Administrator

Administrator

በሚችሉት ሁሉ ሀገራቸውንና አፍሪካን ያገለገሉ፣ በአቋማቸው ጽኑ፣ ሕዝቦችን ለማቀራረብ የተጉ፣ እውነት ነው ብለው ያመኑትን የትምና መቼም የሚናገሩ ነበሩ።
እንዲህ ዓይነት ብርቱ ሽማግሌዎችን ማጣት ጉዳቱ ለሀገር ነው። ፈጣሪ ነፍሳቸውን ይቀበላት።

አሚጎስ የገንዘብ ቁጠባና ብድር የህብረት ሥራ ማህበር፣ በ2016 በጀት ዓመት 145 ሚሊዮን ብር ባጠቃላይ ማትረፉንና ከ101 ሚሊዮን ብር በላይ የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡ የማህበሩ አባላት የትርፍ ክፍፍል ድርሻ 53 በመቶ ነው ተብሏል፡፡
አሚጎስ ይህን ያስታወቀው ባለፈው ቅዳሜ ታሕሳስ 19 ቀን 2017 ዓ.ም፣ 11ኛ የባለአክስዮኖች ዓመታዊ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በኢንተር ላግዠሪ ሆቴል ባካሄደበት ወቅት ነው፡፡
ለግማሽ ቀን በተካሄደው በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የ2016 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻፀም ሪፖርት የቀረበ ሲሆን፤ በበጀት ዓመቱ ማህበሩ 145 ሚ ብር ማትረፉንና ከ101 ሚ. ብር በላይ የተጣራ ትርፍ ማግኘቱ ተነግሯል፡፡ የማህበሩ ጠቅላላ ሃብቱም 3 ቢሊዮን ብር ደርሷል ተብሏል፡፡
ተደራሽነትንና የአባላት የአገልግሎት አሰጣጥ እርካታን ለመጨመር አሚጎስ  የቅርንጫፍ ቢሮዎችን በማብዛት፣ለአባላት ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እንዲቻል ጥናቶችን እያካሄደ እንደሚገኝ ተገልጿል።  ማህበሩ፣ በተለያዩ ሀገራት እያደረጋቸው ያሉ የልምድ ልውውጦችና የስራ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተም ገለፃ ተደርጓል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ አሚጎስ የ12ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በተለያዩ ኹነቶች ባለፈው ቅዳሜ ያከበረ ሲሆን፤ ለስኬታማ የማህበሩ አባላት የዋንጫ ሽልማትና ዕውቅና ተሰጥቷል፡፡ በኢንተር ላግዠሪ ሆቴል በተከበረው የማህበሩ የ12ኛ ዓመት የምስረታ ክብረ በዓል ላይ የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ሽጉጤ፣ ምክትል ኮሚሽነር አቶ አብዲ ሙሃድ እንዲሁም የአዲስ አበባ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ወ/ሮ ልዕልት ግደይ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል፡፡
በዚህ ክብረ በዓል ላይ የሕብረት ስራ ማህበሩን በትጋት ሲያገለግሉ ለቆዩት የአሚጎስ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍፁም አብርሃ፣ የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ሽጉጤ ሽልማት አበርክተውላቸዋል፡፡ በተመሳሳይ፣ በአግባቡ በመቆጠብና በመበደር ለሌሎች የማህበሩ አባላት አርአያ የሆኑ ስኬታማ አባላትም የዋንጫ ሽልማትና ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡
የዛሬ 12 ዓመት በሦስት ዓይን ገላጭ መሥራቾች ተጠንስሶ ዛሬ ወደ 10ሺ የሚጠጉ አባላትን ያፈራው አሚጎስ የህብረት ሥራ ማህበር፤ከ120 በላይ ሰራተኞችን ይዞ በተለያዩ የክልል ከተሞች ቅርንጫፎቹን በማብዛት ተደራሽነቱን እያሰፋ ይገኛል ተብሏል፡፡

በሲዳማ ክልል እና ወላይታ ዞን መካከል የተፈጠረው የ”ወሰን ይገባኛል” ውዝግብ የዜጎችን ሕይወት ቀጥፏል። መንግስት ለዚህ ውዝግብ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጥ ተጠይቋል።
በወላይታ ዞን፣ አበላ አባያ ወረዳ፣ “አባያ ክላስተር” በሚባል የእርሻ ልማት ላይ “ከሲዳማ ክልል መጡ” የተባሉ የልዩ ሃይል እና ሚሊሻ አባላት ባለፈው ሐሙስ ታህሳስ 17 ቀን 2017 ዓ.ም. ጥቃት መፈጸማቸውን አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአካባቢው ነዋሪ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል። ነዋሪው አክለውም፣ በሲዳማ ክልል እና ወላይታ ዞን መካከል የተከሰተው የ”ወሰን ይገባኛል” ውዝግብ መፍትሔ አለመበጀቱ በአካባቢው ላይ ውጥረት እንዲፈጠር እና ለዜጎች ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።

የእርሻ ልማቱ በመንግስት ሲተዳደር ቆይቶ፣ ኋላ ላይ “አሚባራ” በተሰኘ ድርጅት በኪራይ ሲለማ እንደነበር ያወሱት ነዋሪው፣ እርሻው የነበረበትን ዕዳ በመክፈል የወላይታ ልማት ማሕበር ላለፉት አራት ዓመታት በባለቤትነት እንደያዘው አብራርተዋል። ነዋሪው አክለውም፤ “ለእርሻው ከብላቴ ውሃ የሚያስተላልፈው ትልቅ ቱቦ በመሰበሩ ሳቢያ ውሃው ፈስሶ እርሻውን አበላሽቶ ለሁለት ዓመታት ያህል ስራ ቆሞ ነበር። ዘንድሮ ግን የልማት ማሕበሩ የራሱን ባለሞያዎችና ትራክተር በመያዝ ዳግም ለማልማት ወደ እርሻው አመራ።” ይላሉ።

ይሁንና ታህሳስ 17 ቀን 2017 ዓ.ም. ትራክተር በመያዝ ወደ ስፍራው የተጓዙት ባለሞያዎች ላይ “ከሲዳማ ክልል መጡ” የተባሉ የልዩ ሃይል እና ሚሊሻ አባላት ጥቃት ማድረሳቸውን የተናገሩት ነዋሪው፤ “የጥቃቱ መነሻ ምክንያት የእርሻውን ስፍራ ወደ ሲዳማ ክልል ለማካለል ነው” በማለት ነው። የአበላ አበያ ወረዳ ጥቃት ወደ ተፈጸመበት ስፍራ የፖሊስ ሃይል ቢያሰማራም፣ ሁኔታም “ከአቅሙ በላይ” እንደሆነበት ነዋሪው ይገልጻሉ። ከተላከው የፖሊስ ሃይል ጋር አብረው በተጓዙት የወረዳው አመራሮች እና የወላይታ ልማት ማሕበር ስራ አስኪያጅ ላይ እነዚሁ የልዩ ሃይሎች ጥቃት እንዳደረሱ የሚናገሩት ነዋሪው፣ ነገር ግን ጉዳት ሳይደርስባቸው ከስፍራው መሸሻቸውን ይጠቅሳሉ። ሆኖም ግን ሁለት ወጣቶች ተገድለው፣ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ደግሞ ቆስለው ሆስፒታል መግባታቸውን አመልክተዋል።

ነዋሪው በ1994 ዓ.ም. ተመሳሳይ ጥቃት ተፈጽሞ እንደነበር ያወሱ ሲሆን፣ በጥቃቱም በርካታ መኖሪያ ቤቶች እንደተቃጠሉና በንጹሃን ዜጎች ላይ ግድያ መፈጸሙን ይገልጻሉ። “ያኔም ሆነ አሁን የሲዳማ እና ወላይታ አካባቢዎችን የሚለይ ግልጽ ወሰን አለመኖሩ የችግር መንስዔ ነው። ወሰኑን ለመለየት ባለመቻሉ ችግሩ ተባብሶ ቀጥሏል። በዚያ ላይ ጥቃት ፈጻሚዎች ላይ መንግስት ሕጋዊ እርምጃ እየወሰደ አይደለም።” ብለዋል፣ ነዋሪው።የአገር መከላከያ ሰራዊት ጥቃት ከደረሰ በኋላ ዘግይቶ ወደ አካባቢው መግባቱንና ለነዋሪዎቹ በቂ ጥበቃ እያደረገ አለመሆኑን ያስረዱት እኚሁ ነዋሪ፣ “በነዋሪዎች ላይ ድብደባና ወከባ እየፈጸመ ነው።” ሲሉ ስሞታቸውን አቅርበዋል።
“የአካባቢው ሕዝብ ለወላይታ ዞን አስተዳደር በተደጋጋሚ ቅሬታ አቅርቧል። ነገር ግን የሕዝቡ ቅሬታ ሰሚ አላገኘም።” ያሉት ነዋሪው፣ አካባቢው በውጥረት ውስጥ እንደሚገኝና ሕዝቡ የደህንነት ስጋት እንዳለበት አያይዘው አመልክተዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የአበላ አባያ ወረዳ እና የሲዳማ ክልል የመንግስት ሃላፊዎችን አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።

አስረኛው ኃይሌ ሆቴልና ሪዞርት ጅማ፣ ባለፈው ሐሙስ ታህሳስ 24 ቀን 2017 ዓ.ም በጅማ ተመርቆ ተከፈተ፡፡ ባለ 4 ኮከቡ ኃይሌ ሆቴልና ሪዞርት ጅማ፤ የተለያዩ ዘመናዊ አገልግሎቶች የተሟሉላቸው 105 የመኝታ ክፍሎች ያሉት ሲሆን፤ የቪአይፒ አገልግሎት የሚሰጡና እያንዳንዳቸው አራት ክፍል ያላቸው ሁለት ቪላዎች፣ 5 የኦዲዮቪዥዋል መሳሪያዎች የተገጠሙላቸው የስብሰባ አዳራሾች አሉት፡፡ ሆቴልና ሪዞርቱ አራት ባህላዊና ዘመናዊ ምግቦችን የሚያቀርቡ ሬስቶራንቶች፣ለመዝናናትም ሆነ ጤንነትን ለመጠበቅ የሚያስችሉ የአዋቂና የህፃናት የመዋኛ ገንዳዎች ያሉት ሲሆን ጂምናዚየም፣ ስፓና ስቲም ባዝ፣ ሳውና ባዝና ሞሮኮ ባዝ ተሟልቶለታል፡፡ በይቻላል መርሁ የሚታወቀው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ የወላይታውን ኃይሌ ሆቴልና ሪዞርት ባስመረቀ በ10ኛ ወሩ የጅማውን ያስመረቀ ሲሆን፤ “ይህም በአንድ ዓመት ከአምስት ወር አንድ ሆቴል ለመገንባት የገባነውን ቃል ማክበራችንን ያሳያል” ብሏል፡፡ በምርቃት ሥነስርዓቱ ላይ የተገኙት የጅማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር ባደረጉት ንግግር፤ “ጥንታዊቷና ታሪካዊቷ ጅማ የበለጠ እንድትፈለግና የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን ሻለቃ ኃይሌ ትልቅ ስራ ሰርቶልናል፤ እኛም በሕይወት እስካለን የጅማን ሰላም እንጠብቃለን” ሲሉ በሆቴሉ ግንባታ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ግንባታው መጠናቀቁ የተነገረለት ኃይሌ ሆቴልና ሪዞርት ጅማ፤ 1.7 ቢሊዮን ብር ፈጅቷል ተብሏል፡፡ ኃይሌ ሆቴልና ሪዞርት ጅማ በአሁኑ ወቅት ለ210 ቋሚ ሰራተኞች የሥራ እድል የፈጠረ ሲሆን፤ በሙሉ አቅሙ ስራ ሲጀምር የሰራተኞቹን ቁጥር ወደ 400 እንደሚያሳድግ ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ አቶ ጋዲሳ ግርማ ገልጸዋል። ኃይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶች በቅርቡ የሻሸመኔውንና የደብረብርሃን ከተማ መዳረሻውን ለማስመረቅና ሥራ ለማስጀመር ቀን ከሌት እየሰራ መሆኑንም አቶ ጋዲሳ ግርማ ተናግረዋል። ኃይሌ ሆቴልና ሪዞርት ቀጣይ መዳረሻውን ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ በማዞር፣ በድሬደዋና በሐረር አድርጎ፣ በዚያው ወደ ጎረቤት አገር የመሻገር እቅድ እንዳለውም ተጠቁሟል፡፡የሃዋሳው ኃይሌ ሆቴልና ሪዞርት እንዲገነባ መሬት በመፍቀድ ከ24 ዓመት በፊት አስተዋፅኦ ያደረጉት የቀድሞው የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አባተ ኪሾ በምርቃቱ ላይ በክብር እንግድነት ታድመዋል፡፡

የ25 ዓመት ረዥም ጉዞ የተጀመረው በዚህ ነው!!

ውድ የአዲስ አድማስ ቤተሰቦች፡- የመጀመሪያው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ታትሞ ለንባብ የበቃው ታህሳስ 29 ቀን 1992 ዓ.ም ነበር - የዛሬ 25 ዓመት በዕለተ ቅዳሜ፡፡ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ያለ አንድ ቅዳሜ በስተቀር ጋዜጣው ያልወጣበት ቀን የለም፡፡ እሱም ቢሆን የተከሰተው በ97 ምርጫ ማግስት በተከሰተው ፖለቲካዊ ቀውስ ሳቢያ ነበር፡፡

የዛሬ 20 ዓመት፣ የአዲስ አድማስ ጠንሳሽ፣ መሥራችና ባለቤት አሰፋ ጎሳዬ (አሴ) በድንገተኛ ህመም ህይወቱ ባለፈበት ወቅት እንኳን ጋዜጣው ሳይታተም አልቀረም፡፡ ረቡዕ ከቀብር በኋላ ቢሮ ገብተን የቅዳሜውን ጋዜጣ ስናዘጋጅ ትዝ ይለኛል፡፡ እያነባንም ቢሆን የቅዳሜውን ሳምንታዊ ጋዜጣ በጉጉት ለሚጠብቀን ውድ አንባቢ አድርሰናል፡፡

አሁን ሳስበው ታዲያ ያኔ ትክክለኛ ሥራ ነው የሰራነው፡፡ የአሴ ነፍስ በዚያ ተግባራችን ጮቤ እንደረገጠች አልጠራጠርም፡፡ እርሱ በህይወት ባይኖርም አዲስ አድማስ መታተሟ፣ ህልምና ራዕዩን ማስቀጠያ ብቸኛ መንገድ ነበር፡፡

እነሆ ከዚያም በኋላ ሁለት አሰርት ዓመታትን አስቆጥራ፣ በብዙ ውጣ ውረዶችና ተግዳሮቶች አልፍ እነሆ ለ25ኛ ዓመቷ በቅታለች፡፡ በግሉ ፕሬስ ሩብ ክፍለዘመን ቀላል ጊዜ አይደለም፡፡ ቀላል ዕድሜ አይደለም፡፡ የ25 ዓመት ጉዞ ሀ ብሎ የተጀመረው ግን በዚህ ነው፡፡ ታህሳስ 29 ቀን 1992 ዓ.ም በታተመችው አዲስ አድማሰ ጋዜጣ፡፡

እንኳን አደረሳችሁ፤ አደረሰን!!

ከተመሰረተ 16 ዓመታትን ያስቆጠረው ዝግባ የሕጻናትና አረጋውያን መርጃ የበጎ አድራጎት ድርጅት፤ በአማራ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስና የኑሮ ውድነት ፈተና እንደሆኑበት አስታውቋል። ድርጅቱ የምስረታ ክብረ በዓሉን ለማክበር በዝግጅት ላይ መሆኑንም ገልጿል።

ባለፈው ሐሙስ ታህሳስ 24 ቀን 2017 ዓ.ም. በጌትፋም ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የድርጅቱ ሃላፊዎችና የበጎ ፈቃድ አምባሳደሮች የተገኙ ሲሆን፣ ስለድርጅቱ ዝርዝር ማብራሪያ አቅርበዋል። በማብራሪያቸውም ላይ ድርጅቱ ዋና መቀመጫውን በባሕር ዳር ከተማ በማድረግ ከ2 ሺሕ 650 በላይ ወላጆቻቸውን በሞት ላጡና ለከፋ ችግር የተጋለጡ ሕፃናትና ጧሪ አልባ የሆኑ አረጋውያን በመደገፍ፣ እንዲሁም ችግረኛ ሴቶችን በገቢ ማስገኛ ስራ በማሰማራት ኑሯቸውን እንዲያደላድሉ ማስቻሉን የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ስለሺ ጌታቸው አመልክተዋል።

በ27 በጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች የተቋቋመው ይህ የበጎ አድራጎት ድርጀት፣ የራሱ ተሽከረካሪዎች እንደሌሉት፤ የቦታ ጥበት እንዳለበት፤ የከርሰ ምድር ውሃ ችግር ስለመኖሩ በዚሁ መግለጫ ተነግሯል። ከዚህም ባለፈ በአማራ ክልል የተፈጠረውን የጸጥታ መደፍረስና የኑሮ ውድነቱን ተከትሎ፣ የተፈጠረው የፍጆታ ዕቃዎች አቅርቦት ዕጥረት "እየፈተነኝ ነው" ሲል ድርጅቱ አስረድቷል።

"ለአካል ጉዳተኞች እና ዕድሜያቸው ለገፋ ሰዎች የሚያገልግል ዊልቸር ዕጥረት ተፈጥሮብኛል" ያለው ድርጅቱ፣ በጎ ፈቃደኛ የሆኑ ግለሰቦች፤ በተለይም ከዚህ ቀደም ድጋፍ ለማድረግ ቃል የገቡ ባለሃብቶች ቃላቸውን ተግባር ላይ እንዲያውሉ ጠይቋል። የድርጅቱ የገቢ ምንጭ በአብዛኛው ከአባሎች በሚገኝ መዋጮ፣ በድርጅቱ ስር ካለው ትምሕርት ቤት እና በባሕር ዳር ከተማ ከከፈተው የፍራፍሬ ጭማቂ መሸጫ ቤት የሚመነጭ በመሆኑ፣ በስሩ ለሚገኙ 50 ቋሚ ሰራተኞች ደመወዝ ከመክፈል እና በማዕከሉ ላሉ ድጋፍ የሚሹ ወገኖች ድጋፍ ከማድረግ በዘለለ መጠነ ሰፊ ስራዎችን እንዳይሰራ ተግዳሮት እንደሆኑበት ጠቁሟል።

ዝግባ የሕጻናትና አረጋውያን መርጃ የበጎ አድራጎት ድርጅት 16ኛ ዓመት የምስረታ ክብረ በዓሉን ለማክበር መዘጋጀቱን በመጠቆም፣ ገቢ ከማሰባሰብ በተጨማሪ የመገናኛ ብዙሃን ትኩረታቸውን ለድርጅቱ እንዲያውሉ ዕንቅስቃሴ እንደሚያደርግ አብራርቷል።

ዓለምፍሬ ፒንክሃውስ ካንሰር ፋውንዴሽን ለመላ ኢትዮጵያውያን የድጋፍ ጥሪ አቅርቧል። ፋውንዴሽኑ በተደጋጋሚ የመሬት ጥያቄ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጥያቄ ቢያቀርብም፣ ምላሽ እንዳላገኘ አመልክቷል።

ባለፈው ዓርብ ታሕሳስ 25 ቀን 2017 ዓ.ም. በግዮን ሆቴል ሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ፋውንዴሽኑ በዶክተር ፍሬሕይወት ደርሶ ከአስራ ሶስት ዓመታት በፊት በአሜሪካ አትላንታ እንደተመሰረተ በማውሳት፣ በካንሰር ሕመም ላይ ቅድመ መከላከል የግንዛቤ መስጠት ስራ ሲሰራ መቆየቱ ተብራርቷል። በአዲስ አበባ እና ጎንደር ከተሞች ከ8 ሺሕ በላይ የካንሰር ታማሚዎችን የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እያደረገ የሚገኝ ድርጅት መሆኑም ተገልጿል።

የድርጅቱ የቦርድ አባል ወይዘሮ ጸዳለ ጽጌ እንዳስታወቁት፣ ፋውንዴሽኑ በዓመት ሁለት ጊዜ በካንሰር ሕመም ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ኮንፈረንስ ያዘጋጃል። አክለውም፣ በሁለተኛው ኮንፈረንስ አማካይነት በሕመሙ የተጠቁ ወገኖች እርስ በርሳቸው የውይይት መድረክ እንደሚያካሂዱ አስረድተዋል።

"የካንሰር ታማሚዎች ጤና የእርስዎም፣ የእኔም፣ የሁላችንም ጉዳይ ነው" የሚለው ፋውንዴሽኑ፣ መላ ኢትዮጵያውያን የድጋፍ እጃቸውን እንዲዘረጉ ጠይቋል። አሁን ላይ እየሰራቸው ካሉ ስራዎች በተጨማሪ፣ በቀጣይ ሌሎች በርካታ ዕንቅስቃሴዎችን ለማድረግ የተለያዩ ዕቅዶችን እንደነደፈ ተነግሯል።

• ለግንባታው እውን መሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድጋፍ
እንዲያደርግ ተጠይቋል


ባቡል ኸይር የበጎ አድራጎት ድርጅት፣ በቤተል አለም ባንክ የምገባና የአረጋዊያን መጠለያ ሁለገብ ማዕከል ፕሮጀክት ዋና መሥሪያ ቤትን በ1.2 ቢ.ብር ለማስገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ያስታወቀ ሲሆን፤ ለግንባታ ሥራው አቅም ይሆን ዘንድ ከ11 ሚሊዮን በር በላይ ወጪ በማድረግ የከርሰ ምድር የንጹህ ውሃ መጠጥ ማውጣቱንና በ5 ሚሊዮን ብር ወጪ የመብራት ዝርጋታ ማከናወኑን ገለጸ፡፡

በ5ሺ ካሬ ሜትር ላይ መሰረቱ የተጣለውን የባቡል ኸይር የምገባና የአረጋዊያን መጠለያ ሁለገብ ማዕከል ለመገንባት የሁሉም ኢትዮጵያውያን ድጋፍና እገዛ ያስፈልጋል ተብሏል፡፡

 

በሌላ በኩል፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቱ የፊታችን ጥር 4 ቀን 20፞17 ዓ.ም ከጠዋቱ 3:00 ጀምሮ «አምስት ዓመታትን በሰብአዊነት» በሚል መሪ ቃል የተመሰረተበትን አምስተኛ ዓመት የሚያከብር ሲሆን በዕለቱም በአለም ባንክ አካባቢ መሠረቱ የተጣለለት ይኸው የባቡል ኸይር የምገባና የአረጋዊያን መጠለያ ማዕከል ይጎበኛል ተብሏል፡፡

በዛሬው ዕለት ታህሳስ 26 ቀን 2017 ዓ.ም ጠዋት ረፋድ ላይ የባቡል ኸይር በጎ አድራጎት ድርጅት መሥራች ወይዘሮ ሀናን መሀመድና ወጣቱ ባለሃብት ምህረተአብ ሙሉጌታ እንዲሁም ኡስታዝ አብዱር አማሊ ሱልጣን በክብረ በዓሉ ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ እንደተብራራው፤ የበጎ አድራገት ድርጅቱ አምስተኛ ዓመት በዚሁ ማዕከል ከባቡል ኸይር ቤተሰብና አረጋዊያን ጋር አብሮ በማሳለፍና በጉብኝት ይከበራል፡፡

የድርጅቱ አጋርና ደጋፊ እንዲሁም የበዓሉ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል ወጣቱ ባለጸጋ ምህረትአብ ሙሉጌታ ባደረገው ንግግር፤ “ባቡልኸይር ራሱን በራሱ ለመርዳት መንግስት በሰጠው መሬት ላይ ትልቅ ህንጻ ለመገንባት የጀመረው አካሄድ ይበል የሚያሠኝና የእኛን ድጋፍ የሚሻ በመሆኑ ደጋግ ኢትዮጵያውያን በቻላችሁት አቅም በማገዝ አሻራችሁን ልታሥቀምጡ ይገባል።” ብሏል፡፡

በተጨማሪም ለ5ኛ አመት ክብረ በአሉም ሁላችንም ተገኝተን የቻልነውን እናግዝ ሲል ጥሪ አስተላልፏል።

126 ሰዎችን በመመገብ የበጎ አድራጎት ሥራውን ሀ ብሎ የጀመረው ባቡል ኸይር፤ ዛሬ ላይ ከ5 ሺህ በላይ ችግረኛ ወገኖችን በቀን ሁለት ጊዜ ምሳና እራት እየመገበ የሚገኝ ሲሆን፤ የጤና መድህናቸውንም ማረጋገጥ ችሏል ተብሏል፡፡

በርካታ ቁጥር ያላቸውን ወጣቶችና ሴቶችን በተለያዩ ሙያዎች (ልብስ ስፌት፣ የኮምፒዩተር ስልጠና፣ የጫማ ስራ) እያሰለጠነና የስራ እድሎችን ጭምር እያመቻቸ እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል፡፡


ዛሬ ላይ ባቡል ኸይር በአበበ ቢቂላ የመመገቢያ ማዕከልና የሙያ ስልጠና ማሳያ ስፍራ፣ በአቃቂ ቃሊቲ የስልጠና ማዕከልና የህፃናት ማቋያ ያለው ሲሆን፤ በኦሎንኮሚ ለወጣቶች የስራ እድልን እየፈጠረ የሚገኝ የብሎኬት ፕሮጀክት ግንባታ እያከናወነ ይገኛል።

ከአንድ ሳምንት በፊት በሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የታገደው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ሃይለማርያም፤ “ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የጣለብንን ዕግድ እንደሚያነሳ ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ ለአዲስ አድማስ ተናገሩ፡፡ የሚመሩት ማዕከል ከሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ጋር በዕግዱ ዙሪያ እየተመካከረ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ከታገደ አንድ ሳምንቱ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ አዲስ አበባ የሚገኘው የማዕከሉ ዋና ጽሕፈት ቤት ስራ አቁሞ መዘጋቱን ገልጸዋል። የማዕከሉ የባንክ ሂሳብ መታገዱንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ሕጋዊ መንገድን ተከትሎ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን ያስረዱት አቶ ያሬድ፤ ድርጅቱ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ባሳለፋቸው አራት ዓመታት ከመንግስት ጫና ደርሶበት እንደማያውቅ አስታውቀዋል። ይሁንና በሌሎች የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋማት ላይ የሚደርሱ ጫናዎችን አስመልክቶ መግለጫዎችን ሲያወጣ መቆየቱን አልሸሸጉም፡፡

በማያያዝም፣ ማዕከሉ ትኩረቱን በጋዜጠኞችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ላይ በማድረግ፣ ከተለያዩ ወገኖች የሚደርስባቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሚያጋልጥ ዋና ዳይሬክተሩ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል።

ታህሳስ 16 ቀን 2017 ዓ.ም. የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ለማዕከሉ ደብዳቤ ከመጻፉ አስቀድሞ ምንም ዓይነት የማስጠንቀቂያም ሆነ የምርመራ ሂደት እንዳልተከናወነ አቶ ያሬድ አስረድተዋል። ይህንን አስመልክቶም ማዕከሉ ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ደብዳቤ እንደጻፈና በዕግዱ ዙሪያ ከመስሪያ ቤቱ ጋር እየመከረ መሆኑን ጠቁመው፤ “ባለስልጣኑ የጣለብንን ዕግድ እንደሚያነሳ ተስፋ አደርጋለሁ” ተናግረዋል።


የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል፣ በሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ዓዋጅ መሰረት በ2013 ዓ.ም. የተመሰረተ ተቋም ነው።

በቅርቡ ወደ ፋይናንስ ሴክተሩ የተቀላቀለው መባዕ ማይክሮ ፋይናንስ አ.ማ.፣ አንደኛ መደበኛ እና አንደኛ አስቸኳይ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤውን፣ ነገ ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 26 ቀን 2017 ዓ.ም. ከጠዋቱ በ2:00 በራስ ዓምባ ሆቴል ያካሒዳል፡፡

ከ850 በላይ በሚኾኑ ባለአክሲዮኖች የተቋቋመውና ከአምስት ወራት በፊት ሥራ የጀመረው ተቋሙ፣ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤውን ለማካሔድ ዝግጅቱን አጠናቋል።

ጠቅላላ ጉባኤው፣ በተቋሙ የዳይሬክተሮች ቦርድ በሚቀርበው ሪፖርት፣ የተቋሙን ካፒታል ማሳደግ፣ በውጪ ኦዲተር ሪፖርት እና መሰል አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል፡፡

በጠቅላላ ጉባኤው ላይ፥ ባለአክሲዮኖች፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ፣ የተቋሙ አመራር እና ሠራተኞች እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና የሰነዶች ማረጋገጫ ተወካዮች እንደሚገኙ ይጠበቃል፡፡

Page 4 of 749