Administrator

Administrator

 ጆሃንስበርግ 23‚400፣ ካይሮ 10‚200፣ ሌጎስ 9‚100 ሚሊየነሮች አሏቸው
            አፍሪካ በድምሩ 670 ቢ. ዶላር ሃብት ያካበቱ 163 ሺህ ሚሊየነሮች አሏት

   የደቡብ አፍሪካዋ ጆሃንስበርግ በአፍሪካ አህጉር በርካታ ሚሊየነሮች የሚገኙባት ቀዳሚ ከተማ መሆኗን አፍርኤዥያ ባንክ እና ኒው ወርልድ ዌልዝ የተሰኙ ተቋማት ሰሞኑን ይፋ ያደረጉትን አህጉራዊ የጥናት ውጤት ጠቅሶ ቢቢሲ ዘገበ፡፡ “የወርቅ ከተማ” ተብላ የምትጠራው ጆሃንስበርግ፤ 23 ሺህ 400 ሚሊየነሮች የሚኖሩባት የአፍሪካ የባለጸጎች ከተማ መሆኗን የገለጸው ዘገባው፣ ደቡብ አፍሪካ በአህጉሩ ከሚገኙ ሚሊየነሮች 30 በመቶው የሚገኙባት አገር መሆኗንም አስታውቋል፡፡
10 ሺህ 200 ሚሊየነሮች ያሏት የግብጽ መዲና ካይሮ፤ በሚሊየነሮች ብዛት ከአህጉሩ ከተሞች ሁለተኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን 9 ሺህ 100 ሚሊየነሮች ያሏት የናይጀሪያዋ ሌጎስ ደግሞ ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች፡፡
ባለሃብቶቹ በዝርዝሩ ውስጥ ለመካተት ቢያንስ 1 ሚሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት ሊኖራቸው እንደሚገባ የጠቆመው ዘገባው፣ አፍሪካ በድምሩ 670 ቢሊዮን ዶላር ሃብት ያካበቱ 163 ሺህ ሚሊየነሮች እንዳሏትም አክሎ ገልጿል፡፡

 ጋዜጠኛ የደስደስ ተስፋ በቅርቡ ያሳተመው “እንጀራ ከመከራ” የተሰኘ የግጥም መድበል በዛሬው ዕለት ከቀኑ 9 ሰዓት በሀገር ፍቅር ትንሿ አዳራሽ ይመረቃል፡፡ በ72 ገፆች የተቀነበበው መድበሉ፤ በ25 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

  በዶክተር ምህረት ደበበ በተፃፈውና በቅርቡ ለንባብ በበቃው “ሌላ ሰው” የተሰኘ ልቦለድ መጽሐፍ ሃሳብ ላይ የአንባቢያን ውይይትና የመጽሐፍ ማስፈረም ዝግጅት ዛሬ ከቀኑ 9፡30 ጀምሮ በደሳለኝ ሆቴል ይካሄዳል፡፡ መጽሐፉም ለሽያጭ ይቀርባል ተብሏል፡፡ ደራሲው ከዚህ ቀደም “የተቆለፈበት” የተሰኘ በተደጋጋሚ የታተመ ልብ ወለድ መጽሐፍ ለንባብ ማብቃቱ ይታወሳል፡፡

     ክሮሲንግ ባውንደሪ” የተሰኘ ዓለም አቀፍ የትውን ጥበባት ፌስቲቫልና ጉባኤ በመጪው መስከረም ወር አጋማሽ ላይ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ የቲያትር ባለሙያዎች ማህበር አስታወቀ፡፡
በፌስቲቫሉ ላይ ከሐገር ውስጥ 9 ትያትሮች የሚቀርቡበት ሲሆን ከውጪ ሀገራትም ከአፍሪካ  እንዲሁም ከአሜሪካና ከእስራኤል የሚመጡ የቴአትር ቡድኖች ስራዎቻቸውን እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል፡፡ ፌስቲቫሉ በክውን ጥበባት ላይ የሚካሄድ ዓለም አቀፍ ጉባኤንም ያካትታል ተብሏል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ በሚካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይ ከተለያዩ ሀገራት የተጋበዙ የዘርፉ ምሁራን ጥናታዊ ፅሁፎችን እንደሚያቀርቡ ተጠቁሟል፡፡
በፌስቲቫሉ ላይ የሚካፈሉት ትያትሮች በብሄራዊ ቴአትር፣ በሀገር ፍቅር፣ በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ፣ በኦሮሞ ባህል ማዕከል፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴዝና በአስኒ አርት ጋለሪ ለዕይታ ይቀርባሉ፡፡
የትውን ጥበባት ፌስቲቫሉን የኢትዮጵያ የቲያትር ባለሙያዎች ማህበር፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከብሄራዊ ቴአትርና ከሰንዳንስ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር እንዳዘጋጁት ለማወቅ ተችሏል፡፡

Saturday, 05 September 2015 10:03

ገጣሚ ወንድዬ አሊ ስለ ግጥም…

“የአገራችን ግጥም በተስፋና በፅልመት መካከል ያለ ግራጫ ሆኖ ይታየኛል!”
             እንባና ሳቅን አሥማምቶ፣ ያለ ሸንጎና ፍርድ በሀረጋትና ስንኞቹ ትከሻ ለትከሻ ትቅቅፍ ህይወትን አዲስ የሚያደርግ ሰው - ገጣሚ ነው፡፡ ሰማይና ምድርን አሳስሞ ባንድ መኝታ ላይ የሚያጋድም ተዓምረኛም እንደዚሁ … ገጣሚው ነው፡፡ የመላዕክት ክንፎችን ላንብብ፣ የእግዜርን ጓዳ ልፈትሽ ብሎ መጋረጃ ገለጣ የሚደፍር ገጣሚ ነው፡፡
የጠፋን ነገር አሥሶ፤ የራቀን ነገር አቅርቦ የሚያሳይ ንሥር ዓይን ያለው ገጣሚ ከአደባባይ ሲጠፋ፣ … “የት ገባ?” ማለት ያገር ነው፡፡ “የወፌ ቆመች” እና የ “ውበት እና ህይወት” የግጥም መጽሐፍት አባት የሆነው ወንድዬ ዓሊ-የት ጠፋ? የአዲስ አድማስ ፀሐፊና ሃያሲ ደረጀ በላይነህ፣ ከገጣሚ ወንድዬ ዓሊ ጋር በሕይወቱና በግጥም ጥበብ ዙሪያ ተከታዩን ውይይት አድርገዋል፡፡

    ወንድዬ፡- ከአሥር ዓመታት በላይ በግሌ እየሰራሁ ነው፤ ቤቴ ቢሮዬም ሆኗል፡፡ ሥራ ለመቀበል፣ ለማስረከብም ካልሆነ ወይንም የጥናት ወረቀት ከሌለ በስተቀር ከቤቴ አልወጣም፡፡ በየቀኑ ከ12 - 16 ሰዓታት ድረስ እሰራለሁ፤ ይኼ አሰረኝ፡፡ በተለይ ደግሞ ሥነ ጽሑፍ የሕይወትህ ጥሪ - እንጀራህም ሲሆን የበለጠውን እርጋታና ፀጥታ ፍለጋ ከአደባባይ ትጠፋለህ፡፡
በጠፋህባቸው ዓመታት ምን ምን ሰራህ ታዲያ?
በትምህርት (ሙያዬ ልበል ይሆን) ደረጃ ኮሚዩኒኬሽን አጠናሁ - በማስተርስ ደረጃ፡፡ በዚህ ረገድ ከበራሪ ወረቀቶች አንስቶ እስከ ትልልቅ ጥናቶችና መጻሕፍት ዝግጅት ድረስ (እንደ ደንበኞቼ ፍላጎት) ስሰራ ከረምኩ፡፡ አጫጭር ዘገባዊ ፊልሞችም አሉ፣ ሦስት አራት የሚሆኑ፡፡ ይዘታቸውን በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ (ኤችአይቪ፣ የሴት ልጅ ግርዛት፣ የልጆች አስተዳደግ፤ የህይወት ክህሎት) እስከ ግለታሪክ ዝግጅቶችና ህትመቶችን ይጠቀልላሉ፡፡ ለነገሩ ኮሚዩኒኬሽን ስትማር ብፌ እንደተመገብክ ቁጠረው፣ ሳይኮሎጂው፣ ስነ ሰብዕ (Anthropology)፣ ስነ - ጽሁፍ እንዲሁም ወደፍልስፍናና አንዳንድ ደረቅ ሳይንሶችም ትጠጋለህ፡፡ ልባም ከሆንክ በንባብና ጥናት አሳድገህ ባለብዙ ፈርጅ ባለሞያ ትሆናህ፡፡ ይህ ደግሞ ኮሚዩኒኬሽን በመማር የሚገኝ ትሩፋት ብቻ ሳይሆን የምንማርበት ተቋም ሥርዐተ ትምህርት፣ የመምህራኑ አቅምና መሰጠት እንዲሁም ተማሪዎች በትምህርት ቤት ቆይታቸው እውቀትን ለመበዝበዝ ባላቸው ዝንባሌና ጥረት የሚወሰን ይሆናል፡፡
አንዳንድ ሰዎች ጠነን ያለ፣ ምናባዊ ሸጋ ቋንቋ የሚጠቀም ገጣሚ ነው - ይሉሃል፡፡  ምን ዓይነት ግጥሞች ነው የምትወድደው?
ከስነ ግጥም ዓይነቶች ይልቅ የሚገደኝ ምንጫቸውና አፈጣጠራቸው ነው፡፡ ሰይፉ መታፈሪያ፤ “ግጥም ምንጩ ግለሰባዊ፣. ባፈጣጠሩ ዐይነ - ልቡናዊ፣ ባቀነባበሩ ጭምቅ፣ በቋንቋው ስልታዊ ነው” የሚለው አባባላቸው ይጥመኛል፡፡
ጋሼ ጸጋዬ ደግሞ ማቲው አርኖልድን ጠቅሶ፤ “ሥነ ግጥም ያው የገዛ ሕይወቱ ሂስ ነው” ይላል፡፡ ይህም ግሩም ነው፡፡ ሥነ ግጥም የገዛ ህይወት ሂስ ከመሆኑ ጋር የምደምረው ቁም ነገር አለኝ፤ ይኸውም ከደበበ ሰይፉ የተማርኩት ነው፡፡ “ባድማ ልቡን አድምጦ የሚጽፍ ጸሐፊ ከማህበረሰቡ የተጣላ ነው፡፡” የሚለውን አነጋገሩን እወድለታለሁ፡፡
ከጸጥታና እርጋታ ባሻገር በራስህ ዓለሙን ረስተህ፣ ዓለሙም አንተን ሸጉሮብህ (ቀርቅሮብህ) የምትጽፈው ግጥም የምድረበዳ ምኞት ዓይነት ነው፡፡ በጠየቅኸኝ መሰረት፤ ባብዛኛው የምወደው የግጥም ዓይነት ምሰላን ትርጉም ያላቸውን ይመስለኛል፡፡ የአንድ ቀን ክስተት ተንተርሰው የሚገጠሙ የአዝማሪ ዓይነት ግጥሞችን ብዙም አልወድም፡፡ የአንድ ቀን ገጠመኝ ግን ወደ ህይወት ምሰላ ተለውጦ፣ ሁለንታዊነትን ተላብሶ፣ ሳነብበው ደስ ይለኛል፡፡ ውበት እና ሕይወት ውስጥ “በጥላዬ” የሚለውን ግጥም የጻፍኩት ኃይሌ ገብረስላሴ በኦሎምፒክ መድረክ አንደኛነቱን ለቀነኒሳ ባስረከበበት ቀን ውድድሩን በቴሌቪዥን ካየሁ በኋላ ነበር፡፡ ግና በግጥሙ ውስጥ ኃይሌም ቀነኒሳም የሉም፣ ህይወት ግን ነበረች፡፡ እኔም ነበርኩ፡፡
“ጥላዬ”
የቀደመው ቀረ
   ጀማሪው ፊተኛ
   ፊተኛው ከኋላ
   የኋላው አንደኛ፡፡
    ያልዘቀጠው ወጣ
    የወጣው ዘቀጠ፡፡…
ፊት የወጣች ፀሐይ
    በ-ምዕራብ ሰማይ
    መጥለቂያው በር ላይ፡፡
አዲሷ ከምሥራቅ
    በንጋት አልፋ ላይ
በማለዳ ‘ርከን ላይ፡፡
    እርከኑ እስቲሰበር
    በጭለማ በትር፡፡
የቀደመው ሲቀር፣
የወጣው ሲዘቅጥ፣
ምዕራብ ሲጠልቅበት፣
ጐህ ሲቀድ ለምሥራቅ፣
እነሱን ሲታዘብ … በወጣ … ዘቀጠ
ከገቡበት መቅረት
ከወጡበት መግባት
እንዴት ባመለጠ!?
“ውበትና ሕይወት”ን ካሳተምክ ዘጠኝ ዓመታት አለፉ፤ አሁንስ ግጥም፣ ትጽፋለህ?
ባልጽፍማ ሞቼአለሁ ማለት ነው፡፡ “ውበት እና ሕይወት” በ1998 ዓ.ም ታተመች፡፡ “ወፌ ቆመች” ረቂቁ ለኩራዝ አሳታሚ ድርጅት የተሰጠው በ1982 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ነበር፡፡ የታተመችው በ1984 ዓ.ም ይመስለኛል፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮተቤ የመምህራን ትምህርት ኮሌጅ እንደተጨማሪ ማስተማሪያ ሆነች፡፡
“ወፌ ቆመች ቅጽ 2 (ውበት እና ህይወት)” ስትታተም ድፍን አገሩ በነፃ ፕሬሶች የተጥለቀለቀበት ጊዜ ነበር፡፡ ስለዚህ ድምፅዋ ሳይሰማ ከገበያ ጠፋች፤ ተሸጠች፡፡ አዳዲሶቹን ግጥሞች “ወፌ ቆመች ቅጽ 3” ለማሳተም የዘመኑን ነገር እያደባሁ ነው፡፡
በዚህ ዘመን በግጥም ሥራዎች ረገድ ምን ገረመህ?
ያልተዘመረላቸው ጀግኖች እንዳሉ ሁሉ ያልተዘመረላቸውም መጻህፍት መኖራቸው! … የኔ መጽሐፍ “ውበት እና ሕይወት” እንኳ በጎምቱ አንባቢዎች እጅ ብቻ ገብታ ለአዲሱ ዘመን ገጣሚያን የስልትና የፍልስፍና ግብዐት ሣትሆን ልሂቃን ልብ ውስጥ መቅረቷ ገርሞኛል፡፡ ጥቂት የተጠቀመበትና ወደ ቀጣዩ ትውልድ ልብ ያሻገራት ሟቹ ብርሃኑ ገበየሁ ብቻ ይመስለኛል፡፡ በነገራችን ላይ የሥነ - ግጥምን ጥበብ የሚመለከት “ወፌ ቆመችን እንደ ዘሪሁን አስፋው (የሥነ ፅሁፍ መሰረታዊያን በሚለው መጽሐፍ) “ውበት እና ህይወት”ንና “ወፌ ቆመች” ን አዳብሎ በመተንተን እንደ ብርሃኑ ገበየሁ ያሉ ምሁራን አላገጠሙኝም፡፡
“ፎክር ፎክር አለኝ”
ፎክር!
ፎክር!
    አለኝ፣
ነዘረኝ
ነሸጠኝ
ፎክር - ፎክር አለኝ፣
    ሽለላ - ሽለላ፣
አለ ይሆን ዛሬ
    ግብር የሚበላ!? …
ፎክር
ፎክር
አለኝ፡፡
እንዴ …. !
በነ አባጃሎ አገር
በጀግኖቹ ጎራ፣
ገዳይ በጎራዴ
ገዳይ በጠገራ፡፡
በሾተለ አንደበት
    ገዳይ በአፈር ሳታ፣
በነገር ነጎድጓድ
            ገዳይ በቱማታ፤ …
በነዘራፍ ስንቁ
    ባለ ብር ሎቲ፣
በተሞላች አገር ፡-
ጅረት ባበጀባት
ዘንቦ የደም ዕምባ፤
ተራህ ነው ይለኛል፣
ተሠራ ሹርባ፡፡
በአማርኛ ሥነ ግጥም ምን ይታይሃል?
በተስፋና በፅልመት መካከል ያለ ግራጫ ነገር ሆኖ ይታየኛል፡፡
(ይቀጥላል)

Saturday, 05 September 2015 09:55

የግጥም ጥግ

 የዕንቁጣጣሽ አበባ!

           -ነ.መ.
አንዳንድ ህፃን ዕድሏ፣
ያስታውቃል ከብቅሏ
አበቅቴዋ አይስትም ውሉን
ለእንቁጣጣሽ ልትወለድ፣ ተፅፏል ቃሉ
  ቀድሞውን!
በአበባ ወር የመጣች፣ የዕንቁጣጣሽ አበባ
ትስቃለች ታለቅሳለች - ፣
      የዕድሏን ያህል ለዕማማ!
    የዕድሏን ያህል ለአባባ!!
እንኳን መጣሽ አንች አበባ፣
እንኳን መጣሽ አንች ወለባ!
የጎመንም፣ የገንፎሽም፤ ምንቸቱ
       አንቺው ቤት ይግባ!!
(ለኪዳኔና ለጤና አዲሷን
የዕንቁጣጣሽ
አበባይቱን ለሚቀበሉ፣
ልጆቻቸው ሁሉ)
                 - ነሐሴ 29 2007 ዓ.ም.

Saturday, 05 September 2015 09:54

የኪነት ጥግ

ዝነኛ ስትሆን ድክመትህ ሁሉ የሚጋነን ይመስለኛል፡፡
ማሪሊን ሞንሮ
ዝነኛ መሆን ሳይሆን ስኬታማ መሆን ነበር የምፈልገው፡፡
ጆርጅ ሃሪሰን
ዝነኞች ዕድሜ ልካቸውን ታዋቂ ለመሆን ሲለፉ ኖረው በኋላ ላይ እንዳይታወቁ ፊታቸውን በጥቁር መነፅር የሚሸፍኑ ሰዎች ናቸው፡፡
ፍሬድ አለን
የዝነኛ አማካይ የህይወት ዘመን በከሰል ማዕድን ማውጪያ ውስጥ ከሚሰራ ሰው በ20 ዓመት ያንሳል፡፡
ሞቢ
ምን መስራት እንደምፈልግ ብትጠይቁኝ - ዝነኛ መሆን አልፈልግም፤ እኔ የምሻው ትርጉም ያለው ለውጥ መፍጠር ነው፡፡
ሌዲ ጋጋ
የእኔ የስኬት መለኪያ ገንዘብ ወይም ዝነኝነት አይደለም፡፡ የስኬት መለኪያዬ ደስተኛነት ነው፡፡
ሉፔ ፊያስኮ
ዝነኛ ስትሆን ዓለም አንተንና መልካም ስምህን የራሱ ንብረት ያደርገዋል፡፡
ሜጋን ፎክስ
በመጀመሪያ የእግዜአብሔር ልጅ ነኝ፡፡ ዝነኛ ከመሆኔ በፊት የተጠመቅኩ ክርስትያን ነኝ፡፡
Mr.t
ወደፊት ሁሉም ሰው ለ15 ደቂቃ ዝነኛ ይሆናል
አንዲ ዋርሆል
ዝነኛ የመሆን አስከፊው ነገር የግል ህይወትህ መጣሱ ነው፡፡
ጀስቲን ቲምበርሌክ
ብዙ ባጨበጨቡ ቁጥር ደሞዝህ ያድጋል
አና ኸልድ

Saturday, 05 September 2015 08:53

የፀሐፍት ጥግ

(ስለ ግጥም)
- ግጥም በደስታ ተጀምሮ በጥበብ
ይቋጫል፡፡
ሮበርት ፍሮስት
- ማንኛውም ጤነኛ ሰው ያለ ምግብ
ለሁለት ቀ ናት ሊ ቆይ ይ ችላል፡፡ ያ ለ
ግጥም ግን አይሞከርም፡፡
ቻርለስ ባውድሌይር
- ለእኔም ለራሴ የማይገቡኝ ጥቂት
ግጥሞችን ፅፌአለሁ፡፡
ካርል ሳንድበርግ
- ሙዚቃን መተርጎም እንደማይቻል
ሁሉ፣ ግጥምንም መተርጎም
አይቻልም፡፡
ቮልቴር
- ለእኔ ግጥም ዓላማ ሆኖ አያውቅም፤
ፍቅር እንጂ፡፡
ኤድጋር አላን ፖ
- ዓይን የገጣሚ የማስታወሻ ደብተር
ነው፡፡
ጄምስ ረስል ሎዌል
- ግጥም የተጣራ ህይወት ነው፡፡
ግዌንዶሊን ብሩክስ
- ግጥም ከብርሃኑ መጨረሻ ያለው ዋሻ
ነው፡፡
ጄ. ፓትሪክ ሌዊስ
- ግጥም ል ክ እንደ ጨ ረቃ ም ንም ነ ገር
አያስተዋውቅም፡፡
ዊሊያም ብሊሴት
- ግጥም ሁሉ ቦታ አለ፤ የሚፈልገው
አርትኦት ብቻ ነው፡፡
ጄምስ ታት
- ግጥም ፈጠራ ነው፤ ገጣሚነት ዓለምን
ዳግም መፍጠር ነው፡፡
አሌክሳንድሬ ቪኔት
- ጸሎትህ ግጥም፤ ግጥምም ፀሎትህ
ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ቴሪ ጉይሌሜትስ
- ግጥም ግግር እሳት ነው፡፡
ጄ. ፓትሪክ ሌዊስ
- ግጥም ቢያንስ ውበት፤ ቢበዛ ራዕይ
ነው፡፡
ሮበርት ፊትዝጌራልድ
- በግጥም ትቀሰቅሳለህ፤ በስድ ፅሁፍ
ታስተዳድራለህ፡፡
ማርዮ ኩርኖ
- ግጥም ሙያ አይደለም፤ እጣ ፈንታ
ነው፡፡
ሚክሃዬል ዱዳን
- ገጣሚያን ዕውቅና ያልተሰጣቸው
ዓለም ህግ አውጪዎች ናቸው፡፡
ፔርሲ ባይሺ ሼሊይ

የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር፤ ከ900 በላይ የቤተ ክርስቲያኒቱን ልኡካን እያወያየ ነው
“እንደ ሌላው መድረክ አታስቡት፤ ለዓላማና ለለውጥ የሚደረግ ጉባኤ ነው” /ሚኒስትሩ/

      በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ንብረቶች አላግባብ ሀብት ያፈሩና ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለምዝበራ ያጋለጡ የአድባራት ሓላፊዎች ጉዳይ በሕግ እንዲታይ የቀረበውን ውሳኔ ቋሚ ሲኖዶስ አጸደቀ፡፡
በሙሰኛ የአድባራት ሓላፊዎች ላይ ለተላለፈው ውሳኔ መሠረት የኾነውንና በ58 አድባራት የገቢ ማስገኛ ተቋማት ዙሪያ በሚታዩ የአፈጻጸም ችግሮች ላይ የተዘጋጀውን ጥናታዊ ሪፖርት ያዳመጠው ቋሚ ሲኖዶሱ፣ የመፍትሔ ሐሳቦቹንም በሙሉ ድምፅ ተቀብሎ ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ ተጨማሪ መመሪያዎችን ሰጥቷል፡፡
ለቤተ ክርስቲያኒቱ መገልገያነት ከመንግሥት የተሰጡ መሬቶች፣ የተገነቡ ሕንጻዎች፣ ሱቆች፣ መካነ መቃብርና ሌሎች የገቢ ማስገኛ ተቋማት ሕጋዊ፣ ፍትሐዊና ቤተ ክርስቲያኒቱን ተጠቃሚ በማያደርጉ ውሎች ለሦስተኛ ወገን እየተከራዩ ለግለሰቦች በመሸጥ ላይ እንደኾኑ ጥናታዊ ሪፖርቱ ይዘረዝራል፡፡የአድባራት ሓላፊዎች ጥፋት በሕግ አግባብ እየታየ ክሥ ለመመሥረትም፤ ጥናቱ በሸፈናቸው አድባራትና ገዳማት የተደረጉ ሕገ ወጥ ውሎች የተፈጸሙበትን ትክክለኛ ጊዜ፣ የወቅቱን የአካባቢ የመሬት ዋጋ፣ በውል አሰጣጡ የተሳተፉ ሓላፊዎችና የመሳሰሉት ዝርዝር መረጃዎች በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ተጣርተው መታወቅ እንደሚገባቸው ቋሚ ሲኖዶሱ ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ ተጨማሪ መመሪያ ሰጥቷል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ የሀገረ ስብከቱን የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ማኅበረ ካህናት፣ ሰባክያነ ወንጌል፣ የሰንበት ት/ቤቶች ሊቃነ መናብርት እና የአንድነት አመራሮች በተናጠል ሲያነጋግር የቆየው የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ ከትላንት ጀምሮ ኹሉንም አካላት ያቀፈ የማጠቃለያ ውይይት በማካሔድ ላይ ነው፡፡
937 ያኽል የቤተ ክርስቲያኒቷ ልኡካን በሚሳተፉበት በዚኹ የኹለት ቀናት ውይይት፣ በሃይማኖት ተቋማት የውስጥ አሠራር ችግሮች ላይ ያተኰረ ጽሑፍ በሚኒስትሩ ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም የቀረበ ሲኾን በቡድንና በጋራ ውይይት ይካሔድበታል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀደምትና ጥንታዊት መኾኗን ያወሱት ሚኒስትሩ÷ በአካባቢና በጥቅመኝነት ላይ የተመሠረተ የሰው ኃይል አሿሿምና አመዳደብ፣ ግልጽነት በጎደለው የፋይናንስ ዝውውርና አጠቃቀም በውስጥ የሚነሣው አለመግባባት እየሰፋ መምጣቱ ጥያቄ እያስነሣ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
እኔ ብቻ ልጠቀም በሚል ከሕግና ሥርዐቱ ውጭ የመንቀሳቀስ ስሜት በራሱ የሚፈጥረው አደጋ እንዳለ ያሳሰቡት ዶ/ር ሺፈራው፣ መድረኩም እንደሌላው መርሐ ግብር የሚታይ ሳይኾን ለዓላማና ለለውጥ የሚካሔድ የምክክር ጉባኤ ነው በማለት ውይይቱን ተከትሎ በተከታይ ሊወሰድ የሚችል ርምጃ እንደሚኖር ጠቁመዋል፡፡

ከፍተኛው የሆቴሎች ዋጋ ጭማሪ የታየው በሻርም አል ሼክ ነው

   ኤስ ቲ አር ግሎባል የተባለው አለማቀፍ የጥናት ተቋም በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ከተሞች የሆቴሎች ዋጋ ዙሪያ ባደረገው ጥናት፤ አዲስ አበባ በሆቴሎች ዋጋ ውድነት ቀዳሚውን ደረጃ መያዟን ትናንት ባወጣው ሪፖርት መግለጹ ተዘገበ፡፡
ተቋሙ ይፋ ባደረገው የጥናት ውጤት፤ ባለፉት ስድስት ወራት በአዲስ አበባ ሆቴሎች ለአንድ መኝታ ክፍል ለአንድ ቀን አዳር በአማካይ 231.78 ዶላር ሲከፈል መቆየቱን ጠቁሞ፤ ይህም የከተማዋ ሆቴሎች ዋጋ ከሌሎች የአፍሪካ ሆቴሎች የበለጠና እጅግ ውዱ መሆኑን እንደሚያሳይ ጋና ቢዝነስ ኒውስ ድረገጽ ዘግቧል፡፡
የናይጀሪያዋ ሌጎስ 215.75 ዶላር፣ የኬንያዋ ናይሮቢ 144.76 ዶላር፣ የደቡብ አፍሪካዋ ኬፕታውን 122.30 ዶላር ለአንድ አዳር በማስከፈል እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውንም ዘገባው ጠቁሟል፡፡የአገሪቱ ኢኮኖሚ ላለፉት አስር ያህል አመታት በአማካይ ከ10 በመቶ በላይ ዕድገት ማስመዝገቡ፣ የተለያዩ አለማቀፍ ጉባኤዎችን ማስተናገዷ፣ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ መሆኗ እና በእድገት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመዳረሻዎቹንና የተሳፋሪዎቹን ቁጥር ማሳደጉ፣ በአገሪቱ የዘመናዊ ሆቴሎች ፍላጎት እንዲጨምር አድርጓል ያለው ጥናቱ፣ ይሄም ሆኖ ግን አዲስ አበባ አሁንም ድረስ ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያላቸው ሆቴሎች እጥረት አለባት ብሏል፡፡ባለፉት 12 ወራት በአፍሪካ የተለያዩ ከተሞች የታዩ የሆቴሎች ዋጋ ጭማሪዎችን የዳሰሰው ጥናቱ፣ በተጠቀሰው ጊዜ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የታየው በግብጹ የመዝናኛ ስፍራ ሻርም አል ሼክ መሆኑን ጠቁሞ፣ የዋጋ ጭማሪውም 42.5 በመቶ እንደሆነ ገልጿል፡፡በተጠቀሰው ጊዜ በሆቴሎች ዋጋ ላይ አዲስ አበባ የ14.9 በመቶ፣ ጆሃንስበርግ የ11 በመቶ፣ ኬፕታውን የ10.8 በመቶ ጭማሪ ማድረጋቸውንና በአንጻሩ ግን የካዛብላንካ ሆቴሎች ዋጋ በ4 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን አስታውቋል፡፡