ከሁለት ወራት በኋላ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የአዲስ አበባ አስተዳደርና የአካባቢ ምርጫ ላይ የተቃዋሚ ፓርቲዎች መሣተፍና አለመሳተፍ ለኢህአዴግ ትርፍም ኪሳራም እንደሌለውና የሚያጐድለው ነገርም እንደማይኖር ኢህአዴግ ገለፀ፡፡ የኢህአዴግ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ሬድዋን ሰይድ ትናንት በፅ/ቤቱ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአብዛኛው በአካባቢ ምርጫ ተሳትፈው አያውቁም፡፡ በአካባቢ ምርጫ የሚገኝ ሥልጣን በአብዛኛው ለታይታና ለወሬ የማይመች እና ሥራ ላይ ትኩረት ያደረገ በመሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ፓርላማ መግባትን የመዋደቂያ ነጥብ አድርገው ሲንቀሣቀሱ ይታያሉ ብለዋል፡፡ የፓርቲዎቹ በምርጫው ላይ መሣተፍና አለመሳተፍ ትርፍም ኪሣራም የለውም ያሉት አቶ ሬድዋን፤ ለሥርዓቱ ግን መሣተፋቸው ጠቃሚ ይሆን እንደነበርና በምርጫው ውስጥ መሣተፋቸው ራሳቸውን ለማየትና ለመማር እንዲችሉ ያደርጋቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ከተቃዋሚ ፓርቲዎች አንዳንዶቹ አንድ ግለሰብ በአራት ማህተም የሚያንቀሣቅሣቸውና በህይወት በሌሉ፣ የመጀመሪያውን ማህተም ባልመለሱ ሰዎች የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች እንደ ፓርቲ ተቆጥረው ምርጫ ውስጥ ገቡ አልገቡ ሊያሰኝ እንደማይችል ገልፀዋል። ብዙዎቹ ፓርቲዎች አባልም፣ ፅ/ቤትም እንደሌላቸው የተናገሩት ኃላፊው፤ እነዚህ ፓርቲዎች በምርጫው ቢሣተፉ ምንም እንደማይጠቅሙ ጠቁመው፤ ቀድሞውኑ የሚያንቀሣቅሱት ዓላማ ስለሌላቸው፤ ባይሣተፉ ደግሞ ምንም እንደማያጐሉ ምክንያቱም ቀድሞውኑ ያልነበሩ ስለሆነ ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በምርጫው ውስጥ የብዙ ፓርቲዎች መሣተፍ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መገለጫ አይደለም ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም፤ ምርጫው በ29 ፓርቲዎች መካከል የሚካሄድ ምርጫ መሆኑን አስታውሰው፣ ሃያ ዘጠኝ ፓርቲዎች የሚርመሰመሱበት ምርጫ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ እንደሆነና በአሜሪካንም ሆነ በእንግሊዝ ሁለት ፓርቲዎች ብቻ የሚወዳደሩበት ምርጫ እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡ የምርጫ ዲሞክራሲያዊነት የሚለካው ምን ያህል ፓርቲ በምርጫው ውስጥ ይርመሰመሳል በሚል እንዳልሆነና መለኪያው ህዝቡ በነፃነት ውሣኔ ይሰጣል ወይ፣ የቀረበው አጀንዳ ለህዝቡ ምን ያህል ፋይዳ አለው የሚሉ መመዘኛዎች እንደሆኑ አቶ ሬድዋን ጨምረው ገልፀዋል፡፡ በእኛ አገር ኪዎስክ ከመክፈት በላይ ፓርቲ መመስረት ቀላል ነው ያሉት አቶ ሬድዋን፤ ሕጉ እስከዚያ ድረስ ቀላል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የአንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ከምርጫ ራሳቸውን ማግለል አስመልክተው ሲናገሩም፤ በታላቁ መሪያችን ሞት ምክንያት ህዝቡ ስሜቱን የገለፀበትን መንገድ በማየታቸውና በምርጫው እንደማያሸንፉም ስለተረዱ ነው ብለዋል፡

፡ ኢህአዴግ በአዲስ አበባ ውስጥ 100ሺ አባላት እንዳለው የተናገሩት አቶ ሬድዋን፤ ከእነዚህ አባላቱ ውስጥ የምርጫው ጊዜ እየተቃረበ መምጣቱንና የካርድ መውሰጃው ጊዜ ሊጠናቀቅ መቃረቡን የማስታወስ ተልእኮ ለአባላቶቹ መሰጠቱን ገልፀዋል፡፡ ማንኛውም ተቃዋሚ ፓርቲ ይህን ተልዕኮ ለአባላቶቹ የመስጠት መብት አለው ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ኢህአዴግ ለመጪው ሚያዝያ ወር ምርጫ ያዘጋጃቸውን እጩዎች በቀጣዮቹ ቀናት ይፋ እንደሚያደርግም አቶ ሬድዋን በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተናግረዋል፡፡

Published in ዜና
  • •ውሳኔውን የተቃወሙት የቅ/ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ የመልቀቂያ ደብዳቤ አስገብተዋል
  •  የሰላሙና የዕርቅ ሂደቱ ‹‹ኹኔታዎች ሲመቻቹ›› በሌላ አደራዳሪ አካል ይቀጥላል
  •  ‹‹6ውን ፓትርያሪክ በአንድነት ለ መምረጥ የተደረገው ጥረት አል ተሳካም›› የቅ/ሲኖዶሱ መግለጫ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ የስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ ሂደት ሕገ ቤተ ክርስቲያንንና ቀኖናውን ጠብቆ እንዲቀጥል ወሰነ፡፡ ቅ/ሲኖዶሱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ከጥር 6 - 8 ቀን 2005 ዓ.ም በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳይ ላይ ሲያካሂድ የቆየውን የምልአተ ጉባኤ አስቸኳይ ስብሰባ ሲያጠናቀቅ ባወጣው ባለሦስት ነጥብ የውሳኔ መግለጫው ነው፡፡

ከአምስተኛው ፓትርያሪክ ኅልፈተ ሕይወት በኋላ በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ አባቶች ጋር ተጀምሮ ለቆየው የሰላምና አንድነት ጉባኤ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ልኡካኑን በመላክ፣ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ፣ ሊያቀራርቡ የሚችሉ በርካታ የሰላም አማራጮችን ማቅረቡን በመግለጫው ያስታወሰው ቅ/ሲኖዶሱ፤ ‹‹በዚያ በኩል ባሉ አባቶች ምንም ዐይነት የሰላም ፍንጭ አለመታየቱንና የሰላም ስምምነት ለመፈጸም አለመቻሉን›› ገልጿል፡፡ በአሁኑ ወቅት በመንበረ ፕትርክናው ከሚታየው ክፍተት አኳያ ቤተ ክርስቲያን ያለመሪ ለብዙ ጊዜ እንድትቆይ ማድረግ÷ ‹‹መንፈሳዊና ማኅበራዊ ሥራዋ እንዲስተጓጎል፣ መልካም አስተዳደሯ እንዲዳከም፣ ዕድገቷም እንዲቀጨጭ የሚያደርግ በመኾኑ›› ለስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ የተጀመረው ዝግጅት እንዲቀጥል መወሰኑን ቅ/ሲኖዶሱ አስታውቋል፡፡

ቅ/ሲኖዶሱ አሜሪካ ድረስ አራት ጊዜ ልኡካኑን መላኩን፣ በሰላም ፈላጊነቱም ‹‹ኑ እና አብረን እንሥራ፣ አብረን እንምረጥ›› ከማለት ውጪ ሌላ የሚጠበቅበት ሓላፊነት ሊኖር እንደማይችል በመግለጫው አመልክቷል፡ ፡ የስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ ከመከናወኑ በፊት የሰላምና አንድነት ጉባኤው ተካሂዶ ከቀድሞው አራተኛ ፓትርያሪክ ጋር በሰሜን አሜሪካ ያሉት አባቶች ወደ አገራቸውና ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲገቡ፣ የመምረጥና የመመረጥ መብታቸው እንደሚጠበቅላቸው፣ በዚህም ስምምነቱ እንዲፈጸምና ነገሩ እንዲቋጭ በሚገባ ቢያስረዳም የተጠበቀው ስምምነት ሳይፈጸም መቅረቱን በመግለጫው አትቷል፡፡ ይህንንም ቅ/ሲኖዶሱ እጅግ አሳዛኝ ኾኖ እንዳገኘው ገልጿል፡፡

በመሪ አለመኖር ምክንያት የቤተ ክርስቲያን ሥራ በእጅጉ እየተጎዳ እያየ ተጨማሪ ጊዜ መስጠት ቤተ ክርስቲያንን ለከፍተኛ ውድቀት የሚዳርግ፣ በእግዚአብሔርና በታሪክ ፊት ወቀሳን የሚያስከትል መኾኑን በመገንዘብ ቀደም ሲል አስመራጭ ኮሚቴ መሠየሙን ያስታወሰው የቅ/ሲኖዶሱ መግለጫ፣ የምርጫውም ሂደት ‹‹በእግዚአብሔር ቸርነትና በምእመናን ድጋፍ ሕገ ቤተ ክርስቲያንና ቀኖናው ተጠብቆ እንደሚከናወን ፍጹም ጥርጥር የለንም›› ብሏል፡ ፡ የፓትርያሪክ ምርጫ ጊዜው በቁርጥ ባይታወቅም እስከ ጥር መጨረሻ ድረስ ዕጩ እንዲያቀርብ የተሠየመው የአስመራጭ ኮሚቴው ሂደት እንደሚወስነው ከመግለጫው በኋላ ለጋዜጠኞች ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከፍተኛ ሓላፊዎች ተገልጿል፡፡

ውጥረት ሰፍኖበት እንደነበር በተገለጸው የምልአተ ጉባኤው ስብሰባ÷ ‹‹የዕርቀ ሰላሙን ፍጻሜ በጊዜ ገደብ ጠብቀን በውጭ ከሚገኙት አባቶች ጋር ምርጫውን በአንድነት እናካሂድ›› የሚሉ ሊቃነ ጳጳሳት በውሳኔ መልክ የወጣውን የቅ/ሲኖዶሱን መግለጫ በከፍተኛ ደረጃ መሞገታቸው ተዘግቧል፡፡ ከእኒህም አንዱ የኾኑት የቅ/ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ የማክሰኞውን ስብሰባ ትተው መውጣቸው የተገለጸ ሲኾን፤ ዘግይቶ በደረሰን ዜና መሠረት ደግሞ ከዋና ጸሐፊነት ሓላፊነታቸው የመልቀቂያ ደብዳቤ ለዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ማቅረባቸው ተሰምቷል፡፡

ዋና ጸሐፊው በወቅታዊ አጀንዳ በተላለፈው ውሳኔ በአቋም ከመለየታቸው ባሻገር፤ ‹‹በጽ/ቤቱ ስም ሳላውቃቸው የሚወጡ ደብዳቤዎች አሉ›› የሚለው አቤቱታቸው በሓላፊነታቸው ላለመቀጠል እንደምክንያት እንደሚጠቅሱ የመንበረ ፓትርያሪኩ ምንጮች ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ ብፁዕ ዋና ጸሐፊው ሳላውቃቸው በጽ/ቤቱ ስም ይወጣሉ ካሏቸው ደብዳቤዎች መካከል ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴርን እገዛ ጠይቀውበታል የተባለው ደብዳቤ እንደሚገኘበት ተመልክቷል፡፡

በዚህ ደብዳቤ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪክ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የጠቅላይ ቤተክህነቱ ከፍተኛ ሓላፊዎች ሥራቸውን እንዳይሠሩና ምርጫውን በአስቸኳይ እንዳያካሂዱ ዕንቅፋት እየፈጠሩባቸው በመኾኑ፣ መንግሥት እገዛ እንዲያደርግላቸው መጠየቃቸው ነው የተዘገበው፡፡ ዐቃቤ መንበሩ የመንግሥትን እገዛ በደብዳቤ መጠየቃቸውን ተከትሎ ቅድሚያ የዕርቀ ሰላሙ ጉዳይ እንዲቋጭና ወደ ምርጫው እንዲገባ በሚበዙት ተሳታፊዎች ተይዞ የነበረው አቋም እንዲዳከም አስተዋፅኦ ማድረጉን ነው ታዛቢዎች የሚናገሩት፡፡ ለጋዜጠኞች ጥያቄዎች ምላሽ ከሰጡት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከፍተኛ ሓላፊዎች አንዱ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ፣ ዐቃቤ መንበሩ ለመንግሥት የጻፉት ደብዳቤው እንዳለ አምነው ይዘቱ ግን ‹‹በአጠቃላይ ስለ አንዳንድ ሥራዎች ሂደት እንጂ ከዐቢይ ጉባኤው ጋር የሚገናኝ ጉዳይ የለውም›› ብለዋል፡፡

ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ በሦስት ዙር ሲካሄድ ስለቆየው የሰላምና አንድነት ጉባኤ ቀጣይነት የተጠየቁት ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ፣ ‹‹ከግማሽ መንገድ በላይ ተኪዷል፤ እንደ አቋም የኢትዮጵያው ሲኖዶስ መኾን መደረግ ያለበትን የሰላም አቋም አሟጦ ጨርሷል፤ ከዚህ በላይ የሚደረግ ነገር የለም›› ቢሉም ቀደም ሲል ከነበረው አደራዳሪ አካል ይልቅ÷ ግራ ቀኙን አይቶ የተለያዩ አማራጭ ሐሳቦችን ደፍሮ ለማቅረብ፣ ተጽዕኖ ለማሳደር የሚችል ብቃትና አቅም ያለው አካል ሲገኝ ቅ/ሲኖዶሱ እያጠና የመጨረሻዋ ሰላም እስክትረጋገጥ ድረስ ይቀጥልበታል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በቅ/ ሲኖዶሱ መግለጫ ላይም እንደተመለከተው÷ በውጭ ያሉት አባቶች የተሰጠውን የሰላም ዕድል ተጠቅመው ወደ ሰላሙና አንድነቱ ለመምጣት ፈቃደኞች ኾነው እስከተገኙ ድረስ ኹኔታዎች ሲመቻቹ ቀደም ሲል የተጀመረውን የሰላምና ዕርቅ ሂደት እስከ መጨረሻው ለመቀጠል አሁንም ዝግጁ መኾኑን አረጋግጧል፡፡

ቅ/ሲኖዶሱ በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳይ ላይ ያደረገው ውይይትና ያሳለፈው ውሳኔ÷ ከኅዳር 26 - 30 ቀን 2005 ዓ.ም በዳላስ ቴክሳስ ለሦስተኛ ጊዜ በተካሄደው ጉባኤ አበው ላይ የተሳተፉት ልኡካን ባቀረቡት አጠቃላይ ሪፖርት ላይ የተመሠረተ መኾኑ በቅ/ሲኖዶሱ መግለጫው ላይ ተመልክቷል፡፡ በዳላሱ ድርድር ላይ ለዕርቁና ሰላም ስምምነቱ አለመፈጸም እንደዋነኛ ምክንያት የተጠቀሰው÷ ‹‹የቀድሞው ዐራተኛ ፓትርያሪክ መንበራቸው ክፍት ስለሆነ ወደ መንበራቸው መመለስ አለባቸው፤ በሙሉ የፓትርያሪክነት ሥልጣንም ቤተ ክርስቲያንን መምራት አለባቸው፤ ይህ የማይደረግ ከኾነ ግን አንስማማም›› የሚለው በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ አባቶች አቋም ነው፡፡

ቅ/ሲኖዶሱ ይህን አስመልክቶ በመግለጫው በሰጠው ማብራሪያ÷ ከዛሬ ኻያ ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ዐራተኛ ፓትርያሪክ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በወቅቱ ባደረባቸው ሕመም ነሐሴ 18 ቀን 1983 ዓ.ም በጠሩት አስቸኳይ የቅ/ሲኖዶስ ጉባኤ ሥልጣናቸውን ለማስረከብ መጠየቃቸውን አስታውሷል፡፡ ይኹንና ቅ/ ሲኖዶስ የቀድሞው ፓትርያሪክ በሕክምናም በጠበልም እየተረዱ ሊድኑ እንደሚችሉና ሐላፊነታቸውን ይዘው እንዲቀጥሉ ፈቃዳቸው እንዲኾን ቢለምናቸውም ሐሳባቸውን ከማጽናት በቀር ተለዋጭ መልስ እንዳልሰጡት ገልጧል፡፡

በመኾኑም ጉዳዩ በጥልቀት ሲጠና ሰንብቶ ነሐሴ 28 ቀን 1983 ዓ.ም የቀድሞውን ዐራተኛ ፓትርያሪክ ጥያቄ ተቀብሎ ሥልጣኑን መረከቡን፣ ኾኖም ግን ፓትርያሪኩ ሓላፊነታቸውን ለመወጣት የሚችሉበት ዕድል እንዳለ የሚጠቁም ፍንጭ ለማግኘት ለዐሥር ወራት ያህል ቢጠብቅም ባለመስጠታቸው ለኑሯቸው የሚያስፈልገውን ሁሉ፣ ደመወዝም መኪናም ፈቅዶላቸው በገዳም በጠበል እየታገዙ፣ በሕክምናም እየተረዱ በጸሎት ተወስነው እንዲኖሩ መወሰኑን አውስቷል፡፡ ከዚህ በኋላ ቤተ ክርስቲያን ያለመሪ ለብዙ ጊዜ እንድትቆይ ማድረግ የሚያስከትለውን ጉዳት በመገንዘብ የአምስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ እንዲካሄድ ግንቦት አራት ቀን 1984 ዓ.ም መወሰኑን ጠቅሷል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ አራት ሊቃነ ጳጳሳት ከሀገር ውስጥና ከውጭ አህጉረ ስብከት ከቤተ ክርስቲያናቸው ተነጥለው ሲወጡ፣ ዐራተኛ ፓትርያሪክ የነበሩትም በሞያሌ በኩል ኬንያ ገብተው ለሰባት ዓመት ከቆዩ በኋላ፣ ሁሉም በሰሜን አሜሪካ ተሰብስበው በታሪክ ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ ድርጊት በመፈጸም በስደት አገር ሲኖዶስ አቋቁመናል ማለታቸው ተገልጿል፡፡ ፓትርያሪክም ኾነ ሊቀ ጳጳስ ከአገር ውጭ ሲኖዶስ ማቋቋም ይቅርና ያለቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ አንድ የፋሲካ በዓል ከሀገሩና ከሀ/ስብከቱ ውጭ ማክበር በቀኖና ቤተ ክርስቲያን የተከለከለ በመኾኑ ስሕተቱን በመነጋገር ለማረም በታኅሣሥ ወር 1999 ዓ.ም ልኡክ ቢላክም አናነጋግርም ከማለት አልፎ፣ በዚያው ዓመት ወርኃ ጥር የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት በማከናወናቸው የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና ለማስጠበቅ ሲባል ቅ/ሲኖዶስ ቃለ ውግዘት ማስተላለፉን፣ ስማቸውንና ሐዋርያዊ ሥልጣናቸውን ማንሣቱን ጠቅሷል፡፡

ከዚህ በኋላ ጉዳዩ በዕርቅና በሰላም ተቋጭቶ በውጭ ያሉት አባቶች ወደሀገራቸውና ወደ ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲገቡ ለማግባባት ጥያቄ ያቀረቡ ወገኖችን ሐሳብ ተቀብሎ በሐምሌ 2002 ዓ.ም በሰሜን አሜሪካ ቨርጂኒያ በሦስተኛ ወገኖች የሐሳብ ልውውጥ ቢያደርግም ‹‹ከመሠረተ ጉዳዩ ጋር ተያያዥነት የሌለውና ያልተጠበቀ ቅድመ ኹኔታ›› በመቀመጡ ሰላምና አንድነቱ ሳይሳካ ቀርቷል ብሏል፡፡

ከዚህ በኋላ ቅ/ሲኖዶሱ ለሰላሙ መፋጠን ያጸደቀውን ‹‹ወሳኝ የኾነ የመጨረሻ የሰላም አቋም›› ሲዘረዘር÷ ዐራተኛው ፓትርያሪክ ወደ አገራቸው ተመልሰው፣ ደረጃቸውና ክብራቸው ተጠብቆ፣ የሚያስፈልጋቸው ሁሉ ተሟልቶላቸው፣ በመረጡት ቦታ በጸሎት ተወስነው እንዲኖሩ፣ ነባሮቹንም ኾነ በእነርሱ አንብሮተ እድ የተሾሙ አዲሶቹ አባቶች አስመልክቶም ቀኖናውን በቀኖና አሻሽሎ፣ ሐዋርያዊ ሥልጣናቸውን ሰጥቶ፣ ስማቸውን መልሶ፣ በሀገረ ስብከት መድቦ ለማሠራት ፈቃደኛ መኾኑን በየካቲት ወር 2004 ዓ.ም በአሪዞና ፊኒክስ በተካሄደው ጉባኤ ይፋ ማድረጉን አስረድቷል፡ ፡ ይኹንና አሁንም ከቤተ ክርስቲያን ጋር ተያያዥነት የሌላቸው ጉዳዮች በማንሣታቸውና የቀረበውንም ጥሪ ባለመቀበላቸው የተጠበቀው ሰላምና አንድነት ሊገኝ እንዳልቻለ አብራርቷል፡፡

የዐራተኛውን ፓትርያሪክ ስደት ከተለመደው የአባቶች ስደት ልዩ የሚያደርገው የቀድሞው ዐራተኛው ፓትርያሪክ መንበራቸውን ራሳቸው በመልቀቃቸውና በማስረከባቸው፣ ያለምንም ምክንያት ሀገራቸውንና ቤተ ክርስቲያናቸውን ጥለው ከአገር በመውጣታቸው፣ በስደት አገር ሲኖዶስ በማቋቋማቸው መኾኑን ቅ/ሲኖዶሱ በመግለጫው አትቷል፡፡

ቅ/ሲኖዶሱ የቀድሞውን ዐራተኛ ፓትርያሪክ በፓትርያሪክነት የሥልጣን ደረጃ የማይቀበልባቸውን ምክንያቶች ሲዘረዝርም፡- ‹‹ይህን የመሰለ ታላቅ መንፈሳዊ ሥልጣን ሲፈልጉ ተረከቡኝ፣ ሲፈልጉ መልሱኝ እየተባለ የሚከራከሩበት ባለመኾኑና ይህን ጥያቄ ማስተናገድ በቤተ ክርስቲያን ሥርዐተ አልበኝነት እንዲሰፍን መፍቀድ በመኾኑ፣ ቅ/ሲኖዶሱ ለምኗቸው አይኾንም ብለው ጥለው የሄዱ በመኾኑ፣ ከዚህም የታሪክ መዛግብት እንደሚመሰክሩትና የቅ/ሲኖዶስ አባላትም እንደሚመሰክሩት የቀድሞውን ዐራተኛ ፓትርያሪክ ከመንበረ ፓትርያሪኩ አስወጪም ወጪም ኾነው ድርጊቱን ያፋጠኑ በወቅቱ ሰብሳቢ የነበሩና ኋላም ከእነርሱ ጋር የነበሩት አባት እንጂ ሌላ ባለመኾኑ፣ አምስተኛው ፓትርያሪክ በሕገ ቤተ ክርስቲያን ተሹመው የተሠራው የኻያ ዓመታት ሥራ ደምስሶና ሠርዞ ወደኋላ በመመለስ ዐራተኛ ፓትርያሪክ ብሎ መቀበል ፍጹም የማይቻል በመኾኑ ነው›› ብሏል፡፡ ስለዚህም በመግለጫው በቀዳሚ ተራ ቁጥር በተገለጸው አቋሙ÷ ቅ/ሲኖዶሱ የቀድሞውን ዐራተኛ ፓትርያሪክ በፓትርያሪክነት የሥልጣን ደረጃ እንደማይቀበል በማያሻማ ኹኔታ በድጋሚ መወሰኑን አስታውቋል፡፡

የአገር ቤቱን ቅ/ሲኖዶስ መጠናቀቅ ተከትሎ በሰሜን አሜሪካ በሚገኙት የቀድሞው ዐራተኛ ፓትርያሪክና ሌሎች ሊቃነ ጳጳሳት በስደት የተቋቋመው ሲኖዶስ ተሰብስቦ በመምከር ላይ መኾኑ ታውቋል፡፡ በተለይም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ‹‹በፓትርያሪክነት ማዕረግ ላለመቀበል በማያሻማ ኹኔታ በድጋሚ ወስኛለኹ›› ባለው በኢትዮጵያው ቅ/ሲኖዶስ ውሳኔዎች በእጅጉ ማዘኑንም ገልጧል፡፡ የስብሰባው ተሳታፊ በኾኑት አንድ ሊቀ ጳጳስም ‹‹በሰሜን አሜሪካ ነጻና ገለልተኛ የኾነ ሲኖዶስ ይቋቋማል›› መባሉም ተዘግቧል፡፡

የሀገር ቤቱን ቅ/ሲኖዶስ ውሳኔዎች የሚተቹ ወገኖች፣ የቀድሞው ዐራተኛ ፓትርያሪክ በሕመም ምክንያት ሥልጣናቸውን እንደሚለቁ ቢያሳውቁም በብዙ አባቶች ምክር ወደ መንበራቸው ለመመለስ ወስነው እንደነበር፣ ኾኖም በወቅቱ ሰብሳቢ የነበሩት አባት ፈጥነው በሚዲያ እንዲሰጥ ባደረጉት መግለጫ ነገሩ መሰናከሉን በመጥቀስ÷ ‹‹ቅ/ሲኖዶስ በወቅቱ ለምኗቸው አይኾንም ብለው ጥለውት ሄደዋል›› የሚለውን የመግለጫውን ክፍል ይቃወማሉ፡፡

መግለጫው ሁሉም የቅ/ሲኖዶስ አባላት የሰጡበት ትችት ተካቶና ይኹንታቸውን አግኝቶ ለመውጣቱ ጥርጣሬ ያላቸው አስተያየት ሰጭዎች÷ ከፓትርያሪክ ምርጫው በፊት የዕርቀ ሰላሙን ሂደት ለማሳካት ተስፋው ጨርሶ ያልጨለመ በመኾኑ ሁሉም ወገኖች በየፊናቸው በተለያዩ መድረኮች የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡ በእነርሱ አስተያየት በሁለቱም ‹ሲኖዶሶች› ውሳኔና መግለጫ የተነሣ የሰላሙ ሂደት ላይ ተስፋ ከተቆረጠ ‹‹የቤተ ክርስቲያን አንድነት ዳግም በማይመለስበት ኹናቴ በከፋ የመከፋፈል አደጋ ውስጥ ይወድቃል፡፡››

Published in ዜና

በመጪው ሚያዚያ ወር በሚካሄደው የአዲስ አበባ አስተዳደርና የአካባቢ ምርጫ የአፈጻጸም የጊዜ ሰሌዳ አስቀድሞ በምርጫው ፍትሃዊነት እና በሌሎች 18 አጀንዳዎች ላይ ሊወያዩ እንደሚገባ በማመን ፒትሽን ተፈራርመው ጥያቄያቸውን ለምርጫ ቦርድ ካስገቡ 33 ተቃዋሚ ፓርቲዎች አምስቱ የምርጫ ምልክታቸውን የወሰዱ ሲሆን 28ቱ ፓርቲዎች በቅርቡ ሕዝባዊ ስብሰባ እንደሚጠሩ አስታወቁ፡፡

የመድረክ ሥራ አስፈፃሚ አባልና የፓርቲዎች ሰብሳቢ አቶ አሥራት ጣሴ እንደገለፁት፤ ፓርቲዎቹ ጥር 26 ቀን 2005 ዓ.ም. ከሦስት በላይ የአዳራሽና የመስክ ሕዝባዊ ስብሰባ ለመጥራት ያቀዱ ሲሆን ለአዲስ አበባ መስተዳደር የሰላማዊ ሰልፍና የስብሰባ ፈቃድ ክፍል ደብዳቤ ለማስገባት በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡

የምርጫ የጊዜ ሰሌዳውን በመቃወም ፒትሽን ከፈረሙት 33 ፓርቲዎች ውስጥ አምስቱ የምርጫ ምልክታቸውን እንደወሰዱ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡ 

፡ የኢትዮጵያ ፍትህና ዲሞክራሲያዊ ሃይሎች ግምባር(ኢፍዲሃግ)፣ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሕብረት(ኢዲህ)፣ የባህር ወርቅ መስመስ ሕዝቦች ዲሞክራሲ ድርጅት(ባመህዴድ)፣ ዱቤና ደጀኔ ብሄረሰብ ዲሞክራሲያዊ (ዱብዴፓ) የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ፓርቲ(ሲአንፓ) የምርጫ ምልክት መውሰዳቸውን ቦርዱ አስታውቋል፡፡

“በሲዳማ ዞን ሕዝብ ጥያቄ በምርጫ ለመሳተፍ ተገደናል” ያለው የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ፓርቲ በበኩሉ የምርጫ ምልክት ወስዶ ለምርጫው ዝግጅት እያደረገ ቢሆንም በትግል ከ28ቱ ፓርቲዎች ጎን እንደሚሰለፍ ገልጿል፡፡

የ28ቱ ፓርቲዎች ሰብሳቢ አቶ አስራት ጣሴ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ “የምርጫ ቦርድ ፓርቲዎች ያቀረቡትን ጥያቄዎች ሳይመልስ ዐዋጁን ጥሶ ሕጋዊም፣ ሞራላዊም፣ ዲሞክራሲያዊ ባልሆነ መንገድ ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓት መጠንከር ወሳኝነት ያላቸውን ፓርቲዎች በመተው የሚያደርገውን ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ በመቃወም ሕዝባዊ ስብሰባ እንጠራለን” ብለዋል፡፡ የሕዝባዊ ስብሰባው ዓላማ ሁለት መሆኑን የጠቆሙት አቶ አስራት፤ አንደኛው የምርጫ ቦርድን ህገወጥ እንቅስቃሴ መቃወም ሌላው በሀገሪቱ በወቅቱ ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከሕዝቡ ጋር መወያየት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

 ‹‹ምርጫውን እርስዎም ይሞክሩት አናደርገውም፤ ቴክኒካሊ እኛ እየወጣን ነው›› ያሉት አቶ አስራት እንደ “በ2002 ዓ.ም ምርጫ ህብረ ብሄራዊና ብዙ ተከታዮች ያሏቸውን የፓለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫው ውጪ ለማድረግ ቦርድ ከኢህአዴግ ጎን እየሠራ ነው” ብለዋል።

ቀድሞ ሲል በ33ቱ ፓርቲዎች ውስጥ ተካተው ከነበሩት አንዱ የሆነው የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ፓርቲ ጸሃፊ አቶ ለገሰ ላቃሞ፤ ‹‹የምርጫ ምልክቴ የሆነውን አውራ ዶሮ ከምርጫ ቦርድ የወሰድኩት ሐዋሳን ጨምሮ የሲዳማ ሕዝብ ጥያቄው የክልል ጥያቄ ስለሆነ ሕዝቡ በዚህ ምርጫ ተሳትፎ በምርጫ ካርድ መብቱን ሊያስከብር ስለሚፈልግ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ወደ ምርጫ እንድንገባ ወስኗል›› ብለዋል፡፡ በምርጫ ይሳተፉ እንጂ ከ28ቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ትግል ጎን እንደሚቆሙ አቶ ለገሰ ተናግረዋል፡፡

ከሁለት ወር በኋላ ለሚደረገው የአዲስ አበባ አስተዳደርና የአካባቢ ምርጫ 19.5 ሚሊዬን ሕዝብ የምርጫ ካርድ መውሰዱን ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

Published in ዜና

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና እነ አንዱዓለም አራጌ በድጋሚ ተቀጠሩ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሰው የዕድሜ ልክ፣ የ25 ዓመትና የ18 ዓመት እስራት የተፈረደባቸው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ አንዱአለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን እና ክንፈ ሚካኤል አበበ የይግባኝ ክርክራቸውን አጠናቀው ለትናንት ተቀጥረው የነበረ ቢሆንም ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔውን ለአንድ ወር አራዝሞታል፡፡

ውሳኔው ለአንድ ወር የተራዘመበትን ምክንያት የዕለቱ ዳኛ አቶ ዳኜ መላኩ ሲገልፁ፤ በአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) የባህርዳር አመራር የሆኑት አቶ አንዱአለም አያሌውና ሻምበል የሺዋስ ይሁንዓለም በስር ፍ/ቤት የተከሰሱበትና የተቀጡበት መዝገብ ከእነ አንዷለም አራጌ ጋር አንድ ቢሆንም ይግባኝ የጠየቁት ግን በተለያየ መዝገብ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በሌላ መዝገብ የይግባኝ ጥያቄያቸውን ያቀረቡት እንደ አንዱዓለም አያሌውም ባለፈው ሰኞ ታኅሣሥ 6 ቀን ቀርበው ለየካቲት 8 መቀጠራቸውን ገልፀዋል፡፡ በመሆኑም ሁሉንም የይግባኝ አቤቱታዎች መርምሮ በአንድ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ይቻል ዘንድ ለየካቲት 8 ቀን 2005 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡

 

Published in ዜና

አንድ የአገራችን ገጣሚ ስለ አይጥ፣ ስለድመት፣ ስለውሻና ስለሰው የፃፈው ግጥም ጭብጡ በስድ ንባብ ቢታሰብ የሚከተለውን ተረት ይመስላል፡፡

አንዲት አይጥ ከዕለታት አንድ ቀን “ድመት” የሚል ግጥም ትጽፋለች አሉ፡፡ የግጥሙ ይዘት “ድመት ባይርባት ኖሮ እኔን አሳዳ አትበላኝም ነበር” የሚል ነው፡፡ አይጥ የፃፈችውን ግጥም ድመት ታገኛለች፡፡ ድመትም “አይጥ” የሚል ግጥም ትጽፋለች - እንደምላሽ መሆኑ ነው፡፡

አይጥና ድመት የፃፉትን ግጥሞች ሰው ያገኛል፡፡

ሰውየው፤ የቤቱ ባለቤት መሆኑ ነው፤ እጅግ አድርጐ ይናደዳል፡፡ ወረቀት ጽፈው በማየቱ እንጂ ስለምን እንደፃፉ አላነበበውም፡፡ ብቻ በንዴት

“አሃ! አይጥና ድመት በእኔ ላይ ግጥም መፃፍ ከጀመሩ፤ ተስማምተው ተነሱብኝ ማለት ነው። አድማ ነው! በጭለማ ወረቀት መበተን የመጥፎ ጊዜ ምልክት ነው፡፡ ትውልዱ ከፋ ማለት ነው። ስለዚህ እርምጃ መውሰድ ይገባኛል!” ሲል አሰበ፡፡ በመጨረሻም እንዲህ የሚል ውሳኔ አሳለፈ፡፡

“በቃ ሁለቱም ይቀጡ

ለዚያችም ወጥመድ ዘርጉ

ለዚችም ገመድ አምጡ!”

በትዕዛዙ መሠረት ወጥመድ ተዘረጋና አይጢት ተያዘች፡፡ ድመትም በገመድ ተጠፍራ ታሠረች። አይጥ ልትሞት ወደማጣጣሩ ደረሰች፡፡ ድመት በታሰረችበት እህል ውሃ አጥታ በረሃብ ልትሞት ተቃረበች፡፡

አይጥ ድመትን፤ “ለባለቤቱ ከምታሳብቂ፣ ልብ ካለሽ መልስ አትጽፊልኝም ነበር?” አለቻት፤ ወጥመድ ውስጥ ሆና!

ድመትም፤ ብስጭትጭት ብላ፤

“ቀጣፊ ነሽ! የፃፍኩልሺን መልስ ለጠላት አሳልፈሽ ከመስጠት አታነቢውም ነበር? በግልጽ አቋሜን ትረጂ ነበር! ከእንግዲህማ ስፈታ ቁም - ስቅልሽን ባላሳይሽ ዕውነት ድመት አደለሁም!” በማለት ትዝታለች!

አይጥ ድመት አሳብቃ በወጥመድ አስያዘችኝ ስትል፣ ድመት ደግሞ ለሷ የፃፍኩላትን ምላሽ ለጠላቴ (ለቤቱ ባለቤት) ሰጠችብኝ ትላለች፡፡ የቤቱ ባለቤት ደግሞ ስለምን እንደተፃፉም ሳያነብ ፍርድ ይሰጣል፡፡

ይህን የሆነውን ሁሉ ውሻ ቁጭ ብሎ ይታዘባል፡፡

“ወይ ግሩም! እነዚህ ፍጡሮች ሲሞቱም አይማማሩም!

ጠላት እንደሆኑ ኖረው ጠላት እንደሆኑ ሊሞቱ ነው፡፡ ጌታችንም፤

ጨካኝ ፍርደ -ገምድል ነው

በቀሉን ብቻ የሚያምን

በቋፍ በሥጋት የሚኖር

አንዱን ጥፋት ለማጥፋት፣ ሌላ ጥፋት የሚሠራ

ቁጥቋጦዎችን ለመንቀል፣ የሚጣላ ከተራራ…

ማንም ከማንም ላይሻል፣ ማንም ከማንም ላይበልጥ

አገር እንደበሬ ጠልፎ፣ ጥሎ ለመብላት መሯሯጥ

መንተፍተፍ…መተላለፍ፣ መጠላለፍ ሁሉን ማርገፍ!

ሁሉም መርገፍ!!” አለ፡፡

* * *

ከመጠላለፍ ይሰውረን፡፡ አደቡን ይስጠን፡፡ በተጠራጠርነው ሁሉ ፍርድ ከመስጠት ያድነን፡፡

እየደጋገምን የምናጠፋው ጥፋት እኛን ራሳችንን ይዞ እንዳይጠፋ መጠንቀቅ ያባት ነው! የምንገባው ቃል መፈፀሙን የሚያረጋግጥልን አንድም ታሪካችን፣ ሁለትም ለራስ መታመናችን ነው! በተግባር የምንሠራው በቃል የምናወራውን ካልመሰለ ዕቅዳችን፣ ስትራቴጂያችን ሁሉ፤ ውሃ የበላው ቤት እንደሚሆን አንርሳ! በታሪክ ያየነው ስህተት እንዳይደገም መጣጣር አዲስ ታሪክ መሥራት ነው!

“ታሪክ ራሱን ይደግማል” ፣ ይላል ታሪከኛው ሁሉ

እኔን ያሳሰበኝ ግና፡- ታሪክ በደገመ ቁጥር፤ ዋጋው እጅግ መቀጠሉ፤”ይለናል ሜይ ግሪንፊልድ፡፡ የሚያስከፍለን ዋጋ ብዙ ነው እንደ ማለት ነው፡፡

በርናርድ ሾው የተባለው ፀሐፊ “የአንዱ ሥጋ ለአንዱ መርዝ ነው፡፡ የአንዱ ዕድሜ ናፍቆት፤ የሌላው ዕድሜ መከፊያና ማዘኛ ነው! (one man’s meat is one man’s poison, one age’s longing another age’s loathing) የሚለው ይሄን ብጤውን ነው፡፡ የሚያስከፋን እየቀነሰ የሚናፍቀን የሚጨምርበትን ሁኔታ ለመፍጠር መደማመጥ፤ መግባባትና መተሳሰብ ያሻናል፡፡

ከፊል በእጅ፣ ከፊል በዲጂታል የሚከፈት ሠረገላ ቁልፍ (both manual and digital at the same time) ይዘን ለውጥ ማምጣት ከባድ ነው - ዘይትና ውሃ እንዲሉ፡፡ “ባለራዕይ-ለማኝ ዐባይ ሲገደብ የምሰጥህ ሁለት ብር አበድረኝ ይላል” እያሉ የአራዳ ልጆች እንደሚሳለቁት እንዳይሆን፤ በማንኛውም ረገድ ራስን መቻል እንደሚኖርብን ልብ እንበል፡፡ በምግብ ራሳችንን ችለን ረሀብተኛ ዲሞክራሲ ይዘን እንጓዝ ብንል የማያዋጣንን ያህል፤ በባዶ ሆድም ዲሞክራሲን አንግቦ መጓዝ ወንዝ አያሻግረንም፡፡ ጥቂት የናጠጡ ሀብታሞችና አያሌ የኔ-ብጤዎች ያሏት ሀገርም ሆነ ሰላሟን አጥታ ብዙ ሀብታሞችን ያፈራች ሀገር እንድትኖረን አይደለም ደፋ-ቀና የምንለው፡፡ እንደጥንቱ መፈክር “ጉዟችን ረጅም ትግላችን መራራ” ነው ማለትም አያዛልቀንም፡፡ ሁሌም ረጅም፣ ሁሌም መራራ መሆን የለበትምና! “ጊዜ ነው ይላል ሻጥረኛ፤ በጊዜ አሳቦ ሊተኛ!” ይለናል ፀጋዬ ገ/መድህን፡፡ “ሁሉ ነገር ሂደት ነው” በሚል መጠቅለያ ያለ ለውጥ፣ ያለ ዋስትና መራመድ አይቻልም፡፡ The change should be incremental እንደሚሉት ነው ፈረንጆቹ። የለውጥ አንቀሳቃሹ በአብዛኛው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ በዕውቀት የተገነባ፣ ለውጥ የገባው፣ ዛሬ ላይ የተደረሰው ብዙ ለውጥና መስዋዕትነት ታይቶ መሆኑን የተረዳ ወጣት እንጂ “Fast” በሚል ታርጋ የታሸገ የቢዝነስ ተሯሯጭ ለብ-ለብ ትውልድ ብቻ እንዳይሆን አገርና ነገር የገባው ወጣት መገንባት ያስፈልጋል፡፡ ያልፈጠርነውን፣ ያላስተማርነውን፣ በአግባቡ ያላነፅነውን ልጅ የሌለ ቅፅል ሰጥተን ብናሞካሸው ረብነት የለውም፡፡ በአናቱ ቅቤ ጣል ያለበት ሹሮ ዓይነት ካፒታሊዝም ኑሮአችን ቅቤ በቅቤ ነው እንደማያሰኝ ሁሉ፤ በእንዲህ ያለ ሥርዓት ውስጥ የሚያድግም ልጅ በአርቲፊሻል የተኳኳለ ከመሆን በቀር ኦርጅናሌ እንደማይሆን እናስተውል፡፡ “በወጉ ያላሳደገውን ልጅ የእከሌን ልጅ ይመስላል፤ ይላል” ማለት ይሄው ነው፡፡

Published in ርዕሰ አንቀፅ

አቶ ተካ አስፋው ጀባ የተባሉ የቅመማ ቅመም ነጋዴ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ መርካቶ በሚገኘው ምዕራብ ሆቴል ከሊፍት ስር ባለ ጉድጓድ ውስጥ ሞተው ተገኙ፡፡ የ65 አመት እድሜ ባለፀጋ የሆኑት አቶ ተካ እሁድ ታህሳስ 21 ቀን 2005 ዓ.ም ከጠዋቱ አራት ሰዓት አካባቢ ጀምሮ ከሚሠሩበት የቅመማ ቅመም ንግድ መደብራቸው እንደጠፉ የሚናገሩት ቤተሰቦቻቸውና የስራ ባልደረቦቻቸው፤ ከአራት ቀናት በኋላ ታህሳስ 24 ቀን 2005 ዓ.ም ምዕራብ ሆቴል ውስጥ ከሊፍት ስር ወድቀው መገኘታቸውን ከፖሊስ ተደውሎ እንደተነገራቸው ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡

ሟች በጠፉ ማግስት በኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች የአፋልጉኝ ማስታወቂያ ማስነገራቸውን እንዲሁም በአካባቢው ለሚገኘው 4ኛ ፖሊስ ጣቢያ ስለመጥፋታቸው ማስታወቃቸውን የገለፁልን ቤተሰቦቻቸው፤ እያሽከረከሯት የነበረችው መኪና ድሬ ታወር አካባቢ ቆማ መገኘቷንም ተናግረዋል፡፡

የወላጅ አባታቸውን መጥፋትና በኋላም ሞቶ መገኘት በሚኖሩበት አሜሪካን ሃገር ሆነው በስልክ መስማታቸውን የነገሩን አቶ ፈለቀ ተካ፤ ዝርዝር ጉዳዩን እዚህ ከመጡ በኋላ ከሟች የስራ ባልደረቦችና እዚህ ካሉ ቤተሰቦቻቸው መረዳታቸውን ለዝግጅት ክፍላችን ገልፀዋል፡፡

ሟች የሆቴል አገልግሎትን ጨምሮ በተለያዩ የንግድ ስራዎች በመርካቶ አካባቢ ይሠሩ እንደነበርና እስከ እለተሞታቸውም በቅመማ ቅመም ንግድ ይተዳደሩ እንደነበር አቶ ፈለቀ ገልፀውልናል፡፡ የስምንት ልጆች አባት የነበሩት አቶ ተካ ከሁለቱ ልጆቻቸው በስተቀር ሁሉም በአሜሪካን አገር እንደሚኖሩ ከቤተሰቦቻቸው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከሟች ልጆች አንዱ የሆኑት አቶ ግዛው ተካ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉት መሆኑን በመግለፅ የሟች አስከሬን ከአንድ ሜትር ተኩል በማይበልጥ ጉድጓድ ውስጥ ሲገኝ አብሮ የእጅ ሠአት፣ ሞባይል ስልካቸው፣ የተለያዩ ቼኮችና 2700 ብር ጥሬ ገንዘብ መገኘቱን ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል፡፡ በወቅቱ ሟች ያሽከረክሯት የነበረችው መኪና ቁልፍና የቁም ሣጥን ቁልፍ ግን እስካሁን አለመገኘቱ ግራ እንዳጋባቸውና ይህም እንዳሣሠባቸው ገልፀዋል፡፡ እሁድ ጠዋት ላይ ጭላሎ ሆቴል አካባቢ ቀጠሮ አለኝ ብለው ከቤት መውጣታቸውን የሚናገሩት የሟች ቤተሠቦች እስካሁን ከማን ጋር ተቀጣጥረው እንደነበር አለመታወቁ እንዳሣሠባቸው ይህንንም ፖሊስ እንዲያጣራ ማሣወቃቸውን ገልፀውልናል፡፡ ከቤት የወጡ እለትም ስልካቸው እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ድረስ ላይ በተደጋጋሚ ሲደወል ነገር ግን እንደማይነሳ አስረድተዋል፡፡

የምዕራብ ሆቴል የካፍቴሪያ ሃላፊ አቶ አዳነ ሸለሙ ስለሁኔታው ብዙም እንደማያውቁና ግለሰቡ እንደማንኛውም ተስተናጋጅ ለመስተንግዶ ወደ ሆቴሉ ከምጣታቸው በስተቀር የብዙ ቀን ቆይታ በሆቴሉ እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ ከተፈጠረው አደጋ ጋር በተያያዘም የሆቴሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ተፈራ ክፍሌን ጨምሮ በወቅቱ የነበሩ ጥበቃዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን አቶ አዳነ ተናግረዋል፡፡

ጉዳዩን እየተከታተለ ከሚገኘው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ “ፍቃድ ያስፈልጋል” በመባላችን ሳይሳካልን ቀርቷል፡፡

Published in ዜና

ከእነህይወታቸው የሚቀበሩ ሰዎችን መታደግ ይቻላል - ዶ/ር ዘካሪያስ ገሰሰ

በመቀሌ ህይወታቸው አልፏል ተብሎ ሊቀበሩ የነበሩ አንዲት እናት፤ ድንገት ነፍስ ዘርተው መንቃታቸው ቤተሰቦቻቸውንና የአካባቢውን ነዋሪዎች አስደነገጠ፡፡ መግንዛቸው ተፈትቶ ወደ ሆስፒታል የተወሰዱት እኚህ እናት፤ በአሁኑ ወቅት በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ሃኪም ገልጿል።

በመቀሌ ከተማ ቀበሌ 03 ውስጥ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ወይኒ ፀጋዬ ከሐሞት ጠጠር እና ከኩላሊት ችግር ጋር በተያያዘ በገጠማቸው የጤና መቃወስ በመቀሌ ሆስፒታል ከአንድ ወር በላይ በመተኛት ህክምና ሲከታተሉ ቆይተዋል፡፡ የወ/ ሮዋ ሐኪም ዶ/ር ዘካሪያስ ገሰሰ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ ሴትየዋ የሽንት ባንቧቸው ተዘግቶ ኩላሊታቸው ውሃ ቋጥሮ ለከፍተኛ ሥቃይ ዳርጓቸው ነበር። ከዚህ ችግር ጋር በተያያዘም አንደኛው ኩላሊታቸው መስራት ያቆማል፡፡ በሆስፒታሉ በተደረገላቸው ህክምና ግን የሴትየዋ ጤና መሻሻል ከማሳየቱም በላይ አገልግሎት መስጠት አቁሞ የነበረው ኩላሊታቸው ወደ ትክክለኛ ሥራው መመለስ ጀመረ፡፡ በመጨረሻም ጤናቸው በእጅጉ በመሻሻሉና የገና በዓልም እየተቃረበ በመምጣቱ ሴትየዋ ከሆስፒታሉ ለመውጣት ጥያቄ ያቀርባሉ” በጥያቄያቸው መሰረትም ከሆስፒታሉ ወጥተው በዓልን በቤታቸው እንዲያሣልፉ መፈቀዱን ዶ/ር ዘካሪያስ ይገልፃሉ፡፡ የገናን በዓል ከልጆቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው ጋር በሠላም እንዳሳለፉ የሚናገረው ልጃቸው ቴዎድሮስ ፍስሃ፤ የጤንነታቸው ሁኔታ መልካም በመሆኑና እምብዛም የሚያሣስባቸው ችግር ስለላጋጠማቸው ወደ ሆስፒታል እንዳልተመለሱ ገልጿል፡፡ ጥር 5 ቀን 2005 ዓ.ም ማለዳ ላይ ግን ወ/ሮ ወይኒ ቀስ በቀስ እየደከሙ በመሄዳቸው ልጆቻቸው ተደናግጠው እየተጯጯሁ የአካባቢ አንጋፋ ሰዎችን ይጠራሉ፡፡ የወ/ሮ ወይኒን ሰውነት መቀዝቀዝና የልብ ምታቸው መቆሙን ያስተዋሉት የአካባቢው ሰዎች፤ ሴትየዋ መሞታቸውን ያረዳሉ፡ ፡ ይሄኔ ልጆቻቸውና ቤተሰቦቻቸው በመሪር ሃዘን ተውጠው ለቅሶአቸውን ያቀልጡታል፡፡ እንደ አካባቢው ወግና ሥርዓትም የወ/ሮ ወይኒ አስከሬን ታጥቦና ተገንዞ በሰሌን እየተጠመጠመ ጥብቅ ተደርጐ ይታሰራል፡፡

በአካባቢው ባህል ሰው ከሞተ ማሣደርና ማቆየት ስለማይገባ የፍትሃት ፀሎት ተደርጐላቸው ቀብራቸው ከቀኑ 8 ሰዓት እንዲሆን ይወሰናል፡፡ ወደ ስድስት ሰዓት ገደማ በሀዘን ተውጠው የእናታቸውን አስከሬን እያዩ ከነበሩት ልጆች መካከል አንዱ ድንገት ጩኸት ያሰማል፡፡ ሌሎቹ ተደናግጠው የሆነውን ሲጠይቁት “አስከሬኑ ይንቀጠቀጣል” በማለት ይናገራል - ወደ አስከሬኑ በፍርሃት እያየ፡፡ ነገሩ ያስደነገጣቸው ልጆችና የአካባቢው ሰዎች፣ አስከሬኑን ከበው ሁኔታውን መከታተል ይጀምራሉ፡፡ የሴትየዋ መንቀጥቀጥ እየጨመረ ሲመጣ አስከሬኑን በመፍታት ሐኪማቸውን ያስጠራሉ፡፡ በሰሌን ተጠቅልሎና በጥብቅ ታስሮ የነበረው በተፈታ ጊዜ ሴትየዋ በእፎይታ እንደተነፈሱ የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡

ሃኪሙወዲያውኑ ሴትየዋን ወደ ሆስፒታል በማስወሰድ ጉሉኮስ እንዲሰጣቸዉ ያደረጉ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙና ከጥቂት ቀናት በኋላም ወደ ቤታቸው እንደሚመለሱ ሃኪማቸው ዶ/ር ዘካሪያስ ገሰሰ ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ዘካሪያስ በዚህ አጋጣሚ ባስተላለፉት መልዕክት፤ “አንድ ሰው ሞተ ተብሎ መሞቱ መረጋገጥ የሚቻለው በህክምና በመሆኑ የሞት ማረጋገጥ ህክምና ቢለመድ ከነህይወታቸው የሚቀበሩ ሰዎችን ነፍስ መታደግ ይቻላል፡፡ እናም የሞት ማረጋገጥ ህክምና መለመድ ይገባዋል” ብለዋል፡፡ 

Published in ዜና

በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የተፃፈውና ሰሞኑን ለንባብ የበቃው “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” የተሰኘው መጽሐፉ ሀ ብሎ ሲጀምር እንዲህ በሚል ያልተለመደ ማስጠንቀቂያ ይንደረደራል፡፡

“ቁም! በመጀመሪያ ለአንባቢው አንድ ማስጠንቀቂያ ልስጥ፡፡ መጽሐፉ በጠቅላላ በተለይ ይህ መቅድም የከረረ ንዴት መግለጫ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አጠቃላይ ሁኔታ ያልተናደደ፣ የማይናደድና ያልተበሳጨ ወይም ደልቶት የሞቀው ይህንን መጽሐፍ በተለይም ይህንን መቅድም አያንብበው። የረጋውን መንፈሱን ያስሸብረዋል” የሚል ማስጠንቀቂያ በማስፈር መጽሐፉን ንዴተኞች እና ብስጩ ሰዎች ብቻ እንዲያነቡት ቢጋብዙም፣ ይህንን መፈክር መሰል አጥር በማለፍ በተለይም የመጽሐፉን መቅድም ማለትም የከረረውን ንዴት ማንበብ ጀመርኩ፡፡ መቼም መግቢያው ላይ እንደሰፈረው፤ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሁኔታ የሚናደድ ወይም በኢትዮጵያ አጠቃላይ ሁኔታ የሚደሰት ሰው ማግኘት በራሱ ትልቅ ጥያቄ የሚያስነሳ ቢሆንም በግሌ በአጠቃላይ ሁኔታ የምናደድ ወይም በአጠቃላይ የሀገሬ ሁኔታ የምደሰት እንዳልሆንኩ ለመግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ በአጠቃላይ ሁኔታ ደስተኛ ነኝ የሚል ሰው በጭፍን ፍቅር የታወረ መሆኑን ለመገንዘብ የምችለውን ያህል፣ በአጠቃላይ የሀገሪቱ ሁኔታ የከረረ ንዴት እና ብስጭት ውስጥ ነኝ ባዩም የጭፍን ጥላቻ ውጤት መሆኑን ለመረዳት ብዙ የሚያስቸግር አይመስለኝም፡፡

በመሆኑም ከጭፍን ንዴትና ደስታ ወጣ ብዬ የመስፍን ወልደማርያምን መጽሐፍ መቅድም ሳነብ የፈጠረብኝን ንሸጣ እንደሚከተለው ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡
መጽሐፉ በመቅድሙ በስፋት ካነሳው የመክሸፍ ታሪክ ከመዳሰስ አልፎ በርካታ የታሪክ እና የፖለቲካ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚያነሱ ምዕራፎች ቢኖሩትም፣ አብዛኞቹ አንዱን ንጉስ ለማወደስ ሌላውን ንጉስ የማንቋሸሽ የወንዝ ልጅነት አባዜ እና የግል ዝንባሌ የሚታይባቸው፣ በጥላቻ የታጨቁ የንዴት ውጤቶች በመሆናቸው፣ ለዛሬው መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ የተሰኘው የመጽሐፉ ዋነኛ ድርሰት ላይ አተኩራለሁ፡፡

ንዴተኛ እና ብስጩ ሰዎች ብቻ እንዲያነቡት የሚገልፀውን ማስጠንቀቂያ በማስከተል የመክሸፉን ምንነት እና ትርጓሜ በመስጠት የሚጀምረው የመስፍን ወልደማርያም መጽሐፍ፤ በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ስለሚከሰተው መክሸፍ አንድም የታሪክ ምሁር ትኩረት ሰጥቶ ጽሑፍ ጽፎ እንደማያውቅ በምሬት በመጥቀስ፣ በምሳሌነት ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ የለውጥ ፈር ቀዳጆች በማለት በእንግሊዝኛ የፃፉትን መጽሐፍ ይተቻሉ። ይተቻሉ ያልኩት መደበኛውን አገላለጽ ለመጠቀም ያህል ነው፡፡ መስፍን ሁልጊዜ እንደሚያደርጉት እዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚያነሷቸውን ምሁራን ሃሳባቸውን ብቻ ሳይሆን የሚተቹት ግለሰባዊ ማንነታቸውን ጭምር ነው የሚዘልፉት፡፡
“ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ አንዱ አስተማሪው ያስታጠቀውን” ብለው ጀምረው “ባህሩ የፈረንጅ ትምህርት ፍሬ በመሆኑ የጥንቱን ላያውቀው ይችላል፡፡
ታዲያ ሊቅነት የማያውቁትን ለማወቅ መጣር አይደለም እንዴ?” በማለት ያሳርጋሉ፡፡ እንደሁልጊዜው ያልኩት በቅርቡ ለፕ/ር ገብሩ ታረቀ የሰጡትን ከተነሳው ሃሳብ ጋር የማይገናኝ “የባህር ማዶ” ሰው የሚል መልስ የሚያስታውስ ያስታውሰዋል በማለት ነው፡፡

እዚህ ላይ ምሁራኑ ላይ ያወረዱባቸውን ናዳ ትተን ታሪክ ፀሐፊዎቻችንን የተቹበትን መንገድ ሳናደንቅ ማለፍ ያለብን አይመስለኝም፡፡
በተለይም በታሪክ ምሁራኖቻችን ላይ የሚታየውን ለሕዝባቸው በሚገባ ቋንቋ እና በሚደርስ መልኩ ታሪክን ከመፃፍ ይልቅ በባዕድ ቋንቋ ባዕዳንን በሚያስደስት መልኩ ለከፈላቸው ብቻ የመፃፉን አዝማሚያ መተቸታቸው ከመቅድሙ የምናገኘው ጠንካራ የመጽሐፉ አካል ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም፡፡ ባህሩ ዘውዴ ከዚህ ወቀሳ የዘለሉ በአማርኛም ሆነ በእንግሊዝኛ በርካታ ጽሑፎችን ያቀረቡ መሆናቸው ሳይዘነጋ፡፡

በመቀጠል ትኩረት ሰጥተው በተከታታይ አንቀፆች ያስቀመጧቸው ነጥቦች ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ለመነሳት እየሞከረች የከሸፈችበትን ምክንያት ነው። በተለይም በየጊዜው እና አሁንም ድረስ ባንዳዎች እያደረሱባት ያለውን ኪሳራ በከረረ ንዴት ለመግለጽ በመጽሐፉ ሽፋን ላይ ያስቀመጡትን “ኢትዮጵያ ሀገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” የሚለውን አስተሳሰብ አጽንኦት ሰጥተውይሞግታሉ፡፡

“በትክክል ባላውቅም በግምት እንደ ኢትዮጵያ አርበኞቹን የገደለ አገር በአለም ላይ ያለ አይመስለኝም፡፡ እነ በላይ ዘለቀ፣ አበበ አረጋይ፣ ራስ ስለሺን እና ስንትና ስንት አርበኞች ገለናል” የሚሉን መስፍን ወልደማርያም፤ “ባንዳን እያደነቁና እያከበሩ አርበኞችን እየናቁ ለአደጉ ትውልዶች አዘንሁ፤ ለኢትዮጵያ አዘንሁ፤ ስለዚህም የአሁኑ ባንዳ አክባሪ ትውልድ በአጥንት ላይ መቆሙን እንዲገነዘብ ለማድረግ ፎቶግራፎች ትንሽ ይረዳሉ ብዬ አሰብኩ” በማለት በመጽሐፉ መጨረሻ ገፆች ላይ የጣሊያን ወታደሮች በኢትዮጵያውያን ላይ ያደረሱትን ስቃይ የሚያሳይ ፎቶግራፍ የማስቀመጣቸውን ምክንያት ይገልፃሉ፡፡ መግለፃቸው ባልከፋ “የአሁኑ ባንዳ አክባሪ ትውልድ” የሚለው አገላለጽ ግን ምን ለማለት ተፈልጐ እንደገባ ቢያንስ ለኔ ግልጽ አይደለም፡፡ ሌላው ቢቀር ለበላይ ዘለቀ ከዚህ ትውልድ በላይ የዘፈነለት፣ ውዳሴ ያጐረፈለት፣ ቅኔ የተቀኘለት እና የተወነለት ትውልድ ያለ አይመስለኝም፡፡ ከሸሹበት ሀገረ እንግሊዝ ተመልሰው በላይ ዘለቀን የሰቀሉት ኃ/ሥላሴ “ግርማዊነትዎ” እየተባሉ ለምን ይወደሳሉ የሚል ጥያቄ ቢሆን የተነሳው ክርክር ሊገባን ይችላል፤ ነገር ግን እዛው እነ በላይን ገደልን በሚሉበት አንቀጽ ላይ ለኃ/ሥላሴ ሀውልት እንዳይሰራ ነፈግናቸው በማለት ለገዳዩም ለተገዳዩም ጥብቅና ሲቆሙ እናገኛቸዋለን፡፡ በዚህ ሰዓት የአሁኑ ባንዳ አክባሪ ትውልድ የት እንዳለ ይጠፋብናል፡፡ ይባስ ብለው ወደሃያ የሚጠጉ የአፄ ኃ/ሥላሴ ባለስልጣናትን ስም ጠቅሰው፤ የኢጣሊያ ገባሮች ሆነው የወር ደሞዝ የሚያገኙ ባንዳዎች እንደነበሩ በመግለጽ የሚያቅለሸልሻቸውም እውነት “አንገታቸውን የሚደፉ የአርበኞች ልጆችና ደረታቸውን የሚነፉ የባንዳ ልጆች መታየታቸው” እንደሆነ ከዚህም የሚበልጥ መክሸፍ እንደሌለ ይገልፃሉ፡፡

በባንዳነት ከተጠቀሱት መካከል አቶ ከበደ ሚካኤል፣ አቶ ብርሃኑ ድንቄ፣ ሼክ አሊ ሆጀሌ፣ ራስ ስዩም መንገሻ፣ ሱልጣን መሐመድ ሀንፍሬ፣ ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረየሱስ እና አቶ ይልማ ደሬሳ ይገኙባቸዋል፡፡ ልጆቻቸው መቼ ደረታቸውን እንደነፉብን ግን አላውቅም። አንዳንዶቹ በአንድ ወቅት የጣሊያን አገልጋይ የነበሩ መሆናቸውን ብናውቅም የአንዱን ሰው የአንድ ወቅት ቁራጭ ሕይወት እንደ አጠቃላይ የሕይወቱ ተልዕኮ አድርጐ በመውሰድ ከበደ ሚካኤልም ሆኑ ይልማ ደሬሳ፤ አፈወርቅም ሆኑ ብርሃኑ ድንቄን ጠቅልለን የጥላቻ ወይም የአድናቆት ቅርጫት ውስጥ መክተት ያለብን አይመስለኝም፡፡
ያጠፉትን ጥፋት ብቻ ጠቅሰን ግለሰቦቹ ያበረከቱትን መልካም ተግባራት ለማን ልንሰጥ ይሆን? በቅርቡ ፖስታ ቤት የአፈወርቅ ገ/እየሱስን ፎቶ ከሌሎች ደራሲያን ጋር በማሳተሙ የተነሳውን አቧራ ሁላችንም የምናውቀው ነው፡፡

በዛ ላይ ይህን ወቀሳ የሚደረድሩት የመጽሐፉ ደራሲ፤ ስልሳዎቹ የአፄው ባለስልጣናት በሞት ሲቀጡ የሸንጐ አባል የነበሩ ሲሆኑ ይህ አልበቃ ብሏቸው ልጆቻቸው ዘነጡብን ብሎ ለሌላ በቀል መነሳሳት ምን ይሉታል፡፡ የአፄው ስርዓት እነዚህን ባንዳዎች አክብሮ ልጆቻቸው አሁን በምንኖርበት ዘመን ደረታቸውን መንፋታቸው የሚያቅለሸልሻቸው መስፍን፤ የአሁኑ ባንዳ አክባሪ ትውልድ በማለት ወደ ገለፁት ዘመን መለስ ብለው ሀይለኛ ወቀሳ የሚያሳርፉት የኃ/ሥላሴን መልካም ጅምሮች ማስቀጠል ባለመቻሉ ነው በማለት ጭርሱኑ የባሰ መደናቆርና ግራ መጋባት ውስጥ ይከቱናል፡፡
“በምንኖርበት ዘመንም ቢሆንም የኢትዮጵያን ውድቀት ለመረዳት ብዙም ጊዜ አይፈጅም፡፡ የትልቅነትና ታሪካዊ ምልክቶች ሁሉ ደብዛቸው እንዲጠፋ እየተደረገ ነው፡፡ የብሔራዊ መዝሙሩ ሁለት ጊዜ ተለውጧል፡፡ በሰንደቅ አላማው በአየር መንገዱ፣ በቴሌ የአንበሳ ምልክት እየተነቀለ ተጥሏል” በማለት ቁጭታቸውን ይገልፃሉ፡፡
መቼም አንድ በዚህ ዘመን የሚኖር የሰለጠነ ዕውቀት ያለው ኢትዮጵያዊ፤ “የሁሉ ነገራችን መሠረት ንጉሳችን ነው” የሚል መዝሙር ለምን ተቀየረ ብሎ የሚቆጭ አይመስለኝ፡፡
“ኢትዮጵያ ሆይ ደስ ይበልሽ በአምላክሽ ሀይል በንጉስሽ” ብሎ ጀምሮ “ድል አድራጊው ንጉሳችን ይኑርልን ለክብራችን” የሚለውን መዝሙር የአሁኑ “ባንዳ አምላኪ ትውልድ” መወቀስ ካለበት መዝሙሩን ባይቀይረው ኖሮ እንጂ በመቀየሩማ ሊወደስ ነው የሚገባው፡፡

ባንዲራዉ ላይ የነበረው ዘውድ የጫነ አንበሳስ ግልፅ አይደለም፡፡ አንበሳው እኮ ዘውድ ብቻ አይደለም ጭኖ የሚታየው በአንዱ እጁ የጨበጠው መስቀልም ጭምር እንጂ፡፡ ሙስሊሙ እና ክርስቲያን ያልሆነው ወገናችን የማይከበርበት ግርማ እንዴት ነው የኢትዮጵያዊነት ግርማ እየተነቀለ ተጣለ ሊባል የሚችለው?
የመስፍን ወልደማርያም ያለፈውን ዘመን መናፈቅ እና የአሁኑን ዘመን የመርገም አባዜ በዚህ ቢያበቃ ጥሩ፡፡
በአንዱ በኩል ባንዳዎችን አከበረ የሚሉት የኃ/ሥላሴ ስርዓት፤ በሌላ በኩል አሁን ካለው ትውልድና ሥርዓት የተሻለ እንደሆነ ለማሳመን ያቀረቡት ምክንያት የእውቀት ነው ወይስ የጤና ችግር ብዬ እንድጠይቅ አስገድዶኛል፡፡ በጭፍን ጥላቻ እና በከረረ ንዴት የተዋጠ ሰው፣ ጤናማ አመለካከቱ ጥያቄ ውስጥ መግባቱ አይቀሬ መሆኑ መቼም አይካድም፡፡

የሚከተለውን ማብራሪያ ስትመለከቱ እንደኔ እጅግ መደንገጣችሁ እና መገረማችሁ አይቀርም የሚል እምነት አለኝ፡፡ “በስንት ዘመናት ጥራትና በሰለጠነ የሰው ሀይል የተገነቡና የአገር ኩራት የነበሩ መስሪያ ቤቶች ተንኮታኩተዋል፡፡ ያሉትም ቢያንስ ሠላሳና አርባ ዓመት ወደኋላ ተመልሰዋል ወይም ጭራሹኑ ጠፍተዋል፤ ሆነ ተብሎ በስልት ከተዳከሙት ውስጥ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርስቲ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ይገኙበታል። እነዚህ ሁሉ በመክሸፍ ላይ የሚገኙ ናቸው” በማለት እጅግ በጣም ድፍረት የተሞላበት ትንታኔ ይሰጣሉ፡፡

እየተስፋፉ ያሉትን ዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት ጥራት ጥያቄ በይደር እናቆየውና የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ቴሌ እና መብራት ኃይል በምን አይነት አዕምሮ ነው ወደ ኋላ ሠላሳና አርባ አመት ተመልሰዋል ሊባሉ የሚችሉት፡፡ ልብ በሉ መስፍን ወደ ኋላ ተመልሰዋል ብቻ አይደለም የሚሉት “ጭራሽኑ ጠፍተዋል” ነው ያሉት፡፡ ይህን ጊዜ ነው የከሸፈው የመስፍን አስተሳሰብ ወይስ የኢትዮጵያ እውነት ብለን ለመጠየቅ የምገደደው፡፡

እንዲህ አይነቱን ተራ እጅግ በጣም በዘለፋ የተሞላ መፅሐፍ ፅፎ “በኢትዮጵያ አጠቃላይ ሁኔታ ያልተናደደ እና ያልተበሳጨ ሰው ይህንን መፅሐፍ በተለይም ይህንን መቅድም አያንብበው፤ የረጋውን መንፈሱን ያስሻክረዋል” ማለትስ ምኑ ሊገባን ነው ለኛ? ለምንድነውስ በሀገራችን ሁኔታ የተበሳጨ እና የተደሰተ በሚል ከሁለት ሊከፍሉን የተነሱት፡፡
እንዴትስ ያለ ዜጋ እና እውቀት ነው በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሁኔታ የሚበሳጭ እና የሚደሰት? ሌላው ቢቀር ከድህነት ወለል ለመላቀቅ በትግል ላይ ያለች፣ ከእርዳታ እና ከብድር ያልተላቀቀች፣ በሥራ አጥነትና በብዙ መሰል ችግሮች የተተበተበች ሀገር ይዞ እንዴት ሰው በአጠቃላይ ሁኔታ ሊደሰት ይችላል? በምንስ ሁኔታ ነው ኢትዮጵያ የምታደርገውን የኤሌክትሪክ ሀይል ግንባታ እና ግድብ ሥራ፣ ከፍተኛ የሆነ የትራንስፖርት እና የመንገድ ግንባታ እንዲሁም የጤና እና የትምህርት ሽፋን እንቅስቃሴ እየተመለከተ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሁኔታ የተናደደ ሰው ፍለጋ የምንወጣው? ከጭፍን ፍቅርና ከጭፍን ጥላቻ ይሰውረን ከማለት በቀር ሌላ ልንለው የምንችለው ነገር ይኖር ይሆን?

Saturday, 19 January 2013 15:04

ጋዜጠኞች ምን ይላሉ?

ወደ ደቡብ አፍሪካ ከሚጓዙ 25 ጋዜጠኞች መካከል በአራት አጭር ጥያቄዎች የቀረበ መጠይቅ በማቅረብ የሚከተሉትን ምላሾች አግኝቷል፡፡ አራቱ ጥያቄዎች ከዚህ በታች የቀረቡት ሲሆን የስፖርት ጋዜጠኞቹ ምላሻቸውን በቅደምተከተል እንዲህ መልሰዋል
1. በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለጋዜጠኞች የተፈጠረው እድል ምን ምን ስሜት ፈጠረብዎ? 2. የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከ31 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ በማለፉ ምን ተሰማዎት? በቀጣይ የአፍሪካ ዋንጫዎች ለመሳተፍ ምን ይደረግ?

3. በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ምን ውጤት ይጠብቃሉ?
4. በምድብ 3 የኢትዮጵያን ውጤት ይገምቱ ሀ. ኢትዮጵያ ከዛምቢያ ለ.ኢትዮጵያ ከቡርኪናፋሶ ሐ.ኢትዮጵያ ከናይጄርያ
1. የስፖርት ጋዜጠኞች ላደረጉት ጥረት ጥሩ ምላሽ ነው፤ ፊታቸውን አውሮፓ ላይ ብቻ ያደረጉትም ለሀገር ውስጥ ትኩረት እንዲሰጡ የሚያበረታታ ነው፡፡
2. በስፖርት ጋዜጠኝነት ህይወቴ ከገጠመኝ ትልቅ ደስታዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ አሁን ካለው እንቅስቃሴ ጐን ለጐን Grass root level ላይ መስራት ያስፈልጋል፡፡
3. Surprising team ይሆናል፡፡ በእርግጠኝነት ሩብ ፍፃሜ እንደርሳለን፡፡ ሳንታሰብ ግማሽ ፍፃሜም ልንደርስ እንችላለን፡፡
4. ሀ.2 - 1 ለ.1 - 0 ሐ.0 - 1
ምስጋናዉ ታደሰ ከፕላኔት ስፖርት

1. ጋዜጠኛና የዚህን መሠሉ ዕድል ባለቤት ሆነው ማየትን ለዘመናት አጥብቄ እመኝ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለጋዜጠኞችና ለሙያተኛው ዋጋና ክብር ሠጥቶ የዚህ ዕድል ባለቤት እንዲሆኑ የልምድና የዕውቀት ሽግግር እንደያግዝ ትልቅ በር የሚከፍት ነው፡፡ የፌዴሬሽኑ አመራር ሊመሰገን ይገባል፡፡
2. ስፖርት ወዳዱ ህዝባችን ይሄንን ቀን አጥብቆ ሲናፍቀው ቆይቷል፡፡ ይሄ የዘመናት ህልማችን ዕውን ሆኖ ማየቴ እንደ አንድ ጋዜጠኛ ብቻ ሣይሆን እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ትልቅ ደስታ ተሰምቶናል፡፡ ቁም ነገሩ ለውድድሩ አንድ ጊዜ ማሳያ ብቻ ሣይሆን ቀጣይነቱ እንዲኖረው ብዙ መሥራት ነው፡፡
3. ብሄራዊ ቡድናችን በውድድሩ ጥሩ ተፎካካሪ ከመሆን በዘለለ የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ዙር ያልፋል፡፡
4 .ሀ.1 - 0 ለ.2 - 1 ሐ.1 - 2
ይስሐቅ በላይ ከሀትሪክ የስፖርት ጋዜጣ

1. ከምንም በላይ ኢትዮጵያ ከ31 አመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉ ታላቅ ነገር ነው፡፡ ይሄን ሁኔታ ተከትሎ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በታሪክ ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ ለ26 ጋዜጠኞች ሙሉ ወጪያቸውን ሸፍኖ ለመውሰድ የተደረገውን የመጀመሪያ ጥረት በእጅጉ አደንቃለሁ፡፡ አለም ሰገድ ሰይፉ የሊግ ስፖርት ጋዜጣ አሳታሚና ማኔጂንግ ኤዲተር  በቀጣይነትም ለሀገሪቱ ስፖርት ቁልፍ ሚና ያላቸውን ጋዜጠኞች በዚህ አይነቱ ውድድር ላይ እንዲጋበዙ ቢደረግ የተሻለ ነው እላለሁ፡፡

2. በጣም ታላቅ ደስታ ነው የተሰማኝ፡፡ የስፖርት ቤተሰቡን ስሜት ፈንቅሎ የወጣው የሀገሪቱን የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ለተተኪ ስፖርተኞች የሚፈጥረው ተነሳሽነት የጐላ በመሆኑ የሀገሪቱን ማለፍ የላቀ ትርጉም ይሰጠዋል፡፡ በቀጣይነት ጠንክሮ መስራት ያስፈልጋል፡፡
3. የብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች አሁን ካላቸው ተነሳሽነት አንፃር በደቡብ አፍሪካው ዋንጫ ያልተጠበቀ ውጤት በማስመዝገብ የአፍሪካ የስፖርት ቤተሰብ የሚያስደንቅ ነገር የሚያመጡ ይመስለኛል፡፡
4. ሀ.0 - 0 ለ.1 - 0 ሐ.1 - 1
አለም ሰገድ ሰይፉ የሊግ ስፖርት ጋዜጣ
አሳታሚና ማኔጂንግ ኤዲተር
/*******************************8

1. ዕድሉ መፈጠሩ መልካም ነው የስፖርት ጋዜጠኞችም ለሀገር ውስጥ ስፖርት ትኩረት እንዲሰጡም ያበረታታል፡፡ ነገር ግን የጉዞ ሂደቱን ለማሳጠር በፌዴሬሽኑ በኩል ብዙ መሰራት ነበረበት፡ ፡ አሰልቺና መንገላታት የበዛበት ነበር፡፡
2. ለአሁኑ ትውልድ የመጀመሪያ ታሪክ ነው - ከረዥም ጊዜ በኋላ የተገኘ ተሳትፎ መሆኑ ያስደስታል፡ ፡ እግር ኳሳችን አደገ ለማለት ግን ተሳትፎው ተከታታይነት ያለው እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ ለተሳትፎም የዘለለ ውጤት ያስፈልጋል፡፡ ፌዴሬሽኑም ለዚህም የሚያበቃ የእግር ኳስ ልማት መስራት፣ ፕሮጀክቶችና ክለቦችን ማጠናከር ተገቢ ይመስለኛል ፡፡
3.ከረዥም ጊዜ በኋላ የመጣ ተሳትፎ እንደመሆኑ ሩብ ፍፃሜ መግባት መቻልን እንደ ትልቅ ውጤት እቆጥረዋለሁ፡፡ ምድቡን ነጥብ ይዞ ማጠናቀቀ መቻልም መልካም ነው እላለሁ፡፡ ሀ.1-1 ለ.2 - 1 ሐ.0 - 1
ሰለሞን ያለው ከሬድዮ ፋና  
/**********************88

1. በርካታ የስፖርት ጋዜጠኞች ውድድሩን እንዲዘግቡ ዕድል መመቻቸቱ ጥሩ ነው፡፡ ሆኖም በሂደቱ ላይ በተለይ በቪዛ ላይ ጋዜጠኞቹ ብቻቸውን መከታተላቸው አሰልቺና ተስፋ አስቆራጭ ነበር፡፡ በዚህ በኩል ፌዴሬሽኑም ሆነ መንግስት ሊያግዛቸዉ ይገባል፡፡
2. በዚህ ትውልድ ይህ ዕድል መገኘቱ ሁሉንም ያስደሰተ ነው፡፡ መታሰብ ያለበት ግን ስለቀጣይነቱ መሆን አለበት፡፡ በአጭር ማጣሪያ ለዚህ መድረስ ቢቻልም ቀጣዮቹ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያዎች ከባዶች ይሆናሉ፡፡ ዘለቄታና ከስር መሰረቱ የጠነከረ ስራ መስራት አለበት፡፡
3. ሩብ ፍፃሜ ድረስ ይዘልቃል የሚል ግምት አለኝ፡፡
4. ሀ.1 – 0 ለ.0 - 0 ሐ.0 - 2 ታምሩ አለሙ ከዛሚ አገሬ ስፖርት

/********************

1. በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ አንደኛ ምዕራፍ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ጋዜጠኛውም ላለፉት አመታት ያላገኘውን ወርቃማ ዕድል በማግኘቱ ወርቃማ አጋጣሚ ነው፡፡
2. ባላዝንም ብዙ አልተደሰትኩም፡፡ ምክንያቱም በቅተን፤ አውቀን ወደ አፍሪካ ዋንጫ ብናልፍ በነገው ጨዋታ ስጋት አይገባንም ነበር፡፡ በቀጣይ አድምቶ ከሥር ጀምሮ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ 3. የመጀመሪያውን ዙር የማለፍ አቋም ያለው ይመስላል፡፡ ካልሆነ ግን የሊቢያው የ1974 ውጤት ይደገማል ብዬ እገምታለሁ፡፡ በተለይ ከዛምቢያ የምናደርገው ጨዋታ ለቀጣይ ውጤት አመላካች ይሆናል፡፡
 4. ሀ.1 - 1 ለ.2 - 1 ሐ.0 - 3
ማንደፍሮ ለማ ከኢቴቪ ስፖርት
/*****************
1. ዕድሉ በጣም የሚበረታታና በተለይ ለስፖርት ጋዜጠኞቹ ወደፊት ለሚሰሩት ሥራም ከፍተኛ መነቃቃት የፈጠረ ነው፡፡
2. እንደ ዜጋ ደስታ እንደ ባለሙያ ደግሞ ባለፉት ጥቂት ወራት በተሰሩት ሥራዎች እዚህ ከተደረሰ ወደፊት የበለጠ ነገሮች ሊመጡ እንደሚችሉ ያሳየ ነው፡፡ ለወደፊቱም እንቅስቃሴው በተጠናከረ መልኩ ከቀጠለ የአህጉር የየጊዜው ተሳታፊ መሆናችን አይቀርም፡፡
3. የመጀመሪያውን ምድብ ማጣሪያ ማለፍ በቂ ነው!
4. ሀ.1 - 1 ለ.2 - 1 ሐ.1 - 2
ሙሉነህ ተስፋዬ ከዘ-ገነርስ የስፖርት ጋዜጣ

/*********************
1. እድሉ በጣም ጥሩ ነው ግን ውጣ ውረዱ በሙሉ ወደ ጋዜጠኛው ስለመጣ ትንሽ አድካሚ ሆኗል፡፡
2. በጣም ደስታ ፌሽታ
3. ግማሽ ፍፃሜ 4. ሀ.1 - 0 ለ.2 - 1 ሐ.0 - 0
ፍስሐ ይድነቃቸው ከኢቢኤስ ቴሌቭዥን

የኩባ ፕሬዚዳንት የነበሩት ፊደል ካስትሮ ሩዝ፣ ከኢትዮጵያ ጋር በነበራቸው አፍላ የወዳጅነት ጊዜ፣ “የኢትዮጵያ አብዮት እውነተኛ አብዮት ነው፤ መሪውም ትክክለኛ አብዮተኛ ነው” ብለው ማለታቸው በደርጉ ዘመን ተደጋግሞ ይጠቀስላቸው ነበር፡፡ ካስትሮ በተጨማሪም የኢትዮጵያ አብዮት በባህሪው ከፈረንሳይና ከቦልሼቪክ አብዮት የተቀየጠ ነው ሲሉም የአድናቆት ምስክርነታቸውን ሰጥተው ነበር ይባላል፡፡ በዚያን ዘመን በኢትዮጵያ በተከሰተው ለውጥ የተደነቁትና የተሳቡት ኩባዊ ፊደል ካስትሮ ብቻ አልነበሩም፡፡ በዚች አፍሪካዊት አገር በተካሄደው ለውጥ አትኩሮታቸው ከተሳበው አብዮተኞች መካከል ኩባዊው ጋዜጠኛ፣ ደራሲና ዲፕሎማት ቫልዲስ ቪቮ አንዱ ነበር፡፡ ይህ ሰው ወደ ሥራ ዓለም የተሠማራው፣ እነፊደል ካስትሮን ወደ ሥልጣን ያመጣው የኩባ አብዮት ከመቀጣጠሉ 13 ዓመት ቀደም ብሎ፣ “ሜላ” በተሰኘ መጽሔት ላይ መጻፍ ሲጀምር ነበር፡፡ አምባገነኑ የባቲስታ አገዛዝ የ “ሜላ” መጽሔት እንዳይታተም እስካገደበት ጊዜ ድረስ፣ ቫልዲስ ቪቮ ደረጃ በደረጃ እያደገ ሄዶ የመጽሔቱ ዋና አዘጋጅ እስከመሆን ደርሶ ነበር፡፡ ከእገዳው በኋላም የቫልዲስ ቪቮ ዕጣ ፈንታ እሥርና ስደት ሆነ፡፡

እነካስትሮ የመሩት የትጥቅ ትግል የባቲስታን የግፍ አስተዳደር እስኪያስወግድ ድረስም ኩባ ለዚህ ሰው ወሕኒ ቤቱ ነበረች፡፡ የኩባ አርበኞች ግፈኛውን ባቲስታን ድል ነስተው ሶሻሊዝምን ሲያውጁ፣ ቫልዲስ ቪቮና መሰሎቹ በአዲሲቷ ኩባ ብሩሕ ቀን ወጣላቸው፡፡ ድህረ አብዮት ቫልዲስ ቪቮ ሥራ የጀመረው “ሆይ” በተሰኘ መጽሔት ላይ ሲሆን እስከ ምክትል ዋና አዘጋጅነት ደረጃ በመድረስ ለስምንት ዓመታት ያህል በስራው ላይ ቆይቶበታል፡፡ ከዚህ በኋላም ወደ ኩባ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ተዛውሮ እ.ኤ.አ ከ1967 ዓ.ም እስከ 1974 ዓ.ም ድረስ በካምቦዲያ እና በቬትናም ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ የኩባ ዲፕሎማሲ እንደራሴ (አምባሳደር) ሆኖ ሰርቷል፡፡ ቫልዲስ ቪቮ በኩባ ውሥጥ ከዲፕሎማትነቱ ይልቅ በይበልጥ የሚታወቀው ግን በበርካታ መጻሕፍት ደራሲነቱ ነው፡፡ ከዋና ዋና ሥራዎቹም መካከል The Blind Blacks, The Brigade and the Mutilated Man, አጫጭር ታሪኮች ከደቡብ ቬትናም፣ የጫካ ውስጥ ኤምባሲ፣12 የቬትናም አጫጭር ታሪኮች፣ Angola: an end to Merceneries Myth የተሠኙት የሚገኙበት ሲሆን መጻሕፍቱ በስፓኒሽ ቋንቋ ታትመው በኩባና በሌላው ዓለም ተነብበውለታል፡፡ ቫልዲስ ቪቮ ስለ ኢትዮጵያ ማሰብ የጀመረው፣ ከባምቦዲያ የኩባ አምባሳደር ሆኖ ሲሰራ፣ ዐጼ ኃይለ ሥላሴ ካምቦዲያን በይፋ በጎበኙበት ጊዜ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ወደ ቬትናም ከተዘዋወረ ወዲህ ደግም በኢትዮጵያ ሕዝባዊ ተቃውሞ ተቀስቅሶ በስተመጨረሻም ለዐጼ ኃይለ ሥላሴ ከሥልጣን መውረድና ለዘውድ ሥርዓት ፍጻሜ ምክንያት ሲሆን በሩቅ ተመልክቷል፡፡ የታሪክ አጋጣሚ፣ አገሩን ኩባንና አፍሪቃዊቷን ጥንታዊ አገር ወንድማማች ሲያደርጋቸው ደግሞ በዚች አገር ይካሄድ የነበረውን ለውጥ በቅርብ ለመመልከት አስችሎታል፡፡

ቫልዲስ ወደ ኢትዮጵያ የመጣበት ትክክለኛ ጊዜን ለማወቅ ባይቻልም፣ ኩባ ያለማወላወል ከኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ጎን የቆመችበት ጊዜ ተደርጎ ከሚቆጠረው (ደርግ የውስጥ ተቃዋሚዎቹን በቤተ መንግሥት ከደመሰሰበት) ከጥር 26 ቀን 1969 ዓ.ም ወዲህ ይመስላል፡፡ ቫልዲስ በኢትዮጵያ ጉብኝቱ በዘመኑ አጠራር “አብዮቱ የመጣላቸው” የሚባሉት ጭቁኖችንና እና “አብዮቱ የመጣባቸው” የተሠኙትን ባላባቶችና አድሀሪዎችን ተመልክቷል፡፡ የወዳጅ አገር ከፍተኛ ባለሥልጣን እንደመሆኑም ስለአብዮቱና ስለ ለውጡ ይፋ ያልሆኑ መረጃዎችን ለመሰብሰብ ሳይችል አልቀረም፡፡ ቫልዲስ ቪቮ በኢትዮጵያ ጉብኝቱ ያገኛቸውን ጥቂት መረጃዎችና ምልከታዎች በመቀመርም፤ ስለ አብዮቱ በውጭ ተመልካቾች ከተጻፉት የመጀመሪያው ሊባል የሚችለውን መጽሐፍ እ.ኤ.አ በ1978 ዓ.ም (ኢትዮጵያ፤ ያልታወቀው አብዮት) Ethiopia: the Unknown Revolution በሚል ርእስ ኩባ ውሥጥ አሳተመ፡፡ ዘጠኝ ምዕራፎችና 147 ገጾች ያሉት ይህ መጽሐፍ መጀመሪያ የታተመው በስፓኒሽ ቋንቋ ሲሆን፤ በኋላ በኩባ የትርጉም ማዕከል ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ ተመልሶና ታትሞ ለሰፊው የዓለም አንባቢ ቀርቦ ነበር፡፡ ቫልዲስ ቪቮ ይህንን መጽሐፍ ባሳተመበት ጊዜ የኩባ ኮሙኒስት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የፓርቲው የውጭ ጉዳዮች ኃላፊ ነበር፡፡ “ያልታወቀው አብዮት” ከየካቲት 1966 ዓ.ም እስከ መስከረም 1967 ዓ.ም የነበረውን ጸረ ዘውድ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ እንዲሁም ከለውጡ ወዲህ በነበሩት ሶስት “የአብዮት ዓመታት” ላይ አተኩሮ የተጻፈ መጽሐፍ ነው፡፡ ደራሲው ራሱ አብዮተኛ እንደመሆኑ በኢትዮጵያ የተፈጸሙ ድርጊቶችንና ኩነቶችን የተመለከተውና የተነተነው በዚያው ማርክሳዊ በሆነ መነጽር ነው፡፡ ይሁን እንጂ የአንድን አገር ርዕዮተ ዓለምም ሆነ መሪዎቿን በቅርብ ማወቅ ብቻውን ያንን አገር ለመረዳትም ሆነ ስለዚያ አገር ለመጻፍ አይጠቅምም፡፡ ቫልዲስ ቪቮም የዚህ ችግር ሰለባ ነበር፡፡

ስለ ኢትዮጵያ በሚያውቃቸው ጥቂት ነገሮች ላይ ብቻ ተመስርቶ መጽሐፍ ለመጻፍ በመነሳቱ የተነሳ፤በአገሪቱ በተካሄደው ሥር ነቀል የለውጥ ሂደት ውሥጥ ግልጽና በጣም መሠረታዊ የሆኑ ክስተቶችና ሐቆችን አዛብቶ ለማቅረብ ችሏል፡፡ ለምሣሌ ዐጼ ኃይለ ሥላሴ ከሥልጣን ወርደውበታል ተብሎ በመጽሐፉ የተገለጸው ሁናቴ ከእውነተኛው ታሪክ ጨርሶ የራቀ ነው፡፡ ቫልዲስ ቪቮ እንደሚለው፣ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ጃንሆይ ከሥልጣን መውረዳቸው የተገለጸላቸው መጀመሪያ ከቤተ መንግሥታቸው በሶስት ወታደሮች ወደ አንድ ጦር ሠፈር በቮልስዋገን መኪና ተወስደው አንድ ሰፊ ክፍል ውሥጥ ካረፉ በኋላ ነበር፡፡ እንዲሁም ሉሉ የተሠኘችው የጃንሆይ ለማዳ ውሻ የተቀበረችው በወርቅ ከታነጸ መቃብር ነበር ማለቱን፣ በተጨማሪም የቤተ መንግሥቱ መጸዳጃ ቤት መቀመጫ እና የጃንሆይ ብስክሌት ፍሬም የተሠራው ከንጹህ ወርቅ ነበር ብሎ ያለ ማስረጃ መጻፉ ከተራ የፕሮፓጋንዳ ጽሁፍነት ማለፍ የሌለበት ነበር፡፡ ደርግ የተሠኘው የንዑስ ወታደራዊ መኮንኖች ስብስብ፣ ባቀረቡት የተለየ አስተያየት ብቻ ያለ ፍርድ እየጨፈጨፈና እያረደ የትም የጣላቸውን ኢትዮጵያውያን አስመልክቶ ቫልዲስ በመጽሐፉ የሠጠው አስተያየት፣ ደርግን ለመደገፍ ሲል ከሠብዓዊ አስተያየትና ከሚዛናዊነት አምባ ምን ያህል እንዳፈነገጠ የሚጠቁም ነው፡፡ ደራሲው ይህንን አስተያየቱን የገለጠው “በአብዮቱ እንዲረሸኑ የተፈረደባቸው ከፍተኛ ሚኒስትሮችና ጀነራሎች ቁጥር በዐጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የነበሩ ባለመሬቶች (ባላባቶች) በአንድ ወር ይፈጇቸው ከነበረው ጭሰኞች ጋር ሲነጻጸሩ ቁጥሩ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም” በማለት ነበር፡፡ ደርግ፣ የሕዝባዊውን ፀረ ዘውድ ተቃውሞ አመራር መጀመሪያ በዘዴ፣ በኋላ ደግሞ በጉልበት ጠልፎ የሥልጣን ኮርቻን የተቆናጠጠ የወታደሮች ቡድን መሆኑ ቀርቶ ሕዝባዊውን አብዮት ያቀጣጠለ፣የመራና ለሥልጣን ያበቃ ልዩ አካል ተደርጎ በመጽሐፉ ቀርቧል፡፡ ይህም ኢትዮጵያውያን ከሚያውቁትና ከለመዱት የደርግ የጭካኔ ባሕሪና መልክ ፍጹም ርቆ የቀረበ አጉል ውዳሴ “የኢትዮጵያ አብዮት” ለተባለ ፊልም የተጻፈ ስክሪፕት ይሆን እንደሆነ እንጂ የታሪክ ማስታወሻ ተደርጎ ሊቆጠር የሚችል አይደለም፡፡ “ያልታወቀው አብዮት” ደርግን እና መሪዎቹን ያለ ተግባራቸውና ውሏቸው እያሞጋገሰ “የኢትዮጵያ አብዮትንም” ከዓለም ታላላቅ አብዮቶች ተርታ እያሰለፈ በጸዓዳ ሸራ ላይ ባማረ ቀለም ያሰማመራቸው ቢሆንም ከንቱ ውዳሴው ፈሩን ስቶ የደርጉን ሊቀመንበር ማስቀየሙ አልቀረም፡፡ ቫልዲስ ሊቀመንበሩን የማስቀየም ስሕተት የሠራው፣ የአብዮቱ ቀያሾች ናቸው ያላቸው የደርግ መሪዎች እንደሌላው አፍሪካ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የተቆናጠጡ ሳይሆኑ ብዙኃኑን፣ የተገፋውንና የታችኛውን መደብ የሚወክሉ እውነተኛ የአብዮት መሪዎች አድርጎ ለማቅረብ ሲሞክር ነበር፡፡

በተለይ ኮሎኔል መንግሥቱን ቅር ያሰኘው በመጽሐፉ ምዕራፍ ሁለት ከገጽ 30 እስከ 31 በሠፈረው አንቀጽ አንድ ሐረግ ላይ ነበር፡፡ የአንቀጹ ትርጉም እንዲህ ይነበባል፡፡ “[ቅድመ አብዮት] በኢትዮጵያ ማርክሲዝም ሌኒኒዝም ሥር ሰዶ ንቅናቄ ለመፍጠር ወይም ፓርቲ ለመመሥረት ባይችልም፤ የሶሻሊስት ፍልስፍና ሁለንተናዊነት ግን በጦር ሠራዊቱ መካከለኛው የመኮንኖች መደብ ለመዝለቅ ችሎ ነበር፡፡ ከመካከላቸው አንዱ፣ የባርያ ልጅ የሆነው፣ እጩ መኮንን ሳለ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ለትምህርት በተላከበት ጊዜ የዘር መድልዎ ሰለባ ሆኖ ነበር፡፡ ይህ መኮንን በቬትናም ስለተደረገው ጦርነት፣ ብዙኃን ጥቁሮችን ስላስቆጣው የዲትሮይት ተኩስ፣ እንዲሁም ስለ ተማሪዎች አመጽና ስለ ዋተር ጌት ቅሌት ጠንቅቆ ያውቅ ነበር፡፡ በዩናይትድ ስቴስት በነበረው ልምድ የተነሳ መንግሥቱ ኃይለማርያም አሁን ባለው ዓለም እየጨመረ ስለመጣው ከቁጥጥር ውጪ የሆነ አብዮት፣ አመጽና ግጭት ጥርት ያለ ምልከታ ሊኖረው ቻለ” ቫልዲስ በዚህ አንቀጽ “የባሪያ ልጅ” በማለት የጻፈው ሐረግ መንግሥቱ ኃይለማርያምን “እውነተኛ አብዮት የወለደውና” ከታችኛው መደብ የፈለቀ የሕዝብ ልጅ አድርጎ ለመግለጽ ፈልጎ እንጂ ሊቀመንበሩን ዝቅ ለማድረግ ወይም ለማዋረድ አስቦ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ ከላይ የቀረበው አገላለጽም ለጓድ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለ ማርምምም ሆነ፤ በግዙፍ ሠሌዳ ላይ ምስላቸው በሥዕል ሲሰራ እንኳን ተፈጥሮ የሠጠቻቸው ገጽታ ተስተካክሎ እንዲሰራ ትዕዛዝ ለሚሰጡት ጓደኞቻቸው የሚዋጥ አልነበረም፡፡ መጽሐፉ በአንድ በኩል ይህ “ይቅር የማይባል እንከን” የሚታይበት ቢሆንም በሌላ በኩል ደግሞ ደርጋውያንን፣ መሪያቸውን እና የጠለፉትን አብዮት አለመጠን እያሞጋገሠ እና እያወደሠ ያቀረበ በመሆኑ የመጽሐፉን ሥም ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ ከተከለከሉ የውጪ መጽሐፎች ዝርዝር ውሥጥ ለማስገባት አልተፈለገም፡፡ በመሆኑም “ዐሣውም እንያልቅ ውሃውም እንዳይደርቅ” እንደሚባለው፣ደርጋውያን ከመጽሐፉ ላይ “እንከኑን” የመንቀስ ሀሳብ መጣላቸው፡፡ ይህ ሐሳብ የመጽሐፉን ዝውውር ሳይከለክልና ስርጭቱን ሳያግድ ቅሬታ የፈጠረውን ሐረግ የሚያስወግድ በመሆኑ ተቀባይነት አገኘ፡፡ በዚህም መሠረት ወደ ኢትዮጵያ የገባው የ “ያልታወቀ አብዮት” ቅጂ አንድ በአንድ እየተገለጠ “የባሪያ ልጅ” የሚለው ሐረግ በጥቁር ቀለም ከተሠረዘ በኋላ መጽሐፉ ለሕዝብ እንዲሰራጭ ተደረገ፡፡ ይህ አስገራሚ ሥራ በደርጉ ዘመን ኢትዮጵያ ሐሳብን በነጻ የመግለጽ መብት ላይ የተጣለበት ገደብ ምን ያህል ጠንካራ እንደነበረ እና ሳንሱርም ለታተመ መጽሐፍም እንኳን ቢሆን እንደማይራራ ያስመሰከረ ታሪካዊ ክሥተት ነው፡፡ ደርጎች ሳንሱርን አንድ እርምጃ ወደፊት በማራመድ በመጽሐፍት ሕትመት ታሪክ ውሥጥ ያልታየ አዲስ የሐሳብ ጭቆና ድርጊት የሆነውን ድሕረ ሕትመት ሳንሱር ለዓለም በማስተዋወቃቸው ታሪክ ያስታውሳቸው ይሆናል፡፡ ቫልዲስ ቪቮ በመጽሐፉ ላይ የተደረገበትን ድሕረ ሕትመት እርማት ያወቀው አይመስልም፡፡

መጽሐፉ ከታተመ በኋላ ወደ ኢትዮጽያ በመጣበት ጊዜ ግን ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም ሊያነጋግሩት ስላልፈቀዱ ሳያገኛቸው ወደ አገሩ መመለሱ ታውቋል፡፡ ምንም እንኳ በኢትዮጵያ ስለተካሄደው አብዮት በውጭ ተመልካቾች ከተጻፉት መጻሕፍት ውሥጥ የቫልዲስ ቪቮ ሥራ ቀዳሚ ቢሆንም ሐቅ፣ ሚዛንና ገለልተኝነት ተዛብተውና ተጣመው የቀረቡበት በመሆኑ ሥራዉ የታሪክ መጻሕፍትን መስፈርት ቀርቶ የጋዜጣ መጣጥፍን ሚዛን የሚደፋ መስሎ አይታይም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ “ያልታወቀው አብዮት” ሲታተም በኢትዮጵያ የተካሄደው ለውጥ ገና ሶስት ዓመት እንኳን ያልሞላው በመሆኑ፣ እንቅስቃሴው በመላ አገሪቱና በሕዝቧ ላይ ያመጣውን ለውጥ ለመገምገም ጊዜው በጣም አጭር ነበር፡፡ እንዲያውም ቫልዲስ ቪቮ መጽሐፉን ባቀረበበት ጊዜ፣ ደርግ የተነሳበትን ተቃውሞ ለማዳፈን በኢትዮጵያ ታይቶ የማይታወቅ አዲስ የጅምላ ጭፍጨፋ ታሪክ የሚሰራበት ጊዜ ስለነበር ቆም ብሎ ለውጡን ለመገምገም የሚያስችል ስክነት በአገሪቱ በጭራሽ አልሰፈነም ነበር፡፡ በተጨማሪም ደራሲው ክስተቶችን ከሶሻሊስት አብዮት አንጻርና በማርክሲስት ርዕዮት መነጽር ብቻ ማየቱ የአመለካከት አድማሱን እንደገደበበት በመጽሐፉ ከቀረቡ ቁንጽል፣ የተጋነኑና ሐሰተኛ ታሪኮች መረዳት ይቻላል፡፡ የመጽሐፉ ሚዛን አጋድሎ ለተጻፈለት ለደርጉም ቢሆን ታሪኩ ለስላሳና ያማረ ግምጃ እንዳልሆነለት፣ መጽሐፉ ታትሞ ኢትዮጵያ ውሥጥ ከገባ በኋላ የደረሰበት ድህረ ህትመት ሳንሱር ታላቅ ማስረጃ ነው፡፡

Published in ጥበብ
Page 3 of 11