Administrator

Administrator

"እንዲህ ያለም የለ"መጽሐፍ ረቡዕ ይመረቃል

የገጣሚ ሀብታሙ ሀደራ "እንዲህ ያለም የለ" የተሰኘ የግጥም ስብስብ መጽሐፍ የፊታችን ረቡዕ መጋቢት 25 2016 ዓ.ም ከ10:30 ጀምሮ በወመዘክር አዳራሽ ይመረቃል።

  • • ጎሳዬ ተስፋዬ፣ ሳሚ ዳንና ጃኪ ጎሲ ይሳተፉበታል

           ታዋቂ የኢትዮጵያ ድምፃዊያን የሚሳተፉበት “የኢትዮጵያ ሙዚቃ ቀን” በእስራኤል ቴላቪቭ እንደሚካሄድ  አፍሮ ስታይል ኢንተርቴይመንት አስታወቀ፡፡  
    የእስራኤል የነፃነት ቀንን ምክንያት በማድረግ፣ ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ፣ም የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቀን በቴላቪቭ የሚካሄድ ሲሆን፤ አፍሮ ስታይል ኢንተርቴይመንት ባዘጋጀው በዚህ  ኮንሰርት ላይ ጎሳዬ ተስፋዬ፤ ሳሚ ዳንና ጃኪ ጎሲ እንደሚጫወቱ ተገልጿል። ታዋቂ የጃማይካ ዳንስሆል አርቲስትም በኮንሰርቱ ላይ  እንደሚሳተፍ  ተጠቁሟል።
    የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቀንን ለማክበር የተሰናዳው መርሐግብር ከሚያዚያ 29 እስከ ግንቦት 10 ቀን 2016 ዓ.ም  የሚቆይ ሲሆን፤ በተለያዩ የሙዚቃ ዝግጅቶችና በእስራኤል ከተሞች በሚካሄዱ ጉብኝቶች የሚታጀብ ይሆናል ተብሏል።
    ከሚያዚያ 29 እስከ ግንቦት 4 ቀን 2016 ዓ.ም በእየሩሳሌም ከተማ ጉብኝቶች የተዘጋጁ ሲሆን፤ ግንቦት 5  በሃንገር 09 አዳራሽ ቴላቪቭ ላይ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ቀን ልዩ  ኮንሰርት እንደሚካሄድ ተጠቁሟል፡፡  በተመሳሳይ ቀን የቴላቪቭ ከተማን ለማስጎብኘትም ታቅዷል።  ግንቦት 8 ቀን 2016 ዓ.ም በሚር ያቆብ አዘጋጅነት በቴላቪቭ ሐንገር 09 አዳራሽ፣ የሬጌ ሙዚቃ ዝግጅትና ዳንስ እንደሚቀርብም ታውቋል።

ይህ ተከታታይ ድራማ 42 ክፍሎች ያሉት ሲሆን በሳምንት ሁለት ቀናት ማለትም ቅዳሜና እሁድ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ለተመልካቾች ይቀርባል።

"ዕንቁ ሴት፣ ንቁ ሴት፣ ዝግጁ ሴት"

"ዕንቁ ሴት፣ ንቁ ሴት፣ ዝግጁ ሴት"የተሰኘ  ቅዳሜ መጋቢት 21 2016 ዓ.ም ከቀኑ 10:00 ጀምሮ ሰንጋተራ በሚገኙ ፐርፐር ብላክ አዳራሽ ውስጥ ይካሄዳል።

በዕለቱም ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ፣ አርቲስት መቅደስ ፀጋዬ ፣ ሲሰተር ዘቢደር ዘውዴ ጭምሮ የተለያዩ እንግዶች ሀሳቦቻቸውን ያቀርባሉ ተብሏል።

ሃያኛው የባለአክሲዮኖች አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤውን መጋቢት 14 ቀን 2014 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ ያካሄደው ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ የተከፈለ ካፒታሉን ወደ 20 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ውሳኔ አሳለፈ፡፡    
የባንኩ አዲሱ የዲሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ሺሰማ ሸዋነካ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክን ወደ ቀድሞ ከፍታው ለመመለስና ላቅ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ በሚያስችል ጉዞ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
“ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በበርካታ ደንበኞች በተለይም በንግዱ ማኅበረሰብ ዘንድ ተወዳጅ ባንክ ነው’’ ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ባለአክሲዮኖች ከምንጊዜውም በበለጠ ድጋፋቸውን እንዲያረጋግጡለት ጠይቀዋል።
ቀደም ሲል እንደ አገርም ሆነ በዘርፉ እንዳሉ ሌሎች ተቋማት ሁሉ ያጋጠሙ የገንዘብ አከል ችግሮች በንብ ባንክ ደረጃ በባሰ መልኩ መስተዋላቸውን በመጥቀስ፣ አሁን ግን አዲስ የተመረጠው የዲሬክተሮች ቦርድ ችግሮችን እያቃለለ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡
ባንኩ፣ “በአዲስ መንፈስ፣ ለላቀ ከፍታ!” በሚል መሪ ቃል ያስጀመረውን የማርኬቲንግ ንቅናቄ ተከትሎም፣ በሂደት የባንኩ ቅርንጫፎች ምንም አይነት የስንቅ ችግር እንዳያጋጥማቸው መሠራቱን ተናግረዋል፡፡ ደንበኞች ከቼክ ምንዛሪ ጋር በተገናኘም ስጋት እንዳይገባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
ባንኩ በምንጊዜም ባለውለታነት ሊጠቀሱ የሚችሉ የረጅም አመታት ባለአክሲዮኖችና ደንበኞች ያሉት መሆኑን የጠቀሱት ሊቀመንበሩ፤ አሁን ላይ ሁሉም ገንዘባቸውን ሲያስወጡም ሆነ ሲያስገቡ በንብ ኢንተርናሽናል ባንክ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡
የደንበኞቹን እምነት መልሶ ለመገንባት የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ የሚገኘው ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፤ አስቸጋሪ ባለው የሥራ ወቅት የተከፉ ደንበኞቹን በይፋ ይቅርታ በመጠየቅ በጀመረው አገራዊ የማርኬቲንግ ንቅናቄ መልካም ለውጦችን እያመጣ መሆኑን የቦርድ ሊቀመንበሩ አቶ ሺሰማ አስታውቀዋል።
በቀጣይም ወደ ትግበራ በገባው የዘጠና ቀናት ፍኖተ ካርታ ዕቅድ መሠረት በሁሉም የባንክ አገልግሎቶች ፈጣን ለውጦችን በማምጣት ንብ ባንክን ወደነበረበትና ከዚያም ላቅ ወዳለ ደረጃ ለማሸጋገር ትልቅ ቁርጠኝነት መኖሩን በአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤው ለተገኙ ባለአክሲዮኖች ገልጸዋል፡፡
አዲሱ ቦርድ ወደ ሥራ ከገባበት አጭር ጊዜ አኳያ ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ መሆኑን መገንዘባቸውን የገለጹት የጉባኤው ተሳታፊ ባለአክሲዮኖችም፤ ቦርዱ ባንኩን ከግል ባንኮች ዘርፍ ከፊት ለማሰለፍ የሚያደርገውን ጥረት በመደገፍ ከጎኑ እንደሚቆሙ በሰጡት ቃል አረጋግጠዋል።
በጉባኤው ከተነሱ አጀንዳዎች መካከል አንዱ፣ እ.ኤ.አ በ2022 የተገኘውና ያልተወሰነበት የትርፍ ድርሻ ክፍፍል ላይ ውይይት በማድረግ ገንዘቡ ለባንኩ ካፒታል ማሳደጊያነት እንዲውል የባለአክሲዮኖች ጉባኤ በአብላጫ ድምፅ ወስኗል።
በባንኩ በ18ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ የተወሰነውን የካፒታል ማሳደጊያ ጊዜ እንዲሻሻል በተደረገው ውይይትም፣ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ተጠናቅቆ እንዲከፈል መወሰኑን ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በአማራ ክልልና በትግራይጊዜያዊ አስተዳደር መካከል የተከሰተው ውዝግብ ተባብሶ ቀጥሏል። ሁለቱም ወገኖች በየፊናቸው ማስጠንቀቂያና መግለጫ እያወጡ ነው፡፡
የአማራ ክልል  ትናንት ባወጣው መግለጫ፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ሀገሪቱን ና ሁለቱን ክልሎች ወደ ቀውስ ከሚያስገቡ ተግባራቱ  እንዲቆጠብ አስጠንቅቋል። የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር  ያወጣው መግለጫ ጠብ አጫሪ  እንደሆነም ገልጿል። ክልሉ ባወጣው በዚሁ መግለጫው፤  “የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር  መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም የራያ አላማጣ ወረዳ ቀበሌዎችን በመያዝ  የአካባቢው ነዋሪዎችን በመግደልና በማሰቃየት ላይ ይገኛል” ሲል ከስሷል።
የአማራ ክልል በመግለጫው፤ “የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ከመማሪያ መጽሐፍ ካርታ ጋር በተያያዘ በአማራ ክልል ላይ ጥቃት ከመፈጸም የማይመለስ መሆኑን የሚገልጽ የጠብ አጫሪ መግለጫ ማውጣቱ ካለፉት ድርብርብ ውድቀቶች ትምህርት አለመውሰድን ከማሳየት የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም” ብሏል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ለሀገሪቱ ቋሚ ቀውስ ምንጭ ከሚያደርጉት ተግባራት እንዲታቀብና ሀገሪቱንና ሁለቱን ክልሎች ወደ ቀውስ ከሚያስገቡ ተግባራት እንዲቆጠብም የአማራ ክልል መንግስትአስጠንቅቋል።  በተጨማሪም ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከለመደው አጓጉል የካርታ ፖለቲካ ጨዋታ እንዲወጣና የህዝብን ፍላጎት ማዕከል ባደረጉ ውይይቶች ላይ እንዲያተኩር ክልሉ  መክሯል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ በበኩሉ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫው፤ “የአማራ ክልል መንግሥት የትግራይ መሬቶችን የግዛቱ አካል በማድረግ፣ በክልሉ ካርታ ላይ አስፍሯል፤ የትግራይ ክልል መሬቶች የሰፈሩበትን ካርታ በትምህርት ካሪኩለሙ በማካተት እያስተማረበት እንደሚገኝ ተረድቻለሁ” ብሏል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ፣ የአማራ ክልል በመማሪያ መጽሐፍት ላይ ያወጣውን የተሳሳተ ካርታ በአስቸኳይ ማስተካከያ እንዲያደርግ በመግለጫው  ያስጠነቀቀ ሲሆን፤ ይህ የማይሆን ከሆነ ግን “ይህን ተከትሎ ለሚመጣው ነገር ሁሉ ሃላፊነቱን የሚወስደው የአማራ ክልል መሆኑን ልናሳውቅ እንወዳለን” ብሏል።

ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ 500 ተሳታፊዎች ይወዳደራሉ  

የአዲስ አበባ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ከሳኦል ኩነቶች አዘጋጅ ጋር በትብብር  ለሚያዘጋጁት የአዲስ አበባ ወርልድ ቴኳንዶ ኦፕን ቶርናመንት የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረሙ ሲሆን፤ ውድድሩ ከሚያዚያ 19  እስከ ሚያዚያ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ይካሄዳል ተብሏል፡፡

ለውድድሩ አሸናፊ የ1 ሚሊዮን ብር ሽልማት  መዘጋጀቱ ተነግሯል፡፡

አዘጋጆቹ ትላንት አርብ መጋቢት 20 ቀን 2016 ዓ.ም በአራት ኪሎ ስፖርት ትምህርት ስልጠና ማዕከል የስብሰባ አዳራሽ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የአዲስ አበባ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ከሳኦል ኩነቶች አዘጋጅ ጋር በትብብር የሚያዘጋጁት የአዲስ አበባ ወርልድ ቴኳንዶ ኦፕን ቶርናመንት በተለያየ የእድሜ እርከን እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡

ለውድድሩ አሸናፊዎች  የአንድ ሚሊዮን ብር ሽልማት መዘጋጀቱ የተገለጸ ሲሆን፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሁሉም ክልሎች እንዲሳተፉ እንደሚደረግና ከክልል ለሚመጡ ተወዳዳሪዎች የማረፊያ ቦታ ለማዘጋጀት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አዘጋጆቹ ገልጸል፡፡

 በዚህ ቶርናመንት እስከ 500 ተወዳዳሪዎች ይሳተፉበታል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ተወዳዳሪዎች እንድ የእድሜ  እርከናቸው ለመመዝገቢያ ከ300 ብር እስከ 1000 ብር  እንዲከፍሉ ይጠበቃል ተብሏል፡፡

የሳኦል ኩነቶች አዘጋጅ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት ደረጄ በመግለጫው ላይ እንደተናገሩት፤ ውድድሩን ለማዘጋጀት የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በማጠናቀቅ ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ለዝግጅቱ ማስኬጃ እስከ 700ሺ  ብር እንደመደቡ ገልፀዋል።

በእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ፣ የወተት ላሞች እርባታና የወተት ማቀነባበሪያ ሥራ ላይ የተሰማራው ርሆቦት ኃ.የተ.የግል ማህበር፤የፊልም ተዋናይዋን አርቲስት ራሄል እንግዳን የእናት ወተት ብራንድ አምባሳደር አድርጎ ሾማት፡፡

በዛሬው ዕለት ከሰዓት በኋላ በሸራተን አዲስ በተዘጋጀ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ርሆቦት ኃ.የተ.የግል ማህበርና አርቲስት ራሄል እንግዳ በጋራ ለመሥራት ተፈራርመዋል፡፡   

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ እንደተጠቆመው፣ አርቲስቷ  በርሆቦት ኃ.የተ.የግል ማህበር ሥር ከሚተዳደሩት አንዱ የሆነው  የእናት ወተት  የብራንድ አምባሳደር ሆና ምርቱን ታስተዋውቃለች ተብሏል፡፡

በመጋቢት 2010 ዓ.ም የተመሰረተው ድርጅቱ ዓላማው፣ ኢትዮጵያን የወተት ማማ ማድረግና የወተት እጥረትን መቅረፍ መሆኑን ይገልጻል፡፡  

ድርጅቱ፤ ትኩስ (ፍሬሽ) ወተት፣ፕሌን ዮገርት፣ የተለያዩ ጣዕም ያላቸው ፍሌቨሮች፣ ሁሉም ዓይነት የቺዝ ምርቶች እንዲሁም  የምግብና የገበታ ቅቤ የሚያመርት ሲሆን፤ ምርቶቹን በአዲስ አበባ ሁሉም ክፍለ ከተሞች ፣በኦሮሚያ ቡራዩ፣ ገላን፣ ዱከም፣ ቢሾፍቱ፣ ሞጆና አዳማ  እንደሚያከፋፍል አስታውቋል፡፡

አርቲስት ራሄል እንግዳ ከፊልም ተዋናይነቷ ባሻገር ለዓላማዋ የጸናች ትልቅ የጥበብ ባለቤት መሆኗን የገለጸው ድርጅቱ፤ የእናት ወተት  አምባሳደር ሆና  ብራንዱን በማስተዋወቅ ረገድ ጉልህ ሚና እንደምትጫወት እምነቱን ገልጧል፡፡

ሃያኛው የባለአክሲዮኖች አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤውን መጋቢት 14 ቀን 2014 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ ያካሄደው ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ የተከፈለ ካፒታሉን ወደ 20 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ውሳኔ አሳለፈ፡፡    
የባንኩ አዲሱ የዲሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ሺሰማ ሸዋነካ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክን ወደ ቀድሞ ከፍታው ለመመለስና ላቅ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ በሚያስችል ጉዞ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
“ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በበርካታ ደንበኞች በተለይም በንግዱ ማኅበረሰብ ዘንድ ተወዳጅ ባንክ ነው’’ ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ባለአክሲዮኖች ከምንጊዜውም በበለጠ ድጋፋቸውን እንዲያረጋግጡለት ጠይቀዋል።
ቀደም ሲል እንደ አገርም ሆነ በዘርፉ እንዳሉ ሌሎች ተቋማት ሁሉ ያጋጠሙ የገንዘብ አከል ችግሮች በንብ ባንክ ደረጃ በባሰ መልኩ መስተዋላቸውን በመጥቀስ፣ አሁን ግን አዲስ የተመረጠው የዲሬክተሮች ቦርድ ችግሮችን እያቃለለ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡
ባንኩ፣ “በአዲስ መንፈስ፣ ለላቀ ከፍታ!” በሚል መሪ ቃል ያስጀመረውን የማርኬቲንግ ንቅናቄ ተከትሎም፣ በሂደት የባንኩ ቅርንጫፎች ምንም አይነት የስንቅ ችግር እንዳያጋጥማቸው መሠራቱን ተናግረዋል፡፡ ደንበኞች ከቼክ ምንዛሪ ጋር በተገናኘም ስጋት እንዳይገባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
ባንኩ በምንጊዜም ባለውለታነት ሊጠቀሱ የሚችሉ የረጅም አመታት ባለአክሲዮኖችና ደንበኞች ያሉት መሆኑን የጠቀሱት ሊቀመንበሩ፤ አሁን ላይ ሁሉም ገንዘባቸውን ሲያስወጡም ሆነ ሲያስገቡ በንብ ኢንተርናሽናል ባንክ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡
የደንበኞቹን እምነት መልሶ ለመገንባት የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ የሚገኘው ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ፤ አስቸጋሪ ባለው የሥራ ወቅት የተከፉ ደንበኞቹን በይፋ ይቅርታ በመጠየቅ በጀመረው አገራዊ የማርኬቲንግ ንቅናቄ መልካም ለውጦችን እያመጣ መሆኑን የቦርድ ሊቀመንበሩ አቶ ሺሰማ አስታውቀዋል።
በቀጣይም ወደ ትግበራ በገባው የዘጠና ቀናት ፍኖተ ካርታ ዕቅድ መሠረት በሁሉም የባንክ አገልግሎቶች ፈጣን ለውጦችን በማምጣት ንብ ባንክን ወደነበረበትና ከዚያም ላቅ ወዳለ ደረጃ ለማሸጋገር ትልቅ ቁርጠኝነት መኖሩን በአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤው ለተገኙ ባለአክሲዮኖች ገልጸዋል፡፡
አዲሱ ቦርድ ወደ ሥራ ከገባበት አጭር ጊዜ አኳያ ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ መሆኑን መገንዘባቸውን የገለጹት የጉባኤው ተሳታፊ ባለአክሲዮኖችም፤ ቦርዱ ባንኩን ከግል ባንኮች ዘርፍ ከፊት ለማሰለፍ የሚያደርገውን ጥረት በመደገፍ ከጎኑ እንደሚቆሙ በሰጡት ቃል አረጋግጠዋል።
በጉባኤው ከተነሱ አጀንዳዎች መካከል አንዱ፣ እ.ኤ.አ በ2022 የተገኘውና ያልተወሰነበት የትርፍ ድርሻ ክፍፍል ላይ ውይይት በማድረግ ገንዘቡ ለባንኩ ካፒታል ማሳደጊያነት እንዲውል የባለአክሲዮኖች ጉባኤ በአብላጫ ድምፅ ወስኗል።
በባንኩ በ18ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ የተወሰነውን የካፒታል ማሳደጊያ ጊዜ እንዲሻሻል በተደረገው ውይይትም፣ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ተጠናቅቆ እንዲከፈል መወሰኑን ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በቀድሞው ዘመን አንድ የወረዳ ገዢ ነበሩ፡፡ መቶ አለቃ ናቸው፡፡ ዛሬ እንደ ተረት ሊወሱ አንድ ሐሙስ ነው የቀራቸው፡፡
አንድ ቀን የወረዳውን ህዝብ በሙሉ ጠርተው “ንቃት ልንሰጣችሁ ነውና አንድ ሰው እንዳይቀር፤ የቀረ ወዮለት” የሚል ማስፈራሪያ - አዘል ማሳሰቢያ ሰጡ፡፡ ህዝቡ በነቂስ ወጣ፡፡ ባይወጣ ምን እንደሚከተለው አሳምሮ ያውቃል፡፡
ለተሰበሰበው ህዝብ እንዲህ ሲሉ ንግግር አደረጉ፡-
“አብዮታችን በደረሰበት ደረጃ ይህ የዛሬው የንቃተ-ህሊና ማዳበሪያ ስብሰባ ቁልፍ ሚና  እንደሚጫወት ጠላቶችን ባይገባቸውም፣ በወገኖቻችን ዘንድ አንዳችም የጥርጣሬ መንፈስ የማይፈጥር ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም፡፡ ዛሬ የተሰበሰብነው ስለማንኛውም የሀገራችን ጉዳይ ያለንን አስተያየት፣ ጥያቄ ወይም ሌላ ማንኛውም ግንዛቤ የማስጨበጫ ሀሳብ እንድትሰጡና በእኔና በጓዶቼ በኩል ማናችንም ጥያቄ ለመመለስ የሚቻለንን ሁሉ እንድናደርግ በማሰብ ነው። የጓድ ሊቀመንበር አመራር የተመሰገነ ይሁንና፣ ንቃተ - ህሊናችሁ ከፍ እንደሚል ጠንካራ ዕምነት አለን፡፡ በዚህ መሰረት አሁን የምናድለውን ወረቀት ትወስዱና ስለ አብዮታችን ለመጠየቅ የምትፈልጉትን ማንኛውንም ጥያቄ ትጽፉልናላችሁ፡፡”
በተነገረው መሰረት ወረቀት ታደለ፡፡ ጥያቄ መጠየቅ የፈለገ ሁሉ ስሙን ሳይጽፍ አቀረበ፡፡
መቶ አለቃው የመጡትን በርካታ ጥያቄዎች እየተመለከቱ ለየሚመለከተው የፖለቲካ ኃላፊዎች መደቡ፡፡ ከሳቸው አጠገብ የወጣቶች ተጠሪ፣ የሴቶች ጉዳይ ኃላፊ፣ የሠራተኛ ማህበር ተወካይ ወዘተ ተቀምጠዋል፡፡ ስለዚህ መቶ አለቃ ለእነዚህ የፖለቲካ አጋሮቻቸው ጥያቄዎቹን አከፋፈሉ። ስለወጣቶቹ ከተጠየቀ ለወጣቱ ተጠሪ፣ ስለሴቶች ከሆነ ለሴቶች ጉዳይ ኃላፊዋ - በየዘርፋቸው አከፋፈሉ ማለት ነው፡፡ ኃላፊዎቹም በበኩላቸው የፖለቲካ ገለጻ አደረጉ፡፡ ከየአንዳንዱ ገለጻ በኋላም ተገቢው ጭብጨባ ተበረከተላቸው፡፡
በመጨረሻ የራሳቸው የመቶ አለቃ ተራ ደረሰ፡፡ “በዕውነቱ ሁሉም ጓዶች ተገቢውን ዕውቀትና ንቃት እንዳስጨበጡዋችሁ ከፍተኛ ዕምነት ነው ያለኝ፡፡ አሁን ደግሞ በእኔ በኩል ለደረሰኝ ጥያቄ እንደሌሎቹ ጓዶች መልስና ማብራሪያ እሰጣችኋለሁ” አሉና ተደላድለው ተቀመጡ፡፡ ከዚያ ቃለ-ምልልስ በሚያደርግ ሰው ቅላፄ ቀጠሉ፡-
“ለእኔ የመጣው ጥያቄ ከዋና ዋና የፖለቲካ ጥያቄዎች ሊመደብ የሚችል ነው፡፡ ይኸውም “የፓሪስ ኮሚዩን ለምን ፈረሰ?” የሚል ነው፡፡ እኔ ለዚህ ያለኝ መልስ”… አሉና ድምፃቸው በድንገት ወደ ቁጣ ተለወጠ፤
“የፓሪስ ኮሚዩን፤ ፈረሰ ፈረሰ! በቃ ምን መጨቃጨቅ ያስፈልጋል? ጨርሻለሁ” አሉና ተቀመጡ፡፡
***
“ፈረሰ ፈረሰ!” የሚል መሪ ወይ አለቃ ካጋጠመን ዕድለኞች አይደለንም ማለት ነው፡፡ የፈረሰው “ለምን ፈረሰ?”፣ “በፈረሰው ቦታ ምን ይተካ?”፣ “እንዴትስ ይህን ጥያቄ የህዝቡ ጥያቄ መሆኑን ማስገንዘብ ይቻላል?” መባል አለበት፡፡ ይህን የሚጠይቅ ሀላፊ ያስፈልገናል፡፡ ነገ የተሻለ ህይወት ይኖር ዘንድ የወደቀው እንዲነሳ፣ የፈረሰው እንዲገነባ፣ አወዳደቁንና አፈራረሱን ማወቅና ማሳወቅ ያስፈልጋል፡፡
“ታማኝ ነው ያሉት የስለት ዕቃ ይሰርቃል” ይባላልና የሚተማመኑበት መሪ ቀን አይቶ ይከዳል የሚል ጥርጣሬ ከህዝብ አዕምሮ አይጠፋም፡፡ ይህን ጥርጣሬ በጊዜ ካላስወገዱ ደግሞ ጥርጣሬ አድጎ ወደ ተቃውሞ፣ አድሮም ወደ ጠንካራ ፍጭት እንዳይለወጥ መጠንቀቅ የግድ ይሆናል። የሥልጣን  ሁሉ ጥልቅ ተዓምር ተለዋዋጭነቱ፣ ተሸርሻሪነቱ ከርሞም ጠዋት ያሉትን ማታ ለመካድ መመቸቱ ነው፡፡ ሥልጣን ለዚህ ኃይል ያጎናጽፋል፡፡ ስለዚህም ህዝብ ሁሌ መጠራጠሩና ለጥርጣሬው ተጨባጭ መፍቻ ካላገኘ አገር ችግር ላይ መውደቅ ጀመረች ማለት ነው፡፡ እንደ ድርቅ ሙስናና አስተዳደራዊ ኢ-ፍትሃዊነት ያለ ጎጂ ባህል ሲታከልበት፣ በችግሩ እሳት ላይ ቤንዚን ማርከፍከፍ ይሆናል፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያን ውስብስብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር ለመፍታት የበርካታ ድርጅቶችን፣ ፓርቲዎችን፣ ታዋቂ ግለሰቦችን ርብርብ ይጠይቃል። በዓላማና በጠባይ ባይመሳሰሉም፣ የደም የአጥንት ቂም ቢኖራቸውም፣ ዕድሜ ልካቸውን የሚታረቁ ባይመስላቸውም፣ የችግሩ ጥልቀት ያግባባቸዋል - የግዳቸውን! የዛሬው ዕውነታ ወደድንም ጠላንም ይሄው ነው!
ሁሌ እሥር ቤት የሚያስታርቃቸውን የፖለቲካ ድርጅቶች ማየት አገራችን ሳትታክት አልቀረችም፡፡ “የመቀመጥ ብዛት የደረቀ ቁስል ያስፍቃል” እንዲሉ ብዙ ተቀምጠው የቆዩ ፖለቲከኞች ዋና ችግር የተረሳ ጉዳይን እየቀሰቀሱ መናቆር ነው፡፡ ይሄ ሊያበቃ ግድ ነው፡፡ ጊዜ ሳያልፍ፣ ሌላ ዕድል ሳያመልጥ፣ ጀንበር ሳትጠልቅ የአገራችንን ችግር በጥሞና ማስተዋል እጅግ ተገቢ ነው፡፡ አለበለዚያ ውጤቱ፡-
“ውሎ ይደር ያሉት ነገር ዕዳ ይሆናል፤ እባብ እቤት ገብቶ ዘንዶ ይሆናል” የሚለው ተረት ነው።
መከራውን ወደ መከር ለመለወጥ ጨክኖ መታገስን ይጠይቃል፡፡ ጨክኖ መከባበርን ይጠይቃል፡፡ ጨክኖ መቻቻልን ይጠይቃል፡፡ ከማንኛውም ጉዳይ፣ ከማንኛውም ወገን፣ ከማንኛውም ሰው በላይ አገርን ለማየት የሚችል የፖለቲካ ፓርቲ ማግኘት ዛሬ እንደመለኮታዊ ፀጋ የሚቆጠር ሆኗል፡፡ ከችግሮቻችን ማለትም ከአስተዳደራዊ አሽክላችን፣ ከሙስናዊ ምዝበራችን፣ ከሀሳዊ-ዲሞክራሲያችን፣ ከየአሥር ዓመት የድርቅ ልደታችን፣ ከእርስ በርስ ግጭቶቻችን፣ ከየማን-አለብኝ ዕብሪታችን ሁሉ ለመገላገል ቢቆረቁረንም፣ ቢያጎሰቋቁለንም፣ በእልህ ቢያቃጥለንም---ከሁሉ ባሻገር ያለውን ተስፋ ለመጨበጥ ሁሉን በትዕግስት ተቀብሎ አገርን ማዳን ዛሬ ተቀዳሚ ተግባር ነው፡፡
 በአሁኑ ሰዓት፤
“ከሸኘኸኝ አይቀር መቃብሩን አሳልፈኝ” የሚለው የሁላችንም ጥሪ የሚሆነውም ለዚህ ነው፡፡ መቃብሩን በሰላም ለመሻገር ያብቃን! አሜን!

የቴሌግራም ቻናልችንን  በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

Page 5 of 701