Administrator

Administrator

    ከስድስት አመታት በላይ በጠፈር ላይ የቆየቺው ሉናር ሪኮኔሳንስ ኦርቢተር የተባለች የናሳ የጠፈር መንኮራኩር፣ ይሄን አጀብ የሚያሰኝ ዜና ይፋ አድርጋለች - ጨረቃ እያደር መጠኗ እያነሰና እየተኮማተረች መሄዷን ቀጥላለች፡፡
የጠፈር መንኮራኩሯ በተገጠመላት የረቀቀ ካሜራ ያነሳቻቸው ፎቶግራፎች፣ የጨረቃ መጠን ከዚህ በፊት ከነበረው እያነሰ መምጣቱን አመላክተዋል ሲል የዘገበው ሮይተርስ ነው፡፡
የጨረቃን ሶስት አራተኛ ክፍል መሸፈን በቻለው በዚህ ካሜራ የተነሱት ጥራት ያላቸው ፎቶግራፎች፣ በጨረቃ ላይ ከ3ሺህ በላይ ሰፋፊ ስርጉድ ስፍራዎች እንዳሉ የጠቆሙ ሲሆን ከአምስት አመታት በፊት የተነሱ ፎቶግራፎች ግን፣ በጨረቃ ላይ የነበሩት ስርጉድ ስፍራዎች 81 ብቻ እንደነበሩና የቁጥራቸው መብዛት ከጨረቃ መጠን እየቀነሰ መምጣት ጋር የተያያዘ ነው መባሉን ዘገባው አስታውቋል፡፡
የናሳ የጠፈር ተመራማሪዎች የጨረቃ መጠን እያነሰ የመጣው ከመሬት  ስበት ጋር ተያይዞ በተፈጠረ ተጽዕኖ ነው ማለታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ በራሷ በጨረቃ ውስጥ የሚታዩ የሙቀት መጠን ለውጦችም ለመጠኗ መቀነስ አስተዋጽኦ አበርክቷል ሲሉ መናገራቸውን አክሎ ገልጧል፡፡

    ከስድስት አመታት በፊት ለተካሄደው የ2009 የኖቤል ሽልማት የአመቱ ተሸላሚዎችን የመረጠውን የተቋሙ የሰላም ኮሚቴ በጸሃፊነት የመሩት ጌር ሉንደስታድ፣የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን ለኖቤል የሰላም ተሸላሚነት በመምረጣቸው መጸጸታቸውን እንደገለጹ ቢቢሲ ዘገበ፡፡በወቅቱ ኮሚቴው ኦባማን ለኖቤል የሰላም ሽልማት በዕጩነት ሲመርጣቸው፣ ለዚህ ትልቅ ሽልማት የሚያበቃ ጉልህ ስራ አልሰሩም በሚል ተቃውሞ ገጥሞት እንደነበር ያስታወሱት ሉንደስታድ፣ሽልማቱ መነቃቃትን ፈጥሮላቸው ተጨባጭ ስራ ይሰራሉ ብሎ በማመኑ ኦባማን ተሸላሚ እንዳደረጋቸው ሰሞኑን ለንባብ ባበቁት የግለ ታሪክ መጽሃፋቸው ገልጸዋል፡፡ ኦባማ ግን ኮሚቴው እንደጠበቀው ለአለም ሰላም ይህ ነው የሚባል ጉልህ ተግባር አልፈጸሙም ያሉት ሉንደስታድ፣ በወቅቱ ኦባማን የኖቤል የሰላም ተሸላሚ ለማድረግ በነበራቸው ተሳትፎ መጸጸታቸውን በግልጽ ጽፈዋል፡፡ኦባማ የ2009 የዓለም የኖቤል የሰላም ተሸላሚ መሆናቸውን በሰሙበት ቅጽበት ነገሩን ለማመን መቸገራቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ብዙዎቹ የኦባማ ደጋፊዎችም የሽልማቱን ዜና የተሳሳተ ሳይሆን አይቀርም ብለው ተጠራጥረውት እንደነበር ጠቁሟል፡፡
ጌር ሉንደስታድ እ.ኤ.አ ከ1990 እስከ 2015 መጀመሪያ በኖቤል የሽልማት ድርጅት የሰላም ኮሚቴ ጸሃፊ በመሆን ማገልገላቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ተሸላሚዎችን በመምረጡ ሂደት ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደነበራቸው ጠቁሟል፡፡ የዘንድሮው የአለም የኖቤል የሰላም ተሸላሚ ከ20 ቀናት በኋላ ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት መፈንቅለ መንግስቱን አውግዘው፣የታሰሩ ባለስልጣናት እንዲፈቱ ጠይቀዋል
   የቡርኪናፋሶ የቤተ-መንግስት ጠባቂዎች ከትናንት በስቲያ ምሽት በመዲናዋ ኡጋዱጉ ባደረጉት መፈንቅለ መንግስት፣በፕሬዚዳንት ሚሼል ካፋንዶ የሚመራውን የአገሪቱን የሽግግር መንግስት በማፍረስ፣ ጄኔራል ጊልበርት ዴንድሬን በፕሬዚዳንትነት መሾማቸውን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
የቤተመንግስቱ ጠባቂዎች ባለፈው ረቡዕ በተከናወነ የካቢኔ ስብሰባ ላይ የሽግግር መንግስቱን ፕሬዚዳንት ሚሼል ካፋንዶ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩን አይዛክ ዚዳን በቁጥጥር ስር በማዋል ማሰራቸውንና በነጋታውም መፈንቅለ መንግስቱን ማድረጋቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡የአገሪቱን የቴሌቪዥን ጣቢያ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ጠባቂዎቹ በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር የሰዓት ዕላፊ አዋጅ በማውጣትና የአገሪቱ የየብስና የአየር ክልሎች ሙሉ ለሙሉ እንዲዘጉ በማድረግ ባከናወኑት በተኩስ የታገዘ መፈንቅለ መንግስት፣ የሽግግር መንግስቱን ጊዚያዊ መሪ ፕሬዝዳንት ሚሼል ካፋንዶን ከስልጣን አውርደዋል፡፡
አገሪቱን ለ27 አመታት ያህል የመሩት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ብሌስ ኮምፓዎሬ፤ ባለፈው አመት ባጋጠማቸው የህዝብ ተቃውሞ ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ ስልጣኑን የተረከበውና በፕሬዝዳንት ሚሼል ካፋንዶ የሚመራው የአገሪቱ የሽግግር መንግስት በመጪው ጥቅምት ወር ይከናወናል ተብሎ በሚጠበቀው የአገሪቱ ምርጫ ለሚያሸንፈው አዲስ መንግስት ስልጣኑን ለማስረከብ አቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ መፈንቅለ መንግስቱ ተካሂዶበታል፡፡የሽግግር መንግስቱ የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ብሌስ ኮምፓዎሬ ታማኞች እንደሆኑ የሚነገርላቸውን ፖለቲከኞች በመጪው ምርጫ እንዳይሳተፉ መከልከሉንና የፕሬዚዳንቱ ጠባቂ ሃይል እንዲበተን መገፋፋቱን የጠቆመው ዘገባው፣በዚህ የተቆጡ የፕሬዚዳንቱ ጠባቂዎች መፈንቅለ መንግስቱን ማካሄዳቸውን አመልክቷል፡፡ አገሪቱን በቅኝ ግዛት ታስተዳድር የነበረችዋ ፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ፍራንኮይስ ሆላንዴ በበኩላቸው፣ መፈንቅለ መንግስቱን አውግዘው በእስር ላይ የሚገኙት የሽግግር መንግስቱ ፕሬዚዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡

   ዘላኖች (አርብቶ አደር የሚል መጠሪያ ተሰጥቷቸዋል) በተፈጥሮአዊ የአኗኗር ዘይቤያቸው የተነሳ በአንድ አካባቢ ወይም ቦታ ረግተው አይቀመጡም. . .አይቆዩም፡፡ በየጊዜው ጓዛቸውን ተሸክመውና  በግመል አሸክመው መሄድ ነው-- ...መሄድ...መጓዝ....፡፡ የበረሃውን ሀሩር ሽሽት፤ ምግብና ውሃ፣ ለከብቶቻቸውም መኖ ፍለጋ .....ይሄዳሉ፣ይጓዛሉ፡፡የአዲስ አበባ ቤት ተከራዮችም እንዲሁ ናቸው፡፡ በአንድ ቤት ወይም ሰፈር አይረጉም...አይቆዩም፡፡ በየጊዜው እቃቸውን በአይሱዙና በፒክአፕ ጭነው መሄድ...ነው----መሄድ..መሄድ...ብቻ፡፡ የኑሮ ውድነቱን ሽሽት፤ ዋጋው ጣራ ያልነካ ወይም ከጣራው በላይ ያልዘለለ ቤት ፍለጋ---መጓዝ፡፡
ዘላኖች ቋሚ መንደር ወይም ቀዬ አልባ ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ ተከራዮችም ሰፈር አልባ ናቸው፡፡ የሥነልቦና ጫና ሰለባም ይሆናሉ፡፡ አንድ ቦታ ተረጋግቶ መኖር እንደማይቻል ማሰቡ የሚፈጥረው የስነልቦና ተፅእኖ፣ በየጊዜው እቃ ማስጫን ማስወረዱ፣ አዲስ ሰፈር የመላመዱ ፈተና፣ በተለይ ደግሞ ወላጆች ልጆቻቸውን በየጊዜው ከአንዱ የሰፈር ትምህርት ቤት ወደ ሌላ ሰፈር ትምህርት ቤት በማዘዋወር የሚያዩት ፍዳ ቀላል አይደለም፡፡
የአዲስ አበባ #ዘላኖች” ፤በአኗኗራቸው ሁኔታ ምክንያት ቤት ጎረቤት፣ እድርና  ማህበር አልባም ጭምር ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ የማህበራዊ ህይወት ወጎች ለተከራይ ቅንጦት ናቸው፡፡
በነገራችን ላይ የቤት ተከራዮች ዋንኛ አመታዊ ጭንቀት፣ኪራይ ይጨምር ይሆን ወይንስ አይጨምር ይሆን የሚለው ሳይሆን ስንት ይጨምር ይሆን የሚለው ነው፡፡ መጨመሩማ አይቀሬ ነው፡፡ እንደውም በነጋ በጠባው ኪራይ አለመጨመር በህግ ያስቀጣል ተብሎ የተደነገገ ነው የሚመስለው፡፡ ቤቱ ምንም ሳይለወጥ በየጊዜው ኪስን የሚያራቁት ኪራይ መቆለል፣ ለአከራዮች ሙዝ የመላጥ ያህል ቀላል ነው፡፡
ቆዳህን የላጡህ ያህል የሚሰማህ ግን አንተ ነህ - ተከራዩ. . . የአዲስ አበባው ዘላን!!
ደግሞ ለምን እንደሁ እንጃ፣ አከራዮች ሲባሉ የቤት ኪራይ መጨመሩን የሚገልፁት ወይ ጠዋት አልያም ማታ ላይ ነው፡፡ ጠዋት ወይም ማታ ላይ በር አንኳኩተው ወይም ስልክ ደውለው ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ይሄን ያህል ጨምሩ፡፡ አለቀ በቃ፡፡ ከቻልክ ትከፍላለህ፤ ካልቻልክ ትወጣለህ፡፡ ጭማሪው ከተሰማ በኋላ ቀኑ አንዴት እንደሚያልፍ ወይም ሌሊቱ እንዴት እንደሚነጋ አስቡት፡፡ ያው በጭንቀት ይዋላል፤በጭንቀት ይነጋል፡፡
ከገቢያችሁ በላይ የሆኑ  የቤት ኪራይና መሰል የኑሮ ጉዳዮች የሚፈጥሯቸው የወጪ ቀዳዳዎች መስፋት እንዴት ናላ እንደሚያዞር ለእናንተ መንገር ለቀባሪው እንደማርዳት ነው፤ ኑሯችሁን ታውቁታላችኋ፡፡
አንዳንድ አከራይ ደሞ አለ፡፡ መጨመሩ ላይቀር ከጭማሪው ጋር የሰበብ መዓት አግተልትሎ የሚመጣ፡፡ ትንሽ እያመመኝ ስለሆነ ለህክምና ብር ያስፈልገኛል ኪራይ ጨምር፤ ጤፍ፣ ምስር፣ ዘይትና በርበሬ ተወዷል ኪራይ ጨምር፤ እንዲህ ስለሆነ ነው ኪራይ ጨምሪ፣ እንዲያ ስለሆነ ነው ኪራይ ጨምሩ....ጨምሩ...ጨምሩ......፡፡ ኤዲያ ምንድነው በተከራይ ጫንቃ ላይ መወዘፍ (ጠብቆም ላልቶም መነበብ ይችላል) እኔ የህክምና ወጪ ደረሰኞቼን ባሳይ፣ የወሩን ኪራይ ይቀንሱልኛል? ጤፍ፣ ምስር፣ ዘይትና በርበሬ የሚጨምረውስ በአከራይ ላይ ብቻ ነው? ግርም እኮ ነው የሚለው፡፡
አንድ አከራይ ነበሩኝ፡፡ ግቢያቸው ተከራይቼ እንደገባሁ ከሰጡኝ ማስጠንቀቂያዎች መካከል መብራት እያበሩ (ቴሌቪዥን እያዩ፣ እያነበቡ ወይም ስራ እየሰሩ--) ማደር፣ ቤት ውስጥ ተጨማሪ ሰው ማስገባት አይደለም እግር የሚያበዙ ሌሎች ሰዎች መመላለስ ከጀመሩ ያለምንም ማስጠንቀቂያ የቤት ኪራይ እንደሚጨምር እወቅ-----የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡ ማስጠንቀቂያውን ሰጥተውኝ፣ ዱሮ ጠዋት ጠዋት በሬዲዮ በምንሰማው የቡናና ሻይ ማስታወቂያ ዜማ ስልት፤
የኢኮኖሚ ዋልታ ኪራይ ኪራይ
የገቢ ምንጫችን ኪራይ ኪራይ ...
የእድገታችን ገንቢ ኪራይ ኪራይ ..... እያሉ በኪራይ ሰብሳቢነታቸው እየተኩራሩ ወደ ቤታቸው ገቡ፡፡ እኔም ማስጠንቀቂያውን በሚገባ ነበር ተግባር ላይ ያዋልኩት፡፡  ሌሊት ማንበብ ካለብኝ በሞባይል ባትሪዬ፤ ፊልምም ካየሁ በላፕቶፕ፣ ጓደኞቼም ካስፈለጉኝ፣ ሄጄ ቤታቸው ነበር የማገኛቸው፡፡
ሰውየው ኪራይ መጨመራቸው ላይቀር ሰበብ ይፈልጉ ነበርና አንድ ቀን ማታ ከስራ ስገባ ሳሎን ቤታቸው አስጠሩኝ፡፡ አየኸው!?»
ወደ 32 ኢንች ቴሌቪዥናቸው ዞር ስል፣ በቅርቡ የተመረቀ አንድ ትልቅ ህንፃ ማስታወቂያ ይተላለፋል፡፡ እሳቸው ቀጠሉ ማብራሪያቸውን፡-
«አለም አቀፉ የምጣኔ ሀብት ቀውስ በሁሉም ሀገራት ላይ ተፅእኖውን እያሳደረ ነው፡፡ ሰሞኑን ዜናው ሁሉ እሱ ነው፡፡ እውነቱን እኮ ነው፡፡... የኑሮ ወድነቱማ ሀገራችን ከገባ ቆይቷል፡፡ የሰሞኑ ደሞ ባስ ያለ ነው፡፡ አሁን በቀደም ዕለት ለልጆቼ ጫማና ልብስ ልገዛ መርካቶ ሄጄ . . . . . . »
ሰውየው ይሄን ሁሉ ለምን እንደሚነግሩኝ ቢያንስ ለጊዜው አልገባኝም ነበር፡፡ ድክም ብሎኝ ስለነበር ወሬያቸውም ከኑሮው ጋር ተዳምሮ ስልችት ስላለኝ ከልቤ አልነበረም የማዳምጣቸው፡፡ መጨረሻ ላይ ግን ያሉት ነገር የመጀመሪያውን አሰልቺ ልፍለፋቸውን ዳርዳርታ ግልፅ አደረገልኝ፡፡ በል እስኪ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ኪራይ ጨምር፡፡ ከገባሁ ገና 3 ወር እንኳን አልሞላኝም ብዬ ለመከራከር ባስብም የትም እንደማያደርሰኝ ስለገባኝ  እሺ ብዬ ወጣሁ፡፡
አስቡት እስኪ ኪራይ ለመጨመር ከምዕራቡ አለም የኢኮኖሚ ቀውስ እስከ መርካቶ የልጆች ልብስ ገበያ የሚደርስ ኢኮኖሚያዊ ትንታኔን ያዘለ ሰበብ፡፡
ከጨመሩ ዝም ብለው አይጨምሩም፡፡ ተከራይ እንደሁ ከመክፈል አልያም እቃውን ሸክፎ ቤት ፍለጋ ከመሰደድ ውጪ አማራጭ እንደሌለው ያውቁታል፡፡ ሀይ ባይ የለማ፡፡ ማን የሚጠይቃቸው አለ፡፡ ከሚመለከተው አካል የሚጠበቀው የአከራይ ተከራይ መመሪያ እንደሆነ የውሃ ሽታ ሆኗል፡፡ የከተማውን ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ችግር የሚፈታ የተባለለት የቤቶች ልማትም፣ ችግሩን ማቃለል አባይን በጭልፋ ሆኖበታል፡፡ በዚያ ላይ የኮንዶሚኒየም ቤት ገዝቶ አትርፎ መሸጡ የደራ ቢዝነስ ሆኗል፡፡
በአንድ በኩል በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ለህዝብ በእጣ ይከፋፈላሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ እነ አጅሬ (የከተማይቱ ሀብታም የቤት ነጋዴዎች) ወደድ ሲል ለመሸጥ አልያም በውድ ለማከራየት በርካታ ቤቶችን ከህዝቡ ላይ ይገዛሉ፡፡
ሰው ስንት አመት ሲጠብቅ የኖረውን ቤት የማግኘት እድል ሲደርሰው እልል ብሎ በመቀበል ፈንታ የሚጠበቅበትን ክፍያ ለማሟላት ጭንቀት በጭንቀት መሆን ከጀመረ ከራረመ፡፡ ኮንዶምንየም ቤት ደርሷቸው ቅድሚያ ክፍያውን ለመክፈል ስንት እናቶችና አባቶች ልመና እንደወጡ፣ እራሱ ኮንዶምንየም ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ ይሄን ማድረግ ባለመፍቀዳቸው ወይም እርዳታ ለምነውም ስላልተሳካላቸው የመጣላቸውን እድል በውክልና ስም ለነጋዴ የሸጡትን ደግሞ ውልና ማስረጃ ይቁጠራቸው፡፡
እነዚህ ሰዎች የመክፈል አቅም አንሷቸው የሸጡትን ቤት ነገ መልሰው በውድ ዋጋ ተከራይተው ለመኖር ይገደዳሉ፡፡ አንዱ ሰፈር ሲወደድባቸው ወደ አንዱ፣ከዚያም ወደ ሌላው እያሉ እንዲሁ እንደ ዘላን ሲንከራተቱ ይኖራሉ፡፡
አንዱ የቤት ችግር ከአንዱ ሰፈር ወደ አንዱ ሰፈር የሚያላጋው አርቲስት፤ #ለምን ልጅ አትወልድም?; ተብሎ ሲጠየቅ፤ “እኔ ሰፈር የሌለው ልጅ መውለድ አልፈልግም” አይደል ያለው፡፡ ሸጎሌ ይረገዛል፣ ኮልፌ ይወለዳል፣ ሳሪስ ያድጋል (ቤተሰቦቹ ኪራዩን መቋቋም ከቻሉ እስከ 2 አመቱ)፣ ከዚያ አሁን ባለው ሁኔታ ጭማሪውን ችሎ አንድ ሰፈር ውስጥ ከሁለት አመት በላይ መቆየት ስለማይቻል ከቤተሰቡ እቃዎች ጋር በአይሱዙ እየተጫነ የዘላን ኑሮውን ይገፋል፡፡ ይሄንን ልጅ ሰፈርህ የት ነው ብሎ መጠየቅ፣ ውጤቱ ልጁን ማወዛገብ ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ ምን ብሎ ሊመልስ ይችላል?
እንደው ግን ለአዲስ አበባ ተከራይ የዘለቄታ መፍትሄው ምን ይሆን? አብረን የምናየው ይሆናል፡፡ እኔ ግን በቀጣዩ የአዝማሪዎች የቅብብሎሽ ግጥም ልሰናበታችሁ፡-  
ፈረንሳይ ባስጠይቅ ገባች አሉኝ አስኮ
ምን ታርግ ትልቀቅ እንጂ....
የዘንድሮ ኪራይ ያሳቅቃል እኮ
አስኮ ላይ ባስጠይቅ ገባች አሉኝ ገርጂ
መንግስትና አከራይ ለሰው እዘኑ እንጂ
ገርጂ ላይ ባስጠይቅ ሄዳለች አቡዋሬ
እዛ ይቀንሳል የሚል ሰምታ ወሬ
አቡዋሬ ባስጠይቅ ሄደች አሉ ሰሚት
ኮንዶሚኒየም ግቢ ይሻላል ብለዋት
ሰሚት ላይ ባስጠይቅ ሄዳለች ኮተቤ
እንክርቱዋን ሲያስብ ተሰበረ ልቤ
ኮተቤ ባስጠይቅ ገባች አየር ጤና
የገቢዋን እጥፍ ክራይ ከወሰደው ምን ሰላም አለና
አየር ጤና ስደርስ ሄዳለች ሰበታ
ከራቀ ቅናሽ ነው የሚል ወሬ ሰምታ
ሰበታ ባስጠይቅ ሄደች አሉኝ ገላን
መቼም ቋሚ የለው የከተማ ዘላን፡፡

የአንጋፋው ደራሲ የአበራ ለማ አዲስ ስራ የሆነው “ቅንጣት የኔዎቹ ኖቭሌቶች” አዲስ መጽሐፍ ዛሬ ከቀኑ 8፡00 -10፡30 ሰዓት በኢትዮጵያ ቤተ መፃሕፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ አዳራሽ ይመረቃል፡፡ በአግዮስ ህትመትና ጠቅላላ ንግድ ኩባንያ የታተመው መጽሐፉ በምረቃው እለት በታዋቂው ሃያሲ አብደላ ዕዝራ ዳሰሳዊ ግምገማ እንደሚቀርብበትም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ባቡሩ ነገ ማለዳ ስራውን ይጀምራል
   በነገው ዕለት ስራ ለሚጀምረው የአዲስ አበባ የቀላል ባቡር ፕሮጀክት የሃይል አቅርቦት የማሟላት ሃላፊነቱን የወሰደው “ቻይና ኤሌክትሪክ ፓዎር ኢኩፒመንት ኤንድ ቴክኖሎጂ” የተባለው ኩባንያ የሃይል አቅርቦቱን ያልተቆራረጠና አስተማማኝ አደርጋለሁ ሲል ቃል መግባቱን ዥንዋ ዘገበ፡፡
የኩባንያው ምክትል ጄኔራል ማናጀር ቼን ዊ፤ ኩባንያው በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ አምስት ቦታዎች የገነባቸውን የቀላል ባቡሩ የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ ንኡስ ጣቢያዎች ባስጎበኙበት ወቅት እንዳሉት፣ ምንም እንኳን ኩባንያው የጊዜ መጣበብና በአገር ውስጥ ገበያ የቁሳቁስ አቅርቦት እጥረት ቢያጋጥመውም ንኡስ ጣቢያዎቹን በወቅቱ ገንብቶ የጨረሰ ሲሆን፣ የባቡር ኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦቱን አስተማማኝ ለማድረግ በቻለው አቅም ሁሉ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ቻይና ኤሌክትሪክ ፓዎር ኢኩፒመንት ኤንድ ቴክኖሎጂ ኩባንያ በአዲስ አበባ ያስገነባቸው የቀላል ባቡር የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ ንኡስ ጣቢያዎች አምስት ሲሆኑ በቃሊቲ፣ አያት፣ ሚኒልክ፣ መስቀል አደባባይ፣ እግዚያብሄርአብ ቤተ ክርስቲያንና በጦር ሃይሎች አካባቢ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በሌላ በኩል ተሳፋሪዎች በጉዞ ወቅት እስከ 10 ኪሎ የሚመዝን እቃ ብቻ ይዘው ለመጓዝ እንደሚፈቀድላቸው የተገለፀ ሲሆን አንዳንድ በባቡሩ ላይ እንዳይጫኑ የሚከለከሉ እቃዎች እንደሚኖሩ ታውቋል፡፡
የባቡር ትራንስፖርቱ ክፍያ እስከ 4 ኪሎ ሜትር ሁለት ብር፣ እስከ 8.8 ኪሎ ሜትር 4 ብር እንዲሁም ከመነሻ እስከ መጨረሻ ፌርማታ 6 ብር ነው ተብሏል፡፡ ትኬት ሳይዙ መጓዝ ከፍተኛ ቅጣት እንዳለውም ተጠቁሟል፡፡

  መመሪያ ያልተሰጠበት የደብሩ የሚሊዮን ብሮች የበጀት ጥያቄ እንዲዘገይ አዟል
 •  የሀገረ ስብከቱን ሥራ አስኪያጅና ምክትላቸውን እያወዛገበ ነው


    የአራዳው መናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር፣ እያሠራው የሚገኘው የሁለገብ ሕንፃ ግንባታ፣ ተደርጎለታል ባለው የዲዛይን ማሻሻያ ሳቢያ በልዩነት የሚያስፈልገው ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪና ከባለሀብቶች ጋር በመተባበር ለማስገንባት ያቀዳቸው የሌሎች ሁለት ሕንፃዎች ግንባታና በጀት እንዲጸድቁለት ያቀረባቸው ጥያቄዎች፣ ለፓትርያርኩ ቀርበው መመሪያ ያልተሰጠባቸው በመሆናቸው “በአሉበት ሁኔታ እንዲቆዩ” የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት አዘዘ፡፡
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አስተዳደር ጉባኤ፣ በደብሩ ግንባታዎችና የበጀት ይጸደቅልኝ ጥያቄዎቹ ላይ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር መጨረሻ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ለአፈጻጸም ወደ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ሳይላኩለት የቆዩበት ምክንያት እንዲብራራለትም ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከትላንት በስቲያ ለሀገረ ስብከቱ በጻፈው ደብዳቤ ጠይቋል፡፡
የደብሩ ሰበካ ጉባኤ፣ የልማት ዕቅዶቹ በሀገረ ስብከቱ በኩል እንዲጸድቁለት ባለፈው ዓመት ሚያዝያ 16 ቀን 2007 ዓ.ም. መጠየቁን ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ባስታወሰበት ደብዳቤው፤ ዲዛይኑ ለተሻሻለው ሁለገብ ሕንፃ ማሠሪያ እንዲሁም በስተምሥራቅ የሚገኙት ሱቆች ፈርሰው በምትካቸው ባለሁለት ፎቅ ሕንፃ መሥራት ይቻል ዘንድ የብር 6 ሚሊዮን በጀት በደብሩ እንደተመደበ፣ በጥያቄው ላይ ለመወሰን ሰኔ 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ከተሰበሰበው የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ቃለ ጉባኤ መረዳቱን ጠቅሷል፡፡
በዕለቱ፣ በምክትል ሥራ አስኪያጁ መጋቤ ብሉይ አእመረ አሸብር በተመራው የአስተዳደር ጉባኤው ስብሰባ፣ በደብሩ የቀረበው የበጀት ይጸድቅልኝ ጥያቄ፣ “ከባድና ከሀገረ ስብከቱ አቅም በላይ” ሊሆን እንደቻለ ተጠቁሟል፡፡ ወጪው ከ61 ሚሊዮን ወደ 152 ሚሊዮን ያደገው የዲዛይን ክለሳ ጥናት፤ በገለልተኛ ባለሞያዎች ተገምግሞ፣ ውጤቱ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ እንዲላክና በዚያው በኩል እንዲጸድቅ፤ የሁለት ተጨማሪ ሕንፃዎች ግንባታ ውሎችም ለአስተዳደር ጉባኤው ቀርበው እንዲታዩና የውሳኔው ቃለ ጉባኤም በምክትል ሥራ አስኪያጁ ሸኚ ደብዳቤ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት እንዲላክ ከስምምነት ተደርሶበት እንደነበር ጠቅላይ ጽ/ቤቱ አውስቷል፡፡
ይኹንና ውሳኔዎቹም ኾኑ የውሳኔዎቹ ቃለ ጉባኤ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ እንዳልተላከ ጠቅሶ፣ ለሦስት ወራት ሳይላክ የዘገየበት ምክንያት ከተጨባጭ ማስረጃ ጋር እንዲብራራለት የሀገረ ስብከቱን ጽ/ቤት አዟል፤ የመናገሻ ገነተ ጽጌ ደብርን ጨምሮ የ48 አድባራትን የመሬትና የገቢ ማስገኛ ተቋማት አጠቃቀምና የኪራይ አፈጻጸም ያጣራው አጥኚ ኮሚቴም፣ ጉዳዩን ተከታትሎ እንዲያስፈጽም በደብዳቤው ግልባጭ መታዘዙን ጠቅላይ ጽ/ቤቱ አስታውቋል፡፡
በቤተ ክርስቲያኒቱ የቃለ ዐዋዲ ድንጋጌ አንቀጽ 12 ንኡስ አንቀጽ 8፣ ቋሚ ንብረትንና ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቁ ጉዳዮች በሥራ ላይ ሊውሉ የሚችሉት ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ፈቃድ ሲያገኙ ብቻ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ ከረዳት ሊቀ ጳጳሱ አልፎ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት እንደመኾኑ፣ በአጥቢያ ሰበካ ጉባኤያቱ ለሀገረ ስብከቱ የሚቀርቡ ጥያቄዎች በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ አማካይነት ለፓትርያርኩ እየቀረቡ አመራር ሲሰጥባቸው፣ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ በመመሪያው መሠረት ማስፈጸም ይኖርበታል፡፡
በዚሁ አግባብ፣ በሀገረ ስብከቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሰብሳቢነት የተላለፈው ውሳኔ፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ አማካይነት ለፓትርያርኩ ቀርቦ መመሪያ እስከሚሰጥበት ድረስ የደብሩ የግንባታና የበጀት ይፅደቁልኝ ጥያቄዎች በአሉበት ሁኔታ እንዲቆዩ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሀገረ ስብከቱን አዟል፡፡
ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ይህን ይበል እንጂ፤ ደብሩ በጥያቄው መሠረት ግንባታውን እንዲቀጥል የሚገልጽ ነው የተባለ ደብዳቤ፤ በሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ለደብሩ አስተዳደር አስቀድሞ መጻፉን የሀገረ ስብከቱ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ የደብሩም ዋና ጸሐፊ እንደኾኑ የጠቀሱት ምንጮቹ፣ በአንድ በኩል ጥያቄ አቅራቢ በሌላ በኩል ውሳኔ ሰጪና አፅዳቂ በመኾን የፈጸሙት ተግባር የተጠያቂነት መርሆዎችንና የአስተዳደር ጉባኤውን ውሳኔ ከመፃረሩም በላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከምክትል ሥራ አስኪያጁ ጋር እየተካረሩ ለመጡት አለመግባባቶችም አንድ መንሥኤ መኾኑን አስረድተዋል፡፡
የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር፣ በሕንፃዎች፣ በሱቆችና በባዶ መሬት አጠቃቀምና የኪራይ አፈጻጸም፣ የአሠራር ችግር እንዳለባቸው ከተዘረዘሩት 15 ገዳማትና አድባራት አንዱ እንደኾነ፣ በፓትርያርኩ ትእዛዝ የተሠየመው ኮሚቴ ባካሔደውና በጠቅላይ ጽ/ቤቱ አማካይነት ለቋሚ ሲኖዶስ በቀረበው ጥናታዊ ሪፖርት ተጠቅሷል፡፡
እንደ ሪፖርቱ፣ የደብሩ ሁለገብ ሕንፃ፣ የዲዛይን ማሻሻያ በሚል ወጪው ከ61 ወደ 171 ሚሊዮን ብር ያደገ ሲኾን አዲስ ተቆጣጣሪ መሐንዲስም በደብሩ ዋና ጸሐፊ ጠቋሚነት ያለጨረታ ተቀጥሯል፡፡ ሀገረ ስብከቱና ሊቀ ጳጳሱ ለአዲሱ የዲዛይን ጥናትና ከብር 110 ሚሊዮን በላይ ላሳየው የዋጋ ጭማሪ ዕውቅናና ፈቃድ ባልሰጡበት ሁኔታ ግንባታው መቀጠሉም አግባብነት እንደሌለው በሪፖርቱ ተገልጧል፡፡
ቋሚ ሲኖዶስ፣ ጥናታዊ ሪፖርቱን ሙሉ በሙሉ በመቀበል ውሳኔዎችን ማሳለፉን ጠቅላይ ጽ/ቤቱ በደብዳቤው ገልጾ÷ የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብርን ጨምሮ በተዘረዘሩት 15 ገዳማትና አድባራት ተፈጸመ በተባለው ኢ-ፍትሐዊ አሠራር፣ በተናጠልም ኾነ በጣምራ ተጠያቂ የሚኾኑ የአመራር አካላት ከተሰበሰቡት ማስረጃዎች ጋር በንጽጽር እንዲቀርቡለት፤ የሕንፃዎቹ፣ የሱቆቹና የባዶ መሬቶቹ የኪራይ አፈጻጸምና የመካናተ መቃብሩ አጠቃቀም የሚመሩበት መተዳደርያ ደንብ፣ የጨረታ ደንብ፣ የአከራይና ተከራይ የውል ሰነድ በማእከላዊነት በባለሞያዎች ተዘጋጅቶ እንዲቀርብ፤ ጥናቱ ባልሸፈናቸው ሌሎች ገዳማትና አድባራት ላይም እንዲቀጥል መታዘዙንም አስታውቋል፡፡

    ከ200 በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት 12ኛው አለማቀፍ የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ከትላንት በስቲያ ጀምሮ እየተካሄደ ነው፡፡ በኤግዚቢሽኑ ላይ ከ120 በላይ የሃገር ውስጥ ኩባንያዎች ተሣታፊዎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ከ17 የተለያዩ የአለም ሀገራት የተውጣጡ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሠማሩ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ ከውጪ ከተገኙት መካከል የጣሊያን፣ የቱርክ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስና የቻይና ኩባንያዎች ተጠቃሽ ሆነዋል፡፡ ለ12ኛ ጊዜ የሚካሄደው ኤግዚቢሽኑ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሠማሩ አምራቾችን፣ አሠሪዎችን፣ የሪልእስቴት ኩባንያዎችን፣ የግንባታ ማሽነሪ አስመጪዎችን፣ የፋይናንስ ተቋማትንና በዘርፉ ተዋናይ የሆኑ አካላትን በአንድ ቦታ የሚያገናኝ ይሆናል ተብሏል፡፡ ኤግዚቢሽኑ የፊታችን ሠኞ ይጠናቀቃል፡፡

     ከተለያዩ የአለም ክፍሎች የተውጣጡ በአቬሽን ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችን የሚያሳትፍ “አይማ አፍሪካ” የተሰኘ ዓለም አቀፍ ጉባኤ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ፣ ከፊታችን ማክሰኞ ጀምሮ ለ3 ቀናት ይካሄዳል፡፡ ጉባኤው በተለይም በአገሪቷ ያለውን የኤርፖርት የመሰረተ ልማት እድገት ለማስተዋወቅ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ጠቁሟል፡፡ የድርጅቱ የኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ወንድም ተክሉ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ ድርጅቱ ከሌሎች የኤርፖርት አገልግሎት ሰጪና መሰረተ ልማት አቅራቢ ድርጅቶች ጋር የንግድና የወዳጅነት ትስስር ለመፍጠር ጉባኤው መልካም አጋጣሚ ይሆንለታል፡፡ በጉባኤው ላይም ድርጅታቸው፣ “የአሁኑ እና የወደፊቱ የኤርፖርት መሰረተ ልማት” በሚል ርዕሰ ገለፃ እንደሚያቀርብ ኃላፊው አክለው ገልፀዋል፡፡
የአይማ (AIMA – Airport infrastructure maintenance repair & over hall (Mro) aviation) ጉባኤ በአለም ለ20ኛ ጊዜ፣ በአፍሪካ ደግሞ ለ3ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ ከ200 በላይ ተሳታፊዎች ይገኙበታል ተብሏል፡፡  

   አብርሃም ግዛው ኢንተርቴይመንትና ፕሬስ ስራዎች ድርጅት ከኢትዮጵያ ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር ልዩ የመስቀል በዓል ፕሮግራም ያካሂዳል፡፡ በኢቴቪ 3 ከቀኑ 11፡30 እስከ ምሽት 1፡30 ሰዓት ድረስ በሚተላለፈው በዚሁ ፕሮግራም ላይ የእርድ፣ የደመራ ማብራት፣ እና የአገር ሽማግሌዎች የምርቃት ስነስርዓት የሚካሄድ ሲሆን ባህላዊና ዘመናዊ ሙዚቃዎች፣ የኮሜዲ ዝግጅትና የመስቀል በዓል አከባበር ታሪካዊ ዳራ እንደሚቀርቡም ጋዜጠኛና ፕሮሞተር አብርሃም ግዛው ተናግሯል፡፡
በእለቱ ታዋቂ ሰዎች የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይታደማሉ ተብሏል፡፡ አብርሃም ግዛው ኢንተርቴይመንትና ፕሬስ ስራዎች ድርጅት “የጥበብ ብልጭታ” የተሰኘና በብስራት ኤፍኤም የሚተላለፍ የኪነ ጥበብ ፕሮግራም አዘጋጅ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን የመስቀል በዓልን ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ማዘጋጀቱም ታውቋል፡፡