Administrator

Administrator

  በህንድ ባለፈው ሐሙስ ብቻ ከ75 ሺ በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ሪፖርት መደረጉንና ይህም በአለማችን ወረርሽኙ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ በአንድ ቀን የተመዘገበው ከፍተኛ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር መሆኑ ተዘግቧል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት በአንዳንድ አገራት በተወሰነ ደረጃ የመቀነስ አዝማሚያ ቢያሳይም፣ በአብዛኞቹ አገራት በአንጻሩ በስፋት መሰራጨት መቀጠሉን የሚጠቁሙ መረጃዎች እየወጡ ሲሆን፣ ቫይረሱ እስካለፈው ሃሙስ አመሻሽ ድረስ 24.5 ሚሊዮን ያህል ሰዎችን ማጥቃቱን የወርልዶ ሜትር ድረገጽ መረጃ ያሳያል፡፡
ድረገጹ እንደሚለው፤ ቫይረሱ እስከተጠቀሰው ጊዜ ድረስ በመላው አለም ለሞት የዳረጋቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 832 ሺህ የደረሰ ሲሆን፣ ያገገሙት ሰዎች ቁጥር ደግሞ ወደ 17 ሚሊዮን ተጠግቷል፡፡
6 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በቫይረሱ የተጠቁባትና ወደ 184 ሺህ ሰዎች ለሞት የተዳረጉባት አሜሪካ፤ በተጠቂዎችና በሟቾች ቁጥር አሁንም ከአለማችን አገራት በቀዳሚነት የቀጠለች ሲሆን ብራዚል በ3.7 ሚሊዮን ተጠቂዎችና በ118 ሺህ ሟቾች፣ ህንድ በ3.4 ሚሊዮን ተጠቂዎችና 62 ሺህ ያህል ሟቾች እንደሚከተሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ፈረንሳይ፣ ጣልያን፣ ስፔን፣ ስዊዘርላንድና ክሮሽያን ጨምሮ በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ኮሮና ቫይረስ እንደገና በስፋት መሰራጨት መጀመሩ የተነገረ ሲሆን፣ ወረርሽኙ በድጋሚ ሊያገረሽ እንደሚችል መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የአለም የጤና ድርጅት፤ፍቱንነቱ የተረጋገጠ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ወይም መድሃኒት በሚገኝበት ጊዜ በእኩልነትና በሚዛናዊነት ለሁሉም አገራት እንዲዳረስ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ከሰሞኑ አስታውቋል፡፡ የሩስያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ታቲያና ጎሊኮቫ፤ አገራቸው በቅርቡ አገኘሁት ያለችውን አወዛጋቢውን የኮሮና ክትባት ስፑትኒክ 5 ለመግዛት 27 ያህል የአለማችን አገራት ፍላጎት ማሳየታቸውን እንደተናገሩ የተዘገበ ሲሆን፣ ከእነዚህ አገራት መካከልም ቤላሩስ፣ ብራዚል፣ ቬንዙዌላና ካዛኪስታን እንደሚገኙበት ተነግሯል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከሚያዝያ እስከ ሰኔ በነበሩት ወራት ክፉኛ የኢኮኖሚ ጉዳት ካደረሰባቸው አገራት መካከል እንግሊዝ በቀዳሚነት እንደምትቀመጥ የዘገበው ቢቢሲ፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት በተጠቀሰው ጊዜ በ20.4 በመቶ ያህል መቀነሱንና ስፔን በ18.5 በመቶ የዕድገት መቀነስ እንደምትከተል ጠቁሟል፡፡ በ7ቱ የአለማችን ሃያላን አገራት በሁለተኛው ሩብ አመት የተከሰተውን የአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት ቅናሽ በተመለከተ ዘገባው ባወጣው መረጃም፣ በፈረንሳይ የ13.8 በመቶ፣ በጣሊያን የ12.4 በመቶ፣ በካናዳ የ12 በመቶ እንዲሁም በጀርመን የ9.7 በመቶ ቅናሽ መከሰቱን አስነብቧል፡፡  
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአለማችን ቱሪዝም ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን እንደሚቀጥል ባለፈው ማክሰኞ ያስጠነቀቀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ በ2020 የፈረንጆች አመት የመጀመሪያዎቹ 5 ወራት በመላው አለም አገራትን የጎበኙ አለማቀፍ ቱሪስቶች ቁጥር ከግማሽ በላይ መቀነሱንና በቱሪዝም ኤክስፖርት የ320 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መታጣቱን አስታውሷል፡፡ በመላው አለም ከቱሪዝሙ መስክ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ባላቸው የስራ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ 120 ሚሊዮን ያህል ሰዎች የስራ ዋስትና አደጋ ላይ እንደወደቀም የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አንቶኒዮ ጉቴሬስ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
እስከ ትናንት በስቲያ አመሻሽ በመላው አፍሪካ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ከ1.2 ሚሊዮን በላይ መድረሱን የዘገበው ኦልአፍሪካን ኒውስ፣ በአህጉሪቱ በቫይረሱ ሳቢያ ለሞት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር ወደ 30 ሺህ እየተጠጋ እንደሚገኝና ያገገሙት ሰዎች ቁጥርም 950 ሺህ መድረሱን አመልክቷል፡፡ ከ615 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተጠቁባትና ከ13ሺህ በላይ ሰዎችም ለሞት የተዳረጉባት ደቡብ አፍሪካ፤ በአህጉሩ በቫይረሱ ክፉኛ የተጎዳች ቀዳሚዋ አገር ስትሆን ግብጽ በ98 ሺህ፣ ሞሮኮ በ55 ሺህ ተጠቂዎች እንደሚከተሉ ተነግሯል፡፡
20 የአፍሪካ አገራት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት በሚል ድንበሮቻቸውን አሁንም ድረስ ሙሉ ለሙሉ ዘግተው እንደሚገኙ የአፍሪካ የበሽታ መከላከልና ቁጥጥር ማዕከል ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡


      ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ጨዋታ አዋቂ ሰው፣ ማእከላዊ ምርመራ ድርጅት እስር ቤት ይታሰራሉ። በእስረኞቹ ዘንድ የተለመደ የሻማ በመባል የሚታወቅ  አንድ ደንብ አለ፡፡ አዲስ የገባ እስረኛ ያለውን ገንዘብ ይሰጣል፤ የሚያውቀውን ቀልድ ያቀርባል፡፡ እኝህ ሽማግሌም ይሄንኑ ተጠየቁ፡፡ እሳቸው ጨዋታ አዋቂ ናችውና የሚሰጡት ቤተሰብ  ወይ ጓደኛ  ካመጣላቸው ገንዘብ መሆኑን ገልጠው፤ "ለጨዋታው ግን አንዴ ደብረማርቆስ ውስጥ የሆነውን ላጫውታችሁ"፤ ብለው ጀመሩ፡፡  
"ቅዳሜ ምሽት ሁለት ሴቶች ደጅ ውሃ ይወጡና ይመለሳሉ፡፡
አንደኛዋ፡- "በይ እንግዲህ ነገ እሁድ ጠዋት ቤተ ስኪያን እንገናኝ፤ አንቺ ከቀደምሽ አንቺ፣ እኔ ከቀደምኩ እኔ እዚያች ዘወትር  የምንቆምባት የሴቶች መቆምያ ጥግ ቆመን እናስቀድሳለን አደራ" ትላታለች፡፡ ሁለተኛዋም ጨመት ባለ ንግግር፤ "እስኪ እንግዲህ ወንዶቹ እንዴት እንዳሳደሩን አይተን ነዋ" አለች አሉ፡፡ ሽማግሌውም ቀጠሉና፤ "እንግዲህ እኛም እነዚህ አሳሪዎቻችን አንዴት አንዳሳደሩን እንይና የደነገጠ ዘመድም ሆነ ጓደኛ ነገ ከነገ ወዲያ ሲመጣልን፣ የሰጡኝን እሰጣችኋለሁ፤ ወፍራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል እንደሚባለው፣ እንዲሁ ስታዩኝ ወፍራምና ደልዳላ በመሆኔ ያለኝ መስያችሁ ነው እንጂ አሁን ገንዘብ አልያዝኩም" አሉ፡፡
እስረኞቹም፤ "ለመሆኑ በምን ታሰሩ አባባ?" ሲሉ ጠየቁዋቸው፡፡
 አዛውንቱም፤ "አንድ አለቃዬ ከመንግስት መስሪያ ቤታችን ገንዘብ ዘርፎ ጠፋ፤ አንተም ተመሳጥረህ አስጠፍተኸው ይሆናል፤ሚስጥረኛው ልትሆን ትችላለህ ብለው አሰሩኝ እንጂ እስረኛ አይደለሁም"
"ታዲያ ምንድን ነዎት? ምንድን ነኝ ይላሉ?" አሉና እስረኞቹ ቢጠይቁዋቸው፣ ሽማግሌውም "እንዲያው ቀብድ ነኝ፤ እኔ ቀብድ ነኝ፤ እስረኛ አይደለሁም" አሉ ይባላል፡፡
*   *  *
እንግዲህ አያሌ  የመከራ ዘመን  ታልፏል፡፡ በሰው እጅ ያለ ሰው አበሳው ብዙ ነው፡፡ በራሱ አያዝም፡፡ አስተማማኝ የሆነ የራሱ ሕይወትም የለውም፡፡ ጥፋቱም ሆነ ልማቱ በሌሎች ፍቃደ ልቦና ላይ የተንተራሰ ነው፡፡ የሕዝብም ዕጣ ፈንታ ደግ  መንግስትንና ክፉ መንግስትን የተንተራሰ ነው፡፡ የመንግስትን ፍቃደ ልቦና ይፈልጋል፡፡ አንድ በሕዝብ የተመረጠ መንግስት ሃላፊነት፣ የዚህን እውነታ መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ይህ አሌ የማይባል ሃቅ፣ በየዘመኑ አጋጥሞናል፤በሕዝብ ያልተመረጠ መንግስት ደግሞ በየጊዜው ጥርጣሬ የማየለየው፣ እምቢታና ለህዝብ አልታዘዝም ባይነት ነው ምሱ፡፡ ከትንኮሳ ከአሻጥር፣ ከተንኮል፣ ከሴራ፣ ከቅልበሳ፣ ከሽረባ፣ በጅምላ  መልኩ ከማያባራ አመጻ የማይለይ መንግስት ይሆናል አንደማለት ነው።  
ሌት ተቀን መልካም አስተዳደርንና ዲሞክራሲን አስተሳስረን መጓዝ፣ ለህዝባዊ ደህንነትና ለሃገር እድገት በብቃት መስራትን ይከስታል፡፡ በዚህ ላይ የጎረቤቶቻችንን አያያዝ በቅጡ ካወቅንበት፣ ከአነጋገር ይፈረዳል  ከአያያዝ ይቀደዳል የሚለውን ብሂል፣ እዳር አደረስነው ማለት ነው፡፡  እስከ ዛሬ ከንግግር ያላለፉ፣ የመጣ መንግስት ሁሉ አበክሮና ደጋግሞ አሸብርቆ የሚያወሳቸው፣ በወርቅ አልጋና በእርግብ ላባ የሚያስተኙን የሚመስሉ አያሌ ውብ ምኞቶች፣ ዕቅዶችና ሕልሞች አሉን፤ሆኖም ጉዳዩ የተግባራዊነት ጥያቄ ይሆንና በአብዛኛው መሬት የረገጠና ወሃ የቋጠረ  ፍሬ ነገር ሆኖ አናየውም፡፡ ረዥምና መራራ፣ ትእግስትን ፈታኝ የሆነን ለውጥ ማምጣት የሚቻለው አዎንታዊ ኃይልን እንዲያይል በማድረግና አሉታዊ ኃይል እንዲቀንስ በማድረግ ነው፡፡ ረብ ያለው ለውጥንና እድገትን ለመጎናፀፍ፣ የወጣቶችን ትጋት ማዳበር፣ የሴቶችን ተሳትፎ በስፋት ማበረታት፤ ተገቢውን ሰው በተገቢው ቦታ ላይ መመደብ፤ የሙያተኝነት ከበብ እንዲሉ፡፡  ክህሎትን መቀዳጀትንና ማቀዳጀት ዋናው ጉዳዮች ናቸው፡፡ ድህነትን ለመዋጋት ዋናው መሳርያ ከሚሆኑን ዕሴቶች አንዱ፤ ለሙያተኝነት ጥርጊያ ማመቻቸትና የሰው ኃይል አጠቃቀምን ስራዬ ብሎ ትኩረት መቸር ነው፡፡ ከመላላት ወደ መጠንከር በመጓዝ ነው ዕድገት ሊመጣ የሚችለው፡፡ በዲፕሎማሲ የታጀበ ዲሞክራሲ በማለምለምም ነው ዕድገት ሊመጣ የሚችለው፡፡
ገጣሚ ሐይሉ ገ/ ዮሐንስ፡-
"ነገሩ አልሆን ብሎ ሁኔታው ሲጠጥር
 ጠጣሩ እንዲላላ  የላላውን ወጥር " -- እንዲሉ፡፡

በርካቶች አዶኒስ በሚለው የብዕር ስሙ ነው የሚያውቁት፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተወዳጅ የነበረው ;ገመና; ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ደራሲ ነበር - አድነው ወንድይራድ፡፡ #መለከት; የተሰኘው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማም ደራሲ ነበር፡፡
አዶኒስ በ1996 ዓ.ም  #የአና ማስታወሻ;ን በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በየሳምንቱ ተርጉሞ በማቅረብም ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፈ ሲሆን  በኋላም በመጽሐፍ አሳትሞ ለተደራሲያን አቅርቦታል፡፡ ወደ ተውኔትም ተለውጦ ለመድረክ በቅቷል፡፡ በመቀጠልም የአዶልፍ ኤክማንን ታሪክ በአዲስ አድማስ እየተረጎመ ለአንባቢያን ሲያደርስ የቆየ ሲሆን በተመሳሳይ ይሄንንም በመጽሐፍ ማሳተሙ ይታወቃል፡፡
    
       
አዶኒስ ከነዚህ ሥራዎቹ በተጨማሪ የሕጻናት መዝሙሮችና የበርካታ ፊልሞች፤ እንዲሁም የሌሎች የኪነ ጥበብ ሥራዎች ደራሲና ተርጓሚ ነው።
ብዙ ጊዜ በሚዲያ የመቅረብና በአደባባይ የመታየት ፍላጎት ያልነበረው አዶኒስ፤ በሙያው አርክቴክት ሲሆን በዚህም መስክ የበርካታ ሕንፃዎችን ዲዛይን እንደሰራ ይነገርለታል።
አዶኒስ ባደረበት ህመም ህክምና ሲከታተል ቆይቶ ህይወቱ ማለፉ ነው የተነገረው፡፡ አዶኒስ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነበር፡፡   
አዲስ አድማስ ጋዜጣ፤ በተወዳጁ ደራሲና ተርጓሚ አዱኒስ፣ ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን እየገለጸ ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጆቹና ለአድናቂዎቹ መጽናናትን ይመኛል፡፡
***
በአዲስ አድማስ ጋዜጣ በየሳምንቱ #የአና ማስታወሻ; መግቢያ የነበረውን ጽሁፍ ለትውስታ ያህል እነሆ፡-
#የአና ማስታወሻ - አንዲት አይሁድ ልጃገረድ ከተደበቀችበት ጣሪያ ሥር ያሰማችው ሰብአዊ ዋይታ ብቻ አይደለም፡፡ የአና ማስታወሻ-እያንዳንዱ የ20ኛው ክፍለ ዘመን አዕምሮ ከየነበረበት የኑሮ ስርቻ ተወትፎ ሲያሰማው የነበረው ድምጽ አልባ ኡኡታ ነው፡፡ የአና ማስታወሻ - ሌሎች በፈጠሩበት አውላላ የሕይወት በረሃ መሃል ተጥሎ አቅጣጫው ጠፍቶት ብቻውን ይንቀዋለል ዘንድ የተገደደው የእያንዳንዱ የህይወት ስደተኛ የድረሱልኝ ዕሪታ ነው፡፡ የአና ማስታወሻ - ችምችም እያለ በመጣው የሕይወት ቁጥቋጦ ተውጦ በቁሙ እያለ መታየት የተሳነውና ዳግም ለመታየት ሰማይ እየቧጠጠ ያለው እያንዳንዱ የዘመናችን ሰው የሚያንቋርረው የጣዕር ኤሎሄ ነው፡፡;
Tuesday, 25 August 2020 06:31

ሰለሞን ጎሳዬ ገዳ

 ኧረ ጉድ ባየህ ወዳጄ ኧረ ጉድ ባየህ ጓዴ!


ጓዴ ባለህበት ፅና!
ስምንት አመት ሆነው ዝክርህ፤
ይህንን ጉድ ከማየት ያለህበት ነው እሚሻልህ!
ገበያው ተደበላልቋል፤ ተገዢው ጊዜውን ይቃኛል
ገዢው ግና ተሰናብቷል
ስምንት ዓመት ሆነህ ጓዴ፣ ካለፍክ ከዚህ ሀገር እክል
  ተበዳይ አርፎም ቢተኛ፣ በዳይ ዘራፍ ነው አመሉ
“ምሴን አምጡ ነው ጠበሉ”
“ግፍ አይጠግቤ ደም ነው ውሉ!
ሳይመሽ ጨለመበት ባህሉ፡፡
እንዲህ ሆነልህ ብሂሉ፡-
“ቀና ሰው ጫጩት ሲያረባ ጐረቤቱ አየና አሉ
ምቀኛ ሱሱን ሲወጣ፣ ሸለምጥማጥ አረባ አሉ”
የሞተ ፈረስ መጋለብ፣ የተበላ እቁብ ነው ስሙ
የሞተ ዛር ነው ትርጉሙ፤ ዛሬስ ጉድ ባየህ ወዳጄ፡፡
ኧረ ጉዱን ባየህ ጓዴ…
ተቀትሎ በዘር ጐራዴ
ደም በደም ሆኗል መንገዴ
አራሙቻ አብቅሏል ሀገር
ሲወርድ ሲዋረድ እንዲሉ የጐሳ የቡድን ውርዴ
የሀገር ማህፀን አምካኝ እንደ ሞት ጭንጋፍ እንግዴ!
እንኳን አላየህ ወዳጄ….
ሠልፍም እንደ ግብር - ውሃ፣ የትም ሲፈስ በየሜዳ
መንጋ ለሁከት ሲነሳ ሥርዓተ - አልበኛ ሠልጥኖ፣ “ሰይጥኖ” በሀገሩ ፍዳ
በኋላ ቀር ጥፋት ናዳ፣ ነውጥ እንደ ለውጥ ሲሰናዳ
በንብረት ቃጠሎ ውድሚያ፣ ጥሪት ሲፈስ እንደ ጭዳ
ደም እንደ ውሃ ሲቀዳ እንኳን አላየህ ወንድሜ፣ ይህንን የትውልድ እዳ!
አንዱ ለግድብ ሲተጋ፣ ሌላው ለሀገር ሞት ሲሰለፍ
አንዱ ውሃ ሲያጠራቅም፣ ሌላው ከጐርፍ ጋር ሲጐርፍ
እብድ እንደበላው በሶ ሰው ተበትኖ ሜዳ፤
ህንፃ እንደ አሻንጉሊት ሲወድቅ እንደ አላዋቂ ተራዳ፤
ላብና እድሜ እንዳልወጣበት፣ በአንድ ጀንበር ድንጋይ በልቶት
ስንት ንብረት ስንት ጥፋት!
ኧረ ጉድ አላየህ ጓዴ፣ ታሪክ በአንድ ቀን ሲጨልም
የንፁሀን ሞት ሲተምም
የአንተ ዘመን ከዚህ ዘመን ሊወዳደር፣ ምን እና ምን!
ደሞም “በእንቅርት ላይ እኮ፣ ጆሮ ደግፍ” ብሂል እንዲል፣
ተደራራቢ ጣርም ነው፤ የኮሮና እክል ላይ እክል!
ህይወት በቁም ሞት ሲፈተን፣ ማሰብ ሲያቅት ኑሮ ማፍረስ፣
ፍትህ ሲነጥፍ ህግ መጣስ፤ ዛሬ ሰው በራሱ ፈርዶ
የራስ ላይ ክተት አውጆ፤ በገዛ ቤቱ ከትሟል
   ክተት ለሽሽት ነው ቋንቋው፤ ከሞት መራቅ
   አስፈልጓል፡፡
ግን እሱ ነው የሚያዋጣው፤
“ሞት ሳይሞቱት ነው እሚለመድ”፣ ያለን ጋሽ ፀጋዬ ይሄን ነው፡፡
አለመውጣት ነው ቋንቋው፤ እስከ መፍትሔው ማየት ነው፡፡
እና ጓዴ…..
አለምም ዛሬ ጠባለች፤ የሁሉንም ሞት አስተናግዳ፣ በደዌ ተሸማቃለች፡፡
ራሷን በልታ እንደ አብዮት፣  ክፋቷን ገድላ
ቀብራለች፤
ከኛው ቤት እኩል ጠባብ፣ አንድ መንድር አክላለች፡፡
እና ሰሌ ይህን አልኩህ፤  የዓለምን ስቃይ እንዳታይ
እዛው ጽና፣ እዛው ጋ ቆይ
እዛው ባለህበት ጽና…
(ለሰለሞን ጐሣዬ 8ኛ ሙት አመትና ለሁላችንም)
ነቢይ መኮንን - ነሐሴ 2012

 በአሁኑ ወቅት የጤና ባለሙያ ሠራተኞቻችን በመላው ከተማችን፣ አገራችንና ህዝባችን ውስጥ በፍጥነት እየተሰራጨ የሚገኘውን የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ -19) በሽታ ፊት ለፊት በግንባር ላይ እየተፋለሙት በመላው ዓለም በዚህ ታይቶ በማይታወቅ ቀውስ ራሳቸውን ለዚህ ቫይረስ አጋልጠው ይገኛሉ፡፡
ሀኪሞቻችን፣ ነርሶቻችን፣ የላብራቶሪ ቴክኒሻኖቻችን፣ የአምቡላንስ ሹፌሮች እና የመጀመሪያ መልስ ሰጪዎች ፣ የፋርሚሲ ባለሙያዎቻችንና እያንዳንዱ ለበሽተኞች እንክብካቤ ድጋፍ የሚያደርጉ ሁሉ በዚህ ክፉ ቀን ለችግሩ ምላሽ እየሰጡና በእጅጉ ተጋላጭ ለሆነው የህብረተሰባችን ክፍል እንክብካቤም በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
በየዕለቱና በተለይም በዚህ ወረርሽኝ ወቅት ለምትከፍሉት መስዋዕትነት ከሁሉም ወገን ምስጋና ይድረሳችሁ! ለታታሪነታችሁ ለቁርጠኝነታችሁ፣ ለፅናታችሁና ለጀግንነታችሁ የእኛ ጥልቅ ምስጋናና አድናቆት ሊቸራችሁ ይገባል:: ለበሽተኞች የምትሰጡት አገልግሎት የአያሌዎችን ነፍስ እየታደገና ትርጉም ያለው ለውጥ እያመጣ ነው፡፡
በዚህ ዓመት በተለይም ውድ ወገኖቻችንን ሲንከባከቡና ሲደግፉ እንዲሁም አገራችንን በማራመድ ተግባር ላይ ተሰማርተው ሳለ፣ በኮሮና ቫይረስ ህይወታቸውን የተነጠቁ የግንባር ሠራተኞቻችንን እንዘክራለን - እናስታውሳለን፡፡
በዚህ ወረርሽኝ ወቅት ህይወታቸውን የተነጠቁ ሠራተኞችን (ነርሶቻችን፣ ሃኪሞቻችን፣ የእንክብካቤ ባለሙያዎቻችንና ሌሎች ቁልፍ ሠራተኞቻችንን) ውለታ መቼም ቢሆን አንዘነጋውም - ሁሌም ባለ ዕዳ ነን!

አቡ አሊ ሲና (አቬሴና) ማነው?
አቡ አሊ ሲና በስፋት የሚታወቀው አቬሴና በተባለው የላቲን ስሙ ሲሆን የፐርሺያ ሃኪምና ፈላስፋ ነበር፡፡ በቡኻራ በ980 የተወለደው አቬሴና፤ በ1037 በኢራን ሃማዳን ውስጥ ነው ያረፈው፡፡ በዘመኑ እጅግ ታዋቂና ስመ-ጥር ሃኪም፣ ፈላስፋ፣ የኢንሳይክሎፒዲያ ቀማሪ፣ የሂሳብ ሊቅና የህዋ ተመራማሪም ነበር፡፡
ወደርየለሽ የማስታወስ ችሎታ የተቸረው ህፃኑ አቬሴና፤በ10 ዓመቱ በቁራንና በተለያዩ የሳይንስ ዘርፎች ጥናት በእጅጉ የተካነ ነበር፡፡ ፍልስፍና ማጥናት የጀመረው የተለያዩ የግሪክ፣ ሙስሊምና ሌሎች ፅሁፎችን በማንበብ ነው፡፡ ሎጂክና ሜታፊዚክስ ከስራቸው ቁጭ ብሎ ያስተማሩትን መምህራን፣ በዕውቀት ለመላቅም ፋታ አልወሰደበትም፡፡
ከዚያ በኋላ፤ 18 ዓመት እስኪሞላው ድረስ ራስን በማስተማር ሥራ ላይ ተጠምዶ ቆየ፡፡ ከፍተኛ የንባብ ፍቅርና ጉጉትም ነበረው፡፡ በዚህም በእስልምና ህግና በህክምና ሙያ፤ በመጨረሻም፣ በሜታፊዚክስ የተካነ ለመሆን በቅቷል፡፡  ወጣቱ ሃኪም በ17 ዓመቱም የቡኻራ ንጉስ የነበረውን ኑህ ኢብን ማንሱር፤ በወቅቱ አሉ በተባሉት ሃኪሞች  እንደማይድን ይቆጠር ከነበረ በሽታ በማከም ፈውሶታል፡፡
ንጉሱ ከበሽታው ማገገሙን ተከትሎ፣ ወጣቱን ሃኪም ሊሸልመው ፈልጐ ነበር፤ ነገር ግን አቡ አሊ ሲና የንጉሱን በመፃሕፍት የታጨቀ ቤተ መፃሕፍት ለመጠቀም እንዲፈቅድለት ብቻ ነበር የሻተው፡፡ ለዚህ የበለፀገ የሳማኒድስ (ከአረብ ወረራ በኋላ በኢራን የተነሳ የመጀመሪያው ታላቅ አገር በቀል ሥርወ መንግስት) የንጉሳዊ ቤተመፃሕፍት ተደራሽ መሆኑ - በተለይም ለምሁራዊ ሰብዕናው መበልፀግ አጋዥ ነበር:: 21 ዓመት ሲሞላው ሁሉንም የመደበኛ ትምህርት ዘርፎች በስኬት ያጠናቀቀ ሲሆን በላቀ የህክምና ባለሙያነቱም ሰፊ ተቀባይነትና ዝናን ለመቀዳጀት በቅቷል፡፡  
በአስተዳደርነትም ጭምር ያገለገለው አቡ አሊ ሲና፤ ለጥቂት ጊዜ ያህል በፀሐፊነት ለመንግስትም አገልግሏል፡፡ አቬሴና በተለያዩ የኢራን ገዢዎች ቤተ መንግስቶች ውስጥ በህክምና ባለሙያነትና በፖለቲካ አስተዳዳሪነት መስራቱን ቀጠለ - የአባሲድ ሥልጣን በተፈረካከሰ ጊዜ ብቅ ባሉ አያሌ ወራሽ የኢራን መንግስታት ወቅት፡፡ በኋላ ላይም ወደ ሬይ፣ ቀጥሎም ወደ ሃማዳን ተጉዟል፡፡ “Al – qanun fi al - tibb” የተሰኘውን ዝነኛ መጽሐፉን የፃፈውም በሃማዳን ነበር፡፡ በዚህ ወቅት የሃማዳን ንጉስ የነበሩትን ሻምስ አል ዳውላህ ተጠናውቷቸው ከነበረ ከፍተኛ የቁርጠት በሽታም ፈውሷቸዋል፡፡ ከሃማዳን በቀጥታ ያመራው ወደ ኢስፋሃን ሲሆን አያሌ እንደ ቅርስ የሚቆጠሩለትን የጽሑፍ ሥራዎቹን ያጠናቀቀው እዚህ ነበር፡፡
አቪሴና ከ500 በላይ መፃሕፍትና መጣጥፎችን ጽፏል፡፡ ሁለቱ ሥራዎቹ - “Daneshnameh e-Alai” (የፍልስፍና ሳይንስ ኢንሳይክሎፒዲያ) እና በ pulse ላይ  የምታነጣጥር አነስተኛ የጥናት ጽሑፉ ግን በአፍ መፍቻ ቋንቋው በፋርሲ ነበር የተፃፉት::
ከዚህ በተጨማሪም፤ ስለ ተፈጥሮ ፍልስፍና፣ ስለ አስትሮኖሚ፣ ስለ ሥነ- መለኮትና ሜታፊዚክስ እንዲሁም ስለ ህክምና፣ ስለ ሥነልቦና፣ ስለ ሙዚቃ፣ ስለ ሂሳብና ፊዚካል ሳይንሶችም ጽፏል፡፡ የፐርሺያ ባለ አራት ስንኞች ግጥም (ሩባያት) እና የአጫጭር ግጥሞች ደራሲ እንደሆነም ይነገራል፡፡
አቬሴና ከዚያ በኋላ በተለያዩ የ ኾራሳን ከተሞች ሲዘዋወር የቆየ ሲሆን በኋላም ማዕከላዊ ኢራንን ይገዛ ወደ ነበረው የቡዪድ ልኡላን ቤተ መንግስት አምርቷል፤ መጀመሪያ ወደ ሬይ (ከዘመናዊ ቴህራን አቅራቢያ)፣ ከዚያም ወደ ቃዝቪን  የተጓዘው አቬሴና፤ እንደተለመደው በህክምና ባለሙያነት ነበር የሚተዳደረው፡፡ በሰሜናዊ ፐርሺያ የበለፀገች ከተማ የነበረችው የሬይ ንጉስን ከሜላኮሊያ በማከም ከበሽታው የፈወሰ ሲሆን እኒህን ምልከታዎቹን በኋላ ላይ “State of the Human Soul” በተሰኘ ጽሑፉ ገልፆታል:: በእነኚህ ከተሞች በቂ የማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ ማግኘት ያልቻለ ሲሆን ሥራውን ለመቀጠል ወሳኝ የሆነውን ሰላምና መረጋጋትም ተነፍጐ  ነበር፡፡ በዚህም ሳቢያ በምዕራብ - ማዕከላዊ ኢራን ወደ ሃማዳን ተጓዘ - ሌላው የቡዪድ ልኡል (ሻምስአድ - ዳውላህ) ገዢ ወደነበረበት ሥፍራ ማለት ነው፡፡
ጉዞው በአቬሴና ህይወት ውስጥ የአዲስ ምዕራፍ ጅማሮን አብስሮለታል፡፡ የቤተ መንግስት ሃኪም ሆኖ ከማገልገሉም በላይ በገዢው ዘንድ በነበረው ተወዳጅነትም ሁለት ጊዜ የከፍተኛ ባለሥልጣንነት ሹመት እስከማግኘት ደርሷል፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰውም፤ የሃማዳንን ንጉስ ከከፋ የሆድ ቁርጠት ህመም አክሞ ማዳንም ችሏል፡፡
ከሃማዳን ወደ ኢስፈሃን በመጓዝም፣ በፊዚክስና ሜታፊዚክስ ላይ የሰራቸውን እንደ ቅርስ የሚቆጠሩ አያሌ ጽሑፎች አጠናቅቋል፡፡ በመጨረሻም ወደ ሃማዳን ተመልሶ በ1037 በሃይለኛ የሆድ ቁርጠት ህመም ህይወቱ አልፏል፡፡
የህክምና ሳይንስ መርህ ተደርጐ የሚቆጠረው አቬሴና፤ በህክምናና በአርስቶቴሊያን ፍልስፍና ዘርፎች ባበረከተው አስተዋጽኦው ይበልጥ ይታወቃል፡፡ ሁለቱ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጣቸው ሥራዎቹ - “The Book of Healing” እና በምዕራቡ ዓለም የህክምና መርህ በሚል የሚታወቀው “Al Qanun” የተሰኙት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ሳይንሳዊ ኢንሳይክሎፒዲያ ሲሆን ሎጂክ፣ የተፈጥሮ ሳይንስ፣ ሥነልቦና፣ ጂኦሜትሪ፣ አስትሮኖሚ፣ አሪትሜቲክና ሙዚቃን ያካትታል፡፡ ሁለተኛው (Circa 1030 A.D) በህክምና ሳይንስ ታሪክ እጅግ ዝነኛ ከሆኑት መፃሕፍት አንዱ ተደርጐ የሚቆጠር ነው፡፡
“The canon” የህክምና ሳይንስ መርህ ወይም ሚዛን ለመሆን የበቃ ሥራው ሲሆን በአውሮፓ ትላልቅ ዩኒቨርሲቲዎች ሁሉ ከሂፖክራተስ (460-377B.C) እና ጋሌን (129-199A.D) ሥራዎች ጋር በእኩል ደረጃ ላይ የሚቀመጥ ነበር፡፡ “The Canon of Medicine” አምስት መፃሕፍትን የያዘ ነው፡፡ እነዚህ መጽሐፍት በአናቶሚ፣ ፊዚዮሎጂና ፌርማኮሎጂ (መጽሐፍ 1 እና 2) ያለውን ዕውቀት በስልትና በተጠና መንገድ ይመድባሉ፡፡ ሌላው የበሽታ ጥናት ዘርፍ፤ የውስጣዊ አካላትን በሽታዎችና ዓይነተኛ የበሽታ ምልክቶች በጋሌን የአመዳደብ ሥርዓት መሰረት ይገልፃል (መፅሐፍ 3)፤ ትኩሳት (መፅሐፍ 4) እና ማቴሪያል ሜዲካል (መፅሐፍ 5) ናቸው፡፡
አቬሴና በዚህ የመጨረሻ መጽሐፉ፤ 760 መድሃኒቶችን ከአዘገጃጀት መመሪያዎች ጋር የሚገልጽ ሲሆን፤  በአጠቃላይ “The Canon of Medicine” በ1ሺ ገፆች ተቀንብቦ፣ በግምት አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ቃላትን የያዘ ሲሆን፤ በስልታዊ መንገድ የተፃፈ ነው፡፡
“Canon” መጠነ - ሰፊ ታዋቂነትን የተቀዳጀው በ15ኛውና 16ኛው ክ/ዘመን ቲፖግራፊ ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ ነው፤ ነገር ግን እስከ 18ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ ድረስ ተፅእኖው በመላው አውሮፓ ፀንቶ ቆይቷል፡፡

አቬሴና ለዘመናችን ያስፈልገን ይሆን?
ፈር ቀዳጅ የሆነ ሥራው - “Al-Qanun” ከህክምና ጽሑፍና አካዳሚያዊ መርሀ ግብሮች ዕድገት ውስጥ ቁልፍ ሚና የነበረው ሲሆን በመድሃኒቶች ታሪካዊ ትውስታ ውስጥ የማዕዘን ድንጋይ ነበር:: በታሪክ ሊቁ ጃማል ሙሳቪ መሰረት፤ በሙስሊሙ ዓለምና በአውሮፓ ህይወቱ ካለፈ በኋላ ባሉት 600 ዓመታትም የአቬሲና ሥራዎች በመድሃኒቶች ዕድገት ውስጥ ቁልፍ ሚና መጫወቱን ቀጥሎ ነበር፡፡
በአሁኑ ወቅት የአቬሴና ሌጋሲ የፀረ - ወረርሽኙን ጥረት በዓለም አቀፍ ደረጃ እያገዘ እንደሆነ የህክምና አዋቂዎች ለዓለም በኩራት እያስታወሱ ነው፡፡  
ለመጀመሪያ ጊዜ.  እ.ኤ.አ በ1025 የተጠቀሰውና #የመድሀኒቶች መርህ (The Canon of Drugs); በሚለው 5ኛ ቅፅ የህክምና ኢንሳይክሎፒዲያው  አቪሴና፤ በሳይንሳዊ ስራው የኳራንቲን ወይም የለይቶ ማቆያ ትክክለኛ ፅንሰ-ሃሳብን  በሽታ እንዳይሰራጭ፣ ለመቆጣጠር  እንዴት እንዳስቀመጠው ሳይጨምሩ፤ ሳይቀንሱ አረጋግጠዋል፡፡
በዚህ በአብዛኛው በምክንያታዊነት  ሊወደስ በሚገባው ትውስታ ውስጥ፣ የተዘነጋው ወሳኙ እውነታ፣ አቪሴና የህክምና ሳይንቲስት ብቻ ሳይሆን፣ በተጨማሪም ታላቅ የፍልስፍና አዋቂ መሆኑ ነው፡፡ በሌላ አገላለፅ.፣ ቀደም ባለው ታሪካዊ የመድሀኒት ሳይንስ ውስጥ ወሳኝ ሚና የነበረው አቪሴና፣ በተጨማሪም ወጤታማ ፈላስፋም ነበር፡፡


Tuesday, 25 August 2020 05:14

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

 የማከብረው
                    ቴዎድሮስ ፀጋዬ

            ይሄ ሰውዬ እጅግ ከማከብራቸው ቃለ-መጠይቅ አድራጊዎች መሀል ፊት መሪው ነው። ለቴዎድሮስ ፀጋዬ ቃሌን ስሰጥ በኩራት ነው።
ቴዲ ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረ ጊዜ ማንም ስለ ኢትዮጵያዊነት ሳይደፍር ደፍሮ ይሰራ ነበር። “አሁን የሚያነሳቸውን አጀንዳዎች ያኔ ሀገር ቤት እያለ ለምን አያነሳም ነበር?“ የሚሉ ተደጋጋሚ አስተያየቶች እሰማለሁ። ያን ጊዜ አለማወቅ ነው።
በመንግሥት የአየር ሰዓት እንኳን መስራት መሞከሩም ከስቱዲዮ አስጎትቶ ያስወስዳል። የመጣንበትን መንገድ መርሳት ይሆናል።
በተለይ ቃለመጠይቅን እንደ ቴዲ አድምቶ የሚሰራ አላውቅም። እንግዳውን ዛሬ ደውሎ ነገ ስቱዲዮ ይዞ የሚገባ አይደለም። ለአንዱ እንግዳ የሚያደርገው ዝግጅት እኔን ያደክመኛል። በሙያው ቀልድ አያውቅም። በትምህርት ዝግጅቱ የህግ ባለሙያ ቢሆንም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በስራዎቹ ራሱን ተፈላጊ ማድረግ የቻለ ብርቱ ሰው ነው።
በሙያ መዘሞትን አምርሮ ይጠላል። ገንዘብ እያስፈለገው እንኳ አንድም ጊዜ ስራው ብር ብር ሸቶኝ አያውቅም። ቴዲ ባለፈባቸው መንገዶች ለማለፍ የሞራል ድፍረት ያለው ራሱ "Tewodros_Tsegaye ብቻ ነው። ይህ ማለት ግን በቃለመጠይቆቹም ሆነ በሚያነሳቸው ሀሳቦች ሁሉ እስማማለሁ ማለት አይደለም። የምቃወማቸውም በዝምታ የማልፋቸውም ይኖሩኛል።
የእጅግ ብዙዎቹ ግን አድናቂ ነኝ። ማንንም ሰው ለማክበር ሀሳቡ እኔን መምሰል የለበትም። እኔ ያዘጋጀሁትን ድንጋይ ስለወረወረልኝ አይደለም ማንንም ሰው የማደንቀው። የቴዲ ሀገር ወዳድነት እንደ የገበያ ስራ አይደለም። ከልቡ ነው። ላመነበት ሀሳብ ችኮ ነው። አይጎናበስም። ግትር ነው። ሀሳቡ ብዙ ሊያስከፍለው እንደሚችል እያወቀም ይሄድበታል። ዋጋም ከፍሎበታል። የማስታወቂያ ገቢ ለፕሮግራሙና ለኑሮው እስትንፋስ መሆኑን እያወቀ ያመነበትን ሀሳብ በማንሳቱ ገቢውን ሲያስቀር አውቃለሁ። አይደንቀውም።
ወዳጄ ቴዲ፤ ስላየሁህ ደስ ብሎኛል። በአካል ወይም በነፍስ የምንገናኝበት ጊዜ ይመጣል።


አለማችንም ሆነ የአለም ጤና ድርጅት፣ ኮሮናን ያህል ፈታኝ የጤና ቀውስ ገጥሟቸው እንደማያውቅና ቫይረሱ በ188 የአለም አገራት በፍጥነት እየተሰራጨ የከፋ ጉዳት ማስከተሉን እንደቀጠለ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫ ያስታወቁ ሲሆን በህንድ ከትናንት በስቲያ ሃሙስ ብቻ 69,672 የኮሮና ተጠቂዎች መመዝገባቸው ተነግሯል::
ቫይረሱ እስካለፈው ሃሙስ አመሻሽ ድረስ በመላው አለም ከ22.6 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ማጥቃቱንና ከ792 ሺህ በላይ ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት መዳረጉን የጠቆመው የወርልዶ ሜትር ድረገጽ መረጃ፣ ያገገሙት ሰዎች ቁጥር በአንጻሩ 15.3 ሚሊዮን መድረሱን አመልክቷል፡፡
በኮሮና ቫይረስ ሟቾችና ተጠቂዎች ቁጥር አሁንም ከአለማችን አገራት በመጀመሪያው ደረጃ ላይ በምትገኘው አሜሪካ የተጠቂዎች ቁጥር ከ5.7 ሚሊዮን ሲያልፍ፣ የሟቾች ቁጥር ደግሞ ከ176 ሺህ በላይ መድረሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ ከሰሞኑ ባወጣው ትንበያ፤ በአሜሪካ የኮሮና ቫይረስ ሟቾች ቁጥር እስከ መጪው ታህሳስ ወር ከ295 ሺ በላይ ሊደርስ እንደሚችል ማስጠንቀቁን የዘገበው ቢቢሲ፣ ወረርሽኙ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከባድ ተጽእኖ ማሳደሩንና እስከ ሰኔ በነበሩት 3 ወራት  ብቻ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት በ33 በመቶ መቀነሱንም አስታውሷል፡፡
ብራዚል በ3.5 ሚሊዮን ተጠቂዎችና በ111 ሺህ ሟቾች ከአለም አገራት በሁለተኛነት ስትከተል፣ ህንድ በ2.8 ሚሊዮን ተጠቂዎች ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች፡፡ 58 ሺህ ያህል ሰዎች ለሞት የተዳረጉባት ሜክሲኮ በበኩሏ፤ በሟቾች ቁጥር በ3ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
ኮሮና ቫይረስ በ55 የአፍሪካ አገራት እስካለፈው ሃሙስ አመሻሽ ድረስ በድምሩ ከ1.15 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ማጥቃቱን የዘገበው ኦል አፍሪካን ኒውስ፣ የሟቾች ቁጥር 27 ሺህ፣ ያገገሙት ሰዎች ቁጥር ደግሞ 870 ሺህ ያህል መድረሱን አመልክቷል፡፡ ደቡብ አፍሪካ በ596 ሺህ ተጠቂዎችና በ12 ሺህ በላይ ሟቾች ከአህጉሩ ቫይረሱ ከፍተኛ ጥፋት ያደረሰባት ቀዳሚዋ አገር ስትሆን፣ የተጠቂዎች ቁጥር በግብጽ ወደ 97 ሺህ፣ በናይጀሪያ ወደ 51 ሺህ፣ በአልጀሪያ ወደ 40 ሺህ፣ በጋና ደግሞ ወደ 43 ሺህ መጠጋቱ ተነግሯል፡፡
ባለፉት ቀናት በተለያዩ የአውሮፓ አገራት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ ዕለታዊ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች መመዝገባቸውን የዘገበው ሮይተርስ፣ በአውሮፓ በየዕለቱ በአማካይ 26 ሺህ አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች እየተመዘገቡ እንደሆነ መነገሩን አመልክቷል፡፡ ባለፈው ረቡዕ ብቻ በጣሊያን 642፣ በስፔን 3 ሺህ 715 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ሃሙስ ዕለት ደግሞ በጀርመን 1 ሺህ 707 የቫይረሱ ተጠቂዎች መመዝገባቸውን አስታውቋል፡፡
በሕንድ ከትናንት በስቲያ ብቻ 69 ሺህ 672 ያህል ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፣ ይህም በአገሪቱ በአንድ ቀን የተመዘገበ ከፍተኛው ቁጥር መሆኑን ሂንዱስታን ታይምስ የዘገበ ሲሆን፣ በአገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ2.8  ሚሊዮን ማለፉና የሟቾች ቁጥር ደግሞ ወደ 54 ሺህ መጠጋቱ ተነግሯል፡፡
በተያያዘ ዜና፤ አገራት በኮሮና ቫይረስ ክትባትና መድሃኒቶች ላይ የጀመሯቸውን ምርምሮች አጠናክረው የቀጠሉ ሲሆን፣ ሲኖፋርም የተባለው የቻይና መድሃኒት አምራች ኩባንያ እስከ መጪዎቹ አራት ወራት የኮሮና ቫይረስ ክትባቱን ምርምር አጠናቅቆ በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች በአነስተኛ ዋጋ ለገበያ እንደሚያቀርብ ያስታወቀ ሲሆን፣ አውስትራሊያ በበኩሏ ወደ መጨረሻው የምርምር ምዕራፍ የተሸጋገረውን የኮሮና ቫይረስ ክትባቷን በስኬት ካጠናቀቀች 25 ሚሊየን ዜጎቿን በነጻ ለመከተብ ቃል መግባቷን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበኩሉ፤ ከአራት ወራት በኋላ በመላው አለም 265 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ ለምግብ እጥረትና ረሃብ ሊጋለጡ እንደሚችሉ ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ ያስጠነቀቀ ሲሆን፣ በወረርሽኙ ሳቢያ ለኪሳራ የሚዳረጉ ኩባንያዎች ቁጥር መጨመሩም ተነግሯል፡፡
ግዙፉ የአውስትራሊያ አየር መንገድ ኳንታስ፣ ከኮሮና ወረርሽኝ መስፋፋት ጋር በተያያዘ በአመቱ ወደ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ኪሳራ እንደደረሰበትና ይህም ኩባንያው ባለፉት 100 አመታት ታሪኩ ገጥሞት የማያውቅ አስከፊ ኪሳራ መባሉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ዎልማርት በ523.9 ቢ ዶላር ገቢ፣ አምራኮ ደግሞ በ329.7 ቢ ዶ ላር ትርፍ ቀዳሚነቱን ይዘዋል

               ከአለማችን ኩባንያዎች መካከል በየአመቱ ከፍተኛ ገቢና ትርፍ ያስመዘገቡትን 500 ግዙፍ ኩባንያዎች ዝርዝር ይፋ የሚያደርገው ፎርቹን መጽሔት፤ ከሰሞኑም የ2019 የአለማችን ግዙፍ ኩባንያዎችን ዝርዝር ያወጣ ሲሆን የአሜሪካው ዎልማርት በ523.9 ቢሊዮን ዶላር ገቢ፣ የሳኡዲው የነዳጅ ኩባንያ አምራኮ ደግሞ በ329.7 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ የአንደኛነት ደረጃን ይዘዋል፡፡
ሲኖፔክ ግሩፕ 407 ቢሊዮን ዶላር፣ ስቴት ግሪድ 383.9 ቢሊዮን ዶላር፣ ቻይና ናሽናል ፔትሮሊየም 379.1 ቢሊዮን ዶላር፣ ሮያል ደች ሼል 352.1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት እንደ ቅደም ተከተላቸው ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ የያዙ የአለማችን ኩባንያዎች መሆናቸውንም ፎርቹን አስታውቋል፡፡
ከሳኡዲው አምራኮ በመቀጠል በአመቱ ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ ከፍተኛ ትርፍ ያስመዘገቡ የአለማችን ኩባንያዎች ደግሞ፣ 254.6 ቢሊዮን ዶላር ያተረፈው ቤክሻየር ሃታዌይ፣ 260.1 ቢሊዮን ዶላር ያተረፈው አፕል፣ 177 ቢሊዮን ዶላር ያተረፈው ኢንዱስትሪያል ኤንድ ኮመርሺያል ባንክ ኦፍ ቻይና እና 125.8 ቢሊዮን ዶላር ያተረፈው ማይክሮሶፍት ኩባንያ ናቸው፡፡
ከ32 አገራት ተመርጠው የተካተቱት የአመቱ የአለማችን 500 ግዙፍ ኩባንያዎች በፈረንጆች አመት 2019 በድምሩ 33.3 ትሪሊዮን ዶላር ገቢ እና 2.1 ትሪሊዮን ዶላር ትርፍ ማግኘታቸውን እንዲሁም ከ69.9 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠራቸውንም መጽሔቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

 ወደ 40 የሚጠጉ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ለህልፈተ ህይወት በተዳረጉባት ናሚቢያ፣ ከሰሞኑ የዝሆን አይነ ምድር ለኮሮና ቫይረስ ፍቱን መድሃኒት ነው የሚል ያልተጨበጠ መረጃ በስፋት መሰራጨቱን ተከትሎ፣ ነገርዬው በውድ ዋጋ በመሸጥ ላይ እንደሚገኝና በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች መሻማት መጀመራቸው ተዘግቧል፡፡
የኮሮና ተጠቂዎች ቁጥር ባለፈው ወር ብቻ በእጥፍ በጨመረባትና ስጋት ባየለባት በናሚቢያ የሚገኙ የባህላዊ ህክምና ባለሙያዎች የዝሆንን አይነ ምድር መታጠንና ማሽተት ለጉንፋን፣ ለነስር፣ ለራስ ምታትና ለሌሎችም የጤና እክሎች ፍቱን መድሀኒት እንደሆነ ሲናገሩ መቆየታቸውን የዘገበው አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ፤ ከሰሞኑ ደግሞ በማህበራዊ ድረገጾች ነገርዬው ከኮሮና ያድናል የሚል መረጃ መሰራጨቱንና ብዙዎች መሻማት መጀመራቸውን አስታውቋል፡፡
ከ4 ሺህ 464 በላይ ሰዎች በኮሮና የተጠቁባት ናሚቢያ የጤና ሚኒስትር ካሉምቢ ሻንጉላ ባለፈው ማክሰኞ በሰጡት መግለጫ፤ ዜጎች ባልተረጋገጠ መረጃ ተገፋፍተው ከኮሮና ቫይረስ ለመዳን ሲሉ ላልተገባ ወጪ በመዳረግ የዝሆን አይነ ምድር መጠቀማቸውን እንዲያቆሙ ማሳሰባቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ለሌላ የጤና እክል እንዳይጋለጡ ያላቸውን ስጋት መግለጻቸውንም አመልክቷል፡፡
የአገሪቱ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሮሚዮ ሙዩንዳ በበኩላቸው፤ የዝሆን አይነ ምድር ፍለጋ የአገሪቱን ብሔራዊ ፓርኮች ጥሰው በመግባት ላይ የሚገኙ ዜጎች፣ ከዚህ ድርጊታቸው ካልታቀቡ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ማስጠንቀቃቸው ተነግሯል፡፡