Administrator

Administrator

  በብዕር ስሙ “ገሞራው” በመባል የሚታወቀው ኃይሉ ገብረ ዮሐንስ ፣ ሐምሌ 1935 ዓ.ም በደብረ ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን አካባቢ፣ አዲስ አበባ ተወለደ። አባቱ መሪ ጌታ ገብረ ዮሐንስ ተሰማ፣ እናቱ ወ/ሮ አመለወርቅ ሀብተወልድ ይባላሉ።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ሲሆን፣ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅና በሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ተከታትሏል። ከዚያም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ፣ በኢትዮጵያ የቋንቋ ጥናትና የስነ ልሳን ትምህርት በመጀመሪያ ዲግሪ ተመረቀ። ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ከተመረቀ በኋላ በመጀመሪያ ተግባረዕድ ትምህርት ቤት፣ ቀጥሎም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መምህራን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት (ኮተቤ) በመምህርነት አገልግሏል።
በ1968 ዓ.ም ባገኘው የነፃ ትምህርት ዕድል ወደ ቻይና ሄዶ በቋንቋና በፊሎዞፊ መስክ ሁለተኛ ዲግሪውን የተቀበለ ሲሆን፤ ወደዚያ የተጓዘበትን ትምህርት ከአጠናቀቀ በኋላ በቻይና ቋንቋና ስነ-ጽሑፍ ላይ ምርምር አደረገ። የቻይና ስነ-ጽሑፍ ነፃነት የሌለው ሆኖ ስለታየው በመንግሥቱና በሥርዓቱ ላይ የፅሑፍ ትችትና ነቀፋ ሰነዘረ። በዚህ ምክንያት ከቻይና ወደ ስዊድን ሄደ። ከዚህ በኋላ ስደተኛ ሆኖ ቀረ።
ኃይሉ፣ እ.ኤ.አ ከ1980 እስከ 2010 በኖርዌይና ስዊድን ሀገሮች በስደት ሲኖር በትርፍ ጊዜው በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ከ30 በላይ ጽሑፎችን አስር መጻሕፍትን ለኅትመት አብቅቷል። ከእነዚህም ውስጥ ጥቂቱ የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. በረከተ መርገም፡- የግጥም መጽሐፍ ነው። የጻፈውና በንባብ ያስደመጠው ቀ.ኃ.ሥ. ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበረበት በ1959 ዓ.ም ሲሆን፣ ታትሞ ለንባብ የበቃው ግን በ1966 (ብርናንና ሰላም ማተሚያ ቤት)ነው። በድጋሚ እ.ኤ.አ. የካቲት 1980 ስዊድን አገር ታትሟል።
2. ፍንደቃ፡- በ1968 ዓ.ም ፣ አዲስ አበባ፣ ትንሣኤ ዘጉባዔ ማሚያ ቤት ታተመ።
3. ዜሮ ፊት አውራሪ፡- እ.ኤ.አ. ጥር 1980፣
4. ዛር ነው በሽታዋ:- እ.ኤ.አ. መጋቢት 1981፣
5. በናቴኮ ሴት ነኝ፡- እ.ኤ.አ. የካቲት 1982፣
6. ወይዘሪት ወይዘሮ፡- እ.ኤ.አ ግንቦት 1983.
7. እናትክን በሉልኝ፡- እ.ኤ.አ  ሕዳር 1984.
8. ቆርጠሃት ጣልልኝ፡- እ.ኤ.አ ሰኔ 1985፣
9. የመንጎሌ ጥሪ፡- እ.ኤ.አ. ጥቅምት 1985፣
10. የሽግግር ደባ፡- እ.ኤ.አ. የካቲት 1986፣
(ከተራ ቁጥር 2-10 የተጠቀሱት መጻሕፍት የታተሙት፣ በNina Printing press, Kungsangsvagen  25፣ S-753 23 Uppsala Sweden ማተሚያ ቤት ነው።)
ኃይሉ (ገሞራው)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቆይታው፣ የኢትዮጵያ ተማሪዎችን እንቅስቃሴ በብዕሩ በማጋጋል የታወቀ ነበር። በዚህም የተነሳ በተደጋጋሚ የእስር ቤት ሰለባ ከመሆኑም በላይ ከዩኒቨርሲቲው እስከ መባረር ደርሶ ነበር። በሕዝቡ፣ በተለይም በዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አድናቆት፣ እውቅናና ሽልማት ያገኘበት “በረከተ መርገም” የተባለው ግጥም ነው። በ1960ዎቹ ውስጥ የነበሩት የመንግስት ፀጥታ ሠራተኞችና ፖሊሶች “ባለ መርዛሙ ብዕር” ብለው ይጠሩት እንደነበር ይታወቃል። ከ“መርዛሙ ብዕር” የቀለም ጠብታ ለአብነት እነሆ፡-
“በመንቃት ላይ ባሉ ፍጡራን መካከል፤
ሕይወት የምንለው እንደ ጥሬ እህል፤
በኑሮ ምጣድ ላይ ቢቆላ ቢማሰል፣
የበሰለው ያራል ጥሬው እስኪበስል።
በሰበብ አስባቡ ራስን ለመጥቀም፤
ንብረት ለማደርጀት እያጋነኑ ስም፤
በህግ አመካኝቶ እየተወጡ ቂም፤
ደግሞም ለመፈንጠዝ በማዕዘን ዓለም፤
ጭቆና ባርነት፣ አድልዖና አመጽ፣ እንዲስፋፋ በጣም።
እንዲሆን ከሆነ አስበው መርምረው፣ ስልጣንን የሰሩት፣
ደግሞም አስተዳደር፣ ሕግም ሆነ መንግሥት፤
እነዚያ ጀጁዎች የዋሆቹ ፍጥረት፣
ፕሌቶ አርስቶትል ሁላቸው ሊቃውንት፣
ይህን ግብዝ ሐሳብ፣ ከግብ ሳያደርሱት
በሥራ ላይ ሳይውል ገና ሲወጥኑት፣
ይሻላቸው ነበር፣ አፎቿን ከፋፍታ ብትውጣቸው መሬት”
ኃይሉ፣ ከሚወዳት ሀገሩ ርቆ፣ ብሶቱን ሲሰማለት ከነበረው ወገኑ ተለይቶ፣ ለ35 ዓመታት በቻይና፣ በቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት፣ በኖርዌይና በስዊድን እየተዘዋወረ ሲኖር፣ በርከት ያሉ ጽሑፎችን በግእዝ፣ በአማርኛ፣ በኖርዊጂያንና በስዊድንኛ ቋንቋዎች አበርክቷል።
ይህ ታዋቂ ገጣሚ በሀገራችን የተፈራረቁ የመንግስት ስርዓቶችን አንዱንም ደግፎ አያውቅም። ይልቁንም ባለበት ሀገር ሆኖ በተባ ብዕሩ ሲሄሳቸውና ሲነቅፋቸው ኖሯል።
ኃይሉ (ገሞራው) ባደረበት ፅኑ ሕመም ምክንያት በተወለደ 72 ዓመቱ ጥቅምት 30 ቀን 2007 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። በኑዛዜው መሰረት አስክሬኑ ከኖረበት ስዊድን፣ ወደሚወዳት ሀገሩ መጥቶ፣ በደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ዐረፈ።
(በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ከታተመው “ማህደረ ደራስያን" አዲስ መፅሐፍ የተወሰደ) መላው አለም ውጤታማነታቸው ከተረጋገጠ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች ጋር ተመሳስለው የተሰሩና ለጤና ጎጂ የሆኑ ሃሰተኛ ክትባቶችን በህገወጥ መንገድ በድብቅ ለመሸጥና ትክክለኛ ክትባቶችን መዝረፍን ጨምሮ በርካታ “ኮሮና ነክ ወንጀሎችን” ለመፈጸም ያቆበቆቡ የተደራጁ ወንጀለኞችን ነቅቶ እንዲጠብቅ አለማቀፉ የፖሊስ ተቋም ኢንተርፖል አስጠንቅቋል፡፡
የተለያዩ አገራት ኩባንያዎችና የምርምር ተቋማት ውጤታማነታቸው የተረጋገጡ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ጥቅም ላይ ለማዋል የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ በደረሱበትና አገራት ክትባቶችን ቀድመው ለማግኘት በሚሯሯጡበት እንዲሁም የግዢ ስምምነት በመፈጸም ላይ በሚገኙበት በአሁኑ ወቅት፣ የተደራጁ ወንጀለኛ ቡድኖች ሃሰተኛ ክትባቶችን ለመቸብቸብ እንዲሁም ትክክለኛ ክትባቶችን ለመዝረፍ እየተዘጋጁ እንደሚገኙ መረጃ ደርሶኛል ብሏል ኢንተርፖል ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ።
ተቀማጭነቱ በፈረንሳይ የሆነው አለማቀፉ የፖሊስ ትብብር ተቋም ኢንተርፖል፣ በአባልነት ላቀፋቸው 194 የአለማችን አገራት በላከው የማስጠንቀቂያ መልዕክት፣ የተደራጁና ረጅም የወንጀል ሰንሰለት የፈጠሩ ወንጀለኞች ከኮሮና ክትባቶች ጋር በተያያዘ አካላዊም ሆነ በኢንተርኔት በኩል የሚካሄድ የወንጀል ድርጊት ሊፈጽሙ ስለሚችሉ የህግ አስከባሪ አካላት ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተለያዩ የአለማችን አገራት ባልተጠበቀ ሁኔታ ለስግብግብ ወንጀለኞች መጠቀሚያ መልካም እድል ከሆነ መሰነባበቱን ያስታወሰው ተቋሙ፣ በቀጣይም ከጥራት በታች የሆኑ ሃሰተኛ ክትባቶችን በድብቅ አምርቶ መሸጥ፣ የክትባቶች ዝርፊያና ህገወጥ የክትባት ማስታወቂያዎችን ጨምሮ ኮሮና ተኮር የወንጀል ወረርሽኝ በስፋት ሊሰራጭ እንደሚችል ያለውን ስጋትም ገልጧል፡፡
ወንጀለኛ ቡድኖቹ ከዚህ ባለፈም ሃሰተኛ የኮሮና መመርመሪያ መሳሪያዎችን በህገወጥ መንገድ አምርተው ለገበያ የማቅረብ ዕድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ የጠቆመው ተቋሙ፣ የአለም አገራት መንግስታት፣ የጸጥታ ሃይሎች፣ ህግ አስፈጻሚና የደህንነት ተቋማት እነዚህን ወንጀለኞች ለመከላከልና በቁጥጥር ስር ለማዋል በንቃት እንዲሰሩና ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ጥሪ አቅርቧል፡፡
መድሃኒቶችን በመሸጥ ስራ ላይ ከተሰማሩ 3 ሺህ ያህል ድረገጾች ላይ ባደረገው ምርመራ፣ ከ1 ሺህ 700 በላይ የሚሆኑት ለወንጀል የተቋቋሙ ወይም በቫይረስ አማካይነት የኢንተርኔት ጥቃት የሚያደርሱ መሆናቸውን ለማረጋገጥ መቻሉን የሚናገረው ተቋሙ፣ ህብረተሰቡ በድረገጾች አማካይነት ከሚከናወኑና ሰዎችን ለሞት አደጋ ብሎም ለከፋ የጤና ችግሮች ከሚያጋልጡ የሃሰተኛ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ሽያጮች ራሱን እንዲያርቅም ምክሩን ለግሷል፡፡
የአሜሪካው የአገር ውስጥ ደህንነት ምርመራ ቢሮ በበኩሉ፣ ከሰሞኑ በአገሪቱ ሁለት የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች እውቅና አግኝተው በስራ ላይ ይውላሉ ተብሎ ከመጠበቁ ጋር በተያያዘ አጭበርባሪዎች ይበራከታሉ ተብሎ በመገመቱ አዲስ ዘመቻ እንደሚጀምር ማስታወቁን ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል፡፡
ከዚህ በፊት ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ባደረገው ዘመቻ ከጥራት በታች የሆኑ የፊት መከላከያ ጭንብሎችንና ለኮሮና ፈዋሽነቱ ያልተረጋገጠውን ክሎሮኪን የተባለ የወባ መድሃኒት አስመስለው ማምረትና ማከፋፈልን ጨምሮ ከ700 በላይ ኮሮና ነክ ወንጀሎችን መመርመሩን ያስታወሰው ቢሮው፣ ከመሰል ህገወጥ ንግድ የተገኘ 27 ሚሊዮን ዶላር መያዙንና በመሰል ድርጊቶች ላይ ተሰማርተው የተገኙ ከ70 ሺህ በላይ ህገወጥ ድረገጾችን መዝጋቱንም አክሎ ገልጧል፡፡
በሌሎች የኮሮና ቫይረስ ዜናዎች ደግሞ፣ ብሪታኒያ ፋይዘርና ባዮንቴክ የተባሉት ኩባንያዎች ያመረቱትና ከኮሮና ቫይረስን በመከላከል ረገድ 95 በመቶ አስተማማኝ እንደሆነ የተረጋገጠው የኮሮና ቫይረስ ክትባት በግዛቷ ውስጥ በጥቅም ላይ እንዲውል በመፍቀድ ከአለማችን አገራት ቀዳሚ መሆኗን የዘገበው ቢቢሲ፣ አገሪቱ ከኩባንያዎቹ 40 ሚሊዮን ክትባቶችን ማዘዟንና የአገሪቱ የመድሃኒት ቁጥጥር ተቋም ክትባቱ ከመጪው ሳምንት ጀምሮ ጥቅም ላይ መዋል ይችላል ሲል ፈቃድ መስጠቱንም ገልጧል፡፡ የጃፓን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መንግስት በበኩሉ፤ ባለፈው ረቡዕ ባሳለፈው ውሳኔ፣ መንግስት በአገሪቱ ውስጥ ለሚኖሩት 126 ሚሊዮን ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ክትባትን በነጻ እንዲያዳርስ መወሰኑን ያሁ ኒውስ የዘገበ  ሲሆን፣ የአገሪቱ መንግስት ሞዴርና ከተባለው የክትባት አምራች ኩባንያ ለ85 ሚሊዮን ሰዎች፣ አስትራዜንካ ከተባለው ክትባት ደግሞ ለ120 ሚሊዮን ሰዎች የሚሆን ክትባት ማዘዙን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ቢዝነስ ኢንሳይደር በበኩሉ፤ የሰሜን ኮርያው መሪ ኪም ጁንግ ኡን በቻይና የተመረተና ውጤታማነቱ ያልተረጋገጠ የኮሮና ቫይረስ ክትባት መከተባቸውን የዘገበ ሲሆን፣ ባለፉት ሶስት ሳምንታት ሌሎች የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናትና ቤተሰቦቻቸውም ክትባቱን ወስደዋል መባሉን አክሎ ገልጧል፡፡  ኢንተርናሽናል ኤስኦኤስ የተባለው ተቋም በ2021 የፈረንጆች አመት ለጎብኝዎችና መንገደኞች እጅግ አደገኛ የሆኑና ከፍተኛ የደህንነት ስጋት ይኖርባቸዋል ያላቸውን የአለማችን አገራት ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ሊቢያ፣ ሶርያና አፍጋኒስታን ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
የፖለቲካ ነውጥ፣ ማህበራዊ አለመረጋጋት፣ የደህንነት ሁኔታ፣ የአደጋ ጊዜ ምላሽ አገልግሎቶች ሁኔታ እና የወንጀል ድርጊቶችን ጨምሮ በተለያዩ የደህንነት ስጋት መመዘኛዎች ተጠቅሞ በመገምገም፣ የአለማችን አገራትን የአመቱ የስጋት ደረጃ ይፋ ያደረገው ተቋሙ፣ ኢራቅና ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ የአራተኛና አምስተኛ ደረጃ መያዛቸውንም አመልክቷል፡፡
በአመቱ እጅግ አነስተኛ የስጋት ደረጃ ይኖራቸዋል ተብለው በሪፖርቱ የተጠቀሱት ሰባት የአለማችን አገራት በሙሉ የአውሮፓ አገራት ሲሆኑ፣ አይስላንድ፣ ዴንማርክ፣ ኖርዌይ፣ ፊንላንድ፣ ስዊዘርላንድ፣ ስሎቫኒያና ሉግዘምበርግ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአንደኛ እስከ ሰባተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተጓዦች መይም መንገደኞች ላይ እጅግ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረባቸው ሶስቱ የአለማችን አገራት ብሎ ተቋሙ የጠቀሳቸው አገራት ሩስያ፣ ዩክሬንና ኦስትሪያ ሲሆኑ፤ በአንጻሩ አነስተኛ ተጽዕኖ ያደረሰባቸው ያላቸው አገራት ደግሞ ኒውዚላንድ፣ ታንዛኒያና ኒካራጓ ናቸው፡፡


በአለም ዙሪያ በየ100 ሰከንዱ 1 ህጻን በኤችአይቪ ቫይረስ እንደሚጠቃ እና ባለፈው የፈረንጆች አመት 2019 በመላው አለም 110 ሺህ ያህል ህጻናት በኤድስ ምክንያት ለሞት መዳረጋቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ ከሰሞኑ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
በአመቱ በመላው አለም 320 ሺህ ያህል ህጻናትና ወጣቶች በቫይረሱ መያዛቸውን ያስታወቀው ድርጅቱ፤ በቫይረሱ የሚያዙና ለሞት የሚዳረጉ ህጻናት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ሲሆን የጸረ ኤች አይቪ ህክምና አገልግሎት በበቂ ሁኔታ እያገኙ እንዳልሆነም ገልጧል፡፡
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ለህጻናት፣ ወጣቶችና ነፍሰጡር እናቶች የሚሰጡ የጸረ ኤች አይቪ ህክምና አገልግሎቶች በከፍተኛ ሁኔታ እየተስተጓጎሉ እንደሆነ የጠቆመው የድርጅቱ ሪፖርት፤ መንግስታት አገልግሎቶቹን ለማሟላት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸውም አመልክቷል፡፡
በ2019 የፈረንጆች አመት በመላው አለም 1.7 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በኤችአይቪ ቫይረስ መጠቃታቸውን ያስታወሰው የተመድ የዜና ድረገጽ በበኩሉ፣ በአመቱ በድምሩ 690 ሺህ ያህል ሰዎች ከኤችአይቪ ጋር በተያያዘ ለሞት መዳረጋቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡

 የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በቅርቡ ለንባብ ያበቁት “ኤ ፕሮሚስድ ላንድ” የተሰኘው መጽሐፍ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ በ1.7 ሚሊዮን ቅጂዎች መሸጡንና በዚህም አዲስ የሽያጭ ክብረወሰን ማስመዝገብ መቻሉን ዴይሊ ሜይል ዘግቧል፡፡
መጽሐፉ በአሜሪካና ካናዳ ታትሞ ለገበያ በቀረበበት የመጀመሪያው ቀን ብቻ ከ887 ሺህ በላይ ቅጂዎች እንደተሸጡ ያስታወሰው ዘገባው፣ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ደግሞ በ1 ሚሊዮን 710 ሺህ 443 ቅጂዎች በመሸጥ አዲስ ክብረ ወሰን ማስመዝገቡን ፔንጉዊን ራንደም ሃውስ የተባለው የመጽሐፉ አሳታሚ ድርጅት ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው አመልክቷል፡፡
ሽያጩ የወረቀት፣ የድምጽና የዲጂታል ቅጂዎችን እንደሚያጠቃልል የጠቆመው ዘገባው፣ በመጀመሪያ ዙር በ3.4 ሚሊዮን ቅጂዎች የታተመው “ኤ ፕሮሚስድ ላንድ” ከሰሞኑ በተጨማሪ ቅጂዎች እንደታተመና እስካሁን ድረስ ለህትመት የበቃው አጠቃላይ ቅጂ 4.3 ሚሊዮን መድረሱንም አክሎ ገልጧል፡፡

አለም በስልጣኔና በቴክኖሎጂ በረቀቀችበት በዛሬው ዘመን በመላው አለም ከ40 ሚሊዮን በላይ ሰዎች “የዘመናዊ ባርነት” ሰለቦች ሆነው እንደሚገኙ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
አለማቀፉ የስራ ድርጅት ባወጣው መግለጫ እንዳለው፣ በመላው አለም ከአስር ህጻናት አንዱ ወይም 150 ሚሊዮን የሚሆኑ ህጻናት ለዕድሜያቸው የማይመጥንና አደገኛ የግዳጅ የጉልበት ስራ በመስራት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ተጨማሪ 1 ሚሊዮን ያህል ህጻናትም በህገወጥ የሰዎች ዝወውር በቂ ክፍያ የማያገኙበትን ሥራ እንዲሰሩ ወይም ወሲባዊ ብዝበዛ እንዲፈጸምባቸው እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡
“የዘመናዊ ባርነት” ሰለቦች ከሆኑት 40 ሚሊዮን ያህል ሰዎች መካከል 25 ሚሊዮን ያህሉ የግዳጅ የጉልበት ስራ እንደሚሰሩና 15 ሚሊዮን ያህሉም ያለፈቃዳቸው ተገድደው ወደ ትዳር እንዲገቡ መደረጋቸውንም ድርጅቱ አስታውቋል፡፡
የጉልበት ስራ፣ የግዳጅ ጋብቻ፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ጨምሮ በተለያዩ የጥቃትና የሃይል ድርጊቶች ዜጎችን “የዘመናዊ ባርነት” የሚያደርጉ አካላት፣ በየአመቱ 150 ቢሊዮን ዶላር ያህል ትርፍ ያለአግባብ በማካበት ላይ እንደሚገኙ ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ ያስታወቀ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ በበኩላቸው፤ “የዘመናዊ ባርነት” ሰለቦች ሆነው ከሚገኙት የአለማችን አገራት ዜጎች መካከል 71 በመቶ የሚሆኑት ሴቶችና ልጃገረዶች መሆናቸውን በትዊተር ገጻቸው ባወጡት ጽሁፍ ገልጸዋል፡፡

 ኢስት አፍሪካ ኢንተርቴይመንትና ኢቨንት ኦርጋናይዘር ከፌደሬሽን ምክር ቤት ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና 10ሩ ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተሳተፉበት ቁንጅና ውድድር ነገ  ከቀኑ 7፡30 ጀምሮ በሸገር ፓርክ እንደሚካሄድ ተገለጸ።
የቁንጅና ውድድሩን ክልላቸውን በመወከል ከአንድ እስከ ሶስተኛ በመውጣት የሚያሸንፉ የሰላምና የአንድነት አምባሳደር ሆነው ክልሎቻቸውን እንደሚገለግሉ የኢስት አፍሪካ ኢንተርቴይመንትና ኢቨንት ኦርጋናይዘር መስራችና ዋና ስራ አስኪጅ አቶ ሞቲ ሞረዳ ባለፈው ረቡዕ ረፋድ ላይ በሀያት ሬጀንዲ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀው ነገ በሚካሄደው ውድድር ላይ ሁለተኛና ሶስተኛ የሚወጡ ቆነጃጅት ሽልማትና አምባሳደርነታቸውን ከክብር እንግዶች እንደሚቀበሉም   ተናግረዋል።
ከየክልሉ 1ኛ የሚወጡ አሸናፊዎች ደግሞ 15ኛው የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ዕለት ከኢፌደሪ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴና ከጠቅላይ ሚንስትር አቢይ አህመድ (ዶ/ር) እጅ እንደሚቀበሉም ታውቋል።
የቁንጅና ውድድሩ ዋና አላማ አሁን አገራችን ያለችበትን በዘርና በሃይማኖት ተከፋፍሎ መባላትና መናቆር ያስከተለውን ችግር ለመቅረፍ ቆነጃጅቱ ለየክክላቸው ወጣቶች አንድነት፣ ፍቅርና ሰላም ላይ አበክረው እንደሚሰሩና በቀጣዩ አመት ለቀጣዮቹ አምባሰደሮች ሃላፊነታቸውን እስከሚያስረክቡ ድረስ ይሰራሉም ተብሏል።


 ሰምና ወርቅ ሚዲያና ኢንተርቴይመንት የሚያዘጋጀው ወርሃዊ የኪነ-ጥበብ ምሽት የዚህ ወር መሰናዶ “የሀገሬ ጥያቄ” በሚል ርዕስ የፊታችን ረቡዕ ህዳር 30 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ 11፡30 ጀምሮ ጊዮን ሆቴል ውስጥ በሚገኘው ግሮቭ ጋርደን ዎክ ውስጥ ይካሄዳል።
ይህ ምሽት በኮቪድ 19 የምሽት መቋረጦች በኋላ የሚካሄድ የሰምና ወርቅ የመጀመሪያው መሰናዶ እንደሚሆን የመርሃ ግብሩ አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ዓለሙ ተናግሯል።
በዕለቱ ወዳጄነህ ማህረነ (ዶ/ር)፣ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ፣ አንጋፋዋ ከያኒ አለምፀሐይ ወዳጆ ፣ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት፣ ረ/ፕ ነብዩ ባዬ፣ ገጣሚ ኤፍሬም ስዩም፣ አርቲስት ሱራፌል ተካ፣ ኮሜዲያን አዝመራው ሙሉሰው፣ ጋዜጠኛ ሰለሞን ሀይለየሱስ፣ ገጣሚ ገዛኸኝ ጤራ እና ገጣሚ መንበረማርያም ሀይሉ ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ ተብሏል። የመግቢያ ዋጋው 100 ብር ሲሆን ትኬቶቹ በብሄራዊ ቴአትር የሰምና ወርቅ የመፅሐፍት አውደ ርዕይ ላይ እንደሚገኙም ታውቋል።

  ሰዓሊ ኪሩቤል መልኬ “ከእኔ እስከ ቤቴ”  በሚል ርዕስ ያዘጋጀው የስዕል ዓውደ ትርዒት ሰኞ በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴስ ይከፈታል።  
 በአውደ ርዕዩ መግለጫ ላይ እንዳሰፈረው በስራዎቹ የአልባሳትን ታሪካዊ አመጣጥ ለማሳየት አይምክርም፡፡ ይልቁንም ከዚህ ሰፊ ታሪክ ውስጥ ጨርቅ እንዴት የሥነ-ጥበብ አንድ ዘርፍ ሆኖ እንደመጣ ትንሽ ታሪካዊ ዳራውን ጥቆማ በመስጠት ከሥዕል ሥራው ጋር ያለውን ሐሣብ ያይዛል፡፡ ጨርቅን ከቀለም ጋር ወይም ከሌላ ቁስ ጋር በማዋቀርና በማዋሀድ የሚሰራውን፤ “Quilt Art” በመባል የሚታወቀውን ዘርፍ ከራሱ   አጋጣሚ በማዛመድ  የሚያሳይበት መሆኑንም  ባዘጋጀው ፅሁፍ አብራርቷል።
ሰዓሊ ኪሩቤል  መልኬ ስለሚያቀርባቸው ሥራዎች ሲገልፅ በተለያዩ ጊዜያትና ሐሳቦች ላይ ተሰርተው የተጠራቀሙ  መሆናቸውን ሲጠቅስ
…ቤቴ ሐሳቤ ነው በሚል የስዕሎችን ጉዞ አጠቃሎታል። “ከእኔ እስከ ቤቴ”  የሥዕልዓውደ ትርኢት በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴስ እስከ ታሕሳስ 23 ለዕይታ ይቀርባል።

  በአወዛጋቢው የ2020 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የገጠማቸውን ያልተጠበቀ መራራ ሽንፈት አሜን ብለው ለመቀበል አሻፈረኝ ሲሉ የሰነበቱት ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ከ4 አመታት በኋላ በሚካሄደው የ2024 ምርጫ ዳግም እንደሚወዳደሩ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ መናገራቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
የምርጫ ማጭበርበር ተፈጽሞብኛል በሚል ያቀረቧቸው ተደጋጋሚ ክሶች ሰሚ ያላገኙላቸውና እስካሁንም ድረስ  ሽንፈታቸውን መቀበላቸውን በይፋ ያላስታወቁት ትራምፕ፣ ባለፈው ማክሰኞ በዋይት ሃውስ ባደረጉት ንግግር በስልጣናቸው ላይ ለመቆየት የቻሉትን እያደረጉ እንደሚገኙና ካልሆነ ግን በቀጣዩ ምርጫ ተወዳድረው ወደ ነጩ ቤተ መንግስት እንደሚመለሱ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡
ትራምፕ በቀጣዩ ምርጫ ለመወዳደር ሃሳብ እንዳላቸው ለአንዳንድ ደጋፊዎቻቸውና አማካሪዎቻቸው በሚስጥር መናገራቸውን አልፎ ተርፎም የምርጫ ቅስቀሳቸውን የሚጀምሩት ተመራጩ ጆ ባይደን በዓለ ሲመታቸውን በሚያከናውኑበት ቀን እንደሆነ መግለጻቸውን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሲዘግቡ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ በምርጫው እንደሚወዳደሩ በይፋ ሲናገሩ ግን ይህ የመጀመሪያቸው መሆኑንም አክሎ ገልጧል።
በአሜሪካ ታሪክ በምርጫ ተሸንፈው ከስልጣን ከወረዱ በኋላ ዳግም በሌላ ምርጫ ተወዳድረው ወደ ስልጣን የተመለሱ ብቸኛው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ግሮቨር ክሊቭላንድ መሆናቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ እ.ኤ.አ በ1884 አሸንፈው ስልጣን የያዙት ግለሰቡ በምርጫ ስልጣን ከለቀቁ በኋላ እ.ኤ.አ በ1892 ዳግም በምርጫ አሸንፈው ወደ ነጩ ቤተ መንግስት መመለሳቸውን አክሎ ገልጧል፡፡
ከአወዛጋቢው ምርጫ ጋር በተያያዘ ቢቢሲ ባለፈው ረቡዕ ባወጣው ዜና እንዳለው፣ የአሜሪካ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዊሊያም ባር፣ የአገሪቱ ፍትህ መስሪያ ቤት ምርጫው ተጭበርብሯል ብሎ እንደማያምንና የትራምፕን ተጭበርብሪያለሁ ክስ የሚደግፍ ማስረጃ እንዳላገኘ ቢያስታውቁም፣ ትራምፕ ግን ዐቃቤ ሕጉ ይህን ባሉ በሰዓታት ልዩነት “ድምጼን ተሰርቄአለሁ” የሚሉ ፅሁፎችን በትዊተር ገጻቸው ላይ መለጠፋቸውን ገልጧል፡፡