በራሱ ላይ መቀለድ የሚችለው አርቲስት
ዳንኤል ታደሰ ይባላል፡፡ ብዙዎች “ጋጋኖ” በሚል ቅፅል ስም ይጠሩታል። በተለያዩ ቴአትሮችና ፊልሞች ላይ በመተወን

የሚታወቅ ሲሆን በተለይም “ሳምራዊ” በተሰኘ ፊልም ላይ በመተወን ይበልጥ ዝነኝነትን አትርፏል፡፡ ለየት ያለ የሰውነት

አቋም ያለው ዳኒ ጋጋኖ፤ ራሱን በመተረብና ሰዎችን በማሳቅ ይታወቃል፡፡ “አንዳንዴ ራሴን ስስለው ባለ ቆቡን ምስማር

የምመስል ይመስለኛል” ከሚለው አርቲስት ዳንኤል ጋጋኖ ጋር የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ቀጣዩን አዝናኝ

ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡

ራስህን አስተዋውቀን?
ዳንኤል ታደሰ በላይነህ እባላለሁ፡፡ አዲስ አበባ ጋንዲ ሆስፒታል ተወልጄ፣ አዲሱ ገበያና ደጃች ውቤ ነው ያደግሁት፡፡
የአባትህ ስም ጋጋኖ ይመስለኝ ነበር፤ ቅጽል ስምህ ነው እንዴ? ዳኒ ጋጋኖ ስትባል  እሰማለሁ..
ድሮ ፑሽኪን የሚታይ “ዶክተር ጋጋኖ” የተሰኘ አንድ ቴአትር ሰርቼ ስለነበር፣ በዛው ጋጋኖ ተብዬ ቀረሁ፡፡ ብዙ ሰው ዳኒ

ጋጋኖ ይለኛል፡፡
መቼ ነው ቴአትሩን የሰራኸው?
ጊዜው ትንሽ ቆየት ብሏል፡፡ ትርጉሙ የጋሽ አያልነህ ሙላት ነው፤ የኒኮላይ ጐጐልን ድርሰት ተርጉሞ በቴአትር መልክ

አቅርቦት ነበር፡፡ እዛ ላይ ዶ/ር ጋጋኖን ሆኜ ተጫውቻለሁ፡፡
ትምህርትህን የት ነው የተማርከው?
ቤተልሄም፣ ራስ አበበ፣ ዘርፈሽዋል እና መነን ት/ቤቶች ተምሬያለሁ፡፡  
የአዲስ አበባን ት/ቤቶች አዳርሰሃቸዋላ?
ት/ቤቶቹን ብቻ ሳይሆን ያደግኩትም ብዙ ሰፈር ነው፡፡ ከላይ አዲሱ ገበያንና ደጃች ውቤን ጠቀስኩልሽ እንጂ ብዙ ሰፈር

ነው ያደግኩት፡፡  
ወደ ጥበብ የገባህበት አጋጣሚ ምን ይመስላል?  
ወደሙያው የገባሁት እንደቀልድ ነው፡፡ ት/ቤት ውስጥ አንዳንድ ተሳትፎዎች ነበሩኝ፤ እነሱም ቢሆኑ እንደ ቀልድ

የሰራኋቸው ነበሩ፡፡ ግን እያደር እያመረርኩ መጣሁ፡፡ ከዚያ በኋላ እነ ቴዎድሮስ ለገሰ የነበሩበት “ዩኒቲ” የተሰኘ የቴአትር

ክበብ ተከፍቶ ነበረ፡፡ “የልብ እሳት” ቡድኖችን ተቀላቀልኩኝ፡፡ የቀልድ የነበረው ጅማሬ ይህን ቡድን ስቀላቀል ወደ

እውነት ተቀየረ፡፡
“ዶ/ር ጋጋኖ” … የመጀመሪያ ስራህ ነበር?
አይደለም፤ ከዚያ በፊት ሌሎች ቴአትሮችን ሰርቻለሁ፡፡ የመጀመሪያ ስራዬ “የልብ እሳት” ቴአትር ነው፡፡ ቀጥሎ “ዋናው

ተቆጣጣሪ” የተሰኘ ቴአትር የሰራሁ ሲሆን በየክልሉ እየተዘዋወርን እናሳይ ነበር፡፡ እኔም የተለያዩ ገፀ ባህሪያትን

እየቀያየርኩ አዘጋጁ ባስገባኝ ቦታ ሰርቼአለሁ፡፡ የተፈሪ አለሙ ትርጉም የሆነው “አሉ” ቴአትር “የቀለጠው መንደር”

ከዶክተር ጋጋኖ በፊት የሰራኋቸው ናቸው፡፡ ሌላው “የአራዳ ትዝታ” በሚል ከአንጋፋ አርቲስቶች ጋር ትዊስት ዳንስ

ሰርቻለሁ፡፡ ማስተር ሳውንድ ሙዚቃ ቤት ነው ቪሲዲውን ያሳተመው፡፡ በዚህ ስራ ላይ ችሮታው ከልካይ፣ በላይነሽ

አመዴ (ኩንዬ)፣ ሙናዬ መንበሩ፣ ፍሬ ህይወት ባህሩ፣ ፋንቱ ማንዶዬና ሌሎች አንጋፋ አርቲስቶች አሉበት፡፡ ምን

አለፋሽ … እኔ ብቻ ነኝ ወጣት ሌሎቹ አንጋፋዎች ናቸው፡፡ የሚገርም ስራ ነው፡፡
ዳንስ ስትል መድረክ ላይ ነው?
በፊት “የቀለጠው መንደር” ላይ ስሰራ፣ ዳንስ መለማመድ እንደምፈልግ ተናግሬ፣ ሀገር ፍቅር ቴአትር ውስጥ

ተለማመድኩ፡፡ አንድ ጊዜ እንደውም ለአዲስ አመት ሀገር ፍቅር  ቴአትር ቤት ዳንስ አቅርቤያለሁ፡፡
ለዳንስ ሰውነትህን በደንብ ማዘዝ ትችላለህ?
በምንም መልኩ አያስቸግረኝም፤ በደንብ አዘዋለሁ፡፡ በቃ ሰውነቴን ላስቲክ በይው፡፡
ብዙ ሰዎች እንደሚሉት፤ እኔም እንዳስተዋልኩት ከሰውነት አቋምህ ጋር በተያያዘ በራስህ ላይ መቀለድ ታበዛለህ፡፡

“ቀልድና ጽዳት ከራስ ሲጀምር ጥሩ ነው” ብለህ ነው?
በእኔ እምነት በሰው ከመቀለድ በራስ መቀለድ ቀላልም ጥሩም ነው፡፡ የእኔ ሰውነት ደግሞ ራሴ ከቀለድኩበት ለቀልድ

የተመቸ ነው፡፡
እንዴት ማለት?
አንዳንድ ሰዎች ለማንጓጠጥ ብለው ወይም በስድብ ፎርማት የሚናገሩትን አርቲስቲክ ማድረግ ጥሩ ነው፡፡ ይህን ሳደርግ

ሰዎችም ዘና ይላሉ፤ እኔም እዝናናለሁ፡፡
እስቲ በራስህ ላይ ከቀለድካቸው ጥቂቱን አጫውተኝ…
“ከኋላ ለሚያዩኝ ባለቆቡን ምስማር ልመስል እችላለሁ፣ ከመሃል ለምታዩኝ ደግሞ ዣንጥላ እመስላችሁ ይሆናል፡፡ ከፊት

ለፊቴ ያላችሁ ያላለቀ ኮንዶሚኒየም ስለምመስል ያለሁበትን ሳይት ለማወቅ እየተነጋገራችሁ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡” ስል

ሰዎች በሳቅ ይሞታሉ፡፡
“ባለቆቡን ምስማር እመስላለሁ” ስትል ከምን ተነስተህ ነው? ወይስ ሰዎች ትመስላለህ ብለውህ ያውቃሉ?
አንዳንዴ ራስሽም እኮ ትፈጥሪያለሽ፡፡ ፀጉሬን ፈትቼ ስለቀው ጅፍ ይላል እና ከሩቅ ሲያዩኝ ባለቆቡን ምስማር

እንደምመስል ለራሴ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ራሴን ስስለው እንደዛ ይሰማኛል፡፡
አንተ ከምትለው ውጭ ጓደኞችህ ተርበውህ ያውቃሉ? ማለቴ ለየት ያለ ነገር …
ይገርምሻል፤ እነሱ እንደውም አይተርቡኝም፡፡ እኔ ራሴን ስተርብ ግን በጣም ይዝናናሉ ይስቃሉ፡፡
ከሁለት ወይም ከሶስት አመት በፊት ጅማ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ አንድ ፕሮግራም ላይ ተገናኝተናል እናም ስታንድ አፕ

ኮሜዲ አቅርበህ ሰዎችን ስታስቅ ነበር፡፡ እስቲ ስለዛ መድረክ ትንሽ አጫውተኝ?
እንዳልሽው ሁለት ወይም ሶስት አመት ይሆነዋል፡፡ የጅማ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ኤችአይቪ ኤድስ ላይ የምትሰራ

አምባሳደር ሞዴል ለመምረጥ ባዘጋጁት ፕሮግራም ላይ “ሶል ኤጀንት” የተባለ ድርጅት ነው የወሰደን፡፡ እንደውም

በመድረክ ላይ ደፍሬ ቀልድ  ሳቀርብ የመጀመሪያዬ ይመስለኛል፡፡ ከአለባበሴ ጀምሮ ለየት ብዬ ለመቅረብ ሞክሬያለሁ።

ቅድም እንዳልኩሽ ነው ቀልዱ፡፡ “ከኋላ ላላችሁ ባለ ቆቡን ምስማር ልመስል እችላለሁ፤ ከመሀል ላላችሁ ጃንጥላ፤ ከፊት

ለፊቴ ላሉት ያላለቀ ኮንዶሚኒየም ቤት እየመሰልኳቸው ይነጋገራሉ፡፡ ከሁለም የገረመኝ ከመድረክ ጀርባ አብረውኝ

የሚሰሩት ልጆች የሚያወሩት ነው፡፡ ግማሾቹ ዝናብ የመታው አውራ ዶሮ ይመስላል ይላሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ አስፋልት ዳር

የበቀለ ጥድ ነው እያሉ ሲከራከሩ ይሰማኛል” እያልኩ ነበር ያ ሁሉ ሰው ሲስቅ የነበረው፡፡ “ለማንኛውም እዚህ መሀላችሁ

ያቆመኝ የቅርስ ጥበቃና ባለደራ ባለስልጣን ሲሆን ዋና አላማው ከሙዚየም የማይወጡ ቅርሶችን እንደኔ ባለ ተንቀሳቃሽ

ቅርስ ለመለወጥ ባለው ፅኑ ፍላጐት ነው” ስል የነበረውን የሳቅ ሁካታ በቦታው ስለነበርሽ ታስታውሽዋለሽ። እንዲህ

እንዲህ እያልኩ ነው ቀልድ የጀመርኩት፡፡
በነገራችን ላይ አሁን ያለህን የሰውነት አቋም የያዝከው ስትወለድ ጀምሮ ነው ወይስ ከተወለድክና ካደግክ በኋላ?
ቤተሰቦቼ እንደነገሩኝ ከሆነ ኖርማል ነበርኩኝ፤ በህፃንነቴ ከሰራተኛ እጅ ላይ አምልጬ ወድቄ በደረሰብኝ ጉዳት ነው

ይህን አይነት አቋም ሊኖረኝ የቻለው፡፡ በፊት በፊት አንገት የሚደግፍ ነገር ነበረኝ፤ ካደግሁ በኋላ ትቼው ነው፡፡ ምቾት

ስለማይሰጠኝ እያለቀስኩ ሳስቸግር አውጥተው ጣሉልኝ፡፡
ባለህ የሰውነት አቋም የተነሳ ምን የሚሰማህ ነገር አለ?
በነገራችን ላይ እንደዚህ መሆኔ ራሱ ትዝ አይለኝም! ትዝ የሚለኝ ራቁቴን ሆኜ በቁም ሳጥን መስታወት ፊት ስቆም ብቻ

ነው፡፡ ራሴን እንደረጅም ሰው ነው የምቆጥረው እና አስቤውና አሰላስዬው አላውቅም፡፡
እኔም ሆንኩ ብዙ ሰው በትወና ያውቅሀል ብዬ የማስበው በ“ሳምራዊ” ፊልም ቁጥር አንድና ቁጥር ሁለት ላይ ነው፡፡

በዚህ ፊልም ላይ የአስተናጋጁን ገፀባህሪ ተላብሰህ ለመጫወት እድሉን እንዴት አገኘህ?
በወቅቱ የፊልሙ ባለቤት አርቲስት ዮሐንስ ፈለቀ “ሳምራዊ” ፊልምን መስራት ይፈልግ ነበርና ከ“ስርዬት” ደራሲ ደረጀ

ፍቅሩ ጋር ይገናኛሉ፡፡ እኔም ለአስተናጋጅነት ካስት ተደረግሁኝ፡፡ በዛን ጊዜ የምተውናት ክፍል በጣም አጭር ነበረች፡፡

ዮሀንስና ደረጀ ከተወያዩ በኋላ፣ እኔ የምጫወተውን ክፍል በደንብ አሰፉት፡፡ ጥሩ ተጫወትኩት፡፡ በዚህ የተነሳ

ለ“ሳምራዊ” ቁጥር ሁለት ፊልም ታጭቼ እሱንም ሰራሁ ማለት ነው፡፡
“ሳምራዊ” ቁጥር አንድ ላይ አስተናጋጅ ሆነህ ስትሰራ የሚያስፈራሩህ ሰዎች ራቁትህን ይዘውህ ስትንቀጠቀጥ ይታያል፡፡

እኔ ልክ እንዳየሁህ ደንግጬ ነበር፡፡ በወቅቱ የሌሎች ተመልካቾች ስሜት እንዴት ነበር? የደረሰህ አስተያየት ካለ

ብትነግረኝ?
እውነቱን ልንገርሽ … ብዙዎች የሰውነት ቅርፅ ተወዳደርበት ነው ያሉኝ፡፡ ይህንን ሰውነት ይዘህ ቁጭ ትላለህ እንዴ

ብለው ወቅሰውኛል፡፡ አንቺ ላታምኚኝ ትችያለሽ፤ አንዳንዶቹ ጩኸታቸውን ለቀውታል፤ ሌሎቹ እንዲህ አይነት ሰው

ራቁቱን ስናይ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ እና ቁጭ ብዬ ፊልሙን እንደተመልካች ሳይ፣ ልክ ራቁቴን

ስመጣ ተመልካቹ ሁሉ ጩኸቱን ይለቀዋል።
ለምን ይመስልሀል?
አንቺ ለምን ይመስልሻል፤ ቅርፄን ወደውት ነዋ! አንዳንዴ እኔን ያዝናናኛል፡፡ እኔን ካዝናናኝ ሌላውም እንደሚዝናና

ይሰማኛል፤ ዘና ያለ ስሜት ይፈጥርብኛል፡፡ ምክንያቱም አንቺ በምትፈጥሪው ነገር ሰዎችን ማዝናናት ከቻልሽ የበለጠ

ፈጠራ ለመስራት ትተጊያለሽ፡፡ እኔ ስንፍና ነው እንጂ ብዙ መስራት እችል ነበር፡፡ ለምሳሌ ጓደኞቼ የስልካቸው ባትሪ

ሲያብጥ “ወይኔ ባትሪው ጐበጠ” ሲሉ ዞር ብዬ አትሳደቡ እላቸዋለሁ፤ ወዲያውኑ ሳቅ ይጀመራል። እነሱ ስለ ባትሪው

መጉበጥ ነው በትክክል የሚያወሩት፤ ሳያስቡት ከራሴ ጋር አገናኝቼ ስናገር ይስቃሉ እና ለፈጠራ ነው የምትዘጋጂው፡፡
ከ“ሳምራዊ” ፊልም በኋላ ምን ሰራህ?
ከሳምራዊ በኋላ “ላገባ ነው”፣ “ማቶት”፣ “ላም አለኝ” የተሰኙ ፊልሞች ላይ ሰርቻለሁ፡፡ “ላም አለኝ” የቤዛ ሀይሉ ፊልም

ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ቤዛን ላመሰግናት እፈልጋለሁ፡፡ በጣም ጠንካራ ልጅ ናት፡፡ ይህ ፊልም ሁለተኛዋ ነው፡፡

ልትበረታታ ይገባታል፡፡ የደረጀ ፍቅሩ “አፍሮኒዝም” የዮሀንስ ፈለቀ “ሄሎ ኢትዮጵያ” ፊልም ላይም ሰርቻለሁ። “ሄሎ

ኢትዮጵያ” አሁንም በዓለም ሲኒማ እየታየ ይገኛል፡፡ በዚህ ፊልም ላይ ለራሱ ህይወት ግዴለሽ የሆነን ልጅ ገፀ-ባህሪ ነው

የተጫወትኩት፡፡ ግዴለሽ ሆኖ ግን የሚፈጥራቸው ነገሮች ለሌሎች ሰዎች ጥሩና ጠቃሚ ይሆናሉ እና ገፀ-ባህሪውን

እወደዋለሁ፡፡
አጫጭር ዘጋቢ (ዶክሜንታሪ) ፊልሞችን እንደሰራህ ሰምቻለሁ …  
አዎ ሰርቻለሁ፡፡ ከስፔናዊያን ጋር ነው የሰራሁት፡፡ ይህን ስራ አርቲስት ዮሐንስ ፈለቀ ነው ያገናኘኝ፡፡ በመጀመሪያ እኔና

አርቲስት ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) ያለንበት “where is my dog?” የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም ሰራሁ፡፡ ዩቲዩብ ላይ

ብትገቢ ታገኝዋለሽ፡፡ ቀጥሎ “Children” የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም ሰራሁ፡፡ አሁን በቅርቡ ደግሞ ከስፔናውያኑ ጋር “ችግር

አለ” የሚል ዘጋቢ ፊልም ሰርቻለሁ፡፡ አዶልፍ ሂትለርን ሆኜ ነው የተጫወትኩት፡፡ ስፔን አገር ተወዳድሮ አንደኛ ወጥቷል

ፊልሙ፡፡ እነዚሁ ስፔናዊያን በቅርቡ ሙሉ ፊልም ለመስራት በጀት መድበው ይመጣሉ፡፡
ጥሩ ተከፈለህ ታዲያ?
በጣም የተጋነነ ጥቅም አታገኚም ግን ያለው ነገር ያበረታታል፡፡ ከስፔናዊያኑ ጋር ስሰራ ከገንዘቡ ይልቅ ለአክተሮች

ያላቸው መረዳት ያስደንቃል፤ ያስደስታል፡፡ አንዳንዴ ስሰራ ይደነቃሉ፡፡ “እንዲህ አይነት ልጅ ማግኘት ያስደንቃል”

ይላሉ፡፡ በውጭው አለም ብትኖር ምን አይነት እድሎች ይኖሩህ ነበር ይሉኛል፡፡ አረዳዳቸው አብሬያቸው እንድሰራ

ይገፋፋኛል፡፡ በቅርቡ ይመጣሉ፤ እዚህ ሲመጡ ማናጀራቸው ዮሐንስ ፈለቀ ነው፡፡
እስካሁን ትወናው ላይ ነው የታየኸው፡፡ ፊልም (ቴአትር) መፃፍና ማዘጋጀትስ አትሞክርም?
ፑሽኪን በነበርኩበት ጊዜ እዚያ የሚታዩ ስራዎችን ነበር የምፅፈው፡፡ አሁን አሁን ፊልሞች ሲሰሩ ከጓደኞቼ ጋር ሆኜ

የሚሰሩት ስራ ላይ ሀሳብ የማዳበር፣ ሀሳብ የማዋጣት ስራዎችን እሰራለሁ። አንዳንዴ ስንፍናውም አለ እንጂ ሀሳቡ

ይኖራል፡፡
በባህሪህ ምን አይነት ሰው ነህ? ዝምተኛ ወይስ ተጫዋች?  
አይ … እኔ እንኳን ክፍት አፍ ቢጤ ነኝ፡፡
እንዴት?
ዝም ካልኩ መናገር የማልችል ዲዳ የሆንኩ ስለሚመስለኝ እለፈልፋለሁ፡፡ አወራለሁ፡፡  
አሁን ከማን ጋ ነው የምትኖረው? ለቤተሰብህ ስንተኛ ልጅ ነህ? ትዳር ይዘሀል?
ከቤተሰቦቼ ጋር ነው የምኖረው፤ አምስተኛ ልጅ ነኝ፡፡ ገና አላገባሁም፡፡
የማግባት ፍላጐት የለህም?
አለኝ ግን ዝም ብሎ ይገባል እንዴ? እንዴት ያለ ነገር ነው? ጊዜና ወቅት አለው፡፡
እድሜህ ስንት ነው?
ሰላሳዎቹን እያለፈ ነው፤ ወደ 34 አካባቢ ነኝ  
ታዲያ ከዚህ በላይ ምን ይጠበቃል?
ቀንድ!
ቀንድ ካላወጣህ አታገባም ማለት ነው?
መሆኑ ነዋ!
ፍቅረኛ ነበረችህ?
ነበረችኝ፡፡ ከቤተሰቧ ጋር ውጭ ሄደች፤ ተለያየን፡፡ አሪፍ ሰው ነበረች፤ አሁን አንገናኝም፡፡ ሌላ ጓደኛም አልያዝኩም፡፡
እሷን እየጠበቅህ ነው ወይስ ፍቅር እንደኩፍኝ በልጅነትህ ወጣልህ?
አልወጣልኝም፤ ወጣ ገባ እያለ ነው
ስለ ፍቅር ስታስብ የሚያስገርምህ ነገር አለ?
ስታፈቅሪ ያፈቀርሻትን ሴት ወንድሟ ሲያቅፋት እንኳን ትናደጃለሽ እኮ፡፡ ወንድሟ መሆኑን እያወቅሽ እኮ ነው፡፡ ካለፈ

በኋላ ግን ያስቅሻል፤ ምን ነክቶኝ ነው ትያለሽ፡፡
በስራ ላይ እያለህ በርካታ አዝናኝ፣ አስገራሚና አሳዛኝ ገጠመኞች ሊኖሩህ እንደሚችሉ እገምታለሁ። እስቲ ከገጠመኞችህ

አካፍለኝ …
ብዙ አጋጣሚዎች አሉ፡፡ አንዳንዴ እስከ ህይወት ማጣት የሚቀርቡ ገጠመኞች ይኖራሉ። ለምሳሌ “የአፍሮኒዝም” ፊልም

የመጨረሻው ቀን ቀረፃ ላይ ነው ነገርዬው የተከሰተው፡፡ ትዕይንቱ ላይ አንዱ ካራቲስት ከፊት ይዞ ኋላ ላለው ካራቲስት

ነው የሚወረውረኝ፡፡ ቀረፃው ተጀምሯል፡፡ የፊተኛው ይዞ ሲወረውረኝ የኋለኛው ፈፅሞ ረስቶኛል፡፡ ስለዚህ

እንደወረወረኝ ሄጄ በጭንቅላቴ ድንጋይ ላይ ቆምኩኝ፡፡ በእግሬ አይደለም ያልኩሽ በጭንቅላቴ ነው፡፡
ከዚያስ ተረፍክ?
ተርፌማ ነው አሁን የማዋራሽ፡፡ ካሜራ ማኑ በድንጋጤ ካሜራውን ለቆታል፡፡ ተስፉ ብርሃኔ “በመድሀኒያለም” ብሎ

መሬት ላይ ቁጭ አለ፡፡ ሌሎቹ የሚይዙ የሚጨብጡትን አጥተዋል፡፡ እኔ እራሴ የዛን ቀን ያየሁትንና የተብለጨለጨብኝን

የከለር አይነት ድጋሚ የማየው አይመስለኝም፡፡ የእኛ አገር ፊልም ያው ኢንሹራንስ የለውም፡፡ ብትሄጂም በቃ እስካሁን

ተረስተሽ ነበር፡፡ እስክረጋጋ ተቋረጠና ቆይተን ቀረፃው ተጀመረ፡፡
ሌላ ገጠመኝ?  
“ሄሎ ኢትዮጵያ”ን እየሰራን ነው፡፡ ከከተማ ውጭ ነው፡፡ አንዱ ሄዶ ሳያስፈቅድ የሰው ፈረስ ይዞ ይመጣል፡፡ ለቀረፃው

ፈረስ ያስፈልግ ነበር፡፡ የፈረሱ ባለቤት የድንጋይ እሩምታ ጀመረ፡፡ ከዚያ ሲያግዙን የነበሩትም የአካባቢው ሰዎች

ለሰውየው ተደርበው፣ እኛን በድንጋይ ጠመዱን፡፡ እግሬ አውጭኝ ብለን ፖሊስ ጣቢያ ገባን፡፡
ከመሀላችሁ የተጐዳ ነበር … በድንጋይ ውርወራው?
በአጋጣሚ አልተጐዳንም፤ በኋላማ የጨበጣ ውጊያ ሆነ፤ እጅ በእጅ ተያያዝን እኮ፡፡ ፈረንጆቹ ሁሉ መደባደብ ጀመሩ፡፡
ፈረሴን መልሱ ማለት ሲገባው፣ ሞቅ ብሎት መጥቶ ድንጋይ ነው ያነሳው። በአገራችን ፀጉረ ልውጥ መሆናችን የገባን ያን

ጊዜ ነው፡፡
ገጠመኞችህ ተመችተውኛል፤ ሌላ ገጠመኝ ይኖርሀል?
አንድ ጊዜ “ሳምራዊ” ፊልምን ስንቀርፅ ጅብ አጋጠመን፡፡ ምሽት ላይ ነው ቀረፃው፡፡ ጫካ ውስጥ ነው፡፡ መጀመሪያ

መብራት ሲበራ ምንም ነገር አልነበረም፡፡ መብራት ሲጠፋ ጅቦች ከበውናል፡፡  
ስንት ናቸው?
ሶስት ወይም አራት ይሆናሉ፡፡ ከዚያ መጯጯህ ተጀመረ፤ ማን ያረጋጋ?
ወንዶች አይደላችሁም እንዴ? ምን እንዲህ ያደርጋችኋል?
እንዴ! ምን ነካሽ ጅብ ቆሞ ወንድነት አለ እንዴ? አልሞከርሻትም ያቺን ስሜት … ሽንትሽ እኮ ነው የሚመጣው፡፡
መጨረሻ ላይ እንዴት ሆናችሁ? ከመሀላችሁ ደፈር ያለ የለም?
በእግዜር ኪነ-ጥበብ ተረፍን፡፡ በቃ መሯሯጥ ተጀመረ፡፡ ለነገሩ ጅቦቹ እግዜር ይስጣቸው! ምንም አላሉንም፡፡ በሰዓቱ ግን

በጣም ያስደነግጣል፡፡ ደፈር ያለው ካሜራማኑ ነው፤ ምክንያቱም ካሜራዎቹ የእሱ ናቸዋ! ምን ያድርግ?
ዳይሬክተሩ ዮሀንስ ፈለቀስ ሮጠ?
አይባልም እንጂ ያልሮጠ የለም፡፡ አንድ ሌላ ገጠመኝ ልጨምርልሽ?
አርገኸው ነው?
አንዴ ደግሞ “Where is my dog”ን ለመቅረፅ ቆሼ የሚባለው ቦታ (ረጲ ነው መሰለኝ የሚባለው) ሄድን፡፡ ቆሻሻው

አካባቢ ቆሜ ቀረፃው እየሄደ ሳለ፣ አንድ ትልቅ ጆፌ አሞራ ይዞኝ ሊሄድ ሲል እግዜር ነው ያተረፈኝ፡፡ እኔ ምን መስዬ

እንደታየሁት አላውቅም፡፡ በጣም ነበር የደነገጥኩት፡፡ ብቻ አሁን አላስታውስም እንጂ ብዙ አስገራሚ ገጠመኞች ነበሩኝ፡፡

ሳስታውስ እነግርሻለሁ፡፡
ቤተሰብህ በስራህ ዙሪያ ድጋፍ ያደርግልሀል?
ስጀምር ደስተኞች አልነበሩም፡፡ እንደማንኛውም ቤተሰብ ዶክተር እንድትሆኚላቸው ነው የሚፈልጉት። ነገር ግን በስራዬ

እያሳመንኳቸው መጣሁ፤ አሁን ደስተኛ ናቸው፡፡
እንደ ጋዜጠኛም ያደርግሀል ልበል?
በትንሹ! ዮፍታሄ ሲኒማ ያሳትመው የነበረውን “ዮፍታሄ” መፅሄት ከአንድ ጓደኛዬ ጋር እናዘጋጅ ነበር፤ አሁን ቆሟል፡፡
ካስክ እንዴት እንደሚያቃጥል ቀምሰኸዋላ?
በ“አፍሮኒዝም” ያልቀመስኩት የለም፡፡
ወደፊት ምን አስበሀል?
በቀጣይ መድረክ ላይ ያቀረብኳቸውን ቀልዶቼን በቪሲዲ የማሳተምና ሌሎች ስራዎችንም የመስራት ሀሳብ አለኝ፡፡
ከኮሜዲያን የማን አድናቂ ነህ?
ተስፋዬ ካሳ የማይተካ ኮሜዲያን ነው፤ በጣም አደንቀዋለሁ፤ አብርሀም አስመላሽም ይመቸኛል፡፡ በህይወት ካሉት

ክበበው ገዳን አደንቀዋለሁ፡፡
ቀጠን ያልክ ነህ፡፡ ለመሆኑ ኪሎህ ስንት ነው?
ኪሎ ላይ ወጥቼ አላውቅም፤ እስካሁን በግራም ነው የምመዘነው፡፡  
ልክ እንደወርቅ ማለት ነው?
ታዲያ! እኔስ ወርቅ አይደለሁ እንዴ!
እሱማ ነህ፡፡ ለመሆኑ ምግብ ላይ እንዴት ነህ?
ከጠጠር ውጭ የማልበላው ነገር የለም፤ ያገኘሁትን ነው የምበላው፡፡  
እስካሁን ያላነሳነውና መጨመር የምፈልገው ነገር ካለ?
በስራዬ የሚያበረታቱኝና አይዞህ የሚሉኝን የኪነ-ጥበብ አድናቂዎች አመሰግናለሁ፡፡ ጓደኞቼን ዮሐንስ ተፈራን (ዳጊ

ማኛ)፣ ተስፉ ብርሃኔን፣ ዮሀንስ ፈለቀንና ደረጀ ፍቅሩን በጣም አመሰግናቸዋለሁ፡፡ ሁሌም ከጐኔ በመሆን የጓደኝነት

ፍቅራቸውን ይለግሱኛል፡፡ በርካታ ስራዎችን እንድሰራ ሁኔታዎችን ያመቻቹልኛል፡፡ ከልቤ አመሰግናቸዋለሁ፡፡

እወዳቸዋለሁ፡፡ በመጨረሻም በጣም እንደማከብረው፣ እንደማደንቀውና እንደምወደው እንዲያውቅልኝ የምፈልገው

ከያኒው ፈለቀ የማር ውሀ አበበ፣ መልዕክቴ ይድረሰው፤ አመሰግናለሁ፡፡ 

Published in ጥበብ

“ድንቅና ግሩም ስራ ነው” - ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ
“መዝገቡ በኢትዮጵያ ጥበብ ላይ የራሱን አሻራ አስቀምጧል” - ሰዓሊ ታደሰ መስፍን
“እጁ ይባረክ”፤ “የስዕል ስራን ሰቀለው” - በርካታ ሰዓሊያን
ለወትሮው የስዕል አውደርዕይ ለመመልከት የሚመጣ ሰው በጣም ትንሽ ነው፡፡ ሰዓሊ መዝገቡ ተሰማ ግን ይለያል።

“ንግስ” ተብሎ በተሰየመው የመዝገቡ የሥዕል አውደርዕይ ላይ ከእስከዛሬው የተለየ ብዙ የስዕል ተመልካች

አስተውያለሁ። ከተከፈተበት ከህዳር 5 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ በየእለቱ ጠዋት ጠዋት የብሔራዊ ሙዚየሙ አዳራሽ

አካባቢ እስኪከፈት ተሰባስበው የሚጠብቁ ተመልካቾችን አይቻለሁ፡፡ 11 ሰዓት ላይ አዳራሹ ሊዘጋ ነው ሲባሉ

ከዓውደርዕይ ለመውጣት የማይፈልጉ ተመልካቾችም አጋጥመውኛል፡፡
የስዕል ዓውደርዕይ ለማየት የሚመጣ የሰዎች ጐርፍ በእድሜዬ የተመለከትኩት በሰዓሊ መዝገቡ ተሰማ “ንግስ” የተሰኘው

የስዕል አውደርዕይ ነው፡፡
እንደመነሻ
የሰዓሊና የመምህር መዝገቡ ተሰማ የስዕል ስራዎች የቀረቡበት “ንግስ” እስከመጪው ሰኞ ክፍት ሆኖ ይቆያል ቢባል፤ ቀኑ

እንዲራዘም ከተመልካቾች ጥያቄ እየቀረበ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ የስዕል ተመልካቾችም እየመጡ እንደሆነ

ሰምቻለሁ። የፅሁፌ አንኳር ጉዳይ ግን፣ የሰዓሊውን ትንቢታዊ ሐሳቦች በማንሳት፤ እንዲሁም ከ13 ዓመት በፊት በተለያዩ

ቃለመጠይቆችና ጽሑፎች ያሰፈራቸውን ሃሳቦች ከሁለት ስዕሎች ጋር (ማለትም “ንግስ” እና “የተዘረጋ” ከተኑ ስዕሎቼ

ጋር) በማያያዝ ለአንባቢያን ማካፈል ነው፡፡
የስራዎቹ ይዘት እና የአሳሳል ዘዬው ከሰዓሊውና ከእኛ ጋር ያላቸውን የጠበቀ ግንኙነት እዳስሳለሁ፡፡
በነገራችን ላይ “ንግስ” እና “የተዘረጋ” ከተሰኙት ስዕሎቹ አጠገብ ብቻ ነው መዝገቡ አጫጭር ግጥሞችን ያሰፈረው፡፡

“ንግስ”ን ለመስራት ሶስት ዓመት የፈጀበት ሲሆን፤ “የተዘረጋ” ደግሞ አንድ ዓመት ወስዶቦታል፡፡ በጠቅላላ 15 ስዕሎች

ናቸው በአውደርዕዩ ላይ የቀረቡት፡፡
መዝገቡ ማን ነው?
“የረባ የስዕል ትምህርት በማይሰጥበትና በይሆናል በሚሰራበት ሃገር ውስጥ፣ “ሰዓሊ ለመሆን አስበህ ታውቃለህ ወይ?”

የሚለውን ጥያቄ መመለስ ያስቸግራል፡፡ እኔ እንደአብዛኛው  ኢትዮጵያዊ አንድ የገጠር ከተማ ውስጥ ነው

የተወለድኩት፡፡ ያደግኩበት መሬት፤ ወላጆቼ፣ የማገኛቸው ሰዎች ፣ ከት/ቤትና ከመንደር ጓደኞቼ ጋር የምጫወታቸው

ነገሮች ሁሉ በእኔነቴ ላይ ድርሻ አላቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ፈጣሪ እያንዳንዱ ሰው ከሌላው የተለየ ችሎታ

እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ ተሰጥኦውን ፈልጐ ያገኘ ሰው እድለኛ ይሆናል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ይህን ሣያውቀው የሚያልፍበት

ሁኔታ አለ” ይላል ሰዓሊና መምህር መዝገቡ ተሰማ፡፡
መዝገቡ ተፈጥሮ ከቸረችው ጥበብ ጋር የት/ቤት መጽሐፍት ላይ የሚያያቸው ስዕሎች ናቸው ልዩ ፍቅር ያሳደሩበት፡፡  

ክፍል ውስጥ በተለይ ደግሞ የወላጆች ቀን በሚከበርበት ዕለት የሚሰራቸውን ስዕሎች የተመለከቱ ሰዎች፤ ከሌሎች

ጓደኞቹ የተሻለ እንደሆነ እየነገሩ ሲያደንቁት  ቀስ በቀስ ስዕል መስራት ጀመረ፡፡ መዝገቡ በልጅነቱ ያደገበትን አካባቢና

መልክዐምድር፣ የተጓዘባቸውን መንገዶችና መስኮች በጭራሽ አይረሳም፡፡ የአካባቢው አኗኗርና ባህላዊ ስርዓቶችም

በአእምሮው ተቀርፀዋል፡፡ በስራዎቹ ላይ የሚያሳየን ግን፣ እውነታውን “ኮፒ” በማድረግ ሳይሆን በምናቡ ቀምሞና

አድምቆ በሚያፈካ የፈጠራ ጥበብ ነው፡፡  የመዝገቡ ስራዎች ከፍተኛ ጉልበትን፣ ሃሳብን፣ ጊዜን፣ ጥበባዊ ክህሎትን

በእጅጉ የተላበሱ ናቸው፡፡  በስዕሎቹ ውስጥ የትላንትን ታሪክ፣ የዛሬውን ማንነት እና የነገን ምኞት በእርግጥ

ትመለከታላችሁ፡፡
ከዚህ ቀደም በአልያንስ ኢትዮ ፍራንሲስና በሸራተን አዲስ የመዝገቡን በርካታ ስራዎች ተመልክቼአቸዋለሁ፡፡ ስራዎቹ

ከእለት ወደ እለት፣ ከዓመት ወደ ዓመት፣ በይዘትና በቅርጽ፣ በአሣሣል ዘዬና በቀለም አጠቃቀም….እያደጉና እየመጠቁ

ሲሄዱ አስተውያለሁ፡፡
የመዝገቡ ስራዎች ትላንት እና ዛሬ
ሰዓሊ መምህር መዝገቡ ተሰማ ተወልዶ ያደገበት አካባቢ በስራዎቹ ላይ ብቻ ሳይሆን በአስተሳሰቡም ላይ ተጽእኖ

እንዳለው በ1993 ዓ.ም በወጣው ፈርጥ መጽሔት ቁ.24 ተናግሯል፡፡ “የአስተዳደግ ተጽእኖ በጣም ብዙ ነው፡፡ አንዳንዴ

በቃላት የሚነገር አይደለም፡፡ ገጠር ውስጥ የሚደረጉና የሚታዩ ነገሮችም አሉ፡፡ በአካባቢያችን ቤተክርስቲያን አለ።

የታቦትና የክብረ በዓላት ንግስ አለ፡፡ ከብቶችን ተከትለህ በእረኝነት ትሄዳለህ፡፡ ከጓደኞችህ ጋር ሆነህ ስትጮህ የገደል

ማሚቱ አለ፡፡ እነዚህ ነገሮች  ዝም ብለው  የትም ዋዥቀው የሚቀሩ አይደሉም። ስላደግህ፣ ስለተማርክ፣ ስላወቅህ

ከውስጥህ አይወጡም፡፡” መዝገቡ ከዛሬ 13 ዓመት በፊት በሰጠው በዚህ ቃለመጠይቅ፤ ወደፊት የሚሰራቸውን ስዕሎች

አመልክቷል፡፡ ሁለቱ ትንቢታዊ ስራዎቹ
በመዝገቡ ስራዎች ውስጥ፣ ከትላንት እስከ ዛሬ፣ የገጠር ህይወት አለ፤ ከብቶች፣ እረኝነት፣ የገጠር ሴት…ስራዎቹ ላይ

ፍንትው ብለው ይንፀባረቃሉ። ለአብነት፣ “ነጭ በነጭ” “ከስራ መልስ”፣ “እሷ” ፣ “የአገር ልጅ” ፣ “ጥበብ” የሚል ስያሜ

የሰጣቸው ቀደምት ስራዎቹ ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡
ዘንድሮ “ንግስ” ብሎ በሰየመው የስዕል ዓውደርዕይ ላይ ደግሞ፣ ጥበቡን ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግሮታል፡፡ በተለያየ ይዘትና

ቅርጽ፣ ቀምሞና ልቅም አድርጐ፣ የገጠር ህይወትን ከመልከዓምድር ጋር፣ ከብቶችን ያሰማሩ ወጣቶችን ከአካባቢው

አስገራሚ ቋጥኞች ጋር አዋህዶ የሰራቸውን ስዕሎች ስትመለከቱ፣ በልጅነት እድሜ ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ ሲጮህ

የሚሰማውን የገደል ማሚቶ ማዳመጥ የምትችሉ ይመስላችኋል፡፡
ከዛሬ 13 ዓመት በፊት በሰጠው ቃለመጠይቅ ላይ ሌላ ነገርም ጠቅሷል፡፡  አካባቢያቸው ላይ ቤተክርስቲያን፣  ታቦትና

የክብረ በዓል ንግስ እንዳለ ተናግሮ ነበር፡፡ ይህ የያኔው ቃለምልልሱ፣ የኋላኋላ “ንግስ” የሚል ስራ እንደሚሰራ ለእኔ

ጠቋሚ ነበር፡፡ የስነጥበብ ሰው ወደፊት የሚሰራውን ስራ አስቀድሞ አእምሮው ውስጥ ይታየዋል ማለት ነው ያስብላል፡፡

ደግነቱ፣ መዝገቡ በምናቡ ውስጥ የነበረውን አውጥቶ የመግለጽና የማሳየት ጥበብ ተክኗል፡፡  ይሄውና “ንግስ” የተሰኘውን

5ሜትር በ2 ሜትር ስፋት የተሰራውን ድንቅ ስዕል አበርክቶልናል፡፡ ይህ የስዕል ስራ ከያዘው ሃሳብ ጀምሮ የገፀባህሪያቶቹ

ብዛትና ስብጥር፣ የቀለም አጣጣል፣ የታሪክ አወቃቀርና ቅንብር፣ በአጠቃላይ ልቅም ተደርጐና አምሮ፣  መሰራቱን

ስንመለከት፣ የንግስ ስርዓቱ በእውን እየተከናወነ እንደሆነ ይመስለናል፡፡ ከዚያም በላይ አስደናቂ የክብር እና የሞገስ

መንፈስ ያድርብናል፡፡  
መዝገቡ ስለስራዎቹ ቀድሞ መተንበዩን “ንግስ” በሚለው ስራው ላይ አይተናል፡፡ ከአመታት በፊት በሃሳቦቹ ወጥኖ፣

በምናቡ ውስጥ ፀንሶ ዛሬ በእውን ያቀረበልን ሌሎች ስዕሎችም ነብይነቱን ይመሰክራሉ። ከእነዚህ ስዕሎች መካከል

አንዱ፣ በ1.5 X 3.9 ሜትር ስፋት የተሰራውና “የተዘረጋ” የተሰኘው ስዕል ነው፡፡ ሙሉ ለሙሉ የ“3D” ባህርይ

እንዲጐናፀፍ ተደርጐ የተሰራው ይሄው ስዕል፣ የእንቅስቃሴ ባህርይ ተላብሷል፡፡ ከበስተኋላ ብዙ ርቀት የሚጓዝ የቁጥሮች

መልክዐምድር አለ፡፡ ከብቶች ከተሰማሩበት መስክ ወዲህ ደግሞ በመሃለኛ ስፍራ ከቋጥኝ ላይ የተንጠራራ ወጣት እጁን

ወደፊት ዘርግቷል፡፡
መዝገቡ ዛሬ ያቀረበልን ይህን ድንቅ ስዕል እንደሚሰራ የሚጠቁም ሃሳብ ያካፈለን ከበርካታ አመታት በፊት ነው፡፡
“መስመር፤ በሥነ ጥበብ ንድፈ ሃሳብ ቀማሪዎች እይታ” በሚል ርዕስ “ብርሃንና ጥላ” በተሰኘው ጋዜጣ ላይ ግንቦት 1993

የፃፈው ሃሳብ እንዲህ ይላል:-
“መስመሮች (በስዕል) ጥበብ ቅንብር ውስጥ በአግባቡ እና በጥንቃቄ ካልተያዙ የስዕልን የቅንብር ህብረት ያዛባሉ፡፡

ስዕሉንም ለሁለት እና ከዚያም በላይ የተከፋፈለ፤ እንዲሁም በአላዋቂነት እና በዘፈቀደ የተሰራ ያስመስሉታል፡፡ ለምሣሌ፣

ጣት ወደ አንድ አቅጣጫ ሲቀሰር፣ በፍጥነት ወደተቀሰረበት አካል የምንዞረው፣ በጣቱ እና በአካሉ መሃከል (ምናባዊ)

መስመሮችን እየሞላን ነው”
መዝገቡ ከዚህ የመስመር ንድፈ ሃሳብ በመነሳት፣ ከሰው ሃሳብና እንቅስቃሴ ጋርም አስማምቶ በማጥናት የራሱን ስሜት

የሚገልጽባቸው እውን መስመሮችንና ከሰው እንቅስቃሴ ጋር የሚጣጣሙ ምናካዊ መስመሮችን በማዋሃድ፣ የ3D ባህርይ

የተጐናፀፈ ድንቅ የስዕል ስራ በ “ንግስ” የስዕል ዓውደ ርዕይ ላይ አቅርቦናል፡፡
የመዝገቡ ስዕሎች በሙሉ በከፍተኛ ጥናትና ምርምር የተሰሩ ናቸው፡፡ ያለምክንያት አይደለም። “እኔ ከዓለም አንደኛ የሆነ

ስዕል ለመስራት ነው የምነሳው፡፡ አለምን የሚያነቃንቅ ስራ እንዲሆንልኝ እፈልጋለሁ፡፡” ብሎ ነበር ከዛሬ 13 ዓመት

በፊት፡፡ እውነትም መዝገቡ የትንቢት ቃሉ ዛሬ እውን ሆኖ ድንቅ የሆኑ የስዕል ስራዎቹን አሳየን፡፡
ሰዓሊ መዝገቡ ተሰማ፣ ትልቅ ነገር ተመኝቶ፣ ያንን በሚመጥን ጥረት ቃሉን አክብሯል፡፡  እኔ የሚያሳስበኝ፤ እኛ የዚህ

በረከት ተቋዳሽ ለመሆን የታደልን ሰዎች፤ የተቻለንን ያህል እየተመኘን ለጥረት መነሳትና ቃላችንን ማክበር እንችላለን

ወይ የሚለው ጥያቄ ነው፡፡
እነዚህ ድንቅ የሐገር ሃብት የሆኑ የመዝገቡ ስዕሎች፣ በክብር እንዲቀመጡና ሁሉም ሰው እንዲያጣጥማቸው ማድረግ

ያቅተናልን? የመንግስት አካላትና ግለሰቦች (ባለሃብቶች) በመተባበር ስዕሎቹ በቅርስነት ለህዝብ ዘወትር በቋሚነት

እንዲታዩ ወደ ብሔራዊ ሙዚየም በማስገባት፣ ኃላፊነታችን መወጣት ይገባናል፡፡ ከእንግዲህ የመዝገቡ ስራዎች

የኢትዮጵያ ሃብት ናቸው፡፡
በ “ንግስ” የስዕል ዓውደርዕይ ላይ የቀረቡትን 15 ስዕሎች ለመስራት  6 ዓመት ፈጅቶበታል፡፡ በአጭር ጊዜ ብዙ ስራ

መስራት እየተቻለ፣ ለምን ብዙ ጊዜ የሚወስድ ስዕል ትሰራለህ ብትለኝ የምርጫ ጉዳይ ነው ይላል መዝገቡ፡፡ “በአንድ

ስዕል ላይ ብዙ ጊዜ መውሰዴ ምንም አይቆጨኝም፡፡ ይልቅ ለመስራት እየፈለግሁ በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ስጠመድ

ነው የምበሳጨው፡፡” በማለት ለጥበብ ያለውን ፍቅርና ጽናት ይገልፃል መዝገቡ፡፡
የመዝገቡ ተሰማ 15 የስዕል ስራዎች፣ ማንኛውንም ተመልካች የሚያስደንቁ ቢሆኑም ይበልጥ ደግሞ ሰዓሊዎችን

አስደምመዋል፡፡ በርካታ ሰዓሊያን ስራዎቹን እየደጋገሙ ለማየት ሲመላለሱም  አስተውያለሁ፡፡

Published in ጥበብ

የቱሪዝም ትልቁ ነገር ኢትዮጵያዊነትህን ለሌላው መሸጥ ነው…
“ጋሽ አበራ ሞላ” ይኑርም አይኑርም፣ ጥሩ ኢትዮጵያዊ አባወራ ነው…
ባለፈው ሰሞን ከአርቲስት ስለሺ  ደምሴ ጋር የተገናኘነው ቦሌ ሚሌኒዬም አዳራሽ ግቢ ውስጥ ነው፡፡ ከአጋሮቹ ጋር

በመተባበር ለገና በዓል ‹‹ያምራል አገሬ›› የሚለውን አዲስ አልበሙን በልዩ የመድረክ ትርኢት ለማቅረብ አስቧል፡፡

ከሁለት ወራት በፊት አልበሙ በብሄራዊ ትያትር ሲመረቅ ጋሽ አበራ ሞላ ከ250 በላይታዳሚዎችን ያረካ ትርኢት

አቅርቧል፡፡ ተመሳሳይ ትርኢት በሚጠበቅበት በገናው የሙዚቃ ዝግጅት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፤ ሙዚቃ አድናቂዎችና

የክብር እንግዶች የተካተቱበት 12ሺ ተመልካቾች ይታደማሉ፡፡ ከ10 በላይ የሙዚቃ መሳርያዎች የሚጫወቱ

ባለሙያዎችና ከ20 በላይ ዘማሪዎች ያሰባሰበ የኪነጥበብ ቡድንም ያሳትፋል። አርቲስት ስለሺ ደምሴ ከአዲስ አድማስ

ጋር ባደረገው ልዩ ቃለምልልስ ስለታሪክ አዋቂነቱ፤ ስለተረት አባትነቱ ታሪኮችና ተረቶችን ስለሚያገኝባቸው ምንጮቹ

እና ይዘታቸው፤ ምእራባውያን በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዛቸው ስላስጣሉን ወይም ስላሳጡን ባህላዊ ትውፊቶች እና ሌሎችም

ጉዳዮች ይናገራል፡፡
በሙዚቃ ባለሙያነትህ የሙዚቃ መሳርያዎችን መጫወት ብቻ ሳይሆን በመስራትና በማስተማርም ትታወቃለህ፡፡ ደግሞም

ታሪክ አዋቂ ነህ፡፡ የተረት አባትም ትመስለኛለህ ፡፡ ለመሆኑ ታሪክና ተረት ከሙዚቃ ጋር ምን ያስተሳስራቸዋል?
ህብረተሰቡ ውስጥ በተረት፤ በምሳሌ፤ በፍልስፍና፤ በምክር፤ በትንቢት መልክ የሚነገሩ ታሪኮችን በአንድ ላይ እና

በተናጠል ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የቆዩ  አፈታሪኮች ናቸው፡፡ ብዙዎቹ በፅሁፍ የወጡና የቀረቡ አይደሉም፡፡

ከድሮ ጀምሮ በቃል ሲነገሩ የኖሩ ናቸው። እየተወራረደ እና እየተወራረሰ የመጣ ባህል ነው፡፡ ራሱን የቻለ ትልቅ

ማህበረሰባዊ ትውፊት ነው። ስለ አንድ ህብረተሰብ ልዩ ልዩ ታሪኮችን መተረክ ቀደም ሲል የነበረ ነውና አንድም

በተናጠል ራሱን ችሎ ይሄዳል፡፡ በሌላ በኩል  ከሙዚቃ ጋር ተያይዘው  ተረትና ታሪክ የሚሰሩበት ባህልም አላቸው፡፡

ከሙዚቃ ጋር ተቀናጅተው ይሰራሉ፡፡
ምሳሌ ላቅርብልህ፤ ሁለት ሌቦች ናቸው፡፡ ከብት እንስረቅ ብለው አንድ ሃብታም ቤት ይገባሉ፡፡ አንደኛው አዝማሪ

ነው፡፡ አዝማሪው ምድነው የሚያደርገው ሰዎቹን በሙዚቃ ያጫውታል፡፡  ሌላኛው በጓሮ በኩል ሰተት ብሎ ገብቶ

ከብቶቹን ነድቶ ሊያወጣ ነው፡፡ በዚህ  ተስማምተዋል፡፡  ይህ ተረት ነው፡፡ ከጀርባው ሙዚቃ አጅቦት እንዴት ይዘጋጃል

መሰለህ፡፡
በጓሮ ዞሮ የገባው ሰውዬ ከብቶቹን ከበረት እያስወጣ ሲነዳ፣ ግቢው ውስጥ ሃይለኛ ውሻ ስላለች “ውውውውውው…”

ብላ አንዴ ስታናጋው፣ የቤቷ እመቤት በጓሮ በኩል የሆነ ነገር ስለሰሙ፤  ‹ኧረ ምንድነው የከብት ኮቴ ይሰማል› እያሉ

ይናገራሉ፡፡ ይህን ጊዜ ቤት ውስጥ ያለው አዝማሪ ‹‹አሮጊቷ መቼም አትተኛ ፤ ነይ ቡቺ ጥጥጥጥጥጥ” እያለ ያዜማል፡፡

ውሻዋ “ውውውውውው” ማለቷን ስትቀጥል፤ አዝማሪው “ነይ ቡቺ ጥጥጥጥጥ” እያለ ደጋግሞ ሲጠራት ጩኸቷን ትታ

ወደሱ ትመጣለች። አዝማሪው በጨዋታው የቤቱን ሰዎች አዘናጋ ማለት ነው፡፡ ሌላኛው ከብቶችን ዘርፎ ይወጣል። ተረቱ

እንዲህ በሙዚቃ ተውቦ አንድ ላይ ተቀናጅቶ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ይህን ተረት እኔ በሙዚቃ ስጫወት መጀመርያ ታሪኩን

እንደተረት እተርከዋለሁ፡፡ ታዳሚው ሁኔታው ፍንትው ብሎ እንዲታየው  ነው፡፡ በዚህ መልክ የሚነገሩ የተለያዩ አይነት

ተረቶች፣ አባባሎች፣ ዘይቤዎች፣ ፈሊጦች ከሙዚቃ ጋር እየተቀናጁ የሚሄዱበት መንገድ ነው፡፡
እነዚህን ታሪኮችና ተረቶችን ከየት ሰበሰብካቸው? ከተለያዩ የህይወት ተመክሮዎች ነው? ከሰዎች ሰምተህ ነው? ታሪክ

አጥንተህ ነው? በፈጠራ ችሎታህስ የሰራሃቸው አሉ?
 ሲነገሩ የነበሩ ታሪኮችን በመስማት ነው፡፡ ቀደም ሲል ከቤተሰቦቼ በተለይ ከአባቴ ብዙ ታሪኮች ይነገረኝ ነበር፡፡ አባቴ

ክራር ተጫዋች፤ ተረት ነጋሪና ታሪክ አዋቂ ነበር፡፡ ብዙ ነገሮች ያውቃል፡፡ በየጊዜው አዳዲስ ነገሮችን እየነገረ ነው

ያሳደገኝ፡፡ ሌላው ምንድነው አብሮ ከሚኖሩ ጎረቤቶች ጋር ቤተሰብ ቡና ሲጠጣ ከነበሩ ወጎች ነው። የድሮ ሰፈሬ

ጃንሜዳ አካባቢ የሚገኘው ቸሬ የተባለ አካባቢ ነበር፡፡ በዚያ ሰፈር ሰዎች ድግስ፣ ሰርግ፣ ለቅሶ እና ተስካር

የምትሰማቸው ብዙ ጨዋታዎች እና ታሪኮች አሉ፡፡ ይገርምሃል እኔ በልጅነቴ አሮጊቶችና አዛውንቶች ተሰብስበው

ሲያወጉ፤ ቡና ላይ የነበሩ ጨዋታዎችን መስማት ልማዴ ነበር፡፡ ብዙ ብዙ ታሪኮችን ሲጫወቱ ዛሬም ድረስ

አስታውሳቸዋለሁ፡፡ ቡና ተፈልቶ ጎረቤት ከተጠራ በኋላ እያንዳንዱ ጎረቤት በራሳቸው የጨዋታ ለዛ የሚያወራቸው

ታሪኮች ነበሩ፡፡ ቡና እስከ ሶስተኛ ይጠጣል፡፡ ሶስተኛ ሳይጠጣ ማንም ከቡናው አይነሳም።  ሲጫወቱም ትዝ ይለኛል፡፡

በሰርግና በሃዘን ህብረተሰቡ በእነዚህ ታሪኮች ፈጠራ ውስጥ ይኖራል፡፡ የአገራችን አባቶች ቋንቋቸው የረቀቀ፤

አመለካከታቸው የዳበረ፤ ፍልስፍናቸው ብዙ የሚያስረዳ ነው፡፡ የእነሱ ታሪኮች እና ጨዋታዎች ከቤተሰብ፤ ከጎረቤት፤

ከማህበረሰብ፤ ከአፈታሪክ ዘመን ከዘመን ሲሸጋገሩ የቆዩ ናቸው፡፡
ሌላው ምንጭ ታሪክ ነው፡፡ ብዙ የኢትዮጵያን ታሪክ የከተቡ መፅሃፍት ደግሞ እዚህ አገር ከተዘጋጀው እና ከሚገኘው

ይልቅ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተሰብስበው የሚገኙት ይልቃሉ፡፡ በፖርቹጊዝ፣ በስፓኒሽ፣ በጣሊያንኛና በእንግሊዝኛ

ቋንቋ ፀሃፊዎች የተዘጋጁ ናቸው፡፡ በ14ኛው እና በ16ኛው ክፍለዘመን ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ብዙ ጥናት ያደረጉ አሉ፡፡

እነዚህ ፀሃፍት ከኢትዮጵያ ተረቱን፣ አባባሉን፣ ዘይቤውን ወስደው በተለያዩ ቋንቋዎች ፅፈዋቸው ይገኛሉ፡፡ አንድ

በፈረንሳይኛ የተዘጋጀ መፅሃፍ አለ፤ ስለአማርኛ ቋንቋ የተፃፈ ነው፡፡ በዚህ መፅሃፍ በጣም የሚገርምህ አገኘሁ እንግዳ

ስለተባሉ በሐይለስላሴ ጊዜ ስለነበሩ ታዋቂ ሰዓሊ ይናገራል፡፡ በዚያን ጊዜ የነበረውን ብር ምስል የሰሩ ናቸው፡፡

በበጌምድር፣ በወሎና በሸዋ አካባቢዎች የተነገሩ  የድሮ ተረቶችን ከግዕዙ እና ከሰምና ወርቁ እያጣቀሰ፤ ከፈረንሳይኛው

ቋንቋ ጋር እያነፃፀረ ያቀርባል፡፡ በዚህ መፅሃፍ የአገኘው እንግዳ  ታሪክ ምንድነው? ጓደኛሞች ስለነበሩ አንድ በሬና አህያ

የሚተርክ ስዕላዊ ድርሰት ነው፡፡ በሬ እና አህያው በአንድ ሃብታም ቤት ሲያገለግሉ ቆይተው አቅም ሲያንሳቸው በሬው

እንዳይታረድ፤ አህያው ደግሞ እንዳይባረር ሰግተው ሰነበቱ፡፡ አልቀረላቸውም፤ ብዙም ሳይቆይ አባወራው ከቤቱ

ያሰናብታቸዋል፡፡ የኖሩበትን አገር ጥለው በመንገድ ሲሄዱ አንድ ደግሞ ከዶማ በቀር በሬ እና አህያ አይቶ የማያውቅ

የተቸገረ ደሃ ገበሬ ያገኛቸውና…. እንዲህ እያለ የሚቀጥል ደስ የሚል ታሪክ ነው፡፡
ብዙ ታሪካዊ ስብስቦችና ተረቶች በዚህ መልክ በውጭ አገር ተሰባስበው የተዘጋጁበት ነው፡፡ በሙዚቃውም ታሪክ ስብስቡ

በአብዛኛው በፈረንሳውያን፣ በፓርቱጋላዊያን በጣሊያናዊያን እና በሌሎች አገራት ሰዎች የተሰሩ ናቸው።
ከተረቶች እና ከታሪኮቹ ምን ምን ይገኛል?
ለምሳሌ የከበደ ሚካኤልን ታሪክና ምሳሌ ብትወስደው፤ በዚህ መፅሃፍ የሚገርም የጊዜን ምስል ያሳያል፤ የማይረሳ ምክር

ይሰጥሃል፤ ልዩ ልዩ የህይወት ዘዴዎችን ይነግርሃል፤ የተለያዩ አመለካከቶችን ያስገንዝበሃል፡፡ የአኗኗር ዘዴ፤ የአመለካከት

ዘዴ፤ የፈጠራ ዘዴ ትማርበታለህ፡፡ አሁን ለምሳሌ በከበደ ሚካኤል ታሪክና ምሳሌ መፅሃፍ ውስጥ የአንድ አዝማሪ እና

ወራጅ ውሃ ታሪክ አለ፡፡ አዝማሪው ያ ወንዝ በጎርፍ ሞልቶበት በመሰንቆው ለወንዙ፣ ይጫወትለታል፡፡ ከታች ወንዙ

የአዝማሪውን ጨዋታ ሰምቶ ሲያልፍ፣ ከላይ ያልሰማው ይመጣል፡፡ ሰውዬው በሰማ እና ባልሰማ ወንዝ ላይ ሲተክዝ

ታስተውላለህ፡፡ ሰውዬው ይህን ጎርፍ ባዜምለት ችግሬን አይቶ ያቆምኛል ብሎ አስቦስ እንደሆነ ማን ያውቃል፡፡ የሰማው

ሲሄድ ያልሰማው ሲመጣ እያለ ሲያዜም፣ ይህ ትልቅ አመለካከት ነው፡፡ የጠለቀ ነገር ነው። ብዙ እንድታስብ የሚያደርግ

ነው፡፡ አንድ ዋና ከሆነ ነገር የተለያየ አመለካከት መኖሩን የሚያሳይም ነው፡፡ አሁን በከበደ ሚካኤል ታሪክና ምሳሌ

ያለውን ያን አዝማሪ ሞኝ ልትለው ነው፡፡ አዝማሪው ብልህ ነው፡፡ ለዚያ ወንዝ እንደዚያ ብሎ ከልቡ ሲነግረው

አስበው፡፡ ያ ወንዝ ሰምቶ የሚቆም መስሎት እንደሆነስ፡፡ መፅሃፉ እንደሚለው፤ ክርስቶስ በውሃ ላይ ሄዷል፡፡ ከዚያ

በኋላ በውሃ ላይ የሄዱ ሰዎች የሉም፤ አሉ፡፡ የሰው ልጅ ከዚህም በላይ ሊያስብ ሊሰራ ይችላል ብሎ የሚያሳይ ነው፡፡

ከአናኗር ባህል ብልህነት እንደሚገኝ፤ ፈጠራ ሊኖር እንደሚችል የምትማርበት ነው፡፡
በተለያየ  ተፅእኖዎች ሳቢያ እነዚህ የገለፅካቸውን የባህል ትውፊቶች የራቅናቸው፤ የተውናቸው ይመስላል። መቼም ይህ

ሁኔታ ብዙ ነገር አሳጥቶናል አይደል?
ዛሬ በሚሰሩ የሙዚቃ ስራዎች እንዲህ በብቃት የሚታይ ትእይንት የሚሰራበት ሁኔታ ብዙም የዳበረ አይደለም፡፡

ሙዚቃዎች ከህብረተሰቡ ነባራዊ ሁኔታ እና አኗኗር ምንም አይነት ግንኙነት የላቸውም፡፡ ይህ በመሆኑ ከድሮ የባህል

ትውፊቶቻችን ጋር ተለያይተናል። ከኢትዮጵያዊነታችን ጋር የተሳሰረ የነበረው ሁሉ ግንኙነቱ እየጠፋ ቆይቷል፡፡

የመጀመርያው ያጣነው ስነምግባርን ነው፡፡ ስነምግባር ማለት ማክበርን፤ ጎንበስ ብለህ ሰላምታ መስጠትን፤ ተነስቶ

ተቀመጡ ማለትን፤ ማንኛውንም ሰው እንደእድሜው እንደማንነቱ ማክበርን … ዛሬ ቁምነገር አይሰጠውም፡፡ ይህን

በትምህርት ቤት አትማረውም፡፡ አክብሮት ባለማወቅህና ባለመማርህ ለሰው ክብርና ዋጋ አትሰጥም፡፡ ትሳደባለህ፤

ትሳለቃለህ፤ መብትህን ታጣዋለህ፤ ከወገኖችህ አክብሮት ስታጣ ቅሬታ ይሰማሃል፡፡ ማንነትህን ታጣለህ፡፡ ሌላው

የምታጣው ጠቃሚ እና ብልህ የሆኑ ዘዴዎችን ፈጠራዎችን ነው፡፡ አሁን ለምሳሌ ዛሬ ክራር፤ መሰንቆ፤ በገና የሚሰራ

የለም። እነዚህን ባህላዊ ትውፊቶችን ከኛ ተርፎ ለሌሎች መሸጥ የምንችልበት ጊዜ መሆን ነበረበት፡፡ የቱሪዝም ትልቁ

ነገር ኢትዮጵያዊነትህን ለሌላው ዓለም መሸጥ ነው፡፡ አመጋገቡን፤ አለባበሱን፤ ብልህነቱን አኗኗሩን፤ ስራውን

በኢትዮጵያዊ ትውፊት አዳብሮ፤ ራስን መሆን አዳጋች የሆነበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ አሁን እኔና አንተ ኮራጅ ሆነናል፡፡

ከውጭ የሚመጣ ሰልባጅ ለብሰህ፣ ቤትህን አጊጠህ፣ ያልሆነ ነገር ይዘህ ከሌላ ዓለም የሚመጣ ሰው ከአንተ የሚያገኘው

ነገር የለም፡፡ ስለዚህ ማነትህን ስታጣ አገርህን ትጎዳለህ፤ ራስህን ትጎዳለህ፡፡ ቀደም ሲል ስለኢትዮጵያ ሲነገር የነበረውና

የኖረው ቅድመ ስልጣኔው፤ ታሪኩ ፤ፍልስፍናው ፤ዘይቤው የክዋክብት ጥናት በለው፤ ምርምሩ በለው … እነዚህ ሁሉ  አሉ

የሚባሉት ነገሮች ጠፉ ማለት ነው፡፡ እነዚህ የኢትዮጵያዊነት መገለጫዎች ከጠፉ ከውጭ አገር የሚመጣ ቱሪስት ምንም

የሚያገኘው ነገር አይኖርም፡፡ እኛ ቋንቋችንን ብናዳብር፤ መፅሃፍት ብንፅፍ፤ ያሉትን ትውፊቶችን በመፅሃፍ ብናስቀምጥ፤

በሙዚቃ ብናዘጋጅ የሌላው ዓለም ሰው የማያገኘው ልዩ ነገር በመሆኑ ይገዛል፡፡ አንድ የውጭ አር ዜጋ እዚህ አገር ወዳለ

ሙዚቃ መሳርያ መሸጫ ቢሄድ የሚያየው ጊታሩን፤ ኪቦርዱን፤ ሳክስፎኑን ነው እንጂ ኢትዮጵያዊ የሆነ ክራር፤

እምቢልታ፤ ዋሽንትና ከበሮ አያገኝም፡፡
ትልቁ ተፅእኖ በእጅአዙር  ቅኝ አገዛዝ ተቀይሮ የተፈጠረው  ነው፡፡ ሁኔታው በቀጥታ አሽከር አያደርግህም፡፡

በትምህርት፤በአስተዳደር፤ በቋንቋ እና በሁሉም መስክ የእነሱን አካሄድ እንድትከተል በማድረግ ማንነትህን ማጥፋት

ነው፡፡  ዛሬ ዘመናዊ ትምህርት ቤቶች የተባሉት በምዕራቡ ዓለም አስተሳሰብ የተቀረፁ ናቸው። የኢትዮጵያ  ታሪክን

ትተህ የምትማረው ስለ አውሮፓ ሆኗል፡፡ ድሮ  በተማሪ ቤት በእነ“ለማ” በ“ገበያ” ምንባቦች የተማርንበት ጊዜ ላይ

ደርሸበታለሁ፡፡ በእነለማ ገበያ ፈንታ ታድያ ከውጭ እነ ሬድ ፕራይመር፣ እነ ሪደር ዋን፣ እነ ማርች ኦፍ ታይም የተባሉ

መፅሃፍት መጡ። ይገርምሃል እኔ ለማ በገበያ፤ ለማ በትምህርት ቤት የተባሉ መፅሃፍትን እያነበብኩ ነው ያደግሁት፡፡

ህፃናት የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ሲገቡ ለጀማሪ የሚሆን የአፍ መፍቻ ቋንቋ በንባብ የምትማርባቸው የታሪክ

መፅሃፍት ናቸው፡፡ ለማ በእነዚህ መፅሃፍት ውስጥ ባሉ ታሪኮች ውስጥ የሚገኝ ዋና ገፀባህርይ ነው፡፡ ያኔ ገጠርም ሆነ

ከተማ ልጅ አንድ አይነት አስተዳደግ ነው ያለው። ለማ ቁምጣ የሚለብስና ቁንጮ ያለው ትንሽዬ ልጅ ነው።  አሁን

ለምሳሌ “ለማ በገበያ” በሚባለው ታሪክ ለማ ዘወትር በጠዋት ተነስቶ የአባቱን ጥራጥሬዎች በየስልቻው አስገብቶ፣

አባቱን አጫጭኖ፣ ቁምጣውን ለብሶ እና በትሩን ይዞ፣ አባቱን እያገዘ ገበያ ይወጣል፡፡ የተጫነውን የእህል ጆንያ

ያወርዳል፤ ለገበያተኛ ይሰፍራል፡፡ ለማ ጎበዝ ልጅ ነው፡፡ታታሪ ነው … እያለ ታሪኩ ምክሩን ያስተላልፋል፡፡ “ለማ

በትምህርት ቤት” በሚለው ታሪክ ደግሞ ሰኞ ሆነ፤ ለማ በጠዋት ተነስቶ ልብሱን አዘጋጅቶ ወደ ተማሪ ቤት ሄደ፤

ትምህርት ቤት ገብቶ ሲማር ምን ያህል ጎበዝ እንደሆነ ታታሪነቱን  ያወጋል፡፡ “ለማና ዘመዶቹ” በሚለው ታሪክ ደግሞ

ለማ በቤተሰቡ ያለውን ጨዋነት ፤ ስነምግባሩን ሲማር እየተረከ የሚመክር ነው፡፡ የለማ ታሪኮች በየትምህርት ቤቱ

መማርያ መፅሃፍት ሆነው የተዘጋጁ ነበሩ፡፡ ከዚያ በፊት እኔ ትዝ ይለኛል … ትምህርት ቤት ሄጄ የለማን ታሪኰች

ሸምድጄ፣ እቤት ስገባ እናቴ የማገኛት እንጀራ እየጋገረች ይሆናል፡፡ ለማ ጎበዝ ልጅ ነው፤ ለማ ትምህርት ይወዳል

እያልኩ ሳነበንብላት፤ “ጎሽ የተባረከ ልጅ ነው፤ እግዚአብሄር ይስጠው” እያለች ትመርቀው ነበር፡፡ የለማ መፅሃፍት

ከየትምህርት ቤቱ መጥፋት የጀመሩት በ1950ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ነው፡፡  ከዚያ በኋላ የውጭ መፅሃፍት መጡ፡፡ ከዚያ

ኋላ ትዝ የሚለኝ ተማሪ ቤቱን ያጥለቀለቁት የእነ ሎንግማንሺፕ ህትመቶች የሆኑ የብሪቲሽ መፅሃፍት ናቸው፡፡ በእነዚህ

መፅሃፍት በትምህርት ቤት ውስጥ ማንነትህን ረስተህ፣ በሌላው አገር ታሪክ መማር የምትገደድበት ጊዜ ሆነ፡፡
የለማ ታሪኮች ከቀሩ በኋላ ሬድፕራይመር የተባለው መፅሃፍ መጣ፡፡ በዚህ መፅሃፍ በቀይ ቀለም በተፃፈ ንባብ በምስል

ድመት አለች፤ ጠረጴዛ ስር ቁጭ ብላለች፤ ከስሩ ‹‹ዘ ካት ኢዝ አንደር ዘ ቴብል ››ይላል ፤ በሌላ ምስል ደግሞ ድመቷ

ጠረጴዛው ላይ ወጥታ ከምትታይበት ስር ‹‹ዘ ካት ኢዝ ኦን ዘ ቴብል›› የሚለው አለ፡፡ መፅሃፉ ገፁ በሙሉ በድመቷ

የተሞላ ነው፡፡ በመፅሃፉ አዲስነት እና ማራኪ አቀራረብ ልጅ ስለሆንን በጉጉት እንሸመድደው ነበር። እኔ እቤት ገብቼ

እናቴ ዛሬ እንግሊዘኛ ተማረ ጎበዝ ትለኛለች ብዬ፤ ‹‹ዘ ካት  ኢዝ ኦን ዘ ቴብል›› ፤‹‹ ዘ ካት ኢዝ አንደር ዘ ቴብል››

እያልኩ ስለፈልፍ ብትሰማኝ ብትሰማኝ ለማ የለም፤ በኋላ ‹‹አንተ ይከትክትህና  መድሃኔያለም፤ ለማ የት ሄዶ ነው ካት

ካት የምትለው›› ብላ በማማሰያ ታባርረኛለች፡፡ እናቴ ይህ የለማ ነገር አንገብግቧት፣ በአይምሮዋ ገብቶ፣ ዣንጥላዋን ይዛ  

ትምህርት ቤት ሄደች፡፡ በአጠቃላይ ለማለት የፈለግሁት ከውጭ የመጣው ይህን የመሰሉት ተፅእኖዎች፣ በአገራችን

ያለውን ትውፊት ማሳጣቱን ነው። ትምህርቱ ብቻ አይደለም፤ በሙዚቃውም ተመሳሳይ ወረራ ነው፡፡ መሰንቆው፣ ክራሩ፣

ዋሽንቱ፤ ከበሮው የተረሳበትና የማያስፈልግበት ነገር ቀጠለ፡፡
በ1960ው በ1970ው በሙዚቃው ያለው ነገር ሁሉም ከምዕራቡ ዓለም መጥቶ ነው፡፡ እናም በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ

ጭንቅላታችን ተደብድቧል፡፡ ወደን በሰጠነው ፍቃድ በውጭው አገር ባህል ተበርዘናል። ይህም የራሳችንን ታሪክ

እንድንርቅ፣ ባህላችንን እንድንጠላ አድርጎናል፡፡ መማር ማወቅ ማለት የውጭ ስልጣኔ ተባለ። ስልጣኔ የራሱን ቋንቋ፣

ባህል እና ታሪክ አስተወው፡፡ ዛሬ የምታየው ይህ ሁሉ መደነቃቀፍ፤ ይህ ሁሉ ሌላ ሆኖ መተያየት ከዚህ የተነሳ ነው፡፡

ይህ፤ ሰው ወዶ በራሱ እንዴት ባርያ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ እነ ዩኔስኮ እኮ ዛሬ እኮ ቋንቋችሁን አዳብሩ፤ ልብሳችሁን

አትተው፤ ማንነታችሁ እየጠፋ ነው ብለው እየጨቀጨቁ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ዛሬ በኪነት ስሜትን የሚገዛ፤ ማንነትህን

የሚገልፅ አቀራረብ እንደገና ፈልገን እየሰራን ያለነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ማንነትን መልሶ ለማምጣት እንደገና ለማስተማር

ነው፡፡ እኔ ወደ ራስ ጉዞን እመኛለሁ፡፡ ፍላጎቱንም እያየሁ ነው፡፡ የሰው ልጅ ትልቁ ነገር ራሱን ማወቅ ነው፡፡ አለበለዚያ

ቀውስ ውስጥ ይገባል፡፡ ከአዲሱ ‹‹ያምራል አገሬ›› አልበም በፊት በመፅሃፍት እና ሙዚቃ መልክ የሰራናቸው፣ ለህፃናት

ማስተማርያ ይሆናሉ ያልናቸው ሁለት ስራዎች አሉን፡፡  ለምሳሌ ስለ እነሶረኔ ስለ እነዳንኪራ፤ ስለ እነ አያጅቦ በሙዚቃ

በማጀብ ብቻ ሳይሆን ህፃናትን ሊያስረዱ በሚችሉ ትእይንቶች ተቀናብረው ተዘጋጅተዋል፡፡ እነዚህን መፅሃፍት፤ የዘፈን

ስብስቦች እና ቪድዮዎች ያዘጋጀነው ለህፃናት፤ ለወጣቱ እና ለአዛውንቱ እንደየእድሜው ነው፡፡ የማህበረሰቡን አኗኗር፣

አመለካከት፣ የፈጠራ ችሎታ ወዘተ የሚያንፀባርቁ ብዙ ታሪኮች ተሰባስበዋል፡፡ ስለባህላዊ የሙዚቃ መሳርያዎች አሰራር

እና አጨዋወት የሚያስገነዝቡ፤ የኢትዮጵያን ታሪኮች የሚያወሱ የመማርያ መፅሃፍት ተዘጋጅተው እንዲሰራጩ ለማድረግ

ከትምህርት እና ባህል ሚኒስቴር መስርያ ቤቶች ጋር በመተባበር ለመስራት ተስማምተናል፡፡
ባህላዊ የሙዚቃ መሳርያዎቻችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነት ያገኛሉ?  ተፈላጊ የሚሆኑበት ገበያስ ይኖራቸዋል?
ክራር ዓለም አቀፍ የሙዚቃ መሳርያ አይደለም የሚሉት መጫወት የማይችሉት ናቸው፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ስለ

ኢትዮጵያ ሙዚቃ አያውቁም፡፡ ማወቅ ስላልፈለጉ ወደ ውጭ አለም ገቡ፤ ማንነታችሁን አሳዩ  ሲባሉ የሚቀበላቸው

አጡ፡፡ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ለማወቅ ሂድ እስቲ ጋምቤላ፤ ሂድ እስቲ ኢሊባቡር፤  ሂድ ጋሞጎፋ… ዛሬ ጃዝ ብለህ

የምታገኘውን ሙዚቃ እዚያ በየመንደሩ በባህላዊ ሙዚቃዎች ተሰርቶ ታገኛለህ፡፡
እነዚህን አገር በቀል የሙዚቃ ፈጠራዎች በልዩ ሁኔታ አቀናብረህ ለዓለም አቀፍ ገበያ ተፎካካሪ አድርገህ ማቅረብ

ትችላለህ፡፡ የራሳችንን ሙዚቃ አፍረን ትተነው እንጅ ባህላዊ የሙዚቃ መሳርያዎቻችን ስላልተፈለጉ አይደለም፡፡ እኔ

አለሁ አሁን፣ በባህላዊ ሙዚቃ መሳርያዎች እየተጫወትኩ ዓለምን የምዞረው፡፡ ስንት አፍሪካዊ በራሱ ሙዚቃ ባህል

ዓለምን ማርኮ የለም እንዴ፡፡ የዓለም ሙዚቃ መሰረቱ እኮ ከአፍሪካ ነው፡፡ አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ እንዲህ በዓለም

አቀፍ ደረጃ የገነነ የሙዚቃ ባለሙያ የሆነው በኢትዮጵያ ጨዋታ ስልት ነው፡፡ ባሉን ባህላዊ ትውፊቶች ለዓለም አቀፍ

ደረጃ የምንበቃበት ጅማሮዎች አሉ፤ ደረጃ በደረጃ እየታመነበት መጥቷል፡፡ በ“ያምራል አገሬ” አልበም ባህላዊ የሙዚቃ

መሳርያዎችን የምንጠቀመው ለዚህ ነው፡፡ ዋሽንት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ዋና የሚባል የሙዚቃ መሳርያ ነው፡፡ ሰዎች

በእረኝነት በየጫካው በየዱሩ፤ በየአካባቢው እራሳቸውን የሚያዝናኑበት፤ ከእንስሳቱ ጋር የሚጫወቱበት፤ ራሳቸውን

የሚያዩበት … የትንፋሽ መሳርያዎች አንዱ ነው፡፡ ክራርም እንደዚሁ ቅድመ ታሪክ ያለው፣ ስለክር መሳርያዎች ስናወራ

ግንባር ቀደም ሆኖ የሚጠቀስ፣ በብዙ የጨዋታ ስልቶች የዳበረ ትልቅ ሚና ያለው መሳርያ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ባህላዊ

ሙዚቃ ቅኝቶች ከክራር ገመዶች የመነጩ ናቸው። ከበሮዎችም በየሰርጉ፣ በየድግሱ፣ በማህበረሰባዊ ጨዋታዎች

የሚያስፈልግ መሳርያ እንደሆነ ይታወቃል። የሌሎች የሙዚቃ መሳርያዎች ድጋፍ ሳያስፈልግ በከበሮ ጨዋታ ሊደምቅ

ይችላል፡፡ ከበሮ የሌሎች የሙዚቃ መሳርያዎችን አጀብ ሳትፈልግ የምትሰራበት ነው፡፡ መሰንቆ ደግሞ ራሱን የቻለ

እንደክራር ትልቅ ጥቅም ያለው፣ ከአገር ወደ አገር ተሸክመኸው በቀላሉ የምትጓዝበት ነው፡፡ የአዝማሪ ዋና መለያው

መሳርያ ነው። እነዚህንና ሌሎች የሙዚቃ መሳርያዎችን በመጠቀም ታሪኩን ማንነቱን በአንድ ላይ አዋህዶ በማቅረብ

ዓለምን መማረክ አያዳግትም። በባህላዊ ሙዚቃ መሳርያዎች ኢትዮጵያዊ ባህልን ማሳየት ይቻላል፡፡ ባህሉን በባህል

መስራት ነው፡፡ ከታሪክ እና ከማንነት የተዋሃደ አቀራረብ እንጅ ከሌላ በመጣ ባህል ጉራማይሌ መሆን የለበትም፡፡
በዘፈኖችህ ላይ የድምፅ ቅላፄህን በተለያየ መንገድ እና ስሜት ታወጣለህ፡፡ በሌላ በኩል ብዙውን ጊዜ ሙዚቃዎችህን

መድረክ ላይ ስትጫወት የምትጨማምረው ነገር አታጣም፤ ከምን የተነሳ ነው?
የኢትዮጵያ ሙዚቃ ከሌላው አለም የሚለይበት አንዱም ምክንያት፣ የአዘፋፈን ስልቱ እና የድምፅ ቅላፄ አወጣጥ ነው፡፡

ማንሾካሾክ ነው፡፡ ከአፍ ሳይሆን ከሆድ ውስጥ የሚወጣ ማንሾካሾክ ነው፡፡ የድምፅ ሂደቶች አሉ፡፡ በጣም የተኛ፣

ከመሬት ውስጥ ቆፍሮ የሚወጣ የሚመስል ድምፅ አለ፡፡ ለምሳሌ አባይ በሚለው ዘፈን ላይ ስትሰማ፣ በመጀመርያው

ስንኞች ‹‹አባቱ መጀን እናቱ ጣና›› የሚለው ድምፅ ላይ ከስር እንደ እሳተ ጎመራ የሚወጣ ድምፅ አለ፡፡ ነፍስ ያለው፣

ከስሜት ጋር የተገናኘ ድምፅ ነው፡፡ የተለያዩ ሙዚቃ ማጀቢያ ምታዊ ዘዴዎችም አሉ፡፡ እንደማጨብጨብ ፤ እንደጣትን

ማንጣጣት እንደማፏጨት አይነት  ነው፡፡ በማንሾካሾክ እና የተለያዩ ድምፆችን በማውጣት መዝፈን ነው፡፡ በዚህ

መንገድ ሙዚቃዎቼን መስራት ፍላጎቴ በመሆኑ ነው፡፡ ለእኛ አገር ሰዎች የነበረውን አዘፋፈን እና የራሴን ፈጠራ በማከል

የምሰራው ነው፡፡ ድምፆቹ ከመመራመር፤ ታሪኮችን ከመመርመር የሚፈልቁ ናቸው፡፡ ቀስ በቀስ የሚዳብሩ ናቸው፡፡ አሁን

በአገራችን ባሉት ሙዚቃዎች  አዘፋፈን የተለመደው አንድ አይነት ድምፅ ነው፡፡ አንድ አይነት አገላለፅ ነው፡፡ አንዱ

ዘፈን ከሌላው የሚለይበት መልክ የለውም፡፡ እኔ ራሴ የማወጣቸው ድምፆች ግን በየዘፈኑ እንደየመልኩ እና

እንደሁኔታው በፈጠራ የማወጣቸው ናቸው፡፡ የተለያዩ ድምፆችን የማውጣት ጥቅም በሙዚቃው ነገሮችን በተለያየ

አቅጣጫ ማየት ስለሚያስችል ነው፡፡ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቅኝቶች አራት ናቸው ይባላል፡፡ ባቲ፣ አምባሰል፣ አንቺ ሆዬ..  

እየተባሉ የተሰጡ የሙዚቃ ቅኝቶች ስያሜዎች ናቸው። ለእኔ ቃኘ ማለት አየ ማለት ነው፡፡ ቃኘ ማለት አዳመጠ ማለት

ነው። አሁን ድምፅ የምትቃኘው ሰምተህ እንደ አላርም ነው፡፡ ሰማ ማለት አየ፤ አየ ማለት ደግሞ ሰማ ነው። ስለዚህ

ምንድነው…. ሁኔታዎችን በተለያየ መንገድ ማየት መቻል አለብህ፡፡ ጠዋት ተነስተህ ውለህ፣ ማታ ተኝተህ በየቀኑ አንድ

አይነት ነገሮችን የምታደርግ ከሆነ፣ የሰውነት ባህርይ ወይንም የማሰብ ባህርይ እንደ ሰው አይደለም፡፡፡ ማንም ሰው

ነገሮችን በብዙ መንገድ እና በተለያየ ሁኔታ ማየት እና መገንዘብ አለበት፡፡ በያይነቱ መንገድ  ፈልጎ መቃኘት አለበት፡፡

ከሰጭነት ይልቅ ተቀባይነቱ፤ የተሰጠህን ስትቀበል በተለያየ አቅጣጫ ማየት ይኖርብሃል፡፡ የሰጭው ብቻ ሁኔታ መሆን

የለበትም፡፡ አንተ መፅሃፍ ሰርተህ እኔ ሳነበው እኔ በሚሰማኝ ስሜት፤ ከምሄድበት ጎዳና ጋር እያነፃፀርኩ እና

እያመሳከርኩ መጓዝ አለብኝ፡፡ እኔ ያንተን ህይወት ከእኔው ጋር አዛምጄው  የራሴን ግንዛቤ እንድፈልግ ማድረግ ነው፡፡
እኔ በተፈጥሮዬ አስተዳደጌ ላይ ከነበረው ነፃነት፤ ከሰፈር አኗኗር ብዙ የተማርኩት አለ፡፡ ዛሬም ቢሆን እኔ የህብረተሰቡን

አኗኗር እና ሁኔታ ማወቅም መኖርም ስለምወድ የማልገባበት ቦታ የለም፡፡ እኔ ካቲካላ ቤት፤ ጠላ ቤት እገባለሁ፤

ከወገኖቼ ጋር መጫወት ደስ ይለኛል፡፡ አርቲስት ሆነህ የጠላ መጠጫ ሽክናን በእጅህ ካልያዝከው፣ ጠላውን ካልጠጣህ

ስለጠላ ምን ልታወራ ነው፡፡ በሙዚቃዎቼ ያሉት  ሁኔታዎች የማውቃቸው፤ ያደረግኳቸው፣ የለምድኳቸው የማህበረሰብ

ነባራዊ ገፅታዎች ናቸው፡፡ ጥሩ ሙዚቃ ድምፅን እንደ ስዕል በሚያሳይ አገላለፅ የሚቀርብ ነው፡፡ በጥሩ ሙዚቃ ውጥት

ባለ ድምፅ ውስጥ ሃዘኑን፣ ደስታውን፣ ትዝታውን፣ መከራውን፣ ሰቆቃውን ትሰማበታለህ። ግጥሙን ተወው፤ የሰውዬውን

የድምፅ አወጣጥ፣ ቅላፄውን አድምጠህ መረዳት ትችልበታለህ፡፡ ሙዚቃን የሚያዳምጥ ሰው፤ ስሜቱን መግዛት

የምትችለው በተለያየ የድምፅ ሂደት ስትዘፍን እና ስትጫወት ነው፡፡
በሙዚቃዬ ሁሌም እንደአዲስ መስራት መጫወት እፈልጋለሁ፡፡ ዋናው ነፃነቱ ነው፡፡ ኪነት ነፃነት ነው፡፡ ኪነት ከሁሉ

ነገር ነፃ የሚያደርግ ጥበብ ነው፡፡ ለሰው ብለህ አይደለም የምትሰራው፡፡ ስሜትህን ከውስጥ የሚሰማህን ነገር አውጥተህ

በነፃነት መስጠት መቻል አለብህ፡፡ ከብዙ ጊዜ ልምድ በመነሳት ሰው ምን ማወቅ፣ ምን ማየት እንደሚፈልግ በመረዳት

የምታደርገው ነው፡፡ ነገሮችን በይበልጥ እይታ እና ስሜት ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ ነው፤ ‹‹ኢምፕሮቫይዜሽን››፡፡ ማንም

ሰው በሙዚቃህ የበለጠ እይታ እና መግባባት እንዲኖረው ማድረግ ያስደስታል፡፡ በዜማ፣ በግጥምና በውዝዋዜ አሻሽለህ

በመስራትና በማዳበር ማዝናናት ትችላለህ፡፡ እንቅስቃሴን እየሰባበርክ ታዳሚህ የበለጠ እይታ እንዲኖረው፣ በፍላጎት

ስትሰራበት የሚያዋጣ ይሆናል፡፡ ይህ ሁሉ ማንም ሰው ሙዚቃውን በጥልቀት እንዲገነዘበው ነው፡፡
ግጥሞችህን እንዴትና በምን አይነት ሁኔታ ትፅፋቸዋለህ?
እኔ ግጥም ቁጭ ብዬ ቃላት በመደርደርና ቤት በመምታት  አልፅፍም፡፡ በመጀመርያ ስሜቴን ነው የማዳምጠው፡፡

መንገድ እየሄድኩ ከሆነ፣ በየአካባቢው ያየሁትን እንድምታ በጭንቅላቴ አስቀምጠዋለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ በአዕምሮዬ

የተቀመጠውን ነገር በስሜት እገልፀዋለሁ፡፡ ቃላቶች ቤት እንዲመቱ ብዬ አልጨነቅም፡፡ እይታው ላይ ነው የማተኩረው

፡፡ የተፈጠሩ ሁኔታዎች በአግባቡ መገለፅ አለባቸው፡፡ አሁን ብዙዎች ስለዛፍ ሲያወሩ አስበውት ነው፡፡ እኔ የዛፍን እይታ

በደንብ አዕምሮዬ ውስጥ አስቀምጠዋለሁ፡፡ የዛፍን መንፈስ እና ህይወት በአዕምሮ እንደስንቅ ካኖርከው በኋላ፣ የዛፍን

ጠቀሜታ ካዋሃድክ በኋላ ትተነፍሰዋለህ ማለት ነው፡፡ ትንፋሽህን በፅሁፍ መልክ ወረቀት ላይ ታስቀምጠዋለህ። ለምሳሌ

ልጅ ሲወለድ እንዴት ነው? ፅንስ መጀመርያ የሚፈጠረው ከሁለት ህይወት ውስጥ ነው፡፡ ልጁ የሚመጣው በኋላ ነው፡፡

ከዚያ  በፊት ግን ልጅ ቢኖረኝ ብለህ ሃሳቡን ትፀንሳለህ፡፡ ፅንሱ ተፀንሶ ነው ከዚያ በኋላ ልጅ የሚወለደው፡፡ አንድ

ሃሳብ መፀነስ አለበት። በአዕምሮህ ሳይፀነስ የተገጠመ ሃሳብ ግጥም መስሎ አይታየኝም፡፡ ሃሳብን ፀንሰኸው አርግዘኸው

ስትወልደው እያንዳንዱን ህመም፣ ደስታውን፣ አካሄዱን ስትናገር ለሌላው የሚሰማ ይሆናል፡፡ ያንተን ፅንስ ከዚያ በኋላ

ሌላው ይወልደዋል፡፡ በ“ያምራል አገሬ” አልበም ውስጥ ባሉ ዜማዎች ያሉ የግጥም ሃሳቦች መነሻቸው ስዕላዊ ድርሰት

ነው፡፡ ሰው የኖረበትና የሄደበትን ህይወት የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ዘፈኖቹ የተመረጡት ከብዙዎች መካከል ነው፡፡ በሺዎች

የሚቆጠሩ ሙዚቃዎች አሉ፤ የተፃፉ የተቀመጡ ናቸው፡፡ እነዚህ የሙዚቃ ጨዋታዎች የሚያገለግሉት ለምንድነው? አንድ

ራሱን የቻለ ባህል ቀደም ሲል ትውፊቱ  የነበረና ለብዙ አመት ተረስቶ የቆየ፤ እይታው ሁሉ ጠፍቶ የነበረውን እንደገና

እንዲነሳ በታሰበ ዓላማ የተሰሩ ናቸው፡፡ ስለምንትዋብ፤ ስለጋሽ አበራ ሞላ፤ ስለአባይ ስናወራ፣ እነዚህ ሁኔታዎች ጥሩ

እይታ የሚፈጥሩ ይሆናሉ በሚል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ባህላዊ ትውፊቶች ደብዝዘው እና ጠፍተው በነበሩበት ሁኔታ ላይ

እነዚህን አይነት ዜማዊ  ስዕሎች በህዝብ አይምሮ ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ፣ ከህፃናት አንስቶ እስከ አዛውንት

እንዲሰሙት እንዲነሳሱበት ነው፡፡ ሁሉም ሰው ሲሰማው ማንነቱን ማወቅ ይፈልጋል፡፡
ጋሽ አበራ ሞላ ምን አይነት ሰው ናቸው?
ጋሽ አበራ ሞላን በስብዕናቸው ብገልፅልህ ባህርያቸውን  አርቲስት ስለሺ ደምሴ ራሱ ነው የሚል መደምደሚያ ላይ

ትደርስ ይሆናል፡፡ ጋሽ አበራ ሞላ የሚለው ስሙን ራሱን ተርጉመህ ተንትነው፡፡ ጋሽ የሚለው አክብሮት ነው፡፡ ወንድም

ጋሼ፤ መከታዬ፤ ጋሻዬ ብላ አክብሮትህን ትገልፅበታለህ፡፡ ጥላ፤ ከለላዬ፤ ጥንካሬዬ ብለህ የምትረዳው የሙገሳ ማዕረግ

ነው፡፡ አበራ ብለህ ስትጠራ ደግሞ ብሩህ፤ ብርሃን፤ አንድ ነገር አበራ ስትል እይታ ፈጠረ፤ ተስፋ ፈጠረ ብለህ

የምትገልፀው ነው፡፡ ሞላ ደግሞ የሃሳብህን መሙላት፤ ያሰብከው ስለተሳካ የምትገልፅበት ትርጉም ይኖረዋል፡፡ ስሙ

በእነዚህ ትርጓሜዎች አንድነት የሚገለፅ ነው፡፡ ስለዚህ ጋሽ አበራ ሞላ እንደስሞቹ ትርጓሜ አሳቢ ሰው፤ ብርሃንን ማየት

የሚሻ፤ ተስፋን ማግኘት የሚፈልግ፤ አዋቂ ብልህ መካሪ፤ በህብረተሰቡ ውስጥ የተከበረ፣ አንቱ የሚባል ስብዕና ይኖረዋል

ማለት ነው፡፡ ጋሽ አበራ ሞላ የሚባል በህይወት ይኑርም አይኑርም ጥሩ ኢትዮጵያዊ አባወራ ማለት ነው፡፡

Published in ጥበብ
Saturday, 30 November 2013 11:52

የጥበብ ጉዞ

ከ“ፊያሜታ” እስከ “የእኔ እውነት”

በአስመራ ከተማ ተወልዶ በአዲስ አበባ ያደገው ወጣት አስረስ አሰፋ፤ ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ በቦሌ ሁለተኛ ደረጃ

“ፊያሜታ” የተባለ የቲያትር ክበብ በማቋቋም በርካታ ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣቶች ኮትኩቶ ለፍሬ እንዳበቃ ይናገራል፡፡

ለተለያዩ ወጣት ድምፃውያንም ግጥሞችና ዜማዎች ደርሷል፡፡ ለረዥም ጊዜ ከጥበብ መድረክ ከጠፋ በኋላ በቅርቡ “የእኔ

ህይወት” የተሰኘ ትያትር በመፃፍ ለተመልካች አቅርቧል፡፡ ጋዜጠኛ ሰላም ገረመው በስራውና በህይወቱ ዙርያ ተከታዩን

ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡


ትያትር መስራት የጀመርከው ቦሌ ት/ቤት መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡ እስቲ እንዴት እንደጀመርክ ንገረኝ…
ስምንተኛ ክፍል እስክደርስ ምንም አይነት የጥበብ ስሜት አልነበረኝም፤ በኋላ ግን ሚኒስትሪ ወስጄ እቤት

በተቀመጥኩበት ወቅት በርካታ ልቦለድ መፅሃፎችን ማንበብ ጀመርኩ፡፡ ይሄኔ ትንሽም ቢሆን ፍላጎቱ በውስጤ አደረ፡፡

ሚኒስትሪ አልፌ ሁለተኛ ደረጃ የተመደብኩት ምስራቅ አጠቃላይ ቢሆንም የእኛ ቤት ገርጂ ስለነበር፣ ምስራቅ አጠቃላይ

ይርቀኛል ተብሎ ቦሌ ት/ቤት ገባሁ። እዚህ ት/ቤት እንደገባሁ ነው ማስታወቂያ ያየሁት፡፡ የአጭር ጊዜ የትያትር ስልጠና

መውሰድ ለሚፈልጉ ባህልና ቱሪዝም ያወጣው ማስታወቂያ ነበር፡፡ በዚህ እድል ለመጠቀም አስቤ ተመዘገብኩ፡፡ በወቅቱ

አሁን ድረስ የማደንቀው ዳንኤል ተስፋዬ ነበር የሚያስተምረው። አንጋፋ አርቲስቶችም እየመጡ ልምዳቸውን ያካፍሉን

ነበር፡፡ እንደነ በኃይሉ የመሳሰሉት፡፡ እኔ ግን የአዘጋጅነት ስልጠና በተጨማሪ ወሰድኩኝ፡፡ ከዚያም “ፊያሜታ” የተባለ

የቲያትር ክበብ ተቋቁሞ ስለነበር፣ በዛ ክበብ ውስጥ ቲያትሮችን መፃፍና ማዘጋጀት ጀመርኩ፡፡ ብዙ ተስጥኦ የነበራቸው

ወጣቶች፤ በርካታ ልምዶች እንዲያገኙም የአቅሜን አድርጌአለሁ፡፡
እስቲ ለምሳሌ …
ሸዊት ከበደ አሁንም ድረስ በጣም ጓደኛዬ ናት። ስናፍቅሽ ተስፋዬ፣ ዕዝራ ዕጅጉ፣ አንተነህ አለሙ፣ ሰለሞን ሞገስ ወዘተ…

በዚህ ስራ የገፉና ታዋቂ የሆኑ አሉ፤ ሙያውን ሙሉ በሙሉ የተዉም አሉ፡፡
ቦሌ ት/ቤት ለበርካታ ዓመታት የታዩ ትያትሮችን ለምን ወደ ትያትር ቤት አመጣሃቸው?
የዛን ጊዜ የአማተር እንቅስቃሴ ነበር፡፡ ከግቢው ማህበረሰብ አያልፍም፤ ላይብረሪ ውስጥ ነበር የሚታየው። በእርግጥ

ጠንካራ ስራዎችን እንሰራ ነበር፡፡ ግን ወደ ሰፊው ህዝብ የሚደርስበት አጋጣሚ አልነበረም።
ሬዲዮ ላይም ትሰራ ነበር ሲባል ሰምቻለሁ …
ለገዳዲ ሬዲዮ ላይ ብዙ ትምህርታዊ ድራማዎችን ሰርቻለሁ፡፡ በቁጥር አላስታውሳቸውም፡፡ በወቅቱ አንድ ወር

ለሚተላለፍ ድራማ ሰላሳ ብር ይከፈለን ነበር፡፡ በዚህ ጣቢያ ላይ እኔ ብቻ ሳልሆን እነ ሸዊትም ሰርተዋል፡፡
በት/ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ያሳየኸውን ቲያትር ታስታውሰዋለህ?
“የጎዳና ህይወት” የተባለ ለአራት አመታት የታየ ቲያትር ነው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ “ሶስትዮሽ ጦር” የተባለ ሙሉ በሙሉ

በግጥም የተፃፈ ቲያትር ሰራሁ፡፡ በግጥም ያደረኩበት ምክንያት እኔ የሎሬት ፀጋዬ አድናቂና ወዳጅ ነኝ፡፡ የእሳቸውን ስራ

እንድወድና እንድከተል ያደረገኝ ደግሞ ዳንኤል ፀጋዬ ነበር። የሎሬት የሆኑ ስራዎችን በሙሉ አይቻለሁም

አንብቤያለሁም፡፡ በዚህ ምክንያት ነበር “ሶስትዮሽ ጦር”ን በግጥም የፃፍኩት፡፡ ይህ ቲያትር ለስድስት አመታት ታይቷል፡፡
“ፊያሜታ” ክበብ ለምንድነው የፈረሰው?
ሲጀመር ከ15 በላይ ነበርን፡፡ ት/ቤቱ ከፍተኛ ድጋፍ አድርጎልን እንደውም አንድ ክፍል ሰጥቶን ልምምድ እናደርግ

ነበር፡፡ ለመፍረሱ ምክንያት አንደኛው ሁላችንም ትምህርት ቤቱን ለቀን ከወጣን በኋላ፣ እንደበፊቱ ጠንክረን ለመስራትና

ክበቡን ለማሳደግ አልቻልንም። ስለዚህ ቲያትሮቹ ብቻ እየታዩ ክበቡ ግን መቀጠል አልቻለም፡፡ ሌላው ስሜት የተጫነው

ስብስብ ነበር፤ በፍቅር የሚሰራ ቢሆንም መቼና የት ቦታ መውጣት እንዳለበት የሚያውቅ አይደለም፤ የሚጠቁመንም

አካል አልነበረም። ሙሉ ጊዜአችንን የሰጠነው ለዚህ ክበብ ነበር። ከትምህርታችን እየቀረን ሁሉ ልምምድ እናደርግ

ነበር፡፡ ቅዳሜና እሁድ ሳይቀር እየተገናኘን እስከ ምሽት እንሰራለን፡፡ በዚህም ሳቢያ ቤተሰቦቻችን ይቆጡን ነበር፡፡ እናም

በመጨረሻ ፈረሰ፡፡
ክበቡ ባይፈርስ አሁን ምን ደረጃ ላይ ይደርስ ነበር?
በርግጠኝነት ጥሩ ተፅእኖ ፈጣሪ፣ ትልቅ ልዩነት የሚያመጣ ይሆን ነበር፡፡ እኔ 11ኛ ክፍልን ስጨርስ ነበር ከማህበሩ

የለቀቅሁት፤ ምክንያቱም ትምህርት በጣም እወድ ነበር፡፡ የድሃ ልጅም በመሆኔ ቀጥሎ የሚመጣው ደግሞ ማትሪክ

ስለነበር መንቃት ነበረብኝ። ያንን እድል ማጣት የለብኝም በማለት ትምህርቴን ብቻ ለመከታተል ወንድሜ ያለበት ሀገር

ማይጨው ሄድኩኝ። ግን እንደፈለግሁት ውጤት አልመጣልኝም፡፡ 2.8 ነበር ያመጣሁት፡፡ ያን ጊዜ ደግሞ የዩኒቨርስቲ

መግቢያ ነጥብ ከፍ ብሎ ነበር። ለሴት 2.8 ሲሆን ለወንድ 3.0 ነበር፡፡ ከዛ በኋላ በግል ተፈትኜ በማሻሻል፣ አዲስ አበባ

ዩኒቨርስቲ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ተቋም (አይኤልኤስ) ገብቼ እየተማርኩ ሳለ፣ ትምህርቴን መቀጠል የማልችልበት ከባድ

ፈተኛ ገጠመኝ፡፡ የሚያስተምረኝ ወንድሜ ድንገት ሞተብኝ፡፡ ለሁለት አመታት ከሃዘን ማገገም ስላልቻልኩ ትምህርቴን

አቋረጥኩ፡፡ በወቅቱ “ዊዝድሮዋል” ስሞላ፣ አሞላሌ ልክ አልነበረምና ከሁለት አመት በኋላ ለመማር ስሄድ ዩኒቨርስቲው

አልቀበልህም አለኝ። እራሴን አበረታትቼ ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ገባሁና ሲቪክስ ተምሬ ጨረስኩ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ሲፒዩ

ኮሌጅ እያስተማርኩ እገኛለሁ፤ ስድስት አመት ሆኖኛል፡፡
ከጥበብ ሥራ የተለየኸው ለምንድነው?
ጥበብን ከማሰብ ተለይቼ አላውቅም፤ ወደዋሻዬ መመለስ እፈልግ ነበር፡፡ ግን በርካታ ፈተናዎች ነበሩብኝ። ከወንድሜ

ህልፈት በኋላ የቤተሰብ ሃላፊ ሆንኩኝ፤ ባለኝ ጊዜ ግን ሙዚቃን በጣም ስለምወድ ግጥምና ዜማ ሰርቻለሁ፡፡
እስቲ የእነማንን ሰርተሃል?
የዮዲት ዘለቀ “ህልም አለኝ የማስበው” የሚለው አልበሟ ላይ ስድስት የሚሆኑ ስራዎችን ሰርቻለሁ፡፡ የመቅደስ ሀይሉ

እንደዚሁ “ወንድሜ” የሚለው አልበሟ ላይ ወደ ስድስት ስራዎችን ሰርቻለሁ፡፡ ኃይልዬ ታደሰም “አይበልብኝና” የሚል

ስራ ሰጥቼው ቆንጆ አድርጎ ተጫውቶታል፡፡ “ላሌ ሀበሻዎች” ሙሉ ስራቸውን ሰርቼላቸዋለሁ፡፡ አሁን እንደውም ሁለተኛ

ስራቸውን እየሰሩ ነው፤ እዛም ላይ የተወሰኑ ስራዎች ሰጥቼአቸዋለሁ። ለደረጄ በላይነህም በመጀመሪያ አልበሙ ላይ

ስምንት ስራዎችን ሰርቼአለሁ፡፡ እነዚህን አስታውሳለሁ፡፡
“ወንድሜ” የሚለውን ግጥም ስራ የፃፍከው ለወንድምህ ነበር?
መቅደስ በጣም የምትወደው ወንድሟ ውጪ ስላለ፣ ስለእሱ እንድፅፍላት ጠይቃኝ ነው የሰራሁላት፡፡ እሷ ስትዘፍነው

አንድ ቀን ስለምታገኘውና ስለምትናፍቀው ወንድሟ እያሰበች ነው፡፡ እኔ ስፅፈው ደግሞ እየናፈቅሁት መቼም

የማላገኘውን ወንድሜን እያሰብኩ ነው፡፡
ከረዥም ጊዜ በኋላ በቅርቡ “የእኔ እውነት” የሚል ትያትር ፅፈሃል፡፡ ለመፃፍ የነሸጠህ ምንድነው?
ይሄ ስራ የተፃፈው ማስተዋል በጀመርኩበት እድሜ ላይ ነው፡፡ በጣም ተፅእኖ እየፈጠሩ ያሉ የኮሜዲ ስራዎች

በሚወጡበት በአሁኑ ወቅት ይሄንን መስራቴ የምፈተንበት ነው ብዬ አምናለሁ። ተመልካቹ ጥሩ እርካታ ያገኛል ብዬ

አስባለሁ። ትውልዱን የሚያንፅ ሃሳብ የተሸከመ ስራ ይዤ የመጣሁ ይመስለኛል፡፡
ትያትሩ ላይ የሚተውኑት በሙሉ አዳዲስ ፊቶች ናቸው፡፡ ተቀባይነቱ ላይ ተፅዕኖ አያመጣብህም?
ሰዎች አቅም ያለው ነገር ይዘው ከመጡ፣ ዕውቅና ባይኖራቸውም እድል ልንሰጣቸው ይገባል፡፡ እዚህ ስራ ላይ የተሳተፉት

ከፍተኛ እውቀትና ችሎታ ያላቸው ናቸው፡፡ ከዚህ በኋላ እውቅና ሊመጣ ይችላል፤ ስራ ነው የሚያሳውቀው፡፡ በዚህ

ቲያትር ላይ ከተሳተፉት ውስጥ አርቲስት ተዘራ ለማ አንዱ ነው፡፡ በርካታ የቴሌቪዥን ድራማዎችና ክሊፖች ላይ የሰራ

ሲሆን በጣም ጨዋ፣ ሰዓት አክባሪ ሰው ነው፡፡ ሌላዋ ምስራቅ ናት፤ ምስራቅ በአሁኑ ጊዜ በ“ሰው ለሰው” ድራማ ላይ

የሰሚራን ገፀባህሪይ ትተውናለች፡፡
አለም ሲኒማ የሚታወቀው ፊልሞችን በማሳየት ነው። ለትያትር አያስቸግርም … ስላልተለመደ ማለቴ ነው …
እኔም አስቤበታለሁ፡፡ ከዚህ ቀደም “የምሁሩ ፍቅር”፣ ለተወሰነ ጊዜ ደግሞ “ውበትን ፍለጋ” እና “መንጠቆ” ትያትሮች

ታይተውበታል፡፡ አሁን ደግሞ በቁርጠኝነት ቲያትር ለማሳየት የተነሳበት ጊዜ በመሆኑ ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡ እኔና ጓደኞቼ

ይሄንን ቲያትር ወደ አለም ሲኒማ ይዘን ስንሄድ፣ በሌሎች ቲያትር ቤቶች በርካታ ቲያትሮች ለመገምገም ወረፋ እየጠበቁ

ነበር፡፡ ለምሳሌ ብሄራዊ ቲያትር እንዲገመገም ጥያቄ አቅርበን “ይደወልላችኋል” ከተባልን አንድ አመት አለፈን፡፡ ሀገር

ፍቅር ከአራት አመት በፊት ክፍት ቦታ የላቸውም፡፡ ማዘጋጃ ቤት ደግሞ የመንገዱ ጉዳይ አለ፡፡
አንድ ሰው የሰራውን ስራ ፍሬ ለማየት ቦታ ማጣቱ ያሳዝናል፡፡ ፊልም ቢሆን ኖሮ በተለያዩ ሲኒማ ቤቶች በአጭር ጊዜ

አሳይቶ መጨረስ ይቻላል፡፡ ትያትርን የሚያክል አድካሚ ስራ አንድ አመትና ከዚያ በላይ ፈጅቶ ቦታ ማጣት

ለተዋናዮችም ይሰለቻል፤ መቀዛቀዝ፣ መለያየትና መበታተን ይመጣል፤ እናም የተሰባሰቡ ጠንካራ ልጆችን እናጣለን ማለት

ነው፤ ይህ እንዳይሆን ብለን ወደ አለም ሲኒማ ጎራ አልን፤ በደስታ ተቀበሉን፡፡
“የእኔ እውነት” የሚለው ትያትርህ ጭብጡ ምንድነው?
ምክንያታዊነትና ስሜታዊነት ጎልቶ የሚታይበት፣ በአንድ ግቢ ውስጥ ያሉ ሁለት ቤተሰቦች ፍጥጫን የሚያሳይ ነው፡፡

ባልጠበቀችው ሁኔታ ፍቅረኛዋ አባትዋ ላይ አሰቃቂ አደጋ ያደረሰባት ሴት ምክንያቱን ለምን ስትል የምትጠይቅበት

ትያትር ነው፡፡ ይህንን ስክሪፕት የማከብረው ጋሽ ፍቃዱ ተክለ ማርያም አይቶት በጣም እንደወደደው ገልፆልናል፡፡

አርቲስት አዳነች ወልደገብርኤልም የህልሜ አዋላጅ ናት፤ የማንም ህልም እንዲጨናገፍ አትፈልግም፤ ከወላጅ እናት በላይ

ከጎናችን ሆና በስራችን ውጤታማ እንድንሆን ያገዘችንና በጣም እምንኮራባት ሴት ናት። ይህንን ትያትር ያለምንም

መሳቀቅ እንድንለማመድ ቦታቸውን በመፍቀድ የተባበሩንን የረር በር የሚገኙት የማርሻል አርት ባለሙያዎቹንም ከልብ

አመሰግናለሁ፡፡ በዚህ ስራ ላይ ከጎናችን ለነበሩት ሁሉ ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡

Published in ጥበብ
Saturday, 30 November 2013 11:52

የቀዩ ሞት ጭምብል

ቀዩ ሞት ሀገሬውን ሲያስገብር ነው የኖረው!
እንዲህ ያለ ወዲያውኑ አዋክቦ ፀጥ የሚያደርግ አሰቃቂ ገዳይ፣ እንዲህ አይነት አሰቃቂና ለማየት የሚዘገንን መቅሰፍት

ታይቶም አይታወቅ፡፡ ግብሩ ደም ነበረ - በደም ልክፍቱ ለቅፅበት ተጣብቶ አፍታ ሳይሰጥ በደም አበላ መድፈቅ፡፡ በቃ

ድንገት ጠቅ! የሚያደርግ ህመም ይፈጥርና በጭንቅላት ውስጥ ቅዥብርብር ያለ አዙሪት ይለቅቃል፡፡ ወዲያው በሰውነት

ላይ ምንም አይነት ቁስልም ሆነ ጭረት ሳይኖር፤ ብቻ  ከሰራ አካላት ደም እያንዥቀዥቀ ያዘንባል፤ ከዚያ...ሞት!!

በለከፈው ሰው ገላ፤ በተለይም በፊቱ ላይ እየበሳሳ ከሚፈጥራቸው ፍም የመሳሰሉ ቀዳዳዎች ደም እየተንዥረዥረ ሲወርድ

የሚያዩ ያልተያዙ ሰዎችም ህመምተኛውን ከመርዳት ይልቅ ለመሸሽ ይገደዳሉ፡፡ በፍርሃት ተርበድብደው እግሬ አውጭኝ

ይላሉ፡፡ ልክፍቱ የደረሰበት ግለሰብም ቢሆን ህመሙ ከጀመረው አንስቶ ነፍሱ እስክትወጣ ድረስ የሚቆይበት ጊዜ በጣም

ረዘመ ቢባል ከግማሽ ሰዓት አይበልጥም፡፡
የሀገሪቷ ገዥ የነበረው ፐሬስፔሮ ግን፤ ደስተኛ፣ ጀግና እና ብልህ ሰው ነበር፡፡ በቀዩ ሞት ሳቢያ ከግዛቱ ነዋሪዎች ግማሹ

ህዝብ ማለቁን ሲገነዘብ፤ አንድ ሺህ ያህል ጤንነታቸው የተጠበቀ የመንግስቱን ሹማምንት፡ ዘመድ አዝማዱንና  ባለፀጋ

ወደጆቹን አስጠርቶ፤ አብረውት እንዲኖሩ እርቆ ወደሚገኝ ሌላ ቤተ መንግስቱ ይዟቸው ሄደ፡፡
የህንፃውን ንድፍ እራሱ ፐሮስፔሮ  አዘጋጅቶ፤ዙሪያ ገባው በከበሩ ማዕድናት  ተንቆጥቁጦ እንዲሰራ በሰጠው ቀጭን

ትዕዛዝ በጥንቃቄ የተገነባ አስፈሪ ግርማ ሞገስ ያለው እጅግ ግዙፍ ቤተመንግስት ነበር፡፡ ዙሪያውም ሰማይ የነካ

በሚመስል ጠንካራ የድንጋይ አጥር ታጥሯል፡፡ መግቢያዎቹም በጣም ትልልቅ የብረት በሮች ናቸው፡፡ ክቡር እምክቡራኑ

ወደ ውስጥ ከገቡ በኋላ፤ ከእንግዲህ ከእነርሱ ሌላ ማንም ወደ ውስጥ አልፎ እንዳይገባ በሚያስተማምን ሁኔታ፣ በመዶሻ

እየቀጠቀጡ የመገጣጠሚያ ብሎኖቹንና ቅርቃሮቹን ሁሉ በብርቱ አጠባብቀው ሲያበቁ እሳት አቀጣጥለው፣ ትልልቆቹን

የብረት በሮች  እንዳይላወሱና ነፋስም እንዳያሾልኩ አድርገው በየዷቸው፡፡ ከዚህ በኋላ አሰቃቂው መርገምት፤ ቀዩ ሞት

ያሳደረባቸውን ስጋት ወዲያ አሸቀንጥረው እፎይ አሉ፡፡ ከቤተ መንግስቱ ውጭ ያለውን ዓለም «የራሱ ጉዳይ!» ብለው

ረሱት ፡፡
ፕሮስፔሮ፤ ለተከበሩት ወዳጆቹ፤ ምቾታቸውን የሚጠብቁና እርካታ የሚያስገኙላቸውን አስፈላጊ ነገሮች ሁሉ

አቅርቦላቸው ነበር፡፡ በቀልዳቸው ለዛ እያዝናኑ ሳቅ የሚያዘንቡ ጨዋታ አዋቂ ዚቀኞች አሉ፤ ስመ ጥር ገጣሚያን ውዳሴ

ቅኔ እየተቀኙ ሀሴት ይዘራሉ፤ እውቅ ድምፃዊያን በመረዋ ድምፃቸው የየዘፈኑን አይነት ያወርዱታል፤ በባሌት የዳንስ

ጥበብ የሰለጠኑ ተወዛዋዦሀት እንደ እንዝርት ይሾራሉ፤ በዜማ ቅኝት የተካኑ የመሣሪያ ተጫዋቾችን ያሰለፈው ኦርኬስትራ

ሙዚቃውን ሌት ተቀን ያንቆረቁረዋል፤ በየቀኑ ጭፈራ አለ፤ ቆነጃጅቶች ተውበው ይሽቀረቀራሉ፤ በየገበታው ላይ እጅ

የሚያስቆረጥም ምግብ በያይነቱ ሞልቶ እንደተትረፈረፈ ነው፤ የወይን ዋንጫዎቻቸው ቲፍፍ ብለው እንደሞሉ ናቸው...

ሁሉ በሽ በሽ! በአይበገሬ የድንጋይ አጥር በተከለለው የቤተ መንግስቱ እልፍኝ ውስጥ ሁሉ ሙሉ ነው፡፡ የከበባቸው

የጠንካራ አጥር ከለላ በዚያ እስከኖሩ ድረስ ስለደህንነታቸው ጉዳይ እንዳይጨነቁ አስተማማኝ ዋስትና ሆኖላቸዋል፡፡

ከቅፅሩ ውጭ ግን ቀዩ ሞት ይንጎራደድ ነበር፡፡
በዚያ፤ ከጭንቀት ነፃ በሆነ ሰላማዊ ሥፍራ መኖር በጀመሩ በአስረኛው ወራቸው መጨረሻ አካባቢ ነበር፣ ፕሮስፔሮ፤

ታላቅ የጭምብል ዳንስ ምሽት አዘጋጅቶ፤ ወዳጆቹን ሁሉ የጠራቸው። ማንኛውም ሰው ባለባበሱ ተውቦ እንዲገኝና ወደ

ዳንስ አዳራሹ በሚገባ ጊዜም ቢቻል ሙሉ ፊቱን ካልሆነ ግን ቢያንስ ዓይኖቹን በጭምብል እንዲሸፍን የጋበዛቸውን

ክቡራን ወዳጆቹን ጠይቋል - ፕሮስፔሮ፡፡
እንዲያ ዓይነት የጭምብል ዳንኪራ ምሽት ግብዣ፣ የታላቅ ባለፀግነት መገለጫ ነበር፡፡ ሰፊው እልፍኝም በግብዣው

የሚታደሙት ክቡራኑ የፕሮስፔሮ ወዳጆች መርጠው የሚጨፍሩባቸው ሰባት የተለያዩ ክፍሎች ነበሩት፡፡ አብዛኞቹ የዱሮ

ቤተመንግስቶች የዳንስ አዳራሾች የክፍሎቹ አሸናሸን ካንዱ ክፍል  ሆነው ባንድ ጊዜ ዙሪያውንና ሌሎቹን ክፍሎች

ውስጣቸው ድረስ በደንብ ለማየት ለመተያየት እንዲቻል ልቅ ተደርገው ነበር የሚሰሩት፡፡ የዚህኛው ቤተ መንግስት

አሰራር ግን ከዚህ የተለየ ነበር፡፡ ከአንዱ ክፍል በር ሆነው ማየት ቢቻል ምናልባት ሌላኛውን አንድ ክፍል ብቻ ነው።

አንዱ ክፍል ከሌላው በሃያና በሰላሣ ሜትር ርቀት ላይ ወደ ሌላ አቅጣጫ በሚታጠፍ የግድግዳ ማዕዘን ተከልሏል፡፡

እያንዳንዱ ክፍሎች ውስጥ በስተግራ ወይ በስተቀኝ ግድግዳዎቻቸው በኩል መሀል ለመሀል ከፍ ብለው የሚታዩ

መስኮቶች አሏቸው። የየመስኮቶቹ መስተዋት እንደየክፍሎቻቸው ቀለም አይነት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ክፍል

ግድግዳዎች በሰማያዊ መጋረጃ የተሸፈኑ ስለሆነ የመስኮቱ መስተዋትም ሰማያዊ ነው፡፡ የሁለተኛው ክፍል መጋረጃዎች

ሀምራዊ ቀለም ስላላቸው የመስኮቱ መስተዋትም እንዲሁ ሀምራዊ ነው፡፡ በሦስተኛው አረንጓዴ ክፍልም እንዲሁ አረንጓዴ

መስኮት፡፡ የአራተኛው መጋረጃና መስኮት ቢጫ፤ አምስተኛውም ነጭ፤ ስድስተኛውም ወይን ጠጅ ነበሩ፡፡ ሰባተኛው

ክፍል ግድግዳ ላይ የተጋረደው መጋረጃ ግን ውድ በሆነ ለስላሳማ ጨርቅ የተሰራ ጥቁር መጋረጃ ነበር፡፡ ልክ እንደ

ጨለማ የጠቆረ። ወለሉም እንዲሁ ከመጋረጃው የባሰ ድብን ያለ ጥቁር ስጋጃ ተነጥፎበታል፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ ግን

እንደሌላኛዎቹ ክፍሎች የግድግዳው መጋረጃና የመስኮቱ መስተዋት መልካቸው ተመሣሣይ አልነበረም፡፡ ወለሉና

ግድግዳው ጥቁር፤ የመስኮቱ መስተዋት ግን ቀይ ነበር፡፡ ደማቅ፤ ደም መሣይ ቀይ።
ሁሉም ክፍሎች ከውጭ ከሚቀጣጠለው የእሣት ነበልባል በየመስኮታቸው አልፎ በሚገባው ብርሃን ደምቀዋል፡፡ የእሣቱ

ወጋገን በዳንሰኞቹ  ላይ ሲያርፍ በነጸብራቁ የሚፈጠረው ጥላ ያልተለመደ አይነት ነው፡፡ የሰባተኛው ክፍል ድባብ ደግሞ

ከሁሉም ክፍሎች የተለየ ነበር፡፡ ደም ከሚመስለው የመስኮቱ መስተዋት አልፎ በጥቁር መጋረጃዎቹ ላይ  የተረጨው

የእሣት ብርሃን ለመላው ታዳሚያን በጣም የሚያስፈራ ነገር ሆኖባቸዋል። ወደዚያ ክፍል ድንገት በገቡ ሰዎች ፊት ላይ

የሚፈጥርባቸው ደስ የማይል ቀፋፊ ገፅታ ስለነበር፤ ሣይፈሩ ደፍረው በዚያ ጥቁር ግድግዳና ወለል መሀል በረበበው

አስጨናቂ ብርሃን  ወደ ክፍሉ ውስጥ መዝለቅ የሞከሩ በጣም ጥቂቶች ብቻ ነበሩ፡፡ በዚሁ ክፍል ውስጥ፤ ከጥቁር

እንጨት የተሰራ፤ ቁመቱ ጣሪያውን  ሊነካ ምንም ያልቀረው በጣም ግዙፍ ሰዓት ተገትሯል። እያንዳንዷን ሰከንድ

ሲቆጥር በቀስታ የሚሰማ ሲሆን፤ በየሙሉ ሰዓቱ ላይ ግን፤ ኩልል ብሎ በሚወርድ፤ ሙዚቃዊ ቃና ባለው ከፍተኛ

ድምጽ፤ ጮክ ብሎ ሲናገር ይሰማል። ልክ በዚያ ቅፅበትም የኦርኬስትራው ሙዚቀኞች ሙዚቃቸውን፣ ዳንሰኞቹም

ውዝዋዜያቸውን ያቋርጣሉ፡፡ ሰአት በሰው አንደበት ማውራቱ ግራ የሚያጋባቸው ዳንሰኞች መወዛወዛቸውን ገታ

አድርገው፣ ሰዓቱን እንደሞኝ ፈዝዘው ያዳምጡታል። አንዳንዶቹም ሰአቱ ተናግሮ እስኪጨርስ እጆቻቸውን አሻግረው

እየተነካኩ ይንሾካሾካሉ፤ ፊታቸው በፍርሃት ይቀላል። የሰአቱ ድምፅ ሲቆም ማጉረምረም ይነግሳል፡፡ በሁሉም ላይ

የአግራሞት ፈገግታ ይሰፍርባቸዋል፡፡ እናም ከሌላ ስልሣ ደቂቃዎች በኋላ፣ ከሌላ ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሰከንዶች

በኋላም ሰዓቱ በድጋሚ ይጮሀል፤ መላው ታዳሚዎቹም እንዲሁ እንደቀድሞው ድንገት ሙዚቃና ጭፈራቸውን ትተው፤

ማንኛውንም እንቅስቃሴያቸውን ገትተው ድርቅ ብለው ይቀራሉ።
ከመቼውም ጊዜ የተለየ ፍፁም ሀሴት የተሞላበትና ውብ የሆነ የጭምብል ዳንስ ምሽት ነበር፡፡ የታዳሚዎቹ አልባሳት፤

የተጫሙት ጫማና የተንቆጠቆጡባቸው ጌጣጌጦች ወደር የማይገኝላቸው ልዩና እፁብ ድንቅ የሚሰኙ ነበሩ። በአዳራሹ

መብራቶች ውስጥ ዳንሰኞቹ ልክ በአስፈሪ ሕልሞች ውስጥ እንደሚታዩ የቅዠት አለም ምስል ይመስላሉ፡፡ እናም እነዚያ

የሕልም አለም አይነት ሰዎች እንደገቡበት ክፍሎች ቀለም መልካቸው እየተለዋወጠ፣ እንደ ጥላ እየተንሳፈፉ ይደንሳሉ፡፡

እነርሱ የሙዚቃውን ምት እየተከተሉ የሚጨፍሩ ሳይሆን፤ ሙዚቃው ከእነርሱ ውዝዋዜ ውስጥ ተቃኝቶ የሚወጣ ነው

የሚመስለው፡፡ ያም ሆኖ ግን ማናቸውም ወደ ሰባተኛው ክፍል ከመግባት ተቆጥበዋል፡፡ በዚያ ክፍል ውስጥ፤ በመስኮቱ

መስተዋት የሚያንፀባርቀው ቀይ ብርሃንና የግድግዳው መጋረጃዎች ጥቁረት ከፍተኛ ፍርሃት ፈጥሮባቸዋል፡፡ በአጋጣሚ

ወደዚያ የገባ ሰውም ቢኖር ድንገት የትልቁን ጥቁር ሰዓት አስደንጋጭ ድምጽ በቅርበት ሲሰማ ተፈናጥሮ ይወጣል፡፡
ሌሎቹ ክፍሎች ግን በውብ መዓዛ ታውደው፤ በደስታ ፀዳል ፈክተው፤ በሰው ተጨናንቀዋል፡፡ ሰዓቱ፤ ከሌሊቱ ስድስት

ሰዓት መሆኑን እስኪያስተጋባ ድረስ ጭፈራው ቀልጦ ነበር፡፡ ሰዓቱ፤ ስድስት ሰዓት መሆኑን ሲናገር፤ አሁንም ሙዚቃው

እረጭ አለ፡፡ ዳንሰኞቹም እስካሁን ያደርጉት እንደነበረው፤ የሰዓቱ አስጨናቂ ድምፅ እስኪያበቃ ድረስ ከውዝዋዜያቸው

ተገትተው መጠባበቅ ጀመሩ፡፡ ሰዓቱ፤ ንግግሩን ከመጨረሱ በፊት፤ ከዳንሰኞቹ መሀል አብዛኛዎቹ፤ ከመጀመሪያው

ሰማያዊ ክፍል ውስጥ፤ እስካሁን ያልነበረ ባለጭምብል አስተዋሉ፡፡ ቀስ በቀስም፤ አንዱ ለሌላው በቀስታ ማንሾካሾክ

ጀመረና በታዳሚዎቹ መሀል፤ መጀመሪያ የመደነቅ፤ ከዚያም የፍርሃትና የመርበድበድ ስሜት ተሰራጨ፡፡
እንዲህ ባሉ የተከበሩ ሰዎች መሀል፤ ይህን አይነት ባለጭምብል ድንገት ሲከሰት ፍርሃት መንዛቱ አያስገርምም፡፡

ከመሀላቸው «በመኖርና በአለመኖር መካከል ቅንጣት ታህል ልዩነት አይታየኝም፤ እንዲያውም ሞት የሚፈራ ሰው

ያስቀኛል!» የሚል ጀግና ቢኖር እንኳ፤ ቢያንስ እንግዳው ባልተፈቀደ አለባበስ በመታደሙ ብቻ ትኩረት እንዲሰጠው

የሚያስገድደው አንዳች ስሜት በውስጡ ይጫራል፡፡ እንግዳው ረዥምና መጣጣ ቀጭን ሆኖ፤ ልክ ለቀብር እንደተዘጋጀ

አስከሬን ከፀጉሩ እስከ ጥፍሩ በመገነዣ ጨርቅ ተሸፍኗል፡፡ ፊቱን የሸፈነበት ጭምብልም... እውነት ጭምብልስ ነው? ...

እና ፊቱን በሸፈነበት ጭምብልና በሞተ ሰው ፊት መካከል ያለውን ልዩነት በጣም በቅርበት ተጠግቶ ያየ ሰው እንኳ

ለመረዳት አይችልም፡፡ ይኼ ሁሉ እሺ ይሁን ቢባል እንኳ፤ ይህ ማንም የማያውቀው እንግዳ ባለጭምብል፤ በአካኋኑ

ቁርጥ ቀዩ ሞትን መስሎ ነው የመጣው! ቁልቁል በቁሙ አጣፍቶ የለበሰው እራፊ ጨርቅ በደም ነጠብጣብ

ተዥጐርጉሯል፡፡ ፊቱን የሸፈነበትን ጭምብልም እንዲሁ ያ አስበርጋጊ ቀይ የደም ነጠብጣብ ወርሶታል፡፡ ደግሞ

ጭምብልም አይመስልም - አ...ዎ! የገዛ ራሱ መልክ ነው!
 ፕሮስፔሮ ይህንን አስደንጋጭ ክስተት እንዳየ፤ በመጀመሪያ በፍርሃት ተውጦ ቆይቶ፤ ከዚያ ደግሞ ድንገት በቁጣ ቱግ

አለ፡፡
«የማነው ደፋር!» ሲል አምባረቀ
«ያዙት! ያዙና ቀፍድዱት! ጭምብሉን ከፊቱ ላይ ገፋችሁ… የማናባቱ ጋጠወጥ!ስድ! ባለጌ! መሆኑን አረጋግጡ! ጎህ

ሲቀድ ወስደን እናንጠለጥለዋለን!»
ፕሮስፔሮ፤ ይህንን ያለው ከሰማያዊ ክፍል ውስጥ ቆሞ ቢሆንም፤ ድምፁ ግን በዙሪያው ባሉ በሰባቱም ክፍሎች ውስጥ

ጥርት ብሎ ያስተጋባ ነበር፡፡ መጀመሪያ ላይ፤ ልክ ፕሮስፔሮ ቀጭን ትዕዛዝ እንዳስተላለፈ፤ ከዳንሰኞቹ መሀል ወደ

እንግዳው ባለ ጭምብል እየተንደረደሩ ነበሩ። ግን፤ ግማሽ መንገድ ደርሰው በያሉበት ቀጥ አሉ፡፡ ከዚያ በላይ ወደፊት

አንዲትም ጋት ፈቅ ብሎ በእንግዳው ላይ እጁን ለማሣረፍ የደፈረ ማንም አልነበረም። ሁሉም በፍርሃት ተዋጡ፡፡

እንግዳው ግን፤ እየተንጐማለለ ወደ ሁለተኛው ክፍል መራመድ ጀመረ፡፡ አፉን ከፍቶ በመደነቅ የሚያስተውለው

ፕሮስፔሮን ናቅ አድርጐት በጐኑ አልፎት ሄደ፡፡ ታዳሚዎቹ፤ የክፍሉን የመሀል ወለል እየለቀቁ ወደ ኋላ ሲያፈገፍጉ፤

እንግዳው ለአፍታም ቆም ሳይል፣ ቀብረር ባለና በተመጠነ አረማመድ፣ ከሰማያዊው ክፍል ወደ ሀምራዊው ክፍል፤

ከሀምራዊው ክፍል ወደ አረንጓዴው ክፍል፤ ከአረንጓዴው ክፍል ወደ ቢጫው፤ ከዚያ ወደ ነጩ፤ ወደ ወይን ጠጁ ተራ

በተራ ተሽከረከረ፡፡  
ልክ እንግዳው ሰባተኛው ክፍል ሲደርስ ፕሮስፔሮ በቁጣ እመር ብሎ በስድስቱም ክፍሎች ገብቶ እየወጣ ማሰስ ጀመረ፡፡

ማንም አጅቦት ሊከተለው የደፈረ ሰው አልነበረም። እሱ ግን፤ ከቁመቱ የሚረዝም ስለታም ሻምላ ጨብጦ፤ ከእንግዳው

ጋር ሊፋለም ተዘጋጅቷል። ባለጭምብሉን እንግዳ ከርቀት እንዳየውም፤ በቀስታ ኮቴውን አጥፍቶ ከኋላው እያደባ

እየተከተለ፤ ልክ ሊደረስበት ሦሰት አራት እርምጃዎች ሲቀሩት፤ እንግዳው ድንገት ዞር! ብሎ ቆመና፤ በፀጥታ፤ ታ

የፕሮስፔሮን አይኖች በቀሳፊ አተያይ ሰርስሮ አያቸው፡፡ ፕሮስፔሮ እሪ...! ብሎ ከፍተኛ ጮኸት አሰማ፤ ይዞት የነበረው

ሻምላም ከእጁ ላይ ተሽቀንጥሮ፤ ስለቱ እየተብለጨለጨ ጥቁሩ ወለል ላይ አረፈ፡፡ ወዲያውም በወደቀው የራሱ ሻምላ

ስለት ላይ፤ ራሱ ፕሮስፔሮ ተዘረረበትና፤ ሞተ፡፡ በዚያን ጊዜ ታዳሚዎቹ እየተሯሯጡ ወደ ጥቁሩ ክፍል መጡ፡፡ ገዘፍ

ገዘፍ ያሉትና ክንደ ብርቱዎቹ ወንዶች፤ በቁመቱ ከትልቁ የግድግዳ ሰዓት መሳ ለመሳ ሆኖ የቆመውን የዚያን ቀውላላ

ባለጭምብል ገፅታ ጨምድደው ሊይዙት ሞከሩ፡፡ ግን፤ እጆቻቸውን ሰድደው እላዩ ላይ ባሳረፉ ጊዜ፤ ከተሸፈነበት

መገነዣ ጨርቅ ስር የጨበጡት ነገር አልነበረም፡፡ ስጋ እና አጥንትም ሆነ አንዳችም የሚዳሰስ ነገር የሌለው አካል አልባ

ነበር ... በቃ ምንም ... ኦና!
ያኔ ነበር፤ ሁሉም፤ ራሱ ቀዩ ሞት እንደ ሌባ እኩለ ሌሊትን ተታክኮ መከሰቱን የተረዱት። እያንዳንዱ ታዳሚም ተራ

በተራ እየተርገፈገፈ መነጠፍ ጀመረ - እንደወደቀም ወዲያውኑ ፀጥ! ቤተ መንግስቱ ውስጥና በዙሪያው ተቀጣጥለው

ሲንቦገቦጉ የነበሩት  የእሣት ብርሃናትም ሁሉ ወደሙ፡፡ ልክ የመጨረሻው ሰው መሬት በወደቀበት ቅፅበትም ሰዓቱም

መቁጠሩን አቆመ። ያም ውብ እልፍኝ በፅልመትና በሞት ብካይ ተዋጠ፡፡ እነሆ፤ ቀዩ ሞትም፤ ሁሉንም በእኩልነት

አንበርክኮ ይገዛ ዘንድ፤ለዘለአለም ተንሰራፍቶ ነገሰ፡፡


Published in ልብ-ወለድ

በ1997 ዓ.ም ተጀምሮ በየአመቱ እየተካሄደ ያለው “የኢትዮጵያ  ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል” ስምንተኛ ዝግጅት ባለፈው ሰኞ ምሽት በብሔራዊ ትያትር በሚደረግ የሽልማት ሥነሥርዓት እንደሚጠናቀቅ ሊንኬጅ አርት ሪሶርስ ሴንተር አስታወቀ፡፡ ዝግጅቱን የሚያቀርበው የሊንኬጅ አርት ዋና ሥራ አስኪያጅ አርቲስት ይርጋሸዋ ተሾመ ለአዲስ አድማስ እንደገለፀው፣ በፌስቲቫሉ ማጠናቀቂያ ላይ የተለያዩ ፊልሞች በዘጠኝ የሽልማት ዘርፎች ይሸለማሉ፡፡ በዘንድሮው ፌስቲቫል የተሳተፉት ፊልሞች ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በብሔራዊ ትያትር፣ በሲኒማ አምባሳደር፣ በሲኒማ አምፒር፣ በፑሽኪን አዳራሽ እና በጣሊያን የባሕል ማዕከል በቅናሽ ዋጋ እየታዩ ሲሆን የውጭ ሀገራት ፊልሞች በነፃ እየቀረቡ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

“አቦል፣ ቶና፣ በረካ” በሚል ርእስ ቡና ላይ ያተኮረ የሥዕል አውደርእይ እንደሚቀርብ አዘጋጆቹ አስታወቁ፡፡ በመጪው አርብ በአምስት ኪሎው ብሔራዊ ቤተመዘክር ተከፍቶ እስከ ታህሳስ 7 ለሕዝብ በሚቀርበው አውደርእይ የሚገኘው ገቢ፣ ቦንጋ ላይ ለሚገነባው የቡና ቤተመዘክር ሕንፃ ማሰሪያ እንደሚውል አዘጋጆቹ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ሚዩዚክ ሜይዴይ “አመኛው ክልስ” በተሰኘው የዳንኤል ሁክ መጽሐፍ ላይ ነገ ውይይት እንደሚካሄድ ገለፀ፡፡ ከቀኑ 8 ሰዓት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመጻሕፍት የሚካሄደውን የሦስት ሰዓታት ውይይት፣ የመነሻ ሀሳብ በማቅረብ የሚመሩት የሥነ ጽሑፍ ባለሙያው አቶ አስቻለው ከበደ ናቸው፡፡

መሳይ ፕሮሞሽን ከመንሱር ጀማል ፕሮሞሽን ጋር በመሆን የፀረ “የፆታ ጥቃት” ዘመቻ ቀንን የተመለከተ ኪነጥባዊ ዝግጅት ትናንት ጠዋት በሀገር ፍቅር ትያትር ቤት አዳራሽ አቀረበ፡፡ “እኔንም ይመለከተኛል” በሚል መሪ ቃል በቀረበው ዝግጅት ግጥሞች፣ ወግ፣ መነባንብ፣ ሙዚቃዊ ድራማ እና ሥነቃሎች ቀርበዋል፡፡

በአብነት ስሜ የተጻፈው ‘የኢትዮጵያ ኮከብ’ የተሰኘ ኮከብ ቆጠራ (አስትሮሎጂ) መጽሃፍ ባለፈው ሳምንት ለንባብ በቃ፡፡ በአምስት ዋና ዋና ክፍሎችና በአስራ ሰባት ምዕራፎች የተከፋፈለው ‘የኢትዮጵያ ኮከብ’፣ 132 ገጾች ያሉት ሲሆን የግለሰቦችን፣ የአገራትንና የዘመናትን ኮከቦች በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ይዟል፡፡ በመጽሃፉ ውስጥ የ500 ታዋቂ ግለሰቦች ኮከቦች ዝርዝር፣ የኢትዮጵያ ኮከብና የ8ኛው ሺህ ዘመን ኮከብ ማብራሪያ የተካተተ ሲሆን እያንዳንዱ አንባቢ ኮከቡን መሰረት በማድረግ የጤና፣ የሙያ ምርጫና የዝንባሌ ምክር በሚያገኝበት መልኩ መሰናዳቱን ፀሃፊው አስታውቋል፡፡ በ50 ብር ለገበያ የቀረበው ‘የኢትዮጵያ ኮከብ’ በየመጽሃፍ መደብሩና በአዟሪዎች እጅ እየተሸጠ ይገኛል፡፡

Page 1 of 19