Administrator

Administrator

እውነቱ ማውጣት፣ ተጎጂዎችን መካስና የወንጀለኞችን ተጠያቂነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ተገልጿል። የሚዲያ ባለሙያዎች  አገራዊ መግባባቱን ሊያሣኩትም ሊያፈርሱትም ይችላሉ ተብሏል
የሽግግር ፍትህ ሂደቱ በማህበረሰቡ መሃከል የሚኖረውን ስንጥቅ የሚደፍን መሆን አለበት።
በኢትዮጵያ በቅርቡ  ተግባራዊ መደረግ ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው የሽግግር ፍትሕ፤ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን ፤ ግጭትን ወደእርቅ ለመለወጥና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚያስችል ለማድረግ ቁርጠኝነት ሊኖር እንደሚገባና ሂደቱ በገለልተኛ ወገን ሊከናወን እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት አስታወቀ ምክር ቤቱ  “ ለሽግግር ፍትህ ስኬት የሚዲያ ሚና በኢትዮጵያ “  በሚል ርዕስ ትናንት ለሚዲያ ባለሙያዎች  ባዘጋጀው ውይይት ላይ በቀረበው ጥናታዊ ፅሁፍ እንደተገለፀው የተድበሰበሰ የፍትህ ስርዓት የሽግግር ፍትሁን ሊያሣካ አይችልም ተብሏል። ለሠላም ሲባል ብቻ ፍትህን ጨፍልቆ እርቅ እንዲፈጸም  ማድረግ ተጠያቂነትን እንደማያረጋግጥና ነገ ተመሣሣይ ጥፋቶች ላለመፈጸማቸው ዋስትና አይሰጥም ተብሏል ።
ይህ ሁኔታዎች ሰዎች ጥፋት ፈጽመው ከተጠያቂነት ማምለጥ እንደሚችሉና ያለመጠየቅ ዕድሎች እንዳሉ  አመላካች እንደሆነም ተገልጿል። ይህ አሰራር እንደማያወጣና ውጤት እንደሌለው  በ2009 ያደረግነው ጥቅል የምህረት አሰጣጥ ስርአቶች ጥሩ ማሣያዎች ናቸው ተብሏል። ለሽግግር ፍትህ ሂደቱ  የተለያዩ አማራጮችን ለማየት እንደተሞከረ የተናገሩት ጥናታዊ ፅሁፍ አቅራቢው አቶ ዘላለም   ሁሉን አቀፍ  አፕሮች የተባለው መንገድ የተሻለ መሆኑንና ይህ መንገድ የዜጎችን እውነቱን የማወቅ መብት የሚያከብር ፣ የሕግ የበላይነትን የሚያስከብርና ወንጀለኞች ለፍትህ እንዲቀርቡ የሚያደርግ ተጎጂዎችን የሚክስና ዘላቂ ሰላም የሚያሰፍን መንገድ ነው ።
ይህ መንገድ እውነት ማውጣትን ካሣንና እርቅን አጠቃሎ የያዘ ሁሉን አቀፍ መንገድ ነው ብለዋል።

በመንግስት ተቋማቱ ጫና አገልግሎቱን ለማቆም ተገደናል - የማዕከሉ መስራች
“ከገባነው ውል ያጎደልነው የለም” - አዲስ አበባ ጤና ቢሮ እና ምንሊክ ሆስፒታል


ከሁለት ዓመት በፊት በኢትዮጵያዊቷ ዲያስፖራ ትዕግስት አበበ፣ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮና በዳግማዊ ምንሊክ ሆስፒታል ትብብር ለኩላሊት ታማሚዎች ነፃ የኩላሊት እጥበት አገልግሎት መስጠት የጀመረው የአብ ሜዲካል ሴንተርና ሪሀብሊቴሽን ሊሚትድ አገልግሎት መስጠት በማቆሙ ህይወታቸው ለአደጋ መጋለጡን ችግር ላይ መውደቃቸውን ታካሚዎች ለአዲስ ድማስ ገለፁ።
ህይወታችንን ለማቆየት ትግል ላይ በነበርንት ወቅት አብ የኩላሊት እጥበት ማዕከል ተከፍቶ እፎይ አልን ስንል  “የግብአት እጥረት አጋጥሟል” በሚል ማዕከሉ አገልግሎት መስጠት ካቆመ ሶስት ሳምንት አልፎታል ያሉት ታካሚዎች፤ ግማሾቻችን ወደ ልመናና ወዳጅ ዘመድ ማስቸገር፣ ከፊሎቻችን የቀረችንን ጥሪት ወደ መሸጥ፣ ይህን ያልቻልን ፊታችን ከተደቀነው ሞት ጋር መፋጠጥ ዕጣ ፈንታችን ሆኗል ሲሉ አማርረዋል።
“ወዳጅ ዘመድ የሚደግፈን ወደ ግል የኩላሊት እጥበት ማዕከል አገልግሎት ፍለጋ ስንሄድ፣ ከምኒልክ ከመጣችሁ አናስተናግድም የሚል ተግዳሮት እየገጠመን ነው” ሲሉ ከወጣት እስከ ዛውንት የእድሜ ክልል የሚገኙ የማዕከሉ ተጠቃሚ ታካሚዎች ለአዲስ አድማስ ገልጸው፤ የሚመለከተው የመንግስት አካል አስቸኳይ መፍትሄ ይስጠን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። በዳግማዊ ምንሊክ ሆስፒታል ገቢ ውስጥ የሚገኘውና በአንድ ጊዜ 30 ታካሚዎችን የማስተናገድ አቅም ያለው ማዕከሉ፤ ላለፉት ሁለት ዓመታት ለ120 ታካሚዎች ነፃ የኩላሊት እጥበት አገልግሎት ሲሰጥ እንደነበር የሚገልፁት የማዕከሉ መሥራች ትዕግስት አበበ፤ ለማዕከሉ ታካሚዎች፤ አገልግሎት  መስጠት ካቆመ ሦስት ሳምንታት ማስቆጠሩንና በዚህ ሳቢያ ከሞት ጋር ትንቅንቅ የገጠሙ ታካሚዎች እንዳሉ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል።
“ሳይንሱ የሚያዘው አንድ ኩላሊት እጥበት የጀመረ ታካሚ በሳምንት ሶስት ቀን ዲያሊሲስ ማድረግ እንዳለበት ነው ያሉት ታካሚዎቹ፤ “ይህ ማዕከል ከመከፈቱ በፊት በግል የኩላሊት እጥበት ማዕከላት አገልግሎት ለማግኘት በወር እስከ 40ሺህ ብር ለመክፈል ቤት ንብረት ከመሸጥም ባለፈ ወዳጅ ዘመድ እያስቸገርን፤  የሌለን  ደግሞ ጎዳና ወጥተን እየለመንን ነበር” ብለዋል።
ማዕከሉ ምን ችግር ገጠመው በሚል ትላንት ረፋድ ወደ ምንሊክ ሆስፒታል አቅንተን የማዕከሉ መስራች  ትውልደ ኢትዮጵያዊቷን ትዕግስት አበበን ጠይቀን  ታካሚዎቹ በነፃ በሰጡን ምላሽ፤  ላለፉት 2 ዓመታት 120 ታካሚዎች በነጻ ኩላሊታቸውን በሳምንት ሶስት ቀን  እንዲታጠቡ  በማድረግ መቆየታቸውን ይናገራሉ።  ኑሯቸውን ለረጅም ዓመታት በአትላንታ ጆርጂያ ያደረጉት የማዕከሉ መስራች ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የጤና ባለሙያ፤ በዚሁ የህክምና ዘርፍ መቆየታቸውን ገልፀው፣ ለ19 ዓመታት በሜዲካል ሚሽን ትሪፕ ወደ አገራቸው እየመጡ እያገለገሉ ይመለሱ እንደነበር፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ዲያስፖራው ማህበራሰብ ባለው አቅምና ሙያ ሀገሩን እንዲደግፍ ባደረጉት ጥሪ መሰረት፣ በፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሽፕ ይህን ማዕከል በመክፈት ወገንን ለማገልገል ሙያቸውን ይዘው እንደመጡ ይናገራሉ።
ከዚም በኋላ በክብርት ከንቲባዋ አዳነች አበቤ ትብብር ጉዳዩ ተቀላጥፎ ከሁለት ዓመት በፊት በ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር ማዕከሉ ደረጃውን ጠብቆ መከፈቱን 60 ያህል ሰራተኞች መቅጠሩንና አዲስ አበባ ጤና ቢሮና ዳግማዊ ምንሊክ ሆስፒታል አስፈላጊውን ድጋፍ ባለማድረጋቸው ህክምና አሰጣጡ መስተጓጎሉን የገለፁት የማዕከሉ መስራች ትዕግስት አበበ፤ ማዕከሉ በቀን እስከ 120 ታካሚዎችን የማስተናገድ አቅም ያለው ሆኖ በድንገተኛ የሚመጡ አራትና አምስት ታካሚዎችን በሳምንት እየተቀበለ ሲያክም እንደቆየ አብራርተዋል።
ይሁን እንጂ ህክምና መስጠት ስንጀምር የነበረው የታካሚዎቹ የአላቂ እቃ ዋጋ በአራት እጥፍና ከዚያ በላይ በመጨመሩ ከአቅም በላይ ሆኖብን ከ4 ወር  በፊት ማዕከሉ አገልግሎት መስጠት አቁሞ እንደነበር ገልጸዋል። ከዚያ በኋላ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጉዳዩ ገብቶ ረጅም ሂደት ወስደን የገዛነውን የህክምና እቃ የአውሮፕላን ተከፍሎ መምጣቱን ተናግረዋል። እንደ ማዕከሉ መስራች ገለፃ፤ ሀገራችንንና ወገናችንን ለማገልገል ካለን ጥልቅ ፍላጎት አንፃር በኩላሊት እጥበት ሥራ በጣም አስፈላጊውንና ዋናውን እቃ (አሲድ) እዚሁ አገራችን ማምረት ጀምረን፣ እንኳን ለማዕከላችን ለሌሎች ሆስፒታሎችም በጣም በቅናሽ ዋጋ ማቅረብ ጀምረናል፤ ዋናው ችግራችን ግን ወዲህ ነው ብለዋል።
“የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብለን ስንመጣ ከተደላደለና ከሞቀ ኑሯችን ወጥተን ነው” የሚሉት ሃላፊዋ፣ በስምምነታችን መሰረት ከተማ መስተዳድሩ የጤና ቢሮ ሃላፊዎችንና ምንሊክ ሆስፒታል መስተዳድሮችን ይህን አድርጉልን ይሁን አሟሉልን ስንል  ከአራት ወር በፊት  በ90 ቀናት ውስጥ “ጓዛችሁን ጠቅልላችሁ ውጡ” የሚል ከአንድ ትልቅ የጤና ቢሮ ሃላፊ የማይጠበቅ ምላሽ ሰጥተውናል ብለዋል።
ወ/ሮ ትዕግስት አክለውም፤ ይህን ስራ ከጀመርንበት ከአንደኛው  ቀን ጀምሮ በሁለቱ ተቋማት ሃላፊዎች እየተበደልን ወገን ለማገልገል ብንታገስም፣ አሁን ግን በደረሰብን ጫና አገልግሎት መስጠት አቁመን ለ10 ዓመት የተፈራረምነውን ውል፣ በሁለት ዓመቱ ላይ ለማቋረጥ ደብዳቤ ፅፈናል ሲሉ ለምንሊክ ሆስፒታል የፃፉትን የውል ማቋረጫ ደብዳቤ በዋቢነት አቅርበዋል።
“እኛ ወደ መንግስት ሆስፒታል ገብተን ለመስራት የፈለግነው ጉዳዩ የጋራ በመሆኑ የበለጠ መንግስት ሥራችንን ያሳልጣልናል፤ የመጣነው ሀገርን ለማገዝ ነው በሚል ነው ያሉት ሃላፊዋ፣ ነገር ግን በአንዱ ስንለው በሌላው፣ አንዱን ስንፈታ ሌላ ጉዳይ እየታሰረብን በቀን 240 ሰው ማከም ስንችል 120 ሰው ላይ ተቸክለን ቀርተናል ብለዋል።” መሥራቿ  ለአዲስ አድማስ የገጠማቸውን ተግዳሮት ሲያስረዱ።
“ከዚህ ግቢ ጓዛችሁን ጠቅላላችሁ” ውጡ ለሚባለውም ነገር ይህ ማዕከል ሲቋቋም ጠቅላይ ሚኒስትሩ  የቀድሞዋ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰና ከንቲባዋ አዳነች አቤቤ የደከሙበትና ወገንን የሚያገለግል ማዕከል እንደመሆኑ፣ በህግና በስነስርዓት እንደገባነው ሁሉ አዲስ አበባ ጤና ቢሮና ዳግማዊ ምንሊክ ሆስፒታል ያጠፋነው ያጎደልነው ካለ ገልጸውልን፣ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት አውቀው በህግና በስርዓት ለመልቀቅ ዝግጁ ነን፣ ለሀገራችንና ለወገናችን ለመድረስ ብዙ ጥረናል፤ ከዚህ በላይ ምንም ማድረግ አንችልም” ብለዋል።
መግባታቸውን ዙሪያ ያነጋገርናቸው የዳግማዊ ምንሊክ ኮምፕረኸንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ተከተል ጥላሁን፣ ሶስቱ ወገኖች ማለትም የአብ የህክምና ማዕከል፣ ዳግማዊ ምንሊክ ኮምፕረኸንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ በመንግስት የግል አጋርነት ወይም (ፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሽፕ) አማካኝነት ወደ ስራ መግባታቸውን አስታውሰው፤ ሶስቱም አካላት በውልና በህግ የተቀመጠ ግዴታና ሀላፊነት እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡
ዶ/ር ተከተል የሶቱን ተዋዋይ ወገኖች ሀላፊነት ሲገልፁም፤ ዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል የአብ የህክምና ማዕከል ለታካሚዎች የሚሰጠው ህክምና ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን መቆጣጠርና ማረጋገጥ አንዱ ሃላፊነቱ ሲሆን፤ ሁለተኛው የአብ ሜዲካል ሴንተር ለሚሰጠው አገልግሎት የህክምና  ባለሙያዎችን ማቅረብና የአብ ለሚሰጠው አገልግሎት ለሚጠይቀው ክፍያ በውሉ መሰረት ክፍያው በተጠየቀ 3 የስራ ቀናት  ውስጥ ክፍያ መፈፀም እንዲሁም የድጋፍ ደብዳቤ መፃፍና የመሳሰሉት ዋና ዋናዎች ናቸው ብለዋል። ዶ/ር ተከተል አክለውም የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ በዋናነት የአብ ሜዲካል ሴንተር የድጋፍ ደብዳቤ ሲጠይቀው ህጋዊነቱንና አስፈላጊነቱን አጣርቶ ደብዳቤ መፃፍና ማዕከሉ ከቀረጥ ነፃ እቃዎችን እንዲያስገባ ለሚመለከተው አካል የድጋፍ ደብዳቤ መፃፍ በማዕከሉ የሚሰጠው አገልግሎት ሳይቆራረጥ እንዲሰጥ ማገዝ ነው ይላሉ፡፡
ማዕከሉ ምን ያህል ታካሚዎችን እያገለገለ ነበር ለሚለው ጥያቄ ሲመልሱ፤ እኛ የምናውቀው ለሚያገኙት አገልግሎት ክፍያ የምንፈፅምላቸው 104 ናቸው ያሉት ስራ አስኪያጁ፤ ማዕከሉ 120 ናቸው ቢልም 16ቱን ግን አናውቅም ብለዋል፡፡ የአብ ሜዲካል ሴንተር በነፃ ህክምና እሰጣለሁ ቢልም ለታካሚዎች የአገልግሎት ክፍያ ለማዕከሉ የሚከፍለውና ለህክምና ባለሙያዎች ደሞዝ የሚከፍለው ዳግማዊ ምንሊክ ሆስፒታል ነው ብለዋል፡፡ ይህም በውሉ ላይ የተቀመጠና በማስረጃ የሚረጋገጥ ነው ይላሉ፡፡ ከአራት ወር በፊት በግብአት እጥረት ለምን ህክምና ተቆራረጠ የአብ የህክምና ማከል ለጠየቀው የዋጋ ማሻሻያ ለምን ምላሽ አልተሰጠም በሚል ላቀረብነው ጥያቄ ዶ/ር ተከተል ሲመልሱም፤ ለኩላሊት ስንፈት ታካሚዎች ለአንድ ጊዜ አገልግሎት 800 ብር፣ ዘላቂ የኩላሊት ስንፈት ላጋጠማቸው ደግሞ ለአንድ ጊዜ አገልግሎ 1080 (አንድ ሺህ ሰማኒያ ብር) ለማዕከሉ እንከፍል ነበር ያሉት ዶ/ር ተከተል ሆኖም ማዕከሉ የዋጋ ማሻሻያ  ለከተማ አስተዳደሩ ፋይናንስ ተመርቶ ከዚያም የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ አይቶት ሌሎች የዲያሊስስ አገልግሎ የሚሰጡት እንደነ ጳውሎስ ሆስፒታል ያሉ ማዕከላት ያለው ዋጋ ታይቶና የዋጋ ማሻሻያ ጥናት ተደርጎ የሚፀድቅ እንጂ ማዕከሉ ዛሬ ማሻሻያ አድርጉ ስላለ በእኛ ስልጣን የምናሻሽለው አይደለም ካሉ በኋላ፤ “ሆኖም ይህንን ማሻሻያ አስጠንተን እናሻሽላለን እስከዛ ስራው ይቀጥል የሚል ደብዳቤ ብንፅፍም ማዕከሉ ደብዳቤያችንን ውድቅ አድርጎት ከሶስት ሳምንት በፊ የህክምና አገልግሎቱ ተቋርጧል” ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት የህክምና አገልግሎቱ በዋናነት የተቋረጠውም የአብ የህክምና ማዕከል በውሉ መሰረት ስራ ሲጀምር ቢያንስ ከ3-6 ወር የሚበቃ የህክምና ግብአት ስቶክ እንዲይዝ ውል የገባ ቢሆንም አንድም ቀን መጠባበቂያ ስቶክ ይዞ ባለማወቁ ነው ያሉት ዶ/ር ተከተል ይህን ሁሉ ታግሰን ብንቆም ማዕከሉ ግን የግድ ውል ይቋረጥ በማለት አሻፈረኝ ብሏል ብለዋል፡፡
እስካሁን ከውላችን ያጎደልነው የለም ያት ዶ/ር ተከተል፤ የውሃ ቧንቧ ተሰበረ ራውተር ተሰረቀና ሌሎች ቅሬታዎች ማዕከሉ ቢያነሳም የምን ቀበለው የራውተሩን መሰረቅ ነው ያሉ ሲሆን የሆስፒሉ ጥበቃ አውትሶርስ ተደርጎ በጥበቃ ኤጀንሲ የሚሰራ ሲሆን ከዚህም ቀደም የሆስፒታሉ ሌሎች እቃዎች እየጠፉ የጥበቃ ኤጀንሲው እየገዛ እንዲተካ እንደሚደረግና የማዕከሉንም ራውተር የጥበቃ ኤጀንሲው ገዝቶ ለመተካት በሂደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።  ከዚህ ቀደምም ስራው እንዳይቋረጥና አገልግሎቱ እንዲቀጥል ማዕከሉ ከውጪ ገዝቶ ያመጣውን የህክምና ግብአት የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ከውሉ ውጪ 3 ሚ ብር የአውሮፕላን ከፍሎ ግብአቱ መግባቱንና ህክምና እንዲቀጥል ማድረጉን ጤና ቢሮው ከገባው ውል አንዱንም አላማጉደሉን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ዮሃንስ ጫላ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡

ሲንቄ ባንከ አ.ማ ከተለያዩ ስምንት ተቋማት ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ሰነድ ዛሬ የካቲት 7 ቀን 2016 ዓ.ም በባንኩ ዋና መስሪያ ቤት ተፈራርሟል፡፡ ባንኩ ከተቋማቱ ጋር ከተፈራረማቸው የመግባቢያ ሰነዶች በተጨማሪ የ50 ሚሊዮን ብር የኢንቨስትመንት ስምምነት ከኢትዮጵያ የነዋይ ዋስትና ሰነዶች ልውውጥ ጋር ተፈራርሟል፡፡ ከባንኩ ጋር የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረሙት ተቋማት፣ ጨፌ ኦሮሚያ፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ስራ አመራር  ኢኒስቲትዩት፣  የኦሮሚያ ጤና ቢሮ፣ የኦሮሚያ ኢንደስትሪ  ፓርኮች ኮርፖሬሽን ፣ቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ እና የኦሮሚያ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ናቸው፡፡

የዳሸን ባንክ ባለአክሲዮኖች ባካሄዱት 30ኛው መደበኛ ጉባኤ የተመረጠውና የምርጫውም ውጤት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፀደቀለት አዲሱ የዳሸን ባንክ ቦርድ ባደረገው የመጀመሪያ ጉባኤ ላይ ባለፉት ሶስት ዓመታት ባንኩን በዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀ-መንበርነት ያገለገሉትን አቶ ዱላ መኮንንን በድጋሚ በዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀ-መንበርነት መርጧል፡፡   አዲሱ ቦርድ የካቲት 5 ቀን 2016 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ሆቴል ባካሄደው ጉባኤ፣ ለቀጣይ ሶስት አመታት ዳሸን ባንክን በዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀ-መንበርነት እንዲያገለግሉ በድጋሚ የመረጣቸው አቶ ዱላ መኮንን፤ በአሁኑ ወቅት የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የማዕድን ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡   አዲሱ ሊቀመንበር አቶ ዱላ መኮንን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በኤሌክትሪካል ኢንጅነሪንግ፣ እንዲሁም የማስተርስ ዲግሪያቸውንም በቢዝነስ አስተዳደር ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ በአግሪካልቸራል ምህንድስናም ዲፕሎማ አላቸው፡፡
 አዲስ የተመረጡት የቦርድ አባላት እና ባንኩን ላለፉት ሶስት ዓመታት ያገለገሉት የቦርድ አባላት የስራ ርክክብ ያደረጉ ሲሆን ንዑስ ኮሚቴዎችንም አዋቅረዋል፡፡ ባንኩ አዲስ ለተመረጡት የቦርድ አባላት አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴውን አስመልክቶ ገለፃ ሰጥቷል፡፡

የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ታህሣሥ 18 ቀን 2ዐ16 ዓ. ም. የባንኩን ባለአክሲዮኖች 24ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በብሔራዊ ባንክ አመቻችነትና ታዛቢነት ባደረገው ምርጫ የተመረጡት የቦርድ አባላት ዝርዝር ጥር 24 ቀን 2ዐ16 ዓ. ም. በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፀድቋል፡፡ በዚህም መሠረት አዲሱ ቦርድ ባንኩን የማስተዳደር ተግባሩን ከጥር 27 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ተረክቧል፡፡
አዲሱ ቦርድ ባንኩ ያለበትን ከፍተኛ ተግዳሮት በመገንዘብ ፈጥኖ ወደ ሥራ በመግባት የራሱን አመራር እና የንዑስ ኮሚቴዎችን ድልድል በማካሄድ አቶ ሺሰማ ሸዋነካን በሊቀመንበርነት እንዲሁም ዶ/ር ወንድሙ ተክሌን በምክትል ሊቀመንበርነት መርጧል፡፡ በቀጣይም ቦርዱ፣ ባንኩ ያለበት አሁናዊ ሁኔታ ጊዜ የማይሰጥና ቀን ከሌት መስራትን እንደሚጠይቅ ከግንዛቤ በማስገባት የባንኩን ስምና ዝና  ወደነበረበት መመለስን እንዲሁም የባንኩን ዘለቄታዊ ጥቅም ማስጠበቅን ዋነኛ ግቡ ያደረገውን የባንኩን የመልሶ ማደራጃ የዘጠና ቀናት ዕቅድ (90 days Turnaround Plan) ተልሟል፡፡ ቦርዱ ከባንኩ የማኔጅመንት አባላት እስከዋና ክፍል ኃላፊ ድረስ  ካሉት የሥራ ኃላፊዎችም ጋር ትውውቅና ውይይት አካሂዷል፡፡ ቦርዱ በተጨማሪም እንደ ባንክ እንዲሰሩ ባሰባቸው ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ በዚህም ቦርዱ የተለመውን የመልሶ ማደራጃ ዕቅድ ይፋ በማድረግ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በተረጋጋ መንፈስና በጥንቃቄ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ መመሪያ አስተላልፏል፡፡ የቦርዱ ንዑሳን ኰሚቴዎችም ጊዜ ሳይሰጡ ከባንኩ የማኔጅመንት አባላት ጋር በቀረቡ ሪፖርቶችና በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት አካሂደዋል፤ አቅጣጫም አስቀምጠዋል፡፡
አዲሱ ቦርድ የካቲት 6 ቀን 2ዐ16 ዓ. ም. ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ከክቡር አቶ ማሞ ምህረቱ፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ ከክቡር አቶ ሰሎሞን ደስታ እና ከሌሎች የባንኩ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር ትውውቅ አድርጓል፡፡
በስብሰባውም ክቡር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ አዲሱ ቦርድ ከፊቱ የተደቀኑትን ተግዳሮቶች ግዙፍነት በአፅንዖት አስገንዝበው ሃላፊነቱን በልዩ ቁርጠኝነት እና በከፍተኛ የሃላፊነት ስሜት እና ፍጹም ታማኝነት እንዲወጣ በአፅንዖት አሳስበው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የአዲሱን ቦርድ የስራ አፈፃፀም በቅርበት እንደሚከታተልና እንደሚገመግም የባንኩ ገዢ በስብሰባው ላይ ጨምረው አስታውቀዋል፡፡  
በዋነኛነት ክቡር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በባንክ ሴክተር ቀደምት እና ጠንካራ ከሆኑት ባንኮች መካከል የሚመደብ መሆኑን አስታውሰው በቀጣይም አዲሱ ቦርድ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ወደነበረበት ደረጃ በሚያደርገው ጉዞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከጐኑ በመሆን በቅርበት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚሰጠው የባንኩ ገዢ አረጋግጠዋል፡፡
አዲሱ ቦርድ፤ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ከፍተኛ ተግዳሮት በገጠመው በዚህ ወቅት ከጐኑ በመሆን ፈተናዎቹን በስኬት እንዲወጣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እያደረገለት ለቆየው እና ወደፊትም ለሚቀጥለው ሁሉ አቀፍ ድጋፍ፣ ክትትልና ቁጥጥር ከፍተኛ አክብሮቱን እና ላቅ ያለ ምስጋናውን በባንኩ ማህበረሰብ ስም ማቅረብ ይወዳል፡፡

Saturday, 17 February 2024 21:15

ዝክረ ወንድዬ አሊ (1950 - 2016)

“--ወንድዬ ዓሊ በ1950 ዓ.ም  በቀድሞው የወሎ ጠቅላይ ግዛት፣ ወረኢሉ አውራጃ ካቤ በምትባል መንደር ታክል ከተማ ተወለደ፡፡ ለወላጆቹ አምስተኛ ልጅ የሆነው ወንድዬ፤  በእናቱ ፍቅር ተምበሽብሾ፣ ወደ ጫና በሚያደላው በአባቱ ጥብቅ ሥነ- ምግባር ተኮትኩቶ አደገ፡፡ ግጥም መግጠም የጀመረው፣ ገና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳለ ነበር፡፡

‹‹የእናትና አባቴ ትዳር ከፈረሰ በኋላ አባቴ ሌላ ሚስት አገባ፡፡ የእንጀራ እናቴ - በራሷ “ክፉ ቀን! ክፉ ሰው!” ሆነችብኝ፡፡ ፊቷ በገረፈኝ ቁጥር ቁጭቴን የምወጣው ወረቀት ላይ ነበር፡፡ አምስተኛ ክፍል ስደርስ እንጉርጉሮዎቼ አንድ ደብተር ሞሉ፡፡ ጥራዟን “ሲከፉ” የሚል ርእስ አወጣሁላት›› ይላል ወንድዬ፤ አጀማመሩን ሲያስታውስ፡፡

ግጥሞቹ ግን ከባድማ ልቡ ብቻ የወጡ አልነበሩም፤ ከማንበብና መጻፍ በስተቀር ምንም ዘመናዊ ትምህርት ያልቀሰሙት አባቱ፤ ለሕክምናም ሆነ ለፍርድ ቤት ጉዳይ ወደ አዲስ አበባ ጎራ ባሉ ቁጥር ብርቅዬ ጫማና አልባሳት ሳይሆን መጻሕፍት ገዝተውለት ነበር የሚመጡት፡፡ ጦቢያ (የመጀመሪያው ልቦለድ በአፍሪቃ)፣ ወዳጄ ልቤ፣ አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም፣ ፀሐይ መስፍን፣ እንቅልፍ ለምኔ ወዘተዎቹን. . . ያነበበው ካቤ መንደሩ ሳለ በኩራዝ ነው፡፡ የንባብ ፍቅር በዚያው ተጠናውቶት ቀረ፡፡

በጠቅላይ ግዛቱ ዋና ከተማ በሚገኘው በታዋቂው የወይዘሮ ስኅን ትምህርት ቤት፣ የሁለተኛ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱን ለመከታተል ወደ ደሴ ከተማ በ1965 ዓ.ም  ሲሄድ እንጀራ እናቱ ከሚያደርሱበት ሃበሳ ተገላገለ፡፡ እንጉርጉሮ - ጎርጉሮ የመክተቡም ነገር አብሮ ቀጥ አለ፡፡

ኪነ-ጥበባዊው ደመ-ነፍሳዊ አደራ ግን እንደ ጪስ (ጢስ) መውጪያ ስንጥቅ አታጣምና  መንፈሳዊ ግጥሞችን መጫጫር ጀመረ፡፡ በደብረ ዘይት የእንስሳት ሕክምና ኮሌጅ በ1971 ዓ.ም  ገበቶ የደብረ ዘይት መካነ ኢየሱስ ኳየር ሲቀላቀል አምሮቱን ተወጣ፤ 200 ግድም ዜማ-ግጥሞችን (Lyrics) ዘመረ፤ አዘመረ፡፡ ስለ ዜማ-ግጥም ሥራዎቹ ሲናገር እንዲህ ይላል፡- ‹‹እነሱ እኮ! … ግጥሞቼ ሳይሆኑ፣ የዐውደ ዕለት ማስታወሻዎቼ (Diary) ናቸው፤ ግጥሞቼ ደግሞ - ታሪኮቼ››፡፡  ከነፍሱ ጥሪ በተቃራኒ እንስሳት ሕክምና ኮሌጅ የገባው በጊዜው ከነበረው ቀይ ሽብር አደጋ ለመሰወር ያህል ብቻ እንደ ነበረ - ያስታውሷል፡፡

ከኮሌጅ ሲመረቅ በሐምሌ 1972  አርሲ ተመደበ፡፡ በእንስሳት ሐኪምነትና በእንስሳት እርባታ ማኔጀርነት ዘጠኝ ዓመት ተኩል በሠራባቸው ዓመታት እውነተኛ ገጣሚነቱ ተፍለቀለቀ፡፡ በ1984 ዓ.ም  በታተመቺው የመጀመሪያ መድበሉ “ወፌ ቆመች” ውስጥ የተካተቱት ግጥሞች አብዛኛዎቹ የተጻፉት በአርሲ ቆይታው ነበር፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና ኮተቤ ኮሌጅን ጨምሮ በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት “በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ” ክፍል ለማስተማሪያነት በካሪኩለም ውስጥ ለመካተት የበቃቺው “ወፌ ቆመች” እንግዲህ የእንስሳት ሐኪሙ - የቅኔ ዛር ምጥ ናት ማለት ነው፡፡

የወፌ ቆመች መታተም እና ዝና ኋላ ላይ ፍቅሩም፣ እንጀራውም ወደ ሆነው የሥነ ጽሑፍ ሙያ ይቀላቀል ዘንድ መንገድ ጠረገለት፡፡ የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት የሥነ ጽሑፍ ድርጅት ባልደረባ ይሆን ዘንድ ጋበዘው፡፡ (በዚህ ረገድ የአቶ ጌታቸው በለጠ ድርሻ ትልቅ ነበር፡፡ ግብርና ሚኒስቴርን ለቆ (ሞፈሩን ሰቅሎ፣ ቀምበሩን ሰብሮ) በትንሽ ደመወዝ በረዳት መጽሔት አዘጋጅነት ተቀጠረ፡፡

‹‹መጽሔት፡- እንደ ‹ቡፌ› ገበታ የተለያዩ መልእክቶች፣ በተለያዩ አቀራረቦች፣ በተለያዩ የአቀራረብ ቀለሞች፣ የሥነ ጽሑፍ ዘውጎች መከሸን ይገባዋል፤›› ብሎ  የሚያምነው ወንድዬ፤ የቃለ ሕይወትን መጽሔት እንደ ልቡ ናኘባት፡፡ እያንዳንዷን ቅጽ፡- የመጣጥፍ፣ የታዋቂ ሰዎች ፕሮፋይል፣ የቃለ ምልልስ፣ የግጥሞች . . . ገበታ አደረጋት፡፡ (እንዳሰኘው ይጽፍ ዘንድ ሙሉ ነፃነት ያጎናጸፉትን የቅርብ አለቆቹን ያመሰግናል)፡፡ በዚህ ወቅት ነበር ከሥነ ግጥም በተጨማሪ በሌሎችም የሥነ ጽሑፍ ዘውጎች ለመጻፍ ተሰጥዖ እንዳለው ራሱን ያሳመነው፡፡ በተለይም በታሪክ እና የሕይወት ታሪኮች አተራረክ ረገድ ብዙ እርምጃ ተራመደ፡፡ ለዚህም ነበር፣ ከመደበኛ ሥራው ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያንን ከፊል ታሪክ የሚሸፍነውን (1920-1966 ዓ.ም) ለመጻፍ የቻለው፡፡

በሁለት ቅጽ የተዘጋጁት መጻሕፍት “በመከራ ያበበች” እና “የእኩለ ሌሊት ወገግታ” ይሰኛሉ፡፡ እንደ ቅደም ተከተላቸው በ1990 ዓ.ም እና 1992 ዓ.ም የታተሙ ናቸው፡፡ መጻሕፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በአማርኛ ቋንቋ የተጻፉ የፕሮቴስታንት (ወንጌላውያን) ቤተ እምነት ታሪክ በመሆናቸው በርካታ የሥነ መለኮት ኮሌጆች ሥርዓተ ትምህርት (ካሪኩለም) ውስጥ ተካተቱለት፡፡ በዚህ ደስ የተሰኙት አለቆቹ Tear fund England ከሚባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር በመተባበር፣ ኬኒያ - ናይሮቢ በሚገኘው Daystar ዩኒቨርስቲ የትምህርት ዕድል አመቻቹለት፡፡ በ40 ዓመቱ ተመልሶ ትምህርት ቤት ገባ፡፡ በአራት ዓመት ቆይታ ለመጀመሪያ ድግሪ መርሐ ግብር የተላከው ወንድዬ፣ በሦስት ዓመት ቆይታ የማስተርስ ዲግሪውን ይዞ ተመለሰ፡፡ ይህ ለብዙዎች ታምር ያህል እውነት ነው፡፡ ጥያቄም ነው፡፡

‹‹ሰው እንዴት ከveterinary ዲፕሎማ ተነስቶ በሦስት ዓመት፣ ለዚያውም ለMature Students የሚሰጠውን መሸጋገሪያ ኮርስ (Bridging Course) ሳይወስድ፣ ሁለተኛ ዲግሪውን ለዚያውም በሦስት ዓመት ብቻ ሊያጠናቅቅ ይችላል?›› ይህን  ለመዘርዘር ውጥኔ አይፈቅድልኝም፡፡ የወንድዬን የአዕምሮ ጉልበትና ሥራዎቹን በደንብ የተረዱ ሰዎች ‹‹ይህን ሰው ለመጀመሪያ ድግሪ ማስተማር “ማባከን ነው” በማለት ከዩኒቨርስቲው ጋር የተሟገቱ እንደ ነበሩ ወንድዬ ያስታውሳል፡፡ የአቶ ወርቁ ኃይለ ማርያምን ግትገታ (ውትወታ) ግን ከሁሉ የበለጠ ነበርና ወንድዬ ሁሌም ያስታውሰዋል፡፡

ወርቁን እና ወዳጆቹን አላሳፈራቸውም፡፡ የመመረቂያ ወረቀቱን፡, “THE CONTRIBUTION OF ORAL LITERATURE IN COMMUNICATING THE GOSPEL TO THE OMOTIC PEOPLE OF SOUTHERN ETHIOPIA: A CASE STUDY OF THE WOLIATE PIONEER EVANGELISTS” በሚል ርእስ ሠርቶ፣ በ2003 (እኤአ) በማስተርስ ድግሪ ተመረቀ፡፡

ከናይሮቢ እንደ ተመለሰም የቃለ ሕይወት ሥነ ጽሑፍ ክፍል ኃላፊ ሆኖ ተመደበ፡፡ ግና ምን ያደርጋል? ሹመቱን ሰጥተው የቀድሞውን ነፃነቱን ነፈጉት፡፡ ከሁለት ዓመት መፍገምገም በኋላ ሥራውን ለቆ Population Media Center (PMC) በኤክስፐርትነት ተቀጠረ፡፡ ጥቂት፣ ግን መልካም የፊደላት የምርት ዘመን አሳለፈ - 2 ዓመት ብቻ፡፡ በክብር ተሰናብቶ የሙሉ ጊዜ ጸሐፊ ሆነ፡፡ ሁለተኛዋን የግጥም መድበል “ውበትና ሕይወት” (ወፌ ቆመች - ቅጽ -2) የታተመችው በ1998 ዓ.ም  ነበር፡፡ ይህም ማለት በ1ኛዋ እና በ2ኛዋ የግጥም መድበል መካከል የ15 ዓመት ግድም ክፍተት አለ ማለት ነው፡፡ በስሎ፣ ሰክኖ፣ ነትሮ ራሱን የገለጠባት መድብል ሆነች፡፡

ከሌላ 17 ዓመት ቆይታ በኋላ 3ኛ ቅጹን ለማሳተም ኮምተራይዝ እያደረገ ይገኛል፡፡ አልፎ አልፎ በፌስ ቡክ በሚለቃቸው ያልታተሙ ግጥሞቹ፣ የወፌ ቆመች 3ኛ ቅጽ አቀማመር ካለፉት ሁለቱ ለየት እንደሚል ያመላክታሉ፡፡ ለኅትመት ጉድ ጉድ ማለቱን የሰማ አንድ ወዳጁ ‹‹የማያርጠው ገጣሚ›› በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ ሳያሳትማት ዘገየች፤  ‹‹እየታመምን እንጽፋለን፣ እየጻፍን እንታመማለን›› ይላል በራሱ ሲቀልድ፡፡ ከህመሙ በኋላ እንኳን አራት መጽሐፎች ታትመውለታል፡፡
 
ስለ ግጥሞቹ ውበትና  ለዛ፣ ይዘትና ቅርጽ አብዝተው ከጻፉት መካከል፡- አቶ ዘሪሁን አስፋው (በሥነ ጽሑፍ መሠረታውያን መጽሐፉ)፣ እንዲሁም ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ገበየሁ (በሥነ ግጥም ማኑዋል መጽሐፉ)  ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡ ሁለቱም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራን ናቸው፤ (ብርሃኑ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን ያስታውሷል)፡፡ በህትመትሚዲያው ደጋግመው ከጻፉት መካከል ደግሞ፡- ደረጀ በላይነህ፣ ተሻገር ሺፈራው (ዶ/ር) እንዲሁም ወጣቱ ገጣሚ መዘክር ግርማ ይገኙባቸዋል፡፡  ከሁሉም በላይ ሥራዎቹን ተመርኩዘው የመመረቂያ ጽሑፎቻቸውን የጻፉ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች 15 ያህል እንደሆኑ አንድ ወዳጁ ለወንድዬ ነግሮታል፡፡

ታዲያ ምን ያደርጋል፤ ገጣሚውና ሐያሲው ደረጀ በላይነህ ‹‹ዓይናፋሩ ገጣሚ›› ሲል እንደ ገለጸው፣ በእርሱ ዙሪያ የተጻፉትን የትውልድ ቅርሶች ቢያንስ ለልጆቹ እንኳ ሲል ያሰባስባቸው ዘንድ ጥረት አላደረገም፡፡ ይህ ልክ ያለፈ ትህትናው (Humility)፣ ምናልባት ልክ ያለፈ ድካሙ  ሳይሆን አይቀርም፡፡ ጋባዡ ብዙ ቢሆንም፣ በመድረክ፣ በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ . . . ትዕይንታት አይሳተፍም፡፡ ከተሳተፈም በጥንቃቄ መርጦ ነው፡፡ ውካታና ሆያ-ሆዬ አይወድም፡፡---“
***

(ከላይ የቀረበው ታሪክ፣ ደራሲና ገጣሚ ወንድዬ አሊ በህይወት ሳለ፣ የዝነኞችንና የታዋቂ የጥበብ ሰዎችን የህይወት ታሪክ በመሰብሰብና በመሰነድ ከሚታወቀው “ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን” ድረገጽ  የተቀነጨበ ሲሆን፤ ደራሲና ገጣሚ ወንድዬ ዓሊ በተለይ በግጥሞቹ በኩል፣ የአዲስ አድማስ ቤተኛ እንደነበር ለማስታወስ እንሻለን፡፡ በርካታ ግጥሞቹ በጋዜጣው ላይ ታትሞለታል፡፡ ከደራሲና ሃያሲ ደረጀ በላይነህ ጋር ያደረገው ቃለምልልስም፣ በሁለት ክፍል ለንባብ በቅቶለታል፡፡ የዝግጅት ክፍሉ ሰሞኑን በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት በተለየው አንጋፋው የጥበብ ሰው ወንድዬ ዓሊ የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን እየገለጸ፤በተለይ ለቤተሰቦቹ፣ ለቅርብ ወዳጆቹና አድናቂዎቹ መጽናናትን ይመኛል፡፡ ወንድዬ አሊን  በየጊዜው በጥበብ ሥራዎቹ እየዘከርነው እንቀጥላለን፡፡)
***
የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጥሪ፡-
 ከደራሲና ገጣሚ ወንድዬ ዓሊ ጋር በተያያዘ ትዝታችሁን፣ የምታውቁትንና በስራዎቹ ላይ የተጻፉ አስተያየቶችን ለምትልኩልን ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ቅድሚያ ሰጥተን እንደምናስተናግደው ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

 

 

በራሱ ስም በተሰየመው የመጀመሪያ አልበሙ የአፍሪካ ጃዝ አባት ከሆኑት  ከአንጋፋው ዶ/ር ሙላቱ አስታጥቄ ጋር በመጣመር “ዓይፈራም ጋሜ”ን ያስኮመኮመን አርቲስት ጀምበሩ ደመቀ፤ በቅርቡ “እሳቱ ሰ” የተሰኘ ሁለተኛ አልበሙን ለአድማጭ እንደሚያደርስ ተገለጸ፡፡

 ጀምበሩ በቅርቡ ከኡኖ ጋር ባቀነቀነው “ተፍ ተፍ” በተሰኘው ነጠላ ዜማው፣ ከፍተኛ ተቀባይነትን ማግኘቱ የሚታወቅ ነው፡፡  

በ21 አመቱ የመጀመርያውን አልበም በ2014 ዓ.ም ያወጣው ጀምበሩ ደመቀ፤ ወጣት የሂፕሆፕ አድናቂዎችን ልብ ለመግዛት ጊዜ አልፈጀበትም።
 
አርቲስቱ በሁለተኛው አዲስ አልበሙ  ከወጣት አቀንቃኞች ጋር የተጣመረባቸው ስራዎች የተካተቱ ሲሆን፤ ከባህር ማዶ ከኬንያው እውቅ አርቲስት ሬገን ዳንዲ እና ከትውልደ ብሩዎንዲ በዜግነት እንግሊዛዊው ሙቲ  እንዲሁም ከሀገር ውስጥ ከሌሎች ወጣት አርቲስቶች ጋር በአንድነት መሥራቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

አሚጎስ የገንዘብ'ና ብድር ህብረት ስራ ማህበር ለ4ኛ ዙር ስልሳ ዘጠኝ ዘመናዊ መኪኖችን በአሮጌ ላዳ ታክሲዎች ለማህበሩ ቆጣቢዎች'ና ብድር ተጠቃሚዎች ቀይሯል።

ይህ የገንዘብና ቁጠባ ብድር ህብረት ስራ ማህበር ላለፉት አስር ዓመታት ከሰባት ሺ በላይ አካላትን በማቀፍ እንዲሁም ለሶስት ሺ ሰዎች የብድር አገልግሎት በመስጠት በርካቶች ራሳቸውን'ና ቤተሰቦቻቸውን ወደ ተሻለ ህይወት እንዲቀይሩ የድርሻውን የተወጣ ማህበር ነው።

አሚጎስ በአዋጅ ቁጥር 147/91 እና ይሄንን አዋጅ ለማሻሻል በወጣ አዋጅ ቁጥር 402/96 መሰረት ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስ ሲሆን ፤ዛሬ በጎልደን ቱሊፕ ሆቴል ስልሳ ዘጠኝ ዘመናዊ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ መኪኖችን የሚዲያ አካላት በተገኙበት ለተጠቃሚዎች አስረክቧል።

የአሚጎስ መስራች'ና የኮርፖሬት ሴልስ ኃላፊ የሆኑት አቶ እንዳልካቸው በሀይሉ እንደተናገሩት ከሆነ፡ድርጅታቸው አሁን ላይ ለግለሰቦች እስከ አስር ሚሊዮን ብር የሚደርስ ብድር የማቅረብ አቅም አለው ያሉ ሲሆን ፤በእስካሁኑ የስራ ቆይታቸውም አራት ቢሊዮን ብር ብድር እንዳቀረቡና አንድ ሺ አምስት መቶ መኪኖችንም በብድር መያዣቸውን አብራርተዋል።

ከስድስት ወር እስከ አስር ዓመት ድረስ ሊቆይ በሚችል የብድር አከፋፈል ስርዓት ማንኛውም ግለሰብ ሆነ ማህበራት ለመኪናም ሆነ ለቤት ግዥ የሚሆን የብድር አገልግሎት ከአንድ ወር እስከ ሶስት ወር ባለ ጊዜ ውስጥ ብድር ማግኘት ይችላል ብለዋል።

አሚጎስ ኦክሎክ ጀነራል ትሬዲንግ የሚያስመጣቸውን መኪኖች በብድር ተጠቃሚ ያደረጋቸው የታክሲ ማህበራት ፡አዲስ ምቾት ፡ሀገሬ የታክሲ ማህበር ፡ገፅታ የተሰኙ ሲሆን ሌሎች ማህበራትም የዚህ እድል ተጠቃሚ እንደሆኑ ጥሪ አቅርቧል።

ምሽት 5:00 ሰዓት ላይ በተካሄደው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ አስተናጋጇ ኮትዲቯር ናይጄሪያን 2 ለ 1 በማሸነፍ ዋንጫውን አንስታለች።

የኮትዲቯርን የማሸነፊያ ግቦች ፍራንክ ኬሲ እና ሴባስቲያን ሀለር  አስቆጥረዋል።ናይጄሪያን ከሽንፈት ያላዳነችውን ብቸኛ ግብ ደግሞ ዊሊያም ትሩስት ኢኮንግ አስቆጥሯል።
በዚህም ዝሆኖቹ የአፍሪካ ዋንጫን ለሶስተኛ ጊዜ ማንሳት ችለዋል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ ጀግኖች አርበኞች፣ የኃይማኖት አባቶች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

Page 12 of 700