Administrator
የዲናው የሰንበት ውሎ
ዲናውና ሁለተኛ ልጁ ሉዊስ ስላሴ በአሜሪካን ሙዚየም ኦፍ ናቹራል ሂስትሪ
በ1970 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ የተወለደውና በልጅነቱ ወደ አሜሪካ ያቀናው ዲናው መንግስቱ፣ እድገቱ በቺካጎ ሲሆን ከጆርጅ ታውን ዩኒቨርሲቲ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የመጀመሪያ ዲግሪውን፣ ከኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በስነጥበብ ሁለተኛ ዲግሪውን ተቀብሏል፡፡
‘ዘ ቢዩቲፉል ቲንግስ ዛት ሄቨን ቢርስ’፣ ‘ሀው ቱ ሪድ ዘ ኤር’ እና ‘ቺልድረን ኦፍ ዘ ሪቮሊዩሽን’ በተሰኙት የረዥም ልብወለድ መጽሃፍቱ በሃገረ አሜሪካ ከፍተኛ ታዋቂነትን ያተረፈው ደራሲ ዲናው መንግስቱ፣ ሮሊንግ ስቶንንና ዎልስትሪት ጆርናልን በመሳሰሉ ታዋቂ ጋዜጦችና መጽሄቶች ለንባብ በሚያበቃቸው ስራዎቹም ይታወቃል፡፡ በርካታ የስነጽሁፍ ሽልማቶችንም ለማግኘት በቅቷል፡፡
በ2007 ያሳተመው የመጀመሪያ መጽሃፉ የአመቱ የኒዮርክ ታይምስ ታላቅ መጽሃፍ ተብሎ የተመረጠለት ዲናው፣ ዘ ኒዮርከር ጋዜጣም በ2010 ከአርባ አመት ዕድሜ በታች ያሉ ምርጥ ሃያ ደራሲዎቼ ብሎ ከጠቀሳቸው መካከል ተካትቷል፡፡ ሎስአንጀለስ ታይምስ በ2008 የምርጥ መጽሃፍ ተሸላሚ አድርጎታል።
በ2007 የናሽናል ቡክ አዋርድ ፋውንዴሽን ሽልማትን የተቀበለ ሲሆን፣ በተመሳሳይ አመትም ‘ቺልድረን ኦፍ ዘ ሪቮሊዩሽን’ በሚለው መጽሃፉ የጋርዲያንን ፈርስት ቡክ አዋርድ ያገኘ ተደናቂ ደራሲ ነው፡፡
ደራሲ ዲናው መንግስቱ ለመጨረሻ ዕጩ ተሸላሚነት ከታጨባቸው ታዋቂ ሽልማቶች መካከልም፣ የዳይላን ቶማስ ሽልማት፣ የኒዮርክ ፐብሊክ ላይብራሪ ያንግ ላዮንስ ሽልማት፣ ግራንድ ፕሪክስ ዴስ ሌክትሬ ዲ ኤሌ ሽልማት ይጠቀሳሉ፡፡
‘ኦል አዎር ኔምስ’ የሚል ርዕስ የሰጠው አራተኛ መጽሃፉ በቅርቡ ለህትመት የሚበቃለት ዲናው፣ ነዋሪነቱን ከባለቤቱ አና ኢማኑኤሌ እንዲሁም ከሁለት ወንድ ልጆቹ ጋብሬልና ሉዊስ ስላሴ ጋር በዋሽንግተን ዲሲ አድርጓል፡፡
ዲናው የአንድ ሰንበት ውሎውን ገጽታ፣ ለኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጠኛ ጁሊ ቦስማን በራሱ አንደበት እንዲህ ተርኮላታል፡፡ ኒዮርክ ታይምስም የዲናውን ውሎ ባሳለፍነው ሳምንት የዕለተ ሰንበት እትሙ ለንባብ አብቅቶታል፡፡
እነሆ!
‘አላርም’ አንፈልግም!
ከቤተሰባችን አባላት ሁሉ ሰነፉ ሰው እኔ ነኝ፡፡ ማልጄ ከአልጋዬ መውረድ አልወድም፡፡ እኔና ሚስቴ ከእንቅልፋችን የሚቀሰቅሰን አላርም አንሞላም። ቀስቅሰው መንጋቱን የሚነግሩን ሁሌም ማልደው የሚነቁት ልጆቻችን ሉዊስ ስላሴና ጋብርኤል ናቸው። ንጋት አስራ ሁለት ሰዓት አካባቢ ከአልጋቸው ብድግ ይሉና የመኝታ ቤታችንን በር በርግደው ከተፍ ይላሉ፡፡ እየተሯሯጡ እኔና እናታቸው የተኛንበት አልጋ ላይ ይወጣሉ፡፡
“በሉ ተነሱ! ረፍዷል!” ብለው ይቀሰቅሱናል፡፡ እኔና ሚስቴ ግን፣ በተለይ በሰንበት ተኝተን ማርፈድ ነው የምንፈልገው፡፡
“እባካችሁ ተውን! ትንሽ እንተኛ አትረብሹን!” እንላቸውና የተወሰነ ጊዜ ተኝተን እንቆያለን፡፡
ከዚያ ሚስቴ ቀድማኝ ትነሳና ለቤተሰቡ ቁርስ ታዘገጃጃለች፡፡ ቁርሳችንን የምንበላው ከአልጋችን ሳንወጣ ነው፡፡ አሪፍ የሆነ ወፍራም ስፕሬሶ እናዘጋጃለን፡፡ እዛው አልጋዬ ውስጥ እንደተጋደምኩ ስፕሬሶዬን እጠጣለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ነው፣ ከእንቅልፌ ሙሉ ለሙሉ ነቅቼ ከአልጋዬ መውረድና የሰንበት ውሎዬን ‘ሀ’ ብዬ መጀመር የምችለው፡፡
ወደ ኬክ ሩጫ
የእለቱ የአየር ሁኔታ የከፋ ካልሆነ በቀር፣ የመጀመሪያው የእሁድ ተግባራችን ልጆቻችንን በተገቢው ሁኔታ ማለባበስና ለሰንበት ሩጫ መዘጋጀት ነው፡፡ የቤተሰቡ የሰንበት ሩጫ መነሻውን ከምንኖርበት አፓርታማ ደጃፍ አድርጎ፣ ከሰፈራችን አቅራቢያ የሚገኝ አንድ ኬክ ቤት በር ላይ ይጠናቀቃል፡፡ የፈረንሳይ ዜጎች የሚያስተዳድሩት ይህ ኬክ ቤት፣ በከተማዋ ምርጥ ኬኮችን ከሚያቀርቡ አሉ የተባሉ ስመጥር ኬክ ቤቶች አንዱ ነው፡፡
የእኛ ቤተሰብም ዘወትር እሁድ ማለዳ ወደዚህ ኬክ ቤት የሰንበት ሩጫ የምናደርገው፣ ‘ቁራሳ’ የሚባለውን ጣፋጭ ኬክ ለመሸመት ነው፡፡ ፓሪስ ውስጥ ነዋሪ እያለንም ማልደን ወደ ኬክ ቤት መሄድና ቁራሳ መግዛት የተለመደ ተግባራችን ነበር፡፡ እዚህ ከመጣን በኋላም፣ በሰንበት ማለዳ ከልጆቻችን ጋር ወደ ኬክ ሩጫ ማድረጋችንን አልተውነውም፡፡
እንስሳ መሆንን የሚያስመኝ የእንስሳት ፍቅር!
ኬካችንን ገዝተን ወደ ቤታችን ከተመለስንና አጣጥመን ከበላን በኋላ፣ የጠርሙስ ጭማቂዎችንና በግቢያችን ከሚገኙ የተለያዩ የቤት እንስሳቶች የሳምንቱን ተረኛ የቤት እንስሳ እንመርጣለን። ተረኛው እንስሳ ቀኑን ሙሉ ከእኛ ጋር በሄድንበት ሁሉ ይዘነው ስንዞር የሚውል ነው። ጭማቂዎቻችንን፣ ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችንና ተረኛውን እንስሳ ይዘን ረፋድ ላይ ከቤት እንወጣለን - ወደ ጉብኝት፡፡
በየሳምንቱ የምንጎበኛቸውን ቦታዎች እንመርጣለን፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ አንድ እሁድ የጎበኘነው፣ በኒውዮርክ ሲቲ የሚገኘውንና በአለማችን ትልቁ የተፈጥሮ ታሪክ ሙዚየም መሆኑ የሚነገርለትን “አሜሪካን ሙዚየም ኦፍ ናቹራል ሂስትሪ” ን ነበር፡፡ ልጆቻችን በግቢያችን ለምናሳድጋቸው ለሁሉም እንስሳት ልዩ ፍቅር ነው ያላቸው፡፡ በተለይ ታናሽዬው ሉዊስ ስላሴ ለእንስሳት ያለው ፍቅር እጅግ የሚገርም ነው፡፡ እንስሳትን አብዝቶ ከመውደዱ የተነሳ፣ ቀሪ የህይወት ዘመኑን እንስሳ ሆኖ ማሳለፍ እንደሚፈልግ ይናገራል፡፡
ጋደም ብሎ ንባብ
የዕለቱን ጉብኝት ካጠናቀቅን በኋላ፣ ሉዊስ ቢያንስ ለአንድ ሰዓት ያህል መተኛት ስላለበት ወደቤታችን እንመለሳለን፡፡ እሱ ከእንቅልፉ እስኪነቃ ቤቱን ስናዘገጃጅ እንቆያለን፡፡ ከዚያም እኔና የመጀመሪያው ልጄ ጋብርኤል አልጋችን ላይ ጋደም ብለን ማንበብ እንጀምራለን፡፡ እኔ የዕለተ ሰንበት ጋዜጦችን ማገላበጤን ስቀጥል፣ ጋብርኤል ደግሞ በአይፓዱ ጌም ይጫወታል፡፡
ሳትወልድ ብላ!
ምሳ ሰዓት እየደረሰ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ለትንሹ ልጃችን ሾርባ እናዘጋጃለን፡፡ እኔና ሚስቴ ምግብ ላይ እስከዚህም ነን፡፡ ልጆቻችንን ግን በአግባቡ ነው የምንመግበው፡፡ ሳትወልድ ብላ ይባል የለ!... ልጆች ሲኖሩሽ ብዙ ምግብ አትበይም፡፡ ታላቁ ልጅ ምግብ ላይ አደገኛ ነው፡፡ ምግብ በሰዓቱ ካልደረሰ ጉዳችን ይፈላል፡፡ እንደ ሙዝ ያሉ ቢጫ ቀለም ያላቸውን ምግቦች የበለጠ ይወዳል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በመጠኑ የተወሰነ ፒዛ መብላት ጀምሯል፡፡
የተሲያት ብስኩት
ዘወትር እሁድ ከሰዓት በኋላ አንድ የተለመደ ፕሮግራም አለን - ብስኩቶችን መጋገር፡፡ ሁለቱም ልጆቻችን ብስኩቶችን መጋገር ይወዳሉ፡፡ እሁድ ከሰዓት በኋላን ኩኪስ በመጋገር ተጠምደው ነው የሚያሳልፉት፡፡ ሊጥ አብኩተው፣ እንቁላል በጥብ
ጠው ኩኪስ ሲጋግሩና ሲጠብሱ ነው የሚውሉት፡፡
የምሽት እንግዳ
ፓሪስ እያለን ሁሌም እሁድ እሁድ ማታ የሆነ እንግዳ ወደ ቤታችን ጎራ ማለቱ አይቀርም ነበር። ለነገሩ እዚህ ከመጣን በኋላም፣ ቢያንስ ከሁለት እሁድ በአንዱ የሆነ እንግዳ ሳናስተናግድ አንቀርም። ብዙ ጊዜ ለእሁድ ማታ ራት የተጠበሰ ዶሮ ነው የምናዘጋጀው፡፡
በነገራችን ላይ እኔ ራሴ የተዋጣልኝ ምግብ ሰሪ ነኝ፡፡ ቶማስ ኬለር የሚባለው ታዋቂ የምግብ አብሳይ በሚጠቀምበት አዘገጃጀት መሰረት ነው የዶሮ ጥብስ የምሰራው፡፡ ዘይት ወይም ቅቤ የሚባል ነገር አይገባበትም፡፡ በተቻለ መጠን ጥብሱ ደረቅ ያለ መሆን አለበት፡፡ በዚህ መልኩ ሲዘጋጅ የዶሮዋ ቆዳ በሚገርም ሁኔታ ስለሚደርቅ ሲበላ ኩርሽም ኩርሽም ይላል፡፡ ዋው!... እንዴት እንደሚጣፍጥ ልነግርሽ አልችልም!
እንግዶች ከመጡ ጥሩ አድርገን ስናስተናግድ እናመሻለን፡፡ ልጆቻችንም ገላቸውን ታጥበው የሌሊት ልብሶቻቸውን ይለብሳሉ፡፡ ልጆቹ በአብዛኛው ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ ነው የሚተኙት፡፡ ቤታችን ውስጥ ያለውን ሰው በሙሉ ደህና እደሩ ብለው ይሰናበቱና ወደ አልጋዎቻቸው ያመራሉ፡፡ እንቅልፍ እስከሚወስዳቸው ድረስ አንድ ሁለት አጫጭር ታሪኮች ያሏቸው የህጻናት ፊልሞችን ያያሉ፡፡ ከፊልሙ በሚወጣው የህጻናት ጫጫታ ታጅበው ማንቀላፋት ይወዳሉ፡፡
እሁድ ስታልቅ
እሁድ ቀን ከሚስቴና ከልጆቼ ጋር ዘና ስል መዋል እንጂ፣ በስራ ተጠምዶ መዋልም ሆነ ማምሸት አይመቸኝም፡፡ እሁድን ዘና ብዬ በእረፍት አሳልፌ፣ ሰኞን በነቃ ትኩስ ስሜት መቀበል ነው የምፈልገው። አንዳንዴ ግን፣ አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ በመጠኑም ቢሆን ልሰራ እችላለሁ፡፡ ለምሳሌ በጆርጅ ታውን ማክሰኞ ማክሰኞ ተማሪዎችን አስተምራለሁ፡፡ ስለሆነም ለማስተምረው ትምህርት መዘጋጀት ሲያስፈልገኝ፣ እሁድም ቢሆን የተወሰነ ሰዓት አምሽቼ መዘጋጀቴና ከመሸ ወደ አልጋ ማምራቴ አይቀርም፡፡
የሰንበት እንግዶቻችንን በወጉ አስተናግደን ከሸኘን በኋላ፣ ከሚስቴ ጋ አልጋችን ላይ ጋደም ብለን ፊልም እያየን አይስክሬም እንበላለን፡፡ ለምሽቱ የምናየውን ፊልም ከሚስቴ ጋር ተነጋግረን ነው የምንመርጠው፡፡
ፊልሙ የእሷ ምርጫ ከሆነ፣ በአንድ ደራሲ ወይም አርቲስት ህይወት ዙሪያ የሚያጠነጥን ዶክመንታሪ ፊልም መሆኑ አይቀርም። ምርጫው የእኔ ከሆነ ግን፣ እምብዛም ዋጋ የሌለው ፊልም መሆኑ ግድ ነው፡፡
ታላቅ የጥናት ጉባኤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል፣ የተመሰረተበትን 50ኛ ዓመት በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች የሚያከብር ሲሆን በትላንትናው ዕለት በዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋኩልቲ ግቢ፣ በእሸቱ ጮሌ አዳራሽ ታላቅ የጥናት ጉባኤ ተጀምሯል። ዛሬም ይቀጥላል የተባለው የጥናት ጉባኤው 40ኛ ዓመቱን የሞላው “የመጀመሪያው” አብዮትና ተከታይ ክስተቶች በኢትዮጵያ የታሪክ ትርጉም ላይ ያሳረፏቸው ተፅዕኖዎች የሚፈተሽበት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
የፕሮግራሙ አዘጋጆች ለአዲስ አድማስ በላኩት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ በሁለቱ ጉባኤ ቀናት 25 የታሪክ ባለሙያዎች የጥናት ወረቀት የሚያቀርቡ ሲሆን ከታሪክ ጋር በተያያዙ ተግዳሮቶችና ዕድሎች ዙሪያ ሰፋ ያለ ውይይት የሚደረግበት የመጀመሪያው አጋጣሚ እንዲሆን ተጠቁሟል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ አካዳሚክ ማህበረሰቡ፣ የታሪክ ባለሙያዎች፣ ለታሪክ ልዩ ቅናት ያላቸው የህብረተሰብ አካሎችና ጋዜጠኞች በሚገኙበት በዚህ ጉባኤ፤ ፍላጎት ያላቸው ሁሉ እንዲታደሙ አዘጋጆቹ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
“ቅጥልጥል ኮከቦች” ትያትር ለተመልካች ቀረበ
በፀሃፌ ተውኔት ውድነህ ክፍሌ ተፅፎ በተሻለ አሰፋ የተዘጋጀው “ቅጥልጥል ኮከቦች” ትያትር ባለፈው እሁድ ተመርቆ ተከፈተ፡፡
የትያትሩ ጭብጥ በህክምና ስነ ምግባር ጥሰትና በምርመራ ጋዜጠኝነት ላይ የሚያተኩር ሲሆን ትያትሩ ተመርቆ ከመከፈቱ በፊት በባለሙያዎች እንደተገመገመ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በትያትሩ ላይ አርቲስት ሽመልስ አበራ (ጆሮ)፣ መሰረተ ህይወት፣ ስናፍቅሽ ተስፋዬ፣ ሱራፌል ተካና ሌሎችም ይተውኑበታል፡፡
ትያትሩ ዘወትር እሁድ ከ8 ሰዓት ጀምሮ ለተመልካች እንደሚቀርብም ታውቋል፡፡ ፀሃፌ ተውኔት ውድነህ ክፍሌ ከዚህ ቀደም ከአስር በላይ ትያትሮችን ፅፎ ለተመልካች አቅርቧል፡፡
“ስኳር እና ፍቅር” ተመረቀ
የገጣሚና ሙዚቀኛ ቴዎድሮስ ነጋሽ ሁለተኛ የግጥም መድበል “ስኳር እና ፍቅር” በትላንትናው ዕለት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት አዳራሽ ተመረቀ፡፡ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የደራሲው ቀደምትና አዳዲስ ስራዎች ከሙዚቃ ጋር ታጅበው የቀረቡ ሲሆን ባይላሞር የዳንስ ቡድን በሳልሳ ዳንስ ፕሮግራሙን እንዳደመቀው ታውቋል፡፡
የሃዲስ አለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ሲምፖዚየም ያካሂዳል
ባለፈው ዓመት በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ስር የተቋቋመው የሃዲስ አለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ዛሬና ነገ ሁለተኛ ዓመታዊ ሲምፖዚየሙን በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ጊቢ እንደሚያካሂድ ተገለፀ፡፡
በሲምፖዚየሙ ላይ ሰባት ባህል ተኮር ጥናታዊ ፅሁፎች በአገር ውስጥና በውጭ ተመራማሪዎች ይቀርባሉ ተብሏል፡፡ ባለፈው ዓመት የተቋቋመው የባህል ጥናት ተቋሙ፣ ከጀርመኑ “ኢትዮ ስፔር” ጋር በመተባበር፣ በአካባቢው በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ያሉትን የተለያዩ ቅርሳ ቅርሶች በዲጂታላይዜሽን ሥርዓት አደራጅቶ በመያዝ ለትውልድ ለማስተላለፍ እገዛ እንደሚያደርግ የተናገሩት የተቋሙ ዳይሬክተር አቶ መስፍን ፈቃዴ፤ ተቋሙ የአብነት ት/ቤቶች ባህላዊ አስተምህሮቱን ጠብቀው እንዲዘልቁ የማጠናከሪያ ስራ ይሰራል ብለዋል፡፡
የሃዲስ አለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም የአካባቢውን ባህል፣ ወግ፣ ልማድ፣ ትውፊትና ኪነ-ጥበብ ለመጠበቅና በርካታ ትውፊታዊ ሃብቶች ያሏቸው ቅኔና ግዕዝ በምርምር ታግዘው፣ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፉ የማድረግ ዓላማ ይዞ መቋቋሙ ይታወሳል፡፡
“አላቲኖስ” የአድዋ ድልን 120ኛ ዓመት በዓል በጣይቱ ሆቴል ያከብራል
አላቲኖስ ፊልም ሰራዎች ማህበር ከኤድሚክ ፊልምና ቲያትር ካምፓኒ ጋር በመሆን የአድዋ ድልን 120ኛ ዓመት ክብረ በዓል “የዓድዋ ስነ-ጥበብ” በሚል መሪ ቃል በነገው ዕለት ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ በጣይቱ ጃዝ አምባ እንደሚያከብር አስታወቀ፡፡ ማህበሩ ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ እንደጠቆመው፤ የአድዋን ሥነ-ጥበባዊነት የሚያጎሉ ጥናታዊ ዲስኩሮች በፊልም፣ በቲያትር፣ በሙዚቃ፣ በሥነ-ፅሁፍና ፍልስፍና ምሁራን አማካይነት ይቀርባሉ፡፡ ታዋቂ አርቲስቶችም አድዋን የሚያጎሉ ኪነጥበባዊ ትርዒቶች እንደሚያቀርቡ ተገልጿል፡፡ የአድዋ ጀግኖች እና አርበኞች ታሪክ በአርአያነት ለትውልድ እንዲሻገር ይዘከራሉ ብሏል- የአላቲኖስ መግለጫ፡፡
የቀልድ - ጥግ
የፖለቲካ ቀልዶች
ትርጓሜ
“የፖለቲካ ቀልዶች ችግር አንዳንዴ እንደባለቤቶቻቸው ሊመረጡ መቻላቸው ነው”
* * *
የፖለቲከኛ ትርጉም
ፖለቲከኛ ማለት ጀልባዋን ራሱ ነቅንቆ፣ አናግቶ ሲያበቃ፤ ከዚያ እያንዳንዱን ሰው እባህሩ ላይ ማዕበል ተነስቷል ብሎ ለማሳመን የሚችል ሰው ነው!
* * *
የየምርጫ ጣቢያ ትርጉም
የምርጫ ጣቢያ ማለት ገንዘባችሁን የሚያጠፋላችሁን ሰው የምትመርጡበት ቦታ ነው!
* * *
አንድ የሩሲያ መሪ ወደ አሜሪካ መጥቶ የአሜሪካን ወታደሮች እንዲጎበኝ ይጋበዛል። በዚሁ መሠረት ወደ አሜሪካ ጣና ወታደሮቹን ይጐበኝ ጀመር፡፡
የአሜሪካው መሪ፡- “ወታደሮቼ ለእኔና ለአገሬ በጣም ታማኝ ናቸው” አለው ለሩሲያዊው፡፡
የሩሲያው መሪ፡- “እስቲ አንዱን ወታደር ጥራልኝና ጥያቄ ልጠይቀው” አለ
አንድ ወታደር ተጠራና መጣ፡፡
ይሄኔ ሩሲያዊው ወደ አሜሪካኑ ዞሮ፤
“እስቲ ታማኝነቱን ለማረጋገጥ ከገደል አፋፍ ውድቅ በለው” አለው፡፡
የአሜሪካው መሪም ለወታደሩ “በል ከዚህ ገደል ወደ መሬት ተወርወር” አለና አዘዘ፡፡
ወታደሩም፤ “አላደርገውም ጌታዬ” አለው
መሪው፤ “ለምን?”
ወታደሩ፤ “በእኔ ሥር የሚተዳደሩ ብዙ ቤተሰቦች አሉኝ ጌታዬ” አለ፡፡
ሩሲያዊው ሳቀ፡፡ “ይሄንን ነው ታማኝ ወታደር አለኝ የምትለው? ቆይ የእኔን አገር ወታደር አሳይሃለሁ፤ ጋብዤሃለሁ ናና እይ” አለው፡፡ በግብዣው መሠረት አሜሪካዊው መሪ የጉብኝት አፀፋውን ለመመለስ ከሦስት ቀን በኋላ ወደ ሞስኮ በረረ፡፡ የሩሲያን ወታደር ከባድ ሰልፍ ጐበኘ፡፡ ከዚያም ወደ ሩሲያዊው መሪ ዞሮ፤
“በል እስቲ አንተም አንድ ወታደር አስጠራና ስለታማኝነቱ እኔም ጥያቄ ልጠይቀው” አለው፡፡
አንድ ወታደር ተጠራ፡፡
የሩሲያው መሪ ለወታደሩ፤
“በል ከዚህ ገደል ተወርወር!” አለና አዘዘው፡፡
ወታደሩ ሳያቅማማ ሰላምታ ሰጥቶት ወደ ገደሉ ተወረወረ፡፡ የአሜሪካው መሪ በጣም ተገርሞ ወደ ገደሉ ጫም ሄዶ ቁልቁል ተመለከተ፡፡ እንዳጋጣሚ የተወረወረው ወታደር አንድ የዛፍ ቅርንጫፍ ላይ አርፎ ኖሮ መሬት ሲደርስ ለሞት አልተዳረገም። የአሜሪካው መሪ ወታደሩ እንዲመጣ ጠየቀ፡፡ ወታደሩን ተሸክመው አመጡለት፡-
“አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ፡፡ የእኔ ወታደር ወደ ገደል ተወርወር ብለው፤ የምረዳቸው ቤተሰቦች ስላሉኝ አላረገውም አለኝ፡፡ አንተ ግን ተወርወር ስትባል ተወረወርክ ምክንያትህ ምንድነው?”
ወታደሩም፡-“እኔም የምረዳቸው ቤተሰቦች ስላሉኝ ነው”
የአሜሪካው መሪ በመደነቅ ፡- “እንዴት?”
ወታደሩም፡- “ምቢ ብል እኔን ብቻ አይደለም የሚገሉኝ፡፡ ቤተሰቤንም ጭምር ነው!”
ማረሚያ ቤት ለአቶ አሥራት ጣሴ የሰጠው ምላሽ
ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ የካቲት 15 ቀን 2006 ዓ.ም በወጣው አዲስ አድማስ ዕትም ላይ የቀድሞው የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ዋና ፀሐፊ የነበሩትና በአዲሱ ካቢኔ ውስጥ ሳይካተቱ የማዕከላዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ አስራት ጣሴ፤ “የሙስና አዋጁ እንደገና ሊፈተሽና ሊታይ ይገባል” በሚል ርዕስ “በእስር በቆየሁባቸው 10 ቀናት ውስጥ ስለ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የታዘብኳቸው” በማለት ከከፍተኛ ሪፖርተር አለማየሁ አንበሴ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ተመልክተነዋል፡፡ ይሁን እንጅ አቶ አስራት ጣሴ ስለማረሚያ ቤቱ የተናገሩት ወደ አንድ ፅንፍ ያዘመመና የተቋሙን ገፅታ ሙሉ በሙሉ በሚያበላሽ መልኩ የቀረበ ሲሆን ማረሚያ ቤቱን በተመለከተ ትክክለኛው መረጃ ለህብረተሰቡ ይደርስ ዘንድ ምላሻችንን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
1ኛ/ በእስር ቤት ቆይተዎ ምን ታዘቡ? ተብለው ለተየጠቁት ጥያቄ
“በእውነት በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በቆየሁባቸው ስምንት ቀናት በዚች ሀገር የፍትህ ስርዓት እንዴት ፈታኝ እንደሆነ ተረድቻለሁ” ሲሉ መልስ ሰጥተዋል፡፡ (ገፅ 14)
በአሁን ሰዓት መንግስት ዜጎች የፍትህ ተደራሽነት ይኖራቸው ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ተግቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህም መሰረት ከቅርብ ዓመታት በፊትም የፍትህ አካላትን በማዋቀር “ፍትህ ለሁሉም ይዳረስ” በሚል መሪ ቃል፣ የፍትህ አካላት በከፍተኛ ሁኔታ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ከፍትህ አካላትም መካከል የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አንዱ ሲሆን መንግስት በሰጠው ተልዕኮ በፍርድ ቤት ውሳኔ ያገኙ የህግ ታራሚዎችንና የቀጠሮ እስረኞችን ተቀብሎ በመጠበቅ፣የታረመና የታነፀ ዜጋ ለማድረግ ፍትህ በማስጠበቅ የህግ ታራሚዎችም አውቀውም ሆነ ሳያውቁ በፈፀሙት ወንጀል ተፀፅተው ከእርምት በኋላ ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ አምራች ዜጋ ለመፍጠር እየሰራ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡ አቶ አስራት ጣሴ ግን በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ውስጥ ተአማኒነት ያለው አስተያየት ለመስጠት በቂ የእስር ጊዜያትን ሳያሳልፉና ሁኔታዎችን ሳያጤኑ በአጠቃላይ የማረሚያ ቤቱን ስም በሚያጎድፍ መልኩ “ፍትህ የለም” ብለው መናገራቸው አግባብነት የሌለውና ከእውነት የራቀ ነው፡፡ በመሰረቱ ማንኛውም ሰው ነፃ አስተያየት የመስጠት መብት ቢኖረውም እነዚህ አስተያየቶች ግን በማስረጃና በደጋፊ እውነታዎች መመስረት ሲገባቸው፣ ተጠያቂው ግን “በዚች አገር ፍትህ እንዴት ፈታኝ እንደሆነ ተረድቻለሁ” በሚል ያለምንም መገለጫ ከእውነት በራቀ መልኩ የተናገሩት ንግግር ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ስለዚህ አስተያየቱ ከአሉባልታ የማይሻገርና መንግስት ግልፅ የሆነ አሰራር እየተከተለ ባለበት ጊዜ የማረሚያ ቤቱን ፍትህ የማረጋገጥ ጉዞ በሚያሰናክል መልኩ የቀረበ በመሆኑ የሚስተካከል ቢሆን፡፡
2ኛ/ “የማረሚያ ቤት አያያዝ ባልተፃፈ ህግ የሚመራበት ሁኔታ እንዳለም ተረድቻለሁ” በማለት ትዝብታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ (ገፅ 14)
ነገር ግን የፌደራል ማረሚያ ቤቶች መቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 365/95 በተሰጠው ስልጣን እንዲሁም ደንብ ቁጥር 138/99 የታራሚዎች አያያዝ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በወጣው ደንብ መሰረት፣ በፍርድ ቤት ውሳኔ ያገኙ የህግ ታራሚዎችና የቀጠሮ እስረኞችን ተቀብሎ ከውስጥና ከውጭ ሊደርስ ከሚችል ጥቃት በመጠበቅ፣ መሰረታዊ ፍላጎታቸውን በማሟላትና አርሞና አንፆ አምራች ዜጋ የማድረግ ኃላፊነት አለበት ሲል የሚደነግግ ነው፡፡
ከዚህም በመነሳት ታራሚዎች የፍርድ ግዜያቸውን ጨርሰው እስከሚወጡ ድረስ ማረሚያ ቤት የራሱ የሆነ ህግና ደንብ አውጥቶ የህግ ታራሚዎችንም ሆነ የተቋሙ ሰራተኞችን ያስተዳድራል፡፡
ነገር ግን አቶ አስራት ጣሴ፣ በማረሚያ ቤት ውስጥ ምንም አይነት የተፃፈ ህግ እንደሌለና በመተዳደሪያ ደንብ ሳይመራ በዘፈቀደ ማረሚያ ቤቱ ደስ ባለው ህግ እንደሚተዳደር አድርገው መናገራቸው አግባብነት የሌለውና በእርግጥም ስለሚሰጡት አስተያየት ግልፅ እውቀት የሌላቸው መሆኑን ያሳያል፡፡ የህግ ታራሚዎችን ለማስተዳደር በወጣው ደንብ አንቀጽ 27 ላይ በግልፅ እንደሚደነግገው፣ አሁንም ያለው አሰራር እንደሚያሳየው፣ ማንኛውም የህግ ታራሚ ወደ ማረሚያ ቤት በሚገባበት ጊዜ የማረሚያ ቤቱ የስነስርአት ደንቦች በቃልና ግልፅ በሆነ ቦታ ሁሉም ታራሚ በሚመለከተው ሁኔታ የማስቀመጥና በዝርዝር የሚገለፅበት አሰራር አለ፡፡ አቶ አሥራት ግን በማረሚያ ቤቱ ጥበቃ የተደረገላቸውን መረጃ የማግኘት መብት በማጥላላት፣ምንም ዓይነት የተፃፈ ህግ የለም በሚል ያቀረቡት አስተያየት በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ያለውን አሰራር የማያመለክት ከመሆኑም በላይ የህግ ታራሚዎችም መመሪያው በሚፈቅደው የዝውውር፣ የአመክሮ፣ የቅበላና የድልደላ መመሪያዎች እየተዳደሩ የሚገኙ ሲሆን ይህም ጉዳይ በአፋጣኝ ታርሞ የሚቀርብ ቢሆን፣
3ኛ/ ህገ-መንግስቱ ላይ ሰው በሰውነቱ ሊያገኛቸው የሚገባ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ተብለው በዝርዝር ተቀምጠዋል፡፡
ሰብአዊ መብት ተብለው ከተቀመጡትም የመናገር፣ የመፃፍ፣ የማንበብና የመማር ወ.ዘ.ተ ይገኙበታል፡፡ ይሁን እንጂ አቶ አስራት ጣሴ የካቲት 15 ቀን 2006 ዓ.ም በወጣው አዲስ አድማስ እትም ላይ ለህግ ታራሚዎች የግል ጋዜጦችና መፅሔቶች ያለመግባታቸውን ሰብዓዊ መብትን እንደመጣስ ይቆጠራል ብለዋል፡፡ (ገፅ 14)
እርግጥም የማንበብን መብት መንፈግ ሰብዓዊ መብት እንደመጣስ የሚቆጠር ቢሆንም ማረሚያ ቤቶች ባለው ደንብና መመሪያ መሰረት ታራሚዎችን ሲያስተዳድሩ ስነ-ፅሁፎች፣ ጋዜጦችና መፅሄቶች እንዳይገቡ የሚከለክል ሳይሆን የእርምት ሂደቱ ላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳድርና በታራሚዎች መካከል ጤናማ ግንኙነት የሚያበላሽ መሆን ስለማይገባው፣ ወሲብ ቀስቃሽ የሆኑና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን የሚፃረሩ ይዘት ያላቸው መፅሄቶች፣ መፅሀፎችና ጋዜጦች እንዳይገቡ ይደረጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ወንጀል ሰርታችኋል ተብለው በፍርድ ቤት የተወሰነባቸው በእርምት ላይ የሚገኙ የህግ ታራሚዎች፣ ለእርምታቸው መሰናክልን ሊፈጥሩ ይችላሉ ተብለው የታመነባቸው ጋዜጦችና መፅሔቶች እንደየአስፈላጊነቱ የማይገቡ ቢሆንም በአጠቃላይ መፅሀፎች እንዳይገቡ አልተከለከለም፡፡
ይህ ደግሞ ሰብዓዊ መብትን መጣስ ሳይሆን ወንጀለኛ ተብሎ የተፈረደበት የህግ ታራሚን ተመልሶ ወደ ጥፋት እንዳይገባ ለማድረግ እንደሆነና የማንበብ መብቱን ለመንፈግ እንዳልሆነ አንባቢያን እንዲረዱ እንፈልጋለን፡፡ ምክንያቱም የማንበብ መብታቸው ቢነፈግ ኖሮ፣ የተለያዩ መፃህፍቶችና መማሪያ ፅሁፎች እንዲሁም ለማረም ማነፅ የሚያግዙ በራሪ ፅሁፎች ወደ ማረሚያ ቤት ባልገቡ ነበር፡፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ በማረሚያ ቤት ውስጥ ቤተ-መፃህፍት ማቋቋም ባላስፈለገ ነበር፡፡
በአጠቃላይ አስተያየት ሰጭው ተራ የፖለቲካ ተወዳጅነትን ለማትረፍና ህግ ታራሚዎች ላይ የፖለቲካ ቅስቀሳ ለማድረግ የተጠቀሙት መንገድ እንጂ በቂ መረጃና ደጋፊ መገለጫ ችግሮችን አንስተው ህብረተሰቡን ወይም ማረሚያ ቤቱንም ለለውጥ ትግሉ አጋዥ የሚሆን አስተያየት እንዳልሰጡ ተገንዝበናል፡፡ ግለሰቡ በእውቀት ላይ የተመሰረተ አስተያየት ባለመስጠታቸውና ዘለፋና አሉባልታ ላይ በማተኮራቸው ሊታረሙና ለሰጡትም አስተያየት አንባብያንን ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባቸዋል፡፡
የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር
አንድ ሌሊት በማንዴላ እልፍኝ
ወጪት ሰባሪው ኮለምበስና…
ግዞተኛው ኔግሮ የባቢሎን ሰማይ ጨለማ የዋጠው፤
አንድ የካቲት ማለዳ የያማካን ጦማር ሻጭ ወሬ ቢጠይቀው፤
በLe petit ፊት ገጽ ጠሀይቱ ወጥታለች
ከአድዋ ድሏ ጋር ከሚያንፀባርቀው፤
ከአለም ጥቁር ህዝቦች የግፍን እግር ብረት ላንዴው ካወለቀው፡፡
/ውዳሴ አድዋ - ያልታተመ/
ታህሳስ 6 2006 ዓ.ም - ራስ ሆቴል፡፡
ሁለተኛ ፎቅ ላይ በሚገኘውና በኔልሰን ማንዴላ ስም በተሰየመው ኮሪደር (Nelson Mandela Floor) የማስታወሻ ፎቶ እየተነሳን ነው፡፡ እርጋታ የሚስተዋልበት የአፍሪቃዊው የነፃነት ታጋይ ፎቶ፤ በእስራት ዘመናቸው የቁፋሮ የጉልበት ስራ ወቅት በተሰገሰጉ የአቧራ ብናኞች በሞጨሞጩ አይኖቻቸው በትዝብት የሚያስተውሉ ይመስላል፡፡ የምስሉ ትልቅነት ደግሞ ራሳቸው ግዘፍ ነስተው መሀላችን የተገኙ ያህል ይሰማል፡፡ ወደ ዋናው ሳሎን ገብተን ዋንጫችንን ስናነሳ፤ታናሽ ወንድማችን የምሽቱ ዲጄ ደረጄ የሚያጫውተው የሮበርት ኔስታ ማርሌይ ሬጌ ዜማ Africa Unite ይላል፤ If you know your history from where you came…
ከግማሽ ምዕተ አመት በፊት፤እኛ ዛሬ የወይን ብርጭቆ በምናጋጭበትና ታሪካዊ አሻራው በቋሚ ቅርስነት በክብር በተጠበቀው በዚህ ክፍል ውስጥ፤እርሳቸው፤ በሰፊው ልባቸው ውስጥ የታላቁ ራዕያቸውን ወይን እየጠመቁ፤ በያንዳንዱ ሌሊት ስለ አፍሪቃ መፃኢ ዕድል ምን ምን እያውጠነጠኑ አድረው ይሆን? ግድ ሆኖባቸው፤ ከሰላማዊው ትግል ወደ ትጥቁ ትግል ለማምራት፤ጭቆና ያንገፈገፈው የደቡብ አፍሪቃ ህዝብ በየታዛው ስር ከሚያወድስላቸው የሽምቅ ውጊያ መሪነታቸው የተሻለ የውትድርና ስልጠናቸውን አጠናቅቀው፤የእፎይታ አየር እየተነፈሱ ከሰነበቱበት ከዚህ ባለአራት ክፍል የእንግዳ ማረፊያቸው፤ምስራቃዊ የገነት ነፋስ ከሚነፍስባት የአቢሲኒያ ምድር ተሰናብተው በሄዱ ማግስት ነበር፤ 27 አመታትን በማቀቁባት የሮቢን ደሴት ጠባቧ እስር ቤት ውስጥ የተከረቸመባቸው፡፡ እርግጥ ነው፤ የወህኒውን የደንጊያ መቃብር በትዕግስትና ፅናት ፈንቅለው የነፃነትን ትንሳኤ እንደዋጁት ሁሉ፤ኖረው፤የአፍሪቃዊያን ህብረት እውን ሆኖ አይተው ማለፈቸው ሀዘናቸውን ይከላል፡፡
ማዲባ ወደ ኢትዮጵያ ባይመጡ ኖሮ፤የቀብር ስርአታቸው በተፈፀመባት እለት በዚህች ሌሊት፤ መንፈሳቸው ባረበበበት እልፍኛቸው ውስጥ ታድመን በትውስታ ባልዘከርናቸውም ነበር፡፡ ከመሳሳት የተወለደ ‹‹ምነው ተመልሰው ባልሄዱ ኖሮ ?›› የሚል ሞኝ ምኞት ሽው ማለቱ አይቀርም፡፡ መስቀሉን ይሸከሙ፡ ይቸነከሩ ዘንድ ግድ ነበራ፡፡ ተመልሰው እንደ መሄዳቸውም መምጣታቸውም ግድ ነበር፡፡ይህቺ ምድር፤ በዘመናት መሀል እረፍትን የሚሹ፣ መፍትኄን የናፈቁ፣ ነፃነትን የተጠሙ፣ ፍትህን የቃተቱ ሁሉ የክፉ ጊዜ መሸሸጊ ናትና፡፡ አምላከ አማልዕክቱ ዜዩስ በመብረቅ አክናፉ ከኦሊምፐስ ተራራ ከንፎ እፎይ የሚልባት፤ነቢዩ ሙሴ (ወደ አዜብ ምድር) የተመላለሰባት፤እየሱስ በድንግል እናቱ በእምዬ ማሪያም እቅፍ ሆኖ ከንጉሥ ሄሮድስ የሸሸባት፤የነቢዩ መሀመድ ሰሎላ ወአለ ወሰለም ተከታዮች አርሂቡ ተብለው በሰላም ያረፉባት…
ቦብ ማርሌይ If you know your history from where you came…‹‹የታሪክህን ዳና ተከትለህ የእትብት ቀዬህን ብታውቅ›› ሲል ያቀነቀነው፤ በመግቢያችን ላይ ባነበብነው ዘለግ ካለ ግጥም የተቀነጨቡ ስንኞች መሀል፤በጨለማው የባቢሎን ሰማይ ስር ሲንከላወሱ ለኖሩት አፍሪቃዊያን ወንድሞቻችን ነበር፡፡ እኒያ በግፍ እግር ብረት የተጠፈነጉ መከረኞች፤ለዚያ አይነት የዘቀጠ ህይወት የዳረጋቸውን፣ ስብዕናቸውን ያዋረደውን የቅኝ ግዛትና የዘር መድልዎ ካቴና ለመበጣጠስ፤ የኔልሰን ማንዴላንና መስል ጸረ ዘረኝነትን አቋም የሚያራምዱ አብዮተኞችን መፈጠር ግድ ያለበትን የታሪክ ድርሳን እየመዘዝኩ ስቆዝም፤ ከአምስት መቶ አመታት በፊት የተከሰተችውን፤ ለረጅሙ የጥቁር ህዝቦች ጭቆናና የጨለማ ዘመን መነሾዋን፤ ያቺን ክፉ ምሽት አውጠነጥን ነበር፡፡ እነሆ…
1494 እ.ኤ.አ - ያማካ ደሴት፡፡
በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ውድቀት መሰስ ያለው፤በኤደን ገነት አፀድ በየዋህነት ይኖሩ የነበሩትን አዳምና ሄዋንን፤ በእባብ የተመሰለው ሌባው፣ አታላዩ፣ ውሸታሙ ሰይጣን ዲያቢሎስ፤ በሀሰት አቀራረብ ወዳጅ መስሎ በረቀቀ ሴራ ሲያጭበረብራቸውና እነርሱም በምስኪንነት ተታልለው አጥፊ ሀሳቡን በማመናቸው ነበር፡፡
ያማካ Xyamaca የአሜሪካ ኢንዲያን ጎሳዎቹ አራዋክስ በሰላም የሚኖሩባት ደሴት ነበረች፤ኮለምበስና ተከታዮቹ ድንበራቸውን ጥሰው እስከመጡባቸው እስከዚያች ምሽት ድረስ፡፡ ምናልባትም ያ ጊዜ በአውሮጳዊያኑና አራዋክሱ መካከል የተደረገ በታሪክ የመጀመሪያው ግንኙነት ነው፡፡ አሳሹ ኮለምበስ በመርከቡ የሰነቀው የጉዞ ማዕድ ተሟጥጦ፤ የሚቀምሱት ምናምኒት አልነበራቸውም፡፡ ተከታዮቹ ጠኔ ሆድ ባባሰው አመፅ ውስጥ እንደ አውሬ በተፋጠጡበት መአልት፤ዕድል እየመራ ከዚያች የተዋበች ለምለም ደሴት አደረሳቸው፡፡ ሀራዋኮቹ፤ ከተፈጠሩ አይተውት በማያውቁት ጋጠወጥ አቀራረባቸው ኮለምበስና ተከታዮቹን ተጠይፈዋቸው፤ እፍኝ ታህልም ላይሰፍሩላቸው ወስነው ፊት ነሷቸው፡፡ ያኔ ነው እንግዲህ ክርስቶፈር ኮለምበስ፤ የረቀቀ የሴራ መረቡን በላያቸው የጣለውና ኢንዲያኖቹ ተገድደው የሚፈልገውን እንዲያደርጉ ያጠመዳቸው፡፡
ኮለምበስ፤ በዚያ ምሽት የጨረቃ ግርዶሽ እንደሚኖር አስታወሰ፡፡ ለምስኪን ሀራዋኮቹም፤ አሁኑኑ ምግብና መጠጥ ካላቀረቡለት፤ አምላኩ ተቆጥቶ የጨረቃዋን ብርሃን አንደሚያጠፋባቸው አስጠነቀቃቸው፡፡ ሀራዋኮቹ፤ እንኳን የእንግዳው ሰው ነጭነት ተጨምሮበት ለአጉል አምልኮ የሚብረከረኩ ቢሆኑም በእምቢተኝነታቸው ፀኑ፡፡ ምሽቱ እየገፋ ሲመጣ ግን እውነትም ሰማዩ ደበዘዘ፡፡ ጨለመ፡፡ በሀራዋኮቹ ዘንድ ጥልቅ ፍርሀት ነገሰ፡፡ ወዲያውም በጭንቀት እየተደነባበሩ፤ በትልልቅ የሸክላ ሰታቴ ድስቶችና ዋዲያቶች ሙሉ ምግብና መጠጦችን በደሴቲቱ ዙሪያ ከሚበቅሉ አትክልቶች፣ ፍራፍሬዎች እና የተጠበሱ የአሳማ ስጋና አሶች ጋ ጢም አድርገው አስታቀፏቸው፡፡ የሰማይ ላይ ግርዶሹ እንዳመጣጡ ጨረቃዋን አልፎ ሲሄድ፤መርከቡን በምግብና መጠጥ የጠቀጠቀው ኮለምበስም፤ በስጋት ተወጥረው ኋላ ኋላው ሱክ ሱክ እያሉ የሚሸኙትን በድንጋጤ የተንጰረጰሩ ምስኪን ሀራዋኮች በሰይጣናዊ ፈገግታው እያማተረ ወደፊቱ ቀዘፈ፡፡
ኮለምበስ ከመጣ ጥቂት አመታት በኋላ ታዲያ፤ ስፔንያርዶቹ፤ በሁለት ጎኑ የተሞረደ ስለታም ገጀራቸውን እያፋጩና እያፏጩ መጡአ! ወደ ድንግሏ ያማካ፡፡
ሀራዋኮቹ፤ደሴታቸውን ያማካ Xyamaca ብለው የጠሯት፤ለውሃማና የልምላሜ ምድርነቷ ውዳሴ ነበር፡፡ Xyamaca – the land of wood and water. አመቱን ሙሉ ውሃ ያጋቱ ፏፏቴዎች፣ ምንጮችና የማይደርቁ ወንዞች፤ የጥጥ ጫካዎች፣ በማሆጋኒ፣ አዋንጎ፣ ማሮኢና ካስያ ዛፎች የተቸመቸሙ ጥቅጥቅ ደኖች፡፡
ስፔንያርዶች፤ ጃማይካን Xyamaca ወርረው በቅኝ ግዛት ስር ካዋሉ በኋላ ቀስስስስ እያሉ የሀራዋኮቹን ዝርያ አርደው ጨረሷቸው፡፡ ከዚያስ? ከዚያማ በግዙፍ መርከቦች እያጨቁ በሚዘረግፏቸው ጥቁሮች ደሴቲቱን አጥለቀለቋታ፡፡ ሰዎቹ ተማርከው የሚወሰዱት ከእኛዋ አኅጉር ከምዕራብ አፍሪካ ሲሆን፤ እዚያ ከደረሱ በኋላም በሸንኮራ አገዳ ማሳ ስራ ተጠምደው በባርነት የሚያገለግሉ የዕድሜ ልክ ግዞተኞች ይሆናሉ፡፡ ባሮቹ የማያከናውኑት ተግባር አልነበረም፡፡ ሴቶቹ ለጌቶቻቸውና ለባሪያ አለቆቹ የወሲብ ጥማት መርኪያነትም ይውላሉ፡፡ ቢሆንም ግን፤ የሴቷ ሆነ የወንዱ፣ የህፃናቱም፣ የወጣቱም፣ ሰየሽማግሌውም የአሮጊቱም፣ ብቻ የመላው አፍሪቃዊያን ባሮች የሰውነት ክብራቸው መጠን መገለጫው ከእንስሳነት መሳ የሆነ፤ በሚተነፍሱ ግዑዛን ፤በሚናገሩ እቃዎች ወይም በተንቀሳቃሽ ፍጡራንነት ደረጃ የተቀነበበ ሆኖ ቀረ፡፡
ስፔንያርዶች እስከ 1665 ድረስ ገዟት፡፡ እንግሊዛዊያን በተራቸው መጡ፡፡ ስፔንያርዶቹንና ከእነርሱ ጋር ሆነው ለመዋጋት የሞከሩትን ባሮች፤ አፍንጫው ድረስ በታጠቀው የጦር ኃይላቸው ብርቱ ክንድ እየደቆሱ አሽመደመዷቸው፡፡ ወደ ኩባም አስፈረጠጧቸው፡፡ ደሴቷ በእንግሊዛዊያኑ መዳፍ ውስጥ ገባች፡፡ የታላቋ ብሪታኒያ ንግስት ኤልሳቤጥ ቀዳማዊት፤‹‹ዌስት ኢንዲያ የባሪያ ንግድ ኩባንያ››ዋን በይፋ አቋቋመች፡፡ ከዚያማ ምኑ ይነገራል? ከአፍሪቃ ምድር ተግበስብሰው ታድነው በትልልቅ መርከቦች እየተጠቀጠቁ ወደ ብሪትሽ ዌስት ኢንዲስ የሚጋዙ ብዛታቸው ለቁጥር የሚታክት ባሮች እንደማይነጥፍ ዥረት እየተግተለተሉ በመንጋ ሲነዱ ‹‹ይብቃ!›› የሚል ጠፍቶ፤ እልፍ አዕላፍ እስኪደርሱ አራት መቶ አመታት ነጎዱ፡፡
አፍሪቃዊያን ወንድሞቻችን ለባርነት በገፍ ሲጋዙ፤ በገዛ ምድራቸው ላይ በቁጥጥር ስር ከሚውሉበት መንገድ አንዱን፣ የቀንደኛውንና ምስጉን የባሪያ አዳኝ ‹‹ዠግናውን›› ስልት እንይ…ሀውኪን!
የሀውኪን የባሪያ አደን ከሌሎች የተለየና ላቅ ያለ ነው ተብሎ የሚደነቅለት፤ቆፍጣና፣ ኮስታራ፣ ጭካኔ የተሞላበትና ‹‹በባሪያ ምርቱ›› የተትረፈረፈ ውጤት ማስገኘቱ ነበር፡፡ በድንገት ባንድ ሰላማዊ የአፍሪካ መንደር ላይ ታጣቂዎቹን አሰማርቶ ጥቁሮቹን ያስከብባቸዋል፡፡ በዚህ ከበባ ቀለበት ውስጥ የገቡ ሁሉ በሰልፍ እርስ በእርስ ተያይዘው ወደ መርከቡ እንዲደርሱ በተዘጋጀላቸው በእጅ፣ እግር ወይም ባንገት የሚጠልቅ ብረት ሰንሰለት ተቆላልፎ መነዳት ብቻ ነው፡፡ ወደ መርከብ ከመግባትም ሆነ በመርከቡ ውስጥ የምድር ቤትና ተደራራቢ ፎቆች ወለል ላይ ተፋፍገው ከሚጫኑበት ውልፍት ለማለት የሞከረ ደመ ከልብ ይሆናል፡፡ በቃ! በዚሁም አሰቃቂ የጭካኔ ተግባሩ ሀውኪን በከፍተኛ ክብርና ሙገሳ ሲምነሸነሽ ኖሯል፡፡ የሰርነትን ማዕረግ ጨምሮ፡፡ Sir John Hawkins.
በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪቃዊያን ወንድሞቻችንን እትብታቸው ከተቀበረበት ምድራቸው ወደ ጃማይካ ሲያጓጉዙ ከኖሩት መርከቦች ሁለቱ እጅግ ግዙፎቹ ኤስ ኤስ ዞንግ እና ኤስ ኤስ ይባላሉ፡፡ በተለይ ሀገር የሚያህል ስፋት ባለው ሆዱ አፍሪቃዊያኑን የቂጣቸው ጫፍ ብቻ ወለል እንዲስም ተደርጎ፣ በአየር ላይ የማንጠላጠል ያህል እንደ ጡብ ሰካክቶ አጭቆ በመውሰድ ጉልህ ድርሻ የነበረው ኤስ ኤስ በጎኑ ላይ በትልቁ የተፃፈ ጽሁፍ ነበረው Jesus of Lubeck የሚል፡፡ የላቲን ቋንቋው ትርጉም ‹‹እየሱስ እስኪመጣ›› ማለት ነው፡፡ ታዲያ፤ለዘመናት ቢጠብቁ… ቢጠብቁ… እየሱስ ከየት ይምጣ? ወንጌሉ ደሞ ‹‹በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻ አወጣን›› ይላል-ገላትያ 5-1፡፡ ስለዬህ ነበር ባሮች ወንድሞቻችን የራሳቸውን ነጻ አውጪ መሲህ ከወደ ምስራቅ ፀሀይ መውጫ ያስተውሉ ዘንድ ግድ የሆነባቸው፡፡ ራስ ተፈሪ መኮንን፤ በጥቅምት ወር 1923 ዓ.ም፡፡
የእንግሊዙን የዌልስ ልዑል ጨምሮ የአውሮጳ ንጉሣዊያን ቤተሰቦች በተገኙበት፤በአዲስ አበባ በሞአ አንበሳ ዘ እምነገደ ይሁዳ ስያሜ የንጉሰ ነገስትነት ዘውድ ደፉ፡፡ His Imperial Majesty Emperor Haile Sellassie I King of Kings, Lords of Lords, Conquering Lion of the Tribe of Judah, Lebna Denghel, Keeper of the Faith of the Dynasty of Judah, Keeper of the Faith of the Dynasty of David, and The Elect of God. ይህን ለንግስናቸው የተሰጠ ስያሜ ከመጽሐፍ ቅዱስ የትንቢት ድርሳናት ሀረጋት ጋር እያመሳከሩና እያስተነተኑ በንጉሱ መሲህነት አምነው ተጠመቁ፡፡ በእግዚአብሄር የተቀባ፤የዳዊት ዙፋን ወራሽ፤የይሁዳ አንበሳ…
ከዚህ ክስተት መቶ አመታት አስቀድሞ፤ በነሀሴ 1 1826 ዓ.ም፤የእንግሊዝ ንግስት ቪክቶሪያ በመላው የእንግሊዝ ግዛት ያሉ ባሮችን የይስሙላ የነፃነት አዋጅ አናፍሳ፤ለካሪቢያን ደሴቶች ጥቁር አፍሪቃዊያን ካሳ የሚሆን 20 ሚሊዮን ፓውንድ ብትበጅትም፤አንድም ባሪያ ሽራፊ ድምቡሎ ሳይደርሰው የባሮቹ አለቆች ገንዘቡን ተቀራመቱት፡፡
ከዚያ በኋላ 60 አመታት አልፈው ነው፤በሞአ አንበሳ ዘ እምነገደ ይሁዳ ንጉሰ ነገስት ዘ ኢትዮጵያ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ መሪነት፤ ክርስቲያኑም እስላሙም፤ አራሹም ተኳሹም፤ ወንዱም ሴቱም፤ወጣቱ አዛውንቱ፤ ሀገር ከዳር ዳር ነቅሎ በዘመተበት ጦርነት ኢትዮጵያ የተቀዳጀችው የጥቁር በነጭ ላይ የድል ብስራት ዜና ከአፅናፍ አፅናፍ ያስተጋባው፡፡ በፈረንሳይኛ ቋንቋ የሚታተመው Le petit ጋዜጣ የአድዋን ድል ከእቴጌ ጣይቱ ደርባባ ምስል ጋ በፊት ገጹ ይዞ ሲወጣ፤ በባርነት ቀንበር ስር በነበሩ በመላው አለም ጥቁር ህዝቦች ልብ ውስጥ ተስፋ ናኘ፡፡ የአርነት ጎህ ቀደደ፡፡ ጨለማው በራ፡፡ ጥቁር ህዝብ ሁሉ ‹‹ለካ ይቻላል!›› አለ፡፡የጨካኝ ነጭ ጌቶቹን ጉሮሮ ማነቅ ጀመረ፡፡ እነሆ ከኢትዮጵያ አብራክ ፍትህ ፈለቀ፡፡
ከአድዋ ድል 40 አመታት ቆይቶ፤ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ፤ በብፁዕነታቸው አቡነ ባሲሊዮስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ፓትርያርክ ቅዱስ ቡራኬ እንደነገሱት ሁሉ፤ ከ5 አመታት በኋላ ደግሞ፤ ጣሊያንን ከመልቀቃቸው በፊት ለጥፋት ዘመቻቸው ስኬት በሮማ ካቶሊክ የእምነት አባቶች እኩይ ቡራኬ የተሸኙት፤በአምባገነኑ ቤኒቶ ሙሶሎኒ ትዕዛዝ፤ በማርሻል ባዶሊዮ የሚመሩት የጣሊያን ወታደሮች ኢትዮጵያን ወረሩ፡፡ ይህም በምድር ዙሪያ ያሉ ጥቁሮችን ቁጣ ቀሰቀሰ፡፡ ‹‹የተስፋ ምድራችንን አትንኩ!››…ንጉሠ ነገስቱ ለመንግስታቱ ጉባኤ ያደረጉትን ‹‹በዛሬው ጊዜ ታላላቅ ሀገሮች አንኳን የራሳቸውን እድል ለመወሰን አይችሉም፡፡ የሁላችንም እድል ያው አንድ ነው፤ወይ መጥፋት ወይ መዳን፡፡ እድል ስናገኝ ጊዜ ሳያልፍ የሚቻለንን ሁሉ እናድርግ። ደስ የማይል እርምጃ ከመውሰድ እንዳን። …የመጀመሪያውን እሳት የሚለኩሰው ማን እንደሆን ይታወቃልን?...›› ንግግራቸውን ተከትሎ፤ በተለይ አውሮጳዊያኑን እርስ በርስ ያስተላለቀው ሁለተኛው የአለም ጦርነት መጣና አረፈዋ፡፡ ያን ጊዜ፤ A Nation without the knowledge of its past history is like a tree without its root. ‹‹ያለፈ ታሪኩን የማያውቅ ህዝብ፤ ሥር እንደሌለው ዛፍ ነው›› በሚል መርሁ የሚታወቀው የህዝቦች ንቅናቄ መሪው ማርከስ ጋርቬይ ተከታዮች Garveyites ‹‹ይኸዋ!ትንቢቱ ደረሰ! መሲሁን አልሰማ ብለው ጉድ ሆኑ!›› እያሉ፤ የኢትዮጵያዊውን ንጉስ ወንጌል አስፋፉ፡፡That H.I.M Emperor Haile Sellassie I of Ethiopia is the returned Messiah, the God Head, the Ancient of Days. የንጉሱ የጃማይካ ጉብኝትና ድንገቴ ግጥምጥሞሾች ሁሉ ደግሞ ጉዳዩን ሰማይ አስነካው፡፡ በራሳቸው በንጉሰ ነገስቱ ‹‹እኛ አምላክ አይደለንም!›› ብለው እንዲሰብኩ የተላኩ ሀበሻ ካህን በራስ ተፈሪያኑ ተሰብከው፣ አምነው፣ ተጠምቀው እስኪቀሩ፡፡ እንደእምነታችሁ ይሁንላችሁ ተብለው መጥተው ለኢትዮጵያ (ሻሸመኔ) ምድር እንደበቁትም፤ ጋርቬይ ይዞት የተነሳው One God,One aim and One Destiny መሪ ቃል፤ መላው ጥቁር ህዝብ ነገውንና ዘላለሙንም በተስፋይቱ ምድር በኢትዮጵያ ላይ እንዲያንተርስ አደረገው፡፡ ዝማሬዎች ሁሉ የኢትዮጵያን ምድር መቀኘት ጀመሩ፡፡ የኖህን ቃል ኪዳን አርማ የቀስተ ደመና ቀለማት ሰንደቅ የሚያውለበልቡ ስንኞች ተዥጎደጎዱ…
Ethiopia, the land of our fathers;
The land where all Gods love to be,
As swift bees to hive suddenly gathers;
So thy children come rushing to thee.
With red, yellow , and green floating ‘oer us,
And our emperor to shield us from wrong.
With our God and our future before us;
We hail thee with shouts and with songs!
ዶሮ ሊጮህ ገደማ - ማዲባ እልፍኝ፤ አዲስ አበባ።
በስማቸው በተሰየመው የእንግዳ ማረፊያ ክፍል በር ላይ ከቁጥር 206 ስር Nelson Mandela Room የሚል ጽሁፍና የጎልማሳነታቸው ፎቶ ተለጥፏል። በፎቶው ላይ የነፃነት ታጋዩን የሰውነት አቋም ያየ ሰው፤ ለቦክስ ስፖርት የነበራቸውን ፍቅር ማስታወሱ አይቀርም፡፡ በሙሉ ሱፍ ሽክ ብለዋል፡፡ በዚህ እድሜያቸው ነበር ወደ ኢትዮጵያ የመጡት። እርሳቸውም እንደአብዛኛው የአለም ጥቁር ህዝቦች ሁሉ ስለ ኢትዮጵያ የነበራቸው ላቅ ያለ ክብር በመለኮታዊ እምነት የታሸ እንደነበር በእድሜያቸው አመሻሽ ላይ በከተቡት Long Walk To Freedom መጽሀፋቸው ገጾች ውስጥ ሰፍሮ ይገኛል፡፡
ማዲባ፤በነጮች ጫማ ስር ከመረገጥ ነፃ የመውጣትን አላማ አንግበው ወደ ሀገራችን በመጡ ጊዜ የነበራቸውን ትዝታ የተረኩት፤‹‹ጥቁር ሰው ክብር ያገኘባትን ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ ማየታቸውን›› በመጥቀስ ነበር፡፡ ተሳፍረው የመጡበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አይሮፕላን አብራሪ ካፒቴን ጥቁር በመሆኑ በእጅጉ ስለመገረማቸውና መልሰው ‹‹ግን ለምንድር ነው የሚገርመኝ?›› ስለማለታቸው፡፡ ለዚህ መሰል ደካማ አስተሳሰብ ምርኮኛ ያደረጋቸውን አፓርታይድን በውስጣቸው መኮነናቸውን፡፡ ውለው ሲያድሩ ደግሞ ጥቁር ጄኔራሎችን አዩና አፋቸውን ያዙ፡፡ ‹‹እኛም አንድ ቀን እንዲህ እንሆናለን›› ሲሉም ተመኙ፡፡ ኢትዮጵያን በቀደምት መጠሪያዋ ‹‹አቢሲኒያ›› ብለው እየጠሩ፤ከንግስት ሳባና ጠቢቡ ሰለሞን በልጃቸው ቀዳማዊ ምኒልክ በኩል የሚመዘዘውን ሰለሞናዊ ስርወ መንግስት ወራሽ ንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴን ሲገናኙ፤ ‹‹እነሆ ከይሁዳው አንበሳ ጋር ተገናኘሁ!›› ሲሉ ተአምራትነቱን ይመሰክራሉ። በዕድሜ ዘመናቸው በየትኛውም አለም ካደረጉት ጉብኝት ሁሉ የኢትዮጵያን ምድር መርገጣቸውን እጅግ ላቅ ያለ ስፍራ ይሰጡታል፡፡ ‹‹ምድሪቱ፤ ያለማቋረጥ ወረራ የተፈፀመባትና ግን ለአንዲትም ጊዜ እንኳ በቅኝ ግዛት ስር ያልተንበረከከች፤የነፃነት ቀንዲል፣ የአፍሪቃዊያን እምብርት፣ ሉዐላዊት ሀገር ናት፡፡››ይላሉ፡፡ ምስክርነታቸው በአዛውንትነት ዕድሜ የተሰጠ መሆኑ የሚያመለክተውም ፤ንፅፅሩ፤ኃያላን ሀገራቱን ጨምሮ በአለም ዙሪያ በመቶ የሚቆጠሩ ዶክትሬት ዲግሪዎችንና ሽልማት መአት ያንበሻበሿሰቸውንም ሁሉ ሚዛን ደፍቶባቸው መሆኑን ነው፡፡ ጉዳዩ የነፃነት ጥያቄ ነዋ!
ያኔ ጥቁር አፍሪቃዊያን እንደ ከብት ሲነዱ ለ400 አመታት አላየንም አልሰማንም ብለው፤እንደ መለኮታዊ ቁጣ እነርሱው በጫሩት እሳት ውርጅብኝ ሀምሳ ሚሊዮን ዜጎቻቸውን ባረገፈው የሁለተኛው አለም (የእርስ በርስ) ጦርነታቸው ብድራታቸውን ዋጥ ያደረጓትን ሀገራትንም ያጠይቃል የማንዴላ ሩህ፡፡ ከ500 አመታት በፊት የአሳሽነት እቅዱ እንዲሳካ ምርኩዝ (ስፖንሰር) ለሆኑት ለስፔኑ ንጉስና ለሚስቱ ለንግስት ሳቤላ ሀራዋኮችን በገፀ በረከትነት አሳልፎ ከሰጠው፤ ከበላበትን ወጪት ሰባሪው ኮለምበስ የክህደት ተግባሩና መዘዙ ተምረው ተፀፅተው ይሆን እውነት? እላለሁ፤ ተሲያት ላይ እርሳቸው በተወለዱባት በትንሷ ኩኑ መንደራቸው፣ አስከሬናቸው በሰላም በሚያርፍ ጊዜ፤ ለቴአትር ትወና ቆሜበት በነበረው የቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ (የኢትዮጵያ ብሔራዊ) ቴአትር ቤት መድረክ ላይ ካከናወንነው የቀለበት ስነ ስርአት መልስ፤የጫጉላ ምሽታችንን ለማሳለፍ በተከራየነው፤ማንዴላ ልክ ከ55 አመታት በፊት በዚሁ በታህሳስ ወር 1961 ዓ.ም በእንግድነት መጥተው ባረፉበት በአፍሪቃ መዲና፤በሉአላዊቷ፤የነጻነት አርማዋ፤የእምዬ ኢትዮጵያ ምድር ዋና ከተማ፤መሀል አዲስ አበባ ፤ራስ ሆቴል፤ ሁለተኛ (ማንዴላ) ፎቅ፤ መኝታ ክፍል ቁጥር 206 የማንዴላ እልፍኝ ውስጥ፡፡ ወዳጆቼና ቤተሰቦቼ ዘና ባለ ስሜት ውስጥ ናቸው፡፡ የምሽቱ የዜማ ዘዋሪያችን፤ ዶሮ ሳይጮህ፤ ድምፃዊው ስቲቪ ወንደር ለታታ ማንዴላ ያበረከተላቸውን I just called to say I love you ዜማ እንዲጋብዘን ልጠይቀው አሰብኩ፡፡ ላሁኑ ግን የእልፍኙን ድባብ ሬጌ ሙዚቃ ሞልቶታል…Babylon is falling , Ethiopia she is calling ይላል፡፡ ሙሽራዬና የበኩር ልጃችን በግራና ቀኝ ጎኔ በኩል ተደግፈውኛል፡፡ በዛሬው እለት በአ.አ ስብሰባ ማዕከል በተመረቀውና ሶስታችንም በትረካ በተካፈልንበት የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ትርጉም ፊልም ውስጥ ስለ ኃጢዐት ምግባር እንዲህ የሚል ዐረፍተ ነገር አለ…‹‹ሽብር ሲነዛ ክፋት ሲያውጅ ጊዜ የሰጠው ሹመኛ፤ሰለባ ይሆናል ቀሪው የፍርሀቱ ምርኮኛ!››… ወደ ባቢሎናዊያኑ ሙግት ላንዴ መለስ አልኩ…
አዎን! በፈጠረችው የባቢሎን ምድር የባሪያ ንግድን ያለ እረፍት ስታጧጡፍ የኖረችው እንግሊዝ፤ ዛሬ በከተማዋ አደባባይ ለኔልሰን ማንዴላ ሀውልት ያቆመችው እውን የነፃነት ታጋዩን ህልምና ራዕይ የምትጋራ ሆና ነውን? በነፃነት ታጋዩ ህልፈት ሰሞን ማዲባን በክብር ተሰናብቶ ለመሸኘት ከአለም ዙሪያ የተሰባሰቡት የየሀገራቱ ክቡራን መሪዎች ሁሉስ? እንቅልፍ አጥተው ውብ ቃላቶችን አርቅቀው ሆድ የሚያባቡ ንግግሮችን የቀሸሩት፤ የየሀገራቸውን ሰንደቅ ዝቅ አድርገው ያውለበለቡት፤ ብሔራዊ የሀዘን መግለጫዎችን ያወጁ፤ለሰውየው ራዕይ ከሆነ እንዲያ የባጁ፤ መልካም…ገብቶናል ካሉ…ዛዲያ ዛሬም ድረስ እየታደኑ ወደ ማጎሪያ ጣቢያ የሚዶሉትን ጂፕሲዎች ለምን ነፃ አያደርጓቸውም? በመላው አለም በተለይም በአውሮጳ ምድር የተንሰራፋው በጥቁር ህዝቦች ላይ ያነጣጠረ የአድልዎና ማግለል Xenophobia ምግባራቸውስ? በምድሪቱ ዙሪያ ዳግም እየተቆሰቆሰ ያለው የፀረ - ጽዮናዊነት ጉዳይስ?....ወዘተ፤ ሌሎችም…!?አባባ ጃንሆይም፤በሊግ ኦፍ ኔሽን መድረክ ቆመው ለመንግስታቱ ጉባኤ መሪዎችና ታዳሚዎች ይህንኑ ነበር ያሉት...
‹‹...በአንድ ሀገር ውስጥ አንደኛና ሁለተኛ ዜጋ የሚባለው ነገር እስካልተወገደ፤ሁላችንም የምንደክምለት የአለም ሰላም ጉዳይ ዋጋ ቢስና ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር ያሰጋናል . . .፡፡››
ኔልስን ማንዴላ የታገሉት ለጥቁር ወይም ለነጭ የበላይነት አይደለም፡፡ በፍፁም! ለመላው የሰው ዘር እኩልነት እንጂ!ይኼ የዘር ነቀርሳ ሰንኮፉ የሚነቀልበት ዘላቂ መፍትኄ እስካልተገኘ ድረስ ፤ በማንኛውም ጊዜ፤ በየትኛውም ስፍራ ፤ የሰው ልጆች ሁሉ እኩልነትና ሰብአዊ መብት እንዲከበር ትግሉ ይቀጥላል! ሀኩና ማታታ!
የገንዘብ ቀለማት!
“ገንዘብ ንጉሥም ሎሌም ያደርግሃል”
ሲጀመር
የልጆች የአስተሳሰብ ነፃነት መቼም ያስቀናል። እኛ ትልልቆቹ በማህበራዊ፣ ሀይማኖታዊ፣ ዘልማዳዊ ፣ መንግስታዊ ፣ ምናምናዊ--- ወጥመዶች አስተሳሰባችንን ከማሰራችን በፊት ያለውን ንፅህና ማለቴ ነው፡፡ ይህንኑ ባርነታችንን እንደሚረባ ውርስ፣ ሲለን በሽንገላ ሳይለን በቁጣ፣ አሳልፈን ነፃነታቸውን እስክንነጥቃቸው ያለውን፡፡ የነፃነታቸው መገለጫ ደሞ ያልተገደበው ንግግራቸው ይመስለኛል፡፡ ድንገት ሲያወርዱት፣ ለእኛ ለትልልቆቹ፣ በባርነት ላለነው የአይምሮ ፈተናም የሃሳብ ፍንዳታም ነው፡፡
አንድ ማታ እቤት እራት እየበላን ነበር። ናታን፣ እድሜ 9፣ በትንንሽ እጆቹ የእንጀራ ቁርጥራጮች እያንገላታ “ሀብታም ብንሆን ደስ ይለኝ ነበር” አለ። ለተወሰኑ ደቂቃዎች ፀጥታ ሆነ፡፡ ሃሳብ ፈነዳ። በቀላሉ “እኔም ደስ ይለኝ ነበር” ብሎ ለመዝጋት የወላጅነት ህሊና ይፈቅድ እንደሆን እንጃ፡፡ በተቃራኒው “ገንዘብ አጋንንታዊ ነው፡፡ ባለህ መደሰት አለብህ ምናምን” ብሎም ለማለፍ፣ ለወላጅ ግልግል ቢመስልም ፣ ህፃኑ ይቀበለዋል ወይ ብሎ ማሰብ የአባት ነው፡፡ ከእኛው ጀምሮ፣ በትምህርት ቤትም በመዝናኛም በመፅሃፍትም፣ ሁሉ ቦታ ሰበካው ሁሉ ገንዘብና ሀብት ነው፡፡ ለወላጅ “ገንዘብ የለኝም” ፣ “ገንዘብ ሳገኝ---” እና የመሳሰሉት ለሕፃናት የሚሰጡ የዘወትር መልሶች ናቸው፡፡ እናማ “ባለፈው ሎተሪ ከደረሰን ዱባይ እንሄዳለን ተብያለሁ” ብሎ ቀን ሲቆጥር የነበረ ህፃን፣ ሀብታም መሆንን ቢመኝ ምኑ ይገርማል? እኔ ግን መጠየቄ አልቀረም -
“ምን ማለት ነው ሀብታም መሆን?”
“ብዙ ብር ማግኘት”
“ምን ለማድረግ?”
“ቲቪ ለመግዛት! እነ እንትና እኮ ሀብታም ናቸው። እሱ ክፍል ቲቪ አለው፡፡ እኔም ቲቪ እፈልጋለሁ” አለኝ ናታን፣ የአንዱን ጓደኛውን ስም እየጠራ፡፡
የተንተባተበ ነገር መልሼለት ፣ ነው ሰብኬው፣ ባለህ ብትደሰትስ ምናምን ብዬው አለፍኩት። “ሴክስ” ምንድነው ብሎ እንዳፋጠጠኝ ቀን፣ የራሴው ቃላት ከጉሮሮዬ ተቀርቅረውብኝ፣ የፈለኩትን ሳይሆን የተባልኩትን አሳልፌ ሰጥቼው፣ የወሬውን ቻናል አስቀይሬ አረሳሳሁት፡፡
ይቆጠቁጠኝ ገባና ፣ ማሰቤን ቀጠልኩ፡፡ እንዲህ ብለውስ ኖሮ አልኩኝ…..
….የገንዘብ ሀይል ምትሃታዊ እንጂ ጋኔላዊ አይደለም። ገንዘብ በራሱ ያሰክራል እንጂ ነፍስ አያረክስም፡፡ ገንዘብ ነፃነትንም ባርነትም አጣምሮ የያዘ ይመስለኛል፡፡ ይህን ሀይል በቅጡ መረዳት ከፈለግህ መልሱ ያለው እውስጥህ እንጂ ከውጭ አይደለም፡፡ ገንዘብን ቀርበህም እርቀህም ማየት፣ ያየኸውንም ከውስጥህ ማስታረቅ ግድ ይልህ ይሆናል፡፡ እኔ ግን የገባኝን ልንገርህና መነሻ ከሆነህ ጥሩ፣ ከረከሰብህና የተሻለ የመሰለህን ካፈለቅህም እሰየው። ልጅ ከወላጆቹ የተሻለ ካላሰበ ፣ ወላጆች የተፈጥሮን ግዴታ ከማሟላት ያለፈ ስራ አልሰሩም ማለት አይደል?
ይኸውልህ እንግዲህ….ገንዘብ ቁሳዊ፣ ማህበራዊና ስነልቦናዊ ገፅታዎችን ያዘለ ነው፤ እየረቀቁ የሚሄዱ የተሳሰሩ ትርጉሞችን ያቀፈ አስገራሚ የሰው ልጅ ፈጠራ። አዎ እንደምትመገብበት ሳህን ሰው ሰራሽ ቢሆንም፣ የሰው ልጅ ሊገለገልባቸው ሰርቶ ተገልብጠው ጌታው ከሆኑበት ውልዶቹ ገንዘብ ምናልባትም ቀዳሚው ነው፡፡
ቁሳዊው ሀይሉ የሚመነጨው ገንዘብ ባንተና በምትፈልጋቸው ወይም ያስፈልጉኛል ብለህ በምታስባቸው ነገሮች መሃል ርቀትን መፍጠር በመቻሉ ነው፡፡ ገንዘብ ባልነበረበት ዘመን እንዴት ነበር ብለህ እስኪ አስብ፡፡ የሚያስፈልግህን አድነህ፣ ካልሆነ ቆፍረህ ሲልም ሁለት ሶስቱን አንድ ላይ አስረህ ትገለገላለህ። ተፈጥሮ ታቀርብልሃለች፣ አንተ ታመሰግናታለህ። ጅል ካልሆንክ በስተቀር ለማያስፈልግህ ጉልበትህን አታባክንም፡፡ የሚያስፈልግህን ውስጥህ ይነግርሃልና ሌሎች እንዲወስኑልህ አትጠብቅም፣ ምናልባትም አትፈቅድም፡፡
አሁን ነገሮች እንደዛን ዘመን ቀላል አይደሉም። ሲጀምር የሚያስፈልጉህ ነገሮች ምግብና ከወገብ በታች የምታገለድመው ብጣሽ ቅጠል አይደለም። በቃኝ ማለት ብትችል እንኳ፣ እራስህን ከዋሻ ቆልፈህ ካልዘጋህ በስተቀር የምትኖርበት ህብረተሰብ፣ እኔንም ጨምሮ፣ አበድክ ብለን ሰው ሰራሽ ዋሻ ውስጥ እንቆልፍሃለን፡፡
ስለዚህ በእኛ መለኪያ፣ እንደ ጤነኛ ሰው የሚያስፈልግህን ካበዛኸው ገንዘብ ማግኘት ግድ ይልሃል፡፡ በምትፈልጋቸው ነገሮችና በማግኘትህ መሃል ገንዘብ መሰናክል ሆኖ ቆሟል ማለት ነው። ምን ያህል ገንዘብ የሚለው ትርጉም አልባ ነው፡፡ ሁሌም የፍላጎትህ ደንቃራ ገንዘብ ሆኖ ታገኘዋለህ። ምንም ያህል ወደምትፈልገው ብትጠጋ፣ ምንም ያህል የገንዘብ እጦት የዘጋብህን በሮች ብትከፍት፣ የጎደለህን እስክትሞላ የምትፈልገው ከፍላጎትነት ሳያልፍ ይቆይሃል፡፡ አገኘሁት ስትል የሚርቅህም ብዙ ነው፡፡
ሁሉንም ባትችልም ታዲያ ፣ የምትፈልጋቸውን ነገሮች በሂደት ማግኘትህ አይቀርም፡፡ አንዳንዱን በቀላል፣ ሌላውን ለፍተህ የግልህ ታደርጋለህ። ደሞ ያኛው ዋጋ የማይወጣለትን ያሰዋሃል፡፡ ካገኘሃቸውም በኋላ ፣ አንዳንዱ የምትጠቀምበት፣ ሌላው ቢቀር ምንም የማያጎድልብህ ሆኖ ሊሰማህ ይችላል፡፡ ያኛው ደሞ በጊዜያዊ ሞኝነት ተታለህ እንጂ እድሉ ቢሰጥህ ደግመህ የማትሰራው ስህተት መስሎ ይታይህ ይሆናል፡፡
ግን ሁለት ነገሮች አይቀሬ ናቸው፡፡ አንድም ያ እንደዛ የለፋህለት፣ ተሟላ ብለህ የተደሰትክበት ፍላጎትህ ክብሩን ያጣብሃል፡፡ ያንተ ያልነበረው ያንተ ሲሆን፣ በሌሎች እጅ ያማረህ ተራ ይሆንብሃል፡፡ ዋጋ ከፍለህ ገንዘብ ሰርተህ፣ ቁሳቁስ ገዝተህ ያገኘህ የመሰለህ ልባዊ እርካታ፣ እንደ በልግ ዳመና ድንገት ብን ብሎ ይሰወርብሃል፡፡ ገንዘብ ጊዜያዊ ደስታ ሰጥቶህ መልሶ ይነጥቅሃል፡፡
ያን ጊዜ፣ በሁለተኛ ደረጃ፣ ካለህ የተሻለ ፍለጋ ታንጋጥጣለህ፡፡ የሚገርምህ ታዲያ ካንተ የተሻለ ያላቸው ብዙሃን እንደሆኑ ትረዳና፣ አዲስ ፍላጎት ፈጥረህ፣ ያለህን ንቀህ በምትፈልገውና በአንተ መሃል እንደገና ገንዘብን ደንቃራ ትገትራለህ፡፡ እንዳንተው፣ አንተ ባለህ ማልለው፣ እነሱ ሽቅብ አንተ ቁልቁል የምታያቸውም ብዙሃን እንደሆኑም አትገነዘብም፡፡ ወደ ላይ አንገትህን ሰብረህ እንዴት ወደ ታች ልታይ ትችላለህ? የገንዘብ የመጀመሪያው ምትሃታዊ ሀይሉ እዚህ ላይ ነው፡፡
እንዳትሳሳት አደራህን! 1 ሺህ ወይም 1 ቢሊዮን አልያም ከዛም በላይ ይኑርህ፣ አይኑርህ እያልኩህ አይደለም፡፡ ግን ምንም ያህል ገንዘብ እንደ ፈንዲሻ በድስትህ ሲንከተከት ቢውል፣ ምትሃታዊ ሀይሉ ካወረህ ቅምም አይልህም ማለቴ ነው፡፡
ይህንን አልፈህ ማየት ስትችል - ከፍ ስትል ማለት አይደል? - የገንዘብ ማህበራዊ ትርጉም ሌላ ፈተና አዝሎ ያፈጥብሃል፡፡
ሲቀጥል----
ባጭሩ ሁለት ነገር ላስጨብጥህ ሞክሬያለሁ። ገንዘብ በራሱ ጥፋተኛ እንዳልሆነ፣ ሆኖም የፍላጎታችን ጣሪያ አድማሳዊ ብቻ ስለሆነ፣ የሚበቃንን ያህል መቼም ማግኘት እንደማንችል ነገርኩህ፡፡ ይህም ለገንዘብ ያልታቀደለትን ሀይል እንዳጎናፀፈውም አወራን፡፡
ይህንን ተከትሎ ሁለተኛው የገንዘብ ምትሃት ያለው ከማህበራዊ ገፅታው ላይ ይመስለኛል፡፡ ያለህ የገንዘብ መጠን በምትኖርበት ማህበረሰብም ሆነ ከዛ በዘለለ ከባለፀጎች ተርታ ያስመድብሃል፡፡ ከመናጢ ድሃ ይጀምርና፣ መካከለኛ ደሃ፣ ከድህነት ሊወጣ የደረሰ፣ መሃል ሰፋሪ፣ ጀማሪ ሀብታም፣ የናጠጠ ሀብታም ሌላም ሌላም እየተባለ ማህበረሰቡ ይከፋፈላል፡፡ እያንዳንዱ ክፍል ከታቹ ካለው የበለጠ፣ ከላይ ካለው ያነሰ “ሀይል/ጉልበት” አለው፡፡ ይህ ጉልበት የገንዘብ ማህበራዊ ምትሃት መቀመጫ ነው፡፡
ጉልበቱ ምንድ ነው አትልም?
ነገሮችን ከመግዛት አቅም ተከትሎ የሚመጣው ሰዎች ባለህ ሀብት መጠን የሚሰጡህ ቦታና ክብር ነው። በዚያው ምልከታ የምትገዛቸው ነገሮች መጠቀሚያ ብቻ ሳይሆኑ ያለህበትን የማህበረሰብ ክፍል መግለጫም ናቸው፡፡ ይህን ያህል ገንዘብ አለኝ፣ ሀብቴ ይህን ያህል ነው፣ እንደዚህ ብላችሁ ልታዩኝ ይገባል፣ በናንተ መሃል ያለኝ ደረጃ ይኸውላችሁ ---- ብለህ የምታውጀው በምትገዛቸው ቀሳቁሶች ዋጋ ሸፍነህ ይሆናል፡፡ ያኔ ከአንተ በታች ያሉትን ቁልቁል የማየትን ሀይል ገንዘብ ይሰጥሃል፡፡ እነሱም ባለህ ሀብት ያከብሩሃል፡፡ ድሮ ቢሆን የሀገር ንጉስም ሊያደርግህ ይችል ነበር፡፡ አሁንም ትንንሽ ንግስናዎች ያንተ ይሆናሉ፡፡ ከዚህም የአሸናፊነትን፣ የስኬትን መንፈስ ታጭዳለህ፡፡ ያሰክርሃል ቢባል ያስኬዳል፡፡
የሀብት ደረጃዎችን ስትቀበል፣ የስኬትህ መለኪያነታቸውንም ያንተ ማድረግህ ግድ ነው፡፡ መቶ ብር ካረረበት ጀምሮ፣ ቢሊየነር እስከምትለው፣ ሁሉም ያለውን ምድራዊ ስኬት ባለበት የሀብት ክፍል ለመለካት ሲገደድ፣ ገንዘብ የቁሳዊ ፍላጎት ማሟያ መሆኑን አልፎ መጠሪያ ይሆናል፡፡ ለዚህም ነው በየጊዜው የአገራችን 100 ሁብታሞች፣ የአለም አንደኛ ሀብታም፣ የአፍሪካ ደሃዋ አገር እየተባለ ደረጃ የሚወጣው፡፡ በግልባጩ ከተመደብክበት የሀብት ደረጃ በላይ ያሉትን መመልከትህ አይቀርም፡፡ “የት ጋ ነው ያለሁት?” ብለህ ትጠይቃለህ፣ ከበላይህ ብዙ ደረጃዎች ይታዩሃል። ከፍ ወዳለው ክፍል መግባትን ትሻለህ፤ የንግስና ርስትህን ለማስፋት መሆኑ ነው፡፡
ገንዘብ መጠሪያህ ከሆነ በኋላ ማብቂያ የለውም። ሁሌም ብዙ ገንዘብ ስምህን ተከትሎ እንዲጠራልህ ትፈልጋለህ፡፡ የቱንም ያህል ብታባክነው የማያልቅ ገንዘብ ብትይዝ፣ በሀብት ምድብ ቁንጮ ላይ ብትቀመጥ፣ በስምህ የተመዘገበልህን ለመጨመር ስትል ብቻ ገንዘብን ትሻለህ፡፡ ይህን ጊዜ ገንዘብ ሁለተኛውን ምትሃቱን ጣለብህ ማለት ነው፡፡ ከሰዎች በልጦ መታየትን አቅምሶህ፣ የዘላለም ሱሰኛው አደረገህ፡፡
ገንዘብ ንጉስም ሎሌም አደረገህ ማለት አይደል፡፡
መጨረሻው
ገንዘብን ለጥቅሙ ሳይሆን ለስሙ ስትል ማሳደድ ከጀመርክ፣ ያንተው የስነልቦናህ አካል ይሆንልሃል፡፡ ይህንን ሲያደርግ ጫማ ቆንጥጦ ሽቅብ እንደሚያዘግም ጉንዳን፣ ሳታየው በዝግታ ነውና የማንነትህ አካል፣ የስሪትህ ምሰሶ ሲሆን ላታውቀው ትችላለህ፡፡ ያለህ ገንዘብ የስራህን ስኬት መግለፅ ብቻ እጣው ሊሆን ሲገባ፣ የልብህ ማማ እንዲሆን ስትፈቅድለት ፣ እሱ ጌታ አንተን ሎሌ የማድረግ ስልጣንን ይቀዳጃል፡፡ ሶስተኛው ምትሃትም እዚህ ላይ ነው ያለው፤ ገንዘብ ከላይ ያወጋናቸውን ውጫዊ ገፅታዎቹን ዘሎ ነፍስህ ላይ ሲጠመጠም የማይነካ ኃያል ይሆንብሃል፡፡
ምትሃቱን የሚያገኘውም በሁለት ምክንያት ይመስለኛል፡፡
መጀመሪያ ገንዘብን በዚህ መልኩ ስታሳድደው፣ ለክብሩ ብለህ የምትፈፅማቸው ድርጊቶች በአብዛኛው ንፁህም ህጋዊም አይሆኑም፡፡ ሱሰኛ ነህና እሱን ለማርካት ስትል አስተካክለህ ከተከልከው ከማጨድ ይልቅ ካልዘራህበት መሻትህ ግድ ነው። በስራ ብቻ ካለህበት ፈቀቅ ማለት ሲከብድህ፣ የምታልመውን የተሸነቆረ የገንዘብ ጎተራ በስራህ ልትሞላው እንደማትችል ስትረዳ፣ ሌሎች ሰርቀው ሲከብሩ፣ ከታችኛው ምድብ በድንገት ተፈትልከው ከላይኛው ሲሰኩ፣ የምትኖርበት ህብረተሰብ ተሸናፊ ነህ ብሎ ሲሳለቅብህ ፣ አንተም ሽንፈት ይውጥሃል፡፡ ስለዚህ ላለመሸነፍ ስትል አንተም ትገባበታለህ፡፡ ሲሰርቁ ትሰርቃለህ፡፡ ተራ ሌባም ባትሆን፣ ያንተ ባልሆነው መክበርን መሻትህ ግን ከተራዎቹ ተርታ ያስመድብሃል፡፡
ሰርቀው ላልተያዙ ሲጨበጨብ አብረህ ታጨበጭባለህ፡፡ መስረቅን ሸሽተው ከድሃው ተርታ በተመደቡ ሲሳለቁ፣ በስንፍናቸው ሲገረሙ ትታደማቸዋለህ፡፡ ‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› የእለት ፀሎትህ አካል ይሆናል። ለገንዘብ ብለህ ዋጋ የማይወጣላቸውን ነገሮች ስታጣ ብዙም አይሰማህም። ከጓደኛህ ነጥቀህ ስትከብር ትደሰታለህ፣ ብዙዎችም በተራህ ያጨበጭቡልሃል፡፡ የቤተሰብህን ፍቅር በገንዘብ ስትለካ ምንም አይመስልህም፡፡
ታሪክ መሰረት ከሆነን ደሞ፣ እያንዳንዱ ስርቆት ቅጣትን ሳይሆን ሽልማትን ሲያድል ታያለህ። መጀመሪያ ግራ ይገባህ ይሆናል፣ ከዛ መቀበልን ትመርጣለህ፣ በመጨረሻም መብትህ እንደሆነ ትቆጥረዋለህ፡፡ ከሽልማቱም አልፎ የስርቆትን ድብብቆሽ ትወደውም ይሆናል፡፡ መጀመሪያ በፍራቻ ታጥረህ የፈፀምከው ስርቆት ልምድህ ሲዳብር እንደ ጥሩ ጨዋታ ማየትም ትጀምራለህ፡፡ በደም ስሮችህ የሚለቅብህን እፅ አጣጥመህ ትወደዋለህ ቢባል ማጋነን አይሆነም፡፡
በሁለተኛ ደረጃ በእጅህ ያለህን የማጣት ፍርሃት ይጠናወትሃል፡፡ ልብ በል! ምንም የሚያስፈራህ ነገር እንኳን ባይኖር ፣ ቀናቶች የሚሰግዱልህ ቢመስልህ፣ የማጣት ፍርሃት ግን የቀን ተሌት ህልምህ አካል ይሆናል፡፡ የገንዘብ ማግኘት ሱስህን ከፍ ወዳለው ደረጃ የማሻገር አቅም ያላቸው ነገሮች መሪ ሆኖ እንዲቀመጥ ትፈቅድለታለህ፡፡ ከማጣት ፍርሃት ለመገላገል መልሱ የበለጠ፣ የማያልቅ ገንዘብ ነው ብለህ ስለምታምን ለዚሁ ትንከራተታለህ፡፡ የማያስፈልግህን ላታገኘው!
ይሄን ጊዜ ሶስተኛውና የመጨረሻውን ምትሃቱን ገንዘብ አሰፈረብህ ማለት አይደል? ስራውን ጨረሰ! እስከመጨረሻው ጌታህ ሊሆን ዙፋኑን ተቆናጠጠ፡፡
እናማ ምን ይሻላል ካልከኝ ፣ ጥቂት ልጨምር፡-
ቤንጃሚን ፍራንክሊን እንዳለው “ገንዘብ ደስተኛ እድርጎን አያውቅም፣ ሊያደርገንም አይችልም። ገንዘብ በራሱ ደስታን ማምረት የሚያስችለውን ስጦታ አልታደለም፤ ባገኘነው መጠን ጭማሪ እንሻለን እንጂ።” ደስታና እርካታም ይለያያሉ፡፡ ገንዘብ ሁለቱንም ሊሰጥህ የሚችለው አጠቃቀምህን ተከትሎ ነው። በገንዘብ ከምትገዛቸው ነገሮች እርካታን እንጂ ደስታን አትሻ፡፡ እርካታ አንፃራዊ ስለሆነ፣ የተሻለ ቁስ የበለጠ እርካታ ይሰጥሃል፡፡ እርካታ እንዲሁ ጊዜያዊ ነው፡፡ ሁሌም እድሳት ይፈልጋል፡፡
በተመሳሳይ ደስታንም አንፃራዊና ጊዜያዊ አድርገህ መመልከት ግን ስህተት ይሆናል፡፡ ከገንዘብ ደስታን የምትሻ ከሆነ፣ ካለህ ላይ ለሌላቸው ወይም ላነሳቸው ያለቅድመ ሁኔታ አሳልፈህ ስጥ። በማትጠቀምበት ቁሳቁስ መከበብን አትምረጥ። የህይወት ስኬትህን በገንዘብ ሳይሆን ባሉህ ዋጋ የማይወጣላቸው በረከቶች መዝነው፡፡ ይህ ከተሳካልህ ገንዘብ ከመገልገያ መሳሪያነቱ እንደማይዘልብህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። የገንዘብን መጥፎ ገፅታ እስከገባኝ ነገርኩህ፣ ጥሩውንማ እራሱ ያስተምርህ የለ? …..ብዬ ናታንን ብመክረው ምን ያህል ትርጉም ያገኝበት እንደሆነ አንጃ፡፡ ከዛ አልፎ “ደስታ ግን ምንድነው?” ካለኝ ሌላ አርእስት አገኘን ማለት አይሆንም?