Administrator

Administrator

በወንጀል ምርመራ ታሪኮች ላይ ባተኮሩ የልብወለድ ሥራዎቿ የምትታወቀው እንግሊዛዊቷ ደራሲ አጋታ ክርስቲ፤ ከ2 ቢሊዮን በላይ መፃህፍቶቿ ተቸብችበውላታል፡፡ የመጀመሪያ ሥራዋ The Mysterious Affair at Styles እ.ኤ.አ በ1920 ዓ.ም የታተመላት ሲሆን And Then There Were None የተባለው ሥራዋ 100 ሚሊዮን ቅጂዎች እንደተሸጡላት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ከ60 በላይ በወንጀል ምርመራ ላይ የሚያጠነጥኑ ልብወለዶች የፃፈችው አጋታ ክርስቲ፤ 14 የአጭር ልብወለድ መድበሎች ያሳተመች ሲሆን ከ12 በላይ የመድረክ ትያትሮችንም ጽፋለች፡፡ በብዛት በመታተም ከሼክስፒርና ከመጽሐፍ ቅዱስ ቀጥሎ በ3ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ በዓለም ላይ ለረዥም ጊዜ በመድረክ ላይ በመቆየት የአጋታን ትያትር የሚወዳደር የለም፡፡ The Mousetrap የተሰኘው ትያትሯ እ.ኤ.አ ከ1952-2012 ዓ.ም ከመድረክ ሳይወርድ ታይቶላታል፡፡ ለ60 ዓመት ገደማ ማለት ነው፡፡
በልብወለድ መፃሕፍቷ ላይ ተመስርተው የተሰሩ ከ30 በላይ ፊቸር ፊልሞች ያሉ ሲሆን ወደ ቴሌቪዥን፣ ሬዲዮ፣ ቪዲዮ ጌምና ኮሚክ መፃህፍት የተቀየሩ በርካታ ስራዎችም አሏት፡፡ ስድስት የፍቅር ልብወለድ መፃሕፍትን ሜሪ ዌስትማኮት በሚል የብዕር ስም ያሳተመችው ደራሲዋ፤ ስራዎቿ ከ100 በሆኑ በላይ ቋንቋዎች ተተርጉመውላታል፡፡
በከፍተኛ ሽያጭና ተወዳጅነት የምንጊዜም ምርጥ ደራሲ የሚል ክብርና ሞገስ የተቀዳጀችው አጋታ፤ ከግማሽ ክ/ዘመን በላይ የፃፈች ሲሆን የእሷን ሥራዎች ማንበብ ዓለምአቀፍ የጊዜ ማሳለፊያ ተደርጐ እስከመቆጠር ደርሷል፡፡ ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ የአጋታ ሥራዎች ወደ አማርኛ ተተርጉመው ለኢትዮጵያውያን ተደራሲያን መቅረባቸው ይታወቃል፡፡

  በዋሽንግተን ዲሲ አሜሪካ በየአመቱ እየታተመ የሚወጣው ‘ኢትዮፕያን የሎው ፔጅስ’ የተባለ የንግድ መረጃ መጽሃፍ መስራችና አሳታሚ ኢትዮጵያዊቷ የንግድ ባለሙያ የሺመቤት በላይ፤ በዋሽንግተን ዲሲ ዙሪያ በሚከናወነው የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ተጠቃሽ ስራ ላከናወኑ ግለሰቦችና የማህበረሰብ መሪዎች በየአመቱ የሚሰጠው የ”ሾው አዋርድ” ተሸላሚ ሆነች፡፡
‘ሾው ሜን ስትሪትስ’ የተባለውና በዋሽንግተን ዲሲ ዙሪያ የሚከናወነውን የንግድ እንቅስቃሴ ለማበረታታትና ለማስፋፋት የሚሰራው ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት፣ ዘንድሮ ለአስረኛ ጊዜ ባዘጋጀው አመታዊ ሽልማቱ ኢትዮጵያዊቷን የንግድ ስራ ባለሙያ የሺመቤት  በላይ ጨምሮ ለሶስት ግለሰቦች ሽልማቱን አበርክቷል፡፡
ድርጅቱ፤ የሺመቤት በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘውን የኢትዮ-አሜሪካ የንግድ ማህበረሰብን በማስተዋወቅና የተሻለ እንቅስቃሴ የሚያደርግበትን ዕድል በመፍጠር ረገድ ላከናወነቻቸው ተግባራት እውቅና ለመስጠት በ”ሾው ስታር አዋርድ” ዘርፍ ሽልማቱን እንዳበረከተላት ገልጿል፡፡
የዋሽንግተን ዲሲ ከንቲባ ቪንሸንት ግሬይ፣ የአካባቢውን የንግድ እንቅስቃሴ ለማፋጠን የሚያስችል የበጀት ድጋፍ በማድረጋቸው፤ የሽልማት ድርጅቱ የቀድሞው የቦርድ ሊቀመንበር ቲም ማክ ደግሞ ድርጅቱን በብቃት በመምራት ባበረከቱት አስተዋጽኦ፣ ሁለቱም በ‘ሾው ሻምፒዮን አዋርድ’ ዘርፍ የዘንድሮ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
በጅግጅጋ ተወልዳ ያደገችው የሺመቤት፤ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በድሬዳዋ ከተማ ከተከታተለች በኋላ ወደ አሜሪካ በማቅናት፣ በባተን ሮግ ሳውዘርን ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ ማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪዋን ተቀብላለች፡፡ በመቀጠልም ኑሮዋን በዋሽንግተን ዲሲ በማድረግ አመታትን የፈጀ ጥናት በመስራት፣ በአካባቢው የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የንግዱ ማህበረሰብ አባላትን የሚያገናኘውንና የንግድ መረጃ የሚያቀርበውን ‘ኢትዮፕያን የሎው ፔጅስ’ የተሰኘ መጽሃፍ እ.ኤ.አ በ1993 ዓ.ም እያዘጋጀች ማሳተም ጀመረች፡፡
ላለፉት 20 ዓመታት በፕሬዚዳንትነት በምትመራው ‘ዘ ኢትዮፕያን የሎው ፔጅስ ኢስታብሊሽመንት’ (ፍቅር ኩባንያ) አማካይነት የሚታተመውን የንግድ መረጃ መጽሃፍ፤ ከጊዜ ወደጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ የቻለችው የሺመቤት፤ እ.ኤ.አ በ2008 ዓ.ም በአሌክሳንድሪያ ቨርጂኒያ ከሚገኘው ስትራየር ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን ሁለተኛ ዲግሪዋን ያገኘች ሲሆን ከባለቤቷ ከታዋቂው ድምጻዊ ይሁኔ በላይ ጋር በመሆን በተለያዩ የንግድ ስራዎች ላይ ተሰማርታ በዋሽንግተን ዲሲ የንግድ ማህበረሰብ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡
በኢትዮጵያውያን ማህበረሰብና በተለያዩ ተቋማት መካከል የጠነከረ ግንኙነት የመፍጠር ዓላማ አንግቦ የሚንቀሳቀሰው “ዘ ኢትዮፕያን ኤክስፖ” የተባለ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት እ.ኤ.አ በ2000 በመመስረትና በፕሬዚደንትነት በመምራት አመታዊ ደማቅ ዝግጅቶችን በማዘጋጀት የምትታወቀው የሺመቤት፤ በንግድ መስክ በተሰማሩ የተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ በአመራርነትና በአባልነት ትሳተፋለች፡፡
በንግድ፣ በባህል፣ በኪነጥበብና በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ በአለማችን የሚታዩ እንቅስቃሴዎችን ለኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ የማቅረብ ዓላማ ይዞ፣ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች እየተዘጋጀ በህትመትና በድረገጽ ለንባብ የሚበቃውን ‘ባውዛ’ የተሰኘ መጽሄት፣ እ.ኤ.አ  በ2008 በመመስረት፣ በአሳታሚነት እየሰራች ትገኛለች፡፡
በዋሽንግተን ዲሲ ሾው ሃዋርድ በተባለ አካባቢ የሚገኘውን ‘ሊትል ኢትዮጵያ’ የተሰኘ ታዋቂ ሬስቶራንት በማኔጂንግ ዳይሬክተርነትና በባለቤትነት ለበርካታ አመታት ያስተዳደረችው የሺመቤት፤ በንግዱ ዘርፍ ለረጅም አመታት ባከናወነቻቸው ተግባራት፣ “የማህበረሰብ ስኬት ሽልማት” (2005)፣ “የአመቱ ምርጥ ሴት የንግድ ባለሙያ ሽልማት” (2004) እና “የዋሽንግተን ዲሲ የሴቶች ማህበር የአመቱ ምርጥ ሴት ሽልማት”ን ጨምሮ በርካታ የተለያዩ ሽልማቶችን ለማግኘት ችላለች፡፡

አቶ ደረጀ ሺበሺ የወረኩማ ባርና ሬስቶራንት ዳይሬክተር

ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘው ጣፎ ከተማ እንደከተማ ራሷን ችላ መተዳደር የጀመረችው ከ1999 ዓ.ም ወዲህ ነው፡፡ በዚህች ከተማ ባለሀብቶች በተለያዩ ዘርፎች መዋዕለ - ንዋያቸውን እያፈሰሱ ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም መካከል ቀደም ሲል በኮንስትራክሽን ዘርፍ ተሰማርተው የነበረው አበባየሁ ከበደ የህንፃ ስራ ተቋራጭ አንዱ ነው፡፡ ባለሀብቶቹ አካባቢውን በማጥናትና ምቹነቱን በማረጋገጥ በሆቴል ኢንደስትሪው የተሰማሩ ሲሆን ከሁለት ሳምንት በፊት የተመረቀውን “ወረ - ኩማ” ባርና ሬስቶራንት ለአገልግሎት አብቅተዋል፡፡ “ከተማዋ ለኢንቨስትመንት ምቹ እንድትሆን የተደረገው ከፍተኛ ጥረት፣ እንደ ወረ ኩማ - ያሉ ለከተማ ጌጥ የሆኑ ሬስቶራንቶችን ለማየት አስችሎናል” ብለዋል የከተማዋ ኃላፊዎች፡፡ በከተማዋ እንደተግዳሮት የሚነሱት የውሃና የመብራት መቆራረጥ ሲሆን ውሃውን በተመለከተ የጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ ተደርጐ ከተማዋ በተወሰነ መልኩ ችግሯን እንደቀረፈች የጠቆሙት ኃላፊዎቹ፤ በመብራት በኩል ያለው ችግርም እንዲሁ በቅርቡ እልባት እንደሚያገኝ ተናግረዋል፡፡
የዛሬ ሁለት ሳምንት በወረ - ኩማ ባርና ሬስቶራንት የምረቃ ስነ - ሥርዓት ላይ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ከባለቤቱና ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ከአቶ ደረጀ ሺበሺ ወ/ማርያም ጋር በአዲሱ የባርና ሬስቶራንት ቢዝነስ ዙሪያ፣ ስለ ኮንስትራክሽን ዘርፉ፣ ስለ ከተማዋና የንግድ እንቅስቃሴው እንዲሁም ስለወደፊት ህልምና ራዕያቸው አነጋግራቸዋለች። እነሆ፡-

እስቲ እንዴት ነው ወደ ቢዝነስ ሙያ የገባኸው?
ቢዝነስ የጀመርነው ከቤተሰብ ጋር ነው፡፡ የቤተሰብ የጋራ ቢዝነስ ነው ያለን፡፡ ኤሌክትሮኒክስ እያስመጣን እናከፋፍላለን፡፡ በኮንስትራክሽን ዘርፍም ተሰማርተናል፡፡ አበባየሁ ከበደ የህንፃ ሥራ ተቋራጭ የተባለ ድርጅት አለን፡፡ ደቡብ ሱዳን ጁባ ውስጥ ሆቴል አለን - “ኦአሲስ” የሚባል ቃሉ እንግሊዝኛ ሲሆን የ “በረሃ ገነት” የሚል ትርጓሜ አለው፡፡
ደቡብ ሱዳን እንደ አገር ራሷን ችላ ከተቋቋመች ገና ሶስተኛ አመቷ ነው፡፡ ሆቴላችሁ መቼ ነው የተከፈተው?
ነፃነታቸውን ከማግኘታቸው ከአንድ አመት በፊት ነው ተከፍቶ ስራ የጀመረው፡፡
ዛሬ እዚህ ጣፎ ከተማ የተገናኘነው “ወረ ኩማ” የተሰኘው ባርና ሬስቶራንታችሁን ምርቃት ምክንያት በማድረግ ነው፡፡ ለመሆኑ ጣፎ ላይ በዚህ ዘርፍ እንድትሰማሩ ያነሳሳችሁ ምንድን ነው?
ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ በኮንስትራክሽን ዘርፍም ተሰማርተናል፤ ደረጃ ሁለት ተቋራጮች ነን። ይህ ቢዝነሳችን ከአምስት ዓመት በላይ ሆኖታል። እናም ጣፎ የመጣነው በዋናነት ለኮንስትራክሽን ስራ ነው፡፡ በመጀመሪያ የቤተሰብ የመኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ተሰማራን፡፡ የእህቶቻችንና የእናታችንን ቤት ስንገባ፣ የስራችንን ጥራትና ቅልጥፍና ያዩ ሰዎች ሌሎች ተጨማሪ ስራዎችን አገኘን በኮንትራት ሰጡን፡፡ ለኮንስትራክሽን ስራው ስንንቀሳቀስ ከተማዋን ተዘዋውረን የማየት እድል ነበረን፡፡ እናም አካባቢው አየሩ፣ የመሬት አቀማመጥና ሁሉ ነገሩ ምቹ ሆኖ ታየን፡፡ የከተማ አስተዳደሩም በማንኛውም ኢንቨስትመንት ከተማዋ ላይ ለሚሰማራ አካል የሚፈጥረው ምቹ ሁኔታ ማራኪ መሆኑን በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ስንሰማራ ለመታዘብ ቻልን፡፡ ከተማዋ አዲስ በመሆኗ ብዙ ኢንቨስት ሊደረግባቸው የሚችሉ ዘርፎች እንዳሉ ተገንዝበናል፡፡ ከዘርፎቹ አንዱም የሆቴልና የሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪው በመሆኑ እኛም ወደዚሁ ገባን፡፡ በዚህ ዘርፍ መሰማራት እንፈልጋለን ስንል ከተማ አስተዳደሩም በደስታ ነው የተቀበለን። ይሄው ለከተማዋ ድምቀት የሆነውን “ወረ ኩማ” ባርና ሬስቶራንትን አስፋፍተን ዛሬ ምረቃው ነው፡፡
አስፋፍተን ስትል?
መጀመሪያ ከፊት ለፊት የምታያት ቤት ብቻ ነበረች፡፡ ትንሽዬ ምግብ ቤት፡፡ እኛ ይህን ቦታ ተከራይተነው ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ያለው ጠቅላላ ግንባታ በአንድ ወር ውስጥ ተጠናቆ ነው ስራ የጀመረው፡፡ ፊት ለፊት ካለው ቤት በስተቀር ይህን የምታይውን የመናፈሻ ባር፣ መፀዳጃ እና መሰል ግንባታዎች ከከተማ አስተዳደሩ ባገኘነው ይሁንታ አስፋፍተነው ነው፡፡ አሁን ከባለቤቱ ጋር ለአራት አመት ኪራይ ተፈራርመናል፡፡ የአንድ አመት ክፍያ ቅድሚያ ከፍለናል፡፡ እንደዚህ በማድረግ በዘርፉ አገልግሎት ላይ እሴት ለመጨመር እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ሌላው በአካባቢው በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶችን ለማነቃቃት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረናል፡፡ ወረ ኩማንና መስተንግዶውን ሲመለከቱ፣ ሆቴላቸውንና የአገልግሎት አሰጣጣቸውን ለማሳደግና ተፎካካሪ ለመሆን እንዲተጉ ያደርጋል የሚል ከፍተኛ እምነት አለኝ፡፡
ቦታው አስፋልት ዳር ነው፡፡ ሆኖም ተከራይታችሁት እንጂ የእናንተ አይደለም፡፡ የራሳችሁ ለማድረግ ያደረጋችሁት ጥረት አለ?
ይሄ ትልቁ ሀሳባችን ነው፡፡ በዚህ ላይ ትልቅ እቅድ አለን፡፡ ተጨማሪ ቦታ እንዲኖረን በማድረግ ትልቅ ስራ የመስራት ፍላጐት አለን፡፡ ቀደም ሲል እንደጠቀስሽው ጥሩ ቦታ ላይ ነው ያለው፤ ለዘርፉ ስራ የሚመጥን ነው፡፡ በዚህ ቦታ ላይ ከዚህ የተሻለ ስራ መሰራት እንደሚችል እናምናለን፡፡ እና የራሳችን ለማድረግ እንጥራለን፡፡ የጣፎ ከተማ አስተዳደርም ይህንን ያመቻቻል ብለን እናስባለን፡፡ ምክንያቱም ከተማዋ እንደከተማ ራሷን ችላ መተዳደር የጀመረችው ከ1999 ዓ.ም ወዲህ በመሆኑ፣ ከተማ አስተዳደሩ አማራጭ ኢንቨስትመንቶች ወደከተማዋ እንዲመጡ የሚያሳየው ፍላጐት እንድትሰሪ ያበረታታሻል፡፡ ሌሎች ኢንቨስተሮችም መጥተው ቢሰሩ ሁኔታው ምቹና የሚያሰራ ነው ልላቸው እፈልጋለሁ፡፡
”ወረ ኩማ” ባርና ሬስቶራንት መጀመሪያ ከነበረው ቤት ውጭ ሙሉ በሙሉ የተሰራው አገር በቀል በሆኑ ቁሳቁሶች ነው፡፡ እንደ ቀርከሃ፣ ሸምበቆ እና የመሳሰሉትን ለምን መረጣችሁት? አጠቃላይ የቤቱ አደረጃጀትም ባህላዊ ገፅታው ያመዝናል፡፡ ምክንያቱ ምንድነው?
እንግዲህ ሁሉም ነገር ባህልን መሰረት ያደረገ ሲሆን ደስ ይላል፡፡ ለምሳሌ ሁሉም ቁሳቁሶች ከዚሁ ከጣፎ የወጡ ናቸው፡፡ ቢዝነስ ሲሰራ ጐን ለጐን ባህልንም አብሮ ማስተዋወቅ ተገቢ ነው። ይህ እንግዲህ ሌሎች በዘርፉ የሚሰማሩ ሰዎች እንዲህ አይነት ቢዝነስ ውስጥ ሲገቡ የግድ ውድ ማቴሪያል መጠቀም እንደሌለባቸው ማሳያ ይሆናል። ሸምበቆው እንጨቱ፣ የጐጆዎቹ ክዳን ሳሩ ሁሉ… እዚሁ አካባቢው ላይ በቀላሉ የሚገኙ ናቸው። ዋናው ነገር ለተስተናጋጅ ምቾት በሚሰጥና በሚያዝናና መልኩ መስራቱ ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ እኔና አንቺ እዚህ ተቀምጠን ስናወራ፣ ድባቡ ደስ ይልሻል፤ አየሩ ተስማሚ ነው፤ ለአካባቢው ጌጥ የሆነ ባርና ሬስቶራንት ሆኗል፡፡ ማራኪና የሚያዝናና የሆነው በውድ ቁሳቁስ ስለተሰራ አይደለም፡፡ ባህልን መሰረት አድርጐ በአገር በቀል ቁሳቁሶች በማራኪ ሁኔታ ስለተሰራ እንጂ፡፡
በሬስቶራንቱና በካፌው ዙሪያ ያሉ ቦታዎች በጌጣጌጥነት ከተጠቀማችሁባቸው ባህላዊ አልባሳት ውስጥ የዶርዜ ደንጉዛ፣ የኦሮሚያ፣ የአማራ፣ የሃድያና መሰል ብሔሮች አልባሳት ይገኙበታል ለምን ተመረጡ?
ያው የቢዝነስና የመዝናኛ ቦታ የሁሉም ሰው ነው። አሁን ከከተማ ወጣ ብሎ መዝናናት ተለምዷል፡፡ ለምሳሌ ሱሉልታ፣ ዱከም፣ ሰበታ፣ ቡራዩ ብቻ በአዲስ አበባ ዙሪያ ወጣ ብሎ መዝናናት ተለምዷል፡፡ እዚህ ቦታ የትኛውም ብሔር ብሔረሰብ መጥቶ ይዝናናል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ቱሪስቶችም ወደዚህ ሊመጡ ይችላሉ፡፡ አንድም ኢትዮጵያዊነትን ማስተዋወቅ ነው፤ ሁለትም እነዚህ አልባሳት በጌጥ መልክ ሲታዩ አይንን ይማርካሉ፡፡ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ማለት ነው፡፡ ህብረ - ኢትዮጵያን ያቀፈ፣ ባህላችንን የሚያንፀባርቅ፣ በአገር በቀል ቁሳቁሶች የተዋበ መሆኑ ቤቱን ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እንዲሸት ያደርገዋል፡፡
እነዚህ ተጨማሪ የመዝናኛ ቦታዎች ማለትም ጐጆዎቹና ማስፋፊያው በአንድ ወር ተሰርቶ መጠናቀቁ የኮንስትራክሽን ባለሙያ በመሆናችሁ ነው ወይስ ሥራውቀላል ነው?
ብዙ ሰው የተገረመው በዚህ ነው፡፡ “ይሄ የማስፋፊያ ግንባታ አንድ አመት ፈጀ ወይስ ስድስት ወር?” ይሉናል። ነገር ግን በአንድ ወር ነው የተጠናቀቀው፡፡ በአንድ ወር ያለቀው በኮንስትራክሽን ዘርፍ ስለተሰማራን ብቻ አይደለም። የእኛ ጥረትና ትጋት ነው በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ያደረግነው፡፡ እርግጥ በዘርፉ ውስጥ መኖራችን አንዱ ግብአት ሊሆን ይችላል፡፡ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ባሳየነው የሥራ ጥራትና ፍጥነት ሌሎች ስራዎችንም አግኝተናል። ይሄን ሥራ በአንድ ወር የጨረስነው ግን ትኩረት ሰጥተን በመስራታችን ነው እንጂ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ውስጥ በመኖራችን ብቻ አይደለም፡፡ በኮንስትራክሽን ውስጥ ኖረው፣ በጥራትና በፍጥነት ስኬታማ ያልሆኑ ብዙ ድርጅቶች አሉ እኮ፡፡ እኛ አሁን ኮንስትራክሽን ላይ ባለን የስራ ብቃት “ቻይኖች ናቸው የሰሩት” የሚሉን አሉ፡፡ ግን ኢትዮጵያውያንም በደንብ መስራት እንደሚችሉ እያሳየን ነው፡፡ ይህም የማስፋፊያ ግንባታ በአንድ ወር ውስጥ ማለቁ የኢትዮጵዊያንን ብቃት ያስመሰክራል፡፡ የራሳችንን ብቃት ስለማናውቅ ነው እንጂ የሚያክለን የለም፡፡ ግን የአመለካከት ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን በምንም ነገር የላቀ ብቃት አለን፡፡ ነገር ግን በውጭ ባለሙያዎች የማመን ነገር ተጠናውቶናል፡፡
የማስፋፊያ ግንባታው ምን ያህል ወጪ ወጣበት?
ያው እንግዲህ ያላለቁና በመገንባት ላይ ያሉ ነገሮች አሉ፡፡ ነገር ግን እስካሁን 1.8 ሚሊዮን ብር ወጥቶበታል፡፡ የተጀመሩት ሲያልቁ ወደ ሁለት ሚሊዮን ይጠጋል፡፡
በከተማዋ ብዙ የኢንቨስትመንት አማራጭ እንዳለ ነግረኸኛል፡፡ በቀጣይ በምን ዘርፍ ለመሰማራት አስባችኋል?
ተዘዋውረሽ እንደተመለከትሽው ከጀርባው ሰፋ ያለ ቦታ አለው፡፡ ከፊት ለፊት የፓርኪንግ ቦታ ስለሌለው ያንን ቦታ ለፓርኪንግ ልናደርገው አስበናል። እንደነገርኩሽ ቦታውን ለመግዛትና የራሳችን ለማድረግ የጀመርነውና መስመር የያዘ ነገር አለ፡፡ ከዚያ በተረፈ ያሰብነው ትልቁ ነገር፣ በዚሁ አካባቢ ትልቅ የመዝናኛ ማዕከል ለመስራት አቅደናል፡፡ ቀደም ሲል እንደነገርኩሽ፣ በአሁኑ ወቅት ሰው ከከተማ ወጣ ባሉ ትንንሽ ከተሞች የመዝናናት ፍላጐት አለው፡፡ እንደነ ሱሉልታና በመሰል አካባቢዎች ማለቴ ነው፡፡ የህዝቡን ፍላጐት ለማሟላት ጣፎን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን የሚያስጠራ ትልቅ የመዝናኛ ቦታ ለመስራት አስበናል፡፡ አሁን የተለያዩ ጥናቶች እያደረግን በጥሩ ሂደት ላይ ነው ያለው፡፡ ዋና ግባችን የአገር ውስጥ ደንበኛን ብቻ ሳይሆን ቦታው የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆንም እቅድ አለን፡፡
እንዲህ አይነት ኢንቨትመንቶች ሲካሄዱ ለአካባቢው ነዋሪ የስራ እድሎች ይፈጥራሉ፡፡ ወረ ኩማ ባርና ሬስቶራንት ለስንት ሰዎች የስራ እድል ፈጠረ?
በግንባታው ወቅት መቶ በመቶ ሰራተኛ የወሰድነው ከዚሁ አካባቢ ነው፡፡ በጉልበት ስራም በሙያተኝነትም ማለቴ ነው፡፡ አሁን ሬስቶራንቱ ተከፍቶ ስራ ከጀመረ በኋላም በሰርቪሱና ላይ በተለያየ ስራ ላይ ያሉት 80 በመቶዎቹ የአካባቢው ሰዎች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ለ40 ሰዎች የስራ እድል ተፈጥሯል፡፡ ማስፋፊያው ሲያልቅ ለተጨማሪ ሰዎች የስራ እድል መፈጠሩ የማይቀር ነው፡፡
ባርና ሬስቶራንቱ ስራ ከጀመረ በኋላ ገበያው እንዴት ነው?
በጣም አሪፍ ነው፤ እኛ ደስተኞች ነን፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ሰዎች እየመጡ ይጐበኙናል፤ ያበረታቱናል። አሁን ገበያውም ጥሩ ነው፡፡ የአካባቢው ሰዎችም ሆኑ ከአዲስ አበባ የሚመጡት እየተስተናገዱበት ነው፡፡ ይሄ ለአዲስ አበባ ቅርብ ነው፤ መንገዱም ጥሩና ቀጥ ያለ ነው። ጣፎ ለወደፊት ተስፋ ያላት ከተማ ናት፤ እንደነ ሮፓክ እና ሲሲዲ የመሳሰሉ ትልልቅ ሪል እስቴቶች እዚሁ አሉ። ወደፊት ትልቅ የመዝናኛና የንግድ ከተማ የመሆን እድል አላት፡፡ እኛም ለከተማዋ ማደግ በተለያየ ዘርፍ አስተዋጽኦ እያደረግን እንገኛለን። በነገራችን ላይ የደንበኛ ችግር የለም፡፡ ብዙ ባለሀብቶች ሩቅ ሳይሄዱ እዚሁ ብዙ ነገር መፍጠርና መስራት ይችላሉ ባይ ነኝ፡፡
ለአንተ የሥራ ትጋትና ጥንካሬ አርአያ የሆነህ ሰው አለ?
ታላቅ ወንድሜ አበባየሁ ከበደ ነው አርአያዬ። ለምን ብትይ… በጣም በጣም ጠንካራና አስተዋይ ሰው ነው፡፡ ከምንም ተነስቶ ነው እዚህ የደረሰው፡፡ የቤተሰባችን ቢዝነስ ያልኩሽ ኮንስትራክሽኑ “አበባየሁ ከበደ የህንፃ ስራ ተቋራጭ ነው” የሚባለው፡፡ ለዚህ ባርና ሬስቶራንት እዚህ መድረስም የእሱ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡ ጠንካራ ሰራተኛና ስራ ወዳድ ስላደረገኝ አመሰግነዋለሁ፡፡ ሌሎችም ለዚህ ባርና ሬስቶራንት እዚህ መድረስ የበኩላቸውን ያደረጉ በርካታ ሰዎች አሉ በጥቅሉ እናመሰግናለን፡፡

Saturday, 07 June 2014 13:54

ስኬትን ማረጋገጥ

እጅግ በጣም ጥሩ ለሆነ የተሽከርካሪ ማኔጅመንት የሚከተሉትን ጠቃሚ ልምዶች ይሞክሩ፡፡
በድርጅትዎ ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው፣ ተሽከርካሪ ፣ የድርጅቱ የደም ስር መሆኑን መረዳቱን እርግጠኛ ይሁኑ፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ ከመጠቁ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ጋር ይወዳጁ።
በቲሲኦ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ መሰረት አዲስ መኪና መፈብረክን ያራርቁ
ከፍተኛ ጥራትና ብቃት ያለው ተሽከርካሪ መስራት ምንድነው ጥቅሙ? የኢንሹራንስ ወጪ ይቀንሳል? የጥገና ወጪስ? በማለት ይጠይቁ ይላሉ፤ ሚ/ር ኦልደንበርግ፡፡

         በአገራችን ስንት ተሽከርካሪዎች እንዳሉ ያውቃሉ? እሱን ተውት፤ በአዲስ አበባ ከተማ በየቀኑ ስንት ተሽከርካሪዎች በየመንገዱ ይመላለሳሉ? ትክክለኛው አኃዝ ባይታወቅም በሺ የሚቆጠሩ ናቸው፡፡  
እነዚህ ተሽከርካሪዎች የሚጠቀሙት ቤንዚንና ናፍጣ ስለሆነ፣ በየቀኑ ወደ ከባቢ አየር የሚለቁትን ካርቦንዳይ ኦክሳይድ (የተቃጠለ በካይ ጋዝ) አስቡት። ምን ያህል እየተጎዳን እንደሆነ መገመት አያቅትም፡፡
ከአሜሪካ የትራንስፖርት መ/ቤት በተገኘ መረጃ መሰረት፣ በአብዛኛው ቀን በመላ አገሪቱ 12 ሚሊዮን ያህል ተሽከርካሪዎች አስፈላጊ ዕቃዎችን በማመላለስ ሲርመሰመሱ ይውላሉ፡፡
እነዚህ ተሽከርካሪዎች ሁሉንም ዓይነት መኪኖች ያጠቃልላሉ፡፡ ከባድ ዕቃ ጫኝ ካሚዮኖች፣ የሰዎች መጓጓዣ፣ ሽፍን ዕቃ ጫኝ ቫኖች፣… ይጨምራል፡፡ እነዚህ ተሽከርካሪዎች በተወሳሰበ ከባቢ፣ በሺዎች በሚቆጠሩ የተወሳሰቡና የተጠላለፉ መንገዶች፣ ፕሮግራሞች፣ ሕግና የደህንነት ጥንቃቄ፣… የሚጓዙ ቢሆንም የሚጠቀሙት አማራጭ ኃይል ስለሆነ ከባቢ አየር አይጎዳም፡፡ የእነዚህ ተሸከርካሪዎች ግዳጃቸውን በብቃት መወጣት የኩባንያዎቻቸው ሀብት ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የብሔራዊ ኢኮኖሚው ጭምር ነው፡፡
“የተሽከርካሪ ማናጀሮች ማየት ያለባቸው በርካታ ፈታኝ ሁኔታዎች አሉ” ይላሉ የቶዮታ ናሽናል ፍሌት ማርኬቲንግ፣ ሞቢሊቲና ስትራቴጂክ ፕላኒንግ ማናጀር ሚ/ር ማርክ ኦልደንበርግ፡፡ አያይዘውም “ከወጪና ትርፋማነት ጫና በተጨማሪ በየጊዜው የሚለዋወጡ ሕጎችን፣ ለኢንሹራንስ፣ ለጥገናና ለሾፌሮች አስተዳደር ተገቢውን ምላሽ መስጠት አለባቸው፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፤ ለዕለት ተዕለት ቢዝነሳቸው በጣም ተስማሚ የሆነ ተሽከርካሪ መምረጥና ንብረታቸው ማድረግ አለባቸው” ብለዋል ኦልደንበርግ፡፡
ስትራቴጂያዊ የዋጋ ቁጥጥር፡- እጅግ በጣም የተሳካላቸው የተሽከርካሪ ማናጀሮች፣ ከመኪናው መግዣ ዋጋ ይልቅ የመኪናውን አጠቃላይ የባለቤትነት ዋጋ (ቶታል ኮስት ኦፍ ኦውነርሺፕ ቲሲኦ) ይመለከታሉ። ከፍተኛው የቲሲኦ ስሌት “መኪናን አረንጓዴ አድርግ” (green the fleet”) የሚል መሆን አለበት፡፡ ይኼውም የተለመደው የነዳጅ ኃይል በውስጡ በሚያቃጥል ሞተር ወደ ኤሌክትሪክ ወይም ቅይጥ ወይም የታፈነ የተፈጥሮ ጋዝ ወይም ፈሳሽ የፔትሮሊየም ጋዝና በቅርቡ ገበያ ላይ ይውላል ተብሎ የሚጠበቀውን ሃይድሮጂን በመጠቀም ከጊዜው ጋር የሚስማማ የኃይል ፍጆታ ሊኖረን ይገባል፡፡
“በመላው ዓለም ጎዳናዎች የሚርመሰመሱ ከ6 ሚሊዮን በላይ Privs ሞዴል መኪኖች አሉን፡፡ እኛ ግን ሌሎች አምራቾች የሰሯቸውንና ከፍተኛ ብቃት ያላቸውን መኪኖች እየተጠቀምን ነው፡፡ ስለዚህ አረንጓዴ መኪኖች የሚገነባ ማንኛውንም ኩባንያ እየደገፍን ነው ያለነው” ብለዋል ሚ/ር ኦልደንበርግ።
የሃይድሮጂን የነዳጅ ሴል የተገጠመለት የቶዮታ መኪና ከዓመት በኋላ በ2015 ገበያ ላይ ይውላል። የዚህ መኪና ተረፈ ምርት ወይም ዝቃጭ ነገር ውሃ ብቻ ስለሚሆን የግሪን ጋዝ ልቀትን በፍፁም በማስቀረት “አረንጓዴን” ወይም አማራጭ ኃይልን ወደላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል፡፡ ሚ/ር ኦልደንበርግ፣ የዛሬ ዘመን የቴክኖሎጂ ጥበብ ርቅቀት የተሽከርካሪ ማናጀሮችን እየረዳ መሆኑን ሲናገሩ፤ “አረንጓዴ የሀይል አማራጭ ስትጠቀም ጥሩ ስለምትሰራ ገንዘብ ታጠራቅማለህ፡፡ ብዙ የንግድ ተቋማት ሀይብሪድ የሆኑትን ተሽከርካሪዎች ሲለውጡ (ሲገዙ) አይተናል። ከነዳጅ ውጪ የሚያገኙት ትርፍ ብቻ የሚያስገኘው ጥቅም ዝቅተኛ ለነበረው ምርት ከሚያወጡት ወጪ ይበልጣል፡፡ ይህ ለንግድ ተሽከርካሪ ማናጀሮች እጅግ ጠቃሚ ነው” ብለዋል።


ህፃናት አካላዊና አዕምሮአዊ ጤንነታቸው ተጠብቆ የሚያድጉበትን መንገድ የሚያመቻችና በህፃናት አያያዝ፣ አመጋገብ እንዲሁም የህፃናትን ባህርይ በመረዳትና በመንከባከብ ላይ ያተኮረ ዘመናዊ የህፃናት አስተዳደግ ስልጠና የወሰዱ 55 ሞግዚቶችን ማስመረቁን “እሹሩሩ” የሞግዚቶች ማሰልጠኛ ተቋም አስታወቀ፡፡
ድርጅቱ ለመጀመሪያ ጊዜ አሰልጥኖ ያስመረቃቸው እነዚሁ ሞግዚቶች፤ በህፃናት እንክብካቤና አስተዳደግ ላይ በቂ እውቀት ኖሮአቸው፣ ህፃናቱን በአግባቡ ለማሳደግ የሚያስችላቸውን ሥልጠናና እውቀት ያገኙ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ በህፃናት አስተዳደግ ላይ ጥናት አካሂደው ወደ ሥራው መግባታቸውን የሚናገሩት የድርጅቱ ኃላፊዎች፤፤ በአገራችን ህፃናትን የሚንከባከቡ ሞግዚቶች በእውቀት የታገዘ ልምድ ስለሌላቸውና ሳይንሳዊ የሆነ ሥልጠና ስለአልወሰዱ በህፃናቱ አስተዳደግና የወደፊት ህይወት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደራቸውን ገልፀዋል፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍም ሞግዚቶቹን አሰልጥነው ወደ ሥራ ለመሠማራት ማቀዳቸውንና የመጀመሪያ ዙር ሰልጣኞችን ማስመረቃቸውንም ገልፀዋል፡፡

በእናቶችና ህፃናት ጤና፣ በተላላፊ በሽታዎች፣ በንፁህ የመጠጥ ውሃ፣ በህክምናና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በስፋት በመንቀሳቀስ የሚታወቀው አምሬፍ ኢትዮጵያ (Amref Health Africa በሚል ስያሜውን መቀየሩንና አዲስ አበባን ጨምሮ በአማራ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልል ሥራውን በስፋት እንደሚያከናውን አስታወቀ፡፡
የድርጅተ ካንትሪ ዳይሬክተር ዶ/ር ፍሎሬንስ ቲሙ ሰሞኑን ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ ድርጅቱ በእናቶችና ህፃናት ጤና፣ በንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና በአቅም ግንባታ ሥራዎች ላይ በስፋት ይንቀሳቀሳል፡፡
የድርጅቱ ዓመታዊ በጀት ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነ የጠቆሙት ዶክተሯ፤ ከዚህ ውስጥ 7 በመቶ የሚሆነው ድርጅቱ በአገሪቱ ለሚያከናውናቸው የጤናና የልማት ተግባራት እንደሚውል ተናግረዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ1998 ተመዝግቦ በኢትዮጵያ ሥራ የጀመረው አምሬፍ ኢትዮጵያ ሰሞኑን ስያሜውን ወደ አምሬፍ ኸልዝ አፍሪካ  በመቀየር ሥራውን በስፋት መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡

Saturday, 07 June 2014 13:31

የፖለቲካ ጥግ

ገንዘብ ሊገዛው የሚችል ምርጥ መንግስት አለን፡፡
ማርክ ትዌይን
ሰዎች መላዕክት ቢሆኑ ኖሮ መንግስት የሚባል አያስፈልገንም ነበር፡፡
ጄምስ ማዲሰን
ገንዘብና ሥልጣን ለመንግስት መስጠት፣ ውስኪና የመኪና ቁልፍ ለታዳጊ ወጣት እንደመስጠት ነው፡፡
ፒ.ጄ ኦ‘ሮዩርኬ
ተጨቋኞች በተወሰኑ ዓመታት አንዴ የትኛው የጨቋኝ መደብ በፓርላማ ውስጥ እንደሚወክላቸውና እንደሚጨቁናቸው እንዲወስኑ ይፈቀድላቸዋል፡፡
ቭላድሚር ሌኒን
መንግስት ለችግሮች የሚሰጠው መፍትሄ የችግሮቹን ያህል የከፋ ነው፡፡
ሚልተን ፍሪድማን
ምርጡ መንግስት ራሳችንን ማስተዳደር የሚያስተምረን ነው፡፡
ጆሃን ዎልፍጋንግ ቮን ገተ
ከሁሉም ምርጡ መሳሪያ እውነት ናት፡፡ የመንግስት ህንፃ ውስጥ ግን ምንም አይነት መሳሪያ ይዞ መግባት እንደማይቻል ሁላችንም እናውቃለን፡፡
ያልታወቀ ሰው የተናገረው
ከላይ ሆኖ የሚመለከተን ነገር እንዳለ አምናለሁ፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ መንግስት ነው፡፡
ውዲ አለን
እጅግ በርካታ ህጎች ያሏት አገር፣ እጅግ በርካታ ችግሮች ያሉባት አገር ናት፡፡
ኮድሩት ማግሄሩ
ጠበቆች፣ ዳኞችና ፖለቲከኞች በሞሉበት የፍርድ ቤት ህንፃ ውስጥ አስርቱ ትዕዛዛት ለምን እንደማይጠለፍ ታውቃላችሁ? ወዳጃዊ ያልሆነ የስራ ድባብ ስለሚፈጥር ነው፡፡
አንክል ቦብ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በነገው ዕለት በካይሮ በሚከናወነው የአዲሱ የግብጽ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ በዓለ ሲመት ላይ እንደሚገኙ አህራም ኦንላይን ዘገበ፡፡ኢትዮጵያና ግብጽ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ግንኙነታቸው መሻከር ከጀመረ አንድ አመት ያህል እንዳለፈው የጠቀሰው ዘገባው፣ ከዚያ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ካይሮን ሲጎበኙ ይህ የመጀመሪያው እንደሚሆን አስረድቷል፡፡
የቱርኩን የዜና ተቋም አናዶሉ ኒውስ ኤጀንሲን ጠቅሶ አህራም ኦንላይን ከትናንት በስቲያ እንደዘገበው፣ የግብጽ መንግስት ባለፈው ሳምንት በአገሪቱ በተከናወነው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አሸናፊ በሆኑት አል ሲሲ በዓለ ሲመት ላይ እንዲገኝ፣ ለኢትዮጵያ መንግስት በላከው ግብዣ መሰረት ነው፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የተመራ የከፍተኛ ባለስልጣናት ልኡክ በበዓሉ ላይ የሚገኘው፡፡
የከፍተኛ ባለስልጣናቱ በበዓለ ሲመቱ ላይ መገኘት፣ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን እየሻከረ የመጣ ግንኙነት በማሻሻል ረገድ የራሱን ሚና ሊጫወት እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡
የግብጽ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ኮሚሽን ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው የምርጫ ውጤት መሰረት፣ የቀድሞው የአገሪቱ የጦር ሚኒስትር አል ሲሲ በምርጫው 96 ነጥብ 9 በመቶ ድምጽ በማግኘት የፕሬዚዳንትነት ስልጣኑን በይፋ በሚረከቡበትና በሄሊፖሊስ በሚገኘው ብሄራዊ ቤተመንግስት በሚከናወነው በዓለ ሲመት ላይ የ22 አገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የምርጫ ውጤቱ ይፋ መደረጉን ተከትሎ፤ የተመድ ዋና ጸሃፊ ባንኪ ሙን፣ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ ኢራንና ሩሲያን ጨምሮ የተለያዩ አገራት ለተመራጩ ፕሬዚዳንት የደስታ መልዕክቶቻቸውን ያስተላለፉ ሲሆን፤ የቀድሞው የግብጽ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ ሙርሲ ደጋፊ የሆነው ‘ዘ ናሽናል አሊያንስ ቱ ሰፖርት ሊጂቲሜሲ’ የተባለው ቡድን በበኩሉ፣ ባለፈው ረቡዕ በሰጠው መግለጫ፣ ህዝቡ በአል ሲሲ መሾም ላይ ያለውን ተቃውሞ አደባባይ ወጥቶ እንዲገልጽ ይፋዊ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የሰንበቴ ማህበራቱ በደብረ ምጥማቅ ሰአሊተ ምህረት ቅድስት ማርያም እና ክርስቶስ ሰምራ ካቴድራል አስተዳደር ላይ ያለንን የመልካም አስተዳደር ቅሬታ ለቅዱስ ፓትርያርኩ እንዳናቀርብ ተከለከልን፤ ለእንግልትም ተዳርገናል አሉ፡፡
በቤተክርስቲያኑ የሚገኙ የሰባት ሰንበቴ ማህበራት ጥምረት ተወካዮች ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ ከሌላ ደብር ተቀይረው በመጡ የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳደሮች እየተፈፀመብን ነው የሚሉትን በደልና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለቅዱስ ሲኖዶስና ለፓትርያርኩ ለማቅረብ ከ12 ጊዜ በላይ ቢመላለሱም ጉዳያቸው እልባት አላገኘም፡፡
የማህበሩ አባላትና የደብሩ አጥቢያ ምዕመናን የሚያቀርቡት ጥያቄ በአግባቡ ለፓትርያርኩ አልደረሰም የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ የሰንበቴ ማህበራቱ የመሬት ወረራ እያካሄዱ ነው የሚል የተሳሳተ መረጃ ለፓትርያርኩ መድረሱን ተከትሎ “አስቁሟቸው” የሚል ትእዛዝ መተላለፉን፤ ይህን ትዕዛዝ ተገን በማድረግም ያልተስማሙበትንና የቤተክርስቲያኒቱን ቃለ አዋዲ ያልጠበቀ መመርያ አምጥተው በ3 ቀን ውስጥ ፈርሙ በማለት  የደብሩ ኃላፊዎች እንዳስጨነቋቸው ገልፀዋል፡፡
መመሪያውን በ3 ቀን ውስጥ ፈርሙ የሚለውን ትዕዛዝ በመቃወምም ረቡዕ ግንቦት 27 ቀን 2006 ዓ.ም ለቅዱስ ሲኖዶስ ቅሬታ ለማቅረብ ከ400 በላይ ምዕመናን ወደ ፅ/ቤት ቢያመሩም በደህንነትና በፖሊስ አባላት እንዳይገቡ መከልከላቸውንና የፓትርያርኩ ዋና ፀሐፊ “ከእናንተ መሃል 10 ሰው ብቻ በነገው እለት (ሃሙስ) ጥያቄያችሁን ይዞ ይቅረብ” በሚል እንዳሰናበቷቸው የቅሬታ አቅራቢዎቹ ተወካዮች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
በቀጠሮው መሰረት ከትናንት በስቲያ ሃሙስ፣ ለፓትርያርኩ የሚቀርብ የአቤቱታ ደብዳቤ ይዘው ቢሄዱም  የሚያስተናግዳቸው አካል ማጣታቸውን ቅሬታ አቅራቢዎቹ ጠቁመው፣ በተደጋጋሚ የፓትርያርኩ በር ቢዘጋብንም ቤተክርስቲያኒቱን ከጥፋት ለመታደግ አሁንም በድጋሚ ጥያቄያችንን ይዘን እንቀርባለን ብለዋል፡፡