ጥቃቱ ከአይሲስ ጋር ሊያያዝ ይችላል እየተባለ ነው
ባለፈው ረቡዕ ማለዳ በካናዳ ርዕሰ መዲና ኦትዋ በሚገኘው የአገሪቱ የጦርነት መታሰቢያ አደባባይና በፓርላማ ውስጥ በተከሰተውና ሁለት ሰዎችን ለህልፈት በዳረገው የተኩስ ጥቃት ዙሪያ የተጀመረው ምርመራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ሲ ኤን ኤን ዘገበ፡፡
ሚካኤል ዜሃፍ ቢቤው የተባለ የታጠቀ ግለሰብ፣  የአገሪቱን የጦርነት መታሰቢያ አደባባይ በመጠበቅ ላይ በነበሩ ሁለት ወታደሮች ላይ ተኩስ በመክፈት አንደኛውን የገደለ ሲሆን፣ ከሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ጋር በተደረገው የተኩስ ልውውጥ ሌሎች ሶስት ወታደሮችን ካቆሰለ በኋላ የግለሰቡ ህይወት ማለፉን ዘገባው ገልጧል፡፡
ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት በአገሪቱ ፓርላማ ተገኝተው ለምክር ቤቱ አባላት ንግግር እያደረጉ የነበሩት የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ስቴፈን ሃርፐር ጉዳዩን በተመለከተ ረቡዕ ምሽት በሰጡት መግለጫ፣ አገሪቱ በመሰል ጥቃቶችና ነውጦች እንደማትሸበር ገልጸው፣ ጥቃቱ ካናዳ ከአጋሮቿ ጋር በመሆን ጽንፈኝነትን ለመዋጋት የያዘችውን አቋም የበለጠ እንድታጠናክር የሚያደርግ ነው፤ ጽንፈኞች እንደፈለጉ የሚፈነጩበት ምቹ ቦታ አያገኙም ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥቃቱን የፈጸመው ሚካኤል ዜሃፍ ቢቤው የተባለ ግለሰብ መሆኑን ከመግለጽ ባለፈ ማንነቱንም ሆነ ድርጊቱን ለመፈጸም ያነሳሳውን ምክንያትና አላማውን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ያልሰጡ ሲሆን፣ ስለአሸባሪው ተጨማሪ መረጃ ለማግኘትና ሌሎች ተባባሪዎች እንዳሉት ለማጣራት የተጀመረው ምርመራ በጥቂት ቀናት ውስጥ ውጤት ያስገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል፡፡በወሩ መጀመሪያ ላይም የካናዳ መንግስት በኢራቅ የሚገኙ የአይሲስ ታጣቂዎችን ለማጥቃት በሚደረገው ዘመቻ ላይ ለመሳተፍ እቅድ እንዳለው ማስታወቁን የጠቆመው ዘገባው፣ ባለፈው ሰኞ አንድ የአገሪቱ ወታደር አሸባሪ ተብሎ በተጠረጠረ ግለሰብ ሞንትሪያል ውስጥ በመኪና ተገጭቶ መገደሉን ተከትሎም፣ አገሪቱ ያለባትን የሽብር ስጋት መጠን ከዝቅተኛ ወደ መካከለኛ ደረጃ ከፍ ማድረጓን አስታውሷል፡፡
ካናዳ አይሲስ የተባለውን ጽንፈኛ ቡድን ለመዋጋት በተጀመረው አለማቀፍ እንቅስቃሴ እንደምትሳተፍ በይፋ ማስታወቋንና በቡድኑ ላይ ለሚደረገው የአየር ድብደባ ላይ የሚሳተፉ ስድስት ተዋጊ ጀቶችን ለመላክ መወሰኗን ተከትሎ ጥቃቱ መከሰቱ፣ ጉዳዩ ከአይሲስ ጋር ተያያዥ ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ መፍጠሩን ዘገባው አስታውቋል፡፡አይሲስ ካናዳውያንን ለሽብር ጥቃት እየመለመለ እንደሆነ በቅርቡ ማስታወቁን ያስታወሰው ዘገባው፤ የአገሪቱ መንግስት ባለፈው ነሃሴ ወር ላይ ባወጣው ሪፖርትም፣ 130 ያህል ካናዳውያንም ወደሌሎች አገራት በመሄድ ከአሸባሪ ቡድኖች ጋር መቀላቀላቸውንና ከእነዚህ ውስጥም 30 የሚሆኑት በሶርያ በሚካሄደው ጦርነት ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ ተብሎ እንደሚገመት ማስታወቁን ገልጧል፡፡
በአገሪቱ መሰል የሽብር ጥቃቶች በጂሃዲስቶች ሊሰነዘሩ እንደሚችሉ ይገመት እንደነበር የጠቆመው ሲ ኤን ኤን፤ አሜሪካም መረጃ አግኝቻለሁ በማለት በቅርቡ በካናዳ በሚገኘው ኤምባሲዋና ቆንስላዋ ላይ ያለውን የደህንነት ሁኔታ በጥብቅ መከታተል መጀመሯን አስታውሷል፡፡አይሲስም ሆነ ሌሎች ቡድኖች ለጥቃቱ ሃላፊነት አለመውሰዳቸውን የገለጸው ዘገባው፣ የአገሪቱ የደህንነት መስሪያ ቤትም አይሲስ ወይም ሌሎች የሽብር ቡድኖች ከጥቃቱ ጋር በቀጥታ እንደሚያያዙ የሰጠው መግለጫ በይፋ ባያስታውቅም፣ በጉዳዩ ላይ ጥብቅ ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡ቢቢሲ በበኩሉ፤ በካናዳ የተለያዩ የጽንፈኛ ቡድኖች አባላትና ግለሰቦች አክራሪነትን መስበክ ከጀመሩ መቆየታቸውን በመጥቀስ፣ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ብጥብጦችን መፍጠር እንደሚገባ ብዙዎችን ማሳመን መቻላቸውን ዘግቧል፡፡ የአገሪቱ ፖሊስ 90 ተጠርጣሪዎችን ያሳተፉና ከሽብርተኝነት ጋር የተያያዙ 63 የብሄራዊ ደህንነት ጉዳዮችን በመመርመር ላይ እንደሚገኝ ባለፈው ሳምንት ማስታወቁንም አስታውሷል፡፡




Published in ከአለም ዙሪያ

* ተኩስ ሊያቆምና ያገተውን ሊፈታ ተስማምቷል የተባለው ቦኮ ሃራም፣ ግድያና ጠለፋውን ቀጥሏል

   ቦኮ ሃራም የተባለው የናይጀሪያ አሸባሪ ቡድን፣ በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የሸሪያ ህግ ተግባራዊ እንዲሆን የማስቻል አላማውን ለማሳካት ባለፉት አምስት አመታት፣ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃቶችን እንደፈጸመና ከ5ሺህ በላይ ናይጀሪያውያንን እንደገደለ ይነገራል፡፡
ቡድኑ ባለፈው ሚያዝያ ወር ቺቦክ ወደተባለችው ከተማ ድንገት ብቅ ብሎ የፈጸመው ድርጊት ግን፣ ያልተጠበቀና ብዙዎችን ያስደነገጠ ነበር፡፡ የታጠቁ የቦኮ ሃራም ወታደሮች፣ አገር አማን ብለው ወደ ትምህርት ቤታቸው በመጓዝ ላይ የነበሩ 276 ልጃገረዶችን አፍነው፣ ወዳልታወቀ ስፍራ አጋዙ፡፡
ይህ ድርጊት የአገሪቱን መንግስት፣ የልጃገረዶቹን ወላጆችና የቺቦክ ከተማ ነዋሪዎችን ብቻ ሳይሆን፣ መላውን ናይጀሪያዊና አፍሪካውያንን ብሎም አለምን አስደነገጠ፡፡ መገናኛ ብዙሃን ጉዳዩን ትኩረት ሰጥተው አስተጋቡት፡፡ በአሸባሪው ቡድን የታገቱት ናይጀሪያውያን ልጃገረዶች ዕጣ ፋንታ ብዙዎችን አስጨነቀ፡፡
የተወሰኑ ልጃገረዶች ለማምለጥ ቢችሉም፣ እንደታገቱ ያሉት 219 ያህል ልጃገረዶች ጉዳይ ይህ ነው የሚባል እልባት ሳያገኝ ስድስት ወራት አለፉ፡፡ የአገሪቱ መንግስት ያሰረብኝን ታጣቂዎቼን ካልፈታ፣ ልጃገረዶቹን ለባርነት እሸጣለሁ በማለት ሲዝት የቆየው ቡድኑ፤ የሽብር ጥቃት መፈጸሙን አጠናክሮ እንደገፋበት ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
“አላህ ልጃገረዶቹን መሸጥ እንዳለብኝ ነግሮኛል፡፡ እሸጣቸዋለሁ፡፡” ብሏል የቦኮ ሃራም መሪ ነኝ ያለ ግለሰብ ከሶስት ሳምንታት በፊት በይፋ፡፡የናይጀሪያ መንግስትም ለታገቱት ዜጎቹ ጉዳይ ተገቢውን ትኩረት አልሰጠም የሚል ትችት ሲሰነዘርበት ቆይቷል፡፡ የአገሪቱ የጦር ሃይል አባላት የሆኑ ወታደሮችም፣ መንግስት የቡድኑን ጥቃት በተገቢው ሁኔታ ለመመከት የሚያስችል ድጋፍ እያደረገላቸው አለመሆኑን መናገራቸውን የዘገበው ሲኤንኤን፣ የአሜሪካ መንግስት እገታው ከተፈጸመ ከአንድ ወር በኋላ፣ ልጃገረዶቹን የሚያፈላልጉ 80 አሜሪካውያን ወታደሮችን ወደ ቻድ መላኩን አስታውሷል፡፡በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ግን፣ የናይጀሪያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ተስፋ ሰጪ መግለጫ አወጡ፡፡ የአገሪቱ መንግስት ከአሸባሪው ቡድን ጋር ባለፈው ሳምንት በቻድ የተኩስ አቁም ስምምነት መፈጸሙንና ቡድኑ ያገታቸውን ልጃገረዶች ለመልቀቅ መስማማቱን አስታወቁ፡፡
በጀርመን መዲና በርሊን ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የናይጀሪያው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አሚኑ ዋሊ በበኩላቸው፤ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ስምምነት ላይ መደረሱንና ልጃገረዶቹ በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንደሚለቀቁ በእርግጠኝነት ተናግረዋል፡፡
“አሸባሪ ቡድኑ ልጃገረዶቹን እስከ መጪው ሰኞ ለመልቀቅ ተስማምቷል” ብለዋል፡፡ የናይጀሪያ መንግስት ቃል አቀባይ ማይክ ኦሜሪም፤ የታገቱት ልጃገረዶች በደህና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
ሲኤንኤን እንደዘገበው፣ ቦኮ ሃራም በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁን ድረስ የራሱን መግለጫ አለማውጣቱ ብዙዎችን አጠራጥሯቸዋል፡፡ የአለማቀፍ ፖለቲካ ተንታኞችም በሁለቱ ሃይሎች መካከል የተደረሰውን ስምምነት በጥርጣሬ እንደሚያዩት አስታውቀዋል፡፡
ቡድኑ እስላማዊ መንግስት የመመስረት ዓላማውን ለማሳካት በጦርነት ሊቀጥል ይችላል የሚሉት እነዚሁ ተንታኞች፣ ስምምነቱን ያደረገውም የበለጠ ለመደራጀትና ራሱን ለማጠናከር የሚሆን ጊዜ ለመግዛት ሲል እንደሚሆን ግምታቸውን ሰጥተዋል፡፡
መንግስት ከቡድኑ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት መፈጸሙን ቢያስታውቅም፣ የቦኮ ሃራም አባላት እንደሆኑ የተነገረላቸው ታጣቂዎች ግን በሁለት መንደሮችና በአንድ ከተማ ላይ በከፈቱት ተኩስ ስምንት ያህል ሰዎችን ሲገድሉ፣ ሌሎች ልጃገረዶችንም አግተዋል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

አፍሪካ ፕሮፌሽናሎች ለምን የሏትም?
በአዲስ አበባና ከናይጄርያ በመጣው ኢኮዬ የተባለ የሜዳ ቴኒስ ክለቦች መካከል ለሶስት ቀናት የሚቆይ የወዳጅነት ውድድር  በድሪም ቢግ ስፖርትስ አካዳሚ ተዘጋጅቷል ፡፡ በወዳጅነት ውድድሩ ከ50 በላይ አንጋፋ የሜዳ ቴኒስ  ስፖርተኞች ተሳታፊ ናቸው፡፡ በግብዣ ከናይጄርያ ድረስ ከመጣው ኢኮዬ የሜዳ ቴኒስ ክለብ ፤ ከአዲስ አበባ ቴኒስ ክለብ፤ ከፓይለቶች ማህበር እና ከድሪም ቢግ ስፖርትስ አካዳሚ ተውጣጥተዋል፡፡ በሜዳ ቴኒስ የወዳጅነት ውድድሩ ባለፈው ሃሙስ ብስራተ ገብሬል በሚገኘው ኢንተርናሽናል ቴኒስ ክለብ ሜዳዎች ተጀምሯል፡፡ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፤ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች እና የስፖርቱ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈው ውድድር ዛሬ ይፈፀማል፡፡
ሀሙስ በተደረገው የመክፈቻ ስነስርዓት ላይ የተገኘችው ታዋቂዋ ድምፃዊት፤ በጎ አድራጊ እና ስፖርተኛ ቻቺ ታደሰ፤ ኢትዮጵያ በስፖርት ልታድግ የምትችል  አገር መሆኗን ተናግራለች ከወዳጅነት ውድድሩ ከፍተኛ ልምድ ስለሚገኝበትና አገር ስለተዋወቅበት አዘጋጅተነዋል ብላለች፡፡ በበጎ አድራጎት ተግባራቷ በጣም የምትደነቀው አርቲስት ቻቺ ታደሰ ህፃናት በራስ መተማመናቸው እንዲያድግ፤ ሃላፊነት ተሰምቷቸው እንዲያድጉ እና ምርታማ ዜጋ እንዲሆኑ ስፖርት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው እምነቷ ነው፡፡ በቻቺ አርት ማኔጅመንት ኢንተርናሽናል የሚመራው ድሪም ቢግ ስፖርትስ አካዳሚ ባለፈው ሐሙስ ውድድሩ አስጀምሮታል፡፡ የሜዳ ቴኒስ የወዳጅነት ውድድሩ የተዘጋጀው የስፖርቱን እድገት ለማነቃቃት፤ የቱሪዝም  ስራዎችን ጎን ለጎን ለማከናወንና የመዝናኛ መድረክ ለመፍጠር እንደሆነም አስታውቋል፡፡ በኢትዮጵያ የፌደራል ስፖርት ኮሚሽን የእውቅና ሰርተፊኬት ያለው ድሪም ቢግ ስፖርት በአካዳሚ ደረጃ በሜዳ ቴኒስ ስፖርት በመስራት ፈርቀዳጅ ነው፡፡ የአካዳሚው ዲያሬክተር እና የሜዳ ቴኒስ አሰልጣኝ አቶ ሰለሞን ደመቀ እድሜያቸው 4 ዓመት እና ከዚያም በላይ ለሚሆናቸው ታዳጊዎች ብቁ የሜዳ ቴኒስ ስፖርት ስልጠና እየሰጠ ነው ይላሉ፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃ ውስጥ የሚገቡ ታዳጊ የሜዳ ቴኒስ አትሌቶችን ለማፍራት ራእይ መኖሩንም ገልጿል፡፡ የድሪም ቢግ ስፖርትስ አካዳሚ ዲያሬክተር  አቶ ሰለሞን ደመቀ በሜዳ ቴኒስ ስፖርት በ15 ዓመቱ በብሄራዊ ቡድን አባል ለመሆን የበቃ ነው፡፡ በአሜሪካዋ ግዛት ሚሲሲፒ በሚገኘው ስቴት ዩኒቨርስቲ  በስኮላርሺፕ እድል ተምሮ በማርኬቲንግ ቢኤ ዲግሪ ሰርቷል፡፡ ከኮሌጅ ትምህርቱ ጎን ለጎን በሜዳ ቴኒስ ተጨዋችነት እና አሰልጣኝነት አሜሪካ ውስጥ ስኬታማ ዓመታትን አሳልፏል፡፡ በተለይ  በሜዳ ቴኒስ ስፖርት በታዋቂ የአሜሪካ አካዳሚዎች ኮርሶችን ለመከታተል ከመብቃቱም በላይ የአሰልጣኝነት ትምህርቱን በተግባር ከፍተኛ ልምድ አካብቶበታል፡፡  በዚሁ ዓለም አቀፍ ልምድ መነሻነትም ከቻቺ ታደሰ ጋር አካዳሚውን በአገር ውስጥ ለመክፈት መቻሉን በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተገልጿል፡፡
የናይጄርያውን ኤኮዮ ሜዳ ቴኒስ ክለብ ወክለው ድሪም ቢግ ስፖርትስ አካዳሚ ባዘጋጀው የወዳጅነት ውድድር ላይ ለመሳተፍ የመጡት በውድድሩ ደስተኛ ናቸው፡፡ በኢንተርናሽናል ቴኒስ ክለብ ሜዳ ያገኘናቸው እነዚህ ናይጄርያውያን ስፖርቱ በአፍሪካ ደረጃ ፐሮፌሽናል ተጨዋቾች አለማፍራቱ ያስቆጨናል ብለዋል፡፡ በናይጄርያ የሜዳ ቴኒስ ስፖርት ሰፊ ተሳትፎ እንዳለው የገለፁት ናይጄርያውያኑ፤ እስከ 25 ሺ ዶላር የሚያሸልሙ አገር አቀፍ ውድድሮች ቢኖሩም  በአመዛኙ ግን እንደጤና ስፖርት የሚዘወተር ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በአዲስ አበባ የሚገኘው ኢንተርናሽናል ቴኒስ ክለብ ሜዳ በሸክላ አፈር መሰራቱ እንደተመቻቸው የገለፁት ናይጄርያውያን፤ በተለይ ለጤና ስፖርተኞች ይህ አይነቱ ሜዳ የአካል ብቃትን ለማጠናከር ይጠቅማል ብለዋል፡፡ አፍሪካ በዓለም የሜዳ ቴኒስ ስፖርት የውድድር መድረኮች መሳተፍ የማትችለው ስፖርቱ ለልምምድ እና ለአጠቃላይ ዝግጅት በርካታ ወጪ ስለሚጠይቅ መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ታዳጊዎችን አሰልጥኖ  እና በክለቦች አቅፎ በየደረጃው ውድድሮችን በማድረግ በትጋት ከተሰራ ግን ፕሮፌሽናል ስፖርተኞችን ማፍራት ይቻላል  ብለዋል፡፡ ፕሮፌሽናል ደረጃ የሚደርሱ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋቾች በዓለም የውጤት ደረጃ ከገቡ በዓመት ከ5 እስከ 20 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚኖራቸውም ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውጥ በሜዳ ቴኒስ ስፖርት ከ50 ዓመታት በላይ እንቅስቃሴ ሲደረግ ቢቆይም አገሪቱ በስፖርቱ ከክፍለ አህጉራዊ ዞን እንኳን መውጣት አልቻለችም፡፡  በአዲስ አበባ ከተማ በበርካታ ስፍራዎች ለሜዳ ቴኒስ ስፖርተኞች በአባልነት ክፍያ የሚንቀሳቀሱ  የማዘውተርያ ስፍራዎች ይገኛሉ፡፡ ከጤና ስፖርተኞች ባለፈ ግን ስፖርቱ ወደ ፕሮፌሽናል ደረጃ ማደግ ተስኖታል፡፡ ዋናው ምክንያትም የናይጄርያ ስፖርተኞች እንደገለፁት ለዝግጅት፤ ለስልጠና እና ለጉዞ የሚያስፈልገው በጀት ከፍተኛነት ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ ሁለት ተወዳዳሪዎች በኢትዮጵያ ቴኒስ ፌደሬሽን የስፖንሰርሺፕ ድጋፍ በቦትስዋና በተካሄደው የአፍሪካ የቴኒስ ሻምፒዮና ተሳትፈዋል፡፡ ይሁንና እነዚህ ስፖርተኞች በላቀ ደረጃ ከታዳጊነታቸው ስልጠናውን በማግኘት የተዘጋጁ ባለመሆናቸው የረባ ውጤት አላስመዘገቡም፡፡
ፕሮፌሽናል ስፖርተኞችን ለማግኘት አገር አቀፍ ውድድሮች ያስፍጋሉ አለማካሄዳቸውም የስፖርቱን እድገት ያጓተተ ምክንያት ሆኖም ይጠቀሳል፡፡ አንዳንድ መረጃዎች በአገሪቱ ከ16 በላይ የሜዳ ቴኒስ ክለቦች እንደሚንቀሳቀሱ ያመለክታሉ 10 በአዲስ አበባ፤ እያንዳንዳቸው ሁለት ክለቦች በኦሮምያ እና በደቡብ ክልሎች እንዲሁም በሃረሪ እና በድሬዳዋ ሌሎች ሁለት የሜዳ ቴኒስ ክለቦች ሲገኙ በፌደሬሽኑ አባል ሆነው እየሰሩ መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡ አንዳንድ የቴኒስ ስፖርት አፍቃሪዎች ኢትዮጵያ ውስጥ የስፖርቱ ማሰልጠኛ አካዳሚ መገንባት ለውጥ ያመጣል ብለው በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቆይተዋል በአይነቱ ፈር ቀዳጅ የሆነው ድሪም ቢግ ስፖርትስ አካዳሚ በዚሁ አቅጣጫ ከፍተኛ ሃላፊነት ተጥሎበታል፡፡
የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር አባል የሆነው የአፍሪካ ቴኒስ ኮንፌደሬሽን 50 አገራትን በአባልነት በማቀፍ በቱኒዚያ ተቀማጭ ሆኖ ይሰራል፡፡ ባለንበት ጊዜ በብሩንዲ እና በሴኔጋል አበረታች የሜዳ ቴኒስ ስፖርት እንቅስቃሴዎች ሰሉ፡፡ ፕሮፌሽናል ሜዳ ቴኒስ ተጨዋቾችን በማፍራት ከአፍሪካ ብቸኛዋ ተጠቃሽ አገር ግን ደቡብ አፍሪካ ናት፡፡ በዓለም የሜዳ ቴኒስ ተጨዋቾች ደረጃ ለመግባት የቻሉት ሁለት የደቡብ አፍሪካ ስፖርተኞች ናቸው፡፡ ኬቨን አንደርሰን 35ኛ እንዲሁም ቻኔሌ ቺፕርስ 92ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡  ዓለም አቀፉ የሜዳ ቴኒስ ማህበር በአፍሪካ ሶስት የእድገት እንቅስቃሴ ኦፊሰሮች በመመደብ ለረጅም አመታት ቢሰራም ውጤት አላገኘበትም ፡፡ስለዚህም ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን መላው አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪ የሚሆኑ ፕሮፌሽናል የሜዳ ቴኒስ ተጨዋቾች ማፍራት ተስኖታል፡፡ ብዙ የአፍሪካ አገራት ለሜዳ ቴኒስ ስፖርት ዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሳታፊነት ከመንቀሳቀስ ይልቅ በትራክ የአትሌቲክስ ውድደሮች ላይ ያተኩራሉ፡፡
 የሜዳ ቴኒስ ስፖርት በመወዳዳርያ ቁሳቁሶቹ ውድነት፤ በዝግጅት ከፍተኛ ወጪው እና በሚያስፈልገው የላቀ የአኗኗር ደረጃ ለብዙ አፍሪካውያን እንደቅንጦት የሚታይ ወይንም ለጤና ብቻ የሚደረግ ስፖርት አድርጎታል፡፡ በዓመት ለስልጠና እና ለዝግጅት እንዲሁም ለጉዞዎች ለአንድ ስፖርተኛ እስከ 80ሺ ዶላር በጀት እንደሚያስፈልግ የሚያመለክቱ መረጃዎች አሉ፡፡

በ2014 የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ የዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ በሴቶች ምድብ ከመጨረሻዎቹ ሶስት እጩዎች ተርታ የገባችው የ23 ዓመቷ  ገንዘቤ ዲባባ፤ ቢያንስ በዓመቱ ምርጥ ብቃት የመሸለም እድል እንደሚኖራት ተገመተ፡፡
የዓለም ኮከብ አትሌት ምርጫ አሸናፊዎች ከ3 ሳምንት በኋላ በፈረንሳይ ሞናኮ ውስጥ በሚደግ ልዩ ስነስርዓት ይታወቃሉ፡፡ በሁለቱም ፆታዎች ለመጨረሻ ፉክክር ሆነው የቀረቡ አትሌቶች የተለዩት  ለሁለት ሳምንት በአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ ድረገፅ  በተሰበሰበ ድምፅ ነው፡፡ የዓለም አትሌቲክስ ቤተሰብ በሚል የሚጠቃለሉት የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ እና የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ አትሌቲክስ ፋውንዴሽን ምክር ቤት አባላት፤ የየአገሩ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች፤ የውድድሮች ዲያሬክተሮች እና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃናት ተሳትፈውበታል፡፡የዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫን በሞናኮ የሚገኘው አለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፋውንዴሽን ምክር ቤት ያዘጋጀዋል፡፡ በሁለቱም ፆታዎች የዓለም ኮከብ አትሌት ሆነው የሚመረጡ አትሌቶች ልዩ የዋንጫ ሽልማት እና 100ሺ ዶላር ቦነስ ይበረከትላቸዋል፡፡
 በሴቶች ምድብ የመካከለኛ ርቀት ምርጥ አትሌት የሆነችው ኢትዮጵያዊቷ ገንዘቤ ዲባባ፤ ከኒውዝላንዳዊቷ አሎሎ ወርዋሪ ቫለሪ አዳምስ እና ከሆላንዳዊቷ የሄፕታተሎን ስፖርተኛ ዳፍኔ ሺፐርስ ጋር በመጨረሻ እጩነት ቀርባለች፡፡ በወንዶች ምድብ ደግሞ የመጨረሻዎቹ 3 እጩዎች የሆኑት ዘንድሮ የዓለም ሪከርድ በማራቶን ያስመዘገበው ኬንያዊው ዴኒስ ኪሜቶ፤ የኳታሩ ሙታዝ ኢሳ እና የፈረንሳዩ ሬናውድ ላቪኔ ናቸው፡፡
በውድድር ዘመኑ ከ8 ወራት በፊት ገንዘቤ ዲባባ በ15 ቀናት ልዩነት በ1500 እና በ3000 ሜትር የቤት ውስጥ ውድድሮች እንዲሁም በ2 ማይሎች ሩጫ ሶስት ሪከርዶችን ማስመዝገቧ ለኮከብ አትሌት ምርጫው ልዩ ተቀናቃኝ አድርጓታል፡፡ ገንዘቤ 2014 ከገባ በኋላያስመዘገበቻቸው ሌሎች ትልቅ ውጤቶች ለዚህ እጩነቷ አስተዋፅኦ አላቸው፡፡ በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና በዓለም አትሌቲክስ ኮንትኔንታል ካፕ በ3ሺ ሜትር ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን ተጎናፅፋለች፡፡
የዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፋውንዴሽን ምክር ቤት እና በአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር (IAAF) ቅንጅት  መካሄድ የጀመረው በ1988 እኤአ ላይ ነው፡፡ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ተሸላሚ በ1998 እኤአ ላይ ኃይሌ ገብረስላሴ ነበር፡፡ ኃይሌ በዚያን ወቅት በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳልያ በ10ሺ ሜትር ባርሴሎና ላይ ከማስመዝገቡም በላይ በ10ሺ እና በ5ሺ የዓለም ሪከርዶችን በመያዝ ከፍተኛ የበላይነት ስለ ነበረው ኮከብ ሆኖ ለመመረጥ ብዙም አልተቸገረም፡፡ ከዚያ በኋላ በ2004 እኤአ ላይ ቀነኒሳ በቀለ ሁለተኛው የዓለም ኮከብ አትሌት ለመሆን በቃ፡፡ ቀነኒሳ በዚህ የውድድር ዘመን  እስካሁን በእጁ የተያዙትን የ10ሺ እና የ5ሺ ሜትር የዓለም ሪከርዶችን አስመዝግቧል፡፡ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናም በድርብ የወርቅ ሜዳልያዎች በማግኘትም የነገሰበት ዘመን ነበር፡፡ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በ2005 እኤአ ላይም በረጅም ርቀት እና በዓለም አገር አቋራጭ ውድድሮች የበላይነቱን ቀጠለበት፡፡ ስለሆነም ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመት የዓለም ኮከብ አትሌት ሆኖ ለመሸለም በቅቷል፡፡ ቀነኒሳ በዓለም ኮከብ አትሌትነት ሽልማቱን ለሁለት ጊዜ በመቀበሉ  ብቸኛው ኢትዮጵያዊ አድርጎታል፡፡ በሴቶች ምድብ ከቀነኒሳ በቀለ  ጋር ሁለቱንም ተከታታይ ዓመታት የዓለም ኮከብ አትሌት ሆና ለመሸለም የበቃችው ራሽያዊቷ የምርኩዝ ዘላይ ዬሌና ኢዝንባዬቫ ነበረች፡፡ ከቀነኒሳ በኋላ በዓለም ኮከብ አትሌትነት ለመሸለም በመብቃት የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊ ሴት አትሌት ለመሆን የበቃችው ደግሞ መሰረት ደፋር ናት፡፡ በ2007 እኤአ በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና እንዲሁም በ5ሺ ሜትር ከፍተኛ ስኬት ያገኘችው መሰረት ደፋር በወቅቱ ለመጀመርያ ጊዜ በዓለም ኮከብ አትሌትነት የተሸለመች ኢትዮጵያዊት ሴት አትሌት ሆናለች፡፡ በዚያ የውድድር ዘመን በወንዶች ምድብ አብሯት ለመሸለም የበቃው አሜሪካዊው የአጭር ርቀት ሯጭ ታይሴን ጌይ ነበር፡፡ ከዓለም ኮከብ አትሌትነት ባሻገር አይ.ኤ.ኤፍ በሚያዘጋጀው ዓመታዊ የሽልማት ስነስርዓት ሌሎች ክብሮችን ያገኙ ኢትዮጵያውያን የአትሌቲክስ ጀግኖችም አሉ፡፡ አሰልጣኝ ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ ብቸኛውን የአይኤኤኤፍ የህይወት ዘመን ስኬት ሽልማት ተቀብለዋል፡፡ በ2005 እና በ2008 እኤአ ላይ ደግሞ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የዓመቱ ምርጥ ብቃት ያሳየች አትሌት ተብላ ለሁለት ጊዜያት ተሸልማለች፡፡

የሕጽናዊነት መሠረታዊያን
“የአብሮነት ቃል” ከተባለ መጽሔት ጋር በተደረገ ቃለ ምልልስ አዳም ረታ “የሕጽናዊነት ስነግብር ንጥረ ነገሮች እነዚህ ናቸው” ብሎ ያስቀመጣቸው አራት የሕጽናዊነት መሠረታዊያን ነበሩ፡፡ እነኚህ አራት ነጥቦች የሚያስረዱትም፡-
“1/ ሁሉ ነገር በታቀደና ባልታቀደ ግንኙነት ውስጥ መሆኑን
2/ ሁሉ ነገር በታቀደና ባልታቀደ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን በታቀደና ባልታቀደ ለውጥ ውስጥ መሆኑን
3/ አሁን ተነጣጥሎ የተቀመጠ የሚመስለው ቢያንስ አንድ የጋራ የግንኙነት መስመር እንደማያጣ (ከአዳምና ከሄዋን ተገኘን ማለት)(ሙሉኩሌው ወይም የፀ ሐይ ስርዓት ከአንድ ታላቅ ፍንዳታ (big bang) ተፈጠረ እንደማለት)
4/ አንድ ወጥ አጭር ታሪክን ወይም ረዥም ልብ ወለድን የተሳካ ማለት ጎደሎውን መቀበል መሆኑን፡፡ ለአባባል ሕጽናዊነት ሁሉን ነገር ቀናንሰን ስናነበው ግንኙነት አለው፡፡ ዋናው የስነ ጽሑፍ አላባው ይሄ ነው፡፡ እንጀራ ውስጥ የተቀበረው ሚስጥር ይሄ ነው፡፡ ከላይ ሲያዩህ ነጠላህን ያለህ ይመስልሃል ግን አነሰም በዛም፣ አወኩትም አላወኩትም፣ ገባኝም አልገባኝም፣ ተከሰተ አልተከሰተ መረብ ውስጥ ነኝ ማለት ነው˝
(አዳም በ”እቴሜቴ ሎሚ ሽታ” ውስጥ የሚገኙትን ታሪኮች ግንኙነት በባለ ሁለት ወይም ባለ ሦስት ዲሜንሽናል ግራፍ ማስቀመጥ እንደሚቻል ከተናገረ በኋላ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ታሪኮቹን/ የገጸ ባሕሪያቱን ግንኙነት በባለ ሁለት ዲሜንሽናል ግራፍ ለማስቀመጥ ሞክሯል፡፡ ውጤቱም በምስሉ ላይ እንደሚታየው የእ.ሎ.ሽ. ገጸባሕሪያት ግንኙነት መረባዊ እንደሆነ በተጨማሪም በታቀደና ባልታቀደ ግንኙነት ውስጥ መሆኑን አረጋግጧል)፡፡

ሕጽናዊነት እና ትውስታ
መኖር ማስታወስ ነው፡፡ ጥበብ ደግሞ የማስታወሶች ሁሉ ቁንጮ፡፡ To live is to remember. Art is the highest form of remembrance. (እ.ሎ.ሽ.)
“የሕጽናዊነት ዘፍጥረት ጤፍ እንጀራን እንደ ትውስታ (memory) ከመቁጠር ይነሳል፡፡ የሆነ ዓይነት ትውስታ ጤፍ ውስጥ እንደተከማቸ እገምታለሁ፤ አምናለሁም፡፡ ሕጽናዊነት የሚያደርገው ነገር ቢኖር ይሄንን ትውስታ ቆፍሮ ማውጣት ነው”፡፡ The genesis of Hisinawinet is Tef Injera as memory. I assumed and believed that memory is stored in the injera. What Hisinawinet does is retrieve it. What is stored is in a spatial form. What we particularly retrieve is connectivity at the center of existence. We are teasing our pagan past in search of fruitful meaning. Hisinawinet is a robust technology of writing fiction (at least in my current case). Definitely, it is a technology of connectivity, of empathy and positive liaison.
“ማንኛውም ልቦለድ አያልቅም፡፡ ማለቁ ምትሃት ነው (ምሉዕ አይደለም)፡፡ የመስፋፋት ድብቅ ኃይል (ፖቴንሽያል) አለው፡፡ ይሄ እኔ የምጠቅሰው መስፋፋት ግን በመለጠጥ የሚመጣ አይደለም፣ ቢያንስ በእኔ የግል ትውፊት፡፡ መለጠጥ ግራና ቀኝን ያሳያል እንበል--ከመጀመሪያውና ከመጨረሻው ይዞ (ልክ እንደ ላስቲክ) በመጎተት ማስፋት፡፡ እኔ የምለው መስፋፋት ከመሃል ልክ እንደ ወሽመጦች (ሕጽኖች) አቢይ ምዕራፎች በማስገባት ‹‹ያመለጡ›› አዳዲስ የእንጀራ/ እንጆሪ ዐይኖችን (ታሪኮችንና መረጃዎችን) በማስገባት መስራት ማለቴ ነው፡፡ … ስለዚህ እኔ ስለሚስፋፋው ልቦለድ ሳወራ ስለስግሰጋ ማለቴ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ወሽመጦች ተዋረድ ሳይጠብቁ ከተጠቀሱበት ምዕራፍ ወጥተው የበላይ ነን ሊሉ ይጥራሉ፡፡ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ የተረሳ ነገር ከምናስታውሰው የበለጠ የበላይነት ሊኖረው ይችላል፡፡ ሕጽን ከዝንጉነት መውጫ መሣሪያ ልትሆን ትችላለች፡፡” ግራጫ ቃጭሎች፤ እንደ መግቢያ፡፡ (አፅንኦቱ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ነው)፡፡
“ሕጽናዊነት የሚነግረን ነገር ቢኖር ወደ ደራሲው፣ ወደ ገጸባሕሪውና ወደ አገሪቷ ትውስታዎች በጥልቅ መግባትና እነዚህን ማገናኘትን ነው፡፡ ትርጉሙም የሚገኘው በግንኙነታቸው ውስጥ ነው”፡፡
ስለ ግንኙነት በምሳሌ ለማስረዳት አዳም በአንድ ወቅት በቪዲዮ ያየውን ቃለ ምልልስ ቀላል አብነት ያደርጋል፡፡ አዳም በዚህ ቃለ ምልልስ ውስጥ ያዳመጠው/ የተመለከተው አፄ ኃይለሥላሴ በእስር በነበሩበት ወቅት ከጠባቂያቸው ወታደር ጋር ያደረጉትን ጭውውት ነው፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀን አፄው ወታደሩን ጥያቄዎች ይጠይቁታል… ስሙን፣ የአባቱን ስም፣ የትውልድ ቦታውን ወዘተ፡፡ ወታደሩ ስሙንና የአባቱን ስም ነገራቸው፡፡ የተወለደውም ሐረርጌ ውስጥ ኤጀርሴ  ጎሮ እንደሆነ ሲነግራቸው “የአያትህ ስም እከሌ አይደለምን?” ብለው ይጠይቁታል፡፡ ኃይለሥላሴ የተወለዱት ኤጀርሴ ጎሮ ነበርና የወታደሩን አያት በአካል ያውቋቸዋል፡፡ ወታደሩ ዕውነትም ኃይለሥላሴ የጠሩት ስም የአያቱ ስም መሆኑን አረጋገጠላቸው፡፡ ከዚያም ወታደሩ ድብርት ያዘው፡፡
ታዲያ አዳም ይሄን ምሳሌውን ሲያብራራ እንዲህ ይላል፡-  “አሁን ደግሞ ኃይለሥላሴ እስር ላይ አልነበሩም፤ ወታደሩም አንድ ግሮሰሪ ውስጥ ቢራ እየጠጣ ነበር ብለን እናስብ፡፡ እርስዎም ግሮሰሪው ውስጥ ነበሩ፡፡ እነኚህ ሁለት ሰዎች በአያትዬው ትውስታ አማካኝነት ግንኙነት ሊኖራቸው ይችላል ብለው ሊገምቱ ይቻልዎታል? ሕጽናዊነት በምናቡ ዓለም ውስጥ ይሄንን ነው የሚያደርገው /That is what Hisinawinet does in a fictional world”፡
በተፈጥሮም ሆነ በሰው ልጅ ባሕል ውስጥ ጠፋ/ተረሳ የተባለ ጉዳይ አብዛኛውን ጊዜ ተመልሶ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ እንደጠፋ የሚታወቅ ሲለካንስ የተባለ የዓሳ ዝርያ አለ፡፡ በደቡብ አፍሪካ የባሕር ዳርቻ በ1938 ሊታይ ችሏል፡፡
“የሰውን ተፈጥሮ ከምንጩ ለመረዳት (በእኛ ሁኔታ አገርና ማሕበረሰብን) የቆዩ መዛግብትን ትርጓሜ በሰፊው ይሠራል፡፡ ፍሮይድ በኤዲፐስ ያደረገው ይሄንን ነው፡፡ አንድን ድራማ ነው የተነተነው (analyze ያደረገው)፡፡ ያንግ ደግሞ ሕልሞችን፣ አፈታሪኮችን/ተረቶችንና mandala-ዎችን፡፡ ፍሮይድ የሠራውን ነገር ከፖሊዮግራፊ [ጥንታዊ የፊደል አጣጣል ስርዓቶችንና ታሪካዊ ሰነዶችን የማጥናት ዘዴ]፣ ከቁፋሮ፣ ከትርጉም ሥራ እና ከጥንት ቋንቋዎች ጥናት ጋር ያወዳድረዋል፡፡ በርካቶች ዛሬ ላይ የተከሰተን ኩነት ለማብራራት መጻሕፍትን ያጣቅሳሉ፡፡ ሆኖም መጻሕፍት በትርጉም ልዩነት ሰበብ ተበክለዋል ወይም የትርጉም መዛነፍ ሰለባ ናቸው/ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
የቀደሙት ኢትዮጵያዊያን/ሰንደቅ ዓላማ/ ያደረገው ለሁሉም ወገን ገዢ የሚሆን ፅላት (iconic) ወገንተኝነትንና አይዲዮሎጂዎችን የሚደመስስ “ዳቦ” መፍጠር ነበር፡፡ እንጀራ በየዕለቱ ይጠቀሳል፤ በየዕለቱ ፉክክር ውስጥ ይዶላል፡፡ ታዲያ የዚህን ግኝት የተደበቀ ምስጢር ስለምን አንበረብርም?
በጠቅላላው የባሕል ዝግመተ ለውጥ ውስጥ እንጀራ የሚይዘው ቦታ ትልቅ ነው፡፡ የአበው ትውስታዎች በእንጀራ ውስጥ ተሰግስገዋል፤ እንጀራ ደግሞ ሁሉም የሚጋራው ነገር ነው፤ ደካማውም ጠንካራውም፡፡ በሌላ አነጋገር ታሪክ በሁሉም ዜጋ አምሮቶችና ፍላጎቶች ውስጥ ይገኛል፡፡ የሚጨበጥ የሚዳሰሰው ማስረጃ (የድንጋይ ላይ ፅሑፍ፤ ወፋፍራም ብራና፤ ቋንቋ) በጦርነት እና በፕሪጁዲስ በንኖ ሲጠፋ ረቂቋ እንጀራ ግን በገበሬዎች፣ በሸክላ ሠሪዎች፣ በልዣገረዶች፣ በማቡኪያዎች… ጀርባ ታዝላ ዛሬን አይታለች”፡፡ The place of injera in the general process of cultural evolution is important. The memories of the old were embedded in the injera, an element which both the powerful and the weak shared. In other words, History was embedded into the need and necessities of everyone.
“ሕጽናዊነት የሚያደርገው ትውስታዎችን ቆፍሮ ማውጣትና እነዚህን ትውስታዎች ክቦች፣ መረቦችና ስድስት ጎኔዎች ወደሚመስሉ ቀላል ቅርፆች ጨምቆ ማቅረብ ነው”፡፡ What Hisinawinet does is retrieve these memories by abstracting them into ‘simple forms’ of circles, labyrinths and hexagons.
አበው እና ሕጽናዊነት
“የጥንት ሰዎች ሙሉዕ የሆነ ሕይወት ነበራቸው፡፡ ማለት የሚያደርጉት፣ የሚያስቡትና የሚያመልኩት ሁሉ በአንድ ወጥ የፍልስፍናና እና የእምነት ሥርአት የታገገ ነው፡፡ ታዲያ እንጀራ ከምግብነቱ ሌላ ይሄንን ተንተርሶ ምን ተጨማሪ መልዕክት (ሃይማኖታዊ፣ ማህበራዊ፣ ስነልቦናዊ፣ ታሪካዊ) ሊኖረው ይችላል? ለእኔ ይሄ “ዳቦ” ምን ያወራልኛል? እንጀራ ራሱ ልክ እንደ መጽሐፍ ወይም እንደ ሃውልት ታሪክ ማስተላለፊያ ወይም የፍልስፍና ማስተላለፊያ ከሆነስ?
…ብዙ ጊዜ ሰዎች ሃሳባቸውን በቋንቋ (በተረት)፣ በዕብነታ-ፅሁፍ፣ በብራና፣ በወረቀትና በእንጨት ላይ ታሪካቸውን ብቻ ሳሆን ራዕያቸውንም ይፅፋሉ” (አዳም “የአብሮነት ቃል” ለተሰኘው መጽሔት ካደረገው ቃለ ምልልስ የተወሰደ)
“ሕጽናዊነት ስለሚታይ እና የማይታይ ግንኙነት (connectivity) የሚያስረዳ እሳቤ ነው፡፡ አበውን ሳስብ የሚገባኝ የምንበላውን ነገር እና ስለ አበላላችን ጭምር በያንዳንዱ ነገር ውስጥ ምስጢር እንደሚተክሉ ነው”፡፡
“አበው ይሄን የተገናኝነት ነገር ሲያገኙ/ሲፈለስፉ ሕይወታችንን እናቆይበት ዘንድ የምንበላው እንጀራ ብቻ አይደለም ያወረሱን፤ ጥልቁን የዩኒቨርስ፣ የአገርና የግለሰብ የተገናኝነት ጽንሰ ሐሳብ ጭምር እንጂ”፡፡ When the ancients discovered/ invented this form they not only bequeathed to us the “Injera” as a font of sustenance, but also a transporter of the deep and necessary understanding of the concept of connectivity in the universe, the nation and the self.
“እንጀራን አቅርበን ብናየው ዐይኖቹ ባለ ስድስት ጎን ጉድጓዶች ናቸው፡፡ ይሄ ደግሞ የሰው ልጅ ቆዳ ሴሎች ቅርጽ ነው፣ የደም ሴሎች፣ እንጨት፣ ብረት፣ አፈር ወዘተ ይሄው ቅርፅ አላቸው፡፡ ይሄን የመሳሰለው ሙሉኩሏዊ (universality) የቅርጽ መመሳሰል እንጀራን የሆነ ትዕምርታዊ ኃይል (symbolic power) እና የሆነ ዓይነት የታቀደ/በዕውቀት የተደረገ/ ዓላማ (a sense of planned purpose) ይሰጠዋል”፡፡
በተጨማሪም “አበው በዩኒቨርስ ውስጥ ያሉ ነገሮች ሁሉ አንዱ ከሌላው የተገናኙ መሆናቸውን አውቀው በእንጀራ ውስጥ በሚስጥር ማስቀመጣቸው አዲስ የልቦለድ ቅርጽ ዲዛይን ለማድረግ ያገለግል ይሆናል፡፡ እንጀራ የአንድ ሀሳብ ትውስታ ነው፤ ህብር ያለው ተገናኝቷዊነትን የማግኘት/የመፈልሰፍ ሀሳብ”፡፡ The realization of the ancients about the interconnection of the universe as coded in the injera can be an instrument in designing a fictional form. Injera is the memory of an idea; the idea of discovering or inventing a harmonious connectivity.
“አፄ ሰንደቅ ዓላማ እንስሳትን ሲያዳቅሉ ያደረጉት ቢኖር ከዚያ በፊት ተገናኝተው የማያውቁ ዘረመሎችን አገናኝተው ከዚያ በፊት ያልነበረ አዲስ ችሎታ/መለያ ባሕሪ መፍጠር ነበር፡፡ ይሄ ማለት በቸልታ የጠፉ ወይም ሆን ተብሎ የወደሙ የግንኙነት መረቦችን መፈለግ አለብን ማለት ነው”፡፡
ሕጽናዊነት ልዩ ተአብ ነውን?
“ልቦለዶቻችን በአብዛኛው ቀጥታዊ ወይም ክባዊ (linear or circular) እንደሆኑ ብዙ ጊዜ ሲባል ሰምተናል፡፡ እኔ ደግሞ ሁሌ  በተቃራኒው ቀጥታዊ ትረካ ዕውነታን ለማሳየት ጥንካሬ የለውም ብዬ አስባለሁ፡፡ አንድ ሰው ደግሞ የቀጥታዊ ትረካ ስልቶች አቅም ላይ ጥርጣሬ ካለበት ሌላ የተለየ ጂኦሜትራዊ ዘይቤ መፈለግ ይኖርበታል፡፡
የ1974 የኢትዮጵያ አብዮት የቀጥታዊ ተረክ ሞት መጀመሪያ ነበር፡፡ ያኔ የተፈቱት ብትንታኞች እስካሁን ድረስ በማንኛውም ዓይነት የሕይወት እንቅስቃሴያችን ላይ ተፅዕኖ ሲያሳርፉ ይታያል፡፡ (The fragmenting elements unleashed then are still working their way through all aspects of life) በዝብርቅርቅ ውስጥ ያለ ማሕበረሰብ ደግሞ ቀጥታዊነት የሚስማማቸው ግለሰቦችን ሊወልድ አይችልም፡፡ እነኚህን ዕውነታዎችና ሂደቶች ለማሳየት ደግሞ ሌላ መንገድ መፈለግ ነበረብኝ፡፡ ከእንደዚህ ዓይነቱ ዝብርቅርቅ የሚገኘው ጂኦሜትሪያዊ ዘይቤ ደግሞ መረባዊ አወቃቀር ወይም ውስብስባዊ ነው፡፡  ታዲያ ይሄንን ለመወከል ከእንጀራ በላይ ምን ተገቢ ነገር አለ?”
እንጀራን መሠረት ያደረገውን ይሄን “የአፃፃፍ ስነግብሬን (method) ሕጽናዊነት እለዋለሁ፡፡ የምናገርለት ጉዳይ በእኛ አገር አዲስ ቢሆንም በሌሎች አገሮች የተሠራበት ወይም እየተሰራበት ያለ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚያ በኩል በሰፊው ልናገርለት የምችል የአለቃ ግንዛቤ የለኝም፡፡ ግን የአፃፃፍ ስልቴን ከመግለጫዎች በፊት በድርጊት ለማምጣት ሞክሬያለሁ፡፡ ይሄም የራሱ መሰረት አለው፡፡ በ”ግራጫ ቃጭሎች መግቢያ ላይ የሞከርኩት መንደርደሪያ ቢሆንም ቦታው እንዳልሆነ የተቹኝ አሉ፡፡ የሆነ እውነትነት አለው፡፡ ምናልባት ቆየት ብዬ ስለ ስነግብሬ በሆነ መልክ ለአንባቢያን ለብቻው ማቅረብ እንዳለብኝ አምናለሁ፡፡
እኔ በተመጠነ ደረጃ በፅሁፍ ወይም ስርዓት ባለው መንገድ ግልፅ ባላደርገውም ሕጽናዊነት አንዳንድ የሚያዋጣ አቅጣጫ ሊይዝ እንደሚችል ከፍንጭ በላይ መከራከሪያ አለኝ፡፡ አንዱ ድርጊቱ ነው፡፡ “ግራጫ ቃጭሎች”፣ “እቴሜቴ ሎሚ ሽታ” እና “ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ” ድርጊቶቹ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ኮስታራ ከሆነ ወይም ከተባ የስነፅሁፍ ወይም የባሕል ሂስ ካለበት ሕብረተሰብና ልብወለድ ሳይሆን ንዑስ ዘውጎች ያልተሰሙለት ዘመናዊ ከተባለ የስነፅሁፍ ባሕል የተመዘዝኩ ነኝ፡፡   
ይሄ እጥረት በሆነ መልክ ድጋፍ ያጣሁ ደራሲ ያደርገኛል፡፡ የራሴን ፍልስፍና ስናገር በአገራችን የመጻፍ ካርታ ላይ ከማንና የት ጋ እንደምታስቀምጠው ግራ ሊያጋባ ይችላል፡፡ ይሄ ባይተዋርነት ሆነ ተብሎ ከሚሰነዘር አግላይነት ጋር ሲደመር ሕጽናዊነት የሚለው ቃል ገቺ ወይም አግላይነት ይኖረዋል” (የአብሮነት ቃል)
በተጨማሪም… “አንድ ጽንሰ-ሐሳብ በትንሽ ነገር እንኳን ቢለይ አዲስ ስያሜ ማውጣት መብት አለኝ፡፡ ማንም አለው፡፡ ለምሠራቸው የፈጠራ ሥራዎች በቅርፅ የራሳቸውን ባህርይ ልሰጣቸው እሞክራለሁ፡፡ አዲስ ጉዳይ ቅርፅ ነው፡፡ ለአስተማሪነት ቀበቶዬን አጥብቄ አላውቅም፤ የማን ወገብ ከማን ይበልጣል፡፡ የማንስ ድግ” (ግራጫ ቃጭሎች፤ እንደ መግቢያ)፡፡ ይሄ የአዳም አባባል ወጥ ሆኖ እስካሁን ቀጥሎ “ሕጽናዊነት ያሳያል እንጂ አይሰብክም” ይላል፡፡ (መረቅ፤ ገጽ 599) “ስራዬ በገለልተኛ ንቅናቄ መስታዎቱን የመገለባበጥ ነው፡፡ ተዳፋቱን እዚያ እና እዚህ በማድረግ ያለመጠን እውነታ ከፍርድ ሳይጠጉ ለአንባቢ ዐይን ማብቃት ነው፡፡” (“ግራጫ ቃጭሎች”፤ እንደ መግቢያ፡፡) ወይም ደግሞ በቀላሉ ለማስቀመጥ፡- “ሕጽናዊነት ያሳያል እንጂ አይሰብክም”፡፡
ሕጽናዊነትና ራይዞም (Rhyzome)
“ጂኦሜትሪና ልቦለድ አፃፃፍ ያላቸው ግንኙነትና ትርጉም ስለሳበኝ ንባቤን በመጠኑ አሰፋሁና ይሄን በሚመለከት የተደረጉ ነገሮች እንዳሉ ለማጥናት ልሞክር ብል ከመጀመሪያ መጀመር ግድ ይላል፡፡ ከላይ እንዳልኩት ያለሁበት የግል ሁኔታ የተለየ ነው፡፡ ከጀርባዬ ሰፊ የድርሳን ትንታኔ፣ ረቂቅ የሂስና የፍልስፍና ባህል የለም፡፡ ያን አድካሚ ጉዞ ካላሳለፈ ህብረተሰብ ነው የወጣሁት፡፡ በግልም ደረጃ በሁሉም አቅጣጫ ሊያስኬደኝ የሚችል የፍልስፍና ዕውቀት ያጥረኛል፡፡ እኔ የመጣሁት ከጉዳዩ ጀርባ ነው፡፡ ይህ ማለት በመከወን ሂደት ውስጥ ካጋጠመኝ ጥቅንጥቅ እንጂ ከትወራ ጥናት አልተነሳሁም፡፡ ያለሁበትን ሁኔታ በቲዮሪ ለመረዳት ስሞክር ካደረግሁት ትንሽ ልፋት የተረዳሁት፣ [ሕጽናዊነት] ጓታሪና ደሉዝ፤ “ካፒታሊዝምና ስኪዞፌርኒያ” (Capitalism and Schizophrenia) በተባለው መጽሐፋቸው ከጠቀሱት ራይዞም [Rhizome] ከተባለው ሞዴላቸው (የማሕበረሰብና የዕውቀት ሞዴል) ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ነው፡፡ ራይዞምን የሀሳብ ምስል ነው ይሉታል፡፡ በተለይ የኢንተርኔት መምጣት የዚህን ፅንሰ ሀሳብ ቦታ ከፍ አድርጎታል፡፡ በብዙ በኩል ሕጽናዊነት ከዚህ የሚመሳሰል ሆኖ ሳለ፣ ራይዞም ተዋረድን (hierarchy) ቦታ ባለመስጠቱ የሚለይ ይሆናል፡፡ በተለይ እ.ኤ.አ. ከዘጠናዎቹ መጨረሻ አካባቢ ጀምሮ ተፅዕኖ ማሳደር የጀመረው በይነ ዲሲፕሊናዊው ኢኮሎጂካል ትወራ የግንኙነትን ቸል መባል ፍቆታል፡፡
የሕጽናዊነት አንዱ አጀንዳ በመስመር ሳይሆን በመረብ ስልት የማሰብ ነው፡፡ ይሄ የሰለጠኑት በተባሉ አገሮች እንግዳ ላይሆን ይችላል፡፡ የትራንስፖርት፣ የኤሌክትሮኒክስ ቴክኖሎጂ መርቀቅና የመረጃ መረቦች መንሰራፋት እንግዳ አያደርጉትም፡፡ እንደኛ ባለ ቴክኖሎጂ ባልዳበረበት ሕብረተሰብ ውስጥ ይሄን ማንሳት ነገሩ ሳይመጣ ትንሽ መቅደም ይመስላል፡፡ ግን አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ አካባቢ ለብዙ ሺህ ዘመናት የኖረ ነው፡፡ መረቡ ትራንስፖርትና ኤሌክትሮኒክስ ባይሆንም ጀነቲክ፣ ቋንቋ፣ ጦርነትና የንግድ ግንኙነት ነው”፡፡ (የአብሮነት ቃል)
ከሕጽናዊነት ባሻገር፡ ጠጠር መጣልና ብዕር መጣል
በ”እቴሜቴ ሎሚ ሽታ” ውስጥ የሚገኘው መስኮት ገረሱ የተባለ ሰዓሊ የስዕል ሥራዎቹ ከየትና እንዴት እንደመጡ (እንዴት ሊፈጥራቸው እንደቻለ ባለማወቁ) ስዕል መሳልን ከጠጠር ጣይነት ጋር ያወዳድረዋል፡፡ “ስዕል መሳል ከጠጠር መጣል ጥንቆላ ጋር ስለሚመሳሰልብኝ ነው፡፡ አንዳንድ ኪነታዊ ውጤቶቼን ሳይ በአብዛኛው ሳላስባቸው የመጡ ናቸው፡፡ ከየት መጡ? ማን መራኝ? እነዚህ ጥያቄዎች ያገሬን ጠንቋይ ያስታውሱኛል፤ የኪነት የፈጠራ ሂደትን የአስማታዊነት ፈርጅ አያለሁ፡፡ ከየት እንደመጡ ካላወቅሁ ከጠጠር ጣይና ከኮከብ ቆጣሪ ምን ይለየኛል?” (ገጽ 43 - 44)፡፡
እኛስ “ጠጠር መጣል” ተብሎ “ብሩሽ መጣል” ከተባለ “ብዕር መጣል” ማለት እንችል ይሆን? የአዳም ማብራሪያ ለዚህ ይሁኝታ የሚሰጥ ይመስላል፡፡ “አለንጋና ምስር” በተባለው መጽሐፉ ውስጥ የሚገኘውን “ዘላን” የተሰኘ ትረካ በጠልሰም መልኩ ለማስቀመጥ እንደሚቻል ሲያብራራ፤ “እንዲህ ስናደርግ [ጠልሰም ስንሠራ] ያልታቀዱ/ያልተገመቱ ግንኙነቶችን ነው የምንስለው፡፡ የሚመጣው ውጤትም ቀድሞ የታቀደ አይደለም”፡፡ There are of course stochastic processes involved in this. Outcomes are not a priorily designed ይላል አዳም፡፡ አዳም ይሄንን ያለው ለሁሉም ልቦለዶቹ ነው ብለን ብንለጥጠው ታዲያ ድርሰት መጻፍ ብሩሽ መጣል አልሆነም? መስኮት ከ”ጠጠር መጣል” ወደ “ብሩሽ መጣል” ከሄደ እኛስ አዳምን ወደ “ብዕር መጣል” ብንወስደው ምን ይለናል? አዳምም ያለነገር አይደለም ስለ “ጠልሰም” እና “ክታብ” ብዙ የሚያብራራው ብንልስ ያስኬደናል?
አዳም ስለ ሕጽናዊነት ሲያብራራ በተደጋጋሚ የሚጠቅሳቸው ሁለት ቃላት አሉ፡፡ እነኚህን ቃላት በተለምዶ የምናውቃቸው ከአስማት፣ ከድግምትና ከመሳሰለው ነገር ጋር በተያያዘ ነው፡፡ እነኚህ ቃላት “ጠልሰም” እና “ክታብ” ናቸው፡፡ ትርጓሜያቸውን አስቀምጠን እንቀጥል፡-
 ጠልሰም፡- የተለያየ ስዕል ያለበት የጥንቆላና የአስማት ጽሑፍ የያዘ ጥቅል ብራና ወይም ወረቀት፡፡ (አማርኛ መዝገበ ቃላት፤ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናት እና ምርምር ማዕከል፤ 2001 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ) ክታብ፡ ከበሽታ እንዲያድን ወይም ከክፉ ነገር እንዲጠብቅ ተብሎ በብራና ወይም በወረቀት ላይ ተፅፎና ተጠቅልሎ በአንገት ወይም በክንድ ላይ የሚታሰር መድኃኒት፡፡ (ዝኒ ከማሁ) እነኚህ ከላይ ከመዝገበ ቃላት ፍቻቸው ጋር የተቀመጡት ሁለት ቃላት ከአዳም ድርሰት በተለይም ከሕጽናዊነት ጋር ምን አገናኛቸው? በወረቀትና በብራና ላይ ተስሎ ከበሽታና ከክፉ ነገር እንዲያድን በክንድ ወይ በአንገት ላይ የሚንጠለጠለው ጠልሰም ወይም ክታብ ውስጡ ተፈትቶ ቢታይ ሌላ ተዓምር የለውም፡፡ መረባዊ ግንኙነት ያላቸው መስመሮችን የሚያሳይ ስዕል እንጂ፡፡ “ጠልሰም ማለት መረባዊ ግንኙነት ነው፤ ሕጽናዊነትም ያለ ጥርጥር እንደዚያው” … Telsem is all about interconnectivity which hitsinawinet undoubtedly is.
ታዲያ በታሪኮቹ ውስጥ ጠልሰምን መሥራት ብቻ ሳይሆን በአንገታችን እንድናንጠለጥል የሚጋብዘው ይሄ “ምትሃተኛ” ደራሲ፤ “…ይሄም ማለት በአጋጣሚ የጠፉ ወይ ደግሞ ሆነ ተብለው እንዲጠፉ የተደረጉ የግንኙነት መረቦችን ፍለጋ መውጣት ነው ይላል”፡፡
…meditate on the injera. Carry an injera Telsem around your neck……in your mouth. This means look for connections, arbitrarily lost or purposely subdued.
በቅርቡ የወጣው “መረቅ” የተሰኘ መጽሐፉ በፊት ሽፋኑ “ሞዴል ጠልሰም” ይዞ ከመውጣቱ በፊት ደግሞ አዳም ይሄን ብሏል… “ለወደፊት ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ውስብስብ የሆኑ ልቦለዶችንና ታሪኮችን ባለ ሁለትና ባለሦስት ዲሜንሽናል ጠልሰሞችን በማዘጋጀት ከልቦለድነትም ባሻገር እንደሚታዩ የጥበብ ውጤቶች (visual art products) ወስደን ልናነፃፅራቸው (ልናደንቃቸውም) እንችል ይሆናል”.”
ደራሲው ቀድሞ እንዳለውም  “መረቅ” ላይ ጠልሰሙን ከነ”የአሠራር ቅደም ተከተል መመሪያ”ው ይዞ መጣ፡፡ በዚህ መጽሐፍ መውጫ የመጽሐፉ ትዕምርት መሆን የሚችለው ጠልሰም እንዴት እንደሚሠራ ሲያብራራ በመጽሐፉ የመጨረሻ ገጾች ላይ ማየት ይቻላል፡፡ የሽፋን ስዕሉ ላይ ያለውን ጠልሰም ሲያብራራ…  ”ደራሲው ይሄን ጠልሰም ለመስሪያ የተጠቀመባቸው ቃላቶች አንጓ፣ መለልታና መረቅ የተባሉትን ብቻ ነው፡፡
 ስዕሉ ‘መረቅ’ የተባለው ይሄን ልቦለድ ‘ወካይ’ ነው” ብሏል፡፡በሌላ በኩል ደግሞ ሕጽናዊነት እስከዛሬ ከለመድናቸው የተለዩ የሂስ ስራዎችን እንድናዳብር ይገፋፋናል፡፡  በቋንቋ ብቻ ከማጥናት በምስልና በአሃዝ ማጥናትና መተቸት ያስችለናል፡፡
ለምሳሌ በመረብ ካርታ (network mapping) ወይም በአክተር ኔትወርክ ቲዮሪ ቋንቋ ውስብስብ ካርታዎች (complexity mapping) በመስራት፣ ወይም በዲስኮርስ አናሊሲስ ካርታ (discourse analysis mapping) አልፎ ተርፎም በአሃዝ ማስላት እንድንችል ይገፋፋናል፡፡ ከቃላት ዘልቆ የገጸባሕሪያት ቦታ (space) በነዚህ ዓይነት ውስብስብ ጠልሰሞች ሊታይ፣ ሊገለጽና ሊገመገም ይችላል፡፡   
በመጨረሻም እንጀራውን እንብላው…
እንጀራ ሊበላ የሚችል/በምግብ መልኩ የቀረበ/ ብራና ነው … “It is an edible Brana” እንዲል ደራሲው፡፡
እንግዲህ ደራሲው አዳም ረታ ከዚህ በፊት በነበሩት መጻሕፍቱ እንጀራው እንዴት እንደሚሠራ ከሚለው ጀምሮ የመጋገር ሂደቱን፤ አቀራረቡን፤ የተመጋቢዎችን አሰላለፍ፤ ጉርሻውን፤ የጉርሻ አሠራርና ይዘቱን ወዘተ ሲያስረዳን ቆይቶ በስምንተኛው መጽሐፉ መረቅ ደግሞ እንድንበላው አቅርቦልናል፡፡
  “የሴራ ሂደት/ ምት/ የቃላት አሰዳደር ወዘተ ለእኔ ወጡ በእንጀራው ላይ ከሚያደርገው ፍሰት ጋር ይመሳሰላሉ፤ ልክ ውሀ በስፖንጅ ውስጥ ወይም ደግሞ በአፈር ውስጥ ሰርጎ ሲገባ ዓይነት” የሚለው አዳም፤ “የማንበብ ሂደቱ እንጀራውን መዘርጋት፣ እንጀራው ላይ ወጥ/መረቅ የማፍሰስ፣ በሂደቱም መጎራረስ፣ በስተመጨረሻም የቀረውን አንድ ገጽ የመረቅ ቅሬት ጠርጎ መብላትን ያካትታል፡፡ ‘የመጽሐፍ ቀበኛ’ አለነገር አላሉም አበው” ይላል በገጽ 600፡፡

Published in ጥበብ
Saturday, 25 October 2014 10:50

አንድስን‘ኳ (ምናባዊ ወግ)

     በፍጥነት የሚያልፍ ቅጽበትን ለመያዝ የማደርገው ሙከራ ተሳክቶልኝ የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ ብዙ አይነት ሰዎች በአጠገቤ ያልፋሉ፤ እነሱ በእኔ አንፃር ያለፉትን ያህል እኔም በእነሱ አንፃር አልፌባቸዋለሁ፡፡ ግን የሚያልፈውን ሁሉ በማያልፍ ማስታወሻ ማስቀመጥ እፈልጋለሁ፡፡
ለማስታወሻ አይን አይጠቅምም፡፡ የአይን ካሜራ የቀረፀውን ነገር ከከተተበት ጐተራ መልሰህ አውጣልኝ ቢሉትም ‹በጄ› አይልም፡፡ ስለዚህ የምመለከታቸውን ሰዎች እና ነገሮች በአንድ ምልክት መሰየም ጀመርኩ፡፡ ለምሳሌ፤ በአንዲት ሴት ላይ አይኔ ያርፋል፡፡ ሰው መሆኗ ግልጽ ነው፡፡ ከሰውነት ባሻገር ምንድናት? በእይታዬ እሷን በአንዴ አጠቃልዬ የምገልጽበት መወከያ ያሻኛል፡፡ ጊዜ የለኝም፡፡ ጊዜ ቢኖረኝ ኖሮ፣ ቅጽበቷን ለጥጬ ሴቲቱንም እንዳታልፈኝ አስቁሜ “ስምሽ ማነው? ከየት ነው የመጣሽው? ወደ የትስ ነው የምትሄጂው? ወደዚህ ቦታ ከመምጣትሽ በፊት በማን በኩል ወደ ምድር መጣሽ? አመጣጥሽስ ምን ይመስል ነበር?...” ወዘተ… ማለቂያ የሌላቸው ጥያቄዎችን አቅርቤላት፣ ስለ ቅጽበቷ እና ቅጽበቷን ስለወከለችው ስለ ሴት የተሻለ፣ የተለጠጠ ማስታወሻ አሰፍር ነበር፡፡ ግን ጊዜ የለም፡፡
እኔ በመሰረቱ እንደ ትራፊክ ፖሊስ ነኝ፡፡ ሰዎች እና ነገሮች ወደ እኔ ሲመጡ አሳልፋቸዋለሁ እንጂ እያንዳንዳቸውን ስለ መምጪያቸው እና ስለ መድረሻቸው አስቁሜ ልጠይቅ አይቻለኝም፡፡
ትራፊክ ፖሊስ ራሱ አንዳች የተለየ ነገር ካላገኘ የሚያልፍ እና የሚያገድመውን ተሽከርካሪ ሁሉ አቁሞ መመርመር አይችልም፡፡ ትራፊክ ፖሊስ ለተሽከርካሪ አሳላፊ እንደሆነው እኔ ደግሞ የተራማጆቹን የሰው ልጆች በዓይኔ እየፈተሽኩ እልካቸዋለሁ፡፡  
ለምሳሌ፣ ይሄ ልጅ ከፊለፊቴ እየመጣ ነው፡፡ የተለየ ቁመትም ሆነ የተለየ ውፍረት የለውም፡፡ እድሜው በጣም አላረጀም ወይንም እንጭጭ አይደለም፡፡ ምን ብዬ ልሰይመው?... ጐባጣም ወይንም ሰንካላም አይደለም፡፡ ገጠሬም ይሁን ከተሜ ጐልቶ የወጣ ነገር የለውም፡፡ ይኼንን ሁሉ የምመዝነው በፍጥነት ነው፡፡ አልፎ ከመሄዱ አስቀድሞ፡፡ አልፎ የሚሄደው፣ ለማለፍ ተከትሎ ከበስተጀርባ የሚመጣው ሳይደረብ ለእያንዳንዳቸው ነጠላ ትርጉም ማግኘት አለብኝ፡፡ ስላለብኝ አገኘዋለሁ፡፡ ደግሞም አገኘሁለት፡፡ ከአይኑ ስር አንድ ትልቅ ጠባሳ አለው፡፡ የአይን አምላክ ውድ ልጅ መሆኑን አወቅሁኝ፡፡
“እጓለ አይን አምላክ” ብዬ አጠቃለልሁት፡፡
ከእሱ ተከትላ የተከሰተችውን በተመሳሳይ መንገድ በቅጽበቷ አቅም መረመርኳት፡፡ “ደርባባ” የሚለው ይጠቀልላታል፡፡ እንደዚሁ እያልኩ የሚመጡትን ሁሉ መጠቅለል ያዝኩ፡፡ ሁሉም አንድ ቃል ይገኝላቸዋል፡፡ “ኮራ ያለ ዳሌ” ብዬ ሌላኛዋን ቦሎ ከለጠፍኩላት በኋላ ተወዛገብኩ፡፡ “ኩራት” ከእራት ጋር እንጂ ከዳሌ ጋር ምን ግንኙነት አለው? ብዬ ትንሽ አሰብኩ፡፡ የኢትዮጵያዊ ኩራት በሴት ዳሌ ላይም ይገኛል ማለት ነው? … ስለ ዳሌ ኩራት ትቼ አዲስ የሚመጡትን በስያሜ መወከል ቀጠልኩ፡፡
“ቆፍጣና፣ ግሮ ኗሪ፣ ጐባጣው፣ ፍሪክ፣ ፍሪክ ነኝ ባይ፣ አኩራፊው …ንቅሳቷን ለመደበቅ የምትኖር መሳይዋ መጣች፡፡ አንገቷ ላይ ተጽፎ ሳይላክ የቀረውን ደብዳቤ ለመደበቅ እየሞከረች በስልኳ ፌስ ቡክ ትላላካለች፡፡ “ወግን በወግ” አልኩና ሰየምኳት፡፡ አለፈች፡፡ እሷ በአለፈችኝ መጠን እኔም አልፌበታለሁ፡፡
እንደ ትራፊክ ፖሊስ ነኝ፤ እየፈለኩ ያለሁት ግን ወንጀለኛን አይደለም፡፡ ገፀ - ባህሪን ነው፡፡ ትራፊክ ፖሊስ ወንጀለኛ ካጣ ስራ ማጣቱ እንደማይቀረው እኔም ገፀ ባህርየ ካላገኘሁ ፀሐፊነቴ ብዙም አያስጉዘኝም፤ ማግኘት ካልሆነልኝ መፍጠር እገደዳለሁ፡፡ እኔ ራሴ በመፈጠር ሂደት ላይ ነኝ፡፡ የመሞቻዬ እለት ተፈጥሬ እጨርሳለሁ
ቀጠልኩ፡-
“ቀጭን”፣ ሳቋን ተቆጣጥራ ኮስታራ ለመምሰል የምትሞክር “ሳቂታ”፣ ከሷ በኋላ “ነጭናጫዋ” አለፈች፣ ሸንኮራ ለመብላት ሲል ሸንኮራ ሻጭ የሆነ ልጅ “ጥርስ ፍልጥ”፣ ዘመናዊ እናት፣ ከውጭ ሀገር የመጣ ለመምሰል የሚጥር የገጠር ወጣት እና እሱን መሳይ ሚስቱ፣ ካድሬ፣ መኪና መግዛት የሚመኝ ሾፌር፣ ተማሪዎቹን የሚጠላ አስተማሪ…
በአይኔ እየመዘንኩ የይለፍ ቦሎ በስም መልክ እየለጠፍኩባቸው ነው፡፡ አንዳንዴ ልክ የእኔን መሳይ ተፈጥሮ ካለው የደራሲ ነፍስ ተሸካሚ ጋር አይን ለአይን እጋጫለሁ፡፡ እኔም እሱን… እሱም እኔን ሰይመን፣ ተሰያይመን… ቦሎ እርስ በራሳችን ግንባር ላይ ተለጣጥፈን እንተላለፋለን፡፡
እኔ ተቀምጬ እንደሁ የሰው ትራፊኩን የማሳልፈው… አምሳያዬ ደግሞ ወደ መንገዱ ጥግ ሄዶ ጋዜጣውን እያገላበጠ ስራውን ይሠራል፡፡
እኔ እና መሰሎቼ (ደራሲዎች/ፀሐፊዎች) ከትራፊክ ፖሊስ የምንለይበት ነገር አንድ ብቻ ነው፡፡ እኔ ለመያዝ የምፈልገውን ገፀ ባህርይ ሌሎቹ  ላይፈልጉት ይችላሉ፡፡ እነሱ ያለፉትን እኔ ጨምድጄ ልይዝ … እኔ የጨመደድኩትን ደግሞ እነሱ ቦሎ ለጥፈው ሊያሳልፉ ይችላሉ፡፡
“ባለንቅሳት (ባለታቱ)፣ አይን አልባው ባለ መነጽር (ሲደናበር መኪና ሊገጨው ስለነበር)፣ “የወንዶች ፈተና” (አጭር ቀሚስ ለብሳ ከመኪና ወረደች፤ ትንሽ ቆማ በሌላ መኪና ተጠለፈች)፣ በመሬት ላይ እየተንፏቀቀ የሚጓዘውን የእኔ ብጤ “ባለ ኩሽኔት” አልኩት… ቦርጭ ጠንክሮ እያሰባሰበ ያለ ንዑስ ባለሀብት፣ በጀርባ መታዘል የለመደ ልጅ የፈረንጅ ማዘያ ግራ አጋብቶት ቀና ብሎ ያዘለውን የጉዲፈቻ አባቱን ፊት እየተመለከተ አለፈ፤ ቦሎ ለእሱም ቢሆን ለጠፍኩለት “አለማየሁ ቴዎድሮስ” - የሚል፡፡ እኔ ቦሎ እንደለጠፍኩለት እሱም በጉዲፈቻ አንቀልባ ላንጠለጠለው ፈረንጅ ካለበት ቅርጫት ቀና ብሎ… ቦሎ የመለጠፍ አቅም ላይ ደርሶ ይሆናል? አላውቅም!
“ገጣሚ መሆን የሚፈልግ የባንክ ሰራተኛ… (Poet and Shylock)… ጫት መቃም በቅርቡ ያቆመ ጴንጤ፣ ሴንጢ በቀረበት ዘመን ሳንጃ በጀርባው የያዘ የመንደር ፍንዳታ “ባላቶሊ”፣ ሴቴ ሎቲ (አንጠልጣይ ሳይሆን አጣባቂ)፣  በሽታ ኪሎውን የፈተነበት፣ ሲጋራ ማጨሻ ቦታ በአይን የሚያስስ…፣ አጭር፣ በጣም አጭር፣ ከድንክ በመለስ ሁሉም ቦሎ አገኙ፡፡ ከመጠን ያነሰ መጠን ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ምናልባት ገፀ-ባህርይ ማለት ከመጠን ያነሰ መጠን ይሆን እንዴ… ወይንም ከመጠን በላይ የገዘፈ “ጃይንት”?… እንደዚያ አይነቱን ነው የምፈልገው… ለገፀ ባህርይነት፡፡ ግን ሁሉም እስካሁን ያገኘሁዋቸው መሀል ቤተኛ ናቸው፡፡ ከሆኑት በላይ አሳድጌ…. ወይንም አኮስሼ (ካልከሰስኳቸው) ያለ በቂ ምክኒያት ወስጄ ካላፃፍኳቸው በቀር… አሁን ሆነው እንደተገኙት ምንም ወንጀል የለባቸውም፡፡ አይጠቅሙም ወይም አይጐዱም፣ ጥሩንም መጥፎንም ለማስተማር አያገለግሉም፤ ለእውነትም ሆነ ለእውቀት ማስፈንጠሪያ ደጋን አይሆኑም፡፡
ወንጀለኛ ለካ የሆነ የተለየ ነገር ያለው የሰው አይነት ነው፡፡ ውስጡ የሆነ ተራራ ወይንም ዋርካ ቆፍሮ የቀበረ… ግን በውስጡ የቀበረውን በሆነ ቅንጣትም መግለጫ ቢሆን በስተውጭ ማንፀባረቅ ነበረበት፡፡ አንድም ወንጀለኛ አላገኘሁም፡፡
አስቀያሚ ቀን ሆነብኝ፡፡ ቦሎ ስለጥፍ ዋልኩ፡፡ አንድም ገፀ-ባህርይ ግን አልያዝኩም፡፡ ጸሐፊ ልዩ ያልሆነ ሰው ያስጠላዋል፡፡ ምናልባት ለትራፊክ ፖሊስ ደግሞ ህግ አክባሪ ተራ ሆኖ ሳያስጠላው አይቀርም፡፡ ዘበኛ የሚጠላው የማይሰርቅን ሰው አይደል? ምክኒያቱም የማይሰርቅ ሰው በሞላበት ሀገር ዘበኛ አያስፈልግም፡፡ እኔ እንደ ሄማንግዌይ “ሽማግሌ እና ባህሩ” ገፀ ባህርይ (ሳንቲየጐ) እድለ ቢስ የሆንኩ መሰለኝ፡፡ ይሄው ምንም አይነት የገፀ ባህርይ አሣ ሳላጠምድ ድፍን አመት ሞላኝ፡፡ አንድንስ‘ኳ! በየቀኑ የአሣ አጥማጅ መረቤን እና የፖሊስ ፊሽካዬን ይዤ በጠዋት ከቤት እወጣለሁ… መረቤን በህዝቡ ፊት ላይ ጥዬ ስቤ ሳወጣ የማገኘው የምፈልገውን አይደለም፡፡ እኔ እምፈልገው ትልቅ አሣ ነው፡፡ ትልቅ ገፀ ባህርይ፡፡ ትልቅ ገፀ-ባህርይ ብዙ ጊዜ ትልቅ ወንጀለኛ ነው፡፡ አንዱም ሶስቱም ከህዝብ መሀል አልተገኙም፡፡  ምናልባት ሳንቲያጐ (የሄሚንግዌይ ገፀ ባህርይ) እንዳደረገው፣ በባህሩ ላይ ርቄ መሄድ ሳይኖርብኝ አይቀርም፡፡ ወደ መሬት ሳይሆን ወደ ሰማይ መመልከት ይኖርብኛል፡፡ ሰዎች በመሰረቱ ትልቅ አሣም ሆነ ትልቅ ገፀ ባህርይ አይሆኑም፡፡ ትልቅ ወንጀለኛም አይወጣቸውም፡፡
ወገቤን ወደ ባህሩ ሳይሆን ወደ ሰማዩ መጣል ይኖርብኛል፡፡ ምናልባት እዛ… የትልቅ ገፀ ባህርይ መሰረት የሆነውን እግዚአብሔር ወይንም የትልቅ ወንጀለኛ አባት የሆነውን ሰይጣን በዓሣ መልክ የማጥመድ እድል አገኝ ይሆናል፡፡ ቦሎ መለጠፍ ካለብኝ፣ የሰማዩ አካላት እንጂ የምድሮቹ አይረቡኝም፡፡ለሚቀጥለው አመት መረቤን በብርሐን እና በጥላ አጠንክሬ… በፍትህ እና ክፋት ጠላልፌ እሰራዋለሁ፡፡
 ይሄ ራሱ አመታትን ሊወስድ ይችላል፡፡ ይውሰድ እንጂ አደርገዋለሁ፡፡ ያኔ መረቤን በሰማይ ላይ እጥላለሁ፡፡ የረጅሞቹን ረጅም እና የአጭሮቹን አጭር አጥምጄ የገፀ ባህርይ ትንግርት እፈጥራለሁ፡፡
ከሰዎች ከእንግዲህ ምንም አላገኝም፡፡ ሰዎች መሀከለኛ ናቸው፤ በጣም ትልቅ ወይንም ትንሽ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ሰዎች ጠፍጣፋ ናቸው፡፡
 ጠፍጣፋን የእውነተኛ ቁመት እና ወርድ መስጠት አይቻልም፡፡ ለመስጠት እየሞከርኩ መረብ ስለምጥልም ነው ምንም ገፀ ባህርይ አመቱን ሙሉ ያላጠመድኩት፡፡ ከዚህ ቀደም የነበረው ተሞክሮዬ ግን ከሚቀጥለው አመት ጀምሮ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይቀየራል፡፡

Published in ጥበብ
Saturday, 25 October 2014 10:47

የፀሃፍት ጥግ

* ደራሲ ልብወለድ ሲፅፍ ህያው ሰዎችን መፍጠር አለበት፡፡ ገፀባህርያትን ሳይሆን ህያው ሰዎችን፡፡ ገፀባህርያት አስቂኝ ስዕሎች ናቸው፡፡
ኧርነስት ሄሚንግዌይ
* የፃፍኩት ነገር ፅሁፍ ከመሰለ ደግሜ እፅፈዋለሁ፡፡ በእንግሊዝኛ የድርሰት አፃፃፍ ትምህርት ላይ የተማርነው ነገር የታሪኩን ድምፀትና ዜማ እንዲረብሽ አልፈቅድም፡፡
ኢልሞር ሊኦናርድ
* መፃፍ፡፡ እንደገና መፃፍ፡፡ ሁለቱም ከሌሉ  ደግሞ ማንበብ፡፡ ሌላ አቋራጭ መንገድ አላውቅም፡፡
ላሪ ኤል ኪንግ
* ለረዥም ልብወለድ ህጎች የሉም፡፡ ኖረውም አያውቁም፡፡ ሊኖሩም አይችሉም፡፡
ዶሪስ ሌሲንግ
* ዘይቤ ማለት ዘይቤዎችን በሙሉ መርሳት ነው፡፡
ጁሌስ ሬናርድ
* ፀሐፍት ሁለት ጊዜ ነው የሚኖሩት፡፡
ናታሊ ጎልድበርግ
* የመጨረሻው ዓረፍተነገር እስካልተፃፈ ድረስ የመጀመሪያው ዓረፍተነገር ሊፃፍ አይችልም፡፡
ጆይስ ካሮል አትስ
* ምክርን ተጠንቀቅ - ይሄኛውንም ጭምር፡፡
ካርል ሳንድበርግ
* ቀስቃሽ ሰዓት አልፈልግም፡፡ ሃሳቦቼ ከእንቅልፍ ይቀሰቅሱኛል፡፡
ሬይ ብራድበሪ
* ፅሁፍ የተባለ ነገር ሁሉ ልክፍት ይመስለኛል፡፡ ልትገቱት አትችሉም፡፡
ዊሊያም ካርሎስ ዊልያምስ
* ሁልጊዜ መፃፍ የምጀምረው በንፁህ ወረቀትና በቆሻሻ አዕምሮ ነው፡፡
ፓትሪክ ዴኒስ
* መፅሐፍ የሃሳብ መያዣ ብቻ ነው - ልክ እንደጠርሙስ፡፡ ዋናው ጉዳይ መፅሃፉ ውስጥ ያለው ቁም ነገር ነው፡፡
አንጄላ ካርተር

Published in ጥበብ

የኤችአይቪ ቫይረስ በወሊድ፣ በእርግዝና እንዲሁም በጡት ማጥባት ወቅት ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ እድሉ እጅግ ከፍተኛ ነው ተገቢው የህክምና ክትትል ካልተደረገም የመተላለፍ እድሉ ከ25-35% የጨመረ ነው፡፡
 Prevention of Mother-to-Child Transmission (PMTCT) of HIV/AIDS in Ethiopia: IntraHealth  International/Hareg Project End-of-Project Report: September 15, 2004 - December 31, 2007
ደሴ የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር PMTCT ኤችአይቪ ኤድስ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የሚሰራባቸው የተለያዩ የግል የህክምና ተቋማት ከሚገኙባቸው ከተሞች መካከል አንዷ ነች፡፡ እነዚህ ህክምና ተቋማት እናቶች ተመርምረው እራሳቸውን እንዲያውቁ ብሎም ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ እየሰሩ ያሉትን ስራ በጥቂቱ ልናስነብባችሁ ወደናል፡፡ በባቲ ጠቅላላ ሆስፒታል ያገኘናቸውን ሲስተር ዘነበች መኮንንን እናስቀድም፡፡ በሆስፒታሉ ያለው የነብሰጡር እናቶች ክትትል ምን ይመስላል? ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄ እንዲህ ብለውናል፡-
“ሆስፒታሉ ይህን አገልግሎት በመስጠት ቀደምት እንደመሆኑ መጠን ክትትላችን ጥሩ     ነው አንድ እናት ከኤችአይቪ ነፃ የሆነ ልጅ እንድትወልድ ነው የምንፈልገው ስለዚህ     ነብሰጡር እናቶች ሲመጡ ቅድሚያ የኢችአይቪ ምርመራ እንዲያደርጉ የምክር     አገልግሎት እናደርጋቸዋለን የምንሰጣቸው ከዛ በኋላ ፈቃደኛ ከሆኑ ምርመራ     ይደረግላቸዋል ፖዘቲቭ ከሆኑ መድሀኒቱን ለመጀመር እንዲያስችላቸው በሳምንቱ  ሲዲፎራቸውን እንለካለን ከዛም በየስድስት ወሩ ያለውን ለውጥ እናያለን ይህም     መድሀኒት ከመጀመራቸው በፊትና ከዛ በኋላ ያለውን ለውጥ እንድናውቅ ይረዳናል፡፡”     ጨምረውም ሆስፒታሉ ለደሴ ከተማ ነዋሪዎች ብቻም ሳይሆን ባቅራቢያው ለሚገኘው    ማለትም ከሰሜን ሸዋ፣ ከሚሴ፣ አጣዬ፣ ሸዋሮቢትና ኮምቦልቻ እንዲሁም በደሴ ዙሪያ     ከሚገኙት አሳይታ፣ ዱብቲ፣ ወልዲያ፣ መርሳ፣ ውጫሌና ሀይቅ ለሚመጡ ነዋሪዎችም     ጭምር ግልጋሎት እንደሚሰጥ ገልፀውልናል፡፡
የኤችአይቪ ቫይረስ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ በሚደረገው እንቅስቃሴ ቫይረሱ በደሟ እንዳለ ያወቀች እናት ለትዳር አጋሯ እንዲሁም ለሌሎች የቤተሰብ አባላት በግልፅ መንገሯ ቫይረሱ ወደ ሌሎች እንዳይዛመት በይበልጥም እናቲቱ የሚያስፈልጋትን እንክብካቤ እንድታገኝ በማድረግ እረገድ የሚኖረው አስተዋፅኦ ይህ ነው የሚባል አይደለም፡፡ ይሁንና ከቫይረሱ ጋር የምትኖር አንዲት እናት ወደ ሌሎች የህክምና ተቋማት ስትሄድ ሊደረግላት የሚገባውን እንክብካቤ በሚመለከትም የሚከተለውን ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተውናል፡-“ቫይረሱ በደሟ የተገኘባት እናት መጀመሪያ ለማን መንገር እንዳለባት ምክር     እንሰጣታለን ለባሏ፣ ለምትቀርበው ዘመድ ለእህትም ይሁን ለጓደኛ ማሳወቅ     እንዳለባት እንነግራታለን፤ እንዳንዶች ፈቃደኝ አይሆኑም፡፡
ከባላቸው እራሱ ይደብቃሉ፡፡ ቤቴ ይፈርሳል በሚል ለባላቸው እንኩዋን አይነግሩም፡፡ PMTCT     ኤችአይቪ ኤድስ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የሚያስችለው የህክምና አገልግሎት     አንዲት ነብሰጡር እናት ምንም እንኳን ቫይረሱ በደሟ ውስጥ ቢኖርም የህክምና     ክትትል በማድረግ ብቻ ከቫይረሱ ነፃ የሆነ ልጅ መውለድ እንድትችል የሚደረግበት አገልግሎት ነው፡፡
 ሲስተር ዘነበች እንደገለፁልን ሆስፒታላቸው ይህን አገልግሎት በተሟላ መልኩ በመስጠቱ ቀደም ሲል የነበረው የህፃናት ሞት እንዲሁም በቫይረሱ መያዝ በእጅጉ ቀንሷል፡፡ “አገልግሎቱን ከጀመርን በኋላ የተወለዱት ህፃናቶች ሁሉም ከቫይረሱ ነፃ ናቸው፡፡ በአሁኑ ሰአት ቫይረሱ በወሊድ ጊዜ ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ እድሉ ቀንሷል” ሲሉ የሚከለተውን ብለውናል፡-
“በአሁኑ ሰአት ምንም አያስፈራም ምክንያቱም ሰዉ ስለ ኤችአይቪ ያለው ግንዛቤ ጥሩ ነው፡፡ ቀደም ሲል ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ነሽ የሚል ውጤት ሲሰሙ በጣም ይደነግጣሉ፡፡ ለመቀበል ይከብዳቸዋል፡፡ አሁን ግን የትኛዋም እናት ስትመጣ የኤችአይቪ ምርመራ እናደርግላሻለን ስንላት በቀላሉ ትቀበለናለች ፖዘቲቭ ብትሆን እንኳን ጉጉቷ ልጇ ነፃ ሆኖ እንዲወለድላት ነው ስለዚህ የመተላለፍ እድሉም ቀንሷል የሰዉም ግንዛቤ ጥሩ ነው፡፡”  
             -----------///----------
በቀጣይ ያነጋገርናቸው በደሴ አዲስ ህይወት ሆስፒታል ያገኘናቸው ሲስተር አዝመራ ስዩምን ነው፤ ”...ሆስፒታላችን በወር ከመቶ ሀያ እስከ መቶ ሰላሳ ለሚሆኑ እናቶች የእርግዝና ክትትል አግልግሎት ይሰጣል፡፡ ባሳለፍነው ነሀሴ ከተመረመሩት እናቶች ውስጥም ሶስቱ ብቻ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ተገኝቷል ይህም ቁጥር ካለፈው ጋር ሲነፃፀር እጅግ ትንሽ ነው” በማለት ሲስተር አበባ ይገልፃሉ፡፡ የህክምና ገልግሎቱን እንዲሁም በታካሚዎቹ ዘንድ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ላነሳንላቸው ጥያቄዎች የሰጡንን ምላሽ እነሆ፡-
ጥ፡ አንዲት እናት ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ነሽ ስትባል እንዴት ነው የምትቀበለው እናንተስ እንዴት ነው የምታነጋግሯት?
መ፡ በዚህ ላይ ስልጠና ወስደናል ስለዚህ መጀመሪያ ከመመርመራችን በፊት የምክር አገልግሎት እንሰጣቸዋለን፡፡ በኋላ ላይ ውጤቱን ስንነግራቸው አዲስ  አይሆንባቸውም፡፡ ከዛም በኋላ መድሀኒቱን ማቋረጥ እንደሌለባቸው የእድሜ ልክ እንደሆነ በደንብ እንነግራቸዋለን ስለዚህ ብዙም ችግር አይኖርም፡፡
ጥ፡     ለክትትል የመጡ ሁሉ እናንተ ጋር ይወልዳሉ?
መ፡     ብዙዎቹ እኛ ጋር አይወልዱም፡፡ ምክንያቱም ከቦታ እርቀት፣ ከትራንስፖርት እጥረት     ወይም ከገንዘብ ችግር ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዶች ለአንድ ግዜ ክትትል ነው     የሚመጡት፡፡    የተወሰኑት ግን እኛ ጋር ይወልዳሉ፡፡
ጥ፡    ወደ ገጠሩ አካባቢ ያሉትን እናቶችስ በምን መልኩ ነው የምታስተምሯቸው?  
መ፡     ኤችአይቪ ይኑራትም አይኑራትም አንዲት እናት በህክምና ብትወልድ ነው የሚመረጠው፡፡ ቫይረሱ በደሟ ውስጥ ካለ ደግሞ እቤት መውለድ ለእሷም፣     ለልጇም፣ ለሚያዋልዷትም ሰዎች መልካም ስለማይሆን ልጇም ጤነኛ ሆኖ     እንዲወለድ ለእራሷም ጤንነት ወደ ጤና ተቋም ሄዳ እንድትወልድ እንገፋፋታለን፡፡
ጥ፡     ከወለዱስ በኋላ ለክትትል ይመጣሉ ታገኙዋቸዋላችሁ?
መ፡  በድጋሚ ለመውለድ ካልሆነ ብዙ ግዜ አይመጡም፡፡ ከሩቅ ስለሆነም የሚመጡት     መውለጃቸው ሲቀርብ ይታያሉ ከዛ በኋላ ባሉበት ቦታ ነው የሚወልዱት፡፡
ጥ፡     ልጆቹ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ይኑር አይኑር እንዴት ማወቅ ይቻላል?
መ፡     ክትትላቸውን በሚያደሩጉ ግዜ ያለውን ነገር እንነግራቸዋለን፡፡ ተመልሰው የማይመጡ     ከሆነ ግን ባሉበት እንዲከታተሉ እንነግራቸዋለን፡፡
መ፡     የትዳር ጉዋደኞች (ባሎች) አብረው ለምርመራ ይመጣሉ?
መ፡     ብዙዎቹ አይመጡም፡፡ እንዲት እናት ገና ለእርግዝና ክትትል ሰትመጣ ባለቤቷ     አብሯት እንዲመጣ እንጠይቃታለን፡፡ አብሯት ከመጣ የምክር አገልግሎት ሰጥተን     ምርመራውን እናደርጋለን፡፡ ያለውን ሁኔታ እናት እንዴት መውለድ እንዳለባት፣ ምን     አይነት እንክብካቤ እንደሚደረግላት፣ እናት ህይወት እየሰጠች ህይወት ማጣት     እንደደሌለባት በሰፊው እንነግራቸዋለን፡፡
                                          --------------///---------------
ዶክተር ምስጋናው ከፍተኛ ክሊኒክ በደሴ ከተማ አገልግሎቱን በመስጠት ይታወቃል ሲስተር ዛሀራ አሊን PMTCT ክፍል ውስጥ ነው ያገኘናት፡፡
    “...በቫይረሱ መያዝ ከቫይረሱ ነፃ የሆነ ልጅ መውለድ አያግድም በሚለው ሀሳብ     ትስማማለች ምክንያቱ ደግሞ በሆስፒታሉ ቁጥራቸው ሰላሳ አምስት የሚሆኑ ቫይረሱ     በደማቸው ያለ መድሀቱን የጀመሩ እናቶች ከቫይረሱ ነፃ የሆኑ እንዲወልዱ በማስቻሉ     ነው፡፡
እናቶቹ መድኒቱን መጀመራቸው ታካሚዎቹን እንደልብ ለማግኘት እንደሚረዳ ይገልፃሉ
“አንድ እናት ፖዘቲቭ ከሆነች መድሀኒቱን ወዲያው ነው የምንጀምርላቸው ስለዚህ ሁልጊዜም አናጣቸውም”
አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችሉ የህክምና መገልገያ እቃዎች አቅርቦትንም በተመለከተ ምንም ችግር እንዳልገጠማቸው ይናገራሉ
“አንዳንዴ ችግር ይፈጠራል፡፡ ነገርግን ይህነው የሚባል ችግር አልገጠመንም”
ሲስተር ዘሃራ አሊ በሆስፒታሉ የምትታወቅበት አንድ አገልግሎት አለ፡፡ ይኼውም ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ እናቶች ምርመራውን በጸጋ ተቀብለው ክትትሉን እንዲያደርጉ የሚያስችላቸውን አሰራር ለመዘርጋት ቅርበትን መፍጠር የሚለው ነው፡፡ ሲ/ር ዘሀራ እንደገለጸችው፡-
“...አንዲት እናት ከቫይረሱ ጋር እንደምትኖር ውጤቱ ሲያሳይ እኔ ሴትየዋን ማግባባት እና የተፈጠረው ነገር ምንም እንዳልሆነ እንዲያውም በጊዜው ተመርምራ እራስዋን     በማወቅዋ እድለኛ መሆንዋን በዚህ የህክምና ዘዴ እራስዋን በደንብ መከታተል እንደምትችል ...ወዘተ እነግራታለሁ፡፡
 ከዚያም በስልክ በፈለጉት ጊዜ ሊያገኙኝ እንደሚችሉ ቃል ስለምገባላቸው በምሽት ሁሉ ይደውሉልኛል፡፡ በዚህ መንገድ ቅርበትን     ስለምፈጥርላቸው በጥሩ ስሜት ወደእኔጋ ይመጣሉ፡፡ ሕክምናቸውም ሳያቋርጡ እንዲቀጥሉ ያደርጋቸዋል፡፡”

Published in ላንተና ላንቺ
Saturday, 25 October 2014 10:39

በነፍሴ ውስጥ እኔ


        ዕድሜዬ በአርባዎቹ አጋማሽ ላይ ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም የፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ አባል ነበርሁ፡፡ ኦጋዴን ኖሬአለሁ፡፡ ሰራዊቱ ውስጥ ምድብ ሥራዬ የነበረው ሾፌርነት ነው፡፡ ሰራዊቱን በየግንባሩ አጓጉዛለሁ፡፡ አንድ ቀን በጉዞ ላይ እያለን፣ ትከሻዬ ላይ ከባድ አረር መታኝና በረጅም ጊዜ ህክምና ተረድቼ በፈጣሪ ዕርዳታ ተረፍሁ፡፡ በዚህም የተነሳ ከሰራዊቱ ጡረታ ተገለልሁ፡፡
ይኸውና ዛሬ በአንድ ሲቪል የመንግስት መሥሪያ ቤት በሾፌርነት ሙያዬ እያገለገልሁ ነው፡፡ ለመስክ ሥራ ከቀያሾችና ከሌሎች የሙያ ሰዎች ጋር በየገጠሩ እዘዋወራለሁ፡፡ በዚህ ሥራ የተነሳ የሀገሬን መልክዓ ምድር በአብዛኛው ተዘዋውሬ አይቻለሁ ብል አልሳሳትም፡፡ በትንሽ ነገር ብው ብዬ የምገነፍል ነኝ፡፡ ወዲያው ደግሞ ከእሳት ላይ እንደ ወረደ የሻይ ጀበና እሆናለሁ፡፡ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ እሳትና ውሃ ያደርገኛል፡፡ ክፋት የለኝም፡፡ ቂም የሚባል ነገር አላውቅም፡፡ ሚስት አግብቼ ልጅ ወልጃለሁ፡፡ እኔ ማለት ይህ ነኝ፡፡
አንድ ቀን ከመሥሪያ ቤቱ አስተዳደር ቢሮ ተጠራሁ፡፡ የኃላፊውን ቢሮ ከፍቼ ስገባ፣ እንደኔው ተጠርተው የመጡ ሁለት የማውቃቸው ሰዎች ተቀምጠው አየሁ፡፡ አንዱ ቀደም ሲል በሰራዊቱ ውስጥ ያገለገለ የመቶ አለቃ ነበር፡፡ ሌላውን ግን ከዚህ በፊት ብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት፣ አሁን ግን በመ/ቤቱ አንድ የሥራ ክፍል ውስጥ በቴክኒሻንነት ይሰራል፡፡
“ቁጭ በል አስታጥቄ!” አለኝ፣ የአስተዳደር ኃላፊው፡፡
“እሺ!” ብዬ ተቀመጥሁ፡፡
ኃላፊው ሶስታችንን በየተራ ትክ ብሎ ተመለከተንና፤ የተጠራነው ለምን ምክንያት እንደሆነ ሊያስረዳን መናገር ጀመረ፡፡
“ይኸውላችሁ! … እናንተም በመገናኛ ብዙኃን እንደምትሰሙት ሁሉ ሀገሪቷ ትልቅ ውጥረት ላይ ትገኛለች፡፡ መንግስት ውጊያ ላይ ነው…” ብሎ ንግግሩን ጀመረ፡፡ መግለጫ ይሁን መመሪያ በውል ያልገባኝን ነገር በሰፊው አወራልንና፤
“… እናንተ ሦስታችሁም ቀደም ብሎ በሰራዊቱ ውስጥ ያገለገላችሁ ስለሆነና በሙያችሁም ልምድ ያላችሁ ስለሆናችሁ፣ ሀገራችሁ ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ ጠርታችኋለች” ብሎ፣ ንግግሩን ገታ አደረገና እያፈራረቀ ይመለከተን ገባ፡፡ እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን እንተያያለን፡፡ “እ! እህ!” ብሎ ጉሮሮውን ጠራረገና፣ “እናንተን የመሳሰሉ የውትድርና ልምድ ያላቸው በሀገሪቱ ያሉ ሁሉ እንዲጠሩ ከመንግሥት ጥብቅ መመሪያ ስለደረሰን፣ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ተዘጋጅታችሁ ትዘምታላችሁ” የሚል ቀጭን ትዕዛዝ ሰጠን፡፡
“መዝመቱንስ እንዝመት፡፡ ለሀገር ነው፡፡ ግን አንድ ሳምንት አላጠረም ወይ?”
ስል ጠየቅሁ፡፡
“መመሪያ ነው!” አለ፣ አስተዳዳሪው፡፡
“እኔ ያመኛል” ሲል መቶ አለቃ የነበረው ሰው ተናገረ፡፡
“እዚያው ሄደህ ይረጋገጥልሃል፡፡ ይህ የእኔ ሥራ አይደለም፡፡ ይኸው ነው!...”
ብሎ አሰናበተን፡፡
ሁሉም ነገር በአስቸኳይ ተጠናቅቆ ወደ ምድቤ ሄድኩና ከሰራዊቱ ጋር ተቀላቀልሁ፡፡ ከፍተኛ ፍልሚያ ውስጥ ሰራዊቱን ወደተፈለገው የውጊያ ግንባር ሳጓጉዝ ከረምኩ፡፡ ሙሉ ወታደራዊ ልብስ ለብሻለሁ፡፡ አንድ አውቶማቲክ ክላሽ ጠብመንጃ ተሰጥቶኝ ታጥቄአለሁ፡፡ ውትድርናውን በመሃሉ ለረጅም ጊዜ ያቋረጥሁት ቢሆንም፣ ከእሳቱ አረንቋ ስገባ ግን የለመድሁት ወዲያው ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ለስምንት ወራት ያህል እንደ ሰራሁ ሽንፈት መጣና ሰራዊቱ በየአቅጣጫው ተበታተነ፡፡ የበላይ የለ የበታች፣ ሁሉም በቡድን በቡድን እየሆነ ባሻው መንገድ የሽሽት መልስ ሆነ፡፡ እኔም ከአንደኛው ቡድን ውስጥ ተቀላቅዬ ክላሼን እንደያዝሁ የኋልዮሽ ጉዞዬን ጀመርሁ፡፡
አብዛኞቻችን ደረቅ ራሽን ይዘናል፡፡ የተቻኮለና በድንገተኛ ሁኔታው የተደናገጠው ባዶ እጁን መንገዱን ጀምሯል፡፡ ከጀርባችን የሚያሳድዱን ስላሉ ከዚያ ለማምለጥ ሩጫ ነው፡፡ ቆንጥሩ እየቆነጠረን፣ እንቅፋቱ እያነቆረን፣ ሙቀቱና ፀሐዩ እየጠበሰን፣ ውሃ ጥሙ እያነደደን እንጓዘው ተያያዝን፡፡ ብዙ ርቀት ስለ ተጓዝን ወደ አመሻሹ ላይ ደከመንና አንድ ጎድጓዳ መሬት ስንደርስ በየጥሻው ውስጥ ተበታትነን አረፍን፡፡ በየቦታው ወዳደቅን ማለቱ ነው ሁኔታችንን ሊገልጥ የሚችል፡፡ ስንት ሰው በየቦታው ወድቆ እንደቀረ ምንም ልገምት አልችልም፡፡ አብረን ጉዞ ከጀመርነው ሰዎች መካከል ጥቂቱ እየተመታ ሲወድቅ፣ ሌላው ደግሞ ከዓቅሙ በላይ ሆኖበት በየቦታው እየወደቀ ሲለየን ቡድናችን ሳሳ ይላል፡፡ ጥቂት እንደ ተጓዝን ደግሞ ሌሎች ከዚህም ከዚያም እየመጡ ይቀላቀሉናል፡፡
“ከየት ነው የዘመትከው?” ብሎ ከጎኔ የተጋደመው ወታደር ጠየቀኝ፡፡
“ከአዲስ አበባ” አልሁ፡፡
“እኔ ከባሌ ነው የመጣሁ፡፡ ስሜ ቶልቻ ይባላል”
“እኔ ደግሞ አስታጥቄ እባላለሁ”
“የትኛው ምድብ ነበርክ?” በማለት ጠየቀኝ፡፡ ነገርኩት፡፡ እሱም የነበረበትን ነገረኝ፡፡ በውጊያው ግንባር ጎን ለጎን ነበርን፡፡ ዛሬም በሽሽት ዓለም ውስጥ ሆነን ጨለማ ውስጥ ጎን ለጎን ተኝተናል፡፡
ጥቂት ቀርታኝ የነበረችውን ውሃ ተካፈልንና አለቀች፡፡ ጊዜው እየመሸ ነው፡፡ ከፊሉ ጉዞ እንጀምር ሲል፣ እኔና ጥቂቶች ግን እዚያው ማደሩን መረጥን፡፡ በሃሳባችን ያልተስማማው ጉዞ ጀመረ፡፡ እኔና ጥቂቶች ያለንበት ቦታ ከጥቃት ሊከልለን ይችላል ብለን ስላመንን ከቆንጥር መካከል በመግባት ራሳችንን ሰውረን ቦታችንን አመቻቸን፡፡ ድቅድቅ ጨለማ ዋጠን፡፡ ኮሽ የሚል ነገር የለም፡፡ ሁሉም ነገር ድፍን ብሎ ፀጥ ረጭ ብሏል፡፡ የአውሬ ድምፅ እንኳ አይሰማንም፡፡ ለነገሩማ የጦርነት ቀጠና ውስጥ አራዊት እንዴት ሊኖሩ ይችላሉ? እነሱም ይሸሻሉ፡፡ እኛም እንሸሻለን፡፡ የሽሽት ዓለም!
እኔ አይኔ ፈጥጧል፡፡ ከመካከላችንም እንቅልፍ የጣለው ሰው ነበር ለማለት አልደፍርም፡፡ ወይ እንቅልፍ! … “እዬዬ ሲዳላ ነው!” አይደል የሚባል!? በመካከሉ ድም! ድም! የሚል የሰዎች ኮቴ ሰማን፡፡ መሳሪያዬን ጠበቅ አድርጌ ያዝኩና ጆሮዬን ወደ ላይ አቆምሁ፡፡ እኛ ተሸሽገንበት ካለው ጉድባ በላይ የሰዎቹ ኮቴ እየቀረበን መጣ፡፡ ጣቴን ከምላጩ ላይ አድርጌ ተዘጋጀሁ፡፡ የመጨረሻችን መጨረሻ እንደቀረበ አመንሁ፡፡ ምራቄን ዋጥ አደረግሁ፡፡ ከጎኔ ያለው ቶልቻም ልክ እንደኔው ተዘጋጅቷል፡፡ ከመካከላችን አንድም ሰው ድምፅ አያሰማም፡፡ ሁላችንም አድፍጠናል ማለት ነው፡፡ ሁለት የማይታረቅ አመለካከት ያለን የአንድ ሀገር ልጆች የፖለቲካ ቁማር በሚቆምሩ የበላዮቻችን ትዕዛዝ ስንበላላ ይኸው ስንት ዘመን አለፈ፡፡ አሁንም በዚህ ድቅድቅ ጨለማ እንደ ክፉ አውሬ ልንበላቸው፣ እነሱም ሊበሉን እየተቃረብን ነው፡፡ እነሱ እየተሸሸጉ ስናባርራቸው የነበር ዛሬ እኛ እየተደበቅን፣ እነሱ ደግሞ በፊናቸው እያባረሩን ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ የድብብቆሽ ጨዋታ መሰለኝ፡፡ የመድረክ ተውኔትም እየመሰለ ይታየኛል፡፡
የአንዲት ጥይት ድምፅ ተሰማ፡፡ ወዲያው ሁለት … ሶስት… ድብልቅልቁ ወጣ፡፡ የተኩሱ ድምፅ ከወዴት እንደሆነ መለየት እንኳ ተሳነን፡፡ እኔም ሰው ያየሁ በመሰለኝ አቅጣጫ ሁሉ እተኩሳለሁ፡፡ ቦታ እየቀያየርኩ መሳሪያዬን አንጣጣሁ፡፡ ከላዬ ላይ አንድ ግዙፍ ነገር ዘፍ አለብኝ፡፡ ቅርፁ የሰው ነው፡፡ እግሬንም እጄንም አስተባብሬ የወደቀብኝን ገፍትሬ ከላዬ አስወገድሁ፡፡ ዝርግፍ ብሎ ሲወድቅ፣ “ወይኔ ቶልቻ… ኢጆሌ ባሌ!” ብሎ ፀጥ አለ፡፡ አመሻሹ ላይ ስናወራ የነበረው የባሌ ልጅ ነበር፡፡ ጥቂት እንደ ማዘን ብዬ ወደራሴ ሁኔታ ተመለስሁ፡፡ ማን ማንን መትቶ እንደሚጥል አይታወቅም፡፡ የምተኩሰው ጥይት ሰው ይምታ ወይ ደግሞ ቅጠልና ድንጋዩን፣ አሁንም የማውቀው ነገር የለም፡፡ ጥይቴም እንዳያልቅ በቁጠባ ነው የምተኩሰው፡፡ ስንፏቀቅ ብዙ ሄጃለሁ፡፡ በመካከሉ የጥይቱ ድምፅ እየሳሳ እየሳሳ እየሳሳ መጣና አካባቢው ፀጥ አለ፡፡ ጥቂት ቆይቶም የንጋት ብርሃን ይታየኝ ጀመረ፡፡ አጠገቤ ሰው የለም፡፡ ዙሪያ ገባውን ማየት ጀመርሁ፡፡ በርቀት በደረታቸው ተኝተው ያሸመቁ ሰዎች ስለታዩኝ መሳሪያዬን ወደ እነርሱ አነጣጠርሁ፡፡ የለበስኩት ልብስ በቆንጥሩና በድንጋዬ ተዘነጣጥሎ በግማሽ ተራቁቻለሁ፡፡ እዚህም እዚያም የወደቀ አስከሬን ይታየኛል፡፡ ሰውነቴን ደባበስሁ፡፡ ክንዶቼና ጉልበቴ ላይ ቆስዬ ደም ይፈስሰኛል፡፡ ከተዘነጣጠለው ልብሴ ላይ እየቀደድሁ ቁስሌን አሰርሁ፡፡
“አስታጥቄ!” ሲል አንድ ሰው ጠራኝ፡፡
ከእነዚያ አሸምቀው ከነበሩ ወታደሮች መካከል ነበር ድምፁ የመጣው፡፡ በደንብ ስላልነጋ በርቀት ልለየው አልቻልኩም፡፡ እሱ እንዴት ሊለየኝ እንደቻለ እኔ እንጃ!
“ማነህ አንተ? ራስህን ግለፅ፡፡ ከወገን ነህ?” አልሁ፣ በጥርጣሬ መንፈስ፡፡
“እሱባለው ነኝ” ብሎ፣ ልዩ መጠሪያችን የነበረውን ልዩ የኮድ ስም ተናገረ፡፡ ሌላም አከለበት፡፡ ሁላችንም ካደፈጥንበት ተነሳንና ቅልቅል ሆነ፡፡ የሞቱትን ሰዎች ብንመለከት እንደ እኛው ይሸሹ የነበሩ ወገኖቻችን ናቸው፡፡ ከመጡብን ሰዎች መካከልም የተረፉ ነበሩና በደንብ ነግቶ ከተያየን በኋላ መጥፎ ስሜት ተሰማኝ፡፡ የተላለቅነው እርስ በርስ ነበር፡፡ እጅግ በጣም አዘንሁ፡፡ በወቅቱ ሁላችንም ጭንቅ ላይ ስለነበርን፣ ምንም ማመዛዘን አልቻልንም፡፡ ሞት ከዚህ ከዚያም በየመልኩ ሆነ፡፡
ምክር ያዝንና አብዛኛው የተስማማንበትን የጉዞ ዕቅድ ነደፍን፡፡ ሌሊት ወደ እኛ ከመጡት ወታደሮች መካከል አንደኛው፣ “መሳሪያችንን ጥለን እንደ ማንኛውም ሲቪል ሰው ብንጓዝ ጥሩ ይመስለኛል” የሚል ሃሳብ በማንሳቱ፣ በዚሁ ተስማምተን ከጥቂት በቀር ብዘዎቻችን ክላሾቻችን በየቆንጥሩ ውስጥ ወረወርን፡፡ ወገቤ ላይ አስሬ የያዝኳትን ትንሽ የጨርቅ ከረጢት ከፍቼ፣ አንድ የጨርቅ ሱሪና ሸሚዝ አውጥቼ ለበስሁ፡፡ ጫማዬን አውልቄ የከተማ ጫማ አጠለቅሁ፡፡ ሁላችንም ራሳችንን ለመለዋወጥ ሞከርን፡፡ ሁለት ሁለት፣ ሶስት ሶስት እየሆንን ዕድላችን በፈቀደችልን በተለያየ አቅጣጫ ጉዞ ወደፊት ሆነ፡፡ ከእኔ ጋር የሚጓዙት ወታደሮች ሶስት ሲሆኑ እኔን ጨምሮ አራት ነበርን ማለት ነው፡፡ ይዤው የነበረ ደረቅ ኮቾሮ እያለቀ ነው፡፡ ውሃም የለንም፡፡ ከንፈሮቻችን ደርቀዋል፡፡ የክንዶቼና የጉልበቴ ቁስል ይጠዘጥዘኛል፡፡ ቀን በየጥሻው እየተሽሎከሎክን፣ ለዓይን ያዝ ሲያሰርግ ደግሞ ወደ ገላጣው ብቅ እንላለን፡፡ ረሃቡና ውሃ ጥሙ ፈታን እንጂ ብዙ ርቀት ሄድን፡፡ በጉዟችን ላይ አልፎ አልፎ ሰዎች ሲገጥሙን ፈጠን ብለን ሰላምታ እንሰጥና ራመድ ራመድ እንላለን፡፡
አንድ ቤተክርስቲያን በርቀት ስላየን ወደ እዚያው በእርምጃ ገሰገስን፡፡ ስለ ሰጋን ወደ ኋላ እየተገላመጥን ወደ ውስጥ ዘለቅን፡፡ ቦታው እግዚአብሔርን ማምለኪያ ቅዱስ ስፍራ ነውና ክፉ ነገር እንደማይነካን ተማምነናል፡፡ በዚያውም ምልጃ እናቀርባለን፡፡ አንዲት መነኩሲት ስላየን ወደ እሳቸው አመራን፡፡ ሁኔታችንን በመጠኑ ስንነግራቸው፣ “አፈር ይብላኝ! ወይኔ ወገኖቼ!...” ብለው እንድንከተላቸው ነገሩን፡፡ የባቄላ ንፍሮ ሰጥተውን በችኮላ በልተን በላዩ በማውራ (ከቅል የተሰራ ክብ መጠጫ) ውሃ እስኪበቃን ቸለስንበት፡፡ አንደበታችን ተፈታልን፡፡ ዓይኖቻችን ተገለጡልን፡፡ ምንም እንደማያሰጋን መነኩሲቷ ነግረውን ለማደሪያችን አንዲት ደሳሳ ጎጆ አሳዩን፡፡ ወዲያው፣ “መጣሁ! ቶሎ እመለሳለሁ…” ብለው ሄዱ፡፤ ጆሮዬ ቆመ፡፡ የዘመኑ ነገር አይታወቅምና ሥጋት ነገር አደረብኝ፡፡ መነኩሲቷ ተመልሰው መጡና፡-
“ይኸውላችሁ… ይኼ ልጅ ከትናንት ወዲያ እየተጎተተ መጥቶ ከቤተክርስቲያኑ ደጃፍ ሲደርስ ወደቀ፡፡ ምዕመናን ተሯሩጠው ቢሄዱ እጅግ ጠውልጎና ተንገላትቶ ደክሞ አገኙት…” ብለው፣ በእጃቸው የያዙትን የጧፍ መብራት ወደ አናታቸው ከፍ አደረጉና፡-
“… አፈር ይብላኝ፡፡ ምንም ሳንረዳው እዚያው ከወደቀበት ነፍሱ ወጣች፡፡ ትናንት ቀበርነው፡፡ ይኸውላችሁ ከኪሱ ያገኘነው ፎቶ…” ብለው እንድናየው አቀበሉን፡፡ ፎቶግራፉን ሳይ ክው አልሁ፡፡ ግን ወዲያው ራሴን ተቆጣጠርኩ፡፡ የመስሪያ ቤታችን አስተዳዳሪ ለዘመቻ መጠራታችንን የነገረን ጊዜ ቢሮው ውስጥ ከነበርነው ሶስት ሰዎች መካከል ቀደም ሲል ብሄራዊ ውትድርና አገልግሎ የነበረው የመ/ቤቱ ባልደረባዬ ነው፡፡ እጅግ አዘንሁ፡፡
መሬቱ በደንብ ሳይነጋ ካደርንበት ደብር ተነስተን ጥቂት ራቅ እንዳልን ከወደ ጀርባችን የጥይት እሩምታ ይወርድብን ጀመር፡፡ ወደ ፊቴ ዘልዬ በደረቴ ከመሬት ላይ ተሰፋሁ፡፡ እንደ እባብ እየተሳብሁ ከአንዲት የለመለመች ቁጥቋጦ ውስጥ ገብቼ ተወሸቅሁ፡፡ በርቀት የሰዎች ድምፅ ይሰማኛል፡፡ አሁን ሰማዩ ወለል ስላለ በቅጠሎች ውስጥ አሾልቄ አካባቢውን ተመለከትሁ፡፡ ማንም የለም፡፡ በዝግታ ከቁጥቋጦው ውስጥ ወጣሁና ግራ ቀኙን ከመረመርሁ በኋላ ቁልቁል ወደ ተዳፋቱ ሮጥሁ፡፡ አብረውኝ የነበሩት የጉዞ ጓደኞቼ ይሙቱ ወይ ደግሞ በተለያየ አቅጣጫ ነፍሴ አውጪኝ ብለው እንደሁ የማውቀው ምንም ነገር የለም፡፡ ከያዝኩት የባቄላ ንፍሮ ቃም ቃም አደረግሁና ውሃ ተጎነጨሁ፡፡ ሩጫዬን ቀጥያለሁ፡፡ የጫማዬ ሶል ተገንጥሎ በመውደቁ የውስጥ እግሬ ደም አዝሎ ነፍርቋል፡፡ አማራጭ የለምና ጥርሴን ነክሼ እረግጥበታለሁ፡፡ ዕውር ድንብሬን ነፍሴ በመራችኝ አቅጣጫ ስጓዝ ድንገት መኪና መንገድ ላይ ወጣሁ፡፡
መንገዱ ወዴት ነው የሚወስድ? የት ነው ያለሁት? የሀገሪቱን አብዛኛውን ክፍል በሥራ ምክንያት የማውቀው ቢሆንም፣ እዚህ ቦታ ግን መጥቼ አላውቅም፡፡ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ግራ ተጋባሁ፡፡ በመካከሉ የመኪና ድምፅ ስለሰማሁ ወደ ጫካ ገባሁና በርቀት መመልከት ጀመርሁ፡፡ መኪናው እየቀረበ ሲመጣ ጭነት የጫነ አይሱዙ ፒካፕ መኪና መሆኑን ለየሁ፡፡ ከጫካው ወጥቼ መኪናዋ ስትቀርበኝ እጄን ለእርዳታ አወናጨፍሁ፡፡ ከአሁን በኋላ ቆሜ መራመድ ስለማልችል የሚመጣውን ሁሉ በፀጋ ለመቀበል ተዘጋጀሁ፡፡
“ወንድሜ … ምን ልርዳህ?” አለ ሰውየው፣ አጠገቤ ሲደርስ መኪናዋን አቁሞ፡፡
“ዘመድ ጥየቃ መጥቼ ሳለሁ ሀገር በመረበሹ ከዘመዶቼ ተለይቼ ስባዝን ከዚህ አውራ መንገድ ላይ ደረስሁ”
“ዘመዶችህ የት ናቸው?”
“ስንሸሽ ጫካ ውስጥ ተጠፋፋን”
“እሺ አሁን ምን ልርዳህ?” አለ ሾፌሩ፡፡
“ከመንገዱ ብዛት እግሬ አላስረግጥ ስላለኝ ብትረዳኝ ብዬ ነው”
“ወዴት ነው መሄድ የምትፈልገው? እኔ አዲስ አበባ ነው የምሄድ”
“እኔም እዚያው ነኝ” አልሁ፣ ፈጠን ብዬ፡፡
“ግማሽ መንገድ እረዳሃለሁ፡፡ በየቦታው ፍተሻ ስላለ አብረን መዝለቅ አንችልም
ግባ!” አለኝና ከጋቢናው ገብቼ ከጎኑ ተቀመጥሁ፡፡
በግምት ለሁለት ሰዓት ያህል እንደተጓዝን ለተፈጥሮ ጉዳይ መኪናዋን አቆመና ወደ ጫካ ጎራ አለ፡፡ በዚህች ቅጽበት አንድ ነገር በሃሳቤ ውልብ አለብኝ፡፡ ከመኪናው ወጣሁና ሽንት የሚሸና በመምሰል እስኪመለስ ጠበቅሁት፡፡ ተመልሶ አጠገቤ ሲደርስ ከጆሮው ሥር ጠቅ እያደረግሁት፡፡ እራሱን እንዲስት እንጂ ከበድ ያለ አደጋ እንዳይደርስበት የመታሁት በጥንቃቄ ነው፡፡ ተዝለፍልፎ ሊወድቅ ሲል መሬቱ እንዳይጎዳው ደጋገፍኩትና በጀርባው አጋደምኩት፡፡ ፈጠን ብዬ ኪሱ ገባሁና የመኪናዋን ቁልፍ አወጣሁ፡፡ መታወቂያው ላይ ያለውን ፎቶውን ገንጥዬ ደብተሩን ወሰድሁ፡፡ ጥቂት ብሮች ብቻ አስቀርቼለት የቀረውን ያዝሁ፡፡ ጫማውን አውልቄ አደረግሁ፡፡ ከዚያም መኪናዋን አስነስቼ በረርሁ፡፡
የሰው ልጅ ምን ያህል ራስ ወዳድ እንደሆነ የገባኝ አሁን ነው፡፡ ራሴን ጠላሁት፡፡ “ወርቅ ላበደረ ጠጠር” ሆነ ሥራዬ፡፡ ያም ሆነ ይህ እሱን በእኔ ቦታ ትቼው፣ እኔ የእሱን መኪና ቀምቼ እየበረርሁ ነው፡፡ ሁለት የቆንጥር እሾህ ቆርጬ በቀጭኑ በኩል ቁመቱን በጣም አሳጠርኩና እንዳይታይ አድርጌ ፎቶግራፌን ከደብተሩ ጋር በጥንቃቄ ሰፋሁት፡፡ በዚህ ግርግር ወቅት ብዙ ትኩረት የሚያደርግ ሰው እንደሌለ ገምቻለሁ፡፡ አንዲት አነስተኛ ከተማ እንደ ደረስሁ ሱሪና ሸሚዝ ገዝቼ ለበስሁ፡፡ መታወቂያዬን ለማየት በእጄ እንድሰጠው የጠየቀኝ ሰው ስላልነበር በርቀት እያሳየሁ፣ ምንም እንከን ሳይገጥመኝ በሁለተኛው ቀን አዲስ አበባ መግቢያ ላይ ካለው የፍተሻ ኬላ አካባቢ ደረስሁ፡፡ መኪናዋን ሥራሽ ያውጣሽ ብያት ከመንገድ ገባ አድርጌ አቆምኳትና መንገድ አሳብሬ በእግሬ ወደ ከተማዋ ገባሁ፡፡
አዲስ አበባ ውስጥ ጥቂት ሰዎች ውር ውር ቢሉባትም በአብዛኛው ፀጥ ብላለች፡፡ በየመንገዱ እያስቆሙ ይፈትሻሉ፡፡ ዋና ዋና ጎዳናውን ትቼ መንደር ለመንደር እየሄድሁ፣ አመሻሽ ላይ ሰፈሬ ደረስሁ፡፡ አካባቢው ረጭ ብሏል፡፡ በሬን አንኳኳሁ፡፡ ቆየት ብሎ በሩ ተከፈተ፡፡ ትልቅ እህቴ ነበረች፡፡ ስታየኝ በእልልታ አካባቢውን ልታቀልጠው ስትል አፏን በመዳፌ ከደንኩት፡፡ በሩን ዘጋሁና አረጋጋኋት፡፡ ልጄ ከጓዳ እየሮጠች መጣችና ተጠመጠመችብኝ፡፡
“ባለቤቴ የት ሄዳ ነው?” ብዬ ጠየቅሁ፡፡
“ተባራሪ ጥይት ገደላት” አለችኝ እህቴ፣ ዓይኖቿ እንባ አዝለው፡፡
እኔ ከዚያ መዓት በተዓምር ተርፌ ብመጣ ባለቤቴ ሞታ በመድረሴ ምነው እዚያው ሞቼ በቀረሁ አሰኘኝ፡፡ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ይህ ሁሉ ሥቃይ የደረሰብኝ ምን ያልከፈልከሉት ዕዳ ቢኖር ነው? ሀገሬንስ ምን በድያታለሁ? ሁለት ጭንቅላቶች በአመለካከት ልዩነት ችግር ሲፈጥሩ እኔ ገፈት ቀማሽ መሆን አለብኝ እንዴ? ለማንኛውም ግን እኔ …
እኔ እኮ አሁን የለሁም፡ ከዘመቻ መልስ ጥቂት ከራርሜ ሞትሁ፡፡ እሰራበት ከነበረው መሥሪያ ቤት ላለ ወዳጄ በአፀደ ሥጋ በነበርሁ ጊዜ የነገርኩትን፣ ይኸው ዛሬ ነፍሴ ደግማ በጆሮው እየነገረችው ነው፡፡ እሷ እየነገረችው እሱ ፃፈላችሁ፡፡ ነፍሴም አውልቃ የጣለችውን በድን ቁልቁል እያየች፣ ስለ እኔ ማውራቱን አልተወችም፡፡

Published in ልብ-ወለድ

ሕፅንም ጭን እንጂ ባዶ ቦታ አይደለም!
ባለፈው ሳምንት በወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ጥበብ አምድ ላይ “ምድጃ ዳር ፥ ለገላ ነው ለትዝታ?” በሚል ርዕስ አብደላ ዕዝራ በተባሉ ጸሐፊ የቀረበውን ጽሑፍ በጥንቃቄ አንብቤያለሁ፡፡ በጥንቃቄ ስል የአብደላን ጽሑፎች በፍቅር ስለማነብባቸው “ዛሬስ ምን አዲስ ነገር ይዞልን መጣ ይሆን?” ከሚል ጉጉት የመነጨ ነው፡፡
አብደላ የጽሑፉ መስፈንጠሪያ ያደረገው በኤፍሬም ሥዩም “ተዋነይ ብሎይ የግዕዝ ቅኔያት ፍልስፍና” መጽሐፍ ውስጥ ያለውንና 65ኛውን ጉባኤ ቃና ነው፡፡ ጉባኤ ቃናው የሊቁ ተክሌ ዘዋሸራ መሆኑን በትውፊትም በመጻሕፍትም የተገኙ መረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡ ለጽሑፌ መነሻ የሆነኝ ግን የጉባኤ ቃናው የባለቤትነት ጥያቄ አይደለም፤ ይልቁንም አብደላ ለጉባኤ ቃናው የሰጠው ፍካሬያዊ ትርጉም ነው የጽሑፌ ዋና ዓላማ፡፡
ሊቁ ተክሌ ይህንን ጉባኤ ቃና የዘረፉት የድንግል ማርያም መታሰቢያ ዕለት ነው፤ ድንግል ማርያም ጌታን (ኢየሱስ ክርስቶስን) ስትወልድ ገና 15 ዓመት እንኳ በወጉ ያልሞላት ልጅ ነበረች፡፡ ይህን ሲያደንቅ ነው ሊቁ ተክሌ፡-
“ድንግል ወለት ትመስለነ ዕቤርተ፤
አኮኑ ትውዕል እንዘ ተሐቅፍ እሳተ”
የሚል ቅኔ የዘረፉት፡፡ ትርጉሙ “ማርያም ድንግል ገና ህፃን ሳለች እመበለት ትመስላለች፡፡ ምክንያቱም እሳት ታቅፋ ትውላለችና!” ማለት ነው፡፡ ይህ ሰሙ ነው፤ ወርቁ ግን ድንግል ማርያም ሰማይና ምድር መሸከም ያልቻሉትን የእግዚአብሔርን ልጅ ወልድን፤ አባ ሕርያቆስ የተባለው ሊቀ ጳጳስ “አብ እሳት ነው፣ ወልድ እሳት ነው፤ መንፈስ ቅዱስም እሳት ነው” ብሎ ባህርየ መለኮቱን ግርማ ርዕየቱን ያደነቀውን እሳት ለመታቀፍ የበቃችበትን ተአምራዊ ኃይል ለማድነቅ ነው እንጂ አብደላ እንደተገነዘበው በምንም መንገድ ከፍትወት ጋር የተያያዘ ምስጢር የለውም፡፡
አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ላይ ይህንኑ ጉዳይ በአንክሮ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፤ “… ኦ ድንግል ሶበኀደረ ውስተ ከርስኪ እሳተ መለኮት፤ ገጹ እሳት፣ ልብሱ እሳት፣ ክዳኑ እሳት እፎኒ ኢያው ዐየኪ?” ነጠላ ትርጉሙ “ድንግል ሆይ! ፊቱ እሳት፣ ልብሱ እሳት፣ መሸፈኛው እሳት የሆነ የመለኮት እሳት በማህጸንሽ ባደረ ጊዜ እንዴት አላቃጠለሽም?!” ማለት ነው፡፡
ይህ ማለት ታዲያ የመለኮትን ኃይል፣ ሙሴና ኤልያስ እንኳ ደፍረው ከፊቴ ለመቆም ያልቻሉትን እንዴት አንቺ በማህጸንሽ ለዘጠኝ ወራት ተሸከምሽው? እንዴትስ እሳቱን ታቅፈሽ እንደ ህፃን አጫወትሽው?” እያለ ረቂቁን ባህርየ መለኮት አጠየቀ እንጂ አብደላ እንዳሰበው ከርካሹ ዓለማዊ ፍትወት ጋር የሚያቆራኘው አንድም ምክንያት የለም፡፡
“ከጳጳሱ ቄሱ” እንዲሉ ካልሆነ በቀር መቸም አብደላ የአለቃ ተክሌን ቅኔ ከተክሌ በላይ ሊገነዘበው አይችልም፤  ያ ባይሆን ኖሮ “ከትዳር ቀለበት ሾልከው፣ ሌላውንም በወሲብ መቅመስ ሳይደፍሩ የቀሩት፤ በስተርጅና ለመቆጨትም በትዝታም ለመፍለቅለቅ እንደ ስንቅ ነው፤ ዕድሜ መች መክሰም ብቻ ሆነ? ዘዋሸራ ተክሌ ከነገረ መለኮት ሱባኤ ስሜታቸውን ጎትተው ግራ ቀኝ ገላምጠው ድንግል ልጃገረድ ያቀፈችው እሳት እንዴት አባበላቸው? እንዴት ለመቀኘት እርሾ ሆናቸው? ቢያሰኝም በሄዋን ውበትና እጣፈንታ መመሰጥ ለባለ ቅኔ አንድ የህይወት ሰበዝ ነው፡፡ … ዘዋሸራ የተቀኘላት ልጃገረድ የታቀፈችውን እሳት ከሰብለወንጌል ጀምሮ በአያሌ ልብወለድ ተቀርፃለች” ሊል አይደፍርም ነበር፡፡
አዎ ድፍረት ነው፤ ቅድስት ማርያም በድንግልና ፀንሳ በድንግልና አምላክን መውለዷን መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ቅዱስ ቁርዓን ያረጋግጣሉ፡፡ ባለቅኔውም እንደ ጸሐፊው እምነት ፍትወት አቃጥሏቸው፣ የልጃገረድ ፍቅር አማልሏቸው የዘረፉት ሳይሆን ባህርየ መለኮትን በድንግልና እናትነትን ገለጹበት እንጂ ስለተባለው ነገር በቅኔው ውስጥ የሰናፍጭ ቅንጣት ያህል ሰበብ እንኳ የለም፡፡
እናም ቅኔን ሲፈቱ ታሪኩን ማወቅ በእጅጉ ጠቃሚ ከመሆኑም በላይ፤ የቅኔው ባህርይ ወይም ዓይነት ሰምናወርቅ፣ ወይም ውስጠዘ፣ ወይም ህብር፣ ሰረዝ፣ ወፍ እግር፣ ዝምዝምወርቅ፣ ወዘተ መሆኑን መለየት ትክከለኛ ትርጉሙን ለመስጠት ይረዳናል፡፡ ክርክር የገጠምንበት የአለቃ ተክሌ ጉባኤ ቃና ግን “ሰምና ወርቅ” በሚባለው መንገድ የተዘረፈ በመሆኑ አስተያየት ስንሰጥም የሰምናወርቅ ቅኔ ህግጋት የሚጠይቁትን መስፈርት ግምት ውስጥ በማስገባት ቢሆን የግድ ነው፡፡
ሌላውና አብደላ በተደጋጋሚ ጊዜ ተገቢ ባልሆነ መንገድ የተጠቀመበት የቅኔው ባለቤት ስም ነው፡፡ የቅኔው ዘራፊ “አለቃ ተክሌ ዘዋሸራ” ይባላሉ፤ “አለቃ” የማዕረግ ስማቸው ሲሆን ትክክለኛ ስማቸው “ተክሌ” ይባላል፡፡ “ዘዋሸራ” ማለት ግን “የዋሸራው” ማለት ነው፡፡ በአንድነት “ተክሌ ዘዋሸራ” ሲባል ግን “የዋሸራው ተክሌ” ተብሎ ይነበባል፤ ወይም ይታወቃል “አብደላ ዕዝራ ከሰነአ እንደማለት፡፡
ምንም እንኳ ከአብደላ ሥራ ጋር ባይገናኝም በዚሁ ጋዜጣ ጥበብ አምድ ላይ “ዮሐንስ ገለታ” የተባሉ ጸሀፊ “የአዳም ረታ ሕጽናዊነት ምንድን ነው?” ሲሉ በተጠቀሙበት ቃልም ትንሽ ማብራሪያ መስጠት አስፈላጊ መስሎ ታይቶኛል፡፡
ጸሐፊው ህፅናዊነትን ሲተረጉሙት “የቃሉ አፈጣጠር/ አመጣጥ ሕጽናዊነትና ዘይቤ ምን አገናኘው ብሎ የሚጠይቅ ይኖር ይሆናል፡፡     ሕጽን የግዕዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙም በሁለት ፊደሎች መሃል ያለው ክፍተት ማለት ነው፤ ጽሑፍ ሊነበብ የሚችለው ይሄ ባዶ ቦታ በየፊደላቱ መካከል በመኖሩ ምክንያት ነው፡፡ በፊደል ገበታ ውስጥ ያሉት ክፍት ቦታዎች ደግሞ ማህጸን ይሰኛሉ” ብለዋል፡፡ ከየትኛው የግዕዝ መፍትሔ ቃላት ላይ እንዳገኙት ባላውቅም እንዲህ የሚል የግዕዝ መጽሐፍ ወይም መፍትሄ ቃላት አላየሁም፡፡
በግዕዝ መፍትሔ ቃላት ዝግጅት እስካሁን ተጠቃሽ የሆኑት ሊቁ አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ “መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ፣ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ” በተባለው ታላቅ መጽሐፋቸው ለሕፅን የሰጡት ትርጉም እንዲህ የሚል ነው፡፡
“ሕፅን በቁሙ፣ ማቀፊያ፣ ጭን፣ ደረት፣ ደረትና የእጅ መካከል ብብት፣ ጎን፣ ግብጣ፣ እንቢርቢጣ፣ የቀሚስ ሰላጤ፣ በሰላጤው ላይ የሚሰፋ ኪስ፣ ጀብ፣ ጥግ፣ ቅርብ፣ አጠገብ፣ የቦታ” የሚል ትርጉም ሰጥተዋል፡፡
ለማስረጃነትም “ውስተ ሕፅነ እሞሙ፤ አንበሮሙ ውስተ ሕፅኑ፡፡ ደይ እዴከ ውስተ ሕፅንከ (… በእናታቸው ጭን ውስጥ፤ በጭኑ ላይ አስቀመጣቸው፤ እጅህን በብብትህ ውስጥ አኑር…)” የሚሉ ጥቅሶችን ከማርቆስ ወንጌል 10፥16፣ ኦሪት ዘፀዓት 4፡6 እና 7 እንዲሁም ኩፋሌ ስምንትን በማስረጃነት በማስደገፍ አሳይተዋል፡፡
የቅኔና የትርጓሜ መጻሕፍት ሊቁ መምህር አፈወርቅ ተክሌ በ2005 ዓ.ም ባሳተሙትና “መጽሐፈ ታሪክ ወግስ” የሚል ርዕስ በሰጡት የመፍትሔ ቃላት መጽሐፋቸው ለ “ሕፅን ሕፀን፣ ታናሽ ልጅ፣ ብብትና ክንድ አጠገብ፣ እንግዴ ልጅ” የሚል ትርጉም ሰጥተዋል፡፡
ለዚህም ነው የአቶ ዮሐንስ ገለታ ጽሑፍ ዋና ፍሬ ሃሳብ የሆነው ሕንጽ የትመጣው አይታወቅም የምለው፡፡ ከሁለቱም ሊቃውንት መጻሕፍት ውጭ ያሉ ተመሳሳይ መፍትሔ ቃላትንም ለማየት ሞክሬያለሁ፤ ግን አንድም ከአቶ ዮሐንስ ትርጉም ጋር የሚቀራረብ ቃል እንኳ ማግኘት አልቻልሁም፡፡ እናም እባክዎ አቶ ዮሐንስ የተጠቀሙበትን ምንጭ ይንገሩን?

Published in ጥበብ
Page 1 of 15