Saturday, 19 January 2013 14:43

የምርቃናዎች ወግ

በጫት ሳቢያ ከሥራ ተባርሬያለሁ፡ የምቅመው ለማንበብ ነው፡፡ ሰሞኑን የሊዮ ቶልስቶይን War and Peace በቶልስቶይ አይነት ተመስጦ እያነበብኩ ነው፡፡
የመቃሚያ ብር የለኝም፡፡ እንዳልኩት የምቅመው ለማንበብ ነው፡፡ መቃሚያ ብር ስላልነበረኝ ግን War and Peace ን ሸጬ ወደ ጫት ቤት ሄድኩኝ፡፡
እንግዲህ ጫት እዚህ ድረስ ነው፡፡ ለማንበብ ብሎ የሚቅም ሠውን መጽሐፍ አስሽጦ ያስቅማል፡፡
አብዛኛው ጊዜ ቃሚዎች ጫትን እንደ ግብአት ተጠቅመው ምርቃና ላይ ለመድረስ ለመነቃቃት ወይም ለመዝናናት እንደሚቅሙ ያስባሉ፡፡ (ይህን ሲያስቡ ወይም ሲሰሙ ምርቃናዎች ሁሉ ይስቃሉ)
በነገራችን ላይ ምርቃናዎች ቃሚዎችን እንደ አሻንጉሊት ነው የሚያዩዋቸው፡፡ ነገርየው የተገላቢጦሽ ነው፤ እስከዛሬ ስናስብ እንደኖርነው አይደለም፡፡ ግብአቱ ሠው፤ መዳረሻው ደግሞ "ምርቃና" ነው፡፡
ምርቃናዎች ወዳሰኛቸው መንገድ፤በተመቻቸው ሁኔታ ነው ቃሚውን የሚጋልቡት፡፡ ይህ መገለጥ የተከሠተበትን አጋጣሚ ልንገራችሁ፡፡ በአንድ ወቅት እንደተለመደው ጫት ቤት ጎራ ብዬ የተለመደውን አዝዤ ጥጌን ይዤ ተቀምጫለሁ፡፡ ጫት ቤት ደርሰው ወይም ቅመው የማያውቁ ሠዎች ቢሠሙት የሚገርማቸው ቃሚዎች ደግሞ ሁሌ የማያስተውሉት አንድ ነገር አለ፡፡ ጫት ከታዘዘ በኋላ የመጀመሪያውን ጉንጭ ለመጉረስ ያለው ማመንታት እና ውዝግብ ይገርማል፡፡ ቃሚዎች በዚህ ሁኔታ ባሉበት ሰዓት ካለሁበት ገዢ ቦታ ሆኜ ቃኘሁ፡፡ የሁሉም ፊት ይገርማል፡፡ ያሳዝናል፡፡
ሁለት ጓደኛሞች ኪሳቸው ውስጥ ያለውን ገንዘብ አጋጭተው እንኳ ለአንድ ሰው ፍጆታ ብቻ የሚሆነውን ለሁለት ለመቃም እየተጉ ቢሆንም አሁንም ፍራንክ ያጥራቸዋል፡፡ ከፊቴ የተቀመጠው ሰውዬ አለቃው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንደሰጠው ከትላንት በስቲያ መርቅኖ ነግሮኛል፡፡ ከሱ በስተግራ በኩል የተቀመጠው ጫት ዱቤ ተከልክሏል፡፡ ለማልቀስ አምስት ጉዳይ ላይ ነው፡፡ ከሱ አጠገብ ያለው ደግሞ በር በሩን ይመለከታል፡፡ ከሚያውቃቸዉ ሠዎች አንዱ በተአምር ብቅ እንዲል ይጠብቃል፡፡ ለሌላ አይደለም፤አንድ ሁለት እንጨት የሚረብሠው እግዜር እንዲልክለት ነው፡፡
በር ላይ የተቀመጠው ወጣት ልጅ ነው፡፡ አስር ሲደመር ሁለት ይማራል፡፡ ቤተሰቦቹ ኮሌጅ ገብቶ የአዋቂዎች አዋቂ እንዲሆን፣ ለወግ ለማዕረግ እንዲበቃ አጥብቀው ይፈልጋሉ፡፡ ጫት መቃም መጀመሩን ሲሰሙ ትንፋሽ እስኪያጥራቸው ደነገጡ፡፡ መጀመሪያ መከሩት፡፡ ከዚያ በጓደኛ፣ በዘመድ አዝማድ፣ በሰፈር ሽማግሌዎች አስመከሩ፡፡
በየተራ ለሁሉም ታቦቶች ተሳሉ፡፡ አንዳቸውም ተሳስተው አልሠሙም፡፡ ፀበሎች ባሉበት ይዘውት ዞሩ፡፡ በከተማው ውስጥ ያሉ ሳይካትሪስቶች ሁሉ በሠዓት እየተከፈላቸው አዋሩት፡፡ (ይህ ሁሉ
የምርቃናዎች ወግ
ሲሆን ልጁ ይበሳጫል፡፡ ምርቃና ደግሞ የበለጠ ትበሳጫለች፡፡)
ያው በመጨረሻ እቤት ውስጥ ያለውን እቃ ሸጦ ሳይጨርስ ብለው ለመቃሚያ በቂ በጀት በጀቱለት፡፡ ይኸው ከትምህርት ቀርቶ እየቃመ ነው፡፡
ልክ ከዚህ ወጣት ፊት ለፊት ፀጉራቸው ጥጥ የመሠለ ሽማግሌ እየቃሙ ነው፡፡ ጡረታ በ55 አመታቸው ከወጡ በኋላ ነው መቃም የጀመሩት፡፡ አሁን 65 አመታቸው ነው፡፡ በአስር አመታት ውስጥ ግን አንድ ሠው በእድሜ ዘመኑ የሚቅመውን ያህል ቅመዋል፡፡ ወጣት እና ትጉህ እያሉ፣ በጉብዝናቸው ወራት ምንም ሡስ አልነበራቸውም፡፡ (…,ሽማግሌው ሚስት አላገቡም፡፡ ልጅ የላቸውም፡፡) ጥሩ ጥሪት ቋጥረዋል፡፡ ቋጥረው ነበር፡፡ በአስር አመት ውስጥ አወደሙት፡፡ አብራቸው የኖረችውን ማርቼዲስ መኪና በቅርቡ ነው የሸጡት፡፡ ብቻቸውን ይኖሩበት የነበረው እና በደህና ጊዜ የሠሩትን ቪላ አከራይተው እራሳቸው አንዷ ሠርቪስ ውስጥ ይኖራሉ፡፡ እየቃሙ ነው፡፡
እዚህ ቤት ደንበኛ የሆኑ እና እዚህ የተዋወቁ ሶስት ሴት ቃሚዎች አንድ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ አንዷ የህግ ምሩቅ ናት፡፡ ኮሌጅ ለጥናት ብላ የጀመረችው ጫት ሡስ ሆኖ ቀረ፡፡ አንደኛዋ ሴተኛ-አዳሪ ናት፡፡ ለምን እንደምትቅም ስትጠየቅ "ለራስ ነዋ" ትላለች፡፡ "መጠጡን እንዴት ሳልቅም እችለዋለሁ?!" ትላለች፡፡ ስትቅም ግን ብዙ፤ በጣም ብዙ እንደምትጠጣ ማወቅ አትፈልግም፡፡
"በዚያ ላይ የዚያን ሁሉ ሠው ፀባይ እንዴት ያለ ምርቃና እችለዋለሁ?!" ብላ ትጠይቃለች፡፡ "ባልቅም ይኼኔ አሳብደውኝ ነበር" ትላለች እየሳቀች፤ ሳቋ የሰማይን ጣራ አልፎ እየተሰማ፡፡ "መርቅኜ ግን ስንቱን አሳብጄዋለሁ መሰላችሁ?!" ቁጥሩን የምታውቀው እሷው ናት፡፡ የምታውቀው አትመስልም እንጂ፡፡
ሶስተኛዋ ከተማው ውስጥ በደንብ የሚታወቅ ሚሊየነር ልጅ ናት፡፡ ገና አስራ ሰባት አመቷ ነው፡፡ ፍቅር ያስጀመራት የሷው ቢጤ የቱጃር ልጅ ነው፡፡ ፍቅር ብቻ ሳይሆን ጫትም አብሮ ነው ያስጀመራት፡፡
አሁን አብረው አይደሉም፡፡ አሁን የሱ አይደለችም፡፡ አሁን የማንም አይደለችም፡፡
አሁን የሁሉም ናት፡፡ አሁን የጫት ሆናለች፡፡ (የሌሎቹን ቃሚዎች ጉድና ገመና በኋላ ምርቃናዎች ይነግሩአችኋል) እየቃምኩ ነው ይህን ሁሉ የምከታተለው፡፡ ሁሉም ቃሚዎች ጫታቸውን ማላመጡን ተያይዘውታል፡፡ በደንብ መርቅነው አፋቸው ከመለጎሙ በፊት ተራ እየተሻሙ ሁሉም ይንጫጫሉ፡፡ ጨዋታው ደራ፡፡ ሠዓቱ በሄደ መጠን እንደሚጠበቀው እና እንደተለመደው ቀስ እያለ የጨዋታው ድምጽ እየከሠመ መጣ፡፡ ሁሉም ቃሚ እንደ ቀንድ-አውጣ እየራሱ ቀፎ ውስጥ ገባ፡፡ ፀጥታ ሠፈነ፡፡ እና፣ እና፣ እና …
በዚህ መሀል ልክ አርኬሜዴስ የተባለው ጥንታዊ ሳይንቲስት የግኝቱን ቅፅበታዊ መገለጥን የገለፀበት  ሁኔታ በኔም ደረሠ፡፡ "Eureka!" አልኩ፡፡ "Eureka! ድምፅ አገኘሁ፡፡" (ይህ ግኝት አርኪሜዴስ እና ግሪኮች እንደሚኮሩበት ግኝት እኔና ኢትዮጵያዊያንም በመጪዎቹ ግዜያቶች እንኮራበታለን ብዬ አስባለሁ)
ድምጽ ሠማሁ፡፡
ሁሉም ፀጥ ብሏል ብያችኋለሁ፡፡ ታዲያ የምን ድምፅ ሠማህ? አትሉም? የምርቃና፡፡
የምርቃናዎች ድምፅ ሠማሁ፡፡
ብታምኑትም፣ ባታምኑትም ምርቃናዎች እርስ በርስ ሲያወሩ ሠማሁ፡፡
ምርቃና አንድ፡-
ለወትሮው ለወሬ ቀዳሚ የነበረችው ምርቃና እንደ ቃሚዋ ጨምታለች፡፡
"ያንቺ ሠውዬ ዛሬም እንደተለጎመ ነው አይደል?" አላት አንድ ቀዥቃዣ ምርቃና፡፡
"እስከ ዛሬ የደበቅኋችሁን አንድ ነገር ልንገራችሁ ወይም አልንገራችሁ ወይስ ምን? እያልኩ እያሰብኩ ነበር"
"ንገሪን"
"አትንገሪን"
"እንደፈለግሽ"
"እነግራችኋለሁ"
"እንደፈለግሽ ተብለሻል"
"እስከዛሬ በምርቃና አለም ተከስቶ የማያውቅ ነገር ስለሆነ ነው እስከ አሁንም ዝም ያልኳችሁ፡፡ አታምኑኝም ብዬ፡፡ አላስቻለኝም ዛሬ፡፡ የኔ ሰውዬ መርቅኖ አያውቅም"
"ምን?!"
"ምርቃና ሆዬ መርቅነሻል መሰል!"
"እንዴት ነው በየቀኑ ሁለት ሙሉ በለጬ እየቃመ የማይመረቅነው?!" ተንጫጩ ምርቃናዎቹ
"ከፈለጋችሁ እሱ የሚቅመው ምርቃናውን ለመስበር ነው"
"ያንተ ያለህ! ጉድ ሳይሰማ ምርቃና አይሰበርም አሉ" አለ አንዱ ምርቃና፡፡
"አያችሁ ታሪኩ ትንሽ ሳይወሳሰብባችሁ አይቀርም፡፡ ለዚህ ነው ቶሎ ያልገባችሁ" አለች የጭምቱ ምርቃና ሚስጢራዊ በሆነ ድምፅ፡፡
"አቦ እንዳልመረቀነ ነገር፣ ነገር አታንዛዢ፡፡ ንገሪና፡፡ ምንድነው ቅሞ ሳይመረቅኑ ምርቃና በጫት መስበር ማለት?"
"አብሽር እንግራችኋለሁ፡፡ ሠውየው የተወለደው መርቅኖ ነው እና የግድ እንደ ሌሎች ሰዎች ለመሆን መቃም አለበት፡፡ የሚቅመው ምርቃናውን ለማጥፋት ነው፡፡ የተፈጥሮ-ምርቅን ነው ባጭሩ፡፡ ገቢቶ?!
ሁሉም ምርቃናዎች አጉረመረሙ፡፡ በሰው ልጆች ላይ በተለይ በቃሚዎች ላይ (በቃሚዎች በኩል በሌሎች ላይ) በሚያሳድሩት ተፅእኖ ሁሌም እንደኮሩ ነበር፡፡ ለካ እንዲህ አይነትም ሠርጎ ገብ አለና! ላለመመርቀን መቃምም አለ ለካ! ወይ ጉድ! ይኼን ሌሎች እንዳይሰሙ ብቻ፡፡)
"ይህቺን 'ምርቃና' በሌላ የምርቃናዎች ስብስብ እናወራታለን፡፡ እኔ ይህ ቃሚ በጣም ገርሞኛል፡፡ 'የባሰ አለና አወዳይን አትልቀቅ' ያለው ማነው?!" አለ የአወዳይ ምርቃና፡፡
ምርቃና ሁለት፡-
"የኔ ሠውዬ" አለች አንዷ ጠይም ምርቃና፣ ምርቃና አንድ የፈጠረችውን አግራሞት ለማሸነፍ እየጣረች፡፡ "የኔ ሠውዬ ጫት መቃም ደብሮታል፡፡ በመከራ ነው የሚቅመው፡፡ አሁኑኑ ጉንጩ ውስጥ ያለውን ተፍቶ ተነስቶ ሁለተኛ ባይመለስበት ደስ ይለዋል"
"ለምን ይቅማል ታዲያ?" የሁሉም ጥያቄ ነው፡፡
"ለሚስቱ ብሎ"
"ኡውውድ" በአንድ ላይ፡፡
ይኼኔ አንድ ሽማግሌ ምርቃና አግራሞቱን ገለፀ፡- "ዛሬ ምንድነው የምሰማው አንዱ ላለመመርቀን ይቅማል፡፡ አንደኛው ደግም ጫት ለጉድ ቀፎታል ግን ለሚስቱ ብሎ ይቅማል፡፡
ምንድነው ነገሩ? እስከዛሬ ስንት ሚስቶች ናቸው ስንት ባታሊዮን ሽማግሌ አሰልፈው ውድ መርቃኞቻችንን ከኛ የለያዩት? ስንቶቹስ ናቸው 'ከጫት እና ከኔ ምረጥ' ብለው ምራጭ የሆኑት?! ይህ እኛ ምርጥ ተመራጭ ለመሆናችን በቂ ምስክር ነው፤ ጉራ አይሁንብኝና፡፡
እና ዘንድሮ ምን አይነት ባልና ሚስት መጡ ልትሉኝ ነው? 'እባክህ ቃምልኝ' የምትል ሚስት ወይስ 'ላንቺ ስል የማልሆነው የለም፤ መመርቀን ጭምር' የሚል ባል መጣ?! ጉድ እኮ ነው፡፡ ምርቃና ሁለት ምርቃና አንድ የተናገረችውን ቃል በቃል ኮርጃ እንዲህም አለች፡-
"አያችሁ ታሪኩ ትንሽ ሳይወሳሰብባችሁ ምርቃና ከገፅ 17 የዞረ
አይቀርም፤ ለዚህ ነው ቶሎ ያልገባችሁ"
"የምርቃና ዋነኛውና ትልቁ ቁም ነገር፣ ነገር ማወሳሰብ ሳይሆን ማቅለል ነው፡፡ We are here to make things simple. Not complex. Not at all' ይል ነበረ አንድ መርቃኝ መሀንዲስ፡፡" አለ አንድ ብልህ ምርቃና፡፡ "ይኸውላችሁ ነብሶቼ እንዲህ ነው፡፡
የኔ መርቃኝ ምርቃናዎች ብቻ ሳይሆን ሴቶችም የሚሳሱለት ነው፡፡ ቆንጆ ነው፡፡ አሪፍ ስራ አለው፡፡ ታማኝ ነው፡፡ ምርጥ brain አለው፡፡ ሁሌም ትሁት ሁሌም ፍቅር ነው፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ he is a man of all season."
"አቦ አሳጥሪው!"
"አቦ ተረጋጋ፡፡ ወደ ዋናው ነጥብ እየመጣሁ ነው፡፡ ሚስቱ ትወደዋለች፡፡ ወይ መውደድ! በቀን አርባ ስምንት ሰዓት ስለሱ ነው የምታስበው፡፡ ፍፅምናው ያስፈራታል፡፡ አንድ ድክመት እንዲኖረው ትፈልጋለች፡፡ አስተውላችሁ ካያችሁ ጥንካሬ ብቻ ሣይሆን ድክመትም ፍቅርን የሚያደረጅበት ሁኔታ አለ"
"አቦ አትፈላሰፊ"
"እፈላሰፋለሁ"
"እሺ ታሪኩን ንገሪን"
"Okay"
"እንግሊዝኛ አታብዢ ደሞ"
"Okay"
"እባክሽን ንገሪን፣ ለምንድነው ለሚስቱ ብሎ የሚቅመው?"
"ፍቅራቸውን ለማደርጀት፡፡ ጓደኞቼ፣እሱ ጫት መቃም ያቆመ ለታ ስለምን ያወራል? ስለምንም፡፡ እሱ ስለምንም አያወራም ድሮም፡፡ እሱ የሚቅም ከሆነ ግን እሷ ቢያንስ 'ፍቅርዬ ይኼን ነገር ለምን አትተውም? አይጎዳህም?' ብላ ወሬ መጀመሪያ ታገኛለች፡፡ ፍቅሯንም፣ ለሱ ሃሳቢነቷንም መግለጫ ይሆናታል፡፡ እንጂ ሁልጊዜ ከመሬት ተነስቶ 'እኔ እወድሃለሁ' ሲባል አይኖር ነገር፡፡ ምክንያት ያስፈልጋል ፍቅርንም ለመግለፅ፡፡"
ምርቃና ሶስት፡-
"የእነሱ እንኳን ደስ ይላል፡፡ አለላችሁ እንጂ ይኼ"
"የቱ?"
"ይሄ ወዲያ ማዶ ጥግ ላይ የተቀመጠው ቀፋፊ ነዋ! ይኼ ትልቅ ጭንቅላቱ በምን ሀሳብ እንደተሞላ ታውቃላችሁ?"
"በብር"
"አይደለም"
"በተንኮል?"
"አይደለም አቦ"
"በዕውቀት?"
"እንዲያም አድርጎ የለምi"
"በፍርሃት?"
"ሌላ"
"በስልጣን ምኞት?"
"አሁንም ሌላ"
"እና ታዲያ በምን?"
"በሴቶች"
"እና ታዲያ ይኼ ምኑ ይገርማል?"
"አሁን እራሱ እዚህ ተቀምጦ ምን እያደረገ እንዳለ ብታውቁ 'ታዲያ ይሄ ምኑ ይገርማል?' አትሉም ነበር፡፡"
"ምን እያደረገ ነው በአላህ?"
"እየባለገ በሃሳቡ፡፡ ይህቺ ቃሚዎችን ከምታስተናግደው ልጅ ጋር በሀሳቡ እየባለገ ነው፡፡ ማታ አብሯት ነው ያደረው የሚገርማችሁ"
"ምን አይነቱ ባለጌ ነው?" አለች አንዷ ጨዋ ምርቃና፡፡
"የክፍለ ዘመኑ ባለጌ!" አለች ሌላዋ፡፡
እስካሁን ዝም ብላ የነበረች ምርቃና፡- "እናንተ?!" አለች በቀስታ፡፡
"እህስ?!"
"እኔ ፈርቻለሁ!"
"ምንድነው ያስፈራሽ?"
"የኔው መርቃኝ በቅርቡ ሊያብድ ይችላል፡፡"
ሁሉም ምርቃናዎች ዞረው የተፈራለትን ሠውዬ አዩት፡፡ ቀይ፣ ረዥም፣ ቀጭን ሠው ነው፡፡ ፊት ለፊቱ ያለው ግድግዳ ላይ አፍጥጧል፡፡ "እውነቴን ነው በቅርቡ ሳያብድ አይቀርም፡፡ ውጪ አያስታውቅበትም እንጂ ውስጡ ተመሳቅሏል፡፡"
ልክ ይኼን እንዳለች ሶስት በስድስት የሆነችው ጫት ቤት በጩኸት ተሞላች፡፡ ሠውዬው ነው የጮኸው፡፡ ሁሉም ምርቃናዎች ደንግጠው ወደ መርቃኞቹ ተመለሱ፡፡

Published in ልብ-ወለድ

ጥንታውያን ግሪኮች ከባድ የህመም ስቃይን ለመቀነስ ወይንም ከበድ ላሉ የቀዶ ህክምና ሥራዎች በድብደባ ራስን የማሳት ዘዴን ይጠቀሙ ነበር፡፡ ለጥርስ ህክምናም ሐኪም ዘንድ የቀረበ ታማሚ በደህና ቡጢኛ መንጋ ጭላውን በቦክስ ይመታና ራሱን እንዲስት ይደረጋል፡፡ ግሪካውያኑ ይህንን ዘዴ በሥራ ላይ ከማዋላቸው በፊት ከበድ ያለ ቀዶ ህክምናን ለማከናወን የታማሚውን እጅና እግር ጥፍር አድርጐ በማሰርና እንዳይንቀሳቀስ በማድረግ ህክምናውን ያከናውኑ ነበር፡፡ ይህ ዘዴ በሽተኛውን ለከፍተኛ ስቃይና ለተጨማሪ ህመም በመዳረጉ የህክምና ባለሙያዎቹ ታማሚውን ደብድቦ ራሱን እንዲስት በማድረግ የማከም ዘዴን ተግባራዊ ማድረግ ጀመሩ፡፡ ታማሚው ለቀዶ ህክምና ወደ ኦፕሬሽን ክፍል በሚገባበት ወቅት የህክምና ባለሙያው አሳቻ ቦታ ላይ ጠብቆ በዱላ አናቱን ይለውና ራሱን ስቶ እንዲወድቅ ያደርገዋል፡፡ ከዚያም ቀዶ ሐኪሙ ሰውየው ነቅቶ ራሱን ከማወቁ በፊት በአፋጣኝ የቀዶ ህክምናውን አከናውኖ ማጠናቀቅ ይኖርበታል፡፡

ይህ ዘዴ ለዓመታት ተግባራዊ ሲደረግ የኖረና የበርካቶችን ህይወት የታደገ ቀደምት የህክምና ዘዴ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ኋላቀር አሠራር በዚህ ሁኔታ መቀጠል እንዳይችል ያደረገው ግኝት እ.ኤ.አ በ1772 ዓ.ም ጆሴፍ ፕሪስትሪ በተባለ ተመራማሪ እውን ሆነ፡፡ በህክምናው ዓለም እጅግ ታላቅ ግኝት ከሚባሉት መካከል አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት የማደንዘዣ መድሃኒት፤ የቀዶ ህክምና አገልግሎት ወደተሻለ ደረጃ እንዲሸጋገር ከፍተኛውን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የማደንዘዣ (የሰመመን) መድሃኒት ስሙን ያገኘው ከጥንት የግሪክ ስልጣኔ ሲሆን (anesthesia) ወይንም (without sensation or feeling) በማደንዘዝ የህመም ስሜትን ማስወገድ የሚል ስያሜ ተሰጥቶት እ.ኤ.አ በ1772 ዓ.ም ሥራ ላይ ዋለ፡፡ ለማደንዘዣ አገልግሎት ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራ ላይ የዋለው መድሃኒት ናይትረስ ኦክሳይድ (Nitrous Oxide) በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ የማደንዘዣ መድሃኒት ተጠቃሚውን ሰው በሳቅ የማፍነክነክ ባህርይ ስላለው "Laughing gas" (አስቂኙ ጋዝ) የሚል መጠሪያም ተሰጥቶት ነበር፡፡

የዚህ ማደንዘዣ የማደንዘዝ አቅም ጥሩ ቢሆንም ታማሚውን በቀዶ ህክምናው ወቅት እንደደነዘዘ የማቆየቱ ጉዳይ እምብዛም አጥጋቢ አልነበረም፡፡ በዚህ ምክንያትም ተመራማሪዎቹ ከዚህ የተሻለ የማደንዘዝ አቅም ያላቸውና ረዘም ላሉ ሰዓታት ታማሚው እንደደነዘዘ ለማቆየት የሚያስችሉ የማደንዘዣ መድሃኒቶችን ለመሥራት ጥረታቸውን ቀጠሉ፡፡ የአመታት ድካምና ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ እ.ኤ.አ በ1846 ዓ.ም ይበልጥ ጠንካራና አስተማማኝ የሆነ Either (ኢተር) የተባለ ማደንዘዣ ተሰርቶ በሥራ ላይ ዋለ፡፡ ቀስ እያለም ክሎሮፎርም፣ ሃሎቲንና ኬታሚን የተባሉ የማደንዘዝ ብቃታቸው ከፍ ያለ የማደንዘዣ መድሃኒቶች እየተሰሩ በጥቅም ላይ መዋል ጀመሩ፡፡ የማደንዘዣ መድሃኒት የምጥ ህመምን ለማስወገድ ለመጀመሪያ ጊዜ በጥቅም ላይ የዋለው ለንግስት ቪክቶሪያ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወጉናል፡፡ የማደንዘዣ (የሰመመን መድሃኒቶች) ዛሬ ዛሬ እጅግ ወደተሻለ ደረጃ ላይ በመድረሳቸው ታማሚው አንዳችም አይነት የህመም ስሜት ሳይሰማው ህክምናውን ለማከናወን እንዲችል እያደረጉት ይገኛሉ፡፡ በቀዶ ህክምናም ሆነ በሌሎች ከበድ ያሉ ህክምናዎች ወቅት በአብዛኛው ተግባራዊ የሚደረጉት ሁለት አይነት የማደንዘዣ አሰጣጥ ሥርዓቶች ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል አንደኛው (General Anesthesia) የሚባለው ሲሆን ይህም በአብዛኛው ከወገብ በላይ ላሉ ማለትም ለሆድ ውስጥ ህክምና፣ ለኩላሊት፣ ለሳንባ፣ ለልብና ለጭንቅላት ህክምናዎች ተግባራዊ የሚደረግ የማደንዘዝ ህክምና ነው፡፡ በዚህ የሰመመን ህክምና ጊዜ የማደንዘዣ ባለሙያው (አንስቴቲስቱ) የሰውየውን ትንፋሽ ተቀብሎ ለበሽተኛው ትንፋሽ በመስጠት ቀዶ ህክምናው እስከሚጠናቀቅ ድረስ የሚቆይበት አሠራር ነው፡፡ ይህ የማደንዘዣ ህክምና በርካታ አደጋዎች ያሉትና የማደንዘዣ ሰጪ ባለሙያውን ከፍተኛ ትኩረት የሚጠይቅ ሥራ ነው፡፡ ሁለተኛው የማደንዘዣ የምንለው ሲሆን ይህ የማደንዘዣ አይነት በነርቮች ውስጥ ባሉ መዋቅር ውስጥ መድሃኒቶችን በማስገባት ሰውየው ራሱን ሳይስት ህክምናው በሚደረግበት አካባቢ ብቻ እንዲደነዝዝ የማድረግ ሥራ ነው፡፡ ለምሣሌ ሄሞሮይድና ፌስቱላን ለመሳሰሉ ህክምናዎች ይህ ዘዴ እጅግ ተመራጭ ነው፡፡ አሁን አሁን ይህ የማደንዘዣ ህክምና በኦፕሬሽን ለሚወልዱ ሴቶችም በጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል፡፡ ይህ የማደንዘዝ ህክምና አንዲት እናት ለወሊድ ስትሄድ ከወገብ በታች በማደንዘዝ ምንም አይነት ህመም ሳይሰማት ልጁን ማውጣት የሚያስችል ነው፡፡ ህክምናው በዋጋው አነስተኛ ከመሆኑም በተጨማሪ ሐኪሙ (የወላዷን) ሁኔታ በሚገባ እየተከታተለና ከወላዷ ጋር ስላለችበት ሁኔታ እየተነጋገረና መረጃ እየተቀበለ የሚሰራው ህክምና ስለሆነ ባለሙያዎቹ ይህንን የማደንዘዝ ህክምና ተመራጭ ያደርጉታል፡፡

የሰመመን መድሃኒት ከሚሰጣቸው ህሙማን መካከል በመድሃኒቱ ደንዝዘው በቀዶ ህክምናው ወቅት የሚከናወኑትን ተግባራት ፈጽመው የማያውቁና የማያስታውሱ በርካታ ህሙማኖች ቢኖሩም በተሰጣቸው የማደንዘዣ መድሃኒት አማካኝነት ደንዝዘው መንቀሳቀስ ባይችሉም ህመሙ የሚሰማቸውና በቀዶ ህክምናው ወቅት የሚደረጉ ነገሮችን የሚያዳምጡ ህሙማንም አሉ፡፡ ይህንንም (Anesthesia Awarenes) ይሉታል ባለሙያዎቹ፡፡ እነዚህ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ከተለያዩ ሱሶች ጋር በተያያዘ (ሲጋራና ሐሺሽ ማጨስ፣ የአልኮል መጠጦችን) በብዛትና ረዘም ላሉ ጊዜያት ከመጠቀም ጋር ሊገናኝ እንደሚችልም ባለሙያዎቹ ይናገራሉ፡፡ አንድ ሰው ሊቀበለው ከሚችለው የማደንዘዣ መድሃኒት በላይ መስጠት ሰውየውን ለአደጋ በማጋለጥ ወደ ሞት ሊወስደው እንደሚችልም እነዚሁ ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡ ይህንን ክስተትም ባለሙያዎቹ "Death on the table" (የጠረጴዛ ላይ ሞት) ሲሉ ይጠሩታል፡፡ ይህ ክስተት ህመምተኛው ከተሰጠው ማደንዘዣ (የሰመመን መድሃኒት) መንቃት ሲያቅተውና በዚያው ህይወቱ ሲያልፍ ወይንም ለፈውስ ተጋድሞበት የነበረው የቀዶ ህክምና ጠረጴዛ መገነዣው ሲሆን ባለሙያዎቹ የሚጠቀሙበት መግለጫ ነው፡፡ ለጠረጴዛ ላይ ሞት በርካታ መንስኤዎች ቢኖሩም ዋናዋናዎቹ ከዚህ የሚከተሉት ናቸው፡፡ የበሽታው ሥር መሰደድና የኦፕሬሽኑ አስቸጋሪነት፣ በኦፕራሲዮኑ ወቅት በሚደረግ የጥንቃቄ ጉድለት፣ የማደንዘዣ አለርጂነት፣ ለማደንዘዣ መድሃኒቶች ያልተጠበቀ ምላሽ መስጠትና ከአቅም በላይ መጠን ያለው የማደንዘዣ መድሃኒት መጠቀም ዋነኞቹ ናቸው፡፡

በኦፕሬሽን ክፍል ውስጥ ከቀዶ ሐኪሙ እኩል ለህክምናው ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርገውና ለበሽተኛው በህይወት መመለስ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የሰመመን ሰጪ ባለሙያው ነው፡፡ ለዚህም ነው የአኒስቴዥያ ሙያን "ህይወትን በአደራ ተቀብሎ በአደራ የመመለሻ ሙያ ነው" የሚሉት፡፡ የማደንዘዣ ሰጪ ባለሙያ ወይንም የሰመመን ሰጪ ባለሙያ በሚሉት ስያሜዎቻቸውም ባለሙያዎቹ አይስማሙም፡፡ ይህ ስያሜ ሙያውን በትክክል የሚገልጽ አይደለም ሲሉ ይቃወሙታል፡፡ ሙያው የአንስቴዥያ ሙያ እየተባለ ሊጠራ ይገባዋልም ይላሉ፡፡ የአንስቴዥያ ሙያ የሰው ልጅ በህይወትና በሞት መካከል በሚገኝበት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ በመገኘት የሰውየውን ህይወት በአደራ አቆይቶ የመመለስ ጉዳይ እንደመሆኑ ሙያው ከፍተኛ ጥንቃቄና አትኩሮትን የሚሻና ለቅንጣት ስህተት ቦታ የማይሰጥ ነው፡፡ በዚህ ሙያ ውስጥ ያለ ሙያተኛ በሥራው ላይ የሚፈጽመው ቅንጣት ስህተት ህመምተኛው በዛው በተጋደመበት የኦፕሬሽን ጠረጴዛ ላይ እስከዘለዓለሙ እንዲያሸልብ ሊያደርገው ይችላል፡፡ በአኒስቴዥያ ሙያ ውስጥ ያለ አንድ አኒስቴቲስት በአንድ ጊዜ ለምን ያህል ጊዜያት ለህሙማን ማደንዘዣ መስጠት እንደሚችል በግልጽ የተቀመጠና የተገደበ ነገር ባይኖርም፣ በውጪው ዓለም የማደንዘዣ ባለሙያው በአንድ ቀን ከሶስት ጊዜያት በላይ የማደንዘዣ መድሃኒቶችን እንዲሰጥ አይፈቀድለትም፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የሰመመን ሰጪ ባለሙያው የሰመመን መድሃኒቱን በሰጠ ቁጥር በተለያዩ መንገዶች ወደ ራሱ የሚያስገባቸው መድሃኒቶች በመኖራቸውና እነዚህ መድሃኒቶች ደግሞ ቀስ በቀስ የሰመመን ሰጪ ባለሙያው ራሱን በማደንዘዝ ሥራውን ትኩረት ሰጥቶና አስቦ ለማከናወን እንዳይችል ያደርገዋል የሚል ነው፡፡

በአንድ የቀዶ ህክምና ክፍል ውስጥ ከቀዶ ሐኪሞቹና ከነርሶቹ ጋር ተመሳሳይ የሥራ ቱታ ለብሰውና ፊታቸውን በጭንብል ሽፍነው - እያንዳንዷን የህመምተኛውን እንቅስቃሴ በከፍተኛ ትኩረት እየተከታተሉ የሰመመን መድሃኒቶችን በመስጠት ህመምተኛውን ለኦፕሬሽን ዝግጁ የሚያደርጉት እነዚህ ባለሙያዎች፣ ከቀዶ ህክምናው በኋላ በህመምተኛው ላይ የሚያስተውሏቸው ለየት ያሉ ገጠመኞችና በሥራቸው ላይ ያጋጠሟቸው በርካታ አሳዛኝና አስደሳች ገጠመኞችም አሏቸው፡፡ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለ17 ዓመታት በአንስቴዥያ ሙያ ውስጥ ሲሰራ የቆየው አንስቴቲስት ክብረት አበበ፤ በእነዚህ ረዘም ያሉ የሥራ ጊዜያት በርካታ አስደሳች፣ አሳዛኝና አስገራሚ ገጠመኞችን አስተናግዷል፡፡ ሙያውን እጅግ አጥብቆ እንደሚወድ የሚናገረው አቶ ክብረት፤ አንድ ህመምተኛ በአንስቴቲስቱ በኩል ካላለፈና ዝግጁ ካልሆነ በስተቀር ወደቀዶ ህክምናው ሊያልፍ አይችልም፡፡ የማደንዘዝ ሥራ ያለፍላጐትና ያለፍቅር ከተሰራ የሰውን ህይወት በቀላሉ ሊያሰነጥቅ የሚችል ሥራ ነው ይላል፡፡ በ17 ዓመት የአኒስቴቲስትነት የሙያ ዘመኑ እጅግ በርከት ያሉ ገጠመኞችን ቢያስተናግድም ከእውቁ የማህፀን ሐኪም ከፕሮፌሰር ሉክማን ጋር ያደረገውን ግን ፈጽሞ አይረሳውም፡፡ አንዲት የሃምሣ አመት ሴት በማህፀን እጢ ችግር ወደ ሆስፒታሉ ይመጣሉ፡፡ በወቅቱ የሴትየዋ ክብደት 67 ኪሎ የሚመዝን ሲሆን በማህፀናቸው ውስጥ ያደገው እጢ መጠን ደግሞ ከሰላሣ ኪሎ በላይ ክብደት ያለው ነበር፡፡ ይህ ከሴትየዋ ጠቅላላ ክብደት ጋር ተመጣጣኝነት ያለውን እጢ ለማውጣት ሲታሰብ ዋንኛውና አሳሳቢው ጉዳይ ለሴትየዋ የሚሰጠው የማደንዘዣ ህክምና በምን መልኩ ይሰጥ የሚለው ነበር፡፡ የማደንዘዣ መድሃኒቶች በአብዛኛው የሚሰጡት ታማሚውን በጀርባው በማስተኛት ቢሆንም ይህንን አሠራር በእኚህ ሴት ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ፈጽሞ የማይታሰብ ሆነ፡፡ ምክንያቱም በጀርባቸው በሚተኙበት ወቅት የእጢው ክብደት ሙሉ በሙሉ በሰውነታቸው ላይ በማረፍ ስለሚሸፍናቸው ነበር፡፡ ሁኔታው አስቸጋሪ ቢሆንም ለእኚህ ሴት በመቀመጥ የሚሰጠው የማደንዘዣ መድሃኒት እንዲሠራላቸው ይወሰንና ህመምተኛዋ በዚህ መልኩ የማደንዘዣ መድሃኒት ተሰጥቶአቸውና የተሣካ ኦፕሬሽን ተደርጐ የማህፀን እጢው ወጥቶላቸዋል፡፡ ይህም በሆስፒታሉ የህክምና ታሪክ ውስጥ እጅግ ስኬታማ የህክምና ተግባር የተከናወነበት እና እስከቅርብ ጊዜ ድረስም በሪከርድነት ተጠቃሽ የነበረ ስራ መሆኑን አቶ ክብረት ይናገራል፡፡ ህሙማን የማደንዘዣ መድኒቶችን በሚወስዱበት ጊዜ የተለያዩ ባህሪያትን ያሳያሉ፡፡

በመድሃኒቱ ኃይል መደንዘዝ ሳይችሉ ቀርተው ህመሙ እየተሰማቸው ህክምናው ከሚደረግላቸው ጀምሮ ከሰመመን መድሃኒቱ በቶሎ መንቃት አቅቷቸው ለሰዓታት ራሳቸውን ስተው እስከሚቆዩት ድረስ በርካታ ህሙማንን አግኝቷል፡፡ አቶ ክብረት በዚህ የአስራ የአንስቴቲስትነት ሙያው ገና ከተወለደ ህፃን ልጅ ጀምሮ 100 ዓመት እስከሆናቸው አዛውንት ድረስ አስተናግዷል፡፡ በተለይ በህፃናት የማደንዘዣ መድሃኒት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄና ትኩረት መደረግ እንዳለበት የሚናገረው አቶ ክብረት፤ በአንድ ወቅት ሣንቲም በመዋጡ ምክንያት የመተንፈሻ አካሉ ተዘግቶ ወደ ሆስፒታሉ መጥቶ የነበረውን ህፃን ታሪክ ያስታውሳል፡፡ ህፃኑ የዋጠው ሳንቲም በአየር ማስተላለፊያ ቱቦው ላይ በማረፍና ቱቦውን በመዝጋቱ ምክንያት የአየር እጥረት አጋጥሞት ነበር፡፡ ለህፃኑ ተገቢውን የሰመመን መድሃኒት ይሰጠውና ሐኪሙ ወደ ህፃኑ ጉሮሮ ውስጥ መሣሪያ በማስገባት ሳንቲሙን በቀላሉ ከህፃኑ ጉሮሮ ላይ ያወጣዋል፡፡ እንደ ህክምና ሙያ ሥርዓትና ደንብ መሠረት፣ ከህፃኑ ጉሮሮ ላይ የወጣው ሳንቲም ለህፃኑ ቤተሰብ ተሰጠ፡፡ ሆኖም ህፃኑ ከኦፕሬሽን ክፍሉ መውጣት አልቻለም፡፡ ምክንያቱም በህፃኑ የአየር መተላለፊያ ቱቦ ላይ ተቀምጦ የነበረው ሣንቲም የአየር ማስተላለፊያ ቱቦው እንዲያብጥ በማድረጉና ህፃኑ መተንፈስ እንዳይችል ቱቦው ተዘግቶ በመቅረቱ ነበር፡፡ ሐኪሙ ከእሱ የሚጠበቀውን አከናውኖ ከክፍሉ ቢወጣም ህፃኑ ባለመውጣቱ ቤተሰቦቹ ግር አላቸው፡፡ ቆየት ብሎም ግርታው ቁጣ አስከተለ፡፡ ሐኪሙ ህክምናውን በአግባቡ አከናውኗል፡፡ ከዚህ በኋላ ያለው ጉዳይ የሰመመን ሰጪ ባለሙያው ነው፡፡ ህፃኑ ቢሞትም የገደለው እሱ ነው ብለው ቤተሰቦቹ የአቶ ክብረትን ከክፍሉ መውጣት በቁጣ መጠባበቅ ያዙ፡፡ ሁኔታው ከበድ ያለ ሲመስለው አቶ ክብረት ዶክተሩን ያስጠራዋል፡፡ የህፃኑን ህይወት ለመታደግ ሙያው የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ሁሉ በመክፈል ላይ ያለ መሆኑን የተገነዘበው ሐኪሙም፤ ስለሁኔታው ለህፃኑ ቤተሰቦች ማስረዳት ጀመረ፡፡ ጉዳዩ ባይዋጥላቸውም የልጃቸውን የመጨረሻ እጣ ለመጠበቅ ዝምታን መረጡ፡፡ ከሰዓታት በኋላ የልጁ ትንፋሽ ሲመለስ ህፃኑን ጥብቅ ክትትል ወደሚሰጥበት ክፍል በማዛወር በከፍተኛ ክትትልና ጥበቃ ወደ ትክክለኛ የአተነፋፈስ ስርዓቱ እንዲመለስ በማድረግ የቀድሞውን ጤናማ ህፃን መልሶ ለቤተሰቦቹ ለማስረከብ ቻለ፡፡ ከህፃናት ጋር በተያያዘ አቶ ክብረት ሌላ ገጠመኝም አለው፡፡ ህፃኑ ከቤተሰቦቹ ጋር ምሽቱን ከአሜሪካ አዲስ አበባ ገባ፡፡ ጉዞ ያደከማት እናት ጡቷን ለህፃን ልጇ እንዳጐረሰች እንቅልፍ ሸለብ ያደርጋታል፡፡ ስትነቃ በአንገቷ ላይ ያደረገችው ሃብል ተበጥሶ መስቀሉ የልጇ ጉሮሮ ውስጥ መሰንቀሩ አወቀች፡፡ ልጇ ትንፋሽ አጥቶ ሲቃትት በከፍተኛ ድንጋጤ ተውጣ ልጇን ይዛ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በረረች፡፡ የህፃኑ ትንፋሽ ከደቂቃ ደቂቃ እየደከመ፣ የሰውነቱ ቀለም እየጠቆረ ሄደ፡፡ ወደ ቀዶ ጥገና ክፍል ሲገባ ህፃኑ በህይወት ይመለሳል ብሎ ያሰበ አልነበረም፡፡ በቀላል የሰመመን መድሃኒት ህፃኑ ራሱን እንዲስት ተደርጐ ሐኪሙ መስቀሉን ከህፃኑ ጉሮሮ ውስጥ በቀላሉ ፈልቅቆ አወጣው፡፡ በአስገራሚ ፍጥነት የልጁ ሰውነት ወደ ቀድሞው ቀለሙ እየተቀየረ መጣ፡፡ የህፃኑም ቤተሰቦች ሆኑ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ሁኔታውን ለማመን አስቸግሯቸው ነበር፡፡


Published in ዋናው ጤና

በገና በዓል ዋዜማ ወደተለያዩ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ ባንክ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች … የሄዱ ሰዎች በዋናው መግቢያ በር ወይም በእንግዳ መቀበያ ክፍል ቀልባቸውን የሳበና በተለያየ አንፀባራቂ ነገሮች የተጌጠ የገና ዛፍ ስለማየታቸው በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ወቅትን ጠብቀው የልብስ አሰቃቀላቸውን የሚያሳምሩት ቡቲኮችም የገና አባትን ልብስ ሰቅለው በብዛት ታይተዋል፡፡ በመስቀለኛ መንገዶች ቀይ መብራት ያስቆማቸው መኪኖች ስር እየተሽለኮለኩ "የአባባ ገና"ን ልብስ ለብለው ተመሳሳዩን ግዙን የሚሉ ወጣቶችም ቁጥራቸው ጥቂት የሚባል አልነበረም፡፡
ባለፈው ሳምንት ባየው ነገር የተገረመ አንድ የሥራ ባልደረባዬ ትዝብቱን የገለፀው "አባባ ገና እማማ ገናን እየጨቆናት ነው" በሚል ነበር፡፡
ድንቅ ነው፣ ልዩ ነው፣ በሌሎች ዘንድ አይገኙም … የሚባሉትና ኢትዮጵያዊ መልክ ካላቸው የበዓል አከባበሮች መካከል አንዱ የገና በዓል ነበር፡፡ በአዲስ አበባና በአንዳንድ ከተሞች የሚታየው ጅማሬ መላ አገሪቱን ይወክላል ማለቱ ቢከብድም በመዲናችን እየታየ ያለው የገና በዓል አከባበር ግን "አባባ ገና" ያሳደረብን ተጽዕኖ ከባድ መሆኑን ጠቃሚ ነው፡፡
በተቃራኒው ደግሞ ዛሬ የምናከብረው የጥምቀት በዓል አገራዊ የአከባበር መልክና ሥርዓቱን እንደያዘ አሁን ላይ ከመድረሱም ባሻገር በተለይ የብሔር ብሔረሰብ አልባሳትን በመልበስ ወጣቶች በማንነታቸው እንደሚኮሩ ማሳያ መድረክ እየሆነም መጥቷል፡፡ ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ እንደታየው በየጥምቀተ ባህሩ በተለያዩ ብሔረሰቦች ባህላዊ አልባሳትና የፀጉር አሰራር አጊጠው ለበዓሉ ተጨማሪ ድምቀት እየፈጠሩ ያሉ ወጣቶች ቁጥር እየተበራከተ መጥቷል፡፡
በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ በሚከበሩት በሁለቱ በዓላት ውስጥ የሚታየው እውነት በተቀላቀለ መስመር ላይ መሆናችንን ያሳያል፡፡
በአንድ በኩል በማንነት መኩራትና ማንነትን የማስጠበቅ ተግባር ሲታይ፤ በሌላ ጎን የራስን ጥሎ የሌላውን የማንሳት ፍላጎት ይንፀባረቃል፡፡
በተቀላቀሉት ነገሮች ውስጥ ባለው ትግል ማንኛው ያሸንፋል? አሸናፊው ምን ጠቃሚ ነገር ያስገኝልናል? የሚያስከትልብን ጉዳትስ ምንድነው? በትግሉ ተሸንፎ ከሚጠፋውስ ምን ጠቃሚና መልካም ነገርን እናጣለን? የሚሉ ጥያቄዎች ያስነሳሉ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶች፣ የህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የሰራውን ጥናት ሰሞኑን ይፋ አድርጓል፡፡ "መጤ ባህሎችና ልማዳዊ ድርጊቶች በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በተለይም፤ በወጣቶችና ሴቶች ላይ እያስከተለ ያለው አሉታዊ ተፅዕኖ" በሚል ርዕስ በቀረበው ጥናት ላይ የመገናኛ ብዙኃንና የኪነጥበብ ባለሙያዎች ለሁለት ቀናት እንዲወያዩበት ተደርጓል፡፡
ጥር 3 ቀን 2005 ዓ.ም በራስ ሆቴል በተሰናዳው መድረክ ላይ የጥናቱ ባለቤትና በሥራው የተሳተፉ ባለሙያዎች ስለ ባህልና ልማድ ምንነት፤ መጤ ልማድና ባህሎች በማህበራዊ፣ ስነልቦናዊ፣ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ስለሚያስከትሉት አደጋ፤ለመጤ ድርጊቶች መስፋፋት ግሎባላይዜሽን፤መገናኛ ብዙኃንና የመረጃ መረቦች ስላላቸው አስተዋጽኦ፤በተለያየ አተገባበር ተፈፃሚ የሚሆኑት መጤ ልማድና ባህሎች በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ እየታየ እንዳለና ችግሩን ለመከላከል ያሉት ዕድልና አማራጮች ምን እንደሆኑ ባለሙያዎቹ ማብራርያ ሰጥተውበታል፡፡
መጤ ባህልና ልማዶች በአዲስ አበባ ከተማ ከመስፋፋቱ ጋር በተያያዙ ሱስ አስያዥ ዕፅ ተጠቃሚው መበራከቱን፣የቀንና የምሽት የራቁት ጭፈራ ቤቶች መብዛታቸውን፣ ግብረሰዶማዊነት መስፋፋቱን፣ "እኔን ይመቸኝ እንጂ ለሌላው ግድ የለኝም" የሚል የግለኝነት ስሜት እየጨመረ መምጣቱንና ሌሎች መሰል ችግሮች ዙሪያ ገለፃ ከተሰጠ በኋላ መድረኩ ለአስተያየትና ጥያቄ ክፍት ሆነ፡፡
"ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ" የሚለውን ብሂል አስቀድመው አስተያየት መስጠት የጀመሩት የማስታወቂያ ባለሙያው አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ ነበሩ፡፡ የግብረ ገብ ትምህርት መቋረጡ ለችግሮቹ መከሰት አንድ ምክንያት መሆኑን የጠቀሱት አቶ ውብሸት፣ብዙ ዜጎቻችን የኤችአይቪ/ኤድስ ሰለባ ከሆኑ በኋላ ጥናቱ ተሰርቶ የቀረበው መንግሥት ወይም የሚመለከታቸው አካላት የት ከርመው ነው? የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡
በጥናቱ ወረቀት የቀረበው ቀደም ብለን እንሰማው የነበረን ጉዳይ ነው ያሉት አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ፣የነገ አገር ተረካቢ ወጣት ትውልድን ለመታደግ እንዲህ ዓይነት ጥናት፣ የተግባር እንቅስቃሴና እሳት የማጥፋት ሥራ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ናዝሬት፣ ሐዋሳ፣
ባህርዳርና በመሳሰሉት ከተሞችም በአፋጣኝ ተግባራዊ እንዲሆኑ አሳስበዋል፡፡
"ለችግሩ መፍትሔ የሚሰጥልን ማነው ብለን በተጨነቅንበት ሰዓት፤ የዘገየ ቢሆንም ይህ ጥናት መሰራቱ አስደሳች ነው" በማለት ንግግር የጀመረው ደግሞ ጋዜጠኛ በፍቃዱ አባይ ነው፡፡
"ማርፈድን ባላበረታታም ከመቅረት ማርፈድ ይሻላል" እንደሚባለው ዘግይቶ የቀረበው ጥናት፣ ሕብረተሰባችን እየተፈራራ እንዲሄድ ያደረጉትን ችግሮች ይቀርፉለታል" በሚል ምሳሌዎችን ሲያቀርብ "ዛሬ ጋብቻ ለመመሥረት ፍርሐት ላይ ባንወድቅም ልጅ መውለድ ግን የብዙዎች ፍርሐት ሆኗል፡፡ በቀድሞ ዘመን ልጅን ለጎረቤት በአደራ ሰጥቶ የመሄድ መልካም ባህል ነበር፡፡
ዛሬ ልጄን ጠብቅልኝ ብሎ ለጎረቤት የሚሰጥ ሰው ካለ፣ልጄ ምንም ሳይሆን መልሼ አገኘሁ ይሆን? ከሚል ፍርሃትና ስጋት ጋር ነው፡፡"
የመንግሥት መዋቅርና የልማት አካሄድ ሰውን ትኩረት ያደረገ አይመስልም ያለው ጋዜጠኛው፤ መገናኛ ብዙኃን የሕብረተሰቡን የእኔነት ስሜት ሲገድሉ ይታያል፡፡ ማንቼና አርሴ ለእኛ ሕብረተሰብ ምንድን ናቸው? ሲልም ጠይቋል፡፡ ሕብረተሰቡ ማንነቱን እንዲያጣ የከበቡት ችግሮች በጥናት ወረቀት ከቀረበውም በላይ ሰፊና ጥልቅ ነው ያለው ጋዜጠኛ በፍቃዱ፣ ተተርጉመው እየቀረቡልን ያሉት የፍልስፍና መፃሕፍት አስተሳሰባችንን እያናጉትና ብዙዎችን የትም ወድቀው እንዲቀሩ እያደረጉ መሆኑን ገልጿል፡፡
የመፃሕፍት የፊት ገፅ ሽፋን የሴቶችን እርቃን ገላ የሚያሳይ መሆኑ፣ ስለ መሳሳም ጥበብ፤ ሴትን በፍቅር ስለማንበርከክ፤ የወንዶችን ትኩረት ስለመሳብ ችሎታ … በሚል የሚቀርቡት መፃሕፍትም የከበበን አደጋ አንዱ ማሳያ ናቸው ያለው ጋዜጠኛው፣ "ሕብረተሰቡ ይሄ የእኔ ጉዳይ አይደለም ብሎ ራሱን እስኪከላከል ድረስ የሚጠብቀው ያስፈልገዋል" ብሏል፡፡ የማስታወቂያ ባለሙያው አቶ ተስፋዬ ማሞ በበኩሉ፣ በኑሮ አስገዳጅነት ብዙ ወላጆች በቀን ከ12 ሰዓት በላይ በሥራ ላይ ከመቆየታቸው ጋር በተያያዘ የወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የመገናኘት ዕድል እየጠበበ መምጣቱን የራሱን ገጠመኝ ሲያቀርብ "በሳምንቱ ውስጥ ልጆቼን የማገኝበት ጊዜ ስደምረው ከ20 ሰዓት እንዳማይበልጥ አስተውያለሁ" ካለ በኋላ ትውልዱ ልዩ ጥበቃ እንደሚያስፈልገው ጠቁሟል፡፡
ካፒታሊዝም ሁሉንም ነገር እየሸጠ ሁሉንም ነገር የሚያጠፋ ሥርዓት ነው ያለው አቶ ተስፋዬ፣ በስመ ኢንተርናሽናል ሥም በከተማችን እየተስፋፉ የመጡት ትምህርት ቤቶች አንዱ የችግር ምንጭ ሆነዋል ብሏል፡፡ ለዚህ ችግር ከመንግሥት ባልተናነሰ ማህበራዊ ኃላፊነትን መሸከም የሚችል የኪነ ጥበብና የመገናኛ ብዙኃን ያስፈልጋል፡፡ ሕብረተሰብ ተለይቶ የማይታወቅ ነገር ስለሆነ የወላጆች ካውንስል በአገር አቀፍ ደረጃ በማቋቋም መንግሥት ሕጉ እያለ ማህበረሰቡን መከላከል ያልቻለበትን ምክንያት መሞገት ይኖርባቸዋል ብሏል፡፡
"የተበላሸው ነገር ብዙ ነው፡፡ ያልተበላሸው ነገራችንን ለማዳን ብንሰራ የሚል ሀሳብ አለኝ" ያለችው የኢትዮጵያ ሴት ደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ የምወድሽ ስዩም በበኩሏ፣ በዚህ ዓላማ መሰረት እሷ የምትመራው ማህበር ስላከናወናቸው ተግባራት፤ በተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳይና ገጠመኞቿ ዙሪያ እርሷም በግሏ ስላከናወነቻቸው ተግባራት ማብራሪያ ከሰጠች በኋላ፣ ስለ ኒውዮርክ ያቀረበችው ምሳሌ እኛስ ወዴት እየሄድን ነው? የሚያስብል ነው፡፡ "ኒውዮርክ በዓለማችን ትንሿ የሲኦል ምሳሌ ናት፡፡ አገሪቱ እናትና ልጅ ባል የሚቀማሙባት በመሆኗ ክስተቱ የውይይት ርዕሰ ነገር ሆኖ በቶክ ሾው ይቀርባል፡፡ ባል ሴት ፍለጋ፣ ሚስት ወንድ ፍለጋ አገልግሎቱን ወደሚሰጡ ተቋማት በሄዱበት ይገናኛሉ፡፡ በእኛስ አገር አሁን የሚታየው ጅማሬ በዚያ ደረጃ አያድግም ወይ?" ብላለች - የምወድሽ፡፡
አርቲስት ፈለቀ ጣሴ በበኩሉ፣ "ከጥቂት ዓመታት በፊት በትምህርት ቤቶች ግቢ መኖሪያ ቤት ያላቸው ሰዎች ጠላ ንግድ መጀመራቸው አነጋጋሪ ነበር። ዛሬ የዕፀ-ፋሪስ ተጠቃሚዎች መበራከት መነጋገሪያ ሆኗል፡፡
የዛሬ 20 ዓመትም በአዲስ አበባ ከተማ የእርቃን ዳንስ ቤቶች ነበሩ፡፡ልዩነቱ አሁን ተበራክተዋል፡፡

በጥናት ከቀረበው በላይ የግል ሚዲያዎች በችግሩ ዙሪያ በስፋት ሰርተዋል፡፡ ከእናንተም በተሻለ እነሱ መረጃው አላቸው፡፡ ዕፀፋሪስ በመርፌ የሚወሰድባቸው አካባቢዎች አሉ። የእናንተ ጥናት ይህንን የደረሰበት አይመስልም፡፡ በጥናታችሁ የተቀመጠው የሱስ አስያዥ ስሞችና የመሸጫ ዋጋ አሁን በከተማው ካለው ጋር በጣም ይለያያል። ከዚህ ችግር ጋር በተያያዘ በተለያየ ጊዜ ሕግና መመሪያዎች ወጥተዋል። ሕጉ ግን ችግሩን ሲቀርፍ ሳይሆን ሕግ አስፈፃሚዎችን ሲጠቅም ነው የታየው" ብሏል፡፡
ከፊልም ሰሪዎች ማህበር የመጡት አቶ ደሳለኝ ኃይሉ፣የዓለም ኀያላን መንግሥታት ዛሬ በኢኮኖሚ ያልበለፀጉ አገራትን የሚወሩት እንደ ቀድሞ ዘመን ጦር በማዝመት ሳይሆን በቴክኖሎጂ ውጤቶች መሆኑን እንደማሳያ ያቀረበው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን መመልከት ትቶ ወደ ዲሽ ስርጭቶች ትኩረት ያደረገውን ሰው ብዛት በመጥቀስ ነው። ስለዚህ የመንግሥት ትኩረትም ሆነ ልማት ሰውን ማዕከል ያደረገ መሆን አለበት ሲል አስተያየቱን አቅርቧል፡፡ ጥናቱን ያሰራውና መድረኩን ያሰናዳው ቢሮ፤ችግሮቹን ለመቅረፍ ከማንም በተሻለ የኪነጥበብና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ትልቅ ሚናና ድርሻ ይኖራቸዋል በሚል እምነት መድረኩን ማሰናዳታቸውን በማጠቃለያቸው አስምረውበታል - አቶ ደሳለኝ፡፡ ደራሲና ጋዜጠኛ የምወድሽ ስዩም "የተበላሸውን ለማስተካከል ያልተበላሸውን እንጠብቅ" እንዳለችው በእጅ ያለውን ወርቅ ማክበር በኋላ ከመቆጨት ያድናል፡፡
አባባ ገና ጭቆና የደረሰባት እማማ ገናን ነፃ ለማውጣት ብዙ ሥራ ይጠይቃል፡፡ የአባባ ጥምቀት ጭቆና ያላረፈባት እማማ ጥምቀትን መጠበቅ ግን ያን ያህል ከባድ አይደለም፡፡ በየጥምቀተ ባህሩ በብሔር ብሔረሰብ ልብሶቻቸው ተውበው የሚመጡትን ወጣቶች ማድነቅ ተገቢ የሚሆነውም ለዚህ ነው፡፡ መልካም የጥምቀት በዓል!

Published in ባህል
Saturday, 19 January 2013 14:36

“አይ አም ኤ ታክስ ፔየር…”

እንዴት ሰነበታችሁሳ! እንኳን ለብርሀነ ጥምቀቱና ለነቢዩ መሀመድ የልደት በዓላት በሰላም አደረሳቸሁማ! ስሙኝማ…ይሄ የአገልግሎት አሰጣጥ ነገር ግራ እያጋባ አይመስላችሁም! አንድ ሰሞን እንደዛ ሰዉ ሁሉ 'እንዳልሾረ' አሁን ነገርዬው ሁሉ ባለቤት የሌለው እየመሰለ ነው፡፡ "ደንበኞች አቤቱታ እንዳያቀርቡብኝ…" ብሎ ስጋት እየቀረ ነገርየው "እና ምን ይጠበስ!" እየሆነ ያለ ነው የሚመስለው፡፡ ስሙኝማ…ይሄ ሥራዎች ሁሉ በዘመቻ ወይም እንደ ሰሞኑ 'ኤሌክሽን' ምናምን ሲመጣ ብቻ ትኩረት የመስጠት ነገር…አለ አይደል…ባህል እየሆነ የመጣ ይመስላል፡፡ እኔ የምለው…አለቃ ምናምንን ሳይሆን ሥራ የሚከበርበት ዘመን አይናፍቃችሁም! ሳትለምኑ፣ ሳትለማመጡ፣ "እባክህ፣ እንትን መሥሪያ ቤት የምታውቀው ሰው ይኖራል?" ሳትባባሉ ጉዳያችሁ በዘመቻ ሳይሆን በቋሚነት የሚፈጸመበት ዘመን አይናፍቃችሁም! "ከከሰስክ ሁሉም አድመውብህ አበሳሀን ያሳዩሃል…" መባባላችን አክትሞ በ'ኮንፊደንስ' "እየጠየቅሁ ያለሁት የማይገባኝን ሳይሆን መብቴን ነው…" የምንልበት ዘመን አይናፍቃችሁም! ነገሮች ለተወሰኑ ወራት ብልጭ ካሉ በኋላ በዛው ድርግም ብለው የሚጠፉበት የ'እንቁልልጭ' ነገር ቀርቶ ሥራዎች በቋሚነት የሚቀጥሉበት ዘመን አይናፍቃችሁም! መአት ነገር መደርደር ይቻላል፡፡"ሄደህ ክሰስና ምን እንደምታመጣ አያለሁ!" የሚል የበታች ሠራተኛ ድፍረት "ከጀርባው ምን አቃፊ፣ ደጋፊ ቢኖረው ነው!" ያሰኛችኋል፡፡ (ጥያቄ አለን… የድሮዎቹ 'የለውጥ ሀዋርያት' አይነት የሲ.ፒ.ኤ. ፕሳ እና ጽሂ መዝገቦች የማያውቃቸው 'የሥራ ሀላፊነቶች' ያሏቸው ሰዎች አሉ እንዴ! አሀ…እቅጩ ይነገረንና… አለ አይደል… ከእነማን ጋር 'ቦሶቻችንን' ከእግር ጥፍር እስከ ራስ ጸጉር (የራስ ጸጉር ባለበት ቦታ ብቻ የሚሠራ! ቂ…ቂ…ቂ…) ማማት እንደምንችል፣ እነማን ሲመጡ ወሬያችንን ወደ አርሴና ማንቼ 'መለወጥ' እንዳለብን እንወቃ! እና…ይሄ አገልግሎት አሰጣጥ ነገር…አለ አይደል… 'ከርሞ ጥጃ' ነገር እየሆነ ግራ እየገባን ነው፡፡ ሌላው ችግር ምን መሰላችሁ…"ለአለቃህ እነግራለሁ…" "ለበላይ ሄጄ አመለክታለሁ…" ምናምን ማለት እንኳን እየጠፋን ነው፡፡ "ጭራሽ ይዘጉብንና ጭራሽ ስንንከራተት እንኖራለን…" ብለን እንፈራለና! ደግሞም እንዲሀ አይነት ነገር እንክት አድርጎ ይሆናል፡፡ ልጄ… ፈሪ ይኑር፣ ፈሪ ይኑር ቢሻው አተላ መሸከም ይወዳል ትከሻው፣ ምናምን ግጥም ድሮ ቀርቷል፡፡ ልክ ነዋ…መፍራት የወኔ ጉዳይ ሳይሆን የ'ስትራቴጂ' ጉዳይ ነው፡፡ እግረ መንገድ ግን በዚህ ሁሉ መሀል… አለ አይደል… በተሰማሩበት ቦታ የሚፈልግባቸውን አገልግሎት የሚሰጡ መአት ሠራተኞቸ አሉ፡፡ ከኑግ ጋር ሰሊጡን አብሮ መውቀጥ አሪፍ አይደለም፡ ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ሰውየው የሆነ የገንዘብ ተቋም በኃላፊነት ደረጃ የሚሠሩ ነበሩ አሉ፡፡ እናላችሁ… የዛ "ምን ጊዜ ተጩሆ ምን ጊዜ ደረሱ…" የሚባልበት ዘመን ሰው ሆነውላችሁ ዕድሜ ያቺን ስሜት ገና አላበረደውም፡፡ ታዲያማ…አንድ ቀን በሚሠሩበት ቦታ የሆነ ደንበኛ ጭቅጭቅ ቢጤ ይፈጥራል፡፡ እሳቸውም ከቢሯቸው ባላቸው አቅም ሊያግባቡት ይሞክራሉ፡፡ ሰውየው ጉዳዩ ከተጠናቀቀለት በኋላ ሁሉ 'እላፊ‚ ነገሮች መናገር ይቀጥላል፡፡ እና…እንግዲህ 'ሲሉ ሰምተን' የምንላቸው ነገሮች አሉ አይደል… "ዘ ከስተመር ኢዝ ዘ ኪንግ…" ይልና እሳቸውን እንደ መገፍተር ይሞክራል፡፡ ይሄን ጊዜ "መገን የአራዳ ልጅ እነ ድንጋይ ኳሱ…" ቢጤ ነገር ብልጭ ትልባቸውና "ሰምታይምስ ስታፍ ኢዝ ዘ ኪንግ… " ይሉና በውቤ በረሀ 'አፐር ከት' ይዘርሩታል፡፡ እናላችሁ… በአለቆቻቸው ይጠሩና ምንም ነገር ቢገጥም ለበላይ ማሳወቅ እንጂ በራሳቸው ምንም እርምጃ መውሰድ እንደሌለባቸው ሲነገራቸው ምን አሉ መሰላችሁ… "ደንበኛ ስለመታኝ መልሼ እንድመታው እንዲፈቀድልኝ እጠይቃለሁ ብዬ ማመልከቻ ላስገባ ነው?" አሉላችሁ፡፡ እናማ…አገልግሎት ሰጪ እንዲህ 'ጭራ እንደሚያስበቅሉ'… ሁሉ እኛ ተገልጋዮችም ቀዩን መስመር የምናልፍበት ጊዜዎች መአት ናቸው፡፡

እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…በቅርቡ ነው አሉ፡፡ በአንድ ገንዘብ ምናምን በሚሰበስብ መሥሪያ ቤት አንድ ደንበኛና አገልግሎት ሰጪ ሠራተኛ በሆነ ጉዳይ ሳይግባቡ ቀርተው አንድ ሁለት ይባባላሉ፡፡ ሠራተኛው ይበልጥ ትህትና ነበረው አሉ፡፡ እናማ ሰውየው…አሁንም 'ሲሉ ሰምተን' እንደሚባለው… "አይ አም ኤ ታክስ ፔየር" ("ግብሬን የምከፍል ሰው ነኝ…" የማለት አይነት…) ይልላችኋል፡፡ ይሄኔ ሠራተኛው ምን አለ አለመሰላችሁ… "ታዲያ ምን አባክ ላድርግህ!" ቂ…ቂ…ቂ… ልጄ አገሪቱ የእኛዋ ጦቢያ፣ ሰዎቹም እኛዎቹ ጦቢያኖች ነና! (ኩረጃ የሚሠራው ለ'ቫለንታይን ዴይ' ብቻ ነው እንዴ!) እናላችሁ…የራፕ ምትን ከአንቺ ሆዬ ጋር 'ለመደባለቅ'፣ ካልጠፋ ምትክ ትራንስፎርሜሽን፣ ቢ.ኤስ.ሲ. ምናምን የሚሉ ቃላትን ለመጠቀም፣ ለ'ታንስክ ጊቪንግ ዴይ' ልዩ የኤፍ.ኤም. ፕሮግራም ለማዘጋጀት… ምናምን እንጂ ለአቅመ "ዘ ከስተመር ኢዝ ዘ ኪንግ…" "አይ አም ኤ ታክስ ፔየር" ገና የደረስን አይመስልም፡፡ አሀ…እነኚህ ነገሮች ከመብት መከበርና ማስከበር ጋር የተያያዙ ናቸዋ! መብት ለማስከበር መለኪያዎቹ ፈራንካ ወይም ትልቅ የቆዳ ወንበር ወይም የ'እንትና ዘመድነት' የማያስፈግበት ዘመን ይምጣልንማ! እኔ የምለው… ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የፈራንካን ነገር ካነሳን አይቀር፣ የዚህ አገር 'ሀብታምነት' የማሳያ መንገዶች የሚገርሙ እየሆኑ ነው፡፡ የምር…ሀብታምነትን የማሳያ ፉክክሮች…አለ አይደል…አፈ ታሪክ አይነት ሊመስሉ ምንም አልቀራቸው፡፡

አንድ ወዳጄ የነገረኝን ስሙኝማ… እዚሁ ከተማ አንድ ውስኪ ቤት ነው አሉ፡፡ እናላችሁ… አንዱ ሀብታም የውስኪ ቤቱ ባለቤትየዋ ላይ…የቀረ የአራዳ አባባል ለመጥቀስ… 'ጆፌ ጥሏል'፡፡ ታዲያላችሁ…አንድ ማታ ጓደኞችን ይዞ ሲገባ እሷዬዋን ሌሎች እነ ሬሚ ማርቲንን ምናምን ጠርሙሶች የደረደሩ ሰዎች ከበዋታል፡፡ (ለጣይ ፈንጋይ እንደሚያዝለት ሁሉ ለሀብታምም ሀብታም ያዝለታል መሰለኝ፡፡ቂ…ቂ…ቂ…) እናማ…ምልክት ቢሰጣት ከአንገት ሰላምታ በላይ ካለችበት ንቅንቅ ስላላለች ይበሽቃል፡፡ ታዲያላችሁ…እሱም ጎርደን ጂን ጠርሙስ ያወርድና ሴትዮዋን ይጠራታል፡፡ ይሄኔ ሴትዮዋ ትመጣለች፡፡ እሱም መጀመሪያ አንዱ ጓደኛውን "የት አገር ነው ያለነው?" አይነት የሦስተኛ ዲቪዥን ጉራ ነገር ጣል ያደርግላችሁና ምን ያደርጋል…ከኪሶቹ የኢትዮዽያ ብር፣ ዶላር፣ ዩሮና ፓውንድ አውጥቶ ይደረድርና ለሴትየዋ ምን ቢላት ጥሩ…"የአገርሽን ገንዘብ መርጠሽ ውሰጂ!" አዎ…እዚቹ ከተማ ውስጥ ነው እንዲሀ አይነት ነገር የሚደረገው! በነገራችን ላይ በመጨረሻ በጨረታው አሸነፈ አሉ፡፡ የገንዘብ ነገር ካነሳን አይቀር፣ ይቺን ስሙኝማ…ሰበሰብ ብለው ሳለ ከመሀላቸው አንዱ ምን ይላል… "እዚህ አካባቢ በላስቲክ የታሰረ ብር የጠፋው አለ?" ብሎ ሲጠይቅ አንደኛው ተጣድፎ "እኔ ጠፍቶኛል…" ይላል፡፡

ሰውየው ምን ቢለው ጥሩ ነው… "እንግዲያውስ ብሩ ታስሮበት የነበረውን ላስቲክ አግኝቼልሃለሁ፡፡" ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ይሄ የኳሳችን ነገር… አንድዬ ከአጠገባችን አይለየንማ፡፡ (እግረ መንገዴን ሳላነሳ እንዳላልፍ…አንዳንዴ ከሰሞኑ ኳስ ጋር የተያያዙ ዘገባዎችንና ዝግጅቶችን ስንሰማና ስናይ "ይሄ ኳስ የአፍሪካ ዋንጫ ጉዳይ ብቻ ነው ወይስ ሌላ ነገር አለው?" አይነት ጥያቄዎች ይመጡብን እንደነበር ይመዝገብልንማ! አንዳንዶቻችንም ሲቪያችንን ለማድለቢያ እንደ ምቹ ነገር የቆጠርነው ያስመስልብን እንደነበር ልብ ይባልማ!) እናማ… ልጆቹ የአቅማቸውን ተጫውተው የፈለገ ውጤት ቢመጣ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል ማለት ነው፣ አለቀ፡፡ ልኩን ያላለፈና እውነታውን ያገናዘበ በራስ መተማመንም አሪፍ ነው፡፡ (ከሽልማቱ ጋር የአንዳንድ ሰዎቻችን የቃለ መጠይቆች ቋንቋ እየተለወጠ የ'ኦቨርኮንፊደንስ ቃና' ሰማሁ ልበል!) እናማ…የኳስ ነገር የኳስ ነገር ነውና…አለ አይደል… ለእኔ ለአምደኚስት ተብዬው (ቂ…ቂ…ቂ…) በአንደኛ ዙር የመሰናበትም ሆነ ለዋንጫ የመድረስ ዕድሎች እኩል ናቸው፡፡

ልጆቹን የእኛ ጸሎትና የአንድዬ እርዳታ አይለያቸውማ! እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ቬንገር የኢትዮዽያን ስም በሁለት አረፍተ ነገር አንድ ሁለቴ ጠቀሱ ተብሎ እንደ 'ሰበር ዜና' ሲደጋገም የነበረው ነገር ግርም አይላችሁም! እና ምን ይሁን! የኳስ አሰልጣኝ ናቸው፣ ስለ ኳስ ያወራሉ፣ እናም ስለ አፍሪካ ዋንጫ ሲያወሩ እኛም ተሳታፊዎች ስለሆንን ስማችንን መጥቀሳቸው "ከኢትዮዽያ አምስት ተጫዋቾች ለአርሴናል ላስፈርም ነው…" ያሉ ይመሰል ይሄን ያህል ሽፋን ማግኘቱ ግርም ይላል፡፡ በነገራችን ላይ ቬንገር እኛን የጠቀሱበትን 'መንፈስ'…አለ አይደል… 'ቢትዊን ዘ ላይንስ' በሚሉት አይነት ጠለቅ ብሎ ማየቱ ጥሩ ነበር፡፡እናማ…ለአቅመ "ዘ ከስተመር ኢዝ ዘ ኪንግ…" "አይ አም ኤ ታክስ ፔየር" ያብቃንማ! በድጋሚ ለኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞችና ለመላው ሙስሊሞች መልካም የበዓላት ሰሞን ይሁንላችሁማ! ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ህብረተሰብ
Saturday, 19 January 2013 14:31

ለምን ይዋሻል? በስመ-ልደቱ

ነገር ዜሮ፣ እንደ ተለመደው በዓለ-ገናው ሰበብ ሆነልኝና ርቄያት ወደ ከረምኩት ዋናይቱ ከተማ አዲስ አበባ ከተፍ አልኩኝ (ከስራ አድራሻዬ ከተራራማይቱ ገጠራማ ቀበሌ ከየተቦን) እንዲህ ከረም እያልኩ ብቅ ስል መዲናይቱም የግንባታ ብቅል አበቃቅላ ታስገርመኛለች፡፡ እደጊ ሸገር እደጊ፡፡ ‹‹እደጊ ግን ደግሞ ሰውም በመልካም የሚያድግብሽ ከተማ ያድርግሽ›› ማለቴም የተለመደ ነው፡፡ታዲያ መዲናይቱን የተራራቅኳትን ያህል አዲስ አድማስ ጋዜጣንም እንዲሁ ተራርቂያት መክረሜ ገራሚ የሚሆን አይመስለኝም፡፡

ታዲያ አውደ-ገናው ግድ ብሎኝ ወደ መዲናይቱ አዲስ አበባ ብቅ ስል፣ቀነ- ቅዳሜ በሆነ አዚምኛ ሰበብ ስልብ ብላ ከእጄ ካላፈተለከች በቀር፣‹‹የቅዳሜ ውበት›› የምትመስለኝ አዲስ አድማስ ጋዜጣ እንድታመልጠኝ አልሻም፡፡ እናም በዚህ ሳምንት ‹‹ተወዳጅ ናት›› የምላት ጋዜጣ በእጄ ገባች፡፡ ገና አንድ ገፅ ስገልጥ ‹‹ታህሳስ የበርካታ ዓማልክት የልደት ቀን›› በሚል የገደፈ ርዕስ፣ ግድፈታምነቱ የጠነነ የገናውን በዓል ተተግኖ የተዘለጎሰ መጣጥፍ ገጠመኝ፡፡ ርዕሱ የታህሳስን ‹‹ወር››ነት ዘንግቶ ‹‹ቀን›› እያለ መጮሁ ሲደንቀኝ፣ የ‹‹ቅጥፈቱንም›› የ‹‹ልኩንም›› አማልክት መደበላላቁ መፈናፈኛ ያሳጣኝን የጊዜ ጉልበት ተገዳድሬ ብዕር እወድር ዘንድ ግድ አለኝ፡፡ ይሄ መጣጥፍ እውነተኛውን ‹‹ባለ ልደት›› ከሃሰተኞቹ ልደተኞች ጋር ቀያይጦ ከማላቆጡ ብዛት፣ለየዋህ ታዳሚ መነሾ እሳቤው ስለ ዓመት በዓለተኞቹ አማልክት ለመዘከር የተጣጣረ ሊመስል ይችል ይሆናል፡፡ ጠጋ ብሎ ላተኮረበት ግን ዋናው ኢላማ ‹‹ታህሳስ ልደቴ የሚሉ ዓማልክትን የምታመልኪ ሁሉ የምታመልኪው አፈ ታሪክ መሆኑን ልንገርሽ›› ለማለት መሆኑ ብዙም አያመራምር፡፡ ስለሆነም ምላሽ ቀርቅቦ በአዲስ አድማስ በኩል ብቅ የማለቱ አስፈላጊነት ታየኝ፣እናም ብቅ አልኩ፡፡

የተለቋቆጠው ጭብጥ ሰፊነት በአንዲት መጣጥፍ የመጠናቀቁ ጉዳይ ቢያጠራጥረኝም እንደሚኖረኝ ጊዜ መጠን ጉዳዩን ማብራራት ተገቢ ነው ብዬ ብዕር ወረቀቴን ሸክፌአለሁ፡፡ የታመንኩበት ቅዱስ አምላክ የእናንተንም የእኔንም ጊዜ ይባርክልና፡፡ እንግዲህ የእርግጠኝነቴ ፍርጣሜ ሰበቡ በእምነት የተገለጠልኝ እውነት ህያውነት ቢሆንም፣በእምነት አልባነት ድንዳኔ በገነገነ ብዕር መንፈሳዊውን ሃቅ በ‹‹ዓለማዊ›› ሽሙጥ ለጎሰመ ፀሃፊ፣ከዛው ከሰፈሩ የተመዠረጠን ትክክለኛ ምንጭ ማሳየት እና ለጋዜጣይቱ ታዳሚ ደግሞ የቅብጥርጥሮሹን አስመሳይነት በእውነተኛው ታሪክ መገላለጥ ወደድኩኝ፡፡ ለእኔ እምነት በቂዬ ቢሆንም ከእምነት ወዲያ ማዶ ያሉት በተበራረዘ ታሪክ ሰበብ በእምነት በሚገኝ ህይወት ላይ እንዳይዘብቱ እውነተኛውን የታሪክ ምንጭ መምዘዝ የውዴታ ግዴታዬ አደረኩት፡፡‹‹እንዴት? እንዴት?›› ለሚል ‹‹እንደተለመደው›› ነው መልሴ፡፡ ነገር አንድ ፣ ደረቅ ምንጭ የታህሳስ ሃያ ሰባቱ ስም-አልባ ፀሃፊ ‹‹በየአገሩ እና በየዘመኑ ከድንግል የተወለዱ፣ የአምላክ ልጅ አምላክ ተብለው የሚመለኩ ቸር ጌቶች፣ ስማቸው ቢለያይም ታሪካቸው በጣም ተመሳሳይ ነው፡፡ በተለይ የሆረስና የኢየሱስ፣ የሚትራና የኢየሱስ ተመሳሳይነት በጣም ሰፊ በመሆኑ ለበርካታ ምዕተ አመታት ሲያወዛግብ ቆይቷል›› ብለዋል፡፡ ከዚህ አባባላቸው ልብ ሊባል የሚገባው ሃቅ ኢየሱስ ላይ መተኮሩ ነው፡፡ ሆረስም፣ ሚትራም ከደረቅ ምንጭ በመነጨ የለበጣ እይታ የተገናዘቡት ከኢየሱስ ጋር ነው፣ ምክንያቱ ደግሞ በስመ ልደቱ ተመካኝቶ ኢየሱስን ‹‹የተኮረጀ አምላክ›› ለማድረግና ታሪኩን ለመደፍጠጥ መሆኑ አይጠረጠርም፡፡ ሆኖም ሚትራም ይሁን ሆረስ ከኢየሱስ ጋር ያላቸው ተመሳሳይነት በጣም ሰፊ ሳይሆን እጅግ መንማና ነው፡፡ የኢየሱስን እውነተኛ አምላክነት ላለመቀበል በፀሃፊው እይታ በ ‹‹ዚጊየስት ሙቪ›› ለስክሪፕትነት ከዛም ከዚህም ቦጨቅ ቦጨቅ ተደርጎ በተለጣጠፈ የታሪክ ቡቱቶ ላይ መመስረት ለጊዜው እንቅልፍ ሊሰጥ ቢችልም ዘላቂ መልስነቱ ግን የከቸረረ ነው፡፡

አካሪያ፣ ጀራልድ ማሲ፣ ቶማስደን፣ ጀምስ ፍሬዘር፣ ፍሬክ እና ጋንዲ የፃፏቸው መፅሃፍት የታህሳስ ሃያ ሰባቱ ፀሃፊ ‹‹እንደተጠቀሙት›› ለጠረጠርኩት የዚጊየስት (zeitgeist) ትዕይንተ ትሪት ስክሪፕት ዋና ምንጮች ናቸው፡፡ እነዚህም ጊዜ የተፋቸው ብቻ ሳይሆን በ ‹‹ይሆን ይሆናል›› ላይ ተደላድለው ሲያበቁ ብዙ ታሪካዊ ማመሳከሪያዎችን እነሱ ሊሉ የፈለጉትን ስላላሉላቸው ወዲያ አሽቀንጥረው ጥለው ከደረቅ ምንጭ ያነቀሩ ረጋ-ሰራሽ ስራዎች ናቸው፡፡ እነሱም ቢሆኑ በዋቢነት በታህሳስ 27 ፀሃፊ ሊጠቀሱ እምነት ያልተጣለባቸው በመሆኑ ፀሃፊው ‹‹ለምን ይዋሻል?›› ይባሉ ዘንድ ሰበብ ሆኗል፡፡ ታሪኩን በራሳቸው ስልጣን እንዳሻቸው አርከፍክፈውታልና ‹‹ለምን ይዋሻል?›› ማለታችን አግባብነቱ ያስማማን ይመስለኛል፡፡ ጽሁፉ ጭርቅ ጭርቅ የሚል ስለሆነ ከደረቅ ምንጭ መቧጠጡን ገና ሳይጠየቅ ያትታል፣ መጠየቁ ባይቀርም፡፡ ታዲያ በጭርቅርቅታው መነሻ ላይ ‹‹የሆረስ ታሪክ በአጭሩ ይሄን ይመስላል›› ብለው ያስቀመጧት ቁምጥምጥ ያለች ‹‹ታሪክ››፣ የሆረስን አፈታሪክ አትመስልም፡፡ አትመስልም ብቻ ሳይሆን ‹‹ሆረስ›› ስሙን ብቻ ይዞ ጥልቅ ያለባት የአንቀፅ ኩሬ መስላኛለች፡፡ እንግዲህ የአህዛብ አፈታሪካዊ አማልክት የሆኑትን ሆረስ፣አቲስ፣ክሪሽና፣ ደዮኒስስ፣ ሚትራና ሌሎችም በታህሳስ ሃያ ሰባቱ ፀሃፊ የተጠቀሱና ያልተጠቀሱ አማልክት ጸሃፊው የተመኙትን ያህል ከክርስቶስ ኢየሱስ አምላክነት ጋር ሊሸረቡና የክርስቶስን እውነተኛ አምላክነት ሊሸፍኑ የማይችሉ መሆናቸውን ከየምንጫቸው እያጣቀስኩ ማብራራቴን ጊዜ ቀይ እስኪያበራብኝ ድረስ በብዕር ሩጫዬ እፋለመዋለሁ፡፡ በመጀመሪያ ሖረስ(ሆረስ)፡፡

ነገር ሁለት ፣ ነገረ ሆረስ (ከምንጩ) የሆረስ አፈታሪክ ሁለት ምንጮች አሉት፡፡ የዚህ ሆረስ የተባለው የግብፅ አፈታሪካዊ አምላክ ምንጮች ራሳቸው ግብፃውያንና ለጥቆም ደግሞ ግሪካዊያን ናቸው፡፡ ታዲያ የታህሳስ ሃያ ሰባት ስም አልባው ፀሃፊ የሁለቱንም የማይመስል ኩስምን ያለች ታሪክ ሲወረውሩልን፣ መነሻ ሃሳባቸው ተመሳሳይ የልደት ‹‹ቀነ- ወር›› ሊነግሩን ብቻ አልመሰለኝም፡፡ ነገር ግን አማልክቱ የልደት ‹‹ቀነ-ወር›› ብቻ ሳይሆን ታሪክም የሚኮራረጁ፣ አንዱ ከሌላው የማይሻል ‹‹አፈ ታሪኮች›› ናቸው እና ‹‹በአፈ ታሪክ አልሸወድም ወይም አልተሸወድኩም›› ነው ነገሩ፣ አዬዬዬ! የነገረ ሆረስ እውነታ ግን ከዚህ እንደሚከተለው ታትቷል፡፡ ዋና የሚባሉት ምንጮች፣አንዱ ግብፆቹ ራሳቸው በየ‹‹ድግምቶቻቸው›› እና በየ‹‹ጥንተ- ስዕሎቻቸው›› ላይ ቸክችከው እና ፈቅፍቀው ካስቀሯቸው መካነ ቅርሶቻቸው የሚቀዳ ሲሆን ዝክረ ፒራሚድ (pyramid texts) ልንለው እንችላለን፡፡ ሌላው ደግሞ በግሪኮቹ የታሪክ ጥራዝ ተዘክረው በብዛት ወደ ላቲን ተተርጉመው የአፈታሪክ መዓት የሚቀፈቀፍባቸው መፅሃፍት ናቸው፡፡ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን የተጻፈው የፕሉታርክ De Iside et Osiride (Plutarch On Osiris & Isisi) ዋንኛው ነው፡፡ እነዚህ መጻህፍትና ቅርሳ ቅርስ ስለአፈ ታሪኮቹ ‹‹ስልጣን ያለን ማመሳከሪያ ነን›› ቢሉ እድሜያቸው ምክንያታቸው ነው፡፡ ከእነዚህ ምንጮች ያልቀዳ በአፈታሪክ ስም ያሻውን የቀባጠረ መሆኑ አያጨቃጭቅም፡፡ ሆረስ የግብፆች አምላከ-ጭልፊት (falcon-god) ሲሆን የሰማያት-ጌታም "lord of sky" ይባላል፤ የአምላካዊ ንጉስነትም ምስል ነው፡፡ በግብፅኛ ስሙ "ሃር" ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ትርጓሜውም " ከ ፍ ተ ኛ ው " ፣ " የ ማ ይ ደ ረ ስ በ ት " ፣ "የትየለሌው" እንደማለት ይቆጠራል፡፡ ደግሞም "ህራይ" ከሚለው የግብፅ ቃል ጋርም ሊዛመድ ይችላል፣ፍችውም "ከፍ ብሎ ያለ፣ከላይ የሚገኝ" ማለት ነው፡፡ ይህ ስም በግብፃውያን ምስለ-ፅሁፎች (hieroglyph) ላይ በነገስታት ማዕረግ ከክርስቶስ ልደት 3000 ዓመት አካባቢ ጀምሮ ይከሰት የነበረ ታሪከኛ አፈ-ታሪክ ነው፡፡

አፈ-ታሪክ (myth)!! የኦሲሪስ አፈ ታሪክ እንዳይፈረካከስ ገና ከጥንት ሙሉ በሙሉ ጥበቃ ባይደረግለትም የአፈ ታሪኩ አንኳር ትረካዎች በግሪካዊው Plutarch (ፕሉታርክ) On Isis & Osiris ለታሪክ እንዲበቃ ተደርጓል፡፡ የፕሉታርክ ትረካዎች ከግሪክ ወደ ላቲን ተመልሰው De Iside e osiride በሚል ስም በአፈ- ታሪክ ምንጭነት እያገለገሉ ነው፡፡ ይህ ላቲነኛው ትርጉም ዋንኛ የሆረሶች ታሪክ ምንጭ ነው፡፡ ስለሆነም በሆረስ ዙሪያ ለሚነገሩ አዲስና አሮጌ ትረካዎች ዋና ከሚባሉት ማጣቀሻዎች ግንባር ቀደሙ በመሆኑ ለዚህም ጽሁፍ የማጣቀሻ ማጣቀሻዎች ምንጭ እሱ ነው፡፡ ይኸው ከግብፆች አማልክት ዋንኛ የሚባለው ሆረስ በብዙ ማዕረጎችና ቅፅል ስሞች የተንበሸበሸ ሲሆን ጭልፊት፣ ጭልፊት-ራስ ሰውዬ፣ ክንፋም እንጎቻ (winged disk) ወዘተ ተብሎ ይጠራል፡፡ ስለሆነም ጥናተ-ግብፃውያን (Egyptologists) ስለተለያዩ አይነት ሆረሶችና አምላከ ሆረሶች መተረክ የውዴታ ግዴታቸው ሆኖ ቀርቷል፡፡ ለማንኛውም በጥንታዊ ግብፃውያን ከተተረኩ መንጋ ሆረሶች መካከል ዝነኛው የ"ኦሲሪስ (Osiris) እና የኢሲስ (Isis) ልጅ የሆነው በግብፅ ንጉስነት የሚታወቀው ሆረስ ነው፡፡ የሆረስ አባት ኦሲሪስ "ስብዕናን የተላበሰ መሬት" ተብሎ ከሚታወቀው (Geb) (ገብ) እና የ‹‹አማልክት እናት›› ደግሞም የሰማይዋ (የጠፈሯ) እመቤት ("mother of gods" and ''goddess of the sky'') ከምትባለው Nout/Nut (ኑት/ነት) የተወለደ ሲሆን ሚስቱ ደግሞ ኢሲስ ትባላለች፡፡ ይህቺ ኢሲስ ታዲያ በፈርኦኖቹ ዘመን እጅግ ገናናዋ ባለ አፈታሪክ እና እጅግ የተስፋፋ የኑፋቄ ምንጭ ነበረች፣ ነችም፡፡ ሆረስ በህያው የምድር ንጉስነቱ ተለይቶ የሚወሳ ሲሆን አባቱ ኦሲሪስ ደግሞ በሙት (በሙትቻ) ነገስትነቱ ይታወቃል፡፡ ሆረስ የአባቱ አልጋ ወራሽና ምትክ ነበረ፡፡ Heliopolitan Ennead (ሄሊዮፖሊቲን ኤንያድ) በተሰኘ የእነሆረስ አፈታሪካዊ የዘር ግንድ መዘርዝር ውስጥ የGeb (ገብ) እና Nut (ነት) ልጅ የሆነ የኦሲሪስ ወንድም አለ፡፡ ስሙ ደግሞ ሴት/ሴዝ (Seth) ይባላል፡፡

ይህ ትልቅየው ሆረስ [Horus the Elder (Haroeris)] ተብሎ የሚታወቀው ሴዝ (Seth)አንዳንዴ የዋነኛው ሆረስ አጎት ወይም ወንድም እየተባለ ቢጠቀስም አጎትነቱ ከወንድምነቱ ይልቅ በሚበዙት ማጣቀሻዎች ላይ ይጎላል፡፡ እንግዲህ ሆረስ የግብፅን ንግስና ለመጎናፀፍ ለ80 አመታት ያህል ከአጎቱ ከ Seth (ሴዝ) ጋር ተፋልሟል ታዲያ በዚህ ጦርነት ሆረስ አንድ አይኑን አጥቷል፡፡ የሚደንቀው ግን ያልጠፋችው የሆረስ አይን ዝናዋ ከሆረስ ከራሱ አለመተናነሱ ነው፡፡ በየዶላሩ ላይ በትኩረት ስትመለከቱ በፒራሚዱ አናት ላይ ተድቦልቡላ የምታፈጥባችሁ እሷ የሆረስ ዓይን ትሆን እንዴ@ ከሆነች ይኸው እስከዛሬ እያሾለቀች ነው - በብርም በመጣጥፍም ላይ፡፡ አይ ሆረስ!ነገር ሦስት፣ ውልደተ ሆረስ (የድንግል ጭልፊት ልጅ)ኦሲሪስ የግብፅን ምድር ያስተዳድር ነበር፡፡ ነገር ግን ቀናተኛ በሆነው በገዛ ወንድሙ ተታሎ ለህልፈት በቃ፡፡ ቲፎን "Typhone" እየተባለም የሚጠራው የኦሲሪስ ወንድም ''ሴዝ'' ወይም "ሴት" በኦሲሪስ ልክ የሆነ ሬሳ ሳጥን አዘጋጀ፡፡ ከእለታት አንድ ቀን አንድ ታላቅ ግብዣ ላይ 72 ከሚጠጉ ሴረኞች ጋር በማበር የሬሳ ሳጥኑ ልኩ ለሚሆን ቃልኪዳን አፀደቁ፡፡ እናም እያንዳንዱ እንግዳ ከሬሳ ሳጥኑ ውስጥ እየተጋደመ በመለካት ተጠመደ፡፡ በመለካት ከተጠመዱት ሁሉ ሬሳ ሳጥኑ ለኦሲሪስ ልክክ አለለት፡፡ ነገር ግን ኦሲሪስ ከሳጥኑ ከመውጣቱ በፊት ሴትና ሌሎቹ ሴረኞች ሳጥኑን በኦሲሪስ ላይ ጠረቀሙት፡፡ ከዛም በምስማር ከርችመው፣ በመዳብ አሽገው ወደ አባይ ወንዝ ወረወሩት፡፡ የሬሳ ሳጥኑም ከጊዜ በኋላ Byblos (ቢብሎስ) ከተሰኘ ቦታ በደረቅ መሬት ላይ ተገኘ፡፡

የኦሲሪስ ሚስት ኢሲስ ያለመታከት ባሏን ስታፈላልግ ከርማ በመጨረሻ የሬሳ ሳጥኑ ያለበትን ስፍራ ደረሰችበት፡፡ ኢሲስ ሬሳውን ወደ ግብጽ እንዲመለስ ብታደርግም Seth (ሴዝ) ሬሳውን አገኘና ብዙ ቦታ ቆራርጦ ቦጫጭቆ በምድሪቱ ሁሉ ላይ በተነው፡፡ የኦሲሪስ ባለቤት ኢሲስ ራሷን ወደ ጭልፊትነት ቀይራ ከእህቷ Nephthys (ነፍዚስ) ጋር በምድሪቱ ሁሉ እየበረረች ቁርጥራጮቹንና ቡጭቅጫቂዎቹን ሁሉ አሰባስበለች - አንድ ነገር ብቻ ሲቀር፡፡ እሱም የባለቤቷ ብልት፡፡ ቁርጥራጮቹን ሁሉ መልሳ ገጣጠመችና ኦሲሪስ ወደ ዘላለማዊ ጥበቃው ከመግባቱ በፊት ህይወት ዘርታበት ስታበቃ፣አስመስላ በሰራችው የወንድ ብልት አማካኝነት ተገናኝታው ሆረስን ፀነሰች፡፡ (እዚህች ጋ ቆም ብሎ ኢሲስ ባል እንደነበራት፣ባል ካላት ደግሞ ድንግልና መደንገሉ ማብቃቱን መጠርጠር ይገባል፣ ባል ያላት ድንግል በአፈ-ታሪክ ይቻል ይሆንን@) ተጨማሪ እንዲሆነን ፕሉታርክ በ Molaria V የሚለውን አብረን ብናነብ መልካም ነው ብዬ አሰብኩ፡፡ "…of the parts of Osiris' body the only one which Isis didn't find was the male member for the reason that this had been at once tossed into the river, & the lepidotous, the sea-bream and the pike had fed upon it. But Isis made a replica of the member to take its place, and consecrated the phallus, in honor of which the Egyptians even at the present day celebrate festival…'' በነገራችን ላይ ኢሲስ የባሏ የኦሲሪስ ሚስት ብቻ ሳትሆን እህቱም እንደነበረች በአፈ-ታሪኩ ቅብጥርጥሮሽ ውስጥ መተረቱን በፕሉታርክም በዝክረ ፒራሚድ (pyramid texts) ውስጥም ተሰንቅሮ ይገኛል፡፡ እና ኢሲስ እህት-ሚስት ነች ይባላል፡፡ ከላይ በፕሉተርክ እንደተገለፀው ደግሞም በሌላኛው ግሪካዊ የታሪክ ሰው Diodorus እንደፀናው ‹‹የኦሲሪስ ክፍለ አካላት በወንድሙ በሴዝ ተቆራርጦና ተቦጫጭቆ በአባይ ውሃ ላይ ሲወረወር በአሳ ከተዋጠው በትረ ወንዳወንድነቱ (male member) በቀር ሌላ አካሉ በ"እህት-ሚስቱ" በኢሲስ ተሰብስቦ በአስማቷ ህይወት ለብሶ ከምን እንደሰራችው ባልተገለፀ ነገር (አንዳንድ ማጣቀሻዎች ከወርቅ ይላሉ) በእራሷ የተበጀውን በትረ-ወንድነት አካሉ ላይ ገጥማ ትፀንስ ዘንድ ተቻላት፡፡›› ይላል አፈ ታሪኩ፡፡ እንግዲህ ልብ በሉ ሆረስ በዚህ መልኩ ነው የተፀነሰው፡፡ስለሆረስ አፀናነስ ጥቂት ምንጮችን አከል አከል ባደርግ ነገሬን ማፈርጠሙ አይጠረጠርም፡፡ ትክክለኛ ምንጭ እስካልተጠቀሰ ድረስ "ለምን ይዋሻል?" ማስባሉ አይቀሬ ነውና፡፡ የአሁኑ ምንጮቼ ነው የተፀነሰው፡፡ስለሆረስ አፀናነስ ጥቂት ምንጮችን አከል አከል ባደርግ ነገሬን ማፈርጠሙ አይጠረጠርም፡፡ ትክክለኛ ምንጭ እስካልተጠቀሰ ድረስ "ለምን ይዋሻል?" ማስባሉ አይቀሬ ነውና፡፡ የአሁኑ ምንጮቼ ደግሞ የጥናተ ግብፃውያን ሊቃናት ናቸው፡፡ሌስኮ (Lesko)በ ‹‹Great Goddesses of Egypt›› ላይ “Drawings on contemporary funerary papyri shows her as a kite hovering above Osiris, who is revived enough to have an erection & impregnate his wife” ብሎ ፅፏል፡፡

ባጭሩ‹‹ጭልፊት ነገር ሆና ወንድነቱ እስኪነሳ ተንሳፈፈችበት …›› ለማለት ነው፡፡ አፈ ታሪኮቹ እፍረት አያቁም፤ሁሉ ነገር በቁሙ ነው፡፡ እንደኛ እንደዱሮው፡፡
በ”Gods & men in Egypt” ዱናንድ እና ዚኮች “after having sexual intercourse in the form of a bird, with the dead god she restored to life, she gave birth to a posthumous son, Horus.” ብለው ከትበዋል፡፡ ‹‹ ወፍ ነገር ሆና ከሞተው አምላክ ጋር ግንኙነት ከፈጸመች በኋላ … የሙት ልጅ የሆነውን ሆረስን ወለደች›› ለማለት ይመስላል፡፡
Richard Wilknson ደግሞ በ “complete gods and goddess of Ancient Egypt’’ በተባለ መጽሃፉ “through her magic Isis revivified the sexual member of Osiris and become pregnant by him, eventually giving birth to their child, Horus” ብሎ መስክሯል፡፡
እንግዲህ ከላይ በጥቂቱ ዳሰስ ዳሰስ ያደረኩት በታሪክነትና በስነ-ፅሁፍ ቅርስነት ዋጋ ሊኖረው ይችላል ተብሎ የሚታሰበው ግብፃዊው አፈታሪካዊ ቅብጥርጥሮሽ ለተነሳሁበት ጭብጥ መረጃ ቢሆን ብዬ እንጂ ጣፋጭነትና ተወዳጅነት የሌለበት ከንቱነቱ አስደምሞኝ አይደለም፡፡
ነገር ግን ይህ ‹‹የኦሲሪስ-ኢሲስ-ሆረስ›› አምላከ-ግብጽ ‹‹ከድንግል የተወለደ አምላክ ነው›› ብለው በእውነተኛው አምላክ ልደትና በዚያ ድንቅ ታሪክ ላይ የኩረጃና የአፈታሪክነት ቅብ ለመቀባባት በአሽሙር ብዕር ቀለም ለረጩ ማጣፊያነት ቢበዛ እንጂ አያንስም፡፡ ከላይ በማስረጃ እንዳያችሁት የሆረስ እናት ኢሲስ የተቦጫጨቀ አስክሬን ቀጣጥላ ያውም ለመፀነስ ዋና የተባለውን በትረ ወንድነት እራሷ ‹‹በትራ›› ሆረስን ለመፀነስ አንዴ ጭልፊት፣ አንዴ ወፍ ፣ አንዴ ሌላ አይነት በራሪ ነገር እየሆነች ስትርመሰመስ ሁሉም ምንጮች ቁልጭ አድርገው አሳይተዋል፡፡ በየትኛውም ተቀባይነት ባለው የሆረስ ታሪካዊ ትውፊት ላይ ኢሲስ ከሞተው ‹‹ባል-ወንድሟ›› ጋር ስትገናኝ ‹‹ድንግል ነበረች›› ተብሎ አልተፃፈም፡፡ ታዲያ ‹‹ለምን ይዋሻል?›› ከሆነችም ‹‹ድንግል ጭልፊት›› ወይም ‹‹ድንግል ወፈ-በራሪ›› ትሆን እንደሆነ እንጃ፡፡ እኔ ‹‹ድንግል ጭልፊት›› ብያታለሁ፣ ምክንያቱም በፀነሰች ጊዜ ጭልፊት ሆና ነበርና፡፡ የልጃገረድ ሳይሆን የጭልፊትነቷ ‹‹ድንግልና›› ነው የተፃፈላት፡፡
አቤት አለመመሳሰል፡፡ የሚገርመው የኢሲስ አፈ-ታሪካዊ ታሪኳ ሳይሆን ታሪክንና አፈታሪክን በአንድ ማነቆ ለማቆራኘት ከዚህ እዚያ የተንሳፈፉት የታህሳስ ሃያ ሰባቱ የአዲስ አድማስ ፀሃፊ ናቸው ፡፡ እንግዲህ የአፈ ታሪክ ገድለኛው ሆረስ ከድንግል አለመወለዱን ልብ በሉልኝ፡፡
የሆረስ ውልጃ ‹‹ድንግለ ውልደት›› ሳይሆን ‹‹ምትሃተ ውልደት›› ነው፡፡ የእንዲህ አይነት ታሪኮችና ውልደቶች ምንጭ ሰፈሩ ከየት እንደሆነ እውነተኛውን ድንግለ-ውልደት ለተቀበሉ ብዙም አምታች አይደለም፡፡ ነገር ግን ተአምራት ሁሉ ምትሃት ሆኖ ለቀሰፈው፣‹‹ደምረህ፤አባዝትህ ቁጭ አድርግልኝ›› ብሎ ለገረረ፣ የሆረስ አይነት ታሪኮች ድንቅ መሸሸጊያ ዋሻዎች ናቸው፡፡

ብርቱ ምሽግ ለመሆን ቢከጅላቸውም ‹‹ከፍ ያለውን በእግዚአብሄርም እውቀት ላይ የሚነሳውን ነገር›› ማፍረስ የሚችል እውነት የሚባል መዶሻ መኖሩ መረሳት የለበትም፡፡ ያ መዶሻ ደግሞ የማይሻረው ቃል ነው፣ እሱም ‹‹የጦር እቃችን ስጋዊ አይደለምና ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሄር ፊት ብርቱ ነው›› ይላል፡፡
ታዲያ እንዴት እንዴት ተደርጎ በዚያም በዚህም ይዋሻል; ‹‹ሃይልህ ብዙ ሲሆን…ዋሹብህ›› የሚለው የመፅሃፉ ቃል ተተገበረን?እንግዲህ ሆረስ ስለተባሉ አማልክት ስለ ክንፋቸው፣ስለ ፀሃይ እና ጨረቃ አይኖቻቸው ወዘተ በዝርዝር መተረኩ አላስፈላጊ አይደለም፡፡ የታህሳስ 27 ቀን 2005 ዓ.ም ፀሃፊ ‹‹ወደተናቀ ወደ መጀመሪያ ትምህርት›› ትዝታ የግድ ስበውናልና መልስ መስጠት ተገቢ ስለነበር ነው ከላይ ያለውን ከጥንተ መዛግብት ብቻ ሳይሆን ከ‹‹ጥንተ›› ንባቤ ጨለፍ አድርጌ እንካችሁ ማለቴ፡፡ ጊዜና ስፍራ ለዛሬ ከዚህ አስቁመውኛልና የቀረውን ለሳምንት አሻግሬ ‹‹ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን›› እያልኩ ልሰናበት፡፡

Published in ህብረተሰብ

 በአጭሩ አይ ኦ ኤም (IOM) እየተባለ የሚጠራው አለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት የተቋቋመው በመላው አለም የሚገኙ ስደተኞችን ለመርዳት ነው፡፡ ይህንን ዋነኛ አላማውን ከግብ ለማድረስም በመላው አለም በሚገኙ የተለያዩ ሀገራት ቢሮዎቹን ከፍቶ እንደ አቅሙ ደፋ ቀና ይላል፡ ፡ በየመን የሚገኘው ይሄ የስደተኞች ድርጅት ግን ራሱ ስደተኛ ነው፡፡ በየመን የሚገኙትን ስደተኞች እንደፍላጐቱና እንደ እቅዱ ለመርዳት የሚያስችል የሚያወላዳ የገንዘብም ሆነ የቁሳቁስ አቅም የሌለው፣ የለጋሾችንና የበጐ አድራጊዎችን እጅ አይቶ የሚኖር ምስኪን ድርጅት ነው፡፡ በየመን ከሚገኙት ስደተኞች ከፍተኛውን ቁጥር የያዙትና በአስከፊ ሁኔታ ላይ የሚገኙትን የእኛን ሰዎች ለመርዳት የቻለውን ያህል ቢፍጨረጨርም፣ በየቀኑ ለሚጐርፉት አዲስ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እርዳታ ለመስጠት ከአቅሙ በላይ ስለሆነበት ልክ እንደ ስደተኞቹ ድርጅቱም እርዳታ ለማግኘት ለመሯሯጥ ተገዷል፡፡ ሰንአ ሄዳችሁ ወደ ድርጅቱ ቢሮ ጐራ ብትሉ፣ በእንዴት ያለ ችግር ውስጥ እንዳለና ሠራተኞቹ እነዚያን እጅግ አስከፊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ የወደቁ ስደተኛ የእኛን ሰዎች ለመርዳት እየፈለጉ ነገር ግን ካቅማቸው በላይ ሆኖ በስደተኞቹ ብሶትና ምሬት ተማረው አብረዋቸው ሲያዝኑና ሲያነቡ ልትመለከቷቸው ትችላላችሁ፡፡

በየመን የሚገኙትን ስደተኞች ለመርዳት ከሚንቀሳቀሱት በርካታ ድርጅቶች ውስጥ የተሻለ አቅም አላቸው የሚባሉት በአውሮፓ ህብረት የገንዘብ እርዳታ የሚደገፉት የዴንማርክ የስደተኞች ካውንስል እና Mixed Migration Secretariat (MMS) ከነአጋሮቹ ናቸው፡፡ እነዚህ ድርጅቶችም ቢሆኑ ከአይ ኦ ኤም ጋር ሲወዳደሩ በብዙ እጥፍ ይበልጣሉ ለማለት እንጂ በየመን የሚገኙ ስደተኞች በተለይ ከሁሉም የሚበዙትና በአስር ሺዎች የሚቆጠሩት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ነገር ከአቅማቸው በላይ እየሆነባቸው እንደመጣ ሳይደብቁ በግልጽ ይናገራሉ፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ቀድሞውኑ አለመጠን የከፋውን የስደተኞች ችግር ይበልጡኑ እንዲከፋና ከቁጥጥር ውጭ እንዲወጣ እያስገደዱት ያለው በየቀኑ ወደ የመን የሚጐርፉት በመቶዎች የሚቆጠሩት የእኛው ሰዎች ናቸው፡፡ ሰንአ ከተማ ወደሚገኘው የዴንማርክ የስደተኞች ካውንስል ቢሮ የእንግዶች መቀበያ ክፍል ጐራ ብትሉ፣ የዴንማርክ የስደተኞች ካውንስል ከተባበሩት መንግስታት የስደኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር የመስክ ተቆጣጣሪዎች ቡድን ጋር በመሆን ያጠናቀሩት የየመን የስደተኞችን ሁኔታ የሚያስረዳ መረጃ የያዘ ትልቅ የግድግዳ ላይ ቻርት ታገኛላችሁ፡፡

ይህ በግድግዳ ላይ የተሰቀለ ትልቅ የመረጃ ቻርት አንዱ ክፍል፣ ባለፉት ስድስት አመታት ውስጥ ብቻ ሁለት መቶ ሠላሳ ሺ ኢትዮጵያውያን በስደተኝነት ወደ የመን መግባታቸውንና አብዛኞቹም በሠንአ፣ በኤደንና በሀራድህ ከተሞች እንደሚገኙ የሚገልጽ መረጃ ይዟል፡፡ የተወሰነው ክፍል ደግሞ ከእነዚህ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ውስጥ እጅግ የሚበዙት ምናልባትም ሁሉም ሊባል በሚችል ሁኔታ ወደ የመን የገቡት በህገወጥ መንገድ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ሰንአ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የዴንማርክ የስደተኞች ካውንስል ቢሮ ውስጥ ያገኛችሁትን ይህን ዝርዝር የስደተኞች መረጃ፣ ኤደን ከተማ በሚገኘው የመስክ ቢሮው ውስጥም ታገኙታላችሁ፡፡ የዚህን ድርጅት መረጃ ትክክለኛነቱን ለማረጋገጥ ከፈለጋችሁ ደግሞ፣ ስልሳ ሰባት በመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደሚገኙባት ወደ የመን ዋና ከተማ ሰንአ ብቅ ማለትና ሁኔታውን መመልከት አያስፈልጋችሁም፡፡ ኤደን ከተማ በቂያችሁ ናት፡፡ ኤደን ከየመን ታላላቅ ከተሞች ውስጥ ከዋና ከተማዋ ከሠንአ ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ትልቋ ከተማ ናት፡፡ የኢትዮጵያን ስደተኞች በመያዝ በኩልም ከሰንአ ቀጥላ ሁለተኛዋ ናት፡፡ ኤደን የየመን ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ ብቻ ሳትሆን ከፍተኛ የየመን ወጪና ገቢ ንግድ የሚስተናገድባት ትልቅ የወደብ ከተማ መሆኗ ይታወቃል፡፡ የኤደን ከተማ ልክ እንደ ሰንአ ሁሉ በውስጧ ሲዘዋወሩ በጥቂት ሜትሮች ርቀት የሚያጋጥሙትን ኢትዮጵያውያንን ብዛት ከግምት ውስጥ በማስገባት በየመን ይገኛሉ የተባሉትን ስደተኛ ኢትዮጵያውያንን ቁጥር ማገናዘብ ይህን ያህል ከባድ ነገር አይደለም፡፡ ይህን ማድረግ የሚቻለው ለዚያውም "ረግቶ - ኗሪ" (Stable population) የሚባሉትን የኤደን ከተማ ኗሪ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በማየት ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ከሠንአ ከተማ ቀጥላ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩትን ረግቶ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን የያዘችው ከተማ ኤደን ስለሆነች ነው፡፡

ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ይልቅ እነዚህኞቹ ተለይተው ለምን ረግቶ ነዋሪ ስደተኛ እንደተባሉ ለማወቅ ከፈለጋችሁ ደግሞ የተለየ ጥናትና ምርምር ማድረግ ጨርሶ አያስፈልጋችሁም፡፡ አኗኗራቸውን ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ እነዚህ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን በኤደን ከተማ በተለያየ የተሻለ" ስራ ላይ ተሠማርተው፣ የራሳቸውን ቤተሰብ መስርተውና ልጆች አፍርተው፣ አንዳንዶቹም የራሳቸውን የተለያዩ የንግድ ድርጅቶችን ለማቋቋም የተሻለ ጥሪትም ቋጥረውና ተረጋግተው የሚኖሩ ናቸው፡፡ እነዚህን የተረጋጉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በበርካታ ቁጥር የምታዩባቸውን የኤደንን ዋና ዋና የንግድ አካባቢዎች ለቃችሁ ባሳቲን እየተባለ ወደሚጠራው ሠፈር ስትሄዱ ግን ሁሉም ነገር ይቀየርባችኋል፡፡ በኤደን የሚኖሩ አብዛኞቹ ስደተኞች ታጭቀው የሚገኙት በዚህ የባሳቲን ሰፈር ውስጥ ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ድፍን የኢትዮጵያ ህዝብ ግልብጥ ብሎ ወደ የመን የተሰደደ የሚመስላችሁ ወደዚህ ወደ ባሳቲን ሰፈር ስትመጡ ነው፡፡ በባሳቲን ሠፈር ውስጥ እንደ አንዳች ነገር ከሚርመሰመሱት በህገወጥ መንገድ ወደ የመን የገቡ ስደተኞች ውስጥ ቁጥራቸው ከሰማኒያ አምስት በመቶ በላይ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ናቸው፡፡ ወደዚህ ሰፈር ስትመጡ መጀመሪያ የሚቀበላችሁ ቋንቋ አረብኛ እንዳይመስላችሁ፡፡ በዚህ ሰፈር ውስጥ መጀመሪያ የሚቀበላችሁ ቋንቋ ኦሮምኛ ነው፡፡ በኤደን የባሳቲን ሠፈር እንደዚያ ታጭቀው የሚኖሩት ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ከቁጥራቸው መብዛት በተጨማሪ ተለይተው የሚታወቁበት ሌላም ነገር አላቸው፡፡ ይኸውም የኑሮአቸው ሁኔታ እጅግ አስከፊ መሆን ነው፡፡

ከእነዚህ ስደኞች ውስጥ አብዛኞቹ የጐዳና ተዳዳሪዎችና የእለት ምግባቸውን ለማግኘት በየአውራ ጐዳናው ላይ ተሠማርተው አላፊ አግዳሚውን ሲለምኑ የሚውሉ ናቸው፡፡ በባሳቲን ሠፈራ አውራ ጐዳና ዳርና በየጥጋጥጉ ላያቸው ላይ የተበጣጠሰ አዳፋ ሸሚዝና ሽርጥ አድርገው የተኙ አስር ስደተኞችን ካገኛችሁ ስምንቱ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ በዚህ ሰፈር ውስጥ አውራ ጐዳና ላይ የሚለምኑ አስር ለማኞችን ካገኛችሁ ደግም ዘጠኙ ኢትዮጵያውያን ለመሆናቸው ምንም የሚያጠራጥር ነገር የለውም፡፡ ይህ ወደ ኤደን ጐራ ማለት የቻለ ማንኛውም ሠው፣ በባሳቲን ሰፈር የአንድ ሰአት ጊዜ እንኳን ሳያጠፋ በቀላሉ ማረጋገጥ የሚችለው ተራ እውነት ነው - መራራ እውነት!! ሌላም አንድ ጉዳይ አለ፡፡ በኤደን ከተማ የሚገኘው የዴንማርክ የስደተኞች ካውንስል የመስክ ቢሮ፣ በኤደን የባሳቲን ሰፈር ውስጥ የሚኖሩትን የኢትዮጵያ ስደተኞች በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ እንዲሠጣችሁ ብትጠይቁት፣ በብርሀን ፍጥነት የስደተኞቹን የጾታ፣ የብሔርና የሀይማኖት ስብጥር በዝርዝር ያቀርብላችኋል፡፡ በዚህ መሠረት ታዲያ በባሳቲን ሰፈር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን አብዛኞቹ ወንዶች፣ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችና የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች መሆናቸዉን ትረዳላችሁ፡፡ በባሳቲን ሰፈር ከሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች አንዱ የሆነው የጂማ ዞን የሶከሩ ወረዳው ግርማ በዳዳ (ስሙ የተቀየረ) ድንገት በሰፈሩ ስትዘዋወሩ ካያችሁና ፊታችሁ አዲስ ከሆነበት፣ ወደ እናንተ እየሮጠ በመምጣት "አበበቺን ካን አርጌ ጂራ?" እያለ በኦሮምኛ ልባችሁ እስኪወልቅ ይጠይቃችኋል፡፡ (አበበችን ያየ አለ ማለቱ ነው) ግርማ በዳዳ ማነው? እንዴት እዚህ ሰፈር ተገኘ? አበበችስ ምኑ ናት? በሚቀጥለው ሳምንት አሰቃቂውን የግርማን ታሪክ አስነብባችኋለሁ፡፡ ቸር ያገናኘን!!

Published in ህብረተሰብ

በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ የሚሆነው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ካሉት ጠንካራ ጎኖች አንዱ ምርጥ አጥቂዎችን መያዙ ነው፡፣ ቁልፍ ሚና ይኖራቸዋል ከሚባሉት አጥቂዎች ደግሞ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አዳነ ግርማ እና የደደቢቱ ጌታነህ ከበደ ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ሁለቱ አጥቂዎች ብሄራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት ሲያደርግ በተቀመጠበት የኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል በማረፊያ መኝታ ቤታቸው ጎረቤታሞች ነበሩ፡፡ ሁለቱ ተጨዋቾች ኢትዮጵያ ከ31 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ከሱዳን ጋር እዚህ አዲስ አበባ ጋር ባደረገችው የመልስ ጨዋታ በፈጠሩት ጥምረት ታሪክ ሰርተዋል፡፡ ጥቅምት 4 ቀን 2005 ተደርጎ በነበረው በዚሁ ታሪካዊ ፍልሚያ ኢትዮጵያ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የበቃችብትን ጎል አዳና በጭንቅላቱ ከመረብ ያሳረፈው ከጌታነህ ከበደ የተሻገረለትን ክሮስ በአግባቡ በመጠቀም ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የግራ መስመር ተመላላሽ ተጨዋቾች የሆኑት የደደቢቱ ምን ያህል ተሾመ እና የስዊድኑ ሴሪናስካ ክለብ ተሰላፊ ዩሱፍ ሳላህ ደግሞ ሌሎቹ የብሄራዊ ቡድናችን ምርጦች ናቸው፡፡አሉላ ግርማንም ሁላችንም እናውቃለን፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወሳኝ የቀኝ ተመላላሽ ተጨዋች ነው፡፡ ሰሞኑን ከእነዚህ አምስት የብሄራዊ ቡድን ቁልፍ ተጨዋቾች ጋር በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል ተገናኝቻለሁ፡፡ በርግጥ 23ቱም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች ባነጋግር ፍላጎቴ ነበር፡፡ እንደ ዋና አሰልጣኙ ሰውነት ቢሻው አነጋገር ሁሉም ቋሚ ተሰላፊዎች፤ ወሳኝ ሚና የሚኖራቸው ኮከቦቻችን ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በ29ኛው አፍሪካ ዋንጫ አለችበት፡፡ አዳነ፤ጌታነህ፤ ዩሱፍ፤ ምንያህልና አሉላ በዚህ ዙርያ እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች አስተያት ሰጥተውኛል፡፡

ጭውውታችንን በትውልድ ስፍራ ብንጀምርስ---ጌታነህ
የተወለድኩት በዲላ ነው፡፡ ዲላ በቡና ምርቷ ትታወቃለች፡፡ አምስት ኳስ ተጨዋቾችን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ አፍርታለች፡፡ እነ ከፍያለሁ፤ ብርሃኔ አንለይ፤ ዳንኤል ደርቤ የዲላ ልጆች ናቸው፡፡አዳነ
እኔ የተወለድኩት በሃዋሳ በምትገኘው ኮረም የተባለች ሰፈር ነው፡፡ ኮረም ብዙ ኳስ ተጨዋቾች እና ሾፌሮችን ያፈራች ሰፈር ናት፡፡ እዚያ ኮረም ሜዳ የሚባል ስፍራ አለ፡፡ ያ ሜዳ በርካታ ተጨዋቾችን ወደ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ያመጣና ለብሄራዊ ቡድን ያበቃ ነው፡፡ እነ ሙሉጌታ ምህረት፤ ዮናታን ከበደና ሌሎችም ከዚያ ነው የወጡት፡፡ምንያህል
ተወልድጄ ያደግኩት እዚሁ አዲስ አበባ ነው፡፡ ሰፈሬም መገናኛ አካባቢ 24 ቀበሌ ነው፡፡አሉላ
ትውልዴ በ6 ኪሎ ጃንሜዳ ሰፈር ነው፡፡
ኳስ ተጨዋችነትን የጀመራችሁት በልጅነት ነው ወይስ አዋቂ ከሆናችሁ በኋላ?አዳነ
ከልጅነቴ ጀምሮ ከኳስ ጋር ነው ያደግሁት እናም ታዋቂ ኳስ ተጨዋች የመሆን ህልም ነበረኝ፡፡ ይህን ህልም ይዤ አድጌያለሁ፣ አሁን እውን ስለሆነ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ጌታነህ
እግር ኳስ ተጨዋችነት ሙያዬ እንደሚሆን ባላስብም በሰፈር ውስጥ እየተጫወትኩ ሳድግ ፍላጎቱ የተፈጠረ ይመስለኛል፡፡ ካደግኩ በኋላ ግን ሙያዬ እንደሚሆን እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ምንያህል
ታዳጊ ሳለሁ የፕሮጀክት ተጨዋች ነበርኩ። አንዳንዴ የብሔራዊ ቡድን ማሊያ ለልምምድ እንድለብስ ሰዎች ሲሰጡኝ አልፈልግም እላቸው ነበር፡፡ ወደፊት የራሴን መልበሴ አይቀርም ብዬ አስብ ነበር፡፡ በውስጤ ይህ እምነት ነበረኝ፡፡ አሁን እዚህ ደረጃ ደርሼ የሚያኮራ ሙያ ሆኖልኛል፡፡ አሉላ
ያደጉት በጃን ሜዳ አካባቢ ስለነበር ለስፖርቱ ቅርበት ነበረኝ፡፡ አባቴ በቀለም ትምህርት እንድገፋ ቢመክረኝም እግር ኳስን አዘውትሮ መጫወት አበዛ ነበር፡፡ በትምህርት ቤት የደረጃ ተማሪ ነበርኩ፣ በእግር ኳሱ በጣም እየገፋሁበት ስሄድ ግን ሙያዬ እንደሚሆን እያወቅሁ መጣሁ፡፡ዩሱፍ
ከልጅነቴ ጀምሮ ኳስ ተጨዋች መሆን እፈልግ ነበር፡፡ በቲቪ እያየሁ ያደግሁት ስፖርት ነው፡፡ ቤተሰቤ በተለይ አባቴ እንድማር ይፈልግ ነበር፡፡ ኳስ እንድጫወት የሚፈቀድልኝ በትምህርቴ ስበረታ ብቻ ነበር፡፡ በኋላ ግን በስዊድን ፕሮፌሽናል ሊግ ውስጥ ገብቼ አሁን ላለሁበት ደረጃ በቅቻለሁ፡፡ እናም የምከበርበት ሙያ ሆኖልኛል። ማንም እግር ኳስ ተጨዋች ትልቁ ዓላማው በብሔራዊ ቡድን ውስጥ መጫወት ነው፡፡ እኔም በስዊድን ወጣት ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ተጫውቻለሁ፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስገባ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል፡፡ አሁን ደግሞ የመጀመርያው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ልሳተፍ ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የገባሁበትን የመጀመሪያ አጋጣሚ የፈጠረው አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ነው፡፡ በኢሜልና በስልክ ባደረግነው ግንኙነት በምጫወትበት ክለብ ውስጥ ያለኝን ብቃት የሚያሳዩ የቪዲዮ ምስሎች እንድልክለት ስዩም ጠየቀኝ፡፡ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ፊልሞችን መመልከት እንደሚፈልግ ነገረኝ፡፡ በምጫወትበት የስዊድን ክለብ ሴሪናስካ ዘንድሮ እና ባለፈው የውድድር ዘመን ያደረግኋቸውን ጨዋታዎች የሚያሳዩ ፊልሞች ላኩኝ፡፡ ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ፊልሞቹን ተመልክተው ወደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመቀላቀል ልሠራ እንደምችል በስልክ ነገሩኝ፡፡ በዚህ መንገድ ብሔራዊ ቡድኑን ለመቀላቀል ችያለሁ፡፡
ብሄራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ ካለፈ በኋላ ያገኛችሁት አጠቃላይ የገንዘብ ሽልማት ስንት ደረሰ?አዳነ
355ሺ ብር
ጌታነህ
335ሺ
ምንያህል
300ሺ ብር
አሉላ
350ሺ ብር
ከትልቅ ጨዋታ በፊት በየትኛውም ቡድን ውስጥ ተጨዋቾች መጨነቅና መወጠራቸው አይቀርም፡፡ ከሱዳን ጋር ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በተደረገው የመጨረሻው ፍልሚያ የብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች መብላትና መተኛት ሁሉ ተቸግረው ነበር ይባላል፡፡ አሁን ደግሞ ከ31 ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዋንጫ አልፋለች፡፡ የሚያጨናንቅ ነገር አለ?አዳነ
በሱዳኑ ጨዋታ እንቅልፍ ማጣታችንንና መጨነቃችንን የተናገርነው ከ31 ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የምታልፍበት ወሳኝና የመጨረሻ ምእራፍ ላይ ደርሰን ስለነበር ነው፡፡ ታሪክ መስራት፤ ህዝባችንን ማስደሰት፤የሚሉትን ማሰብ ያስጨንቃል። አሁን ግን በከፍተኛ የራስ መተማመን ውስጥ ነው ያለነው። አንዴ ማለፋችንን ስላረጋገጥን ምንም አይነት ጭንቀት እና ጫና የለብንም፡፡ እንደውም ጫናው ለእነ ዛምቢያ ነው የሚሆነው፡፡ እኔ በበኩሌ አልጨናነቅም፡፡ ዛምቢያ አሁን ሻምፒዮናነቷን ለማስጠበቅ ትጨናነቃለች። እኛ ግን ማንም አያውቀንም፡፡ አለመታወቃችን ጭንቀት የሚፈጥረው በምድቡ ተቀናቃኞች ላይ ነው፡፡ጌታነህ
ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያን የምናሳልፍበት እድል በፈጠረው ፍልሚያ የነበረው ጭንቀት የተፈጠረው ቅድም አዳነ በዘረዘራቸው ምክንያቶች ነው፡፡ የተለየ የምጨምረው ቢኖር በወቅቱ ባይሳካልንስ ብለን መስጋታችንን ነው፡፡ ከጨዋታ በፊት በየሚዲያው "የመጨረሻው እድላቸው" ተብሎ መነገሩም ያስጨንቅ ነበር፡፡ አሁን ግን በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ መሳተፋችን በመረጋገጡ በምድብ የምናደርገው ውድድር ስለሆነ ብዙም የሚያስጨንቅ ነገር አለ ብዬ አላስብም፡፡ምንያህል
አሁን እየገባን ያለው ወደ አህጉራዊ ውድድር ነው። ባለፈው በሱዳን ጨዋታ ጭንቀት የተፈጠረብን ወደዚህ የውድድር ምዕራፍ ለመሸጋገር ወሳኝ ፍልሚያ ላይ በመድረሳችን ነበር፡፡ ወደ ታላቅ ምዕራፍ ለመሸጋገር ዋዜማ ላይ ስለነበርን ነው ከፍተኛ ጫና የተፈጠረብን፡፡ አሁን ስለአፍሪካ ዋንጫ ለማውራት የበቃነው ያንን ወሳኝ ፍልሚያ አልፈን ነው፡፡
በምድብ 3 የመክፈቻ ጨዋታ ስለምትገጥሟት ሻምፒዮኗ ዛምቢያ ወቅታዊ የአቋም ሁኔታ ምን መረጃ አላችሁ?አዳነ
ከፍተኛ ትኩረት የሰጠነው ካለፈው የአፍሪካ ሻምፒዮን ዛምቢያ ጋር የምናደርገው የምድቡ መክፈቻ ጨዋታን ነው፡፡ ሁላችንም እንደተከታተልነው ዛምቢያ በወዳጅነት ጨዋታዎች ተከታታይ ሽንፈት ስላጋጠማት በጥሩ አቋም ትገኛለች ለማለት ያጠራጥራል፡፡ በአንፃሩ የኛ ዝግጅት የተሳካ ነው፡፡ ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎች አሸንፈናል፡፡ በአንዱ አቻ ወጥተናል፡፡ በተለይ ከአፍሪካ ኃያል ቡድኖች አንዷ ከምትባለው ቱኒዚያ ጋር አቻ የወጣንበት ሁኔታ ጥንካሬያችንን ያጎላዋል፡፡ ከዚህ አንፃር የምድብ 3 የመክፈቻ ጨዋታ ከእኛ ይልቅ ፈታኝ የሚሆነው ለዛምቢያ ይመስለኛል፡፡ እነሱ ተሸብረው ይገባሉ። እኛ ግን ከዚህ በፊት ከሚያውቁን የተሻለ ጥንካሬ ይዘን እንገጥማቸዋለን፡፡
አዳነ እና ጌታነህ ሁለታችሁም የዋልያዎቹ ወሳኝ አጥቂዎች እንደመሆናችሁ አንድ የታዘብኩትን ሁኔታ እንዴት እንደምታዩት ማወቅ እፈልጋለሁ፡፡ ከ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አራት ምድቦች መካከል ምድብ 3 በጥንካሬው ብቻ ሳይሆን በርካታ ምርጥ አጥቂዎች የተሰባሰቡበት ሆኖ ይለያል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የአጥቂ መስመር ከመቸውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ በምርጥ ስብስብ የተዋቀረ ይመስለኛል፡፡ የናይጄርያ ብሄራዊ ቡድንም የአፍሪካ ዋንጫውን ምርጥ አጥቂዎች በመያዝ የሚጠቀስ ነው፡፡ በዛምቢያም ቢሆን አንዱ ልዩ ጥንካሬ የአጥቂ መስመሩ ነው፡፡ በፈረንሳይ ሊግ ምርጥ የተባሉ አጥቂዎችን የያዘውና ከፍተኛ ልምድ ያላቸው የፊት መስመር ተሰላፊዎችን ያካተተው የቡርኪናፋሶ ቡድንም የሚናቅ አይሆንም። ይህን የምድብ 3 የአጥቂዎች መብዛት እንዴት ታነፃፅሩታላችሁ?ጌታነህ
ብዙ የማውቃቸው የናይጄርያ አጥቂዎችን ቢሆንም አንዳንድ የዛምቢያ አጥቂዎችንም አውቃለሁ፡፡ ይሁንና የእኛ ቡድንም በአጥቂዎቹ ብዙ የሚተናነስ አይደለም። የቡድናችን ሁላችንም አጥቂዎች ጠንካሮች ነን፡፡ በየጨዋታው ሁሉም አጥቂዎች ጎል እያገባን ቆይተናል። አንዳችን ገብተን ጎል ማስቆጠር ቢያዳግተን ተቀይረን በመግባት ጎል እያገባን እየወጣን ነው፡፡ አጥቂ ሆነህ ሜዳ ስትገባ ጎል ማግባት አለብህ። በእኛ ቡድን ያሉ አጥቂዎች ጥንካሬም ይህንኑ ሃላፊነት በአግባቡ እየተወጣ ነው። ሁላችንም ወደ ሜዳ የምንግባው በአንድ ሆነ በሌላ አጋጣሚ ጎል ለማስቆጠር እምነትና ጥንካሬ ይዘን ነው፡፡
አዳነ
ከዚህ በፈት የነበሩ የብሄራዊ ቡድን አጥቂዎች ጎል የማግባት ችግር ነበረባቸው፡፡ አሁን ያለን አጥቂዎች ግን ለውጤት የሚያበቁ ወሳኝ ጎሎችን በሜዳችን ሆነ ከሜዳ ውጭ ለማስቆጠር ብዙ ችግር የለብንም፡፡ የሁላችንም ወቅታዊ ብቃት ይህን ለማለት የሚያስተማምን ይመስለኛል፡፡ ቡድናችን ድሮ ከሜዳ ውጭ አያገባም ነበር፡፡ ያ ነገር አሁን ባለው የአጥቂ ትውልድ ተሰብሯል፡፡ ለዚህም ነው በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጎል ለማግባት ብቃቱ እንዳለን በእርግጠኝነት ነው የምናገረው። በወዳጅነት ጨዋታዎቹ እንደታየውም በርካታ የግብ ሙከራዎችንም እናደርጋለን፡፡ በቡድናችን ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ የማድረግ ብቃት እና ጥንካሬ ያላቸው አጥቂዎች መኖራቸውን ማንም አይክደውም፡፡ ስለሆነም በተቃራኒ ቡድኖች ስላለው የአጥቂ መስመር ጥንካሬ ብዙ ማሰብ አልፈልግም፡፡ የኢትዮጵያ አጥቂዎች ጥንካሬ በአፍሪካ ዋንጫው ማጣርያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዋንጫው ማጣርያ ሲታይ የቆየ በመሆኑ ይህ ጥንካሬ አሁንም በአፍሪካ ዋንጫው ቀጥሎ ለውጤት እንደሚያበቃን ነው ተስፋ የማደርገው፡፡
እንግዲህ የአፍሪካ ዋንጫን ለየት ከሚያደርጉት ባህርያት መካከል ጎል ከገባ በኋላ በየቡድኖቹ ተጨዋቾች የሚታየው የደስታ አገላለፅ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጐል ሲያገባ ደስታውን እንዴት ለመግለፅ ታስቧል?አዳነ
እንደ ብዙ የአፍሪካ አገራት ኢትዮጵያም ብዙ ባህል ያላት አገር ናት እና መልካም ገፅታዋንና እና ባህሏን የሚያስተዋውቅ የደስታ አገላለፅ ለማድረግ እንሞክራለን። በዚህ ታላቅ መድረክ ጎል በማግባት የሚፈጠረውን አጋጣሚ ማንነታችንና አገራችንን ለማስተዋወቅ ብንችል ደስ ይለናል፡፡ ሁሉም ይህን ያስባል ብዬ እገምታለሁ፡፡ በቡድን ደረጃ እንዲህ አይነት የጎል ደስታ አገላለፅ እንስራ ብለን የመከርነው ነገር የለም፡፡ ግን ቀላል ነገር ነው። በየጨዋታው መግቢያ ላይ ተመካክረን የምናደርገው ነው፡፡ጌታነህ
ልክ ነው ከወዲሁ የተዘጋጅንበት ነገር የለም፡፡ እኔ ግን የማስበው ጎል ያገባው ተጨዋች የሚያሳየውን ደስታ አገላለፅ በመከተል የምንፈልገውን ጭፈራ የምናሳይ ይመስለኛል፡፡ አሁን አዳነ አግብቶ ኦሮምኛ ቢጨፍር እሱን አጅበን ነው ኦሮምኛ የምንጨፍረው። ጎል አግቢው ያሳየውን የደስታ አገላለፅ ሁላችንም የቡድኑ አባላት በደስታ የምንጋራው ይመስለኛል፡፡ አስቀድመን ብንዘጋጅም ባንዘጋጅም በአንድ መንፈስ ማራኪ ደስታ አገላለፅ እንደምናሳይ አውቃለሁ፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ስኬታማ እየሆነ መጥቷል፡፡ የዚህ ልዩ ብቃት ምስጢር ምንድነው? የቀድሞዎቹ ቡድኖች ግብ አያስቆጥሩም ነበር፤ ከሜዳ ውጭ ማሸነፍም ሆነ ነጥብ መጋራት በጣም ሲከብዳቸው ቆይቷል። አሁን ግን ከሜዳ ውጭ ግብ ማስቆጠርና ነጥብ ይዞ መውጣት እየተለመደ ነው፡፡ አስቀድሞ ቢገባም ከኋላ ተነስቶ ግብ በማስቆጠር ውጤት ማስጠበቅ እየተቻለ ነው። ይህ አይነቱ ስኬት በአጋጣሚ የሚገኝ አይደለም፡፡ ለሚታዩት ለውጦች አበይት ምክንያቶች ምንድን ናቸው?አዳነ
የመጀምሪያው ምክንያት ይህን ቡድን ለረጅም ጊዜ ሲያሰለጥን የቆየው አንድ አሰልጣኝ መሆኑ ነው። ከዚህ በፊት እንደሚታወቀው የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ በየጊዜው ይቀያየራል፡፡ ይህም ቋሚ ቡድን ለመስራት የሚያመች አልነበረም፡፡ የአሰልጣኞች መቀያየር በየጊዜው በአዳዲስ ልጆች ወጥ አቋም ሊኖረው የማይችል ቡድን መስራትን ያስገድዳል፡፡ ይህ ደግሞ የውጤት እንቅፋት ነው፡፡ አሁን ያለው ብሄራዊ ቡድን ለሁለት ዓመታት በአንድ አሰልጣኝ ሲገነባ እና ሲሰለጥን የቆየ ነው። ብዙዎቻችን አንድ ላይ ሆነን እሰከ 10 ጨዋታዎች አድርገናል። ይሄ ሁኔታ የቡድኑ ተጨዋቾች አብረን በመስራት ለረጅም ጊዜ እንድንቆይ ከማድረጉም በላይ፣ ከፍተኛ መግባባት እና መተዋወቅ ፈጥሮልናል፡፡ ጥሩ እና አሳማኝ ብቃት ያላቸው አዳዲስ ተጨዋቾች በየጊዜው ወደ ብሄራዊ ቡድኑ ይገባሉ፡፡ በየጨዋታው አዲስ ቡድን አዲስ ስብስብ እየተሰራ አልነበረም፡፡ ለየትኛው ቡድን ውጤታማነት ይሄ አይነቱ የቡድን መዋቅር እጅግ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል፡፡ጌታነህ
በአዳነ አስተያየት ላይ የምጨምረው ቢኖር ባለፈው አንድ አመት ተጨዋቾችን በየጊዜው መቀያየር እና ቡድን ማፍረስ አልነበረም፡፡ ይህ ቡድን አዲስ ተጨዋች ቢጨመርበት እንጅ ባለፉት 10 ጨዋታዎች ቋሚ ልጆች አብረን ቆይተናል፡፡ ከዚህ ቀደም በየጊዜው አሰልጣኝ ሲቀያየር፤ ወደ ብሄራዊ ቡድን የሚመጣው አዳዲስ ስብስብ ችግር ነበረው፡፡አዳነ
የአመጋገብና የስነልቦና ባለሙያዎች ከቡድኑ ጋር መስራታቸውም ሌላ ለውጥ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች በቡድኑ የተሰባሰቡ ተጨዋቾች በሁሉም ረገድ ተዋህደው እና ተግባብተው በአላማ እንዲሰሩ ምክንያት ነበር። የትኛውም የቡድን ተጨዋች ከሌላ የቡድን አጋሩ ጋር የመግባባት ችግር የለበትም፡፡ በሜዳ ላይም ሆነ ከሜዳ ውጭ ባለ ብቃት እና ባህርይ የሚጣጣም እና የሚግባባ ነው፡፡ አሁን በብሄራዊ ቡድን ያለው የተጨዋቾች ስብስብ ተበትኖ አንድ ሳምንት ልምምድ ሳይሰራ ቆይቶ በድጋሚ ቢሰባሰብ በቀላሉ ተቀናጅቶ ለመስራት አይከብደውም፡፡የብሄራዊ  አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ብሄራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈው በተደረገው የማጣርያ ድልድል በተፈጠረለት ምቹ እድል ነው ይላሉ፡፡ የተወሰኑ ደግሞ ስኬቱን ተዓምር ያደርጉታል፡፡ ለዚህ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ወሳኝ አጋጣሚ የምትሉት ምንድነው? አዳነ
በአፍሪካ ዋንጫው ማጣርያ በተለይ ከሜዳ ውጭ ከቤኒን ጋር ተጋጥመን በአቻ ውጤት ነጥብ ተጋርተን ስንወጣ ወሳኙ አጋጣሚ ተፈጥሯል ብዬ አምናለሁ። ከቤኒን ጋር እዚህ በሜዳችን 0ለ0 ወጥተን፣ በመልስ ጨዋታ ወደዚያ አቅንተን ከሜዳችን ውጭ፤ በሌሎች ደጋፊዎች ጩኸት ተከበን የተጫወትን ሲሆን፣ አንድ እኩል በመውጣት ወደ ቀጣይ የማጣርያ ምእራፍ ያለፍነው ከፍተኛ መስዕዋትነት ከፍለን ነው፡፡ጌታነህ
በማጣርያው ያደረግናቸው ጨዋታዎች በሁለት ምእራፍ የተደረጉ ቢሆንም አራት ጨዋታዎች አድርገናል። ይህ ማለት እንግዲህ ማጣርያው በምድብ የተዘጋጀ ቢሆን የቀረን ተጋጣሚ አንድ አገር ብቻ ብቻ መሆኑ ነው፡፡ በምድብ ማጣርያ ሦስት፤ በሜዳችን ሶስት ከሜዳ ውጭ ሦስት በአጠቃላይ ስድስት ጨዋታዎች ነበር የሚደረገው። በሁለት ዙር በተካፈልነው ማጣርያ ያደረግነው ሁለት በሜዳችን ሁለት ደግሞ ከሜዳ ውጭ አራት ጨዋታዎች ነው፡፡ ስለዚህ የማጣርያው አይነት ብዙም እድል የሚፈጥር አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።አሉላ
ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈው ብሔራዊ ቡድን እንደ ቤተሰብ የተጠናከረ የቡድን ስብስብ አለው። ውጤታችን የህብረት ነው፡፡ በአገር ፍቅር መንፈስ የተገኘ ነው። በስነልቦናና በስነምግብ የነበረን አጠቃላይ ዝግጅትና አደረጃጀት ከፍተኛ ኃላፊነት ውስጥ ከቶን ነበር። ብሔራዊ ቡድኑ በከፍተኛ ልምምድ ነው ተገቢውን ብቃትና ጥንካሬ ሊያገኝ የቻለው፡፡
የአትዮጵያ እግር ኳስ ለበርካታ አመታት በፌደሬሽን ውዝግብ በአገር ውስጥ ሊግ አለመጠናከር እና በተለያዩ ምክንያቶች ተዳክሞ ቆይቷል፡፡ በእግር ኳሱ ዛሬ ለተከፈተው አዲስ የለውጥ እና የእድገት ምእራፍ በር ከፋች የሆኑ ክስተቶች እና ምክንያቶችን ልትነግሩኝ ትችላላችሁ?አዳነ
ካለፉት አምስት አመታት ወዲህ ለውጦች እየተፈጠሩ መጥተዋል፡፡ በተለይ አስቀድሞ የነበረው የፊርማ ክፍያ 35 ሺ ነበር፡፡ በ2000 ዓም እኔ ወደ ጊዮርጊስ ስገባ ወደ 70ሺ ብር አደገ፡፡ ይህ ብሩህ ተስፋ ነበር፡፡ ለብዙ ተጨዋቾች መነሳሳትም ምክንያት ሆኗል፡፡ አሁን የፊርማ ክፍያ በአማካይ እስከ 400ሺ ብር ነው፡፡ ከፍተኛው እስከ 800ሺ ብር ደርሷል። ተጨዋቾች ጠንክሮ ለመስራት ይሄ ጥቅም በቂ ምክንያት ይሆናቸዋል፡፡ጌታነህ
ከጊዮርጊስ ክለብ ባሻገር የፊርማ ክፍያ በሌሎች ክለቦች ባለሃብቶች ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራበት መጀመሩም ሌላው የለውጥ በር ከፋች ይመስለኛል። አሁን እኔ በደደቢት ክለብ በ75ሺ ብር ፊርማ ስገባ የባለሃብቶች ትኩረት ወደሌሎች ክለቦች መስፋፋቱን ያሳየ ነበር፡፡ በደደቢት ክለብ ለተጨዋቾች ብቃት ማደግ ይሄው የፊርማ ክፍያ ከፍተኛ መነሳሳት እየፈጠረ ነው። ሁላችንም ተጨዋቾች ጠንክረን የምንሰራው ነገ ደህና የፊርማ ብር በማግኘት ለመጠቀም ነው፡፡ በብዙ ክለቦች የተጨዋቾች ደሞዝ እኩል ነው፡፡ የሚለያየን የፊርማው ክፍያ ነው፡፡አሉላ
እግር ኳስ ከኢኮኖሚ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በአገራችን እግር ኳስ የመዕለ ንዋይ ፍሰት እየጨመረ መምጣቱ እየታየ ላለው ለውጥና እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰው በገንዘብ አቅም ነው፡፡ የዚህ ዘመን ተጨዋቾች በእግር ኳስ ከፍተኛ ስኬት እያገኛችሁ ነው፡፡ ስኬታማነት አድናቆት እና ዝና ያመጣል፡፡ ዝነኛ መሆን ደግሞ አንዳንዴ ያዘናጋል፡፡ አዳነ
ስኬታማ ሲሆኑ አድናቆት እንደሚኖር ሁሉ፤ ስኬታማ ባለመሆንም ትችት ያጋጥማል። ስለሆነም አድናቆት ለእኔ ብዙ አይገርመኝም፡፡ አድናቆቱንም ትችቱንም ተላምጄዋለሁ፡፡ አድናቆት የሚያዘናጋ አይመስለኝም፡፡ ያው እንደምታውቀው የምጫወትበት ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ብዙ ደጋፊ ያለው ነው፡፡ አንዳንዴ በጨዋታ ላይ ሃትሪክ ስሠራ ከፍተኛ አድናቆት አገኛለሁ። ደጋፊዎች ያለናንተ ሰው የለም ሁሉ ይሉናል፡፡ በጨዋታ ላይ ደጋፊዎች ስሜን እየጠሩ ሲያወድሱኝ በውስጤ ጥሩ ስሜት ይፈጥራል። ግን አልኮፈስበትም፡፡ የደጋፊ ባህርይ ነገ ጥሩ ካልሆንክ ደግሞ ወደ ስድብ ይቀየራል፡፡ በርግጥ ለምን ተሰደብኩ ብዬ አልናደድም፡፡ ደጋፊዎች በብቃቴ ጥሩ አለመሆን ተበሳጭተው የፈለገውን ቢሰድቡኝ ምንም አይመስለኝም፡፡ ቤተሰቤን ሲነኩ ግን ደስ አይለኝም፡፡
እግር ኳስ ስሜታዊ ያደርጋል፡፡ በስሜት የምትሳደበውና የምትተቸው ደግሞ ጥላቻ ነው ብዬ አላስብም፡፡ አሉላ
አሁን የደረስንበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ መስዋዕትነት ከፍለናል፡፡ ያገኘነው ስኬት ደግሞ ብዙ አድናቆት አትርፎልናል፡፡ ምንያህል
ከታዳጊነቴ ጀምሮ በርካታ ድጋፍ ባለው የቡና ክለብ መጫወቴ ከአድናቆት ጋር አላምዶኛል፡፡ አድናቆት ኃላፊነትን ይጨምራል፡፡ በምትሠራው፣ በምታደርገው ሁሉ ጥንቁቅ ያደርግሃል፡፡ አድናቆት ክብር ያመጣል፡፡ እናም በክብር እንቀበለዋለን፡፡ ዩሱፍ
የኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፍ በጣም ደስ የሚል ነው። በደቡብ አፍሪካም ብዙ ድጋፍ እንደሚጠብቀን አውቃለሁ፡፡ አድናቆት ለተሻለ ውጤት ያነሳሳል፤ ትበረታታለህ፡፡ በጣም ደስ ይልሃል፡፡ የተሻለ ትሠራለህ። በሙያህ አድናቆት እንዲኖርህ ትፈልጋለህ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኑን በተሳካ ሁኔታ ለመቀላቀል በመቻሌ የክለቤ ኃላፊዎች፣ የቡድን አጋሮቼ እና በስዊድን ያሉ ቤተሰቦቼ እጅግ በጣም ተደስተዋል፡፡ እርግጠኛ ነኝ፣ ብዙዎቹ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተሰልፌ በደቡብ አፍሪካ በሚደረገው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ስሳተፍ በትኩረት ሁሉንም ይከታተላሉ፡፡
እንግዲህ የኢትዮጵያ ህዝብ ስፖርት አፍቃሪ ነው። ባለፉት 30 ዓመታት አትሌቶች በኦሎምፒክና በዓለም ሻምፒዮና መድረክ ባስመዘገቡት ውጤቶች ሲኮራና ሲደሰት ኖሯል፡፡ አሁን የእናንተ ትውልድ ለአፍሪካ ዋንጫ ካለፈ በኋላ በእግር ኳሱ እያበደ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ተወዳጅ ስፖርት እግር ኳስ ነው አትሌቲክስ?ጌታነህ
ለኢትዮጵያ ህዝብ ተወዳጁ ስፖርት እግር ኳስ ነው የሚመስለኝ፡፡ ለአፍሪካ ዋንጫ ባለፍን ወቅት በመላው አገሪቱ ህዝቡ አደባባይ ወጥቶ ደስታውን የገለፀበትን ሁኔታ ስትመለከት ይህን ለማለት ያስደፍርሃል፡፡ አዳነ
እግር ኳስ የስፖርቶች ንጉስ ነው፡፡ ለምን ብትለኝ እግር ኳስ የቡድን ስራን መሠረት አድርጐ ውጤት የሚገኝበት መሆኑ ተወዳጅ ያደርገዋል፡፡ ሩጫ ብዙውን ጊዜ የአንድ ሰው ጥረት የሚታይበት ነው፡፡ እግር ኳስ የ90 ደቂቃ ልፋት፣ የህብረት ትግል የሚታይበት ነው፡፡ የፉክክር ደረጃውም ከፍተኛ መዝናናት የሚፈጥር ስለሆነ እግር ኳስ ከሩጫ ይልቅ ተወዳጅ ይመስለናል፡፡ ዮሴፍ
በልቤ እግር ኳስ የማስበልጥ ቢሆንም ለኢትዮጵያውያን አትሌቲክስ ኩራት መሆኑን አውቃለሁ፡፡ እግር ኳስ ግን እጅግ ግዙፍና ትልቅ ስፖርት ነው፡፡ ምን ያህል
የህዝቡን ቀልብ የሚስበው እግር ኳስ ነው፡፡ በፊት በውጤቱ አለመኖር ፍቅሩ ቀንሶ ሊሆን ይችላል። አሁን የተገኘው ስኬት የኢትዮጵያ ህዝብ ለእግር ኳስ ፍቅር የተገዛ መሆኑን አስመስክሯል፡፡ እግር ኳስ ቅጽበታዊ ውሳኔን የሚጠይቅ፣ ከፍተኛ የፉክክር ደረጃ ያለው መሆኑ ልዩ ስፖርት ያደርገዋል፡፡
እስቲ በቅጽል ስያሜዎች ዙሪ እናውራ፡፡ የብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች ልዩ ልዩ ቅጽል ስሞች አላቸው፡፡ አሁን አዳነ አዴ፣ ወፍጮ ይሉሃል፣ ጌታነህስ ማን ብለው ነው የሚጠሩህ? አዳነ
ወፍጮ ብለው የሚጠሩኝ ደጋፊዎች ምን ማለታቸው እንደሆነ ከሌላ ነገር ጋር የሚያያዙት አሉ፡፡ እኔ ግን እንደስድብ የሚቆጠር ቅጽል ስያሜ ቢሆን እንኳን ምንም አይመስለኝም፡፡ አሁን የቡና ደጋፊዎች ወፍጮ ብለው እየጠሩ ሊሰድቡኝ ሲሞክሩ የሚገርምህ እልህ ውስጥ ገብቼ ከፍተኛ ውጤት ለማግኘት እነሳሳለሁ፡፡ ጌታነህ
አሁን አዳነን ወፍጮ ሲሉት ብዙ ምግብ ይበላል ከማለት ጋር የሚያያዙት ይኖራሉ፡፡ ይህ ስም የወጣለት ግን በሜዳ ላይ ሲጫወት በነበረው ሚና ነው፡፡ በአንድ ጨዋታ ላይ አዳነ ተሰልፎ የተቃራኒ ቡድን ተጨዋቾችን እየተጋፈጠና እየተጋጨ ሲጫወት ተመልክተው ነው አሰልጣ ሰውነት ይሄን ስም ያወጡለት፡፡ ስላደነቁት የወጣ ቅጽል ስም መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ለነገሩ አዳነ ለብዙ የቡድን ተጨዋቾች ቅጽል ስም በማውጣትም ይታወቃል፡፡ እኔን አሁን ገዬ ነው የሚለኝ፡፡ አዳነ
በቅጽል ስም ሰው የምጠራው ሙሉ ስም መያዝ ልማዴ አልሆን ብሎ ነው፡፡ በተለይ በጨዋታ ላይ ከቡድን አጋሮቼ ጋር ለመግባባት እዚያው የመጣልኝን አጠራር እጠቀማለሁ፡፡ የቡድን ልጆች ይህን አጠራሬን ሰምተው ያፀድቁታል፡፡ አሁን ጌታነህን ኳስ እንዲያቀብለኝ ስፈልግ ጌታነህ ብዬ ከምጠራው የመጀመሪያውን ፊደል "ገ" እና ለማቆላመጥ "ዬን" ጨምሬ ገዬ ብዬ እጠራዋለሁ፡፡ ለአንዳንዶቹ ደግሞ ከአጨዋወታቸው እና ከድርጊታቸው ተነስቼ ስም አወጣላቸዋለሁ፡፡ አሁን አምበላችንን ደጉን "ስለ"ብዬ የምጠራው፡፡ ዩሱፍ
ብሄራዊ ቡድኑን ከተቀላቀልኩ በኋላ ሜዳ ላይ ብቻዬን ኳስ ሳንጠባጥብ አሰልጣኙ ተመልክተው በቃ የውጭ አገር ሰው መሆንህ ቀርቷል፡፡ አሁን አበሻ፣ እንደውም ጐንደሬ ሆነሃል አሉኝ፡፡ ይህንኑ ተቀብሎ ተጨዋቹ ሁሉ "ጐንደሬ" ይለኝ ጀመር፡፡ የቡድን አጋሮቼ በዚያ ሲጠሩኝ ደስ የሚላቸው ከሆነ ብዬ ተቀብዬዋለሁ፡፡ በስዊድን ስጫወት በአባቴ ስም ሳላህ ብለው ይጠሩኛል ፡፡ ምን ያህል
በክለብ ደረጃ መጫወት ስጀምር እናትና አባቴ ባወጡልኝ ስም ነበር የምጠራው፡፡ ድሮ ከሰፈር ጀምሮ ግን የወጣልኝ የቅጽል ስም ቤቢ ነው፡፡ አሁን ከፍተኛ ዕውቅና ካገኘሁ በኋላ ዋናው ስሜ ምንያህል መታወቅ ጀመረ እንጂ ብዙ ሰው ቤቢ እያለ ነው የሚጠራኝ፡፡ በቅጽል ስም መጠራራት ያዝናናል፡፡
ባለፈው ሰሞን እውቁ የአርሰናል አሰልጣኝ አርሴን ቬንገር ስለአፍሪካ ዋንጫ ተጠይቀው ባልተጠበቀ ሁኔታ ኢትዮጵያን ጠቅለዋል፡፡ በዘንድሮ የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ አለችበት፣ ግን ከኢትዮጵያ ቡድን የአምስት ተጨዋቾችን ስም ማንም አያውቅም ብለዋል፡፡ ከዚሁ የቬንገር አስተያየት ጋር ተያይዘው በወጡ ዘገባዎች፣ ኢትዮጵያ በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ የምትሳትፈው ለዓለምና ለቬንገር ማንነቷን ለማሳወቅ ነው ብለዋል፡፡ እኔ በበኩሌ የቬንገር አስተያየት የብዙ አሰልጣኞች፣ የእግር ኳስ መልማዮችና የዝውውር ደላሎችን ቀልብ የሚስብ የዝውውር ጥሪ ይመስለኛል፡፡ እናንተስ?አዳነ
የቬንገር ንግግር ያለምክንያት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የሚታወቅ ምንም ፕሮፌሽናል ተጨዋች ስለሌላት ይመስለናል፡፡ እኛ እግር ኳስ ሙያችን አድርገን የምንጫወት ፕሮፌሽናሎች ብንሆንም የምንወዳደርበት ፕሮፌሽናል ሊግ አለመኖሩ ዕውቅናችንን ቀንሶታል። ብዙውን ጊዜ ግን በእግር ኳስ ዙሪያ ያሉ ባለሙያዎች ለሚታወቁ ተጨዋቾችና ቡድኖች ትኩረት ከመስጠት ይልቅ አዲስ መጤ ለሆኑት ይጓጓሉ፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ቬንገር ኢትዮጵያን በተለይ ሊጠቅሱ የቻሉት፡፡ እነ ጋና፣ ናይጀሪያ ይታወቃሉ ታይተዋል፡፡ ኢትዮጵያን ግን ማንም አያውቃትም፡፡ ቬንገር ብቻ ሳይሆኑ ብዙዎች እኛ ላይ ትኩረት ያደርጉብናል፡፡ ጌታነህ
በአፍሪካ ዋንጫ የሚሳተፉ አገራት እነ ናይጀሪያ፣ ጋና፣ እና ሌሎችም በአውሮፓ አሰልጣኞች ይታወቃሉ። ቬንገር ኢትዮጵያን የጠቀሱት ስለማውቃት እናያታለን ብለው ነው፡፡
አሰልጣኝ ሰውነት፣ በአፍሪካ ዋንጫ ራሳችንን እናስተዋውቃለን፣ እናሳያለን ብለው ለቬንገር ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ እስከ ሩብ ፍጻሜ የመድረስም ፍላጐት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው፤ ዋንጫ ባታመጡ እንኳን ጥሩ ተጫውታችሁ አገራችሁን አስጠሩ ብለዋችኋል፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ አፍሪካ ዋንጫ ምን አይነት ውጤት ትጠብቅ?አዳነ
ያለንበት ምድብ ጠንካራ ነው፡፡ የኛ ቡድንም ግን ጠንካራ ነው፡፡ አንዳንድ ሚዲያዎች በተለይ የአገር ውስጥ ቡድናችንን የሚያነሳሳ ግምት ከመሰንዘር ይልቅ በጣም በሚያሳዝን ግምት የቡድናችንን አቅም የሚያወርድ አስተያየት መስጠታቸው ያሳፍራል፡፡ እኛ በቡድናችን ውጤታማነት የራሳችን እምነት እና እቅድ ቢኖረንም ሚዲያው ባለን አቅም ላይ የተሻለ ሞራልና መነሳሳት የሚፈጥር ግምት መሰንዘር ቢለምድ ጥሩ ነው፡፡
አንድ ምሳሌ እዚህ ጋ ልጥቀስልህ፡፡ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን በሚሳተፍባቸው የዓለም ዋንጫና የአውሮፓ ዋንጫ ውድድሮች በአገሪቱ ሚዲያ ከጅምሩ የሚሰጠው ግምት ተጋንኖ ነው የሚቀርበው፡፡ ውድድሮቹ ከመጀመራቸው በፊት በርካታ የእንግሊዝ ሚዲያዎች ቡድናቸውን በሚሰጡት ግምት ለዋንጫ ያጩታል። ተጨዋቾቹ የዓለም ምርጦች መሆናቸውን አድንቀው ይዘግባሉ፡፡ በእኛ አገር ሚዲያዎች ግን አነስተኛ ግምት የመስጠት አባዜ አለ፡፡ አላግባብ የማናናቅ እና የማውረድ ተግባር በተደጋጋሚ አጋጥሟል፡፡ እኛ በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ የምንሳትፈው ራሳችንንም አገራችንንም ወደተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ነው፡፡ የመጀመሪያ ዙር አልፈን ጥሎ ማለፍ ውስጥ መግባት እንፈልጋለን፡፡ ጌታነህ
የመጀመሪያው ዓላማችን ከምድባችን ማለፍ ነው። ከዚያ በኋላ ያለውን የጥሎማለፍ ምዕራፍ በሂደት የመወጣት ፍላጐት ነው ያለኝ፡፡ አሉላ
የእኛ ስብስብ እዚህ ደረጃ መድረሱ አልተጠበቀም ነበር፡፡ ይህን ግምት ፉርሽ አድርጐ ለአፍሪካ ዋንጫ ደርሷል፡፡ እናም በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በሚኖረን ተሳትፎ በተደጋጋሚ እንደተገለፀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ክስተት ይሆናል፡፡ ብዙ እየተወራልን ነው። ዛምቢያ ሳይታሰብ ዋንጫ ወስዳለች፡፡ ማንም ወደ ውድድር ሲገባ ለማሸነፍ ነው ሌላ ትርጉም የለውም። እያንዳንዱን ጨዋታ ለክብር ነው የምንጫወተው። እርግጠኛ ነኝ በዚህ አፍሪካ ዋንጫ በኢትዮጵያ ቡድን ማንም ያልገመተው ውጠት ይመጣል፡፡ ሁሉም ቡድን ዋንጫ ለመውሰድ ያስባል፡፡ እኔ እያንዳንዱን ጨዋታ በትኩረት አድርገን ውጤታማ በመሆን ክስተት ሆነን ለመምጣት እንፈልጋለን፡፡
ዋንጫውን ከወዲሁ አናስብም፤ ከመጀመሪያ ጨዋታ ጀምሮ ትኩረታችን ተመሳሳይ ነው፡፡ ዩሱፍ
ጥሩ ቡድን አለን፡፡ በራሳችን ጨዋታ ማንንም ሳንፈራ በጥሩ ፉክክር እንሳተፋለን፡፡ ቡድናችን ከፍተኛ በራስ መተማመን አለው፡፡ ስለዚህ በማራኪ እግር ኳስ ተሳትፎ እናደርጋን፡፡

መልክአ ኢትዮጵያ ፩

ከከተማ ወጣ ካልኩ ጥሬ ሥጋ አሊያም ጥብስ መብላት ያስደስተኛል፡፡ ይኸው ዛሬ ከአዲስ አበባ ወጥቼ የሚያስጐመዥ ምርጥ ሥጋ እያወረድኩ ነው፡፡ ብቻዬን ግን አይደለሁም፤ ሶምሶን ከተባለው ዘመዴ እና መላኩ ከሚባለው ጓደኛው ጋር ነኝ፡፡ ጥሬ ሥጋ ደስ የሚለው ከሰው ጋር ስብስብ ብለው ሲበሉት ነው፡፡ ሳሚ የሥጋ ቤቱ ደንበኛ ስለሆነ ለዘመድ የሚሆን ምርጥ ሥጋ ነው ያስቆረጠልን፡፡ ሥጋው ለስላሳ ነው፤ ጣዕሙ ደግሞ የጉድ ነው፡፡ መላኩ ቶሎ በልተን እንድንነሳ ስለፈለገ ደጋግሜ ጨዋታ ለመጀመር ያደረኩትን ሙከራ አከሸፈብኝ፡፡ “ቶሎ ቶሎ ብሉ እንጂ” ይላል - እየደጋገመ ጦርነት የመጣ ይመስል፡፡ ከፊት ለፊታችን በትልቅ ረከቦት የቡና ስኒ ተደርድሮ፣ ሣሣ ባለ የዕጣን ጢስ ታጅቧል፡፡ የፈላ ቡና መዓዛ አካባቢውን አውዶታል፡፡የሀገር ባህል ልብስ የለበሰችው የጠይም ቆንጆ ቡናው ተንተክትኮ እስኪወጣለት ትጠባበቃለች፡፡ከዚህ ጀበና ላይ አንድ ስኒ ቡና ለመጠጣት ጐምዥቼ ነበር፡፡ መላኩ ግን ትዕግሥት አልነበረውም፡፡ የደንቡን ለማድረስ እንደተጣደፈ አልጠፋኝም፡፡ “በቃ፣ቡናውን እዚያው ታመጣልናለች እንግባ” አለ፡፡ “ቡናችን ከመጣ ምን ቸገረኝ” ብዬ አብሬው ተነሳሁ፡፡ ሳሚም ተከተለን፡፡ ከነበርንበት ክፍል ወጥተን በስተግራ በኩል ባለው ኮሪደር ዘወር እንዳልን በርካታ ክፍሎች ተደርድረው ተመለከትኩ፡፡ በስተቀኝ በኩል መሀል በሩ ወለል ብሎ የተከፈተ መጸዳጃ ቤት አየሁ፡፡ በመጸዳጃ ቤቱ ወለል ላይ አገልግሎት የሰጠ የመጸዳጃ ቤት ወረቀት በግዴለሽነት ተጥሏል፡፡ የመፀዳጃ ክፍሉ ሽታ ቆይቶም ቢሆን መረበሹ አይቀርም በሚል ያዝ አድርጌ ለመዝጋት ሞከርኩ፡፡ መዝጊያው የተገጠመ መስሎ ተመልሶ ተከፈተ፡፡ ሳይበላሽ አልቀረም፡፡ መላኩ ከተደረደሩት ክፍሎች የአንደኛውን መዝጊያ ገፋ አድርጎ ዘው አለ፡፡ ሳሚም ተከተለው፡፡ እኔም እያመነታሁ ገባሁ፡፡ ክፍሉ ጢቅ ብሎ ሞልቷል፡፡ መጅሊስ ላይ የተቀመጡት በሙሉ አፈጠጡብን፡፡ እንግዳ በመሆኔ ብዙ ዓይኖች ያረፉት እኔ ላይ ነበር፡፡ ከእነዚያ ዓይኖች ለመሸሽ ቀረብ ያለኝ ቦታ አረፍ አልኩ፡፡ ጥቂት ከተረጋጋሁ በኋላ ቀስ ብዬ ዙሪያ ገባውን ማማተር ያዝኩ፡፡ ሳሚ እንደ መላኩ ቤተኛ አለመሆኑ ያስታውቃል፡፡ መላኩ ግን ከሁሉም ጋር ያወራል፡፡ ከፊት ለፊቴ በመጋረጃ የተከለለ ክፍት በር ይታየኛል፡፡ ከመጋረጃው ጀርባ ሌላ ክፍል እንዳለ ገባኝ፡፡ ከበሩ በስተኋላ ፊታቸውን ለእኛ የሰጡ ወጣቶች ተቀምጠዋል፡፡ ነፍሷን በጨርቅ ያንጠለጠለች የምትመስል ቀጭን ልጅ ጉልበቷን ከደረቷ ጋር ገጥማ ተጣጥፋ ተቀምጣለች፡፡ በመልክም በአለባበስም የሚመሳሰሉ ሴትና ወንዶች በመጅሊሱ ላይ ተሰይመዋል፡፡ ከሴቶች ይልቅ የወንዶች ቁጥር በርከት ይላል፡፡ በክፍሉ በስተግራ ጥግ ላይ 42 ኢንች የሚጠጋ ፍላት ስክሪን ቴሌቪዥን ከመሬት ትንሽ ከፍ በምትል ማስቀመጫ ላይ ጉብ ብሏል፡፡ አጠገቡ ከተቀመጠ ተለቅ ያለ የሲዲ ማጫወቻ የአብዱ ኪያርን “እቴ ሜቴ የሎሚ ሽታ” ዘፈን በቀስታ ያጫውታል ቤቱ ውስጥ ጐልቶ የሚሰማው ግን ዘፈኑ ሳይሆን ሌላ ድምፅ ነው፡፡ “…ዱቅ…ዱቅ…ዱቅ” ያደርጋሉ የቤቱ ታዳሚዎች - በየተራ፡፡ አንዱ ሲያቋርጥ ሌላው ይቀጥላል፡፡ ከአፋቸው የሚወጣው ወፍራም ጭስ ቤቱን በከፊል አዳምኖታል፡፡ ሁሉም ሺሻ እያጨሰ ነው፡፡ በየሰው ፊት ባለው ጠረጴዛ ላይ የኮካ ጠርሙሶች እና ውኃ የያዙ ፕላስቲኮች ተቀምጠዋል፡፡ ነጭ የሻይ ሲኒዎች ከማንኪያ ጋርም ይታያሉ፤ ሻይ መስሎኝ ነበር፡፡ ግን አይደለም፡፡ ምን እንደሆነ ለማወቅ ጓጉቼአለሁ፡፡ ቀጠን ያለች ጠይም አስተናጋጅ ሁለት የሺሻ ጠርሙሶች አምጥታ አጠገባችን አኖረች፡፡ ‹‹ሙአሰል›› ተሞልተው ፎይል የተጠቀለሉ ቡሪዎች (የሚጨሰው ነገር ተሞልቶ አናታቸው ከተበሳ በኋላ ከጠርሙሱ ላይ የሚቀመጡ ሸክላዎች) አምጥታ አስቀመጠችበት፡፡ ያመጣችውን እሳት በቀጭን መቆንጠጫ እያነሣች ቡሪው ላይ አደረገች፡፡ ሺሻውን አዘጋጅታ ከጨረሰች በኋላ ፊት ለፊታችን ተቀምጣ ትምገው ጀመር፡፡ በአጫሾች ቋንቋ ማቀጣጠል (ማፈንዳት) ይባላል፡፡ አንዱን ሺሻ ልቧ እስኪጠፋ ስባ ጭስ ማውጣት ሲጀምር፣ ለአንዱ አጫሽ አቀበለችው እና ሁለተኛውን ተያያዘችው፡፡ እኛ በተቀመጥንበት መደዳ በስተግራ በኩል ካለው የኋላ በር ቀጭን፣ ፀጉሩን ወደ ላይ ያቆመ ወጣት እሷ ያመጣችው ዐይነት የእሳት ማቀጣጠያ ፍም ከመሰለ እሳት ጋር ይዞ ወጣ፡፡ ፊቱ ላይ አመድ ቦኖበታል፡፡ እሳት ሲያቀጣጥል እንደነበር መገመት አላቃተኝም፡፡ ሳሚ እና መላኩ ሺሻቸውን እየሳቡ ጨዋታ ይዘዋል፡፡ እስካሁን የነገርኳችሁ ሁሉ የተከሰተው ኢትዮጵያ ውስጥ ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ በሚገኝ አንድ አካባቢ ሊመስላችሁ ይችላል፡፡ ነገር ግን አሜሪካ ነው፡፡ ሺሻ ቤቱም ያለው ቁርጥ ሥጋ ካወራርድንበት ቤት በስተኋላ፡፡ በጆርጂያ ግዛት አትላንታ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ********* ቅድም ሻይ ከመሰለኝ ብርጭቆ ነገር ውስጥ አንድ ሁለቱ የቤቱ እንግዶች በማንኪያ እያወጡ ወደ አፋቸው ሲልኩ ተመለከትኩ፡፡ ሺሻ እያጨሱ በየመሃሉ በማንኪያ የሚበሉት ነገር ምን እንደሆነ መላኩን ጠየቅኹት፡፡ “ሺሻው በደንብ ይሙቅ ብለን ነው እንጂ እኛም አለን እኮ፤ እንደውም ቆይ ላምጣው” አለና ተነሥቶ ወጣ፡፡ መላኩ በላስቲክ ይዟት የመጣውን የታሰረች ትንሽ ነገር ተቀብዬ ፈታኹት፡፡ ክው ብሎ የደረቀ ኮሰረት የሚመስል ነገር ነው፡፡ የአሜሪካ አገር ‹‹ጫት›› ይሄ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከደረቀ በኋላ በተለያየ መንገድ ወደ አሜሪካ እንደሚገባ ተነገረኝ፤ አስመጪዎቹም ሻጮቹም በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ኤርትራውያን፣ ሶማሌዎች እና ጥቁር አሜሪካውያንም የዚህ ንግድ ተሳታፊዎች መሆናቸውን ሰምቻለሁ፡፡ እንደኔ ለምለም ጫት እያየች ላደገች የድሬ ልጅ “የደረቀ ኮሰረት” የመሰለ ነገር “ጫት” ነው ብሎ ለመቀበል ያዳግታል፡፡ ያ ቀልቡ የራቀው አስተናጋጅ በሻይ ቅመም የፈላ ውኃ በሻይ ብርጭቆ ከሻይ ማንኪያ ጋር አምጥቶ ለመላኩ ሰጠው፡፡ እሱም ያንን የደረቀ ጫት ብርጭቆ ውስጥ ከቶ በማንኪያ ገፋ ገፋ እያደረገ ወደ ውስጥ አስገባው፡፡ ከጥቂት ደቂቃ በኋላ “ጫቱ ራሰ” ተባለና በማንኪያ እያወጣ መጉረስ ጀመረ፡፡ ሳሚ ግን የራሰውን አልፈልግም ብሎ ደረቁን እንደብስኩት ከሽ ከሽ እያደረገ ያኝከው ገባ፡፡ ሰዓቱም እየገፋ ወጪ ገቢውም አንዴ እየቀነሰ አንዴ ደሞ እየጨመረ ቀጠለ፡፡ ጆንያ መሳይ ጣራ ያላት የአትላንታዋ ጫትና ሺሻ ቤት እየጋለችና እየታፈነች መጣች፡፡ አሁን እኔም ከማላውቃቸው ወጣቶች ጋር ትውውቅ ፈጥሬ ወሬ ጀምሬአለሁ፡፡ ድንገት ከመጋረጃው ውስጥ ሁለት ወጣቶች እየተጨቃጨቁ ወጡ፡፡ አንዱ የሌላኛውን ወጣት ስልክ በእጁ ይዟል፡፡ “ክፈለኝ፣ አለበለዚያ ይህን ስልክ አልሰጥም፤ በ163 ዶላር እሸጠዋለሁ” ሲለው ችግር እንዳለ ገባኝ፡፡ “ከፈለግህ ሽጠው እንጂ እኔ ያለኝን ገንዘብ ጨርሻለኹ” አለ ሌላኛው ወጣት፡፡ ስልኩ የተያዘበት ልጅ የሚቀልድ እንጂ ከልቡ የሚያወራ አይመስልም፡፡ አንደኛው ወጣት በእጁ የያዘውን ‹‹አይፎን 5›› ስልክ ወደ ላይ ከፍ አድርጎ “ይህን ስልክ በ163 ዶላር የሚገዛ?” ሲል ጠየቀ፡፡ ነገሩ ምን እንደሆነ ባይገባኝም “እኔ” ብዬ እጄን አወጣኹ -እንደ ልጅነቴ፡፡ ሁሉም ሰው ዓይኑን እኔ ላይ ወረወረ፡፡ ግማሹ ፈገግ ሲልልኝ፤ ከፊሉ ደግሞ ኮስተር አለብኝ፡፡ ልጁ ቀጥ ብሎ ወደኔ በመምጣት ስልኩን አቀበለኝና ወደባለቤቱ እያሳየኝ፤ “እኔ ስጭው ሳልልሽ እንዳትሰጪው፤ ገንዘቡን ካላመጣ ባልኩት ዋጋ ትወስጂዋለሽ” አለኝ - ኮስተር ብሎ፡፡ ሳላስበው የማላውቀው አጉል ጨዋታ ውስጥ እየገባሁ እንደሆነ ተሰማኝ፡፡ ልጁ ዞር ሲልልኝ ፊቴን ወደ መላኩ መልሼ “እዚያ ክፍል ውስጥ ምንድነው የሚሠሩት?” ስል ቀስ ብዬ ጠየኩት፡፡ ባለስልኮቹ ወደወጡበት ክፍል እየጠቆምኩት፡፡ “ቁማር እየተጫወቱ ነው” አለኝ ዘና ብሎ፡፡ ነገሩ እንግዳ የሆነብኝ እኔ እንጂ ለእርሱ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ “የምን ቁማር?” ስል ጠየቅኹት፤ “የገንዘብ ነዋ! አንዱን መደብ በ50 ዶላር እያስያዙ ቁማር በካርታ ይጫወታሉ፡፡ ቀኑን ሙሉ እዚህ የሚውሉ አሉ፤ ከሥራ የሚመጡ አሉ፤ ክፍተት ሲያገኙም ሥራ አቋርጠው የሚመጡ አሉ፤” በማለት አስረዳኝ፡፡ መላኩ የቤቱን ደንበኞች አንድ በአንድ ያውቃቸዋል፡፡ ሱሰኞች የሚባሉትን ለይቶ አሳየኝ፡፡ “በጓሮ በር ወጣ ገባ የሚሉት ደግሞ የያዙት ገንዘብ ሲያልቅባቸው ከካርዳቸው ላይ በማሽን ለማውጣት የሚሄዱ ናቸው፡፡ሁሉንም ሲጨርሱ እንደ ልጁ ስልክ ያስይዛሉ” አለኝ፡፡ “ወይ የቁማር ነገር!” አልኩኝ ለራሴ፡፡ አኩርፈው የሚቀመጡት ደግም ብዙ ገንዘብ የተበሉ እንደሆኑ መላኩ ነገረኝ፡፡ ልጁ የሰጠኝ ስልክ እጄ ላይ እንዳለ ሲጠራ ለባለስልኩ ልሰጠው ስል ከግራ ቀኝ ጮኹብኝ፤ “ስጪ ሳትባይ መስጠት የለም” እያሉ፡፡ አሁን ቁማሩ የምር እንደሆነ ገባኝ፡፡ እነሱ ወደሚጫወቱበት ክፍል መግባት ፈለግኹ፡፡ ለባለሺሻ ቤቱ የመቀመጫ 5 ዶላር፣ የመደብ ደግሞ 50 ዶላር ከፍዬ የካርታው አባል ካልሆንኩ መቀላቀል እንደማልችል ሳሚ ሹክ አለኝ፡፡ ስልክ ያዡም አስያዡም ተመልሰው ወደ ቁማር ክፍሉ ሲገቡ አየኋቸው፡፡ እኔ ስልኩን እንደያስዝኩ ከተቀሩት ጋር ጨዋታዬን ቀጠልኩ፡፡ መላኩ የታክሲ ሹፌር ቢኾንም የከተማው ከንቲባ ነው የሚመስለው፡፡ ሁሉንም ያውቃቸዋል፡፡ ከቤቱ ደንበኞች ጋር ያለውን ትውውቅ ነገረኝ፡፡ “እነዚህ ጅንስ ቲሸርት ምናምን የለበሱት የታክሲ ሹፌሮች ናቸው፣ ከሴቶቹ ውስጥ ሁለቱን ነው የማውቃቸው፤ አንዷ የሬስቶራንት አንዷ ደግሞ የናይት ክለብ አስተናጋጆች ናቸው፤ ዛሬ ዕረፍታቸው ነው መሰለኝ…” አለኝ፡፡ ሌሎቹን ሴቶች ግን አያውቃቸውም፡፡ የአንደኛቸው ጓደኞች ሳይሆኑ እንደማይቀሩ ግምቱን ነገረኝ፡፡ ሌሎች ሁለቱ ደግሞ በሚሊዮን ዶላር የሚያንቀሳቅሱ እንደሆኑ ነገረኝ፡፡ የገንዘብ ምንጫቸው ምን እንደሆነ ባይታወቅም፡፡ ሐሺሽ ይነግዳሉ እየተባሉ እንደሚታሙ አልደበቀኝም፡፡ “ሱፍ የለበሱትስ?›› ስል ጠየቅሁት -ወደ ጎልማሶቹ እያየሁ፡፡ ‹‹የሊሞዚን ባለቤቶች ናቸው፡፡ ሊሞዚን የሚነዳ ሰው ሙሉ ሱፍ መልበስ ግዴታው ነው” ሲል መለሰልኝ፡፡ “እንደዚህ ቁጭ ብለው እየዋሉ ምን ሰዓት ነው የሚሠሩት?” ስል ጠየቅሁት “የታክሲ እና የሊሞዚን ሥራ ቁማር ነው፤ አንዳንዴ ይኖራል አንዳንዴ ደግሞ ይጠፋል፡፡ ልምዱ ያለን ልጆች ሥራው ላይ ችክ አንልበትም፡፡ ስለምናውቀው ሥራ ሲኖር እንወጣለን፣ ከሌለ ደግሞ ዘና እንላለን፡፡ ባለሊሞዚኖቹም ሥራ ሲኖር ይደወልላቸዋል፡፡ በዛ ላይ ብቅ ብለን ጨስ ጨስ አድርገን ውልቅ እንላለን እንጂ እንደቁማርኞቹ አፋችን ላይ ተክለን አንውልም” አለኝ፡፡ ፓርኪንግ እና ነዳጅ ማደያ የሚሠሩ እንዲሁም የት እንደሚሠሩ የማይታወቁ ደንበኞችም እንደሚመጡ አጫወተኝ፤ ወደ ሳሚም ዞር ብሎ “ለምሳሌ እሱ እኔ ይዤው ካልመጣኹ ብቻውን አይመጣም፡፡ እዚህ ከሚመጣ ቤቱ ቁጭ ብሎ ከሚስቱ ጋር ቢያጨስ ነው የሚመርጠው” አለኝ፡፡ ሳሚ ሣቅ አለ፡፡ ሺሻ በአሜሪካ እየተስፋፋና እየተለመደ የመጣ ነገር እንደሆነ ተገነዘብኹ፡፡ መላኩ ልክ ነበር፤ ሳሚ ከሚስቱ ጋር ቁጭ ብሎ ሲያጨስ ቤቱ አይቸዋለሁ፡፡ አሁን ያለሁባት ቤት ከእነዚያ ትለያለች፡፡ መተሐራ ካየኋት ጋራ ትመሳሰላለች፡፡ ከአዲስ አበባ ወደ ምሥራቅ በተለይ በምሽት የሚጓዝ ሰው መተሐራን ሳይረግጥ አያልፍም፡፡ እኔም በዛ መንገድ ላይ በምሽት እየተወነጨፉ በሚሄዱት ሚኒባሶች ተሳፍሬ ብዙ ጊዜ ተመላልሻለሁ፡፡ በመኪና መንገዱ ላይ በከተማዋ እንብርት በሚገኙት ምግብ ቤቶች ተመግቤያለሁ፡፡ ወደ ጓሯቸውም ዘወር ብዬ ሺሻ ቤቶቻቸውን ጐብኝቻለሁ፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀንም ስለነሱ ጽፌያለሁ፡፡ የመተሐራ ሺሻ ቤቶች አብዛኛዎቹ ደንበኞች የሚኒባስ፣ የአይሱዙ፣ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች እንዲሁም በምሽት ቡና ቤቶች እና ዳንስ ቤቶች የሚሠሩ አስተናጋጆች ናቸው፡፡ የሚያወጡት ገንዘብ በብር እና በዶላር ካልተለያየ በስተቀር የአትላንታ እና የመተሐራዎቹ ደንበኞች የሥራ ዐይነት ተመሳሳይ ነው፡፡ የመተሐራው ሺሻ ቤቶች አሠራር የተዳከመ ይዞታ ያለው ሲሆን የአትላንታው ደግሞ ዘመናዊ ገጽታ አለው፤ የሁለቱም ቤቶች የመቀመጫ አደራደር ግን አንድ ዓይነት ነው፡፡ የመተሐራዎቹ ሺሻ ቤቶች ለአንድ ቡሪ 10 ብር ሲያስከፍሉ፣ የአትላንታዎቹ ደግሞ ለአንድ ቡሪ 15 ዶላር(280 ብር) ያስከፍላሉ፡፡ ያገመትኩትን የኢትዮጵያውያ የአትላንታ ውሎ በማየቴ ተገረምኩ፤ሱስን ይዞ መሰደድን ምክንያት አጣሁለት ምናልባት አንዳንዶቹ የለመዱት እዛው ሊሆን ይችላል፡፡ ጥቅሙን መጠየቅ ምክር ቢጤም መለገስ አምሮኝ ነበር ‹‹ይኼ እኮ መብት የሚከበርበት አገር ነው›› የሚል አጭር እና ግልጽ መልስ ተሰጠኝ፡፡ የቤቱ ጨዋታ ደርቷል፡፡ የቁማር ቤቱ መጋረጃ ተከፈተ፤ ስልክ ያስያዘኝ ልጅ ስልኩን ለባለቤቱ እንድሰጠው ነገረኝ፡፡ ድጋሚ ተበላልተዋል ማለት ነው አልኩ፡፡ ስልኩን ለባለቤቱ እየመለስኩ፤ “እኔ ደግሞ ስልክ በርካሽ አገኘሁ ብዬ” በማለት ለመቀለድ ሞከርኩ፡፡ “ስልክ ትፈልጊ ነበር እንዴ?” ሲል መላኩ ጠየቀኝ፡፡ ሳሚ ቀደም አለና፣ “ለሷ ነበር እኮ ፈልግ ያልኩህ?” አለው፡፡ ግራ ተጋብቼ ሁለቱንም እየተዟዟርኩ አየሁዋቸው፡፡ ከየት ነው የሚፈልጉልኝ? በርግጥ ዘመናዊ ስልክ መግዛት ፈልጌ ነበር፤ ግን በምድረ አሜሪካ የስልክ መሸጫ ሱቆች ሞልተው እነሱ ከየት ነው የሚፈልጉልኝ? “እኛ ጋ እኮ ስልክ አይጠፋም፡፡ ተሳፋሪ ጥሎ ስለሚወርድ ሁሌ እናገኛለን፡፡ እኔ አገር ቤት ለመላክ ያዘጋጀሁት ነው እንጂ አራት አይፎን ነበረኝ” አለኝ - መላኩ፡፡ ከዚያ ወደ ጓደኞቹ ፊቱን መልሶ ስልክ እንዳላቸው ጠየቀ፡፡ “እስካሁን ለምን አልነገርከንም፤ እኔ የለኝም ቆይ እንትና አለው …” እያሉ ስልካቸውን መጠቅጠቅ ጀመሩ፡፡ “ባለታክሲዎች ዘንድ ስልክ አይጠፋም” አለ፤ቀጠን ያለው የመላኩ ጓደኛ፡፡ “አስቀድመህ ብትነግረኝ ኖሮ ጥሩ ነበር፡፡ ከትናንት በስቲያ ነው ሁለት አይፎን አገር ቤት የላክኹት፡፡ ታገሠኝና ሰሞኑን እንፈልጋለን” አለው፡፡ እናፈላልጋለን የሚሉት እኮ ከደንበኞቻቸው ኪስ ሾልኮ የሚወድቀውን ነው፡፡ “አንዳንዴ ስልክ ሲጠርብኝ ከኋላ ተቀምጠው የሚሳሳሙ ሰዎች ከጫንኹ አውቄ አወዛውዛቸውና ከኪሳቸው እንዲወድቅ አደርጋለኹ” ሲል እየሣቀ ነገረኝ፡፡ ለካ እነሱ “ሿሿ እየሠሩ የሚልኩትን ስልክ ነው እኛ በሿሿ የምንሰረቀው” አልኩ በሆዴ፡፡ የስልኩ ጨዋታ ወደሌላ ጨዋታ ይዞን ነጐደ፡፡ የሚሳሳሙት ደንበኞቻቸው ወንድ እና ሴት ብቻ አይደሉም፡፡ አንዳንዴ ወንድና ወንድ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሴትና ሴት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በዲሲ፣ በሳንፍራንስሲስኮ፣ በቺካጐ እና በአትላንታ ጉብኝቴ ወንድ ለወንድ እና ሴት ለሴት ሲሳሳሙ በዐይኔ ተመልክቻለሁ፡፡ ድርጊቱን ማየት እንደመስማት እና ማውራቱ ቀላል አይደለም፤ለእንደኔ ዓይነቷ ሊብራል ነኝ ባይ እንኳን መሣቀቁ ነፍስን ከሥጋ ያላቅቃል፡፡ ግን ደግሞ ያየሁትን ጽፌ ለማስነበብ ጓጉቼ ስለምጓዝ እየተሳቀቅኹም ቢሆን እንዲህ ያሉትን ቦታዎች ጐብኝቻለሁ፡፡ ኢትዮጵያውያኑም አንዳንዶች እነርሱን ሆነውና መስለው፣ ሌሎቹ ደግሞ ለእነርሱ ተሣቀው፣ ከፊሎቹ ከእነርሱ ጋር እየሠሩ፣ወላጆች ደግሞ ለልጆቻቸው እየሰጉ፣ ጥቂቶች ምንም እንዳልተፈጠረ እየቆጠሩ አብረው ይኖራሉ፡፡ አንድ ማታ እርቃናቸውን የሚደንሱ ሴቶች ያሉበት ዳንስ ቤት ጐራ ብዬ አንዲት ሐበሻ መልክ ደናሽ አይቼአለሁ፡፡በእርግጥ የዜግነቷ ጉዳይ በደንብ የለየለት አይመስልም፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ኤርትራዊ ነች ሲሏት፤ ኤርትራዊያኑ ደግሞ ኢትዮጵያዊት ነች ይሏታል፡፡ ይቺ ሴት እርቃን ገላዋን አጋልጣ ሲያሻት በወንዶቹ ሲላት ደግሞ ከሴቶቹ ጋር እየተሻሸች ዶላር ስትሰበስብ ተመልክቻለሁ፡፡(ይቀጥላል)

Published in ባህል

የስፖርት ውድድርና የኪነጥበብ ዋጋ - በአየን ራንድ ፍልስፍና

ሕይወቱን የሚያፈቅር ሰው፣ ለሦስት ነገሮች ከሁሉም የላቀ ትልቅ ክብር መስጠት እንደሚገባው አየን ራንድ ስተምራለች። ከሁሉም የላቁ የተባሉት ሦስቱ እሴቶች እኚሁና፡ እውነታን አንጥሮ የሚገነዘብ የአእምሮ አስተውሎት (Reason)፣ የሕይወት አላማ (Purpose)፣ በራስ ብቃት መተማመን (selfesteem)። የኪነጥበብ ዋጋ እጅጉን  ልቅ የሆነው፤ እነዚህ እሴቶች ጎልተውና ጠርተው፣ በተጨባጭ ተቀርፀውና እውን ሆነው እንድናያቸው የሚያደርግ

ምናባዊ አለም ለመፍጠር ስለሚያስችል ነው። ሶስቱ የኪነጥበብ መሰረታዊ ባህርያትም፣ ከመሰረታዊዎቹ ሦስት እሴቶች ጋር (ከትኩረት፣ ከአላማ እና ከብቃት ጋር) የተሳሰሩ ናቸው። የኪነጥበብ ባሕርያት ከስፖርት ባሕርያት ጋር ምን ያህል እንደሚመሳሰሉ ተመልከቱ። 1. ኪነጥበብ፣ ዋና ዋና ቁም ነገሮችን ከትርኪምርኪ ለይቶና አጥርቶ ማሳየት ይችላል (selection and magnification)። ምርጥ የስፖርት ውድድር፤ በአላስፈላጊ ነገሮች ላይ ሳይሆን በዋና ዋና ነገሮች ላይ እንድናተኩር ያደርጋል። ስለ ተጫዋቾች ችሎታ እንጂ ስለ ዘመዶቹ ቁጥር ወይም ስለ ጥርሱ ብዛት አናወራም። በቀጥታ የሚተላለፈው ውድድር ላይ፤ ተጫዋቾች ተቀባብለውና አብዶ ሰርተው ሲያልፉ፣ ኳስ ሲመቱና ጎል ሲያስገቡ ነው ማየት የምፈልገው? ወይስ የሜዳው የሳር ቅጠል ስፋትና ርዝመት፤ የተጨዋቹ ገምባሌ ስፌትና የክር አይነት ለ90 ደቂቃ ማየት እንፈልጋለን? ዋና ዋና ቁም ነገሮቹ ናቸው ጎልተው የሚወጡት። ከገምባሌ ስፌት ይልቅ የጎሉን አገባብ ለይቶ ያሳየናል፤ ደጋግሞም እንድናየው ያቀርብልና - አጥርቶ አጉልቶ። (selection and magnification) 2. ኪነጥበብ፤ ብቃትን በተጨባጭ ስጋና ደም አልብሶና በአርአያነት ሊጠቀስ የሚችል ጀግናን ቀርፆ ማሳየት ይችላል (concretization and model building)። ምርጥ የስፖርት ውድድር፤ የሰውን ብቃት በእውን በተጨባጭ እንድናይ ያደርጋል። 3. ኪነጥበብ፤ የሩቁን አላማ በቅርበት እንድናጣጥመው የስኬት ጉዞውን አስተሳስሮ ማሳየት ይችላል (projection and recreation)። 

ምርጥ የስፖርት ውድድር፤ በትልቅና በከባድ አላማ እንዲሁ፤ በእልህ አስጨራሽ ትንቅንቅና ፉክክር ላይ የተመሰረ ነው - በዙር ጨዋታና በጥሎ ማለፍ ፉክክሩ ጦዞ በፍፃሜው ለዋንጫ ሲደረስ እናይበታለን። ምርጥ የስፖርት ውድድር እና ምርጥ ድራማ (ድርሰት) በጣም ተመሳሳይ ከመሆናቸው የተነሳ፤ ይዘታቸውም ይዛመዳል።

ገፀ ባሕርያትና ተጫዋቾች ስፖርታዊ ውድድር ደማቅና ማራኪ የሚሆንልን፤ በብቃት የገነኑና ከባድ አላማ የያዙ ተፎካካሪ ተጫዋቾች የሚታዩበት ከሆነ ነው።

ድርሰትም ውብ እና መሳጭ የሚሆንልን፤ በጀግንነት የገነኑና ፈታኝ አላማ የያዙ ተቀናቃኝ ገፀባሕርያትን መቅረፅ ሲችል ነው። በግጭት እየጦዘ የሚሄድ የድርጊት ሰንሰለት (ሴራ) ምርጥ ስፖርታዊ ውድድር ቁጭ ብድግ

የሚያሰኘን፤ ተጫዋቾች በእያንዳንዷ ደቂቃ አላማቸው ላይ አነጣጥረው የሚጣጣሩበት ታሪክ ስለምናይበት ነው። አታልሎ ማለፍ፣ ጎል ማስገባት፣ ማሸነፍ፣ ዋንጫ መውሰድ... የተጫዋቾቹ ድርጊት በሙሉ፣ ፉክክሩና ጥሎ ማለፉ ሁሉ እርስ በርስ የተሳሰሩ ናቸው። በአላማ ላይ ያነጣጠረ የፍልሚያ፣ የግጭት፣ የፉክክር መርሃ ግብር የምርጥ ስፖርታዊ ውድድር መለያ ነው - በግብግብ እየጦዘ የሚሄድ የውድድር ሰንሰለት (ሴራ) ልንለው እንችላለን።

ምርጥ ድርሰት ልብ ሰቅሎ የሚያጓጓን፤ ገፀባሕርያት በእያንዳንዷ ደቂቃ አላማቸው ላይ አተኩረው ሲታገሉ፣ ሲወጡና ሲወርዱ የሚያሳይ ታሪክ ስለሚያቀርብልን ነው። መውጪያ ወይም መግቢያ ቀዳዳ መፈለግ፣ ማምለጥ ወይም ማሳደድ፣ መያዝ ወይም ነፃ መውጣት... የገፀባሕርያቱ እንቅስቃሴ በሙሉ አላማን ለስኬት ለማብቃት

የሚደረግ ነው። ሁሉም ድርጊቶች የተሳሰሩ ናቸው - በአላማ ላይ ያነጣጠረ የትንቅንቅ፣ የግጭትና

የፉክክር ታሪክ ነው - በግጭት እየጦዘ የሚሄድ የድርጊት ሰንሰለት (ሴራ)። የአቀራረብ ዘይቤ (ስታይል)

የስፖርታዊ ውድድሮች አቀራረብ በአዘጋጆቹ መንፈስና ዝንባሌ ይለያይ የለ? በድርሰትም እንደዚያው ነው። የሁለት ድርሰቶች ታሪክ ተመሳሳይ ቢሆን እንኳ እንደደራሲዎቹ መንፈስ አቀራረባቸው ሊለያይ ይችላል። የአንዱ ደራሲ የአቀራረብ መንፈስ (ስታይል) እንደ አፍሪካ ዋንጫ በወግ የደበዘዘ በጥሬ ስሜት የተንዘፈዘፈ ይሆናል። የሌላኛው

ደራሲ ስታይ ደግሞ፣ እንደ አሜሪካ የቅርጫት ኳስ ዋንጫ ያሸበረቀና የተሽቀረቀረ ይሆናል። የአንዱ

ደራሲ፤ እንደ ጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ ቆጠብ ደደር ያለ፤ የሌላኛው እንደ እንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የተጯጯኸና የተቀወጠ። ስፖርታዊ ወድድርና ድርሰት፣ ሌላ ተመሳሳይ ተፈጥሮ አላቸው። ሁለቱም፤ በቅጡ የሚታወቅ ጭብጥ (ጥቅል ሃሳብ) ሊኖራቸው ይገባል። ጭብጥ፡ የምን ጨዋታ የምን ድርሰት? ስለተጫዋቾችም ሆነ ስለ ዋንጫ፤ ስለ ጥሎ ማለፍም ሆነ ስለ ፉክክሩ ጡዘት፣ አልያም ስለውድድሩ የአቀራረብ መንፈስ መነጋገር የምንችለው፤ በቅድሚያ የውድድሩን ምንነት ስናውቅ ነው። በአጭሩ የውድድሩ ይዘት፣ ሂደትና

አቀራርብ፤ በውድድሩ ምንነት ላይ የተመሰረተ መሆን ይገባዋል። “የ2013 የአፍሪካ እግርኳስ ዋንጫ”፣ “የ2012 ኦሊምፒክ”፣ “የ2014 የአለምአትሌቲክስ ሻምፒዮና”፣ “የሰፈር ልጆች የእግር ኳስ ግጥሚያ”፣ “የባለስልጣናትና የነጋዴዎች የእግር ኳስ ጨዋታ”... እነዚህ ሁሉ አንድ አይነት ይዘት ወይም አቀራረብ ሊኖራቸው አይችልም። የውድድሩን ጭብጥ ለይተን በጥቅሉ ስናውቅ ነው፤ ምን አይነት ተጫዋቾችና ዋንጫ፣ ምን አይነት ትንቅንቅና

የውድድር መርሃ ግብር እንደሚኖር በአጠቃላይ የውድድሩ ይዘትና ሂደት ምን መምሰል እንዳለበት

መምረጥና መወሰን የሚቻለው። የውድድሩ ይዘት፤ ሂደትና አቀራረብ፤ በውድድሩ ጭብጥ ይወሰናል

ማለት ነው። የወዳጅነት ወይም የእርዳታ ማሰባሰቢያ ውድድርንና የአለም ዋንጫንና ኦሊምፒክን በአንድ አይነት መንፈስ ማቅረብ አይቻልም፤ ውድድሮቹና ተጫዋቾቹም ይለያያሉ።

 

በድርሰትም እንዲሁ፤ ገፀባሕርያቱንና አላማቸውን፣ ግጭቱንና ሴራውን ለመምረጥና ለመወሰን፣ በቅድሚያ ደራሲው በምን ዙሪያ ለመፃፍ እንደሚፈልግ ጭብጡን ለይቶ ማወቅ ይጠበቅበታል። ለምሳሌ የዴርቶጋዳ ጭብጥ፤ “በጥንታዊ መሰረት ላይ ለኢትዮጵያ ትንሳኤ የሚባትሉ ዜጎች” የሚል ነው። “የሰዎችን ህይወት የሚያሰናክልና የሚያዋርድ ኋላቀር ህብረተሰብ ውስጥ የሚኖሩ ሚስኪን ፍቅረኞች” ... ይሄ ደግሞ የፍቅር እስከ መቃብር ጭብጥ ነው። “ድሆችን የሚበድል ፍትህ የተጓደለበት ስርዓት ውስጥ የሚኖር ጀግና” ... ዘ ሚዘረብልስ የተሰኘ መፅሃፍ። “አገርን የሚዋጅና ፍትህን የሚፈፅሙ ጀብደኞች” ... ዘ ስሪ ማስከቲርስ። “ፍቅሩንና ነፃነቱን ተቀምቶ ፈተና ውስጥ የገባ ቅን ሰው” ... ዘ ፍዩጀቲቭ የተሰኘ ፊልም። የጭብጡ ስፋትም ሆነ ጥልቀት የደራሲው ምርጫ ነው። ቅልብጭ ያለ እና የሾለ ሊሆን ይችላል። የእውቀቱንና የአቅሙን ያህል የሚመጥን፣ የዝንባሌውንና የፍላጎቱን አዝማሚያ የሚጣጣም መሆን አለበት።

ከላይ እንደተጠቀሰው፤ የድርሰት ዋና አላባዊያን 1. ጭብጥ፣ 2. የገፀባሕርያት አሳሳል (አላማን ጨምሮ)፣ 3. ሴራ (ግጭትን ጨምሮ)፣ 4. የአቀራረብ ዘይቤ (ስታይል) ናቸው። በስፖርታዊ ውድድርም ውስጥ፤ አላባዊያኑ ተመሳሳይ ናቸው። እስቲ በገፀባሕርያት አሳሳልና በሴራ ላይ በማተኮር ተመሳሳይነታቸውን በደንብ ለመመልከት እንሞክር።

የገፀ ባሕርያት አሳሳል፡

ከ31 አመት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የተመለሰ፤ ባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ የወሰደ፤ በማጣሪያው ያለፈ፤ በፕሮፌሽናል ተጫዋቾች የተገነባ፣ በውዝግብ የተበጠበጠ፤ በሽልማት ቃል የተገባለት፣ ብዙ ፈተና ያለበት ... የቡድን አወቃቀርና አመራር፣ የስፖርተኞች ብቃትና ዝግጅት፣ የአሰልጣኝ ብቃትና ዝግጅት ... ዋና ዋና ነገሮች ላይ ማተኮር። ለምሳሌ የፊዚክስ ሳይንቲስት፣ የአውሮፕላን ኢንጂነር፣ የአንጎል ሃኪም፣ የፋብሪካ ምርጥ ማኔጀር፣ የቢዝነስ ጥበበኛ፣ ምርጥ አልሞ ተኳሽ .... ላይ አናተኩርም። በዘመድ፣ በጓደኝነት፣ በጉቦ፣ በእጣ፣ በሃይማኖት ተከታይነት፣ በብሄረሰብ፣ ... አጓጉል ሃሳቦችን አናመጣም። በጉዳይህ ላይ ዋና ዋና ነገሮችን ለይቶ ማወቅና እነሱን በትኩረት ማስተዋል... የተዘበራረቀ፣ የተንሸዋረረ፣ የዘፈቀደ፣ የፈዘዘ፣ የደነዘዘ፣ የተደናበረ አስተሳሰብ እንዳይኖረን ያደርጋል።

የተወዳዳሪ ቡድኖች፣ የአሰልጣኞች፣ የተወዳዳሪዎች ... ማንነት፣ አላማ፣ ብቃት፣ አቅም፣ ዝንባሌ... የተወሰነ መረጃ “ከኤክስፖዚሽን” እናገኛለን። እንግዲህ የስፖርታዊ ውድድር ኤክስፖዚሽን የሚቀርበው፤ በማጣሪያ ውድድሮች ላይ፣ በዝግጅትና በልምምድ ወቅት፣ እንዲሁም በሚዲያ ዘገባዎች አማካኝነት ነው። የገፀባሕርያቱ ማንነት እየጎላ የሚመጣውና እየጠራ የሚታየን ግን... ታሪኩ ከጀመረ በኋላ ወይም በግጭት የተወጠረ የድርጊት ሰንሰለት ውስጥ (ሴራው ውስጥ) ነው። የተጨዋቾቹ ማንነትና ብቃት በግላጭ የምናየውም፤ ጨዋታው ከጀመረ በኋላ በትንቅንቅ የከረረ በውድድሩ ሂደት ውስጥ (በሴራው ሰንሰለት ውስጥ) ነው። ይሄኔ መሪውና ተቀናቃኝ ፍንትው ብለው ይወጣሉ። የገፀባሕርያቱ ልዩ መልክ ነጥሮ ይወጣል - ዋና መሪ ገፀባሕርይ፣ ዋና ተቀናቃኝ ገፀባሕርይ፣ ደጋፊ ገፀባሕርያት፣ እኩይ ገፀባሕርያት...

እንደ ጥሩ ድርሰት ሁሉ፤ ጥሩ ስፖርታዊ ውድድርም ቢያንስ ሁለት ጀግና ገፀባሕርያት (ጠንካራ ተፎካካሪዎች) ያስፈልጉታል። ነገር ግን፣ ጀግኖቹ እንደ የብቃታቸውና እንደ የዝንባሌያቸው፤ አላማቸውን ለማሳካት የሚመርጡት መንገድ ይለያያል። መጥፎ ነገር የመስራት አባዜ አልተጠናወታቸውም። ግን፤ አንዱ በፅናት ትክክለኛውን መንገድ የሚከተል፣ ሌላኛው ግን አንዳንዴ ወደ ስህተት ለመግባት የሚቃጣው ሊሆን ይችላል - ለምሳሌ ሰዓት ማባከንና ተጠለፍኩ ብሎ የውሸት መውደቅ። ቢሆንም፤ በጨዋታው ህግ እየተዳኙ የሚጫወቱ ናቸው። ሜዳ ውስጥ የገቡት፣ በሰዓት ማባከን ችሎታ ወይም ተጠለፍኩ ብሎ ዳኛ በማታለል ጥበባቸው አይደለም። የእግር ኳስ ብቃታቸውና ጥረታቸው ነው ዋናው ነገር። ዋና አላማቸውም ማታለልና ማሰናከር አይደለም። ዋና አላማቸው ተጫውቶ ማሸነፍ ነው። የተለያዩ ጉድለቶች ቢኖሯቸውም፣ በጥቅሉ ጀግኖች ናቸው። እንደየጉድለታቸው መጠንም ችግር ይገጥማቸዋል።

1. ዋናው መሪ ገፀባሕርይ (ፕሮታጎኒስት)፡ እንግዲህ በላቀ ብቃትና በጥሩ ጨዋታ እያሸነፈ ዋንጫ ለመውሰድ ቆርጦ የተነሳ ነው ዋናው መሪ ገፀባሕርይ። በምርጥ አጥቂዎች ላይ የተገነባ ቡድን ነው እንበል። (ከድርሰት አለም ውስጥ አንድ ሁለት ፕሮታጎኒስቶችን ብንጠቅስስ? ለምሳሌ የባንክ ዘራፊውን አሳድዶ ለመያዝ የሚፈልግ ፖሊስ፣ ወይም ፍቅረኛውን ከአጋቾች ለማዳን የሚፈልግ እጮኛ)

2. ዋናው ተቀናቃኝ ገፀባሕርይ (አንታጎኒስት)፡ የተወሰኑ ጉድለቶች እንዳሉት በማመን በመከላከል ላይ አተኩሮ ለማሸነፍ በእልህ የሚጫወት ቡድን ሊሆን ይችላል። (በድርሰቱ አለም ደግሞ፤ የባንክ ዘራፊውን ለመያዝ ግብረአበሮቹን ማግባባት አለብን የሚል ፖሊስ፤ አልያም ከአጋቾቹ ጋር በመደራደር ታጋቿን ለማስለቀቅ የሚጣጣር አባት...)

ተጨማሪ ገፀባህርያት

1. ደጋፊ ገፀባሕርያት፡ ዳኞች፣ አሰልጣኞች፣ ተመልካቾች፣ አድናቂዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ሸላሚዎች...

2. እኩይ ገፀባሕርያት (ቪሌይን)፡ ተሳዳቢ ቲፎዞ፣ አድሏዊ ዳኛ፣ የሚያዛባ ጋዜጠኛ፣ የቁማር ማፊያ፣ በዘርና በአገር ተቧድኖ ውድድሩን የሚበጠብጥ ጋጠወጥ፣ ኳስ መጫወትም ሆነ ማየት የለባችሁም የሚል አክራሪ፣ ከኳስ ደስታ ይልቅ ለችግረኞች ሃዘኔታ ቅድሚያ እንስጥ የሚል ዘመነኛ ባህታዊ... ወዘተ

ጠንካራ ሴራ፡ የጀግኖች ግጭት

ሁለቱ ጀግና ገፀባሕርያት (በወኔ የታነፀው ፖሊስና ትእግስት የተላበሰው ባልደረባው) አላማቸው ተመሳሳይ ቢሆንም ተቀናቃኝ መሆናቸው አይቀርም። ሁለቱም ጀግኖች ስለሆኑም ግጭታቸው ጠንካራ ይሆናል - (የፍፃሜ ውድድር ላይ እንደሚገናኙ ተፎካካሪ ቡድኖች ማለት ነው)።

ለምሳሌ ዘ ሚዘረብልስ የተሰኘው የቪክቶር ሁጎን ድርሰት መጥቀስ ይቻላል። ዋናው ገፀባሕርይ ፍትሕ ለማግኘት የሚታትር ነው። ተቀናቃኙ ደግሞ፣ ህግ መከበር አለበት ይላል - ዣቬር። ለያዙት አላማ ፅኑ ናቸው፤ ብቃታቸውን ተጠቅመው ይፋጫሉ። ዣቬር ባይኖር የዣን ቫልዣ ታሪክ ይኮሰምናል። ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሌለው የፍፃሜ ውድድር፤ እርባና ቢስ ታሪክ ይሆናል።

ታዲያ በሁለቱ ጀግኖች ግጭት መሃል፤ ዣን ቫልዣን እንደ አባት የምትወደው ወጣት ሴት አለች። ይህችን ሴት በመጠቀም ዣን ቫልዣን ለመዝረፍና ለመጉዳት የሚፈልጉ መናኛ እኩይ ገፀባህርያትም ይኖራሉ። ግን የዣን ቫልዣ ትንቅንቅ ከመናኛና ከእኩይ ገፀባሕርያት ጋር አይደለም። ከጠንካራውና ከጀግናው ዣቬር ጋር ነው ትግሉ። ድርሰቱ ከምዕተ አመት በኋላም እግጅ ተወዳጅ ታሪክ ለመሆን የበቃበት ትልቁ ሚስጥር ይሄው ነው።።

ከዘመኑ ፊልሞችም አንድ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል - ሃሪሰን ፎርድ የሚሰራበት ዘ ፊጁቲቭ የተሰኘው ፊልም። ሚስትህን ገድለሃል ተብሎ በሃሰት የተፈረደበት ሃኪም ከእስር ሲያመልጥ ነው ታሪኩ የሚጀምረው። ሚስቱን የገደሉበትና በተንኮል ለእስር የዳረጉትን ሰዎች አጋልጦ ንፁህነቱን ሳያስመሰክር ወደ እስር መመለስ አይፈልግም። ይህን አላማ ማሳካት አለበት። ኮምጫጫው ህግ አስከባሪ ደግሞ፤ ከእስር ያመለጡ ሰዎችን የገቡበት ገብቶ መያዝና ማሰር ስራው ነው። ህግ መከበር አለበት ባይ ነው። የሁለቱም አላማ ትክክል ነው፤ ፅናት አላቸው። አላማቸውን የሚያሳኩበት ብቃትና ብርታት አላቸው። ፍጭቱ ሃይለኛ ነው። ፊልሙ ደግሞ እጅግ መሳጭ ታሪክ።

መናኛዎቹ እኩይ ገፀባሕርያት፣ በራሳቸው አቅም የታሪኩን አቅጣጫ የመቀየር አቅም የላቸው - ጀግኖቹ ገፀባሕርያት ደካማ ካልሆኑና ካልፈቀዱላቸው በቀር። የጀግኖቹ ግጭት ተባብሶና ጦዞ እልባት ላይ ሲደርስ፤ እኩዮቹ ገፀባሕርያት እርቃናቸውን ይቀራሉ። በእግር ኳስ ውድድርም ተመሳሳይ ነው። ጨዋታው የሚያምረው፣ ከፍተኛ ብቃት ባላቸው ምርጥ ተጫዋቾች ሲወዳደሩ ነው።

ሦስቱ የኪነጥበብ ባሕርያት ሲጓደሉ

ዋና ዋና ነገሮች ላይ አለማተኮር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለመገንዘብ ምሳሌዎችን ልጥቀስላችሁ። ያህል ይሉሃል ይሄ ነው። የተፈነከተ ተመልካች ላይ የሚደረግ የረቀቀ ህክምና ስናይ ብንውል? አጥቂው እያታለለ ሲያልፍ ለአፍታ አሳይቶ ከዚያ በኋላ ለ10 ደቂቃ ያህል የሜዳውን የሳር ቅጠል ብዛትና ስፋት ከተለያየ አቅጣጫ እየቀረፀ ቢያሳየንስ? አንድ ሁለት ተቀባብለው፣ ወደ ግራ ክንፍ አሻግረው፣ ወደ ግብ... ካሜራው ይህንን አቋርጦ ጨዋታው እስኪያልቅ ድረስ የተጨዋቹ የገምባሌ ስፌት እና የፀጉሩ ቀለም ከተለያየ አቅጣጫ እየደጋገመ ቢያሳየንስ? በቲቪ በቀጥታ የሚተላለፈው ጨዋታው ሳይሆን፤ የአሰልጣኞችን ክርክርና ዛቻ ወይም የተጫዋቾችን ተረብና የቅፅል ስም አጠራር ቢሆንስ? ወይም፤ በትንታኔና በቲዎሪ ፉክክር ብቻ ነገሩ ቢጠናቀቅስ? ተጨባጭ ታሪክ ሳይኖረው፤ በገለፃና በትንታኔ የታጨቀ ድርሰትም፤ ከሬድዮ ቶክ ሾው የተሻለ ዋጋ አይኖረውም።

ብቃት የማያስፈልገው ውድድር ቢሆንና ማጣሪያና ምርጫ ባይኖርስ? ለምሳሌ በእጣ ሊሆን ይችላል። እግር ኳስ ማየት፤ የሎተሪ እጣ ሲወጣ ከማየት የተለየ አይሆንም ነበር። የተጫዋቾችን ብቃት መመዘን ባንችል ኖሮስ? ስለ ቼዝ የማናውቅ ከሆነ የቼዝ ጨዋታ ለማየት እንጓጓም። ምክንያቱም የተጨዋቾችን ብቃት መመዘን አንችልም። ማሸነፍና ዋንጫ ማግኘት የሚቻለው በእርዳታ ቢሆንስ ኖሮ? አንዱ ቡድን በባዶ እግር በአምስት ሰው ብቻ እንዲጫወት የሚፈረድበት ቢሆን?ተጫዋቾች በብቃታቸው የማይመረጡ ቢሆንስ? ስማቸው በ”ኤ” የሚጀምርና በውድቅት ሌሊት የተወለዱ ብቻ የሚካፈሉበት ውድድር ቢሆንስ? ብቃትን አጉልቶ የማያወጣ ውድድር፤ ከንቱ ልፊያ ይሆናል። ይህ ነው የሚባል ብቃት በሌላቸው ገፀባሕርያት የታጨቀ ድርሰትም እንደዚያው ነው።

ግብ እና ዋንጫ ባይኖርስ? (7 ቁጥሩ ለ9 አሳለፈ፣ ጠለዘ፣ ነዳ ... ይህንን ለስንት ደቂቃ ሳይሰለቸን ማየት እንችላለን? አሸናፊው ተለይቶ የሚታወቀው በቲፎዞ ብዛት ቢሆንስ? ጎል ሲያገባ እንደ ዳኛው ፍላጎት፣ ለሌኛው ቡድን ነጥብ ቢሰጥስ? ለማሸነፍ ባይጫወቱስ? በይሉኝታ መሸነፍ፣ ለሌላው አዝኖ ራስን መስዋዕት ማድረግ፣ ያሸነፈ ቡድን ራስ ወዳድ ተብሎ ቢወገዝስ? የዘንድሮው ሻምፒዮና፣ በስህተት በራሱ ላይ ብዙ ግብ ያስቆጠረ ቡድን ነው ቢባልስ?

የሠዐሊና መምህር ዘርዓዳዊት አባተ የሥዕል ስራዎች የሚቀርቡበት አውደርዕይ የፊታችን ሃሙስ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም እንደሚከፈት ተገለፀሰዓሊው የሚያቀርቡት የሥዕልና ቅርጻቅርጽ አውደርእይ እስከ ጥር 15 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ ለሕዝብ ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ታውቋል፡፡ሠዐሊው ካሁን ቀደም ለአስራ ሰባት ጊዜ ያህል አውደርእዮችን ያዘጋጀ ሲሆን ያሁኑን አውደርዕይ የሀገር ባለ ውለታ ጀግኖችን በማሰብ እንዳዘጋጀው ተናግሯል፡፡

Page 5 of 11