Administrator

Administrator

 የአንጋፋው ደራሲ አበራ ለማ “ቅንጣት - የኔዎቹ ኖቭሌቶች” የተሰኘ አዲስ የልብወለድ መፅሃፍ ሰሞኑን ለገበያ ቀረበ፡፡ በ264 ገፆች የተመጠነው መፅሃፉ፤ በ70 ብር እንደሚሸጥ ታውቋል፡፡
ነዋሪነቱን በኖርዌይ ያደረገው ደራሲው፤ በበርካታ የአጫጭር ልቦለድና የግጥም መድበሎቹ የሚታወቅ ሲሆን ከቀደምት ሥራዎቹ መካከል፡- “ኩል ወይም ጥላሸት” (የግጥም መድበል)፣ “ሸበቶ” (የግጥም መድበል)፣ “ሕይወትና ሞት” (የአጫጭር ልቦለዶች መድበል)፣ “ሞገደኛው ነውጤ” (ኖቭሌት) እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡
በ1980ዎቹ የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ዋና ፀሃፊ ሆኖ ያገለገለው አበራ ለማ፤ በአሁኑ ሰዓት በኖርዌይ ደራስያን ማህበር የመጀመርያውና ብቸኛው ጥቁር እንዲሁም በአፍ መፍቻው ቋንቋ የሚፅፍ አባል ደራሲ ነው ተብሏል፡፡

“የቤት ሥራ” የቴሌቪዥን ድራማ በቅርቡ መታየት ይጀምራል
   በጋዜጠኛና ፀሐፌ ተውኔት ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ ተደርሶ፣ በካሌብ ዋለልኝ የተዘጋጀው “ከትዳር በላይ” የተሰኘ ዘመናዊ ኮሜዲ ቲያትር የፊታችን ረቡዕ  ከ11፡30 ጀምሮ በብሄራዊ ቴአትር ይመረቃል፡፡ ቲያትሩ በየሳምንቱ ዘወትር ረቡዕ በተመሳሳይ ሰዓት በዚሁ ቴአትር ቤት እንደሚታይ ታውቋል፡፡ በሌላ በኩል በቴዎድሮስ ተ/አረጋይ እና በሰዓዳ መሃመድ ተደርሶ፣ በኢሳያስ ግዛው የሚዘጋጀው “የቤት ሥራ” የቴሌቪዥን ድራማ፣በያዝነው ወር መጨረሻ ላይ በኢቲቪ-1 መታየት እንደሚጀምር ተገለፀ፡፡ በቴዎድሮስ የትያትር ኢንተርፕራይዝ ፕሮዱዩሰርነት የሚቀርበው የቲቪ  ድራማ፤ በትዳርና በቤተሰብ ግንኙነት ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው ተብሏል፡፡ በድራማው ላይ አርቲስት ሽመልስ አበራ፣ ሰላም ተፈሪ፣ ስዩም ተፈራ፣ ቶማስ ቶራ፣ ጀምበር አሰፋ፣ ሳምሶን ታደሰ (ቤቢ) እንደሚተውኑበት ለማወቅ ተችሏል፡፡

  በወግ ፀሐፊነቱ የሚታወቀው በኃይሉ ገ/እግዚአብሔር የጻፋቸው በማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ መጣጥፎች የተካተቱበት “ኑሮ እና ፖለቲካ- ቁ 3” የተሰኘ አዲስ መፅሃፍ ትትሞ ለንባብ ቀረበ፡፡ መፅሃፉ ቀላል የማይባሉ አዳዲስ ሥራዎች እንደተካተቱበት የጠቆመው ደራሲው፤ ቀድሞ የተሰሙና የተደመጡትም እንኳ በደጋሚ እንዲነበቡ ተደርገው በደንብ መቃናታቸውንና አዳዲስ ነገር እንደተጨመረባቸው ለአዲስ አድማስ አስታውቋል፡፡ በ157 ገፆች የተቀነበበው መፅሀፉ፤ለአገር ውስጥ በ40.50፣ለውጭ አገር በ15 ዶላር ይሸጣል፡፡  ደራሲው ከዚህ ቀደም “መንታ መልኮች”፣ “ኑሮ እና ፖለቲካ” (ቁጥር 1 እና 2) የሚሉ መጻህፍትን ያሳተመ ሲሆን በተለያዩ የፕሬስ ውጤቶች ላይ በአሽሙር የተጠቀለሉ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ወጎችን በማቅረብም ይታወቃል፡፡

“ቦቃፍ ቡሬ” የተሰኘ አዲስ የኦሮምኛ ኮሜዲ ፊልም፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ባለፈው ሳምንት ሐምሌ 12፣ በኦሮምያ የባህል ማዕከል በተከናወነ ደማቅ ስነ-ስርዓት የተመረቀ ሲሆን በሲዲ ለሽያጭ እንደቀረበም ታውቋል፡፡
በታምራት አዳሙ ተጽፎ በታዴማ ሚዲያ ኤንድ ኢቨንት ኦርጋናይዘር ኤክስኪዩቲቭ ፕሮዲዩሰርነት እና በኢሉ ኮ ፕሮዳክሽን ተሰርቶ የቀረበውን #ቦቃፍ ቡሬ#፣ ዳይሬክት ያደረገው ራሱ ታምራት ሲሆን የአንድ ሰዓት ከ30 ደቂቃ ርዝማኔ አለው፡፡ሰርቶ ለማጠናቀቅ 7 ወር በፈጀው በዚህ ፊልም ላይ አንጋፋው ተዋናይ አድማሱ ብርሃኑና ኦሊ ነጋ በመሪ ተዋናይነት የተጫወቱበት ሲሆን ሌሎች ከ15 በላይ አንጋፋና ወጣት ተዋንያንም ተሳትፈውበታል ተብሏል፡፡

 በመስከረም አበራ የተፃፉ የተለያዩ ፖለቲካዊ መጣጥፎችን ያካትተው “ስለ ስልጣን” የተሰኘ አዲስ መፅሃፍ ሰሞኑን ታትሞ ለንባብ ቀረበ፡፡ መፅሃፉ በ7 ምዕራፎች የተከፋፈለ ሲሆን  “የብሄር ፖለቲካችን”፣ “የአቶ መለስ ትዝታዎች”፣ “ቅይጥ ፖለቲካዊ ጉዳዮች” እና ሌሎችም ርዕሶችን አካትቷል፡፡
በ230 ገፆች የተቀነበበው “ስለ ስልጣን”፤ በ57 ብር ከ65 ሳንቲም ለገበያ ቀርቧል፡፡
ፀሃፊዋ በተለያዩ የፕሬስ ውጤቶች ላይ ፖለቲካዊ መጣጥፎችን በማቅረብ ትታወቃለች፡፡

Monday, 27 July 2015 11:15

የኪነጥበብ ጥግ

(ስለ ኮሜዲ)
እኔ ጣቴን ስቆርጥ ትራጄዲ ነው፡፡ አንተ ክፍት ቱቦ ውስጥ ገብተህ ስትሞት ኮሜዲ ነው፡፡
ሜል ብሩክስ
ህይወት፡- ለብልሆች… ህልም፣
       ለሞኞች… ጨዋታ፣
       ለሃብታሞች … ኮሜዲ፣
       ለድሆች … ትራጀዲ ነው፡፡
                    ሻሎም አሌይቼም
የኮሜዲ ሥራ ሰዎችን እያዝናኑ ከጥፋታቸው ማረም ነው፡፡
ሞሌር
ኮሜዲበ ሌሎች ሰዎች ላይ የሚከሰት ትራጄዲ ነው፡፡
አንጄላ ካርተር
ሳቅንና ስቃይን፣ ኮሜዲንና ትራጄዲን፣ ጨዋታንና ጉዳትን የሚለይ ቀጭን መስመር አለ፡፡
ኢርማ ቦምቤክ
ህይወት በቅርት ሲታይ ትራጀዲ፣ በርቀት ሲታይ ኮሜዲ ነው፡፡
ቻርሊ ቻፕሊን
የኮሜዲ ትርኢት ላይ የምትመጡት ለመዝናናት ነው፡፡
ቢል ኮስቢ
የራስን ዝምታ ማዳመጥ የኮሜዲ ቁልፍ ነው።
ኢላይኔ ቡስለር
ኮሜዲ ለሰው ልጅ ብቸኛ ተስፋ ነው፡፡
ሮዝአኔ ባር
ነፃ ትግል ለእኔ እንደ ስታንድ አፕ ኮሜዲ ነበር፡፡
ዲዋይኔ ጆንሰን
እውነተኛ ኮሜዲ ሰዎች እንዲስቁና እንዲያስቡ ብቻ ሳይሆን እንዲስቁና እንዲለወጡም ያደርጋል፡፡
ሳም ኪኒሶን
ኮሜዲ የሚመነጨው ከውዥንብር ነው፡፡
ቪር ዳስ
ኮሌጅ በመሄድ ፋንታ ኮሜዲ መስራትን መረጥኩ፡፡
ቦ ቡርንሃም

    ክብደትን መቀነስ የልብ በሽታን ለማስወገድ ትክክለኛውመንገድ ነው፡፡ ከፍተኛ የሰውነት ክብደት የደም ቅዳ ሴሎቻችን እንዲጠቡ ያደርጋቸዋል፡፡ በዚህ ሳቢያም የኮሌስትሮል ዝቃጮች እንዲሰበሰቡና እጢ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ ይህ ደግሞ አደገኛ የልብ ህመም እንዲከሰትብዎ ምክንያት ይሆናል፡፡ ክብደትዎን በመቀነስ በተለይም የሆድ አካባቢ ቦርጭዎን በማጥፋት የደም ቅዳ ሴሎች ሥራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ ይርዱዋቸው፡፡

         የምግብዎን ዓይነት እና መጠን ያስተካክሉ

    ለመልካም ጤንነት ከሚመከረው የምግብ ዓይነትና መጠን በላይ መመገብ ለከፍተኛ የሰውነት ክብደትና የኮሌስትሮል መጠን ያጋልጣል፡፡ የሚመገቡት ምግብ በዓይነቱና በመጠኑ የተስተካከለ እንዲሆን ያድርጉ፡፡ ከየዕለታዊ  የምግብ ገበታዎ ላይ አትክልትና ፍራፍሬዎች መኖራቸውን ያረጋግጡ፡፡ ገበታዎ የተመጠነ እንዲሆንም ያድርጉ፡፡
ጭንቀትዎን ያስወግዱ
ከፍተኛ ጭንቀት የደም ግፊት ይጨምራል፡፡ በደም ቅዳዎች ውስጥ እጢ እንዲፈጠር የሚያደርጉ ነገሮችንም ያባብሳል፡፡ ይህም ለልብ በሽታ ያጋልጣል፡፡ ከልብ በሽታ ለመጠበቅ ከፈለጉ ጭንቀትና ውጥረትን ያስወግዱ፡፡
ያልተፈተጉ/ ገለባቸው ያልተለየ/ እህሎችን ለምግብነት ይምረጡ
ገለባው ያልተነሳላቸውት (ያልተፈተጉ/እህሎች ጥሩ የአሰርና የሌሎች አልሚ ምግቦች ምንጮች ናቸው፡፡
    እንደ ቫይታሚን ኢ፣ ታያሚን፣ ሪቦፍላቪንና ናያሊን ያሉ ቫይታሚኖች እንዲሁም ማግኒዚየም፣ ፎስፈረስ፣ ዚንክና ብረት መሰል ማዕድናት የሚገኙት ባልተፈተጉ እህሎች ውስጥ ነው፡፡ ባልተፈተጉ እህሎች ውስጥ የሚገኙት ቫይታሚኖችና ማዕድናት፣ የደም ግፊትንና የልብ ጤንነትን በመቆጣጠሩ ረገድ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል ለምሳሌ ለመጥቀስ ያህል ካልተፈተገ ገብስ ወይም ስንዴ የተሰሩ ዳቦዎች፣ ቡናማ ሩዝ፣ ካልተፈተገ በቆሎ የሚሰሩ ምግቦች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
አነስተኛ የስብ መጠን ያላቸውን የፕሮቲን ምንጮች ይምረጡ
ቀይ ሥጋ፣ ዶሮና ዓሳ አነስተኛ የስብ መጠን ያላቸው የፕሮቲን ምንጮች ናቸው፡፡ የእንቁላል ነጩ ክፍል፣ የወተት ተዋፅኦዎችም ከአነስተኛ የስብ መጠን ውስጥ የሚመደቡ ናቸው፡፡ ዓሣ አነስተኛ የስብ መጠን ያለው የፕሮቲን ምንጭ ነው፡፡ የተወሰኑ የዓሣ ዓይነቶች ደግሞ የደም ውስጥ ስቦችን በመቀነስ በድንገተኛ የልብ ህመም የመሞት አደጋን በሚቀንሱትና ኦሜጋ 3 ፋቲ አሲድ ተብለው በሚታወቁ ማዕድናት የበለፀጉ ናቸው፡፡ ሌሎች ኦሜጋ 3 ፋቲ አሲዶች ምንጮች አኩሪ አተርና ተልባ ናቸው፡፡
በምግብ ውስጥ የሚኖረውን የጨው መጠን ይቀንሱ
ብዙ ጨው መመገብ ለከፍተኛ የደም ግፊት አስተዋፅኦ በማድረግ ለስርዓተ ልብ መዛባት ችግር ያጋልጣል፡፡ በምግባችን ውስጥ የሚገኘውን ጨው መቀነስ ጤናማ ልብ እንዲኖረን ከሚረዳን የአመጋገብ ሥርዓት ውስጥ ዋንኛው ነው፡፡ አንድ ጤናማ ሰው በቀን ውስጥ መውሰድ የሚኖርበት የጨው መጠን ከአንድ የሻይ ማንኪያ መብለጥ የለበትም፡፡
ኦቾሎኒ ለልብ ጤንነት
እንደ መክሰስ ያለ ነገር ካማረዎ፣ ኮሌስትሮል በመቀነስ የታወቀውን ኦቾሎኒ ይጠቀሙ፡፡
ኦቾሎኒ ጉዳት በማያስከትሉ ስቦች የተሞላና ጎጂ ስቦችን ከሰውታችን በማስወገድ የሚታወቅ ምግብ ነው፡፡     በርካታ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፤ በየዕለቱ ጥቂት ኦቾሎኒን የሚመገቡ ሰዎች ከልብ በሽታ የመያዝ ዕድላቸው በእጅጉ ቀንሶ ተገኝቷል፡፡ ኦቾሎኒ በከፍተኛ ስብና ካሎሪ የተሞላ ስለሆነ በአንድ ጊዜ ከአንድ እፍኝ  በላይ አይጠቀሙ፡፡ በስኳር ወይም በቸኮሌት ጣፍጠው ከተዘጋጁ ኦቾሎኒዎች ይጠበቁ፡፡
የአካል እንቅስቃሴ ያድርጉ
በሳምንት ለ5 ቀናት በቀን ለ30 ደቂቃ ያህል ቀለል ያሉ የአካል እንቅስቃሴዎችን ያድርጉ፡፡ እንደ ኤሮቢክስ ያሉ ወይንም የልብን ጡንቻዎች ለማሰራት ይጠቅማሉ እንደሚባሉት የእግር ጉዞ አይነት እንቅስቃሴዎች በልብ ድካምና በሌሎች የልብ በሽታዎች የመጠቃት ዕድልን ይቀንሳሉ፡፡ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች በበዙ ቁጥር ጠቀሜታቸውም በዚያው ልክ እየጨመረ ይሄዳልና፣ በየዕለቱ አካላዊ እንቅስቃሴ ያድርጉ፡፡

  የታይፎይድ አምጪ ባክቴሪያ የሚከሰተው በሰው ላይ ብቻ ነው
            ለበሽታው የሚታዘዙ አብዛኛዎቹ መድኀኒቶች ከበሽታው ጋር ተላምደዋል
    አብዛኛውን ጊዜ በተበከለ ምግብና ውሃ ሳቢያ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈውና በተለምዶ የአንጀት ተስቦ እየተባለ የሚጠራው ታይፎይድ መነሻው “ሳልሞኔላ ታይፊ” የሚባል ባክቴሪያ ነው፡፡ ይህ ባክቴሪያ የሚኖረው (ህይወት የሚያገኘው) በሰው ልጅ አንጀት ውስጥ ብቻ ነው፡፡
በሽታው በሽታ አምጪ በሆነው ባክቴሪያ በተበከለ ምግብና መጠጥ አማካኝነት በወረርሽኝ መልክ ሊከሰት ይችላል፡፡
በበሽታው የተያዘ ሰው በጥቂት ቀናት ውስጥ ምልክቶችን ማሳየት ይጀምራል፡፡ ከበሽታው ምልክቶች መካከል ትኩሳት ዋንኛው ሲሆን ራስ ምታት፣ ሰውነትን የመቀረጣጠፍና መገጣጠሚያ አካባቢ የሚኖር የህመም ስሜት ከምልክቶቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸነው፡፡
እ.ኤ.አ በ1862 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን 16ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት አብርሃም ሊንከን ለሞት ማብቃቱ የሚነገርለት ታይፎይድ አሁንም በዓለማችን በየዓመቱ ከ220 ሺህ በላይ ሰዎችን ለሞት እየዳረገ ይገኛል፡፡
ከጥቂት የሰሜን አፍሪካ አገራትና ከደቡብ አፍሪካ በስተቀር በመላው የአፍሪካ አገራት በስፋት መኖሩ የሚነገረው የታይፎይድ በሽታ በተለይ የሃሞት ከረጢት እና እጢ ያለባቸው ሰዎች በይበልጥ ያጠቃል፡፡ ባክቴሪያው ከአንጀት ውስጥ በደም ተሸካሚነት ወደ ሃሞት ከረጢት ሊሄድና በዚያ ተደብቆ ህመምተኛውን ሊያጠቃና በሰገራ አማካኝነት ወደሌሎች ሰዎች ሊተላለፍ ይችላል፡፡
ሳልሞኔላ ታይፊ በሚባል ባክቴሪያ ሳቢያ የሚከሰተውን ይህንኑ የታይፎይድ በሽታ ለማከም ጥቅም ላይ የሚውሉት መድኀኒቶች በአብዛኛው ከበሽታው ጋር የመላመድ ባህርይን አምጥተዋል፡፡
ቀደም ሲል በጥቅም ላይ ይውሉ የነበሩና የታይፎይድ በሽታን ለማከም ያገለግሉ ከነበሩ መድኀኒቶች መካከል አሞክሳሲሊን፣ ክሎሞፌኒከልና፣ ስትሬፕቶማይሰን የተባሉት መድኀኒቶች ሙሉ በሙሉ ከበሽታው ጋር በመላመዳቸውና የሚያስከትሉት የጎንዮሽ ጉዳቶችም እየጨመሩ በመምጣታቸው ከአገልግሎት ውጪ እንዲሆኑ እየተደረጉ ነው፡፡
 በአሁኑ ወቅት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው ሲፕ ሮፋሎክሳሲን የተባለው መድኀኒት ነው፡፡
በሽታው በወቅቱ ህክምና ካላገኘ ለሞት ሊዳርግ የሚችልና በቀላሉ ከሰው ወደሰው በተበከለ ምግብና መጠጥ ሳቢያ ሊተላለፍ የሚል በሽታ ነው፡፡
 በተለይ እንዲህ ክረምት በሚሆንባቸው ወቅቶች ለመጠጥነት የምንጠቀመውን ውሃና የምንመገበውን ምግብ በጥንቃቄ መያዙ በታይፎይድ ከመያዝ እንደሚታደገን ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

ሳምሰንግ ኤሌክትሮኒክስ ለምርቶቹ የጥገና አገልግሎት የሚሰጥበት የደንበኞች አገልግሎት ማዕከል በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከፈተ፡፡
ለሳምሰንግ ሞባይልና ለሁሉም የሳምሰንግ ኤሌክትሮኒክ ምርቶች የጥገና አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል የተባለውንና በአዲስ አበባ ከተማ ቴሌ መድኀኒዓለም አካባቢ የተቋቋመውን የደንበኞች አገልግሎት ማዕከል ከትናንት በስቲያ መርቀው የከፈቱት የኩባንያው የኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ታዲዮስ አወል ናቸው፡፡ ማዕከሉ ከጥገና በተጨማሪ (Software upgrades, application installation, new devises setup) አገልግሎቶችን ይሰጣል፡፡ አጠቃላይ የማማከር አገልገሎትም ለደንበኞቹ እንደሚሰጥ አቶ ታዲዮስ ተናግረዋል፡፡
ማዕከሉ የዋስትና ፈቃድ ላላቸውም ሆነ ለሌላቸው የሳምሰንግ ምርቶች አገልግሎቱን እንደሚሰጥ የጠቆሙት አቶ ታዲዮስ፤ ደንበኞች ጥራት ባላቸው የመለዋወጫ ዕቃዎች በሙያው በተካኑ ባለሙያዎች የህግና ሌሎች አገልግሎቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲያገኙ እንደሚደረግ ገልፀዋል፡፡
 እንደፍሪጅ እና የልብስ ማጠቢያ ማሽን ላሉና የትራንስፖርት ወጪን ለሚጠይቁ የሳምሰንግ ምርቶች የማዕከሉ የጥገና ባለሙያዎች ቤት ለቤት በመሄድ አገልግሎቱን እንደሚሰጡና ይህንንም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገልጿል፡፡

 አስደማሚ … አስገራሚ … አስደናቂ እውነታዎች!?
          የኬንያው ጠንቋይ፤ “ኦባማ የአባቱን አገር ይጎበኛል” ሲል ተነበየ
             “የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ይሆናሉ ብሎ ተንብዮ ነበር” (USA Today)
   ባራክ ኦባማ በፕሮግራም መጣበብ የተነሳ በኬንያ ቆይታቸው የአባታቸውን የትውልድ ሥፍራ (ኮጌሎ) ለመጎብኘት እንደማይችሉ እየተነገረ ቢሆንም ዕውቅ አንድ የኬንያ ጠንቋይ ፕሬዚዳንቱ የአያት ቅድመ አያቶቻቸውን አገር ይጎበኛሉ ሲል ሰሞኑን ተንብየዋል፡፡
ጆን ዲሞ የተባለው የኮጌሎ ጠንቋይ፤ ኦባማ በእርግጠኝነት የአባታቸውን የትውልድ ቀዬ እንደሚጎበኙ ታይቶኛል ብሏል፡፡ ኦባማ እስካሁን ኮጌሎን እንደሚጎበኙ ማረጋገጫ ባይሰጡም የመንደሩ ነዋሪዎች ግን አሁንም በተስፋ እየጠበቁ ነው፡፡ ስለዚህም ምናልባት ከመጡ በሚል ዝግጅታቸውን ቀጥለዋል፡፡
“እመኑኝ … ኦባማ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ይሆናል ብዬ ነበር፤ ሆነ፡፡ አሁንም የወላጆቹን የትውልድ ቀዬ የመጎብኘት ዕቅድ እንዳለው ታይቶኛል፡፡ ይመጣል፡፡” ሲል ተንብየዋል ዲሞ፡፡ ጆን ዲሞ እ.ኤ.አ በ2006 ዓ.ም ኦባማ ፕሬዚዳንት ይሆናሉ ብሎ መተንበዩን “ዩኤስኤ ቱዴይ” አስታውሷል፡፡ “ውጤቱ ኦባማ ኮጌሎ እንደሚመጣ ነው የሚጠቁመው፡፡ ይሄ ትልቅ ምስጢር ነው፡፡ የቅድመ አያቱን አገር እንደሚጎበኝ ለማንም መንገር የለበትም!” በማለት ጠንቋዩ በጉጉት ለተሞሉት የመንደሯ ነዋሪዎች ተናግሯል፡፡ ኦባማ በትላንትናው ዕለት ኬንያ የገቡ ሲሆን የሦስት ቀናት ጉብኝት ያደርጋሉ፡፡ በምዕራባዊ ኬንያ የሚገኘው የኮጌሎ መንደር፤ የአያቱ የሳራ ኦባማ የትውልድ ሥፍራ ሲሆን የአባቱ የባራክ ኦባማ (ሰር) የቀብር ስፍራም ያለው እዚያው ነው፡፡