Administrator

Administrator

በመርካቶ ሸማ ተራ አካባቢ የተከሰተውን የእሳት አደጋ ለመቆጣጠር እሳት አደጋ እና ስጋት መከላከል እንዲሁም ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመሆን ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ፡፡
 
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልእክት፤ በመርካቶ ሸማ ተራ አካባቢ በተከሰተው የእሳት አደጋ በንብረት ላይ ለደረሰው ጉዳት እጅግ አዝነናል ብለዋል።
 
አደጋውን ቶሎ ለመቆጣጠር እየተደረገ ባለው ጥረት የአካባቢው መንገድ የእሳት አደጋ መኪና በተሟላ ሁኔታ ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ በመሆኑ ሄሊኮፕተር ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።   
 
ይህንን አደጋ ለመቀነስ ርብርብ እያደረጋችሁ ያላችሁ አካላት ሁሉ ጥረታችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ አሳስባለሁ ብለዋል ከንቲባዋ በመልእክታቸው።

እሳቱ ከተነሳ በርከታ ደቂቃዎች ቢቆጠሩም እስካሁን መቆጣጠር እንዳልተቻለ በስፍራው የሚገኙ የቤተሰባችን አባላት ገልጸዋል።

" እሳቱ ጠንከር ያለ ነው ፤ በስፍራው እሳት አደጋዎች ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ ቢሆንም ምንም ሊጠፋ አልቻለም። በስፍራው ላሉ የአደጋ ሰራተኞች ተጨማሪ ቦቴና እገዛ ያስፈልጋል ፤ በውሃ ብቻም የሚሆን አይደለም " ብለዋል።

" በአካባቢው ያሉ እሳቱ ያልደረሰባቸው ሰዎች ንብረታቸውን እያሸሹ ይገኛሉ " ሲሉም አክለዋል።



ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን መገናኛ ብዙኃን ስርጭት ድርጅት የተገነባው አዲስ ዘመናዊ ስቱዲዮና 50 ሚሊየን ብር የሚያወጣ ስክሪን ተመርቋል፡፡  

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በማኅበራት ምዝገባና ቁጥጥር መምሪያ እውቅና የተሰጠው "ፍኖተ ጽድቅ ጠቅላላ ማኅበር"፣ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን ሥርጭት ድርጅት ያስገነባው ዘመናዊ ስቱዲዮ ባለፈው ቅዳሜ ጠዋት  በታላቅ ድምቀት ተመርቋል።

አዲሱ ስቱዲዮ አንድ ዘመናዊ ስቱዲዮ ማሟላት የሚገባውን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማሟላቱ የተነገረ ሲሆን፤ስቱዲዮው ግዙፍ 8k ስክሪን የተገጠመለትና የተለያዩ ቀረጻዎችን ማከናወን የሚያስችሉ ገጽታዎችና የግንኙነት ካሜራ የተገጠመለት የስቱዲዮ መቆጣጠሪያ ክፍል እንዳለው ታውቋል፡፡

የስቱዲዮ ግንባታው ከ3 ዓመታት በላይ መፍጀቱ  በምረቃው ሥነስርዓት ላይ ተገልጿል።

በምረቃው መርሐግብር ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ፣ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ  የባሕርዳና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሁም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡


በፍኖተ ጽድቅ ማኅበር መሥራች መጋቤ አእላፍ ጸጋዬ ደበበ ሙሉ ወጪ የተገነባው ይኸው ስቱዲዮ፤ ድርጅቱ በሚያሰራጫቸው ይዘቶች የፕሮዳክሽን ጥራት ለመጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተጠቁሟል፡፡

የቴሌቪዥን ተቋሙ በቅርቡ ከሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከት ኅብረት በተደረገለት ድጋፍ የቀጥታ ሥርጭት የጀመረ ሲሆን፤ በሣተላይት በኢትዮ ሳት እና በዲኤስ ቲቪ እንዲሁም በዲጂታል ሚዲያ ሥርጭቱን ይበልጥ በማሳደግ ላይ ይገኛል ተብሏል።


አንቴክስ ጨርቃጨርቅ ኃ.የተ.የግ.ማ. የ20 ሚ. ብር ውድድር አዘጋጀ

•  በኢኮኖሚና በሰላም ዘርፍ ያሸነፉ 2 ተወዳዳሪዎች በነፍስ ወከፍ 10 ሚ. ብር ይሸለማሉ


•  የሽልማት ሥነስርዓቱ ታህሳስ 17 በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ይካሄዳል




ላለፉት 7 ዓመታት በአዳማ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በጨርቃጨርቅ ምርት ላይ የተሰማራው የቻይናው አንቴክስ ጨርቃጨርቅ ኃ.የተ.የግ.ማ፤ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ልማትና ሰላም የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ግለሰቦችና ድርጅቶችን አወዳድሮ 20 ሚሊዮን ብር ሊሸልም መሆኑ ተገለጸ፡፡


የአንቴክስ ኢትዮጵያ አመራሮችና ዝግጅቱን የሚያስተባብረው በሻቱ ቶለማርያም መልቲሚዲያ፣ ዛሬ ተሲያት በኋላ፣ በአዳማ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የድርጅቱ አዳራሽ  በሽልማቱ ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡


በመግለጫው ላይ እንደተብራራው፣ ድርጅቱ በኢኮኖሚ ልማትና በሰላም ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ግለሰቦችና ድርጅቶችን አወዳድሮ  ያሸነፉ ሁለት ግለሰቦች ወይም ድርጅቶችን ለእያንዳንዳቸው 10 ሚሊዮን ብር ይሸልማል፡፡


ለዚህ ሁለት የሽልማት ዘርፎች የሚመረጡ እጩዎች ከመላው ኢትዮጵያ በህዝብ ጥቆማ ታሪካቸው ወይም ሥራቸው እንደሚሰበሰብ የተጠቆመ ሲሆን፤ አሸናፊዎች ለዚህ ውድድር በተመረጡ ዳኞችና በህዝብ ድምጽ ተለይተው የሽልማት ሥነስርዓቱ ታህሳስ 17 ቀን 2017 ዓ.ም በአፍሪካ ህብረት የስብሰባ ማዕከል እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡



አንቴክስ ኢትዮጵያ ላለፉት 7 ዓመታት በአገሪቱ ውስጥ በነበረው ቆይታ፣ ያሉትን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውጣ ውረዶች በመገንዘብ፣ መፍትሄ የማፈላለግ ሂደት ውስጥ የራሱን ሚና ለመወጣት ባቋቋመው ፉድ ኤንድ ፕላስ የተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅት አማካኝነት በርካታ እርዳታዎች ሲያደርግ መቆየቱ በመግለጫው ላይ ተጠቁሟል፡፡


በአሁኑ ወቅት ደግሞ የዚሁ አካል የሆነ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ልማትና ሰላም የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦችና ድርጅቶች ዕውቅና የሚሰጥ ምርጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሥራዎች (Best Influencer Work Prize)ሽልማትን ለመስጠት እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፤ ከዛሬ ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም አንስቶ የእጩ ተወዳዳሪዎችን ታሪኮችና ሥራዎች መቀበል እንደጀመረ ተነግሯል፡፡