Administrator

Administrator

  የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሙስና ቅሌት እየታመሰ የሚገኘውን አለማቀፉን የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፊፋ ለረጅም አመታት በፕሬዚዳንት የመሩት ሴፕ ብላተር፣ የዓለም የኖቤል ሽልማት ሊሰጣቸው የሚገባ ታላቅ ሰው ናቸው ሲሉ መናገራቸውን ዘሂንዱ ታይምስ ዘገበ፡፡
ፕሬዚዳንት ፑቲን ባለፈው ሰኞ ከስዊዝ ቲቪ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ሃሜት የበዛባቸው የፊፋው ፕሬዚዳንት ሴፕ ብላተር ለአለማችን እግር ኳስ ባበረከቱት አስተዋጽኦ የኖቤል ሽልማት ሊሰጣቸው የሚገባ ታላቅ ሰው ናቸው ብለዋል፡፡  እንደ ብላተር ያሉ ትጉሃን ሰዎች፣ የተሰጣቸውን ሃላፊነት በአግባቡ በመወጣት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ልዩ እውቅና ሊሰጣቸው ይገባል ሲሉም አክለዋል ፕሬዚዳንት ፑቲን፡፡ ብላተር በበኩላቸው፤ የፑቲን ንግግር እንዳስደሰታቸውና ስሜታቸውን እንዳነቃቃው ገልጸው፣ ለፑቲን ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ፑቲንና ብላተር የ2018 የአለም የእግር ኳስ ዋንጫን አዘጋጅ አገር ለመምረጥ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በሩስያ ሴንት ፒተርስበርግ በሚገኘው ኮንስታንቲን ቤተ-መንግስት በተደረገው የመጀመሪያ ዙር እጣ አወጣጥ ስነ-ስርአት ላይ ተገናኝተው እርስ በርስ መወዳደሳቸውን ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

 - ከፌስቡክ ደንበኞች 65 በመቶው በየዕለቱ ይጠቀማሉ
            - ባለፉት ሶስት ወራት ገቢው 4 ቢሊዮን ደርሷል
   ኢንተርኔትን ከሚጠቀሙ 3 ቢሊዮን ያህል የተለያዩ የአለማችን አገራት ዜጎች መካከል ግማሽ ያህሉ ወይም 1.49 ቢሊዮን የሚሆኑት የታዋቂው ማህበራዊ ድረገጽ ፌስቡክ ተጠቃሚ መሆናቸውን ኩባንያው ረቡዕ እለት ማስታወቁን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
የተጠቃሚዎቼ ቁጥር ባለፉት ሶስት ወራት በ13 በመቶ አድጓል ያለው ፌስቡክ፣ ከተጠቃሚዎቹ ውስጥ 65 በመቶ የሚሆኑትም በየዕለቱ አካውንታቸውን ከፍተው የሚጠቀሙ ትጉህ ደንበኞቹ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
የስማርት ፎን ተጠቃሚዎች በየአምስት ደቂቃው ለአንድ ደቂቃ ያህል ጊዚያቸውን ከፌስቡክ ጋር ያጠፋሉ ያለው ፌስቡክ፣ የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት መስፋፋት ለማህበራዊ ድረገጹ ተጠቃሚዎች ቁጥር ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ አስታውቋል፡፡
በስማርት ፎን ተጠቃሚዎች በኩል የሚያገኘው የማስታወቂያ ሽያጭ ገቢ ጠቀም ያለ እንደሆነ የገለጸው ፌስቡክ፣ ገቢው ባለፉት ሶስት ወራት በ39 በመቶ በማደግ 4 ቢሊዮን ዶላር መድረሱንና ከዚህ ውስጥም 2.9 ቢሊዮን የሚሆነውን ከስማርት ፎን ማስታወቂያ እንዳገኘው ጠቁሟል፡፡

Saturday, 01 August 2015 14:48

የየአገሩ ምሳሌያዊ አባባል

የሴት ውበት የክረምት ሌሊትን አያሞቅም።
የዩክሬናውያን አባባል
ውሻ ጭራውን ካልረገጥከው በስተቀር አይነክስህም፡፡
የካሜሩያውያን አባባል
ጓንት ያጠለቀች ድመት አይጥ አትይዝም፡፡
የፈረንሳውያን አባባል
የተውሶ ድመት አይጥ አትይዝም፡፡
የጃፓናውያን አባባል
ትኩረት የሚስቡ ሴቶች ከኋላህ እንዲጓዙ አትፍቀድ፡፡
የካምቦዲያውያን አባባል
ከነገ ጫጩት የዛሬ እንቁላል ይሻላል፡፡
የቬትናማውያን አባባል
ዘማሪ ወፍ መዝሙር እየበላች አትኖርም፡፡
የሩሲያውያን አባባል
አሪፍ ውሻ ተሳስቶ አይጮህም፡፡
የፈረንሳውያን አባባል
ማለፊያ የወይን ጠጅ የያዘ ፋሽኮ ቡሽ አይፈልግም፡፡
የፈረንሳውያን አባባል
ቀበሮ በተመሳሳይ ወጥመድ ሁለቴ አይያዝም፡፡
የላቲን አባባል
 ሞኝ በራሱ ይስቃል፡፡
የናሚቢያውያን አባባል
እግዚአብሔር በሳቅ እንዲፈርስ ከፈለግህ ዕቅድህን ንገረው፡፡
የናሚቢያውያን አባባል
ህፃን፤ እግሮቹ በጨመሩ ቁጥር ክንፎቹ የሚቀንሱ መላዕክ ነው፡፡
የፈረንሳውያን አባባል
አፍህ ቢላዋ ከሆነ ከንፈርህን ይቆርጠዋል፡፡
የአፍሪካውያን አባባል
እግዚአብሔር አንድን አገር መቅጣት ሲፈልግ፣ መሪዎቹን ጥበብ ይነፍጋቸዋል፡፡
የጣልያኖች አባባል

 አሜሪካ በመላው አለም የሚገኙ ዜጎቿ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ አይሲስን የመሳሰሉ አሸባሪ ቡድኖች ከሚሰነዝሯቸው የሽብር ጥቃቶች ራሳቸውን እንዲጠብቁ ማስጠንቀቋን ዘ ሂንዱ ታይምስ ዘገበ፡፡
አሜሪካ በኢራቅ በሚገኘው አይሲስ ላይ ጥቃት መሰንዘሯን ተከትሎ፣ ቡድኑ የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጥ ማሳወቁን ያስታወሰው ዘገባው፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ቡድኑ በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮፓና በእስያ አገራት በሚኖሩ አሜሪካውያንም ሆነ በምዕራባውያን አገራት ዜጎች ላይ የሽብር ጥቃት ሊሰነዝር ስለሚችል ተገቢው ጥንቃቄ እንዲደረግ ማሳሰቡን ጠቁሟል፡፡
ከአይሲስ በተጨማሪ በህንድ የሚንቀሳቀሱት ሌቲን የመሳሰሉ የሽብር ቡድኖች ከሰሞኑ በአገሪቱ ጥቃት ሊሰነዝሩ ይችላሉ ያለው የአሜሪካ መንግስት ማስጠንቀቂያ፣ በህንድ የሚኖሩ አሜሪካውያንም ራሳቸውን ከጥቃት እንዲጠብቁ አሳስቧል፡፡
በምዕራባውያን አገራት ላይ የከፋ ጥላቻ ያላቸው ሃረካት ኡል ጂሃዲ ኢስላሚ እና ሃረካት ኡል ሙጅሃዲንን የመሳሰሉ እስላማዊ አክራሪ ቡድኖች በህንድ በስፋት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ጠቁሞም፣ቡድኖቹ ከዚህ ቀደምም በምዕራባውያን አገራት ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ የሽብር ጥቃቶችን ሲፈጽሙና በርካቶችን ለህልፈተ ህይወት ሲዳርጉ እንደነበር አስታውሷል፡፡
አሸባሪ ቡድኖች በደቡብ እስያ አገራት የሽብር ጥቃት ሊፈጽሙ እንደሚችሉ የሚያመለክቱ መረጃዎች ደርሰውኛል ያለው የአሜሪካ መንግስት፣ ጥቃቶቹ በአሜሪካውያንና በተቋማቷ ላይ ያነጣጠሩ ሊሆኑ እንደሚችሉም ጠቁሟል፡፡

Saturday, 01 August 2015 14:47

የኪነጥበብ ጥግ

ስለ ኪነ - ህንፃ)
እኛ ህንፃዎቻችንን እንቀርፃለን፤ ከዚያም እነሱ እኛን ይቀርፁናል፡፡
ዊንስተን ቸርችል
ማናቸውም የገነባቸውና ጥሩ ነገሮች የማታ ማታ እኛን ይገነቡናል፡፡
ጂም ሮህን
ከተሞች የሰው ልጅ ድንቅ ፈጠራዎች ናቸው፡፡
ዳንኤል ሊቤስኪንድ
በአሜሪካ የቪክቶሪያን ኪነ - ህንፃ በቀጥታ የተቀዳው ከእንግሊዝ ነበር፡፡
ስቲፈን ጋርዲነር
ሎስ አንጀለስ ውስጥ 35 ዓመት ሲሞላችሁ፣ አብዛኞቹን ህንፃዎች በዕድሜ ትበልጧቸዋላችሁ፡
ዴልያ ኢፍሮን
ስለ ሙዚቃ ማውራት ስለ ኪነ-ህንፃ እንደ መደነስ ነው፡፡
ሉዊስ ካህን
ኪነ-ህንፃ ግግር ሙዚቃ ከሆነ፣ ሙዚቃ ፈሳሽ ኪነህንፃ መሆን አለበት፡፡
ኪውንሲ ጆንስ
ኪነ-ህንፃ ዘላለማዊነት ላይ ያለመ ነው፡፡
ክሪስቶፈር ሬን
ሙዚቃን እንደ ፈሳሽ ኪነ ህንፃ እቆጥረዋለሁ።
ጆኒ ሚሼል
ኪነ ህንፃ ጥበብ እንጂ ሌላ ምንም አይደለም።
ፊሊፕ ጆንሰን
ጥሩ ነገር መስራት ቀላል አይደለም፤ ነገር ግን መጥፎ ነገር መስራት እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡
ቻርለስ ኧርነስ
ምንጊዜም ክብ ስሰራ፣ ወዲያውኑ ከዚያ ውስጥ መውጣት እፈልጋለሁ፡፡
አር. ቡክሚኒስተር ፉለር
ቤት የመኖሪያ ማሽን ነው፡፡
ሊ ኮርቡስየር
ልክ እንደ መድሃኒት (ኪነህንፃ) ከማዳን ወደ መከላከል መሻገር አለበት፡፡
ሴድሪክ ፕራይስ
እያንዳንዱ ህንፃ ልክ እንደ ሰው ነው፡፡ ብቸኛና የማይደገም፡፡
አየን ራንድ (ዘ ፋውንቴይንሄድ)

Saturday, 01 August 2015 14:44

የንባብ - አደባባይ!

    ቴክኖሎጂ ሲቀብጥ ትውልድም መልኩን ለቅቆ፣ ጨርቁን ጥሎ እንዳያብድ፣ በትይዩ ቦይ እንዳንለቀው፣ የሚተልምልን መሪ፤ መረን እንዳይወጣ የሚገታ የፍቅር ልጓም ያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ ዕውቀትን በቅጡና በወጉ ለመጠቀም፣ በሥርዐት ለህይወት ጉልበት መስጫ ለማድረግ መማር አንዱ መንገድ ቢሆንም ቅርፅ ለመስጠት፣ ውበት ለማምጣት ደግሞ ንባብ ሻካራችንን እያለሰለሰ፣ ለማህበረሰቡ ምቹ እንደሚያደርገን ይታመናል፡፡  
ከሀገር ውጭም ሆነ በሀገራችን ውስጥ አያሌዎች እሳት የላሱ ጠቢባን ይሆኑ ዘንድ አእምሮዋቸውን ገርቶ፣ ላባቸውን አቅንቶ፣ዘመን የማያቆመው ድምቀት የሰጣቸው ንባብ እንደሆነ ደጋግመን ያወሳነው ጉዳይ ነው፡፡
በእኛም ሀገር የንባብ ባህል እንዲያድግና እንዲጎለብት የተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማት ታላቅ ተጋድሎ አድርገዋል፡፡ ለዚህም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የሀዋሳና የዲላ ዩኒቨርሲቲ በየራሳቸው ያደረጉትን ጥረት ልንዘነጋው የምንችል አይመስለኝም፡፡ ይበልጥ የሚመለከተው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበርም ከነዚሁ ጎራ የሚመደብ ነው፡፡ በግለሰብ ደረጃ ደግሞ ደራሲ ዳንኤል ወርቁ “አዲስ አበባ ታንብብ”ን በመሳሰሉ ፕሮግራሞቹ የተቻለውን ያህል ተግቷል፡፡  በጥቅሉ ሲታይ በሀገራችን የንባብ ባህልን ለማበረታታት የሚደረገው ጥረት በእጅጉ እየበረታና እየደመቀ የመጣ ይመስላል፡፡ ሌላው ቀርቶ በቅርቡ ብቻ የተካሄዱትን የመጻህፍት አውደ ርዕዮች ስናይ ጉዳዩ ምን ያህል የልብ ትርታ እየሆነ መምጣቱን የሚያሳይ ነው፡፡
በተለይ ለዛሬ ጽሁፌ መነሻ የሆነኝ፣በማስተር ፊልምና ኮሙኒኬሽን አዘጋጅነት ከትላንት በስቲያ የተጀመረውና እስከ ነገ (»ሐምሌ 23-26 2007 ዓ.ም) የሚቆየው “ንባብ ለህይወት” የመፃህፍት አውደ-ርዕይ፤በዓይነቱና በይዘቱ ግዙፍና ታላቅ ነው፡፡ ምናልባትም ከዚህ ቀደም ከለመድናቸው የሚለዩ በርካታ አላባዎችን አጭቆ የያዘ ዝግጅት ነው፡፡ ከነዚህም ውስጥ አንዱና ዋነኛ ጠባዩ፣  አውደ ርዕዩ በየዓመቱ በቀጣይነት የሚካሄድ መሆኑ ነው። ከዚህም ሌላ በየክልሉ እንዲላመድ በማድረግ ሀዲዱን ቆንጥጦ ይቀጥላል፡፡
ብዙ ጊዜ ስለ ንባብ ስናወራ፣ ስለ ንባብ ስንሰብክ፣ በእዝነ ህሊናችን የሚመጡት ፊታቸው በጢም የተሞላ፣ ምናልባት ሽበት ጣል ጣል ያደረገባቸው አዛውንትና ጎልማሶች ናቸው፡፡ ንባብ ለህይወት ዓይኖቹን ወደ ችግኞቹም ላይ ጥሏል። ሕፃናት ከሥር ጀምረው እንዲኮተኮቱ፣ እኩይ መልኮችን እንዲዘልሉ ከአሁኑኑ ክትባት ያገኙ ዘንድ ለእነርሱም በቂ ዝግጅት አድርጓል፡፡ የሚመጥኗቸው መፃህፍት፣ የሚያጫውቷቸው አሻንጉሊቶችም ተዘጋጅተዋል፡፡
በዚህ አውደ ርዕይ፣120 ያህል የመፃህፍት አሳታሚዎችና የትምህርት ተቋማት በአንድ ዓላማና ድንኳን ስር ይተሳሰራሉ፡፡ እውነት ለመናገር የትምህርት ተቋማት ተሰባስበው በአንድ ሰፈር መች ተገኝተው ያውቃሉ! … ይኸው አሁን በንባብ ለህይወት ችቦዋቸውን እየለኮሱ ደመራውን ሊያደምቁት ታድመዋል፡፡
በንባብ ለህይወት፣ መጻሕፍት ቢያንስ በ10 በመቶ የዋጋ ቅናሽ ለገበያ የሚቀርቡ ሲሆን ቅናሹ  እስከ 50 በመቶ ሊዘልቅ እንደሚችል አዘጋጆቹ ይገልጻሉ፡፡ ስለዚህ መጻሕፍት ለመሸመትም ጥሩ አጋጣሚ ይሆናል ማለት ነው፡፡ የዘመኑ ቴክኖሎጂ በፈጠረው ዕድል ጎብኚዎች ከ100,000 ሺህ በላይ በመረጡት ርዕሰ ጉዳይ ላይ የተፃፉ መፃህፍትን ሶፍት ኮፒ በነፃ ያገኛሉ ተብሏል፡፡  
በዚህ ዐውደ-ርዕይ ባልተለመደ መልኩ አዳዲስ መጻህፍት ቬሎዋቸውን ለብሰው ብቅ እንደሚሉም ታውቋል፡፡ ከአዘጋጆቹ በተገኘው መረጃ መሰረት፤12 አዳዲስ መፃህፍት እዚያው ተመርቀው፣የደራስያኑ ፊርማ አርፎባቸው፣በትኩሱ ወደ ተደራሲያን እጅ ይገባሉ፡፡
ሌሎቹ ሁለት ታላላቅ የበዓሉ ድምቀቶችም እንደዚሁ ያልተለመዱ ናቸው፡፡ ከነዚህ አንዱ በየሙያ ዘርፉ “አንቱ” የተባሉና በአንባቢነታቸው የተመሰከረላቸው ሰዎች  የንባብ አምባሳደር ተብለው ዕውቅና የሚያገኙበት ሲሆን በቀጣዩ ጊዜ በየትምህርት ቤቱና በሌሎች ክበባት በመገኘት አንብበው የሚያስነብቡበት የኃላፊነት ሹመት ነው። ይህ ደግሞ ዓመቱን ሙሉ ለሚካሄደው የንባብ ልምድ ማበልፀጊያ ጉዞ ትልቁን ድርሻ ሊጫወት እንደሚችል እሙን ነው፡፡  ታዲያ ይህ ሁሉ ዘመቻ፣ ዕውቀትን ጓዳችን ለማስገባት፣ እንደ ሰው አውቀን፣ እንደ ሰው አስበንና የተሻለውን መርጠን እንድንኖር ነው። ማወቅን ካለማወቅ የሚለየው አንዱ፣ ህይወትን የምናጣጥምበትን ምላስ መንጠቁ ሲሆን ሌላኛው ህይወትን የምናጣጥምበትን አቅም መስጠቱ ነወ፡፡ ይህንንም እንድናውቅ የሚያደርገን በልብ አይኖቻችን ላይ የተጋረደው መጋረጃ መነሳቱ ነው፡፡ ይህ አውደርይ የማንበብ ጥቅምንና ወደዚህ የጥቅም እልፍኝ የምንገባበትን መንገድ ለመጥረግ ያዘጋጀው ሌላም ነገር አለ፡፡ በአንድ ወገን የተወዳጅ ደራስያንን ወግ እያነበቡ በማዝናናት፣ በሌላ ወገን ደግሞ የንባብን ጥቅምና ፋይዳ ወደ ኋላ እየፈተሹ፣ ታሪክ በማጣቀስ መወያየትም አለ፡፡
 ሙዚቃ የነፍስ ጥበብ ናት! … በጥበብ እልፍኝ ውስጥ ሽር ብትን እያለች የዓውደ ርዕዩን እልፍኝ ታድምቀው በሚል ጥንታዊውን የሙዚቃ ዓለም በቀደመው ዘመን ከያንያን ዜማ - ታንቆረቁረዋለች ይላሉ - የንባብ ለህይወት አዘጋጆች፡፡ ታዲያ ይህ ቀን አይናፍቅም? … ንባቡስ አይርብም? … የነፍሳችን ከንፈር እስኪላጥ እያፏጨን ብንጠራውስ? … እልልል!  

በአክመል ሺፋ የተፃፉ ግጥሞች የተሰባሰቡበት “ዝምታሽ አስፈራኝ” የተሰኘ የግጥም መድበል እየተሸጠ ነው፡፡
መምህር አይቸህ ሰይድ በመጽሐፉ ጀርባ ላይ ባሳፈረው አስተያየት፤ “አክመል የሰራቸው የግጥም ሥራዎች አብዛኞቹ አጫጭር ቢሆኑም መልዕክታቸው ሰፋ ያለና ጥልቅ ስሜትን የሚገዙ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ” ብሏል፡፡ በ110 ገፆች የተመጠነው መድበሉ፤ ዋጋው 35 ብር እንደሆነ ታውቋል፡፡

 በዳንኤል ንጉሴና ዮሐንስ ሙሉጌታ ተፅፎ፣ በመልካሙ ማሞ ዳይሬክት የተደረገው “የነገርኩሽ ዕለት” ፊልም በነገው ዕለት ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ በሀገር ፍቅር ትያትር ቤት ይመረቃል፡፡
የፊልሙ ታሪክ፤ አባት ለልጁ የሚከፍለው መስዋዕትነት የሚታይበትና ጊዜያዊ ችግርን ለማለፍ ተብሎ የተዘየደው መላ ኋላ እውነቱ ሲታወቅ የሚያስከትለውን የህይወት ውጣ ውረድ የሚያስቃኝ ነው ተብሏል፡፡
በፊልሙ ላይ፤ ደሳለኝ ኃይሉ፣ አሸናፊ ማህሌት (ይበቃል)፣ ችሮታው ከልካይ፣ ዋሲሁን በላይና ሌሎችም ተውነውበታል፡፡ የ1፡38 ደቂቃ ርዝመት ያለውን ፊልም ሰርቶ ለማጠናቀቅ 1 ዓመት እንደፈጀ ፕሮዱዩሰሩ ደስይበልህ መልቲ ሚዲያ ፕሮዳክሽን ገልጿል፡፡

 በሩሲያ ህፃናት ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፉት “ዶ/ር አይቦሊት” እና “ቫክሳ ክሊያክሳ” የተሰኙ የህፃናት መፃህፍት ወደ አማርኛ ተተርጉመው በትላንትናው ዕለት ምሽት በሩሲያ የሳይንስና ባህል ማዕከል የተመረቁ ሲሆን በኢትዮጵያ ለሚገኙ ህፃናት እንዲደርሱ በየት/ቤቱ በስጦታ እንደሚበረከቱ ታውቋል፡፡
መፃህፍቱን ወደ አማርኛ የተረጎሙት በሞስኮ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መምህር የሆኑትና በርካታ የሩሲያ ሥነ-ፅሁፎችን ወደ አማርኛ በመመለስ የሚታወቁት ፕሮፌሰር ንጉሴ ካሣዬ ወልደሚካኤል ናቸው ተብሏል። ሁለቱ መፃህፍት ወደ አማርኛ ተተርጉመው ለኢትዮጵያ ህፃናት እንዲዳረስ “ሩስኪ ሚር” የተባለ የሩሲያ ተቋም ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል፡፡  

  የዊሊያም ብሉም “Killing Hope” የተሰኘ መጽሐፍ በተርጓሚ ዳሩሰላም “የመንግስታት ዕንባ” በሚል ወደ አማርኛ ተመልሶ ሰሞኑን ለንባብ በቃ፡፡
መጽሐፉ፤በዓለም ላይ በሚገኙ ህጋዊ መንግስታት ላይ ስለደረሰው ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት፣ መፈንቅለ መንግስት፣ የሥነ ልቦና እና የስውር ጦርነቶች በደል የሚናገር ሲሆን አገራቱ በተገደለው የወደፊት ተስፋቸው ምክንያት መሪር እንባቸውን ሲረጩ ያሳያል፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ ከ50 በላይ የሚሆኑ በሲአይኤ እና በወታደራዊ ጣልቃ-ገብነት የተደረጉ መፈንቅለ መንግስቶች፣ የፖለቲካ ሁከቶች፣ወረራዎች፣ ብጥብጦች እና ሌሎችም ቀርበውበታል ተብሏል፡፡
በ287 ገፆች የተቀነበበው መጽሐፉ፤በ55.80 ለገበያ ቀርቧል፡፡