Administrator

Administrator

በሞንጎሊያ ከተማ ከብዙ አመታት በፊት ተስቦ ገብቶ ብዙ ሺ ህዝብ ፈጀ፡፡ ጤነኞቹ በሽተኞቹን እየጣሉ ሸሹ፡፡ እንዲህም አሉ፡፡
“እጣ ፈንታ እራሱ’ኮ ኗሪውን ከሚሞተው ያበጥረዋል”
ያን ቦታ ለቅቀው ከሄዱት መካከል ታሪቫ የተባለ የ15 ዓመት ልጅ ይገኝበታል፡፡
የታሪቫ ነብስ ስጋውን ለቅቃ ከሞቱት የሬሳ ክምሮች መካከል አቋርጣ ወደ ደቡብ ሄደች፡፡     
በመጨረሻም የገሃነም  ኃላፊ ዘንድ ደረሰች፡፡ ኃላፊውም በመገረም፤
“ስጋሽ ገና ህይወት አልባ ሳይሆንና እየተነፈስሽ ሳለ ለምን ጥለሽው መጣሽ? ሲል ጠየቃት ነብሲቱን፡፡
የታሪቫ ነብስም፡-
“ጌታዬ ነዋሪዎቹ ሁሉ ስጋዬ እንደሞተ ነው የተገነዘቡት፡፡ ስለዚህ እኔ ለአንተ ታማኝነቴን ለመግለፅ ነው የመጣሁት፡፡“
የገሃነሙ ኃላፊ ከታሪቫ ነብስ በሰማው በጣም ተገረመና፤ “ታሪቫ የአንተ ጊዜ እንዳልደረሰ አረጋግጥልሀለሁ፡፡ ስለዚህ የእኔን ፈጣን ፈረስ ውሰድና በወፎች ግዛት ወዳለው ጌታ ሂድ፡፡ ሆኖም ሳትሄድ በፊት ከዚህ አንድ የፈለግከውን ነገር ይዘህ ለመሄድ እንድትችል የመምረጥ እድል እሰጥሀለሁ፡፡ ግን ተጠንቀቅ! እዚህ ሀብት፣ መልካም እድል፣ ጤና፣ ናፍቆት፣ ሀዘን፣ ለቅሶ፣ ብልህነት፣ ጉጉትና ምስጋና  ሁሉ አሉ፡፡ ና ከነዚህ ሁሉ አንዱን ምረጥ፡፡”
“ጌታዬ እኔ የምመርጠው ታሪኮቹንና ተረቶቹን ነው” አለው፡፡ ከዚያም ታሪኮቹንና ተረቶቹን ሁሉ በኮሮጆ አጨቀለትና ፈጣን ፈረሱን ይዞ ፈረጠጠ፡፡ እዚያ ሲደርስ አንድ ቁራ ከስጋ-አካሉ አይኑን ፈልፍሎ አውጥቶ ወስዶት ደረሰ፡፡ በመሆኑም ሥጋ-አካሉ ታወረ፡፡ ታሪቫ ወደሬሳዎቹ ክምችት ተመልሶ ለመሄድ አልደፈረም፡፡ ስለሆነም ያንኑ የጥንቱን የገዛ ስጋውን ለበሰ፡፡
ከዚያን ጊዜ ወዲህ አይነ-ሥውር ሆኖ መኖር ጀመረ፡፡ ያም ሆኖ በመቶ ለሚቆጠሩ አመታት በሞንጎሊያ ምድር በፈረስ ከአልዩ ተራሮች በስተምእራብ፣ ወደ ደቡብ እስከ ጉቢ በረሀ እስከ ሀንቴ ኑራ ድረስ እየተዘዋወረ፣ ተረቶችን እየተናገረ፣ የወደፊቱን እየተነበየ ለጎሳዎች አገራቸውን መልካም ለማድረግ ምን ማድረግ እንደሚገባቸው ሲያስተምር ኖረ፡፡ እንግዲህ ከዚያ ወዲህ ነው ሞንጎላውያን አንዱ ለሌላው ተረት መንገር የጀመሩት ይባላል፡፡
“እስቲ እንደ ታሪቫ ወደ ደቡብ ልሂድ፡፡ በእውነተኛው ኑሮዬ ውስጥ የረባ መመሪያ ካጣሁ ምናልባት በአፈ- ታሪኮቹ ውስጥ አገኝ ይሆናል” የሚሉት ለዚህ ነው፡፡
*    *    *
ነዋሪው ህዝብ ስጋህ ሞቷል፡፡ ነብስህንም ለሲኦል አዘጋጃት ከሚልበት ክፉ ጊዜ ይሰውረን፡፡ ጊዜያችን ሳይደርስ ሞተናል ከማለት፣ ጊዜያችን ደርሶም “አለሁ ዘራፍ” ከማለት ይሰውረን፡፡ በባህላችን ውስጥ ያለውን ትልቁ-እሴት የምናይበት አይን እንዳናጣ እንጠንቀቅ፡፡ መልካሙን ነገር ለማየት የግድ ሲኦል ደጃፍ መድረስ የለብንም፡፡ ዛሬ ውሎዬ እንዴት ነበር ብለን እራሳችንን እንጠይቅ፡፡ ዛሬ ግፍ የተሞላ ቀን ውለን ከሆነ፣ ለነገ ራሳችንን ወቅሰን ንስሀ ገብተን እንዘጋጅ፡፡ ታሪኮቻችንና ተረቶቻችን ቅርሶቻችን ናቸው፡፡ ሁሉም መሬት የረገጠ እውነታ ጭማቂዎች ናቸው፡፡ የውሏችን አሻራ ናቸው፡፡ የሚነግሩንን ልብ ማለት ብቻ ሳይሆን መተግበርም ይጠበቅብናል፡፡ የተወሳሰበ ጭንቅላት ውስጥ በቀላሉ መግባት የሚችሉትን ያህል፣ ጭንጫ-ድፍን ልብንም አረስርሰው ሊሰርጉበት ይችላሉ፡፡ የየእለት ውሎአችን ንጥር ውጤቶች በመሆናቸውም፣ እውነቱን ገላጭ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ የህብረተሰቡን ቅርፊቱን ሳይሆን ቡጡን የማሳየት ሀይል አላቸው፡፡ እንደሞንጎሎች የወደፊቱን ለመተንበይና ጎሳዎች አገራቸውን መልካም ለማድረግ ምን መፈፀም እንደሚገባቸው እንናገርባቸዋለን፡፡ እንደሞንጎሎች በእውነተኛው ኑሮ ውስጥ ረብ ያለው መርህ ሲታጣ፣ አፈታሪኮቹ ውስጥ ለማግኘትም ይቻል ይሆናል ማለት አይከፋም፡፡
ለሀገር ህልውናና ለህዝብ ብልፅግና አንዳች ነገር ማገዝ አለብኝ ያለ ሁሉ አስቀድሞ አቅሙን ከልቡናው ጋር ማስታረቅ አለበት፡፡ አለበለዚያ ልብ ወዲህ አቅም ወዲያ ይሆንና ለፍቶ -መና መሆን ይከተላል፡፡ “ክረምት የሚያወጣን ቁርስና ዳገት የሚያወጣን ጉልበት ባለቤቱ ያቀዋል” ይባላል፡፡ በሀገራችን ጉዳይ ያገባናል የሚሉ መንግስታዊ ተቋማት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ድርጅታዊ ሃይሎች ሁሉ ቁርሳቸውንና ጉልበታቸው መመርመርና ዳግም ማየት ይገባቸዋል፡፡ የያዙትን ህዝባዊ አቅም አጥርተው ማወቅ አለባቸው፡፡ የህዝብ ድጋፍ ሲባል እውነተኛ የህዝብ ድጋፍ መሆኑንም ልብ ማለት ይኖርባቸዋል፡፡ ከዳር-አገር እስከ ማህል-አገር ያለውን ህዝብ እንደምን ልብ ለልብ አግባባዋለሁ ማለት ይገባቸዋል፡፡ ትላንት የደገፈኝ ዛሬ ሊገፋኝ ይችላል ብለው ማጤን ይኖርባቸዋል፡፡ ትላንት አለህ ያለኝ ዛሬ ሞተሃል ቢለኝስ ብሎ ማውጠንጠን ተገቢ ነው፡፡ ስህተትን፣ ማንነትን፣ የወደፊት ጎዳናን ለማየት ህዝቡስ ምን አለ? ማለት ደግ ነው፡፡ “እረኛ ምን አለ?” እንዲል፡፡
የሀገራችን የፖለቲካ ሰዎችና ቡድኖች ታሪክ በሰፊው እንደሚያስገነዝበው አንዱ ትልቅ እክላቸው መናናቅ ነው፡፡ አንዱ አንዱን ቁልቁል ማየት! ሽማግሌ መሞቱን፣ ልጅ ማደጉን መዘንጋት! እኔ እዚህ እደርሳለሁ፣ ይሄንን አደርጋለሁ ከማለት ይልቅ እነገሌ የትም አይደርሱም ማለት! ትልቅ የማይመስል ግን እጅግ ግዙፍ እክል ነበር፤ ነውም፡፡ አንድ ደራሲ እንዳለው፤ “ልብ ብጉንጅ ካበቀለ መፍረጥ እንጂ ደግ መሆን አይሆንለትም፡፡” ደግ ማሰብ ደግ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ስለ መቻቻል ሲባል፣ ስለ ሰላም ሲባል፣ ስለ ዲሞክራሲ ሲባል፣ ደም ላለመፋሰስ ሲባል ደግ መሆን ያስፈልጋል፡፡ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ብልጭታን የማያደንቅ ልብ ሊኖር ያሻል፡፡ ቀና አስተሳሰብን ማጎልበት ያስፈልጋል፡፡ በመናናቅ፣ አንዱ አንዱን በማኮሰስ ቤት ማፍረስ እንጂ መገንባት ዘበት ነው፡፡ ወላይታዎች “ሚስት የራሱ ጉዳይ ስትል፣ ባል ቸል ሲል፣ ቤቱ ለውሻ ይቀራል፡፡” የሚሉት ለዚህ ነው፡፡ አገር ቤት መሆኗን አንርሳ፡፡   

Saturday, 14 September 2024 12:34

የጃፓን ትዝታዎቼ

በ1984 ዓ.ም አስራ አንድ ወራት ያህል ለሚፈጅ ስልጠና  ጃፓን ሀገር ሄጄ ነበር፡፡ በጃፓን ሀገር ቆይታዬ ከማይረሱኝ ትዝታዎቼ መሀከል የተወሰኑትን እነሆ፡፡
ስልጣኔ፡  ሁላችንም እንደምናውቀው ጃፓን፣ የስልጣኔ ማማ ላይ ከደረሱ ጥቂት የአለማችን ሀገሮች አንዷ ናት፡፡ ካስደነቁኝ ነገሮች መሀከል ለማሳያነት ሁለቱን እዚህ ላይ እጠቅሳለሁ፡፡
ትራንስፖርት፡ ከትራንስፖርት ሥርዓታቸው ውስጥ የማነሳው የባቡር ትራንስፖርትን ነው፡፡ የባቡር ትራንስፖርት ሥርዓታቸው እጅግ በጣም የተደራጀና የተሳለጠ ነው፡፡ እኔ የተማርኩት የጃፓን ሁለተኛ ከተማ በሆነችው ኦሳካ ነው፡፡ ጧት ከምኖርበት አፓርታማ በብስክሌት ባቡር ጣቢያ ድረስ እሄዳለሁ፥ ብስክሌቴን እዚያው ባቡር ጣቢያ ውስጥ በሚገኝ የብስክሌት ማቆሚያ ቦታ አቆማትና በባቡር ት/ቤቴ ወደሚገኝበት ኪዮቶ ከተማ እሄዳለሁ፡፡ ብስክሌት በማቆምበት ቦታ ምንም ጠባቂ የለውም፥ በመሆኑም የህዝቡን የታማኝነት ባህል ልብ እንበል፡፡ ባቡር የምይዝበት ሰአት የተወሰነ ነው፡፡ ከዚያ ባቡሩ ምን ያህል ሰአት እንደሚያከብር ለማወቅ አሰብኩኝና ማጥናት ጀመርኩኝ፡፡ በወቅቱ የነበረችኝ ሰአት በጣም ትክክለኛ(very accurate) ነበረች፡፡ ከዚያ አንድ ቀን በስንት ሰአት እኔ ባቡር የምይዝበት ጣቢያ እንደደረሰ መዘገብኩ፥ የመዘገብኩት ሰአቱን፥ ደቂቃውንና ሰከንዱን ነበር፡፡ በመቀጠልም በተከታታይ ቀናት ባቡሩ በጣቢያው ስንት ሰአት እንደደረሰ መዝግቤ መጀመሪያ ከመዘገብኩት ጋር ሳወዳድረው የጥቂት ሰኮንዶች ልዩነት እንኳን አላገኘሁበትም፡፡ ባቡሩ ደግሞ በየ20 ደቂቃው ይመጣል፡፡ በመሆኑም የባቡር አገልግሎት የጊዜ አጠባበቃቸው(time accuracy) በጥቂት ሰኮንዶች የሚለካ መሆኑን ተረዳሁ፡፡ ይህ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ውጤታማነታቸውን ከሀገራችን ሁኔታ ጋር አወዳድሬ ስላየሁት ነው መሰለኝ እጅግ በጣም አደነቅሁት፡፡ ጃፓን ለሚኖር ግለሰብ ለቅንጦት ካልሆነ በስተቀር የግል መኪና መጠቀም አስፈላጊነቱ ብዙም አልታየኝም ያስባለኝን አገልግሎት ነው ያየሁት። ከሀብታቸው፥ ከከተማቸው ዘመናዊነትና ከቁሳዊ ብልፅግናቸው የበለጠ የገረመኝ ለስራ ያላቸው አክብሮትና ለጊዜ የሚሰጡት ዋጋ በጣም ከፍተኛ መሆኑ ነው፡፡ ለነኚህ ሁለት ትልልቅ እሴቶች ያላቸው አክብሮት በባቡር ትራንስፖርት ሥርዓታቸው ብቻ ሳይሆን፣ ባየኋቸው የስራ ቦታዎች ሁሉ የታዘብኩት ነገር ነው፡፡ የጃፓን ህዝብ የስራ ክቡርነትና የጊዜን ጠቀሜታ በሚገባ ተገንዝቦ እነኚህን እሴቶች ተግባራዊ በማድረጉ፣ በኢኮኖሚ በልፅጎ አሁን የደረሰበት ደረጃ ደርሷል፡፡ እኛስ? እኛም የስራ ክቡርነትና የጊዜን ጥቅም በሚገባ ተረድተን ተግባራዊ ማድረግ ስንጀምር ማደግ አንጀምራለን፡፡ መቼ? ለሚለው ጥያቄ መልሱን ለናንተ ትቼዋለሁ፡፡
የደን ሽፋን፡ የጃፓን የቆዳ ስፋት የኢትዮጵያን ሲሶ ያህል ቢሆን ነው፡፡ ከዚህ የቆዳ ስፋት ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው ሰው ሊኖርበት የማይችል ጋራና ተራራ ነው፡፡ በመሆኑም ሰው ሊኖር የሚችልበት መሬት ከቆዳ ስፋቷ 30 በመቶ ላይ ብቻ ነው፡፡ ቶኪዮና ኦሳካን ጨምሮ ትላልቅ ከተሞቿ በአብዛኛው በባህር አጠገብ(Coastal area) የተቆረቆሩ ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የህዝብ ብዛቷ ወደ 127 ሚሊዮን ይጠጋል፡፡ የደን ሽፋኗ እኔ በሄድኩበት ወቅት 66% አካባቢ ነበር፡፡ ይህም ማለት ሰው ሊሰፍርበት የማይችለው ጋራና ተራራዎቿ ቢያንስ ከሰማኒያ በመቶ በላይ ሊባል በሚችል ደረጃ በደን የተሸፈነ ነው፡፡ ይህ እውነታ ደግሞ ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ በባቡር ሲኬድ በግልፅ የሚታይ ነገር ነው፡፡
የጃፓን ከተሞች ፅዱና የተዋቡ ናቸው፡፡ ፓርኮች በብዛት አሉዋቸው፡፡ ከከተማ በባቡር ወይም በመኪና ሲወጣ የሚታየው በአብዛኛው የሩዝ እርሻ ወይም እርሻ ከሌለ የተፈጥሮ ደን ነው፡፡ ከከተማቸው ባልተናነሰ የገጠሩ አካባቢ ልምላሜ እጅግ በጣም ይማርካል፤ ያስቀናል፡፡ አሁን ያለው የደን ሽፋናቸው ቢያንስ ቢያንስ ከዛሬ ሰላሳ ሁለት ዓመት በፊት ከነበረው 66%  እንደማያንስ እርግጠኛ  ሆኖ መናገር ይቻላል፡፡ ምክንያቱም የጃፓን መንግስት በፖሊሲው የደን ሽፋኑን በመጠበቁ ብቻ ሳይሆን፣ ህዝቡም ከተፈጥሮ ጋር ተከባብሮ፤ ተጠባብቆና ተዋዶ የመኖር የረዥም ጊዜ ባህል ያለው በመሆኑ ነው፡፡ (በኛም ሀገር የተፈጥሮ ደንን መጠበቅ ባህላቸው የሆኑ ብሄረሰቦች እንዳሉ ይታወቃል፡፡)
ይህ የጃፓን ህዝብ አመለካከት ከሚከተሉት ፍልስፍናና እምነት ጋርም በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ ከተማን ከመገንባት ባሻገር ከተፈጥሮ ጋር ተከባብሮና ተደጋግፎ በመኖር ደኖችን መጠበቅ የስልጣኔ አንዱና ዋናው ምልክት መሆኑን በተግባር ያስመሰከረች ሀገር ናት፥ ጃፓን፡፡ በዚህም ጉዳይ ላይ እኛስ? ብሎ መጠየቁ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በኔ ግምት መልሱ የሚታዩ ጅምሮች አሉ፥ ይሁን እንጂ ብዙ መንገድ ይቀረናል።
የቤተሰብ ስም (Family name)፡ ጃፓን በወሰድኩት ትምህርት ላይ ከ8 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጣን 8 ተማሪዎች ነበርን፡፡ ፕሮግራሙ አስር ተማሪዎች እንዲኖሩት የታቀደ ቢሆንም፥ ከኮንጎ ኪንሻሳ መምጣት የነበረበት ልጅ ሀገሪቱ በእርስ በርስ ጦርነት ላይ ስለነበረች ባለመምጣቱ፥ የዚምባብዌው ልጅ ደግሞ ጃፓን ድረስ መጥቶ ትምህርት ከመጀመራችን በፊት ሙሉ የጤና ምርመራ በተደረገልን ወቅት ከባድ የጤና እክል ስለታየበት ወደሀገሩ እንዲመለስ በመደረጉ ስምንት ተማሪዎች ብቻ ነበርን በስልጠናው ላይ የተሳተፍነው፡፡ የተሳተፍነው ከኢትዮጵያ፥ ኬንያ፥ ታንዛኒያ፥ ሱዳን፥ ማላዊ፥ ዛምቢያ፥ ጋናና ሴኔጋል የተውጣጣን የአፍሪካ ልጆች ነበርን። የእኔና የሱዳኑ ልጅ የቆዳ ቀለማችን፥ የፀጉራችን የከርዳዳነት ደረጃ፥ የአፍንጫና የከንፈራችን ቅርፅ በጣም ተመሳሳይነት ስላለው “መንትዮቹ”፥ “the twins” እያሉን ይጠሩን እንደነበረ አስታውሳለሁ፡፡ ወደ ፍሬ ነገሩ ልመለስ፡፡ አንድ ቀን ምሳ በልተን የትምህርት ሰአት እስኪደርስ  በመጫወት ላይ እያለን፣ በጨዋታ መሀከል ታንዛኒያዊው ጓደኛዬ፤ “What is your Family name?” “የቤተሰብ ስምህ ማነው?” አለኝ፡፡  እኔም፤ “እኛ ፋሚሊ ኔም የሚባል ነገር የለንም” አልኩት፡፡ ታንዛኒያዊው፤ “እንዴት? ምን ማለትህ ነው?” አለኝ፡፡ እኔም፤ “አንተስ ምን ማለትህ ነው? አልገባኝም” አልኩት፡፡ የሁለታችን ንግግር በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እያለ የቀሩት ስድስቱም ጓደኞቻችን እሱን ደግፈው፤  “እንዴ ምን ማለትህ ነው? እንዴት ፋሚሊ ኔም የለንም ትላለህ?” ብለው አፋጠጡኝ፡፡ ክርክራችን ሰባት ለአንድ ሆነ ማለት ነው፡፡ ወዲያው በውስጤ እንዴት የኔ አመለካከት ከነሱ ተለየ? እኔ ምን ከነሱ የተለየ ያለኝ ወይም የሌለኝ ነገር ኖሮ ነው ሀሳቤ ከሰባቱም ሊለይ የቻለው? ብዬ አሰላሰልኩ፥ ወዲያው ትዝ ሲለኝ ልዩነታችን ገባኝ፡፡ “Famiy name” የሚባለው አጠራር የአፍሪካውያን ባህል ሳይሆን፤ የፈረንጆቹ፥ ማለትም የቅኝ ገዢዎቹ ባህል ነው፡፡ ደግሞም የሁሉም ጓደኞቼ ሀገራት በቅኝ የተገዙ ናቸው፡፡ የኔ ሀገር ግን አልተገዛችም፡፡ ይህ ነው የልዩነታችን መሰረት፡፡ ከዚያ ወኔ ተሰማኝ፡፡ በጣም ጥሩ መከራከሪያና ማሳመኛ ነጥብ አገኘሁ ብዬ አሰብኩ፡፡ ይሄኔ ፍርጥም ብዬ በልበ ሙሉነት፤ “ስሙ ይሄ “Family name” የምትሉት ነገር መሰረቱ ወይም ምንጩ የአፍሪካ ባህል ቢሆን ኖሮና እኔ ባላውቀውና ባህሌ ባይሆንም እንኳን ትልቅ ክብር ይኖረኝ ነበር፥ ነገር ግን የባህል መሰረቱ የፈረንጆቹ ወይም የቅኝ ገዢዎቹ ስለሆነ ብዙ ቦታ አልሰጠውም፥ ምክንያቱም በቅኝ ገዢዎቻችሁ የተጫነባችሁ ነገር ስለሆነ ነው” አልኳቸው፡፡ ቀጠሉናም፤ “ፋሚሊ ኔም ከሌለህ ማንነትህ እንዴት ነው የሚታወቀው?” አሉኝ፡፡ እኔም፤  “ማንነቴ የሚታወቀው በራሴ ስም፥ በአባቴ ስም፥ በአያቴ ስም፥ በእናቴ ስም፥ በተወለድኩበት አካባቢ ወዘተ” ብዬ መለስኩላቸው፡፡ በጣም የገረመኝ ነገር ይህ አባባሌ ሊገባቸው አለመቻሉ ነው፡፡ እዚህ ላይ አንባቢ ልብ ሊለው የሚገባውና የሚያሳዝነው ነገር፣ ሁሉም ጓደኞቼ ፋሚሊ ኔም የሚለውን ስያሜ ልክ እንደራሳቸው ባህልና ቅርስ አድርገው ከማየታቸው የተነሳ እኔ የምላቸው ነገር ፍፁም ሊገባቸው አለመቻሉ ነው፡፡ ይገርማል! ያሳዝናል! እነኚህ አፍሪካዊ ጓደኞቼ የነጩ ባህል በደምስራቸው ውስጥ ገብቶ ከደማቸው ጋር የተዋሀደ መሆኑን በመረዳቴ ሀዘን ተሰማኝ፡፡ በመጨረሻም ብዙ ተከራክረን መስማማት ባለመቻላችን፣ ላለመስማማት ተስማምተን፥ እኔም እነሱም የምናምንበትንና የምናውቀውን ይዘን ወደ ሌላ ጨዋታ ውስጥ ገባን፡፡
ስንቅ፡ ጃፓን በሄድኩበት ወቅት እናቴ ለስንቅ ይሆንሀል ብላኝ በትልቅ አገልግል እኔ ነኝ ያለ ጩኮ አዘጋጅታ ይዤ መሄዴን አስታውሳለሁ፡፡ እናቴ በሴት ልጅ ሙያ እንከን የማይወጣላት ነበረች፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለእናቴ የሚገባትን ዋጋ፥ “credit”፤ ለመስጠት በሚል ስሜት አንድ ነገር አንስቼ ልለፍ፡፡ ከዛሬ 50 አመት በፊት በ1960ዎቹ አጋማሽ አካባቢ እናቴ የምትጥለው ፊልተር ጠጅ በጣም ምርጥና ተወዳጅ ስለነበረ፥ አንድ ሊትር ፊልተር ጠጅ በአንድ ሙሉ ውስኪ የአባቴ ጓደኞችና ዘመዶች እንደተቀያየሩ አስታውሳለሁ፡፡      
ከዚያ ዕቃዬን ሸክፌ(pack አድርጌ) ጉዞ ወደ ጃፓን ሆነ፡፡ በአንድ ትልቅ አገልግል በደምብ የታጨቀ ጩኮ ምን ያህል እንደሚከብድ ይታያችሁ፡፡ በኤርፖርቶች ለዕቃ ማመላለሻ የሚያገለግሉ ጋሪዎች ባይኖሩ ጩኮው ወገቤን ይፈትነው ነበር፡፡ ከአዲስ አበባ በሙምባይና በሆንግኮንግ አድርጌ ቶኪዮ ደረስኩ፡፡ በቶኪዮ ደረጃ ያለ ዘመናዊ ከተማ ሳይ በህይወቴ  ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር፡፡ የቶኪዮ ኤርፖርት ከመሀል ከተማው በግምት ሰባ ኪሎሜትር የሚርቅ ሲሆን፥ በኤርፖርቱ የደረስኩት ከቀኑ አስራ አንድ ሰአት ላይ ነበር። የኤርፖርት ውስጥ ፍተሻ ጨርሰን ቶኪዮ ከተማ መሀል ስንደርስ መሽቶ ነበርና ከተማዋ በተለያዩ ውብ መብራቶች የተንቆጠቆጠች ሆነችብኝ። በዚያ ምሽትና በወጣትነት አእምሮዬ ያየሁዋት የቶኪዮ ከተማ ምስል እስከዛሬ  ከአእምሮዬ አልጠፋም፡፡ ያ የቶኪዮ ምስል በድሮ ዘመን የጎጃም ነጋዴ ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ከሀገሩ ተነስቶ እንጦጦ ጫፍ ደርሶ አዲሳባን ሲያያት፤ “እንጦጦ ላይ ሆኜ አዲስን ሳያት ባለፈርጦች ሰማይ መስላ አገኘኋት” ብሎ የገጠመውን ሲያስታውሰኝ ይኖራል።
በመቀጠል ኤርፖርት ውስጥ የመግቢያ ቪዛችንና የያዝነው ዕቃ ሲፈተሽ ፈታሾቹ አገልግሉን ሲያዩ ግራ ገባቸው። ከዚያ ክፈተው አሉኝ፥ ከፈትኩት፥ ጩኮውን ሲያዩ ይበልጥ ግራ ገባቸው፥ ግራ ከመጋባት አልፈው አንድ እኔ ነኝ ያለ ሀሺሽ አስተላላፊ(drug trafficker) የያዙ መስሎዋቸው በጥርጣሬ አይን አዩኝ። “ይሄ ምንድነው?” አሉኝ። “የሀገራችን ባህላዊ ምግብ ነው” አልኳቸው። እነሱ ግን አላመኑኝም። ከዚያ ለምርመራ ለሌላ ሰው አስተላልፈው ሰጡኝና፣ እነሱ የፍተሻ ስራቸውን ቀጠሉ። ወደ ከተማው መግባቴ ቀርቶ ወደ ማረፊያ ሊወስዱኝ ነው ብዬ ፈራሁ፥ አንድ ክፍል ውስጥ አስገብቶ ጩኮውን በአንክሮ ተመለከተው፥ አሸተተው። ከዚያ ፈታሾቹ የጠየቁኝን “ይሄ ምንድነው” የሚለውን ጥያቄ በድጋሚ ጠየቀኝ። እኔም ፍርጥም ብዬ ያለፍርሀት “የሀገራችን የባህል ምግብ ነው” አልኩት። ያልፈራሁት የያዝኩትን ነገር ምንነት ሲረዱ በነፃ እንደሚለቁኝ ስለማውቅ ሲሆን፥ ፈራሁ ብዬ ከላይ የገለፅኩት ደግሞ ምንነቱን እስኪያውቁ ድረስ ሊያጉላሉኝ ይችላሉ ብዬ ነው።  የያዝኩት ሀሺሽ-ነክ ነገር ቢሆን ኖሮ “ምን ያለበት ዝላይ አይችልም” እንደሚባለው ሊነቃብኝ ይችል እንደነበር ገመትኩ። “ከምንድነው የሚሰራው?” አለኝ። “ከገብስና ከቂቤ ነው የሚሰራው” አልኩት። “እስቲ ቅመሰው” አለኝ። እኔም በማንኪያ ቀመስኩት። ግራ የመጋባት ነገር ግማሽ ልብ እንዲሆን አስገደደው። በሙሉ ልብ እንዳያምነኝ ጥርጣሬ አእምሮውን ሰቅዞ ያዘው። ከዚያ ንፁህ ቢላ ይዞ መጥቶ ጩኮውን ከሁለት ቦታ ከፍሎ ከውስጡ በማንኪያ ቆንጥሮ በማውጣት እንደገና ቅመሰው አለኝ። እኔም በትዕዛዙ መሰረት ቀመስኩት። ከላይ ያለውና ከውስጥ ያወጣው የተለያየ ቢሆን ኖሮ፣ በዝርዝር እስኪጣራ ድረስ ችግር ይፈጠርብኝ እንደነበረ ተረዳሁ። በመቀጠልም ከአለቃው ጋር ረዘም ላለ ጊዜ በስልክ ከተነጋገረ በኋላ አገልግሉን መልሶ በማሰር ሰጠኝና አሰናበተኝ። እኔም ዕቃዬን ይዤ የሚቀጥለውን ፍተሻ ከጨረስኩ በኋላ በኤርፖርቱ መግቢያ ላይ ሙሉ ስሜን በሰፊ ወረቀት ላይ ፅፎ ከሚጠብቀኝ ሰውዬ ጋር ተገናኝቼ፣ ቶኪዮ በሚገኘው የአለም አቀፍ ሰልጣኝ ተማሪዎች ወደሚያርፉበት ማዕከል ወሰደኝ።
ብርሀኔ ዳምጠው፡
አቶ ብርሀኔ ዳምጠው በኦሳካ ኮቤ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ነው። በ1967 ዓ.ም አካባቢ ጃፓን ለአጭር ጊዜ ስልጠና ሄዶ እዚያው የቀረ ሀበሻ ነው። ሙያው ከመኪና ጥገና ጋር የተገናኘ የቴክኒክ ሙያ በመሆኑ የሚሰራው ከሙያው ጋር በተገናኘ መስክ እንደሆነ አጫውቶኛል።
አቶ ብርሀኔ የሀገሩ ሰው ይናፍቀዋል። እኔ ጃፓን በሄድኩበት ጊዜ አንድ ኢትዮጵያዊ በኦሳካ ኢንተርናሽናል የስልጠና ማዕከል መኖሩን ሰምቶ በማሰልጠኛው የማዞሪያ ስልክ ደውሎ በስልክ ተገናኘን። ከዚያም በአካል በተገናኘንበት ወቅት ስንጨዋወት አልፎ አልፎ ወደማሰልጠኛው ስልክ ይደውልና ኢትዮጵያዊ ሰልጣኝ መኖሩን ካጣራ በኋላ፣ ካለ ደውሎለት በስልክ ያገኘዋል። ከዚያም በአካል አግኝቶት ስለሀገር ቤትም ሆነ ስለተለያዩ ነገሮች ይጫወታሉ። እንደገመትኩት አቶ ብርሀኔ ጃፓን ለስልጠና በሄደበት ዘመን እንኳን ኢትዮጵያዊ ይቅርና ማንኛውንም ጥቁር ሰው በጃፓን ሀገር ውስጥ ማየት ብርቅ ነበር። የዚህን አባባል እውነትነት እኔ በ1984 ዓ.ም. ጃፓን በሄድኩበት ዘመን በአንዳንድ አካባቢዎች እኔንና አፍሪካዊ ጓደኞቼን ሲያዩን እንደብርቅ ያዩን የነበሩ ሰዎች የመኖራቸው ሀቅ ምስክር መሆን ይችላል።         
ከላይ በጠቀስኩት ምክንያት ከአቶ ብርሀኔ ጋር ብዙ ጊዜ በአካል ተገናኝተን ተጫውተናል፥ ቤቱም ጋብዞኛል፥ በአፓርታማ ውስጥ ነው የሚኖረው፥ ፓርኮችና የተለያዩ ቦታዎች አስጎብኝቶኛል። አንድ ቀን እሱ በሚኖርባት ኮቤ በምትባል፥ በኦሳካ ከተማ አጠገብ የምትገኝ የወደብ ከተማ ውስጥ ያለ አንድ ጃፓናዊ የሬስቶራንት ባለቤት ጓደኛው ጋ ወስዶ የጋበዘኝ ሾርባ የሚመስል የጃፓን ምግብ እስካሁን አይረሳኝም። ሾርባው ውስጥ ያለው ስጋ ከባህር ውስጥ የሚገኝ የአሳ ዝርያ መሆኑን ነው የነገሩኝ፥ እውነቱን ግን እግዜር ይወቀው፥ ምክንያቱም ቅርፁ የእባብ ስለሚመስል ነው። ስጋው በጣም ለስላሳ ነበር፥ እኔ በምግብ ላይ ብዙ ወግ አጥባቂ ስላልሆንኩ የቀረበልኝ ምግብ በጣም ጣፍጦኝ ነበር የተመገብኩት።
ታዲያ እንደወትሮው አንድ ቀን የሆነ ቦታ ተገናኝተን ሻይ ቡና እየተባባልን እያለ አንድ ፍፁም ያልጠበቅሁት ነገር ተፈጠረ። በጨዋታ ድባብ ውስጥ የነበረው የአቶ ብርሀኔ ፊት ቀስ በቀስ ተለውጦ በሀሳብ ባህር ውስጥ ሲሰምጥ ታየኝ። “አቶ ብርሀኔ ምን ሆንክ? ደህና አይደለህም እንዴ?” አልኩት። እሱም ምንም መልስ ሳይሰጠኝ አንገቱን ደፋ ከአደረገ በኋላ ቀና ብሎ ምንም ሳልጠብቀው እንባ በግራና በቀኝ ጉንጮቹ እየወረዱ ስቅስቅ ብሎ ማልቀስ ጀመረ። እየሆነ ያለው ነገር ፍፁም ሊገባኝ አልቻለም። ግራ ገባኝ። “አቶ ብርሀኔ ምን ሆንክ? ለምንድነው የምታለቅሰው?” አልኩት፤በድጋሚ።
 አቶ ብርሀኔ ገዘፍ ያለ መልከመልካም ጠይም ሰው ነው። ከኔ በግምት አስር አመት ይበልጠኛል። በዚህ ላይ ስልጠናውን ከጨረሰ በኋላ በታወቀ የጃፓን የመኪና አምራች ኩባንያ ውስጥ ሲሰራ ቆይቶ ከሙያው ጋር የተገናኘ የግል ስራ እንደሚሰራ አጫውቶኛል። ስራው መኪኖችን ወደ ጎረቤት የእስያ ሀገራት  መሸጥ ነበር። በጣም ጥሩ ገቢ ያለው ሰው መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነገር ነው። ታዲያ ከአፍሪካ የሄደ እንደኔ አይነቱ ቺስታ እንዴት ብዬ፣ ይህ ሰው ስቅስቅ ብሎ ያለቅሳል ብዬ ልገምት? አቶ ብርሀኔ ለቅሶው ቀለል ሲለው የሚከተለውን አጫወተኝ። “እኔ እዚህ ጃፓን ላለፈው 17 አመታት ኖሬያለሁ፥ በዚህ ዘመን ውስጥ ትምህርቴን ጨርሼ በታወቀ ኩባንያ  ውስጥ ጥሩ ስራ ነበረኝ፥ ከዚያ የራሴን የግል ስራ ጀምሬ ጥሩ ገቢ ማግኘት ችያለሁ፥ ምንም የኢኮኖሚ ችግር የለብኝም፥ ከራሴ አልፌ ለሰው የምተርፍ ነኝ። ነገር ግን ይሄን ያህል ዘመን እዚህ ሀገር ውስጥ ስኖር ጃፓንን እንደራሴ ሀገር አላያትም፥ የትም ቦታ ስሄድ የሚያጋጥመኝ ሰው እንደ አዲስ የሀገሩ ሰው ነው የሚያየኝ ወይም የሚቀበለኝ፤ ይህ ሁኔታ የባይተዋርነት ስሜት እንዲያድርብኝ አደረገኝ፥ ለዚህ ነው ሆድ ብሶኝ ያለቀስኩት” አለኝ።
አቶ ብርሀኔ ሀበሻና ሌሎች ጥቁሮች በብዛት በሚገኙበት በምዕራባውያን ሀገሮች፥ ለምሳሌ አሜሪካና እንግሊዝ፥ ውስጥ የሚኖር ቢሆን ኖሮ፣ ይህ የባይተዋርነት ስሜት አይሰማውም ነበር። አቶ ብርሀኔን ሆድ አስብሶት እስከማልቀስ ያደረሰው የስነ ልቦና ችግር እንደሆነ ገባኝ። አቶ ብርሀኔ ለሀገሪቱ በፈረንጆቹ አባባል “belongingness” አልነበረውም ማለት ነው። ይህ ተሞክሮ በዚያ የወጣትነት እድሜዬ አንድ ትልቅ ትምህርት አስተምሮኝ አለፈ፥ ሀብትና ገንዘብ ብቻ ለሰው ልጅ ምንም ነገር እንደማይፈይዱ። የታወቀው የማኔጅመንት ምሁር አብርሀም ማስሎው፤ “Hierarchy of needs” ብሎ ካስቀመጣቸው መሀከል አቶ ብርሀኔ በተሰማው የባይተዋርነት ስሜት ምክንያት የተሟላ “safety” (ደህንነት) እና “love” (ፍቅር) ስላልነበረው ሆድ አስብሶት ተንሰቅስቆ እንዲያለቅስ አደረገው።
ምግብ፡ የጃፓን ምግብ በአብዛኛው አትክልት፥ ቅጠላቅጠልና የባህር ምግቦች ናቸው። የራሳቸው የምግብ ማጣፈጫ(sauce) አላቸው። አንዳንድ የምግብ ማጣፈጫዎቻቸው ጣዕም ለየት ስለሚሉ በአማርኛ ቃላት ላገኝላቸው ባለመቻሌ ጣዕሙ ምን አይነት እንደሆነ ለሰው ለመግለፅ በወቅቱ አስቸግሮኝ እንደነበር አስታውሳለሁ። በሂደት ግን ምግባቸውን ለምጄ በጣም ወድጄው አረፍኩት። ሀገር ቤት ከተመለስኩ በኋላ የጃፓን አሉምኒ አሶሲዬሽን ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ስለነበርኩ (በአንድ ወቅት የአሶሲዬሽኑ ፕሬዚደንት ሆኜ አገልግያለሁ)፣ አልፎ አልፎ እዚህ ያለው የጃፓን ኤምባሲ ግብዣ ይጠራን ነበርና፣ እንደሱሺ አይነቱን የጃፓን ምግብ በኤምባሲው ውስጥ በሚጋብዙን ወቅት በጣም በፍቅር ነበር እበላ የነበረው። (ሱሺ ባህር ውስጥ በሚገኝ ቅጠል መሰል አልጌ የተጠቀለለ አሳና ሩዝ ያለበት የጃፓን ምግብ ነው። አረንጓዴው አልጌ “Spirulina” የሚባለውና የምግብ ይዘቱ በጣም ከፍተኛ የሆነ ምግብ ነው፥ የምግብ ይዘቱ በጣም ከፍተኛ ስለሆነ ውጪ ሀገር በታብሌት መልክ በየሱፐርማርኬቶቹ ይሸጣል፥ እኔ አላጋጠመኝም እንጂ በኛ ሀገርም ሊገኝ ይችላል)።
 ምግባቸው ጨው፥ ስኳርና የከብት ቅባት(ቅቤና ጮማ) ስለሌለበት ለጤና በጣም ተስማሚ መሆኑን እመሰክራለሁ። የጃፓን ህዝብ በአለም ላይ ረዥም ዕድሜ ከሚኖሩ ህዝቦች መሀከል በአንደኝነት የሚጠቀስ የመሆኑ ሚስጥር በዋናነት  በሚበሉት ምግብ እንደሆነ የተረጋገጠ ነገር ነው። ከምግብ ጋር የተያያዘ ሌላ ነገር ላንሳ። ከጓደኞቼ ጋር አንድ ቀን ምሳ እየበላን በነበረበት ወቅት አንዱ ጓደኛዬ ትኩር ብሎ አየኝ። አበላሌ ከሌሎቹ የተለየ አልነበረም፥ ገበታ አስደንጋጭ የምባል አይነት ሰውም አይደለሁም፤ ኖርማል አበላል ነበር የምበላው፥ እየበላን የነበረውም የተለመደ ምግብ ነው፡፡ ጓደኛዬ፤ “እዚህ አሁን እንዲህ እንደልብህ እየበላህ ሆድህን አስፍተህ ሀገርህ ስትመለስ ምን ትበላ ይሆን?” አለኝ። ምናልባት ሌላ ሰው እንዲህ ቢባል ቢያንስ ሊናደድ ወይም ሊጣላ ይችል ነበር። የኛ ሰው ውጪ ሀገር ሲሄድ የዚህ አይነት ነገር እንደሚያጋጥመው ጠንቅቄ አውቃለሁ፥ በተለይ እኔ ጃፓን የሄድኩበት ዘመን ከ1977ቱ ረሀብ 7 አመት ብቻ ስለሚራራቅና በወቅቱ የነበረው የሀገራችን ረሀብ ትዝታ ትኩስ ስለነበረ የዚህ አይነት ነገር ቢያጋጥም አይገርምም። በመሆኑም ጥያቄው ብዙ አልገረመኝም፥ ወይም አልተናደድኩም። እኔም በምላሼ፤ “ኢትዮጵያ ተራበች ሲባልኮ ሁሉ ቦታ ረሀብ አለ ማለት አይደለም፤ ረሀብ የነበረው በሰሜኑ ክፍል ነበር” አልኩት። እሱም(ሌሎቹም አብረው) “ሰሜኑም ይሁን ደቡቡ እኛ የምናውቀው ኢትዮጵያ ረሀብተኛና ችጋራም መሆንዋን ነው” ብለው ረሀብተኛነታችንን ለመሸፋፈን የፈለግሁ አስመሰሉኝ፡፡ ኢትዮጵያ ተራበች ሲባል ህዝቡ በሙሉ በጠኔ ያለቀ አስመስሎ የማቅረብ አባዜ አለባቸው፤ የምዕራብ ዘመም አመለካከት ያለባቸው የውጪ ዜጎች። በሌላ ጊዜ ደግሞ ታንዛኒያዊው ጓደኛዬ፤ “እኔ ሁልጊዜ ግርም የሚለኝ ሆዳችሁን መሙላት ሳትችሉ ኢትዮጵያ አየር መንገድን የመሰለ ኩባንያ  እንዴት መመስረት እንደቻላችሁ ነው!” አለኝ። የዚህ አይነት ክብረ-ነክ ጥያቄዎች በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች ያጋጥማሉ፥ ኢትዮጵያዊ ከሆንክ።

መቻያ ትዕግስቱን ካልሰጠህ አስቸጋሪ ነው። ትልቁ ቁምነገር በምትጠየቀው እነኚህን መሰል ጥያቄዎች ምክንያት የሚሰማህ ስሜትና የምትመልሰው መልስ ነው። የሚሰማህ ስሜትና የምትመልሰው መልስ አይነት ያንተን የውስጥ ጥንካሬ መለኪያ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ሁኔታ ቪክቶር ፍራንኬል  የተባሉ ታላቅ ሰው ያሉትን አስታወሰኝ፤ “You cannot control what happens to you in your life; but you can always control what you will feel and do about what happens to you.” “በህይወትህ ውስጥ የሚያጋጥሙ ነገሮችን መቆጣጠር አትችልም፥ ነገር ግን በአንተ ላይ በሚያጋጥሙ ነገሮች ምክንያት የሚሰማህን ስሜትና የምትወስደውን ርምጃ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ትችላለህ።” ይህን አባባል እንደ አንድ የህይወታችን መመሪያ ወስደን ብንተገብረው ይጠቅመናል።
(ይቀጥላል)



የማሽቃሬ ባሮ (የመስቀል በዓል) በካፋ ዞን በአደባባይ ከሚከበሩ ደማቅ በዓላት መካከል ዋንኛው ነው፤ የበዓሉ ተሳታፊዎች ደግሞ ከማንኛውም የሐይማኖት ተቋማት የተውጣጡ ታዳሚዎች ሲሆኑ፣ በዕድሜ ያልተገደበ፣ በጾታ ያልተወሰነ እና ሁሉን የሚያሳትፍ በዓል እንደሆነ  ይታወቃል።
በዓሉን በአደባባይ ማክበር የተጀመረው ከዛሬ 150 ዓመታት በፊት እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፤ የበዓሉ ዋና ዓላማ ጭጋጋማው ወር መገባደዱን፣ ጭፍና በፍካት መተካቱን፣ ዝናብ በጸዳልና ፍካት መወረሱን እና የእርሻ ወቅት መጠናቀቁን አስመልክቶ ከንጉሡ ምርቃትን ለመቀበል የመሰባሰቢያ በዓል ነው፡፡ በዓሉ፣ ከካፋ ዞን፣ ከክልሉ እና ከሌሎች የአገራችን አካባቢዎች በመጡ ታዳሚዎች በቦንጋ ከተማ በሚገኝ ቦንጌ ሻንቤቶ በተባለ ስፍራ ይከበራል።
ዘንድሮም በዓሉ የሚከበረው በመስከረም 12 እና 13 ሲሆን፣ የተለያዩ የካፋ ሕዝቦች ታሪክ፣ የጥንት የጦርነት ይትባሃል፣ ትውፊት፣ ሙዚቃ፣ ጥንታዊ የፖለቲካዊ አስተዳደር፣ አንትሮፖሎጂ፣ የእርቅ ሥነ-ሥርዐት፣ እርሻ፣ የአዝመራ ቀመር፣ ባሕል፣ አመጋገብ፣ ባሕላዊ መጠጦች እና ሌሎች የካፋ ሕዝቦች መገለጫዎች ይዘከራሉ፤ ለአገራችን ሠላም፣ ለከብቱ ጤና፣ ለቀዬውና ለሰብሉ ማማር እና ለመልካም ዕድል ምርቃት ይያዛል።
የካፋ ሕዝብ በደቡብ ምዕራብ ክልል ከሚገኙ ሕዝቦች መካከል አንዱ ሲሆን፣ የመናገሻ ከተማዋ የቦንጋ ከተማ ከአዲስ አበባ በ460 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ይገኛል፤ የካፋ ዞን የአረቢካ ቡና መገኛ መሆኑን የታሪክ አሳሾች፣ ተመራማሪዎች፣ ተጓዦች እና ሌሎች ግለሰቦች እማኝ ሆነዋል፤ ከ7ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ቡና የእለት ፍጆታ፣ አነቃቂ እና ፍቱን መድኀኒት ሆኖ ሲያገለግል ኖሯል፤ አገራችን ኢትዮጵያ ለሰው ልጆች ካበረከተቻቸው ገጸ-በረከቶች መካከል የካፋ ቡና አንዱ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ፤ የካፋ ዞን በጫካ ማር፣ በግዙፍ በግ፣ በዝባድ፣ በሻይና ቅመማ ቅመም፣ በእንሰት ምርትና በተለያዩ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎች የታወቀ ነው፡፡       


”1ቢ. ብር የሚገመት ኪሳራ ሊያስከትሉ የሚችሉ ድርጊቶች ተፈጽመዋል”

አሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር) በፕሬዚዳንትነት የሚመሩት የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ከተዋቀረበት ጊዜ አንስቶ የኦዲት ምርመራ አለማድረጉ ተገለጸ፡፡  ይህ ይፋ የተደረገው ከትላንት በስቲያ  ሐሙስ  አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ፣ አትሌት ገዛኸኝ አበራ፣ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽንና የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን በጋራ በመሆን በኮሚቴው ላይ የመሰረቱትን ክስ በጠበቃነት የወከሉ የሕግ ባለሞያዎች በሃይሌ ግራንድ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።
በዚሁ መግለጫ ላይ ከሳሾችን የወከሉት ጠበቃዎች አቶ ሃይሉ ሞላ፣ አቶ ጳውሎስ ተሰማና አቶ አያሌው ቢታኔ በኦሎምፒክ ኮሚቴ ላይ በተመሰረተው ክስ ዙሪያ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።  የኮሚቴው ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደጊዮርጊስ፣ ዋና ጸሐፊ አቶ ዳዊት አስፋው፣ ምክትል ዋና ጸሐፊ አቶ ገዛኸኝ ወልዴና የኮሚቴው አቃቤ ንዋይ ኤደን አሸናፊ (ዶ/ር) ክሱ እንደቀረበባቸው አቶ አያሌው ቢታኔ ተናግረዋል።
አቶ አያሌው በሰጡት ማብራሪያ፤ “ተከሳሾቹ በባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር ተሻሽሎ የወጣውን መመሪያ 907/2014 እና በአገሪቱ የወጡ ዘርፈ ብዙ ሕግጋትና ደንቦችን ጥሰዋል” ብለዋል። የኦሎምፒክ ኮሚቴ ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. በአስቸኳይነት እና ሰኔ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. በመደበኛነት ያደረጋቸው ጠቅላላ ጉባዔዎች በግልጽ የሕግ ጥሰቶች እንደታጀቡ ያመለከቱት እኚሁ ጠበቃ፤ ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ለተካሄደው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴና አትሌት ገዛኸኝ አበራ “መጥሪያ አልደረሰንም። ጥሪ አልተደረገልንም። ያለአግባብ በማናውቅበት መልኩ በድብቅ የተደረገ ስብሰባ ነው” ማለታቸውን በመጥቀስ፣ ጉባዔው የስነ ምግባር መመሪያውንና የኦሎምፒክ ኮሚቴውን መተዳደሪያ ደንብ፣ እንዲሁም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን መመሪያ መጣሱን ጠቁመዋል፡፡
“ሰኔ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. በተካሄደው መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ በማያውቅበትና ፈቃደኛ ባልሆነበት አግባብ እርሱን ያካተተ ምርጫ ተደርጓል። ይህም የተደረገው እርሱ ምርጫውን በተቃወመበት ሁኔታ ነው።” በማለት ያብራሩት አቶ አያሌው፤ “ጠቅላላ ጉባዔ የሚጠራው የኦሎምፒክ ውድድር ከተደረገ በኋላ ቢሆንም፣ ይህ ጉባዔ የተደረገው ግን ኦሎምፒክ ከመከናወኑ ሁለት ወር በፊት ነው። ከዚህም ሌላ ጉባዔው ከመካሄዱ ከ30 ቀን በፊት ጥሪ መተላለፍ ነበረበት። ምርጫው ውስጥ የሚገቡ ሰዎችና የፌዴሬሽን አባላት በሙሉ ጥያቄዎቻቸውንና ተመራጭ የሚሆኑ አካላትን ሊልኩ ይገባ ነበር።” ብለዋል።
በመመሪያው መሰረት፣ የውጭ ዜግነት ያለው ግለሰብ የየትኛውም ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት ሆኖ ሊሰራ እንደማይችል ቢደነገግም፣ የኦሎምፒክ ኮሚቴው ዋና ጸሐፊ አቶ ዳዊት አስፋው የእንግሊዝ ዜግነት እንዲሁም አቃቤ ንዋይ ኤደን አሸናፊ (ዶ/ር) የአሜሪካ ዜግነት እያላቸው በሃላፊነት ላይ እንደሚገኙ ጠበቃው ጠቁመዋል፡፡  
በሌላ በኩል፤ የኢትዮጵያ መንግስት የ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክን ምክንያት በማድረግ ለኦሎምፒክ ኮሚቴው የሰጠው 150 ሚሊዮን ብር የት እንደገባ በኦዲት ምርመራ አለመረጋገጡን በማብራራት፣ የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር በተደጋጋሚ ለኮሚቴው ኦዲት የማስደረግ ጥያቄ አቅርቦ ከኮሚቴው ምክትል ዋና ጸሐፊ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ በቂ ምላሽ እንዳልተሰጠው ጠበቃ አያሌው በማብራሪያቸው አንስተዋል። በተጨማሪም፣ የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ለኦሎምፒክ ኮሚቴ ኦዲት ለማድረግ ጥያቄ አቅርቦ ከኮሚቴው አመራሮች “አሁን ቢሮ ውስጥ የለንም” የሚል ምላሽ ተሰጥቷል  ሲሉ አስታውቀዋል።
“መንግስት የክትትል ሃላፊነቱን አልተወጣም። የገንዘብ ሚኒስቴር ለኦሎምፒክ ኮሚቴ የሰጠውን ገንዘብ ተከታትሎ የመጠየቅ ሃላፊነት ቢኖርበትም፣ ሃላፊነቱን ሊወጣ አልቻለም” ያሉት አቶ አያሌው፤ “ለስብሰባ” በሚል ምክንያት በፈረንጆቹ አቆጣጠር ታሕሳስ ወር 2020፣ 47 ሚሊዮን ብር ከመንግስት መከፈሉን ጠቁመዋል። እንዲሁም ለቶኪዮ ኦሎምፒክ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ከኢትዮ ቴሌኮም እና ሌሎች የመንግስት የልማት ድርጅቶች የተሰበሰበ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ የት እንደገባ እንደማይታወቅ፣ በገንዘብ ሲገመት እስከ 400 ሺህ ዶላር የሚገመት የስፖርት ትጥቅ ተቀማጭነቱ ጀርመን አገር ከሆነው፣ ከአዲዳስ ኩባንያ የኮሚቴው አመራሮች በየዓመቱ የትጥቅ ድጋፍ ሲረከቡ ቢቆዩም፣ ለማንና እንዴት እንደተላለፈ ምንም መረጃ አለመኖሩን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ መልኩ፣ በዚሁ ኩባንያ ከእያንዳንዱ የኦሎምፒክ ውድድር በኋላ 600 ሺህ ዶላር የሚያወጣ የስፖርት ትጥቅ አመራሮቹ እንደተረከቡ ጨምረው ያብራሩት አቶ አያሌው፤ “ከባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር ለኮሚቴው አመራሮች በተደጋጋሚ የግልጽነት ጥያቄ ቀርቦ ነበር። አመራሮቹ ምላሽ ሊሰጡ ግን አልቻሉም።” ብለዋል። በመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ወቅት ከ500 ሺህ ዶላር በላይ የሚያወጣ የስፖርት ትጥቅ አመራሮቹ ከአዲዳስ ኩባንያ ቢረከቡም፣ የት እንደደረሰ እንዳልታወቀም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በጥር ወር 2005 ዓ.ም. ባወጣው የፋይናንስ አስተዳደር መመሪያ፣ አንቀጽ 33፣ ንዑስ አንቀጽ 4 መሰረት፣ ከ200 ሺሕ ብር በላይ የሚሆን ማናቸውም ግዢ በጨረታ መሆን አለበት  እንደሚል አቶ አያሌው ጠቅሰው፤ ኮሚቴው የውሃ ፋብሪካ ለመገንባት ከውጭ አገር በ64 ሚሊዮን ብር ያለጨረታ ማሽኖችን አስገብቷል ብለዋል፡፡  አክለውም ሲያስረዱ፤ “ማሽኖቹ በትክክል የውሃ ፋብሪካን ለማሰራት እንደሚችሉ የምናውቀው ነገር የለም። ለዚህ ጉዳይ ለኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ ድርጅት ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ መክፈል የነበረበት ዕዳ አለ። ኮሚቴው በዕዳ እየተዘፈቀ ነው። የፋይናንስ ግልጸኝነት የጎደለው አሰራር አለ።” በማለት የቀረበውን ክስ አብራርተው፣ በመንግስት ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ኮሚቴው ኦዲት እንዲደረግ “ትዕዛዝ ይሰጥልን” የሚል የዳኝነት ትዕዛዝ  መቅረቡን አመልክተዋል።
ክሱ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍትሐ ብሄር ችሎትና በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስተዳደር ችሎት እንደሚታይ በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ ተጠቁሟል። ከተጠቀሱት ተከሳሾች በተጨማሪ፣ በክስ ሂደቱ ሌሎች ግለሰቦች ሊካተቱ እንደሚችሉ ጠበቆቹ ፍንጭ ሰጥተዋል።
በሌላ በኩል፤ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በሰጠው ምላሽ፣ በአትሌት ሃይሌ ገብረስላሴና አትሌት ገዛኸኝ አበራ፣ እንዲሁም በሁለት ፌዴሬሽኖች የቀረቡበትን ክሶች አጣጥሏል። አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ ባለፉት አራት አመታት የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆኖ መቆየቱን በማውሳት፣ “ራሱን ‘ከደሙ ንፁህ ነኝ’ በሚል እና ከዚህ ቀደምም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት በነበረበት ወቅት ለማናጀሮችና ለስፖርት ትጥቅ አምራች ካምፓኒዎች አሳልፎ በመስጠት ብሄራዊ ቡድን ያፈረሰው ራሱ ሆኖ እያለ የስፖርቱ ተቆርቋሪ ሆኖ መምጣቱ እጅግ አሳዝኖናል።” ሲል ነቅፌታ አቅርቧል።
“ለመሆኑ ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ ባለፉት ዓመታት የት ነበር?” የሚል ጥያቄ ያቀረበው የኦሎምፒክ ኮሚቴ፤ “ጀግናው አትሌት ገዛኸኝ አበራ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት እንደሆነ ይታወቃል። በፌዴሬሽኑ ውስጥ ያለበትን የማኔጅመንት ክፍተት ወደ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ይዞ መምጣቱ ‘ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ!’ የሚባለው ብሂል ዓይነት ነው።” በማለት ለጥያቄው ምላሽ ሰጥቷል። አክሎም፣ “አንዳንድ የሚዲያ ባለሙያዎች ከግለሰቦች ጋር በግልፅ በገንዘብ በመደለልና በጥቅም በመተሳሰር -- ለዚህም በቂ ማስረጃዎች አሉ --ለሕብረተሰቡ የተዛቡና ሚዛናዊ ያልሆኑ የአንድ ወገንን መረጃ ብቻ በማቅረብ የስፖርት ቤተሰቡን እያሳሳቱት ይገኛሉ።” ብሏል።
ኮሚቴው ክስ ያቀረቡበትን አትሌቶችና ፌዴሬሽኖች በሕግ እንደሚጠይቅ ገልጾ፣ ”የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ምርጫ ‘ታገደ’ ለሚባለው የደረሰን ነገር ባይኖርም፣ በውሸት ቃለመሀላቸው የተሳሳተ ዳኛ ካለ በሕግ አግባብ እናስቀለብሳለን።” ሲል የአትሌቶችንና የፌዴሬሽኖችን የክስ እንቅስቃሴ አጣጥሏል።

ኢትዮጵያ በቻይና ገበያ የነበራት የሰሊጥ ምርት ድርሻ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እያሽቆለቆለ መምጣቱ ተነግሯል። በድንበር ላይ የሚደረገው የኮንትሮባንድ ንግድም የራሱን ፈተና እንደጋረጠ ተጠቁሟል።
 ባለፈው ሰኞ ጳጉሜ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር፣ በቅርቡ ተግባራዊ የተደረጉት የውጭ ምንዛሪ ፖሊሲ ማሻሻያዎች፣ በግብርና ዘርፉ የኤክስፖርት ንግድ ላይ በሚኖራቸው ዕድሎችና ፈተናዎች ላይ  ባዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ያስሚን ዋሃብ ረቢ፣ የውጪ ንግድ በተፈለገው መጠን ያለማደጉን፤ በአብዛኛው  የሚያተኩረውም ብዙም እሴት ያልተጨመረባቸው የግብርና ውጤቶችን ኤክስፖርት በማድረግ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል። የውጪ ንግድ ለአገራዊ ኢኮኖሚው የሚያደርገው አስተዋጽዖ አነስተኛ እንደሆነ የተናገሩት ሚኒስትር ዲኤታው፣ ዘርፉ   የእሴት ጭመራና የጥራት ችግር የሚታይበት መሆኑን ጠቅሰዋል።
“የ2016 የኤክስፖርት መጠን ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር፣ በሚፈለገው ደረጃ ዕድገት አልመጣበትም። ወደ 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር  ገቢ ነው የተገኘው። በኤክስፖርት ንግድ ከሌሎች ተቀራራቢ አገራት አንጻር፣ ከአገራዊ ጥቅል ምርት ድርሻ ጋር ሲነጻጻር፣ እጅግ በጣም አነስተኛ ነው። በውጭ ንግዳችን ለዓለም አቀፍ ገበያ እያበረከትን ያለነው አስተዋጽዖ በመቶኛ ሲሰላ 1 ነጥብ 4 ነው።” ብለዋል ሚኒስትር ዲኤታው። ይህንን ሁኔታ መቀየር እንደሚያስፈልግ በመጠቆምም፤ በቅርቡ የተደረገው የምንዛሪ ስርዓት ለውጥ የውጭ ንግዱን ለማሳደግ የራሱን አስተዋጽዖ እንደሚያደርግና  ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ በአጽንዖት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ኤዳዎ አብዲ በበኩላቸው፤ “ለአስር ዓመት ያህል የኤክስፖርት ንግድ በኪሳራ ስንሰራ ቆይተናል። ከመንግስት ጋር በምናደርጋቸው ውይይቶች ዋናው ነጥብ ‘እንዴት ከኪሳራ መውጣት እንችላለን?’ የሚለው ነው።” ያሉ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት የሚስተዋለው የንግድ ሚዛን ጉድለት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል። በቅርቡ  ተግባራዊ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ይህንን ጉድለት ሊያስተካክለው እንደሚችልም ጠቁመዋል።
ከጥቂት ጊዜያት በፊት፣ ከአፍሪካ አገሮች በሰሊጥ ምርት ግንባር ቀደሟ አገር ኢትዮጵያ እንደነበረች ያወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ከአስር ዓመታት በፊት በቻይና ገበያ የኢትዮጵያ የሰሊጥ ምርት የ50 በመቶ ድርሻ እንደነበረው አስታውሰዋል። “አሁን ግን ይኼ ድርሻ ወደ አምስት በመቶ ወርዷል፤ የገበያ ድርሻችን እየቀነሰ ነው” ብለዋል።
 “ሌሎች አገሮች -- እንደሱዳንና ቡርኪናፋሶ ያሉት -- ከኢትዮጵያ አምራቾች በላይ እያመረቱ ነው” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ “ፓኪስታን ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ብቻ 350 ሺ ሜትሪክ ቶን ማምረት ስትችል፣ ኢትዮጵያ ግን ከ220 ሺ ሜትሪክ ቶን ያልበለጠ ሰሊጥ ለውጭ ገበያ አቅርባለች። ይሁንና ከ10 ዓመታት በፊት የሁመራ ሰሊጥ በ400 ሺ ሜትሪክ ቶን ያህል ይመረት ነበር።” ሲሉ አስታውሰዋል፡፡  “ከሌሎች አገራት ጋር በዋጋ እየተወዳደርን አይደለም። የገበያ ድርሻችንን እያጣን ነው። ለዚህም የአቅርቦት ሰንሰለትና የምርታማነት እንከኖች በጉልህ ይጠቀሳሉ” ያሉት  አቶ ኤዳዎ፤ ከምንዛሪ የገበያ ስርዓት ለውጥ ባሻገር መታሰብ ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ጠቅሰዋል። “ለውጭ ገበያ በሚቀርቡ ምርቶች ላይ የእሴት ጭመራ ቢደረግ፣ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይቻላል” ብለዋል።
ሰሊጥ፣ ቡና እና የቀንድ ከብትን ጨምሮ፣ 21 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ምርት በኮንትሮባንድ እንደሚወጣ ፕሬዚዳንቱ ጠቁመው፤ የድንበር ቁጥጥሩ የላላ ከመሆኑ ባለፈ፣ በድንበር በኩል የሚደረገው የንግድ እንቅስቃሴ በእኩል ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ስርዓት ካልተበጀለት በስተቀር በዚህ መልክ የሚወጣው ምርት መጠኑ ቀላል አለመሆኑን ተናግረዋል።ከአዲስ አድማስ ጋር አጭር ቆይታ ያደረጉት አቶ ኤዳዎ አብዲ፣ መንግስት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ማድረጉን በማስታወስ፣ ይህ መድረክ በዚህ ማሻሻያ ዙሪያ የማሕበሩ አባላት በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙ ታልሞ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል። “ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ይህ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ትልቅ ለውጥ ነው።” ብለዋል፤ ፕሬዚዳንቱ።
በጥራጥሬና ቅባት እህል የውጭ ንግድ ዘርፍ ላይ ስለሚስተዋሉ የተለያዩ ተግዳሮቶች ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ኤዳዎ፤ “ተግዳሮቶቹ ከስጋት የመነጩ እንጂ በሂደት እየተቀረፉ የሚመጡ ናቸው።” በማለት አስረድተው፣ “ከኤክስፖርት የሚገኘው የገቢ መጠን ኢትዮጵያን የሚመጥን አይደለም። ከ3 ነጥብ 8 እና ከ4 ቢሊዮን ዶላር የዘለለ አይደለም።” ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ አክለውም፣ የኮንትሮባንድ ንግድ ላይ ቁጥጥር ሊደረግበት እንደሚገባና ለዘርፉ ባለሃብቶች ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።  ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንደሚገባቸውም ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር፣ ከ500 በላይ አምራቾችን በአባልነት ያቀፈ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ)፣ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ “አድርገውታል” በተባለ ንግግር ዙሪያ ከመንግሥት ማብራሪያ እንደጠየቀ ባለፈው ረቡዕ መስከረም 1 ቀን 2016 ዓ.ም. በይፋዊ ማሕበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
ፓርቲው፤ “ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ኦብነግ በግብጽ መንግስት የተመሰረተና የኢትዮጵያ ጠላት እንደሆነ አድርገው ተናግረዋል። ይህ ንግግር መሰረተ ቢስ ብቻ ሳይሆን፣ የኦብነግን ሕጋዊነትና ድርጅታዊ አንድነት የሚያጠቃ ነው” ብሏል፤ በመግለጫው፡፡
ኦብነግ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ “ተናግረውታል” ሲል የጠቀሰው ንግግር፣ ከሰሞኑ በበይነ መረብ ሲዘዋወር መቆየቱን ለማወቅ ተችሏል።
ጥቅምት 11 ቀን 2011 ዓ.ም. በአስመራ ከተማ በመንግስትና በፓርቲው መካከል የሰላም ስምምነት እንደተፈረመ ያስታወሰው ኦብነግ፤ በዚሁ ስምምነት “ሁለቱም ወገኖች ግጭቶችን ለማቆም የተፈጠረው ቁርጠኝነት ተገልጿል” ሲል በመግለጫው አትቷል። በማያያዝም፣ ፖለቲካዊ ዓላማዎቹን በሰላማዊ መንገድ ለማራመድ በማሰብ ስምምነቱን እንደፈጸመ አስረድቷል።
ሆኖም ግን በጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ “ተደርጓል” የተባለው ንግግር፣ “ከሰላም ስምምነቶች ጋር የሚቃረን” እና “እየቀጠለ ያለውን የሰላም ሂደት የሚያጣጥል” መሆኑን ፓርቲው አስታውቋል። “ኦብነግ ለሰላም ስምምነቱ ያለውን ቁርጠኝነትና የሶማሌ ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እንዲረጋገጥ በሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴያችንን እንቀጥላለን። ነገር ግን ማናቸውም የእኛን የሕግ ዕውቅና ወይም በሰላም ስምምነቱ የፈጠርነውን መተማመን የሚያጣጥሉ ድርጊቶች ወይም ንግግሮች የምንቀበላቸው አይደሉም” ሲል አመልክቷል።
ፓርቲው፤ መንግስት የንግግሩን “ትክክለኛነት እንዲያረጋግጥ” እና “ትክክለኛ ሆኖ ከተገኘ ከዚህ ጎጂ አስተያየት ራሱን በማራቅ ለሰላም ሂደቱ ያለውን ቁርጠኝነት በአስቸኳይ እንዲገልጽ” ጥያቄ አቅርቧል። መንግስት ይህን ካላደረገ ግን ኦብነግን እንደ ሕጋዊ ፓርቲ ማየት እንዳቆመ “ያሳያል” ያለው የፓርቲው መግለጫ፤ “ይህም በሰላም ሂደቱ ላይ አደገኛ መዘዝ ይኖረዋል” በማለት አስጠንቅቋል።
ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ “አድርገውታል” ተብሎ በበይነ መረብ ተሰራጭቷል ስለተባለው ንግግር፣ ከመንግስት በኩል ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ የተባለ ምንም ነገር የለም፡፡


Friday, 13 September 2024 08:55

“ጠይቆሀል በይው”

ከደጃፉ ቆመሽ እናቴ አታኩርፊኝ
ከበር እንድመለስ በእጆችሽ አትግፊኝ
በደማቅ ትዝታሽ
በማይጠፋው ፍቅርሽ አስረሽ
አትጥለፊኝ
ይልቅ አሳልፊኝ!
ልክ እንደ እኩዮቼ ልሂድ ልሰደደው
ባይተዋርነቱን እራቡን ልልመደው
በእኔ አትዘኝብኝ ስሚ ምን እንዳሉኝ
ምን እንደረገሙኝ ምን እንደበደሉኝ
እይው ምን እንዳሉኝ...
“ዘመኑ ያ’ድር ባይ
ልጆች አውቃለሁ ባይ
ጊዜው ነው በራሪ፣ ልጆች አሸባሪ
ከነዚህ መካከል
ሃገር ወዳድ ካለ ይመስክር ፈጣሪ!
ዛሬ ክብር አጥተዋል የሚባርኩ እጆች
ስራቸው የክፋት የዘመኑ ልጆች
ለዚህ ነው ይቺ ሀገር ተረካቢ ያጣች
የቤት ገመናዋን እዳሪ ያወጣች”
...እያሉ ያሙናል
ለወጪ ወራጁ ይጠቁሙቡናል
እኛን ይወቅሳሉ ላንቺ ክሳት ጥቁረት
እኛን ይሰድባሉ ለኪሳቸው እጥረት
እኛን ያደርጋሉ ለፀባቸው ምክንያት
ተስፋን ደበቁብን ነገን እንዳናያት
አየሽው ሀገሬ?!
አንዴ ከዘመን ጋር ከጊዜ ሲያጣሉን
አንዴም ካገራችን ታሪክ ሲነጥሉን
በማይራራ አንደበት ሲያነሱ ሲጥሉን
ሲያሰቃዩን ባጁ
እኛን መኮነኛ ተረት እያበጁ
በሃሜት አረጁ!
እናም ውድ ሀገሬ
በእኔ አትዘኝብኝ አታልቅሽ አይክፋሸ
እኔ ግፍ አልሰራም አንገት የሚያስደፋሽ
እስኪ ልሂድና ደግሞ ልመልከተው
ነገር ይቀል አይደል? ከመራቅ
ከመተው
እናም ከሄድኩበት ስደት እስክመለስ
እውነት ማረፊያዋ ጎጆዋ እስኪቀለስ
አምላክን ለምኝው
አምላክን ጠይቂው እሱ ይነግርሻል
የተደበቀውን እሱ ያሳይሻል...
ደግሞም ፈጣሪሽን
ደግሞም አምላክሽን
ፍርድ ስትለምኚው ከችሎት ስትደርሺ
አሁን የምልሽን ፍፁም እንዳትረሺ
ከውሳኔው በፊት
“እንዲህ ብሏል” በይው
“ጠይቆሀል” በይው
የልቤን ውስጥ ሀዘን ከፍተሽ አቀብይው
“እንዲህ ብሏል” በይው...
“አምላክ ሚዛናዊው ያው
እንደምታውቀው
እነሱስ ያለፉት
ቅድመ አያት በፌሽታ አያቶች በዘፈን
የልጅ ልጅ ልጆች ነን ሀዘን የተረፈን
እናም በሃገሬ
የቀለደ ትውልድ ያጣመማት
ትውልድ
መቀጣት ካለበት፤
እኛነን እነርሱ የሚጠየቁበት???”
እንዲህ ብሏል በይው
የልቤን ውስጥ ሀዘን ከፍተሽ አቀብይው
“ጠይቆሀል” በይው።
(ሳሚ አንተነህ)


ከሳምንት በፊት፣ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የአንድርያስ እሸቴ (ፕ/ር) የቀብር ስነ ስርዓት በመንበረ ጽባዖት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል። በዚሁ የቀብር ስነ ስርዓት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች፣ የፕሮፌሰሩ ቤተሰቦች እና ወዳጆቻቸው በተገኙበት እንደተፈጸመ ለማወቅ ተችሏል።

በስነ ስርዓቱ ላይ የአንድርያስ (ፕ/ር) የሕይወት ታሪክ በአቶ ነቢዩ ባዬ በንባብ የቀረበ ሲሆን፣ የእርሳቸው የሕይወት ጉዞ በሰፊው ተወስቶበታል። በተጨማሪም፣ ከፕሮፌሰሩ የረዥም ጊዜ ወዳጅ እና የታሪክ ምሁር ዓለምሰገድ ተስፋይ የተላከ መልዕክት ተነብቧል። በመልዕክታቸውም ከአንድርያስ (ፕ/ር) ጋር የነበራቸውን ወዳጅነት ያወሱት ዓለምሰገድ፣ የፕሮፌሰሩ ምሁራዊ ልሕቀት ምን ይመስል እንደነበር አመልክተዋል። ለፕሮፌሰሩ ዘላለማዊ ዕረፍት በመመኘት መልዕክታቸውን ቋጭተዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ ቡራኬ እና ቃለ ምዕዳን አስተላልፈዋል።

የቀብር ስነ ስርዓታቸው ዛሬ የተፈጸመው አንድርያስ እሸቴ (ፕ/ር)፣ የካቲት 23 ቀን 1937 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የተወለዱ ሲሆን፣ በዳግማዊ ምኒልክ ትምሕርት ቤት ትምሕርታቸውን ከተከታተሉ በኋላ ወደ አሜሪካ በማምራት፤ በዊሊያምስ ኮሌጅ የመጀመሪያ ዲግሪ ትምሕርታቸውን ተከታትለዋል። በመቀጠልም፣ ከየል ዩኒቨርስቲ የማስተርስ እና የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በፍልስፍና ተቀብለዋል።

በብራውን፣ ካሊፎርኒያ፣ ሎሳንጀለስ፣ በርክሌይ እና ፔንሲልቫኒያ ዩኒቨርስቲዎች እና ሌሎች የትምሕርት ተቋማት አስተምረዋል። በተለያዩ የምርምር መጽሔቶች ላይ ሃሳባቸውን እና ጥናታዊ ስራዎቻቸውን ያቀርቡት እንድርያስ (ፕ/ር)፣ በሞራል እና ፖለቲካዊ ፍልስፍና ላይ ትኩረታቸውን አድርገው ሲጽፉ ባጅተዋል።

ከተለያዩ ኢትዮጵያውያን ጋር በመተባበር “እምቢልታ” የተሰኘ መጽሔት ለተወሰኑ ዓመታት ሲያዘጋጁ መቆየታቸው ይነገራል።

በአገረ አሜሪካ በኖሩባቸው ጊዜያት፣ በሲቪል መብት ዕንቅስቃሴዎች ላይ ጉልህ ተሳትፎ ያደረጉ ሲሆን፣ “ብላክ ፓንተር” የተሰኘው ፓርቲ ውስጥ በስፋት ሰርተዋል። ከዚህ በመነሳት በአሜሪካ እና በአገር ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች የተደራጀ ዕንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባቸው ተሞክሮ እንደቀሰሙ ይነገራል።

ከመጀመሪያዎቹ የመላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስታዊ ንቅናቄ (መኢሶን) አባላት መካከል አንዱ የነበሩት እንድርያስ (ፕ/ር)፣ የደርግ መንግስት ከመንበረ ስልጣኑ ከወረደ በኋላ በሽግግር ምክር ቤት እና በሕገ መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን ውስጥ በነበራቸው ተሳትፎ የሚወሱ ምሁር ነበሩ። የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት በመሆንም ለዓመታት ሰርተዋል።

እንዲሁም፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ልዩ አማካሪ በመሆን አገልግለዋል።

የአንድ ወንድ ልጅ አባት የሆኑት እንድርያስ እሸቴ (ፕ/ር)፣ ባደረባቸው ሕመም ሳቢያ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

ኢትዮ ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል ለአራት የልብ ሕሙማን ሕጻናት የነጻ ሕክምና አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጿል። ይህንን የገለጸው ዛሬ ጳጉሜ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ባዘጋጀው መርሃ ግብር ላይ ነው።


ሆስፒታሉ የተመሰረተበትን አንደኛ ዓመትና መጪውን አዲስ ዓመት በማስመልከት፣ ለአራት የልብ ሕሙማን ሕፃናት በነፃ ሕክምና እያከናወነ መሆኑን አስታወቋል። "ሕፃናትን በልብ ሕመም ከመሞት ተባብረን እንታደጋቸው" በሚል መሪ ቃል፣ ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ ለ32 ሕፃናት የተሳካ የልብ ቀዶ ሕክምና በነፃ ማከናወኑን የኢትዮ ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል ባለቤትና ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ብርሃን ተድላ በመርሃ ግብሩ ላይ ተናግረዋል።


ሆስፒታሉ 300 ሕፃናትን ለማከም አቅዶ፣ ከእነዚህ ውስጥ የ32 ሕጻናትን ያከናወነ ሲሆን፣ ይህም ነፃ የልብ ቀዶ ሕክምና በገንዘብ ሲሰላ፣ 26 ሚሊዮን ብር እንደሚገመት አቶ ብርሃን አመልክተዋል። ባለፈው አንድ ዓመት ሆስፒታሉ ብቻውን በመሆን ማሕበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን የጠቀሱት አቶ ብርሃን፣ በአሁኑ ወቅት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከ16 ሺህ በላይ የልብ ሕሙማን ሕፃናት ወረፋ ይዘው እየተጠባበቁ መሆናቸውን አስረድተዋል። በተጨማሪም፣ አንዳንዶች ወረፋ ላይ እያሉ ሕክምና ሳያገኙ እየሞቱ ስለሆነ፣ ተቋማትና ግለሰቦች ድጋፍ በማድረግ ሕጻናቱን ከሞት እንዲታደጓቸው ጥሪ አቅርበዋል።


"አንድን ሕፃን በቡድን ለአስር ማሳከም ይቻላል። በመተባበርና በመተጋገዝ ለውጥ ማምጣት ይቻላል” ብለዋል፣ አቶ ብርሃን ንግግራቸው ሲቋጩ።



የዕለቱ የክብር ዕንግዳ እና የኢትዮጵያ የልብ ማሕበር ፕሬዝዳንት አቶ እንዳለ ገብሬ ባደረጉት ንግግር፣ ከ11 ወራት በፊት ማሕበራቸው ከኢትዮ ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል ጋር በመነጋገር እና የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ለልብ ቀዶ ጥገና እየጠበቁ ከሚገኙት ታካሚዎች መካከል በጎፈቃደኞችን በማስተባበር በዓመት 3 መቶ ሕጻናትን በኢትዮ ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል ለማሳከም እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል። አያይዘውም፣ ማሕበራቸው በተለያዩ የመንግስት ሆስፒታሎች፣ ይልቁንም በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተመዝግበው ወረፋ እየጠበቁ ከሚገኙ 16 ሺሕ ያህል ታካሚዎች መካከል፣ ባቋቋመው እና ሰባት አባላት ባሉት የሕክምና ባለሞያዎች ኮሚቴ እየመረጠ እንደሚልክ አቶ እንዳለ ተናግረዋል።


እስከ ዛሬ ድረስ 20 ያህል ታካሚዎች በኢትዮ ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል ነጻ የሕክምና አገልግሎት እየተሰጣቸው “ይገኛል” ያሉ ሲሆን፣ የሆስፒታሉን ባለቤት እና መላ የሕክምና ባለሞያዎችን በማሕበሩ እና ታካሚዎች ስም ምስጋናቸውን በማቅረብ፣ ይህን የበጎአድራጎት ስራ ሌሎችም እንዲቀላሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የነፃ ሕክምና ተጠቃሚ የሆኑ ሕፃናትና ቤተሰቦቻቸው በተደረገላቸው የሕክምና ድጋፍ የታካሚዎቹ ጤና መመለሱን በመመስከር ለኢትዮ ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል ምስጋና አቅርበዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ ከተገኙ ዕንግዶች መካከል፣ አርቲስት ሰለሞን ቦጋለ ሕክምና ተደርጎላቸው የተፈወሱ ልጆች የነገ አገር ተረካቢ መሆናቸውን አስታውሷል። አያይዞም፣ በአቶ ብርሃን ተድላ የተመሰረተው ኢትዮ ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል ባከናወነው ሰብዓዊ ተግባር ያለውን ምስጋና ገልጿል።


በዚህ መርሐግብር ላይ ተጋብዘው ከተገኙት ዕንግዶች መካከል፣ የሆስፒታሉን ጥረት ለማገዝና አጋርነታቸውን ለማሳየት ባለሃብቶቹ አቶ ገበያው ታከለ 200 ሺህ ብር፣ አቶ ጌቱ ገለቴ 500 ሺህ ብር ለግሰዋል። አቶ ብርሃን ተድላ ለተደረገው የገንዘብ ድጋፍ በልብ ሕሙማኑ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

አድማስ ዩኒቨርስቲ 16ኛውን ዓመታዊ የጥናትና ምርምር ጉባዔውን በዛሬው ዕለት ጳጉሜ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. የተለያዩ የዩኒቨርስቲው አመራሮች በተገኙበት በአዲስ አበባ፣ ኢንተርሌግዠሪ ሆቴል አካሄዷል። ዩኒቨርሲቲው ለዘንድሮው ጉባዔ የመረጠው የጥናትና ምርምር ርዕስ “የከፍተኛ ትምሕርት ጥራት፣ ጥናትና ምርምር፣ እንዲሁም የማሕበረሰብ አገልግሎት በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ” የሚል እንደነበር ተገልጿል።


ለአንድ አገር በወሳኝነት የሚጠቀሰውን የትምሕርት ጥራትና ከዩኒቨርሲቲዎች ተልዕኮ አንዱና ዋነኛ የሆነውን የማሕበረሰብ አገልግሎት ምን እንደሚመስል፣ ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ ቀንድን የሚዳስስ የጥናትና ምርምር ወረቀት በጉባኤው ላይ ቀርቧል።


የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ሞላ ጸጋ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ዩኒቨርስቲያቸው ባለፉት 14 ዓመታት የትምሕርት ጥራትን ማዕከል ያደረገና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ጉባዔዎችን ሲያካሂድ መቆየቱን አስታውሰው፣ በዚህም ረገድ ሃላፊነታቸውን ሲወጡ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

 
በዘንድሮውም የጥናትና ምርምር ጉባኤ በተመረጠው ርዕስ ዙሪያ፣ ምሁራን የጥናትና ምርምር ስራቸውን እንዲያቀርቡ በመጋበዝና ከቀረቡት ውስጥ የተሻለ ይዘት ያላቸውን በማወዳደር በዛሬው ዕለት ለጉባዔው ማቅረባቸውን የገለጹት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት፣ በዚህም ዘርፍ እየታየ ያለውን ክፍተት ለመሙላት መፍትሔ ጠቋሚ የሆኑ የጥናትና ምርምር ውጤቶች እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

 
ከትምሕርት ሚኒስቴር፣ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ከባለድርሻ አካላት የተወከሉ ሃላፊዎች በዚህ ጉባኤ ላይ ተገኝተዋል።


አድማስ ዩኒቨርሲቲ በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ባሉ ካምፓሶቹ ከ20 ዓመታት በላይ በርካታ ዜጎችን በተለያዩ የትምሕርት ዘርፎች በማስተማር፣ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎችን ባለሞያ ማድረጉ ሲነገር፣ በዚህ በአገሪቱ ያለውን የሰለጠነ የሰው ሃይል ዕጥረት በመሸፈን የበኩሉን አስተዋጽዖ እያደረገ ያለ ተቋም “ነው” ተብሏል፡፡

Page 12 of 733