Administrator

Administrator

የአይፎን ሞባይል ቀፎ የሚገዛበት ገንዘብ ለማግኘት ሲል፣ ሴት ልጁን በተወለደች በ18ኛው ቀን በድረ-ገጽ አማካይነት ሽጧል በሚል ሰሞኑን በፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋለው አ ዱኣን የተባለ ቻይናዊ፣ የ3 አመት እስር እንደተፈረደበት ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
ነዋሪነቱ ፉጂያን በተባለቺው የቻይና ግዛት እንደሆነ የተነገረለት ግለሰቡ፣ ኪውኪው በተባለው የአገሪቱ ታዋቂ ማህበራዊ ድረገጽ ላይ ልጁን ለመሸጥ ያወጣውን ማስታወቂያ የተመለከተ ግለሰብ ልጅቷን ለመግዛት 2ሺህ 500 ፓውንድ መክፈሉን ዘገባው ገልጧል፡፡
አባትዬው ልጁን በመሸጥ ያገኘውን ገቢ አይፎንና ሞተር ብስክሌት ለመግዛት ሊያውለው አስቦ እንደነበር የተነገረ ሲሆን፣ ልጅቷ የተረገዘቺው ያለ እቅድ እንደነበረና አባትዬውም ሆነ እናትዬው የ19 አመት ዕድሜ ያላቸው ወጣቶች እንደሆኑ ዘገባው አስረድቷል፡፡
እናትዬው ዢያኦ ሚ የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ገቢ ታገኝ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ አባትዬው በበኩሉ አብዛኛውን ጊዜውን በኢንተርኔት ካፌዎች ተጎልቶ የሚያሳልፍ ስራ ፈት እንደነበረና ልጁን ለመሸጥ የወሰነውም ለማሳደጊያ የሚሆን በቂ ገንዘብ የለኝም በሚል ስጋት እንደሆነ አብራርቷል፡፡
ልጁን የሸጠው ይሄው ግለሰብ በቁጥጥር ስር የዋለው እናትዬው ለፖሊስ በሰጠቺው ጥቆማ መሰረት እንደሆነም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Saturday, 12 March 2016 10:36

የኪነት ጥግ

(ስለ ካሜራ ባለሙያ)
- አባቴ ተዋናይና ፀሐፊ ነበር፤ እናቴ የድራማ
መምህርት ነበረች፤ ሴት አያቴ ደግሞ
ተዋናይት፡፡ ወንድ አያቴ እንዲሁ የካሜራ
ባለሙያ ነ በር፡፡ እ ኔ የ ጥርስ ሃ ኪም ወ ይም
በዚያ አይነት ሙያ ለመሰማራት ብፈልግ ኖሮ
ተገርመው አያበቁም ነበር፡፡
ቻርሊ ሮሄ
- የካሜራ ባለሙያ ወይም ዲዛይነር አሊያም
ተዋናይ ልሆን አልችልም - ዳይሬክተር
ነው መሆን ያለብኝ፤ ምክንያቱም ያ እንዴት
እንደሚሰራ ከአባቴ ተምሬዋለሁ፡፡
ጆ ራይት
- ሰዎች ሁልጊዜ ሙሉ የድጋፍ ቡድን -
(ሜክአፕ፣ አልባሳትና ሹፌር) የሚኖረን
ይመስላቸዋል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በጦርነት
ቀጠና ውስጥ ግን እኔና የካሜራ ባለሙያው
ብቻ ነን፡፡
ኬት አዲ
- ካሜራ ለሴቶች በጣም ከባድና ቀድሞውኑም
የተሰራው ለወንዶች በመሆኑ ደህና የካሜራ
ባለሙያ ያስፈልጋችኋል፡፡
ሚትራ ፋራሃኒ
- በእያንዳንዱ ምስል ላይ ሁለት ሰዎች አሉ
-ፎቶግራፍ አንሺውና ተመልካቹ፡፡
አንሴል አዳምስ
- የሰውን ፊት በትክክል የሚያየው ማነው?
ፎቶግራፍ አንሺው፣ መስተዋቱ ወይስ
ሰዓሊው?
ፓብሎ ፒካሶ
- ሁልጊዜም አማተር ፎቶግራፍ አንሺ ነው
የምሆነው፡፡
ኢሊዮት ኢርዊት
- የፋሺን ፎቶግራፍ አንሺ መሆን ምንም ችግር
የለውም፤ ግን ትንሽ ውሱንነት አለው፡፡
ዴቪድ ባይሌይ
- በአሜሪካ የፎቶግራፍ ባለሙያ ያለፈውን
የሚቀርፅ ብቻ አይደለም፤ የሚፈጥርም
ጭምር እንጂ፡፡
ሱሳን ሶንታግ
- እናቴ የፎቶግራፍ ባለሙያ ነበረች፤ እናም
ለሞዴሊንግ ሥራ ህፃን ልጅ ሲፈልጉ ካሜራ
ፊት ትገትረኛለች፡፡ እንደዚያ ነው ነገሩ
የተጀመረው፡፡
አሊሶን ሃኒጋን

በድሮው ዘመን አንድ አዛውንት እስር ቤት ይገባሉ፡፡ በዚያን ጊዜ እስረኞች እራሳቸው ባወጡት ህግ መሰረት፤ አዲስ ገቢ ሲመጣ ለእስር ቤቱ መኖሪያ ማዋጣት ያለበት ገንዘብ ነበር፡፡ የእስር ቤቱ የህዝብ ግንኙነት፤
“እንግዲህ በክፍላችን ህግ መሰረት ያቅምዎትን አዋጡ” አላቸው አዛውንቱን፡፡
አዛውንቱም፤
“ቤተሰቤ ምን ይስጠኝ ምን ሳላውቅ ይሄን ያህል አዋጣለሁ ማለት ያስቸግረኛል” አሉ፡፡
“ግዴለም ከመጣልዎት ውስጥ ይሄን ያህሉን እለግሳለሁ፤ ቢሉና ቃል ቢገቡ እንኳ በቂ ነው” አላቸው፡፡
ይሄኔ አዛውንቱ፤
“እስቲ አሳቤን በወግ ልግለጥ” አሉና፤ “ጥንት ጎጃም ውስጥ ሁለት ሴቶች ሜዳ ሊወጡ ከቤት ወደ ደጅ ይሄዳሉ፡፡ ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ ማታ ነው፡፡
አንደኛዋ፤ ‹እንግዲህ አደራ፣ ነገ በተስኪያን ጠዋት ስንመጣ፣ አንቺ ከቀደምሽ አንቺ፤ እኔ ከቀደምኩ እኔ፤ ቀድመን ቦታ እንያዝ - እሴቶች መቆሚያ ቦታ› አለቻት፡፡
በተስኪያን ውስጥ ማልዶ መጥቶ ቦታ ካልያዙ ሰው ብዙ ስለሆነ ደጅ ሆኖ ማስቀደስ ግድ ስለሚሆን ቀድሞ መገኘት ዋና ነገር ነው፡፡ ይሄኔ፤ ሁለተኛይቱ ሴት፣ በሚያቅማማ ድምፅ፤
“እንግዲህ ማልዶ ቦታ ለመያዙም፣ በተስኪያን ውስጥ ገብቶ ለማስቀደሱም፤ ወንዶቹ እንዴት እንዳሳደሩን አይተን ነዋ!” አለች፡፡
(በዕምነታቸው መሰረት ከወንድ ተገናኝታ ያደረች ሴት፤ በተስኪያን ውስጥ መግባት ክልክል በመሆኑ ነው፡፡ ያ ደግሞ በድሮው ዘመን በተለይ የወንዱን ፍቃድና ፍላጎት የሚሻ ጉዳይ ነው!)
የእሥር ቤቱ አዲስ እስረኛ አዛውንት አሳሪዎቻችን (ወንዶቹ) እንዴት እንደሚያሳድሩን ሳናይ ‹እንዴት ብዬ ቃል ልግባላችሁ … ሊገድሉንምኮ ይችላሉ፤ በሰው እጅ ያለን ሰዎች ነን› ማለታቸው ነው!
*             *           *
በሰው እጅ ያለ ሰው በራሱ ለመቆም እጅግ ያዳግተዋል፡፡ በተለይ ፍትሕ በሌለበትና” “ንጉሥ የቆረጠው እጅ እንዳለ ይቆጠራል” በሚባልበት ዘመን ከሆነ፤ በማናቸውም ሰዓት ህይወት ስጋት ላይ መውደቋ የዕለት የሰርክ ጉዳይ ይሆናል፡፡ ካጠፉ ቅጣት አይቀሬ ነው! ዘረፋና ምዝበራ ሲበዛ ጥርጣሬ አንድ የማሰሪያ ቅድመ ሁኔታ መሆኑ አያጠያይቅም። በተለይ ህጋዊ ሽፋንን ተጠቅሞ ምዝበራውን የሚያካሂድ ሹም ራሱ መዝባሪ፣ ራሱ ጠርጣሪ ስለሚሆን በቀላሉ የሚደረስበት አይደለም፡፡ ከተደረሰበት ግን “የነብርን ጅራት አይይዙም ከያዙም አይለቁም” የሚባል መሆን ይኖርበታል፡፡ አያሌ ሹማምንት ከሙስናም ከፖለቲካዊ ሁኔታም ጋር በተያያዘ የሚገመገሙበት ሰዓት እነሆ ደረሰ፡፡ በማናቸውም የሥራ ኃላፊነት ላይ የተቀመጠ ሹም ማለትም ሚኒስትር፣ ኤክስፐርት፣ አማካሪ፣ ፖሊስ፣ ትራፊክ፣ ሳይንቲስት፣ ኦዲተር፣ የመሬት አስተዳዳሩ፣ የፖለቲካ መሪ፣ ካድሬ ወዘተ … እከሌ ከእከሌ ሳይባል የሚመረመሩበት፣ የሚፈተሹበት ወቅት መጣ፡፡ “ጊዜ የሥልጣን እጅ ነው” ይላሉ ፀሐፍት፡፡ የቪላ መዓት፣ የውድ ውድ መኪናዎች ጥርቅም፡፡ በዘር - ሐረግ የተያዘ መሬት ብዛት … አንድ የመንግሥት ሰራተኛ እንዴት ሊኖረው ይችላል? ብሎ መጠየቅ ማንም ጅል የማይስተው ነገር ነው፡፡ በሙስና የተገኘ ሐብት መሆኑ ከታወቀ ደግሞ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ መንግስትን መንግስት የሚያሰኝ ተግባር ነው፡፡ የመንግስት ሰራተኛ ከየትኛውም ነጋዴ ወይም ሀብት ያካበተ - ዜጋ ጋር በመመሳጠር ያንድ ጀምበር ባለፀጋ (nouveau riche ኑቮ ሪሽ እንዲሉ) ለመሆን የቻለበትን ሁኔታ ለማጣራት፣ መፈራራት ከሌለ በስተቀር፣ ያፈጠጠ ያገጠጠ ነገር ነው፡፡ ዛሬ በአገራችን ማናቸውም ሌብነት፣ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ የሚፈፅሙት፣ ስሙ “ቢዝነስ” ሆኗል፡፡ “ይሄኮ እልም ያለ ዘረፉ ነው” ሲባሉ “የሥራው ፀባይ ነው” ብሎ መመለስ እንደመመሪያ ተወስዷል፡፡ “የማይበላ ሰው” ፋራ መባሉም እንደ እለት ሰላምታ ተለምዷል፡፡
“ኢንቨስተሩ ከባንክ የወሰደውን ገንዘብ ለጥገኛ ጥቅም አውሎታል” ካልን፤ የደረስንበትን ማስረጃ ለፈጣን እርምጃ ማዋል መዘግየት የሌለበት ጉዳይ ነው፡፡ ያውም እስካሁን ካልረፈደ! በችሎታውና በሙያው የሚተዳደር እንደ ሐቀኝነት ነውር ሆኗል፡፡ እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ አሠራር ይኖራል ማለት እጅግ አስቂኝ ጨዋታና ስላቅ (irony)  ይሆናል፡፡ ዊንስተን ቸርችል፤ “የዲሞክራሲ ሥርዓት ከሌሎች ተሞክረው ከከሸፉ ሥርዓቶች ጋር ሲነፃፀር ነው እንጂ ደግ ነው የሚባለው፤ በራሱ ፍፁም ሥርዓት አይደለም” ይሉናል፡፡ ዲሞክራሲ እንደኛ ባለና በሙስና አዘቅት በገባ አገር ውስጥ ሲታሰብ እንዴት ውስብስብና አያዎአዊ (paradoxical) እንደሚሆን መገመት አያዳግትም፡፡ ከዚሁ ባልተናነሰ መልኩ፤ የመልካም አስተዳደርን አናሳነት፣ የጠንካራ ተቋማትን መጥፋት፣ ወገንተኝነትን፣ የዕውቀት መንማናነትን፣ አለመቻቻልን፣ ከልብ አለመነጋገርን፣ ራስ - ወዳድነትን፣ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብት መታጣትን ወይም መሟሸሽን ወዘተ አክለን ስናስበው… “አይ ዲሞክራሲ እኔን ክንብል ያርገኝ!” ማለታችን አይቀርም፡፡ “አግዝፈው ያሞገሱት ለማማት ያስቸግራል” ነው ነገሩ፡፡ አሳሳቢ መንታ መንገድ ላይ ቆመን ነው ግምገማ እያካሄድን ያለነው። ሆኖም መገማገም ግዴታ ነው፡፡ አንዲት ክር ስትነካ አገሩ የሚታመስ ከሆነ ሁኔታውን መገምገም ግዴታ ነው፡፡
የተነካካውን ሰው ሁሉ ስናጠራ ጊዜ ማለፉ ደግሞ አይቀሬ ነው፡፡ ሆኖም በአቅም ካልፈጠንን ሁኔታዎች ሊቀለበሱ ይችላሉ ብሎ መስጋት ያባት ነው፡፡ ወትሮውንም ሰዎቹን እናውቃቸው ነበርኮ፡፡ “እቃ ስላጣን አብረን በላን፤ እንጂ መች እኩያሞች ሆንን” የሚለውን ተረት ስናሰላስል፣ የዛሬው የበሰለ ቀን እንዳያመልጠን ጠንክረን እንሥራ፡፡ ሙስና የድህነት አቻ ጠላት የሆነበት ሰዓት ደርሷልና!

ዓመታዊ ትርፉን 10ቢ. ዶላር ለማድረስ አቅዷል
   በትርፋማነቱ ከአፍሪካ አየር መንገዶች መሪነቱን የያዘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ በፈረንጆች የ2014-15 አመት የ3.53 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱንና ትርፉ ከቀደመው አመት የ12 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን “ብሉምበርግ” ዘገበ፡፡
ምንም እንኳን አመቱ ለአፍሪካ አየር መንገዶች ፈታኝ የነበረ ቢሆንም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን፣ ፈተናዎችን በመጋፈጥ፣ ወጪዎቹንና የሽያጭ አገልግሎቶቹን በማስፋፋትና አሰራሮቹን በማሻሻል በትርፋማነቱ መቀጠሉን የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም መናገራቸውን ዘገባው ገልጿል፡፡
አየር መንገዱ ከ2.1 ቢሊዮን ዶላር በላይ በመመደብ፣ 20 ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ማዘዙንና በመጪዎቹ አስር አመታት ጊዜ ውስጥ አመታዊ ትርፉን 10 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ አቅዶ እየታተረ እንደሚገኝም ዘገባው አስታውሷል፡፡

ኤጀንሲዎች ህጻናትን እየላኩ ገንዘብ በመሰብሰብ ተጠምደዋል ተብሏል
    የዴንማርክ የማህበራዊ ጉዳዮችና የአገር ውስጥ ሚኒስቴር፤ በኢትዮጵያውያ የሚታየው የጉዲፈቻ አሰራር ያልተገባና ህጻናትን ወደ ውጭ አገራት በመላክ ገንዘብ መሰብሰብ ላይ ያተኮረ መሆኑ በጥናት መረጋገጡን ጠቁሞ፣ ከአሁን በኋላ ኢትዮጵያውያን ህጻናትን በጉዲፈቻ ላለመቀበል መወሰኑን አስታውቋል፡፡
“ዘ ኮፐንሃገን ፖስት” የተባለው የአገሪቱ ጋዜጣ እንደዘገበው፣ በኢትዮጵያ ያለው ህጻናትን በማደጎ ወደ ውጭ አገራት የመላክ አሰራር ዴንማርክ በአለማቀፍ የማደጎ ሂደት የምትከተለውን መርህ የማያሟላ ሆኖ በመገኘቱ ውሳኔው ሊተላለፍ ችሏል፤ ሲል ዘግቧል፡፡
በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የጉዲፈቻ አስፈጻሚ ኤጀንሲዎች ወደ ዴንማርክ የሚልኳቸውን ህጻናት በተመለከተ የሚሰጡት መረጃ በአብዛኛው ወጥነት የሌለው ነው ያለው ዘገባው፣ ኤጀንሲዎቹ ትኩረታቸውን ያደረጉት ከውጭ አገራት ኤጀንሲዎች ገንዘብ በመሰብሰብ ላይ መሆኑንና አገራዊ መፍትሄ ከመሻት ይልቅ ህጻናቱን ወደ ውጭ አገራት በማደጎ በመላክ እንደተጠመዱ ጠቁሟል፡፡ በተጠናቀቀው የፈረንጆች አመት 2015 ብቻ በአለማቀፍ የጉዲፈቻ ቅበላ ሂደት 100 ያህል ህጻናት ወደ ዴንማርክ መግባታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ከእነዚህ ህጻናት መካከል ሰባቱ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን አስታውቋል፡፡

በአርባምንጭ ሆስፒታል ከ140 በላይ ህሙማን ህክምና እየተሰጣቸው ነው

     በደቡብ ክልል አርባምንጭ ዙሪያ አማሮና አባያ ወረዳዎች በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን ገላን ወረዳና በሶማሌ ክልል ሞያሌ ወረዳዎች ላይ የኮሌራ ወረርሽኝ መከሰቱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ሚኒስቴር መ/ቤቱ ሰሞኑን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይፋ እንዳደረገው፤ በሶስቱ ክልሎች በተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ በአተት በሽታ የተያዘ ሰው አፋጣኝ ህክምና ካላገኘ የመሞት ዕድሉ ከፍተኛ ነው ያለው መግለጫው፤ህብረተሰቡ በሽታውን ለመከላከል ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባዋል ብሏል፡፡
የአርባ ምንጭ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ቀፀላ ለማ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት በሽታው በወረርሽኝ መልክ ከተከሰተበት ከአለፈው እሁድ ጀምሮ ከ140 በላይ ህሙማን በዚሁ በሽታ ተይዘው ወደ ሆስፒታሉ መጥተዋል፡፡ ለህሙማኑ የህክምና ማዕከል ተቋቁሞ ዕርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን ዶ/ሩ ገልፀዋል፡፡ በበሽታው ሳቢያ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ስለመኖራቸው እንደማያውቁ የተናገሩት ዶ/ሩ፤ ወደ ሆስፒታሉ የመጡ ህሙማን ግን ተገቢው ህክምና እየተደረገላቸው በመሆኑ የሞት አደጋ አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡  
ከሰሞኑ ዝናባማ የአየር ንብረት ጋር በተያያዘ በሚከሰተው ጐርፍ፤ ምንጮች፣ የውሃ ጉድጓዶችና ወንዞች ስለሚበከሉና ይህም በሽታውን በቀላሉ ለማስተላለፍ የሚችል በመሆኑ ህብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል ያለው ጤና ጥበቃ ሚ/ር፤ ለመጠጥነት የሚውሉ ውሃዎች በአግባቡ ተፈልተውና ቀዝቅዘው አሊያም በውሃ ማከሚያ መድሃኒቶች ታክመው ጥቅም ላይ ሊውሉ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡   

   - ቢል ጌትስ በ75 ቢ. ዶላር፣ ዘንድሮም አንደኛ ነው
                 - የፌስቡኩ ዙክበርግ ከፍተኛውን የሃብት ጭማሪ አግኝቷል
                 - ቻይና ዘንድሮ 70 አዳዲስ ቢሊየነሮችን አፍርታለች
    በየአመቱ የዓለማችንን ባለጸጎች የሃብት መጠን በመገምገም ይፋ የሚያደርገው ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት፣ ዘንድሮም የተለያዩ አገራት ዜግነት ያላቸው 1ሺህ 810 ባለጸጎች የተካተቱበትን የ2016 የዓለማችን ቀዳሚ ቢሊየነሮችን ዝርዝር ባለፈው ማክሰኞ ይፋ አድርጓል፡፡
የማይክሮሶፍቱ መስራች ቢል ጌትስ የሃብት መጠናቸው ከአምናው የ4.2 ቢሊዮን ዶላር ቅናሽ በማሳየት ወደ 75 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ቢልም፣ ዘንድሮም የፎርብስ የዓለማችን ቀዳሚ ቢሊየነሮችን ዝርዝር በአንደኛነት ከመምራት የሚያግዳቸው አልተገኘም፡፡ እኒሁ ስመጥር ባለጸጋ በሃብታቸው መጠን አለምን ሲመሩ የአሁኑ ለ17ኛ ጊዜ ነው ተብሏል፡፡
ዛራ ፋሽን የተባለው አለማቀፍ የአልባሳት አምራች ኩባንያ ባለቤት የሆኑት ስፔናዊው አማኒኮ ኦርቴጋ፤ በ67 ቢሊዮን ዶላር ሁለተኛ ደረጃን ሲይዙ፣ 60.8 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት ያላቸው አሜሪካዊው ቢሊየነር ዋረን ቡፌት ሶስተኛ ሆነዋል፡፡ ሜክሲኳዊው የቴሌኮም ዘርፍ ባለጸጋ ካርሎስ ስሊም በ50 ቢሊዮን ዶላር አራተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ፣ የአማዞን ኩባንያ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ጄፍ ቤዞስ፣ በ45.2 ቢሊዮን ዶላር አምስተኛው የዓለማችን ቢሊየነር ሆነዋል፡፡
በዘንድሮው የፎርብስ መጽሄት የዓለማችን ቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ 190 ሴት ቢሊየነሮች መካተታቸውና የወንዶች የበላይነት መግነኑ የታወቀ ሲሆን በ11ኛነት የተቀመጠችውና ከአለማችን ሴቶች በሃብት ቀዳሚውን ስፍራ የያዘችው፣ 36.1 ቢሊዮን ዶላር ያፈራችው የታዋቂው የፋሽንና የመዋቢያ ቁሳቁስ አምራች ኩባንያ ሎሪል መስራችና ባለቤት ፈረንሳዊቷ ሊሊያን ቤተንኮርት ናት፡፡
በአመቱ ዝርዝር ውስጥ 540 ዜጎቿ የተካተቱላት አሜሪካ በርካታ ቢሊየነሮችን በማስመዝገብ ቀዳሚዋ አገር ስትሆን ቻይና በ251፣ ጀርመን በ120፣ ህንድ በ84 እና ሩስያ በ77 ቢሊየነሮች ከሁለት እስከ አምስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
በ2016 በርካታ አዳዲስ ቢሊየነሮችን በማፍራት ቀዳሚነቱን የያዘቺው ቻይና ስትሆን፣ 70 ባለጸጎቿን በአመቱ የቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ አካትታለች። በዘንድሮው የፎርብስ ዝርዝር በዕድሜ ለጋዎቹ ባለጸጎች ተብለው የተጠቀሱት ደግሞ፣ የ19 አመቷ የኖርዌይ ተወላጅ አሌክስንድራ አንደርሰንና አንድ አመት የምትበልጣት ታላቅ እህቷ ካትሪና አንደርሰን ናቸው፡፡
ባለፈው አመት 1826 የነበረው የአለማችን ቢሊየነሮች ቁጥር፣ ዘንድሮ ወደ 1810 ዝቅ ብሏል ያለው ፎርብስ፣ ባለፈው አመት ከነበራቸው ሃብት 20.1 ቢሊዮን ዶላር ቅናሽ ያሳዩት ሜክሲኳዊው ቢሊየነር ካርሎስ ስሊም ከፍተኛ ኪሳራ የገጠማቸው ባለጸጋ መሆናቸውንም አመልክቷል፡፡
በአንጻሩ ከአምናው ሃብቱ የ11.2 ቢሊዮን ዶላር የሃብት መጠን ጭማሪ በማስመዝገብ 44.6 ቢሊዮን ዶላር ያደረሰውና በዓለማችን የቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ ደረጃውን ወደ ስድስተኛነት ከፍ ያደረገው የፌስቡኩ መስራች ማርክ ዙክበርግ፣ በአመቱ ከፍተኛውን የሃብት ጭማሪ ያስተናገደ ባለጸጋ ተብሏል፡፡

     - ድርቁ በአካባቢው በሚገኙ 7 አገራት ተከስቷል
     በሶርያና በምስራቃዊ ሜዲትራኒያን አካባቢ በሚገኙት ቆጵሮስ፣ እስራኤል፣ ዮርዳኖስ፣ ሊባኖስ፣ ፍልስጤምና ቱርክ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የተከሰተው ድርቅ፣ በአካባቢው ያለፉት 500 አመታት ታሪክ የከፋው ሊሆን እንደሚችል መጠቆሙን ዘ ጋርዲያን ዘገበ፡፡
ከአሜሪካ የጠፈር ምርምር ተቋም ናሳ፣ ከኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲና ከአሪዞና ዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ ተመራማሪዎች ባደረጉት ጥናት፣ በአካባቢው እ.ኤ.አ ከ1998 ጀምሮ የተከሰተው ድርቅ እየተባባሰ መምጣቱን ማረጋገጣቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ድርቁ በዚሁ ከቀጠለ ባለፉት 500 አመታት የአካባቢው ታሪክ የከፋው የመሆን ከፍተኛ እድል እንዳለው መናገራቸውንም አመልክቷል፡፡
ጆርናል ኦፍ ጂኦፊዚካል ሪሰርች አትሞስፌርስ በተባለ የህትመት ውጤት ላይ ለንባብ የበቃውና የአካባቢውን አገራት የረጅም ዘመናት የአየር ንብረት ሁኔታ በመዳሰስ የተዘጋጀው የተመራማሪዎቹ የጥናት ውጤት እንደሚለው፣ በአካባቢው አገራት የተከሰተው ድርቅ እየተባባሰ እንደሚሄድ ይጠበቃል፡፡ ለድርቁ በምክንያትነት ለተጠቀሰው የአየር ንብረት ለውጥ የበካይ ጋዞች ልቀት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውና ድርቁ በግጭትና በእርስ በእርስ ግጭት ለሚታመሱት የአካባቢው አገራት ዜጎች ከፍተኛ ፈተና እንደሚሆን መነገሩንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

    የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፤ በአገሪቱ የህዝብ ቁጥርና በፖሊስ ሃይሏ መካከል መመጣጠን ለመፍጠር በማቀድ ተጨማሪ 10 ሺህ አዳዲስ የፖሊስ መኮንኖች እንዲቀጠሩ ለሚመለከተው አካል ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን አፍሪካ ኒውስ ዘገበ፡፡
ፕሬዚዳንቱ ባለፈው ረቡዕ ኢምባካሲ በተባለቺዋ የኬንያ ከተማ ባደረጉት ንግግር፣ የፖሊስ ሃይልን ማጠናከር አገሪቱን ከወንጀል ድርጊቶችና ከወንጀለኞች የጸዳች ለማድረግ የሚጫወተውን ወሳኝ ሚና ከግምት ውስጥ በማስገባት ተጨማሪ የፖሊስ መኮንኖችን ለመቅጠርና ወደ ስራ ለማሰማራት መወሰናቸውን ተናግረዋል፡፡
የአገሪቱ የፖሊስ መኮንኖች አገራቸውን ከወንጀል ድርጊቶች ለመከላከል በቁርጠኝነት እንዲሰሩ ጥሪያቸውን ያስተላለፉት ኡሁሩ ኬንያታ፣ መንግስታቸው ከዚህ በፊት ያደርገው እንደነበረው ሁሉ የፖሊስ አባላትን የአኗኗር ሁኔታ ለማሻሻል መስራቱን እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡
የኬንያ ብሄራዊ የፖሊስ አገልግሎት ኮሚሽን የፕሬዚዳንቱን የፖሊስ ሃይል የማጠናከር አገር አቀፍ እቅድ ለማስፈጸም እየተዘጋጀ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፣ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት የሚመለመሉት 10 ሺህ የፖሊስ መኮንኖችን በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ስልጠናቸውን አጠናቀው ወደ ስራ ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁሟል፡፡

    የአሜሪካው የጠፈር ምርምር ተቋም ናሳ በቅርቡ ላወጣቸው 8 የተለያዩ ክፍት የስራ ቦታዎች ማስታወቂያ፣ 18 ሺህ 300 ያህል አመልካቾች መመዝገባቸውንና ይህም በተቋሙ ስራ ለማግኘት በርካታ አመልካቾች የቀረቡበት የመጀመሪያው ክስተት ሆኖ መመዝገቡን ስካይ ኒውስ ዘገበ፡፡
ለክፍት የስራ ቦታዎቹ ያመለከቱት ሰዎች በዚህ መጠን ለመብዛታቸው እንደ ምክንያት ከተጠቀሱት ጉዳዮች መካከልም ማህበራዊ ድረገጾች የስራ ማስታወቂያዎችንና የቅጥር አገልግሎቶችን ማስፋፋታቸው እንዲሁም በጠፈር ጉዞ ላይ ያለው ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱ ይገኙበታል፡፡
በተቋሙ ታሪክ እጅግ ፉክክር የበዛበት ይሆናል ተብሎ በሚጠበቀው በዚህ የቅጥር ሂደት፣ በመስፈርትነት የተቀመጡትን የዜግነትና የትምህርት ደረጃ ሁኔታዎችን ያላሟሉ አመልካቾች ወዲያውኑ ከውድድር ውጭ ይደረጋሉ ተብሎ ይጠበቃል ተብሏል፡፡ ናሳ ላወጣቸው ክፍት የስራ ቦታዎቹ መቅጠር የሚፈልገው አሜሪካውያንን ብቻ እንደሆነና በምህንድስና፣ በባዮሎጂካል ሳይንስ፣ በፊዚካል ሳይንስና በሂሳብ ወይም በኮምፒውተር የትምህርት መስኮች ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸውን እንደሆነ ተነግሯል፡፡
የጠፈር ምርምር ተቋሙ እ.ኤ.አ በ1978 ላወጣቸው ክፍት የስራ ቦታዎች 8 ሺህ አመልካቾች የቀረቡበት አጋጣሚ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አመልካቾች የቀረረቡበት ሆኖ ተመዝግቦ እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡