውያን እየሸጠ እንደሚገኝ ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
በዚህ ወር መጀመሪያ የቻይና የአየር ብክለት መጠን ከፍተኛው ደረጃ ላይ መድረሱንና ለጤና ጎጂ መሆኑ ታምኖበት በመዲናዋ ቤጂንግ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉና የግንባታ ስራዎች እንዲቋረጡ መደረጉን ያስታወሰው ዘገባው፣ ቪታሊቲ ኤር የተሰኘው የካናዳ ኩባንያም ከሰሞኑ የታሸገ አየር ለቻይና ማቅረብ መጀመሩን ገልጧል፡፡
ኩባንያው ፕሪሚየም ኦክስጂን በሚል አሽጎ የሚሸጠው ንጹህ አየር በጠርሙስ 27.99 ዶላር እየተቸበቸበ ነው ያለው ዘገባው፣ የኩባንያው ተወካይም ገበያው እንደደራላቸውና ምርቱ በቻይና ገበያ ውስጥ ከፍተኛ ተፈላጊነት ሊያገኝ መቻሉን መናገራቸውን አስታውቋል፡፡
የኩባንያው ተወካይ ሃሪሰን ዋንግ እንዳሉት፤ ኩባንያው በመጀመሪያ ዙር ለቻይና ገበያ ያቀረበው 500 ጠርሙስ የታሸገ ንጹህ አየር ተሸጦ ያለቀ ሲሆን፣ ተጨማሪ 700 ጠርሙስ የታሸገ ንጹህ አየርም በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ቻይና ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

     በብሩንዲ ሶስት ወታደራዊ ጣቢያዎች ላይ በመንግስት ተቃዋሚዎች በተፈጸመ ጥቃት በርካታ ዜጎች መሞታቸውን ተከትሎ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ዛይድ ራድ አል ሁሴን አገሪቱ ዳግም ወደ አስከፊ የእርስ በርስ ጦርነት እያመራች ነው ሲሉ ማስጠንቀቃቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገበ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብሩንዲ የተለያዩ አካባቢዎችና በመዲናዋ ቡጁምቡራ እየተባባሰ የመጣው ግጭት እንደሚያሳስባቸው የገለጹት አል ሁሴን፣ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ ለሶስተኛ ዙር የስልጣን ዘመን በምርጫ እንደሚወዳደሩ መግለጻቸው የቀሰቀሰው ቁጣ በተቃዋሚ ሃይሎችና በመንግስት ደጋፊዎች መካከል ለወራት የዘለቀ ግጭት መፍጠሩንና በርካታ ዜጎች መሞታቸውን አስታውሰዋል፡፡
የፖለቲካ መሪዎችና ከፍተኛ ባለስልጣናትን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትርጉም ያለውና አካታች የሆነ ውይይት በማድረግ በብሩንዲ የተከሰተውን ግጭት ለመግታትና አገሪቱን ከከፋ ጥፋት ለመታደግ እንዲንቀሳቀሱም ጥሪ አቅርበዋል።
ባለፈው ሳምንት አርብ እጅግ የከፋ የተባለ ግጭት መከሰቱንና በመዲናዋ ቡጁምቡራ በሚገኙ ሶስት ወታደራዊ ጣቢያዎች ላይ በመንግስት ተቃዋሚዎች በተፈጸመ ጥቃት 79 ያህል የመንግስት ተቃዋሚዎችና ስምንት ወታደሮች መሞታቸውን ዘገባው አስታውቋል፡፡
አገሪቱ ለረጅም አመታት ከዘለቀውና ከፍተኛ እልቂት ካስከተለው በጎሳ የተከፋፈለ የእርስ በርስ ጦርነት የወጣችው ከአስር አመታት በፊት እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ ፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ ስልጣናቸውን ለማራዘም ማሰባቸው የፈጠረው ተቃውሞና አመጽ፣ አገሪቱን ወደቀድሞው አስከፊ የእርስ በእርስ ጦርነት ሊያስገባት ይችላል የሚል ስጋት መፍጠሩን ገልጧል፡፡
ካለፈው ሚያዝያ ወር አንስቶ የተከሰተው ግጭት፣ በፕሬዚዳንቱ ላይ በተሞከረ ያልተሳካ መፈንቅለ መንግስት ሳያበቃ ተባብሶ መቀጠሉን የዘገበው ቢቢሲ፣ ከአመቱ መጀመሪያ አንስቶ በአገሪቱ ከ600 በላይ ሰዎች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውንና ከ220 ሺህ በላይ ዜጎችም አገራቸውን ጥለው መሰደዳቸውን አስታውሷል፡፡