Administrator

Administrator

    አትሌት ሃይሌ ገብረ ስላሴ በኬንያ ሰላምን ለማስፈን ታስቦ በተዘጋጀውና በአጠቃላይ 800 ኪሎ ሜትሮችን በሚሸፍነው የሰላም ጉዞ የተሰኘ የታዋቂ አትሌቶች የእግር ጉዞ ላይ እንደሚሳተፍ ዘ ጋርዲያን ረቡዕ ዘገበ፡፡“የዜጎች መገደልና ከመኖሪያ ቤታቸው መፈናቀል በሁላችንም ልብ ውስጥ ጥልቅ ሃዘን የሚፈጥር ነገር ነው” ሲል ባለፈው ሳምንት ለጉዳዩ የሚሰጠውን ትኩረት ያሳወቀው ሃይሌ፣ በኬንያ ሰላምን ለማስፈን ታስቦ በሚከናወነው የሰላም ጉዞ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደሚሳተፍ መግለጹንም ዘገባው ገልጧል፡፡ኬንያውያን ሰላምን ጠቀሜታ እንዲገነዘቡና በተለይም በአገሪቱ ሰሜናዊ አካባቢዎች የሚታየውን የጎሳ ግጭት ለመግታት የሚያስችል አገራዊ ንቅናቄ ለመፍጠር ታስቦ የተዘጋጀው ይህ የሰላም ጉዞ፣ በመጪው ነሃሴ ስድስት ቀን የሚጠናቀቅ ሲሆን ሃይሌም በእለቱ በሚደረገው የመጨረሻው ጉዞ እንደሚሳተፍ ይጠበቃል፡፡
የማራቶን የአለም ክብረወሰን ባለቤት የሆነውን አትሌት ፖል ቴርጋት ጨምሮ ታዋቂ ኬንያውያን
አትሌቶች የሚካፈሉበት ይህ የሰላም ጉዞ፣ በሰሜናዊቷ የኬንያ ከተማ ሎድዋር ባለፈው ረቡዕ የተጀመረ ሲሆን፣ ለ24 ተከታታይ ቀናት በየቀኑ 40 ኪሎ ሜትሮችን በመሸፈን በአጠቃላይ 836 ኪሎ ሜትሮችን ይሸፍናል ተብሏል፡፡አትሌቶቹ በጉዞው ከ250 ሺህ ዶላር በላይ ገንዘብ በማሰባሰብ በአገሪቱ ተለያዩ አካባቢዎች ለሚከናወነው የሰላም ማስፈን ፕሮግራም ለመለገስ ማቀዳቸውንም ዘ ጋርዲያን አክሎ ገልጧል፡፡በህገወጥ የሰዎች ዝውውር የተጠረጠሩ 15 ኢትዮጵውያንን በኬንያ ታሰሩበኬንያ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተግባር ላይ ተሰማርተው ሲንቀሳቀሱ ነበር ተብለው የተጠረጠሩ 15 ኢትዮጵውያን ባለፈው ረቡዕ ኢምቡ በተባለችው የኬንያ ከተማ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኢንቲቪ ኬንያ ዘገበ፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በአገሪቱ መዲና ናይሮቢና በኢምቡ ከተማ አካባቢ በስውር በህገወጥ መንገድ ሰዎችን ሲያዘዋውሩ እንደነበር የጠቆመው ዘገባው፣ ፖሊስ የደረሰውን ጥቆማ መሰረት በማድረግ ባደረገባቸው ክትትል እንደዛቸው ገልጧል፡፡የከተማዋ ፖሊስ የአካባቢው ነዋሪዎች በሰጡት ጥቆማ ተጠርጣሪዎቹን በአንድ የበቆሎ እርሻ ውስጥ ተደብቀው እንዳሉ በቁጥጥር እንዳዋላቸውና ኢትዮጵውያን መሆናቸውን ከመግለጽ ውጭ፣ ስለተጠርጣሪዎቹ ማንነት መረጃ አልሰጠም፡፡

አንዳንድ ተረት አንዴ ተነግሮ የማይበቃውና ሰዎች ተገርተው እስኪበቃቸው የሚተረት ይሆናል፡፡ የሚከተለው ተረት የእዛ ዓይነት ነው፡፡
አንድ ቤት ውስጥ አባት፣ እናትና ህፃን ልጅ ይኖራሉ፡፡
አንድ ቀን ማታ ህፃኑ በምን እንደከፋው አይታወቅም ክፉኛ ያለቅሳል።
አባት - “አንተ ልጅ ምን ሆንኩ ብለህ ነው የምታለቅሰው?” ይሉታል።
ልጅ ለቅሶውን ይቀጥላል፡፡
እናት - “ዝም በል ማሙሽ፡፡ ዝም ካልክ የማረግልህን አታቅም” አሉት በማባባል ቃና፡፡
ልጅ አሁንም ማልቀሱን ይቀጥላል፡፡
አባት ተናደዱና፤
“እንግዲህ ዝም ካላልክ ለጅቡ ነው የምሰጥህ!”
ልጅ አሁንም ያለቅሳል፡፡
እናት ይጨመሩና፤
“ዋ! ይሄንን በር ከፍቼ እወረውርሃለሁ!”
ለካ ቤት ውስጥ ይሄ ሁሉ ሲሆን አያ ጅቦ ውጪ ቆሞ ያዳምጥ ኖሯል።
ከአሁን አሁን ህፃኑን ይጥሉልኛል ብሎ ይጠብቃል፡፡
ቀስ በቀስ ልጁ ፀጥ አለ፡፡ ባልና ሚስት ራታቸውን በሉ፡፡ ልጁን አስተኙና ተቃቅፈው ተኙ፡፡
ጅቡ ቢጠብቅ፣ ቢጠብቅ ምንም የሚጣልለት ልጅ አላገኘም፡፡
በመጨረሻም፤ ወደ በሩ ጠጋ ብሎ፤
“ኧረ የልጁን ነገር ምን ወሰናችሁ?” አለ፡፡
ባለቤቶቹ በራቸውን ቆላልፈው ለጥ ብለዋል፡፡ አያ ጅቦ ጠብቆ ጠብቆ ሊነጋበት ሲል ወደ ጫካው ሄደ፡፡
*   *   *
በማስፈራራት ልጅን ማስተኛት አይቻልም፡፡ ልጁ የተከፋበትን ምክንያት ማወቅ እንጂ ማባበልም ጥቅም አይኖረውም፡፡ በአንፃሩ እንደ አያ ጅቦ የቀቢፀ ተስፋ ምኞት መመኘትም ራስን የባሰ ረሀብ ውስጥ መክተት ነው!
በሀገራችን የተመኘናቸው የነፃነት፣ የዲሞክራሲና የፍትህ ጥያቄዎች በዱላም በካሮትም (Carrot and stick እንዲሉ) እየተሞከሩ ረዥም ዕድሜ አሳልፈዋል፡፡ ዛሬም የጠራ ጐዳና ላይ አልወጡም፡፡ የተኙ ተኝተዋል፡፡ የሚያለቅሱ ያለቅሳሉ፡፡ እንደ አያ ጅቦ ደጅ የቀሩም ይቀራሉ።
“…አሁን የት ይገኛል፣ ቢፈልጉ ዞሮ
መስማት ከማይፈልግ፣ የባሰ ደንቆሮ”
የሚለውን የከበደ ሚካኤልን ግጥም ልብ ማለት ለሀገራችን በጣም ጠቃሚ ነው፡፡
አሁንም የህዝብን ብሶት እናዳምጥ፡፡ ዛሬም ያልተመለሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ቀና ልቦና ይስጠን፡፡ ሌላው ቀርቶ የዓለም መንግሥታት የሚያደርጉልንን ድጋፍ ለመቀበልም ቀና ልቡና ያስፈልጋል፡፡ መረጃዎችን፣ አገራችንን የሚመለከቱ ጉዳዮችን እናውቅ ዘንድ ቀና ልቡና አለንና በወጉ የማወቅ መብታችን ሊጠበቅ ይገባል፡፡
የደረስንበት እንዳይርቅ፣ ከእጃችን ያለው እንዳይፈለቀቅ ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ዛሬም መደማመጥ፣ መቻቻልና ዛሬም ረብ ያለው የፖለቲካ አቅጣጫና ተጨባጭ የሀገር ጉዳይን ማንሳት ይጠበቅብናል። የአሸነፈም፣ የተሸነፈም ሀገር ለምንላት የጋራ ቤት ምን ዓይነት አስተዋጽኦ እያደረግሁ ነው ብሎ መጠየቅ አለብን፡፡
ማንም ቢሆን ማን ምርቱ ይታወቃል፡፡ መንገዱም ይለያል፡፡ መሸሸግ የማይቻሉ በርካታ ነገሮች መኖራቸውን ህዝብ ያውቃል፡፡ ምክንያቱም ፍሬ ከዛፉ ርቆ አይወድም።

በድቅድቁ የቀለመውን ፅልመት ሃዘን በከረቸመው ከንፈሮችዋ መሃል በማትጐለጐል ነበልባል የነገን ጭላንጭል ተስፋ እያየች ትዕግስት የሚሉት ተሰጥኦ እንደዛር ተከምሮባት ከባዱን ችላ ስለምትወዳቸው መስዋዕትነት የከፈለች በእውነት ጐበዝ ጀግና ነች…”
ከላይ የቀረበው ቅንጭብ የተወሰደው ደራሲ ዝናሽ ኤልያስ (ዲና) ከጻፈችውና “መስዋዕት” የሚል ርዕስ ከሰጠችው ረዥም ልብወለድ ሲሆን መጽሐፉ ሰሞኑን ለገበያ ቀርቧል፡፡ የታሪኩ ጭብጥ በአንዲት ሴት የህይወት ውጣ ውረድ ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው ተብሏል፡፡
“መስዋዕት” በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተፃፈና በ214 ገፆች የተሰናዳ ሲሆን በ60 ብር ለሽያጭ እንደቀረበ ታውቋል፡፡

በዓለማየሁ ማሞ የተፃፈው “የህይወቴ ፈርጦች” የተሰኘ ግለታሪክ ከትላንት በስቲያ በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አዳራሽ ተመርቆ ለንባብ በቃ፡፡
ደራሲው በመግቢያው ላይ መጽሐፉን የፃፈበትን ምክንያት ሲያስረዳ፤ “ልጅነቴን፤ የትምህርት ቤት ውሎዬን ኋላም መርከበኛ፤ የጤና ባለሙያ፤ ጋዜጠኛና ደራሲ ሳለሁ ወይም እያለሁ የሆኑትን ግን አንኳር የመሰሉኝን ነው የመረጥኳቸው፡፡ ካሰብኩት ቆየሁ። በዚህም ላይ በጨዋታ መሃል የተነሱ ፈርጦችን ወዳጆቼ ስለወደዷቸው በወረቀት ላይ እንዳኖራቸው ገፋፍተውኛል፡፡” ብሏል፡፡
መጽሐፉ በዘጠኝ ምዕራፎች ተከፋፍሎ በ268 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን ለአገር ውስጥ በ80ብር፣ ለውጭ በ20 ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡ ፀሐፊው አለማየሁ ማሞ ነዋሪነቱ  በአሜሪካ ሜሪላንድ ሲሆን ባለፉት 17 ዓመታት ለጠቅላላ ዕውቀት የሚጠቅሙና ይልቁንም ለነፍስ ዕውቀት የሚበጁ በርካታ መፃህፍትን እንዳዘጋጀ ታውቋል፡፡

የዘንድሮ የትምህርት ጊዜ ማብቃትን ምክንያት በማድረግ “ኑ እናንብብ” የተሰኘ የተማሪዎች የክረምት የመፅሃፍ ንባብ፣ የባህልና የኪነ ጥበብ ፌስቲቫል ሐምሌ 11 እና 12 በአዲስ አበባ የስብሰባ ማዕከል እንደሚካሄድ ተገለፀ፡፡
በፌስቲቫሉ ላይ ከ30 በላይ በመፅሀፍ ህትመትና ሥርጭት ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችና ከ20 በላይ የአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሏል፡፡ በሁለት ቀን ፌስቲቫሉ ላይ አንጋፋና ወጣት ደራስያን፣ አርቲስቶችና ምሁራን ለህፃናትና ወጣቶች መፃህፍት የሚያነቡ ሲሆን የህፃናት ቴአትሮች፣ መዝሙሮች፣ ፊልሞች፣ የፖፔት ትዕይንቶች እንዲሁም የባህልና ታሪክ የማስተዋወቂያ ዝግጅቶች እንደሚቀርቡ ታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሥነ - ፅሁፍ፣ የስዕልና የተሰጥኦ ውድድሮችም ተዘጋጅተዋል፡፡
የፌስቲቫሉ ዋና ዓላማ ተማሪዎች የንባብ ባህላቸውን እንዲያዳብሩ ግንዛቤ መፍጠር ሲሆን ከተለያዩ የሙያ መስኮች የተጋበዙ ስኬታማ እንግዶችም የህይወት ልምዳቸውንና የንባብ ጠቀሜታን በተመለከተ ተመክሮአቸውን ለተማሪዎች እንዲያጋሩ ማድረግ ነው ተብሏል፡፡
የተማሪዎች የክረምት ፌስቲቫሉን በኢቢኤስ ቴሌቪዥን “የኢትዮጲስ ጊዜ” የተሰኘ የህፃናት ፕሮግራም አዘጋጅ የሆነው አማራጭ ሚዲያና ኢንተርቴይመንት ከአዲስ ምዕራፍ ፕሮሞሽን ጋር በመተባበር እንዳዘጋጁት ለማወቅ ተችሏል፡፡

Saturday, 11 July 2015 12:38

የኪነጥበብ ጥግ

(ስለ ጃዝ ሙዚቃ)
ጃዝ ከሌሎች የሙዚቃ ዘውጎች የተዋሰውን ያህል፣ ለሌሎች የሙዚቃ ዘውጎችም አውሷል፡፡
ኸርቢ ሃንኮክ
የጃዝ ሙዚቃ ገብቶኛል፡፡ አሰራሩንም ተረድቼዋለሁ፡፡ ለዚያም ነው በሁሉም ነገር ላይ የምጠቀምበት፡፡
ቫን ሞሪሰን
 ለውጥ ሁልጊዜ በመከሰት  ላይ ያለ ነገር ነው። የጃዝ ሙዚቃ አንድ ድንቅ ነገር ያ ነው፡፡
ማይናርድ ፈርጉሰን
የጃዝ ሙዚቃ በተፈጥሮው የብዙ የተለያዩ ዓይነት ሙዚቃዎች ጥምረት ነው፡፡
ዴቪድ ሳንቦርን
በቀን ለ3 ሰዓት ያህል ጃዝ አዳምጣለሁ፡፡ ሉዊስ አርምስትሮንግን እወደዋለሁ፡፡
ፊሊፕ ሌቪን
የጃዝ ሙዚቃ እጅግ በርካታ ተዓምረኛ ዝነኞችን ፈጥሯል፡፡
ዊንቶን ማርሳሊስ
ጃዝ ለእኔ ህያው ሙዚቃ ነው፡፡ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የሰዎችን ስሜት፣ ህልምና ተስፋ ሲገልፅ የኖረ ሙዚቃ ነው፡፡
ዴክስተር ጎርዶን
ጃዝ በጣም ዲሞክራሲያዊ የሙዚቃ ዓይነት ነው፡፡ ከጋራ ተመክሮ ይመነጫል። የየራሳችንን መሳሪያ ይዘን በጋራ ውበትን እንፈጥርበታለን፡፡
ማክስ ሮች
የጃዝ መንፈስ የግልፅነት መንፈስ ነው፡፡
ኸርቢ ሃንኮክ
ጃዝ በሶስት ወይም በአራት ዓመት የምትማረው አሊያም የሙዚቃ ተሰጥኦ ስላለህ ብቻ የምትጫወተው የሙዚቃ ሥልት አይደለም፡፡
ዊንቶን ማርሳሊስ
ጃዝ የመነጨው ከአኗኗር ዘይቤያችን ነው። የአገራችን የጥበብ ዓይነት በመሆኑም ማንነታችንን ለመረዳት ያግዘናል፡፡
ዊንቶን ማርሳሊስ
ጃዝ የግሌ ቋንቋ ነው ማለት እችላለሁ፡፡
ኤሚ ዊኒሃውስ
ጃዝ እንደ ወይን  ጠጅ ነው፡፡ አዲስ ሲሆን ባለሙያዎች፣ ሲቆይ ግን ሁሉም ይፈልገዋል።
ስቲቪ ላሲ

     ምንም የተፈጥሮ ሀብት የሌላቸው እንደ ዱባይ ያሉ አገሮች ሰው ሰራሽ የቱሪስት መስህብ እየሰሩ የጎብኚዎችን ልብ ሲያማልሉ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ፣ በሰው ሰራሽና በህዝቦቿ ቱባ ባህል የበለፀገች ብትሆንም አገሪቷም ሆነች ህዝቦቿ ለዘመናት የዚህ ሀብት ተጠቃሚ አለመሆናቸው በርካታ ኢትየጵያውያን የሚቆጩበት ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል፡፡
ሰሞኑን ግን እንደ እግር እሳት የሚለበልበውን ቁጭታቸውን የሚያበርድ ዜና ከወደ አውሮፓ ተሰምቷል፡፡ ይኸውም የአውሮፓ ቱሪዝምና ንግድ ም/ቤት ጠቅላላ ጉባኤ ኢትዮጵያን በ2015 የዓለም ምርጥ የቱሪዝም መዳረሻና ተመራጭ የባህላዊ ቱሪዝም መዳረሻ በማለት በሁለት ዘርፎች መምረጡን የባህልና ቱሪዝም ሚ/ር አስታውቋል፡፡
ሚ/ር መስሪያ ቤቱ ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ፣ ኢትዮጵያ ከ31 የዓለም አገራት ጋር ተወዳድራ በቀዳሚነት መመረጧና እውቅና ማግኘቷ መንግሥት ለቱሪዝም ኢንዱስትሪ በተለይም ባህላዊ ቱሪዝምን ለማስፋፋት ያለውን ፍላጎትና ቁርጠኝነት ያመለክታል ተብሏል፡፡
መንግሥት በ2006 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅትን በአዋጅ አቋቁሞ የቱሪዝም መዳረሻዎችን እንዲያለማና የቱሪዝም ገበያውን እንዲመራ አድርጓል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በዚሁ ዓመት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ም/ቤት አቋቁሞ ለዘርፉ ዕድገት እየሠራ መሆኑ ታውቋል፡፡ ጠቅላይ ሚ/ር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለጪስ አልባው ኢንዱስትሪ መበልፀግ የሰጡት ትኩረት በአውሮፓ የቱሪዝምና ንግድ ም/ቤት ጠቅላላ ጉባኤ እውቅና ከማግኘቱም በላይ ከ28 አገራት መሪዎች ጋር ተወዳድረው ግንባር ቀደም የቱሪዝም መሪ በመባል እንዲመረጡ አድርጓቸዋል፡፡ ሽልማታቸውንም በመጪው ሳምንት አርብ እንደሚቀበሉ ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ ቱሪዝምን ለድህነት ቅነሳ፣ ለስራ ፈጠራ፣ ለዜጎች መተዳደሪያ፣ ለሰላም ግንባታና ለዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና ለአገር ገፅታ ግንባታ፣ … እንዲውል ማድረጓ እንዳስመረጣት መግለጫው አስታውቋል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በርካታ ብሔር/ብሔረሰቦችን አቅፋ መያዟ፣ የአገሪቷ መልክአምድራዊ አቀማመጥ በጣም ውብና አስደናቂ መሆን፣ በተራራማ አቀማመጧ የአፍሪካ ጣሪያ፣ በበርካታ ወንዞችና ድርጅቶቿ የአፍሪካ የውሃ ማማ መባሏ፣ ህዝቦቿ ለዘመናት ያካበቱት የየራሳቸው ድንቅ ባህልና የባህል መገለጫዎች፣ ባለፉት 10 ዓመታት የባህልና የተፈጥሮ መስህቦቿን ሀብት ለዓለም የቱሪስት ገበያ በማስተዋወቅ ከዘርፉ በሚገኝ ሀብት ህዝቦቿን ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ማድረጓ፣ በ2015 ምርጥ የቱሪስት መዳረሻ ለመሆን እንዳበቃት ተነግሯል፡፡  
እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያን በሰው ዘር መገኛነት የሚቀድማት የለም.፡፡ ከማንኛውም አገር የበለጠ በርካታ የቅድመ ታሪክና የሰው ዘር መገኛ መካነ ቅርስ ስላላት ጥናትና ምርምር ከሚደረግባቸው አገሮች አንዷና ተመራጭ ናት፡፡ ከ3 ሚሊዮን በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩትን የሉሲ  ወይም ድንቅነሽና ሌሎች ቅሪተ አካላት፣ የጎና ጥንታዊ ድንጋይ መካነ ቅርስ ቦታዎች፣ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ ታሪካዊ ግብረ ህንፃዎች፣ ሰማይ ጠቀስ ሀውልቶች፣ ዘመናት ያስቆጠሩ የሦስቱ ሃይማኖቶች የታሪክ አሻራዎች (ፍልፍል ቤተክርስቲያናት፣ ጥንታዊ መስጊዶችና ቤተ - እምነቶች) የሃይማኖት አባቶች የመቃብር ቤቶች፣ ለምርጫ ያበቋት ሀብቶቿ ናቸው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት መሆኗም ተገልጿል፡፡ በሚዳሰሱ ቅርሶች የአክሱም ሀውልቶች፣ የጎንደር አብያተ መንግስታት፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የጢያ ትክል ድንጋይ፣ የሀረሩ ጀጎል ግንብ፣ የኮንሶ መልክአ ምድር፣ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የታችኛው አዋሽና የታችኛው ኦሞ ሸለቆዎች በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ሲሆን፣ ድሬ ሼክ ሁሴን ሆልቃ ሶፍ ኡመር፣ የጌዴኦ ጥምር ግብርና መልክአ ምድር፣ የመልካ ቁንጡሬ ቅድመ ታሪክ መካነ ቅርስና የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በዓለም ቅርስነት መዝገብ ውስጥ ለመካተት ተራ እየጠበቁ ነው፡፡
በማይዳሰሱ ቅርሶች ደግሞ የመስቀል በዓል በዓለም የውክልና መዝገብ (ዎርልድ ሬፕሬዘንታቲቭ ሊስት) የተመዘገበ ሲሆን የሲዳማ ዘመን መለወጫ ጨንበላላ በዓልና የገዳ ስርዓት በዓለም የውክልና መዝገብ እንዲካተቱ በቅርቡ ለዩኔስኮ እንደምትልክ ታውቋል፡፡
12 ጥንታዊ ጽሑፎችና መዛግብት በዓለም ሜሞሪ ዝርዝር ውስጥ የተመዘገቡ ሲሆን በቅርቡም ሁለት ጥንታዊ ጽሑፎች መላኳ ተገልጿል፡፡ በጥብቅ የተፈጥሮ አካባቢዎች ከሽካ፣ ከካፋና ያዩ በተጨማሪ የጣና ሐይቅ አካባቢም ባለፈው ወር ተመዝግቧል፡፡
ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያን ምርጥና ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ሆና እንድትመረጥ ያደረጋት ሰላምና ፀጥታ ማስከበሯና ለቱሪስቶች ደህንነት ምቹ መሆኗ እንደሆነ መግለጫው አመልክቷል፡፡  

በዓለም ትልቁን የእንቁጣጣሽ ፖስት ካርድ በጊነስ ቡክ ለማስመዘገብ ታቅዷል

የዘንድሮው የ“ሀበሻ አዲስ ዓመት ኤክስፖ 2008” ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚደረግበትና ኤግዚቢሽኑን ከቀደምቶቹ የተለየ ለማድረግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ መሆኑ ተገለፀ፡፡
የኤግዚቢሽኑ አዘጋጅ የሀበሻ ዊክሊ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ አደኒክ ወርቁ ሰሞኑን በሀርመኒ ሆቴል ለጋዜጠኞች በተሰጠ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ከዘጠኝ ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ዋጋ ጨረታውን አሸንፈው ማዕከሉን ለአዲስ ዓመት ኤክስፖ የያዙት ሲሆን በኤግዚቢሽኑ ከዚህ ቀደም ያልተለመዱና ለየት ያሉ ፕሮግራሞችን ለማዘጋጀት ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ጨረታውን 50 በመቶ ጭማሪ አድርገው ማሸነፋቸውን የተናገሩት አቶ አዶኒክ፤ በቦታ ሽያጭ ላይ ያደረጉት ጭማሪ ግን ከ7 በመቶ በታች መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ በቀን ከ500 ሺህ በላይ ጎብኚ ይኖረዋል ተብሎ በሚጠበቀው የአዲስ ዓመት ኤክስፖ ዝግጅት፣ ከአሁን በፊት ያልተሞከሩና በዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ ሊያስመዘግቡ ይችላሉ የተባሉ ነገሮች መዘጋጀታቸውን ጠቁመው፣ ከእነዚህ መካከል በጥንታዊው ብራና የተዘጋጀ በዓለም ትልቁ የእንቁጣጣሽ ፖስት ካርድና የዓለማችን ትልቁ የሻማ ዛፍ እንደሚገኙበት ተናግረዋል፡፡
ከ100 በላይ ድምፃውያን፣ኮሜዲያን እንዲሁም ቀደምትና ዘመናዊ የሀገሪቱ ስመጥር ባንዶች በኤግዚቢሽኑ ላይ እንደሚሳተፉ የተገለጸ ሲሆን ታዋቂውና አንጋፋው ድምፃዊ ጌታቸው ካሣም ሥራዎቹን በኤክስፖው ላይ እንደሚያቀርብ ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

ቤትና ንብረቶችን በኢንተርኔት ለመሸጥና ለመግዛት የሚያስችል ዘመናዊ የግብይት ሥራ የሚሰራና ላሙዲ የተባለ አለምአቀፍ የኦንላይን ሪልስቴት ኩባንያ ሥራ ጀመረ፡፡
ደንበኞች ንብረታቸውን በቀላሉ ለመሸጥና ለመግዛት ያስችላቸዋል የተባለውና ዘመናዊው የኢንተርኔት የመገበያያ መንገድ ሥራ መጀመሩን አስመልክቶ ከትናንት በስቲያ በኩባንያው ቢሮ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተገለፀው በአገሪቱ የሪል ስቴቶች መስፋፋትና ማደግ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እያሳየ መጥቷል፡፡ ስለዚህም ደንበኞች ስለሚፈልጓቸው ቤቶችና ንብረቶች በቂና ጥልቀት ያለው መረጃ ለማግኘት የሚችሉበት መንገድ በስፋት ሊኖር ይገባል፡፡
ኩባንያው በገዢና ሻጭ በኦንላይን ተገናኝተው ቤትና ንብረታቸውን ለመገበያየት እንዲችሉ ዕድሉን ያመቻቻል፡፡
ኩባንያው ከዚህ በተጨማሪ ዳያል 4 ሆም የተሰኘ ሆት ላይንን ያስተዋወቀ ሲሆን ይህም ሆትላይን ንብረት ፈላጊዎች ያለ ኢንተርኔት ትስስር ተጠቃሚዎችን በስልክ እንዲገናኙ ለማድረግ የሚያስችል አሠራር ማዘርጋቱንም በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተገልጿል፡፡
ላሙዲ በኬንያ፣ በታንዛኒያ፣ በናይጀሪያ፣ በጋና፣ በኡጋንዳና ሩዋንዳ ቢሮዎቹን ከፍቶ እየሠራ የሚገኝ ኩባንያ ነው፡፡   

“ኦባማ አሻፈረኝ ብለው ስለዚህ ጸያፍ ነገር ካወሩ፣ ማዕቀብ እንጥልባቸዋለን!” - የኬንያ ፓርላማ አፈ ጉባኤ
   የኬንያ ከፍተኛ ባለስልጣናት በቅርቡ አገሪቱን ለመጎብኘት ቀጠሮ የያዙትን ባራክ ኦባማን፣ “አደራዎትን በጉብኝትዎ ወቅት የግብረ-ሰዶማውያንን መብት የተመለከተ ነገር እንዳይናገሩ” ሲሉ አበክረው ማስጠንቀቃቸውን ቴሌግራፍ ዘገበ፡፡
የኬንያ ምክትል ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶና የአገሪቱ ፓርላማ አፈጉባኤ ለኦባማ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የግብረ-ሰዶማዊነት ጉዳይ ከክርስትና እምነት ጋር የማይሄድ ጸያፍ ነገር ነውና፣ ሊጎበኙን ሲመጡ ጉዳዩን በተመለከተ ምንም ነገር ትንፍሽ እንዳይሉ ሲሉ አስጠንቅቀዋቸዋል ብሏል ዘገባው፡፡
ከሳምንታት በፊት በመላው ግዛቷ የግብረ-ሰዶማውያንን ጋብቻ በህግ የፈቀደችውን አሜሪካን የሚመሩት ኦባማ ግን፣  ከዚህ ቀደምም ደቡብ አፍሪካ፣ ታንዛኒያ እና ሴኔጋልን ሲጎበኙ እንዲህ ያለ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው፣ አሻፈረኝ ብለው ስለ ግብረ-ሰዶማውያን መብቶች በአደባባይ እንዳወሩት ሁሉ፣ የኬንያን ባለስልጣናት ማስጠንቀቂያንም ጆሮ ዳባ ልበስ ሊሉት ይችላሉ ተብሏል፡፡
ባለፈው እሁድ ናይሮቢ ውስጥ በሚገኝ አንድ ቤተክርስቲያን በተካሄደ ስነስርዓት ላይ፣ በርካታ ምዕመናን ለግብረ-ሰዶማዊነት ያላቸውን ተቃውሞ የገለጹ ሲሆን፣ ኦባማ እና ኦባማ ወይም ሚሼል እና ሚሼል እንዲመጡ አንፈልግም ሲሉ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን ነቅፈዋል፡፡
በስፍራው የተገኙት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ሩቶም፣ የምዕመናኑን ተቃውሞ በመደገፍ፣ እንዲመጡልን የምንፈልገው ኦባማ እና ሚሼልን ነው፤ ልጅ እንዲወለድልንም እንፈልጋለን ሲሉ በመናገር፣ አገራቸውን ከእንዲህ ያለው ጸያፍ ሃሳብ እንደሚከላከሉ ለምዕመናኑ ቃል ገብተዋል፡፡
የኬንያ ፓርላማ አፈ ጉባኤ ጀስቲን ሙቱሪ በበኩላቸው፣ አገራቸውና ህዝባቸው ጸያፍ ነገሮችን እንደማይፈልጉ በመግለጽ፣ ኦባማ ወደ አገራችን ከገቡ በኋላ የግብረ-ሰዶማውያንን መብቶች በተመለከተ ንግግር እንዳያደርጉ እናግዳቸዋለን፣ አሻፈረኝ ብለው ከተናገሩም ማዕቀብ እንጥልባቸዋለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡   
ኦባማ ከሁለት ሳምንታት በኋላ የአባታቸው እትብት የተቀበረባትን ኬንያን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡