Administrator

Administrator

 በሃዋሳ ከተማ በምሥራቅ ክፍለ ከተማ በ280 ሚሊዮን ብር ወጪ በ700 ካ.ሜ ቦታ ላይ የተገነባው ባለ 3 ኮከቡ ፌኔት ሆቴል፣ ታህሳስ 13 ቀን 2016 ዓ.ም  የክልሉ የሥራ ሃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡ የዕለቱ የክብር እንግዳ የሲዳማ ክልል ፕሬዚዳንት አማካሪ አቶ ተሰማ ዲማ በምርቃት ሥነስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “ሃዋሳ የቱሪዝም ከተማ እንደመሆኗ ሆቴሉ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል” ብለዋል።
አዳዲስና ዘመናዊ አገልግሎቶችን ያካተተው ፌኔት ሆቴል፤ የኮንፍረንስ ቱሪዝሙን መደገፍ የሚችሉ የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ክፍሎች ጭምር የያዘ ነው ተብሏል፡፡ለ41 ቋሚና 10 ጊዜያዊ ሰራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥሯል የተባለው ሆቴሉ፤ የከተማዋን የቱሪስት እንቅስቃሴና ገቢ ለማሳደግ የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተነግሯል፡፡
በ1992 ዓ.ም በሃዋሳ ከተማ ጥቂት ሰራተኞችን ይዞ በ50ሺ ብር በጀት በኪራይ ቤት የተጀመረው ሥራ፣ ለረዥም ዓመታት በከተማዋ ተወዳጅ ሆኖ ወደዘለቀው ፌኔት ክትፎ ቤት እንዳደገና  አሁን ደግሞ ባለ 3 ኮኮብ ሆቴል ማዋለድ እንደቻለ በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይ ተጠቁሟል፡፡  ፌኔት ሆቴል፤ በቀጣይ  ባለ 4 ኮኮብ ሆቴል ለመገንባት ያቀደ ሲሆን፤ ለክልሉ የመሬት ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ እየጠበቀ እንደሚገኝ የሆቴሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጤናዬ ዋርጌ ተናግረዋል፡፡

  ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፤ በሃዋሳ ፒያሳ በ500 ሚሊዮን ብር ያስገነባውን ባለ 12 እና ባለ 15 ወለል መንትያ ህንፃ ባለፈው ቅዳሜ ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በተገኙት አስመርቋል፡፡
የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ አዲሱን ህንፃ ከጎበኙ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ “ንብ ባንክ በሲዳማ ክልልም ሆነ በሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ማስፋፋት ለሚያቅዱ ሌሎች አካላት ምሳሌ የሚሆን  ተግባር እያከናወነ ነው፡፡” ብለዋል፡፡
ህንፃው ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ወለል የተለያዩ ሱቆች፣ ከአራት እስከ ስምንተኛ ወለል የሚከራዩ ቢሮዎች ያሉት ሲሆን፤ ዘጠነኛ ወለል ላይ የባንኩ ሃዋሳ ዲስትሪክት ፅ/ቤትና ከአንድ መቶ ሰዎች በላይ ሊያስተናግድ የሚችል አዳራሽ ይዟል፡፡ በተጨማሪም በአስረኛ ወለሉ ላይ የማረፊያ ክፍሎች ያሉት ሲሆን፤ አስራ አንደኛው ወለሉ ላይ ደረጃውን የጠበቀ ሬስቶራንት እንደያዘ ለማወቅ ተችሏል፡፡
 የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ገነነ ሩጋ በምረቃው ሥነስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “ንብ ባንክ፣ በባንክ አገልግሎቱ በበርካቶች ዘንድ ተደራሽ ከመሆኑ በተጨማሪ በአገሪቱ በተለያዩ ከተሞች ህንፃዎችን አስገንብቶ ሥራ ላይ በማዋሉ ከራሱ ባሻገር ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ግንባታ እንዲሁም ለብዙዎች የሥራ እድል በመፍጠር ረገድ የበኩሉን አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡ ባንካችን ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በቀጣይም ይህን ጥረቱን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡” ብለዋል፡፡
ባንኩ ከዚህ ቀደም ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በወልቂጤ፣ በዱከምና በሆሳእና የዋና መሥሪያ ቤት ህንፃዎችን ማስገንባቱ ይታወቃል፡፡

በአንድ አፈ-ታሪክ ውስጥ የሚገኝ የስድስት ሰዎችና የአንድ ትእቢተኛ ንጉሥ ታሪክ አለ፡፡ እንዲህ የሚል፡፡ አንድ መልካም እውቀት ያለው፣ አገሩን ከልቡ የሚወድና በሰራዊቱ ውስጥ በጀግንነት ያገለገለ ጎበዝና ብልህ ወታደር ጦርነቴ እንዳበቃ ለመጓጓዣ ያህል ብቻ ፍራንክ ሰጥቶ፤ ትእቢተኛው ንጉሥ ያባርረዋል፡፡
ወታደሩ በጣም አዝኖ “ንጉሱ እንዴት እንዲህ ጉድ ይሰሩኛል? እኔን የሚመስሉ ሰዎች ፈልጌ፣ እኒህን ንጉስ ያለ የሌለ ሀብታቸውን እንዲያስረክቡኝ አድርጌ ሙልጭ አወጣቸዋለሁ!” ብሎ ዝቶና ተቆጥቶ በእልህ ካገሩ ይወጣል፡፡
 ከዚያም በአንድ ጫካ ውስጥ እየተጓዘ ሳለ አንድ እጅግ በጣም ግዙፍ ሰውዬ ሳር የሚያጭድ ይመስል በተአምረኛ እጁ የጫካውን ግንድ ሁሉ እየገነደሰ ሲሸከም ያገኘዋል፡፡ “ወዳጄ ኃይል ጉልበት አለህና ለምን አብረን ሆነን ችሎታችንን አቀናጅተን በዓለም ውስጥ የተሳካላቸው ሁለት ሰዎች አንሆንም?” ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ ግዙፉ ሰው በሃሳቡ ተስማምቶ ተከተለው፡፡
ጥቂት እልፍ እንዳሉ አንድ አነጣጣሪ አዳኝ ያገኛሉ፡፡ አዳኙ “ከስንትና ስንት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ የአንዲትን ትንኝ ግራ ዓይን ለመምታት እያነጣጠርኩ ነው” ይላቸዋል፡፡ “ችሎታችንን ብናቀናጅኮ በአለም ውስጥ ሶስት የተሳካላቸው ሰዎች እንሆናለን፡፡ እባክህ አብረን እንሂድ” አሉት፡፡ እሺ ብሎ ተከተላቸው፡፡ አሁንም እልፍ እንዳሉ አንድ ትልቅ ዛፍ ጫፍ ላይ ወጥቶ የተቀመጠ ሰው ያገኛሉ፡፡ “እዚያ ዛፍ ጫፍ ላይ ተቀምጠህ ምን ታደርጋለህ?” ሲል ጀግናውና ብልሁ ወታደር ጠየቀው፡፡ ሰውዬውም “ከብዙ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሰባት በንፋስ የሚሰሩ ወፍጮዎች ይታዩኛል፡፡ አቅም አጥተው መሽከርከራቸውን አቁመዋል፡፡ ስለዚህ እነሱን ለማሽከርከር በተአምራዊ ኃይሌ ለመጠቀም አንዱን የአፍንጫዬን ቀዳዳ ደፍኜ በሌላኛው ስተነፍስ ወዲያው መዞር ይጀምራሉ” አላቸው፡፡ “በል ና አብረን እንሂድ፤ እኔ ብልህና ጀግና ወታደር ነኝ፡፡ እነዚህም እንዳንተው ችሎታ ያላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ አራታችን አንድ ብንሆን አለምን ለማሸነፍ እንችላለን” አለው፡፡ አውሎ ንፋስ ከአፍንጫው ማፍለቅ የሚችለው ሰውም ደስተኛ ሆነ፡፡
ጥቂት እንደተጓዙ በቀኝ እግሩ ብቻ የቆመና ግራ እግሩን ከጉልበቱ ፈትቶ መሬት ያጋደመ ሰው ያገኛሉ፡፡ “እግርህ ተቆርጦ እንዴት ተመችቶህ ቆምህ?” አለና ጠየቀው ብልሁ ጀግና፡፡ “እኔ ከወፎች የበለጥኩ ሯጭ ነኝ፡፡ ሁለቱንም እግሬን ከተጠቀምኩ ንፋስም አይቀድመኝም፡፡ ስለዚህ ረጋ ብዬ ለመሄድ እንድችል አንዱን እግር አውልቄ አስቀምጠዋለሁ” ይላል፡፡ “ተከተለንና አምስታችን ችሎታችንን አቀናጅተን አለምን እናሸንፍ” ይለዋል ብልሁ ጀግና፡፡ ሯጩም ተስማምቶ አብሯቸው ይጓዛል፡፡
 በመጨረሻ መንገድ ላይ ያገኙት አንድ ባርሜጣውን በአንድ ጆሮው ላይ ያንጠለጠለ ሰው ነበር፡፡ እሱም ለምን እንደዚያ እንዳደረገ ሲጠይቁት፣ ባርሜጣውን አስተካክሎ ካጠለቀ በኋላ በአካባቢው ያለውን ነገር ሁሉ እንደበረዶ ማቀዝቀዝ እንደሚችል ነገራቸው፡፡ “ስድስታችን አንድነት ቢኖረን አለምን እናሸንፋለንና አብረን እንሁን” አለው ብልሁ ጀግና፡፡ በሀሳቡ ተስማምቶ አብረው ሆኑ፡፡
ተሰብስበው ወደ እብሪተኛው ንጉስ ሲሄዱ ንጉሱ አዲስ አዋጅ አውጀው ደረሱ፡፡ አዋጁም “ከሴት ልጄ ጋር ሮጦ ተሽቀዳድሞ ያሸንፈ ባሏ ይሆናል፡፡ ሩጫው ካልተሳካለት ግን እንገቱ ይቆረጣል” የሚል ነበር፡፡ ብልሁ ጀግናም “የእኔ ሯጭ ያለጥርጥር ይቀድማታል” ሲል በኩራት ተናገረ፡፡ ንጉሱም “ቢሸነፍ ግን ያንተ ሯጭ ብቻ ሳይሆን ያንተም የራስህ አንገት ጭምር ይቆረጣል” ሲሉ ያስፈራሩታል፡፡ ውድድሩ ሩቅ ቦታ ወዳለ የውሃ ጉድጓድ ሮጦ ውሃ በባልዲ ቀድቶ ይዞ መምጣት ነው፡፡ የንጉሱ ልጅ እጅግ በጣም ፈጣን ሯጭ ናት፡፡ ንጉሡ ይተማመኑባታል፡፡
ሯጩ እግሩን ገጣጠመና ውድድሩ ተጀመረ፡፡ መቼ ሄደ ሳይባል በንፋስ ፍጥነት ሮጦ ውሃውን ቀዳና ሲመለስ ትንሽ አረፍ ልበል፤ ብሎ መንገድ ላይ ተኛ፡፡ እንዳይዘናጋና ብዙ እንቅልፍ እንዳይወስደው የሞተ ፈረስ የራስ-ቅል አግኝቶ ያንን ተንተራሰ፡፡ ሆኖም እንቅልፍ ይዞት ጭልጥ አለ፡፡ የንጉሱ ልጅ ገና ጉድጓድ እየሄደች ሳለች ተኝቶ አገኘችው፡፡
የሱን ባልዲ ውሃ ወደራሷ ባልዲ ገልብጣ ወደ ቤተመንግስት ገሰገሰች፡፡ ይህን ሁኔታ አነጣጣሪው ተኳሽ አየ፡፡ ስለዚህ በልዩ ችሎታው አነጣጥሮ ሯጩ የተንተራሰውን የፈረስ - ራስ- ቅል ነጥሎ መታው፡፡ ይሄኔ ሯጩ ነቃ፡፡ ባልዲው ባዶ መሆኑን ሲያይ ተንኮሉ ገብቶት እንደ ንፋስ በርሮ ውሃውን ይዞ የንጉሱን ልጅ ቀድሟት ገባ፡፡
ንጉሱ ተናደዱ፡፡ “ለዚህ ለጭባም ልጄን አልሰጥም!” አሉ፡፡ ስለዚህ ሌላ መላ መቱ፡፡ “በሉ የደስ ደስ ብሉ ጠጡ፡፡ ከዚያ ምቹ አልጋ ባለው ክፍል ተኙ፡፡ ጠዋት ልጄን ትረከባላችሁ” ይላሉ፡፡
ስድስቱ መንገደኞች በልተው ጠጥተው ተኙ፡፡ ለካ የተኙበት ቤት ከብረት የተሰራና በሩ ከተዘጋ መውጫ የሌለው ኖሯል፡፡ የንጉሱ አሽከር ከቤቱ ስር ካለው ምድር-ቤት ሆኖ እሳት ከስር እንዲያነድድና በብረቱ ግለት ታፍነው እንዲሞቱ ትእዛዝ ተቀብሎ ኖሮ እሳቱን ለቀቀባቸው፡፡ ሆኖም ባለባርሜጣው ጓደኛቸው ተንኮሉ ስለገባው ባርሜጣውን አስተካክሎ ሲያደርገው ብረቱ ሁሉ እንደበረዶ ቀዘቀዘና እሳቱም ሊያቀልጠው አልቻለም፡፡
ጠዋት ንጉሱ መጥተው ሲያዩ ስድስቱ ጓደኛሞች በሰላም ሲስቁ ሲጫወቱ አገኟቸው፡፡ በገኑ!! ጮሁ!! በንዴት አሽከራቸውን ትዕዛዜን አልፈፀምክም በሚል እንዲገደል አደረጉ፡፡
ሊሸነፉ መሆናቸውን ሲያውቁም ብልሁን ጀግና ጠርተው “በልጄ ፈንታ የፈለግኸውን ጠይቀኝ አደርግልሃለሁ!” አሉት፡፡ ብልሁ ሰውም “አሽከሬ ሊሸከመው የሚችለውን ያህል ወርቅ ይስጡኝ” አላቸው፡፡ ንጉሱ በጣም ተደሰቱ፡፡ “አሽከርህ መሸከም ካልቻለ ግን ሀብቴን ትመልሳለህ፡፡ በዚህ እንስማማ” አሉት፡፡ ብልሁ ጀግና ተስማማ፡፡ ንጉሱም ልባቸው ጮቤ ረገጠች፡፡ ከዚያ አንድ ዘዴ ፈጠሩ፡፡ የአገሩን ልብስ ሰፊዎች በሙሉ ሰብስበው ሰው ሊሸከመው የማይችል ትልቅ ከረጢት ስፉ ብለው አዘዙ፡፡
ልብስ ሰፊዎች እንደታዘዙት ትልቅ ድንኳን የሚያህል ከረጢት ሰፉ፡፡ ንጉሱ ያለ የሌለ ዕንቁ፣  ወርቅ ጌጣ ጌጥና ብር ሁሉ እንዲሞላ አዘዙና ተሞልቶ ተዘጋጀ፡፡
ያ የጫካውን ግንድ ሁሉ ሲሸከም የነበረው ግዙፍ ሰው ባንዴ ድንኳን አከሉን ከረጢት አንጠልጥሎ ስድስት ጓደኛሞች መንገድ ጀመሩ፡፡ ንጉሱ ተናደዱ፡፡ እብድ ሆኑ፡፡ አይኔ እያየ ምድረ-አቅመ ጎዶሎ፣ ምድረ-ጭባ ሀብቴን አይወስድ ብለው ፈረሰኛ ወታደሮች ሄደው፣ ስድስቱን መንገደኞች ገድለው ወርቁን ይዘው እንዲመጡ በቁጣ ያዝዛሉ፡፡
ፈረሰኞቹ ስድስቱ ተጓዦች ጋ ደርሰው፤ “እጅ ወደላይ!! በሰላም ሀብቱን አስረክቡ! አለዚያ እንጨርሳችኋለን!” ይሏቸዋል፡፡
በዚህን ጊዜ ከአፍንጫው አውሎ-ንፋስ ለማውጣት የሚችለው ተጓዥ፣ አንዱን የአፍንጫውን ቀዳዳ በእጁ ይዞ አንዴ ሲተነፍስ ወታደሮቹ ከእነ ፈረሳቸው ድምጥማቸው ጠፋ!
ንጉሱ የሆነውን ሁሉ ሲሰሙ በንዴት የቤተ-መንግስቱን ሰው ሁሉ በትንሽ በትልቁ ሰበብ አንገቱን እየቆረጡ የቅርብ ወዳጆቻቸውን ሳይቀር እየተነኮሱ፣ ጠበ -እየጫሩ ገድለው ጨረሱ፡፡
በመጨረሻም በነገሥኩበት አገር ውርደት አላይም ብለው ወደሌላ አገር ተሰደዱ፡፡ በተሰደዱበት አገር ሳሉ አእምሯቸው ተነካ፡፡ ይሄው እስከዛሬ ከእንቅልፋቸው በባነኑ ቁጥር “ልጄን ለማንም ጭባ አልሰጥም!” እያሉ ይጮሃሉ!!
***
ለአገሩ ለህዝቡ የሰራ የማይገፋባት፣ የማይገለልባት የማይበደልባት አገር ታስፈልገናለች፡፡ መሪ አለቃ ሃላፊ እብሪት ሲጠናወተው የማይታይባት አገር ታሻናለች፡፡ አቅማቸውን አቀናጅተው ለመስራት ለውጥ ለማምጣት የሚጥሩ “ተአምረኛ” ልጆች ያሉዋት አገር የታደለች ናት፡፡ በዋና ጉዳይ በድሎ በአናሳ ጉዳይ የሚያባብል የማይኖርባት አገር መልካም ቤት ናት፡፡ “ራሴን መትቶኝ እግሬን ቢያክልኝ ምንም አይገባኝ” የማይባልባት አገር ብትኖረን እንፀድቃለን፡፡ ሀገራችን የቅርብ ወዳጁን የማይንቅ የማይሰድብ፤ የቅርብ አጋሩን የማይርቅ፤ ድንገት ጎህ ቅዳጅ ላይ ዘራፍ የማይል፤ ድንገት ጀንበር መጥለቂያ ላይ ደሞ የማይሸማቀቅ እውነተኛ ሰው በመብራት የምትፈልግበት ዘመን ነው፡፡ ህዝብና አገር መሳለቂያ እንዳይሆኑ ስለእውነታቸው ከልብ የሚሟገቱ፣ ፈጠንኩ ብሎ የተመነጠቀውን ተመለስ ለማለት የሚደፍሩ፤ እየተራመደ መስሎ የሚያነክሰውን ወይ ዝለቅ ወይ ራቅ ለማለት የማይራሩ፤ የፈረደ መስሎ የሚሞዳሞደውን ውረድ ለማለት አይናቸውን የማያሹ ደመ መራራ ሹማምንት እንደሚያስፈልጉ ሁሉ ከአሻንጉሊትነት ነፃ የሆኑ ዲፕሎማሲን ግን የተካኑ ልባቸው ያልተደፈነ አእምሯቸው ያልተሸፈነ፣ እንቅፋት በመታቸው ቁጥር “መድኃኒት አድርገውብኝ ነው” የማይሉ፤ አለቃ ባስነጠሰ ቁጥር “መፈክር ይማርህ!” ብለው የማያላዝኑ ልባም ሰዎች የሚፈለጉበት ሰዓት ነው፡፡ ጉልበት እብሪት ንፉግነት ፣ ‘እኔ ብቻ አዋቂ’ ማለት፤ ‘እጁን ያወጣ ወዬለት’ ማለት ወደ ሰላም ሳይሆን ወደ ግጭት፤ ወደ መቀራረብ ሳይሆን ወደሽሽት የሚያመራ ነው፡፡ በዚሁ ፈር የልባቸውን ለመናገር ድፍረት ያጡ እየበረከቱ ከመጡ “ብትር ፈርተን ነው እንጂ የናቶቻችንን መዋያማ እናውቀዋለን” አለች ጥጃ የሚሉ ሰዎች የምናፈራባት አገር ብቻ ናት የምትኖረን፡፡
አንድ ጊዜ አንድ አዋቂ “ሞተር ብስክሌተኛ ማለት ምን ማለት ነው?” ተብሎ ሲጠየቅ የሚሄድ ሰው ነው” ብሎ ነበር፡፡ የሰማነውን በየልቦናችን ያሳድርልን፡፡

ቶሞካ ቡና ኃ.የተ.የግል.ማህበር በንኮማድ ኮንስትራክሽን ኃ.የተ.የግል ማህበር (ደንበል ሲቲ ሴንተር) ላይ የ48.2 ሚሊዮን ብር ክስ መመስረቱ ታወቀ፡፡
ከሳሽ ቶሞካ ቡና ጥር 7 ቀን 2011 ዓ.ም ስፋቱ 137 ካሬ ሜትር የሆነውንና በደንበል ሲቲ ሴንተር ህንፃ ላይ የሚገኘውን ቦታ እስከ ጥር 6 ቀን 2021 ዓ.ም ለአስር ዓመት ለቡና መሸጫ ካፊቴሪያነት አገልግሎት ለማዋል ከንኮማድ ኮንስትራክሽን ጋር የኪራይ ውል መዋዋሉን የክስ ጭብጡ ያስረዳል፡፡ ከሳሽ በዚሁ ውል መሰረት በመጋቢት ወር 2011 ዓ.ም በተፈፀመ የግንባታ ውል ቦታው ለቡና መሸጫነት ምቹና ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን 1 ሚሊዮን 491 ሺህ 403 ብር ወጪ በማድረግ አድሶና አሳምሮ ስራውን መቀጠሉን ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ልደታ ምድብ ችሎት፣ የውል ጉዳዮች ችሎት የቀረበው የክስ መዝገብ ያመለክታል፡፡
ይሁን እንጂ ተከሳሽ ጥቅምት 19 ቀን 2016 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ የኪራይ ውሉ መቋረጡን በመግለፅ  ካፌው የሚጠቀምበትን የኤሌክትሪክ የመብራት መስመር በማቋረጥና አገልግሎት እንዳይሰጥ በማድረግ በድርጅቱ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ማድረሱን ከሳሽ ለፍ/ቤቱ ባቀረበው ክስ አመልክቷል፡፡
ተከሳሽ     ውሉን ያቋረጠባቸው ምክንያቶች ከህግና ከስነስርዓት ውጪ በመሆናቸውና ለኪሳራ ስለዳረገኝ ፍርድ ቤቱ ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ተከሳሽ 48 ሚሊዮን 272 ሺህ 360 ብር እንዲከፍለኝ እንዲወስንልኝ ሲል መጠየቁን የክስ ዝርዝሩ ያስረዳል፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡን በስልክ የጠየቅናቸው የንኮማድ ኮንስትራሽን ኃ.የተ.የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ አበበ መንገሻ “በስልክ ምንም አይነት ምላሽ አልሰጥም” በማለታቸው ምላሻቸውን ማካተት አልቻልንም፡፡

 (የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጋዜጣዊ መግለጫ)

          የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፤ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣በጉራጌ ዞንና በቀቤና ልዩ ወረዳ መካከል የነበረውን አለመግባባት ተከትሎ ጥቅምት 2 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ የተከሰተውን የጸጥታ መደፍረስና ያስከተለውን ጉዳት ከአካባቢው ነዋሪዎች በቀረበለት አቤቱታ መነሻነት ከጥቅምት 20 እስከ 25 ቀን 2016 ዓ.ም.በቦታው በመገኘት ጭምር ምርመራ ያከናወነ ሲሆን፣ አሁንም በአካባቢው ያለውን አጠቃላይ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታም በመከታተል ላይ ይገኛል፡፡ ኮሚሽኑ ከተጎጂዎችና ምስክሮች ጋር 22 ቃለ-መጠይቆች አድርጓል፤ ከጉራጌ ዞን፣ ከወልቂጤ ከተማ አስተዳደርና ከቀቤና ልዩ ወረዳ የሥራ ኃላፊዎች፣ በዞንና በልዩ ወረዳ ደረጃ ከሚገኙ የመንግሥት ኃላፊዎች እንዲሁም በአካባቢው የሚገኘውን የኮማንድ ፖስት ኃላፊዎችን አነጋግሯል፤ ከሃይማኖት መሪዎችና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር 2 የቡድን ውይይቶች አካሂዷል፡፡ በተጨማሪም ዘረፋና ውድመት ደርሶባቸዋል የተባሉ የግልና የመንግሥት ተቋማትን ተዘዋውሮ ጎብኝቷል፤ተጎጂዎች ሕክምና ካገኙባቸው የሕክምና ተቋማት ማስረጃዎችን ጨምሮ የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን አሰባስቧል።
በጉራጌና በቀቤና ማኅበረሰብ መካከል ከዚህ በፊትም የተለያየ መጠን ያለው ግጭትና የሰላም ስምምነት ጥረት የነበረ ሲሆን፤ በተለይ ከቀቤና የልዩ ወረዳነት ምሥረታ ጋር በተያያዘና የልዩ ወረዳው መቀመጫን በተመለከተ በሁለቱ ማኅበረሰቦች አስተዳደሮች መካከል አለመግባባቱ እየተካረረና የግጭት አደጋው እየጨመረ መጥቶ እንደነበር መረዳት ተችሏል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ “በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች አሁንም ዘላቂ መፍትሔ ያልተሰጣቸው የመዋቅርና የአስተዳደር ጥያቄዎች ለሰላምና ደኅንነት እጦት እንዲሁም ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ምክንያት ሆነው መቀጠላቸው እጅግ አሳሳቢ ስለሆነ፤ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ኃላፊዎች ቅሬታና ጥያቄ የቀረበባቸውን አካባቢዎች ሁሉ ተዓማኒ በሆነና ተቀባይነት ባለው ሂደት በማሳተፍ ዘላቂ መፍትሔ ሊያመቻቹ ይገባል” ብለዋል፡፡
ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም፤ “በወልቂጤ ከተማ ጥቅምት 2 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ የተከሰተውን ሁከትና የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ የክልሉና የፌዴራል መንግሥት በመቀናጀትና ተገቢውን ማጣራት በማድረግ ተጠያቂነትን ማረጋገጥና ተጎጂዎችን መካስ ይገባል” ብለዋል፡፡



‘Fly Now Pay Later’


 ዳሽን ባንክና የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ደንበኞች የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቅመው ክፍያውን ቆይተው የሚከፍሉበትን ‘ጉዞዎ ይቀድማል ክፍያው ይደርሳል’ የሚል  አዲስ የክፍያ አማራጭ በዛሬው ዕለት አስተዋወቁ።

የዳሽን ባንክ ዲጂታል ባንኪንግ ዋና መኮንን አቶ ዮሐንስ መኮንን እንደገለጹት፤ ‘ጉዞዎ ይቀድማል ክፍያው ይደርሳል’ የተሰኘው አዲሱ  የክፍያ አማራጭ  በደንበኞች ምርጫ መሰረት በ6 ወር ወይም በ12 ወር የብድር ክፍያ የሚሰጥ ነው፡፡

 ደንበኞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን በዳሸን ባንክ የሂሳብ ቁጥር መክፈት እንደሚገባቸውና በተጨማሪም በባንኩ ቢያንስ ለሦስት ወራት አገልግሎት ያገኙ መሆን እንደሚገባቸውም አመልክተዋል፡፡

አዲሱን አገልግሎት ለመጠቀም አንድ ደንበኛ አስፈላጊ ቅድመ-ሁኔታዎችን ካሟላ በኋላ በቅርንጫፉ የተፈቀደለትን የብድር መጠን የሚወስድ ሲሆን፤ የተፈቀደለትን ገንዘብ ለመጠቀም የሚያስችል የአንድ ጊዜ መለያ ቁጥር መልዕክትም በተንቀሳቃሽ ስልኩ የሚደርሰው ይሆናል። በመቀጠልም ደንበኛው የተሰጠውን መለያ ቁጥር በአየር መንገዱ የሞባይል መተግበሪያ ላይ በማስገባት ትኬት መቁረጥና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን ይችላል።

በሁለቱ ተቋማት ስምምነት በቀረበው በዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን የሚፈቀደው የብድር ገንዘብ መጠን እስከ ስድስት መቶ ሺ ብር የሚደርስ ነው። የሚፈቀደው ብድር ወለድ የሚታሰብበት ሲሆን፤ ይህም ደንበኛው በመረጠውና ብድሩን በወሰደበት የጊዜ ገደብ ከብድሩ ጋር አብሮ የሚከፈል መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና የንግድ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ለማ ያዴቻ በበኩላቸው፤ “የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኛ ተኮር አሰራርን እንደመከተሉ የተለያዩ ዘመናዊና ለመጠቀም ቀላል የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን እያስተዋወቀ ይገኛል። የምናበለጽጋቸው ቴክኖሎጂዎች ለደንበኞቻችን ምቹ መሆናቸው እንደተጠበቁ ሆኖ የአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት ከሚሰጡት አገልግሎት ጋርም የተጣጣሙ እንዲሆኑ እናደርጋለን። ዛሬም አጋራችን ከሆነው የዳሽን ባንክ ጋር በመተባበር ለደንበኞቻችን ያቀረብነው አዲስ የክፍያ አማራጭ ተግባራዊ እንዲሆን የሞባይል መተግበሪያችን ከአዲሱ የክፍያ አገልግሎት ጋር የተቀናጀ እንዲሆን አድርገናል” ብለዋል።

ደንበኞች የተፈቀደላቸው የብድር መጠን ሲያልቅ ማደስ የሚችሉ ሲሆን፤ በአንዴ የወሰዱትን ብድርም ለተለያዩ በረራዎች ከፍለው መጠቀም እንደሚችሉ ታውቋል፡፡  አገልግሎቱ በተለይም በንግድ ስራ ላይ ለተሰማሩ፣ ለጅምላ አስመጪዎችና ለዕረፍት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ ውጭ ለሚሄዱ ደንበኞች አመቺ ነው ተብሏል።

2ኛው ሀገር አቀፍ የህገወጥ ንግድ መከላከል ጉባኤ በዛሬው ዕለት የተካሄደ ሲሆን፤ በመድረኩ ላይ ህገወጥ የቁም እንስሳ ንግድ ከፍተኛ ኪሳራ ማስከተሉ ተጠቁሟል፡፡

በጉባኤው ላይ በቁም እንስሳት፤ በመድኃኒትና ሌሎች የንግድ ዘርፎች ላይ በሚታይ ህገወጥ ንግድ ላይ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጓል፡፡

በንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የንግድ ስርዓትና ፈቃድ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፍሰሀ ይታገሱ  እንደተናገሩት፤ ህገወጥ ንግድን ለመከላከል በዘመናዊ መልኩ የንግድ ስርዓቱን ማስኬድና ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር መስራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በሀገር ደረጃ ጤናማ የንግድ ስርዓት እንዲኖር፤ የግሉን ዘርፍ መብት በጠበቀ መልኩ መንግስትም ተገቢውን ግብር እንዲያገኝ የሚያስችሉ መመሪያዎች እየተዘጋጁ እንደሚገኙ ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ኢንጂነር መላኩ እዘዘው በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በቁም እንስሳት በአፍሪካ አንደኛ ብትሆንም፣ ወደ ጎረቤት ሀገራት በሚደረግ  ህገወጥ ንግድ  ምክንያት ተጠቃሚ መሆን አልቻለችም ብለዋል፡፡

 “በመድሃኒት ንግድ አንድ ቢሊዮን ዶላር ግብይት የሚካሄድ ቢሆንም፣ በዘርፉ ባለው ህገወጥነትና ብልሹ አሰራር ምክንያት የሚፈለገው ገቢ አልተገኘም” ብለዋል፤ ፕሬዚዳንቱ፡፡

በሃዋሳ ከተማ በምሥራቅ ክፍለ ከተማ በ280 ሚሊዮን ብር ወጪ በ700 ካ.ሜ ቦታ ላይ የተገነባው ባለ 3 ኮከቡ ፌኔት ሆቴል፣ በዛሬው ዕለት የክልሉ የሥራ ሃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተመረቀ፡፡

የዕለቱ የክብር እንግዳ የሲዳማ ክልል ፕሬዚዳንት አማካሪ አቶ ተሰማ ዲማ በምርቃት ሥነስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ "ሃዋሳ የቱሪዝም ከተማ እንደመሆኗ ሆቴሉ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል" ብለዋል።

አዳዲስና ዘመናዊ አገልግሎቶችን ያካተተው ፌኔት ሆቴል፤ የኮንፍረንስ ቱሪዝሙን መደገፍ የሚችሉ የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ክፍሎች ጭምር የያዘ ነው ተብሏል፡፡

 ለ41 ቋሚና 10 ጊዜያዊ ሰራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥሯል የተባለው ሆቴሉ፤ የከተማዋን የቱሪስት እንቅስቃሴና ገቢ ለማሳደግ የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተነግሯል፡፡

በ1992 ዓ.ም በሃዋሳ ከተማ ጥቂት ሰራተኞችን ይዞ በ50ሺ ብር በጀት በኪራይ ቤት የተጀመረው ሥራ፣ ለረዥም ዓመታት በከተማዋ ተወዳጅ ሆኖ ወደዘለቀው ፌኔት ክትፎ ቤት እንዳደገና  ዛሬ  የተመረቀውን ባለ 3 ኮኮብ ሆቴል ማዋለድ እንደቻለ በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይ ተጠቁሟል፡፡

 ፌኔት ሆቴል፤ በቀጣይ በከተማዋ ባለ 4 ኮኮብ ሆቴል ለመገንባት ያቀደ ሲሆን፤ ለክልሉ የመሬት ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ እየጠበቀ እንደሚገኝ የሆቴሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጤናዬ ዋርጌ ተናግረዋል፡፡

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞና  ሌሎች ከፍተኛ የክልሉ የሥራ ሀላፊዎች ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በዛሬው ዕለት በመሐል ሐዋሳ ፒያሳ ላይ አስገንብቶ ያስመረቀውን ሁለገብ ሕንጻ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡

 የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ  ደስታ ሌዳሞ ከጉብኙቱ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ ''ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በሲዳማ ክልልም ሆነ በሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ማስፋፋት ለሚያቅዱ ሌሎች አካላት ምሳሌ መሆን የሚችል ተግባር እያከናወነ ነው'' ብለዋል።

''ባንካችሁ ለከተማችን ተጨማሪ ውበት ያጎናፀፈ ዘመናዊ ሕንጻ አስገንብቶ ለምረቃ በማብቃቱ እንኳን ደስ አላችሁ” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ''ንብ ባንክ እንደ ስሙ ጥራት ያለው ስራ የሚያከናውን ባንክ ነውም'' ሲሉ አክለው ተናግረዋል፡፡



በሐዋሳ ከተማ የተሟላ የባንክ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ 20 ዓመታትን ያስቆጠረው ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፤ በከተማዋ የዲስትሪክት ፅ/ቤት ያለው ሲሆን  የቅርንጫፎቹንም ቁጥር 8 አድርሷል።

 ባንኩ በሐዋሳ ፒያሳ ያስገነባውን ባለ 12 እና ባለ 14 ወለል መንትያ ሕንጻ በዛሬው ዕለት የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ሀላፊዎች፣ የባንኩ የቦርድ ከፍተኛ የስራ አመራር፣ ማኔጅመንትና የከተማዋ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት ማስመረቁን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በሀገር አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያው ነው የተባለለት የአንጎል የደም ስር ክሊፒንግ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል።

ይህ ህክምና የተደረገላት ታካሚ ከአዲስ አበባ በጥቂት ርቀት ላይ የምትኖር ሲሆን፤ ድንገት በዕለት ሥራዋ ላይ ሳለች ከፍተኛ የራስ ህመም ይሰማት እንደጀመረና ከዚያም እራስዋን ስታ መውደቋን ታሪኳ ያስረዳል።

ህክምና ተቋም እንደደረሰችም በተደረገላት ምርመራ በአንጎልዋ ውስጥ የደም ቧንቧ መፈንዳት ምክንያት የደም መፍሰስ እንደተከሰተና የፈነዳው የደም ቧንቧ በቀዶ ጥገና ህክምና ባስቸኳይ ካልተስተካከለ ለሞት የሚዳርጋት መሆኑን ይነገራታል።

በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በኒውሮሰርጀሪ ዲፓርትመንት አስተባባሪነትና የአንጎል ደም ቧንቧ ቀዶ ጥገና ህክምና ከፍተኛ ልምድ ባካበቱት ዶ/ር ቶማስ ቦጋለ የሚመራ የህክምና ቡድን፣ ታህሳስ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ሶስት ሰዓት ከግማሽ በወሰደ የቀዶ ጥገና፣ የተስተካከለ የአንጎል የደም ዝውውር እንዲኖራት ማድረግ ተችሏል።

ታካሚዋ በተደረገላት ህክምና እጅጉን እንደተደሰተች ገልጻ፥ ባሁኑ ሰዓት ከህመምዋ አገግማ ወደ ቤትዋ ተመልሳለች፡፡  ይህ ህክምና ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ  በመንግስት ሆስፒታሎች ሲሰራ የአሁኑ  የመጀመሪያው ነው ተብሏል።