Administrator

Administrator

አስደማሚ የሸገር ፕሮጅቶች----ከአድዋ የሚተካከል ድል በህዳሴ ግድብ---ወደ ህዋ ያመጠቅናት ሳተላይት--ጠ/ሚኒስትሩ ያሸነፉት ታሪካዊ የኖቤል ሽልማት--ከ5 ሚ. በላይ ችግኞች በአረንጓዴ አሻራ--
አስከፊው የኮሮና ወረርሽኝ--- የነውጠኞች ሁከትና  ግርግር ---አሰቃቂ ሞትና ውድመት----የዳያስፖራ ጽንፈኞች የአመጽ ጥሪ --የ"ዳውን ዳውን" ፖለቲካ አቀንቃኞች-- ያወዛገበ የብሔራዊ መግባባት መድረክ --የህግ የበላይነትና የታዋቂ ፖለቲከኞች እስር--የሸገር -የመሬት ወረራ--    

     በመላው አለም የተጠቂዎች ቁጥር ከ26.3 ሚሊዮን፣ የሟቾች ቁጥር ከ870 ሺህ አልፏል

           በአፍሪካ ጥቅል የኮሮና ስርጭትና የማጥቃት መጠን ባለፈው አንድ ሳምንት በተወሰነ መልኩ መቀነስ ማሳየቱንና በአህጉሪቱ በቫይረሱ ከተጠቁት ሰዎች መካከል 80 በመቶ ያህሉ በማገገም ላይ እንደሆኑ የአፍሪካ የበሽታ መከላከልና ቁጥጥር ማዕከል ባለፈው ሃሙስ ባወጣው መግለጫ ማስታወቁን አናዶሉ ኤጀንሲ ዘግቧል፡፡
በአህጉሪቱ ጥቅል የቫይረሱ ስርጭት መጠን በሳምንቱ ቅናሽ ቢያሳይም አፍሪካ ቫይረሱን አሸነፈችው ማለት እንደማይቻልና ገና ብዙ መስራት እንደሚገባ ማዕከሉ ማስታወቁን የጠቆመው ዘገባው፣ በአንጻሩ ደግሞ ስርጭቱ በምስራቅ አፍሪካ የ2.4፣ በሰሜን አፍሪካ ደግሞ የ7.5 በመቶ መጨመር ማሳየቱን የጠቆመው ዘገባው፤ በአፍሪካ የአዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ባለፈው አንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ በ14 በመቶ ያህል መቀነስ ማሳየቱንም አክሎ ገልጧል፡፡
ኮሮና ቫይረስ እስካለፈው ሃሙስ አመሻሽ ድረስ በአፍሪካ ከ1.267 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ማጥቃቱን፣ የሟቾች ቁጥር ከ30 ሺህ ማለፉንና ያገገሙት ሰዎች ቁጥርም ከ1 ሚሊዮን ማለፉንም ዘገባው አመልክቷል፡፡ በመላው አፍሪካ ከ11.8 ሚሊዮን በላይ በሚሆኑ ሰዎች ላይ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ መደረጉንና ከዚህ ውስጥም 10.7 በመቶ ያህሉ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ያስታወቀው የአፍሪካ የበሽታ መከላከልና ቁጥጥር ማዕከል፤በአህጉሪቱ በቫይረሱ ከተጠቁ ሰዎች 70 በመቶ ያህሉ በ5 አገራት ውስጥ እንደሚገኙና አገራቱም ደቡብ አፍሪካ፣ ግብጽ፣ ሞሮኮ፣ ናይጀሪያና ኢትዮጵያ መሆናቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡
ወደ አለማቀፍ መረጃዎች ስንሄድ ደግሞ፤ ኮሮና ቫይረስ እስካለፈው ሃሙስ አመሻሽ ድረስ በመላው አለም ከ26.29 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ማጥቃቱንና ወደ 870 ሺህ ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት መዳረጉን የጠቆመው የወርልዶሜትር ድረገጽ መረጃ፣ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ከ18.6 ሚሊዮን በላይ መድረሱን አስታውቋል፡፡ አሜሪካ በ6.3 ሚሊዮን ተጠቂዎቸና ከ190 ሺህ በለይ ሟቾች ከአለማችን አገራት ቀዳሚነቱን ይዛ የቀጠለች ሲሆን ብራዚል በበኩሏ፤ ከ4 ሚሊዮን በላይ ተጠቂዎችና በ124 ሺህ ያህል ሟቾች በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
ከ3.9 ቢሊዮን በላይ ሰዎች ተጠቅተውባትና 68 ሺህ ሰዎች ሞተውባት በሶስተኛ ደረጃ ላይ በምትገኘው ህንድ ባለፈው ረቡዕ ብቻ 83 ሺህ 883 የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች መገኘታቸውንና ይህም አገሪቱን ከአለማችን አገራት መካከል በአንድ ቀን ከፍተኛውን የተጠቂዎች ቁጥር የመዘገበች አገር እንዳደረጋት ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ፤ ህንድ ባለፈው ረቡዕ ብቻ ከ11.7 ሚሊዮን በላይ በሚሆኑ ሰዎች ላይ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ማድረጓንና ይህም በአለማችን በአንድ ቀን የተደረገ ከፍተኛው የምርመራ ቁጥር መሆኑን የአገሪቱ የጤና ሚኒስትር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ በመጪው ህዳር ወር መጀመሪያ ለዜጎቿ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ለመስጠት ማቀዷን ከሰሞኑ ይፋ ያደረገቺው አሜሪካ፣ ለኮሮና ቫይረስ ክትባትና መድሃኒት ለማምረትና በቀጣይም በፍትሃዊነት ለማሰራጨት የሚደረገውን ጥረት በጋራ ለማሳካት በአለም የጤና ድርጅት አስተባባሪነት በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘውና ከ150 በላይ አገራት በአባልነት የተካተቱበት አለማቀፍ ጥምረት ውስጥ እንደማትሳተፍ ከሰሞኑ ማስታወቋን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እስከመጪው አመት በመላው አለም የሚገኙ 47 ሚሊዮን ያህል ሴቶችንና ልጃገረዶችን ለድህነት ሊዳርግ እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ ማስጠንቀቁን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡ የአለም የኢኮኖሚ ፎረም በበኩሉ፤ በመላው አለም ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ህጻናት በኮሮና ወረረሽኝ ሳቢያ ከትምህርት ገበታቸው ውጭ መሆናቸውን፣ 370 ሚሊዮን ያህል ህጻናት የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር እንደተቋረጠባቸው እንዲሁም 80 ሚሊዮን ያህል ህጻናት በክትባት አለማግኘት ሳቢያ ለተለያዩ በሽታዎች ሊዳረጉ እንደሚችሉ ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡
በኮሮና ሳቢያ ባለፉት 6 ወራት 133 ሚሊዮን ዶላር ያህል ኪሳራ የደረሰበት ኬንያን ኤርዌይስ፤ የአለማችን የጤና ሰራተኞች በኮሮና ወረርሽኝ ትግል ውስጥ እየከፈሉት ላለው መስዋዕትነት እውቅናና ምስጋና ለመስጠት በማሰብ ከመጪው ወር ጀምሮ በመላው አለም አገልግሎቱን ለሚጠቀሙ የጤና ሰራተኞች፣ ከመደበኛው ዋጋ በግማሽ ቀንሶ አገልግሎት እንደሚሰጥ ከሰሞኑ ይፋ ማድረጉ ተዘግቧል፡፡

የአለማችንን ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ መስፈርቶች እያወዳደረ በየአመቱ ይፋ የሚያደርገው ታይምስ ሃየር ኢጁኬሽን የተባለው አለማቀፍ ተቋም፣ ከሰሞኑም የዘንድሮውን ሪፖርት ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ላለፉት አራት ተከታታይ አመታት የአለማችን ምርጥ ዩኒቨርሲቲ ሆኖ የዘለቀው የእንግሊዙ ኦክስፎርድ ዘንድሮም ክብሩን አስጠብቋል፡፡
በዘንድሮው የአለማችን ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ዝርዝር ውስጥ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ የያዙት ሁሉም የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ስታንፎርድ፣ ሃርቫርድ፣ ካሊፎርኒያ ኢንስቲቲዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ እና ማሳቹሴትስ ኢንስቲቲዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ ናቸው፡፡ የእንግሊዙ ካብምሪጅ ጣልቃ ገብቶ የ6ኛነት ደረጃ ቢይዝም፣ እስከ 10ኛ ያለውን ስፍራ የያዙትም የአሜሪካዎቹ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ፣ የል ዩኒቨርሲቲ፣ ፕሪንሲተን ዩኒቨርሲቲ እና ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቺካጎ ናቸው::
በአለማቀፉ የምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ዝርዝር ውስጥ የ155ኛ ደረጃን የያዘው የደቡብ አፍሪካው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኬፕታውን፣ ከአፍሪካ በ1ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን፣ ደቡብ አፍሪካ በድምሩ 11 ዩኒቨርሲቲዎችን በዝርዝሩ ውስጥ ለማስፈር ችላለች፡፡
በ2021 የአለማችን ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ዝርዝር ውስጥ እስከ 500 ባለው ደረጃ ውስጥ ከተካተቱ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ደግሞ የግብጾቹ አስዋን እና ማንሶራ፣ የናይጀሪያው ዩኒቨርሲሲ ኦፍ ኢባዳንና የኡጋንዳ ማካሬሬ ዩኒቨርሲቲ እንደሚገኙበት ተነግሯል፡፡ በዝርዝሩ ውስጥ በ20ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የቻይናው ሲንጉዋ ዩኒቨርሲቲ እስከ 20 ባለው ደረጃ ውስጥ የገባ የመጀመሪያው የእስያ ዩኒቨርሲቲ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ታይምስ ሃየር ኢጁኬሽን የተባለው አለማቀፍ ተቋም በ93 የአለማችን አገራት ውስጥ የሚገኙ 1ሺህ 527 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የተለያዩ መስፈርቶችን ተጠቅሞ በመገምገም ባወጣው የአለማችን ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ዝርዝር ውስጥ 141 ዩኒቨርሲቲዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተካትተውበታል፡፡

      ካይሌ ጄነር በ590 ሚ. ዶላር የአመቱ ከፍተኛ ተከፋይ ዝነኛ ተብላለች

         የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር ጄፍ ቤዞስ የቀድሞ የትዳር አጋር የነበረችው አሜሪካዊቷ ደራሲና በጎ አድራጊ ማኬንዜ ስኮት አጠቃላይ የተጣራ ሃብት 68 ቢሊዮን ዶላር መድረሱንና ይህም ግለሰቧን የአለማችን ቀዳሚዋ ሴት ባለጸጋ እንዳደረጋት ብሉምበርግ ከሰሞኑ አስነብቧል፡፡
ማኬንዜ ባለፈው አመት ከአማዞኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጄፍ ቤዞስ ጋር ባለመግባባት ሳቢያ ትዳራቸውን አፍርሰው መፋታታቸውንና በካሳ መልክ ከቤዞስ የአማዞን የአክሲዮን ድርሻ ሃብት ሩብ ያህል እንደተካፈለች ያስታወሰው ዘገባው፣  የ4 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ በወቅቱ 35 ቢሊዮን ዶላር ይገመት እንደነበርና ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን እያደገ መጥቶ አሁን 68 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ገልጧል:: ግለሰቧ በአሁኑ ወቅት የአለማችን 12ኛ ሃብታም ሴት መሆኗን የጠቆመው ዘገባው፣ ባለፈው ሃምሌ ወር ላይ ለ116 ድርጅቶች በድምሩ 1.7 ቢሊዮን ዶላር ያህል የበጎ አድራጎት ድጋፍ ማድረጓንም አመልክቷል፡፡
የአማዞን ኩባንያ የአክሲዮን ዋጋ ባለፉት ሶስት ያህል ወራት በ28 በመቶ ያህል ማደጉን ያስታወሰው ዘገባው ይህም ዋና ስራ አስፈጻሚውን ጄፍ ቤዞስን ከ200 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሃብት ያፈራ የመጀመሪያው የአለማችን ሰው እንዳደረገው አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፤ ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት የ2020 የፈረንጆች አመት የአለማችን 100 ከፍተኛ ተከፋይ ዝነኞችን ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ በአልባሳትና መዋቢያ ቁሳቁስ ኩባንያዋ የምትታወቀው አሜሪካዊት ሞዴልና የሚዲያው ዘርፍ ዝነኛ ካይሌ ጄነር በ590 ሚሊዮን ዶላር አንደኛ ደረጃን ይዛለች:: አሜሪካዊው ራፐር ካንያ ዌስት በ170 ሚሊዮን ዶላር የሁለተኛነት ደረጃን ሲይዝ፣ የሜዳ ቴኒስ ሻምፒዮናው ሮጀር ፌደረር በ106.3 ሚሊዮን ዶላር፣ ፖርቹጋላዊው የአለም የእግር ኳስ ኮከር ክርስቲያኖ ሮናልዶ በ105 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ተፎካካሪው አርጀንቲናዊው የእግር ኳስ ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ በ104 ሚሊዮን ዶላር እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
የአመቱ 100 የአለማችን ከፍተኛ ተከፋይ ዝነኞች በድምሩ 6.1 ቢሊዮን ዶላር እንደተከፈላቸው የጠቆመው ፎርብስ መጽሄት፣ ክፍያው ካለፈው አመት በ200 ሚሊዮን ዶላር ዝቅ ያለ መሆኑንና ይህም ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር የተያያዘ መሆኑን አክሎ ገልጧል፡፡
ቴለር ፔሪ በ97 ሚሊዮን ዶላር፣ ብራዚላዊው የእግር ኳስ ተጫዋች ኔይማር በ95.5 ሚሊዮን ዶላር፣ ሆዋርድ ስተርን በ90 ሚሊዮን ዶላር፣ ሊብሮን ጄምስ በ88.2 ሚሊዮን ዶላር፣ ዋየኔ ጆንሰን በ85 ሚሊዮን ዶላር አመታዊ ክፍያ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከ6ኛ እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ የያዙ የአለማችን ዝነኞች መሆናቸውም ተነግሯል፡፡

 ታዋቂው የአለማችን የቴክኖሎጂ ኩባንያ ጎግል ለሰራተኞቹ ብቻ የሚፈቀድና 40 ሄክታር ስፋት ያለው አዲስ ከተማ በካሊፎርኒያ አቅራቢያ ሊቆረቁር ማቀዱን ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ሚድልፊልድ ፓርክ የተባለ ስያሜ ያለው ይህ አዲስ ከተማ፣ ደረጃውን የጠበቀ መኖሪያ ቤት፣ መደብር፣ ፓርክና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራን ጨምሮ አንድ ከተማ ሊያሟላቸው የሚገባቸው መሰረተ ልማቶች እንደሚሟሉለት መነገሩንም ቴክራዳር ድረገጽ ዘግቧል፡፡
በአዲሱ የጎግል ከተማ 1.33 ሚሊዮን ስኩየር ጫማ ስፋት ያላቸው ቢሮዎችና እስከ 1ሺህ 850 የሚደርሱ የሰራተኞች የመኖሪያ ቤቶች እንደሚገነቡበት የጠቆመው ዘገባው፤ ኩባንያው ከተማውን ለመቆርቆር የወሰነው ሰራተኞቹ ዘና ብለው በነጻነት ስራቸውን እንዲያከናውኑ በማሰብ መሆኑንም አክሎ ገልጧል፡፡
ኩባንያው የከተማውን ዲዛይን በማሰራት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፣ ተቀማጭነቱ በአውስትራሊያ ከሆነው ሌንድሬዝ ከተባለ የሪልስቴት ኩባንያ ጋር የሚከናወነው የከተማዋ ግንባታ ስራ በምን ያህል ጊዜ እንደሚጠናቀቅ ይፋ የተደረገ መረጃ አለመኖሩን አመልክቷል፡፡

 ሊቸትንስቲን በሰከንድ 229.98 ሜጋ ባይት 1ኛ፣ ደ/ ሱዳን በሰከንድ 0.58 ሜጋ ባይት መጨረሻ ሆነዋል

            ከአለማችን አገራት በብሮድባንድ ኢንተርኔት ፍጥነት ሊቸትንስቲን በ1ኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ፣ ደቡብ ሱዳን በአንጻሩ የመጨረሻውን ደረጃ መያዟን፣ ኬብል የተባለው የእንግሊዝ ተቋም ከሰሞኑ ባወጣው የአመቱ የአገራት የብሮድባንድ ኢንተርኔት ፍጥነት ደረጃ ሪፖርት አስታውቋል፡፡
ተቋሙ በአለማችን 221 አገራት ላይ የሰራውን ጥናት መሰረት አድርጎ ባወጣው የ2020 የፈረንጆች አመት የአገራት የብሮድባንድ ኢንተርኔት ደረጃ ሪፖርት እንዳለው፣ ሊቸትንስቲን ከአለማችን አገራት በአንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው በሰከንድ 229.98 ሜጋ ባይት ፍጥነት  ሲሆን፣ ደቡብ ሱዳንን ውራ ያስወጣት ደግሞ በሰከንድ 0.58 ሜጋ ባይት አዝጋሚ ፍጥነቷ ነው፡፡ ጀርሲ በ218.37፣ አንዶሪያ በ213.41፣ ጂብራልታር በ183.09፣ ሉግዘምበርግ በ118.05 ሜጋ ባይት በሰከንድ የብሮድባንድ ኢንተርኔት ፍጥነት እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ የያዙ የአለማችን አገራት መሆናቸውም ተነግሯል፡፡
በኢንተርኔት ፍጥነት አነስተኛነት ከደቡብ ሱዳን በመቀጠል እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ የያዙት አገራት የመን፣ ቱርኬሚኒስታን፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ሶርያ መሆናቸውንና ኢትዮጵያ በ1.12 ሜጋ ባይት በሰከንድ ፍጥነት ከ221 የአለማችን አገራት በ214ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝም ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
የ2020 የፈረንጆች አመት አለማቀፍ አማካይ የብሮድባንድ ኢንተርኔት ፍጥነት በሰከንድ 24.83 ሜጋ ባይት መድረሱን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ጥናቱ ከተሰራባቸው 48 የአፍሪካ አገራት መካከል 45ቱ አነስተኛ ፍጥነት ካላቸው የአለማችን አገራት ተርታ እንደሚሰለፉም አመልክቷል፡፡

Thursday, 03 September 2020 00:00

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

የIQ ደረጃችን ሲበዛብን ነው!
                           (አንዷለም ቡኬቶ ገዳ)·


               ያው ዝምታው በዛ ብለን ተመለስናል!
ድንገት ከወራት ኩርፊያ በኋላ ወደ ቀየው ብዘልቅ፣ ወገኔ ሀገራችን በ IQ ደረጃ (የማንሰላሰል ልኬት) ከመጨረሻው ረድፍ አንዲት ሀገር ብቻ በልጣ በመገኘቷ፣ እንዴት ቢደፍሩን ነው እያለ ሲንጫጫ ደረስኩ!
ወገኞች!!
እንደው መለኪያው ያን ያህል አሳማኝ አይደለም እንጂ ከተወሰኑ አመታት ወዲህ ባለው አያያዛችን እንደውም አንዲት ሀገር እንኳን መብለጣችንስ እሰየው የሚያስብልስ አይደል?
እንደው በዚያ ሰሞን እንኳን የገዛ ወገኑን ገድሎ ቀኑን ሙሉ አስፓልት ላይ ሬሳውን እየጎተተ የሚጨፍር ሰው እያየን፣ ከሁለት አመት በፊት የመዋዕለ ህጻናት መምህር ለአመታት አብሯት የኖረውን ጎረቤቷን "ከክልሌ ውጣ" በሚል ጸብ ሬሳውን በክብሪት ለመለኮስ ስትጣጣር አይተን፣ ለምርምር የሄዱ ሃኪሞች እዚህ ግባ በማይባል ምክንያት በድንጋይ ተወግረው ሲገደሉ ታዝበን፣ የሚረባ የመጠጥ ውሃ እንኳን ያላቀረብንለትን ህብረተሰብ እንወክልሃለን የሚሉት ፖለቲከኞቻችን የሚከራከሩት ስለ መጠጥ ውሃ ማበልጸግ በተበጀተ ገንዘብ መጠን ሳይሆን የዛሬ ሁለት መቶ አመት ስለ ፈሰሰው የቅድመ አያቶቻቸው ደም መሆኑን እያየን እና በዚሁም የጅል ክርክር መነሻ ጠብታ ውሃ ያላፈሰሱለትን ድሃ ህዝብ ደም የሚያፈሱ ከንቱዎች መሆናቸውን ስናይ--- በአጠቃላይ አጠገቡ ሃምሳ አመት በጉርብትና ከኖረው የሌላ ቋንቋ ተናጋሪ ጎረቤቱ ይልቅ በህይወቱ አይቶት የማያውቀውን አምስት መቶ ኪሎ ሜትር ላይ የሚገኝ የሱን ቋንቋ የሚናገር ባእድ የሚያስበልጥ፣ ብሄሬ፣: ጎሳዬ፣ ህዝቤ ደሜ፣ ጎጤ ወዘተ እያለ ኢማጅንድ በሆነ ኮሚኒቲ ውስጥ እራሱን መድቦ ሲጠዛጠዝ የሚውል፣ 80 ምናምን ቡድን ይዘን...የአውሮፓ ሀገራት “ሀገር ምን ይሰራል?!” ብለው ወደ አንድ ለመሰባሰብ ሲጣጣሩ፣ እኛ በክልልና በወረዳ ፍቅር እየናወዝን ስንጫረስ ከርመን፣ ከከተማ ከተማ እንኳን በሰላም መንቀሳቀስ ተስኖን፣ የተፈጥሮ ጸጋ ሞልቶ በተረፋት ሀገር ላይ ተቀምጠን ተመጽዋች ሆነን የቀረን ህዝቦች፣ ከአለም አንደኛ ሀገር ተረክበን በጥቂት አመታት ውስጥ የአለም መጨረሻ ለማድረግ የተሳካልን የዘመን ጉዶች ...በውጤቱ ለምን ይሆን የሚከፋን?!
ደህና ከረማችሁ ግን?!ተናፍቃችኋል!

Wednesday, 02 September 2020 00:00

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

 ወደ ኋላ ወይስ ወደፊት?
                                 (ሙሼ ሰሙ)

           ትናንትን በሚመለከት ሁላችንም በደመቀ እልልታ የምንቀበለው አንድ ዓይነት ሀቅ እንደሌለን አምናለሁ። ሀገራችን የሁላችንንም ገመና በእኩልነት፣ በአንድነትና በሚዛናዊነት መሸፈን አልቻለችም።
ለውጤቱ ደግሞ፣ የፍላጎት ሳይሆን የሁሉም ዓይነት አቅም መጉደል ያመዝንብኛል። በኢትዮጵያ ታሪክ በአንድ ወቅት ላይ አንዱን ያልገፋና በሌላ ጊዜ ደግሞ ያልተገፋ የለም። እንደ ብዝሀነታችን ሁላችንም ገፊም፣ ተገፊም አስገፊም ስለነበርን፣ ለዚህ የገመና መጋለጥ (ድህነት፣ እርዛት ጥማት፣ ቸነፈር፣ ድንቁርና ወዘተ...) መጠነ ሰፊ አስተዋጽኦ በጋራም በተናጥልም አበርክተናል።
“ትናንት” በራሱ ነባራዊ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ ለአንዳንዱ አኩሪ ትዝታውን፣ ለሌላው ጠባሳውን፣ ለአንዱ መዋቅራዊ ፈተናውን፣ ለሌላው ኢኮኖሚያዊ ጥገኝነትን፣ ለአንዱ የሀገር ባለቤትነት፣ ለሌላው ተለጣፊነትን፣ ለአንዱ ከነዘር ማንዘሩ መደምሰስን፣ ለሌላው መዋጥ መሰልቀጥን፣ ለሁላችንም ደግሞ ከእነ ጎዶሎዋም ብትሆን አንድ ሀገርን አውርሶን አልፏል። ዛሬ እዚህ እውነታ ላይ እንገኛለን። ጥያቄዬ ጉዟችን ወዴት ይሆን ነው? ወደ ኋላ ወይስ ወደፊት? ወደ ኋላ ከሆነስ ለስንት ዓመት? ወደፊት ከሆነስ በየእለት፣ እግር በእግር ወይስ አንድ እርምጃ ወደፊት፣ ሁለት እርምጃ ወደ ኋላ? የሁላችንንም መልስ ይጠይቃል?
የትናንትን ታሪክ ከመማሪያነቱና ኢ-ፍትሃዊነትን ለማረም መንደርደርያ ከመሆን ባለፈ ተጋኖ፣ ተንዛዝቶ፣ ተለጥጦና የዘር ግንድ እየተቆጠረ ሲተረክ፤ በሂደት ወደ ሂሳብ ማወራረድ መዝቀጡ አይቀርም። የታሪክ ሂሳብን ማወራረድ ማለት ደግሞ ሌላ ትርጉም የለውም፤ ዛሬን ትናንት ለማድረግ መፍጨርጨር ማለት ነው። መጀመርያም ሆነ መጨረሻ የሌለው የቁልቁለት ጉዞ! በዚህ ጉዳይ ዓለም ላይ የናኙ የዘር ጥፋቶችን መቃኘት ስንቅ ይሆናል!
የሰው ልጅን ሕይወት ለመለወጥም ሆነ ለማሻሻል ከትናንት ይልቅ ዛሬ ትልቅ ዋጋም ሆነ ሰፊ እድል አለው። ትናንትን በትናንት ነባራዊ ሁኔታና ማዕቀፍ ውስጥ እየመዘንን፣ ዛሬን ግን ለለውጥ ለእድገት ለመሻሻል መጠቀም አስተዋይነት ነው። ብዙ ወደ ኋላ ከማለም፣ ጥቂትም ቢሆን ወደፊት ማለም ያዋጣል።
“ወደ ኋላ እየሄድሽ በሃሳብ ከማለም”
ቀኑ እንዳይመሽብሽ ትናንት ዛሬ አይደለም”
--ብሏል ዕውቁ አቀንቃኝ ሙሉቀን መለሰ።Tuesday, 01 September 2020 10:55

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

እንዴት ነህ ህዝቤ? ዘውድአለም ታደሠ

           (አማን መዝሙር)
እንዴት ውለሃል አንተ ስመ ብዙ ህዝብ? ሐገር አማን ነው ወይ? እንደው አንተን ህዝብ ዝም ብዬ የጎሪጥ ስሾፍህኮ እያናደድክ ታሳዝነኛለህ፤ የምር! ደሞ የስምህ ብዛት ... ከሃምሳ ምናምን አመት በፊት ጃንሆይ ያቺን የባቄላ ፍሬ የምታህል ውሻቸውን ፀጉር ዳበስ እያደረጉ «ኩሩው ህዝባችን» ብለው የጠሩህ .. ደርግ መጥቶ ኩሩው የሚለውን ስም ላሽ ብሎ «ጭቁኑ» እያለ የሰየመህ!
በመራራ ትግል ደርግን ጥሎ የመጣው መንግስት ደግሞ ምስኪኑ .. ሰላም ወዳዱ ... ልማታዊው ምናምን እያለ የወል ስም የሰጠህ ... አንዳንዱ ደግሞ እንደ ሰንበቴ ድፎ እየቆራረሰህ ትምክህተኛ፣ ጠባብ፣ ዘረኛ፣ እያለ እንደ ክርስትና ልጁ ስም ሲያወጣልህ አሜን ብለህ የኖርክ፣ ወሰድ ሲያደርግህ ደግሞ ባወጡልህ ስም እየተጠራራህ ስትቧቀስ የከረምክ! ጥሪትህ ትንሽ ስምህ ብዙ የሆንክ፤ እንደ ኬኔዲ መንገሻ ድምፅ አንጀት የምትበላ ህዝብ! ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል የሚል ተረት እየተረትክ፣ ስትፅናና የመቃብር ስፍራ 40 ሺ ብር ገብቶብህ ግራ የገባህ! ትከሻህ እንደ ሴቶች ቦርሳ ሁሉን የሚሸከም፤ የችግር ቤተ-ሙከራ የሆንክ ህዝብ እንዴት ነህ?
ለዘመናት ረሀብና ችጋር መሃል ባልገባ እየተጫወተብህ «ጎተራው ሙሉ፣ ሐገሩ ጥጋብ» ምናምን በሚል ዘፈን ወገብህ እስኪሰበር እስክስታ የምትወርድ፣ ውሃ እንደ ሌባ በሌሊት መጣች አልመጣች ብለህ ተሰልፈህ እየቀዳህ «እምዬ ሐገሬ ፏፏቴሽ ማማሩ» በሚል ዘፈን የምትቦርቅ፣ ጎንህን የምታሳርፍበት ሃሳብ መስጫ ሳጥን የምታህል ጎጆ ተነፍጎህ «ጋራው ሸንተረሩ» ምናምን እያልክ ራስህ ላይ ሙድ የምትይዝ .. የአለም ቀበሌ “የደሃ ደሃ” የሚል መታወቂያ የሰጣት ሐገር ላይ እየኖርክ፣ ዘፈን ላይ ያለችውን ጥጋብ በጥጋብ የሆነች ሐገር የሙጥኝ ብለህ ግራ ተጋብተህ አለምን ግራ የምታጋባ፣ ዘጠኝ የኔታ የማይፈታህ ቅኔ የሆንክ ፍጡር!
ሐገር ውስጥ አቧራና ትቢያ አማሮህ በሊቢያ አቆራርጠህ፣ ባህር ማዶ ከተሻገርክ በኋላ «የኩበቱ ሽታ ናፈቀኝ» እያልክ የምታለቃቅስ ፕሮፌሽናል አዝግ ህዝብ! የተሾመ ሁሉ ቫንዳም ቫንዳም ሲጫወትብህ፣ የእድር ዳኛ እንኳ ባቅሙ አናትህ ላይ ሱቅ ካልከፈትኩ እያለ ሲያማርርህ፣ ሐገርህ ላይ ሶስት ምስክር ጠርተህ ካገኘኸው የቀበሌ መታወቂያ ውጪ ቤሳ ቤስቲ አጥተህ እንዳልኖርክ ሁሉ፤ ሰው ሐገር ሄደህ እህል በልተህ ነፍስህ መለስ ስትል «ምን አለኝ ሐገሬ?» እያልክ ነጠላ ዜማህን የምትለቅ አላጋጭ ፍጥረት!
ዋሽተህ አጣልተህ ዋሽተህ የምታስታርቅ፣ እንደገና ዋሽተህ የምታጣላ ስራ ፈት፣ እንቦጭን በሚያስንቅ የመራባት ጥበብህ መቶ ሚሊዮን የዘለልክ! የምትበላው ሳይኖርህ የሚበሉ ልጆች ፈልፍለህ የምታሳድግ ታምረኛ ዜጋ! ምን የመሰለ የፍቅር ዘፈን ላይ ጦርና ጎራዴ ይዘህ የምትሸልል ጀብደኛ ማህበረሰብ! ብዙ ሰው ከፈወሰው አክሊሉ ለማ ይልቅ ብዙ ሰው የገደለን ሽፍታ የምታወድስ! «ገዳይ ገዳይ ያልሽው አባትሽ አይገድል፣ አርሶ ያብላሽ እንጂ ሆድሽ እንዳይጎድል» እያልክ ከገበሬ ይልቅ ነፍሰ ገዳይነትን ሙያ አድርገህ በረሃብ የምታልቅ ምስኪን ማህበረሰብ!
አያትህ ድንጋይን እንደ ዝግባ ዛፍ ጠርቦ፣ የኪነ-ህንፃ ህግን በመሻር ከላይ ወደ ታች ቤተ መቅደስ ቀለሰ፣ አለት እንደ ቢላዋ ሞርዶ ጡብ እንደ እርሳስ ቀርፆ ስልጣኔውን በአንድ ሃውልት ላይ አተመ፣ ከቅጠላ ቅጠል ውብ ቀለማትን ጨምቆ ፍልስፍናውን በብራና ላይ አኖረ! አንተ ድንጋይ ስታይ ወደ ጭንቅላትህ የሚመጣው ግዙፍ ቤተ መቅደስ መቀለስ ሳይሆን እንደ ቃየን ወንድምህን መፈንከት ነው! አዎ አባትህ ንፋስ ስልክ ቀለም ፋብሪካ ከመፈጠሩ ከሺህ አመታት በፊት ከዛፍ ቅጠል ውብ ቀለማትን ፈጥሯል! አንተ ልጄ በለጬ ወይም ገለምሶ ካልሆነ ወደ ቅጠል ፊትህን አታዞርም! ላንተ ቅጠል ሁሉ የሚከፈለው በሁለት ነው ... የሚቃምና የማይቃም! አያቶችህ ከሺህ አመታቶች በፊት “ገዳ” የሚባል ድንቅ ስርአት ዘርግተው አለምን አስደመሙ! ከአለም ቀድመው ዘመኑ፣ ከአለም ቀድመው የሞራል ልእልናቸውን አስመሰከሩ! አለምን አስተማሩ! አለም “Adoption”ን ከማወቋ በፊት አያቶችህ “ጉዲፈቻ” ብለው ጀምረውታል! አሜሪካ asylum መስጠት ከመጀመሯ በፊት አያቶችህ “ሞጋሳ” ብለው በቀለምና በባህል ለማይመስላቸው ስደተኛ መኖሪያ ስፍራና ዜግነት ይሰጡ ነበር! አንተ ዘንድሮም ስለ ሰው ልጆች አልገባህም፣ ሁለት የህዝብ ሽንት ቤትና አንድ ቦኖ ውሃ ካላት ቀበሌዬ ውጡ እያልክ ወገኖችህን ታሳድዳለህ! አያቶችህ ግን በገዳ ህግ ውስጥ ከሺህ አመታት በፊት ስለ እንስሳት መብትና አያያዝ አርቅቀው ነበር!
አያቶችህ ፊደል ቀርፀው እውቀትና ጥበባቸውን በራሳቸው ቋንቋ ውስጥ ሸሸጉ፤ ግእዝ ፣ እዝል ፣ አራራይ ብለው የራሳቸውን ዜማ ቀመሩ፣ ሰባቴ በወደቁ ጊዜ ከትሏ መነሳትን ተማሩ! ጥጥ አቅጥነው የራሳቸውን አልባሳት ፈበረኩ፣ ሸንበቆ ቦርቡረው ዋሽንት ሰሩ፣ ጅማት ወጥረው መሰንቆ ፈለሰፉ፣ ቆዳ ፍቀው ከበሮ ወጠሩ፣ አያቶችህ በራሳቸው ፍቅር የወደቁ፣ ማንንም የማይኮርጁ፣ ማንንም የማይመስሉ ነበሩ! ቋንቋቸው ፣ ህጋቸው፣ አልባሳቸው፣ የሙዚቃ መሳሪያቸው፣ ዜማቸው ... ሁሉ ማንንም አይመስልም ነበር! አያቶችህ የሰውን የፈጠራ ውጤት እንደ መና ተቀምጠው የሚጠባበቁ አልነበሩም! ራሳቸው ፈጣሪዎች ነበሩ! ፈላስፋና ልሂቃን ነበሩ!
አንተስ? በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን “ከተፀዳዳህ በኋላ እጅህን ታጠብ” ተብለህ የምትመከር፣ ከኢኳቶሪያል ጊኒ ቀጥሎ በመሀይምነት አንደኛ ወጥተህ (ጊኒን ግን እንዴት በለጥካት?) ፤ፖለቲካን ከፖለቲካ ልሂቃኑ በላይ ተዘፍዝፈህ የምትተነትን ደፋር! ጀነን ብለህ አደባባይ መሃል የመንግስት ስልክ እንጨት በሽንትህ የምታጠጣ “ሐገር ወዳድ” ህዝብ! «ጫልቱ»ን የመሰለ ውብ ስም ስድብ መስሎህ ልታንጓጥጥ የምትሞክር፣ የኢትዮጵያ ፓስፖርት ይዘህ “ዳውን ዳውን ኢትዮጵያ!” ስትል የምትውል፣ «ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ» ስትል እየዋልክ ሱርማውን፣ ከፊቾውን፣ ሽናሻውን፣ መዠንገሩን፣ ከእነ መፈጠራቸው የማታውቅ፣ አንድ ደሃ በቆንጨራ ገድለህ ብሔርህን ነፃ ያወጣህ የሚመስልህ፣ ባጭሩ ብሔርተኝነቱንም፣ አሃዳዊነቱንም በቅጡ ሳትችልበት ቀርተህ፣ የአለም መዝናኛ ሆነህ የቀረህ ድፍን መንጋ!
ኑሮ እንዴት ይዞሃል? ረሃብና ድህነት እንዴት እያደረገህ ነው? አሁንም ፀጉርህን በተልባ ፈርዘህ ቺክ ትጀነጅናለህ ወይ? አሁንም የነጋዴ በግ ቀምተህ ሆድህን ትሞላለህ ወይ? አሁንም ሽማግሌን በጠረባ እየጣልክ ቫንዳም ቫንዳም ትጫወታለህ ወይ? አሁንም ዋሊያ ቢራ ጠጥተህ ቆርኪውን ትፍቃለህ ወይ? አሁንም “እኔ ነኝ ያለ” በሚል ዘፈን ልብህ ተነፍቶ፣ በባዶ ሜዳ ትወራጫለህ ወይ? አሁንም ሰው ለፍቶ የገዛውን ቦቴ መኪናና ግሮሰሪ እያቃጠልክ ሰልፊ ትነሳለህ ወይ? አሁንም ኳስ ሜዳ መሀል ምስኪን ዳኛ ደብድበህ፣ በኩራት ትንጎራደዳለህ ወይ? ደህና ነህ ወይ? አማን ነህ ወይ?

 በሰከንድ 178 ቴራባይት ፍጥነት አለው
 
        የእንግሊዙ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለንደን ተመራማሪዎች በአለማችን የኢንተርኔት ፍጥነት አዲስ የአለም ክብረ ወሰን ያስመዘገቡበትንና በአንድ ሰከንድ 178 ቴራባይት መጠን ያለው መረጃ ማስተላለፍ የሚያስችለውን አዲስ የምርምር ውጤት ከሰሞኑ ይፋ ማድረጋቸው ተዘግቧል፡፡
ተመራማሪዎቹ ይፋ ያደረጉት የኢንተርኔት ፍጥነት ከዚህ በፊት በክብረ ወሰንነት ተይዞ ከነበረው የኢንተርኔት ፍጥነት በ20 በመቶ ያህል እንደሚበልጥ የጠቆመው የኢንዲፔንደንት ዘገባ፤በአንዲት ሰከንድ እጅግ በርካታ መጠን ያለውን መረጃ በማስተላለፍ አቻ እንደማይገኝለትም ገልጧል፡፡
በታዋቂው የኔትፍሊክስ ድረገጽ ላይ ያሉትን መረጃዎች በሙሉ በአንድ ሰከንድ ዳውንሎድ ማድረግ ያስችላል የተባለውን ይህንን ፈጣን የኢንተርኔት ኮኔክሽን ለመፍጠር፣ ከተለመዱት የተለዩና የተራቀቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሰራሮችን መከተላቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡ ተመራማሪዎቹ አዲስ የአለም ክብረ ወሰን ያስመዘገቡበትን የምርምር ስራ ለስኬት ያበቁት ኤክስቴራ እና ኬዲዲአይ ከተባለ የምርምር ተቋም ጋር በአጋርነት ባከናወኑት ፕሮጀክት መሆኑንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Page 9 of 499