Administrator

Administrator

  የዛሬ 8 ዓመት ኦባማ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው መመረጣቸውን ተከትሎ በመላው ዓለም ዝናቸው በእጅጉ ናኝቶ ነበር፡፡ ለዚህም ይመስላል ከኬንያ የአባታቸው የትውልድ መንደር አንስቶ እስከ አየርላንድ ገጠር ድረስ ስማቸው ታዋቂ የሆነው፡፡ በተለይ በኬንያ በእሳቸውም ስም ያልተሰየመ ነገር ያለ አይመስልም፡፡ የአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች፣ ኪዮስኮች፣ መደብሮች… ኧረ ህፃናትም አልቀሩ፡፡ ሁሉም የባራክ ኦባማን ስም የታደሉ ይመስላሉ፡፡ አንዳንድ በኦባማ ስም የተሰየሙ ነገሮች ደግሞ አግራሞትን የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ ራሷ ኬንያ ኦባማ መባል ነው የቀራት፡፡ እስቲ Tuko.co.ke የተሰኘው ድረ-ገፅ በኦባማ ስም የተሰየሙ ነገሮችን በተመለከተ ያወጣቸውን መረጃዎች እናስቃኛችሁ፡፡

                “ኦባማ ተራራ”

   አንቲጓ የተባለችው የኬንያ ግዛት በኦባማ ስም የሚሰየም ትንሽ ነገር ያጣች ትመስላለች፡፡ በግዛቱ ያለ አንድ ትልቅ ተራራ በፕሬዚዳንቱ ስም ተሰይሟል፡፡ “ኦባማ ተራራ” ይባላል፡፡ “ቦZ ፒክ” በአንቲጓ በጣም ረዥሙ ተራራ ሲሆን ኦባማ የሚለው ስም የተሰጠው እ.ኤ.አ በ2009 በፕሬዚዳንቱ የልደት ቀን ነበር ተብሏል፡፡

            “ኦባማ ሹሩባ”

     ኦባማ ፀጉራቸውን ሹሩባ ተሰርተው ባያውቁም በአያቶቻቸው መንደር በኮጌሎ ግን አንድ የሹሩባ አሰራር በሳቸው ስም ተሰይሟል - “ኦባማ ሹሩባ” ተብሎ፡፡ አንዳንዶች “የወንዶች የፀጉር አቆራረጥ እንኳን ቢሆን ምንም አልነበር፤ ክፋቱ ግን ይሄ የፀጉር አሰራር ስታይል ያለው በሴቶች የውበት ሳሎን ነው…” ሲሉ ቅሬታቸውን ይገልፃሉ፡፡ የሰማቸው ወይም የሚሰማቸው ግን ያለ አይመስልም፡፡ በነገራችን ላይ በመዲናችን በሚገኙ የወንዶች ፀጉር ሴቶች የኦባማን ምስል (ፖስተር) በተለያዩ የፀጉር አቆራረጥ ስታይሎች ማየት የተለመደ ነው፡፡

             የአይሪሾቹ አልባሰም?! (“ኦባማ ነዳጅ ማደያ”)

      የኬንያውያን እንኳ እሺ… ምክንያት አላቸው፡፡ የአገራችን ልጅ ነው ቢሉ ያምርባቸዋል፡፡
የሚያስገርሙት አይሪሾች ናቸው፡፡ ድንገት ተነስተው እኮ ነው የኦባማን ስም የሙጥኝ ያሉት፡፡
ያውም በአየርላንድ እልም ያለ ገጠር መሃል፡፡ በዱብሊን እና ሊመሪክ መሃል ኦፋሊ ውስጥ የሚገኘው የነዳጅ ማደያ አሁን በይፋ በአሜሪካ ፕሬዚዳንት ስም ተሰይሟል፡፡ “ኦባማ ነዳጅ ማደያ” ነው የሚባለው፡፡ ይሄን እንኳን ራሳቸው ኦባማም የሚያውቁት አይመስለኝም፡፡

               የዬል ዩኒቨርሲቲ ሳይንቲስቶችስ?

   በአሜሪካ የሚገኘው የዬል ዩኒቨርሲቲ ሳይንቲስቶች ደግሞ ምን እንዳሰቡ አይታወቅም፡፡ ከምድረገፅ ጠፍቷል የሚባል ፍጡር በስማቸው ሰይመዋል ተብሏል፡፡ “ኦባማዶን” በዓለም ረዥሙ (አንድ ጫማ ርዝመት አለው) እንሽላሊት ሲሆን እንደ በቆሎ የተደረደሩ ጥርሶች እንዳሉት ሳይንቲስቶቹ ገልፀዋል፡፡ ለዚህ ተሳቢ ፍጥረት ስሙን ያወጡለት ሳይንቲስቶች እ.ኤ.አ በ2012 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፣ ኦባማ ማሸነፋቸው በይፋ እስኪነገር ድረስ ዝም ብለው ሲጠብቁ ነበር፡፡ ለምን ቢባል… ድንገት ኦባማ ቢሸነፉ እንደ እንሽላሊቱ “ከምድረ ገፅ የጠፉ” የሚል በአግቦ ወይም በሾርኒ የተነገረ ስድብ እንዳይመስልባቸው ስለፈሩ ነበር፡፡

            አሁንስ አበዙት ያሰኛል!
    ይሄኛውስ ደስ አይልም፡፡ ኬንያውያን መካሪ የላቸውም እንዴ? ያሰኛል፡፡ የፀጉር ትሎች የተገኙት የኦባማ አባት የትውልድ ስፍራ በሆነችው ኮጌሎ መሆኑን የጠቆመው Tuko.co.ke የተሰኘው ድረ-ገፅ፤ እንደተለመደው አዲስ የተገኘው ትል በፕሬዚዳንቱ ስም ተሰየመ ይለናል፡፡ ለአሜሪካው መሪ ክብር ሲባልም የትሉ ሳይንሳዊ ስም “Paragordius Obamai” ተብሏል፡፡ ግን አይገርምም… የኦባማ ስም?! (ለአፍ ስለሚመች ይሆን?)   

 የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ከሆኑ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የአባታቸውን የትውልድ አገር ኬንያን በመጐብኘት ላይ የሚገኙት ባራክ ኦባማ፤ ትላንት Air Force One በተሰኘው ልዩ አውሮፕላናቸውን ኬንያ ገብተዋል፡፡
ከዋይት ሃውስ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ Air Force One የአውሮፕላን ስም አይደለም፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንትን የሚጭን ማንኛውም የአሜሪካ አየር ሃይል አውሮፕላን በዚህ ስም ነው የሚጠራው፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት በወታደራዊ አውሮፕላን  ላይ ከተሳፈሩ “Army One” ተብሎ ይጠራል፡፡ በልዩ ሄሊኮፕተራቸው ላይ ከተሳፈሩ ደግሞ አውሮፕላኑ “Marine one” ይባላል፡፡
ፕሬዚዳንቱ Air Force One በሚል ስያሜ የሚበሩ በልዩ ትእዛዝ የተሰሩ 2 ቦይንግ 747 ጀቶች ያሏቸው ሲሆን እኒህ ጀቶች የባለ 6 ፎቅ ህንፃ ከፍታ አላቸው ተብሏል፡፡
“Air Force One” በከፍተኛ ፍጥነት ሲበር በሰዓት 1ሺ 126 ኪ.ሜ ገደማ መጓዝ የሚችል ሲሆን አውሮፕላኑ በ45ሺ 100 ጫማ ከፍታ ላይ ነው የሚበረው፡፡ ተመሳሳይ የተጓዦች ቦይንግ 747 አውሮፕላን የሚበረው በ30ሺ ጫማ ገደማ ከፍታ ላይ ነው፡፡
አውሮፕላኑ አንዴ ነዳጅ ጢም ተደርጐ ከተሞላ (Full tank) የዓለምን አጋማሽ ማካለል የሚችል ሲሆን ዳግም ለመሙላት መሬት ላይ ማረፍ አያስፈልገውም፡፡ በአጋማሽ አየር ላይ ሆኖ ነዳጅ የመሙላት አቅም አለው፡፡ ከዚያም ይሄ ነው ለማይባል ጊዜ በአየር ላይ ሊቆይ ይችላል፡፡
የፕሬዚዳንቱ አውሮፕላን የአየር ጥቃት መቋቋም ይችላል፡፡ የእሳት ብልጭታ በመርጨት ሚሳየሎችን ከዒላማቸው ውጭ ከማድረጉም በተጨማሪ የጠላት ራዳርንም አገልግሎት አልባ ያደርጋል፡፡ ሌሎችም ለደህንነት ሲባል በምስጢር የተያዙ ገፅታዎች እንዳሉት ታውቋል፡
ግዙፉ የፕሬዚዳንቱ የአየር ላይ ቢሮ በሚል የሚታወቀው Air Force One  ለሰራተኞች፣ ለኃላፊዎችና ለእንግዶች የመኖሪያ ክፍሎች አሉት፡፡
በአውሮፕላኑ ውስጥ እጅግ ከሚያስደንቁ ገፅታዎች መካከል ብዛት ያላቸው የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ይጠቀሳሉ፡፡ አውሮፕላኑ ፕሬዚዳንቱንና ሰራተኞቹን በአየር ላይ ሆነው ከመላው ዓለም ጋር መገናኘት የሚያስችላቸው አስተማማኝ የስልክ መስመር ያለው ነው፡፡ ከተለያዩ የቢሮ እቃዎች በተጨማሪም 85 ስልኮች፣ 19 ቴሌቪዥኖች፣ ፋክስ ማሽኖችና ሬዲዮኖች ተገጥሞለታል፡፡
የፕሬዚዳንቱ አውሮፕላን 96 ተጓዦችና የበረራ ሰራተኞችን የመጫን አቅም አለው፡፡

                ለኦባማ በወንድና በሴት መካከል ያለውን ልዩነት እናሳያለን ይላሉ
  የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በስልጣን ዘመናቸው 11ኛ ሰዓት ላይ የፈቀዱት የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ በአገራቸው ተቃውሞ አላስነሳባቸውም ይሆናል፡፡ በአባታቸው አገር ኬንያ ግን ተዝቶባቸው ነበር፡፡ ኦባማ በኬንያው ጉብኝታቸው የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ መብትን የተመለከተ ጉዳይ እንዳያነሱ የሪፐብሊካን ሊበርቲ ፓርቲ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ድጋፍ ሲያሰባስብ ነው የሰነበተው፡፡
የፓርቲው መሪ ቪንሰንት ኪዳላ፤ 1ሺ እርቃን ሴቶችና 4ሺ እርቃን ወንዶች በተቃውሞ ሰልፉ እንደሚሳተፉ አስታውቀው ነበር፡፡ በኦባማ የኬንያ ጉብኝት ዋዜማ ላይ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው የተቃውሞ ሰልፍ፤ ለፕሬዚዳንቱ የወንድና የሴትን ልዩነት ለማሳየት ያለመ ነበር ተብሏል፡፡በመጨረሻው ሰዓት ላይ ግን የእርቃን ተቃውሞው ለጊዜው መሰረዙን የሰልፉ አደራጅ አስታውቋል፡፡ የሪፐብሊካን ሊበርቲ ፓርቲ መሪ ቪንሰንት ኪዳላ፤ ከመንግሥት ቢሮ ስልክ ተደውሎ የእርቃን ተቃውሞ ሰልፉን እንዲሰርዙ መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡
“ስልክ ደዋዩ፤ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዩሁሩ ኬንያታ ከባራክ ኦባማ ጋር በግብረ ሰዶማውያን መብት ዙሪያ ለመወያየት እንዳላቀዱና የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻን እንደማይደግፉ ገልጾልኛል” ሲሉ የፓርቲው መሪ ሚዲያ ተናግረዋል፡፡ከብሄራዊ ደህንነት ኮሚቴም ስልክ ተደውሎ፣ የተቃውሞ ሰልፉ እንዳይደረግ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ኪዳላ ገልፀዋል፡፡ ማንነቱን ያልገለፀው ደዋይ፤ “የተቃውሞ ሰልፉን ማድረግ የሽብር ጥቃት ከመፈፀም እኩል ነው” ብሎኛል ሲሉ የፓርቲው መሪ አስረድተዋል፡፡
የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻን በመቃወም ሊካሄድ ታስቦ የነበረው ሰልፍ ለጊዜው ይሰረዝ እንጂ ከእነአካቴው እንደማይቀር አዘጋጆቹ አስታውቀዋል፡፡ ፓርቲው በሰጠው መግለጫም፤ ሰልፉ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል ነው ያለው፡፡ ጊዜውን ግን አልገለፀም፡፡ ለማንኛውም ኦቦማ አምልጠዋል!!

 “ከልጅ ልጅ ቢለዩ…”
የኦባማ ጉብኝት ኬንያንና ኢትዮጵያን ከምንጊዜውም በላይ ቁጭ ብድግ እንዳሰኛቸው እያየን ነው፡፡ የኬንያ ጋዜጦች እንደዘገቡት፤ ናይሮቢን ጨምሮ ፕሬዚዳንቱ ይጎበኙዋቸዋል የተባሉ ከተሞች ሁሉ ሲታጠቡና ሲቀባቡ ነው የሰነበቱት፡፡ በናይሮቢ ጐዳና የኦባማ ትልቅ ምስል ተሰቅሎ ይታያል፡፡የአሜሪካ የፀጥታና ደህንነት ሃይል ኬንያን የመፈተሽና ከሽብር ጥቃት ነፃ የማድረግ እንቅስቃሴ የጀመረው ከሁለት ሳምንት በፊት ነው፡፡ 8 ሄሊኮፕተሮች ከኦባማ ቀድመው ኬንያ መግባታቸው ይታወቃል፡፡ በነገራችን ላይ… ከተማም… ገፅታም… ፀጥታም ያበላሻሉ ተብለው የታሰቡ… ከ3ሺ በላይ የናይሮቢ የጎዳና ተዳዳሪዎች ተሰብስበው የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት ግቢ ውስጥ እንደከተሙ ዘ ስታንዳርድ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ ከጐዳና ተዳዳሪዎቹ ውስጥ ቢያንስ ግማሾቹ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ነው ተብሏል፡፡ የማን ሃሳብ ወይም እቅድ እንደሆነ ባይታወቅም ከ3ሺ በላይ እንደሚሆኑ የተገመቱት የጎዳና ተዳዳሪዎች ት/ቤቱ ውስጥ ተከርችመው አይቀመጡም፡፡ ጊዜያዊ የተሃድሶ ማዕከል እንደሚገቡ ተነግሯል፡፡ የናይሮቢ ከተማ ገዢ ኢቫንስ ኪዴሮ ስለ ፕሮጀክቱ ሲናገሩ፤ “የተሃድሶ ፕሮግራሙ የምግብ፣ የልብስና የመጠለያ አቅርቦትን ይጨምራል፡፡ በጐዳና ላይ ከለመዱት የተሻለ ምቾት ያገኛሉ” ብለዋል፡፡ የናይሮቢ ከተማ መስተዳድር ሰዎቹን ከጎዳና ላይ ሰብስቦ ለማንሳት 40ሚ. የኬንያ ሽልንግ መቀበሉን ኪዴሮ ገልፀዋል፡፡ የገንዘቡ ምንጭ ባይጠቀስም ከኦባማ መንግስት ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡ በተሃድሶው ፕሮግራም የጎዳና ተዳዳሪዎቹን ከእነአካቴው ከጐዳና ህይወት የማላቀቅ ዘላቂ ዕቅድ ይኑር አይኑር አልታወቀም፡፡ ቢሆንላቸውማ በማን ዕድላቸው! “የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች…” ብትሉኝ አመሰግናችሁ ነበር፡፡ ለመሆኑ የእኛስ የጐዳና ተዳዳሪዎች የት ገቡ? ኦባማ መቼም አይረሷቸውም ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ “ከልጅ ልጅ ቢለዩ…” ነው ነገሩ፡፡

 አንዳንዴ ፈረንጆችን ከእኛ የሚለያቸው ስለ ሰማይ ቤትም ለመቀለድ መቻላቸው ነው፡፡ የሚከተለው ተረት አንድ ምሣሌ ነው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ጠበቃ ይሞትና ወደ ሰማይ ቤት ይሄዳል፡፡ በገነት በራፍ ላይ ቅዱስ ጴጥሮስ ያገኘዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ የሁሉም ሰው ኃጢያት መዝገብ በእጁ ነውና የጠበቃውን ስም ፈልጎ ያገኘዋል፡፡ ከዚያ የሰራውን ኃጢያት ዝርዝር ያያል፡-
1ኛ. አንድን ከአየር መበከል ጋር ተያይዞ የተከሰሰን ሰው በመከላከል ጥብቅና ቆሟል
2ኛ. ደህና ገንዘብ ይከፈልሃል ስለተባለ ብቻ በግልፅ በነብስ ግድያ የተከሰሰን ነብሰ ገዳይ በመከላከል ጥብቅና ቆሟል፡፡
3ኛ. አብዛኛዎቹን የጥብቅና ደምበኞቹን ከልኩ - በላይ አስከፍሏል፡፡
4ኛ. አንዲትን የዋህ ሴት ለሌሎች ወንጀለኞች ጥፋት ማምለጫ ሰበብ እንድትሆን በመፈለግ፤ እንዲፈረድባት አድርጓል፡፡
ጠበቃው ይህን ክስ በመቃወም ተሟገተ፡፡ ክሶቹን በሙሉ ተቀበለና አንድ መሟገቻ ግን ይዞ ቀረበ፡-
“አንድ የምፅዋት ስጦታ ለነዳያን በህይወቴ አንዴ ሰጥቻለሁ” አለ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ መዝገቡን አየና፤
“አዎን አዎን ስምህ አለ፡፡ ለአንድ ጎዳና ተዳዳሪ አሥር ሳንቲም ሰጥተሃል! ለአንድ ሊስትሮ ደግሞ አንድ ሳንቲም ሰጥተሃል! ትክክል ነኝ?” ጠበቃው ግራ የተጋባ መልክ እየታየበት፤ “አዎን!” አለ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ አጠገቡ ወዳለው መልዐክ አየ፡፡
“ይሄን ልጅ አሥራ አንድ ሳንቲሙን ስጠውና ወደ ገሀነም አስገባው!” አለው፡፡
*       *     *
በሰው ላይ ግፍ ማስፈረድ፣ አላግባብ ገንዘብ መዝረፍ፣ የአብዬን እከክ ወደ እምዬ ልክክ ማድረግ፣ የማታ ማታ ማስጠየቁ አይቀሬ ነው፡፡
በርካታ ሌብነት፣ በርካት ግፍ፣ በርካታ የማጭበርበር ተግባር ፈፅመን ስናበቃ፣ ቅንጣቷ ደግነቴ ትመዝገብልኝ ማለት ግብዝነት እንጂ ብልጠት አይሆንም፡፡ ዕድሜያችንን ሙሉ የሰራነው ተንኮል እየታወቀ፣ አንድ ቀን የመፀወትኩትስ? ብሎ መከራከር ዐይናውጣነት ከመሆን በቀር ከፍርድ አያድንም! ዐረቦች “ሌባው በሰረቀው ሳይሆን ሳይሰርቅ በተወውም ይታወቃል” ይላሉ፡፡
የሀገራችን ፖለቲከኞች ነገር ለተፎካካሪ የሚመችና የተጋለጠ ነው፡፡ “ብቅል አስጥታ ነበር፤ እሽ ብትል እንዴት ጥሩ ነበር” ተብሎ ሁሌም የሚታለፍ ፌዝ መሳይ ነው፡፡
የሀገራችን ኢኮኖሚም ጥቂቶች ከዝሆን ጥርስ (Ivory - Power) ላይ ሆነው የሚነጩበት፣ ብዙሃኑ ትቢያ ላይ የሚተኙበት ዓይነት እየሆነ ነው፡፡ ቱርኮች “አንዱ በይ አንዱ የበይ ተመልካች የሆነ ዕለት የዓለም መጨረሻ መጣ ማት ነው” ይላሉ፡፡ እንደዚያም ቢባል አይገርምም፡፡
የመሰረተ - ልማት ሂደቱ ደግ ነው ቢባልም፤ በዙሪያው ያለው ሙስና ቀለም በተቀባ ቆርቆሮ እንደሚሸፈን ቆሻሻ ቦታ ሊሆን አልቻለም፡፡ የሚያስደንቀው ሌቦቹ ቀና ብለው የሚሄዱበት፣ ተመዝባሪዎቹ የሚያቀረቅሩበት ሁኔታ መሆኑ ነው፡፡
የካፒታሊዝምን ነገረ - ሥራ ሳንመረምር ተቀብለን አንድምታዎቹ በፖለቲካችንም፣ በኢኮኖሚያችንም፣ በማህበራዊ ኑሯችንም ሲንፀባረቁ መማረራችን አስገራሚ ነው፡፡ ዲሞክራሲ ልሙጥ በሆነ ህብረተሰብ ውስጥ ፋይዳው ከሲታ ነው፡፡ የሚወዳደር፣ የሚፎካከር፣ የሚከራከር፣ የሚታገል፣ የሚደራደር ህብረተሰብን ግድ ይላል፡፡ “ሞኝ ሸንጎ ተሰብስ አገኘሽ፣ ቁርስ የሌለው ቡና አፈላሽ” አይነት ከሆነ ጉዞው ዘገምተኛ ይሆናል፡፡ ቢያንስ “ምቀኛ አታሳጣኝ” የሚለውን አገርኛ ባህላዊ አነጋገር ማስተዋል ይጠቅማል፡፡
ኃያላን መንግሥታት ዐይን ቢጥሉብን ፍፅምና ያለን ሊመስለን አይገባም፡፡ ሁሉም የየራሱ ገበታ እንዳለው አንርሳ፡፡ ዞሮ ዞሮ ራስን ችሎ እንደመገኘት የመሰለ ነገር የለም! “ተሸፋፍነው ቢተኙ፣ ገልጦ እሚያይ አምላክ አለ” የሚለውን ተረት አንርሳ፡፡ የኢኮኖሚ ችግርን መባባስ መደበቅ አይቻልም፡፡
ምድረ - በዳውን እየማተርን የበረሀ - ገነት (oasis) አየን ብንል ራስን ከማታለል በቀር ሌላም መላ የለው፡፡ ያለን አለን፣ የሌለን የለንም፡፡ የማንኖረውን ኑሮ እየኖርን ነው ብለን ብንኩራራና ብንቦተልክ ኑሯችን አጋልጦ እርቃናችንን ያሳየናል!
ሥራችን የሆነውን ኃላፊነት ሳንወጣ ከሁሉም በላይ ደግሞ፤ ሌላው ላይ መላከክ ሀገራችን በየጊዜው የሚያጋጥማት የፖለቲካ ጨዋታ ነው፡፡ ሁሉ ወቃሽ ሁሉ ከሳሽ ሆነና የየራሱን ግዴታ የሚያይበት ዐይን ጠፋ፡፡ “ሁሉም ፈረስ ላይ ከወጣ፣ ማን መንገድ ይምራ?” እንደሚለው የወላይትኛ ተረት ነው፡፡ የጠያቂው ብዛት የተጠያቂውን ደብዛ ያጠፋዋል! ይህ መፈተሽ ያለበት የፖለቲካ ችግራችን ነው፡፡
“ድመት አይጥ እንዲይዝ ተብሎ ችቦ አይበራለትም” የሚለው የጉራጌ ተረት ሁሉም በየራሱ ሥራ መፈተሽና መጠየቅ እንደሚገባው ነው የሚያሳየን፡፡ ይህንን ልብ እንል ዘንድ ልብ ይስጠን!

በደራሲና ጋዜጠኛ አንተነህ ይግዛው የተጻፈው “ባቡሩ ሲመጣ...” የተሰኘ የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ መጽሐፍ፣ የፊታችን አርብ ከ11፡30 ሰዓት ጀምሮ በኢትዮጵያ ሆቴል በሚከናወን ኪነጥበባዊ ዝግጅት ተመርቆ በገበያ ላይ ይውላል፡፡
የደራሲው ሁለተኛ ስራ የሆነው “ባቡሩ ሲመጣ...”  በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ 14 አጫጭር ልቦለዶችን በ210 ገጾች አካትቶ የያዘ ሲሆን፣ የመሸጫ ዋጋውም ለአገር ውስጥ 60 ብር፣ ለውጭ አገራት ደግሞ 16 ዶላር እንደሆነ ደራሲና ጋዜጠኛ አንተነህ በተለይ ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡
ጋዜጠኛና ደራሲ አንተነህ ይግዛው፣ የመጀመሪያ ስራው የሆነውን “መልስ አዳኝ” የተሰኘ የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ መጽሃፍ በ2003 ዓ.ም ለንባብ ያበቃ ሲሆን፤ በቅርቡም የወጎች ስብስብ መጽሃፍ ለህትመት እንደሚያበቃና በአንድ ታዋቂ ኢትዮጵያዊ የቢዝነስ ሰው የህይወት ታሪክ ዙሪያ የሚያጠነጥን መጽሐፍ እያዘጋጀ እንደሚገኝም ገልጿል፡፡
አንተነህ ይግዛው፣ ከሁለት አመታት በፊት በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በኩል ለአንድ አመት ከአራት ወራት የተላለፈውን “ስውር መንገደኞች” የተሰኘ ተወዳጅ ሳምንታዊ የሬዲዮ ድራማ በደራሲነትና በተዋናይነት ለአድማጭ ማቅረቡም ይታወሳል፡፡

የአቶ ካሣዬ ተክለአረጋይ ቤተሰቦች የተለያየ ቅፅ ኢንሳይክሎፒዲያ፣ የወንጀለኛ መቅጫ፣ የተጠቃለሉ ሕጐች፣ የሕግ መጽሔቶችና ጠቅላላ ዕውቀትን ጨምሮ 60 ያህል መፃሕፍትን ለዕውቀትና ትጋት አሰፋ ጎሳዬ የሕዝብ ቤተ-መፃሕፍት ሰሞኑን አበረከቱ፡፡
የሕግ ባለሙያ የነበሩት አቶ ካሣዬ ተክለአረጋይ በሕይወት ሳሉ ሲጠቀሙባቸው የነበሩ መፃሕፍትን ለቤተመፃሕፍቱ ያበረከቱት ልጃቸው አቶ ሰለሞን ካሣዬ ናቸው፡፡ የአቶ ሰለሞን ካሣዬ ባለቤት ወ/ሮ ምህረት ጌታቸው በወቅቱ እንደተናገሩት፤ “መጻህፍቱን እንድንሰጣቸው  የጠየቁ ግለሰቦች የነበሩ ቢሆንም መፃሕፍቱ የበለጠ ከአንባቢያን ጋር ሊገናኙ የሚችሉት በቤተ-መፃሕፍት ውስጥ ቢቀመጡ ነው በሚል እምነት አበርክተንላችኋል” ብለዋል፡፡

 በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ የሰሉ ሥነ ፅሁፋዊ ሂሶችን በማቅረብ የሚታወቀው ደራሲና ሃያሲ ዓለማየሁ ገላጋይ የጻፈው “ወሪሳ - የውድቀት ፈለጎች” የተሰኘ የረዥም ልብ ወለድ መፅሃፍ ሰሞኑን ለንባብ በቃ፡፡
አዲሱ ልብወለድ ለደራሲው 9ኛ መፅሃፉ ሲሆን በ49 ብር እየተሸጠ መሆኑ ታውቋል፡፡
ዓለማየሁ ከዚህ ቀደም “አጥቢያ”፣ “ቅበላ” እና “የብርሃን ፈለጎች” የተሰኙ ግሩም የረዥም ልብወለድ ስራዎችን ያሳተመ ሲሆን “ኩርቢት” የሚል የአጭር ልቦለድ መድበልም ለአንባቢያን አድርሷል፡፡ በደራሲ ስብሃት ገብረእግዚአብሄር ህይወትና ክህሎት ዙሪያ ያሰናዳው መፅሃፉም የሥነፅሁፍ  ምሁራንን ያነጋገረና ያሟገተ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ደራሲው፤ “ፍትህ”፣ “አዲስ ታይምስ” እና“ፋክት” በተሰኙ የህትመት ውጤቶች ላይ ያቀርባቸው በነበሩ ማራኪና ኮርኳሪ መጣጥፎቹ የብዙዎችን ቀልብ ለመሳብ ችሏል፡፡

 አምስት በአማርኛና አንድ በኦሮምኛ ቋንቋ የተፃፉ ስዕላዊ ባለቀለም የህጻናት መፃህፍት ተዘጋጅተው የታተሙ ሲሆን በነገው ዕለት ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ ከደንበል ህንፃ ፊት ለፊት፣ ከዴሉክስ ፈርኒቸር ጀርባ በሚገኘው ኢግሉ አይስክሬም ቤት ይመረቃሉ፡፡
የመፃህፍቱን ታሪኮች በመድረስ አዜብ ወርቁ፣ ዳንኤል ወርቁ፣ ሰላማዊት ሙሉጌታና ሲሳይ ተስፋዬ የተሳተፉ ሲሆን የስዕል ስራዎቹን የሰሩት ሰዓሊ ደረጄ ደምሴ፣ አርክቴክት አሃዱ አባይነህና የህፃናት ስዕል ባለሙያው ይስሃቅ ሳህሌ እንደሆኑ የመፃህፍቱ አሳታሚ “ሚዳቆ ፐብሊሺንግ” ለአዲስ አድማስ በላከው ጋዜጣው መግለጫ ጠቁሟል፡፡ የመፃህፍቱ ዋጋ (እያንዳንዱ) 29 ብር ነው ተብሏል፡፡ “ሚዳቆ  ፐብሊሺንግ” ዋነኛ ትኩረቱን በህፃናት መፃህፍት ላይ ያደረገ የህትመት ተቋም እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸው በማረሚያ ቤት የሚገኙት የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የቀድሞ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አንዷለም አራጌ በማረሚያ ቤት ሆነው ለሁለተኛ ጊዜ የፃፉት “የሀገር ፍቅር ዕዳ” መጽሐፍ ለንባብ በቃ፡፡
አቶ አንዷለም አራጌ ከዚህ ቀደም “ያልተሄደበት መንገድ” የተሰኘ መጽሐፍን ለአንባቢያን ያደረሱ ሲሆን “የሀገር ፍቅር እዳ ከቀሳ ጐንደር እስከ ቃሊቲ አስር ቤት” የተሰኘው አዲሱ መጽሐፋቸው በ32 ምዕራፎች ተከፋፍሎ፣ በ400 ገፆች የቀረበ ነው፡፡ ዋጋው 100 ብር ነው፡፡