Administrator

Administrator

• 34ኛው የቤተ ክርስቲያኒቱ አጠቃላይ የሰበካ ጉባኤ ስብሰባ ሰኞ ይጀመራል

    የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር ማዕከል የሆነው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፣ የሁለትዮሽ የሒሳብ አመዘጋገብ ሥርዐትን በመከተል አሠራሩን ዘመናዊ ማድረጉ ተገለጸ፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ፣ ዘመናዊውን የሁለትዮሽ የሒሳብ አሠራር /Double entry accounting system/ እንድትከተል፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት በባለሞያዎች ያካሔደውን የፋይናንስ ፖሊሲና ማኑዋል ጥናት በቋሚ ሲኖዶስ በማስወሰን ባሳለፍነው የበጀት ዓመት ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩ ታውቋል፡፡ በዚህም “ቤተ ክርስቲያኒቱ ዘወትር ስትወቀስበትና ስትተችበት የነበረውን፣ ለቁጥጥር የማያመቸውንና በሕግም ተቀባይነት የሌለውን የነጠላ ሒሳብ አሠራር” ጽ/ቤቱ ማስቀረቱ ተገልጧል፡፡በፖሊሲው ላይ የተመሠረቱና ከማኑዋሉ ጋር የሚስማሙ የሒሳብ ሰነዶችና ቅጻቅጾች ተዘጋጅተው ጥቅም ላይ የዋሉ ሲሆን የጽ/ቤቱ የሒሳብና በጀት መመሪያ ሠራተኞችም ለትግበራው የሚያስፈልጉ ልዩ ልዩ ሥልጠናዎችን እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡
የተቋሙን አጠቃላይ ሀብትና ዕዳ በማወቅ፣ የፋይናንስና የንብረት አጠቃላይ አስተዳደሩንና እንቅስቃሴውን ለቁጥጥር ግልጽ ለማድረግ፤ ተፈላጊውን መረጃ በሪፖርት በማውጣትና በመተንተን ተገቢ ውሳኔ ለመስጠት ምቹ የሆነውን የሁለትዮሽ አመዘጋገብ ተግባራዊነት ተከትሎ፣ ጽ/ቤቱ ማዕከላዊ የሒሳብ አሠራር በመከተሉ፣ ወጪ ቆጣቢና ውጤታማ ሥራ ለማከናወን መቻሉ ተገልጧል፡፡ ከ16 የጽ/ቤቱ መመሪያዎችና ድርጅቶች፣ በጀታቸውን በራሳቸው እያንቀሳቀሱ ሲሠሩ የነበሩት የሰባቱ የገቢና ወጪ ሒሳብ በአንድ ቋት ተጠቃልሎ በሁለትዮሽ አመዘጋገብ ዘዴ በመሠራቱ ከሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ የተሠራው ሒሳብ ተመርምሮ ተዘግቷል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ በየጊዜው በሚታየው የዋጋ ግሽበት ተጎጂ ሆና የቆየች ሲሆን በሕጋዊና አስተማማኝ የግዢ ሥርዐት ዓመታዊ ግዥ በመፈጸም ዕቃዎች በመጋዘን እንዲቀመጡ በማድረግ፣ ከጉዳቱ ለመዳን መቻሉ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሠራተኞች የደመወዝ ክፍያ፣ የቤቶችና ሕንፃዎች ኪራይ አሰባሰብ በባንክ በኩል በማስፈጸም ሒደቱን ቀልጣፋ በማድረግ ውጤታማ ሥራ መሠራቱ ተመልክቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገር ውስጥና በውጭ ለተቋቋሙት 50 አህጉረ ስብከት የበላይ ሓላፊና አመራር ሰጪ የሆነው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋነኛ የፋይናንስ ምንጭ፣ ቤተ ክርስቲያኒቷ በየአጥቢያው ባቋቋመቻቸው ሰበካ ጉባኤያት የሚሰበሰበው የገንዘብ አስተዋፅኦ ነው፡፡ ከ34 ዓመታት በፊት በሳንቲም ደረጃ የተጀመረውና ለጽ/ቤቱ ፈሰስ የተደረገው የሰበካ ጉባኤያት ጠቅላላ ገቢ በበጀት ዓመቱ ከብር 125 ሚሊዮን በላይ መድረሱ የተገለጸ ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው ተመዝግቧል፡፡
የገቢዋ ዕድገት ቤተ ክርስቲያኒቷ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ልማታዊ አገልግሎቶቿን በራስዋ አቅም ለማከናወን እንደሚያስችላት የሚታመን ሲሆን ለዚህም ጠቅላይ ጽ/ቤቱ መከተል የጀመረው ዘመናዊው የሁለትዮሽ የሒሳብ አያያዝ በተዋረድ በሁሉም አህጉረስብከት እና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ተግባራዊ እንዲሆን ተጠይቋል፡፡ በቀጣዩ ሰኞ በጽ/ቤቱ አዳራሽ የሚጀመረውና ከ800 ያላነሱ የመላው አህጉረ ስብከት ልኡካን የሚሳተፉበት 34ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ በጉዳዩ ላይ ጠንካራ የጋራ አቋምና ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል፡፡

በጎጃም በርካታ ሰዎች እንዲረሸኑና በጅምላ እንዲቀበሩ አድርገዋል ተብሏል


በደርግ የአገዛዝ ዘመን ዜጎችን በመግደል፣ በማሰርና በማሰቃየት ተከስሰው ሞት የተፈረደባቸው አንድ ስማቸው ያልተገለጸ የቀድሞ የደርግ ባለስልጣን፤ በሆላንዷ ከተማ አምስቴልቪን በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኤንኤል ታይምስ የተባለው የአገሪቱ ድረገጽ ትናንት ዘገበ፡፡
በሆላንድ የሚገኘው የአለማቀፍ ወንጀሎች ምርመራ ቡድን አቃቤ ህግ፣ ግለሰቡ እ.ኤ.አ በ1978 ባስተላለፉት ትዕዛዝ፣ በጎጃም አካባቢ ታስረው የነበሩ በርካታ ሰዎች ተረሽነው አስከሬናቸው በጅምላ መቃብር እንዲቀበር ተደርጓል ማለታቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡ተጠርጣሪው ከሁለት ሳምንታት በፊት በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደዋሉ የጠቆመው ዘገባው፣ አምስቴልቪን ከተማ ውስጥ በሚገኘው የግለሰቡ መኖሪያ ቤት ውስጥ በተደረገ ፍተሻ የተለያዩ ማስረጃዎች የተገኙ ሲሆን በሄግ የሚገኘው ፍርድ ቤትም ከትናንት በስቲያ በዋለው ችሎት፣ ግለሰቡ ለ90 ቀናት በእስር ላይ እንዲቆዩ ወስኖባቸዋል ብሏል፡፡የሆላንድ ፖሊስ ግለሰቡ የተጠረጠሩባቸውን የወንጀል ድርጊቶች ስለመፈጸማቸው ምርመራ ማድረግ መጀመሩን ዘገባው ገልጾ፣ ፖሊስም የምስክሮችን ቃል መቀበሉንና ተጠርጣሪው ድርጊቶቹን ስለመፈጸማቸው ምስክርነታቸውን ከሰጡ ግለሰቦች አብዛኞቹ በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን  እንደሆኑ አስታውቋል፡፡ምስክሮቹ በሰጡት ቃል ግለሰቡ በጎጃም አካባቢ የደርግ ባለስልጣን ሆነው ባገለገሉባቸው አመታት የተጠቀሱትን የወንጀል ድርጊቶች ስለመፈጸማቸው ተናግረዋል ያለው ዘገባው፣ የሆላንድ የወንጀል ምርመራ ባለስልጣናትም ግለሰቡን ለሞት ቅጣት ያበቃቸውን የወንጀል ክስ የተወሰነ መረጃ ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት መረከቡን ገልጧል፡፡የአለማቀፍ ወንጀሎች ምርመራ ቡድን፣ በደርግ የአገዛዝ ዘመን በደብረ ማርቆስና በመተከል እስር ቤቶች ውስጥ የግድያና የስቃይ ድርጊቶችን በፈጸሙ ግለሰቦች ላይ ትኩረት በማድረግ ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝ ዘገባው አስታውቋል፡፡
61 አመታቸው እንደሆነ የተነገረላቸው እኒሁ ባለስልጣን፤ ከጥቂት አመታት ወዲህ ነዋሪነታቸውን በሆላንድ እንዳደረጉና የአገሪቱ ዜግነት እንደተሰጣቸው ያስታወሰው ዘገባው፣ ግለሰቡ በኢትዮጵያ ፍርድ ቤት በሌሉበት የእድሜ ልክ እስራትና የሞት ቅጣቶች እንደተጣሉባቸውም ገልጧል፡፡



 ታዋቂው የኮምፒውተርና የስማርት ፎን አምራች ኩባንያ አፕል በዊስኮንሲን ማዲሰን ዩኒቨርሲቲ ስም የተመዘገበን የፈጠራ ውጤት በሚያመርታቸው አይፎን 5 ኤስ፣ አይፎን 6 እና አይፎን  6 ፕላስ ሞባይሎቹ ውስጥ ተጠቅሞ በመገኘቱ እስከ 862 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ቅጣት ሊጣልበት እንደሚችል ተዘገበ፡፡ፕል ይህንን በዩኒቨርሲቲው ባለቤትነት ስር የሚገኝ የተለየ አይነት ፕሮሰሰር ከሞባይሎቹ በተጨማሪ በአንዳንድ የአይፖድ ምርቶቹ ውጥስ መጠቀሙን የጠቆመው የኢንዲፔንደንት ዘገባ፣ ኩባንያው ግን የዩኒቨርሲቲው የባለቤትነት መብት ውድቅ የተደረገ በመሆኑ ልወነጀል አይገባም ሲል ተከራክሯል፡፡
ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የማዲስን ፍርድ ቤት ግን ቴክኖሎጂውን የተጠቀምከው ባለቤቱን ሳታስፈቅድ ነው ሲል አፕልን ጥፋተኛ እንዳደረገውና ዊሊያም ኮንሊ የተባሉ ዳኛም አፕል በካሳ መልክ እስከ 862 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍል ሊፈረድበት እንደሚችል መናገራቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡

  - አማጺው የሰላም ስምምነቱን አፍርሼ ወደ ጦርነት እመለሳለሁ ብሏል
                 
    የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር የአገሪቱ ግዛቶች ቁጥር ከ10 ወደ 28 ማደግ አለበት ሲሉ ያስተላለፉት አወዛጋቢ ውሳኔ፣ ባለፈው ማክሰኞ ልዩ ስብስባውን ባከናወነው የአገሪቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተቀባይነት ማግኘቱን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
የፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር የግዛት ቁጥር ጭማሬ እርምጃ፣ ከአለማቀፉ ማህበረሰብ በስፋት ተቃውሞ ሲገጥመው እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ ኢጋድም የፕሪዚዳንቱ ውሳኔ በምክር ቤቱ ተቀባይነት ማግኘቱ በአገሪቱ ተቀናቃኝ ሃይሎች መካከል የተፈረመውን የሰላም ስምምነት የሚጻረር ነው ሲል እንደተቸው ገልጧል፡፡
ውሳኔው ተግባራዊ የሚሆነው የደቡብ ሱዳን ፓርላማ ካጸደቀው በኋላ እንደሚሆን የጠቆመው ዘገባው፣ አንዳንድ የአማጺው ሃይል አባላትም ውሳኔው የማይሻር ከሆነ የሰላም ስምምነቱን አፍርሰው ዳግም ወደ ትጥቅ ትግል እንደሚገቡ ማስጠንቀቃቸውን ገልጧል፡፡
የአማጺው ሃይል አመራሮች የፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬርን ውሳኔ ህገ መንግስታዊ ያልሆነና ባለፈው ነሃሴ ወር በሁለቱ ሃይሎች መካከል ከተፈረመው የሰላም ስምምነት ያፈነገጠ ነው ሲሉ መተቸታቸውን የዘገበው ደግሞ ሱዳን ትሪቢዩን ነው፡፡ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር ከሁለት ሳምንታት በፊት በአገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ በኩል የአገሪቱን ግዛቶች ቁጥር ለማሳደግ መወሰናቸውን ይፋ ማድረጋቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ በወቅቱም ይህን ያልተጠበቀ ውሳኔ ያስተላለፉት ለደቡብ ሱዳን ህዝቦች ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እንደሆነ ማስታወቃቸውን ገልጧል፡፡
ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር ደቡብ ሱዳን 10 ግዛቶች ያሏት አገር ናት የሚለውን የህገ መንግስቱ አንቀጽ 162 እንዲያሻሽሉ ለአገሪቱ ህግ አርቃቂዎች ጥሪ ማስተላለፋቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

በቦብ ላይ የተቃጣውን የግድያ ሙከራ ይተርካል
   በሬጌ ሙዚቃ ንጉሱ በቦብ ማርሊ የህይወት ታሪክ ላይ ተመስርቶ፣ በጃማይካዊው ደራሲ ማርሎን ጄምስ የተጻፈው “ኤ ብሪፍ ሂስትሪ ኦፍ ሰቨን ኪሊንግስ” የተሰኘ የልቦለድ መጽሃፍ “ማን ቡከር ፕራይዝ” የተባለውን አለማቀፍ ሽልማት እንዳገኘ ቢቢሲ ዘገበ፡፡
በ44 አመቱ ጃማይካዊ ደራሲ ማርሎን ጄምስ የተጻፈው መጽሃፉ፤ እ.ኤ.አ በ1970ዎቹ በቦብ ማርሊ ላይ የተቃጣ የግድያ ሙከራን መሰረት አድርጎ እንደተተረከ የጠቆመው ዘገባው፣ በወቅቱ በጃማይካ ስር ሰድዶ የነበረውን የፖለቲካ ሙስና እንደሚዳስስም ገልጧል፡፡
686 ገጾች ያሉት መጽሃፉ፣ ቦብ ማርሊ እ.ኤ.አ በ1976 በአገሪቱ መዲና ኪንግስተን በተዘጋጀ የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ የአገሪቱን የፖለቲካ ውጥረት ለማርገብ ሲል፣ ሙዚቃውን ለመጫወት ባሰበበት ወቅት የተደራጁ ወንጀለኞች በመኖሪያ ቤቱ ላይ ተኩስ እንደከፈቱና ድምጻዊው ለጥቂት ከሞት እንደተረፈ ይተርካል፡፡
ይህን ሽልማት በማግኘት የመጀመሪያው ጃማይካዊ የሆነው ደራሲው፣ ለህትመት ያበቃው ሶስተኛ መጽሃፉ በሆነው በዚህ ስራው 50 ሺህ ፓውንድ እና ዋንጫ እንደተሸለመ የተገለጸ ሲሆን፣ ደራሲው በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ ሚኒሶታ ግዛት የፈጠራ ጽሁፍ መምህር ሆኖ እየሰራ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡

    - ከግማሽ በላይ የሚሆነው የአለማችንን ሃብት የተያዘው፣ ከህዝቡ 1 በመቶ በሚሆኑ ባለጠጎች ነው
           - ግማሹ ድሃ የአለም ህዝብ፣ ከአለማችን ሃብት 1 በመቶ ብቻ ይደርሰዋል
  በያዝነው የፈረንጆች አመት 2015 ከግማሽ በላይ የሚሆነው የአለማችን ሃብት፣ ከአጠቃላዩ የአለም ህዝብ 1 በመቶ ያህል ብቻ በሚሆኑ የተለያዩ አገራት ባለጠጎች እጅ ውስጥ እንደሚገኝና በከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኘው ግማሹ የአለማችን ህዝብ ከአጠቃላዩ የአለም ሃብት 1 በመቶውን ብቻ እንደያዘ በጥናት መረጋገጡን ዘ ኢንዲፔንደንት ከትናንት በስቲያ ዘገበ፡፡ክሬዲት ሲዩሴ የተባለው ተቋም በ200 የተለያዩ የዓለማችን አገራት ዙሪያ የሰራውንና ባለፈው ማክሰኞ ይፋ ያደረገውን አለማቀፍ የሃብት ስርጭት አመታዊ ሪፖርት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ከአለማችን አገራት መካከለኛ ገቢ የሚያገኙ በርካታ ዜጎች ያሏት ቀዳሚዋ አገር ቻይና ሆናለች፡፡ከአለማችን ህዝብ 14 በመቶ የሚሆነው ወይም 664 ሚሊዮን ያህሉ፣ መካከለኛ ገቢ እንደሚያገኝ የጠቆመው ጥናቱ፣ 109 ሚሊዮን ያህል መካከለኛ ገቢ የሚያገኙ ዜጎች ያሏት ቻይና፣ አምና ቀዳሚ የነበረችውንና ዘንድሮ 92 ሚሊዮን መካከለኛ ገቢ የሚያገኙ ዜጎች እንዳሏት የተረጋገጠውን አሜሪካ ቀድማ የመጀመሪያውን ስፍራ መያዟን ገልጧል፡፡
እስካለፈው ግንቦት በነበሩት 12 ወራት በአለማችን የሃብት ክፍፍል ረገድ የሚታየው ክፍተት ክፉኛ መባባሱን የገለጸው የተቋሙ ሪፖርት፣ ከአለማችን ህዝብ 71 በመቶው ከ10 ሺህ ዶላር በታች፣ 21 በመቶው ከ10ሺህ እስከ 100 ሺህ ዶላር፣ 7.4 በመቶው ከ100 ሺህ እስከ  1 ሚሊዮን ዶላር፣ ቀሪው 0.7 በመቶ ህዝብ ደግሞ ከ1 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሃብት አለው ብሏል፡፡
የአለማችን አጠቃላይ ሃብት አምና ከነበረበት የ12.4 ትሪሊዮን ዶላር ቅናሽ በማሳየት፣ ዘንድሮ 250 ትሪሊዮን ዶላር ደርሷል ያለው ሪፖርቱ፣ ከዚህ ሃብት 16 በመቶውን የያዘችው ቻይና ስትሆን፣ አሜሪካ በ12 በመቶ፣ እንግሊዝ ደግሞ 4 በመቶውን ይዘዋል ብሏል፡፡

Saturday, 17 October 2015 08:52

ኢፕሊፕሲ - የሚጥል በሽታ

• በዓለማችን ከ50 ሚሊዮን በላይ የኢፕሊፕሲ ተጠቂዎች አሉ
• ከነዚህ መካከል 1 ሚሊዮን የሚሆኑት በአገራችን ይገኛሉ
• ከህሙማኑ መካከል 85% የሚሆኑት ህክምና አያገኙም

    በአገረ እንግሊዝ ለሃያ አምስት አመታት ቆይታ ወደ አገሯ በተመለሰችውና የኢፕሊፕሲ (የሚጥል በሽታ) ታማሚ በነበረችው ወ/ሮ እናት የእውነቱ የተቋቋመው Care Epilepsy Ethiopia ህብረተሰቡ ስለበሽታው ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግና በህሙማኑ ላይ የሚደርሰውን የአድልኦና የመገለል ችግር ለማስወገድ የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም ሰሞኑን በጁፒተር ሆቴል አካሂዶ ነበር፡፡ በእለቱም በሽታው በአሁኑ ወቅት በአለም አቀፍ ደረጃ ያለበትን ሁኔታና እንዲሁም በአገራችን ያሉ የበሽታው ተጠቂዎች ቁጥርና የሚደርስባቸወን ስቃይ ለማሳየት ተሞክሯል፡፡ በሽታው ጊዜና ቦታን ሳይመርጥ በማንኛውም ሁኔታ ታማሚውን ስለሚጥለው ህሙማኑ አሳት ላይ በመውደቅ፣ ከፎቅ ላይ በመከስከስና መሰል አደጋዎች ገጥመዋቸው በአሰቃቂ ሁኔታ ጉዳት እንደደረሰባቸው የሚያሳዩ የተለያዩ ፎቶግራፎችም ለፕሮግራሙ ታዳሚዎች ቀርበዋል፡፡የኬር ኢፕሊፕሲ ኢትዮጵያ መስራችንና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ እናት የእውነቱ፤ ድርጅቱን ለማቋቋም ያነሳሳቸውን ነገር አስመልክተው ሲናገሩ፤ በኢፕሊፕሲ በሽታ ተይዤ ለአመታት ስሰቃይ ብቆይም እድለኛ ሆኜ ጥሩ ህክምና በሚሰጥበት አገር በመኖሬ ምክንያት ህክምናውን አግኝቼ ከበሽታዬ ለመዳንና በህይወቴ የምፈልገውን ለመሆን ችያለሁ፡፡ በአሁኑ ወቅት በፐብሊክ ሄልዝ ስፔሻላይዝድ አድርጌአለሁ፡፡ ማስተርሴንም ያገኘሁት በዚሁ ነው፡፡ ይህንን እድል ሳያኙ ቀርተው በበሽታው የተያዙና እጅግ የከፋ ስቃይና እንግልት የሚደርስባቸወ ኢትዮጵያዊ እህት ወንድሞቼ ግን መድሃኒትና ህክምና እንኳን ለማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ከዚህ በከፋ ሁኔታ ደግሞ በህብረተሰቡ የመገለል ሁኔታ ይደርስባቸዋል፡፡ ስለዚህም ይህንን ነገር ለመቀየርና በበሽታው የሚሰቃዩ እህትና
ወንድሞቼን ለመርዳት፣ ህክምናውን ለማግኘት የሚችሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት፣ ህብረተሰቡም በበሽታው ላይ ያለውን አመለካከት ቀይሮ ለህሙማኑ ተገቢውን ፍቅርና እንክብካቤ እንዲሰጣቸው ለማድረግ በማሰብ ድርጅቱን አቋቁመናል፡፡ ከተቋቋመ ቅርብ ጊዜ ቢሆንም በዚህ ዙሪያ በርካታ
የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ስንሰራ ቆይተናል፡፡ አሁን ደግሞ የበለጠ ወደ ህዝቡ ውስጥ ለመግባትና በሽታው በህሙማኑ ላይ እያደረሰ ያለውን ችግር ለማስወገድ ጥረት በማድረግ ላይ ነን ብለዋል፡፡
የሮማውን ገዡ ጁሊየስ ቄሳርን፣ የመቄዶኒያውን ንጉስ ታላቁ እስክንድርንና የፈረንሳዩን የጦር መሪ ናፖሊዮን ቦናፓርት ሲያሰቃይ የኖረው ኢፕሊፕሲ፤ በተወሰኑ የአንጐል ነርቭ ሴሎች ውስጥ በሚከሰት ጊዜያዊ የኤሌክትሪክ ንዝረት ሳቢያ የሚፈጠርና አንጐል ለአጭር ጊዜ የወትሮ ስራውን እንዳይሰራ የሚያደርግ በሽታ ነው፡፡ ሁለት ዋና ዋና የኢፕሊፕሲ አይነቶች እንዳሉና Generalized እና focul በሚል ስያሜ እንደሚጠሩ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ Generalized የምንለው የኢፕሊፕሲ አይነት ታማሚውን መሬት ላይ የሚጥል፣ የሚያንቀጠቅጥና ሰውነትን የሚያግተረትር ሲሆን Focul የሚባለው ደግሞ በዝምታ በመዋጥ፣ ለጥቂት ሰከንዶች አካባቢንና ራስን በመሳት የሚገለፅ ህመም ነው፡፡ በሽታው ከሰው ወደ ሰው የመተላለፍ ባህርይ የለውም፡፡ ህብረተሰቡ በሽታው ከሰው ወደ ሰው እንደሚተላለፍ ስለሚያምን፣ ብዙውን ጊዜ የበሽታው ተጠቂዎች ራሳቸውን ስተው በማወድቁበት ጊዜ ለመርዳትና ጉዳት እንዳይደርስባቸው ለማድረግ ፍርሃት ያድርበታል፡፡ የውስጥ ደዌ ህክምና እና የነርቭ ህክምና ስፔሻሊስቷ ዶክተር ሞህላ ዘበንጉስ ይህንኑ ጉዳይ አስመልክተው ሲናገሩ፤ “ኢፕሊፕሲ በተለያዩ ምክንያቶችና መነሻዎች ሳቢያ
በአንጐላችን ነርቮች ውስጥ በሚከሰት ድንገተኛና ጊዜያዊ የኤሌክትሪክ ንዝረት ምክንያት የሚፈጠር በሽታ ሲሆን ከታማሚ ወደ ጤነኛ ሰው በንኪኪ፣ በትንፋሽና መሰል ሁኔታዎች ፈፅሞ የማይተላለፍ
ነው፡፡ ለበሽታው መነሻ ምክንያቶች ይሆናሉ ተብለው ከሚታሰቡ ነገሮች መካከል በወሊድ ወቅት ከአስቸጋሪ ምጥ ጋር ተያይዞ በአንጐል ላይ የሚሰት አደጋ፣ የአንጐል ኢንፌክሽን፣ አንጐል ውስጥ
የሚያድጉ እጢዎች፣ በጭንቅላት ላይ የሚደርሱ የተለያዩ ጉዳቶች፣ ስትሮክና የደም ውስጥ የስኳር
መጠን በጣም ዝቅ ማለት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በአገራችን በሽታው ወደ አንድ ሚሊዮን በሚጠጉ ሰዎች ላይ የሚታይ ሲሆን ከእነዚህ ህሙማን መካከል ህክምናውን የሚያኙት ከ5-10 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው ብለዋል፡፡ በሽታው በህፃናትና በእድሜ በገፉ ሰዎች ላይ በስፋት እንደሚታይም ሃኪሟ ተናግረዋል፡፡
የኢፕሊፕሲ በሽታን 70% በመድሃኒት መቆጣጠር እንደሚቻል የሚገልፁት ዶክተር ምህላ፤ ታማሚዎች ህክምናውን በአግባቡ ከተከታተሉት በሽታውን ተቆጣጥረው መደበኛ ህይወት ለመምራት እንደሚችሉና በሽታው እንደ ስኳር፣ ደም ግፊት ህመም የሃኪም የቅርብ ክትትል የሚያስፈልገው ተናግረዋል፡፡ህክምናው በሽተኛው እንዴት እንደሚያደርገው መረጃ ከተሰበሰበ በኋላ በምልክቶቹ ተለይቶ ለሚታወቀው በሽታ መድሃኒት በመስጠት ምክንያታቸው የሚታወቁትን የኢፕሊፕሲ በሽታ ለመንስኤው ምክንያት የሆነውን ነገር ነጥሎ በማውጣትና በማከም ለመከላከል እንደሚቻልም ሀኪሟ ገልፀዋል፡፡ ህክምናው ረዘም ያለ ጊዜን የሚወስድ ሲሆን የጭንቃላትን ኤሌክትሪክ ንዝረት በሚለኩ መሳሪያዎች በመለካት ህመሙ ያለበትን ደረጃ በመከታተል፣ ታማሚው መድሃኒቱን በአግባቡ እንዲወስድና ከህመሙ ነፃ በሚሆን ጊዜ መድሃኒቱን እንዲያቆም በማድረግ፣ ጤናማና ሰላማዊ ህይወት እንዲመራ ማድረግ መቻሉንም ሃኪሟ አስገንዝበዋል፡፡
ኢፕሊፕሲ (የሚጥል በሽታ) በህክምና ቁጥጥር ስር እስካልዋለ ድረስ ምን ጊዜና የት ቦታ ህመምተኛውን እንደሚጥለው ማወቅ ስለማይቻል ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ የእሳት፣ የመብራት ወይንም የቴሌቭዥን ማንፀባረቅና ማብለጭለጭ በሽታውን ሊቀሰቅሰው እንደሚችል አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በሽታው ድንገት የሚቀሰቀስና ታማሚውን እጅግ ለከፋ አደጋ የሚዳርግ በመሆኑ የሚጥል በሽታ ያለባቸው ሰዎች መኪና ከማሽከርከር፣ ሳይክል ከመንዳት፣ ከዋና፣ ፈረስና በቅሎ ከመጋለብ፣ ከፍታ ቦታዎች ላይ ከመስራትና እንደ አልኮልና ጫት ካሉ ሱሶች በእጅጉ መቆጠብ እንደሚኖርባቸው ዶክተር ምእላ አስገንዝበዋል፡፡   

ኖር በዪ የኹጅር የጋኸምን ምስ) - የቤተ ጉራጌ ተረት

ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት ጓደኛሞች፤ ገንዘብ በጣም ይቸግራቸውና በምን መንገድ ራታቸውን እንደሚበሉ ያስባሉ፡፡
አንደኛው -  ከሱቅ ገንዘብ እንበደርና የፈለግነውን ምግብ እንብላ
ሁለተኛው - ለባለሱቁ ባለፈው ያለብንን ዕዳ ስላልከፈልነው ምርር ብሎታል፡፡ “ያንን
ካልመለሳችሁልኝ ሁለተኛ ዐይናችሁን አላይም” ብሎኛል፡፡
አንደኛው -  እሺ ሌላ ዘዴ አንተ አምጣ
ሁለተኛው - አጐቴን ሄጄ ላስቸግረዋ?
አንደኛው -  የእራት ስጠን ልትለው ነው? የሆነ ሰበብ ያስፈልግሃልኮ?
ሁለተኛው - የቤት ኪራይ አነሰኝ ሙላልኝ ልበለው?
አንደኛው - አሞሃል? ነገ የሚጣራ ነገር ዛሬ ዋሽተህ የወደፊት እንጀራ ገመድህን በትንሽ ነገር ልትበጥስ ነው?
ሁለተኛው - ታዲያ ምን ማድረግ ይሻለናል?
አንደኛው - አንድ ዘዴ ታየኝ
ሁለተኛው - ምን?
አንደኛው - እዚህ ሠፈር አንድ ድንኳን ተጥሏል፡፡ የሆነ ሰውዬ ሞቷል፡፡ ለምን ራት ሰዓት
አካባቢ እዛ ሄደን፤ መቼም እራት ማቅረባቸው አይቀርምና፤ ቁጭ ብለን   
አንጠብቅም?
ሁለተኛው - አሁን አሪፍ ዘዴ ዘየድክ
አንደኛው - በቃ እዛ እንሄዳለን!
ተያይዘው ወደ ልቅሶው ድንኳን ሄዱ፡፡ ገቡ፡፡
ጠበቁ፡፡ ጠበቁ፡፡ ጠበቁ፡፡ ራት አልመጣም፡፡
12 ሰዓት ተኩል፡፡ አንድ ሰዓት፡፡ ሁለት ሰዓት፡፡ ራት፤ የለም፡፡ ግራ ገባቸው፡፡
አንደኛው - ራት ይቀርባል? አይቀርብም? ለምን አንጠይቅም?
ሁለተኛው - ይሻላል፡፡ ግን ማንን እንጠይቅ?
አንደኛው - እዛ ጋ ወዲህ ወዲያ የሚሉትን ሰውዬ እንጠይቃቸው፡፡
ሁለተኛው - እሺ
አንደኛው ፤ ወደተባሉት ሰው ጠጋ ይልና፤
“እንዴት ነው፣ ራት አይቀርብም እንዴ?”
ሰውዬው - አይ ልጆቼ! ሟቹ ሰውዬ ራሱ የሞተው ርቦት ነው!  
***
ድህነታችንን መጋራት እንጂ መታገል ካቃተን መንገዳችን በእንቅፋት የተሞላ እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ከሥሩ ለመንቀል ሥር-ነቀል እርምጃ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ሥር - ነቀል አስተሳሰብ ማዳበር ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ የምሁራንና ባለሙያዎች አስተሳሰብ መዳበርና የፈቃደ ልቦናቸው መኖር ወሳኝ ነው! በሀገራችን ለምሁራንና ለባለሙያዎች የምንሰጠው ትኩረትና ክብር አናሳ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ድህነትን ለመቀነስ መወሰድ ካለባቸው ዓይነተኛ እርምጃዎች አንዱ ይኸው ለምሁርና ለባለሙያ የምንሰጠው ትኩረት ነው! ምሁራኑም ለሀገራቸው የሚሰጡት ትኩረት ከጥቅም የዘለለ መሆን ይኖርበታል፡፡ የጊዜው ነገር ሆኖ ነው እንጂ ይሄን አይስቱትም! ሹማምንት የህዝብ ፍቅር ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ከህዝብ ጋር መኖር፣ ህዝብ መሀል መኖር አለባቸው፡-
“ዓለም አደገኛ ናት ጠላቶችም በየቦታው አሉ፡፡ ሁሉሰው ራሱን መጠበቅ አለበት፡፡ ምሽግ የመጨረሻ መጠበቂያ ቦታ ይመስለናል፡፡ ከሰው ተነጥሎ መቀመጥ ግን ለበለጠ አደጋ ያጋልጣል፡፡ ከአስፈላጊ መረጃ ያናጥባል፡፡ በግልፅ እንድንታይና ቀላል ኢላማ ያደርገናል፡፡ ስለዚህ ከህዝብ መካከል ሆኖ፣ ወዳጅ እየፈጠሩ መዋሃዱ ይመረጣል፡፡ ከጠላቶች ጥቃት ጋሻ የሚሆንህ ጀማው ነው” ይላል ሮበርት ግሪን፡፡ በተግባር የመፈተኛው ሰዓት አሁን ነው፡፡ ለራስ ጥቅም ከማሰብ ለሀገር ማሰብ ልዩነቱ የሚረጋገጠው ልባችን፣ አፋችንና ተግባራችን አንድ ሲሆኑ ነው፡፡ መለኪያው ከህዝብ ጋር መሆን ነው፡፡ እንደህዝብ ማሰብ ነው፡፡ “ሸክላ ሲሰበር ገል ይሆናል፡፡ መኳንንትም ሲሻሩ ህዝብ ናቸው” የሚለውን ማስተዋል ዋና ነገር ነው፡፡ አዲስ የተሾሙ ሰዎቻችንን ልቦና ህዝባዊነት አይንሳቸው፡፡ ሀገራዊነት አይንሳቸው!
የተሻለ፣ ከትላንት የተለየ ነገር እንዲኖር እንመኝ፡፡ የምናውቃቸው ሰዎች የምናውቀውን ነገር የሚደግሙልን ከሆነ መቀየራቸው ትርጉም ያጣል! አብረን እናስብ! ምሁራንን እናማክር! ለሀገር አሳቢዎች እኛ ብቻ ስላልሆንን ከማህበረሰቡ የረባ አዕምሮና አብራሄ ህሊና (Enlightenment) ያላቸውን ሰዎች የመቀላቀል የተባና ሩህሩህ ልቦና ይኑረን! ይህን ተሐድሶ ያልተላበሱ ሰዎች ይዘን ብዙ አንጓዝም! ይህ ካልሆነ “ኖር በይው ልብሱን፣ ሰውዬውስ የቅድሙ ነው” የሚለው ተረት ዕውን ይሆናልና እንጠንቀቅ!  

 በደራሲ አሳየ ደረበ የተጻፈው “እስኪነጋ ድረስ” የተሰኘ የወጎች፣ የአጫጭር ልቦለዶችና የግጥሞች ስብስብ መጽሃፍ ሰሞኑን በገበያ ላይ መዋሉን ደራሲው በተለይ ለአዲስ አድማስ ገለጸ፡፡
በተለየ አቀራረብ የተሰናዳው መጽሃፉ፤በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ 18 ያህል ወጎችንና አጫጭር ልቦለዶችን የያዘ ሲሆን በታሪኮቹ መካከልም ከታሪኮቹ ሃሳቦች ጋር ተያያዥ የሆኑ 30 ያህል ግጥሞችን አካትቷል፡፡
ደራሲው ለህትመት ያበቃው የመጀመሪያ ስራው የሆነው “እስኪነጋ ድረስ”፤ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች በሚገኙ የመጽሃፍት መደብሮችና አዟሪዎች ዘንድ በ50 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡
ደራሲ አሳየ ደረበ በፌስቡክ ማህበራዊ ድረ-ገጽ አዝናኝና አስተማሪ ወጎችን፣ የግል እይታዎችን፣ ግጥሞችንና የተለያዩ ጽሁፎችን በስፋት በማቅረብና በርካታ አንባብያንና ተከታዮችን በማፍራት የሚታወቅ ሲሆን በቀጣይም ሌሎች የወጎችና የአጫጭር ልቦለድ መጽሃፍትን ለአንባብያን የማድረስ ዕቅድ እንዳለው ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡

ኤፍሬም አርት ስቱዲዮና ጋለሪ የሰዓሊ ናኦድ ክፍሉ በርካታ የስዕል ስራዎች የተካተቱበትን “ትውስታ” የተሰኘ የስዕል አውደ ርዕይ ከትላንት በስቲያ ከቀኑ 11፡30 ጀምሮ በብሄራዊ ሙዚየም ለእይታ አበቃ፡፡“ትውስታ” የስዕል አውደ ርዕይ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ የቀድሞ ባቡሮችን ወደ ሃሳብ ቀይሮ የሳለበትና ሌሎች 48 ያህል ስዕሎች የቀረቡበት እንደሆነ የኤፍሬም አርት ስቱዲዮና ጋለሪ ባለቤት አቶ ኤፍሬም ለሚ ተናግረዋል፡፡ ሰዓሊው ከዚህ ቀደም ከሌሎች ሰዓሊያን ጋር በቡድን ለበርካታ ጊዜያት ስራዎቹን ለእይታ ማቅረቡን የገለፁት አቶ ኤፍሬም፤ “ትውስታ” በግሉ ያቀረበው የመጀመሪያው አውደ-ርዕይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ኤፍሬም አርት ስቱዲዮና ጋለሪ ከዚህ በፊት ሦስት የቡድን አውደርዕዮችን ለተመልካች ያቀረበ ሲሆን የአንድ ሰዓሊ ስራዎችን ለብቻ ሲያቀርብ የአሁኑ የመጀመሪያው መሆኑን የጋለሪው ባለቤት ተናግረዋል፡፡ አውደ ርዕዩ እስከ ጥቅምት 3 ቀን 2008 ዓ.ም ለተመልካች ክፍት ሆኖ እንደሚቆይም ታውቋል፡፡