Administrator

Administrator

ተቋሙ ከኢትዮጵያ ጋር መስራቴን  ሙሉ ለሙሉ አቋርጫለሁ ብሏል

አለማቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ሂዩማን ራይትስ ዎች ለኢትዮጵያ የመረጃ ጠለፋ ቴክኖሎጂዎችን ሸጧል፤ ለደህንነት ባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት የዜጎች መብቶች እንዲጣሱ እገዛ አድርጓል ያለውን “ሃኪንግ ቲም” የተባለ የጣሊያን ተቋም በጉዳዩ ዙሪያ በቂ ምላሽ አልሰጠም፣ የመብቶች ጥሰቶችን ለማስቆምም እርምጃ አልወሰደም ሲል ከሰሰ፡፡
ሃኪንግ ቲም ለተለያዩ አገራት መንግስታት የመረጃ መጥለፊያ ቴክኖሎጂዎችን በመሸጥና ለባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት፣ መንግስታት የዜጎችን ሰብአዊ መብቶች እንዲጥሱ እገዛ ያደርጋል ያለው ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ በኢትዮጵያ ሲከናወን የቆየውን የመረጃ ጠለፋና የመብቶች ጥሰት በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጠው ቢጠይቅም በቂ ምላሽ ሊሰጠው እንዳልቻለ ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ተቋሙ ጉዳዩን በተመለከተ ምርመራ ለማድረግም ሆነ የኢትዮጵያ መንግስት ቴክኖሎጂውን በመጠቀም በዜጎቹ ላይ የሚያደርሰውን የመብቶች ጥሰት ለማስቆም ምንም አይነት ተጨባጭ እርምጃ አልወሰደም ሲል የከሰሰው ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ ሃኪንግ ቲም ለኢትዮጵያ የደህንነት ባለሙያዎች የግለሰቦችን ኮምፒውተሮች ሰብረው መግባት የሚችሉበትን ስልጠና መስጠቱን እንደቀጠለና ቀጣይ ስምምነቶችን ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምሮ እንደነበር የሚያረጋግጡ መረጃዎችን በሃምሌ ወር እንዳገኘ አስታውቋል፡፡
ሃኪንግ ቲም ለኢትዮጵያ መንግስት የሸጣቸው የመረጃ መጥለፊያ ቴክኖሎጂዎች ከቫይረስ መከላከያ ፕሮግራሞች አቅም በላይ እንደሆኑና በቀላሉ ወደ ግለሰቦች ኮምፒውተሮች በመግባት መረጃዎችን እንደሚወስዱ የጠቆመው ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ ከተቋሙ ኢሜይል አፈትልከው የወጡ መረጃዎችም ተቋሙ በሚያዝያ ወር ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ከ700 ሺህ ዶላር በላይ የሚገመት አዲስ የቴክኖሎጂና የስልጠና ስምምነት ለመፈጸም ሲያደርጉት የነበረው እንቅስቃሴ ሳይሳካ መቅረቱን ያመለክታሉ ብሏል፡፡
ሃኪንግ ቲም ጉዳዩን በተመለከተ ምላሹን እንዲሰጥ ባለፈው ሃምሌ ወር ላይ ከሂውማን ራይትስ ዎች ለቀረበለት ጥያቄ በሰጠው ምላሽም፣ የሚያመርታቸው ሶፍትዌሮች የሚንቀሳቀሱት በእሱ ሳይሆን በገዙት ደንበኞቹ መሆኑን ጠቁሞ፣ ቴክኖሎጂው ለስለላ ተግባር ስለመዋሉ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ገልጾልኛል ያለው ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ ከተቋሙ አፈትልከው የወጡ መረጃዎች ግን የኢትዮጵያ መንግስት የስለላ ተግባራት የሰብአዊ መብቶችን የሚጥሱ መሆን አለመሆናቸውን ለማጣራት በርካታ አጋጣሚዎች እንደነበሩት የሚያመለክቱ ናቸው ብሏል፡፡
ተቋሙ በዚሁ ምላሹ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያለውን ግንኙነት በ2015 የመጀመሪያዎቹ ወራት ሙሉ ለሙሉ አቋርጫለሁ ማለቱንም ሂውማን ራይትስ ዎች ጠቁሟል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ ነዋሪ የሆኑ ከ70 በላይ አማርኛ ተናጋሪ ገበሬዎች፣ ቤት ንብረታቸው ተቃጥሎ ከመኖሪያ ቀዬአቸው መፈናቀላቸውን የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) በሪፖርቱ አመለከተ፡፡ የአንድ ሰው ሕይወት መጥፋቱንም አረጋግጫለሁ፤ ብሏል፡፡
ሰመጉ ጉዳዩን ሲመረምር መክረሙን ጠቁሞ፣ “ብሔር ተኮር ማፈናቀልና እንግልት በአስቸኳይ ይቁም” በሚል ርዕስ ይፋ ባደረገው 136ኛ ሪፖርቱ የወረዳው የጸጥታ ሓላፊዎችና ባለሥልጣናት የብሔር ግጭቱን መቀስቀሳቸውን አስታውቋል፡፡
እንደ ሪፖርቱ፣ የወረዳው ባለስልጣናትና የፀጥታ ኃላፊዎች አርሶ አደሮቹን፣ “እናንተ የዚህ የአካባቢው ተወላጅ ሳትሆኑ ሀብት እያፈራችሁ የአካባቢው ተወላጆች ግን ከእናንተ ያነሰ ገቢ ነው ያላቸው፤ … ይህን ገቢ ያገኛችሁት በኛ መሬት ነው፤ የክልሉ ተወላጆች ባለመሆናችሁ ክልሉን ለቃችሁ ውጡ፤” በማለት በተለያዩ ጊዜያት ንብረታቸውን በመንጠቅና ለእስራት በመዳረግ እንግልት ሲፈፅሙባቸው ቆይተዋል፡፡ በተለይ መጋቢት 27 ቀን 2007 ዓ.ም አንድ የአካባቢው ተወላጅ ተገድሎ መገኘቱን ተከትሎ የወረዳው የፀጥታ ኃላፊ “ግድያው የተፈፀመው በአማራ ብሄር ተወላጆች ነው” በማለታቸው ግጭት ተቀስቅሶ፤  ሚያዚያ 9 ቀን 2007 ዓ.ም 85 አርሶ አደሮች ለእስራት መዳረጋቸውን፣ የአማራ ተወላጅ አርሶ አደሮች መኖሪያ ቤቶች እንዲቃጠሉ መደረጉን እንዲሁም የታሠሩትን የነዳጅ በሚል 300 ብር ከእያንዳንዳቸው በመቀበል እንደተለቀቁ ሰመጉ አጣርቻለሁ፤ ብሏል፡፡   በግጭቱ የአንድ ሰው ሕይወት ሲጠፋ 10 ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን፣ 99 የሳር ክዳን ቤቶችና 25 የቆርቆሮ ቤቶች በእሳት ተቃጥለው መውደማቸውን የዘረዘረው ሰመጉ፤ መኖሪያ ቤታቸው ለተቃጠለበቸውና በተለያዩ ቦታዎች ተበታትነው ለሚገኙ ዜጐች አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታ እንዲያገኙ ጠይቋል፡፡ መንግሥትም ለተፈጸመው የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ የተጠናና የማያዳግም የመፍትሔ ርምጃ ከሕዝብ ጋር በመመካከር እንዲወሰድ የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ አመልክቷል፡፡ 

    ያለፈውን የትግል ሂደቱን ሲገመግም የሰነበተው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ፤ አዲስ የትግል ስልት መቀየሱን ጠቁሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከግንባር ወደ አንድ ውህድ ፓርቲ ለመሸጋገር ማቀዱን አስታወቀ፡፡
የአራት ብሄር ተኮር ፓርቲዎች ግንባር የሆነው መድረክ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ እያንዳንዱን የፓርቲ አባላት በማሳመን በውህደት አንድ ፓርቲ እንደሚፈጥር የጠቆሙት አቶ ጥላሁን፤ በቀጣዩ ምርጫም አንድ ፓርቲ ሆኖ ለውድድር ይቀርባል ብለዋል፡፡
መድረኩ በሁለት ቀን ጉባኤው፣ አባል ድርጅቶች በውህደት ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥተው በመወያየት የውህደቱን ሂደት እንዲያፋጥኑ ከስምምነት ላይ የተደረሰ ሲሆን በየ6 ወሩ በሚካሄደው ስብሰባም የውህደቱ አጀንዳ እንደሚገመገም ኃላፊው ገልፀዋል።
ግንባሩ ባለፈው የግንቦት ወር ምርጫ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን መገምገሙን የጠቆሙት አቶ ጥላሁን፤ ገዥው ፓርቲ ምርጫውን ለማሸነፍ ማስፈራራትን፣ ጉልበትንና የገንዘብ አቅምን መጠቀሙን፣ እንዲሁም ምርጫው ህግና ስርዓትን በተከተለ መንገድ አለመከናወኑን ገምግሟል ብለዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ቅዳሜና እሁድ መድረኩ ባካሄደው ጉባኤ፣ እስካሁን ያከናወናቸው ፖለቲካዊ ትግሎች ያስገኙትን ውጤትና በቀጣይ ሊወሠዱ የሚገቡ አዋጭ የትግል ስልቶችን መገምገሙን የጠቆሙት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ጥላሁን እንደሻው፤ ግንባሩ የነበሩበትን ድክመቶች ለይቶ ማስመቀጡንና ከአሁን በኋላ የመንግሥትን ጫና ተጋፍጦ ወደ ህዝቡ በመውረድ፣ የተለያዩ አደረጃጀቶች ፈጥሮ ለመታገል መወሰኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ምርጫዎች መድረኩ ጫናዎችን ተቋቁሞ ህዝቡን ለትግል በማደራጀትና በማንቀሳቀስ ረገድ የራሱ ድክመቶች እንደነበሩበት የገመገመ ሲሆን፤ ግንባሩ በምርጫው ሙሉ ኢትዮጵያን መወከል አለመቻሉም ተጠቅሷል፡፡ በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ የመድረኩ እንቅስቃሴ በደካማነት ተገምግሟል ያሉት አቶ ጥላሁን፤ በትግራይና በኦሮሚያ በአንፃራዊነት ተሳትፎው እንደጨመረ ገልፀዋል። በጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል፣ አፋርና ሌሎች ክልሎች የመድረክ መዋቅር እንዳልተዘረጋ ሃላፊው ጠቁመው በቀጣይ በነዚህ ክልሎች መዋቅር ለማበጀት ግንባሩ እንደሚተጋ አስታውቀዋል፡፡
በሁለቱ ቀናት ጉባኤው ግንባሩ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ሊኖረው ስለሚገባ ግንኙነት መምከሩ የተገለፀ  ሲሆን ከመድረኩ አላማና ፕሮግራም ጋር የሚቀራረቡ ፓርቲዎችን ለመሳብ በሩን ከፍቶ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን የተወሰነ ርቀት ሄዶ ለመጋበዝም እንዳቀደ ታውቋል፡፡

    ግሪን ኮፊ አግሮ ኢንዱስትሪ፤ የመንግሥት ይዞታ የነበረውን የቴፒ ቡና ተክል ልማት ድርጅት በ1 ቢ. ብር  ጠቅልሎ መግዛቱን አስታወቀ፡፡
ትናንት ረፋድ ላይ በሂልተን ሆቴል በተደረገው የሽ    ያጭ ውል ስምምነት፣ የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ በየነ ገ/መስቀልና የግሪን ኮፊ አግሮ ኢንዱስትሪ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደለ አብርሃ ውሉን ተፈራርመዋል፡፡
አቶ ታደለ በተለይ ለአዲስ አድማስ እንደገለጹት፣ ግሪን ኮፊ ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት የቴፒ ቡና ተክል ልማት ድርጅትን ድርሻ 51 በመቶ በመያዝ፣ መንግሥት ደግሞ ቀሪውን 49 በመቶ ይዞ በሽርክና ለመሥራት ተስማምተው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ 12 ሺህ ሄክታር ስፋት ያለውን የእርሻ ልማት፣ በ1 ቢሊዮን ብር እንደገለፁት አቶ ታደለ፤ የፊርማ ሥነ - ሥርዓቱ የተፈፀመው የዋጋውን 35 በመቶ፣ 265 ሚሊዮን ብር ባንክ አስገብተው ሲሆን ቀሪውን 65 በመቶ በ5 ዓመት ውስጥ ከፍለው ለማጠናቀቅ መስማማታቸውንም አስረድተዋል፡፡
12ቱ ሺህ ሄክታር መሬት ባረጁ የቡና ዛፎች የተሸፈነ ስለሆነ፣ ከ8-9 ሄክታሩን የተሻለ ምርት በሚሰጡ አዳዲስ ዝርያዎች መተካቱን ጠቁመው፣ ቀሪውም በየዓመቱ 1000 ያህል ሄክታር በአዲስ ምርታማ ዝርያ ይተካል ብለዋል፡፡ ከእርሻ ልማቱ አጠገብ የጋምቤላ ክልል ይዞታ የሆነውን 3ሺህ ሄክታር መሬት ክልሉን ጠይቀው ስለፈቀደላቸው አዲስ ፕሮጀክት ቀርፀው እንደሚያለሙትም አቶ ታደለ አክለው ገልፀዋል፡፡
ከእርሻው የሚገኘውን የቡና ምርት ኤክስፖርት በማድረግ 20 ሚሊዮን ዶላር እንደሚገኝ የጠቀሱት ባለሀብቱ፤ እርሻው ለማር ምርት አመቺ በመሆኑ በዓለም ተወዳጅ የሆነውን ኮፊ ሀኒ የተባለ የማር ዓይነት በአነስተኛ መሳሪያ እያዘጋጁ ወደ ውጭ ሲልኩ ቆይተዋል፡፡ አሁን በብዛት (50 እና 60 ኮንቴይነር ኮፊ ሀኒ) ወደ ውጭ በመላክ ከ4-5 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ፋብሪካ እየገነቡ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የቴፒ ቡና እርሻ ልማት በረከት ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የተለያዩ ቅመማ ቅመሞች እያመረቱ ለመላክ አቅደዋል፡፡ ብዙም ባይሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ፓልም ኦይል የሚገኘው በቴፒ እርሻ ልማት ብቻ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ታደለ፤ ለሙከራ ከማሌዢያና ኢንዶኔዢያ የተለያየ ዝርያ አምጥተው በ120 ሄክታር መሬት ላይ በመትከል ምርቱ ደርሶ አይተውታል፡፡ በአነስተኛ መሳሪያ እያዘጋጁ በየወሩ አንድ መኪና ዘይት ለተለያዩ ድርጅቶች የሚያቀርቡ ሲሆን፤ ወደ ዘይት ከመለወጡ በፊት ያለውን ድፍድፍ፣ የሳሙና ፋብሪካዎች በጥሩ ዋጋ በሰልፍ እንደሚገዙና በየወሩ አንድ መኪና ድፍድፍ እንደሚሸጡ ተናግረዋል፡፡ የፓልም እርሻውን ወደ 10,000 ሄክታር ለማሳደግ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግ ኩባንያ ማግኘታቸውን ጠቅሰው፣ የእርሻ መሬት ለማግኘት ከክልሉ ጋር እየተነጋገሩ መሆኑንም አቶ ታደለ ገልፀዋል፡፡
በቴፒ እርሻ ልማት ውስጥ ባሉ 6 እርሻዎች፣ 16ሺ ሰራተኞች ተቀጥረው እንደሚሰሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Saturday, 08 August 2015 09:38

የዘላለም ጥግ

(ስለ ስኬት)
ውድቀት አማራጭ አይደለም፡፡ ሁሉም ሰው ስኬትን መቀዳጀት አለበት፡፡
አርኖልድ ሽዋዚንገር
ያለ አንተ ይሁንታ ማንም ሰው የበታችነት ስሜት እንዲሰማህ ማድረግ አይችልም፡፡
ኢሊኖር ሩስቬልት
ስኬት የዕድል ጉዳይ ነው፡፡  ያልተሳካለትን ማንኛውንም ሰው ጠይቁ፡፡
ኢርል ዊልሰን
አሸናፊው ሽንፈትን ይፈራል፡፡ የተቀረው ደግሞ ማሸነፍን ይፈራል፡፡
ቢሊ ዣን ኪንግ
ውድቀት በራሱ ከተማርንበት ስኬት ነው፡፡
ማልኮም ፎርብስ
የስኬት ምስጢሩ ሃቀኝነት ነው፡፡
ዣን ጊራውዶክስ
ተፈጥሮአችን ነው፡- የሰው ልጆች ስንባል ስኬትን እንወዳለን፤ ስኬታማ ሰዎች ግን እንጠላለን፡፡
ካሮት ቶፕ
ስኬትን መቀዳጀቴ ብቻ በቂ አይደለም - ሌሎች መውደቅ አለባቸው፡፡
ዴቪድ ሜሪክ
ስኬት ሁሉንም ነገር አይደለም፤ ነገር ግን ሰውን ቀጥ ብሎ እንዲቆም ያደርገዋል፡፡
ሊሊያን ሄልማን
ስኬት ምንም ምስጢር የለውም፡፡ የዝግጅት፣ ተግቶ የመስራትና ከውድቀት የመማር ውጤት ነው፡፡
ኮሊን ፓውል
ህልሞችህን ገንባ፤ ያለበለዚያ ሌሎች ህልማቸውን እንድትገነባላቸው ይቀጥሩሃል፡፡
ፋራህ ግሬይ
ህይወት ራስህን የመፈለግ ጉዳይ አይደለም፤ ራስህን መፍጠር ነው፡፡
ጆርጅ በርናርድ ሾው
ደስታ ሁልጊዜ ክፍት እንደነበር ባላሰብከው በር ያጮልቃል፡፡
ያልታወቀ ሰው

Saturday, 08 August 2015 09:33

የግጥም ጥግ

 ላንቺ
(በ.ሥ)
እንዳገው ጃንጥላ፤ ሰማይ ተሽከርክሮ
እንደ ጎፋ ፈረስ፤ መሬቱ ደንብሮ
ሁሉ ሲያዳልጠኝ
ሁሉ ሲያዳክመኝ
ቀሚስሽን ይዤ፤ መትረፌ ገረመኝ፡፡

ኤልሻዳይ ምኞት
(በ.ሥ)
እንደ ድሮ ቀሚስ፤ መሬት እየጠረግሁ
ኮቴሽን ምድር ላይ፤ ተግቸ እየፈለግሁ
እንደ ጉም
ሳዘግም
እንደ ሰርዶ ስሳብ
ባካል ብታመልጭኝ፤ ደረስኩብሽ ባሳብ
መች ሊያግደኝ በሩ፤ መች ሊገታኝ መስኮት
በዝግ በርሽ ገባሁ፤ ልክ እንደ መለኮት
ላንዲት መስቲካ ሻጭ ህጻን
(በ.ሥ)
በደብተርሽ ምትክ
ትንሽ ሱቅ ታቅፈሽ
ካልፎሂያጅ እግር ስር፤ እንደ ድንቢጥ ከንፈሽ
ጋሼ ግዙኝ ስትይ፤ ኣንጋጠሽ ወደ ላይ
ለጉድ ተጎልቸ፤ ምታረጊውን ሳይ
ራሴስ ይታመም፤ ምላሴን ምን ነካው
ግራዋ ይመስል፤ መረረኝ ማስቲካው፡፡
ኣፈር ጠጠር ለብሶ፤ በዶዘር ተድጦ
መስኩ ከነጎርፉ
ሰማይ ከነዶፉ
ለጌቶች ተሽጦ
ኣተር ነው እያሉ፤ ኣፈር ዘግኖ መፍጨት
ገነት ነው እያሉ፤ መስክ ላይ መፈንጨት
ጠበል ነው እያሉ፤ ተጎርፉ መራጨት
ይህንን ማን ሰጦሽ
ገና በልጅነት፤ ልጅነት ኣምልጦሽ፡፡
በምቢልታ በዋሽንት፤ በከበሮ ታጥሮ
በክራር ተማግሮ
በቆመ ከተማ
እምባሽ ቅኝት የለው፤ ለሰው ኣይሰማ፡
ጠዋት የፎከረ፤ ቀትር ላይ ሲረታ
ዛሬ ዝሎ ሲወድቅ፤ ትናንት የበረታ
ኑሮን ያህል ሸክም፤ ያላንቀልባ ሲያዝል፡፡
ምን ጸጋ ለብሶ ነው፤ ትከሻሽ የማይዝል፡፡

በዳንኤል ተገኝ ተደርሶ በአለምፀሐይ በቀለ ዳይሬክት የተደረገውና በዳኒሮጐ ማስታወቂያና ፊልም ፕሮዳክሽን የቀረበው “የሴም ወርቅ” የተሰኘ ፊልም ባለፈው ሰኞ ምሽት በቀይ ምንጣፍ ሥነስርዓት ተመረቀ፡፡
የ1፡45 ደቂቃ ርዝማኔ ያለውን ፊልም ሰርቶ ለማጠናቀቅ 2 ዓመት ያህል የፈጀ ሲሆን 1.5 ሚ. ብር እንደወጣበት አዘጋጆቹ ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ልብ አንጠልጣይ የቤተሰብ የፍቅር ፊልም ላይ አርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያም፣ አምለሰት ሙጬ፣ ዳንኤል ተገኝ፣ ሙሉ ሰለሞን፣ ዝናህብዙ ፀጋዬ እና ሌሎች አንጋፋና ወጣት ተዋንያን ተሳትፈውበታል ተብሏል፡፡
በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሩ አቶ አሚን አብዱል ቃድርን ጨምሮ አርቲስት አበበ ተስፋዬ (ፋዘር) እና ሌሎችም ታዋቂ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የተገኙ ሲሆን ሚኒስትሩ ፊልሙን ከተመለከቱ በኋላ በሰጡት አስተያየት፤“በጣም ደረጃውን የጠበቀ የአገራችንን ገፅታ የሚያሳይ ፊልም ነው” ሲሉ ማድነቃቸውን አዘጋጆቹ ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡
የፊልሙ 70 ከመቶ ቀረጻ የተካሄደው በባህር ዳር እና ጎንደር ከተሞች ላይ ሲሆን ቀሪው አዲስ አበባ መቀረጹን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በፊልሙ ላይ ከዕውቅ ተዋናዮች ባሻገር የዳሽን ቢራ ሰራተኞችን ጨምሮ ከ100 በላይ የሚሆኑ ሰዎች መሳተፋቸውን የጠቆመው የፊልሙ ደራሲና ፕሮዱዩሰር አርቲስት ዳንኤል ተገኝ፤ዳሽን ቢራ ለፊልሙ ከ1.3 ሚሊዮን ብር በላይ ስፖንሰር ማድረጉን ገልጿል፡፡
ዳሽን ቢራ ፊልሙ ለተመልካች እንዲበቃ ላደረገው ድጋፍ፣ታዋቂ አርቲስቶችና የውጭ ሃገር ዜጎች የተሳተፉበት ማስታወቂያ ሰርተው ለፋብሪካው በስጦታ ማበርከታቸውን አርቲስቱ ተናግሯል፡፡ ባለፈው ሰኞ በፊልሙ ምረቃ ላይ የታደሙ አንዳንድ ተመልካቾች፤ፊልሙ የዳሽን ማስታወቂያ ይመስላል የሚል ትችት የሰነዘሩ ሲሆን በብስጭት ፊልሙ ከመጠናቀቁ በፊት ጥለው የወጡ እንደነበሩም ለማወቅ ተችሏል፡፡ አርቲስት ዳንኤል፤ ስፖንሰር አድራጊውን የዳሽን ቢራ ፋብሪካን በፊልሙ ውስጥ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ለማስተዋወቅ መሞከሩን አልካደም፡፡ ነገር ግን መላ ፊልሙ የዳሽን ቢራ ማስታወቂያን ይመስላል የሚያሰኝ አይደለም ብሏል፡፡   
 #የሴም ወርቅ” በአዲስ አበባ በሚገኙ ሲኒማ ቤቶች በሙሉ በመታየት ላይ መሆኑን የጠቆሙት አዘጋጆቹ፤በባህር ዳር እና በጎንደር ባለፈው ረቡዕ እና ሐሙስ መመረቁን አክለው ገልጸዋል፡፡  

የደራሲ ኻሊድ ሆሴኒ “A Thousand Splendid Sun” የተሰኘው ልቦለድ በአያልቅበት አደም “ዶስቲ” በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ የተተረጐመ ሲሆን በቅርቡ ለንባብ እንደሚበቃ ተርጓሚው ለአዲስ አድማስ ጠቁሟል፡፡
ኻሊድ ሆሴኒ ይበልጥ የሚታወቀው “The Kite Runner” በተሰኘ የበኩር ሥራው ሲሆን አሁን ወደ አማርኛ የተተረጎመው ሁለተኛው ሥራው ነው ተብሏል፡፡ በ361 ገፆች የተቀነበበው “ዶስቲ”፤በ80 ብር ለገበያ እንደሚቀርብ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የሰዓሊና ገጣሚ ገብረክርስቶስ ደስታ “መንገድ ስጡኝ ሰፊ” የተሰኘ የግጥም መድበል ላይ በነገው ዕለት ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ በብሄራዊ ቤተ መፃህፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ አዳራሽ ውይይት እንደሚካሄድበት ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ አስታወቀ፡፡
ለውይይቱ መነሻ ሃሳብ የሚያቀርቡት ገጣሚና ጋዜጠኛ ባንችአየሁ ዓለሙ ሲሆኑ የጥበብ ወዳጆች በውይይቱ ላይ እንደሚታደሙ ሚዩዚክ ሜይዴይ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
በሌላ በኩል የደራሲ ገዛኸኝ ላቀው “የደቦቃ ጥንስስ” የተሰኘ መፅሀፍ በነገው ዕለት ከጠዋቱ 3 ሰዓት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በሚገኙበት በዚያው በብሄራዊ ቤተ መፃህፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ አዳራሽ እንደሚመረቅ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ገልጿል፡፡  

“ወጣትነት የኪነ ጥበብ፣የማነቃቂያና የፈጠራ ማሳያ ዝግጅት; በሚል መሪ ቃል በዛሬው ዕለት ከቀኑ 10፡30 ጀምሮ በአክሱም ሆቴል የሥነ ፅሁፍ ዝግጅት ይቀርባል።  
በፕሮግራሙ ላይ ግጥሞችና ወጎች እንዲሁም በወጣቶች የተዘጋጁ ወጣቱን የሚያነቃቁ ስራዎች እንደሚቀርቡ ታውቋል፡፡ ፕሮግራሙ የተዘጋጀው ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን በዋናነትም ወጣቱን ለማስተማርና ለማዝናናት ያለመ ነው ተብሏል፡፡