Administrator

Administrator

‹‹የፍራየርስ ክለብ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦፍ ጆክስ›› ካካተታቸው ቀልድ አከል ቁምነገሮች ውስጥ  የሚከተለው ይገኝበታል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሚስተር ሁበርት ሐምፍሬይ የተባሉ ምሁር ለአንድ የዩኒቨርስቲ ተማሪ የመጨረሻ የጥናት ወረቀት መካር (advisor) ሆነው ይቀጠራሉ፡፡ የመካርነቱን ሥራ በታላቅ ደስታ ነበር የተቀበሉት፡፡ እንዲህ ብለው፡-
‹‹በዕውነቱ ወጣት ምሁራን ለወግ ማዕረግ ይበቁ ዘንድ የመጨረሻ የጥናት ወረቀታቸውን ሲያቀርቡ ማገዝና ሙያዊ ክህሎታቸውን ማብቃት፣ ለእኔ ታላቅ ደስታና ዓይነተኛ ክብር ነው፡፡ በተቻለኝ አቅም ዕውቀቴን ላጋራው ፍቃደኛ መሆኔን እገልፃለሁ!›››
ሚስተር ሐምፍሬይ ተማሪውን መርዳት ቀጠሉ፡፡ ተማሪውም በትጋት መሥራቱን ቀጠለ፡፡
ወረቀቱን የማቅረቢያው ወቅት ሲደርስ ተማሪው በቆንጆ ሁኔታ የተጠረዘ ፅሑፉን ይዞ ሚስተር ሐምፍሬይ ዘንድ ከች አለ፡፡
‹‹ሚስተር ሐምፍሬይ፤ በወረቀቴ ላይ አስተያየትዎን ይሰጡኝ ዘንድ ይሄው መጥቻለሁ፡፡ ምን ይሉኝ ይሆን?››
ሚስተር ሐምፍሬይም፤
‹‹መልካም፡፡ አየውና መልስ እነግርሃለሁ›› አሉና አሰናበቱት፡፡ ተማሪው አመስግኖ ከቢሮአቸው ወጣ፡፡
ሁለት ወር አለፈ፡፡ ከሚስተር ሐምፍሬይ በኩል ምንም የተሰማ ነገር የለም፡፡ ስለዚህ ተማሪው ቢሮአቸው ሄደ፡፡
ከዚያም፤ ‹‹ሚስተር ሐምፍሬይ፤ ወረቀቴን እንዴት አገኙት?” ሲል ጠየቃቸው፡፡
ሚስተር ሐምፍሬይም፤
‹‹እርግጠኛ ነህ ይሄ የመጨረሻውና ያለቀለት ሥራህ ነው? ዕውቀትህ ይሄ ብቻ ነው?›› ሲሉ ትኩር ብለው እያዩት ጠየቁት፡፡
ተማሪው  ቅር ያላቸው ነገር እንዳለ በመገመት፤
‹‹አንዴ ወስጄ ልየው?›› አለ፡፡
‹‹ይሻላል›› አሉት፡፡
ተሜ፤ በድጋሚ መሥራቱ እየከፋው የወረቀቱን ጥራዝ ተቀብሎ ሄደ፡፡ ፕሮጄክቱን አንዴ ሊከልሰው ነው፡፡
ከሁለት ወራት በኋላ ተማሪው የከለሰውን ወረቀት አጠናቅሮ፣ ቀንብቦ፣ ለሚስተር ሐምፍሬይ አምጥቶ አስረከባቸው፡፡ ሁለት ወር አለፈ፡፡ ከሚስተር ሐምፍሬይ በኩል ምንም ወሬ የለም፡፡ ስለዚህ ‹‹ቢሮአቸው ብሄድ ይሻላል›› ብሎ ወደዚያው አመራ፡፡ እንደደረሰም፤
‹‹እንዴት ሆነልኝ፤ ሚስተር ሐምፍሬይ?›› ሲል ጠየቀ፡፡
ሚስተር ሐምፍሬይ ግን፤
‹‹በቃ ይሄው ብቻ ነው ችሎታህ? እንደገና ቢሠራ ይሻላል›› አሉት፡፡
‹‹እሺ፤ የመጨረሻ ሙከራ ላድርግ›› አለና ተሜ፤ እየከፋው ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ በጣም ቅር እያለው በነጋታው ጥናት ክፍሉ ገብቶ ለሶስተኛ ጊዜ ወረቀቱን ፃፈና፤
‹‹አሁንስ ‹አልቀበልም› ቢሉኝ፤ የራሳቸው ጉዳይ፤ እተወዋለሁ!›› እያለ ወደ ሚስተር ሐምፍሬይ ቢሮ ሄደና አስረከባቸው፡፡
ሚስተር ሐምፍሬይም፤
‹‹በቃ ይሄ ነው የመጨረሻ ሥራህ?›› አሉት፡፡
‹‹አዎ፤ ከዚህ በላይ ምንም የምጨምረው ነገር የለም›› አላቸው፤ ፍርጥም ብሎ፡፡
ቀጥሎም
‹‹አንዴ ብቻ ሳይሆን ሁለት ሶስቴ ተመራምሬበታለሁ፡፡ ሁለት ሶስት ዓይነት ትንተና ተንትኛለሁ፡፡ ደጋግሜም ፅፌዋለሁ፡፡ ይኸው ነው!››
ሚስተር ሐምፍሬይ ትኩር ብለው ካስተዋሉት በኋላ፤
‹‹ጥሩ! እንግዲያው ከሰጠኸኝ ወረቀቶች ሁሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሄኛውን አነበዋለሁ!›› ብለው አሰናበቱት፡፡ ተሜ ወጣና፤
‹‹ወይኔ! እስከ ዛሬ አንዱንም ሳያነብቡ ነበር ለካ የሚያፈጉኝ!›› እያለ ሄደ፡፡
                                                          *    *    *
የሰውን ድካም ማቃለል የሚችሉ አመራሮችና ኃላፊዎች የየተቋማቱ ምሰሶዎች ናቸው፡፡ በአንፃሩ የሰው ድካም የማይሰማቸው ሰዎች፤ ሙሉ ልብ እንዳይኖራቸው የማያግዙ፣ የራሳቸውን መንገድ ብቻ የሚያሰላስሉና የመልካም አስተዳደር አካላት ያልሆኑ ግለሰቦች አሉ፡፡ ያልተገነዘቡት ነገር አለ፣ ለውጥ አሮጌውን ጥሎ አዲስ ይዞ እንደሚራመድ አዳዲስና ወጣት ኃይሎችን ያላቀፈ ዕድገት ወንዝ አይሻገርም፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን የሲቪክ ማህበራትን ያላጠናከረና አዳዲስ እንዲፈጠሩ ያላገዘ የለውጥ ጉዞ፤ አገራዊ መግባባቶች፣ አገራዊ እርቆች፤ ቀና ውይይቶችና ሽምግልናዎች  የሚሰምሩት ሲቪል ማህበራት እንደ ልብ ሲንቀሳቀሱ ነው፡፡ አመራሮች ስለ ዕቅዳቸው የሚናገሩትና የሚገቡት ቃል የግብር-ይውጣ እንዳይደለ ማረጋገጥ ተገቢ ነው፡፡ የአመራር ለውጦች ሲደረጉ ከነበሩ ተጨባጭ የህዝብ ችግሮች ጋር በቅጡ የተሳሰሩና እነዚያን ችግሮች የሚፈቱ መሆን አለባቸው፡፡ አለበለዛ ‹‹ትሻልን ትቼ ትብስን አገባሁ›› የሚል ሥጋት ይፈጠራል፡፡ በተለይ ከሙስና ጋር ቁርኝነት ያላቸው የኃላፊነት ቦታዎች ብርቱ ጥንቃቄ ይጠይቃሉ። የቢሮክራሲና የደላሎች፣ የኤጀንሲዎች፣ የአስመጪና ላኪዎች ግንኙነት፣ ዛሬ ባገራችን ብዙ የተወራለት ስስ-ብልት ነው፡፡ ‹‹ዛር ልመና ሳይያዙ ገና›› ይሏል አበው፡፡ ከወዲሁ የነገሮችን አካሄድ ማጤንና መንቀሳቀስ ብልህነት ነው። ለትላንትና መልስ ለመስጠት፣ ዛሬም የቆምንበትን ሁኔታ አምርሮ መመርመር፣ የአዳዲስ ሹማምንት ሁሉ ብርቱ ኃላፊነት ነው፡፡
 አንዳንድ ፀሐፍት ስለ አንዳንድ ቢሮክራቶች መመሪያ ይህን ይላሉ፡፡
 ‹‹ ሀ-ኃላፊ ስትሆን ጠያቂና ተመራማሪ ምሰል
   ለ- ችግር ሲፈጠር የበታችህን ወክል (delegate)
   ሐ- ስትጠራጠር የማይገባ ነገር አጉተምትም፤ አነብንብ
   መ- የቢሮክራትነት ዋና ጥበብ ይሄው ነው››
ከዚህ ይሰውረን! ስንት ቢሮክራቶች ይህን አባዜ ተሸክመው ይሆን? ብሎ መጠየቅ የአባት ነው፡፡
በሌላ ወገን ደግሞ ስለ ፕሮጄክት ልዩ ልዩ ደረጃዎች ሲፅፉ ፡- ‹‹ አንደኛው የፕሮጄክት ደረጃ ወይም ምዕራፍ/
           ስለ ፕሮጄክቱ ሥራ መጓተት ነው፡፡ ሁለተኛው/
           ከግራ-መጋባት ነፃ መሆን ነው፡፡ ሦስተኛው/
           መሸማቀቅና መጨናነቅ መጀመር ነው፡፡
አራተኛ/ ጥፋተኛውን ፍለጋ መግባት ነው፡፡ የማነው ጥፋቱ? መባባል ነው፡፡ አምስተኛው/ ምንም ያላጠፋውን የዋህ ሰው እንዲቀጣ ማድረግ ነው፡፡ ስድስተኛውና የመጨረሻው በፕሮጄክቱ ሥራ ምንም ያልተሳተፉ ሰዎችን ማሞገስና ክብር ሰጥቶ ማወደስ ነው፡፡››
ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች እኛም ጋ አሉ የምንል እራሳችንን መፈተሽ ነው፡፡ ሹማምንቶቻችን አገርና ህዝብን ያስቀድማሉ ወይ? ካላስቀደሙስ? ከዚህም ይሰውረን እንበል፡፡ ምክንያቱም የተለያዩ እርስ በርስ የሚግባቡ፣ የሚሞዳሞዱ ወዳጅ አመራሮች፤ የሆድ ለሆድ መርህ ኔት-ወርክ፤ አላቸው፡፡ መደጋገፊያ መረብ ነው፡፡ በዚያም ክፉኛ ይጠቃቀማሉ፡፡ ሀቀኛና ምስኪን ሠራተኞች ግን ላባቸውን አፍስሰው ሥራዎች እንዲሳኩና አገራችን ከድህነት እንድትወጣ ዕለት-ሰርክ ደፋ-ቀና ይላሉ፡፡ ዛሬ ሁኔታችን ይሄን መሳይ ነው፡፡ ‹‹ሹም ለሹም ይጎራረሳሉ፤ ድሀ ለድሀ ይላቀሳሉ›› የሚባለው ለዚህ ነው! ሹመትና ሽረት የተለመደ ነው፡፡ ትልቁ ቁም-ነገር የተሾመው ሹም፤ ብቁና ከተሻረው ሹም ስህተትና ጥፋት ምን ተማረ፤ የሚለው ነው! ‹‹ትላንትና ማታ ቤትህ ስትገባ የመታህ የድንጋይ እንቅፋት፣ ዛሬ ማታም ከደገመህ፤ ድንጋዩ አንተ ነህ›› የሚለውን የቻይናዎች አባባል አለመርሳት ነው! ሹመት የብቃት ማረጋገጫ ይሁን!!

   መንግስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በዓመት ሦስት ጊዜ ፓርላማ ገብተው በውይይት እንዲሳተፉ ለማድረግ ማኑዋል እየተዘጋጀ መሆኑን የገለፀ ሲሆን ተቃዋሚዎች በበኩላቸው፣ ሳይወከሉ በፓርላማ ውይይት ህገ መንግስታዊ አይደለም ሲሉ ተችተዋል። ተቃዋሚዎች ለምን አላማ ከመንግስት ጋር በዚህ መንገድ እንዲወያዩ እንደተፈለገ አይገባንም ያሉት የአረና ም/ሊቀመንበር አቶ ጎይቶም ፀጋዬ፤ ውይይቱ በፓርላማ መደረጉ ምናልባት ኢህአዴግ ብቻውን ተቆጣጥሮታል የሚለውን ሃሜት ለማስቀረት ካልሆነ በቀር ሌላ ፋይዳ አይኖረውም ብለዋል። “የተቃዋሚዎች የመወሰን ሚና ጨርሶ በሌለበት ሁኔታ የሚደረጉ ውይይቶች ጥቅማቸው እምብዛም ነው” ይላሉ አቶ ጎይቶም፡፡
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ም/ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ በበኩላቸው፤ ተቃዋሚዎች የህዝብ ውክልና ሳይኖራቸው በፓርላማ መገኘታቸው በምን አግባብ ነው? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ “ፓርላማው ላይ መገኘት የሚቻለው በህዝብ ሲወከሉ ብቻ ነው” ያሉት አቶ ሙላቱ፤ ተቃዋሚዎች የመወሰን ሚና ሳይኖራቸው የሚያደርጉት ውይይት ምንም ፋይዳ አይኖረውም ብለዋል፡፡
“መንግስት ከተቃዋሚዎች ምክር የሚፈልግ ከሆነ፣ በፓርላማው መሆን የለበትም” ያሉት አቶ ሙላቱ፤ ሌሎች ልዩ መድረኮች መዘጋጀት አለባቸው ይላሉ፡፡ ተግባራዊ ይደረጋል ብለው እንደማያምኑ የተናገሩት ም/ሊቀመንበሩ፤ ከዚህ በፊት መሰል የውይይት መድረኮች ይዘጋጃሉ ተብሎ መቅረቱን ያስታውሳሉ፡፡ አሁን መንግስት ማድረግ ያለበት ለህዝብ ጥያቄ መልስ መስጠት ነው ብለዋል - አቶ ሙላቱ፡፡
የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል የሆነው የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ በበኩላቸው፤ “መንግስት ከተቃዋሚዎች ጋር ይወያያል የተባለው ከ2002 ምርጫ ማግስት ጀምሮ ነው፤ ሆኖም ተፈፅሞ አያውቅም፤ የአሁኑም የፓርላማው ውይይት የተስፋ ቃል ነው” ይላሉ፡፡
የመንግስትና የተቃዋሚዎች ውይይት እስካሁን ተግባራዊ ሲሆን አለማየታቸውን የገለፁት አቶ ተሻለ፤ “በእውን የሚደረግ ከሆነም፣ “በምን አግባብ ይከናወናል? መቼ ነው የሚጀምረው? እንዴት ነው ተቃዋሚዎች የሚሳተፉት? የሚሉትን ጥያቄዎችን መመለስ አለበት” ብለዋል፡፡ “የውይይት መድረኩ እውን ይሆናል ብለን እንድናምንና ምልክቶች መታየት አለባቸው ብለዋል” - ሲሉ አክለዋል፡፡
“የተቃዋሚዎች በፓርላማ መሳተፍ ምንን መርህ አድርጎ ነው? ህገ መንግስታዊ ነው? በአዋጅ የሚያሳትፍ ነው? የፖሊሲ አቅጣጫ አለው?” ሲሉ የጠየቁት የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ በበኩላቸው፤ “ተቃዋሚዎች በምን መንገድ፣ የትኛውን የህብረተሰብ ክፍል ወክለው  ነው በፓርላማ ሊሣተፉ የሚችሉት” ብለዋል፡፡
‹‹መንግስት ቅድሚያ መስጠት ያለበት ለህዝቡ ቀጥተኛ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ላይ ነው ያሉት ዶ/ር ጫኔ፤ በአሁኑ ሰዓት ህዝብ ለተቃዋሚዎችም ለመንግስትም ፍላጎት ባላሳየበት ሁኔታ ተቃዋሚዎች በምን አግባብ ነው ፓርላማ ገብተው ሊነጋገሩ የሚችሉት ሲሉ ጠይቀዋል፡፡  ኢዴፓ ተቃዋሚዎችን ፓርላማ አስገብቶ በመወያየት ብቻ ችግሮች ይቀረፋሉ የሚል እምነት  እንደሌለው የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፤ ፓርቲያቸው የፖሊሲ አቅጣጫዎች እንዲሻሻሉና ህግ ሙሉ ለሙሉ እንዲከበር እንደሚፈልግ ገልፀዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስና የፌደራሊዝም መምህር አቶ ናሁሠናይ በላይ የፓርላማውን ውይይት በተመለከተ ተጠይቀው ሲመልሱ፤ በፓርላማው ለየት ያለ ሃሳብ እንዲንፀባረቅ መፈለጉ መልካምና ጠቃሚ መሆኑን ገልፀው፤ የተቃዋሚዎች ሚና የሚለካው ከገዥው ፓርቲ ጋር በመገናኘታቸው ብቻ አይደለም፤ ገዥው ፓርቲ በተቃዋሚዎች ሚና የሚያምን ከሆነ፣ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ የሚንቀሣቀሱበትን የመጫወቻ ሜዳ ምቹ ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡
“ኢህአዴግ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገንቢ ሚና አላቸው ብሎ ማመን መጀመሩን ለማሳየት ከፈለገ፣ በፖለቲካ እንቅስቃሴያቸው ላይ እንቅፋት ከመሆን መቆጠብ ይኖርበታል፤ በአመት ሶስት ጊዜ ተቃዋሚዎችን በፓርላማ አሳትፋለሁ ማለት ብቻውን በቂ አይደለም፤ የተለያዩ መድረኮች መዘጋጀት አለባቸው” ያሉት ምሁሩ፤ “አሁን የሃገሪቱ ሁኔታ እንደ ቀድሞ የኔ ሃሳብ ብቻ  ይሰማ የሚባልበት ባለመሆኑ፣ ኢህአዴግ ከልቡ ተምሮ ከሆነ፣ ይህን ውጥኑን ተግባራዊ ሊያደርግ ይችላል” ሲሉ እምነታቸውን ገልፀዋል፡፡

     የታዋቂው ሞታውን ሪከርድስ ኩባንያ ፕሬዚዳንትና የአለማችን ትልቁ ሙዚቃ አሳታሚ ኩባንያ የዩኒቨርሳል ሚዩዚክ የኧርባን ሚዩዚክ ፕሬዚዳንት የሆነችው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኩባንያ ስራ አስኪያጅ ኢትዮጵያ ሃብተማርያም፣ በቢልቦርድ የ2016 የአለማችን ምርጥ 100 የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ስራ ስኪያጅ ሴቶች ዝርዝር ውስጥ ተካትታለች፡፡
በአለማችን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ የተሳካ ተግባራት የፈጸሙ የዘርፉ ኩባንያዎችን የሚመሩ ሴት የስራ አስፈጻሚዎችንና ማናጀሮችን እየመረጠ በየአመቱ ይፋ የሚያደርገው ቢልቦርድ፣ ሰሞኑንም ኢትዮጵያ ሃብተማርያምን ጨምሮ በአሳታሚነት፣ በአከፋፋይነትና በሌሎች ተያያዥ መስኮች የተሰማሩ ኩባንያዎችን የሚመሩ የአመቱ 100 ምርጥ ሴቶችን ዝርዝር አውጥቷል፡፡ የ37 አመት እድሜ ያላት ኢትዮጵያ ሃብተ ማርያም በምትመራቸው የሙዚቃ ኩባንያዎች አማካይነት በአመቱ ባከናወነቻቸው ተግባራት፣ ከአለማችን ምርጥ የሙዚቃ ኩባንያ መሪ ሴቶች ተርታ መሰለፏን ቢልቦርድ በድረገጹ ባስነበበው መረጃ ገልጧል፡፡ እ.ኤ.አ በ2011 የታላቁ የአለማችን የሙዚቃ ኩባንያ ሞታውን ሪከርድስ ከፍተኛ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን የተሾመችው ኢትዮጵያ፤ ስቲቪ ዎንደርን ጨምሮ ከአለማችን ታላላቅ ድምጻውያን ጋር ስኬታማ ስራዎችን በማከናወን ወደ ፕሬዚዳንትነት ማደግና በዩኒቨርሳል ሚዩዚክ ኩባንያ የኧርባን ሚዩዚክ ፕሬዚዳንት ሆና መስራት መቻሏ ተነግሯል፡፡
ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2014 በዚሁ የቢልቦርድ የአለማችን ምርጥ 100 የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ሴቶች ዝርዝር ውስጥ ተካትታ እንደነበርም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ስልጠናና የቴክኒክ ድጋፍ እንሰጣለን ብለዋል

   በዓለም ታዋቂና ቀዳሚ ከሆኑት የኬክና ዳቦ አምራች ድርጅቶች አንዱ የሆነው ቤከልስ በቅርቡ ከተከፈተው ራማዳ አዲስ ሆቴል ጋር በመተባበር፣ ደረጃውን የጠበቀ ኬክና ዳቦ ለአዲስ አበባ ነዋሪ ሊያቀርብ ነው፡፡
ታዋቂው ጀርመናዊ ሼፍ ባስቲያን ኤቬርሰማን ትናንት በራማዳ አዲስ ሆቴል፣ ትክክለኛ ኬክና የዳቦ መጋገሪያ ቁሶችን (ዱቄት የተለያዩ ዓይነት ቸኮሌቶች…) በማቅረብ፣ ከተለያዩ ሆቴሎች ለተጋበዙ እንግዶች በመጋገር አሳይቷል፡፡
አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ከተማ በመሆኗ ጥራት ያለውና ደረጃውን የጠበቀ ኬክና ዳቦ ማቅረብ አለብን ያሉት ሚ/ር ባስቲያን፤ ከ5 ኮከብ ሆቴሎች ጀምሮ አነስተኛ ኬክና ዳቦ መጋገሪያዎች፤ ትክክለኛውን ቁስ እንዲጠቀሙ፣ ለሁሉም የኬክና ዳቦና ዘርፍ ኢንዱስትሪ የቴክኒክ ድጋፍ፣ ጥራት ያለውት ምርት….. እናቀርባለን ብለዋል፡፡
ማንኛውም ሆቴልና ኬክና ዳቦ መጋገሪያ ትክክለኛውን ጥሬ ዕቃ ከራማዳ አዲስ ሆቴል ጋር በመነጋገር ሊያገኝ እንደሚችል ተገልጿል፡፡

     የሆላንድ ካር ኩባንያ ግማሽ ባለሀብት የሆኑት ኢ/ር ታደሰ ተሰማ፤ በኩባንያቸው ላይ እየተደረገ ያለውን ምርመራ በተመለከተ ለጠ/ሚኒስትሩና ለፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቤቱታ አቀረቡ፡፡
ባለሀብቱ ህዳር 27 ቀን 2009 ዓ.ም ለዋና ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ጌታቸው አምባዬና ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በፅሁፍ ባቀረቡት አቤቱታ፤ “በፍ/ቤት የኪሳራ ውሳኔ የተላለፈበትን ሆላንድ ካር ኩባንያ በተመለከተ የኪሳራውን ሂደት እንዲያከናውኑ በተሾሙት መርማሪ ዳኛ ላይ እምነት አጥቻለሁ›› ብለዋል፡፡
ባለሀብቱ እየተፈፀመ ነው ያሉት በስልጣን አለአግባብ መጠቀምና ሙስና እንዲጣራላቸው ጠይቀዋል - በአቤቱታቸው፡፡
በዘጠኝ ነጥቦች ዘርዝረው እየተፈፀሙ ናቸው ያሏቸውን ስህተቶች ያቀረቡት ባለሀብቱ፤ ኪሳራ አጋጥሞታል የተባለው ኩባንያቸው በአንድ ወቅት በሀገሪቱ ካሉ ኩባንያዎች ከፍተኛ ግብር ከፋይ የነበረና ታማኝ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ተብሎ የተሰየመ ድርጅት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡  ሆላንድ ካር፤ ዶክ፣ አባይ፣ አዋሽ፣ ተከዜና ናኦሚ የተሰኙ አውቶሞቢሎችን በአገር ውስጥ በመገጣጠም ይታወቅ እንደነበር ይታወሳል፡፡

  አቢሲኒያ ባንክ በቅርቡ ባደረገው የባለአክሲዮኖች 20ኛ መደበኛና 11ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤዎች ላይ ለግብረሰናይ ድርጅቶች እንዲለገስ የተወሰነውን የግማሽ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለተመረጡ 7 ግብረሰናይ ድርጅቶች ሰጠ፡፡
ባንኩ ባለፈው ሳምንት በቅርቡ ለተቀዳሚ ደንበኞች ማስተናገጃ በከፈተው ልዩ ሐበሻ ቅርንጫፍ በተደረገው የርክክብ ሥነ ስርዓት ላይ የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ አስማረ ባደረጉት ንግግር፣ ባንካችን ከምስረታው ጀምሮ ላለፉት 20 ዓመታት ከበርካታ የግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር አብሮ በመስራት ማኅበራዊ ግዴታውን ሲወጣ ቆይቷል ብለዋል፡፡
በዕለቱ ድጋፍ የተደረገላቸው 7 ግብረሰናይ ድርጅቶች፡- የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የ200 ሺህ ብር፣ መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል የ100 ሺህ ብር፣ ለዓለም የሕፃናት ዕርዳታ ድርጅት 60 ሺህ ብር፣ ርዕይ ለትውልድ የ50 ሺህ ብር፣ ነህምያ ኦቲዝም ማዕከል የ40 ሺህ ብር፣ የጎንደር መልሶ ማቋቋምና ልማት ማኅበር የ25 ሺህ ብር፣ ፍሬገነት ኪዳን ለህፃናት የ25ሺ ብር ቼክ ከባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ከአቶ መሰረት ታዬ እጅ ተቀብለዋል፡፡
“ከተመሰረትን አጭር ጊዜ ቢሆንም ይዘን የተነሳነው ራዕይ ትልቅ ነው፡፡ በ2020 ዓ.ም (ከ11 ዓመት በኋላ ማለት ነው) 10 ሺህ ህፃናት ራዕይ ኖሯቸው አገር የሚቀይሩ ትልቅ ቦታ የሚደርሱ ዜጎችን መፍጠር ነው” ያሉት የርዕይ ለትውልድ ፕሬዚዳንት፤ የድርጅቱ ዓላማ፣ ከተለያዩ ድርጅቶች ድጋፍ በመጠየቅ የድሃ ቤተሰብ ልጆች ምግብ እንዲበሉ ማድረግ፣ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችና ዩኒፎርምም ማቅረብ ነው ብለዋል፡፡

Monday, 05 December 2016 10:02

የፍቅር ጥግ

 · አንድ ላይ መሆን የቱንም ያህል አስቸጋሪ ቢሆን ግዴለኝም፤ ለብቻ ከመሆን በላይ የከፋ ነገር የለም፡፡
    ጆሴፊኔ አንጄሊኒ
· የትም ብሄድ ልዩነት የለውም፤ ሁልጊዜ ወዳንተ መመለሺያ መንገዱን አውቀዋለሁ፡፡ አንተ አቅጣጫ ማመላከቺያ ኮከቤ ነህ፡፡
   ዲያና ፒተርፍሬዩንድ
· “እወድሻለሁ” - የሁሉም ነገር መጀመሪያና መጨረሻ ይኸው ነው፡፡
   ኤፍ. ስኮት ፊትዝጌራልድ
· ሁለመናዬ ሁሉመናሽን ይወደዋል፡፡
   ጆን ሌጀንድ
· ፍቅር፤ ለሰው ልጅ ብዙዎቹ ህመሞች ድዌዎች ፈውስ ነው፡፡
   ዊሊያም ሜኒንገር
· እውነተኛ የፍቅር ታሪኮች መጨረሻ የላቸውም፡፡
   ሪቻርድ ባች
· ፍቅር እሳት ነው፡፡ ነገር ግን ልብህን ያሙቀው አሊያም ቤትህን ያቃጥለው መገመት አትችልም፡፡
   ጆአን ክራውፎርድ
· በዓይኖችህ ሳይሆን በልብህ አፍቅር፡፡
   ድሬክ
· በፍቅር ስሜት ብቻ ነው የማምነው፡፡
   ካርሴና ካፑር ክሃን
· መፈቀር ብ ቻ አ ይደለም የ ምሻው፤ መ ፈቀሬም እንዲነገረኝ ጭምር እንጂ፡፡
   ጆርጅ ኢሊዮት
· በህይወት ውስጥ አንድ ደስታ ብቻ ነው ያለው- ማፍቀርና መፈቀር፡፡
   ጆርጅ ሳንድ

Monday, 05 December 2016 09:59

ስናውቃቸው የሚገርሙን!!

 · አንድ ፓውንድ (453.6ግራም) ማር ለማምረት፣ አንድ ንብ 2 ሚሊዮን አበቦችን መቅሰም ይኖርበታል፡፡
· የዓለም የህዝብ ቁጥር እ.ኤ.አ በ2080 ወደ 10.8 ቢሊንዮ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
· በህይወት ዘመናችን ሁለት የዋና ገንዳዎች የሚሞላ ምራቅ እናመርታለን፡፡
· መዝለል የማይችል ብቸኛው አጥቢ እንስሳ ዝሆን ነው፡፡
· እንደ ጣት አሻራ ሁሉ እያንዳንዱ ሰው የተለያዩ የምላስ አሻራዎች አሉት፡፡
· የሲጋራ መለኮሽያ ላይተር የተፈለሰፈው ከክብሪት በፊት ነው፡፡
· የተራራ አንበሶች ማፏጨት ይችላሉ፡፡
· ቢራቢሮዎች ምግባቸውን የሚቀምሱት በእግሮቻቸው ነው፡፡
· ዶልፊኖች የሚተኙት አንድ ዓይናቸውን ገልጠው ነው፡፡
· የጥርስ መቦረሽያ ‹‹ኮልጌት›› በስፓኒሽ ቋንቋ ‹‹ሂድና ራስህን ስቀል›› ማለት ነው፡፡
· አንድ አማካይ ሰው በህይወት ዘመኑ 6 ወራትን ቀይ የትራፊክ መብራት ወደ አረንጓዴ እስኪለወጥ ይጠብቃል፡፡
· የሰው ልጅ ተኝቶ ሳለ፤ በአማካይ 70 የተለያዩ ነፍሳትንና
10 ሸረሪቶችን ይበላል ወይም ወደ ሆዱ ያስገባል፡፡
· ሰው እስትንፋሱን በመግታት ነፍሱን ማጥፋት
አይችልም፡፡

Monday, 05 December 2016 09:57

የማሰላሰያ ጥግ

 ለመጨረሻ ጊዜ አዲስ ነገር የሞከራችሁት መቼ ነው?
መኖር የምትችሉት ለ1 ዓመት ብቻ ቢሆን፣ ምን ለማሳካት ትፈልጋላችሁ?
ዓይናችሁን ስትጨፍኑ ምን ታልማላችሁ?
ስለራሳችሁ እጅግ አድርጋችሁ የምትወዱት ምንድን ነው?
ህይወታችሁን እንደ ፊልም ብትቆጥሩት፣ ርዕሱን ምን ትሉታላችሁ?
ራሳችሁን በ5 ቃላት እንዴት ትገልጹታላችሁ?
በጣም የምትኮሩበት ነገር ምንድ ነው?
ህይወት ትላንት ምን አስተማረቻችሁ?
ምን መጥፎ ልማዶችን ማቆም ትፈልጋላችሁ?
እናንተን ልዩ የሚያደርጋችሁ ምንድ ነው?
በጣም የምትፈልጉት ነገር ምንድን ነው?

ባለፈው 1 ዓመት የታተሙ መፃህፍት ይወዳደራሉ
     በረዥም ልቦለድ፣ በግጥምና በልጆች መፃህፍት ዘርፍ የሥነ ፅሁፍ ሥራዎች ተወዳድረው ሊሸለሙ ነው።
ኖርዝ ኢስት ኤቨንትስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከብሄራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃህፍት ኤጀንሲ ጋር በትብብር ያዘጋጁት ሆሄ የሥነፅሁፍ ሽልማት ፕሮግራም፤ አሸናፊ ደራስያንን ከመሸለም ባሻገር የንባብ ባህል እንዲስፋፋ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ላበረከቱ ክበባትንና ቤተ መፃህፍትም የሚመሰገኑበትና ዕውቅና የሚያገኙበት ይሆናል ተብሏል፡፡
የሽልማት ፕሮግራሙ አዘጋጆች ከትናንት በስቲያ በጎተ ኢንስቲትዩት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ ለውድድር የሚቀርቡት መፃህፍት ከመስከረም 1 ቀን 2008 እስከ ጳጉሜ 5 ቀን 2008 ዓ.ም ድረስ የታተሙ መሆን አለባቸው፡፡ ተወዳዳሪ መፃህፍቱ በዳኞች ኮሚቴ በተዘጋጀላቸው መስፈርቶች መሰረት የሚመዘኑ ሲሆን በዳኞች ኮሚቴ ከሚሰጠው ውጤት በተጨማሪ አንባቢያን በነፃ የስልክ መልዕክትና በድረ ገፅ የሚሰጡት ድምፅም የተወሰነ ነጥብ ይኖረዋል ተብሏል። አጠቃላይ ውጤቱ የሚታወቅ ይሆናል፡፡
በውድድሩ መሳተፍ የሚፈልጉ ደራሲያን ከታህሳስ 4-19 2009 ዓ.ም ሞርኒንግ ስታር ሞል ላይ በሚገኘው የድርጅቱ ቢሮ፣ በጎታ ኢንስቲቲዩትና በቡክላይት መፅሀፍ መደብር መመዝገብ እንዳለባቸው የጠቆሙት አዘጋጆቹ፤ የሽልማት ስነ ስርዓቱ በሚያዚያ ወር አጋማሽ ላይ እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡