ተከታዩ ገጠመኝ በቤተዛታ ሆስፒታል (አዲስ አበባ ለገሀር) ያገኘናት እናት ገጠመኝ ነው፡፡
“...የእርግዝና ክትትል ለማድረግ ወደ ሆስፒታል ስሄድ በመጀመሪያ የተነገረኝ የኤችአይቪ ቫይረስ በደሜ ውስጥ መኖር ያለመኖሩን ማረጋጋጥ እንደሚገባኝ ነበር። ሐኪሞቹ ሲነግሩኝ እንደከባድ ነገር አልቆጠርኩትም፡፡ ምንም ችግር የለም ...እሺ... በማለት ምርመራውን አደረግሁ። ...ያገኘሁት ውጤት ግን ስሜቴን እንደ መጀመሪያው ይዤ እንድቀጥል አላስቻለኝም። ደነገጥኩ... ፈራሁ... ተርበተበትኩ...፡፡ የምክር አገልግሎት የምትሰጠኝ ነርስ በጣም ተቸገረች፡፡ የእኔን ስሜት ለመጠበቅ ብዙ ታገለች። እኔም በተቻለ መጠን ስሜቴን አሰባስቤ ወደቤት ተመለስኩ፡፡ ስሜቴን ሊጋራ የሚችል ማንም ሰው አልነበረኝም፡፡ ለማንም መንገር አልፈለግሁም፡፡ እናቴ፣ እህቴ፣ ወንድሞቼ ሁሉ ዙሪያዬን ቢኖሩም ...በቃ ...ለአንድ ሳምንት ብቻዬን በሬን ዘግቼ ተኛሁ፡፡ የሁዋላ ሁዋላ ግን አስቤ... አሰቤ.. እራሴን አበረታትቼ... ወደ ህክምናው ተመለስኩ፡፡
ከዚያ በሁዋላስ? የእኛ ጥያቄ ነበር፡፡
“...ከዚያ በሁዋላ ጉዳዬን ለእራሴ ይዤ... ከነርስዋ እና ከሐኪሜ ጋር ብቻ እየተወያየሁ ልጄን በሰላም ወለድኩ፡፡ እንደአለመታደል ሆኖ የወለድኩለት ሰው አብሮኝ የለም። ባሌም አይደለም፡፡ ለተወሰነ ጊዜ በነበረን የጉዋደኝነት ቆይታ ነበር ያረገዝኩት፡፡ ...ለነገሩ ገና ተመርምሮ ካልሆነ በስተቀር ልጁ የእርሱ ነው ለማለት አልችልም፡፡ ሌላም ጉዋደኛ ነበረኝ፡፡ ለማንኛውም... ችግሩ ሌላ ነው፡፡
ምንድነው ችግሩ?
“...ችግሩማ... ከወለድኩ በሁዋላ በዚያችው በአንድ ከፍል መኝታቤት ውስጥ እህቴ እናቴ ወንድሞቼ ሁሉ ከበውኛል፡፡ እንዴት አድርጌ ለልጄ የምሰጠውን መድሀኒት ልስጥ? የሚያዩትን ነገር ሁሉ ማወቅ ይፈልጋሉ። ለእራሴም በትክክል መድሀኒቴን መውሰድ ...ልጄንም መንከባከብ... አልቻልኩም፡፡ በተለይም እህቴ ለሁሉ ነገር በጣም ቅርቤ ስለሆነች እጅግ በጣም ነበር የተቸገርኩት። እንዳልነግራቸው ...ሁሉም ጥለውኝ ይሄዳሉ ብዬ ፈራሁኝ፡፡  ዝም እንዳልል ሐኪም በነገረኝ መመሪያ መሰረት ልጄንም እራሴንም መጠበቅ አቃተኝ። ስለዚህ ያለኝ አማራጭ የአራስነት ጊዜዬን ሳልጨርስ መነሳት እና እራሴን መርዳት ነበር...”
ከላይ ካነበባችሁት ገጠመኝ ልንማር የምንችለው ነገር ግልጽነት የሚባለው ነገር እና አድሎና መገለል ዛሬም በትክክል አልተለመዱም የሚለውን ነው፡፡ ገጠመኝዋን የገለጸችው እናት ቤተሰቦቼ ምናልባት መገለል ያደርሱብኛል ከሚል እስዋ በበኩልዋ ድብቅ በመሆንዋ ብዙ እንደተቸገረች ነው፡፡ ነገር ግን አድሎና መገለልን አስወግደን ግልፅነት በተመላበት ሁኔታ መኖር ብንችል ቀጣዩ ትውልድ ከኤችአይቪ ቫይረስ ነጻ እንደሚሆን እሙን ነው፡፡
ከኤችአይቪ ነፃ የሆነ ትውልድን በሚመለከት WHO በ2015 ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው በ2010 በኬንያ 20/ የአፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ የተሰበሰቡ ሲሆን ስብሰባው የተቀናበረው በUNFPA’UNAIDS’ UNICEF እና WHO ነበር፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በስብሰባው የተሳተፉት 20 የአፍሪካ ሀገራት በአለም ከሚቆጠረው ኤችአይቪ ቫይረስ ከእናት ወደ ልጅ መተላለፍ 85% የሚሆነውን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ በኬንያ በተደረገው ስብሰባ ህፃናቱን የማዳን ስራ እንደሌላ ስራ ቀለል ተደርጎ ሊታይ የማይገባውና በየአመቱ በመላው አፍሪካ በቫይረሱ የሚያዙ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ህፃናትን ህይወት ለማዳን እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ተሰምሮበታል፡፡
ዩኒሴፍ በ2012 ባወጣው መረጃ በኢትዮጵያ የኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ከሚገኝ እናቶች መካከል 24% የሚሆኑት ብቻ ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ ለማድረግ የሚሰጠውን ህክምና እንደሚያገኙ ጠቁሟል፡፡ በእርግዝና ወቅት ለእናቲቱ የሚሰጠው የኤች አይቪ የምክር አገልግሎት ህክምናውን በማስፋት እንዲሁም ከቫይረሱ ነፃ የሆነ ልጅ እንዲወለድ በማድረግ እረገድ የሚጫወተው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው።
ኤችአይቪ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የማድረግ እርምጃ ባደጉት ሀገራት ትልቅ ለውጥ እንዳመጣና ከሰሀራ በታች ባሉት የአፍሪከ ሀገራት ግን በየአመቱ (300000) ሶስት መቶ ሺህ ያህል አዲስ ህፃናት በቫይረሱ እንደሚያዙ የአለም የጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡
የWHO መረጃ የሚከተለውን እውነታ ያሳያል፡፡
በ2008 የወጣ መረጃ እንደሚያሳየው በአለም 45% የሚሆኑ እርጉዝ ሴቶች ብቻ ፀረ ኤችአይቪ ህክምና መውሰዳቸው ተረጋግጧል፡፡
በኢትዮጵያ ከኤችአይቪ ቫይረስ ጋር የሚኖሩ እና ልጆቻቸውን ከቫይረሱ ለመከላከል ART የሚወስዱ እናቶች (18269) አስራ ስምንት ሺህ ሁለት መቶ ስድሳ ዘጠኝ ይሆናሉ፡፡
ከቫይረሱ ጋር ይኖራሉ ተብለው የሚገመቱ እና ART መጠቀም ያለባቸው እናቶች (ልጆቻቸውን ከቫይረሱ ለመከላከል) VNAID  እና WHO ባወጡት አሰራር መሰረት ወደ (33000) ሰላሳ ሶስት ሺህ ይሆናሉ፡፡
ስለዚህ ART ተጠቃሚ እርጉዝ እናቶች 55% እንዲሆኑ ይጠበቃል፡፡
                         (World health organization, 2014)
ኤችአይቪ ከእናት ወደ ልጅ ሊተላለፍ የሚችለው በእርግዝና፣ በምጥ፣ በወሊድ እና ጡት በማጥባት ሲሆን ስያሜውም MTCT  ከእናት ወደ ልጅ የሚተላለፍ ይሰኛል፡፡ ይህንን ለመከላከል በሕክምናው ዘርፍ የሚሰራው ስራም PMTCT ወይም ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ መከላከል በሚል ስራ ላይ ውሏል፡፡ የ PMTCT አገልግሎት በማይሰጥበት ሁኔታ ኤችአይቪ ቫይረስ ከእናት ወደ ልጅ የሚኖረው መተላለፍ እንደየ ሀገራቱ ሁኔታ ከ15-45% ሊደርስ የሚችል ሲሆን የመከላከሉ ስራ ውጤታማ ከሆነ ግን ስርጭቱ እስከ 5% ይወርዳል ተብሎ ይታሰባል፡፡
አለማቀፉ የጤና ትምህርት እና ስልጠና ማእከል (I-TECH­) ከUS president’s emergency plan for HIV AIDS Relief ጋር በመተባበር የኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ለሚገኝ ነብሰጡር እናቶች ድጋፍ ይሰጣል። ይህ ፕግራም ባሳለፍነው የፈረንጆቹ አመት ማለትም በ2014 ያበቃ ሲሆን በአክሱም፣ ጎንደር እንዲሁም ዱፍቲ የሚገኙ እናቶች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ ተጠቃሚ ከሆኑ እናቶች መካከል አንዱዋ የሚከተለውን ምስክርነት ሰጥታለች፡፡
“...አለምነሽ ቫይረሱ በደሟ እንዳለ ያወቀችው በፈረንጆቹ 2009 ወደ አረብ ሀገር ለመሄድ ባደረገችው ምርመራ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ወደ ውጪ የመሄድ ህልሟ እውን ሳይሆን ቀርቷል፡፡ በ2013 የመጀመሪያ ልጇን ስታረግዝ ትልቁ ጭንቀቷ የነበረው የሚወለደው ህፃን እንዴት ከቫይረሱ ነፃ ሆኖ ይወለዳል? የሚል ነበር። ...ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ሆኖ ከቫይረሱ ነፃ የሆነ ልጅ መውለድ እንደሚቻል ሳውቅ በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ ምናልባት የዚህ ፕሮግራም አካል ባልሆን ኖሮ ልጄ ነፃ ሆና ላትወለድ ትችል     ነበር፡፡ ዛሬ ሂያብ የሰባት አመት ታዳጊ ሆናለች፡፡”
በኢትዮ ጠቢብ ሆስፒታል ያነጋገርናት ሲ/ር አልጣሽ ደሳለኝ እንደምትመሰክረው እናቶች ለምርመራ ሲመጡ የሚያሳዩት ፊትና ከውጤት በሁዋላ የሚኖራቸው ምላሽ እጅግ ይለያያል፡፡ ይህንን በምሳሌ ስታስረዳም...
“...አንዲት እናት ለእርግዝና ክትትል ስትመጣ በመጀመሪያው የምክር አገልግሎት ጊዜ ...የኤች አይቪ ቫይረስ በደምዋ ውስጥ ቢገኝ ምንም ማለት እንዳልሆነ ...ከባለቤቷ ጋር በሰላም ተፈቃቅራ እንደምትኖር... ልጅዋንም በሰላም ተረጋግታ እንደምታሳድግ ነበር የነገረችኝ፡፡ ነገር ግን ልክ የደም ውጤትዋ ሊነገራት ሲል ሰውነትዋ ሲደፈርስ ይታይ     ነበር፡፡ በጣም ለማግባባት ሞክሬ ሁኔታውን ስነግራት ማመን በሚያስቸግር ሁኔታ ነበር የተለወጠችው፡፡ እዚያው እኔው ፊት ...ባለቤተዋን መውቀስ... ማልቀስ... ጀመረች፡፡ ለማባበል ብዙ ብሞክርም አልሰማችኝም፡፡ ከዚያ በሁዋላ አልተመለሰችም፡፡ በስልክ... እንዲሁም በተለያየ መንገድ ብከታተልም የት እንደገባች ማወቅ አልቻልኩም፡፡ ለካስ     ይህች ሴት ስልኩዋን ከስራ ውጭ አድርጋ በቀጥታ ወደቤተሰቦቿ ጋ ወደገጠር ነበር ያመራችው፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በሁዋላ እራስዋ በአካል ወደ ሆስፒታላችን መጥታ የነገረችኝ ...ሁኔታውን ያወቁት በዚያ የሚኖሩ ወንድሞቿ አግባብተው በቅርብ ወደሚገኘው ጤና ጣብያ እና ሆስፒታል እያመላለሱ... እያግባቡና እያባበሉዋት ልጅዋን በሰላም እንድትወልድ ማድረጋቸውን ነው፡፡ በሁዋላም ልጁ ከቫይረሱ ነጻ መሆኑ እስኪረጋገጥ     እዛው ቆይታ ልጁን ለቤተሰቦቿ ትታ መምጣትዋን ነገረችኝ፡፡ ስለባለቤትዋ ያለውን     ሁኔታም ስጠይቃት... እሱንማ ያኔውኑ ነው የፈታሁት... ምክንያቱም ዋሽቶኛል... ለካስ እሱ አስቀድሞውኑም ቫይረሱ በደሙ ውስጥ እንደሚኖር ያውቅ የነበረና በድብቅም መድሀኒት የሚወስድ ሰው ነበር፡፡ በቃ... አይኑን ማየት አልፈልግም ብላ ለእራስዋ ወዴት     መሄድ እንዳለባትና ምን ማድረግ እንዳለባት ጠይቃኝ መክሬአታለሁ፡፡”
ከዚህችኛዋ እናት ታሪክ የምንረዳው አሁንም ግልጽነት በጎደለው መንገድ ባለቤቷ እንደበደላት እና ...ነገር ግን በቤተሰቦቿ በኩል ያለው እውነታ መገለልን ያስወገዱ እና ነገሮችን በአግባቡ የተረዱ መሆናቸውን ያመላክታል፡፡
ይቀጥላል

Published in ላንተና ላንቺ

     በስፖርቱ ዓለም የላቀ ብቃት ላሳዩ እና በስኬታቸው ከፍተኛ አድናቆት ላገኙ አትሌቶች በሚሸለሙበት ዓመታዊው የላውረስ የምርጥ ስፖርተኛ ሽልማት አትሌት ገንዘቤ ዲባባ የመጀመርያዋ ኢትዮጵያዊ ተሸላሚ አትሌት ሆነች፡፡ በአትሌቲክስ የላውሬስ የዓመቱ ምርጥ ሴት ስፖርተኛ ሆና የተመረጠችው ገንዘቤ ባለፈው ዓመት በሁለት ሳምንታት ውስጥ ሶስት ክብረ ወሰን መስበርዋ፤ በ5000 እና በ2000 ሜትር የዓመቱን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገቧ እና በ3ሺ ሜትር የኢንተርኮንትኔንታል ሻምፒዮና በመሆኗ ነበር፡፡
በ2015 በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር የዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ ከመጨረሻዎቹ ሶስት እጩዎች አንዷ ለመሆን የበቃችው የመካከለኛ ርቀት ምርጥ ሯጭ ገንዘቤ ዲባባ፤ ለመጀመርያ ጊዜ የላውረስ ሽልማትን የተጎናፀፈች ኢትዮጵያዊ አትሌት ሆናለች፡፡ በተያያዘ ሰርቢያዊው ሜዳ የቴኒስ ተጫዋች ኖቫክ ጆኮቪች የላውሬስ የዓመቱ ምርጥ ወንድ ስፖርተኛ ሆኗል። ለ27 ዓመቱ ኖቫክ ድጅኮቪች የላውረስ ሽልማት ለሁለተኛ ጊዜ ያገኘው ሲሆን የመጀመርያውን የተሸለመው በ2011 እኤአ ላይ ነበር፡፡ ታዋቂው የሜዳ ቴኒስ ኮከብ ኖቫክ በ2015 እኤአ ላይ በተለያዩ ውድድሮች ከ5 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሽልማት ገቢ ሲያስገባ፤ በ2014 እኤአ ላይ ደግሞ 11.6 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በማስመዝገብ ከሜዳ ቴኒስ ተጨዋቾች የመጀመርያ ነበር፡፡  ኖቫክ በፎርብስ መፅሄት የሃብት መጠኑ እስከ 90 ሚሊዮን ዶላር ተተምኖለታል፡፡
ለዓመታዊው የላውረስ ሽልማት በሻንጋይ ከተማ በሚገኘው ግራንድ ቲያር አዳራሽ በተዘጋጀው ስነስርዓት ላይ ትልልቅ የሆሊውድ ዝነኛ ተዋናዮች ተገኝተው ነበር፡፡ ከመካከላቸው በሙላቱ አስታጥቄ የማጀቢያ ሙዚቃ በተሰራለት ብሮከን ፍላወርስ ፊልም ላይ የተወነው እውቅ ተዋናይ ቢል ሙራይ እንዲሁም ሱፕር ማን የተባለውን ገፀባህርይ የሚተውነው ሄነሪ ካቪል ይጠቀሳሉ፡፡ የሽልማት ስነስርዓቱ በ100 አገራት የቀጥታ ቴሌቭዥን ስርጭት ሲኖረው ከመሰል የሽልማት ስነስርዓቶች በሁለተኛ ደረጃ የሚቀመጥ ተከታታይ በማግኘት እስከ 2 ቢሊዮን ተመልካች እንደታደመው ተወስቷል፡፡ በላውረስ ሽልማት ከሚጠቀሱ ሌሎቹ አሸናፊዎች መካከል የዓመቱ ምርጥ ቡድን ሽልማትን ያገኘው የዓለም ዋንጫ አሸናፊ የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ይጠቀሳል፡፡
የላውሬስ ሽልማት በየዓመቱ በስፖርቱ ጎልቶ ለወጡ ስፖርተኞች የሚሰጥ የክብር ሽልማት ሲሆን ከተለያዩ የዓለም ስፖርቶች የተውጣጡና የላውረስ አካዳሚ አባላት የሆኑ 50 ዝነኛ የዓለማችን ስፖርተኞች ምርጫውን ያከናውናሉ፡፡ በላውረስ አካዳሚ ካሉ ትልልቅ ስፖርተኞች ጀርመናዊው የእግር ኳስ ቄሳር ፍራንዝ ቤከንባወር፤ ታዋቂው የሜዳ ቴኒስ ኮከብ ቦሪስ ቤከር፤፤ ዝነኛው ራሽያዊ የምርኩዝ ዘላይ ሰርጄይ ቡብካና እንግሊዛዊው የእግር ኳስ ባለታሪክ ቦቢ ቻርልተን ይገኙበታል፡፡
የ24 ዓመቷ ገንዘቤ በመካከለኛ ርቀት 1500፤ 3000 እና 5000 ሜትር ውድድሮች በትራክ እና በቤት ውስጥ ውድድሮች 8 የሩጫ ዓመታት አሳልፋለች፡፡ ያስመዘገበቻቸው ሪከርዶች እና የሜዳልያ ውጤቶች ከዚህ በታች ቀርበዋል፡፡
በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና 2 የወርቅ ሜዳልያዎች በ1500 እና በ3000 ሜትር
በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና 2 የወርቅ ሜዳልያዎች በወጣቶች ውድድር
በዓለም ወጣቶች ሻምፒዮና 1 ወርቅና 1 ብር ሜዳልያ በ5ሺ ሜትር
በአይኤኤፍ ኮንትኔንታል ካፕ 1 ወርቅ ሜዳልያ
3 የዓለም ሪከርዶች በቤት ውስጥ አትሌቲክስ
1500 ሜትር 3፡55.17 በካርልሱርህ ጀርመን በ2014 እኤአ
3000 ሜትር 8፡16.6 በስዊድን ስቶክሆልም 2014 እኤአ
5000 ሜትር 14፡18.86 በስዊድን ስቶክሆልም 2015 እኤአ
6 የአፍሪካ አትሌቲክስ ሪከርዶች
በ1500ና በ5000 ሜትር ትራክ፤ በ2 ማይል፤ እንዲሁም በቤት ውስጥ አትሌቲክስ በ1500፤ በ3000 እና በ5000 ሜትር ውድድሮች

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከአሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ ጋር የተፈራረመው የሁለት ዓመታት የኮንትራት ውል እንዲቋረጥ ተደረገ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከወር በኋላ በተለያዩ አህጉራዊ ውድድሮች የሚሳተፍ ሲሆን የዋና አሰልጣኙ ቅጥር ዝግጅቶችን በትኩረት ለማድረግ ወሳኝ ይሆናል፡፡ የዋና አሰልጣኙ ኮንትራት የፈረሰው ሁለቱ ተዋዋይ ወገኖች በደረሱበት የጋራ ስምምነት መሠረት እንደሆነ ያመለከተው የፌዴሬሽኑ ህዝብ ግንኙነት፤ የአሰልጣኙ ስንብት በመከባበር ስሜትና በሠለጠነ አግባብ እንደተፈፀመ እንዲሁም ውሉን በማቋረጥ ሊከሰት የሚችለውን ውጣ ውረድ በማስወገድ ወደፊት በትብብር  ለመሥራት የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚያስች ነው ብሏል፡፡
የውል ስምምነቱ መቋረጡን ተከትሎ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አንድ ዓመት በብሄራዊ ቡድኑ ለሰሩት አሠልጣኝ   ማሪያኖ ባሬቶ ተጨማሪ የሦስት ወር ደመወዝ ከፍሏቸዋል፡፡ ፌደሬሽኑ እና ማርያኖ ባሬቶ በተተኪ ወጣቶች ላይ የተጀመረው የእግር ኳስ ልማት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግ በመተባበር መንፈስና በጋራ ለመሥራት እንደተስማሙ ተገልፆ፤ አሠልጣኙ ወጣት ተጫዋቾች ከፍተኛ ሥልጠና እንዲያገኙ ለማድረግ የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው ለመቀጠል ቃል መግባታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሌላ በኩል ፖርቱጋላዊው ማርያኖ ባሬቶ በተለይ ለሱፕር ስፖርት በሰጡት አስተያየት በኢትዮጵያ ጥሩ እየሰሩ እንደነበር ተናግረው፤ ከቤተሰብ ጋር ለረጅም ጊዜ በሚያራርቀው ሃላፊነታቸው የተፈጠሩ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለስንብታቸው  እንደ ዋና ምክንያታቸው ጠቅሰውታል፡፡  በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝነት ሲቀጠሩ ገና ከጅምሩ  በፌደሬሽኑ በኩል የተፈጠሩባቸው አንዳንድ ውስብስብ ችግሮች መኖራቸውን በማንሳትም በወቅቱ ከፌደሬሽኑ ይፈልጓቸው የነበሩ ድጋፎች በማነሳቸው ስራቸውን ወዲያውኑ ለመልቀቅ አመንትተው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በስንብታቸው ምንም ፀፀት እንደማይሰማቸው፤ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወጣት ተጨዋቾችን በማሳደግ ባበረከቱት አስተዋፅኦ እንደሚደሰቱ ለሱፕር ስፖርት ያሳወቁት ማርያኖ ባሬቶ፤ ለቡድኑ መጭው ጊዜ የተሳካ እና በውጤት ያማረ እንዲሆንም ተመኝተዋል፡፡
የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ በበኩላቸው ለሱፕር ስፖርት ሲናገሩ የአሰልጣኙ የቅጥር ኮንትራት የመጀመርያ ምዕራፍ ሊገባደድ የቀሩት 10 ቀናት እንደነበሩ ጠቅሰዋል፡፡ ከዋልያዎቹ በኋላ ለማርያኖ ባሬቶ  በስራ ዘመናቸው መልካሙን ሁሉ እንዲገጥማቸው የተመኙት ፕሬዝዳንቱ ምስጋናቸውን ለአሰልጣኙ አቅርበዋል።   የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት ስለ ብሄራዊ ቡድኑ ምትክ አሰልጣኝ ቅጥር ከሱፕር ስፖርት ለቀረበላቸው ጥያቄ ዝርዝር  ምላሽ ከመስጠት  ተቆጥበዋል፡፡
ማሪያኖ ባሬቶ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በፊት በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ያሰለጠኑት ብቸኛው የጋና ብሄራዊ ቡድን ሲሆን የሰባት ወራት ቆይታ አድርገዋል፡፡ ከጋና እግርኳስ ማህበር ጋር የተስማሙትን የአሰልጣኝነት ውል ህገወጥ በሆነ መንገድ በማፍረስ ከሃላፊነት በመልቀቃቸው ፊፋ በጉዳዩ ላይ ጣልቃ በገብቶ ውል በማፍረሳቸው  83 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ለጋና እግርኳስ ማህበር እንዲከፍሉ ቀጥቷቸው ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፌዴሬሽኑ ማርያኖ ባሬቶን ካሰናበተ በኋላ ሃላፊነቱን የሚረከብ ባለሙያ ከየት እንደሚገኝ የታወቀ ነገር የለም፡፡ በተለያዩ ሁኔታዎች ለብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝነት ላለው  ክፍት የስራ ቦታ ላይ ሁነኛ ምትክ ለማግኘት አጠያያቁ ይሆናል። የመጀመርያው ባለሙያው የተፈለገው በብዙ አገራት የእግር ኳስ የውድድር ዘመኑ አጋማሽ ላይ ባለበት ወቅት መሆኑ ብቁ አሰልጣኝ የማግኘት እድሉን ስለሚያጠብበው ሲሆን፤ በሌላ በኩል በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ያው የአመራር ክፍተት እና ልዩነት የቅጥሩን ስኬታማነት እንደሚያስተጓጉል አስተያየት እየ

ዓለም አቀፍ የስፖርት ቀን ለልማትና ለሰላም በሚል መርህ  በአዲስ አበባ ስታዲየም በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ታወቀ፡፡ በኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ የሚከበረው የስፖርት ቀኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላምና የዕድገት መርሆችን መሠረት ያደርጋል።  ባለፈው ዓመት ዓለም አቀፍ የስፖርት ቀን ለሰላምና ለልማት በኢትዮጵያ  እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና በኢትዮ-ጀርመን የረጅም ጊዜ የእግር ኳስ ኘሮጀክት ትብብር አማካኝነት ለመጀመሪያ ጊዜ በድምቀት ተከብሯል፡፡ ለስፖርት ቀኑ በወጣው ኘሮግራም መሠረት በስድስት የወንዶችና ሴቶች ታዳጊ እግር ኳስ ክለቦች የእግር ኳስ ውድድሮች ይካሄዳሉ፡፡  በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የ24 ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ ሀገሮች አምባሳደሮችና ዲኘሎማቶች ፣የፌደራል ስፖርት ከሚሽን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ እግር የፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም  ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የስፖርት ቤተሰቦች ተሳታፊና ተካፋይ እንደሚሆኑ ለዝግጅት ክፍላችን የደረሰው መረጃ ያመለክታል፡፡  ስፖርት በተለይም እግር ኳስ ሕዝቦችን የማቀራረብ፣ ወዳጅነትን የማጠናከር፣ ፍትሃዊነትን የማስፈን፣ ልዩነቶችን የማቻቻልና መከባበርን የማስፈን ጉልህ ፋይዳ እንዳለው የጠቀሰው መግለጫ፤ ዓለም አቀፍ የስፖርት ቀን ለሰላምና ለልማት በዓል ይህን ከግምት በማስገባት እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡

 ለኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ገቢ ማሰባሰቢያ የሚሆንየ 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ከሳምንት በኋላ ሊካሄድ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቡናና የስፖርት ቤተሰቦች የክለቡን የገቢ አቅም ለማጠናከር የጎዳና ላይ ሩጫው በየዓመቱ እንዲደረግ ፍላጎት አላቸው፡፡ በሩጫው ላይ ለመሳተፍ ምዝገባው ሜክሲኮ ቡናና ሻይ የክለቡ ፅ/ቤት እየተከናወነ ሲሆን የመሮጫው ቲሸርት ዋጋ 150 ብር ነው፡፡ የ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫው መነሻው ለክለቡ የመኖርያ ካምፕ በሚገነባበት እና ለስታድየም በተሰጠው ቦታ  ላይ እንደሆነ አዘጋጆቹ ገልፀው፤ ጀሞ ኮንደሚንየም ፣ ሚካኤል አደባባይ ፤ አየር ጤና አደባባይ የሚያቋርጣቸው ቦታዎች እንደሆኑና ዞሮ መድረሻው የተነሳበት ቦታ ላይ እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡
በ1975 ዓ.ም በተጠናከረ መልኩ የተመሠረተው የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ  የተጨዋቾች መኖርያ ካምፕን ለመገንባት እና የስታድዬም ስራውን ለማነሳሳት በጎዳና ላይ ሩጫው ከፍተኛ መነቃቃት እንደሚፈጥር ተጠብቋል፡፡
ሃበሻ ስፖርት ከተባለ ድረገፅ ስለክለቡ ታሪክ ከተፃፈው ዘገባ ለመረዳት እንደተቻለው የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ እንደ አብዛኛዎቹ የሀገራችን ክለቦች የራሱ የሆነ የውድድር ሜዳ የለውም፡፡ በ1997 ዓ.ም የራሱን ስታዲየም ለመገንባት ከአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት 35.000 ካ.ሜ ቦታ ተረክቧል፡፡ በሌላ በኩል የቡና ክለብ በቀደምት ጊዜያት በቡና ገበያ ኮፕሬሽን ቅጥር ግቢ በኋላም ከመንግስት በጊዚያዊነት በተሰጠው ቦታ የተገነባ የተጨዋቾች መኖሪያ ካምፕ ነበረው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በወር 18.000ብር ከግለሰብ የተከራየው የተጨዋቾች መኖሪያ ካምፕ አለው፡፡
ክለቡ የራሱን መኖሪያ ካምፕ መገንባት እንዲችል ለአዲስ አበባ መስተዳድር የቦታ ጥያቄ አቅርቧ 3.000 ካሬ ሜትር ቦታ አግኝቷል፡፡ በዚህ ዓመትም 10ሚሊዮን ብር በመመደብ ጅምናዚየምን ያካተተ ዘመናዊ የተጨዋቾች መኖሪያ ካምፕ ለመገንባት አስፈላጊው የዲዛይን ስራ አጠናቆ ወደ ትግበራ ለመግባት  በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ የጎዳና ላይ ሩጫው እነዚህን እንቅስቃሴዎች ለመደገፍ እና ለማነቃቃት እንደተዘጋጀ ተገልጿል፡፡
ከተለያዩ የክለቡን ታሪክ ከሚያወሱ ምንጮች ለመገንዘብ እንደተቻለው የኢትዮጵያ ቡና ክለብን በባለቤትነት የሚያስተዳድሩት ማህበራት እና ድርጅቶች ከስምንት በላይ ይሆናሉ፡፡ እነሱም የቡና ላኪዎች ማህበር፤ የቡና አቅራቢዎች ማህበር፤ የኦሮሚያ ቡና ገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበር፤ የቡና ቆዪዎች ማህበር፤ የቡና ግሮዎርስ ፕሮዲውስ ኤክስፖርተርስ አሶሴሽን፤ የሀገር ውስጥ ቡና ንግድ ማህበር፤ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ማህበርና ሐበሻ ቢራ አክሲዮን ማህበር  ናቸው፡፡  የቡና ማህበራቱ ከሁለት ዓመት በፊት በቶን 5ብር የነበረውን የመዋጮ ድጋፍ ወደ 30 ብር ከፍ በማድረጋቸው  የክለቡ ዓመታዊ በጀት ወደ 20.000.000 (ሃያ ሚሊዮን) እንዳደገ ታውቋል፡፡
በአፍቃሪ ደጋፊዎች ብዛት ከኢትዮጵያ ክለቦች ግንባር ቀደም ሆኖ የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ በቀድሞው የኢትዮጵያ ሻምፒዮና በአሁኑ ኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ እኩል አንድ ጊዜ የዋንጫ ተሸላሚ ነበር። በኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ውድድር አምስት ጊዜ፤ በኢትዮጵያ ክለቦች አሸናፊዎች አሸናፊም ለስድስት ጊዜ የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል፡፡ በኢንተርናሽናል ውድድር ተሳትፎው ደግሞ በሦስቱ አህጉር አቀፍ የክለቦች ውድድርና በአንድ የምስራቅ አፍሪካ ክለቦች ዋንጫ ውድድር በመወከል ተወዳድሯል፡፡
በዋናው የአፍሪካ ክለቦች ዋንጫ ሁለት ጊዜ በምስራቅና መካከለኛው ክለቦች ዋንጫ አንድ ጊዜ ኢትዮጲያን በመወከል ሲሳተፍ በኮንፌዴሬሽን ካፕና አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ግን ከሁለት ጊዜ በላይ ተሳታፊም ነበር፡፡

 የግድያ ቪድዮዎቹ አለማቀፍ ስነ-ልቦናዊ ተጽዕኖ እየፈጠሩ ነው
      አይሲስ የተባለው አሸባሪ ቡድን እያሰራጫቸው የሚገኙና በተለያዩ አገራት ዜጎች ላይ የፈጸማቸውን አሰቃቂ ግድያዎች የሚያሳዩ የቪዲዮ ምስሎች፣ ቡድኑ በአለማቀፍ ደረጃ የከፈተው የስነልቦና ጦርነት አካል ናቸው መባሉን አሶሼትድ ፕሬስ ዘገበ፡፡
የጀርመን የአገር ውስጥ የስለላ ተቋም ሃላፊ ሃንስ ጆርጅ ማሰን እንዳሉት፣ አገራት እነዚህ አሰቃቂ የግድያ ቪዲዮዎች በወጣት ዜጎቻቸው ላይ የሚያሳድሩትን የስነልቦና ተጽዕኖ ለመቅረፍ የራሳቸውን እርምጃ መውሰድ ይገባቸዋል፡፡
የቪዲዮ ምስሎቹ የአሸባሪውን ቡድን የጥፋት ፕሮፓጋንዳ በወጣቱ ትውልድ ልቦና ውስጥ የሚያሰርጹ ናቸው ያሉት ጆርጅ ማሰን፤ ምስሎቹ ለእይታ ሲበቁ የቡድኑን የጥፋት ተልዕኮ አሰቃቂነት የሚያሳዩ መልዕክቶችን አብሮ ማቅረብ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ቡድኑ በቅርቡ በጀርመን ለሚገኙ ደጋፊዎቹ ባሰራጨው የቪዲዮ መልዕክት፣ ባለፈው ጥር ወር በፈረንሳይ የተፈጸመውን ዓይነት ጥቃት እንዲፈጽሙ ጥሪ አቅርቧል ያለው ዘገባው፣ የጀርመን የደህንነት ባለስልጣናትም መልዕክቱን ያስተላለፈው ትውልደ ጀርመናዊው አለማቀፍ አሸባሪ ዴኒስ ኩስፐርት መሆኑን ማረጋገጣቸውን አስታውሷል፡፡
ሲኤንኤን በበኩሉ፤አይሲስ እያሰራጫቸው ያሉት የግድያ ቪዲዮዎች በአለማቀፍ ደረጃ ፍርሃትን እያነገሰ እንደሚገኝና የቡድኑ ቪዲዮዎች ሌሎችም ለመሰል ጥፋቶች እንዲነሳሱ ተጽዕኖ እንደሚያደርግ ዘግቧል፡፡
በሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ የስነልቦና መምህር ፕሮፌሰር አሪ ክሩግላንስኪ እንዳሉት፤ የአይሲስ የአሰቃቂ ግድያ ቪዲዮዎች፣ ግለሰቦች በግጭት ወቅት  ተመሳሳይ ጥቃቶችን እንዲፈጽሙ የሚያነሳሳ ስነልቦናዊ ጫና የመፍጠር ሃይል አላቸው፡፡
የጀሃዲስቶች አሰቃቂ ግድያዎች በቪዲዮ ምስሎች በስፋት መሰራጨታቸው፣ ግለሰቦች ከዚህ ቀደም የማያስቡትን አንገት ቀልቶ መግደል የሚል የጭካኔ ሃሳብ ትኩረት ሰጥተው ማሰብ እንዲጀምሩ በማድረግ ረገድ በአለማቀፍ ደረጃ አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠረ ነው ብለዋል ፕሮፌሰሩ፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ልትፈጽም እየተዘጋጀች ነው
  በዚህ ወር ብቻ ከ1 ሺህ በላይ ስደተኞች በሜዲትራኒያን ባህር ሞተዋል
በእሁዱ የጀልባ አደጋ የተጠረጠሩ ፍርድ ቤት ቀርበዋል
       የሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ አገራት ለመግባት ሲሞክሩ ለህልፈተ ህይወት በሚዳረጉ ስደተኞች ዙሪያ ለመምከር ከትናንት በስቲያ በብራስልስ አስቸኳይ ስብሰባ የጠሩት የአውሮፓ አገራት መሪዎች፣ ሊቢያውያን ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን ለማጥቃትና አካባቢውን ለማረጋጋት የሚያስችል ወታደራዊ ዘመቻ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ አልጀዚራ ዘገበ፡፡
በዚህ አመት ብቻ 36 ሺህ ያህል የተለያዩ አገራት ዜጎች ባህር አቋርጠው በስደት ወደ ጣሊያን፣ ማልታ እና ግሪክ እንደገቡ የጠቆመው ዘገባው፣ የአውሮፓ መሪዎች ስደተኞችን በህገወጥ መንገድ የሚያጓጉዙ ጀልባዎችን ተከታትሎ በመለየት በቁጥጥር ስር የሚያውልና በሊቢያውያን ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ላይ እርምጃ የሚወስድ የአውሮፓ ጥምር ወታደራዊ ዘመቻ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል ብሏል፡፡
ባለፈው እሁድ ከሊቢያ በመነሳት ሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጣ ወደ ጣሊያን ስትቃረብ በሰመጠችው ጀልባ ከ800 በላይ የተለያዩ አገራት ዜጎች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን ተከትሎ አስቸኳይ ስብሰባ ያደረጉት መሪዎቹ፣ በሜዲትራኒያን ባህር ስደተኞችን ለማዳን ለሚከናወኑ ተግባራት የሚሰጡትን የገንዘብ ድጋፍ በሶስት እጥፍ ለማሳደግ የተስማሙ ሲሆን በወር በድምሩ 9.7 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብተዋል፡፡
የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን ስደተኞችን ለመታደግ የሚሰሩ ስራዎችን ለማገዝ የሚውሉ ሶስት ሄሊኮፕተሮችንና ሁለት መርከቦችን ለመስጠት ቃል ሲገቡ፣ ጀርመንና ፈረንሳይም እያንዳንዳቸው ሁለት መርከቦችን ለመስጠት ቃል መግባታቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡
የውሮፓ አገራት መሪዎች በህገወጥ ስደት ለህልፈተ ህይወት የሚዳረጉ ዜጎችን ጥፋት ለመቀነስና ዜጎቻቸው ከሚሰደዱባቸው አገራትና የስደተኞች መተላለፊያ ከሆኑ አገራት ጋር በትብብር መስራትን ጨምሮ፣ ለስደት ምክንያት የሆኑ ችግሮችን የመቅረፍ ስራ በስፋት ለመስራት ተስማምተዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ ባለፈው ሰኞ በሜዲትራንያን ባህር የሚከሰተውን የስደተኞች ሞት ለመቀነስና ቀጣይ ጥፋቶችን ለመቀነስ የሚያስችል ባለ 10 ነጥብ የድርጊት መርሃ ግብር ቢያወጣም፣ መርሃግብሩ ጥፋትን ከመቀነስ ይልቅ የሚያባብስና ተጨማሪ ስደተኞችን ለስደት የሚያበረታታ ነው በሚል እየተተቸ እንደሚገኝ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡  
በዘንድሮው አመት ብቻ ሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ አገራት ለመግባት ሲሞክሩ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉ ስደተኞች ቁጥር ከ1 ሺህ 700 በላይ መድረሱን የዘገበው ቴሌግራፍ በበኩሉ፣ ይህ የሞት መጠን ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ከተመዘገበው ጋር ሲነጻጸር በ30 እጥፍ እንደሚበልጥም ገልጧል፡፡
አሶሼትድ ፕሬስ በበኩሉ የተመድ የስደተኞች ድርጅትን ጠቅሶ ከትናንት በስቲያ ባወጣው ዘገባ፣ ባለፈው አመት ብቻ 219 ሺህ ያህል ስደተኞች ሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው በህገወጥ መንገድ ወደ አውሮፓ አገራት መግባታቸውንና ከ3 ሺህ 500 በላይ የሚሆኑም በጉዞ ላይ ሳሉ ለሞት መዳረጋቸውን አስነብቧል፡፡ ከእነዚህ መካከልም ከ1ሺህ በላይ የሚሆኑት በዚህ ወር ብቻ መሞታቸውንም አስታውቋል፡፡
ጣሊያን ባህር አቋርጠው የሚመጡ ስደተኞችን ከአደጋ ለመታደግ በሊቢያ ድንበር አቅራቢያ ታደርግ የነበረውን እንቅስቃሴ በጥቅምት ወር 2014 ማቋረጧ፣ ለሟቾች ቁጥር ማሻቀብ ምክንያት ሆኗል ብለው የሚተቹ አስተያየት ሰጪዎች መኖራቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡  
ባለፈው እሁድ ከደረሰውና በአካባቢው ከደረሱ መሰል አደጋዎች ሁሉ የከፋ ጥፋት የደረሰበት ነው በተባለው አደጋ ከ800 በላይ ሰዎች መሞታቸውንና ስደተኞቹ ኤርትራ፣ ሶማሊያና ሶሪያን ጨምሮ የ20 የተለያዩ አገራት ዜጎች እንደሆኑም ሲ ኤን ኤን ዘግቧል፡፡
ከእሁዱ የስደተኞች ጀልባ አደጋ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው ሲሲሊ ውስጥ በፖሊሰ ቁጥጥር ስር የዋሉት የጀልባዋ ካፒቴንና አንድ የህገወጥ የሰዎች ዝውውሩ ተሳታፊ ትናንት ፍርድ ቤት ቀርበው ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

22 የሙስሊም ብራዘርሁድ ደጋፊዎችም በሞት ተቀጥተዋል
የቀድሞው የግብጽ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ ሙርሲ፣ በስልጣን ዘመናቸው ዜጎች ያለአግባብ እንዲገደሉ፣ እንዲታሰሩና እንዲሰቃዩ መመሪያ አስተላልፈዋል በሚል ተከስሰው የ20 አመት እስር እንደተፈረደባቸው ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ከሁለት አመታት በፊት በግብጽ የተቀጣጠለውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ከስልጣናቸው የወረዱት የሙስሊም ብራዘርሁድ  መሪ ሞሃመድ ሙርሲ፣ በታህሳስ ወር 2012 በቤተመንግስታቸው አቅራቢያ ለተቃውሞ የወጡ ከአስር በላይ ግብጻውያን እንዲገደሉ፣ ብዙዎችም እንዲታሰሩና ለስቃይ እንዲዳረጉ ትዕዛዝ መስጠታቸውን አረጋግጫለሁ በማለት ነው ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን የጣለባቸው ተብሏል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ በካይሮ የዋለው ችሎት ከሙርሲ በተጨማሪ በሌሎች 12 የሙስሊም ብራዘርሁድ ባለስልጣናት ላይ ተመሳሳይ የእስራት ቅጣት እንደጣለ ዘገባው ጠቁሟል፡፡
ሙርሲ በተቃዋሚዎች ላይ ግድያ መፈጸምን ጨምሮ የሞት ቅጣት ሊያስጥሉባቸው የሚችሉ ሌሎች ክሶች በተለያዩ ፍርድ ቤቶች እንደተመሰረቱባቸው ያስታወሰው ዘገባው፤ ይሄኛው ፍርድ ቤት ግን የቀረቡለትን የግድያ ክሶች ውድቅ ማድረጉንና ለግድያና ለእስራት ትዕዛዝ መስጠት በሚለው ክስ ብቻ ቅጣቱን እንደጣለባቸው አስታውቋል፡፡
የሙስሊም ብራዘርሁድ የቀድሞ ከፍተኛ ባለስልጣን አምር ዳራግ፤ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ፍትህን ያዛባ ነው ሲሉ ተችተውታል፡፡
ባለፈው ሰኞ 22 የሙስሊም ብራዘርሁድ ደጋፊዎች በካይሮ በሚገኝ የፖሊስ ጣቢያ ላይ ጥቃት አድርሳችኋል በሚል ተከሰው የሞት ቅጣት እንደተላለፈባቸው የገለጸው ዘገባው፤ ታዋቂውን የሙስሊም ብራዘር ሁድ የቀድሞ መሪ ሞሃመድ ባዴን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቀድሞው የግብጽ አስተዳደር ባለስልጣናት ከዚህ በፊት የሞት ፍርድ እንደተጣለባቸውም ጨምሮ አስታውሷል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ
Saturday, 25 April 2015 11:04

የፍቅር ጥግ

(ስለውበት)
ውበት ሌላ ሳይሆን እውነታ በፍቅር አይን ሲታይ ነው፡፡
ራቢንድራናዝ ታጎር
ውበት፤ ዘላለማዊነት ራሱን በመስተዋት ሲመለከት ነው፡፡
ካሊል ጂብራን
ውበት ከወይን ጠጅ ይብሳል፤ ባለቤቱንም ተመልካቹንም ያሰክራል፡፡
አልዶስ ሁክስሌይ
ውበት፤ ጥሩ የትውውቅ ደብዳቤ ነው፡፡
የጀርመናውያን ምሳሌያዊ አባባል
ውበት በዕለት ሥራ ውስጥም ይገኛል፡፡
ማሚ ሲፐርት በርንስ
ውበት፤ የእግዚአብሔር የእጅ ፅሁፍ ነው፡፡
ቻርልስ ኪንግስሌይ
ሰዎች ውበት ውስጣዊ ነው ይላሉ፡፡ እኔ ግን ከቆንጆ ኩላሊት ይልቅ ቆንጆ ፊትን እመርጣለሁ፡፡
ያልታወቀ ምንጭ
ውበት የአፍቃሪ ስጦታ ነው፡፡
ዊልያም ኮንግሪቭ
ውበት የሚጠወልግ አበባ ነው፡፡
ምሳሌያዊ አባባል
አካላዊ ውበት እንደተመልካቹ ሊሆን ይችላል፤ ውስጣዊ ውበት ግን ከውስጥ የሚያበራ በመሆኑ ማንም ሊክደው አይችልም፡፡
ኒሻን ፓንዋር
የሴት እውነተኛ ውበት ያለው ቆዳዋ፣ ፀጉሯ ወይም ተክለ ሰውነቷ ላይ አይደለም … ልቧ፣ ነፍሷ፣ መንፈሷ ላይ እንጂ፡፡
አሌክሳ ዶልም
ለውስጣዊ ውበታችሁ ስትል የምትወዳችሁ ብቸኛዋ ሴት እናታችሁ ናት፡፡
ያልታወቀ ምንጭ
 በዙሪያችሁ ውበትን በፈጠራችሁ ጊዜ ሁሉ ነፍሳችሁን እያደሳችሁ ነው፡፡
አሊስ ዎከር
ሴቶች ሆይ፤ ውበት የሚተረጎመው በጂንስ ሱሪያችሁ ልክ አይደለም፡፡
ሮበርት እስካሌት


Published in የግጥም ጥግ

“ትክ ብዬ ሳያት የምታስቀኝ ሚስት አገባሁ” ያለ አንድ የአገሬ ሰው አለ፡፡ ይሄ ግለሰባዊ መትከንከን ምሳሌያዊ አነጋገር የሆነው ለብዙ ሰዎች በቀጥታ አለያም በተዘዋዋሪ ተተርጓሚነት ስላለው ነው፡፡ ይሄኔ ምሳሌያዊ አነጋገሩ በተወለደበት ዘመን “…አለ፣ አያ እከሌ” እየተባለ ይነገር የነበረ ይሆናል። ከጊዜ ብዛት፣ ከበባታ መስፋት “አያ እከሌ” ተዘንግቶ፣ ምሳሌው እርቃኑን ቀርቶ ይሆናል፡፡ (እንዲያም አለ እንዲህ) ምሳሌው እኔ ጋ ደርሶ ዛሬ መግቢያ አድርጌዋለሁ፡፡ መግቢያ ብቻ ሳይሆን እንግዳ ስሜቴን ቅልብጭ አድርጐ የሚያሳይ ዘዴ ሆኖ አገልግሎኛል፡፡ እንዲህ፡-
“ልብ ብዬ ሳያቸው የሚያስቁኝ መፅሐፍት ገዛሁ” እንዴ? ያሰኛል፡፡ መልሱ እንዲህ ነው፡-
አንዳንድ መፅሐፍት አሉ፤ የአንባቢን ድክመት መሰረት አድርገው የሚዘጋጁ፡፡ እነዚህ መፃህፍት በተለይ ከሰው በስጦታ መልክ ከቀረቡ እንደ ስድብም የሚቆጠሩ አይነት ናቸው፡፡ ለምሳሌ እኔ‘ጋ ካሉትና ልብ ብዬ ሳያቸው ከሚያስቁኝ መፅሐፍት አንዱን ልጥቀስ - “The Complete IDIOT’s Guide” (የተሟላ የደደቦች መመሪያ) የሚል ርእስ አለው፡፡ ይሄን መፅሐፍ አንድ የቅርብ ሰው በስጦታ መልክ ካቀረበልዎ አንድም እርስዎ፣ አለበለዚያም እርሱ (ከሁለት አንዳችሁ) ደደቦች ናችሁ፡፡ ‘እንዴት?‘ ያሰኛል፡፡ ‘እንዲህ‘ ነው፡፡
ሰውየው ይሄን መፅሐፍ የሰጥዎ ሆን ብሎ ከሆነ ድድብናዎን ወይም ጅልነትዎን አለያም ፉዞነትዎን አይቶ ያዘነልዎ፣ ወይም ቀርቦ የተማረረብዎ፣ ካልሆነም ተመራምሮ የደረሰብዎ ሰው ነው ማለት ነው፡፡ ፍቺ በሌለው መንገድ፣ ያለምክንያት፣ በእንዝህላልነት ይሄን መፅሐፍ ገዝቶ ከሰጥዎ ደግሞ ሰውየው እራሱ ደደብ፣ ወይም ጅል አለበለዚያም ፉዞ ነው ማለት ነው፡፡
ይሄ መፅሐፍ የተበረከተበት አግባብ እንዴት ነው? ብሎ ማጤን ደግሞ ደግ ነው፡፡ መፅሐፉ እቤትዎ ድረስ ወይም ብቻዎን ሳሉ ተሸፋፍኖ ከተሰጥዎ “ምክር” ነው፡፡ በአደባባይ ተገላልጦ ከተበረከተልዎ ደግሞ “ስድብ” ነው፡፡ እንዴት? ቢሉ ይሄንን ነባር ምሳሌ ያጤናሉ፡፡ “ለብቻዬ የሰደበኝ - መከረኝ፤ በሰው መካከል የመከረኝ - ሰደበኝ”
“The Complete IDIOT’s Guide” ሦስተኛው እትም (2003 ዓ.ም) እኔ‘ጋ አለ፡፡ ይሄ መፅሐፍ ከያዛቸው ርእሰ ጉዳዮች መካከል እኔ “ደደብ” የሆንኩበትን የቤት አያያዝ መርጬ በማስቀደም አነበብኩ፡፡ አከፋፋይ ቦታ ላይ ቆሞ በመምከር ይጀምራል፡፡ ቤትዎ ጭንቅላትዎ ውስጥ እንዳለው ህልምዎ አድርገው ማደራጀትና መሰደር ከቻሉ፣ ከዚህ ምስቅልቅል አለም የሚሸሹበትን ብቸኛ ቦታ በድል አድራጊነት መመሥረት ችለዋል ይላል፡፡ ጐጆ‘ኮ “ከራስ በላይ ኮርኒስ” ተብሎ የሚጠቃለል ጉዳይ አይደለም፡፡ (Your home doesn’t have to mean just a roof over your head) ይልና ስለቤት አያያዝ ወሳኝነት ይመክራል። ምክሩን አንብቤ እንዲህ እደመድማለሁ፡፡
ያልተደራጀና የተመሰቃቀለ ቤት እንቅፋት እንደበዛበት የባህር ቀዘፋ እንግልት የሞላበት መንፈስ ፈጥሮ ይደክማል፡፡ ሰው በጠዋቱ ከቤቱ ሲወጣ ከደከመው ፉክክር በበዛበት ዓለም ውስጥ ምኑን ተወዳደረው? በአግባቡ የተያዘ መኖሪያ ግን ለልዩ ተልእኮ ማዕከል እንደሚያደርጉት ወታደራዊ ቤዝ ነው…
….ወደ እኔ እውነታ ስመጣ ግን እንደዚያ አይደለም፡፡ ቤቴ በሰዎች “ሥርዓት” ሲይዝ ይዞርብኛል፡፡ ከምስቅልቅሎሹ ጋር ተግባቦት አለኝ። ስላልተሰደረ ደክሞኝ ከቤቴ አልወጣም፣ ቤቴን አልጠላም፣ የፈለኩትን ከቤቴ አላጣም፣ መንፈሴ በቤቴ ላይ አይጐሽም… ለመሆኑ “ከ’Idiot’ እነቴ” ጋር ተስማምቼ ኖርኩ? ወይስ Idiot አይደለሁም? ደግሞስ ምስቅልቅሎሹ ካልተሰማኝና ካልረበሸኝ መፅሐፉ ለምን አስፈለገኝ? እንዴትስ አብሮኝ ለአመታት ቆየ?... እያልኩ ልብ ብዬ ሳየው ከሚያስቀኝ መፅሐፍ ጋር አለሁ፡፡
እኔ ጋ ካሉትና ልብ ብዬ ሳያቸው ከሚያስቁኝ መፅሐፍት ሌላኛው “Bathroom Reader” (ለመታጠቢያ ቤት አንባቢ) የሚል ጠቅላይ ርእስ ያለው ነው፡፡ በ“Bathroom Reader” ኢንስቲትዩት እየተዘጋጀ የሚቀርብ ተከታታይነት ያለው መፅሐፍ ነው፡፡ ለትህትና መታጠቢያ ቤት ይባል እንጂ አላማው መፀዳጃ ቤት ነው፡፡ ሽፋኑ ላይ የመፀዳጃ ቤት ወረቀት፣ የመፀዳጃ ቤት ውሃ መልቀቂያ ይታያል፡፡ ከመፀዳጃ ቤት ወረቀቱ ጋር መፅሐፉ ቦታ ተጋርቷል፡፡ የመፅሐፉ አላማ በመፀዳጃ ቤት ቆይታ ወቅት የተመጠነ እውቀት ማስተላለፍ እንደሆነ ከርዕሱ እና ከሽፋን ምስሉ እንረዳለን፡፡ የፅሁፎቹ መጠን እንደ መፀዳጃ ቤት ቆይታችን እንድንመርጣቸው ሆነው የተዘጋጁ ናቸው፡፡ አጭር (Short)፣ መካከለኛ (Medium)፣ ረጅም (Long) እና ሰፋ ያለ (Extended) በሚል ተከፋፍለዋል፡፡ ይሄን መፅሐፍ ልብ ብዬ ባየሁ ቁጥር አንድ ቀልድ ትዝ ይለኛል፡፡
መፀዳጃ ቤቱ የጋራ የሆነበት መንደር ውስጥ ነው፡፡ ልጁ ገብቶ ብዙ የቆየባቸው ተጠቃሚዎች እየተነጫነጩ ነው፡፡ ከመካከላቸው አንዱ አዛውንት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ልጁን ያናግሩታል፤
“ሰማህ አንተ ልጅ”
“አቤት”
“ሽንት ቤቱን ብቻህን ያዝከው‘ኮ፡፡ እኛም መጠቀም እንፈልጋለን፣ ለምን አትወጣም?”
ልጁ ውስጥ እንዳለ ይመልሳል፡-
“ቢወጣስ የት ይኬዳል?”
እኛ ከምናውቀው የጋራ መፀዳጃ ሽታ በላይ የከረፋ የሥራ አጥነት አለም ልጁን ይጠብቀዋልና ተደበቀበት፡፡ ቀልድ ይመስላል እንጂ መራር እውነት ነው፡፡
…እና (በእኛ ዓይን) የቀበጡቱ ፈረንጆች መፀዳጃ ቤት ተቀምጦ የሚባክን ጊዜን ሥራ ላይ ለማዋል “Bathroom Reader” አቀዱና ተገበሩ። መፅሐፉ ግን “መፅሐፍ” ነው፡፡ ታሪክ፣ አስቂኝ ገጠመኝ፣ ፖለቲካ፣ ሥነ-ፅሁፍ፣ ጥያቄና መልስ፣ ሥነ-ልቦና… ያልያዘው ነገር የለም፡፡ ያለ መፅሐፉ አላማ መኖሪያ ቤት ውስጥ እያነበብኩት ነው፡፡ እንኳን መፀዳጃችን ከተማችን እንደ ጋራ ሽንት ቤት በከረፋችበት አግባብ ሌላ ምን አማራጭ አለ?
ሦስተኛው ሳየው የሚያስቀኝ መፅሐፍ “100 MISTAKES THAT CHANGED HISTORY” (ታሪክ የቀየሩ መቶ ስህተቶች) የሚል ርእስ አለው። መግቢያው እንኳን “History Making Mistake” (ታሪክ ሰሪው ስህተት) የሚል ንዑስ ርዕስ ተሰጥቶታል፡፡ ታዲያ እኛ ምን ሆነን ነው “ታሪክ ሰሪው ሰፊው ህዝብ ነው” እያልን የከረምነው? ከዚህ መፅሐፍ አንፃር “ቆራጡ” (ምናምን) የሚባል መሪ የለም፡፡ ወይም ይቺ አለም እዚህ የደረሰችው በታቀደላት ቀጥተኛ መንገድ ተጉዛ ሳይሆን መሪዎችና ሌሎች ተሳስተው በፈጠሩት ክስተት ነው፡፡ ስለዚህ “Your Kingdom, or your life is a mistake” ይላል መፅሐፉ፡፡ ይሄንንም ለማስረገጥ መቶ ስህተቶች እንዴት የዓለምን ታሪክና ገፅታ እንደቀየሩት ያስነብባል፡፡
2500 ዓመታት ወደኋላ ተጉዞ የአይኦኒያን ከተማ ከሆነችው ከሚሊተስ (Miletus) መሪ አሪስታጐራስ (Aristagoras) ስህተት ይጀምራል። የአሪስታጐራስ ስህተት ምዕራብ አውሮፓ አሁን ባለችበት ሁኔታ እንድትገኝ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ አሪስታጐራስ የፐርሺያውን ንጉስ ቀዳማዊ ዳሪየስ አስደስቶ ለመሾም ለመሸለም ሲል ያመፀችውን የናክሶስ ከተማ ለመውረር ተነሳ፡፡ ድል ሳይቀናው ቀርቶ ተሸነፈ፡፡ ለመሸነፉ ከባቢሎን ንጉስ የሚደርስበትን ቅጣት ያውቃልና የአካባቢውን ከተሞች በባህል ስም ለአመፅ አስተባበረ፡፡ “ቋንቋችንና ባህላችን ለግሪክ እንጂ ለፔርሺያ ባእድ ነው፡፡ ስለዚህ ባቢሎናውያንን አንቀበልም” አለ። የአቴንስንና የመላው ግሪኮችን ድጋፍ አግኝቶ ቢዋጋም ከፔርሺያዎች ሽንፈት አላመለጠም፡፡ በዚህ ስህተት አውሮፓ ከግሪክ ግለሰብን ማዕከል ካደረገ ባህል ባሻገር ጠንካራ ማዕከላዊነት ያለውን የፔርሺያ ባህል ለማካተት ተገደደች፡፡ በዚህም አሁን ያለችውን ሆነች፡፡
ይሄ የመፅሐፉ ጅማሬ እስከ 2008 ዓ.ም የአውሮፓ የኢኮኖሚ ድቀት ድረስ ይጓዛል፡፡ እና ብዙ የፖለቲካ፣ የሳይንስ፣ የማህበራዊ ህይወት ስህተቶች የቀየሩትን ታሪክ ያሳየናል፡፡ እንዲህ ያለው ምርምር ከታሪክ ጋር በባላንጣነት ከመኖርና እሱኑ ከማመንዠግ አይገላግልም ትላላችሁ፡፡
አራተኛውን ልብ ብዬ ሳየው የሚያስቀኝን ያገኘሁት ከወደ ሩሲያ ነው፡፡ ሊያኪሚንኮ (LYAKIMENKO) የተሰኘ የሥነ ፅሁፍ ተመራማሪ፣ ሾሎሆቭ (Sholokhov) የተሰኘ ደራሲ ሥራዎች ላይ ጥናት ያካሄደበት መፅሐፍ ነው፡፡ ርእሱ “Sholokhov፡ A Critical Appreciation” (ቮሎሆቭ፡ የማድነቅ ሂስ) ይሰኛል፡፡ ማድነቅ ብቻ ከሆነ ምኑን ሂስ ሆነ? ስህተት ፈልጐ ማጣት አንድ ነገር ነው፤ ስህተትን ወዲያ ብሎ ማድነቅን ብቻ በማነፍነፍ እንዴት ሂስ ይሰራል? እያልኩ መፅሐፉን ሳየው ያስቀኛል፡፡
ሌላኛው መፅሐፍ የማርክ ክሪክ ነው፡፡ “The Household Tips of the Great Writers” ይሰኛል፡፡ መፅሐፉ በቤት አያያዝና በአትክልት ቦታ እንክብካቤ ውስጥ አጣማጅ አድርጐ ያላነሳቸው ደራሲዎች የሉም፡፡ ፍራንዝ ካፍካ፣ ጄን ሀውስቲን፣ ማርሲል ፕሩስት፣ ኤርነስት ሔሚንግዌይ፣ ቬርጂንያ ዎልፍ፣ ቶማስማን፣ ሆሜር፣ ቻርልስ ዲከንስ፣ ሐሮልድ ፒንተር፣ ጆን ስቴንቤክ፣ ሚለን ኩንዴራ፣ ኤሚል ዞላ፣ ዤን ፖውል ሳርት፣ ኤድጋር አለን ፖ… የሚገርመው ግን አንዱም የሉም፡፡ ደራሲው በፀሐፊዎቹ ስታይልና የሥነ ፅሁፍ አይነት የቤት አያያዙን፣ የመታጠቢያ ቤት እንክብካቤውንና የአትክልት ስፍራ አያያዙን ፅፎ አቅርቧል፡፡ አሁን ይሄ ማታለል ነው ወይስ…?
እንዲህ ያሉ “ግራ” ሥራዎችን ወደፊት እየመላለስን እንዳመቸን እንመለከታለን፡፡ 

Published in ጥበብ
Page 1 of 17