Administrator

Administrator

 “የአባባ ተስፋዬ ተረቶች የስዕል አውደ ርዕይ” ባለፈው ማክሰኞ በብሔራዊ ቴአትር አርት ጋለሪ ተከፍቶ ለ4 ቀናት ክፍት ሆኖ የቆየ ሲሆን በዛሬው ዕለት ይጠናቀቃል፡፡ አውደ ርዕዩን መርቀው የከፈቱት አባባ ተስፋዬ፤በኔክስት ጄነሬሽን የበጎ አድራጎት ማህበር ህፃናትና ወጣቶች የተዘጋጀላቸው በሙካሽ የተጌጠ ካባ ተበርክቶላቸዋል፡፡ “በዓለም ላይ ብዙ አገራትን አይቻለሁ፤ሰርቶ ለመኖር እንደ ኢትዮጵያ የተመቸ አገር አላየሁም” ያሉት አባባ ተስፋዬ፤“አገራችሁንም ሥራንም ውደዱ፤እኔ አርቲስት ሆኜ እየሰራሁ  ሻሸመኔ ላይ በግብርና ሥራም ተሰማርቼ ነበር፡፡ ከግብርናው ባገኘሁት ትርፍም የራሴን ቤት ሰርቻለሁ፤መኪናም ገዝቻለሁ” በማለት የሥራን ጥቅም አስረድተዋል፡፡
በመክፈቻው ላይ ንግግር ያደረገው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩሉ፤“እኛ ዛሬ ላይ የደረስነው በቀደመው ትውልድ ታግዘንና ተረድተን ነው፡፡ ይህንን ውለታ ታሳቢ በማድረግ አባባ ተስፋዬን የሚዘክር መድረክ መሰናዳቱ መስፋፋትና መቀጠል አለበት” ብሏል፡፡
በአባባ ተስፋዬ ሳህሉ መኖሪያ ቤት ይዞታ ላይ ሊሰራ የታቀደው ቴአትር ቤትና የባህል ማዕከል ጋለሪ ህንጻ ዲዛይን በዕለቱ ቀርቦም ገለፃ ተሰጥቶበታል፡፡

 በብሩክ ከድር የተዘጋጀው “የአረቦች ፀደይ” የተሰኘ መፅሃፍ በትላንትናው ዕለት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋካልቲ፣ የፕሮፌሰር እሸቱ ጮሌ መታሰቢያ አዳራሽ ተመርቋል፡፡
መፅሀፉ እ.ኤ.አ ከ2010 ጀምሮ በመካከለኛው ምስራቅ የተከሰተውና እስካሁንም ሙሉ በሙሉ ያልተጠናቀቀው ንቅናቄ ያስከተለውን ዘርፈ ብዙ ምስቅልቅልና ሁለንተናዊ ገፅታውን ይዳስሳል፡፡
በ253 ገፆች በተቀነበበው “የአረቦች ፀደይ” መፅሃፍ ላይ አጭር ውይይት እንደተካሄደም ታውቋል፡፡

በጀምስ ሬድፊልድ “The Celestine Prophecy” በሚል ርዕስ ተፅፎ በደራሲና ተርጓሚ አፈወርቅ በቀለ “የመጨረሻው መጀመሪያ” ተብሎ የተተረጐመው መጽሐፍ የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ በ11 ሰዓት በዋቢሸበሌ ሆቴል አዳራሽ ይመረቃል፡፡ መጽሐፉ ለደራሲው አምስተኛ የትርጉም ሥራው ሲሆን በምረቃው ሥነስርዓት ላይ የሥነጽሑፍ ባለሙያዎችና ጥበብ አፍቃሪያን እንደሚታደሙ ታውቋል፡፡

    በዓመቱ እስካሁን ያሳለፍነው መልካም ነበር፡፡ በስራ ነው ያሳለፍነው፡፡ ከአመት ወደ አመት የስራ አፈፃፀማችን እየተሻሻለ ነው፡፡ ሠራተኞቻችን ጤናቸው ተጠብቆ እንዲሰሩ፣ እንዲማሩ ማድረጋችን፣ ተማሪዎችን ማስመረቃችን እንደቀጠለ ነው፡፡ በሌላ በኩል በየቦታው የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን የመፍታት ብቃታችን ከእለት ወደ እለት እየተሻሻለ ነው፡፡ ችግሮችን በጋራ በመፍታት ረገድ ጥሩ ክንውን ነበረን፡፡
በቀጣይ አመት ደግሞ የጀመርናቸው የ8 ሚሊዮን ብር የማስፋፊያ ስራዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውሉ ምርቶች ላይ ትኩረት ለማድረግ እንፈልጋለን፡፡ ወደ ውጭ መላክ ብቻ አይደለም ትልቅ የሚያደርገን ብለን ስለምናምን፣ ሀገር ውስጥ ያለውን ተጠቃሚ ፍላጐት ማሟላት መቻል አለብን፡፡ የሀገር ውስጥ ተጠቃሚው እያደገ ነው፡፡ ይሄን ፍላጐት ለማሟላት በአዲሱ አመት ጠንክረን እንሠራለን፡፡

  የስልጣን ዘመናቸውን 100ኛ ቀን ባለፈው ሳምንት ያከበሩት አዲሱ የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ሙሃመድ ቡሃሪ፤ በባንክ ሂሳብ ደብተራቸው ውስጥ ያለው ገንዘብ 100 ሺህ ፓውንድ ብቻ መሆኑን በይፋ መግለጻቸውን ቴሌግራፍ ዘገበ፡፡
ፕሬዚዳንት ቡሃሪ ከዚህ ገንዘብ ውጭ ያላቸው ንብረት በጭቃ የተሰሩትን ሁለት ቤቶቻቸውን ጨምሮ አምስት የመኖሪያ ቤቶችና 270 ከብቶች ያሉበት የእርሻ ቦታ ብቻ መሆኑን እንደገለጹ የጠቆመው ዘገባው፤ሰውዬው ያላቸው ሃብት ከተራው የናይጀሪያ ህዝብ እጅግ የበዛ ቢሆንም፣ በመካከለኛና በከፍተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙ ዜጎች ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ገልጧል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ የግል ሃብታቸውን ይፋ ማድረጋቸው ከዚህ ቀደም አገሪቱን ሲመሩ ከነበሩና የህዝቡን ሃብት ወደ ካዘናቸው በማስገባት ከሚታሙ እጅግ ባለጸጋ ፕሬዚዳንቶች የተለዩ መሆናቸውን ለማሳወቅ ነው ተብሏል፡፡ ምክትል ፕሬዚዳንቱ በበኩላቸው፤ከቡሃሪ ሃብት 9 እጥፍ የሚበልጥ የ900 ሺህ ፓውንድ ባለቤት መሆናቸውን ዘገባው ጠቁሟል፡፡ ቡሃሪ ስልጣን በያዙ ማግስት ከመንግስት ካዘና 100 ቢሊዮን ዶላር መንትፈው የግል ሃብታቸው አድርገዋል በሚል የሚታሙትን ሙሰኛ የአገሪቱ ባለስልጣናት ለፍርድ ለማቅረብ እንደሚሰሩ ቃል መግባታቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
በ1980ዎቹ የአገሪቱ ወታደራዊ መሪ የነበሩት ቡሃሪ፤በስልጣን ዘመናቸው ከሙስና የጸዱ መልካም ሰው እንደነበሩ የጠቆመው ዘገባው፣ናይጀሪያን ለአምስት አመታት ያህል አንቀጥቅጠው የገዙት አምባገነኑ የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳኒ አባቻ በአንጻሩ 3 ቢሊዬን ፓውንድ ሃብት እንደነበራቸውና አብዛኛውን ገንዘባቸውን በስዊዝ ባንክ እንዳስቀመጡት አስታውሷል፡፡

     ፖሊስ በአይፎን ተጠቃሚ የወንጀል ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ ጀምሯል
             ማይክሮሶፍትም የወንጀል ተጠርጣሪን ኢሜል ባለመስጠቱ ተከሷል
   የአሜሪካ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ከአደንዛዥ ዕጽ እና ከጦር መሳሪያ ጋር በተያያዘ ለምናደርገው ምርመራ የሚጠቅሙ የጽሁፍ መልዕክቶችን አሳልፎ ሊሰጠን አልፈቀደም ያሉት ታዋቂው የቴክኖሎጂ ኩባንያ አፕል፤ፍርድ ቤት ቀርቦ ቅጣት የሚጣልበትን ሁኔታ እንዲያመቻችላቸው መንግስትን መጠየቃቸውን ኒውዮርክ ታይምስ ዘገበ፡፡
የኤፍቢአይ እና የአሜሪካ የፍትህ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣናት፤ አፕል በሚያመርተው አይፎን አማካይነት ከሰዎች ወደ ሰዎች የተዘዋወሩ አጭር የጽሁፍ መልክቶችን ለወንጀል ምርመራ አሳልፎ አልሰጥም ብሎ በእምቢተኝነት በመጽናቱ ህጋዊ እርምጃ ይወሰድበት ሲሉ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጥያቄ ማቅረባቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡
የአሜሪካ የፍትህ ሚኒስቴር ወንጀል መርማሪዎች የአፕል ምርት የሆነውን አይፎን በሚጠቀሙ የአደንዛዥ ዕጽ እና የጦር መሳሪያ ወንጀል ድርጊቶች ተጠርጣሪዎች ዙሪያ ለሚያደርጉት ምርመራ የአጭር የጽሁፍ መልዕክቶቹ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው መናገራቸውም ተጠቁሟል፡፡
አፕል ከዚህ ቀደም ከፖሊስ ለቀረበለት ጥያቄ፣ የአጭር የጽሁፍ መልዕክቶቹ የተላለፉበት አይሜሴጅ የተሰኘ የመልዕክት መላላኪያ ሲስተሙ ነባር መረጃዎችን የሚያጠራቅምበት ቋት የሌለው በመሆኑ የተጠየቀውን መረጃ ስለማያገኝ አሳልፎ መስጠት እንደማይችል ማስታወቁን ዘገባው አስታውሷል፡፡
የአሜሪካ መንግስት ከአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር ጋር በተያያዘ በተጠረጠረ አንድ ግለሰብ ዙሪያ ለሚደረግ የወንጀል ምርመራ ጠቃሚ የሆኑ የኢሜይል መልዕክቶችን አሳልፎ ሊሰጠው ባለመፍቀዱ ከማይክሮሶፍት ኩባንያ ጋር የፍርድ ቤት ክርክር እያደረገ እንደሚገኝም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

አሜሪካዊው ታዋቂ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ማይክል ጆርዳን፤ያለ ፈቃዴ ዝናዬን ተጠቅሞ ሃብት አፍርቷል ባለው አንድ ኩባንያ ላይ ለመሰረተው ክስ በካሳ መልክ እንዲከፈለው በፍርድ ቤት የተወሰነለትን 8.9 ሚሊዮን ዶላር ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ሊለግስ እንደሆነ ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
የ52 አመቱ ጆርዳን፤ሴፍዌይ የተባለው የአሜሪካ የምግብ አምራችና አከፋፋይ ኩባንያ፣ ሳያስፈቅደኝ ምስሌን ለምርቶቹ ማስታወቂያ ተጠቅሟል፣ ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ ካሳ ሊከፍለኝ ይገባል በሚል የመሰረተውን ክስ ሲመረምር የቆየው ፍርድ ቤት፤ 8.9 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፈለው ወስኗል፡፡
ቺካጎ ውስጥ የተሰየመው ችሎት፤ውሳኔውን ማሳለፉን ተከትሎ ጆርዳን ለጋዜጠኞች እንደተናገረው፤ጉዳዩ ክብርን የማስጠበቅ እንጂ በካሳ ገንዘብ የማግኘት አለመሆኑን ጠቅሶ፣ ኩባንያው የሚሰጠውን 8.9 ሚሊዮን ዶላር የካሳ ገንዘብ ሙሉ ለሙሉ ለበጎ አድራጎት ተግባር እንደሚያውለው አስታውቋል፡፡ ነዋሪነቷ በኒውዮርክ ኢስት ሀምፕተን የሆነው አሜሪካዊቷ ሚሊየነር ሌስሊ አን ማንዴል በበኩሏ፤4 ሚሊዮን ዶላር በሚያወጣው እጅግ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቷ ውስጥ ለምታረባቸው 32 ወፎች፣ 100 ሚሊየን ዶላር ማውረሷን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
ሚሊየነሯ በፈረመችበት ህጋዊ የውርስ ሰነድ ላይ፣ ወፎቼ ጎጇቸው በሳምንት ሁለት ጊዜ እየተጸዳላቸውና ከሱፐርማርኬት ደረጃቸውን የጠበቁ ጣፋጭ ኬኮች፣ ካሮትና ፈንድሻ እንዲሁም የተጣራ ውሃ እየተገዛላቸው በአግባቡ እየተመገቡ እንዲኖሩ እፈልጋለሁ ብላለች፡፡
እ.ኤ.አ በ2007 ሊዎና ሄልምስሌ የተባለች በሆቴል ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማረች አሜሪካዊት ሚሊየነር ለአንድ ውሻዋ 12 ሚሊየን ዶላር ማውረሷንም ዘገባው ጨምሮ አስታውሷል፡፡

      ኢትዮጵያችን ራሷን ከዓለም አግልላ በብቸኝነት አዲስ ዓመትን ለማክበር ሽርጉዷን አጠናቃለች፡፡ ኢትዮጵያውያንም እንደ ህዝብ አሮጌ ሃሳባችን ሳይለወጥ አዲስ ዓመትን ልናከብር ተዘጋጅተናል፡፡ ጀምረነዋል፡፡ ይሁን እንጂ “አዲሱ ዓመት” አዲስ መሆኑ ላይ ጥያቄ ሊነሳበት ይችላል፡፡ በተፈጥሮ የጊዜ ቅመራ ሰሌዳ ላይ ለኢትዮጵያም ይሁን ለዓለም የጳጉሜ 6 ሌሊትና የመስከረም 1 ንጋት ከሌሎቹ ቀናት የተለየ ምንም የላቸውም፡፡ ልዩነታቸውም በእያንዳንዱ ቀን መሀል ላይ ያለ ልዩነት ነው፡፡ አዲስ ዓመት ከማንም የተሰጠን ሳይሆን የለመድነው ነው፡፡ በስምምነት ያፀደቅነውና ይሁነኝ ብለን አምነን የተቀበልነው ነው፡፡ “መስከረም” ፣ “ጥቅምት”፣ “ህዳር”፣ “ምንትስ” ብለን ደርድረን፣ ለእያንዳንዱ ወርም ስያሜ አበጅተን፣ “የመጀመሪያ” ያልነውን ወር የመጀመሪያ ቀን “ዓመት መለወጫ” ያደረግነው እኛው ነን፡፡ በቃ አዲስ ዓመት “ዘንድሮም አለን” ለማለት ካልሆነ በቀር የአሮጌው አይነት ነው፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ስም ስላልሰጠነው እንጂ የትኛውም ቀን በራሱ የአዲስ ዓመት መጀመሪያም መጨረሻም ነው፡፡
ስለ አዲሱ ዓመት ትተን ስለአሮጌው ሃሳባችን እንነጋገር፡፡ አዲሱ ዓመት፣ ቀኑ አይጠቅመንም፡፡ ሃሳባችን ነው የሚበጀን፡፡ የእኛ የሆነውና የምናዝበትም እሱው ነው፡፡ በጥቅሉ መፈረጅ ቢቸግርም ኢትዮጵያውያን ግን እንደ ህዝብ ለአዲስ አስተሳሰብ ክፍት አይደሉም፡፡ ዘመናዊ እውቀት ሲመጣ ከሃይማኖትም ከሞትም ጋር አያይዘን እንደገፋነው፣ ሲኒማ አይተንም ጥበቡን የሰይጣን ሥራ አድረን ቦታውን “ሰይጣን ቤት” ብለን እዚህ ድረስ ለምዕተ ዓመት ገደማ ይኸው ስያሜ ቀንቶን፣ እየጠራን በአሮጌው ሃሳብ ላይ የመጣበቅ ልምዳችን ዛሬም ድረስ ከእቅፋችን አልወጣም፡፡
ግርር አቋማችን ጐልቶ ከሚታይባቸው (አሮጌው ሃሳባችን ከሚገመትባቸው) መስኮች አንዱ ፌስቡክ ነው፡፡ ለመገናኛና ለታላቅ ቁምነገር ጠቢባኑ አምጠው ከወለዷቸው ማህበራዊ ድረገጾች አንዱ የሆነውን ፌስቡክን በጠቃሚ ሚዲያነቱ እውቅና ከሚሰጡትና ከሚገለገሉበት አንዱ ነኝ፡፡
ይሁንና ፈጣሪያኑን የዓለም ቁንጮ ቱጃር አድርጐ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦችን ከአፅናፍ አፅናፍ እያገናኘ ያለው ይኸው ቴክኖሎጂ ወለድ ብዙሀን መገናኛ፤ እኛ ሀገር በወጉ የሚጠቀሙበት፣ ሃሳባቸውን አስበውበት ወደ ህዝብ የሚያደርሱበት ጥቂቶች ቢሆኑ ነው፡፡
አመዛኞቹ ግን እንደጊዜያችን ሁሉ በብክነት የምንጠቀምበት ነው፡፡  
ዓመት ሄዶ ዓመት ሲመጣ፣ ክፍለ ዘመንም ሲቀየር እኛ በሃሳብ ካልተለወጥን፣ ከጊዜው ጋር መዘመን ካቃተን የአዲስ ዓመትን የመቀበል ጉጉታችን ከበዓል ማክበር የተለየ አይሆንም፡፡ ዘመናዊ አስተሳሰብ ማለት ሌላ ሳይሆን ከርረው የያዙትን ላላ አድርጐ ማሰብ ማለት ነው፡፡ ለነገሮች አንድ መንገድ ብቻ አለማበጀት ነው፡፡ እውነት ሌላውም ቤት እንዳለ ማሰብ ነው፡፡ እኛ ያመንነው ፍፁማዊው እውነት፣ እሱ ብቻ እንዳልሆነ ማሰብ ነው፡፡ ወደ አንድ “እውነት” ለመድረስ የተለያዩ መንገዶች መኖራቸውን መቀበል ነው፡፡ በሁሉም ነገር ላይ ጭፍን እምነት አለማሳደር ነው፡፡ ሰዎች እንደኛ ሁሉ የራሳቸው ምርጫ እንዳላቸው ማመን ነው፡፡ ሰዎችን ከእምነታቸው ጋር መተው ነው ስልጣኔ የራስን “እውነት” በሌሎች ላይ ለመጫን መነሳት ወደፊት ማንንም ሊያራምድ አይችልም፡፡ ይህን ሳይጥሉ አዲስ ዓመት ውስጥ መግባት አዲስ አያደርግም፡፡
በፌስቡክ የአጠቃቀም ልምዴ ብዙሀኑን እየጐተቱ አላራምድ ያሉ፣ ብዙዎች ከያዙት አልፈው ሌላ ሊያዩ የማይፈቅዱባቸው የጽንፍ መንገድ እየሆኑ ያሉ ሁለት መንገዶች አሉ፤ ፖለቲካና ሃይማኖት፡፡ ዓመታት እየተለዋወጡም እዚያው በነበርንበት ጐትተው የጐለቱን ጽንፎች ሆነው ይታዩኛል ለእኔ፡፡ ሃይማኖትና ፖለቲካ የሚያመሳስላቸው አንድ ጉዳይ መቧደንን መሰረት ያደረጉ መሆናቸው ነው፡፡ የአንዱ ፖለቲካ ወይም ሃይማኖት አባል የራሱን ቤት ትቶ በሌላው ሳሎንና ጓዳ እየተምነሸነሸ ውሎ የሚያድርበት አካሄድ በሰለጠኑትም ብዙ የሚያጋጥም አይሆንም፡፡ ሁለቱም በተግባራቸው ብቻ ሳይሆን በአባላቶቻቸው ቁጥርም ጭምር ላይ ነው ህልውናቸው የተመሰረተው፡፡ ይህ በመሆኑም ከቻሉ ሌላውን አፍርሰው የራሳቸውን ቢያደራጁ ላይደንቅ ይችላል፡፡ ሌሎች እንዳይደራጁ ማድረግ ግን ተፈጥሯዊው መንገድ አይደለም፡፡
ዛሬ ዛሬ ፌስቡክ ላይ ከሚሰጡ አስተያየቶች አንፃር ፖለቲካና ሃይማኖት በሁለት በሁለት የተከፈሉ ይመስለኛል፡፡ ደጋፊና ተቃዋሚ፡፡ የሃይማኖትም ሆነ ፖለቲካ ደጋፊዎች (የአንዱ ቡድን) የተቃዋሚዎቻቸውን፣ ተቃዋሚዎቹም የእነሱን ተቃዋሚዎች ድምፅ ላለመስማት የተማማሉ ይመስላሉ፡፡ ሆደባሻነት በሀገር ደረጃ ማጐንቆሉን ፌስቡክ በከፈትኩት ቁጥር ይነግረኛል፡፡
በሁለቱም ፅንፎች (በፖለቲካውም በሃይማኖቱም) በራስ ጥንካሬ ሳይሆን በሌሎች ድክመት የመበልፀግ አዝማሚያ ውስጥ ገብተው ይታያል፡፡ የአንዱ ድክመት የራሱ ወድቀት እንጂ በየቱም መልኩ የተቃራኒው ጥንካሬ ሊሆን አይችልም፡፡ በማንም ሞት ዳንኪራ መርገጥ ደስታን ሊያመጣ አይችልም፡፡ እየታየ ያለው ግን ይህ ነው፡፡
እዚያው ፌስቡክ ላይ ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን ሳነሳ፣ በየትኛውም መልኩ የዚያ ሃይማኖት አባላት እንዲያዝኑ የማድረግ ዓላማ የለኝም፡፡ እንደዚያ አይነት ሀሳብን አንስቼም አላውቅም፡፡ የአንድ ሀይማኖት፣ ፖለቲካ፣ ብሔር አባላት ላይ በደምሳሳው ቅሬታ የሚያስነሳ ሀሳብን ማሰራጨት ኃላፊነት የጎደለው እንደሆነ ጠንቅቄ እረዳለሁ፡፡ ይሁንና በሃይማኖቱ ወይም በፖለቲካው አናት ላይ ቆም ብለው ብዙኃኑን ስለሚያሳንሱ ዋልጌዎች ማንሳት በየትኛውም መመዘኛ ስለተቋሙ ወይም መላ አባላቱ ማንሳት ሊሆን አይችልም፡፡ እንደውም በግልባጩ እነሱን ከውርደት ማዳን ተደርጎ መወሰድ ነው ያለበት፡፡
1960ዎቹ መጨረሻ ገደማ፣ በዘመነ ቀይ - ነጭ ሽብር ዘመን መንገድ ሁሉ አንድ ብቻ ሆኖ ነበር፡፡ ግራው ወይም ቀኙ፣ ነጩ ወይም ጥቁሩ፣ ከእኔ ወይም ከጠላቴ ብቻ ሆኖ ነበር፡፡ ከዚህ ያልሆነ ከዚያ እንደሆነ ተደርጎ በጭፍን የሚፈረጅበትና የሚፋጅበት ወቅት ነበር፡፡ መካከለኛውን ወይም ከሁለቱ ውጭ ያለውን መምረጥ በሁለቱም ወገን አደጋን ሲጠራ ታይቷል፡
“መሀል ሰፋሪ” የሚል ስም ይሰጥ ነበር፡፡፡ መሀል ሰፋሪነት ደግሞ በተለይ በአብዮቱ በኩል በግልፅ ተወግዟል፡፡ ማስወንጀያ ምክንያትም ሆኗል፡፡ ያ የእሳት ዘመን ምርቱን ከግርዱ ለመለየት ጊዜ ስላልነበረው፣ ቀላቅሎ አብኩቶ መጋገርና መብላት አሊያም ጠቅሎ ገደል መጣል አይፈረድበት ይሆናል፡፡ በተረጋጋ ጊዜ፣ ጦርነት ሳይመጣ መሸበር ግን የጤንነት ጉድለት ነው፡፡ አሁን እኛ ጤንነት የጎደለን ይመስለኛል፡፡ እንዲህ በሀሳብ አድፈን በዓመት መለወጥ ለመንፃት እየሞከርን ይመስለኛል፡፡ ጊዜ የማንንም እዳ ተሸክሞ አያውቅም፡፡ ሰው ግን የጊዜ ባለዕዳ ይሆናል፡፡
ወደ ፖለቲካውም ስንመጣ (አሁንም እዚያው ፌስቡክ መንደር) ነፃ አሳቢ ሰው እኔ አላገኘሁም፡፡ አግንኜ ካሰብኩት ራሴን ጨምሮ አንድም ሰው እንኳ ወደ ግራም ወደ ቀኝም እኩል በተሰማው ልክ የሚንቀሳቀስ ማንንም አላየሁም፡፡ ፌስቡክ ላይ የሚታየኝ የፖለቲካ መስክ መሀሉ ወለል ያለ ባዶ ሆኖ፣ ግራና ቀኝ በየቁጥራቸው ልክ የተቧደኑ ጨለምተኞችን የያዘ ነው፡፡ በማውቀው ደረጃ አንዳችንም መሀሉ ላይ የለንም፡፡ እኛም መቆም አንፈልግም፣ ብንቆምም ሌሎች ገፍትረው አሊያም ጎትተው ይጥሉናል፡፡ ፍርሀት በፌስቡክ ሰማይ ላይ ነግሷል፡፡ በጭፍኑ ደፋር ፀሐፍት፣ ደፋር ተሳዳቢዎች ያሉ ቢመስልም ከዚያው ከቅርባችን ክብ ውጭ ሌላውን ለማየት ግርዶሽ አለብን፡፡
ገዢውንም ሆነ ተገዢዎቹን የፖለቲካ ድርጅቶች ከመደገፍ ወይም ከመቃወም ውጭ ያለው ምርጫ ተጥሏል፡፡ ቢገኝም ተራምዶ የማለፍ እንጂ የማንሳት ፍላጎት አይታይም፡፡ ሜዳው ሰፊ ይምሰል እንጂ አያራምድም፡፡ ገዢውን ግንባር የሚቃወሙት ወገኖች እርስ በእርስ ባይስማሙ እንኳ ስለግንባሩ አንዳች መልካም ነገር ላለመተንፈስ የተማማሉ ይመስላሉ፡፡ (አሁንም ይህን ሲያነቡ “ድሮስ ምን መልካም ጎን አለውና!” የሚሉ ብዙዎች እንደሚሆኑ ይታመናል) የአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ ላይ እየበረርን፣ “ይህን መንገድ ጥሩ ሰርተውታል” ስለው፣  “ኤጭ! ደግሞ ይሔ መንግሥት ምን ደህና ነገር ይሰራል?” ያለኝ ወዳጅ አለኝ፡፡ ስለ ብርቱካን ጣዕም ስትነግሩት፣ ስለሽንኩርት ዓይን ማቃጠል የሚመልስላችሁ አለ፡፡ ይህ ወዳጅም እንደዚያ ሆኖ ነው የሚታየኝ፡፡ ከገዢው ጎን የተሰለፉትም ተቃዋሚዎች ለዚች ሀገር እስካሁን ብቻ ሳይሆን ወደፊትም ረብ ያለው ተግባር እንደማይከውኑ አምነው ለማሳመን የሚታትሩ ናቸው፡፡ ይህ መሬት ላይ ያለ ግርርና ቀር ሀሳብ ቢሆንም ፌስቡክ ላይ ደግሞ አይሎ ይታያል፡፡ አዲስ ዓመት ለመቀበል ሽር ጉድ የምንለው ከዚህ አሮጌ ሀሳባችን ጋር ፅኑ ጋብቻ ፈፅመን ነው፡፡ እንደ እውነቱ ገላን ሞዥቆ መታጠብ ብቻውን ንፁህ አያደርግም፡፡ ንፁህ መልበስንም ይጠይቃል፡፡ አዲስ ዓመት እኛን በተወሰነ መልኩም አዲስ ሊያደርገን ካልቻለ … 

      የአዲስ አመት ፅንሰ-ሐሳብ መቸም ለሁላችንም ለየቅል ነው። በፆታ ፣ በእድሜ፣ በሐብት፣ በአካባቢ ወግና ልማድ መጠን ይለያያል። በልጅነት እድሜ ምናልባትም ከአዲስ ጥብቆ ጋር የተቆራኘ ይሆናል። ትንሽ ከፍ ሲባል ደግሞ ከትምህርት ቤት ዳግመኛ መከፈት ፣ ከመስክ ልምላሜና ካደይ አበባ ድምቀት፣ ከችቦ ብርሃንና ከሞቀ ጭፈራ ጋር ይታወሳል። በጉልምስና ወራት ግን የትውስታው ጉዞ ሁሉ ወደሁዋላ መሆኑ ቀርቶ ወደፊት ብቻ ይሆናል። ምናልባትም ሕይወት በዚያን እድሜ  ከኃላፊነት ሸክም ጋር ስለምትቆራኝ፣ ካለፈው  ትዝታ ይልቅ ከመጪው አውዳመት አከባበር ጋር በሐሳብ መወዛወዝ የሚጐላበት ዘመን መሆኑ አይቀርም።
ስለአዲስ አመት በሚፃፉ  ሐተታዎች ውስጥ ከላይ ከጠቀስኳቸውም የዘለሉ አያሌ  ያውዳመት ልምዶች፣ ትዝብቶች፣ ጨዋታዎችና ቁምነገሮች ተነግረዋል። ተፅፈዋል። በዚህች አጭር መጣጥፍ ደግሞ የተሻለ የማውቀውን  የራሴንና የሰፈሬን የአዲስ አመት መንፈስ ላውራ። ሁሌም እንደብዙ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ስለራስ ማውራቱ ለኔም የሚደላ ነገር አይደለም ነበር። አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ግን ወደሁዋላ አለማለት የጀመርኩት አንድ የሰለሞን ዴሬሳን አስተያየት ካነበብኩ እለት ጀምሮ ነው። ሰለሞን በዚያ ቃለምልልሱ ሰውን ማዳመጥ እንዲያውም ስለራሱ ሲያወራ ነው። ምክንያቱም በደምብ ስለሚያውቀው ነገር ሲያወራ ነው ማዳመጥ። ስለራሱ ከርሱ በላይ ማን ሊያውቅ ይችላል? ይላል። በጉራ ብዛት እጅ እጅ ካላለ  በስተቀር በርግጥም አንዳንዴ ችግር የለውም፤ ታግሶ ማዳመጡ።
ወደ ሰፈራችን ልመለስ። አዲስ አመት እንደማናቸውም ሰፈር የኛም እንዲሁ ማለዳ የእንኳን አደረሳችሁ አበባ በየቤቱ እያዞሩ፣ ፀሐይ ሳትበረታ፣ ከጃቸው ጨርሰው ወደ ቤት ለመመለስ ወዲያና ወዲህ በሚራወጡ ሕፃናት ትሞላለች። ጥቂት ረፈድ ሲል ጓዳ ባፈራት ቅባትም ትሁን ዘይት ታብሳ ወደሁዋላ የፊጥኝ የተቀፈደደች ቁርንጫጭ ጠጉር ወይም እስክትብለጨለጭ በወዛች ሉጫ ሶስትዮሽ ተሾርበው ያማሩ  ትናንሽ ልጃገረዶች ሰባት ስምንት  ሆነው በየደጃፉ አበባየሆይ ሲሉ ይሰማሉ። እንደኔ ላብ ላብ የማይላቸው ደፋር ታዳጊዎች፤  ፀሐዩ ከርሮ  ልጃገረዶቹ ከመበታተናቸው በፊት  ተንጠራርተውም ቢሆን የሚስሙት የከንፈር ወዳጅ አያጡም። ቀድሞ ተነቅቶባቸው ጥፊ እየላሱ የሚመለሱም አይጠፉም። አበባው ታድሎ አበባየሆይም ተጨፍሮ፣ የተገኘውን ሳንቲም እየቆጣጠሩ የተለበሰችውን አዲስ ጨርቅ አስሬ እያጐነበሱ ማየት የተለመደ ነው። ያን እለት ሰፈሩ በሙሉ በፊሽካና በፊኛ ይጥለቀለቃል። ያኔ ባለቀለም ላባ አናቷ ላይ የታሰረ አጭር ቀሰም ጫፏ ላይ በታሰረላት ተርገብጋቢ ወረቀት አዝናኝ ድምፅ ስለምታወጣ ሁሉም ገዝቶ ሲያስለቅሳት ይውላል። የጥቂቶች ምርጫ የነበረው የእጅ ሰዓት  ለአላፊ አግዳሚው አይን ፈጥኖ ስለማይታይ በብዙ ልጆች ተመራጭ አልነበረም። የከሰዓት በሁዋላው የገበያ ዳር ጭፈራ ከመድረሱ በፊት ባዶ ሆድ እንዳይኮን ወደ ቤት ተመልሶ ከቤተሰብ ጋር ምሳ መብላት ግድ ነው። በዚህ መሐል  ጐረቤቱ ሁሉ  ባንድ ጊዜ ጠበል ጣዲቅ ቅመሱ ማለቱ ስለማይቀር ከምሳ በፊት እያንዳንዱ ቤት በመዞር ሆድ እንደከበሮ እስኪነረት የተገኘውን  ቀማምሶ፣ የተረፈውን በልብስ ቋጥሮ መመለስ ተለምዷል። በስልሳዎቹና በሰባዎቹ እንዲህ እንደዛሬው ሸቀጥ የተትረፈረፈበት ወቅት አልነበረም። ለብዙ ወላጅ ልብስ ከመግዛት ይልቅ ማሰፋት ወጪው የቀለለና ክብሩም የተሻለ ነበር። ለዚህ ይመስለኛል  ከ“ልብስ እገዛልሐለሁ” ይልቅ “ልብስ አስቀድድልሐለሁ” ዝነኛ የዘመኑ ቃል የነበረችው። ከጫማም አይነቶች አሁን በፋኖዎች ሐብትነት  የምትታወቀው አንዳንዴ አሽሟጣጮች “ሰቭን ዶርስ” የሚሏት ባለመስኮትዋ ፕላስቲክ “ኮንጐ” ጫማ  ሲበዛ ተወዳጅ ነበረች። ሸራ ጫማ በገቢ መጠናቸው ሻል ባሉ ቤተሰቦች ዘንድ የምትመረጥ ወይም የጉልበት  ሥራ ሰርቶ መጠነኛ ሳንቲም ማግኘት በሚችሉ ጎረምሶች እግር የማትጠፋ ነበረች። በሙቀት የተነሳ ለክፉ ጠረን ስለምታጋልጥ ገንዘብ እንኳ ቢገኝ  በእንደኔ አይነቱ ሰነፍ ዘንድ ተመራጭ አልነበረችም። የኮንጎ ነገር ከተነሳ የባለ ብሯ የላስቲክ ኳስ ነገርም በቀላሉ የሚዘነጋ አይደለም። ባለብሯ የላስቲክ ኳስ “ሜድ ኢን ቼኮዝሎቫኪያ “ የሚል ፅሑፍ የታተመባት በዘመኑ ታዳጊዎች እንደብርቅ የተወደደች የእግር ኳስ መጫወቻችን ነበረች። የብር ኳስ አዲስ አመትን በመሰለ በተለይ በቅዱስ ዮሐንስ አይነቱ ገንዘብ የሚገኝበት አመት በዓል ሰሞን በመናጢዎች ሰፈር ሳይቀር በብዛት የምትሸመትበት ወቅት ነው። በግልም ተገዛች በቡድን ሹል ጫማና ጥፍር ከግሩ ላይ ያለው ሁሉ እንዲጫወትባት አይፈቀድም። ምናልባትም አንዳች ችግር አጋጥሟት በጨዋታ መሐል ተበስታ ስትተነፍስ ወዲያው በጋለ ሚስማር ቀዳዳዋን በመተኮስ ከተጨማሪ መተርተር ማዳን በየሰፈሩ የተለመደ፣ ሁሉ ታዳጊ የሚያውቀው ዘዴ ነው። የከሰአቱ የገበያ ዳር ጨዋታ ማንም ሳይጠራው በተሰበሰበ በሺህ የሚቆጠር ተመልካችና  ጨፋሪ መድመቅ ይጀምራል። ጭፈራው ዳንስ፣ እስክስታና ረገዳ ይበዛዋል። የጉራጊኛ ጭፈራ በየጣልቃው የማጣፈጫ ያህል አይታጣም። ለምን እንደሆን በማላውቀው ምክንያት የትግሪኛ ጨዋታ ላይን ሲይዝ በከተማው ውስጥ በታወቁ  ሁለት ሶስት ጥጎች ብቻ ተለይቶ እንደሚጨፈር አስታውሳለሁ። ከበሮው ከጀመረ በቀላሉ እንደሌሎቹ ጨዋታዎች ከምሽቱ ጋር በዋዛ የሚፋታ አልነበረም። አልፎ አልፎ ጥቂት ተቀባይ ከተገኘ በሌሎችም ቋንቋዎች የሚያስነካው አይጠፋም ነበር። እንዳሁኑ ቋንቋ ፖለቲካ ሳይሆን። የየሰፈሩ ሐርሞኒካ ነፊዎች የሸሚዞቻቸውን ኮሌታ ሽቅብ ገትረው  በቄንጥ እየተዘዋወሩ ደናሽ ደናሾችን በዜማ ያጅባሉ። ከተመልካቾች መሐል እየተፈናጠሩ የሚጨፍሩ ብዙ ሁለገብ ጨዋታ አድማቂዎችም ነበሩ። በስም የሚታወቁ። ከማዶ ከገበያው ዙሪያ ጥግ ጥጉን ከወደ እህል በረንዳዎቹ በሩቅ የሚታዩ የባለረዣዥም ዱላ ኦሮምኛ  ጨፋሪዎች መሰባሰብ ይጀምራሉ። በዝንጀሮ ፀጉር በተለበጠ ኮፍያ በሐገር ባሕል ነጭ ልብስ አምሮ የጠገበ የሽመል ዱላ በሚያወዛውዝ ሸበላ  ጎልማሳ የሚመራ ሰልፍ “ሆ” እያለ እንደ ዘንዶ በጭፋሮ እየተምዘገዘገ ገበያውን እያጋመሰ፣ በተመልካች ፊት ማለፍ ይጀምራል። ሽቅብ ከእህል በረንዳዎቹ በላይ ትንሹ ኮረብታ ገበያውን በስተምስራቅ ጫፍ አቅፎታል። ከኮረብታዋ አናት ሲኞር ደበሌሪ ሰርቶታል የሚባለው የቅዱስ ሩፋኤል ቤተክርስቲያን፤ በደማቅ አረንጓዴ ዛፎቹ ታቅፎ፣ በአዲሱ የመስከረም ሰማይ ላይ አምሮ ተሰይሟል። የዛሬን አያድርገውና እነዚያ ዛፎች አሁን በቁማቸው የቀብር ቤት በመሻማት ላይ ባሉ ባለገንዘቦችና በአለም ጉዳይ በተጠመዱ ካሕናት ስምምነት የሸቀጥ ቡቲክ በመሰሉ ጉሮኖ ቤቶች ተተክተዋል። የኦሮምኛ ጨፋሪዎቹ ሰልፈኛቸውን እየመሩ ጥግጥጉን መዞር፣ እየጋለ በሚሄድ ዜማ ወደገበያው መዝለቅ ይጀምራሉ። እሱም የራሱ ስነ-ስርዓትና አጨፋፈር አለው። በየተወሰኑ አመታት የዚሕ ጭፈራ መሪዎች ይለዋወጡ ነበር። “አለ ከረሜላ መስቲካ“ እያሉ በአል አክባሪውን ሁሉ መስቲካ አላማጭ የሚያደርጉ ሱቅ በደረቴዎች፣ በየጨፋሪው እግር ስር እየተሽሎከሎኩ ይነግዳሉ። ሲመቻቸው ወይ ሲነሽጣቸው እቃቸውን አስይዘው አንዳፍታ ዳንሱንም ጭፈራውንም ያስነኩታል። ጭፈራ አንዳንዴ በብዙ ሰዎች ዘንድ እንደ ስለት የሚወጡት ግዴታም አይነት ነበር። የየመንደሩ አዶ ከበሬዎችም የየራሳቸው ተመልካችና የጭፈራ ስልቶች ነበሯቸው። የገበያ ዳር ጭፈራ ሲከለከል የአዶ ከበሬዎች ቁጥርም አብሮ እየተመናመነ ሔዶ ሁዋላ ከናካቴው ጠፍተዋል። እያደርም ከጭፈራው አልፎ ሙሾም ተከለክለና አረፈው። ነውረኛ የሌሊት መማገጫዎች በሕጋዊነት ካመት አመት በሚነግዱበት አገር፣ያገር ባሕል፣ያደባባይ ወግና ማዕረግ ባመት አንድ ቀን እንኳ መከልከሉ  እስከ ዛሬ ሳይገባኝ አለሁ። በዜማ መደሰትና እና በዜማ ማልቀስ በሚከለከልበት ምድር ሰው ከሰውነቱ የሚቀረው ወግ ቢኖር ቀን እየሰራ ሌቱን ሲበላ ማደር ብቻ መሆኑ ነው። ሰው መሆን አዲዮስ!
ወደ ራሴ ልመለስ፣ እንግዲህ ይሄ በነበረበት ወቅት፣ በመጪው አዲስ አመት ምን ልታደርግ አቅደሀል በሚል ጥያቄም ሆነ  እንዲህ ላደርግ አቅጃለሁ በሚል መልስ  ሬዲዮም ቴሌቪዥንም ተመልካችና አድማጩን ሲነተርኩ መስማቴን እጠራጠራለሁ። ወይ የልጅነት እድሜ በመሆኑ ሳላስተውል ቀርቼ ይሆናል። በነገራችን ላይ እውነት እውነቱን ለመነጋገር በበኩሌ በራሴ ጀምሬ በራሴ ብቻ  የምጨርሰው  ከማንም የማያነካካኝ የግል ጉዳይ  ካልሆነ በስተቀር አልሜና ተመኝቼ እንደሆን እንጂ አቅጄ ያደረግሁት ነገር የለም። መቸም አንድን ነገር ለማግኘት ቢያንስ መፈለግ ወይም መመኘት ያስፈልጋል። ለማግኘት መጀመሪያ መፈለግ ግድ ነው ። በርግጥ ያገኙት ነገር በሙሉ የፈለጉትና የተመኙት ነው ባይባልም። እናም በመመኘትና  በመፈለግ በኩል እኔም እንደ ብዙ ሰው ገደብ የለሽ ነው ሕልሜ። የሚሆነው ይሆናል የማይሆነው ይቀራል።  የተመኘሁትን  የማገኘው በትጋትና በጥረት መሆኑን ለራሴ ስለማምን በፅናት እደክምለታለሁ። በርግጥም ብዙውን አግኝቼዋለሁ። ያጣሁት ጥቂቱንም ቢሆን  ዘግይቼም ቢሆን ለመጣር አልቦዝንም። የግድ ባጣሁት ግን ተቃጥዬ አላውቅም። ምናልባትም ተመኝቼው እንጂ አቅጄው ስለማላውቅ ይሆን እላለሁ። ለኔ ማቀድ በውስጡ አስገዳጅ ድምፀት ያለበት ሆኖ ይታየኛል። ሳይሆን በቀረ ጊዜ ቁጭትና መቃጠል፣ የሚቆጠር ኪሳራም ያለበት መስሎ ይታሰበኛል። ይሔ አጠቃላይ መንፈሱ ነው ለኔ። በሌላ ቋንቋ  እንደኔ ግምት እቅድ ከአቃጁ በተጨማሪ ለስኬቱ የሌሎችንም በጎ ፈቃድና ቅንጅትን የሚጠይቅ በጋራ ልፋት ላይ የተመሰረተ ክንዋኔ ነው። ሁሉም በጋራ በብቃት ከልብ ካልተሳተፈ በግማሽ አንካሳ ቡድን ማቀድና  ለመፈፀም መባዘን፣ ለኔ ቀድሞ የለየለት ኪሳራ ይመስለኛል። በሌላ በኩል ግን ያንድ ሰው የማሰብና የመፈፀም ጉዳይ ሲሆን “one man mission “ የሚሉት አይነት) ማቀድ የተሻለ የሚያዋጣ ይመውስኛል። ቢያንስ እዚህ አገር ማለቴ ነው። ለምሳሌ ሲጃራ ጠጪ ሰው ሲጃራ አይረባኝም በአዲሱ አመት ላቆም አስቤያለሁ” ቢል ሐሳቡም አፈፃፀሙም ጥቅሙም ያንድ ሰው ጉዳይና ያንድ ሰው  ተልዕኮ በመሆኑ፣ አቅጃለሁ  ብሎ ቢጠራው ተስማሚ የድርጊቱ ወካይ ቃል ሊሆን ይችላል። ችግሬ ከቃሉ ሳይሆን ቃሉ ሊመነዝር ከተፈጠረለት ፅንሰ-ሐሳብ ጋር ነው። ባንድ ሰው ታስቦ በሌሎች ተሳትፎ ሊሳካ ይችላል ተብሎ በሚታሰብ ጉዳይ  ላይ ግን አቅም የሌለው የኔ ብጤ ዝም ብሎ ቢያልም ወይ ቢመኝ ያዋጣዋል። ታክሲና አምቡላንስ  በታሰበ ሰዓት በማይደርስበት፣ ኮረንቲ ባልተጠበቀ ተደጋጋሚ  ቅፅበት በሚቋረጥበት፣ የቋመጥክለትን ዕቃ ለመግዛት ገንዘብ አግኝተህ ተንደርድረህ ስትደርስ ቆጠራ ላይ ነን በምትባልበት፣ መሰረታዊ ጥቅሞች ሁሉ በሻሞ እድል ላይ በወደቁበት አገርና ዘመ፣ን ባንድ ሰው ቢታቀድ እንኳ ባንድ ሰው የማያልቅ ሐሳብ ሲመጣ፣ ከማቀድ ይልቅ አልሞ መልፋት ለኔ አደጋ -አልባ፣  ፀፀት-አልባ ፣ ጉራ-አልባ ትሁት ዘዴ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ሆኖም ምንም ቢሆን ማቀድ ይሻለኛል ለሚሉ ምናልባት አንድ ከበላይ ልንማረው የምንችለው መንሸራተቻ አለ። “ከእቅዴ ይሔን ያህሉን አሳክቼ ይሔን ያህል ረክሶብኛል “የምትል። ለሁሉም ግን “የሚጥመውን ባለቤቱ ያውቃል” አለ በግ ነጋዴው! መልካም አዲስ አመት!!

    ያለፈው ዓመት ለኔ የስራ አመት ነበር፡፡ በርካታ የማስታወቂያና የዶክመንተሪ ስራዎችን ሰርቼበታለሁ፡፡ በተለይም ሰፊ ጊዜዬን የወሰደው የ”ጉማ አዋርድ”ን ማዘጋጀት ነበር፡፡ የ2007 “የጉማ አዋርድ” ከባለፈው በተሻለ በብዙ መልኩ የደመቀ ነበር፡፡ እናም ለኔ 2007 ስኬታማ ነበር፡፡
በአዲሱ ዓመት አዳዲስ የፊልም ስራዎችን የመጀመር እቅድ አለኝ፡፡ የ“ጉማ አዋርድም” ይቀጥላል፡፡ በሌላ በኩል “ሉሲ ውመን ፊልም ፌስቲቫል” የተባለውን የሴቶች ፊልም ፌስቲቫል ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲሱ ዓመት ለማዘጋጀት አቅደናል፡፡
በመጪው ዓመት ከአሁኑ በተሻለ የተሳካ ስራዎችን እንደምሰራ እጠብቃለሁ፡፡ ዓመቱን ያጠናቀቅሁት ወደ ሲሼልስ ሄጄ፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጨዋታን በመመልከት ነው፡፡