Administrator

Administrator

    ያለፈው ዓመት ለኔ ጥሩ ነበር፡፡ የራሴን የበጐ አድራጐት ማህበር መስርቻለሁ፡፡ “Women Can Do It” (ሴቶች ይችላሉ!) በሚል እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፌአለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ሴት ደራስያን ማህበር ደግሞ ለ2007 ካቀደው ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ አሳክቷል፡፡ የቀረውን በተለያዩ ችግሮች ምክንያት አልሰራንም፡፡ በወርሃዊ መዋጮ ብቻ የሚንቀሳቀስ ማህበር በመሆኑ የሚያስቸግሩ ነገሮች አሉ፡፡ በአዲሱ ዓመት የተሻሉ ሰዎች መጥተው እንዲሰሩ ጥረት እናደርጋለን፡፡
በ2008 በእርግጠኝነት የማህበሩ ፕሬዚደንትነቴን እለቃለሁ፡፡ በማህበሩ አባልነቴ ግን የታቀዱት እቅዶችን ለማሳካት እሰራለሁ፡፡ በግልም በስነፅሁፍ በኩል የተሻለ ሥራ እሰራለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ በተጠናቀቀው ዓመት ለፐብሊክ ዲፕሎማሲ ከተመረጡ 10 ሴቶች ውስጥ አንዷ ሆኜ ግብፅና ሱዳን ሄጃለሁ፡፡ በአጠቃላይ ለእኔ ዓመቱ የተሳካ ነበር፡፡

    እግዚአብሔር ይመስገን 2007 ለኔ ስኬታማ ስራዎችን የሰራሁበት ዓመት ነው፡፡ በህብረተሰቡ  ዘንድ ተቀባይነት ያገኙ “ባንቺ የመጣ“ እና #አለም በቃኝ” የተሰኙ ሁለት ፊልሞችን ሰርቻለሁ፡፡ በትወና የተሳተፍኩበት “ሶስት ማዕዘን; የተሰኘው ፊልምም፤ በአሜሪካው የ#ፓንአፍሪካን ፊልም ፌስቲቫል” ላይ ተሸልሟል፡፡ በተጨማሪም በመስከረም ወር ለሚካሄደው African Movie Academic Award/AMMA በምርጥ አክተርነት ዘርፍ ለመጀመሪያ ጊዜ የታጨሁ ኢትዮጵያዊ የሆንኩትም በዚሁ ዓመት ነው፡፡  እኔ ብዙም የእቅድ ሰው አይደለሁም፡፡ በመጪው ዓመት እግዚአብሄር ከፈቀደ በጭንቅላቴ የሚመላለሱ የራሴ ሀሳቦችን የመፃፍ ዕቅድ አለኝ፡፡ የራሴን ስራዎች ለመስራት እሞክራለሁ፡፡ በቲያትሩ በኩልም “3ኛ አይንን” ጨምሮ ሌሎች የምሰራቸው ስራዎች ይኖራሉ፡፡ በሰለሞን ቦጋለ ተፅፎ ዳይሬክት የተደረገውና በትወና የምሳተፍበት “የራስ መንገድ” የሚለው ፊልምም ለእይታ ይበቃል፡፡ በበጎ አድራጎቱ በኩልም ሰለሞን ቦጋለን ጨምሮ ከሌሎች አርቲስቶች ጋር በመሆን የምንሰራቸው ስራዎች ይኖራሉ፡፡

     አመቱ ለኔ ጥሩ ሆኖ ነው ያለፈው፡፡ ሶስት እቅዶቼን አሳክቻለሁ፡፡ አንደኛ የማሳትማቸው መጻህፍት ነበሩ፡፡ ተሳክተውልኛል፡፡ “አራቱ ሃያላን” እና “እኛ የመጨረሻዎቹ” የተሰኙትን መጻህፍት ለአንባቢ ማድረስ ችያለሁ፡፡ ሁለተኛ የማከናውነው ጥናት ነበር፤በዓመቱ አከናውናለሁ ያልኩትን ያህል ሰርቻለሁ፡፡ “የበጎ ሰው ሽልማት;ንም አመቱ ሳይጠናቀቅ አንድ ምዕራፍ ማድረስ ነበረብኝ፤እሱም ጥሩ ደረጃ ደርሷል፡፡ በቀጣዩ አዲስ አመትም 3 ዋነኛ እቅዶች አሉኝ፡፡ አንደኛ፤#የበጎ ሰው ሽልማት”ን ተቋማዊ ማድረግ፣ ሌላው ሁለት መፅሀፍትን ለአንባቢ ማድረስ ነው፡፡ አንዱ አቡነ ተክለሃይማኖት ላይ የሚያተኩር ሲሆን ሌላው እጨጌ እመባቆምን የተመለከተ ነው፡፡ ሦስተኛው፤የጥናት ስራ ነው፡፡ የሚያተኩረውም በተለይ ጥንታዊ የሆኑ የኢትዮጵያ ቦታዎች ላይ ይሆናል፡፡ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ቦታዎችን መጠሪያ ማጥናት ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ድሮ ናዝሬት የሚባለው አሁን አዳማ ሆኗል፡፡ ልክ እንደዚህ ከ20 ዓመት በኋላ ናዝሬት የሚል ቦታ የተጠቀሰበትን መፅሀፍ የሚያነብ ልጅ ግራ ነው የሚገባው፡፡ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ራሱ አንዱ ክርክር የፈጠረው የቦታዎች ስም መቀያየር ነው፤ስለዚህ በዚህ ላይ ጠለቅ ያለ ጥናት ለመስራት እቅድ አለኝ፡፡ እንግዲህ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ፤መልካም አዲስ ዓመት እንዲሆንም እመኛለሁ፡፡

የጫጉላ ሽርሽር የት አሰብክ?
ቤቴ ነዋ… የት አስባለሁ?! በአልም ስለሆነ ቤተሰብ ከቤት እንዳትወጡ ብሎናል፤ ስለዚህ እዚሁ ነው ልጄ … አዲስ አበባ፡፡ “ጫጉላ አብቧል ዛሬ እቴ ሸንኮሬ” ይባል የለ! ስፖንሰር ካደረግሽን ደግሞ የትም እሄዳለሁ፡፡
ለሰርግህ ያሰብከውን ወጪ ለበጎ አድራጎት ሰጥተሃል፡፡ አንዳንዶች ግን “ሰይፉ ካለው ላይ ሳይሆን ያለውን ነው የሚሰጠው” ይሄ እውነት ነው?
ለኔ ሲዘንብ ለነሱም ያካፋ ብዬ ነው (… ሳቅ …) ምን መሰለሽ ሰርግ ላይ ወዳጅ ዘመድ ጠርቶ ማስደሰቱ መልካም ነው፤ ግን አንዳንዱ ቀን የበላው ጠፍቶ ማታ ሲገባ እራት ይላል፡፡ ስለዚህ የማይጠፋውንና ለህሊና ደስታ የሚሰጠውን ነገር ለማድረግ ብዬ ነው… ለሰርጌ ወጪ ያሰብኩትን 300ሺህ ብር፤ 200ሺህ ለሙዳይ፣ 100ሺውን ደግሞ ለሜቄዶንያ የሰጠሁት፡፡
በየዓመቱ ለተመራቂ ተማሪዎች ሱፍ ትሰጣለህ የሚባለውስ እንዴት ነው?
እእእ …. ምን መሰለሽ በሰይፉ ኦን EBS ላይ በዓመት ከ30 እስከ 40 ሾዎች ይቀርባሉ፡፡ ሾው ያቀረብኩባቸውን ሱፎች ነው በዓመቱ መጨረሻ ላይ አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች የምንሰጠው፡፡ ምርቃት ለእነሱ ሰርግ ማለት ነው፡፡ በቀጣይም ከተለያዩ ሱፍ አምራቾች ጋር በመሆን በቋሚነት ሱፍ የምንሰጥበትን ፕሮግራም እናዘጋጃለን፡፡ እናም እኔ ቤት አሁን ብትመጪ ሱፍ ፍትፍት እንጂ ሱፍ አታገኚም፡፡ ለዓመታት ተምረው ሊመረቁ ሲሉ የሱፍ መግዣ የሚያጥራቸው ብዙ ተማሪዎች አሉ፡፡ እነሱ ያሳዝናሉ፡፡ እሱን በጥቂቱ ለመቀነስ ነው፡፡ እንግዲህ ከጀመርነው አንድ አራት ዓመት ሆነን፡፡
ለኮሜዲያን ደረጀ የ100ሺ ብር ስጦታ በአደባባይ መበርከቱን የሚቃወሙ ወገኖች አሉ፡፡ በሌላ መንገድ ማድረግ አይቻልም ነበር?
BGI ኢትዮጵያ የዛሬ ዓመት ለአባባ ተስፋዬ መኪና ሰጥቷቸው ነበር፡፡ ይኸኛው የዚያ ቀጣይ ክፍል ነው፡፡ አላማውም በዋናነት ለኮሜዲያኑ እውቅና መስጠት ነው፡፡ የቢጂአይ ሀሳብ፤ መሰጣጣትን ባህል ልናደርገው ይገባል የሚል ነው፡፡ የሟቹ ኮሜዲያን የሀብቴ ምትኩ እናት 50 ሺህ ብር ሲበረከትላቸው “ልጄ ሞቶም ይጦረኛል” ብለው አልቅሰዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ለጥበብ ላደረጉት አስተዋፆፅኦ ምስጋናና ዕውቅና ስለሚገባቸው ነው፡፡
የሰይፉ ኦን ኢቢኤስ ሾው ፕሮግራሞች እየተደጋገሙ ይቀርባሉ የሚል ቅሬታ በተደጋጋሚ ይሰነዘራል፡፡ ምክንያቱ ምንድነው?
ምክንያቱ የኔ ስንፍና ነው፡፡ ያው የብዙ ጊዜ ስራይፈልጋል፡፡ በስራ ተወጥሮ አቅም የማጣቱ ነገር አለ፡፡ እንግዲህ በአዲሱ ዓመት ወጥሬ እሰራለሁ ብያለሁ፡፡፡
ሰይፉ ከሸገር ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ ሼር ገዝቷል እየተባለ ይወራል፡፡ እውነት ነው?
(…… ሳቅ …..) ሼር እኮ ነው የምንሰራው፤ ከምናገኘው እንካፈላለን፡፡ ያ ማለት ሼር ነው (… ሳቅ ….) ሸገር ውስጥ እራሴን እንደኮሚሽን ሰራተኛ አላይም፤ እንደ ቤተሰብ እንጂ፡፡ ከአበበም ከመዓዚም ጋር ያለን ቅርበት የቤተሰብ ነው፡፡ ያንን ቅርበት ያዩ ሰዎች ናቸው “ይኼማ በቃ ሼር አለው ማለት ነው” ብለው ያሰቡት፡፡ ያው እኔ በሰራሁበት ይከፈለኛል፤ በሸገር በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ እውነቱ ግን ከሚገኘው ገቢ በስምምነታችን መሰረት ከምንካፈለው ውጭ ጣቢያው ላይ ምንም አ…ይ..ነ..ት.. (ሳቅ) ሼ…ር.. የለኝም፡፡
አንዳንድ ሰዎች “ሰይፉ ኢንተርቴይነር እንጂ ጋዜጠኛ አይደለም” ይላሉ፡፡ አንተ ራስህን የምታስቀምጠው የቱ ጋ ነው?
ጋዜጠኛ ባልባል ደስ ይለኛል፡፡ ውጪ አገር ጋዜጠኝነት በራሱ የተለያዩ መመዘኛዎች አሉት፡፡ ዘርፉ ይለያያል፡፡ እኔ TV Host ነኝ፡፡ እውነቱን ለመናገር ጠንከር ያለ ነገር ብዙም አልወድም፡፡ እኔ የምወደው የሚያዝናኑ ነገሮችን ነው፡፡ ሰው እንደየራሱ ስሜት ስያሜ ይስጠኝ፡፡ ለራሴ ግን “ስያሜ አጣሁላት” የሚለውን ዘፈን ጋብዣለሁ፡፡
አንዳንዴ በአርቲስቶች ላይ ክብረ ነክ ቀልዶችን ትቀልዳለህ ይባላል፡፡ እንደውም በአንድ ወቅት አንድ አርቲስትን “ይሄን ፊት ደገምከው” ብለሃል ተብሎ ይወራል፡፡ እውነት ነው?
አንዳንድ ጊዜ የሚባሉ ነገሮች ማስረጃ የላቸውም፡፡ ይኼንን እኔ በጭራሽ አላልኩም፡፡ ዘውዱ እራሱ ሰይፉ ኦን ኢቢኤስ ሾው ላይ ቀርቦ ተናግሯል፡፡ እኔ እንደውም ብዙ ግዜ የምታወቀው እራሴ ላይ በመቀለድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ  በመሆኑ ነው እንጂ ሌላ አገር ፕሬዚዳንቱ ላይ ሳይቀር ይቀለዳል፡፡ የኛ አገር ኮሜዲያን ትልቅ ደረጃ የማይደርሱት በተለያየ ምክንያት ስለሚገደቡ ነው፡፡ እንደ ልብ መቀለድ የለም፡፡
ያለፉትን የሥራ ዓመታት እንዴት ትገልፀዋለህ?
እንግዲህ መጀመሪያ አካባቢ “ሆሊውድ” ጋዜጣ ላይ ነበር የምሰራው፤ የኔ መሰረት ጋዜጣ ነው፡፡ ያኔ የአገር ውስጥና የባህር ማዶ የመዝናኛ ዜናዎችን ጋዜጣ ላይ እሰራ ነበር፡፡ ለጋዜጣ አሁንም ድረስ ልዩ ፍቅር አለኝ፡፡ ከጋዜጣ ሥራ በጣም የሚገርመኝ ምኑ እንደሆነ ታውቂያለሽ    ?  ስትሰሪው አድረሽ ጠዋት ታትሞ ሲወጣ ሁሌ ስህተት አይጠፋውም፡፡ (ሳቅ …) በመቀጠል “አዲስ ዜማ” ኤፍኤም 97.1 ላይ ነው የሰራሁት … ከዚያ በኋላ “ኢቲቪ ሚዩዚክ” …እያለ እያለ አሁን “ታዲያስ አዲስ”፣ “ሰይፉ ኦን ኢቢኤስ” በቃ… ይኸው ነው፡፡
ምነው ፊልሙን እርም አልክ?
እባክሽ ጊዜ ጠፋ፡፡ “ይፈለጋል” የተሰኘው ፊልሜ አድካሚ ነበር፡፡ ፊልም ድካሙና ገቢው አይመጣጠንም፡፡ በርግጥ ወጪውን መልሷል፡፡ ለአምለሰት ሙጬም (የቴዲ አፍሮ ባለቤት) የመጀመሪያ ስራዋ ነበር፡፡ አሁን ግን “ታዲያስ አዲስ” አለ፤ “ሰይፉ ኦን ኢቢኤስ” አለ… አጉል መወጣጠር ነው የሚሆነው፡፡
ከድምፃዊ ሚካኤል በላይነህ ጋር ተዛመድክ አሉ?
(ሳቅ ….) አንዱ እንደውም ባለቤቴ የሚካኤል የሚስቱ እህት ናት ስለው፤ “ለዛ ነዋ ታዲያስ አዲስ ላይ ጠዋት ማታ ሚካኤል በላይነህን የምትጋብዘን” አለኝ፡፡ አዎ … አማች ሆነናል፡፡
አሁን እንግዲህ የቀረህ ልጅ መውለድ ነው …
እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ ነው፡፡ ግን እኛ ቤት 3 ወንድና 1 ሴት ነው ያለው፡፡ እኔ የመጀመሪያ ልጅ ነኝ፡፡ በኔ ህይወትም ይህ ቢደገም ደስ ይለኛል፡፡ ዋናው ግን ጤነኛ ልጅ መሆኑ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ሴት ፀጋ ናት፤ ወንድም በረከት ነው፡፡
ባለቤትህ ሙያዋ ምንድነው?
ባለቤቴ …. ሆስተስ ነበረች፡፡ ነርስም ነበረች፡፡ አየሽ ከዚህ በኋላ የህክምና ወጪ አያሰጋኝም፡፡ የማርኬቲንግም ምሩቅ ናት፡፡ በቃ (…. ሳቅ ….) የማስታወቂያ ነገር እንግዲህ አያሳስበኝም … አሁን በማርኬቲንጉ እየሰራች ነው ያለችው፡፡ ምን አለፋሽ 3 ሚስት ነው ያገባሁት፡፡ ሆስተስ … ነርስ … የማርኬቲንግ ባለሙያ ማለት ነው፡፡
2007 እንዴት አለፈ?
ለ2007 ዘፈን ጋብዘው ብትይኝ… “እያነቡ እስክስታ” የሆነበት ዓመት ነው፡፡ ጥሩም መጥፎም ተከስተዋል፡፡ የኦባማ መምጣት ትልቅ ነገር ነው፡፡ በአገራችን ላይ የተከሰተው የድርቅ አደጋ ደግሞ በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው፡፡ ሁለቱ ለየቅል ነው፡፡ እኔ ደግሞ መቼ ነው ያገባኸው ስባል “በ2007” የምልበት ነው፡፡
የሚገርመው ነገር ያገባሁት ልክ በልደቴ ቀን ነው፡፡ ያው እድሜ እንደሆነ አይገለፅም፡፡ 2008 ሳይገባብኝ ነው የሸወድኩት፤ በአንድ ሳምንት ልዩነት 2008ን መቀላቀሉ አስደስቶኛል፡፡ እንዳልኩሽ ያለፈው ዓመት አሪፍም ነገር አለው ደስ የማይልም ነገር አለው፡፡
በአዲሱ ዓመት ምን …
በ2008 … ወጥሬ አድማጭና ተመልካችን ለማስደሰት እሰራለሁ፡፡ ሰይፉ ኦን ኢቢኤስም የማይደጋገምበት ዓመት ይሆናል፡፡ የቅድሙን ቃል ልጠቀመውና (ሳ…ቅ…) በአዲሱ ዓመት እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ ይሄንን ፊት እደግመዋለሁ፡፡ እስቲ እናንተንም ልመርቅ …
 “አዲስ አድማስ”ን እንደ “ዋሽንግተን ፖስት” በሚሊየን ቅጂዎች የሚሰራጭ ያድርግላችሁ!
አንቺም ከጠያቂነት ወደ ተጠያቂነት የምታድጊበት ያርግልሽ!
መጣ የተባለውንም ርሃብ እግዚአብሔር በአጭሩ ያስቀረው!! የጥጋብ ዘመን ይሁንልን!!
የምንዋደድበትና የምንረዳዳበት የሰላም ዓመት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡
ለኢትዮጵያ ህዝብም እንኳን አደረሳችሁ ብያለሁ!!

    ያለፈው አመት ለኔ በጣም ስኬታማ ነበር፡፡ አዳዲስ ልምዶችን አግኝቼበታለሁ፡፡ እራሴ ፕሮዱዩስ ያደረግሁትና የምተውንበት “ያነገስከኝ” የሚለውን ፊልም ለተመልካች ያበቃሁበት አመት ነው፡፡ በገንዘብም በጊዜም ብዙ የደከምኩበት በመሆኑ ፊልሙ መወደዱ ለኔ ትልቅ ስኬት ነበር፡፡ “ሼፉ 2”ትን ጨምሮ ሌሎች የተወንኩባቸው ፊልሞችም ውጤታማ ነበሩ፡፡ ወደ ብዙ አገራት በመጓዝም ብዙ ልምድን ቀስሜአለሁ፡፡ ከእነ ውጣ ውረዱም ቢሆን 2007 ዓ.ም ለኔ ከምገልፀው በላይ ስኬታማ አመት ነው፡፡
በ2006 የጀመርኩትን የፍቅር ግንኙነት በተጠናቀቀው ዓመት ቋጭቼዋለሁ፡፡ በ2008 አዲስ ጓደኛ የመያዝ እቅድ አለኝ፡፡ ቀጣዩ አመት የ”ዳና” አዲሱን ምዕራፍ ጨምሮ በርካታ ሥራዎችን የምሰራበት ይሆናል፡፡ እራሴ ፕሮዲዩስ የማደርገው አንድ ፊልምም ይኖረኛል፡፡ በተጨማሪም ከናይጄሪያ አክተሮችና ፕሮዲዩሰሮች ጋር የተለያዩ ስራዎችን የመስራት እቅድ አለኝ፡፡ ኢንትሪየር ዲዛይን (የቤት ውስጥ የማስዋብ ስራዎቼን) አጠናክሬ እቀጥላለሁ፡፡  

ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት የአዕምሮ ህመምተኞች የእንቁጣጣሽ ምግብ ሊበሉ በገበታ ዙሪያ ሆነው ይጨዋወታሉ፡፡
አንደኛው - አንድ ዕንቁላል ነው ያለው ማን ይብላት?
ሁለተኛው - ሁለት ላይ ማካፈል ነዋ በቃ
አንደኛው - ማን ይከፍለዋል?
ሁለተኛው - ወይ እኔ ወይ አንተ ነና
አንደኛው - እኔ አልገባበትም
ሁለተኛው - ለምን?
አንደኛው - በትክክል ዕንቁላሏን ሁለት እኩል ቦታ ለመክፈል አልችልም
ሁለተኛው - እንግዲያው እኔው ራሴ እከፍለዋለሁ
አንደኛው - ብትሳሳት ግን መልሰህ ትገጥመዋለህ - ዕወቅ
ሁለተኛው - እንደሱ ከሆነማ እኔም አልገባበትም!
አንደኛው - ታዲያ ምን እናድርግ?
ሁለተኛው - ዕጣ እንጣል
አንደኛው - ዕጣውን ማን ይፅፋል?
ሁለተኛው - ወይ እኔ ወይ አንተ ነሃ!
አንደኛው - እኔ አልገባበትም
ሁለተኛው - ለምን?
አንደኛው - ምልከት ብታረግበትስ?
ሁለተኛው - በደምብ ጠጋ ብለህ እየኛ!
ይህን ሲባባሉ አንድ መንገደኛ ያይ ኖሮ፣
“እንግዲህ ዕጣ እስክትጣጣሉ ድረስ‘ኮ ዕንቁላሉ ቀዘቀዘ” አላቸው፡፡
አንደኛው ብድግ አለና፤
“ዕጣ እማንጣጣለው በአንድ ጉዳይ ብቻ ነው”
መንገደኛው፤
“በምን?”
አንደኛው፤
“ያንተን መንጋጭሌ በማውለቅ!”
አለና መንገደኛውን አገጩን በቡጢ አነገለው!
*  *   *
ያለጉዳያችን ጣልቃ ስንገባ የሚገጥመን ነገር አይታወቅም፡፡ ራስን ችሎ በራስ ተማምኖ መጓዝ መልካም ነው፡፡ በአዲስ ዓመት የማያጠራጥር በምግብ ራስን መቻልን ይስጠን፡፡
በአዲሱ ዓመት ለትንሽ ለትልቁ ዕጣ የማንጣጣልበት እንዲሆንልን እንፀልይ፡፡
አዲሱ ዓመት የተሻለ ሹምና መልካም አስተዳደርን የሚሰጠን እንዲሆንልን እንመኝ፡፡
አዲሱ ዓመት ተስፋችን የሚለመልምበት፣ ከድርቅ የምንርቅበት ያድርግልን፡፡
አዲሱ ዓመት ፍትህ ርትዕ የሚሰፍንበት፣ የተዛባ የሚቃናበት ይሁንልን፡፡
አዲሱ ዓመት ከአምና የምንማርበት፣ የዘራነውን የምንለቅምበት፣ የወለድነውን የምንስምበት፣ ትምህርታችንን ይግለጥልን የምንልበት ይሁንልን፡፡ ከመጠምጠም መማር የሚቀድምበት፡፡ የተማረ የሚከበርበት ይሁንልን፡፡
አዲሱ ዓመት የማንወሻሽበት፣ ግልፅነትን የምናዳብርበት፣ ተንኮልን የምናስወግድበት ያድርግልን!
አዲሱ ዓመት ደግመን ደጋግመን ራሳችንን የምንመረምርበት፣ አንድነታችንን የምናይበት፣ ባህላችንን የምናከብርበት፣ በማንነታችን የምንኮራበት ያድርግልን፡፡
አዲሱ ዓመት አዲስ ትውልድ የምንኮተኩትበት፣ አበባ የምናሰባስብበት፣ ፍሬ የምንለቅምበት ይሁንልን፡፡
አዲሱ ዓመት ምሬት ወደ ምርት የሚለወጥበት እንዲሆን ያድርግልን!
ከሁሉም በላይ አዲሱ ዓመት የጊዜን አጠቃቀም የምናውቅበት፣ አርፍደን የማንፀፀትበትና “በጊዜ የመጣ እንግዳ እንደረዳህ ይቆጠራል” የሚለውን ተረት በቅጡ የምናጤንበት እንዲሆንልን፣ ትጋቱን ይስጠን!


           መልካም አዲስ ዓመት!

አመቱ የምርጫ አመት ነበር፡፡ ምርጫው በአፍሪካም እንኳን ቢሆን ከደረጃ በታች የሆነ፣ በዲሞክራሲ ስም ትልቅ ቀልድ የተቀለበት ውድድር ነበር፡፡ ይሄ በዓመቱ ውስጥ በመጥፎነቱ የተመዘገበ ነው፡፡ በሌላ በኩል በአብዛኞቹ የኦሮሚያ አካባቢዎች ወጣቱ ለመብቱና ለነፃነቱ ለመታገል የነበረው ቁርጠኝነት እንዲሁም አምባገነኖችን ለመሸከም ትከሻ እንደሌለው ያሳየበት ስለነበር በዚያ ምርጫ ውስጥ መግባቴ ልዩ ደስታን ሰጥቶኛል፡፡
በነዚህ በሁለቱ መሃል ነው እንግዲህ አመቱን ያሳለፍነው፡፡ አሁንም ለዴሞክራሲ የምናደርገው ትግል ይቀጥላል፡፡ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር የለውም፡፡ ህዝቡ ተቃዋሚን ለመምረጥ ችግር አልነበረበትም፡፡ የድምፅ ሌባን ለመጠበቅ ግን አልቻለም፡፡ ትልቁ ክፍተታች እሱ ነው፡፡ እንግዲህ ድምፁንም ለማስጠበቅ የሚችል ህዝብ ማደራጀት ይገባል ማለት ነው፡፡
ተቃዋሚው ግን የታሪክ ፈተናውን አሁንም አላለፈም፡፡ የትብብር ጥያቄ ላለፉት 40 ዓመታት ምላሽ አላገኘም፡፡ ይሄ ተቃዋሚው መስራት ያለበት ትልቁ የቤት ሥራ ነው፡፡ ያንን ካላደረገ የትም መድረስ አይቻልም፡፡ ይሄ በቅጡ ሊታሰብበት የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ የተቃዋሚው ትልቁ ፈተና እሱ ነው፡፡
በመጪው አዲስ ዓመት ተቃዋሚው ራሱን እንደገና ያደራጃል፣ ወደተባበረ ትግልም ይገባል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ተቃዋሚዎች ተባብሮ መታገልን መርጠው እንዲንቀሳቀሱ አደራዬ የጠበቀ ነው፡፡

    “ዘ ዊኪንድ” በሚል ቅፅል ስሙ የሚታወቀው  ድምጻዊ አቤል ተስፋዬ፣ ባለፈው ሳምንት በአለም ደረጃ በቢልቦርድ ምርጥ አልበሞች ሰንጠረዥ የ1ኛነትን ደረጃ በዚህ ሳምንትም አለምን እየመራ ይቀጥላል ተብሎ  እንደሚጠበቅ ተዘገበ፡፡“ቢዩቲ ቢሃይንድ ዘ ማድነስ” የተሰኘው አዲሱ የአቤል አልበም፣ ለገበያ በቀረበበት የመጀመሪያው ሳምንት በሽያጭ ብዛት መሪነቱን እንደሚይዝ ተገምቶ የነበረ ቢሆንም፣ ከተገመተው በላይ እንደተሳካለት ፎርብስ ዘግቧል፡፡ በ350 ሺህ የአልበም ሽያጭ አንደኛ እንደሚሆን የተገመተው የአቤል አልበም፣ በ412 ሺህ ያህል ተቸብችቧል፡፡ በአዲሱ አልበሙ ውስጥ የተካተቱት 12 ሙዚቃዎችም በያዝነው ሳምንት የቢልቦርድ 50 ምርጥ ሙዚቃዎች ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል፡፡ካለፉት ሰባት አመታት ወዲህ፣ በቢልቦርድ የምርጥ ዘፈኖች ሰንጠረዥ፣ በአንድ ሳምንት ሁለት ዘፈኖቹ፣
 ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ባለው ደረጃ ውስጥ የተካተቱለት የመጀመሪያው ወንድ ድምጻዊ አቤል ተስፋዬ ብቻ መሆኑን ቢል ቦርድ ገልጿል የሰሞኑን የአቤል ስኬት ሲዘግብም፤ በ57 አመታት የቢልቦርድ ሰንጠረዥ ታሪክ፣ አቤል በአንድ ሳምንት ውስጥ ብዙ ዘፈኖቹ፣ በምርጥ 100 ዘፈኖች ዝርዝር ውስጥ የተካተቱለት ስድስተኛው ድምጻዊ ነው ብሏል፡፡  ዘንድሮ፣ በአንድ ሳምንት ውስጥ፣ ከአቤል የአልበም ሽያጭ የሚበልጥ ሪከርድ ያስመዘገበ ድምፃዊ የለም - ከድሬክ በስተቀር፡፡ አመቱ የአቤል ተስፋዬ ነው ያለው ፎርብስ መጽሄት፤ የድምጻዊው የሙዚቃ ስራዎች የካናዳንና የአሜሪካን ሬዲዮ ጣቢዎች በስፋት መቆጣጠራቸውንና ከፍተኛ ተወዳጅነት ማትረፋቸውን ዘግቧል፡፡ የአቤል ዘፈን በአሜሪካ ሬዲዮ ጣቢያዎች በብዛት በመሰራጨት አቻ አልተገኘላትም፡፡ “ስድ” ቃላትን በሙዚቃዎቹ ውስጥ ይደጋግማል በሚል ትችት የሚሰነዘርበት አቤል ተስፋዬ፤ በሙዚቃዎቹ ኢትዮጵያዊኛ ቃና  ይንፀባረቃል የሚለው አስተያየት ከሁሉም በላይ እንደሚያስደስተው ገልጿል፡፡ በዘፈን መሃልም አልፎ አልፎ አማርኛ ያስገባል፡፡

     የታዋቂው የጫማ አምራች ኩባንያ “ሶል ሪበልስ” መስራችና ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵዊቷ የቢዝነስ ሰው ቤተልሄም ጥላሁን፤ በታዋቂው የአሜሪካ የቢዝነስ መጽሄት “ኳርትዝ” የአመቱ የአፍሪካ 30 ፈርቀዳጅ፣ የድንቅ ፈጠራ ባለቤቶች ዝርዝር ውስጥ ተካተተች፡፡ተቀማጭነቱን በአሜሪካ ያደረገው መጽሄቱ፤ ፈርቀዳጅ፣ አዲስ ሃሳብ አፍላቂና ለአካባቢያዊ ችግሮች ተስማሚ መፍትሄ የሚሰጡ ድንቅ ፈጠራዎችን አበርክተዋል ያላቸውንና ከ15 የተለያዩ የአፍሪካ አገራት የመረጣቸውን 30 ምርጦች ይፋ ባደረገበት ዝርዝር የ35 አመቷን ቤተልሄም አካትቷታል፡፡ከ10 አመት በፊት ቤተልሄም ያቋቋመችው “ሶል ሪበልስ”፣ በአሁኑ ወቅት አለማቀፍ ተፈላጊነትን ያተረፉ የጫማ ምርቶቹን ወደተለያዩ 30 የዓለማችን አገራት ኤክስፖርት እያደረገ መሆኑን የጠቆመው መጽሄቱ፤ ቤተልሄም ያመነጨችው የቢዝነስ ሃሳብ ብዙዎችን ተጠቃሚ ያደረገና ውጤታማ በመሆኑ በዝርዝሩ ውስጥ ልትካተት እንደቻለች ገልጿል፡፡

ዓመቱ ብዙ ሥራ የተሰራበት ነው፡፡ የንባብ ባህል በማሳደግ አቅጣጫ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ ሰኔ 30 የንባብ ቀን በመላው ኢትዮጵያ እንዲከበር አድርገናል፡፡ ቀኑም የንባብ ባህል ንቅናቄ ተምሳሌት ሆኖ ይታይ ዘንድ፣ በመንግስት በኩል ታስቦ እንዲውል ጥያቄ ያቀረብንበትም አመት ነው፡፡ የማህበሩ አባላት ወደተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየሄዱ ልምድ እንዲያካብቱ የተደረገባቸው ጉዞዎች ነበሩ፡፡
ለምሳሌ “የጥበብ ጉዞ ወደ ፀሃይ መውጫ ሀገር” በሚል ወደ ድሬደዋና ወደ ሃረር ያደረግነው ጉዞ ተጠቃሽ ነው፡፡ ወደ ህዳሴው ግድብም የተደረገ ጉዞ አለ፡፡ ባለፈው አመት ከበርካታ ዩኒቨርስቲዎች ጋር ማህበሩን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ አብረን ስንሰራ ከርመናል፡፡ የተለያዩ የሥነ ፅሁፍና የኪነጥበብ ዝግጅቶችንም አከናውነናል፡፡
ሌላውና ዋነኛው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለዘመናት የዘለቀ የትውልድ ጥያቄ መልሷል፡፡ ይኸውም የመሬት ጥያቄ ነበር፡፡ ወደ 3ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ተሰጥቶናል፡፡ በቦታው ላይ የኢትዮጵያ ደራሲያን መቀመጫ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ደራሲያን መቀመጫ ፅ/ቤት እንዲሆን አስበን ለመገንባት እቅድ አለን፡፡
በቀጣይ አመት የምናስበው በየክልሉ ያሉ ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶችን ማጠናከርና ማስፋፋት ነው፡፡ ከተማን መሰረት ያደረጉ ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶችን ወደ ክልል ፅ/ቤትነት ለማሳደግ ነው ያቀድነው፡፡ የንባብ ባህልን በሚመለከት በየኮንደሚኒየሞቹ የማስፋፋት አዲስ አይነት እቅድ አለን፡፡ በተንቀሳቃሽ ቤተመፅሃፍት አማካይነት ወደ ህብረተሰቡ እንደርሳለን ብለን እናስባለን፡፡ የአዲስ አበባውን ተሞክሮ ወስደን በክልሎችም እንተገብራለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በየዓመቱ የምናደርጋቸውን የመፃህፍት ኤግዚቢሽኖች አጠናክረን በክልሎች ጭምር እናካሂዳለን፡፡ የህንፃውን ግንባታ ሂደትም ወደ አንድ ምዕራፍ እናሸጋግራለን የሚል እምነት ነው ያለን፡፡