Administrator

Administrator

Tuesday, 06 October 2020 08:01

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

 "ሰው አትከተሉ፤ ጥበብን እንጂ"

አሜሪካውያን ባለጸጋዎቹ ቢል ጌትስና ዋረን በፌት፣ በንባባቸው በእጅጉ ይታወቃሉ። ቢል ጌትስ በዓመት እስከ 50 መጽሐፍት ድረስ  ያነባሉ። ማንበብ ብቻ አይደለም፡፡ #ህይወቴንና ስራዬን የለወጡ የኔ ምርጥ መጻሕፍት እነዚህ ናቸው; በማለት ከነጭብጣቸው ጭምር በየሄዱበት ሁሉ ለተማሪዎች፣ ለሰራተኞችና ለባልደረቦቻቸው ያስተዋውቃሉ። ድረ ገጻቸው ተናፋቂ ነው። በዕውቀት ማካፈል የተዋበ እንጂ የአተካራ ገጽ አይደለም።
ባለፈው ወር 90ኛ ዓመታቸውን የደፈኑትና የቢል ጌትስ የቅርብ ወዳጅ የሆኑት ዋረን በፌትም የባሰባቸው የንባብ ቀበኛ ናቸው። “በቀን ለስድስት ሰዓታት ያህል አነባለሁ” ይላሉ፡፡ እንዲህ እንዳሁኑ እርጅና ሳይጫጫናቸው በፊት ከ500 ገጽ በላይ በአንድ ቀን ፉት ያደርነበር። "ሀብቴን የገነባሁት በመጻሕፍት ነው" ሲሉ የንባብን ፋይዳ ደጋግመው ተናግረዋል። ባለጸጋው በፌት ለሌሎች ሲመክሩም፤ “እውነትን ከመጻሕፍት ውስጥ የመፈተሽና የመመርመር ስራ ላይ አተኩሩ እንጂ እከሌ ስለጻፈው እያላችሁ መጽሐፉ ውስጥ ካለው እውነት ይልቅ ሰው አትከተሉ።” ይላሉ። ከሰው ይልቅ ጥበብን ተከተሉ ነው ነገርየው!

 ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ህልም ተመልካች፣ አንድ ቀራጺ ሃውልተኛ፣ አንድ ባህታዊ ፀሎተኛ፣ ወደ አንድ መንገድ ይሄዱ ነበር፡፡ ብዙ ከተጓዙ በኋላ ህልም ተመልካቹ አንድ ህልም አየ፡፡ ይኸውም “በመንገዳችን ላይ አንድ ትልቅ ዋርካ እናገኝና ቀራጺው ጓደኛችን ያንን ዋርካ ወደ ቆንጆ ሴት ቅርጽ ሲለውጠው አየሁ” አለ፡፡
ይኼኔ ቀራጺው፡- “እውነት ዋርካውን ካገኘን ያለጥርጥር የተባለችውን ሴት እቀርፃታለሁ፡፡” አለ።
ፀሎተኛው ደግሞ፡- “ያላችሁት እውነት ከሆነ፤ እኔ አምላኬን ነፍስ እንዲሰጣት እለምነዋለሁ” አለ፡፡
ጉዟቸውን ቀጠሉ፡፡ ህልመኛው እንዳለውም አንድ ትልቅ የዋርካ ዛፍ አገኘ፡፡ ቀራጺውም ያንን ግዙፍ ዛፍ ቆርጦ ቅርጽ ማውጣት ጀመረ፡፡ ከብዙ ቀናት ድካም በኋላ ምን የመሰለች ውብና አስገራሚ ቅርጽ ያላት ሴት አነጸና አወጣ፡፡ ሁሉም በቁንጅናዋ እየተደመሙ ሳሉ፣ ያ ባህታዊ ፀሎተኛ “ይህች ሴት ነፍስ ቢኖራት እኮ እንዴት ያለች ተአምር ትሆን ነበር፡፡” ብሎ ነፍስ ትዘራ ዘንድ ወደ አምላኩ ፀሎት ማድረግ ቀጠለ፡፡
ከብዙ ቀንና ሌሊት ምህላ ፀሎት በኋላ ያቺ እንስት መናገርና እንደልብ መንቀሳቀስ ጀመረች፡፡ ታላቅ ተአምርም ሆነች፡፡
ሁሉም በየፊናው ይህች ቆንጆ እንስት “የኔ ናት! የኔ ናት!” ማለት ጀመረ፡፡
በመጀመሪያ በህልሙ ያያት ሰው፤
“ጐበዝ! የኔ ነገር የሚያሻማ አይደለም” ይህችን ሴት እኔ በህልሜ ባላያት ኖሮ ማንኛችሁም ቀጥሎ የሰራችሁትን ተአምር ባልሰራችሁም ነበር፡፡ ስለዚህ ይህች ሴት በዋናነት የኔ ሀብት ናት። እናም ማንኛችሁም ብትሆኑ የኔን ፍቃድ ማግኘት ይገባችኋል፡፡” ሲል የአዋጅ ያህል ጮክ ብሎ ተናገረ፡፡
ሀውልተኛው በበኩሉ፤
“ጐበዝ! ህልመኛው በህልሙ ከማየት በስተቀር ዋርካውን ወደ ቅርጽ የመቀየር ምንም ሞያዊ ክህሎት ስለሌለው፣ ምንም አይነት ተጨባጭ ተግባር የማከናወን ድርጊት አልፈፀመም፡፡ አሁንም ሌላ ዛፍ ብናገኝ ምንም ሊያደርግ አይችልም፡፡” ሲል አጥብቆ ተከራከረ፡፡
ቀጥሎ ጋዜጠኛው እንዲህ አለ፤
“ጐበዝ! ምንም አላችሁ ምንም ይህች ሴት የምትገባው ለኔ ነው፡፡ ምነው ቢሉ… በመጀመሪያ እንጨት፣ ቀጥላም የእንጨት ቅርጽ፣ እንጂ ሰው ለመሆን አትችልም ነበረና! ዋናውን ጉዳይ ባትዘነጉ ጥሩ ነው፡፡ ራሷን ብትጠይቋት በምን አንደበቷ መልስ ትሰጣችሁ ነበር?” አለ፡፡
በዚህን ጊዜ የመጀመሪያው ትገባኛለች ባይ፡-
“እንደውም እራሷ ትናገር፤ የማን እንደሆነች እንጠይቃት” አለ፡፡
ሁለተኛውም፡- “አሁን መልካም ሃሳብ መጣ፤ እራሷ ትጠየቅና ትገላግለን!” አለ፤ በእፎይታ እየተነፈሰ፡፡
ሦስተኛው፤ “እኔም በዚህ ሃሳብ እስማማለሁ፡፡ እሺ ቆንጂት አባቴ ማን ነው ትያለሽ?” አለና ጠየቃት፡፡
ይሄን ጊዜ ቆንጆዋ ሴት፡-
“በበኩሌ፤ መልሴ አንድና የማያሻማ ነው፤ ይኸውም “ሁሉም ነገር ወደመጣበት ይመለሳል” የሚለውን ቃል አትዘንጉ” አለች፡፡
ያ ዋርካ ወደነበረበት ተመልሶ ተሰነጠቀ፡፡ ቆንጆዋ ሴት ተመልሳ ወደ ዋርካዋ ገባች፡፡
*   *   *
ሁሉም ነገር ወደመጣበት መመለሱ “አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ” የሚለውን ቃል ያስታውሰናል፡፡ በየትኛውም መልኩ መወለድ፣ ማደግና መሞት ተመላላሽ እውነታዎች ናቸው፡፡ ከድግግሞሹ መማር ያለብን ግን እኛ ነን፡፡ ያወላለድም፣ የማሳደግም፣ የመሞትም መልክ መልክ አለውና፣ ያንን ተጠንቅቆ በማሳደግ የተሻለ ነገር መፍጠር ይሁነኝ ተብሎ መተግበር ያለበት ጉዳይ ይሆናል፡፡
ዛሬ በሃገራችን ዋና ፋይዳ ናቸው ከምንላቸው ነገሮች አንዱ ለሞያና ለባለሙያ የምንሰጠው ከበሬታ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሞያ የራሱ ባህርይ እንዳለው ሁሉ አተገባበሩም የራሱ ስልት፣ ሚዛን፣ እንዲሁም ስነምግባር አለው፡፡ በተለይ ሙያዊ ክህሎትና ስነምግባር ካልተቀናጁ፣ ግማሽ - ጐፈሬ ግማሽ - ልጭት የሚባለውን አይነት ንፍቀ - ክበብ ይፈጥራል፡፡ አንድ አስተዋይና አሳቢ - ሰው (Thinker) እንዳለው፤ አንድን ሥርዓት ሙሉ አድርጐ አለማደራጀት በሶሻሊስት ቤተ መቅደስ ውስጥ ካፒታሊስት ቄሶች ወይም ቀዳሾች እንዲቀድሱ ማድረግ ነው፡፡ አንድም፤ አንድን ማሽን ግማሹን በእጅ የሚዞር (Along) ግማሹን በአውቶማቲክ መንገድ ወይም (Digital) መግጠም ነው። ያ ሞተር ከነአካቴው እንዳይንቀሳቀስ የማድረግ እቅድ ያለን ካልሆነ በስተቀር በእውነት ውጤት ለማምጣት የማይበጅና የግብር - ይውጣ  ሥራ ነው የሚሆነው፡፡
በአንዳንድ የሥራ መስክ ሠራተኛውን በአዲስ ሠራተኛ የመለወጥ ሃሳብ ቢኖር፣ ያለውን ሠራተኛ ሙልጭ አድርጐ ማስወጣት ወይም ማባረር አደጋ እንዳለው ይነገራል፡፡ ነባሩን ሥራ የሚያስተባብር የሚያለማምድ በተለይም ለዘመናት የሠራ ሠራተኛ ብቻ ሊሠራው የሚችል ዘርፍ በጥንቃቄ ሊታይና እንክብካቤ ሊደረግለት የሚገባ ልዩ ሥራ ነው፡፡ ወረቀት የማይተካው፤ የተካበተ ልምድ ብቻ ሊሠራው የሚችል ፍፁም ወሳኝ ሥራ ያለበት ቦታ አለ፡፡ ሁሉንም ሥራ በማሽን እንተካለን ልንል ብንደፍር፤ ፈረንጆቹ እንደሚሉት፤ “even the most complicated Machine needs some one to push the button” (የመጨረሻው የረቀቀና ውስብስብ የሆነ ማሽን እንኳ የማስነሻዋን ቁልፍ የሚጫን አንድ ጣት ያስፈልገዋል እንደማለት መሆኑ ነው፡፡) ስለሆነም በመጨረሻ ሰዓት፣ ከማሽኑ ጀርባ የሚቆም አንቀሳቃሽ ሰው ያሻል ማለት ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ማሽን በመምጣቱ ምክንያት ከሥራ የሚባረረውን የሰው ኃይል ከጉዳይ ሳንጥፍ መሆኑ ነው፡፡
ዛሬ በሀገራችንም፣ በአህጉራችንም፣ በአለማችንም፤ ለያዥ ለገራዥ አስቸግሮ  የእውር የድንብር ከሚያስኬደው የኮሮና ወረርሽኝ ስጋት ሳንላቀቅ፤ ትምህርት ቤቶች ሊከፈቱ ይችላሉ የሚለው እሳቤ አሳሳቢነቱ ወዲህ ወዲያ የሌለው መሆኑን እየተገነዘብን፤ የሚደረገውን ጥንቃቄ - በተለይ ከሞላ ጐደል በሽታው የሌለ እስኪመስል የተዘነጋበት ወይም የተናቀበት አሊያም ወደ ድሮው ግዴለሽነት እየተመለስን ያለን በሚመስልበት ሁኔታ፤ “ሞት ቢዘገይ የቀረ ይመስላል”   የሚለውን ምሳሌያዊ አነጋገር የሚያስጠቅሰን ይመስላል፡፡ እውነቱ ግን፡- በሽታው አለ! ሰው እየሞተ ነው! በጭራሽ ሙሉ ለሙሉ ልናስወግደው የምንችልበት አቅም ላይ አይደለንም! አሁንም አንዘናጋ! ሰበብ አንፍጠር! “ዋዛ ፈዛዛ ልብ አያስገዛ” የሚለውን ተረትና ምሳሌ፤ አሁንም ልብ እንበል! ትምህርት ቤቶች ለበሽታው ለመጋለጥ አመቺ ሁኔታዎች ሊፈጠርባቸው ከሚችሉ ዋና ዋና ሥፍራዎች ውስጥ ናቸው! እንጠንቀቅላቸው! በሽታው፤ ህፃን፣ ወጣት፣ ጐልማሳ፣ አረጋዊ፣ አሮጊት አይልም፡፡ ስብስብ የሚበዛባቸው ቦታዎች ሁሉ ለወረርሽኙ መጋለጫዎች ናቸው፡፡ ቁጥጥሩ ይጥበቅ! ስህተት ካለ በጊዜ ይታረም! የሚቀመስ ያለው ለሌለው፣ ዛሬም እጁን ይዘርጋ! ባሕላዊ መተሳሰባችን ይጠንክር! ምዝበራ፣ ዘረፋ፣ ሌብነት፣ የኢኮኖሚ አሻጥር፣ ሙስና ለሀገር ንብረት አለመጠንቀቅ ወዘተ… ሞት ቢዘገይ የቀረ መምሰሉ ብቻ ሳይሆን ውድቀትም ቢዘገይ የቀረ እንዲመስለን ያደርጋልና፣ ጥንቃቄያችን ፍፁም እንዲሆን በሕዝብም በመንግሥትም ዘንድ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

Saturday, 03 October 2020 13:12

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

  አገሬን ፋና ላምሮት ላይ አየኋት፤ ፈራኋትም
                          (በድሉ ዋቅጅራ)


         ለወትሮው ሪሞት ጥሎኝ ካልሆነ የፋና ላምሮትን የድምጻውያን ውድድር አልከታተልም፡፡ ትላንት መጨረሻውን አየሁት፡፡ ውጤቱ ከታወቀ ጀምሮ የተወዳዳሪዎቹ አካባቢ ሰዎች፣ በተለመደው መንገድ ጎጥ ለይተው፣ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ውጊያ ገጥመዋል፡፡ አንዳንዶቹም ለሰፈራቸው ተወዳዳሪዎች የሽልማቱን ያህል ገንዘብ አዋጥተን እንሰጣለን እያሉ ነው፡፡ ይህ አይደንቅም፣ ቅኝታችን ሁሉ የጎጥ ነው፡፡ በጎጥ ሰው በሚገደልበት ሀገር፣ በጎጥ መሸለም ከጽድቅ ይቆጠራል፡፡ ሰዎች ስለዚህ ነገር ሲያወሩ ያሳዝነኛል፡፡
ትልቁ ልናወራበት፣ ልናወግዘው የሚገባው ጉዳይ፣ ፋና የህዝብን ድምጽ የተጠቀመበት መንገድ ነው፡፡ ለ27 አመታት በድብቅ በአስተዳዳሪዎቹ እየታዘዘ ያካበተውን ልምድ፣ በቀጥታ ስርጭት ሲጠቀምበት ማየት፣ ተስፋ ማስቆረጥ ብቻ አይደለም - ያስፈራል፡፡
እውን ቴሌ ለስድስት ተወዳዳሪዎች የሚሰጥ ድምጽ መሰብሰብ አቅቶት ነው? እንዳሉት አቅቷቸው ከሆነ ለምን እስከደረሱበት ደረጃ ያለውን አልወሰዱም? እኔ እስካየሁት እንኳን በቴሌቪዥን ስክሪን ላይ ከፍተኛው 26 000፣ ዝቅተኛው 5000 ነበር፡፡ ለምን ችግር ካለ ሌላ ጊዜ አይካሄድም? መልሱ ቀላል ነው፤ እነሱ የህዝብ ድምጽ አያስጨንቃቸውም፤ ለእነሱ የህዝብ ድምጽ ፕሮፓጋንዳና  የገቢ ምንጭ ነው፡፡ ያሳዝናል፡፡ ለመሆኑ ፋናና ቴሌ ስንት ስንት ሚሊዮን ደረሳቸው? ፋና 2ኛ እና 3ኛ ለወጡ ተወዳዳሪዎች እዚያው ላይ ሽልማት ማዘጋጀቱን ስናይ፣ ገቢው ምን ያህል እንዳስፈነደቃቸውና ስሜታዊ እንዳደረጋቸው መገመት አያስቸግርም፡፡ ፋና ያላግባብ የሰበሰበውን  የህዝብ ገንዘብ መመለስ አለበት፤ በንቀት ለወረወረው የህዝብ ድምጽም በግልጽ ህዝብን ይቅርታ መጠየቅ ይገባዋል፡፡
ሀገሬ ውስጥ ምርጫ ከተጀመረ አንስቶ ድምጽ ይጭበረበራል፤ ህዝብ ድምጼን ብሎ ይነሳል፤ በዚህ የተነሳ ሰዎች ይሞታሉ፡፡ በፋና የተደረገው ይኸው ነው፤ ከህዝብ ድምጽ ገንዘብ መሰብሰብ ጀመረ፣ ገንዘቡን ወስዶ ድምጹን አይናችን እያያ ወረወረው፡፡ በዚህ የተነሳ ዛሬ በማህበራዊ ሚዲያ ጦርነት ተጀመረ፡፡ .በመሰረቱ እኔ ስድስቱምን ተወዳዳሪዎች ወድጃቸዋለሁ። በእርግጠኝነት ማሸነፍ አለበት የምለው አልነበረኝም፡፡ በዳኞችና በህዝብ ድምጽ የሚያሸንፈውን ለማወቅም ጓጉቼ ነበር፡፡ የሆነው ግን እንዳያችሁት ነው፡፡
.ሁለት ጥያቄ አለኝ!
አንደኛ፣ ለዲሞክራሲ ግንባታና ለህዝብ ድምጽ መከበር ታላቁን ድርሻ የሚጫወቱት የብዙኃን መገናኛዎች ናቸው፡፡ እንደ ፋና ያሉ ከሀያ ሰባት አመት በሽታ ያላገገሙ ተቋማትን ይዘን (እኔ አሁን ሌሎቹም ተቋማት ተመሳሳይ ናቸው የሚል አመለካከት እያሳሰበኝ ነው)፣ እንዴት ነው የህዝብ ድምጽ የሚከበርበት ዲሞክራሲያዊ ምርጫ የምናካሂደው? ያስፈራል፡፡
ሁለተኛ፣ በየአካባቢው፣ ‹‹እገሌ  (የጎጣችን ተወዳዳሪ) ነበር ማሸነፍ ያለበት›› ብሎ ከመሟገትና በህዝብ ድምጽ ላይ ከተፈጸመው ንቀት የትኛው ነው መሰረታዊ? አንድ ሰው እንደሚያሸንፍ ይታወቅ ነበር እኮ! ውሳኔው ተቀባይነት እንዳያገኝ ያደረገው የህዝብ ድምጽ አለመከበሩና እስኪቋረጥ ድረስ ከፍተኛ ድምጽ ያገኙ ተወዳዳሪዎች አለማሸነፋቸው ነው፡፡ (በነገራችን ላይ ከፍተኛ የህዝብ ድምጽም አግኝተው ሊሸነፉ ይችሉ ይሆናል፤ የህዝብ ድምጽ ምን ያህል ዋጋ እንደተሰጠው አላውቅም) ያም ሆነ ይህ ግን የህዝብ ድምጽ አልተከበረም፡፡ በአጠቃላይ የህዝብ ድምጽ አለመከበር ነው ችግሩን የፈጠረው፤ እና ይህ አያሳስብም? ነገ በድምጻችን መንግስታችንን መምረጥ ስለመቻላችን ምን ዋስትና አለ? እባካችሁ፤ እንደ ህዝብ ትልቁን ጥያቄ ቀድመን እንመልስ፡፡   በአለማችን ታሪክ በአይነቱ የመጀመሪያው እንደሆነ የተነገረለት የጠፈር የፎቶ ኢግዚቢሽን፣ ከመሬት በ130 ሺህ ጫማ ርቀት ላይ በሚገኝ የጠፈር አካባቢ ውስጥ መጀመሩን ብሪትሽ ጆርናል ኦፍ ፎቶግራፊ ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡
የአለማችንን ማህበረሰቦች የተለያዩ የህይወት ገጽታዎች የሚያስቃኙና በዋናነት “ግለኝነት፣ ማህበረሰብ፣ አንድነት” በሚል መርህ ላይ ያተኮሩ 400 ያህል የተለያዩ ፎቶግራፎች የተካተቱበት ይህ ኢግዚቢሽን፣ "1854 ሚዲያ" በተባለው ተቋም አማካይነት ከጠፈር ላይ ተቀርጾ በቅርቡ በፊልም ለተመልካቾች እንደሚቀርብ ተነግሯል።
45 ደቂቃ እርዝማኔ እንዳለው የተነገረለት የኤግዚቢሽኑ ሙሉ ፊልም በመጪወ ማክሰኞ ተሲያት ላይ በድረገጽ አማካይነት በቀጥታ ለተመልካቾች እንደሚተላለፍ የጠቆመው መረጃው፣ በኢግዚቢሽኑ ለእይታ የበቁት 400 ፎቶግራፎች የተመረጡት ፖርትሬት ኦፍ ሂዩማኒቲ ለተሰኘው አለማቀፍ የፎቶግራፍ ውድድር ከግለሰቦችና ከተቋማት ከተላኩት ፎቶግራፎች ውስጥ እንደሆኑም አክሎ ገልጧል።


• በሁሉም ውድድሮች 20 ጊዜ ተገናኝተው ቀነኒሳ በ13 ሲያሸንፍ ኪፕቾጌ በ7 ድል ቀንቶታል፡፡ ቀነኒሳ ትራክ ላይ 11 ጊዜ ሲያሸንፍ ኪፕቾጌ በ4        ማራቶኖች ተገናኝተው ሁሉንም ድል አድርጓል፡፡
     • በሩጫ ዘመናቸው ቀነኒሳ 116 ውድድሮችን አሸንፏል፤ከ1,889,563 ዶላር በላይ ከሽልማት ገንዘብ አግኝቷል፡፡ ኪፕቾጌ 69 ውድድሮችን         አሸንፏል፤ከ2,112,540 ዶላር በላይ ከሽልማት ገንዘብ አግኝቷል፡፡
     • ቀነኒሳ በሁሉም ውድድሮች 31 ሜዳልያዎች (26 የወርቅ፤3 የብርና2 የነሐስ)  ኪፕቾጌ በሁሉም ውድድሮች 17 ሜዳልያዎች (11 የወርቅ፤4 የብርና         2 የነሐስ) ሰብስበዋል፡፡


            ከሳምንት በኋላ በሚካሄደው 40ኛው የለንደን ማራቶን ላይ ኢትዮጵያዊው ቀነኒሳ በቀለና ኬንያዊው ኤሊውድ ኪፕቾጌ ይገናኛሉ። ሁለቱ የረጅም ርቀት የምንግዜም ምርጥ ሯጮች በማራቶን ውድድር ሲገናኙ ለአምስተኛ ጊዜ ሲሆን አስቀድመው በተገናኙባቸው 4 ማራቶኖች ኪፕቾጌ አሸናፊ ሆኗል፡፡
በዓለም አቀፍ ኩባንያቸው ግሎባል አትሌቲክስ ስር ሁለቱንም አትሌቶች በማናጀርነት የሚያገለግሉት  ጆስ ሄርማንስ በሁለቱ ምርጥ አትሌቶች መገናኘት የተደሰቱ ሲሆን  ለሚመዘገበው ውጤት መጓጓታቸውን ሌትስ ራን ድረገፅ በዘገባው አትቷል፡፡ ጆስ ሄርማንስ እንደተናገሩት  ከመደበኛው የለንደን ማራቶን ድባብና መሮጫ በተለየ በተዘጋጀው ጎዳና ላይ መወዳደራቸው ፈጣን ሰዓት የሚመዘገብበትን እድል የሚያሰፋው ቢሆንም፤ የዓለም ሪከርድን የሚሰበርበት ሁኔታ ግን የሚያጠራጥር ነው፡፡ ወደ ማራቶን ውድድር ከገቡ በኋላ በአሜሪካው የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ ናይኪ ስፖንሰር ስር ያሉት ቀነኒሳ እና ኪፕቾጌ ኤንኤን ራነኒንግ በሚል ፕሮጀክት ባንድ ማልያ የሚሮጡ ናቸው፡፡
 በኮሮና ሳቢያ የተፈጠረው የልምምድ መስተጓጎልና  የአትሌቶቹ ወቅታዊ ብቃት በሪከርድ ሰዓት ለመሮጥ እንደማያመች ነው የሚገለፀው፡፡ እንግሊዛዊው የረጅም ርቀት ሯጭ ሞፋራህ በውድድሩ አሯሯጭ ሆኖ እንደሚሰለፍ እየተገለፀ ሲሆን ማራቶኑ በኮሮና ወረርሽኝ የዓለም ስፖርት ለወራት ከተቋረጠ በኋላየሚካሄድ ትልቅ ውድድር በመሆኑ ስኬቱ የዓለምን ልዩ ትኩረት የሚስብ ይሆናል፡፡
የለንደን ማራቶን አዘጋጆች ለውድድሩ 1.9 ኪሜትር ርዝማኔ ያለውና እንደ ቀለበት የሚዞር የመሮጫ ጎዳና አዘጋጅተዋል፡፡ ሙሉ የማራቶን ርቀቱን ለመሸፈን ተሳታፊ አትሌቶች 22 ጊዜ ቀለበታማ ጎዳናውን መዞር ይኖርባቸዋል። ዘንድሮ ብዙሃኑን የሩጫ ተሳታፊዎች የማያካትተው ውድድሩ በመንገድ ላይ ደጋፊዎችም አይኖሩትም፡፡
የመሮጫው ጎዳና በሴንት ጀምስ ፓርክ ዙርያ የሚሽከረከር ሲሆን የአካባቢው የአየር ሁኔታ በብዝሃ ህይወት የደገፈ፤ የኦሎምፒክ መስፈርትን የሚያሟላ የፎርሙላ ዋን እና የኪሪኬት ስፖርቶች መናሐርያ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ‹‹በበርካታ የተለያዩ ሁኔታዎች ላይ ለወራት ስንሰራ ቆይተናል፡፡
የሯጮቻችንን፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶቻችንን፣ የስፖንሰሮቻችንን፣ የበጎ ፈቃደኞቻችንን፣ የህክምና ባለሙያዎቻችንን  እና የከተማችንን ጤና እና ደህንነት ማስጠበቅ ሁል ጊዜ ቅድሚያ የምንሰጠው ነው፡፡›› በማለት የውድድሩ ዲያሬክተር ሁግ ብራሸር ለዎርልድ አትሌቲክስ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
የዓለም ማራቶን ሪከርድን የያዘው ኤሊውድ ኪፕቾጌ የለንደን ማራቶን ከመደበኛው ወቅት በ2 ወራት መሸጋሸጉ የዝግጅት ሁኔታዎችን እንዳስተጓጎለበት ተናግሯል፡፡ ‹‹አስቀድሜ ያቀድኳቸው ነገሮች ፈርሰውብኛል፡፡ እንደፈለግኩ በነፃነት ልምምዶችን እየሰራሁ አልነበረም፡፡ ለብቻ ስልጠና ማድረግ  ተፈታትኖኛል፡፡ ይህም በሁሉም የሰው ልጆች ያጋጠመ ተመሳሳይ ሁኔታ ነው፡፡ ሁላችንም ቅድሚያ የምንሰጠው ነገር ደህንነትን መጠበቅ ነው›› ብሏል፡፡ ከቀነኒሳ እና ከኪፕቾጌ ባሻገር በዘንድሮው ውድድር በሁሉም ፆታዎች ምርጥ የማራቶን ሯጮችም ተሳታፊዎች ናቸው። በወንዶች ምድብ ከ2 ሰዓት 5ደቂቃዎች በታች የገቡ ስምንት አትሌቶች ተሳታፊዎች ሲሆኑ ከእነሱም ማከከል በ2019 በተካሄደው የለንደን ማራቶን ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ያገኙት ኢትዮጵያውያኑ ሞሰነት ገረመው እና ሙሌ ዋሲሁን ይገኙበታል፡፡ ሲሳይ ለማና፤ ታምራት ቶላና ሹራ ኪታታ ሌሎች የኢትዮጵያ ማራቶኒስቶች ናቸው፡፡ በሴቶች ምድብ በለንደን ማራቶን ላይ ከፍተኛ ትኩረት ያገኘችው ኬንያዊቷ ብርጊድ ኮሴጊ ናት፡፡ ተፎካካሪዎቿ የማራቶኑን ርቀት ከ2 ሰዓት ከ20 ደቂቃዎች በታች የገቡ 5 አትሌቶች ሲሆን፤ በ2019 የቫሌንሺያን ማራቶን ያሸነፈችው ሮዛ ደረጄ እንዲሁም በ2019 የአምስተርዳም ማራቶንን ያሸነፈችው ደጊቱ አዝመራው የሚጠበቁ ሲሆን አሸተ በክረና አለም መገርቱም ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ተሳታፊዎች ናቸው፡፡
በለንደን ማራቶን ታሪክ የኬንያ አትሌቶች በብዛት በማሸነፍ ከኢትዮጵያ ብልጫ አላቸው። ባለፉት 39 የለንደን ማራቶን ውድድሮች በወንዶች ምድብ ኬንያውያን 15 ጊዜ ያሸነፉ ሲሆን ኤሊውድ ኪፕቾጌ በ2015 በ2016 በ2018 እና በ2019 ለአራት ጊዜ በማሸነፍ ከፍተኛውን ውጤት አስመዝግቧል፡፡ በወንዶች ምድብ ከኢትዮጵያውያን ያሸነፉት በ2003 ገዛሐኝ አበራ እንዲሁም በ2010 እና በ2013 እኤአ ፀጋዬ ከበደ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል በሴቶች  የኬንያ አትሌቶች 12 ጊዜ ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን በ2001 ደራርቱ ቱሉ በ2010 አሰለፈች መርጊያ እንዲሁም በ2015 ትዕግስት ቱፋ ያሸነፉ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡

   ‹‹….ልጄ በድንገት ከምሽቱ አራት ሰአት ላይ ይደውል ልኛል፡፡ እኔም …..ሄሎ….ስል ….. እማዬ….እማዬ…ድረሽልኝ…ብሎ ስልኩን ዘጋው፡፡ እኔም በምሽት መኪናዬን አስነስቼ እየበረርኩ ከልጄ ቤት ደረስኩ። ….ቤቱ በጭንቅ ተይዞአል፡፡ ….ምንድነው ጉዱ …አልኩ፡፡ ለካስ የልጄ ሚስት እናት ኮሮና በአገር ደረጃ መኖሩ ስለተነገረ እና በይበልጥ ደግሞ በየሆስፒታሉ እና ጤና ጣቢያው ቫይረሱ ሊተላለፍ ስለሚችል ልጄ ወደዚያ አትሄድም…ከቤት መውለድ አለባት። እኔ ማዋለድ የሚያውቁ ሴት አመጣለሁ…እናንተ ግን ከቤት እንዳትወጡ የሚል ትእዛዝ ሰጥተው ሄደዋል … ተባልኩ….፡፡ ልጅትዋ በምጥ ተይ ዛለች። ባለቤትዋን(ልጄ) ….አንተ መኪናህን አስነስተህ ወደ ሆስፒታል አትወስዳትም እንዴ….ስለው… ልጄን ከቤት ይዘህ እንዳትወጣ ብለው ስላስጠነቀቁኝ ፈራሁ ይለኛል። እኔም …ልጅቱን ተነሽ እንሂድ ስላት…እሺ እማማ… ስትለኝ…አማቼ ሳይመጡ ልጅቱን ይዤ ወደጤና ተቋም በረርኩ፡፡ ጤና ጣብያው በተገቢው ሁኔታ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ልጃችንን ሴት ልጅ አሳቀፈልን…››
በ2012 ይህ አምድ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ለንባብ ካላቸው አንዱን ለትውስታ ነበር ያስነበብናችሁ። በ2012 አጋማሽ በወረርሽ ደረጃ በአገራችን መከሰቱ የተነገረለት COVID-19 ዛሬም አለምን እንዳስጨነቀ ይገኛል፡፡ ሕመሙን ለመከላከል ሲባል የወጡ መመሪያዎችን በመ ተግበሩ ረገድ በትክክለኛውም ይሁን በተሳሳተ መንገድ እንደየሰው አረዳድ ብዙዎች ወትሮ ያደርጉት ከነበረው እንቅስቃሴያቸው ስለተገደቡ ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ለማግኘት አለመቻልን የተለያዩ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡ በተለይም ወደ ሆስፒታል መሄድን ፈርተው በቤት ውስጥ መውለድን የመረጡ ብዙዎች መሆናቸውን ለመገንዘብ ተችሎአል።
አንዲት ወጣት ወላድ የሰጠችውን አስተያየትም ለንባብ ማለታችን ይታወሳል፡፡
‹‹…ጎረቤቶቼ እንዲህ ነበር ያሉኝ፡፡ ….በጭራሽ ወደ ጤና ተቋም እንዳትሄጂ…ለመውለድ ብለሽ ከዚያ ብትሄጂ በኮሮና ቫይረስ ትያዣለሽ…የሚል ነበር ንግግራቸው፡፡ ይልቁንስ…አሉ ጎረቤ ቶች…ከቤትሽ ብትወልጂ የኮሮና ቫይረስም ሳይይዝሽ በሰላም ልጅሽን ታቅፊያለሽ የሚል ነበር ምክራቸው…እኔ ግን ከባለቤቴ ጋር ተማክሬ ወጤና ጣቢ በመሄዴ የመጀመሪያ ልጄን በሰላም ወልጃለሁ፡፡ በእርግጥ ጎረቤቶቼም ሆኑ ቤተሰቦቼ  ሊጎበኙኝ መምጣት ባለመቻላቸው አዝኛ ለሁ…ግን ደግሞ ለእነሱም ለእኔም ጥንቃቄ በማድረጋቸው ትክክል መሆኑን እረዳለሁ፡፡›› ነበር ያለችው፡፡
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ፡፡ በቤት ውስጥ በባህላዊ መንገድ ልጅን መውለድና ከዚህ ጋር በተያያዘም በሚከሰቱ የጤና ችግሮች ሞቶች እንደሚኖሩ ይገመታል፡፡  
ያልታቀደ እርግዝናን ለመከላከል የሚያስችሉ መከላከያዎችን ለመው ሰድ እንዲሁም ሳይፈለግ የተጸነሰውን ጽንስ ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ ለማቋረጥ የሚያስችሉትን አገልግሎቶች ለመጠቀም ሰዎች በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ወደ ጤና ተቋማቱ ለመሄድ ስለማይደፍሩ ከነችግሩ በቤታቸው መታቀባቸው ውጤቱ አስፈሪ ነው፡፡
በ Covid-19  ምክንያት በአለም አቀፍ ደረጃ ሚሊዮኖች ያልታቀደ እርግዝናን ለማስወገድና ያልታቀደ እርግዝናን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉ የእርግዝና መከላከያዎችን ለማግኘት አልቻሉም፡፡
ምንጭ….Guttmacher Institute
ሌላው ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ በአለም ላይ የሚስተዋለውና እንደ ትልቅ ችግር የሚቆጠረው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ነው፡፡
ከInternational Food policy Research Institute-- በተገኘው መረጃ Derek Headey እና Marie Ruel እንደሚሉት፤ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአለም አቀፍ ደረጃ ለሚኖረው የተመጣጠነ ምግብ እጦት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በምን ምክንያት ይከሰታል ብለን ስናስብ ይላሉ ባለሙያዎቹ…..
ሰዎች ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በፊት ይሰሩት ከነበረው ስራ መገለል ወይንም ይሰሩት የነበረው ስራ በወረርሽኙ ምክንያት ገቢ የማያስገኝ በመሆኑ እንዲቋረጥ በመሆኑ የገቢ መቀነስ ወይንም መቋረጥ ሲከሰት፤
በኮሮና ቫይረስ ላለመያዝ በተቻለ መጠን በቤት ቆዩ በሚለው መመሪያ መሰረት በተለ ይም ገቢያቸው ዝቅተኛ የሆኑት ሰዎች በቤታቸው ቢቆዩ ለራሳቸው የሚሆን ነገር የማያ ገኙ መሆኑ እና አቅም ያላቸው ሰዎች ደግሞ በቤታቸው በመቆየታቸው ምክንያት ገበያ ዎች ስለሚቀዘቅዙ እና የእለት ፍላጎቶችን ሸጠው የሚጠቀሙ ሰዎች በመቸገራቸው፤
በመንገድ ላይ የሚሸጡ ምግቦችን ደፍሮ የሚገዛቸው ተጠቃሚ በመቀነሱ፤
በትምህርት ቤቶች የትምህርት ስርአቱ ለጊዜው ስለተቋረጠ የምግብ አቅርቦትም አብሮ በመቋረጡ፤ እና በመሳሰሉት ምክንያቶች በተለይም በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ላይ የሚኖሩ ሰዎች የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት ሊያቅታቸው ይችላል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ የጤና ተቋማት ከተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ጋር የተያያዘ አገል ግሎት ይሰጡ የነበሩ ከሆነ የተመጣጠነ ምግብ እጥረቱ ላይከሰት እንደሚችል ጥናት አቅራቢ ዎቹ ይገልጻሉ፡፡ ለምሳሌም የእርግዝና ክትትል፤የተመ ጣጠነ ምግብ አቅርቦት፤ የህጻናትን ተቅማጥ መከላከልና ድጋፍ ማድረግ በተመለከተ በሚዘረጉ ፕሮግራሞች፤ኢንፌክሽን፤እና የተ መጣጠነ ምግብ እጥረት ያለባቸውን የኮሮና ቫይረስን ከመከላከል ጋር ተያይዞ ድጋፉ የሚቀጥል ከሆነ ችግሩ ብዙም አይስተዋልም፡፡
ሌላው የአለም የጤና ድርጅት ለንባብ ያቀረበው ከቤተሰብ እቅድ ዘዴ አገልግሎት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥያቄዎች መኖራቸውንና ለእነሱም የሰጠውን መልስ የሚመለከት ነው፡፡ ሁለት ጥያቄዎችንና መልሶችን እነሆ…
1/ የ COVID-19 ወረርሽኝ ታማሚ በምንሆንበት ወቅት ያልተፈለገ እርግዝናን መከላከያ መጠቀም ይቻላልን?
ማንኛውም በባለሙያ የሚታዘዝ ዘመናዊ የመከላከያ ዘዴን የኮሮና ቫይረስ ታማሚ በሚሆኑበት ወቅት ማቋረጥ አይገባም፡፡ ልክ እንደወትሮው መጠቀም ይቻላል፡፡ በእርግጥ ልጅ ከወለዱ ገና ስድስት ወር ገደማ ከሆነ እና አንዳንድ ሕመሞች ማለትም የስኩዋር ሕመም፤ከፍተኛ የሆነ የደም ግፊት፤ የጡት ካንሰር፤የመሳሰሉት ሕመሞች ታማሚ ከሆኑ ወይንም የሚያጨሱ ከሆነ ከሕክምና ባለሙያዎች ምክር መጠየቅ ተገቢ ይሆናል፡፡ ከባለሙያዎቹም ከጤና ጋር በማይ ጋጭ መልኩ የትኛውን መከላከያ መውሰድ ጠቃሚ ይሆናል የሚለውን ምክር ማግኘት ይቻላል፡፡
2/ የኮሮና ቫይረስ ታማሚ በምንሆንበት ጊዜ እርግዝና እንዳይኖረኝ እፈልጋለሁ፡፡ ምን ማድረግ አለብኝ?
እርግዝና እንዳይኖር በሚፈለግበት ወቅት ይወስዱት የነበረውን መከላከያ ምንጊዜም ሳያቋርጡ ወይንም እንደአዲስ በመጀመር መከላከያውን መውሰድ ጠቃሚ ነው፡፡ ለማንኛውም ለሚወስዱት እርምጃ ከጤና ተቋማት ወይንም ባለሙያዎች የምክር አገልግሎት ማግኘት እና በቂ መረጃ እንዲኖርዎ ማድረግ ጠቃሚ ነው፡፡ ለዚህም የግድ ወደተቋማቱ መሄድ ሳይጠበቅብዎ በስልክ አማካኝነት በመጠቀም ተገቢ የሆነውን ባለሙያ ማነጋገር ይጠቅማል፡፡ ይህንን ዘዴ መጠቀም የማይችሉ ከሆነ ግን በራስዎ ካለሐኪም መድሀኒት ማዘዣ የሚጠቀሙበትን ኮንዶም የመሳሰ ሉትን መከላከያዎች በቅርብዎ ከሚገኙ የመድሀኒት ቤቶች በመግዛት መጠቀም ይቻላል፡፡
በስተመጨረሻም ለትውስታ የምንለው የኢትዮጵያ የማህጸንና ጽንስ ሐኪሞች ማህበር ESOG የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከሚያስ ችሉት ዘዴዎች መካከል የአፍና አፍንጫ መሸፈኛን (Face Mask) ከኢትዮጵያ ውጭ አስመ ጥቶ ማከፋፈሉን ነው። ማህበሩ (ESOG) ግንቦት 29/2012 በአዲስ አበባ ለሚገኙት ሚሽነሪስ ኦፍ ቻሪቲ (ማሪያ ቴሬዛ)፤ ጎጆ (የህሙማን ማረፊያ)፤ የወደ ቁትን አንሱ የነዳያን መርጃ ማህበር፤ ለተሰኙት ድርጅቶች በግንባር በመቅረብ ለእያንዳንዳቸው እስከ አራትሺህ የሚደርስ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን በስነስርአቱም ላይ የኢትዮጵያ የማህጸንና ጽንስ ሐኪሞች ማህበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር መቅደስ ዳባ፤ የማህበሩ አባል የሆኑት ዶ/ር መንግስቱ ኃይለማርያም እና የማህበሩ ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሰላማዊት ክፍሌ ተገኝ ተው ነበር፡፡ ማህበሩ ድጋፍ ያደረገውን (Face Mask) ያገኘው በውጭ ከሚገኙ የሙያ አጋሮች በተደረገ ድጋፍ መሆኑ ታውቆአል፡፡
  እስከ ሰኔ በነበሩት ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ በመላው አለም 15 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውንና የተፈናቃዮች ቁጥር በመጪዎቹ ወራት በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ባለፈው ረቡዕ ይፋ የተደረገን አንድ አለማቀፍ ጥናት ጠቅሶ ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
ተቀማጭነቱ በስዊዘርላንድ የሆነው ኢንተርናል ዲስፕሌስመንት ሞኒተሪንግ ሴንተር የተባለ ተቋም ያወጣውን የጥናት ሪፖርት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፤ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ከ120 በላይ በሚሆኑ የአለም አገራት የእርስ በእርስ ግጭት፣ ብጥብጥና የተፈጥሮ አደጋዎችን ጨምሮ በተለያዩ አስገዳጅ ምክንያቶች ከ15 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የአገር ውስጥ ተፈናቃይ ለመሆን ተዳርገዋል፡፡ በተለያዩ የአለማችን አገራት ከተፈጥሮ አደጋዎችና የእርስ በእርስ ግጭቶች መባባስ ጋር ተያይዞ በመጪዎቹ ወራት የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር በእጅጉ ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተቋሙ ባወጣው መግለጫ አስጠንቅቋል፡፡
ከአጠቃላዩ የተፈናቃዮች ቁጥር ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የሚይዙት ጎርፍ፣ ሃይለኛ ንፋስ፣ የደን ቃጠሎና የአንበጣ ወረራን ጨምሮ በተለያዩ የተፈጥሮ አደጋ ለተፈናቃይነት የተዳረጉት ሲሆኑ፣ 4.8 ሚሊዮን ያህሉ ደግሞ በእርስ በእርስ ግጭትና ብጥብጥ የተፈናቀሉ እንደሆኑም ዘገባው አመልክቷል፡፡
እስካለፈው የፈረንጆች አመት 2019 መጨረሻ በመላው አለም በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ50.8 ሚሊዮን በላይ መድረሱንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡           በአሜሪካዊው ደራሲ ቦብ ውድዋርድ የተጻፈውና ከአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር የተደረጉ 18 ቃለመጠይቆችን ያካተተው “ሬጅ” የተሰኘ አነጋጋሪ መጽሐፍ ለህትመት በበቃ በመጀመሪያው ሳምንት ብቻ ከ600 ሺህ ቅጂ በላይ መሸጡን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ብዙዎች በጉጉት ሲጠብቁት የነበረውና ከሳምንት በፊት ለአንባብያን የደረሰው መጽሐፉ፣ ለህተመት በበቃ በቀናት ጊዜ ውስጥ በአማዞን ድረገጽና በሌሎች ምርጥ ሽያጭ ያስመዘገቡ መጽሐፍት ዝርዝር ውስጥ በአንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጡንና የወረቀት፣ የድምጽ፣ እና የኢሊክትሮኒክ ኪፒዎችን ጨምሮ በድምሩ 600 ሺህ በላይ ቅጂዎች እንደተሸጠ ዘገባው አመልክቷል፡፡ አሳታሚው ድርጅት ሲሞን ኤንድ ሹስተር ባለፈው ረቡዕ በሰጠው መግለጫ፣ መጽሐፉን ለአራተኛ ጊዜ በድጋሜ ለማተም ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝና ህትመቱ ሲያልቅ በወረቀት ታትመው ለገበያ የቀረቡ የመጽሐፉ ቅጂዎች ብዛት 1.3 ሚሊዮን እንደሚደርስም አስታውቋል፡፡
ደራሲው ከሁለት አመታት በፊት ለንባብ ያበቁትና በፕሬዚዳንት ትራምፕ ላይ የሚያጠነጠነው “ፊር” የተሰኘ መጽሐፍ በታተመ በመጀመሪያው ሳምንት ከ1 ሚሊዮን በላይ ቅጂዎች እንደተሸጡለት ያስታወሰው ዘገባው፣ እስካሁን ድረስ 2 ሚሊዮን ያህል ቅጂዎች መሸጣቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡ ፖርቶሪኳዊው ድምጻዊ ሉዊስ ፎንሲ ያቀነቀነውና ዳዲ ያንኪ በአጃቢነት የተሳተፈበት “ዲስፓሲቶ” የተሰኘ ተወዳጅ የሙዚቃ ቪዲዮ፣ በዩቲዩብ ድረገጽ 7 ቢሊዮን ጊዜ በመታየት በአንደኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡
ዩቲዩብ ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ ሃፒ ድረገጽ እንዳስነበበው 5 ቢሊዮን ጊዜ ያህል በዩቲዩብ ተመልካቾች የታየው የኤድ ሼራን ተወዳጅ ሙዚቃ “ሼፕ ኦፍ ዩ” በሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ፣ የዊዝ ካሊፋ “ሲ ዩ አጌን” 4.7 ቢሊዮን ጊዜ በመታየት ሶስተኛ ደረጃን ይዟል፡፡
የማርክ ሮንሰን “አፕታውን ፋንክ” በ3.9 ቢሊዮን፣ የፒኤስዋይ “ጋንጋም ስታይል”፣ በ3.8 ቢሊዮን፣ የጀስቲን ቢበር “ሶሪ” በ3.3 ቢሊዮን፣ የማሮን ፋይቭ “ሹገር” በ3.3 ቢሊዮን፣ የኬቲ ፔሪ “ሮር” በ3.2 ቢሊዮን፣ የኤድ ሼራን “ቲንኪንግ አውት ላውድ” በ3.1 ቢሊዮን እንዲሁም የዋን ሪፐብሊክ “ካውንቲንግ ስታርስ” በ3 ቢሊዮን እይታዎች እንደ ቅደም ተከተላቸው እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙ የዩቲዩብ የሙዚቃ ቪዲዮዎች መሆናቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡  የደመራ ስጦታ ለደንበኞች


           ሃበሻ ቢራ “ቅዳሜ” የተሰኘ አዲስ የቢራ ምርቱን ከዛሬ ጀምሮ ለተጠቃሚዎች እንደሚያቀርብ አስታወቀ፡፡
ከ8ሺ በላይ የአክሲዮን ባለድርሻ ኢትዮጵያውያን ተመስርቶ፣ በ2007 “ሐበሻ ቢራ” እና “ንጉስ” የተባሉ የቢራ ምርቶችን ለገበያ ማቅረብ የጀመረው ሐበሻ ቢራ፤ አዲሱን “ቅዳሜ” የተሰኘ ምርቱን ዛሬ በደመራ እለት ለደንበኞቹ ያቀርባል፡፡
ኩባንያው ለተጠቃሚዎች ይዞ የቀረበው አዲሱ “ቅዳሜ” የተሰኘው የቢራ ምርት ከፍተኛ ጥራት ያለው እርካታን የሚሰጥ ጣዕም ያለው ምርት መሆኑን ኩባንያው በመግለጫው አስታውቋል፡፡
ሀበሻ ቢራን ለገበያ ማቅረብ ከጀመረ 5 አመታት ያስቆረጠውና ከአልኮል ነፃ የሆነውን ንጉስ የተሰኘውን መጠጥ ደግሞ ማቅረብ ከጀመረ ሁለት አመታት የሆኑት ኩባንያው ምርቶቹን ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት እና አሜሪካ እየቀረበ መሆኑን አስታውቋል፡፡