ስንፍና የኃጢያቶች ሁሉ ሥር ነው፡፡
   የግሪካውያን አባባል
እርቃኑን የተወለደ መልበስ ያሳፍረዋል፡፡
   የግሪካውያን አባባል
ወይ በጊዜ አግባ ወይ በጊዜ መንኩስ፡፡
  የግሪካውያን አባባል
በወይን ጠጅ ውስጥ እውነት አለች፡፡
  የሮማውያን አባባል
እናትና ልጅ ሲጣሉ፣ ሞኝ እውነት ይመስለዋል፡፡
  የአፍጋኒስታውያን አባባል
ድመቶች አይጥ የሚይዙት እግዚአብሔርን ለማስደሰት ብለው አይደለም፡፡
  የአፍጋኒስታውያን አባባል
ሞት ሲመጣ ጥሩንባ አይነፋም፡፡
  የኮንጎዎች አባባል
ስለ እሳት ማውራት ድስቱን አያበስለውም፡፡
  የአፍሪካ አሜሪካውያን አባባል
በእናቱ ጀርባ ላይ የተቀመጠ ህፃን የመንገዱን ርዝመት አያውቀውም፡፡
  የአፍሪካውያን አባባል
ቢራቢሮ መብረር ስለቻለች ብቻ ወፍ ነኝ ብላ ታስባለች፡፡
  የአፍሪካውያን አባባል
እስስት ቀለሟን እንጂ ቆዳዋን ፈፅሞ አትቀይርም፡፡
  የአፍሪካውያን አባባል
ቢላ ባለቤቱን አይለይም፡፡
  የአፍሪካውያን አባባል
የክፋትን ዘር በጊዜ ካላጠፋኸው አንተኑ ያጠፋሃል፡፡
  የቻይናውያን አባባል
ባሏ ከሞተ ሴት ጋር ግንኙነት ከመጀመርህ በፊት፣ ባሏን የገደለው ምን እንደሆነ መጠየቅ አለብህ፡፡
  የአፍሪካውያን አባባል

Published in ጥበብ
Monday, 31 August 2015 10:26

የካፍካ፥“ተስፋ ቁረጥ”

የጀርመን ባህል ማእከል እና ፈጠራ ድርሰት
                         
     ድንበር፥ ቋንቋ፥ መልክ ... ቢለያየንም የኅላዌ ጣጣ፥ ፍቅር፥ ለግል ዝምታ፥ ለጋራ ትኩሳት ... ተገጣጥበንም፥ ፈክተንም፥ በጊዜ ጉልበት እያቃሰትን ኖረናልና “ሰዉ” መሆናችን ቀደመ፤ ሥነጽሑፍ ሰበሰበን። የሀገራችን አንባቢ የባህር ማዶ የብዕር ንዝረት እንደ ልብ ትርታ ካልተደመጠዉ፥የሆነ ሥነውበታዊ ክፍተት እየሰፋ ያሰገዋል። ቋንቋ እየገደበን በጀርመንኛ የተጻፈ ለማጣጣም ይሳነን ይሆናል። ይህን በመገንዘብ Goethe Institut የሃያ ደራሲያንን የአጭር ልቦለድ ስብስብ “ከሕግ ፊት እና ሌሎችም ...”በጥራት እነዮናስ ታረቀኝ ወደ አማርኛ መልሰዉት ታትሞ ተነበበ። ለአለም ሥነጽሑፍ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ብዕሮች ተቀብለን ማጣጣም ያነቃቃል፤ አያሌ ጥያቄዎች ይርመሰመሳሉ። (ይህ መጽሐፍ ነገ እሁድ በወመዘክር ለውይይት ይቀርባል) የጀርመን ሥነጽሑፍ አባት የተባለዉ ጐተ በአንድ ግጥሙ ስለ “ዓመታት” ተቀኝቷል። በዘመን ውልደትና መክሰም መካከል የተሰነቀረ ግለሰብ፥እንዴት ጊዜና ዕድሜ ለመንጠፍ ሲባክኑበት አልተሸበረም ?

ደስታን የሚጭሩት፥ ዓመታት
ሰጥተዉን ትላንትናን ፤
ዛሬን አመጡልን።
---------------------------
ደብሩዋቸዉ መስጠት
ነፍገዉ ማበደርን፥
ይወስዳሉ ዛሬን ፤
ይወስዳሉ ነገን።

ግለሰብ ያልፋል፤ ዓመታት ይስለመለማሉ፤ ግን የደራሲ ምናብና ክህሎት ዘመን ተሻግረዉ አልባረቁም። ለዚህም ነዉ ጀርመናዊው ጐተ ከሁለት መቶ ዓመት በፊት የታሸበት ግጥም ዛሬም ብኩርናዉ ያልተገሰሰዉ። ሃያ ደራሲያን፥ አራት ግጥሞችና ሃያ ስድስት አጭር ልቦለዶች ያካተተዉ መጽሐፍ፤“ከሕግ ፊት እና ሌሎችም ...”  በመጠኑም ቢሆን ከትናንት እስከ ዛሬ የጀርመኖች ልቦለድ የገራዉን ጥበባዊ ዉበት በወፍ በረር ያሳየናል፤ የወደድነዉ ደራሲ ካለ በግል አድነን እንድንደመምበት ያነሳሳል።
ለዛሬ በሰባ ሰባት ቃላት ብቻ የተደረሰ -- ሐያሲያን post card short story የሚሉት-- ከጥሪ ካርድ ጀርባ የሰፋ ቦታ የማይለማመጥ ልቦለድ እስቲ አብረን እንድፈረዉ። ደራሲዉ ዝነኛዉ ካፍካ ነዉ። Kafka በሃያኛዉ ምዕተ አመት ልቦለድና አስተሳሰብ ላይ ተፅእኖዉ የጐላ ነዉ። በልቦለዱ የተቀነበበዉ ጭብጥ የግለሰብ ስጋትና ብቸኝነት የደፈረሰበት፥ ማኅበረሰብ ወጥመድ እንጂ ቤተ መቅደስ ያልሆነበት፥ ውስጣዊና ከባቢ ሰቆቃ የበዛበት የጭንቅ ኅላዌ ነዉ። “ተስፋ ቁረጥ” የተሰኘው የአጭር አጭር ልቦለድ የጊዜ ጉልበት፥ ባዳነት፥ ስጋት ... የወረሩት እምቅ ዝርግ ግጥም ለመሆን የበቃ ነዉና ሙሉዉን እንመሰጥበት ።
ተራኪዉ የቀን ሳይሆን የለሊት ጉዞ ነዉ የመረጠዉ፤ ይህ ብቸኝነቱን አጐላዉ። ከተነገረን ይልቅ የማናውቀው ያሳስባል። ወደ ባቡር ጣቢያ የሚገሰግሰዉ ለከተማዉ ባዳ ስለሆነ እንደ  ሽሽት ነዉን? ምናልባት ይህ ባቡር በሳምንት አንድ ቀን ብቻ የሚመጣና ዛሬ ካልደረሰበት መዘዙ  ይደፈጥጠው ይሆን? “መንገዶች ሁሉ ንፁህና ጭር ያሉ ናቸዉ።” መባሉ ቁሻሻ የሚሰበስቡት ተግባራቸውን አገባደው፥ ኗሪዉ እንቅልፉን እያጣጣመ፥ ንጋት በተረጋጋ ሁኔታ መጠበቃቸዉን ይጦቅማል። የተናጋሪዉ ሽብር ከዉስጡ እንጂ የአካባቢዉ ስክነት የቀፈቀፈዉ አይመስልም። የመንገድ ላይ ሰዓት እና የእጁን ሰዓት ሲያነፃፅር ተዛባበት፤ ግን ለምን የራሱ ሰዓት ትክክል እንዳልሆነ አምኖ ደነገጠ? የመንገዱ ሰዓት የተሳሳተ ከሆነስ? ፖሊሱን ሰዓት ስንት እንደ ሆነ ቢጠይቅ ይቀል ነበር፤ ይህን ለምን ሳተ? የተራኪዉ ሥነልቦና የደፈረሰዉና በፍርሃት የራደው ወቅቱ ተዛብቷል ብሎ ስላመነ ነዉና “ጊዜ” ፊቱን ስላዞረበት ሳይሆን ከባቡሩ ሳይደርስ ስለሚያግተዉ ነዉ። ደበበ ሰይፉ እንደ ተቀኘዉ ጊዜ አሸናፊ ሳይሆን መዋለሉ አይደለም ካፍካን የኮሰኮሰዉ። “ጊዜ በረርክ በረርክ / ግና ምን አተረፍክ / ግና ምን አጐደልክ? / ሞትን አላሸነፍክ / ሕይወትን አልገደልክ።”  [ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ፥ ገፅ 96] ካፍካ ምናልባት ከስድሳ ደቂቃ የማይበልጥ ወቅት መፍጠንና መዘግየት እንዴት የግለሰበን ሥነልቦና ሆነ ኅላዌ ሊያደፈርስ ጉልበት እንዳለዉ የተቆጨበት ነዉ።
በካፍካ አብይ ልቦለድ (እንደ the Trial እና the Castle) ተራኪዉ የሚኖረዉ አደናጋሪ፥ ቅዠትና ዕዉነታ የተቀላቀለበት የዕለት ተዕለት ክስተት፥ በዚህም ጠባብ መዳፍ ላይ በተጻፈ ልቦለድ ተካቷል። ገፀባህሪ ከሌላ መግባባት ተስኖት አካላዊና ሥነልቦናዊ ብይትዉርና ሲመዘምዘዉ አቅጣጫዉ እንደ ጠፋበት ያከትማል። ደራሲ አንተነህ ይግዛዉ “ባቡሩ ሲመጣ...” በሚለዉ ስብስቡ ይህን ካፍካዊ አለም ከሰባ በማይበልጥ ቃላት በጥቁር ነጥብ post card በሚሰፋበት ጥበት የቀነበበዉ የሚደንቅ ነዉ። በበኩር ስብስቡ ከስድስት አቅጣጫ የባከነ ትረካዉ “ሁለት መንገድ” ለአማርኛ አጭር ልቦለድ እንቁ ነዉ። በግሉ ሒሳዊ ወረቀት የምመለስበት ጉዳይ ነዉ፤ አንተነህ ካፍካን፥ ኩንዲራን ማንበቡ የበጀዉ ይመስላል።
የካፍካ ተራኪ የሰዓት ቆጠራ መዛባትና እንግዳነቱ፥በአቅጣጫ መደናገር ሸምቅቀዉት ሳለ ፖሊስ ማየቱ አረገበዉ። ይህ መንግስት የሚወክልና ለኗሪ ጥቅም የተመደበው ግን፥ መልሶ ሲያላግጥበት ያስሸብራል። ምናልባት ዘብ የቆመ ሳይሆን ቀውስ ከሆነስ? ወደ ጌታ እየሱስ የሚያሻግረዉን መንገድ የጠየቀዉ ይመስል ሳይቀላቀልበት ይቀራል? “መንገዱን ከኔ ማወቅ ትፈልጋለህ ! ... ተስፋ ቁረጥ!” በማለት ያሾፍበታል። ከመድረሻዉ ሳይደርስ ተስፋዉን ሊቀማ? የደራሲ ዳዊት ፀጋዬ -- እሱም ከካፍካዊ መደናገር እስከ እምነታዊ መብስክስክ የተጓዘ ነዉ -- “የሚከተል ተስፋ” ግጥምን ያስታዉሰናል። “ልጅን እሹሩሩ፥ እያሉ ያዝሉታል። / ጓዝንም ቀርቅበዉ፥ በጀርባ ይጭኑታል። / ታዲያ ! / አኗኗራችን እንደዚህ የሆነዉ? / ተስፋችን ከፊት ሳይሆን፥ ከኋላ ሆኖ ነዉ።” [አርነት የወጡ ሐሳቦች፥ ገፅ 12] የካፍካ ገፀባህሪ ግን ከፊት የሚመራዉ፥ ከጀርባ ያዘለዉ ተስፋ ተነፍጐ ሁሌ የብትዉርናን ጭንቀት እንደ ገፈታተረዉ ያዘግማል። ዘመነኛ ብስል ግለሰብ ዕጣ ፈንታዉ ባይተዋር ሆኖ ለመኖር የተቀነበበ መሰለ።
ከጀርመንኛ ወደ አማርኛ የተሻገሩት ሃያ ስድስት አጭር ልቦለዶች ሰው ሲያፈቅር፥ ክህደት ሲያቆስለው፥ ወሲባዊ አምሮት ሲመዘምዘዉ፥ እድሜና ትዝታዉ ሲቀዝፉት ... ፈክቶም ገርጥቶም በኅላዌ ጥያቄዎች ሲላላጥ ተተርኮበታል። “ከሕግ ፊት ...” ሲያነቡት፥ ሲወያዩበት ምናባዊና ፍልስፍናዊ እሴቱ ስንቅ ያስቋጥራል። ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ በ“የተስፋ ክትባት” እንዳለዉ “ስንቱ ብጭቅጫቂ ፥/ ለጨረር ተብሎ እየተወጠረ / ጸሃይቱ ጠልቃም፥ ተንጠልጥሎ ቀረ።” ካፍካ ይህን ብጭቅጫቂ ነፍስ ነዉ ከጥሪ ወረቀት ጀርባ በተኮማተረ ትረካ አንጠልጥሎ የዘነጋዉ።

Published in ጥበብ

በወጣቷ የፊልም ባለሙያ ሕይወት አድማሱ የተሰራው “አዲስ ዓይኖች” የተሰኘው አጭር ፊልም በዓለም አቀፎቹ የቬነስና ቶሮንቶ ፊልም ፌስቲቫሎች ላይ እንዲታይ መመረጡ ተገለፀ፡፡
ፊልሙ አንዲት የ13 ዓመት ሴት ልጅ የሚጋጥማትን አካላዊና የስሜት ዕድገት ለውጥ ተከትሎ ከማህበረሰቡ ጋር የምትፈጥረውን ግጭት የሚያሳይ ነው ተብሏል፡፡
የፊልሙ ፀሐፊና ዳይሬክተር ህይወት አድማሱ፤ በመላው ዓለም ካሉ 10 ባለተሰጥኦ ወጣት የፊልም ሰሪዎች አንዷ ሆና በቶሮንቶው የፊልም ፌስቲቫል ለሚካሄድ ልዩ ፕሮግራም በመመረጥ ከአፍሪካ ብቸኛዋ እንደሆነች ገልፃለች፡፡
“አዲስ ዓይኖች” በእንግሊዝና በፈረንሳይ የፊልም ኩባንያዎች ፕሮዱዩስ እንደተደረገ ወጣቷ ተናግራለች፡፡
ህይወት በኤሌክትሪክና ኮምፒዩተር ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ያገኘች ሲሆን በብሉናይል የፊልምና የቴሌቪዥን አካዳሚ ገብታም የፊልም ጥበብን ተምራለች፡፡ ወጣቷ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የፊልም ዎርክሾፕና ስልጠናም ላይ መካፈሏንም ጠቁማለች፡፡

በፈቃዱ ሲሳይ የተፃፈው “ምፅኣተ ዓም-ሓራ… በአዲሶቹ ዓም-ሓሮች” የተሰኘ ፖለቲካዊ ልቦለድ መፅሃፍ ሰሞኑን ለንባብ በቃ፡፡ በ269 ገፆች የተቀነበበው ልቦለዱ፤ ለአገር ውስጥ በ75 ብር፣ ለውጭ አገር በ25 ዶላር ይሸጣል፡፡

 በሲሳይ መኳንንት የተዘጋጀው “አይፈራም ጋሜው እና ምናባዊ እንግዶቹ ቁ.2” ሰሞኑን ለንባብ በቃ፡፡ “ይህ… መፅሃፍ ከቅፅ 1 ጋር በይዘት ተመሳሳይነት ስላለው ተከታይ ክፍል ሆኖ የተዘጋጀ ሲሆን የመጀመሪያውን መፅሃፍ አግኝቶ ለማንበብ ያልቻለ አንባቢ ቢኖር ይህን ተከታይ መፅሃፍ ብቻ በተናጠል ሊያነበው ይችላል” ብሏል - ደራሲው መቅድም በሚል ርዕስ ባሰፈረው ማስታወሻ፡፡
የቀድሞውም ሆነ የአሁኑ መፅሃፍ በንግግር ልውውጥ ላይ የተመሰረቱ ሃሳቦችን የሚያስተላልፉ መሆናቸውን የጠቆመው ደራሲው፤ ከአገር ውስጥ ከቀድሞው የአገሪቱ መሪዎች  ከኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምና ከጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር፣ ከውጭ ከኔልሰን ማንዴላ፣ ኦፕራ ዊንፍሬይ፣ ማይክል ጃክሰንና ሌሎች ታዋቂ ሰዎች ጋር ምናባዊ ቃለ ምልልስ ማድረጉን ገልጿል፡፡ መፅሃፉ ለአገር ውስጥ በ75 ብር፣ ለውጭ አገራት በ10 ዶላርና በ8 ዩሮ ለገበያ ቀርቧል፡፡

Monday, 31 August 2015 09:48

የዓውዳመት ግርግር

    ቡሄ ካለፈ በኋላ የዐውደ-ዓመት መአዛ ከተሞችን ያሽቆጠቁጣል፡፡ ወትሮ የተለመዱት ነገሮች ሳይቀሩ አንዳች ቀለም ይረጭባቸዋል፡፡ የሆነ መአዛ ያሳብዳቸዋል፡፡ ሳሩና ቅጠሉ የግዱን አይን ይሰርቃል፡፡ አበቦች እንኳ አፋቸውን ፈትተው “የምስራች” ባይሉም፣ ገና በዋዜማው ሳቅ ሳቅ የሚላቸው ምትሃታዊ ቋንቋ ይነበብባቸዋል፡፡
ከዚያ ባሻገር መንደሮች በአውራ ዶሮና በሲካካ ዶሮዎች ሽር ጉድና ፍልሚያ መናጣቸው የግድ ነው፡፡ እንዲያውም ድሮ-ድሮ በጐች የሚዋጉባቸው መስኮች ናቸው ዛሬ ለአውራ ዶሮ መናከሻ የዋሉት እንጂ ጉዳዩ ሌላ ነበር፡፡ ይህንንም አያሳጣን ማለትን የለመደው የአለታ ወንዶ ሰው ብቻ አይደለም፡፡ ሀገር ሁሉ ነው፡፡
እትዬ አረጋሽም እዚህ ማርያም ሰፈር ልጅነታቸውን ፈጅተው፣ አዋቂነታቸውን አጣጥመው ኖረዋል፡፡ ከጥቁር ቦቃ በግ እስከ ጥቁር ገብስማ ዶሮ ለእንቁጣጣሽ፣ ከዳለቻ በግ እስከ ወሰራ ለመስቀል እያረዱ ዘልቀዋል፡፡
ዘንድሮ እንዳምናው ባይቀናቸውም እንኳ ጥቁር ገብስማ ዶሮዋቸውን ገዝተው ለቅቀዋል፡፡ አንዳንድ ጐረቤቶቻቸው ቀይ፣ ሌሎቹ ነጭ ገብስማ አሰማርተዋል፡፡ ያ-ነገረኛ ከፈለኝ ግን ቁርጥ የራሳቸውን የመሰለ ጥቁር ገብስማ ዶሮ ገዝቶ ስለለቀቀ፣ ነገር እንዳይመጣ ፈርተው፣ እግሩ ላይ ቀይ ጨርቅ ያሰሩት ዛሬ ነው፡፡
“አማከለች ልብ አድርጊልኝ… ኋላ ለሃይማኖትሽ ትመሰክሪያለሽ… ቀኝ እግሩ ላይ ምልክት አድርጌያለሁ” አሏት - ልጅ እግርዋን ጐረቤታቸውን፡፡ እሷም ተሽቆጥቁጣ…. “ኧረ የትም ብሄድ እመሰክራለሁ… አለች፡፡ ለነገሩ ሳታይም ቢሆን ከመመስከር አትመለስም፡፡ አለዚያ ያ ሰካራም ባልዋ በዱላ ሲነርታት ማን ይደርስላታል?.... ቢያማት፣ ቢርባት፣ ሀዘን ቢደርስባት… እትዬ አረጋሽ ናቸው ከትንፋሽዋ ፈጥነው የሚደርሱላት!
እሳቸው ዶሮም ሆነ በግ ሳያርዱ አውደ አመት አያልፍም፡፡ ይፈራሉ፡፡ ለጤንነታቸው፣ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለዘመዶቻቸው ሁሉ ሰላም የሚሆነው ይህን ሲያደርጉ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ባለቤታቸው ናቸው ይህንን የማይወዱላቸው፡፡ “ባንድ ጐን ፈጣሪ፣ በሌላ ጐን ጥንቆላ - ምንድነው!” በማለት ይቆጣሉ፡፡
“አዩ ያያት የቅድማያቶቼ ነው…. ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ነው፡፡ እናቴ አልለማመን ብላ ነው የሞተችው…. አባቴም እንዳንቱ ሲያንጓጥጥ ነው በሽተኛ ሆኖ አልጋ ላይ የወደቀው፡፡ የኋላ ኋላ ፈጣሪ ረዳው እንጂ!”
ማዘንጊያ አይዋጥላቸውም፡፡ እርሳቸውም ለነገሩ ሃይማኖተኛ አይደሉም፡፡ ልብስ ይሰፋሉ፣ ይበላሉ፣ ይጠጣሉ - በቃ! … ፈጣሪን በልባቸው ነው! ግን ተቀጥላ ነገር አይወድዱም፡፡ ልምምጥ - አይሆንላቸውም፡፡
“ቅመም የሌለው ዶሮና ሥጋማ አይዋጥልኝም… እናቴ ሀገር ያወቃት ባለሞያ ነበረች፡፡ ዳቦ እንኳ ስትደፋ የሰፈሩ ሰው እንደ ተአምር ነበር የሚያወራላት!... አሁንማ ምን ሴት አለ፡፡” ሲሉ ይመፃደቃሉ፡፡
አቶ ማዘንጊያ ገበያቸው እንደድሮ ስላልሆነ ለሚስታቸው ለአውደ አመት ምንም አልሰጡዋቸውም፡፡ አሁን ሰው ጣቃ አስቀድዶ ልብስ ማሰፋት ትቷል፡፡ ሁሉም ሬዲ-ሜድ ለባሽ ሆኖዋል፡፡ በተለይ ቻይና ከገባ ወዲህ የልብስ ሰፊ ገበያ ደክሟል፡፡ ልብስ ሰፊ፤ የቻይና ነገር ቆሽቱን ያሳርረዋል፡፡
አንዳንዴ እትዬ አረጋሽም ይከፋቸዋል፡፡
“እነዚያ ኩባዎች ገዳም ነበሩ፤ … ይላሉ፡፡” ወደው ግን አይደለም፤ ያኔ በደርግ ጊዜ ኩባ ደንበኞች ነበሯቸው፡፡ ጠጅ ቤታቸውን ግጥም አድርገው ሞልተው ነበር የሚጠጡት፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ጥሬ ሥጋ ይገዙና ቀዩን ሥጋ በልተው ጮማውን እንዳለ ነበር የሚሰጧቸው፡፡ በተለይ ታናሽና ሽንጥ ከገዙ ብዙው ለሳቸው ነበር የሚቀረው፡፡
ደግነቱ መኖሪያ ቤት ሰርተዋል፡፡ እርሷን ባያከራዩ ምን ይውጣቸው ነበር! በደጉ ጊዜ ቀበሌ መሬት በነፃ ሰጥቷቸው፣ የቤት ባለቤት ሆነዋል፡፡ ያኔ ሳንቲሙም በረከት ነበረው ይላሉ፡፡  እንዲያም ሆኖ ይመስገነው ማለታቸው አልቀረም … ሦስት ሰርቪሶች ለመንግሥት ሠራተኞች አከራይተዋል፡፡ ይህን ሲያስቡ ዘውድ ያልደፋ ንግስትነት ይሰማቸዋል፡፡
ትዳራቸው ብዙም ግጭት፣ ብዙም ፍቅር የለውም፤ ለሰስ ያለ ነው፡፡ ሲያገቡዋቸውም አብደው ክንፍ አውጥተው አይደለም፡፡ በምግብና በመጠጥ ነው የደለሏቸው፡፡ ያኔ ማዘንጊያ የሚያማልሉ ፈርጣማና ተደባዳቢ ነበሩ፡፡ እንዲያውም ከክቡር ዘበኛ ሠራዊት ከድተው ነው የመጡት ይባላል፡፡ የአለቃቸውን አፍንጫ ሰብረው ትንሽ ጊዜ ከተደበቁ በኋላ ነው ብቅ ያሉት፡፡
አለታ ወንዶ ከተማ ዲላ ሰፈር ልብስ ስፌት ጀምረው ተወዳጅነት ቢቀዳጁም ማታ-ማታ መጠጥ ቤት ያመሻሉ፡፡ ጥሎባቸው ጠጅ ይወድዳሉ፤ እትዬ አረጋሽ ደግሞ የጠርሙስ ጠጃቸው ሀገርን ያፋጀ ነበር፡፡ በወረፋ ነበር የሚጠጣው፡፡
አቶ ማዘንጊያ በዚያ ተላመዱ፡፡ አረጋሽም ወደዱዋቸው፡፡ “ቆፍጣናና ጐበዝ እወዳለሁ፡፡ …ጀግና ነው!” ይላሉ፡፡ ሁለቱም አላወቁት አልጋ ላይ ወደቁ፡፡ ከዚያ ጣት የሚያስቆረጥም ቅንጬ ጧት ጧት፣ ቀን በቅመም ያበደ ዶሮ፣ ማታ ክትፎ ሲለምዱ ገነት የገቡ መሰላቸው፡፡ ቀሩ - ቀሩ፡፡ አሁን አሁን ግን ልጅ ስላልወለዱ ይነጫነጫሉ፡፡ መጠጡም የባሰባቸው ለዚያ ነው፡፡ ባእድ አምልኮማ ማየት ጠልተዋል፡፡ እድሜያቸው እየጨመረ ሲመጣ ይሁን በሌላ አያውቁትም፤ ደስተኛ አይደሉም፡፡ ልባቸው ላይ አሎሎ ድንጋይ፣ ነፍሳቸው ላይ እሾህ የተተከለ ያህል ያማቸዋል፡፡ እናም ሁለንተናቸውን አረቄ ውስጥ ይዘፈዝፋሉ፡፡ ያኔ የምድረ በዳ ዋሽንት… የጨረቃ ልቅሶ… የፀሐይ ማላዘን - አይሰማቸውም፡፡ ….ድርግምግም ይላሉ - በሮች ሁሉ፡፡
እትዬ አረጋሽ የዶሮዋቸውን ቀኝ እግር በቀይ ጨርቅ ካሰሩ በኋላ፣ አማከለችን ምስክር ጠርተው፤ ቅመማቸውን - አስጥተው የጐረቤት ቡና ጠጥተው ፣ ወደ ቤታቸው ገቡ፡፡
አቶ ማዘንጊያ ለምሳ ወደ ቤት አልተመለሱም፡፡ ለነገሩ - ደስ ያላቸው ቀን ይመጣሉ፣ ደስ ካላላቸው እዚያው ከጓደኞቻቸው ጋር ምናምኗን ቀማምሰው ይውላሉ፡፡
አረጋሽ ግን ትንሽ ቀማመሱና ወደ ዴላ ገበያ ለመሄድ ተነሱ፡፡
“አማከለች እንግዲህ ሰፈሩን አየት-አየት አድርጊ!... መጣሁ፡፡ አሏትና ነጠላቸውን አሰማምረው ዘንቢል ይዘው ተነሱ፡፡
“በሉ ጠንቀቅ ይበሉ!... የዓመት ባል ሌባ - እንደጭልፊት ነው የሚናጠቀው”
“እኔ ያንቺ እናት - ለዚህ እንኳ ቆቅ ነኝ፤… ተሰረቀች ሲባል ሰምተሽ ታውቂያለሽ!?”
“እሱስ አልሰማሁም! ብቻ አንድዬ ይጠብቅ ማለት ነው”
“እርግጥ ነው … እርግጥ ነው”
ተሰናብተው ቁልቁል ወረዱ፡፡ በከፈለኝ ቤት በኩል ሲወጡ ቤቱ ዝግ ነው፡፡ ሾፌር ስለሆነ ይሄኔ ካገር ሀገር ይንከራተታል፡፡ ከአለታ ወንዶ ሀገረሰላም፣ ቀባዶ፣ ተፈሪ ኬላ፣ ጩኮ፣ ይርጋለም… የማይሄድበት የለም፡፡ “ይሰራል፣ ይበላል፣ ግን አይጠጋውም!...” ይሉታል እትዬ አረጋሽ፡፡ በልባቸው ረግመውት አለፉ፡፡
“እመቤቴ ከሰፈሩ ንቅል ታድርግህ አንተን!” አሉና ለራሳቸው ገረማቸው፡፡ በሌለበት ምን አሳደበኝ የሚል ስሜት በውስጣቸው አደረ፡፡
ሼል ማደያ አካባቢ ሲደርሱ ከዲላ ሰፈር በኩል የብዙ ሰዎች የጭፈራ ድምፅ ሰሙ፡፡ ጠጋ እያለ ሲመጣ ጭፈራው የምን እንደሆነ ለዩ፡፡ ሌባ ተይዞ ነው፡፡“የቱ ነው የፈረደበት?!” አሉና ጥግ ጥጉን ይዘው ቁልቁል ወረዱ፡፡ ሕፃናት ልምጭ ነገር ይዘው ሌባውን ከብበዋል፡፡ እየተጠጉ ሲሄዱ ከፈለኝን አዩት፡፡ “እሱን ደ‘ሞ ሕግ አስከባሪ ያደረገው ማነው!” ብለው አጉተመተሙ፡፡ ያዩትን ነገር አይናቸው ማመን ሲያቅተው ዘንቢላቸውን ወርውረው ሮጡ፡፡
ጠዋት አቶ ማዘንጊያ የተናገሯቸው ትዝ አላቸው፤ “ይህንን ለሰይጣን የገዛሽውን ዶሮ ሸጬ ጉድ ባልሰራሽ!” ብለዋቸው ነበር፡፡
አረጋሽ በድንጋጤ፤ “በሕግ አምላክ! ዶሮው የኔ ነው!” እያሉ ሮጡ፡፡ ዶሮው እግር ላይ ግን ቀይ ጨርቅ የለም!... “ማዘንጊያ ጉድ ሆኗል” አሉ - በልባቸው፡፡ ባለቤታቸው ለከፈለኝ ወጥመድ መዳረጉን እያሰላሰሉ፡፡

Published in ልብ-ወለድ

   460 ሚ.ብር በጀት ተይዞለታል
                             
    ዜጎች ከመንግሥታዊና ህዝባዊ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት መብታቸውን ተጠቅመው የሚፈልጉትን አገልግሎት ለማግኘት እንዴት መጠየቅ እንዳለባቸው ግንዛቤ የሚሰጥ “ከመጠየቅ ….” የተሰኘ ማህበራዊ ተጠያቂነት ላይ ያተኮረ ቲያትር ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለተመልካች ቀረበ፡፡ ቲያትሩ በ20 የተለያዩ መድረኮች ለሙከራ እንደሚቀርብና 460 ሚ.ብር ገደማ በጀት እንደተያዘለት ተገልጿል፡፡
በመንግሥት የሚተገበሩ መሰረታዊ አገልግሎቶች በተጠያቂነት ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ ለማድረግ አልሞ የሚሰራው ይሄ ፕሮጀክት፤ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የክልል ወረዳዎች ተሞክሮ ተጨባጭ ውጤት አስመዝግቧል ተብሏል፡፡ በቲያትር የሚቀርበው የግንዛቤ ማስጨበጪያ ፕሮግራሙ፤ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማትና በተገልጋዩ መካከል ሊኖር ስለሚገባው ግንኙነትና አገልግሎት ሰጪ ሰራተኞችና ተቋማት ያለባቸው ተጠያቂነት ምን ድረስ ሊሆን እንደሚገባ የሚያስገነዝብ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ የቲያትሩ ፀሐፊና የፕሮጀክቱ የህዝብ ግንኙነት አማካሪ ምህረት ማስረሻ እንደገለፀው፤ ቲያትሩ በአዲስ አበባ በ20 የተለያዩ መድረኮች ለሙከራ ያህል የሚቀርብ ሲሆን ከሙከራ በኋላም የተለያዩ ድርጅቶች ለሰራተኞቻቸው በሚያዘጋጁት ስልጠናዎች፣ አውደ - ጥናቶችና ስብሰባዎች ላይ እንዲቀርብላቸው ሲጠይቁ የሚቀርብ ይሆናል፡፡ ባለፈው ረቡዕ ለመጀመሪያ ጊዜ በቂርቆስ ክ/ከተማ ቤተሰብ መምሪያ ግቢ ውስጥ ቲያትሩን ለህዝብ በማቅረብ ፕሮግራሙ በአዲስ አበባ በይፋ የተጀመረ ሲሆን ከዚህ ቀደም ቲያትሩ በቀረበባቸው በአማራ ክልል፡- ደብረ ታቦር፤ በአፋር፣ በትግራይና በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ ባሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ለውጥ ተመዝግቧል ተብሏል፡፡
በደብረ ታቦር ከተማ ከንፁህ የውሃ አቅርቦት አገልግሎት ጋር ተያይዞ በዚህ መንገድ በተዘጋጀ የግንዛቤ ማስጨበጪያ መድረክ አማካኝነት የውሃ አገልግሎቱ እንደተሻሻለ ተጠቅሷል፡፡
በሌሎች አካባቢዎችም በት/ቤቶች፣ በጤና ጣቢያዎች፣ በንፅህና አጠባበቅና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በቲያትር መልክ በተሰጠ የግንዛቤ ማስጨበጪያ ፕሮግራም ለውጥ ማስመዝገብ እንደተቻለ ተጠቁሟል፡፡
ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ 460 ሚሊዮን ብር ገደማ በጀት የተያዘለት ሲሆን 49 መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በፈፃሚ አጋርነት እንደሚሳተፉበት ታውቋል፡፡
በዋናነት በቲያትር የሚቀርበው የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም፤ ህብረተሰቡ በራሱ ገንዘብና በስሙ ተጠይቆ በሚገኘው ብድርና እርዳታ የሚሰሩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በ“የኔነት” ስሜት መብቱን አስከብሮ እንዴት መጠቀም እንዳለበት ትምህርት ይሰጣል ተብሏል፡፡
“ከመጠየቅ”… በማህበራዊ ተጠያቂነት ቲያትር ጥናቶች ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ ሲሆን ፕሮግራሙ በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የበላይ አስተባባሪነት፣ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ድጋፍ፣ እንዲሁም በዓለም ባንክ አጠቃላይ አፈፃፀም ክትትል አድራጊነት እየተከናወነ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡

Published in ጥበብ

የደራሲ ኤልያስ ማሞ “እንጦሽ”፣ “ውቤ ከረሜላ -1” እና “ጉጉት” የተሰኙ ሶስት መፃህፍት ነገ ጠዋት በ 4 ሰዓት በብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃህፍት ኤጀንሲ አዳራሽ ይመረቃሉ፡፡
“እንጦሽ” በ2006 ዓ.ም ለንባብ የበቃ የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ ሲሆን “ውቤ ከረሜላ - 1” የተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮችን የሚዳስስ መፅሀፍ ነው፡፡ በነገው እለት ለንባብ የሚበቃው “ጉጉት”፤ የ“ውቤ ከረሜላ” ሁለተኛ ክፍል እንደሆነ ታውቋል፡፡
ሶስቱም መፃህፍት እያንዳንዳቸው ከ230 ገፆች በላይ ያሏቸው ሲሆን “እንጦሽ” በ48 ብር፣ “ውቤ ከረሜላ” በ50 ብር እንዲሁም “ጉጉት” በ60 ብር ለገበያ መቅረባቸው ተገልጿል፡፡

“ከህግ ፊትና ሌሎችም አጫጭር ታሪኮች” በተሰኘውና በጀርመን የባህል ተቋም አማካይነት ታትሞ በኢትዮጵያውያን ደራሲዎች ከጀርመንኛ ወደ አማርኛ የተተረጐሙ ታሪኮችን በያዘው መፅሃፍ ላይ ነገ ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ ውይይት እንደሚደረግ ተገለፀ፡፡
ለውይይት የሚሆን ሃሳብ የሚያቀርበው አንጋፋው የሥነፅሁፍ ሐያሲ አብደላ እዝራ ነው ተብሏል፡፡ የመፃህፍት ውይይቱ፤ እናት የማስታወቂያ ሥራዎች ድርጅት፣ ጀርመን የባህል ማዕከልና ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ መፃህፍት ኤጀንሲ በጋራ የሚያከናውኑት ወርሃዊ ፕሮግራም ነው፡፡

   በዮፍታሄ ብርሃኔ የተፃፉ ግጥሞችን ያካተተው “በከንፈር እምጷታ” የተሰኘ የግጥም መድበል ከትላንት በስቲያ ምሽት በዋቢሸበሌ ሆቴል ተመረቀ፡፡ በ64 ገፆች ከ 460 በላይ አጫጭር ግጥሞችን ያሰባሰበው መድበሉ፤ በ30 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

Page 1 of 19