Administrator

Administrator

   የኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማዕከልና ኤልሰን ፕሮሞሽን በመተባበር ያዘጋጁት “የጀበና ሙሽሮች” የተሰኘ የቡናና የኪነጥበብ ፌስቲቫል በትላንትናው እለት በብሔራዊ ቴአትር የተከፈተ ሲሆን ፌስቲቫሉ እስከ ነገ እንደሚቆይም ታውቋል፡፡ የተለያዩ ክልሎች የቡና አፈላል ስርዓታቸውን ከነ አቀራረቡና ሙሉ ስርዓቱ ወክለው በተገኙበት በዚህ ፌስቲቫል ላይ የኢፌድሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሙሉጌታ ሰኢድ እና የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ክቡር ዶ/ር ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል፡፡ “”ቡና ከእለት የእለት ህይወታችን ጋር የተገናኘ ቢሆንም በደንብ አናውቀውም፤ ይህን ቡና ለራሳችን በደንብ ለማስተዋወቅ ታስቦ የተዘጋጀ ፌስቲቫል ነው” ብሏል - ፕሮሞተር ዮናስ ታደሰ፡፡ በአሜሪካ የአቦል ቡናና የመርካቶ ገበያ መስራች የሆኑት አቶ ታምሩ ደገፋና ከፈረንሳይ የመጡት ወ/ሮ አለም ፀሐይ ንባብ፤ የኢትዮጵያን ቡና በያሉበት እንዴት እንደሚያስተዋውቁ በፌስቲቫሉ መክፈቻ የገለፁ ሲሆን፤ አቶ ታምሩ ደገፋ በአሜሪካ ለታዋቂው ሙዚቀኛ ለማይክል ጃክሰን በአንድ ወቅት ስለ ኢትዮጵያ ቡና ሰፊ ማብራሪያ እንዳደረጉለት ተናግረዋል፡፡ ፌስቲቫሉ እስከ ነገ የሚቆይ ሲሆን የአማራ፣ የትግሬ፣ የኦሮሞ፣ የጉራጌና የሌሎች ብሔሮች የቡና ስርዓት ለእይታ ቀርቦ እየተጐበኘ ነው፡፡   

ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ዓመታዊ የጥናትና ምርምር ጉባኤውን በትላንትናው ዕለት የጀመረ ሲሆን፤ ዛሬ እንደሚጠናቀቅ ለማወቅ ተችሏል፡፡ መቻሬ ሜዳ በሚገኘው ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኮርፖሬት ሴንተር የሚካሄደው ይሄው ጉባኤ፤ ዘንድሮ ለ13ኛ ጊዜ እየተካሄደ ሲሆን በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የሚሰሩ ምሁራንና የምርምር ተቋማት የሰሯቸው የተመረጡ የጥናትና ምርምር ውጤቶች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሏል፡፡ በየአመቱ የሚካሄደው ይሄው “Multidisciplinary Research Conference” በትላንትናው እለት ከጠዋቱ 2፡30 ሰዓት ተጀምሮ በተለያዩ ምሁራን እየቀረበ ሲሆን የምርምር ውጤቶቹም የማህበረሰቡን ችግር በመፍታትና በማቃለል ረገድ ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡

ካለፈው መጋቢት ወር ጀምሮ “በማቭሪክ ፊልሞች የኢትዮጵያ” አማካኝነት በኢቲቪ ቻናል ሶስት ሲተላለፉ ከነበሩ 12 ፊልሞች ሶስቱ ባለፈው ረቡዕ ምሽት በኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል ተሸለሙ፡፡ ማቭሪክ ፊልሞች የኢትዮጵያ በሚል መጠሪያ በቻናል ሶስት የኢትየጵያ ፎልሞችን ቅዳሜ ምሽት ከ4፡30 ሰዓት ጀምሮ የሚያስተላልፈው ድርጅት ፊልሞቹን ከማስተላለፍ በተጨማሪ በባለሙያዎችና በአዘውታሪ ተመልካቾች የተመረጡና ከ1 እስከ 3 የወጡ ፊልሞችን አወዳድሮ የመሸለም ዓላማ እንደነበረውም የፕሮግራሙ ዳይሬክተር ወ/ሪት ፌቨን ታደሰ በእለቱ ገልፃለች፡፡ ለተከታታይ 12 ሳምንታት ከተላለፉት 12 የአማርኛ ፊልሞች ውስጥ በ2001 ዓ.ም ለእይታ የበቃው “አልተኛም” ፊልም አንደኛ በመውጣት የ20ሺህ ብር ተሸላሚ ሲሆን በ2001 ዓ.ም የተሰራው “የታፈነ ፍቅር” ሁለተኛ በመውጣት የ10 ብር ሽልማት አግኝቷል፡፡ በ2004 ዓ.ም የተሰራው “አየሁሽ” ፊልም ሶስተኛ በመውጣት የአምስት ሺህ ብር ተሸላሚ ሆኗል፡፡
በእለቱ የኢቲቪ የስራ ኃላፊዎች፣ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ የማቭሪክ ፊልሞች የኢትዮጵያ ስፖንሰር የሆነው ፍሊንት ስቶን ሆምስ ባለቤቶችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን አርቲስት ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) በሙዚቃው ታዳሚዎቹን ሲያዝናና አምሽቷል፡፡

    በደራሲ ብርሃኑ አበጋዝ የተፃፈው “ጥምር ቁስል” ልብወለድ መጽሐፍ ሰሞኑን ገበያ ላይ ዋለ፡፡ መጽሐፉ ትኩረት የደረገው በኢትዮ - ኤርትራ ጦርነትና በሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ቁርኝት ላይ ሲሆን የኢትዮጵያና የሶማሊያ ጦርነትም በልብወለዱ ውስጥ ተዳስሷል፡፡ በ161 ገጽ የተቀነበበው ልብወለዱ፤ 37 ክፍሎች ያሉት ሲሆን ታሪኩ በሃሳብ ደረጃ ከተፀነሰ 14 ዓመታት፣ መፃፍ ከተጀመረ ደግሞ ሰባት ዓመታትን እንዳስቆጠረ ደራሲው በመግቢያው ላይ ገልጿል፡፡ ታሪካዊ ልብ ወለድ መጽሐፉ ዛሬ ከቀኑ በ10፡30 በኢዮሃ ሲኒማ የሚመረቅ ሲሆን በ40 ብር ከ60 ሳንቲም እየተሸጠ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያን ፊልም 50ኛ ዓመት በዓል ምክንያት በማድረግ በኢዮሃ ሲኒማና በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የተዘጋጀው የፊልም ስልጠና ረቡዕ ተጠናቀቀ፡፡ ስልጠናው የተሰጠው ወደ 60 ለሚጠጉ የፊልም ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች ሲሆን በፊልም መመሪያና ስነ ምግባር፤ በፊልም ዝግጅት፣ በፊልም ስክሪፕት አፃፃፍና በፊልም ትወና ላይ ያተኮረ እንደነበር በማጠናቀቂያው ላይ ተገልጿል፡፡
ለአራት ቀናት በቆየው በዚህ ስልጠና ላይ ዮናስ ብርሃነ መዋ፣ ብርሃኑ ሽብሩ፣ ሄኖክ አየለ እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመጡ የስነ ልቦና ባለሙያዎች በአሰልጣኝነት መሳተፋቸውም ታውቋል፡፡

የገጣሚ ሶልያና አብዲ “ሼም ይናፍቅሃል” የተሰኘ የግጥም መድበልና ሲዲ ዛሬ ከ3ሰዓት ጀምሮ በጣይቱ ሆቴል ጃዝ አምባ አዳራሽ ይመረቃል፡፡
በመድበሉ ውስጥ የተካተቱት ግጥሞች በሴቶች ጥቃት፣ በህገወጥ ጉዞ አስከፊነት፣ በወጣትነትና በፍቅር ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ሲሆን የግጥሙ ሲዲ ደግሞ በኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድኖች (ዋሊያዎቹና ሉሲዎች) ጀግንነት ላይ የሚያተኩር ነው ተብሏል፡፡ 94 ያህል ግጥሞችን የያዘው መድበሉ በ30 ብር ለሽያጭ ቀርቧል፡፡

“በሰው ለሰው” ድራማ የአዱኛን ገፀ - ባህሪ ወክሎ በመጫወት እና በበርካታ ስራዎቹ አድናቆትን ያተረፈው አርቲስት ይገረም ደጀኔ፤ “ቆምኩኝ ለምስጋና” የተሰኘ የምስጋና የመዝሙር ሲዲ ያወጣ ሲሆን፤ ሰኞ ገበያ ላይ እንደሚውል ተገለፀ፡፡ አርቲስቱ ለመዝሙሩ ከተከፈለው 40ሺህ ብር ላይ 20ሺህ ብሩን ለሜቄዶንያ አረጋዊያን መርጃ በእርዳታ ሲሰጥ ቀሪውን እያገለገለ ላደገበት ሰንበት ት/ቤት መለገሱን ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡
በመዝሙር ሲዲው ውስጥ 11 መዝሙሮች የተካተቱ ሲሆን፤ አምስቱን ለብቻው ሁለቱን ከዘማሪ ዲያቆን ፍቃዱ አዱኛ ጋር በጋራ መስራቱንና ቀሪዎቹ አራት መዝሙሮች በዘማሪ አዱኛ እንደተሰሩ ይገረም ገልጿል፡፡
“የዘመርኩት ማመስገን ስለምወድ” ነው ያለው አርቲስቱ፤ ሌሎችም የተሰጣቸውን ፀጋ ተጠቅመው የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ለማነቃቃት በስራው ላይ መሳተፉን ተናግሯል፡፡  
“ወደፊት ከእኔ ጋር በበጎ ስራዎች ላይ ለመሰማራት የሚፈለግ ሰው ካለ አብሬ ለመስራት ዝግጁ ነኝ” ብሏል - አርቲስት ይገረም ደጀኔ፡፡ አርቲስቱ ከዚህ ቀደም ለአቡነ መልከፀዴቅ ገዳም ለገቢ ማሰባሰቢያ የሚውል የመዝሙር ቪሲዲ ከሙያ አጋሮቹ ጋር መስራቱ ይታወሳል፡፡  

Saturday, 21 June 2014 14:58

የፍቅር ጥግ

(ስለጋብቻና ፍቺ)
አባት ለልጆቹ ሊያደርግ የሚችለው ትልቁ ነገር፣ እናታቸውን ማፍቀር ነው፡፡
ቴዎዶር ኼስበርግ
ሰዎች በትዳር የሚዘልቁት፣ ስለፈለጉ ነው እንጂ በሮች ስለተቆለፉባቸው አይደለም፡፡
ፖል ኒውማን
ፍቺ አካልን እንደመቆረጥ ነው፡፡ አንዳንዴ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡ ከተቻለ ግን ባይሆን ይመረጣል፡፡ ምክንያቱም ዘላቂ አካል ጉዳተኝነትን ያስከትላል፡፡
ቢል ዶኸርቲ
ፍቺ ለልጆች እንዲሁም ለሌሎች ህይወት ያላቸው ነገሮች ሁሉ ጤናማ አይደለም፡፡
ዲያኔ ሶሊ
የተሻለ ነገር እስኪመጣ ድረስ ጋብቻን እንደተቋምከእነችግሮቹ  እደግፈዋለሁ፡፡
ዴቪድ ብላንከንሆርን
(የአሜሪካ እሴቶች ተቋም)
እያንዳንዱ ፍቺ የትንሽዬ ስልጣኔ ሞት ነው፡፡
ፓት ኮንሮይ
የህብረተሰብ የመጀመሪያው ማሰሪያ ጋብቻ ነው፡፡
ሲሴሮ
በማህበራዊ ጥናት አንድ አባባል አለ፡- “እናት በመላው ህይወትህ ሁሉ እናት ናት፡፡ አባት ግን አባት የሚሆነው ሚስት ሲኖረው ብቻ ነው”
ሊህ ዋርድ ሲርስ
(የጆርጅያ ጠ/ፍርድ ቤት ዋና ዳኛ)
ድሮ ወላጆች ብዙ ልጆች ነበራቸው፡፡ አሁን ልጆች ብዙ ወላጆች አሏቸው፡፡
ጉሮ ሃንሰን ሄልስኮግ
አንዳንዴ ባልና ሚስት መጣላታቸው አስፈላጊ ነው፡፡ የበለጠ እርስ በርስ እንዲተዋወቁ ያደርጋቸዋል፡፡
ገተ
ትክክለኛውን ፍቅር ከመፍጠር ይልቅ ትክክለኛውን አፍቃሪ በመፈለግ ጊዜያችንን እናጠፋለን፡፡
ቶም ሮቢንስ

    ያልተቋረጠ የሽብር ጥቃት ከራሳቸው ላይ አልወርድ ብሎ እጅግ ግራ የተጋቡ ሁለት የአፍሪካ ሀገራት አሉ ከተባለ ከኬንያና ናይጀሪያ ውጭ ሌላ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ያላባራ የሽብር ጥቃት ሰለባ የሆነችው ኬንያ፤ ባለፈው እሁድና ሰኞ በተከታታይ የወረደባት የሽብር መአት የጦርነት ቀጠና አስመስሏታል፡፡
የአልሸባብ አባላት ሳይሆኑ እንዳልቀረ በሰፊው የተጠረጠሩ ሽብርተኛ ታጣቂዎች ባለፈው እሁድ የሱማሊያ አዋሳኝ የኬንያ ግዛት ከሆነችው የላሙ ደሴት አቅራቢያ በምትገኘው የምፒኪቶኒ ከተማ ላይ ድንገት አደጋ ጥለው አርባ ስምንት ኬንያውያንን ገድለዋል፡፡ እሁድ እለት ማታ ላይ ከተፈፀመው ከዚህ ጥቃት ያመለጡ የአይን እማኞች፤ ሽብርተኛ ታጣቂዎቹ ቤት ለቤት እየዞሩ የቤቱ አባወራ ሙስሊም መሆኑንና የሶማሊያ ቋንቋ ተናጋሪ መሆን አለመሆኑን ያጣሩ እንደነበረ ጠቁመው በተለይ ሆቴል ውስጥ ካገኟቸው ወንዶች ውስጥ ሙስሊም ያልሆኑትን ብቻ ለይተው በማውጣት፣ሚስቶቻቸው ፊት በጥይት ደብድበው እንደገደሏቸው አስረድተዋል፡፡
የምፒኪቶኒ ከተማ ነዋሪም ሆነ መላ ኬንያውያን የዚህ ጭካኔ የተሞላበት ጭፍጨፋ ድንጋጤ ገና በወጉ እንኳ ሳይለቃቸው ሰኞ እለት ከከተማዋ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው የማጂምቤኒ ከተማ እነዚሁ ሽብርተኛ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት የአስር ኬንያውያንን ህይወት ቀጥፈዋል፡፡
ድፍን አለሙም ሆነ መላ ኬንያውያን እንደጠረጠሩት፣ የሶማልያው ሽብርተኛ ቡድን አልሸባብ ኬንያ በሶማልያ ላይ ለፈፀመችው ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትና በሙስሊሞች ላይ ላደረሰችው በደል ሁለቱንም ጥቃቶች በማድረስ የእጇን እንደሰጣት በመግለፅ ሃላፊነቱን ወስዷል፡፡
የኬንያው ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ ግን አልሸባብ የሰጠው መግለጫ ፈጽሞ ሊዋጥላቸው አልቻለም፡፡ በሽብር ጥቃቱ ከተገደሉት አብዛኞቹ የእሳቸው ብሔር አባላት የሆኑ ኪኩዩዎች መሆናቸውን መሰረት በማድረግ ሃላፊነቱን ከወሰደው አልሸባብ ይልቅ በዘረኝነት የታወሩ ባሏቸው ኬንያውያን ፖለቲከኞች ላይ ጣታቸውን በመቀሰር ተጠያቂ አድርገዋቸዋል፡፡ የፕሬዚዳንቱን ውንጀላ ተከትሎም የኬንያ ፖሊስ በሽብር ጥቃቱ እጃቸውን አስገብተዋል ያላቸውን በርካታ ኬንያውያንን ከያሉበት ለቃቅሞ ወህኒ ከርችሟቸዋል፡፡

Saturday, 21 June 2014 14:51

የብራ መብረቅ በናይጀሪያ

ቦኮ ሃራም ባጠመደው ቦንብ 21 ወጣቶች ሲሞቱ፤ 27ቱ ቆስለዋል

ናይጀሪያውያን የእኛን ቡድን በደርሶ መልስ ጨዋታ አሸንፎ ለ20ኛው የአለም ዋንጨ ባለፈው የአፍሪካ ሻምፒዮን ብሔራዊ ቡድናቸው በእጅጉ ደስተኞች በመሆናቸው የብራዚሉ የአለም ዋንጫ እስኪጀመር በጣም ቸኩለው ነበር፡፡
አብዛኞቹ ናይጀሪያውንም ቡድናቐው ተካፋይ የሆነበት የብራዚሉ የአለም ዋንጫ,ኧ እስከ ፍፃሜው ድረስ (ያለው የአንድ ወር ጊዜ በየአደባባዩ ተሰብስበው የሚዝናኑበት አሪፍ የፌሽታ ጊዜ እንደሚሆንላቸው ሙሉ እምነት ነበራቸው፡፡
የሰሜን ምስራቅ ግዛቶች ውስጥ በሚኖሩት ናይጀሪያውያን ዘንድ ግን ይህን መሰሉ ስሜት ብዙም አልቆየም፡፡ ፅንፈኛ እስላማዊ አሸባሪ ቡድን የሆነው ቦኮ ሃራም በዋናነት ይንቀሳቀስበታል በሚባለው በዚህ አካባቢ የዓለም ዋንጫን መመልከት የታገደው ከጨዋታው ቀደም ብሎ ነው፡፡ ቦኮ ሀራም በዮቤና በአዳማዊ ግዛቶች “አዳሜ ሁሉ የአለም ዋንጫ ውድድርን በአደባባይ ተሰብስቤ እየጨፈርኩ በቴሌቪዥን እከታተላለሁ ስትል ውርድ ከራሴ!” በማለት በበራሪ ወረቀት የሰጠው ማስጠንቀቂያ ብዙዎችን ከፍ ያለ ስጋት ውስጥ መጣሉ አልቀረም፡፡
በእግር ኳስ ፍቅር ልባቸው ክፉኛ የነደደ በርካታ ናይጀሪያውያን ግን ስጋታቸውን እንደያዙም ቢሆን ሰብሰብ ብለው እየጨፈሩ ውድድሩን ከመመልከት ወደኋላ አላሉም፡፡ የዮቤ ግዛት የዳማቱሩ ከተማ ነዋሪ የሆኑ እግር ኳስ አፍቃሪ ናይጀሪያውያን ባለፈው ማክሰኞ ያደረጉትም ይህንኑ ነበር፡፡
ለቦኮ ሀራም ግን የእነዚህ ናይጀሪያውያን ድርጊት ማስጠንቀቂያን ቸል የማለት ተራ ስህተት ሳይሆን በሞት የሚያስቀጣ ከፍተኛ ወንጀል ነበር፡፡ እናም የቅጣት ቦምብ ተጠመደላቸው፡፡ ባለፈው ሳምንት ብራዚልና ሜክሲኮ እየተጫወቱ ሳለ ማንም ባላሰበውና ባልጠበቀው ሁኔታ የተጠመደው ቦምብ ድንገት ፈነዳ፡፡ አገር ሰላም ብለው ጨዋታውን በመከተተል ላይ ከነበሩት ወጣቶች መካከል ሃያ አንዱ ወዲያውኑ ሲሞቱ፤ ሃያ ሰባቱ የሚሆኑት ደግሞ ቀላልና ከባድ ጉዳት ደረሰባቸው፡፡ ብዙዎችን ድንጋጤ ውስጥ የከተተ የብራ መብረቅ!