መንግስት ም/ፕሬዚዳንቱ ከአገር የወጡት ለስራ ጉዳይ ነው ብሏል

   የብሩንዲው ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ፤ ህገ መንግስቱ ከሚፈቅድላቸው ውጭ በቅርቡ በሚካሄደው የአገሪቱ ምርጫ ለሶስተኛ ዙር ለመወዳደር መወሰናቸውን በመቃወማቸው ከመንግስት አካላት ማስፈራሪያ እየተደረገባቸው እንደሆነ የገለጹት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጌርቪያስ ሩፊኪሪ፣ ለህይወታቸው በመስጋት አገር ጥለው መሰደዳቸውን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
የአገሪቱ መንግስት ቃል አቀባይ በበኩላቸው፤ምክትል ፕሬዚዳንቱ ከአገር የወጡት ለስራ ጉዳይ ነው፤ ምንም አይነት ማስፈራሪያ አልተደረገባቸውም ብለዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ዘንድሮም በምርጫ እንደሚወዳደሩ መግለጻቸውን ተከትሎ፣ በአገሪቱ የተቀሰቀሰው ግጭት እየተባባሰ ነው፤ የህዝቡ ተቃውሞም እንደቀጠለ ነው፤ ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጌሪያስ ሩፊኪሪ፣ መንግስት በሌሎች ተቃዋሚዎች ላይ እንደሚያደርገው ሁሉ በእኔ ላይም ዛቻና ማስፈራሪያ እያደረገብኝ ስለሆነ አገሬን ጥዬ ተሰድጃለሁ ብለዋል ከፍራንስ24 የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ፡፡
በቅርቡም የብሩንዲ የህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ፍርድ ቤት ዳኛ እና የምርጫ ኮሚሽን አባልን ጨምሮ ሌሎች የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ የፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛን ውሳኔ በመቃወም አገር ጥለው መሰደዳቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤ በመጪው ሐምሌ ወር አጋማሽ ላይ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የብሩንዲ ምርጫ ሳቢያ የተቀሰቀሰውን ግጭትና የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ፣ የብሩንዲን ገዢ ፓርቲና ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ለማደራደር እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ዘገባው ጨምሮ ገልጧል፡፡
የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቶችም ላለፉት ሁለት ወራት በአገሪቱ ፖሊስና በተቃዋሚዎች መካከል በተደረጉ ግጭቶች፣  ከ70 በላይ ዜጎች መሞታቸውንና 500 ያህልም መቁሰላቸውን አስታውቀዋል ብሏል ዘገባው፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

 በፓኪስታን በተከሰተው ከመጠን ያለፈ የሙቀት አደጋ ከሰባት መቶ በላይ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን ሲኤንኤን ከዋና ከተማዋ ካራቺ የዘገበ ሲሆን የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ናዋዝ ሸሪፍ የአስቸኳይ የአደጋ ጊዜ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ሙቀቱ በድንገት የመታት የመጀመሪያዋ ከተማ፣ ከፓኪስታን በደቡባዊ አቅጣጫ የምትገኘዋን የሲንድ ግዛትን ነበር፤ ባለፈው ሳምንት ማገባደጃ ላይ፡፡ ወሩ በእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች ዘንድ የሮመዳን ፆም  የተያዘበት እንደመሆኑ አደጋው እጥፍ ድርብ ችግሮችን እንዳስከተለ ዘገባዎች ይጠቁማሉ፡፡  ህይወታቸውን በሙቀቱ ያጡት ሰለባዎች ቁጥር የአስከሬን ማቆያዎች ከሚቀበሉት በላይ በመሆኑ ሆስፒታሎች በሬሳ ተጨናንቀው በዜና ማሰራጫዎች ታይተዋል፡፡  እስከ ትላንት በስቲያ ድረስ ወደ 750 የፓኪስታን ዜጎች ሲሞቱ፣ ከሺ በላይ የሚገመቱት ደግሞ ከሙቀቱ ጋር በተያያዘ እንደ ሀይለኛ ትኩሳትና የሰውነት ፈሳሽ ድርቀት (Dehydration) መሰል የጤና ቀውሶች ተጠቅተው፣ አስከፊ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የሙቀቱ አደጋ ከፍተኛ የህይወት መጥፋት ያስከተለው በሀገሪቱ ትልቅ በምትባለው የካራፒ ከተማ ሲሆን ወደ ስድስት መቶ ነዋሪዎችም ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
ከአደጋው ጋር በተያያዘ በተከሰተ የትራፊክ መጨናነቅ ሳቢያ ነዋሪዎች  የሟች ዘመዶቻቸውን አስከሬን ወደ ቀብር ቦታ ለማድረስ መቸገራቸውን ገልፀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሀይል እጥረት ምክኒያት እየተዛባ ይዳረስ የነበረው የውሀ አቅርቦት ጊዜያዊ መፍትሄዎች እንዳይወሰዱ አድርጓል። አንዳንድ ነዋሪዎች የተከሰተውን ሙቀት በውሀ ለማብረድ ቢፍጨረጨሩም  … በከተማው ያሉ የውሀ መስመሮች በመሰባበራቸው መፍትሄ ሊሆኑዋቸው አልቻሉም፡፡ የፓኪስታን ክልል አስተዳዳሪ ከዌም አሊ ሻህ፤ የሙቀቱ አደጋ ጋብ እስከሚልበት ጊዜ ድረስ ትምህርት ቤቶችና የመንግስት መስሪያ ቤቶች ተዘግተው እንዲቆዩ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡ አስተዳዳሪው ለተቀጠፉት ነፍሶች ተጠያቂው መንግስት እንደሆነም ሲገልጹ፤ “ሀይል ማሰራጫ መስመሮች እንዲታደሱ አስቀድመን ብንወተውትም፣ የሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ምላሽ ባለመስጠታቸው አደጋው ከመጠን ያለፈ ጥፋት አድርሷል” በማለት ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

 በያዝነው የፈረንጆች አመት በርካታ ሰራተኞችን ቀጥረው እያሰሩ ከሚገኙ የዓለማችን ተቋማትና ድርጅቶች መካከል፣ 3.2 ሚሊዮን ሰራተኞችን የሚያስተዳድረው የአሜሪካ መከላከያ ሚንስቴር ፔንታገን በሠራተኞች ብዛት መሪነቱን መያዙን ፎርብስ መጽሄት ዘገበ፡፡
የአለም የኢኮኖሚ ፎረም ሰሞኑን ይፋ ያደረገውን የጥናት ውጤት ጠቅሶ ፎርብስ ባለፈው ማክሰኞ እንዳስነበበው፣ የቻይና ህዝቦች የነጻነት ጦር 2.3 ሚሊዮን ሰራተኞችን በመያዝ በሁለተኝነት ሲከተል፣ ታዋቂው አለማቀፍ የሸቀጣሸቀጥ ሱፕርማርኬት  ዎልማርት በ2.1 ሚሊዮን ሰራተኞች ሶስተኛውን ደረጃ ይዟል፡፡ በአመቱ በርካታ ሰራተኞችን በስሩ ቀጥሮ በማስተዳደር ከአለማችን አራተኛውን ደረጃ የያዘው ደግሞ 1.9 ሚሊዮን ሰራተኞች ያሉት ታዋቂው የምግብ አምራች ኩባንያ ማክዶናልድ ነው፡፡
የእንግሊዝ ብሄራዊ የጤና አገልግሎት ድርጅት በ1፣7 ሚሊዮን ሰራተኞች አምስተኛ ደረጃን እንደያዘ የገለጸው ዘገባው፣ የቻይና ብሄራዊ የነዳጅ ኮርፖሬሽን በ1.6 ሚሊዮን፣ የቻይናው ስቴት ግሪድ ኮርፖሬሽን በ1.5 ሚሊዮን፣ የህንድ ምድር ባቡር ኩባንያ በ1.4 ሚሊዮን፣ የህንድ የጦር ሃይል በ1.3 ሚሊዮን እንዲሁም ሆን ሃይ ፕሪሲዥን የተባለው ኩባንያ በ1.2 ሚሊዮን ሰራተኞች እስከ አስረኛ ደረጃ ይዘዋል ብሏል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

 በናይጄሪያ መንግሥት ከፍተኛ ተከፋይ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የህግ አውጪ ባለሙያዎች (ሴናተሮች) የገዛ ራሳቸውን ደመወዝ ለመቀነስ የሚደነግግ ህግ ለማፅደቅ ሀሳብ እንዳቀረቡ ሮይተርስ ዘገበ፡፡
ናይጄሪያ የህግ አውጪ ሆነው የሚሰሩ 469 የከፍተኛ ፍትህ አባላት አሏት፡፡ እነዚህ ህግ አውጪዎች በዓመት የሚቀበሉት የደመወዝና ጥቅማ ጥቅም በጀት በሀገሩ ላይ ያሉት 36 ክልሎች በአመት ከሚመደብላቸው ገንዘብ የበለጠ እንደሆነ ማወቅ ተችሏል፡፡ እነዚህ ክልሎች በአማካይ እያንዳንዳቸው ከሚሊዮን ነዋሪዎች በላይ የሚያስተዳድሩ ናቸው፡፡  
 ለአስር አመታት ያህል በተለይም ከአለፉት አራት አመታት ጀምሮ የናይጄሪያ ኢኮኖሚ ባሽቆለቆለው የዓለም አቀፍ ነዳጅ ገበያ መንስኤነት አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱን ሮይተርስ ጠቁሟል፡፡ የናይጄሪያ መንግስት የሚተዳደረው ነዳጅ ተሸጦ ከሚገኘው ቀረጥ በመሆኑ፣ ከወደቀው የዓለም ነዳጅ ዋጋ ጋር የመንግስት የበጀት አቅምም ላሽቋል፡፡ በዚህም ምክኒያት በሌጎስ የሚገኝ ገለልተኛ ተቋም ቡድን የነዋሪዎቹን የገንዘብ አወጣጥ በቅርብ ሆኖ እየገመገመ ይገኛል፡፡
የዚሁ ተቋም መስራች የሆነው ኦሊሲዮን አጓበንዴ፤ ከሌላው መንግስታዊ ተከፋይ በተለየ ሁኔታ ገንዘብ የሚያገኙትን የፍትህ ስርዓት ባለሙያዎች፣ የህዝብ አገልጋይ መሆን ሲገባቸው ከመጠን ያለፈ የመንግስት በጀት ተጠቃሚ መሆናቸውን በመጠቆም አቤቱታ ያሰማል፡፡
ባለፈው ሳምንት በሌጎስ የወጣው ዴይሊ ሪፖርት፤ እያንዳንዱ የሴኔት አባል በዓመት ለልብስ መግዣ እንዲሆነው 105 ዶላር እንደሚሰጠው ዘግቧል፡፡ ባለፈው ሚያዚያ አዲሱን የፕሬዚዳንት ወንበር የተረከቡት ሞሀመድ ቦሀሪ፤ በሀገሪቱ ላይ የተንሰራፋውን የአባካኝነት ባህል እንደሚለውጡ ቃል መግባታቸው ይታወሳል፡፡ የሀገሪቱ ብሔራዊ ምክር ቤት አባላትም ከፕሬዚዳንቱ ጋር ሆነው ለመስራት በከፊል ተስማምተዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የህግ አውጪ ባለሙያዎቹም የፕሬዚዳንቱን አቋም በመደገፍ የሚከፈላቸውን ወርሀዊ ደሞዝ ዝቅ ለማድረግ ሀሳብ ማቅረብ ጀምረዋል፡፡ ከሀሳብ አቅራቢዎቹ መካከል የኮጂ ክልል ተወካይ በሰጠው አስተያየት፤ “በመንግስት ወጪ የተትረፈረፈ ህይወት ከእንግዲህ ልንመራ አንችልም” ሲል ተደምጧል፡፡ “የናይጄሪያ ህዝብ ይኼንን የደመወዝ አከፋፈል በአንድ ድምፅ ማውገዝ ይኖርበታል” ብሏል፡፡
በ2013 (እ.ኤ.አ) የአንድ በዝቅተኛ እርከን ላይ የሚገኝ ሴናተር (ህግ አውጪ) ዓመታዊ ገቢ 13,000 ዶላር ነበር። ግን በዚህ ደመወዙ ላይ ለመኖሪያ ቤት፣ ለቤት ቁሳቁስ እና መሰል ጥቅማጥቅሞች ከሚፈቀድለት ተጨማሪ ገቢ ጋር ተዳምሮ ወደ 115,000 ዶላር በዓመት እንደሚያገኝ የናይጄሪያ ጋዜጦች ጽፈዋል፡፡  
ከ2013 በኋላ ተጨማሪ ጥቅማ ጥቅሞች ተፈቅደውላቸዋል፡፡ ለምሳሌ፤ የውሎ አበል 930 ዶላር በእየለቱ፣ እንደዚሁም በየአራት ወሩ ደግሞ 38, 000 ዶላር --- በአመታዊው ደሞዝ ላይ ተጨማሪ መውሰድ ይችላሉ፡፡  
ከእነዚህ የህግ ባለሙያዎች የተጋነነ ደመወዝ ጋር የሀገሩ ዝቅተኛ የገቢ መጠን ሲነፃፀር በጣም ማስደንገጡ አልቀረም፡፡ የሀገሩ ዝቅተኛ ተከፋይ 18,000 ኒራ ወይንም 90 ዶላር በወር ነው የሚያገኘው፡፡
በናይጄሪያ ያለ ሴናተር በአሜሪካ በዝቅተኛ እርከን የሚከፈል ሴናተር ከሚያገኘው ገቢ ጋር ሲነፃፀር … በመካከላቸው ጥቂት ልዩነት ብቻ እንዳላቸው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እንደ ናይጄሪያ አይነት 75 በመቶ የመንግስት በጀት ከዘይት ቀረጥ ላይ በሚተማመን ሀገር፤ የዓለም የነዳጅ ገበያ ሲያሽቆለቁል… እንደ ቀድሞው ተንደላቀው ህይወታቸውን የሚመሩ ባለስልጣናት በአንፃራዊ ሁኔታ መለወጥ እንዳለበት የሚያመለክት ነው፡፡ 

Published in ከአለም ዙሪያ

15ኛው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ  የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ምዝገባው የፊታችን ሰኞ እንደሚጀመር ታወቀ፡፡ በሚቀጥለው ዓመት በህዳር ወር በሚካሄደው የጎዳና ላይ ሩጫ     ከሁለት ወር በፊት በማንቸስተር ከተማ የሩጫ ውድድሩን ያቆመው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴም የአገር ውስጥ የመጨረሻ ውድድሩን በማድረግ  ስንብት ያደርጋል፡፡ አትሌት ኃይሌ የመጀመርያው የተላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አሸናፊ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
700 ያህል የውጭ ሀገር ዜጎች በውድድሩ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ይጠበቃል ያለው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በውድድሩ ታሪክ ከፍተኛው የተሳትፎ ብዛት እንደሚሆን አመልክቷል፡፡  የመሮጫ ቲሸርት መሸጫ ዋጋውም ወደ 150 ብር ከፍ ያለ ሲሆን  የሜዳሊያና የዋንጫ እንዲሁም ሌሎች ወጪዎች በመጨመራቸው ነው ተብሏል፡፡
በውድደሩ ለመሳተፍ ከሚመዘገቡት ውስጥ የመጀመሪያ 1 ሺህ ተመዝጋቢዎች የመለማመጃ ቲሸርት በነጻ የሚያገኙ ሲሆን አቅም ለሌላቸው ሌሎች 1 ሺህ የሚሆኑ ሰዋችም በነጻ የመወዳዳሪያ ቲሸርት የሚሰጥ መሆኑን አስታውቀዋል። ምዝገባውም በ10 የተለያዩ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ይካሄዳል፡፡

በውጭ ካሉት  የተረጋጋ የለም

   የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከማርያኖ ባሬቶ በኋላ በአዲስ የለውጥ ምዕራፍ ውስጥ መግባቱን የተለያዩ ሁኔታዎች እያመለከቱ ናቸው፡፡ ከ2 ዓመት በፊት ዋልያዎቹ ለ31 ዓመታት ርቀውበት ወደነበረው የአፍሪካ ዋንጫ ተመልሰዋል፡፡ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕም ቻን  ላይ ለመካፈልም በቅተዋል፡፡ በወቅቱ በኢትዮጵያ እግር ኳስ አዲስ መነቃቃት ስለመፈጠሩ በስፋት ይገለፅ ነበር፡፡ ላለፈው 1 ዓመት ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጥሩ መነቃቃት ላይ አልነበረም፡፡ ዋልያዎቹ ተብለው እነዚያን ታላላቅ ታሪካዊ ስኬቶች ያስመዘገቡ ተጨዋቾች በእድሜያቸው መግፋት ከብሄራዊ ቡድን መውጣት ጀመሩ፡፡ ከአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በኋላ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ያደርጉበት ተብለው በመቁጠር ሃላፊነቱን ተረክበው የሰሩት ፖርቱጋላዊው ማርያኖ ባሬቶ ቡድኑን ብራዚል ድረስ ወስደው ቢያዘጋጁም ውጤት አልነበራቸውም፡፡ በቋንቋ ፣ በእቅድ ትግበራ እና በተያያዥ መሠረታዊ ተግባራት ማርያኖ ባሬቶ ከፌደሬሽኑ ጋር  ተቀናጅተው ለመስራት በመቸገራቸው ከኃላፊነት በገዛ ፍቃዳቸው ለቅቀዋል፡፡ ስልጣኑን ከተረከበ ከ1 ዓመት የተወሰኑ ወራት ያለፈው የእግር ፌደሬሽኑ ያነሰ ልምድ ስለነበረው  ዋልያዎቹን ያንገታገቱ አንዳንድ አስተዳዳራዊ እንቅፋቶችም ነበሩ፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች በብሄራዊ ቡድኑ ዙርያ ተስፋ መቁረጥ እንዲሰፍንም አድርገዋል፡፡
ባለፈው 1 ወር ግን ይሄው ተስፋ መቁረጥ ተቀይሮ ፤ በኢትዮጵያ እግር ኳስ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ እንደተከፈተ የሚያሳዩ ምልክቶች ብልጭ ድርግም እያሉ ናቸው፡፡ ፖርቱጋላዊው ማርያኖ ባሬቶ ሲሰናበቱ ኢትዮጵያዊው አሰልጣኝ ዮሓንስ ሳህሌ ሃላፊነቱን ተረክበው መስራት ጀምረዋል፡፡ ወደ ብሄራዊ ቡድኑ  አዳዲስ እና ወጣት ዋልያዎች እየተቀላቀሉ ናቸው፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑም ለብሄራዊ ቡድን ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት ልዩ ተግባራትን ፈፅሟል፡፡ በአመራሩ በኩል የተለያዩ አስተዳደራዊ እድገቶችም እየታዩ ነው፡፡ ከሁሉም ደግሞ ብሄራዊ ቡድኑ በሁለት ተከፍሎ በገባባቸው ሁለት የማጣርያ ውድድሮች በሜዳው ያደረጋቸውን ሁለት ጨዋታዎች አሸንፎ በውጤት አቅጣጫ ላይ መገኘቱ ይጠቀሳል፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ እና በአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ሁለት ውድድሮች ዋልያዎቹ ከየትኛውም የምስራቅ አፍሪካ ቡድን የተሻለ ውጤት አስመዝግበዋል፡፡ በእግር ኳስ ደረጃቸውም ለውጥ እያሳዩ ናቸው፡፡ ሌላው አስደናቂው የለውጥ ምእራፍ ደግሞ ሁለቱን የብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎች ያስተናገደው የባህርዳር ስታድዬምና የከተማው ነዋሪዎች ናቸው፡፡ ለበርካታ ዓመታት የብሄራዊ ቡድኑ ሜዳ  አዲስ አበባ ስታድዬም እንደነበር ይታወቃል፡፡ አዲስ አበባ ስታድዬም በቅርብ ጊዜ የዋልያዎቹን ጨዋታዎች የማስተናገድ እድሉ ከእንግዲህ የተመናመነ መስሏል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሊገነባ የታሰበው ልዩ እና ዘመናዊ ስታድዬም ወደ ተግባራዊ ስራ እንዲገባ ከፍተኛ መነቃቃት ፈጥሯል - የባህርዳር ስታድዬም፡፡ በኦፌሴላዊ ደረጃ 60 ሺህ ተመልካች ያስተናግዳል የሚባለው ባህርዳር ስታድዬም በሁለቱ የአፍሪካ ዋንጫ እና የቻን ውድድር ማጣርያዎች በድምሩ ከ180ሺ ተመልካች በላይ  አስተናግዷል። የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ከሁለቱ ጨዋታዎች እስከ 2.5 ሚሊዮን ብር ገቢ ሊያደርግም ችሏል፡፡ በሁለቱ ጨዋታዎች ስታድዬም የገባው ተመልካች ብዛት እና የገቢው ከፍተኛነት በአገሪቱ እግር ኳስ ታሪክ ክብረወሰኖች ሆነው የተመዘገቡ ናቸው፡፡
የዋልያዎቹ ስብስብ ብዙ ለውጦች እየታዩበት ነው፡፡ በበረኛ ቦታ  ከጀማል ጣሰው እና ከሲሳይ ባጫ በኋላ ተተኪ እንደማይኖር ቢሰጋም በጨዋታ ላይ ፍፁም ቅጣት ምት ያዳነው  ታሪክ ጌትነት ብቅ ብሏል፡፡ በተከላካይ መስመር ከእነ ደጉ ደበበ፣ አበባው ቡጣቆ እና አሉላ ግርማ በኋላ እነ ሳላዲን በርጌቾ ሃላፊነቱን ተረክበው በብቃት እየተሰለፉ ናቸው፡፡ ከአዳነ ግርማ፤ ከብርሃኑ ቦጋለ በኋላ ደግሞ እነ ጋቶች ፓኖም እና ሁለቱ አስቻለዎች፣ አስቻለው ጌትነት እና አስቻለው ቱጂ አማካይ ስፍራውን በመቆጣጠር ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ አድርገዋል፡፡ በአጥቂ መስመር እነ ሳላዲን ሰኢድ፤ ሽመልስ በቀለ ፣ ጌታነህ ከበደ እና ኡመድ ኡክሪ ባይኖሩም እንኳን በቢኒያም አሰፋ፤ አስቻለው ግርማና ራምኬሎ ተስፋ ማሳደር ተችሏል፡፡ ከቀድሞዎቹ የዋልያዎች ስብስብ ደግሞ አሁንም ድረስ ግልጋሎት በመስጠታቸው ስዩም ተስፋዬና በሃይሉ አሰፋ ዋና ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ሳላዲን በአልጄርያ ክለብ ይፈለጋል
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አምበል የሆነው ሳላዲን ሰኢድ ከሁለት ሳምንት በፊት በባህርዳር ስታድዬም በአፍሪካ ዋንጫ የመጀመርያ ጨዋታ የተሰለፈው ለረጅም ጊዜ ከቆየበት ጉዳት በማገገም ነው፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያው ባህርዳር ላይ ኢትዮጵያ ሌሶቶን 2ለ1 ስታሸንፍ ቡድኑን በአምበልነት የመራው ሳላዲን ለብሄራዊ ቡድኑ 20 ጨዋታዎች በማድረግ የጎሎቹን ብዛት 11 ማድረሱ ነበር፡፡ በዚሁ ሰሞን ታድያ ሳላሃዲን ሰኢድ የግብፁን ክለብ አልሃሊ በመልቀቅ የአልጄርያውን ኤምሲ አልጀርስ ሊቀላቀል እንደሆነ ተዘግቦ ነበር፡፡ ኤምሲ አልጀርስ ሳላዲንን ለመውሰድ ያለውን ፍላጎት በተደጋጋሚ እንደሚገልፅ የሚያነሱ ዘገባዎች፤ ሳላ ከግብፅ በመውጣት ወደ ምርጡ የአልጄርያ ሊግ በመግባት ልምዱን ለማስፋት እንደሚያስብ መግለፃቸው የዝውውሩን ወሬ አሟሙቆታል፡፡ የአልጄርያው ክለብ ኤምሲ አልጀርስ ፕሬዝዳንት ሳላዲን ከአልሃሊ ጋር ያለው ኮንትራትን አፍርሶ ወደ አልጄርያ በማቅናት  በዝውውሩ ላይ ስምምነት ለመፍፀም ፈቃደኛ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡  ሳላዲን ሰኢድ ሰሞኑን በጉዳዩ ላይ ለሱፕር ስፖርት በሰጠው ምላሽ ከየትኛውም ክለብ ጋር ምንም አይነት ድርድር እንዳላደረገ፤ በአልሃሊ ለሚቀጥሉት 2 የውድድር ዘመናት እየተጫወተ ለመቀጠል ኮንትራት እንዳለው እና የዝውውር ወሬው ምንጭ ከየት እንደተገኘ የማውቀው ነገር የለም ብሏል፡፡
ሳላዲን ከአልሃሊ ክለብ ጋር በቆየባቸው 15 ወራት በድምሩ 17 ጨዋታዎች አድርጎ ያገባው 4 ጎሎች ብቻ ነው፡፡ በአልሃሊ በቆየበት ወቅት አብዛኛውን ጊዜ በጉዳት ሳቢያ ሙሉ ብቃቱን ማሳየት አልቸለም፡፡ ከክለቡ ጋር የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ማግኘት ብቻ ሆኖለታል፡፡ የ26 ዓመቱ ሳላዲን ሰኢድ በአልአሃሊ የተፈራረመው ኮንትራት እስከ 2019 እኤአ እንደሚቆይ የተለያዩ መረጃዎች ይገልፃሉ፡፡ እሱ ደግሞ ቢያንስ ሁለት የውድድር ዘመን እንደሚቀጥል እየተናገረ ነው፡፡ የተጨዋቹ ኤጀንት አሊያን ዱጋንጋሎ  በጉዳዩ ዙርያ ምንም የገለፀው ነገር የለም፡፡ በትራንስፈርማርኬት የተመዘገበው መረጃ የተጨዋቹ የዝውውር ዋጋ 400ሺ ዩሮ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ ሳላዲን ሰኢድ ቅዱስ ጊዮርጊስን በመልቀቅ የመጀመርያ ዝውውር ለማድረግ የሞከረው ወደ ሰርቢያው ክለብ ፓርቴዝያን ቤልግሬድ በ2010 እኤአ ላይ ነበር፡፡ ይህ ዝውውር የተሳካ ስላልነበር ወደ አገሩ ተመለሰ፡፡ ከዚያም በ2011 እኤአ መግቢያ በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ በመጫወት የግብፁን ክለብ ዋዲ ደጋላ ሲቀላቀል የዝውውሩ ዋጋ በ185ሺ ዩሮ ነበረ፡፡ በግብፁ ዋዲ ደጋላ ቢያንስ ለሁለት ዓመት ተጫውቶ በመቀጠል የተዛወረው በውሰት ውል ወደ ስዊድኑ ክለብ ሊሬስ ኤስኬ ሲሆን የዝውውር ዋጋው ወደ 200ሺ ዩሮ አድጓል፡፡ ከስድስት ወራት የውሰት ቆይታ በኋላ በ2013 እኤአ ወደ ዋናው ክለብ ዋዲ ደጋላ ሲመለስ የዝውውር ዋጋው በከፍተኛ ደረጃ እድገት አሳይቶ 350ሺ ዩሮ ገብቷል። በዋዲ ደጋላ የሚቆይበት ኮንትራት በ2013 መገባደኛ ላይ እንዳበቃ ተጨዋቹን ለማዛወር በተለይ የደቡብ አፍሪካ ክለቦች ከፍተኛ ጥረት ካደረጉ በኋላ ያስፈረመው ሌላው የግብፁ ክለብ አል አሃሊ ሆኗል፡፡ ሳላዲን ሰኢድ አልሃሊ ከገባ በኋላ የዝውውር ዋጋው 400ሺ ዩሮ ደርሷል፡፡
ጌታነህ ከደቡብ አፍሪካ ሊመለስ ይችላል
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የአጥቂ መስመር ተጫዋች ጌታነህ ከበደ በደቡብ አፍሪካው ክለብ ቢድቭስት ዊትስ ጋር የመቀጠሉ ነገር አጠራጣሪ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ጌታነህ ከበደ ከ2 አመት በፊት ቢድቪስት ክለብን የተቀላቀለው በ175ሺ ዩሮ የዝውውር ሂሳብ ነው፡፡  በብሉምፎንቴይኑ ክለብ ለተጨማሪ አንድ አመት የሚያቆየው ኮንትራት ያለው ቢሆንም  ክለቡ ተጫዋቹን ለማቆየት ፍላጎት እንደሌለው መነገሩ ወደ ኢትዮጵያ ሊመለስ እንደሚችል  አስገምቷል፡፡ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 20 ጨዋታዎችን አድርጎ 9 ጎሎችን ያስመዘገበው ጌታነህ፤ ቢድቨስት ዊትስን ከተቀላቀለ በኋላም ባደረጋቸው የመጀመሪያዎቹ 5 ጨዋታዎች 4 ግቦችን በማስቆጠር  ጥሩ አጀማመር ነበረው፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ባጋጠመው ጉዳት ምክንያት መዝለቅ አልቻለም። በአሁኑ የውድድር ዘመን ጌታነህ ለዊትስ 10 ጨዋታዎችን ያደረገው በግማሹ የቋሚ ተሰላፊነትን ዕድል አግኝቶ ሲሆን 3 ግቦችን ብቻ አስቆጥሯል።
ቢድቨስት ዊትስ ለቀጣዩ የውድድር ዘመን የውጪ ዜጋ ያላቸው ተጫዋቾች ኮታ በ5 ብቻ ስለተወሰነበት፤ ከጌታነህ ከበደ በተጨማሪ የዛምቢያዊውን ክሪስቶፈር ካቶንጎ እንደሚያሰናብት ተገምቷል።
አልኢትሃድ ያልሆነው ኡመድ ኡክሪ
ኡመድ ኡክሪ ከ10 ወራት በፊት ነበር ቅዱስ ጊዮርጊስን በመልቀቅ የግብፁን ክለብ አልኢትሃድ አሌክሳንድርያ የተቀላቀለው፡፡ ባለፈው የፕሪሚዬር ሊግ ውድድር ለቅዱስ ጊዮርጊስ እየተጫወተ ኮከብ ግብ አግቢ እና ኮከብ ተጨዋች የነበረው ኡመድ ኡክሪ ወደ ግብፁ አልኢትሃድ ሲገባ ዓመት ለዝውውሩ የተከፈለበት ዋጋው 500ሺ ዶላር እንደነበር ተገልፆ ነበር፡፡
ኡመድ በዚሁ ክለብ በነበረው ቆይታ ግን ደስተኛ አልነበረም፡፡ በቅርብ ጊዜ በክለቡ እየሰራ ቢሆንም ለ3 ወራት ደሞዝ ሳይከፈለው በመቆየቱ ፤ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታ በኋላ ያለበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ይፋ አድርጓል፡፡ የአልኢትሃድ ኮንትራቱን በማፍረስ  ወደ ቀድሞ ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለመመለስ ወስኗል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይም ለፊፋ ክስ አቅርቦ ነበር። ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር አስፈላጊውን የዝውውር ሰርተፊኬት በማፅደቅ ወደ ጊዮርጊስ እንዲመለስ የሚችልበትን መልቀቂያ ፈቅዶለታል፡፡ ከሰኔ 30 በኋላ ግን ይህን ፈቃዱን ማደስ ይጠበቅበታል፡፡ ለ6 ወራት በግብፁ ክልብ አልኢትሃድ ውስጥ ተቸግሮ የነበረው ኡመድ አሁን ወደ ጊዮርጊስ ተመልሶ መጫወት ከጀመረ በኋላ በተለይ የቻን ቡድንን እንዲያጠናክር እና መጫወት እንዲችል በፌደሬሽኑ በኩል ተፈልጓል፡፡
ሽመልስ ወደ ሌላ የግብፅ ክለብ
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ምርጥ አማካይ የሆነው ሽመልስ በቀለ በግብፁ ክለብ ፔትሮጄት መጫወት ከጀመረ ዓመት ሊሞላው ነው፡፡ ከ2013 እኤአ ጀምሮ ከአገር ወጥቶ መጫወት የጀመረው ሽመልስ እስከ 2014 መግቢያ በሊቢያው ክለብ ኢትሃድ ትሪፖሊ ሲጫወት ነበር፡፡ 2014 እኤአ ከገባ በኋላ ደግሞ ለሱዳኑ ክለብ አልሜሪክ በመፈረም ለተወሰኑ ወራት በዚያው ሲጫወት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ግብፁ ክለብ ፔትሮጄት በ150ሺ ዩሮ የዝውውር ዋጋ በመግባት አስደናቂ ብቃት እያሳየ ነው፡፡ ሽመልስ በቀለ በግብፁ ክለብ ፔትሮጄት እስከመቼ እንደሚቆይ በይፋ የተገለፀ ነገር የለም ባይኖርም ሌሎች የአገሪቱ ክለቦች ለተጨዋቹ ያላቸውን ፍላጎት እያሳዩ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊው አማካይ ሽመልስ በቀለ ባለፈው ሰሞን  የግብፅ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ክለቡ ፔትሮጀት በአል አሃሊ 2ለ1 በተሸነፈበት ጨዋታ  በስምንተኛው ደቂቃ ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡  በዚህች ጎል ሽመልስ በፔትሮጄት ክለብ ቆይታው ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት ስምንት አድርሶታል። በአጠቃላይ በግብፅ ፕሪምየር ሊግ በአጭር ጊዜ ቆይታው በሚያሳየው ብቃት ሽመልስ  በቀለ በሌሎች ተፈልጓል፡፡ ኢ.ኤን.ፒ.ፒ.አይ የተባለው ክለብ እንደሚፈልገው በይፋ በመግለፅ ይጠቀሳል፡፡
የቻን መልስ ጨዋታ ከኬንያ ጋር
ከሳምንት በኋላ በቻን የመጀመርያ ማጣርያ የመልስ  ጨዋታ  ኬንያ እና ኢትዮጵያ ናይሮቢ ላይ ይገናኛሉ፡፡ የኬንያው አሰልጣኝ ቦቢ ዊልያምሰን ቡድናቸው በሜዳው በሚያደርገው የመልስ ጨዋታ ላይ በደጋፊያቸው  በመታገዝ ጫና ፈጥረው በመጫወት ውጤቱን እንደሚቀለብሱ ይናገራሉ፡፡ ዊልያምሰን ለሱፕር ስፖርት በሰጡት አስተያየት ተስፋ የምናደርገው በናይሮቢ ስታድዬም ከፍተኛ ድጋፍ ማግኘታችን ነው ብለው ሲናገሩ፤ ምሳሌ ያደረጉት በባህርዳር ስታድዬም የኢትዮጵያ ደጋፊዎች የተጫወቱን ሚና ነው፡፡  የኬንያ ቡድን በሜዳው በሚያደርገው የመልስ ጨዋታ ኢትዮጵያን ጥሎ ለማለፍ ቢያንስ 3ለ0 ማሸነፍ ይጠበቅበታል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 1ለ0 መሸነፍ እና በማንኛውም ውጤት አቻ መለያየት ያሳልፈዋል። ለ4ኛው ቻን ለማለፍ በመጨረሻው የማጣርያ ምእራፍ  የኢትዮጵያ እና ኬንያ አሻናፊ ቡድን ተጋጣሚ የሚለየው ከጅቡቲ እና ከብሩንዲ ጥሎ በሚያልፈው ቡድን ነው፡፡ በመጀመርያ ጨዋታ ብሩንዲ ከሜዳዋ ውጭ 2ለ1 በማሸነፏ በመልሱ ጨዋታ በሜዳዋ ላይ ጅቡቲን ጥሎ የማለፍ እድሏን አብዝቶታል። በአፍሪካ ዋንጫው የምድብ ማጣርያ የኢትዮጵያ ተቀናቃኝ ከሆኑት ሶስት ቡድኖች ዝቅትኛ ግምት የተሰጣቸው ሲሸልስ ከሜዳዋ ውጭ በሞዛምቢክ 5ለ1 በመረታት እንዲሁም ሌሴቶ በሜዳዋ ከቦትስዋና ጋር 0ለ0 በመለያየት በቻን የማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታቸው አልተሳካላቸውም፡፡ አልጄርያ በቅጣት ማጣርያውን አትካፈልም፡፡

“The power of Negative Thinking” የተሰኘው የስነልቦና መጽሐፍ “የአሉታዊ አስተሳሰብ ልዩ ሃይል” በሚል ርዕስ በአሸናፊ ሰብስቤና በእሩቅነህ አደመ ወደ አማርኛ ተተርጉሞ ለገበያ ቀረበ፡፡
“ለህይወት ወይም ለመኖር ከውስጥህም ሆነ ከውጭ ወይም ለሁለቱም ምንም ዓይነት ዋስትና ሳትሰጥ ስትቀር መኖር ወይም ህይወት በራሱ በመከራ፣ በስቃይ፣ በሀዘን፣ በፍርሃትና ባልተጠበቁ ክስተቶች የተሞላች ትሆናለች” ይላል - መፅሃፉ። በ183 ገፆች የተቀነበበው ይሄው መጽሐፍ፤ በ11 ምዕራፎች ተከፋፍሏል፡፡ “የአሉታዊ አስተሳሰብ ልዩ ሃይል” በ50 ብር ከ65 እየተሸጠ ነው፡፡

 የኢትዮጵያ ሴት ደራሲያን ማህበር ከኢትዮጵያ ባህል ማዕከል ጋር በመተባበር ባህላዊ ህክምናንና አገር በቀል ዕውቀቶችን በተመለከተ የተለያዩ መፃሕፍት የፃፉትን ደራሲ በቀለች ቶላን የሚዘክር ፕሮግራም ባለፈው ረቡዕ በኢትዮጵያ ባህል ማዕከል አዳራሽ ያካሄደ ሲሆን በስራዎቻቸው ላይ የመነሻ ጽሑፍ ቀርቦም ውይይት ተካሂዷል፡፡
ደራሲ በቀለች ቶላ የሴት ደራሲያን ማህበር አባል እንደሆኑ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ሴት ደራሲያን ማህበር ከኢትዮጵያባህል ማዕከል ጋር በመተባበር ባህላዊ ህክምናንና አገርበቀል ዕውቀቶችን በተመለከተ የተለያዩ መፃሕፍትየፃፉትን ደራሲ በቀለች ቶላን የሚዘክር ፕሮግራምባለፈው ረቡዕ በኢትዮጵያ ባህል ማዕከል አዳራሽ ያካሄደ ሲሆን በስራዎቻቸው ላይ የመነሻ ጽሑፍ ቀርቦም ውይይት ተካሂዷል፡፡ደራሲ በቀለች ቶላ የሴት ደራሲያን ማህበር አባል
እንደሆኑ ታውቋል፡፡

Saturday, 27 June 2015 09:41

የኪነት ጥግ

• ቤተሰባችን በጣም ድሃ ስለነበር እኔን
የወለደችኝ ጐረቤታችን ናት፡፡
ሊ ትሬቪኖ
• የአይጦች ውድድር ችግሩ…ብታሸንፍ እንኳ
ያው አይጥ ነህ፡፡
ሊሊቶምሊን
• በውሃ ላይ ብራመድ ኖሮ፣ ሰዎች መዋኘት
አይችልም ይሉኝ ነበር፡፡
ጆን ተርነር
• ስለእኔ የማነበውን አምኜ ብቀበል ኖሮ እኔም
ደፋርነቴን እጠላው ነበር፡፡
ዛሳ ዛሳ ጋቦር
• እውነቱ ምንድነው…በ30 ዓመታት ውስጥ
30 ፊልሞችን ሰርቻለሁ፡፡ ለ30 ዓመታትም
ሌሎችም ተጨማሪ ፊልሞችን ባለመስራቴ
ስተች ኖሬአለሁ፡፡
ደስቲን ሆፍማን
• በውብ ነገሮች መከበብ በመፈለጌ ሰዎች
“እማ ዝራው ናት!” ይሉኛል፡፡ ግን እስቲ
ንገሩኝ ማነው በዝባዝንኬ (ነገሮች) መከበብ
የሚፈልገው?
ኢሜልዳ ማርቆስ
• የዜና ዕረፍቴ ዘገባ በእጅጉ ተጋንኗል፡፡
ማርክ ትዌይን (ዜና ዕረፍቱ በጋዜጣ መዘገቡን
ሲሰማ የመለሰው
• ሥራዬን ስለወደዳችሁት የእናንተ ዕዳ አለብኝ
ማለት አይደለም፡፡
ቦብ ዳይላን
• ሆሊውድ ለመሳሳም 50ሺ ዶላር፣ ለነፍስህ
50 ሳንቲም የሚከፍሉህ ሥፍራ ነው፡፡
ማርሊን ሞንሮ
• በትያትር ዓለም የሚቆጨኝ ፊት ለፊት
ተቀምጬ ራሴን ለመመልከት አለመቻሌ
ብቻ ነው፡፡
ጆን ባሪሞር
• አንዳንዴ በጣም ጣፋጭ ከመሆኔ የተነሳ
እኔም ራሴ ሁኔታውን መቆጣጠር ይሳነኛል፡፡
ጁሊ አንድሪውስ
• ወሲብ እግዚአብሔር በሰዎች ላይ የፈጠረው
ቀልድ ነው፡፡
ቤቲ ዴቪስ
• በመድረክ ላይ ከ25ሺ ሰዎች ጋር ፍቅር
እሰራለሁ፡፡ ከዚያም ብቻዬን ወደ ቤቴ
እሄዳለሁ፡፡
ጃኒስ ጆፕሊን
• በኦሎምፒክ ሁለተኛ መውጣት ብር
ያስገኝልሃል፡፡ በፖለቲካ ሁለተኛ መውጣት
መረሳትን ያጐናፅፍሃል፡፡
ሪቻርድ ኤ.ም ኒክሰን

Published in ጥበብ
Page 1 of 16