ከሁለት ወር በፊት መጋቢት ላይ ነበር “የተቆለፈበት ቁልፍ” የተሰኘው የዶ/ር ምህረት ደበበ ገ/ጻዲቅ ረዥም ልቦለድ መጽሐፍ አንባቢያን እጅ የገባው፡፡ መቼቱን በአገር ውስጥና በባህር ማዶ ያደረገው ልቦለድ፤ በ439 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን ደራሲው የአእምሮ ህክምና ስፔሺያሊስትነት ደረጃ የደረሱት ትምህርታቸውን በአገር ውስጥ በባሕር ማዶ በመከታተል ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአሜሪካንና በኢትዮጵያ እየተመላለሱ በሙያቸዉ እያገለገሉ እንደሆነ በመጽሐፋቸው ላይ ተጠቁሟል፡፡ ዶ/ር ምህረት፤ ከሐኪምነታቸዉ በተጨማሪ በአስተሳሰብና በአእምሮ ለውጥ ዙሪያ እያስተማሩና ጥናት እየሰሩ እንደሆነ የሚጠቅሰው መረጃው፤ ህብረተሰባዊ ለውጥ ከግለሰቦች የአስተሳሰብ ለውጥ እንደሚጀምር የሚያምኑ መሆናቸውን ይገልፃል፡፡ ልቦለድ መጽሐፋቸውም ይሄንኑ የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ ልቦለዱ በፍቅርና ጥላቻ፣ በደግነትና ክፋት፣ በግልጽነትና መሰሪነት፣ በሀብትና ድህነት፣ በትጋትና ስንፍና፣ በእውቀትና መሃይምነት ዙሪያ የሚያጠነጥን ሲሆን በጠንካራ የልብ ሰቀላ የአንባቢውን ስሜት ይዞ ከመነሻ እስከ መድረሻ ይዘልቃል፡፡

ተደራሲው ስለ ራሱም ሆነ ስለ ሌሎች ሰዎች ማንነት እንዲጠይቅ የሚያነሳሳም ነው - ታሪኩ፡፡ ሲኦል ደርሳ የተመለሰችው ሶፍያ አባቷ አፍሪካ አሜሪካዊ ሲሆን እናቷ ግሪካዊ ናት፡፡ ወላጆቿ ተዋውቀው ጋብቻ የመሰረቱት ደግሞ ጀርመን ነው፡፡ ሶፍያ ከተወለደች በኋላ ለጥንዶቹ ትዳር መፍረስ ምክንያት የሆነው፤ አባቷ ቀደም ብሎ ከመሰረተው ትዳር ሦስት ልጆችን መውለዱ ዘግይቶ መሰማቱ ነበር፡፡ ትዳራቸው ሲፈርስ ሶፊያ ከእናቷ ጋር ወደ አያቶቿ አገር ግሪክ ሄደች፡፡ በወቅቱ የአራት ዓመት ልጅ ነበረች፡፡ እናቷ በግሪክ ሌላ ትዳር ስትመሰርት የሶፊያ መኖሪያ አያቶቿ ዘንድ ሆነ፡፡ ከአያቶቿ ጋር የሚኖረው የእናቷ ወንድም ጥሩ ተንከባካቢ ሰው ሆነላት፡፡ የ11 ዓመት ልጅ ሳለች ግን አስገድዶ ደፈራት፡፡ አጎቷ ክብረ ንጽሕናዋን በመድፈር ብቻ አላበቃም፣ እያስፈራራት ለአራት ተከታታይ ዓመታት ተመሳሳይ ድርጊት ፈፀመባት። የማንነቷ ቀውስ እያስጨነቃት፣ የሕይወትና ኑሮ ምንነት ግራ እያጋባት 15 ዓመት ላይ ስትደርስ አመፅ ጀመረች፡፡

አጎቷ ያደረሰባትን በደል ተናገረች፡፡ በፍቺ የተለያዩትን እናትና አባቷን ጨምሮ የእንጀራ አባቷም ከሷ ጐን ቆሙ፡፡ ከዚያ በኋላ አባቷ ዘንድ አሜሪካ ሄደች፡፡ ልጁ ለደረሰባት እንግልትና በደል እራሱን ተጠያቂ ያደረገው አባት፤ ብዙ የተመቻቹ ነገሮች ቢያቀርብላትም ሶፍያ ከገባችበት የማንነት ቀውስ መውጣት አልቻለችም፡፡ ያለ ምርጫ ካገኘችው ወንድ ጋር ሁሉ መውጣት ጀመረች፡፡ ከአልኮል ብቻ ሳይሆን ከአደንዛዥ እፅ ተጠቃሚነቷ ማውጣት ፈተና ሆነ፡፡ በሶፊያ የዕለት ከእለት መጥፎ ድርጊት ስቃይ ውስጥ የገባው አባቷ፤ “በዚህ መልኩ ተሰቃይቼ ከምሞት አንቺ ግደይኝ” በማለት ሽጉጡን አቀባብሎ ይሰጣታል፡፡ “ወንዶች ስትባሉ ሁላችሁም ያው ናችሁ” ትለውና ጥላው ከቤት ትወጣለች፡፡ አባቷ ባቀባበለው ሽጉጥ እራሱን ያጠፋል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ሶፊያ ከገባችበት የሲኦል ዓለም ለመውጣት አንድ ብላ ጉዞ የጀመረችው። አባቷ ወደሚያውቃትና ወደሚወዳት ኢትዮጵያ በመምጣት በፌስቱላ ሆስፒታል በበጎ ፈቃድ መሥራት የጀመረችው 28ተኛ ዓመቷን ስትይዝ ነበር፡፡

አራት ጊዜ አርግዛ ውርጃ የፈፀመችው ሶፊያ፤ ዛሬ ሲያታግላት የምንመለከተው ማንነት፣ በልጅነት ዕድሜዋ የተፈፀመባት በደል ውጤት መሆኑን እናስተውላለን፡፡ የወላጅ አጥፊ ዳናይት የ10ኛ ክፍል ተማሪና የ15 ዓመት ጉብል ናት፡፡ የ13 ዓመት ልጅ እያለች በአንድ ፓርቲ ላይ ሁለት ወንድ ጓደኞቿ ብዙ አልኮል አጠጥተው ክብረ ንጽህናዋን ይገሱታል፡፡ ገና በ15 ዓመቷ ከብዙ ወንዶች ጋር ወጥታለች፡፡ አልኮል ትጠጣለች። አደንዛዥ ዕዳ ትጠቀማለች፡፡ እንዲያም ሆኖ ቤተክርስቲያን አዘውታሪ ናት፡፡ የትም ቦታ ግን የምትፈልገውን ፍቅር አታገኝም፡፡ የወላጆቿን ትኩረት ለመሳብ በራሷ ላይ በተደጋጋሚ የጥፋት ተግባር የምትፈፅመውም ለዚህ ነው፡፡ ዳናይት በውፍረቷ ምክንያት የትምህርት ቤት ጓደኞቿ እያበሸቁ ስላስቸገሯት ለመክሳት የማታደርገው ጥረት የለም፡፡ የበላችው ምግብ ሆዷ ውስጥ እንዳይቆይ ጣቶቿን ወደ ጉሮሮዋ ትሰዳለች፡፡ ደም ስሯን በመብጣት ደሟ እንዲፈስ ታደርጋለች፡፡ የማንነቷ ቀውሷ አይሎ የወሰደችው አንድ መድኃኒት ለሞት ሊዳርጋት ሲል እናቷ የስነ ልቦና ባለሙያ (ሐኪም) አመጣችላት፡፡

በፍቅር የሚያይ፣ ጆሮ ሰጥቶ የሚያዳምጥ ባለሙያ ብታገኝም ወላጅ እናቷን ከማመስገን ይልቅ ስትነቅፋት እንመለከታለን፡፡ “…በቃ እኔ የሷ መሞከሪያ አይጥ የሆንኩ ነው የሚመስለኝ፡፡ የምለብሰውም እንኳ እሷ የፈለገችውን ነው፡፡ እሷ እኮ ናት እኔ ውስጥ ለመኖር የምትጥረው። “አባቴም ስለሚፈራት ራሱን ለማዳን ይሁን አይገባኝም ምንም አይረዳኝም፡፡ እናትሽን ጠይቄ ነው የሚለው፡፡ ለብቻዬ ደግሞ አልችላትም፡፡ እሷ ናት የሁላችንንም ዓለም የምታሽከረክረው…” ለልጆቹ መልካሙን ሁሉ ብትመኝም በልጆቿ የምትጠላው ወ/ሮ አብረኸት፤ በልጅነቷ ያሳለፈችው ስቃይና መከራ፣ የዛሬ መርሆዋንና ፍላጐቷን አጣርሶባታል፡፡ ከወላጅ እናቷና ከእንጀራ አባቷ የሚደርስባት መከራ የበዛባት አብረኸት፤ የ17 ዓመት ጉብል ሳለች ነው ቤተሰቡን ጥላ ከቤት የወጣችው። ከወንዶች ጋር መውጣት የጀመረችውም በልጅነት ዕድሜዋ ነበር፡፡ እንዲያም ሆኖ ያገኘችውን እየሰራች ትምህርቷን መማር በመቻሏ በመንግሥት ድርጅት ውስጥ ሥራ ተቀጠረች፡፡

ከመጀመሪያ ትዳሯም ሁለት ልጆች ወልዳ ዩኒቨርስቲ ገብተዋል፡፡ በኃይለኝነቷ ምክንያት ከመጀመሪያ ትዳሯ ከተፋታች በኋላ ከዳናይት አባት ጋር ጋብቻ ትመሰርታለች፡፡ ከዚያም የመንግስት ሥራዋን በመተው የግል ንግድ አቋቁማ መምራት ትጀምራለች፡፡ በባሏም፣ በቤቷም በልጆቿም ላይ የበላይ ለመሆን የምትፈልገው በሌላ ሳይሆን በልጅነት ህይወቷ በደረሰባት አስከፊ ችግር የተነሳ ነው፡፡ ያለፈችበት ሕይወት “የማታውቀው ችግር በውስጧ ተክሏል” እናም ልጆች ለማሳደግ እየጣረች ልጆቿ ወደ ጥፋት እንዲያመሩ ምክንያት ስትሆን ትታያለች፡፡ “የተቆለፈበት ቁልፍ” በሚል ርዕስ በዶ/ር ምህረት ደበበ ገ/ዳዲቅ ተጽፎ ለአንባቢያን የቀረበው ረጅም ልቦለድ፤ የዛሬ ማንነት ትላንት ላይ መታተሙን፤ የዛሬውም ነገ ላይ እንደሚታይ የሚያመለክቱ፤ ተያያዥ ታሪኮች ቀርቦበታል፡፡ ታሪኩ የሕብረተሰብ መሠረት የሆነውን ትዳርም በልዩ ትኩረት ይዳስሳል። ትዳርን በተመለከተ የቀረበውን የሰላ ሂስ ቀንጭቤ በማቅረብ የመፅሃፍ ቅኝቴን እቋጫለሁ።

“ከጐዳና ተዳዳሪው እስከ ሚሊየነሩ፤ ከገበሬው እስከ ሳይንቲስቱ፣ ከየኔቢጤው እስከ አገር መሪው አብዛኛው ያገባል ይወልዳል፡፡ ከዘጠና እጁ በላይ ግን ለትዳርም ሆነ ለወላጅነት ማይም ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በምድር ላይ ካሉ ሥራዎች እጅግ አስቸጋሪ ለሆነው ሥራ እንዴት ይሆን ሰው ሁሉ እንዲህ ደፋርና ግድየለሽ ሊሆን የቻለው? በዚህ በማይማን ኅብረት በተቋቋመ ተቋም ውስጥ እንደሚወለዱ ልጆች ምን አሳዛኝ ፍጥረት ሊኖር ይችላል? እንደ ትዳር የዕድሜያችንንና የሕይወታችንን ብዙ ድርሻና ዘመን የሚወስድ ምን አለ? ሰውን የሚያህል ነገር ወልዶ እንደ ማሳደግስ ምን ከባድ ኃላፊነት አለ? ታዲያ የትዳርና የወላጅነት ማይማን የተመሳቀለ ኑሮ ኖረው ወደዚህ ዓለም ያመጡትንም ሰው ሕይወትና አስተሳሰብ ቢያመሳቅሉ ይገርማል? አስተሳሰብና አእምሮም በከፍተኛ ደረጃ የሚቀረጸውና የሚወሰነው ትምህርት ቤት ሳይሆን በልጅነት ዕድሜ በቤተሰብ ውስጥ ነው፡፡”

Published in ጥበብ

በዘመናችን ህይወት የሚላወስባቸው፣ እንደመብረቅ የሚያስደነግጥ መልእክትና ውበት ያላቸው ጥቂት ገጣሚያን ተወልደው ፣በአበባ ሳቅ፣በእምባ ጉንጉን አስደምመውናል፡፡በተዘለዘለ የእምባ ቋንጣ አስለቅሰው፣ትኩስ የውበት ወንዞችን በልባችን መልካዎች አፍስሰዋል፡፡ ምንም እንኳ በገዛ ዘመናቸው ኖረው በኛም ዘመን የሚኖሩ ገጣሚያን መጥረቢያ የማይነካቸው የአድባር ዛፎች ተደርገው፣ በአዲሱ ትውልድ ላይ በር ቢዘጋም፣ወደኋላ ሄደን ስናይ ግን አንዳንዶቹ ብዙ ሊገረዙ የሚገባቸው ጭራሮዎች ያንጨፈረሩ፣ከዛሬዎቹ የሚያንሱት ብዙ ስራዎቻቸው በፍርሃት ገደል ውስጥ እንዲደበቁ ተደርጓል፡ዛሬ በሃሳብ ልቀት የትኛውም ያለፈው ዘመን ገጣሚን የሚያስንቁ እጅግ ጥቂት ገጣሚያን አሉን፡፡ግን አንዱ በቋንቋ፣ሌላው በሃሳብ ይበላለጣል እንጂ ሰበብ ተጠቅሞ በዚሀ ዘመን ግጥም የለም የሚለው ጤናማነት የጎደለው በሽታ ነው፡፡

ምናልባትም የቀደሙት ገጣሚያን ግጥሞች በወጣትነታቸው ምን ይመስል እንደነበር ለማስታወስ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን የ50ኛ ዓመት የኮሌጅ ግጥሞች ማንበብ ጥሩ ነው፡፡እኔ ጆን ድራይደን እንደሚል “እያንዳንዱ ዘመን የየራሱ ጂኒየስ አለው ብዬ አምናለሁ፡፡ትናንት ገጣሚ ከነበረ፣ዛሬ የማይኖርበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ይሁንና ገጣሚያንን አናወዳድርም፤ምክንያቱም መልካቸውና ፍሰታቸው ስለሚለያይ፡፡እንግሊዛዊው ሳሙኤል ጆንሰን እንደሚለው አሌክሳንደር ፖፕ ከ ጆን ድራይደን የሚለይባቸው መልኮች አሉት፤ፖፕ ለህዝብ ቅርብ ልብ አለው፤ድራይደን ደግሞ የጠለቀ ምሁራዊነት ለድራይደን አለው፡፡ድራይደን የውስጡን ድምጽ ወጀብ ሲያዳምጥ፤ፖፕ ደግሞ ስለ አጻጻፍ ህግ ያምጣል፡፡ሁለቱም በየመንገዳቸው ሃሳቦችን እንደጧፍ ያቀጣጥላሉ፡፡ ሎረንስ ፔሬኒ እንደሚሉት የታወቁ ገጣሚያንን ማውራት ጣጣ የለውም፤ግን ኣዳዲሶቹን እንዲህ ናቸው ብሎ ማለት ያስቸግራል፡፡

ስለዚህ ደፋር እንድንሆንና ትክክለኛ ግምት እንዲኖረን ጥሩ አንባቢና መመዘኛ ያለን ልንሆን ይገባል፡፡አዲስ ሰው መቀበል ልበሙሉነት ለጎደላቸው በጣም ዳገት ነው-በተለይ ለፈሪዎች፡፡በምክንያት ለማያምኑ ባይተዋሮች፡፡ አሁን የዮሃንስን ግጥሞች ስናይ በዚህ ስሜት ሊሆን ይችላል፡፡እኔ ግን እንዳየሁት፤ደጋግሜም እንዳነበብኩት ዛሬ የጀመረውን ከቀጠለ ረጂም መንገድ በውበት ይጓዛል፡፡ቋንቋው፣ሃሳቡ፣ፍሰቱ ፣ዜማው ሁሉ ለግጥም የተመቸ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ግጥሞቹ ሲነበቡ የገጣሚው መልክና ዕድሜ ከሃሳቡ ጋር አልጣጣም ይልና እንዴት ይህን ነን ያህል አሰበ፡፡እንዴት ይህን ያህል የሚብከነከን ሆነ? ያሰኛል በርግጥ አንዳንድ ቦታ ወረድ ይላል፡፡ግን ያልወረደ ገጣሚ በምድር ላይ ማን አለ?…ያለቃላት በስሜት ብቻ ለሚያነብቡት በሳሎች ውስጥን ያንሾካሹካል የሚባለው ሼክስፒር እንኳ ትንንስ ቁልቁለቶች አሉበት፡፡

እኔ የማምነው ግን አክሱም ሃውልት አጠገብ ሄዶ ምን አይነት ጥበብ ነው እያሉ ረጂሙን በማየት ልካቸውን መለካት እንጂ ትንንሾቹን እያዩ እነዚህ ግን ቀሽሞች ናቸው በማለት አይደለም፡፡ሰማይ ነኩ ግጥሞች ያለው ገጣሚ ያንን ያህል ማሰቡ አቅሙን ያሳያል፡፡ልኩ ያ ነውና! የዮሃንስ ግጥሞች አጫጭርም ረጃጅምም ናቸው።… ረጃጅሞቹ የመንገዱ ርቀት አቅም አልነሳቸውም፤ ትንፋሽ ጠብቀው ፈስሰዋል፤ ሳይንገዳገዱ ደርሰዋል፡፡ቃላት አያጥረውም፤ሃሳቡ አይደርቅም፡፡ ብዙ የፍቅር ግጥሞቹ ረዘም ይላሉ፡፡ አንዳንዶቹም ስነ ቃላዊ ግንድ ያላቸው፣ህዝባዊ ግጥሞች ናቸው፡፡ገጣሚው ብዙ ጊዜ ይህንን ዘይቤ ይጠቀማል፡፡ለምሳሌ ግርማ ሞገሳሟ‹ቴ‹፣”የኔ ፍቅር ላንቺ”…(ትንሽ ቢረዝምም) ምናልባት ለሃገራዊ እሴቶች ጆሮና ልብ የመስጠት ዝንባሌ ይሆናል ብዬ ገምቻለሁ፡፡ለውረንስ ፔረኒ እንደሚከፍሉት ይህ ዘይቤ በ3 ይከፈላል፡፡ ….1. ታሪክ ጠቃሽ 2. ስነ-ጽሁፍ ጠቃሽ 3. መጽሃፍ ቅዱስ ጠቃሽ ናቸው፡፡ እስቲ “ጥምቀትና ሎሚ”ን እንይ፡-(ስለዚህ ስነ-ቃል የቃል ስነ ጽሁፍ ስለሆነ በዚህ ይካተታል፡፡) ከአሲድ፣ከዱላ፣ ከጥፊ፣ከቢላ፣ የተረፈ ገላ…. በሎሚ ታክሞ፣ጃንሜዳ ተበላ፤ ዳግም እስኪታመም፤-- …እስኪያገኘው ሌላ፡፡

                                 * * *

በ‹ስሟ ለማርያም ከደጅሽ ታድሜ፤ ቁራሽ ልማጸንሽ ፣ከበራፍሽ ቆሜ፤ ካ‹የሁሽ ጀምሮ፣… ፍቅርሽ ሰቅዞኛል፣ልብሽ ልቤ ገብቶ፤ ሐሳቤ ካንቺው ነው፣ከደብሩ ሸፍቶ፤ ፍቀጅ እመቤቴ!... ሎሚ መግዣ የለኝ፣ውርወራ አላውቅ ከቶ፣ ጥምቀት ብዬ፣ልንካሽ በ‹ስክሪፕቶ፤ ይህ ግጥም የአሁኑን የፍቅር መግለጫ አሲድና የቀደመውን “ሎሚ ጣሉባት በደረትዋ፣የጌታ ልጅ ናት መሰረትዋን” ያስታውሳል፡፡ዮሃንስ የሁለቱም ትውልድና ቅርስ አድናቂ እንጂ ናቂ አይደለም፡፡ ውበትን አገላብጠው የሚስሙ ድንቅ የተቃራኒ ጾታ ፍቅር ግጥሞችም ቢኖሩት ከምስኪኖች ጋር ተቆራምደው የሚያለቅሱ የጉበኛ ልቦች አሉ፡፡አንዳንዴ ከደሃውና ከተጠቃው ምስኪን፣ወይም ከመላው ምስኪን ጋር ታገኙታላችሁ፡፡ ….ግርማ ሞገሳሟ ቴ ዛሬ እናን ባየሽን… እንኳን ስሙን ጠርተን፣ደርሰን ከሰፈሩ፣ ልኩን አስታጥቀነው፣ገጥመን ከግንባሩ፣… እንዲሁም እንዲሁ ነን፣ትርጁማን አናጣ፣ ያልነውን ተርጉሞ፣ባላልነው ሚቀጣ፡፡ ብናለቅስ--“አበዱ!”፤ጥለን ብንሄድ”ፈሩ!”፣ ብንጠይቅ “ጠገቡ!”፤ብናውቅ--“አሸበሩ!”፤ የሚለን ብዙ ነው፣ሚከሰን ዘርዝሮ፣ እንኳንስ ሊሸኘን፣ካሳ ድርጎ ሰፍሮ፡፡ “ስንብት”አንዱ ራሮት ነው፤አንዱ የሩቅ ድምጽ፣ የሰቀቀን ዜማ ነው፡፡

ስንቱን የቀለም ቀንድ፣ ችኩል ጅብ ነካክሶ፣ ቀለሙን ደፋፍቶ፣ጥበብን አራክሶ፤ አድርባይ ጤፍ ቆዪው፣በዝቶ በመንደሩ፣ ጥራዝ-ነጠቅ እውቀት፣ተስፋፍቶ ባገሩ፣ ብራና በረቀ፤…መቃ ብ‹ር ነጠፈ፤ሊቃውንት ሰፈሩ፤ ፀሃፍት አንገት ደፉ፤አበው ተሸበሩ፤ጠቢባንም ፈሩ፡፡ ድጓ ጾመ ድጓ፣ተሰቃቅለው ቀሩ፤ --እንደተደጎሱ…

                           * * *

ደጅ ሁሉ ተዘጋ፣ሆድ ሁሉ ተከፋ፣ በግ ሁሉ ተነዳ፣በተኩላ ተበላ፤…ቆዳው ሳይቀር ጠፋ፤ ወስፋቱን ሊያስተኛ፣ደበሎሊደርብ፣ተሜ ላይ ታች ለፋ፡፡ ምጣድ ይጥድ ሳይኖር፣”የዕለት እንጀራዬን ስጠኝ”ባዩ በዛ፤ የበሰለ እንጀራም በበዮች ተከብቦ፣በየጥጋጥጉ ሻገተ ጠነዛ፡፡…..

* * *

መንገድ እንዳትባክን፣ልቤ ካለ ልብዋ፣ “ይቅናህ ልጄ!”በይኝ!...ደህና ሁኝ እመዋ! ደህና ሁን አስኳላ !ደህና ሁን መምህሩ! ደህና ሁን ባልንጀር! ደህና ቆይ መንደሩ! --ጋራው ሸንተረሩ፤አድባሩ፣ደብሩ፣ ደህና ሁኑ እንግዲህ!...በችጋር ተገፋ፣ልቤማ ሰነፈ፤ ኑሮውን ሊረታ፣ለከንቱ ብልጭልጭ ውበት ተሸነፈ፡፡ እዚህ ላይ የምናያቸው በርካታ ቃላት እማሬያዊ ብቻ ሳይሆኑ ፍካሬያዊም ፍቺ ያላቸው ናቸው፡፡…እነዚህ ደግሞ ለልብ የልብ ለመናገር ይሆናሉ፡፡ እስቲ እጅግ ከሚመስጡት የፍቅር ግጥሞቹ ጥቂት ስንኞች ልውሰድ፡- መዋስዕት፣ምዕራፍ፣ድጓ፣ጾመ ድጓ፣ አቋቋም፣ዝማሬ፣--ቀልብ እንደሚያረጋ፣ እንደ ነፍስ ወጌሻ፣እንደ ሥጋ አለንጋ፣ እንደምትቃርመው፣መንፈሴ አደግድጋ፣ ሥጋ እንደሚሸሻት፣ቤቱ ስትጠጋ፣ ካንቺ ከውዴ ጋ…ከስሜቴ ሲሳይ፤….እያለ ይቀጥላል፡፡የቓላቱን ውበት እዚህ ጋ ማየት ይቻላል። አሻም ቴ እጅግ መሳጩና አስደኛቂው ግጥም ነው፡

፡--ለኔ!ገጽ 19… የዮሃንስ መጽሃፍ ውበት ከሽፋኑ ይጀምራል።…ቋንቋው በዚህ ዘመን ላለው የቃላት ድህነት እንደማስታገሻ ነው ማለት ይቻላል፡፡በዚያ ላይ አዳዲስ ቃላትን ኮይን ሊያደርግ የሚከረበት መንገድ የሚያበረታታ ነው፡፡….እንደ ችግር እንይ ካልን፣ አንዳንዶቹየግርጌ ማስታወሻዎች ብዙም ጠቃሚ ስላልሆኑና ባብዛኛው የሚታወቁ ስለሆኑ ቢቀሩ ጥሩ ነበር የሚል ሃሳብ አለኝ፡፡ከዚያ በተረፈ ባብዛኛው የተጠቀማቸው ጠቃሽ ዘይቤዎች አንዳንድ ቦታ ዝቅ ማለታቸው አይወደድም፡፡ለምሳሌ በህዝብ ዘንድ እጅግ የተለመዱት፤ግርማ ሞገሳሟ ቴ..ግጥሙን አጋምሶታል፡፡ ይህ ዘይቤ ታዲያ ከፍታው ጨምሮ ወደ ላይ ሲያንጠራራም፣ወደ ታች ዝቅ ብሎ ሲያስጎነብስም ጥሩ አይደለም፡፡ብቻ--ብቻ ዮሃንስ ትልቅ ልብ፣ትልቅ ምናብ አለው፡፡ይህንን አይውሰድበት!! ምሁራዊ ከፍታቸው ጨምሮ ማንጠራራት ዝቅ ብሎ ሲያስጎነብስ አይወደድም፡፡ Over intellectualization

Published in ጥበብ

ሠዓሊ ማህሌት እቁባይ ትባላለች፡፡ ኑሮዋ በሀገረ ኖርዌይ ነው፡፡ እዚያ ለሰባት ዓመታት የሥዕል ሙያን አጥንታ በማስትሬት ዲግሪ ተመርቃለች፡፡ ሥዕል ከማስተማር ይልቅ ፋብሪካ ውስጥ የጉልበት ሥራ ስሰራ ነው ለሥዕል የምነሳሳው የምትለው ሰዓሊዋ፤ ባለፈው ቅዳሜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጥበባት ትምህርት ቤት የተለያዩ የኪነጥበብ ውጤቶች የተካተቱበት በለቅሶ ባህል ላይ የተሰናዳ የኢንስታለሽን ሥራ አቅርባለች፡፡ በዚሁ ወቅት ያገኛት የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መልካሙ ተክሌ ከሰዓሊዋ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡

ኖርዌይ ምን እየሰራሽ ነው? ኑሮዬ ኖርዌይ ሀገር ነው፡፡ እዚያ ሰባት ዓመት ሥእል ተምሬአለሁ፡፡ በ1998 ዓ.ም በማስትሬት ዲግሪ በስእል ተመርቄ የተለያዩ ሥራዎች እየሰራሁ ነው፡፡ ከዚያ ሁለት አመት ቀደም ብሎ የሠራሁትን ነው ባለፈው ቅዳሜ ምሽት በአለ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ያቀረብኩት፡፡ የድምፅ ጥበብ (Sound art) ነው ለቅሶን አስመልክቶ የሠራሁት፡፡ ለስምንት ዓመት የለፋሽበት ነው ማለት ነው? በአንድ ሰዓት ትዕይንስ ያቀረብሽው? አዎ፡፡ ግን ይህንኑ ዝግጅት ካሁን ቀደም ሁለት ጊዜ አቅርቤዋለሁ፡፡ በኖርዌይና በጎረቤት ሀገር፡፡ መጀመርያ ድምጽ ብቻ ነበር የሰራሁት፡፡ ለለቅሶው የራሴን ድምጽ ነው የቀዳሁት፡፡ ለማስተርስ ዲግሪዬ መመረቂያ ሳቀርበው ተወዳጅነት አገኘና የገንዘብና ቁሳቁስ እገዛ አግኝቼ አዳበርኩት፡፡

ለቅሶ ብቻ ሲሆን ተመልካች አፈንግጦ ነው የሚወጣው፤ ይደነግጣል። ማዳመጥ አይፈለግም፡፡ ተመልካቹን ለመያዝ ለድምፄ ጎጆ ነገር ሠራሁ፡፡ ለሌላው ድምፅ ደግሞ ባለ 5 ሜትር ውሃ የተሞላ እቃ አዘጋጅቼ በጨርቅ የተሰሩ ሕትመቶች አከልኩበት፡፡ ሰው ጨርቁን በውሃ ውስጥ ሲያይ ሳይታወቀው ብዙ ይቆያል፤ ፎቶግራፍ ነው፣ ጨርቅ የማያልቅ ርእሰ ጉዳይ መሆኑን አወቅሁ፡፡ እንዴት ነው ሰዓሊ የሆንሽው? ጣሊያን ትምህርት ቤት ነው የተማርኩት። በስእል፣ በጂኦሜትሪ እና በሂሳብ ጎበዝ ነበርኩ። አስተማሪዬ ለቤተሰብ ስዕል ወይ አርኪቴክቸር ብትማር ብሎ ሃሳብ ሰጠ፡፡ ሁለት መሃንዲስ ወንድሞች ነበሩኝ፡፡ ቤተሰብ አካውንቲንግ አስገባኝ። ትምህርት ቤቱ አካውንቲንግና መሃንዲስ ብቻ ነበር የሚያስተምረው፡፡ አካውንቲንግ መማሩ ግን ፍላጎቴ አልነበረም፡፡ ከዚያ ምግብ ዝግጅት ተማርኩ፡፡ ፍላጎት ስለነበረኝ ግን በትርፍ ሰዓት እዚህ እያለሁ ሰዓሊ አብያለው አሰፋ ውሃ ቀለም ያስተምረኝ ነበር። ኖርዌይ እንደገባሁ አጋጣሚዎች ሲመቻቹልኝ ሥእል ትምህርት ቤት ገባሁ፡፡ ሥዕል ስዬ ዝም ብዬ እወረውረዋለሁ፡፡ ያ ተከማቸ፡፡ ጎረቤቴ የሆነች ፈረንጅ “ለጥበብ ለምን ክብር አትሰጪም” አለችኝና ሰበሰበችው፡፡ ይታይህ የምስለው ለማሳየት ሳይሆን ለስሜቴ ነው፡፡ ታዋቂ ኖርዌያዊ ሠዐሊ ነበር፡፡

እሱ ጋ ወሰደችኝ እዚህ እየመጣሽ ስቱዲዮ ተጠቀሚ አሉኝ - ሠዓሊውና ባለቤቱ፡፡ ሠዓሊ ባለቤቱ ሥራዎችሽን ሰብስቢና አመልክቺ አለችኝ፡፡ ሄጂ በሰባት ወሬ አመለከትኩ፡፡ የሥዕል ትምህርቴን ቀጠልኩ፡፡ በሁለት ዓመት ዲፕሎማ ሁሉን ነገር ተምሬ ወጣሁ፡፡ ቅርፃ ቅርፅ፣ ሥእል፣ ኢንስታሌሽን … ተማርን፡፡ ከዚያ አካዳሚ ተወዳድሬ ገባሁ፡፡ ከ1500 አመልካቾች 15 ብቻ ነው የተቀበሉት፡፡ በሥእል ነው የምትተዳደሪው? አይደለም፡፡ በመጀመርያዎቹ አመታት ሥእል ሰርቼ በመሸጥ እኖር ነበር፡፡ ያንን አልፈለግሁም። የተለያዩ የሥእል ጽንሰ ሀሳቦችን ለማወቅ ጓጓሁ። በተመረቅሁ ጊዜ የሠራኋቸው ሥእሎች በሙሉ ተሸጠዋል፡፡ ግን የበለጠ ማወቅ አለብኝ ብዬ ማስተርስ ቀጠልኩ፡፡ አሁን ግን መሳሉን ትተሽ በተመራማሪነት እየሰራሽ ነው… ኢንስታሌሽን ስትሠራ ለስሜት ነው የምትሠራው፡፡ ገቢ የለውም፡፡ አንድ ሰዓሊ ሥዕል ወይም ቅርፃ ቅርፅ አሊያም ግራፊክስ ሰርቶ ሊሸጥለት ይችላል፡፡ የእኔን የለቅሶ ባህል ላይ የተሠራ ኢንስታሌሽን ግን ማንም አይገዛም፡፡ ከኤግዚቢሽኑ በኋላ ግን ረክቻለሁ፡፡ አንዳንዴ ስፖንሰርም ልታገኝ ትችላለህ፡፡ ከኪስህም አውጥተህ ትሠራለህ ለእርካታ፡፡ ለእርካታ ብቻ እየሰሩ ግን መኖር አይቻልም… ትክክል ነው፡፡ ኖርዌይ አንዳንዴ ፕሮጀክት እሰራለሁ፡፡

አንዳንዴ ደግሞ እንደ አርቲስት ማስተማር ይቻላል፡፡ ኪዩሬተር መሆን ይቻላል። ትክክለኛ የአርት ሥራ ለመሥራት የጉልበት ሥራ ነው የምመርጠው፡፡ የማላስብበትና ብዙ እውቀት የማይጠይቅ ሥራ ላይ ስሆን ጭንቅላቴ ለአርት ይዘጋጃል፡፡ ገንዘብ ሲያስፈልገኝ ፋብሪካ ሄጄ የጉልበት ሥራ እሰራለሁ፡፡ ለምሣሌ አንድ ጊዜ ቺፕስ የሚያመርት ፋብሪካ ውስጥ ሠርቻለሁ፡፡ ብየዳና የመሳሰለውን ነው የምሰራው፡፡ በተደጋጋሚ አንድ ሥራ ሥሠራ ያዝናናኛል፡፡ ሥራውን ስለማመደው ስለ ስዕሌ አስባለሁ፡፡ ሥእል ላስተምር ብል ግን አእምሮዬ ሥራ ስለሚበዛበት ሥእል መሳል አልችልም፡፡ አምኜበት ስለምሰራ በጉልበት ሥራዬ እኮራበታለሁ፡፡ አበሾችም ፈረንጆችም አሉ አብረውኝ የሚሰሩ፡፡ ፈረንጆቹ ከስምንተኛ ክፍል ያላለፉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አንዳንዴ ሀበሾቹ ማስተርስ ሆና ከእኛ እኩል ትሠራለች ብለው ይገረማሉ፡፡ በአርቲስትነት ስትሰሪ ትኩረትሽን የሚስቡት ርዕሰ ጉዳዮች ምንድናቸው? በባህል ላይ ያተኮረ ሥራ እሰራለሁ፤ ለምሣሌ የበቀደሙን የለቅሶ ባህል ላይ ያተኮረ የኢንስታሌሽን ሥራ መመልከት ይቻላል፡፡ በእርግጥ ሌሎች አርቲስቶችም በሥራው ተሳትፈዋል። በየቦታው ስሄድ ከቦታው ጋር የተያያዘ ሥራ እሰራለሁ። ሥእል መሳል ከባድ ነው፤ ትልቅ ፈጠራ ይጠይቃል፡፡

አንዳንድ በኮምፒዩተር የታገዘ ስነ ጥበብን የሚቃወሙ ሰዓሊዎች አሉ፡፡ ማህበርም አቋቁመዋል፡፡ እኔ ይኼንን አልደግፍም፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሥራዎቻችን እንዲታወቁ ከፈለግን በኮምፒዩተር መታገዝ አለብን፡፡ ዛሬ እኮ ምዝገባ እንኳን የሚከናወነው በኢሜይል ነው፡፡ ኮምፒዩተር መጠቀም የፈጠራ ችሎታን ያቀጭጫል የሚሉ ሰዓሊዎች እንዳሉ አውቃለሁ? ያንቺ ሃሳብ ምንድነው? ኮምፒዩተር ሥራን በጣም ያግዛል፡፡ የፈጠራ ችሎታን ይቀንሳል ብዬ አላስብም፡፡ ስቱዲዮ ውስጥ ቁጭ ብዬ ብቻ ይህን ዓለም ልከተለው አልችልም፡፡ ከዘመኑ ጋር ካልተራመድክ ተቆራርጠህ ትቀራለህ፡፡ ከኢትዮጵያና ከኖርዌይ ለሰዓሊነት ሙያ የሚመቸው ማነው? በኖርዌይ ስፖንሰርሺፕ በደንብ ታገኛለህ። ኖርዌይ ሆነው ለመሥራት የሚመርጡ ኢትዮጵያውያን ሠዐሊዎች አሉ፡፡ ለኔ ግን ሁኔታዎች ቢሠምሩልኝ ኢትዮጵያ ሆኜ መሣል ነው የምመርጠው፡፡ ኖርዌይ ሀብታሞች ናቸው፡፡ ለአርት ስራ ድጋፍ በመስጠት ያላቸውን አክብሮት ይገልፃሉ፤ ያ ጥሩ ነው፡፡ ጥሩ ፕሮጀክት ካመጣህ ስፖንሰር የማግኘት እድልህ ሰፊ ነው፤ በኖርዌይ። ሀገርህ ሆነህ ስትሥል ግን ዘና ትላለህ፡፡ ጭንቀት የለብህም በጣም ደስ ያለኝ በተለያየ የሥራ አጋጣሚ ከኢትዮጵያ የወጡ አርቲስቶች ኢትዮጵያ ተመልሰው መስራታቸው ነው፡፡

የኖርዌዮች ገብረክርስቶስ ደስታ ወይም አፈወርቅ ተክሌ ማነው? እውቅ ሠዐሊያቸው ጩኸትን አስመልክቶ የሠራው ኤድዋርድ ሞንክ ነው፡፡ አፉን በጣም ከፍቶ ድባቡም ያንን ያጠናከረለት ሥዕል ነው፡፡ ቬጌራን የሚባል ቀራፂም አለ፡፡ በጣም ነው የምወደው፡፡ አንድ ትልቅ ፓርክ ሙሉ ቅርፅ የሳለ ነው፡፡ በጣም አደንቀዋለሁ፡፡ የኖርዌይ የሥእል ታሪክ ግን ከ100 ዓመት የሚበልጥ አይመስለኝም… የሥእል ታሪክ አላቸው፡፡ በዴንማርክና ስዊድን ግዛት ሥር ነበሩ፡፡ ያኔም ግን ሠዐሊዎች ነበሩ፡፡ ልዩነቱ ምንድነው ከዴንማርክና ስዊድን አገዛዝ ነፃ ሲወጡ በራሳቸው ቋንቋ ተጠቅመው ትያትሩንም፣ ሥእሉንም ድርሰቱንም ሌላውንም ማካሄድ መጀመራቸው ነው፡፡ በአገዛዝ ስር የነበሩት አርቲስቶች እኮ እስካሁንም ኖርዌያውያን ናቸው፡፡ ለሕፃናትና ለታዳጊዎች የሚስሉ ሠዐሊዎች ምን ያህል ናቸው? ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል ለልጆች የሚስሉ ሠዐሊዎች እንዳሉ አላውቅም፡፡ ግን አሉ፡፡ እንደውም ለሕፃናት መሣል ያዝናናል፡፡ ካርቱን የሚስሉ ጎበዝ ሠዐሊዎች አሉ፡፡ በመፃሕፍት ሥራቸውን ያኖራሉ። ሕፃናት መጻሕፍትንም በሥእል ያሳምራሉ፡፡ ክህሎትና ትዕግስት የሚጠይቀው አኒሜሽንም አለ። አኒሜሽን እና ካርቱን ብዙ ጊዜ ሊፈጅ ይችላል፡፡ ብዙ ገንዘብም ሊያስገኝ ይችላል፡፣

ኖርዌይ ውስጥ የሕይወታት ዘመናቸውን ለሕፃናት የሰጡ ብዙ ሠዓሊያን አሉ፡፡ እስካሁን ከሰራሻቸው የኢንስታሌሽንም ሆነ ሌሎች ሥእሎች ብዙ ገንዘብ አግኝተሽ ታውቂያለሽ? አዎ፡፡ ይህም የሆነው ዲፕሎማዬን ስጨርስ በሠራኋቸው ሥዕሎች ነው፡፡ በአንዴ ነው ስዕሎቹ የተሸዩት፡፡ በኢንስታሌሽንና ሌላ አርት ሥራም ተሳትፌአለሁ፡፡ በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ በመስራቴ ትልቅ ሥም ባላቸው ዓለም አቀፍ አውደርእዮች ላይ ተሳትፌአለሁ፡፡ በዚህ ረገድ ሥም አለኝ፤ ምንም ገንዘብ ግን የለኝም፡፡ በሥእል ኤግዚቢሽኑ 34ሺህ የኖርዌይ ኪሮነር አገኘሁ፡፡ እንዲህ ይሸጥልኛል ብዬ ስላላሰብኩ ገንዘቡን በአንዴ ነው ያወደምኩት፡፡ ለቅሶን አስመልክቶ ባለፈው ቅዳሜ በአለ የሥነጥበብ ትምህርት ቤት የኢንስታሌሽንና ሌሎች የኪነጥበባት ስራዎች ተቀላቅለው የቀረቡበት ዝግጅት ከቦታ ጥበት አንፃር ለተመልካች ምቹ አልነበረም … ልክ ነው፡፡ ግን ይኼንኑ ተመልክተን ሥራው ሶስቴ እንዲደገም አድርገናል፡፡ ዝግጅቱ የሥዕል ትምህርት ቤቱና የትያትር ክፍለ ትምህርቶቹ መስተጋብር እንዲኖራቸው ተፈልጎ የተሰራ ነው። ከብሔራዊ ትያትርም ተዋንያን ተሳትፈዋል፡፡ ኬሮግራፈር እና ዳንሰኞችም ነበሩን፡፡ ኤግዚቢሽኑ በጥቅሉ ውጤታማ ሆኗል፡፡

አንድ ወር ተኩል ተዘጋጅታችሁ አንዲት ሰዓት ብቻ ማቅረብ አይደንቅም? እንዴ ከዚያ በላይ ከሆነ እኮ ተመልካቹ ይሰለቻል፡፡ እንዲህ አይነት ሥራ አነስ ብሎ ደረጃውን የጠበቀ ነው መሆን ያለበት፡፡ ቅልብጭ ብሎ ሲቀርብ ተመልካች ካልደገምኩ ይላል፡፡ በዚህ ዝግጅት ሁለቴ ለተመልካች፣ ሦስተኛውን ለተሳታፊዎቹ ፎቶ መነሻ ስንደጋግም ሦስቱንም ጊዜ ያዩ አሉ፡፡ ደጋግሞ ሲያይ ሐሳቡ የበለጠ ግልፅ ይሆንለታል፡፡ በዶክትሬት ዲግሪ ደረጃ ትምህርት ለመቀጠል አስበሻል? አስቤአለሁ፡፡ ለዚሁ የሚያዘጋጁኝን ስድስት መፃሕፍት አምና አንብቤአለሁ፡፡ የኤግዚቢሽን ጥያቄ ሲመጣ አቋረጥኩት፡፡ በአስጎብኚነት ስሰራ ደግሞ ኢትዮጵያን ለማየት ለሚፈልጉ ኖርዌያውያን ለሚጎበኙ ሀገር ጎብኚዎች የጉብኝት ማውጫ በጣሊያንኛና ሌሎች ቋንቋዎች እየሰራሁ አድላለሁ። በዚሁ ጊዜም ሰዎቹን ሊያስለቅሳቸው እንደሚችል እየጠየቅሁ ጥናቴን ቀጥያለሁ፡፡ የቀረ ነገር ካለ? በጣም ብዙ ተዳግሮት አለው ሥራው፡፡ ለሙያው ክብር ኖሯቸው ጊዜአቸውን መስዋእት አድርገው የለቅሶ ሥርአቱን ለማሳየት አብረውኝ የሰሩትን በጣም ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡

Published in ጥበብ

የአፍሪካ የፀረ ቅኝ አገዛዝ ትግልና የነፃነት ገድል ተመዝግቦ በሚገኝበት የታሪክ መጽሀፉ ውስጥ የ1960ዎቹ አመታት ልዩና ሰፊ ምዕራፍ ይዘዋል። እነዚህ አመታት በእልህ አስጨራሽ መራራ የትግልና አስደናቂ የድል ታሪኮች የተሞሉ የአፍሪካ የመጀመሪያው የነፃነት ማዕከል አመታት ተደርገው ይቆጠራሉ፡፡ ምንም እንኳ እነዚህ አመታት ታሪከኛ አመታት ተብለው በታሪክ መዝገብ ውስጥ ይስፈሩ እንጂ የአፍሪካ የነፃነት ፀሀይ በወቅቱ ወጥታ ትታይ የነበረው በግማሹ ብቻ ነበር፡፡ ያኔ እጅግ መራራና እልህ አስጨራሽ የፀረ-ቅኝ አገዛዝ ትግልና ይህን ያህል ይሆናል ተብሎ በቁጥር ተሠፍሮ የማይነገር የህይወትና የአካል መስዋዕትነት ከፍለው ከምዕራባውያን የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ነፃነታቸውን መቀዳጀት የቻሉት የአፍሪካ ሀገራት ሠላሳ አንድ ብቻ ነበሩ፡፡ በሀያ ሶስት ሀገራት የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ግን ያኔ ከቅኝ አገዛዝ ለመላቀቅና ነፃነታቸውን ለመጐናፀፍ ጦር ሠብቀው ዘገር ነቅንቀው በሀገራቸው ጫካና በረሀ ውስጥ የመረረ የነፃነት ትግል ውስጥ ተጠምደው ነበር፡፡ ክዌሜ ንከሩማህን የመሳሠሉ አፍሪካውያን የበርካታ ልጆቿን ደምና አጥንት ገብራ ነፃነቷን ጠብቃ የኖረችውን ኢትዮጵያን የትግልና የነፃነት አርአያ በማድረግ በ1950ዎቹ አመታት የፀረ-ቅኝ አገዛዝና የነፃነት ትግላቸውን በየሀገሮቻቸው ማቀጣጠል ችለዋል፡፡

በዘመኑ ከነበሩት አፍሪካውያን የፀረ ቅኝ አገዛዝ ታጋዮች መካከል ግንባር ቀደምና ስመጥር በነበረው ክዋሜ ንክሩማህ የተመራው የጋናውያን የነፃነት ትግል ጐልድ ኮስት በመባል ትጠራ ለነበረችው ሀገራቸውና ለእነሱም በ1957 ዓ.ም ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ነፃነታቸውን አስገኝቶላቸዋል፡፡ እንደ ክዋሜ ንክሩማህ ሁሉ በሊወፖልድ ሴዳር ሴንጐር፣ በሁፌት ቧኝ፣ አህመድ ሴኩቴሬ፣ ሞዲቦ ኬታ፣ ሲልቫነስ ኦሊምፒዎ ጂሊየስ ኔሬጌ፤ ጆሞ ኬንያታ፣ ካሙዙ ባንዳና በመሳሠሉት የተመራው የነፃነትና የፀረ ቅኝ አገዝዝ ትግል የማታ ማታ ፍሬውን አፍርቶ ከ1960ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ ባሉት ጥቂት አመታት ውስጥ ሠላሳ አንድ የአፍሪካ ሀገሮችን የነፃነታቸውን ጌታ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡ የፀረ-ቅኝ አገዛዝ ትግሉን በየሀገሮቻቸው በዋናነት የመሩት እነኝህ ታጋዮች ከነፃነት በሁዋላም ሀገሮቻቸውን የመምራት ከባድ ሀላፊነት የወደቀው በእነሱው ላይ ነበር፡፡ ክዋሜ ንክሩማህ የመጀመሪያው የጋና ፕሬዚዳንት ሲሆን አህመድ ሴኩቱሬ የጊኒ ሞዲቦ ኬታ የማሊ ሊወፖልድ ሴንጐር የሴኔጋል፣ ሲልቫነስ ኦሊምፒዎ ደግሞ የቶጐ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንቶች ለመሆን ችለዋል፡፡ ኬኔት ካውንዳ የዛምቢያ የመጀመሪያው መሪ መሆን ሲችሉ፣ ጆሞ ኬንያታ የኬንያን ጁልየስ ኔሬሬ ደግሞ የታንዛንያን የመጀመሪያ የፕሬዚዳንትነት መንበር ተረክበዋል፡፡ ካሙዙ ባንዳም በበኩላቸው የማላዊን የመጀመሪያ የፕሬዚዳንትነት ስልጣን ለመረከብ ቻሉ፡፡

እነዚህ መሪዎች በፀረ-ቅኝ አገዛዝ ትግሉ ወቅት የተጫወቱት ሚና ከተሸከሙት የመጀመሪያ የመሪነት ሀላፊነት ጋር ተዳምሮ የአፍሪካ መስራች አባቶች The founding fathers የሚል ቅጣያ መጠሪያ ሊያተርፍላቸው በቅቷል፡፡ እነዚህ መሪዎች ነፃነታቸዉን ለማስመለስ ከቅኝ ገዢዎች ጋር ነፍጥ አንግበው የጦር ሜዳ ትግል የገጠሙትን አፍሪካውያን ወድንሞቻቸውን ይህንኑ ትግላቸውን የበለጠ ለመደገፍና በአለም አቀፍ የፖለቲካና የኢኮኖሚ መድረክ ላይ አፍሪካ ተገቢውን ቦታ እንድትይዝና ድምጿም ተደማጭ እንዲሆን ለማድረግ ሲያካሂዱት የነበረው ህብረት የመፍጠር ትግል የማታ ማታ ግቡን መቶ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ለመመስረት መብቃታቸው በአፍሪካ የወንድማማችነት፣ የትብብርና፣ የአንድነት የትግል ታሪክ ውስጥም ጉልህ ስፍራ እንዲይዙ አስችሏቸዋል፡፡ በያዝነው ግንቦት ወር በ1963 ዓ.ም ከቅኝ አገዛዝ ነፃ የወጡ የሰላሳ አንድ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችና ተወካዮች አዲስ አበባ ውስጥ ተገናኝተው ባደረጉት ስብሰባ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን መሠረቱ፡፡ የአፍሪካ አንድነተ ድርጅት በሀምሳ አመት የእድሜ ዘመኑ በርካታ በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፎ አስቸጋሪና ጠመዝማዛ መንገዶችን ተጉዞና በርካታ ስኬቶችንና ውድቀቶችን አጣጥሞ እነሆ ዛሬ ለአፍሪካ ህብረትነትና የምስረታ የወርቅ ኢዩቤልዩ በአሉን በተወለደባት ከተማ በአዲስ አበባ ለማክበር በቅቷል፡፡

ምንም እንኳ ይዘታቸውን መጠናቸው የፈለገውን ያህል ቢለያይ የልደት በአሎች ናቸው። የልደት በአሎች የመጀመሪያም ሆነ የመጨረሻ ዝክራቸው አንዱ የአንዱን እግር ተከትሎ ያለማቋረጥ የሚፈሰው የዘመን ጅረት ነው፡፡ እናም በእያንዳንዱ የልደት በአል ላይ የትናንትናና የኮትናንት ወዲያ የትዝታ ማህደር የትዝታ ሙዳይ መፈከቱ ከቶም አይቀሬ ነው፡፡ ሀምሳኛው የአፍሪካ ህብረት የምስረታ የወርቅ ኢዮቤልዩ የልደት በአልም የመስራች አባት መሪዎችን የከትናንት በስቲያ የሃምሳ አመት የትዝታ ማህደርን ከፍቶልናል፡፡ ለመሆኑ ከእነዚህ መስራች አባት መሪዎች ውስጥ የእነ ንክሩማህ፣ ሴኩቱሬ፣ ኬንያታ ኔሬሬና ሴንጐር ትዝታ እንዴት ያለ ነው? ግለስብዕናቸው እንዴት ያለ ነበረ? ስለ ግለሰ ስብዕናቸው የሚያወሳው የማህደራቸው የመጀመሪያው ክፍል ከዚህ በታች ያለውን ያስቃኘናል፡፡ የዛሬ ሃምሳ አመት ስለተመሠረተው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የምስረታ ስንክሳሩን የሚመረምር ሰው ለምስረታው ወሳኝ ሚና ከተጫወቱት የአፍሪካ መሪዎች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚያገኘው አዲስ አበባ በሚገኘው የድርጅቱ ዋና ጽሕፈት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ሀውልት የቆመለትን የጋናውን የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት ክዋሜ ንክሩማህን ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ክዋሜ ንክሩማህ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት የምስረታ ታሪክ ውስጥ በእርግጥም አንፀባራቂ ኮከብ መሪ ነበሩ፡፡

አባባ ጃንሆይ አንዳች አይነት ሀይለኛ ግርማ ሞገስ ነበራቸው እንደሚባለው ንክሩማህም የቀረቧቸውን ሁሉ እንደማግኔት የሚሰብ ግርማ ሞገስ እንደነበሯቸው በቅርብ የሚያውቋቸው ሁሉ ዛሬም ድረስ ይመሰክሩላቸዋል፡፡ የፕሬዚዳንት ንክሩማህ መላ ህይወት በፖለቲካና በፖለቲካ እንቅስቃሴ የተሞላ ብቻ ሳይሆን ጠቅላላውን የተዋጠ ነበረ፡፡ ለስፖርትና አካላዊ እንቅስቃሴ፣ ለምግብ እንዲሁም ለግላዊ ምቾት ጨርሶ ቁብ አይሰጡም ነበር፡፡ ንክሩማህ በካቶሊክ ሃይማኖት ህግና ስርአት የተጠመቁ ክርስቲያን ሲሆኑ የመጀመሪያ ምኞታቸውም ቄስ መሆን ነበረ፡፡ የቅስና አገልግሎት በውስጡ በያዘው አላማን የማሳካት ግላዊ ተልዕኮ እድሜ ዘመናቸውን ሙሉ በልባቸው እንደተሳቡና እንደተመሰጡ ኖረዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ንክሩማህን ትንባሆ ሲያጤሱና የአልኮል መጠጥ እየጠጡ ሲዝናኑ አይቻቸዋለሁ የሚል ሰው ቢገኝ እርሱ የለየለት ዋሾ ነው፡፡ የንክሩማህ ዋነኛው መዝናኛቸው ስራና ስራ ብቻ ነበረ፡፡ ከዚህ ውጪ የሚያስደስታቸውና በስራ የተወጠረ ስሜትና አካላቸውን ዘና የሚያደርግላቸው ክላሲካል ሙዚቃዎችን ማዳመጥና የባህል ጭፈራዎችን ማየት ነበር፡፡ የሙዚቃን ነገር በተመለከተ ለክላሲካል ሙዚቃዎች ቀልባቸው መሳቡን ያየ አንድ አውሮፓዊ ዲፕሎማት በአንድ ወቅት በአውሮፓ ታዋቂ የሆኑትን የክላሲካል ሙዚቃ አርቲስቶች ስም ዝርዝር ሰጣቸው፡፡

ንክሩማም የደቂቃ ጊዜ እንኳ ሳያጠፉ በእንግሊዛዊቷ ወዳጃቸው ኤሪካ ፓወል አማካኝነት ሁለት መቶ የክላሲካል ሙዚቃ አልበሞች ተገዝተው እንዲመጡላቸው አዘው በሶስት ቀናት ውስጥ ትዕዛዛቸው ተፈጽሞላቸዋል፡፡ ከእነዚህ ሁለት መቶ አልበሞች ውስጥ በጣም የወደዱትና እየደጋገሙ ለሰአታት ያዳምጡት የነበረው ግን The Messiah “Hallelujah chorus” የተባለውን ሙዚቃ ብቻ ነበር፡፡ የፕሬዚዳንት ንክሩማህን አፍዝ አደንግዝ የሆነ ግርማ ሞገሳቸውንና ከሰዎችጋር በቀላሉ የመግባባት አስገራሚ ችሎታቸውን ያየ ብቸኛ ሰው ናቸው ቢባል ለማመን መቸገሩ የማይቀር ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሰውየው ከሁሉም ተለይተው ለብቻቸው የቆሙና እጅግ ብቸኛ ሰው ነበሩ፡፡ ንክሩማህ እጅግ ሲበዛ ተጠራጣሪና የቅርብ አጋሮቻቸውንና የትግል ጓዶቻቸውን እንኳ ጨርሰው የማያምኑ ሰው ነበሩ፡፡ ከቅርብ የትግልና የስራ አጋሮቻቸው ውስጥም በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት የግልም ሆነ የስራ ምስጢራቸውን አካፍለውኝ ያውቃሉ ብሎ የምስክርነት ቃሉን የሚሰጥ ሰው በምድረ ጋሃ ከቶውንም ተፈልጐ አይገኝም፡፡ ፕሬዚዳንት ንክሩማህ በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት የሚያገኟትን ጥቂት የእረፍት ጊዜ ለማሳለፍ የሚፈልጉት ከትግል ጓዶቻቸው ወይም ከቅርብ የስራ ባልደረቦቻቸው ጋር ሳይሆን ከሴቶች ጋር ብቻ ነበር፡፡ የንክ ሩማህ ልብ ስስ የነበረው በእርግጥም ለሴቶች ብቻ ነበር፡፡ ከሴቶች ጋር መቃበጥ ነፍሳቸው ነበር፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

ከላይ የምትመለከቱት የጡት ስእል የጡትን ተፈጥሮአዊ አቀማመጥ የሚያሳይ ነው፡፡ ስአሉን ለእይታ የጋበዝናችሁ ያለምክንያት አይደለም፡፡ የጡት ካንሰርን መሰረታዊ አመጣጥና ለመከላከልም ምን መደረግ ይገባዋል ከሚል የባለሙያ ትንታኔን ልናስነብባችሁ ነው፡፡ ዶ/ር አበበ ፈለቀ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የቀዶ ሕክምና ባለሙያና አሲስታንት ፕሮፌሰር ለርእሱ ማብራሪያ ሰጥተውናል። ከዚያ በማስቀደም በኢንካርታ ኢንሳይክሎፔድያ ላይ ያገኘነውን መረጃ እነሆ፡፡ “በጥንት ጊዜ በህክምና መታወቅ ወይንም መለየት ከተቻሉት የካንሰር ዓይነቶች ውስጥ አንዱ የጡት ካንሰር ነው፡፡ ይህ መሆን የቻለው ደግሞ የበሽታው ምልክቶች በግልጽ መታየት በመቻላቸው ነው፡፡ ጥንት ከተጻፉ መረጃዎች ውስጥ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1500/ ግብጻውያን የህክምና ባለሙያዎች ፓፒረስ ላይ ያሰፈሩት የኤድዌን ስሚዝ የቀዶ ጥገና መጽሐፍ ላይ ስለጡት ካንሰር ያሰፈሩት መረጃ ያሳያል፡፡

የታሪክ ተመራማሪዎች እንደሚሉት ከሆነ መነሻ የሆነው ለመረጃ የተቀመጡ የስምንት ሰዎች የጡት ካንሰር በሽታ ታሪክ ሲሆን የህሙማኑ የህክምና ምርምር ውጤት ሴቶቹ ጡት ላይ እጢ እንዳለ ያሳይ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት በሽታው ምን እንደሆነ ቢታወቅም በሽታው ህክምናና መድሀኒት ግን የለውም ተብሎ ተደምድሞ ቆይቶአል፡፡ ለበርካታ ዘመናትም የነበሩ የህክምና ባለሙያዎች ያሰፈሯቸው መረጃዎች እንደሚያስረዱት ከሆነ የጡት ካንሰር ምንም አይነት ህክምና እንደሌለው የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ለበሽታው መከሰት ምክንያት የሚሆኑ ጉዳዮችን እራሱ ጥንት የነበሩት የህክምና ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች አያውቋቸውም ነበር፡፡” ከላይ ያስነበብናችሁ ጥናታዊ ስራዎች ለንባብ ከሉዋቸው ውስጥ የመረጥነውን ነው፡፡ ዶ/ር አበበ ፈለቀ እንደሚገልጹት የጡት ካንሰር ማለት ጡት ከተሰራባቸው ክፍሎች የሚነሳ ሕመም ነው፡፡ ካንሰር ማለት ጤነኛ የነበረ የሰው ልጅ ሴል ጤነኛ ወዳልሆነ ሁኔታ ሲለወጥ ማለት ነው፡፡

ይህም ማለት አንድ ሴል ስራውን በትክክል የማይሰራ፣ በትክክል የማያድግ ወደመሆን ሲለወጥ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ጤነኛ የነበረው ሴል የሚኖረው ስራ ሲቋረጥ ወይንም ከቁጥጥር ውጪ ሲራባ አለዚያም ሲያድግ እና ከጎረቤቱ ያለውን ሴል ስራና ጤንነት ሲበጠብጥ የሚፈጠረው በሽታ ነው ካንሰር ማለት፡፡ ካንሰር አንድ ቦታ ሲፈጠር እዛው በነበረበት ቦታ አይቆይም፡፡ ወደ ሳንባ ወደጉበት እና ወደሌሎችም የሰውነት ክፍሎች ይሄዳል፡፡ ወደተለያዩ የሰውነት አካሎች ከሄደ በሁዋላም እድገቱን በመቀጠል የሰውነት ክፍሎችን ይበጠብጣል፡፡ ባጠቃላይም ካንሰር እንደእብድ ሰው የሚቆጠር ሕመም ነው፡፡ አንድ ሰው እብድ ነው ሲባል የተፈጥሮ ሕግ በትክክለኛው መንገድ እንዲመራ ስለማያዙትና ሁሉንም ነገር እንደፈቀደው ከተፈጥሮ ስርአት ውጪ የሚከውን ሲሆን ሴልም ወደ ካንሰርነት ሲለወጥ በዚህ መልክ ሊገለጽ ይችላል፡፡ የካንሰር ሴሎች ቁጥራቸው መጠናቸው በተፈጥሮ ሕግ መሰረት ሳይሆን እንደተመቸው ይጨምራል፡፡ መስራት የሌለባቸውን ስራ ይሰራሉ፡፡

ከራሳቸው አልፈው ከጎረቤት ያለውን ሴል ይበጠብጣሉ። ይህ በእንግሊዝኛው Carcinogenesis በመባል ይታወቃል፡፡ ዶ/ር አበበ እንደገለጹት ከ/100/የጡት ካንሰር ታማሚዎች ውስጥ /90/ያህሉ ሴቶች ሲሆኑ ወንዶች /10/ ብቻ ናቸው፡፡ ስለዚህ የጡት ካንሰር በብዛት የሚታየው ሴቶች ላይ ነው፡፡ የዚህ ምክንያቱም የጡት መጠኑ ሴቶች ላይ ትልቅ ሲሆን የወንዶች ጡት ግን ትንሽ እና በአይን የማይታይና በእጅ የማይዳሰስ በመሆኑ በካንሰር የመያዝ እድሉም ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን በጥቅሉ ትልቅ ጡት ያላቸው በካንሰር ሲያዙ ትንህ ጡት ያላቸው ግን አይያዙም ለማለት አይደለም፡፡ ሴቶች በተፈጥሮአቸው ጡታቸው ላይ ብዙ ሴሎች የሚገኙ ሲሆን ወንዶች ግን እንደጡታቸው ማነስ ሴሎቹም ትንሽ ናቸው፡፡

ሴሎች ሲፈጠሩ አስቀድሞውኑ ፕሮግራም ያላቸው በመሆናቸው በዚህ ጊዜ ይህን ያህል ማደግ፣ ይህን ያህል ጊዜ መኖር እንዲሁም በዚህ ጊዜ መሞት የሚል የጊዜ ቀመር አላቸው፡፡ ነገር ግን ሴሎቹ በካንሰር ሲያዙ ይህ በተፈጥሮ የተመደበላቸው የአኑዋኑዋር ባህርይ ይለወጥና ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ባህርይን ያመጣሉ፡፡ ስለዚህ የጡት ካንሰር ሲጀምር በጡት እና አካባቢው ቀድሞ ያልነበረ እብጠት ይታያል፡፡ እብጠቱም ጊዜ እየጨመረ በሄደ ቁጥር እያደገ በመሄድ ለዳሰሳም አስቸጋሪ ከማይሆንበት በግልጽ ከሚታወቅበት ደረጃ ይደርሳል፡፡ ዶ/ር አበበ አክለውም ሁሉም የጡት ክፍል በካንሰር የመያዝ እድል ቢኖረውም ነገር ግን 60 ኀያህል የጡት ካንሰር የሚያድገው በብብት ስር ነው ብለዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ካንሰር ሴሎቹ መሰራጨት ሲጀምሩ ጡቱ ላይ ከሚያብጠው እጢ በተጨማሪ እጅ ስር ያሉት እጢዎች አብረው ማበጥ ይጀምራሉ፡፡ በግዜ ካልተደረሰበትና በጣም ሲያድጉ ወደሌሎች የሰውነት ክፍሎች ይሄዳሉ፡፡ ለምሳሌ ሳንባ ላይ ሲሄድ ሳል ፣ደም የቀላቀለ አክታ ፣የደረት ውጋት ፣አየር ማስወጣትና ማስገባትን መከልከል የመሳሰለውን ጉዳት ያስከትላል፡፡ የካንሰር ሴል ወደ አጥንት ከሄደ በተለይም ጀርባ ላይ ያለው አከርካሪ አጥንት ላይ ከፍተኛ ሕመም ያስከትላል፡፡ ስለዚህ በጡት አካባቢ እብጠት እስኪያድግ መጠበቅ ሳይሆን አስቀድሞውኑ ክትትል በማድረግ እርምጃ መውሰድ ይገባል፡፡ ዋናው የጡት ካንሰር መለያ እብጠት ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ምንም አይነት ምልክትም ይሁን ስሜት ስለሌለው አስቀድሞ ማወቅ አስቸጋሪ ነው፡፡ እብጠቱ ገና ከአንድ ሳንቲ ሜትር በታች እያለ በአንዳንድ ምርመራዎች ማወቅ ሲቻል ከአንድ እስከሁለት ሴንቲ ሜትር ሲደርስ ግን በዳሰሳ ማወቅ ይቻላል፡፡

በዚህ ደረጃ ያለ የካንሰር እጢ ገና ያልተሰራጨ እና ማዳን የሚቻል ነው፡፡ ስለዚህም ከእብጠት ውጪ ሌላ ምልክት ስለሌለው ሴቶች እድሜያቸው ከአርባ አመት ከዘለለ እብጠት ቢኖርም ባይኖርም በየአመቱ ምርመራ አድርጎ ሁኔታውን ማወቅ ያስፈልጋል የሚባለው ፡፡ እንደ ዶ/ር አበበ ፈለቀ ማብራሪያ የጡት ካንሰር ደረጃ አለው፡፡ ደረጃውም ከአንድ እስከ አራት ይከፈላል፡፡ 1ኛ ደረጃ የሚባለው የጡት ካንሰር መጠኑ እጅግ ያነሰና በጡት ላይ ብቻ ያበጠ እጢ ነው፡፡ 2ኛ ደረጃ የሚባለው የጡት ካንሰር ጡት ላይ ያለው እጢም አደግ ይላል፡፡ እንደገናም ብብት ስር እብጠቶቹ ሊዳሰሱ ይችላሉ፡፡ 3ኛ ደረጃ የሚባለው የጡት ካንሰር ጡት ላይ ያለው እጢም ትልቅ ሲሆን ብብት ስር እና ዙሪያውን ያሉት እጢዎችም በጣም ጠንንራ እና ያደጉ ሆነው ይዳሰሳሉ፡፡ 4ኛ ደረጃ የሚባለው የጡት ካንሰር ከጡትም ከብብት ስርም አልፎ ወደሌሎች የሰውነት ክፍሎች የተሰራጩ ሲሆን ነው፡፡ ከ1995ዓ/ም እና ከ2000 ዓ/ም በፊት እንደአውሮፓውያኑ የጊዜ አቆጣጠር የጡት ካንሰር አደገኛ ነበር፡፡ በቅርብ ጊዜ ግን በመላው አለም የእኛን አገር ጨምሮ የጡት ካንሰርን ማዳን ተችሎአል፡፡ ስለዚህም ደረጃ አንድ እና ሁለትን ማዳን ወይንም በደንብ መቆጣጠር ከሚቻልበት የህክምና ጥበብ ተደርሶአል፡፡ ደረጃ ሶስትና አራት ትንሽ የሚከብዱ እና ማዳን ባይቻልም እድገታቸውን ግን መግታት ተችሎአል፡፡ በሕክምናው እርዳታም ሕይወትን በደንብ ማራዘም ይቻላል፡፡ የጡት ካንሰር የህመም ስሜት የሚገለጸው ጡት ላይ እብጠት ተገኘ ከሚል በስተቀር ሌላ ምንም ስሜት የለውም፡፡

ነገር ግን አልፎ አልፎ ማለትም ከመቶ አስር ያህል ታማሚዎች ጡት ላይ የህመም ስሜት አለኝ ወይንም ወተት በሚወጣበት ጫፍ ላይ ፈሳሽ ይታየኛል የመሳሰሉትን ስሜቶች ይገለጻሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አንዳንዴ ጡት መጠኑንና ቅርጹን ቀየረ የሚሉ እና ቆዳው ላይ አንደሚፈርጥ ነገር ወይንም ደም መሳይ ነገር አገኘሁበት የሚሉ ምክንያቶችም ለሐኪም ይቀርባሉ፡፡ ይህ ሁሉ ግን በጊዜው ህክምና ከተደረገለት ምንም ችግር የለውም፡፡ ችግር አለው የሚባለው ውስጥ ውስጡን በተለያዩ አካሉች ላይ ሲሰራጭ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜም በጣም ችላ ከተባለ ጡቱ ላይ ያለው እጢ እያደገ ሲመጣ እዛው ጡቱ ላይ ይቆስላል፡፡ ያ ከሆነ ኢንፌክሽን በመፍጠር ሽታ ያለው ፈሳሽ እና ደም ያመጣል፡፡ ለዚህም የሚሰጠው ሕክምና ቀደም ሲል በተቀመጠው ደረጃ መሰረት አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ላይ ከሆነ ኦፕራሲዮን እንዲሁም ኬሞራፒ መስጠት እና እንደአስፈላጊነቱ የጨረር ሕክምና ማድረግ ሲሆን እንደምግብ የሚያገለግሉ ሆርሞኖች በተለይም ኢስትሮጂን የሚባለው ከሰውነት ውስጥ እንዲጠፋ የሚዋጥ መድሀኒት ይሰጣል፡፡

ይሄ ሁሉ የህክምና ዘዴ በአገራችን የሚገኝ ሲሆን ነገር ግን ሕክምናው የሚሰጠው ውስን በሆነ ቦታ ማለትም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል መሆኑ እንደአንድ ችግር ይጠቀሳል፡፡ ኦፕራሲዮኑ የትኛውም ሆስፒታል ሊሰጥ የሚችል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ዋናው ችግር ሕክምናው ያለመኖሩ ሳይሆን ህክምናው የሚሰጥባቸው ቦታዎች ያለመስፋፋታቸው ነው ብለዋል ዶ/ር አበበ ፈለቀ /አሲስታንት ፕሮፌሰር/ የቀዶ ሕክምና ባለሙያ ፡፡

Published in ላንተና ላንቺ

በዓመት ከ1500 በላይ ፊልሞች ሰርቶ ለዕይታ በማቅረብ 2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ የሚያገኘው የህንዱ የፊልም ማዕከል ቦሊውድ፤ ሰሞኑን 100ኛ ዓመቱን እያከበረ ነው፡፡ የማዕከሉ ፊልሞች ዓለም አቀፍ ገበያ በየዓመቱ 10 በመቶ በማደግ ላይ እንደሚገኝ ያመለከተው “ዘ ታይምስ ኦፍ ኢንድያ” የተባለ ጋዜጣ፤ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የፊልሞቹ አመታዊ ገቢ 3.85 ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ ይችላል ብሏል፡፡ የቦሊውድ 100ኛ ዓመት በዓልን ምክንያት በማድረግ የወጡ ዘገባዎች እንደሚሉት፤ ፊልሞቹ ገቢያቸው እንዲጨምር የመላውን ዓለም ፍላጎት ባማከለ መልኩ መሰራት ያለባቸው ሲሆን የህንድ መንግስት በአክሽን እና በወሲባዊ ፊልሞች ላይ የሚያደርገውን የበዛ ሴንሰርሺፕ መቀነስ ይኖርበታል፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ አብዛኞቹ የቦሊውድ ፊልሞች አማካይ በጀት 1.5 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን በከፍተኛ የጥራት ደረጃ ለዓለም አቀፍ ገበያ የሚሰሩት ደግሞ በአማካይ እስከ 20 ሚሊዮን ዶላር በጀት ይመደብላቸዋል፡፡

በህንድ ፊልሞች ላይ የሚሳተፉት ህንዶች ብቻ ሲሆኑ ለወንድ ተዋናዮች ትልቁ ክፍያ በአንድ ፊልም እስከ 16 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን ለሴቶች ደግሞ 1.5 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ለፊልሞች ስራ የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ ረገድ የህንድ ባንኮች እና የፋይናንስ ተቋማት እንዲሁም በማከፋፈል ስራ ላይ የተሰማሩ የግል ኩባንያዎች ትልቅ ሚና አላቸው፡፡ የመጀመርያው የቦሊውድ ፊልም እ.ኤ.አ በ1913 ዓም ለእይታ የበቃው “ዳዳሼብ ፓላኬ” የተሰኘ ባለጥቁር እና ነጭ ቀለም ድምፅ አልባ ምስል ነው፡፡

በኮሜዲ ፊልሞቹ የሚታወቀው ዊል ፋሬል በሰራቸው ፊልሞች አትራፊ ባለመሆን የአንደኝነት ደረጃን እንደያዘ ፎርብስ መፅሄት አስታወቀ፡፡ ኮሜዲያኑ በሚተወንበት አንድ ፊልም ለተከፈለው 1 ዶላር 3 .30 ዶላር ብቻ በማስገባት ዝቅተኛ ትርፍ ያስመዘገበ ተዋናይ ሊሆን በቅቷል፡፡ በብዙ ፊልሞቹ ላይ ‹የትልቅ ህፃን› ገፀባህርይ እየተጫወተ የሚያሳያቸው ትዕይንቶች እና ንግግሮቹ ተደጋጋሚ እየሆኑ መምጣታቸው እና በአጠቃላይ አሰልቺ መሆናቸው ለተዋናዩ ትርፋማነት መቀነስ ምክንያቶች ናቸው፡፡

ፎርብስ አትራፊ ያልሆኑ 7 የሆሊውድ ተዋናዮችን ደረጃ ይፋ ባደረገበት ወቅት፤ ሁሉም ባለሙያዎች በቅርብ ጊዜ ትርፋማ እና ተፈላጊ በመሆን የማገገም ዕድል ላይኖራቸው እንደሚችል አመልክቷል፡፡ በተወኑባቸው ፊልሞች በተከፈላቸው 1 ዶላር ኢዋን ማክሪጎር 3.75፤ ቢሊ ቦብ ቶርቶን 4 ፤ኤዲ መርፊ 4.43፤ አስ ኪውብ 4.77፤ ቶም ክሩዝ 7.20 እንዲሁ ድሪው ባሪሞር 7.4 ዶላር በማስገባት ከዊል ፋሬል ቀጥሎ እስከ 7 ያለውን ትርፋማ ያለመሆን ደረጃ አግኝተዋል፡፡ በሆሊውድ ትርፋማ ከተባሉ ተዋናች አንዱ የሆነው እና በትራንስፎርመር ፊልሞች የሚታወቀው ሻይ ለበፍ በተከፈለው 1 ዶላር 160 ዶላር ያስገባል፡፡ በሙያ ዘመኑ ከ34 በላይ ፊልሞች ላይ የተወነው ዊል ፋሬል፤ በመላው ዓለም ያስገባው 2.034 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን በአንድ ፊልም በአማካይ እስከ 81.62 ሚሊዮን ዶላር በማስገኘት የሚታወቅ ነበር፡፡ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያስገቡ 7 ፊልሞችን የሰራው ኮሜድያኑ፤ የትወና ብቃቱን በአዲስ መልክ ካልቀየረ ከገበያው መውጣቱ አይቀርም እየተባለ ነው፡፡

ከሳምንት በፊት ላስቬጋስ ከተማ ውስጥ በሚገኘው ኤምጂኤም ግራንድ የተካሄደው የቢልቦርድ ሚውዚክ አዋርድ ስነስርዓት ከ12 ዓመታት በኋላ ከፍተኛውን የቲቪ ተመልካች እንዳገኘ ታወቀ። በካንትሪ ሙዚቃ ስልቷ የምትታወቀው ቴይለር ስዊፊት፤ ስምንት የቢልቦርድ ሽልማቶችን በመሰብሰብ ከፍተኛውን ስኬት አስመዝግባለች፡፡ በሌላ በኩል በቢልቦርድ ሚውዚክ አዋርድ ለሽልማት መታጨት እና ማሸነፍ ገበያ እንደሚያሟሙቅ የቢልቦርድ መፅሄት ዘገባ አመልክቷል፡፡ በቢልቦርድ ሚውዚክ አዋርድ ምሽት ላይ 16 አርቲስቶች ለሦስት ሰዓታት የዘለቀ የሙዚቃ ዝግጅት አቅርበዋል፡፡ የቢልቦርድ ሚውዚክ አዋርድ በ45 የሽልማት ዘርፎች ለአሸናፊዎች ሽልማት የሚሰጥበት ሲሆን ከሳምንት በፊት በኤቢሲ ጣቢያ የነበረውን የቀጥታ ስርጭት በሰሜን አሜሪካ 9.7 ሚሊዮን ተመልካቾች ተከታትለውታል፡፡

ይህ የተመልካች ብዛት ከ12 ዓመታት በኋላ ከፍተኛው ቁጥር ሆኖ ሲመዘገብ ከባለፈው አመት 28 በመቶ እድገት እንዳሳየ ተጠቁሟል፡፡ ብዙ ሽልማት በመሰብሰብ የተሳካላት ቴይለር ስዊፍት የዓመቱ ምርጥ አርቲስት፤ የአመቱ ምርጥ ሴት አርቲስት እና ምርጥ የካንትሪ ሙዚቀኛ በሚሉ ዘርፎች ተሸልማለች፡፡ ሪሃና እና ጎትዬ እያንዳንዳቸው 4 ፤ ማዶና እና ኒኪ ማናጅ እያንዳንዳቸው 3፤ እንዲሁም ጀስቲን ቢበር፤ ጄና ሪቬራ፤ ባወር እና ቶክ ማግ እያንዳንዳቸው 2 የቢልቦርድ ሽልማቶችን ተቀብለዋል፡፡ ጀስቲን ቢበር የቢልቦርድ አዋርድ ልዩ ሽልማት ማይልስቶን አዋርድን አግኝቷል፡፡

ወደ ሙዚቃ ኢንዱስትሪው ከገባች ገና ስድስት አመት ብቻ ያስቆጠረችው ቴይለር ስዊፍት፤ በመላው ዓለም 26 ሚሊዮን የአልበሞቿን ቅጂዎች ከመሸጧም በላይ 75 ሚሊዮን ዜማዎቿ በኢንተርኔት ዲጅታል ገበያ ተቸብችበዋል፡፡ በአጭር የስራ ዘመኗ ባገኘችው ስኬትም 165 ሚሊዮን ዶላር አካብታለች፡፡ በርካታ የሙዚቃ ሽልማቶችን የሰበሰበችውና 7 የግራሚ ሽልማቶችን ያገኘችው ቴይለር፤ ከቢልቦርድ ሽልማቶቿ በኋላ ከፍተኛ የገበያ መነቃቃት ሊኖረው እንደሚችል ቢልቦርድ መፅሄት አብራርቷል፡፡ ከሰባት ወር በፊት ለገበያ ያበቃችው አዲስ አልበም ‹ሬድ›ሲሆን በመላው ዓለም 5.8 ሚሊዮን ቅጂ ተሰራጭቷል፡፡

የአፍሪካ ሕብረት በቀድሞ ስም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተመሠረተበትን ሃምሳኛ ዓመት በማስመልከት የተዘጋጀ የመላ አፍሪካ ቪዥዋል አርት ጉባኤ እየተካሄደ ነው፡፡ ትናንት ጧት ተከፍቶ ዛሬ እንደሚጠናቀቅ በሚጠበቀው ጉባዔ ላይ ርእሰ ጉዳዩን የተመለከቱ 17 ጥናታዊ ጽሑፎች እንደሚቀርቡ አዘጋጁ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥነጥበባት ኮሌጅ አስታውቋል፡፡ የኮሌጁ ዲን መምህር አርቲስት ነብዩ ባዬ ለአዲስ አድማስ ጉዳዩን አስመልክቶ ሲናገሩ፣ የአፍሪካ አንድነት ከቅኝ አገዛዝ ለመላቀቅ በተደረገ ፖለቲካዊ ትግል ብቻ የመጣ ሳይሆን የኪነጥበባትም ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አስታውሰው “Pan African Performing and visual Art” በሚል ጭብጥ የሚካሄደው ጉባዔ በሥእል፣ በትያትር፣ በሙዚቃ፣ በሥነጽሑፍና በሌሎች ኪነጥበባዊ ዘርፎች የነበሩ አበርክቶዎች በጥናቶቹ እንደሚዳሰሱ ጠቅሰዋል፡፡ አቶ ነብዩ በተያያዘም በአፍሪካ ሥነጽሑፍ ከፍተኛ ድርሻ የነበረውና ከትናንት ወዲያ የቀብር ሥነሥርአቱ የተከናወነው ናይጄሪያዊ የአፍሪካ እንግሊዝኛ ሥነጽሑፍ አባት ቺንዋ አቼቤን ለመዘከር ከአንጋፋው ደራሲ ስራዎች የተወሰዱ ታሪኮች በትወና እንደሚቀርቡ ተናግረዋል፡፡

በቦሌ አካባቢ ጌቱ ኮሜርሻል ሴንተር ሕንፃ ላይ የተቋቋመው “ሆሊሲቲ ሲኒማ” ነገ ሥራ እንደሚጀምር የሲኒማ ቤቱ ባለቤት አቶ ኃይለማርያም ኪሮስ አስታወቁ፡፡ ነገ ከቀኑ 8 ሰዓት ሥራ አማርኛ ፊልም በማሳየት ሥራ የሚጀምረው ሲኒማ ቤት፣ በሕንፃው ስድስተኛ ፎቅ ላይ የሚገኝ ሲሆን 250 መቀመጫዎች ያሉት አዳራሽና ካፍቴሪያ አሉት፡፡ የሀገር ውስጥ ፊልም ማሳየቱን በመቀጠልም ከሰኞ እስከ አርብ በቀን ሁለት ፊልሞች፣ ቅዳሜና እሁድ ደግሞ በቀን ሦስት ፊልሞች እንደሚያሳይ ከባለቤቱ መግለጫ መረዳት ተችሏል። ሲኒማ ቤቱ በኮምፒዩተር በታገዘ የትኬት ሽያጭ በመጠቀም ወረፋን ያስቀረ ሲሆን የአካል ጉዳተኞችን ምቾት ታሳቢ በማድረግ እንደተሰራም ለማወቅ ተችሏል፡፡

Page 1 of 14