የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት፣ ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ስድስት ዘመናዊ የእሳት አደጋ መኪኖችን መግዛቱን አስታወቀ፡፡ መኪኖቹ እያንዳንዳቸው ዘጠኝ ሺህ ሊትር ውሃና አንድ ሺ ሁለት መቶ ፎም የመያዝ አቅም አላቸው ተብሏል፡፡ ከእሳት አደጋ መኪኖቹ ውስጥ አንዱን ለአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በማስቀረት፣ ቀሪዎቹ በይበልጥ የቱሪስት መዳረሻ ወደሆኑ የክልል አለም አቀፍ ኤርፖርቶች
እንደሚላኩ ታውቋል፡፡ የመኪኖቹ መገዛት ኤርፖርቱ አለም አቀፍ የደህንነት ህግ እንዲያከብርና ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ያስችለዋል ያሉት አቶ ወንድሙ፤ በቀጣይም 25 ተጨማሪ ተሽከርካሪዎችን
ለመግዛት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡ኤርፖርቱ እስካሁን አራት የ2008 ሞዴል የእሳት አደጋ መኪኖችን በመጠቀም በአደጋ መከላከል ዘርፍ አለም አቀፍ መስፈርት፣ ዘጠነኛ ደረጃን የያዘ ሲሆን የአሁኖቹ ዘመናዊ
የእሳት አደጋ መኪኖች የ2014 ሞዴል እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡ በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ማስፋፊያ ፕሮጀክት 15 በመቶ የደረሰ ሲሆን ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅም የማስተናገድ አቅሙን በ150 በመቶ ያሳድገዋል ተብሏል፡፡ ሁለቱን የመንገደኞች ማስተናገጃ ህንፃዎች ለማስፋትና ተጨማሪ የVIP ህንፃ ለመገንባት ታቅዶ በመከናወን ላይ ያለው የማስፋፊያ ሥራ፤ በአጠቃላይ 345 ሚሊዮን ዶላር
እንደሚፈጅ ለማወቅ ተችሏል፡፡

  • ፖፕ አቡነ ቴዎድሮስ፣ የደመራ በዓልን በመስቀል ዐደባባይ ያከብራሉ
  • አክሱም ጽዮንን፣ ጎንደርን፣ ላሊበላንና የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ይጎበኛሉ


  የግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የሃይማኖት አባቶች፣ በሃይማኖታዊ ጉዳዮችና በማኅበራዊ ግንኙነቶች ዙሪያ በአዲስ አበባ እንደሚመክሩ ተገለጸ፡፡
በእስክንድርያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፖፕ እና የመንበረ ማርቆስ ፓትርያርክ አቡነ ቴዎድሮስ ካልዕ ከሚመራው ልኡክ ጋር በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ የሚካሔደው ምክክር፤ የኹለቱን አገሮችና አብያተ ክርስቲያናት የቆየ ታሪካዊ፣ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ግንኙነት አጠናክሮ በማስቀጠል ወደ ከፍተኛ መተማመን እንዲያመራ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፤ ተብሏል፡፡
በክርስትናው አስተምህሮ ባላቸው የትምህርተ ሃይማኖት አንድነት፣ “እኅትማማች” የሚባሉት ኹለቱ አብያተ ክርስቲያናት፣ የጋራ ተልእኮዎቻቸውን በአንድነት በመፈጸም ጥንታዊውንና ታሪካዊውን ግንኙነታቸውን ለማዳበር የጋራ ኮሚቴ እንዲቋቋም የኢትዮጵያው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ባለፈው ዓመት ጥር ባደረጉት የግብጽ ይፋዊ ጉብኝታቸው ወቅት ጠይቀዋል፡፡
የግብጹ አቻቸው ፖፕ አቡነ ቴዎድሮስም ጥያቄውን በመቀበል፤ በሃይማኖታዊ፣ በጤና እና በማኅበራዊ ጉዳዮች ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር አብሮ የሚሠራና በሊቀ ጳጳስ የሚመራ ኮሚቴ ለመሰየም ዝግጁ መኾናቸውን አስታውቀው እንደነበር ተወስቷል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ፣ ፈለገ ግዮን ተብሎ የሚታወቀውና ኹለቱ አገሮች በጋራ የሚጠቀሙበት ተፈጥሯዊው የዓባይ ውኃ የማኅበራዊ ትስስሩ መሠረት ሲኾን በዝግ በሚካሔደው የኹለቱ ቅዱሳት ሲኖዶሳት ምክክርም ዐቢይ ትኩረት እንደሚያገኝ ተጠቁሟል፡፡
የዓባይ ውኃን በመተማመን ከተጠቀሙበት ከኹለቱ አገሮች አልፎ ለመላው አፍሪካ የሚበቃ የአምላክ በረከት እንደኾነ ለግብጽ ባለሥልጣናት የተናገሩት ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ “የግብጽ እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድ የሚኾኑት የእግዚአብሔር ጸጋ በኾነው በዓባይ ነው፤ እግዚአብሔር አንድ ያደረገውን ደግሞ ሰው ሊለያየው አይችልም፤” ያሉ ሲኾን ፖፕ አቡነ ቴዎድሮስም፤ “እኛ የግብጽ ሕዝቦች ከዓባይ ወንዝ አንድ ብርጭቆ ውኃ በጠጣን ቁጥር ኢትዮጵያን እናስታውሳታለን፤” ማለታቸው ተጠቅሷል፡፡
በወቅቱ ፖፕ አቡነ ቴዎድሮስ ካልዕ በ2008 ዓ.ም. የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ላይ እንዲገኙ ከፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በቀረበላቸው ግብዣ፣ ትላንት ሌሊቱን ዘጠኝ አባላት ያሉትን የሃይማኖት አባቶች ልኡክ በማስከተል ዐዲስ አበባ የገቡ ሲኾን ከዛሬ ጀምሮ የአምስት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ያደርጋሉ፡፡  ለጉብኝቱ የወጣው መርሐ ግብር እንደሚያመለክተው ፓትርያርኩ፣ ትላንትና መስከረም 14 ቀን ሌሊት 9፡00 ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና የፕሮቶኮል ባለድርሻ አካላት አቀባበል ከተደረገላቸው በኋላ፣ በዛሬው ዕለት ከጠዋቱ 2፡30 በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የመንበረ ፓትርያርኩና የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት፣ የእንኳን ደኅና መጡ ፕሮግራም ይደረግላቸዋል፤ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋርም ይወያያሉ ተብሏል፡፡
ጠዋት በቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል ተገኝተው ጸሎተ ቅዳሴውን በመምራት፣ ሥርዐተ ቅዳሴውን የሚያከናውኑ ሲኾን ከቀትር በኋላም በመስቀል ዐደባባይ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ጋር የመስቀል ደመራ በዓልን ያከብራሉ፡፡
ከመስከረም 17 - 19 ቀን የርእሰ አድባራት ወገዳማት አኵስም ጽዮን ማርያምን፣ የጎንደርን፣ የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትንና ታሪካዊ ስፍራዎችን፣ የደብረ ሊባኖስ ገዳምን እንዲኹም በአዲስ አበባ የሰበታ ጌቴሰማኔ ቤተ ደናግል ወጠባባት ገዳምንና የጎፋ መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል በመጎብኘት ጸሎት እንደሚያደርጉና እንደሚባርኩ ታውቋል፡፡ በግብፅና በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ታሪክ የኹለቱ እኅትማማች አብያተ ክርስቲያናት ትብብር እንደ ድልድይ ይታያል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የራሷን ፓትርያርክ በ1951 ዓ.ም እስከሾመችበት ጊዜ ድረስ ለ1600 ዓመታት ከግብጽ ቅዱስ ሲኖዶስ በሚሾሙ ጳጳሳት ስትመራ ቆይታለች፡፡ በሀገራቱ መንግሥታት ምክክር ጭምር የመንበሩ ነጻነት ከተገኘም በኋላ የሚካሄዱ ፕትርክናዊ ጉብኝቶች ለውጭ ግንኙነታቸው መጠናከር አስተዋፀኦ እንዳለው ይታመናል፡፡

Published in ዜና

  በደቡብ ክልል ጋሞጐፋ ዞን፣ የደምባ ጐፋ ወረዳ ዋና ከተማ የሆነችው የሣውላ ከተማ ነዋሪዎችና ለአካባቢው አርሶ አደሮች፤ የዘመናት የመንገድ ጥያቄያችን ባለመፈታቱ
ተቸግረናል ሲሉ አማረሩ፡፡ የከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ፤ የመንገድ ችግር ኢንቨስተሮችን እያሸሸብኝ ነው ብሏል፡፡
ከአዲስ አበባ በ516 ኪ. ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የሣውላ ከተማና በአካባቢው የሚኖሩ አርሶ አደሮች፤ የተትረፈረፈ የኮረሪማ፣ የበቆሎ፣ የለውዝ፣ የሰሊጥ፣ የጤፍና የተለያዩ ሰብሎች ምርት ባለቤት ቢሆኑም በመንገድ ችግር ምክንያት ምርታቸውን ለማዕከላዊ ገበያ በአግባቡ አቅርበው የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
የአካባቢው የአየር ፀባይ ለግብርና ስራና ለተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ምቹ ነው የሚለው የከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ፤ የመንገዱ አለመገንባት ኢንቨስተሮችን እያሸሸ የከተማዋን እድገት አቀጭጮብኛል ብሏል፡፡በወላይታ ሶዶ አድርጐ ሣውላን ከአዲስ አበባ በሚያገናኘው መንገድ ከሣውላ እስከ ወላይታ
ሶዶ ያለው 200 ኪ.ሜትር ያህል የጠጠር መንገድ ወደ አስፓልት ደረጃ እንዲያድግ
ህብረተሰቡና የወረዳው ፅ/ቤት ጥያቄ ማቅረብ ከጀመሩ ከ10 አመት በላይ እንደሆናቸው የገለፁት ነዋሪዎቹ ችግራችን የሚታልን አካል አላገኘንም ብለዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡን የሣውላ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ቱርቃቶ ቱርቶ፤ ከተማዋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመንግስት በተሠጣት ልዩ ትኩረት የተለያዩ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት እየተገነቡ ቢሆንም የመንገዱ አለመሠራት ኢንቨስተሮችን
እያሸሸብን ነው ብለዋል፡፡ ቦታ በነፃ የተሰጣቸው ኢንቨስተሮች እንዳሉ የጠቀሱት ስራ አስኪያጁ፤ በመንገዱ አለመሰራት የተነሳ በቦታው ላይ ኢንቨስት ለማድረግ መቸገራቸውን ጠቅሰው፤ ለዓመታት የዘለቀው ችግሩ
እልባት እንዲያገኝ ጠይቀዋል፡፡    

   ኃላፊነት የሚሰማቸው ትጉህና ተነሳሽነት የሚያሳዩ ህፃናትን ለማፍራት እንደሚረዳ የተነገረለት “አዎንታዊ ዲሲፕሊን” የተሰኘው መፅሀፍ ሰሞኑን ገበያ ላይ ውሏል፡፡ ከዚህ ቀደም “አፍለኝነት”፣ “ቁልፍ ምስጢሮች ለወላጆች” የተሰኘውን መፅሀፍ ለንባብ ያበቃው ደራሲ አብደላ ሙዘይን ያጋጀው ይህ መፅሀፍ፤ በተለያዩ የልጆች ዲሲፕሊን አያያዝ፣ በልጆች ቅጣት፣ በአዎንታዊ ስነ - ምግባር መርሆዎችና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ትንታኔ ይዟል፡፡ በ16 ምዕራፎች የተከፋፈለውና በ233 ገፆች የተቀነበበው መፅሀፉ፤ በ74 ብር ከ85 ሳንቲም ለአገር ውስጥ እንዲሁም በ20.99 ዶላር ለውጭ ገበያ ቀርቧል፡፡

    አቶ አማረ መልካ በህይወታቸው ያጋጠማቸውን ውጣ ውረድ የዳሰሱበት “የደራሲው የህይወት ታሪክ እና የወደፊት ራዕይ” የተሰኘ ግለ ታሪክ መፅሀፍ ለንባብ በቅቷል፡፡ ደራሲው የአንድ ሰው ግለታሪክ በሌሎች ከሚፃፍ ይልቅ በራሱ በባለቤቱ ቢፃፍ ይበልጥ ለእውነቱ እንደሚቀርብና ከአላስፈላጊ ግነት እንደሚርቅ በማመናቸው የራሳቸውን ታሪክ ራሳቸው ለመጻፍ መፈለጋቸውን በመግቢያቸው አትተዋል፡፡ ፀሐፊው፤ ከትውልድ አካባቢያቸው፣ ከአስተዳደጋቸውና ከቤተሰቦቻቸው ጀምሮ በአጠቃላይ ስኬትና ውጣ ውረዳቸውን በመፅሀፉ ተርከዋል፡፡ ከዚህ ቀደም “የማስተዋልና የመገንዘብ ጥረትና ውጤት” የተሰኘ መፅሀፍ ማሳተማቸው ታውቋል፡፡ በአምስት ክፍሎችና በ20 ምዕራፎች የተከፋፈለው መፅሀፉ፤ 323 ገፆች ያሉት ሲሆን በ60 ብር ዋጋ ለገበያ ቀርቧል፡፡

Saturday, 26 September 2015 09:22

“ፍቅር ተራ” ፊልም ተመረቀ

 በደራሲና ዳይሬክተር አብዲሳ ምትኩ ተፅፎ የተዘጋጀውና በቻርዳ ፊልም ፕሮዳክሽን ተሰርቶ በቢኒያም ፊልም ፕሮዳክሽን የቀረበው “ፍቅር ተራ” የተሰኘ ፊልም ባለፈው ማክሰኞ ምሽት በአቤል ሲኒማ ተመርቋል፡፡
የ1፡45 ርዝመት ያለው ፊልሙ ተሰርቶ ለመጠናቀቅ ስድስት ወራትን የፈጀ ሲሆን አርቲስት ሸዊት ከበደ፣ ሄኖክ ወንድሙ፣ መኮንን ላዕከ፣ ህይወት ጌታሁንና ሌሎች ከመቶ በላይ ተዋንያን ተሳትፈውበታል፡፡ በምረቃው ላይም አርቲስቶች፣ ታዋቂ ሰዎች የፊልም አድናቂዎችና ተጋባዥ እንግዶች መገኘታቸው ታውቋል፡፡

Saturday, 26 September 2015 09:20

እድሜና ምርጫ

    ቆንጆ ናት... አፍላ .... 15 አመቷ ነው። ጎረምሶች ሲያዩዋት አይናቸው ይጎለጎላል። ጎልማሶች አይተው ይመኝዋታል። ወንዶች ይከጅሏታል። ሴቶች በቅናት እንደ ሽንኩርት ይልጧታል።
አንድ ቀን እንዲህ ስል ጠየቅኳት፤ “ማግባት የምትፈልጊው ባል ምን መስፈርት እንዲያሟላ ትፈልጊያለሽ?”
በፍጥነት መለሰችልኝ፤
“--- የተማረ መሆን አለበት፤ ማስተርስ ያለው ይመረጣል። ከተቻለ የግል ቢዝነስ የሚሰራ፤ ኢንቨስተር ቢሆን አሪፍ ነው፤ ካልሆነ ግን አሪፍ ደሞዝ ሊኖረው ግድ ነው ----- መኖሪያ ቤቱ G+2 ቢሆን ደስ ይለኛል፤ ከG+1 በታች ግን አልፈልግም።
--- መኪና በጣም ነው የምወደው። አሪፍ መኪኖች ቢኖሩት ሸጋ ነው ---- ካልሆነም ከተጋባን በኋላ እኔ አስገዛዋለሁ። ሙድ የገባው ቢሆን ደስ ይለኛል።
ሁሌ ግን የሚቅም፤ የሚጨብስና የሚያጨስ መሆን የለበትም። ጨዋታ የሚያውቅ፣ ሁሌ የሚያስቀኝ!
---- ቁመቱ በጣም እንዲረዝም አልፈልግም። እኔ አጠር ስለምል በጣም እንዳይበልጠኝ። ደረቱ ሰፋ ያለ ሆኖ ቦርጭ የሚባል እንዲኖረው አልፈልግም። ጸጉሩ ፍሪዝ ቢሆን ደስ ይለኛል፤ ድሬድ ቢሆን ደግሞ ነፍስ ነው። አይኑ የሚያምር፤ መልኩ ጸይም መሆን አለበት፤በጣም ቀይ ወይም በጣም ጥቁር ወንድ አልወድም። አለባበሱ ዘናጭ መሆን አለበት።
---- የሚወደኝ፤ የሚንከባከበኝ፤ ሮማንቲክ የሆነ፤ በሳምንት ቢያንስ ሁለቴ የሻማ እራት ያለበት ሆቴል የሚጋብዘኝ፤ ቢያንስ በወር ሁለቴ ጭፈራ ቤት የሚወስደኝ፤ ከበዓላት እና ከልደቴ ቀን በተጨማሪ ስጦታ እያመጣ ሰርፕራይዝ የሚያደርገኝ፤ ፍቅር የሚያውቅ፤ በተለያየ ቁልምጫ ስም የሚጠራኝና ታማኝ፣ ከእኔ ውጪ አንዲት ሴት የማያይ ...”
ይበቃል አልኳት፣ እንደማታቆም ስለገባኝ። እንዲህ አይነት ወንድ ኢትዮጵያ ውስጥ ቀርቶ አስቴር አወቀ ዘፈን ውስጥ እንኳን አይገኝም፣ አልኩ በውስጤ። ለሷ ግን አልነገርኳትም።
ከአስር አመት በኋላ ሳገኛት 25 አመቷ ነበር። አላገባችም። ዩኒቨርስቲ ጨርሳ ስራ ይዛለች። ጥቂት ቦይ ፍሬንዶች ይዛ ለቃለች። አሁንም ታምራለች፤ እንደድሮው ግን የሰው ሁሉ አይን ማረፊያ አይደለችም።
መልሼ ያንኑ ጥያቄ ጠየቅኳት።
“ማግባት የምትፈልጊው ባል ምን አይነት ነገሮች ማሟላት አለበት?”
 “--- የማፈቅረው ሰው መሆን አለበት፤ ፍቅር ከሌለ ላገባው አልችልም። ከማልወደው ሰው ጋር አንድ ቀን አላድርም፡፡  
 --- ታማኝ እንዲሆን እፈልጋለሁ። እንዲያከብረኝ እፈልጋለሁ።
ጥሩ ስራ ቢኖረው፤ ማንበብ የሚወድና በሃሳብ የምንግባባ ቢሆን ደስ ይለኛል።
---- ቆንጆና ሃብታም ከሆነ ጥሩ ነው፤ ካልሆነም ግን አብረን ሰርተን መለወጥ እንችላለን። ዋናው መግባባት ነው።
---- በተረፈ ቤተሰቡን የሚወድና የማይዋሽ መሆን አለበት። ወንዱ ሁሉ የማይታመን ሆነብን እኮ። ዋናው የሚታመን ከሆነ ሌላው ችግር የለውም”
ጊዜው ይሮጣል!!! ከአስር አመት በኋላ ስንገናኝ አላገባችም። 35 አመት እያለፋት ነበር። ደግሜ ያንኑ ጥያቄ ጠይቅኳት።
“ማግባት የምትፈልጊው ባል ምን አይነት ነገሮች ማሟላት አለበት?”
ትንሽ አሰብ አደረገችና፤
“--- የምግባባው ሰው ከሆነ ሌላው ችግር የለውም” አለችኝ
“መልኩ፤ ጸጉሩ፤ ሃብቱ፤ እውቀቱስ?” አልኳት።
#----ወንድ ልጅ ደግሞ መልክ ምን ያደርግለታል? ከቺምፕ (ቺምፓንዚ) መለስ ካለ ሌላው ችግር የለውም” አለች እየሳቀች።
ከአስር አመት በኋላ ሳገኛት አግብታø ሁለት ልጆች ወልዳ ነበር።
ባሏ አጭር፤ ጥቁር፤ መላጣ፤ የከባድ መኪና ሾፌር አይነት ቦርጭ ያለው፤ ሱሪውን ቦርጩ መሃከል ላይ የሚታጠቅ፤ ሁልጊዜ መላጣውን የሚያልበው፣ ዝጋታም ነገር ነው፡፡
“እንዴት ነው ትወጂዋለሽ?” አልኳት
“ምን ማለትህ ነው ትዳር አይደል?”
“ማለቴ ድሮ የነገርሽኝ አይነት ሰው አይደለም ብዬ ነው?”
#ያኔማ አየር ላይ ነበርኩ፤ እድሜ መስታወት ነው፤ ብዙ ያስተምራል፤ አሁን ተምረን ልብ ገዝተን ነው” አለች ተከዝ ብላ።
“ሁሌ የማይቀያየር አንድ መስፈርት ነበረሽ፤ ታማኝ መሆን አለበት ትይኝ ነበር። ባልሽ ታማኝ ነው?”
“ታማኝ እግዜር ብቻ ነው፤ በቃ ግን ... ትዳር ስለሆነ ከማይታመን ሰው ጋር መኖር ትለምዳለህ፤ አየህ አሁን የገባኝ ነገር ትዳር ማለት እንደ ፖለቲካ ነው። ፖለቲከኞች ውሸት እየነገሩን አብረን እንደምንኖር፣ ትዳር ውስጥም ይሄ ያጋጥማል” አለች
“በትዳርሽ ደስተኛ ነሽ?” አልኳት እያዘንኩ
“ደስታ አንጻራዊ ነው፤ በልጆቼ ደስ ይለኛል፤ ትዳሬን አከብራለሁ። በተረፈ ግን እየኖርኩ ነው” አለች ፈገግ ብላ። በዛች ቅጽበታዊ ፈገግታ ውስጥ የጊዜን ኃይለኝነት አየሁ።
ጊዜ ነው እንጂ ቁምነገራም
ባላባትነት አያኮራም ---- እንዲሉ እመው፡፡

Published in ጥበብ

     ባለፈው ማክሰኞ 80ኛ የልደት በዓላቸውን ያከበሩት አንጋፋው ክላርኔት ተጫዋች መርአዊ ስጦት ተሸለሙ በዳኒ ሮጎ የማስታወቂያ ስራና ፊልም ፕሮዳክሽን ድርጅት አስተባባሪነት በሃርመኒ ሆቴል በተዘጋጀው አርቲስቱን የማክበርና የማመስገን ስነ - ስርዓት ላይ ልጃቸው ኢትዮጵያ መርአዊ ላለፉት 60 ዓመታት የተጫወቱበትን ክላርኔት ያበረከተችላቸው ሲሆን የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበርም ክብራቸውን የሚገልፅ የምስጋና የምስክር ወረቀት እንዳበረከተላቸው ተገልጿል፡፡ በእለቱ አቶ አብነት ገብረመስቀል የ50 ሺህ ብር ስጦታ ያበረከቱላቸው ሲሆን የጃዝ አምባዎቹ ያሬድ ተፈራ፣ አበጋዝ ክብረወርቅ፣ ግሩም መዝሙር፣ ሳምሶን ጃፋር፣ ፋሲል ዊሂር እና አክሊሉ ዘውዴ ለአርቲስቱ ክብር እያንዳንዳቸው ሙዚቃ ተጫውተውላቸዋል፡፡ አርቲስት ጌትነት እንየው፣ ፍቃዱ ተክለማርያምና ሙዚቀኛው ግርማ ይፍራሸዋም በየግላቸው ስጦታ ያበረከቱላቸው ሲሆን ጌትነት እንየው “ድንቅ” የተሰኘ ግጥም እንደገጠመላቸውም የዳኒ ሮጎ ስራ አስኪያጅ አርቲስት ዳንኤል ተገኝ ተናግሯል፡፡
 አቶ አብነት ገ/መስቀል አርቲስቱን እስከመጨረሻው ለመደገፍ ቃል የገቡ ሲሆን የላንድ ማርክ ሆስፒታል ባለቤት ፕ/ር ከበደ ወሌም በማንኛውም ሁኔታ ለህክምና ሲመጡ ሆስፒታላቸው በነፃ እንደሚያክማቸው ቃል ገብቷል፡፡ ቲሞኒየር ልብስ ስፌትም በእለቱ ሙሉ ልብሳቸውን በማልበስ ለአርቲስቱ ያለውን አድናቆት ገልጿል፡፡ 

ሳምሰንግ ምርቶቼ በስፋት መቸብቸባቸውን ይቀጥላሉ ብሏል

      በአለማችን የስማርት ፎን ገበያ ቀዳሚዎቹ ተፎካካሪዎች ሆነው ለአመታት የዘለቁት ሳምሰንግ እና አይፎን፣ ፉክክራቸው ከገበያ አልፎ ችሎት የደረሰ የቴክኖሎጂው ዘርፍ ባላንጣዎች ከሆኑ ሰነባብተዋል፡፡
“ሳምሰንግ የራሱን ፈጠራ እንደመስራት የእኔን እያየ ይኮርጃል” በሚል ሲማረርና ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ ለመሰረተው ክስ፣ ተገቢ ውሳኔ የሚያገኝባትን ዕለት ለአመታት በጉጉት ሲጠባበቅ የነበረው አይፎን ከሰሞኑ በለስ ቀንቶታል፡፡
በዋሽንግተን የፌዴራል ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ባለፈው ሳምንት ሃሙስ የተሰየመው ችሎት፣ “ከአሁን በኋላ ከአይፎን እያየህ መኮረጅህን እንድታቆም፤ ከዚህ በፊት የኮረጅካቸውን ሶፍትዌሮችም ዛሬ ነገ ሳትል መጠቀም እንድታቆም” ሲል ለሳምሰንግ ጥብቅ ትዕዛዝ አስተላልፏል - ሲኤንኤን እንደዘገበው፡፡
ሳምሰንግ በበኩሉ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ በሰጠው መግለጫ፣ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በምርቶቹ ተወዳጅነት ላይ ይህ ነው የሚባል አሉታዊ ተጽዕኖ እንደማይፈጥር ገልጾ፣ ጋላክሲ በሚል መጠሪያ የሚያመርታቸው ስማርት ፎኖቹ በቀጣይም በአለም ዙሪያ በስፋት መቸብቸባቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቋል፡፡
አይፎን ፈጠራዎቼን እየኮረጀ አስቸግሮኛል በሚል በሳምሰንግ ላይ ክስ የመሰረተው ከ3 አመታት በፊት እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ ወቅቱ ሳምሰንግ ኩባንያ ጋላክሲ ኤስ 2 የተሰኘውን ስማርት ፎን ለገበያ ያበቃበት እንደነበርና ከዚያ በኋላም፣ በዚህ አመት ለገበያ ያበቃውን ጋላክሲ ኤስ 6 ጨምሮ የተለያዩ አይነት የተሻሻሉ የጋላክሲ ምርቶቹን ማውጣቱን ጠቁሟል፡፡
አይፎን ክሱን የመሰረተው በጋላክሲ ኤስ 2 ላይ ሲሆን፣ ክሱ ሳምሰንግ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ያመረታቸውን ስማርት ፎኖች የማይመለከት በመሆኑ የፍርድ ቤቱ  ውሳኔ ለአይፎን ያን ያህልም ተጠቃሚ እንደማያደርገው ተዘግቧል፡፡ ሁለቱ ኩባንያዎች በፈጠራ ባለቤትነት ጉዳይ መካሰስ ከጀመሩ ብዙ ጊዜ እንደሆናቸው የታወቀ ሲሆን በቅርቡም “ሳምሰንግ ከአይፎን ኮርጀሃል” በሚል 980 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፍል ተወስኖበት እንደነበር ተጠቁሟል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

 መንግስት በበኩሉ፣ ከ700 ሚ ዶላር በላይ በመዝረፍ ከሷቸዋል
   ሩስያዊው ቢሊየነር ሰርጊ ፑጋቼቭ፣ ፕሬዚዳንት ብላድሚር ፑቲን እና ታማኞቻቸው በህገወጥ መንገድ በሸረቡብኝ ሴራ ግዙፉን የባንክ ኩባንያዬን ለኪሳራና ለውድቀት ዳርገውታል፣ የአገሪቱ መንግስት 10 ቢሊዮን ዶላር ካሳ ሊሰጠኝ ይገባል ሲሉ ክስ መመስረታቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
ከታዋቂ የአገሪቱ ባንኮች አንዱ የነበረው ሜዝፕሮም ባንክ ድንገት ተንኮታኩቶ የወደቀባቸውና በባንኩ ዘርፍ ከሚታወቁ የአገሪቱ ባለጸጎች አንዱ እንደነበሩ የሚነገርላቸው ሰርጊ ፑጋቼቭ፤ ፕሬዚዳንት ፑቲንና ታማኞቻቸው ዋና ዋናዎቹን ንብረቶቼን ነጥቀው ኩባንያዬን ለውድቀት ዳርገውታል ሲሉ፣ ባለፈው ሰኞ ዘ ሄግ በሚገኘው ቋሚ የግልግል ፍርድ ቤት ላይ ክስ መመስረታቸውን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የሩስያ መንግስት በበኩሉ፤ እ.ኤ.አ በ2008 ተከስቶ የነበረውን የገንዘብ ቀውስ ተከትሎ ሜዝፕሮም የተባለውን የግለሰቡን ባንክ ለመደጎም በማሰብ የመደበውን ከ700 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዘርፈው ለግል ጥቅማቸው አውለዋል በሚል፣ በስደት እንግሊዝ ውስጥ በሚገኙት ሰርጊ ፑጋቼቭ ላይ ክስ መመስረቱንና ግለሰቡ ተላልፈው እንዲሰጡት የእንግሊዝን መንግስት እንደጠየቀ ያስታወሰው ዘገባው፤ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን እያጣራ ባለበት ሁኔታ ላይ በመሃል ቢሊየነሩ ከእንግሊዝ መውጣታቸውን ጠቁሟል፡፡
የሩስያን መንግስት ክስ ተከትሎ የእንግሊዝ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተለያዩ የአለም አገራት ውስጥ የሚገኙና 1.3 ቢሊዮን ፓውንድ የሚያወጡ የሰርጊ ፑጋቼቭ ሃብቶች እንዳይንቀሳቀሱ ያዘዘ ሲሆን ቢሊየነሩ ግን ከሩስያ የተሰነዘረባቸውን ክስ፣ መሰረተ ቢስና ፖለቲካዊ መነሻ ያለው ውንጀላ ነው ሲሉ ማጣጣላቸው ተነግሯል፡፡
ፕሬዚዳንት ብላድሚር ፑቲን ወደ ስልጣን እንዲወጡ በማገዝ ረገድ ቁልፍ ሚና እንደተጫወቱ የሚነገርላቸው ቢሊየነሩ ፑጋቼቭ፣ ከእንግሊዝ ከወጡ በኋላ ወደ ፈረንሳይ ሳይሄዱ እንዳልቀሩ ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ
Page 1 of 16